Telegram Web Link
ፀሐይ ናላ በምታዞርበት እና ሁሉም ለማረፍ ወደ አልጋው በሚሽቀዳደምበት በቀትር ሰዓት አብርሃም ግን በድንኳኑ ደጃፍ ላይ ተቀምጦ እንግዳ በተስፋ ይጠባበቅ ነበር።(ዘፍ 18) በዚህ የቃጠሎ ጊዜ (ስድስት ሰዓት) መንገድ ላይ የሚገኝ ሰው ወይ ምንም ማረፊያ የሌለው ምስኪን ነው፣ አለዚያ ደግሞ እንደዚያች ሳምራዊት ሴት ከሰው የተገለለ ብቸኛ ነው።(ዮሐ 4፥6) አብርሃም ድንኳኑን ያሰናዳው ያማረ ለለበሱ፣ ብድር ለሚመልሱ፣ በመልክም በገንዘብም ዓይን ውስጥ ለሚገቡ ሰዎች ሳይሆን፣ ሰው ለሸሻቸው መጠጊያ ለሌላቸው እና በፀሐይ ንዳድ እየተንገበገቡ ማረፊያ ፈልገው ለሚዞሩ አስታዋሽ አልባ ምስኪኖች ነበር።

አብርሃም በደጁ የሚያልፉ ምስኪን እንግዶቹን “ና እስኪ” ብሎ በማቃለል ቃል አይጠራቸውም። እየሮጠ ወደ እነርሱ ሄዶ “ጌቶች (እመቤት) እባካችሁ ወደ ቤቴ ግቡልኝ” ብሎ በትሕትና ይለምናቸዋል እንጂ።

ይህንን ግን በምን አወቅን? በሦስት ሰዎች ተመስለው ወደ ቤቱ ቅድስት ሥላሴ በመጡ ጊዜ አብርሃም እነርሱን ያስተናገደበትን መንገድ አይተን ተረዳን። አብርሃም በዚህች ቀን ተዘጋጅቶ ይጠብቅ የነበረው ሰውን እንጂ እግዚአብሔርን አልነበረም። እግዚአብሔር ግን አብርሃም ለምስኪናኑ ያሳይ የነበረው ቸርነቱን አይቶ በቤቱ ሊስተናገድ ወደደ።

አብርሃም ለድሆች ሲል በከፈተው በር በኩል በመካንነት ምክንያት የተዘጋውን የሣራን ማኅፀን የሚከፍት የሠራዊት ጌታ ገባለት።

የአንተን የብዙ ዓመታት ጥያቄ ለመመለስ እግዚአብሔር ወደ ሕይወትህ የሚገባው፣ ለሌሎች ሰዎች ብለህ በከፈትኸው የመልካምነት እና የቅንነት በር በኩል ነው።

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
ሐምሌ ቅድስት ሥላሴ -2017 ዓ.ም.
https://www.tg-me.com/Dnabel

እንኳን አደረሳችሁ!
120🙏40🔥6🥰4
2025/07/14 21:42:42
Back to Top
HTML Embed Code: