Telegram Web Link
+++ ኦርቶዶክሳዊው ንባብ +++

በዓለማችን ላይ የሚታተሙ ብዙ የታሪክ መጻሕፍት አሉ፡፡ እነዚህ የታሪክ መጻሕፍት ‹‹እንዲህ ነበረ፣ እንዲህ ሆነ፣ እንዲህ ተፈጸመ›› እያሉ ያለፈውን ዘመን አሁን ላይ ሆኖ ለሚያነብ ሰው በትረካ መልክ የሚያስቃኙ ናቸው፡፡ አንባቢው በመጽሐፉ ከእርሱ በፊት ቀድመው ስለሆኑ ነገሮች መረጃዎችን ያገኝ እንደ ሆነ እንጂ ራሱን የታሪኩ አንድ አካል የሚያደርግበት እድል የለውም፡፡ የታጠሩበት የዘመን አጥር ጥብቅ ነው፡፡ በቅጥሩ ያሉ አይወጡበትም፡፡ የሌሉ እና ያልነበሩትም አይገቡበትም፡፡

በክርስቲያኖች እጅ ያለው መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከእነዚህ የታሪክ መጻሕፍት የተለየ ነው፡፡ በውስጡ የሚገኙት ታሪኮች በአንድ ወቅት የተፈጸሙ ቢሆኑም በዛሬ ዘመን ያሉ አንባብያንን ወደ ታሪኩ መጋበዝ የሚያስችል የተከፈተ በር አላቸው፡፡ የትላንቱን ከአሁን ጋር የሚያያይዙበት የተቀደሰ ሰዓት (Sacred time) አላቸው፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ በእለተ አርብ አንድ ጊዜ ስለ ፈጸመው የማዳን ሥራ በሚናገርበት የዕብራውያን መልእክቱ ላይ ‹‹የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና›› ሲል የሚመሰክረው፡፡(ዕብ 4፡12) ቤተ ክርስቲያናችንም ሕያው በሆነው በእለተ አርቡ የቀራንዮ መከራ እለት እለት በቅዳሴ ከልጆቿ ምእመናን ጋር ትመላለስበታለች፡፡ ጌታዋን እግር በእግር እየተከተለች መከራውን ትቆጥራለች፣ በስቅለቱ ታዝናለች፡፡ በመስቀሉ ያፈሰሰውን ደም በጽዋ ቀድታ፣ የቆረሰውን ሥጋ በጻሕል ተቀብላ ለልጆቿ ለምእመናን ትሰጣለች፡፡

ኦርቶዶክሳዊ የሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ባሕል ይህ ነው፡፡ አንባቢው ቃሉን ከላይ ብቻ የሚያነብ ሳይሆን በተዘክሮ ወደ ውስጥ ዘልቆ በመግባት ራሱን የታሪኩ ተካፋይ ያደርጋል፡፡

እግዚአብሔር ከእመቤታችን በተወለደ ጊዜ በጨርቅ መጠቅለሉን፣ በተናቀው ቦታ በበረት ማደሩን አይቶ ትሕትናውን ያደንቃል፡፡ ሰብአ ሰገል እጅ መንሻን ይዘው ወደ ጌታ እንደ መጡ ባነበበ ጊዜ፣ እርሱም ከእነርሱ ጋር ሆኖ የንጽሕናውን እጅ መንሻ ለአምላኩ ሰግዶ ያቀርባል፡፡ ከእረኞቹም ጋር መወለዱን ይናገራል፡፡ በልቡ ደስታም እያሸበሸበ አብሯቸው ይዘምራል፡፡ ወደ ቤተ መቅደስም እንዳገቡት ባነበበ ጊዜ ከአረጋዊው ስምዖን ጋር በተዘክሮ ጌታን ይታቀፈዋል፡፡ ወደ ግብጽም ሲሰደድ ጌታን፣ እናቱና ዮሴፍን ተከትሎ ይሰደዳል፡፡ በእናቱም እቅፍ ያለውን የሕፃኑን ጌታ የተወደደ መዓዛ ያሸታል፡፡ ክፉው ሄሮድስም ሲሞት አብሯቸው ወደ ገሊላ ይመለሳል፡፡

ጌታ በአሥራ ሁለት ዓመቱ ወደ መቅደስ ገብቶ መምህራንን በጠየቀ ጊዜ አጠያየቁን ያደንቃል፡፡ ወደ ዮርዳኖስ ባሕር ለጥምቀት ሲወርድ አብሮት ይወርዳል፡፡ ከሰማይ የወጣውን የአብን ድምጽ ሰምቶ፣ በርግብ ምሳሌ የወረደውን መንፈስ ቅዱስ አይቶ በሦስትነቱ ያምናል፤ በባሕር መካከል ለቆመው አካላዊ ቃልም ይሰግዳል፡፡ በቆሮንቶስም በረሃ ከጌታው ጋር አብሮ ይጾማል፡፡ በጌታ በቃና ዘገሊላ ተገኝቶ ውኃውን ወደ ወይን ሊለውጥ ጋኖቹን በውኃ ሙሉ ባለ ጊዜ፣ ከአገልጋዮቹ ጋር ሆኖ ውኃን ይሞላል፡፡ የተለወጠውንም ወይን ቀድቶ ለአሳዳሪ በመስጠት በጌታው ተአምር ደስ ይሰኛል፡፡ እንዲህ አድርጎ ቅዱሱን መጽሐፍ እያነበበ በተዘክሮ ጌታው ከዋለበት ውሎ ካደረበት ያድራል፡፡

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
ሰይጣን አንድን ኃጢአት ሊያሠራን ሲፈልግ ቀድሞ ስለ እግዚአብሔር መሐሪነት በሰፊው ይሰብከናል። ያን ኃጢአት ከፈጸምን በኋላ ደግሞ ስለ እውነተኛ ፈራጅነቱና ምንም ቢሆን ከቁጣው የማናመልጥ መሆኑን ከቀድሞው ይልቅ እየጮኸ ይነግረናል። በመጀመሪያው ስብከቱ ኃጢአትን እንዳንቃወም ሰነፎች ያደርገናል። በሁለተኛው ስብከቱ ደግሞ ንስሐ እንዳንገባ ተስፋ ያስቆርጠናል።

ይህ የተገለባበጠ ስብከት "የሰይጣን" ነው። ሰው በኃጢአት ከመውደቁ በፊት ሊያስብ የሚገባው የእግዚአብሔርን ፈታሒነት (ፈራጅነት) ሲሆን በኃጢአት ከወደቀ በኋላ ግን ማሰብ ያለበት የእግዚአብሔርን መሐሪነት ነው።

ፈታሒነቱ ኃጢአትን እንዳንሠራ ይጠብቀናል፤
መሐሪነቱ ንስሐ እንድንገባ ያቀርበናል፤

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
+++ "ለዚህ መቼ ጸለይን?" +++

በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ቤተሰባዊ የሆኑ ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲረዳ የተቋቋመ የካህናት (የቀሳውስት) ጉባኤ ነበረ። የቀድሞው የቅብጥ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ሺኖዳም ይህን ስብስብ እንዲቀላቀሉ ለአባ ሚካኤል ባቀረቡላቸው ጥሪ መሠረት የዚህ ጉባኤ አባል ሆኑ። ታዲያ አንድ ቀን አባ ሚካኤልን ጨምሮ የጉባኤው የበላይ ኃላፊ የሆኑት ጳጳስና ሌሎችም ካህናት የተጣሉ ባልና ሚስትን ሊያስታርቁ ተሰበሰቡ። ይሁን እንጂ የባልና የሚስትየው ጠብ እንዲህ በቀላሉ ሊበርድ የሚችል አልነበረምና ጳጳሱም ሆኑ ቀሳውስቱም ሁለቱን ለማስማማት ብዙ ቢጥሩም ግን አልተሳካላቸውም።

በስተመጨረሻም ጳጳሱ ወደ አባ ሚካኤል እየጠቆሙ "አባ ሚካኤል ለምን ዝም ብለው ተቀመጡ? እስኪ እርሶ ይሻላል ብለው የሚያስቡትን ይንገሩን?" አሏቸው። አባ ሚካኤልም "ብፁዕነትዎ፣ እንጸልይበት!" አሉ። ጳጳሱም "ይህን ጉባኤ ከመጀመራችን በፊት እኮ ጸልየናል" ቢሏቸው አባ ሚካኤል "አዎን አባታችን፤ ለዚህ ችግር ግን አልጸለይንም" አሉ። ከዚያ ሁሉም ለጸሎት ተነሡ። በጳጳሱ ፈቃድ በአቡነ ሚካኤል መሪነት ጸሎት አደረጉ። ጸሎቱ እንዳለቀም እነዚያ የተጣሉት ባልና ሚስት ክርክራቸውን ሁሉ ትተው በጉባኤው ፊት በፍቅር ተቃቀፉ። ሰላም አወረዱ። ይህን ጊዜ ከቀሳውስቱ አንዱ "አባታችን ከመጀመሪያ እንዲህ ቢሉን ምን ነበር?! አሳረፉን እኮ" ብለው ጉባኤውን ፈገግ አሰኙት።

እኛስ ያልጸለይንባቸው ስንት ችሮች አሉብን?

ብዙ ቋጠሮ የሚፈታው ግን በብዙዎች የሚረሳው ትልቁ መፍትሔ፣ ጸሎት!!!

(አባ ሚካኤል ኢብራሂም (1899-1975) የግብጽ ቤተ ክርስቲያንን ለበርካታ ዓመታት በትጋት ያገለገሉና እጅግ የሚያስቀና የጸሎት ሕይወት የነበራቸው አባት ናቸው። በእርሳቸው ጉዳይ ከሰሞኑን መመላለሳችን አይቀርም።

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
+++"ስለ እኛ የታመመውን ምን አንደበት ይናገረዋል?!"+++

እጅግ ጥልቅ የጸሎት ሕይወት የነበረው፣ አካሉ አልቆ በአጥንቶቹ እስኪቆም ድረስ የሚጾመው ተሐራሚው ቅዱስ አባ ጳጉሚስ ከእለታት በአንዱ ቀን ይህን ተመለከተ፡፡ ቅዱሱ ዓርብ ዓርብ የጌታችንን ሕማማት እያሰበ ከእንባ ጋር አብዝቶ ይሰግድ ነበር፡፡ ከዓይኑ የሚወርደው እንባ ከሰውነቱ ወዝ ጋር እየተቀላቀለ ወደ መሬት በመውረዱ ምክንያት የሚሰግድበትን ቦታ አረጠበው፡፡ አባ ጳኩሚስም ይህን ወደ ጌታው እያመለከተ "ይኸው አንተን አገኝ ብዬ እንዲህ እደክማለሁ" ሲል ተናገረ፡፡ በዚህ ጊዜም መድኃኒታችን ለአባ ጳጉሚስ ተገልጦ "እኔም እንጂ ላንተ ብዬ እንዲህ ሆኜ ተሰቅያለሁ" በማለት በእለተ ዓርብ እንደ ተሰቀለ ሆኖ የተወጋ ጎኑን፣ የፈሰሰ ደሙን አሳየው፡፡ ቅዱሱም የጌታው ሕማም ከሕሊናው በላይ ሆኖበት ወድቆ ምሕረትን ለምኗል፡፡

+++++++++++++

ሕሊናቸው የክርስቶስን ሕማም ከማሰብ አቁሞ የማያውቀው አባ መብዓ ጽዮን መድኃኔዓለምን :- ‹‹ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ የዕለተ ዓርቡን መከራህን አሳየኝ፡፡ ስለ ራሴ ፈጽሞ አለቅስ ዘንድ›› ሲሉ ለመኑት፡፡ ጌታም ‹‹መከራ መስቀሌን ለማየት ትፈቅዳለህን?›› ብሎ ጠየቃቸው። ጻድቁ አባ መባዓ ጽዮንም ‹‹አዎ! አይ ዘንድ እወዳለሁ›› አሉት። ያን ጊዜም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ እጆቹና እግሮቹ ተቸንክረው ታየ፣ በራሱም ላይ የእሾህ አክሊል ደፍቶ ነበር። እንዲህ ሆኖ በሮም አደባባይ ለቅዱስ ጴጥሮስ እንደታየው ታያቸው። ይህን የመድኃኔዓለም መከራ የተመለከቱ የጻድቁ ዓይኖችም ፈዝዘው እስኪጠፉ ድረስ ትኩስ እንባዎችን ሲያዘንቡ ኖረዋል።

‹‹ኃይልየ ወጸወንየ ውእቱ እግዚእየ›› - ‹‹ኃይሌና መጠጊያዬ እርሱ ጌታዬ ነው!››

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
+++‹‹አርሳንዮስን አትረብሹት!››+++

ሥጋዊ ዓይኑን ያጣ ሰው የፀሐይን መልክ ተናገር ቢሉት እንዴት ይቻለዋል? በሙቀቷ ብቻ የፀሐይን ውበት መግለጽስ እንዴት ይሆንለታል? በጎ ትሩፋት ሠርተን ከቅድስና ጣዕም ላልደረስን ሰዎች አሁን የምንናገረው ነገር ርቆ እንደ ተሰቀለ ፍሬ ነው፡፡ የልቡናን ዓይን በንስሓ እንባ አጥበው ካላጠሩ የማያዩት፣ በተጋድሎ ካላደጉ በጸጋም ካልጎለመሱ የማይደርሱበት ጣፋጭ ፍሬ፡፡ የእኛ የኃጥአን ዓይኖች ትንኝና ጥቃቅን ተሕዋስያን ሳይቀሩ ከሚመለከቱት ከዚህ ግዙፍ ዓለም የተለየ ምን ነገር አዩ? ጆሮዎቻችንስ አዕዋፍ እና አንስርት ከሚሰሙት ድምጽ በተለየ ምን ዓይነት ድምጽ ሰሙ?

ከሰው ተለይተው ወደ በረሃ በመሰደድ በእግዚአብሔር ፊት ራሳቸውን ጥለው የሚያገለግሉ ባሕታውያን ከሚሰጣቸው አምላካዊ ጸጋዎች መካከል አንዱ ተመስጦ ነው፡፡ ሕሊናቸው የጌታዋን መልክ በማየት እና ሌሎች ረቂቅ መንፈሳዊ ቁም ነገሮችን በማሰላሰል ከፍ ብላ ትበርራለች፡፡ ነፍሳቸው ሰማየ ሰማያት ተነጥቃ ጥልቅ የሆነውን የእግዚአብሔርን የጥበቡን ምሥጢር ታደንቃለች፡፡ በዚህ ዓለም ያለውን አኗኗርም ትዘነጋለች፡፡ ሥጋዊ መብል መጠጥን ትታ የጨለማ ወሬ ወደ ሌለበት የብርሃን አዳረሽ ትገባለች፡፡ በዚያም ተመስጦ ብዙ ቀን ትኖራለች፡፡ ከብዙ ቀንም በኋላ ስትመለስ ማደሪያዋ ሥጋ ደሙ ሳይደርቅና ሳይበሰብስ ያገኘችው እንደ ሆነ ትዋሐደዋለች፡፡ ነገር ግን ደርቆ ከአገኘችው በዚያው ትቀራለች፡፡

አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በሥራ መሐል ተመስጦ ሲመጣባቸው ሥጋቸው ይዝላል፣ ኃይል አጥተው ይዳከማሉ፡፡ በዜና አበው እንደ ተጻፈ ከዚህ ጸጋ የደረሰ አንድ ባሕታዊ ፈጣሪውን በሕሊናው እየተዘከረ ሥራውን ሲሠራ ድንገት ተደሞ መጣበትና ሰውነቱ ዝሎ ወደቀ፡፡ ሥራውንም መሥራት ተሳነው፡፡ በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጾለት ‹‹ለሥራው የሚሆን ሥጋዊ ኃይል አንሶህ ቢሆን አተጋህ ነበር፡፡ ይህ ግን የብቃት ነውና ግፋበት›› እያለ አበርትቶታል፡፡

ታላቁ አባት ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርም አንድ ሰው ወደ በዓቱ መጥቶ የሰፋውን እንቅብ እንዲሸጥለት ይጠይቀዋል፡፡ ቅዱሱም እንቅቡን ሊሰጠው ወደ በዓቱ ከገባ በኋላ በሕሊናው የሰማዩን ነገር እያሰበ ከፈጣሪው ጋር በተመስጦ ሲነጋገር እንቅቡን ረሳው፡፡ ከበዓቱ ደጃፍ የቆመውም ሰው እንደ ገና እጁን አጨብጭቦ ቢጠራው፣ ቅዱስ ዮሐንስ ባዶ እጁን በመውጣት ‹ምን ፈልገህ ነው?› ሲል ጠየቀው፡፡ ያም ሰው ‹አሁን እንቅብ ልትሰጠኝ እኮ ገብተህ ነበር ለምን ባዶ እጅህን ተመለስክ?› አለው፡፡ ቅዱሱም ‹አዎን! አዎን!› ብሎ መልሶ ወደ በዓቱ ገባ፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም እንቅቡን ረስቶ በተመስጦ ከፈጣሪው ጋር መነጋገር ቀጠለ፡፡ ከውጭ የቆመውም ሰው ለሦስተኛ ጊዜ አጨብጭቦ ቢጠራው፣ ቅዱስ ዮሐንስ ወጥቶ ‹ምን ነበር የፈለግኸው;› በማለት ደግሞ ጠየቀው፡፡ ገዢውም እንቅብ ነበር የጠየኩህ ሲለው፣ ቅዱሱ ‹እንቅብ፣ እንቅብ፣ እንቅብ› እያለ ወደ በዓቱ ተመልሷል፡፡ በዚህም ምክንያት ከወጣንያን (ጀማሪ) መነኮሳት በቀር ሕሊናቸው በአንክሮ የሚያዝባቸው ፍጹማን መነኮሳት ምንም ዓይነት ተግባረ ዕድ እንዳይሠሩ በገዳም ታዟል፡፡

በተለይ ዕረፍትና ጸጥታ ያለበትን የብቸኝነት ሕይወት የመረጡ አበው ይህን የጽሙና ጊዜያቸውን ማንም እንዲሻማባቸው አይፈልጉም፡፡ በንግግርና በጨዋታ ምክንያት ሕሊናቸው መንፈሳዊውን ነገር ከማሰብ እንዳያቋርጥ ስለሚፈሩ፣ ወደ በዓታቸው ለሚመጡ ሰዎች ሁሉ የሚያቀርቡት ጥያቄ አንድ ነበር፣ እርሱም ‹ሂዱልን!› የሚል ነው፡፡ በዚህ መንገድ ሰዎችን ከበዓታቸው ደጅ ይመልሱ ከነበሩት ቅዱሳን ውስጥ አባ አርሳንዮስና አባ ጴሜን ይጠቀሳሉ፡፡ የፍጹማን መነኮሳትና ባሕታውያን አኗኗራቸው እንዲህ ነው፡፡ ፈቃዳቸው ብዙ ከሆኑ የሰው ልጆች እየሸሹ፣ የእግዚአብሔርን አንዲት ፈቃድ ሌሊትና ቀን በልባቸው በማሰብ ይኖራሉ፡፡ ብቻቸውን ሲሆኑ አይታወኩም፡፡ ሰላማቸውም እንደ ወንዝ ውኃ ይፈስሳል፡፡

እኛ በዓለም ያለን ሰዎች ግን ይህን ተረድተን ዕረፍት አንሰጣቸውም፡፡ የላመ የጣመ ምግብ ይዘን በዓታቸው ድረስ እንሄዳለን፡፡ የዓለሙን ርኩሰትና እርባና ቢስ ወሬዎች እየነገርን የጠራ ሕሊናቸውን እናደፈርሳለን፡፡ ፋታ ሳይሰጥ ለሚፈትናቸው ሰይጣን ጦር አቀባይ እንሆንባቸዋለን፡፡ ብንችል ‹ጸሎት ያደርጉልኛል› በሚል ሰበብ ከበዓታቸው አፍልሰን በከተማ ሰርቢሶቻችን እናስቀምጣቸዋለን፡፡ ያም ባይሆንልን ‹የበቁ አባት በዚህ ቦታ አሉ!›፣ ‹እኚህ አባት አያሳዝኑም!› እያልን ምስላቸውን በየሶሻል ሚዲያው በመለጠፍ ወደ ሸሹት ዓለም በዲጅታል በር ልንመልሳቸው እንሞክራለን፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላም ራሳችን በዘረጋነው ወጥመድ ተጠልፈው ሲወድቁ ደግሞ ገመናቸውን ለመዘገብና ‹አቤት መነኩሴ!› እያሉ የሐሜት ነጋሪት ለመጎሰም ግምባር ቀደሞቹም እኛው ነን፡፡ ለምን በበዓታቸው እንዲመሰጡ አንተዋቸውም?! ለእኛም የሚጠቅሙን እኛን ትተው ከፈጣሪ ጋር ሲሆኑ ነው፡፡ ግድ የለም እስኪ እነርሱን መርጠው ለተሰደዱለት እግዚአብሔር እንተዋቸው?!

በአንድ ወቅት በበረሃ ያሉ አበውን እየዞሩ መጠየቅ ልማድ ያደረጉ ወንድሞች ወደ ቅዱስ ቴዎፍሎስ ዘእስክንድርያ መጥተው ምክረን ሲሉ ጠየቁት፡፡ ቅዱስ ቴዎፍሎስም ለእነዚህ ወንድሞች የሰጣቸው ምክር በጣም የሚያስደንቅ ነበር፡፡ ምን አላቸው? ‹‹አርሳንዮስን አትረብሹት!››፡፡ እውነት ነው፤ እኔም ‹‹አርሳንዮሳውያንን አንረብሻቸው›› ብዬ ጽሑፌን አበቃሁ!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
እግዚአብሔር ሁልጊዜ ወደ መከራ እንዳትገባ አያደርግም። አንዳንድ ጊዜ በወጀብ ውስጥ መንገድ ያዘጋጅልሃል። ግፊው በሚበዛበት ዐውሎ ነፋስ እያለፍህ ተፍገምግመህ እንዳትወድቅ ጉልበትህን ያጸናል፤ ኃይልን ያስታጥቅሃል። እንዲህ እያደረገ በመንፈስ ያጎለምስሃል።

እግዚአብሔር ዳንኤልን በአናባስት ጉድጓድ ከመጣል፣ ሠለስቱ ደቂቅን ወደ እቶን እሳት ከመግባት፣ ጳውሎስና ሲላስን ወደ ወኅኒ ከመውረድ ሊያድናቸው ይችል ነበር። ይሁን እንጂ እንዲህ አላደረገም። አምላካችን ፈተና ካለባቸው ቦታዎች ሁሉ ሊያወጣን ቃል አልገባምና። ነገር ግን በመከራ ጊዜያችን ሁሉ ከእኛ እንደማይለይና በእውነት ይዘነውም እንደ ሆነ በድል ነሺነት እናጠናቅቅ ዘንድ እንደሚረዳን ቃሉን ሰጥቶናል።

የጌታ እናት እመቤታችን የተወደደ ልጇን ይዛ በግብጽ በረሃ እንደ ወፍ ከተንከራተተች በኋላ ሕፃኑን የሚፈልገው ክፉ ሄሮድስ ሲሞት ተመልሳ ወደ ገሊላ ገብታለች። እንደ ድንግል ጌታን በመሐል እጅህ ብትታቀፍ እንኳን  ግብጽ መውረድ  አይቀርልህም። ይሁን እንጂ የመጣብህን መከራ ድል ነሥተህ ወደ ገሊላ መመለስህም እርግጥ ነው።

"ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል"
                              1ኛ ቆሮ 10፥13


ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
+++ የሚመጣው ዓለም ቋንቋ +++

ስለ እርሱ ለመናገር እጅግ ከባድ ነው። የማይታን አካል በእጅ ጠቁሞ ለማሳየት የመሞከር ያህል አስቸጋሪ ነገር ነው። ስለ "ዝምታ" እንዴት የእርሱ ተቃራኒ በሆነው "ንግግር" ልታብራራ ትችላለህ? ዝምታን በሚገባ ሊገልጽ የሚችለው አንድ ነገር ቢኖር ራሱ ዝምታ ነው። ዝዝዝምምም!

ዝምታ በቃል የማናብራራው በተግባር የምንገልጠው ሕይወት ነው። ሕይወት ነው ሲባል እንዲሁ እንዳይመስልህ፣ ያውም ግርማ የሚያላብስ ነዋ። ዝም ያለን እንኳን ሰው መናፍስት ይፈሩታል። ዝም የሚል ሰውን አጋንንት ይፈሩታል። ምክንያቱም የልቡ ሐሳብ ምን እንደ ሆነ ከከንፈሩ ላይ አይሰሙምና "ምን ሊያደርግ ይሆን?" እያሉ ሲጨነቁ እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል። በአንደበቱ የሚፈጥን ግን ያሰበውን በጎ ሐሳብ ገና ሳይጀምር ሰይጣን ሰምቶ ያሰነካክልበታል። ለሰይጣን እንዲህ ያለውን ሰው ከመጣል በላይ የሚቀለው ምንም ዓይነት ሥራ የለምና። አባ ኒለስ (Abba Nilus) እንደሚለውም "የጠላት ቅስቶች ጸጥታ የሚወደውን ሰው አይነኩትም። በተጨናነቀው ጎዳና መንገዱን ያደረገ ግን ደጋግሞ ሳይቆስል አይቀርም።"

ጫጫታና ኹከት በነገሠበት በዚህ ዓለም ንግግር ሰው ሁሉ የሚግባባበት ቋንቋ ነው። የማይናገር ሰው እንደ ሞኝ ወይም ፈዛዛ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል። በእርግጥ ለተፈቀደለት ዓላማ እና መጠን ብናውለው ኖሮ "ንግግር" ግሩም የፈጣሪያችን ሥጦታ ነበር። መናገር እኮ ተአምር ነው። በምድር ላይ ከሚንቀሳቀሱት ግዙፋን ፍጥረታ መካከል ነባቢው የሰው ልጅ ብቻ ነው። ምን ያደርጋል?! በጎውን ለክፋት፣ መልካሙን ለጥፋት ብናውለው ከንግግር ይልቅ ዝምታ የሚበልጥ ምግባር ሆነ። ንግግር በዚህ ዓለም ያለ መግባቢያ ሲሆን ዝምታ ግን ከሞት በኋላ በሚመጣው ዓለም ያለ ቋንቋ ሆነ። ከሞት በኋላ ያለችውን ዓለም ጣዕም ሳትሞት መቅመስ ትፈልጋለህ? እንግዲያውስ መንገዱን በ"ዝምታ" ጀምር። የአገሩን ቋንቋ የማያውቅ ሰው ለአገሩ ባዳ እንደሚሆነው፣ የሰማዩ ቋንቋ ዝምታን በዚህ ምድር ያልተለማመደ ሰው በሚመጣው ዓለም እንግዳ ይሆናል። 

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
ኅዳር 5/ 2015 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
ዓለም በድቅድቅ ጨለማ ሲኖር ሳለ ወደሚደነቅ ብርሃን የተጠራው በአንቺ ምስራቅነት ነው። አሁንም ጽዮን ሆይ ብርሃንን ጠልተን በጨለማ ለምንመላለስ ለእኛ አብሪልን። ክፋትን ወዶ የፍቅር እናቱ ለሆንሽ ለአንቺ ልጅ መሆን አይቻልምና፣ በንጹሕ ልብ ልጆችሽ ሆነን "እናታችን ጽዮን እንድንልሽ" ጽዮን ሆይ አብሪልን። አንቺን በምስጋና እንድንከብብ፣ በዙሪያሽም እንድንመላለስ፣ በፊትሽም እንማለል ዘንድ ጽዮን ሆይ አብሪልን። ኃጢአት ያደቀቀን እኛ አንቺን ተስፋ አድርገናልና፣ በብርታትሽም ልባችንን አኑረናልና፣ አዎን ጽዮን ሆይ አብሪልን!!!

"ጽዮንንም ባሰብናት ጊዜ አለቀስን"
መዝ 137፥1

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
ራስን መውደደ ኃጢአት ነው?
ራስን በመውደድና በራስ ወዳድነት መካከል ያለው ልዩነት?
ለራስ ጥሩ አመለካከት መኖርስ ከትሕትና ጋር ይጋጭ ይሆን?

ይኸው እዚህ ላይ እንዲመለከቱ የሰንበት ግብዣዬን አቅርቤያለሁ!


https://youtu.be/g31fgeYS-dM
እንደ እድል ሆኖ ያደግኹት በመልአኩ ቤት ነው። ስለ እርሱ በቃል የማይገለጽ ልዩ ፍቅር አለኝ። በሄድኩበት ሁሉ ስሙ ሲጠራ ከሰማኹ አንዳች የደስታ ስሜት ሰውነቴን ውርር ያደርገዋል። "ሚካኤል" ብዬ ያልቀለለ ሸክም፣ ያልተመለሰ ጸሎት የለኝም። አንዳንዴ መልአኩ በጣም ቅርቤ ይመስለኛል። ደግሞ ስለ እርሱ ሳስብ ያሳዝነኛል። ለምን? እንጃ ግን ለእኔ ስለሚያዝንልኝ ይሆናል። ስለ እኔ የሚጨነቅ፣ የሚሳሳልኝ ይመስለኛል። ስለዚህ ያሳዝነኛል። ሚካኤል የዋህ፣ ትሑት፣ ሰውን ወዳጅ መልአክ ነው። ሁልጊዜ ሲዘመር ደስ የሚለኝ መዝሙር አለ:- ነዋ ሚካኤል መልአከክሙ
         ይስአል ለክሙ በእንተ ምሕረት
ትርጉም:- "እነሆ ሚካኤል መልአካችሁ ምሕረትን ይለምንላችሁ"

ሚካኤል መልአኬ፣ ሚካኤል መልአካችን!

ከታናሽነቴ ጀምሮ እኔን የመገበኝ፣ ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ነው!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
ኀዳር ቅዱስ ሚካኤል /2015 ዓ.ም.
አዲስ አበባ
[email protected]

ድረ-ገጹን ይጎብኙ
www.dnabel.com
በውጭው ካሉት ይልቅ በአንተ ውስጥ የሚገኙት ፍትወታት ጠንካራ ጠላቶችህ ናቸው። ልክ ያልተሠራለት ምኞት ከባቢሎን እሳት ይልቅ ያቃጥላል። አልጠግብ ባይነትም ከጥፉት ውኃ ይልቅ ያሰጥማል። ያልተገራ ፍላጎት ማንነትን አስጥሎ የሰይጣን ባሪያ ያደርጋል። ራስን መግዛት የሰው ልጆች ጌጥ ነው። ዮሴፍ ግብጽን ከፈርዖን ሁለተኛ ሆኖ ከገዛበት ታላቅ ሥልጣን ይልቅ፣ በጌታው ሚስት ፊት ያሳየው ራስን መግዛት ይበልጥ ይደነቃል። ጠቢቡ "በመንፈሱ ላይ የሚገዛ ከተማ ከሚወስዱ (ከሚገዙ) ይበልጣል" እንዳለ።(ምሳ 16፥32)

ራስህን ነጻ ማውጣት ትፈልጋለህ? እንግዲያውስ ከውስጥህ ጀምር። ሁል ጊዜ ካልበላሁ የሚለው ሆድህ ስስት አስለምዶ በወንድምህ ላይ ጨካኝ እንዳያደርግህ ለሰውነትህ ጾም አስተምረው። "ነገ እሞታለሁና ልብላ ልጠጣ" የሚለውን የዐሣማ ፍልስፍናህን (Pig philosophy) ተውና አንተ በፈቃድህ እየተራብህ (እየጾምህ) ያለ ፈቃዱ የተራበው ወንድምህን በምጽዋት አጥግበው።

ጌታ ወደ እስራኤል የተመለሰው ሄሮድስ ከሞተ በኋላ ነበር።(ማቴ 2፥20) አንተ ውስጥ ያለውን ሄሮድስ የተባለ ክፉ ምኞት እንዲሞት ካላደረግኸው በቀር የተሰደደው ክርስቶስ ወደ አንተ ሊመለስ አይችልም። ይህ ክርስቶስን ከልብህ የሚያሳድድብህን ሄሮድስ እንዴት ልትገድለው ትችላለህ? እርሱንስ ወግተህ የምትጥልበት የብረት ካስማ ምን ይሆን? ለዚህስ ከጾም እና ከጸሎት የሚበረታ ምንም ዓይነት የጦር ዕቃ አታገኝም። በል እነዚህን ይዘህ ዝመትበት።

መልካም የነቢያት ጾም ይሁንልን!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ-ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com

ቴሌግራም
https://www.tg-me.com/Dnabel
†"ገና ሩቅ ሳለ አባቱ አየውና አዘነለት" ሉቃ 15:20†

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ ታሪኮች ሁሉ የእያንዳንዳችን ታሪኮች ናቸው ። በሉቃስ ወንጌል ላይ የጠፋውን ልጅ ታሪክ ስናነብ የምናገኘው አንድ ቁምነገር አለ ፤ ይኸውም የአባት ለልጁ ያለውን ርህራሄ ነው ፤ ምንም ያህል እንኳን ልጅ ቢበድል እና ከአባቱ ቤት ቢኮበልል ፣ ወደ አባቱ ቤት ለመመለስ ቆረጦ የመጣ ቀን ፣ አባት ከበፊቱ በበለጠ ፍቅር ልጁን ይቀበለዋል ፤ ቃሉ የሚለው " ገና ከሩቅ ሳለ አባቱ አየውና አዘነለት "  ነው ።

ምድራዊ አባት ለልጁ ይህንን ያህል ካዘነ ፤ ሰማያዊ አባት የሆነው እግዚአብሔርማ እንዴት አብልጦ አያዝን?  
ገና ከእግዚአብሔር ቤት ሩቅ ሆነን በኃጢአት ስንኖርም አይቶ ያዝንልናል ፤ ከኃጢአት ጋር ተፋተን የአባታችንን ቤት መርጠን ከተመለስን እና አባቴ ሆይ በሰማይና በፈትህ በደልኩ ማረኝ ያልነው እንደሆነ ፈጥኖ ይቅር ለማለት ይቸኩላል ፤ ይህ ልጄ ሞቶ ነበር ደግሞም ህያው ሆኗል ፤ ጠፍቶም ነበር ተገኝቷልም እያለ በሰማይ ካሉ የብዙ ብዙ መላእክቶች ጋር ደስ ይለዋል። 

ታዲያ መች ይሆን ይህን ሰማያዊ አባት ደስ የምናሰኘው ?
ዛሬ በህይወታችን የመጨረሻዋ በዚህ ምድር ላይ የምንኖርባት ቀን ብትሆንስ ማን ያውቃል? ተወዳጆች ሆይ በሉ ዛሬውኑ ተነስተን ወደ ንሰሐ አባታችን እንገስግስ በልባችን ትከሻ ላይ የከበደንን ቀንበር በፈቱ እንጣለው ፤ የእውነት በሆነ መመለስም በንሰሐ እንመለስ ፣ ለነፍሳችንም እረፍት እናግኝ  ፣ ተቅበዝባዥ ማንነታችንም ወደ ሰከነ ማንነት ይለወጥ ። በሉ ተነሱ አብረን እንገስግስ ክርስቲያን ነገ እንደሚሞት ሆኖ ነው ዛሬን መኖር ያለበት ። የመዳን ቀን አሁን ነው እንዳለ ሐዋርያው በሉ ተነሱ እንነሳ የቀጠሮ ሕይወት ይብቃን ።

ዲያቆን ብንያም አለባቸው
ሕዳር 14 /2015 ዓ. ም
+++ "ጌታ ሆይ አሰናብትልን" +++

ጌታ ሠላሳ ዓመት በምድረ በዳ የኖረ የዮሐንስ መጥምቅን ሞት በሰማ ጊዜ በታንኳ ወደ ምድረ በዳ ፈቀቅ ብሎ ሄደ። ብቸኛ ሆኖ ኖሮ የሞተውን ሰው ኃዘን ብቻውን ሆኖ ሊወጣ ወደ በረሃ ተሳፈረ። ነገር ግን የእርሱን መሄድ የሰሙት ሕዝቡ ብቻውን እንዲሆን አልተውትም። እርሱ በታንኳ ቢሄድ እነርሱ በእግር ተከትለውት መጡ። ጌታችንም ጠባቂ እንደ ሌለው መንጋ የሆኑትን ሕዝብ በፊቱ ባየ ጊዜ አዘነላቸው። እስኪመሽም ድረስ አስተማራቸው፤ ድውዮቻቸውንም ፈወሰ።

ታዲያ በዚህ መካከል የአገልግሎቱ አስተባባሪ የነበሩት ሐዋርያትን አንድ ነገር አሳሰባቸው፤ "ይህ ሁሉ ሕዝብ ምን ሊበላ ነው?" የሚለው የምግብ ጉዳይ። ይህን ጥያቄያቸውን ይዘው ወደ መድኃኒታችን መጡና "ቦታው ምድረ በዳ ነው አሁንም ሰዓቱ አልፎአል፤ ወደ መንደሮች ሄደው ለራሳቸው ምግብ እንዲገዙ ሕዝቡን አሰናብት" አሉት።(ማቴ 14፥15) ጌታችንም "አይይ ይህን የመሰለ ቃለ እግዚአብሔር ሲመገቡ አምሽተው እናንተ ስለ ምግብ ትጨነቃላችሁ? ባይበላስ?" ብሎ አላሳፈራቸውም። እርሱ የነፍስም የሥጋም ፈጣሪ ነው። በእለተ ማግሰኞ ለምግበ ሥጋ የሚሆኑ አዝርእትና ፍራፍሬን የፈጠረ አምላክ እንዴት የሰውን ረሃብ ቸል ይላል? ስለዚህም ለሐዋርያቱ "እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው እንጂ ሊሄዱ አያስፈልግም" አላቸው።(ማቴ 14፥16) ደቀ መዛሙርቱም ያለን ጥቂት ነው። ከሁለት ዓሣና ከአምስት እንጀራ በቀር ምንም የለንም አሉ።

ከሐዋርያቱ ጥያቄ እንደምንረዳው የምግብ ጭንቀታቸውን ያባባሰው አንደኛ ቦታው ምድረ በዳ መሆኑ፣ ሁለተኛ ደግሞ ሰዓቱ ማለፉ (መምሸቱ) ነው። ሙት ሲያስነሣ፣ ድውይ ሲፈውስ ያዩትን መምህራቸውን ምንም እንደ ቀደሙ አባቶቻቸው "እግዚአብሔር በምድረ በዳ ማዕድን ያሰናዳ ዘንድ ይችላልን?" ብለው ባያሙትም፣ በምድረ በዳ ሕዝቡን ይመግባል ብለው ግን አላመኑበትም ነበር።(መዝ 78፥19) አብሯቸው ያለው ጊዜ እና ቦታ የማይወስነው የብርሃኑን ጊዜ ቀን፣ የጨለማውን ጊዜ ደግሞ ማታ ብሎ ስም ያወጣላቸው በሰዓታት ላይ የሰለጠነ አምላክ መሆኑን አላስተዋሉም ነበር።

ክርስቶስ ሐዋርያቱን "እናንተ የሚበሉትን ስጧቸው" ብሎ ሲያዝዝ ደቀ መዛሙርቱ ጥቂት ብቻ እንዳላቸው ሳያውቅ ቀርቶ አይደለም። ነገር ግን ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ እንደሚነግረን እምነታቸውን ሊፈትን ነበር። በእርግጥም ፈተናቸው እንደ ጠበቀውም ዓይነት እምነት አላገኘባቸውም። "ያለን ጥቂት ነው" አሉት። ሐዋርያቱ ምን ያህል ቢይዙ ነበር አምስት ሺህ ሰው (ሴቶችና ሕፃናት ሳይቆጠሩ) መመገብ የሚችሉት? መቼም ቢሆን ለአምስት ገበያ ሕዝብ የሚሆን ምግብ ተሸክመው አይዞሩም። ስለዚህ አሁን ካላቸው አምስት እንጀራ እና ሁለት ዓሣ የሚበልጥ ምግብ ቢኖራቸው እንኳን ሕዝቡን ለማጥገብ የእግዚአብሔር በረከት ግድ ያስፈልግ ነበር። እነርሱ ያሰቡት በእጃቸው ያለውን ጥቂት ነገር እንጂ አብሯቸው ያለውን በብዙም በጥቂትም መሥራት የሚችለውን አምላክ አልነበረም። እርሱን ማሰብ ቢያስቀድሙ ኖሮ በጥቂቱ ነገር አይጨነቁም በብዙውም ነገር አይኮሩም ነበር።

እኛስ እጃችን ላይ ያለውን ጥቂት ነገር ብቻ አይተን "አሰናብትልን" ያልንበት ጊዜ የለም? የምእመናኑ ጥያቄ እና የእኛ ዝግጅት አልመጣጠን ሲለን ጥቂቱን ነገር ማብዛት ወደሚችል አምላክ ቀርቦ ከመጠየቅ ይልቅ ስንት ጊዜ "ጌታ ሆይ አሰናብትልን?" እያል ከነገሩ ለመሸሽ ሞከርን? በትዳር ጉዳይ ምክር ፈልጌ ነበር? "ጌታ ሆይ አሰናብትልን?"፣ ልጆቼን እንዴት ላሳድግ? -"ጌታ ሆይ አሰናብትልን?"፣ ኑሮዬን መምራት ቸግሮኛል -"ጌታ ሆይ አሰናብትልን?"፣ ከሱስ እንዴት ልላቀቅ -"ጌታ ሆይ አሰናብትልን?"...

እግዚአብሔር ከሰው ብዙ አይፈልግም። እጅህ ላይ ያለው ጥቂት ነገር ይበቃዋል። ለአምስት ሺህ ሕዝብ አምስት እንጀራን፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ሕዝብ ባሕረ ኤርትራን ለማሻገር አንድ የሙሴን በትር፣ አንድ ሺ ፍልስጥኤማውያንን ለመግደል አንድ የአህያ መንጋጋ ተጠቅሞ ድንቅ ሥራውን አሳይቶናል። ጥቂቱን ነገር ሲጠይቅህ እርሱን ለማቅረብ ወደ ኋላ አትበል። እርሱ ማብዛት፣ ማበርከት፣ ለብዙ ሕዝብ፣ ለብዙ ጉባኤ ማድረግን ያውቅበታል።

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
ኅዳር 16/ 2015 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
2025/07/14 21:35:03
Back to Top
HTML Embed Code: