Telegram Web Link
+++ የሰይጣን ነጻ አውጭ +++

ብዙ ጊዜ በsocial mideaም ይሁን በብዙኃን መገናኛ በስፋት የሚታዩና ትልቅ ተደራሽነት የሚኖራቸው ነገሮች በማኅበረሰቡ ዘንድ የተከለከሉ እና ተቀባይነት የሌላቸው ድርጊቶች ናቸው። እነዚያን ጉዳዮች በማውገዝም ይሁን "ጉድ እኮ ነው" በሚል አግራሞት ለሌሎች የሚያጋራቸውና አስተያየት የሚሰጥባቸው ተመልካች ቁጥር ጥቂት የማይባል ነው። ይህ ግርግር በራሱ ሙሉ በሙሉም ባይሆን በከፊል ግን በውስጣችን ያለውን "በተከለከለ ነገር የሚማረክ" ማንነታችንን በደንብ ያሳያል።(ይህ ሁኔታ በሥነ ልቡናው "forbidden fruit effect" በመባል ይታወቃል)

አይሆንም ተብለን እየተከለከልን በገባንበት ሱስ፣ ወዳጅነት፣ ፍቅር፣ ትዳር የምንሰቃይ ስንቶቻችን እንሆን?

ለመንፈሳዊ ሕይወታችንም ትልቅ እንቅፋት የሚሆንብን ይህ የተከለከለውን የሚያሳድድ ክፉ አመላችን ነው። ፈጣሪያችን "አታድርጉ" ሲለን እኛን ለመጠበቅ ሳይሆን የእኛን ዓለም ለማጥበብ ሲል ያሰረን ያህል ይሰማናል። የተሰጡንን ሕግጋት ካልጣስንም ነጻነታችንን ተግባራዊ ያደረግን አይመስለንም። የተፈቀደልንን አናደርግም፣ ያልተፈቀደልን ያንንም ሳናደርግ አንውልም። እኛ እንዲህ ነን፦ ቀኝ ሲጠብቁን በግራ፣ በግራ ሲያስሱን በቀኝ ብቅ የምንል ጉራማይሌ ነን።

ከሁሉ የሚያስደንቀው ደግሞ በዚህ ጠባያችን "የሰይጣን ነጻ አውጪ" እስከ መሆን መድረሳችን ነው። ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ተናገረው መድኃኒታችን ክርስቶስ ለዘመናት ባሪያ ያደረገንንና ሲረግጠን የኖረውን ሰይጣን በመስቀሉ ጠርቆ (አስሮ) ከመንገድ አስወግዶልናል።(ቆላ 2፥14) እኛን ከእርሱ ጋር በትንሣኤው ሲያስነሣን ያን ዕቡይ ጠላታችንን ግን እንሳለቅበት ዘንድ ከእግራችን ስር ጥሎልናል። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሰይጣን ጌታ ከተሰቀለባት እለተ አርብ በኋላ በብረት ሳጥን እንደ ታሰረ ውሻ ሆኗል ይለናል። ስለዚህ እንደ ፈቃዱ ሊፈነጭና ማንም ላይ ሊሰለጥን አይችልም ማለት ነው። ነገር ግን ሰው በፍላጎቱ ወደ ታሰረው ሰይጣን በሄደና መዝጊያውን በከፈተለት ጊዜ ለታሠረው ሰይጣን ነጻነት ይሰብካል። በክፋት ጥርሶቹ ነካክሶ ያደማው ዘንድ በገዛ እጁ በራሱ ላይ ያነግሠዋል። በዚህም ሰው የተፈቀደለትን ንግሥና ትቶ የተከለከለውን የዲያብሎስ ባርያነት ኑሮን ይገፋል።

አባ መቃርስ እንዳለው "የሚወደውን ባለጠጋ እግዚአብሔርን ጠልቶ የሚጠላውን ደሃ ሰይጣንን ወድዶ የሚከተል" ሰው ምን ያህል ሞኝ ነው?!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
ሰኔ 24፣ 2014 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

ቤተሰብ ይሁኑ

https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
+++ የሚመጣው ዓለም ቋንቋ +++

ስለ እርሱ ለመናገር እጅግ ከባድ ነው። የማይታይን አካል በእጅ ጠቁሞ ለማሳየት የመሞከር ያህል አስቸጋሪ ነገር ነው። ስለ "ዝምታ" እንዴት የእርሱ ተቃራኒ በሆነው "ንግግር" ልታብራራ ትችላለህ? ዝምታን በሚገባ ሊገልጽ የሚችለው አንድ ነገር ቢኖር ራሱ ዝምታ ነው። ዝዝዝምምም!

ዝምታ በቃል የማናብራራው በተግባር የምንገልጠው ሕይወት ነው። ሕይወት ነው ሲባል እንዲሁ እንዳይመስልህ፣ ያውም ግርማ የሚያላብስ ነዋ። ዝም ያለን እንኳን ሰው መናፍስት ይፈሩታል። ዝም የሚል ሰውን አጋንንት ይፈሩታል። ምክንያቱም የልቡ ሐሳብ ምን እንደ ሆነ ከከንፈሩ ላይ አይሰሙምና "ምን ሊያደርግ ይሆን?" እያሉ ሲጨነቁ እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል። በአንደበቱ የሚፈጥን ግን ያሰበውን በጎ ሐሳብ ገና ሳይጀምር ሰይጣን ሰምቶ ያሰነካክልበታል። ለሰይጣን እንዲህ ያለውን ሰው ከመጣል በላይ የሚቀለው ምንም ዓይነት ሥራ የለምና። አባ ኒለስ (Abba Nilus) እንደሚለውም "የጠላት ቅስቶች ጸጥታ የሚወደውን ሰው አይነኩትም። በተጨናነቀው ጎዳና መንገዱን ያደረገ ግን ደጋግሞ ሳይቆስል አይቀርም።"

ጫጫታና ኹከት በነገሠበት በዚህ ዓለም ንግግር ሰው ሁሉ የሚግባባበት ቋንቋ ነው። የማይናገር ሰው እንደ ሞኝ ወይም ፈዛዛ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል። በእርግጥ ለተፈቀደለት ዓላማ እና መጠን ብናውለው ኖሮ "ንግግር" ግሩም የፈጣሪያችን ሥጦታ ነበር። መናገር እኮ ተአምር ነው። በምድር ላይ ከሚንቀሳቀሱት ግዙፋን ፍጥረታ መካከል ነባቢው የሰው ልጅ ብቻ ነው። ምን ያደርጋል?! በጎውን ለክፋት፣ መልካሙን ለጥፋት ብናውለው ከንግግር ይልቅ ዝምታ የሚበልጥ ምግባር ሆነ። ንግግር በዚህ ዓለም ያለ መግባቢያ ሲሆን ዝምታ ግን ከሞት በኋላ በሚመጣው ዓለም ያለ ቋንቋ ሆነ። ከሞት በኋላ ያለችውን ዓለም ጣዕም ሳትሞት መቅመስ ትፈልጋለህ? እንግዲያውስ መንገዱን በ"ዝምታ" ጀምር። የአገሩን ቋንቋ የማያውቅ ሰው ለአገሩ ባዳ እንደሚሆነው፣ የሰማዩ ቋንቋ ዝምታን በዚህ ምድር ያልተለማመደ ሰው በሚመጣው ዓለም እንግዳ ይሆናል።

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
ኅዳር 5/ 2015 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንኹት፥ እርስዋንም እሻለሁ፥ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ የዘላለም ማረፊያው በሆነች በእናቱ ፍቅር እኖር ዘንድ፤ እርሷን ደስ አሰኝ ዘንድ ፤ ያማረው የፊቷንም ብርሃን እመለከት ዘንድ፤ በዓለም ካሉት አእላፋት ዝና ይልቅ ልቤ የድንግልን ፍቅር ይመኛል፣ የዓለሙ ዝና ነፍስን ለሚያቆስል ትዕቢት አሳልፎ ስለሚሰጥ ምን ይጠቅመኛል? የድንግል ፍቅር ግን ዕረፍትና ጸጥታ ይሆነኛል፣ ወደ መዳን መንገድም ስቦ ያስገባኛል፤ ልቡናዬ የክብርሽን ገናንነት ይናገር ዘንድ ይወዳል፥ መላሴ ግን በኃጢአት ፍሕም የተበላ ኮልታፋ ሆኖ ተቸግሯል፤ የልሳኔን ልቱትነት አርቀሽ፥ እኔ ደካማ ባሪያሽን በምስጋናሽ ቃል የምትሞይበት የኃይል ቀን መቼ ነው? ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ እንደ ምትናፍቅ እኔም ምስጋናሽን እየተጠማሁ ያቺን ቀን እናፍቃለሁ። መቼ እደርሳለሁ? መቼስ አንቺን አመሰግንሻለሁ?

ዲ/ን አቤል ካሳሁን
[email protected]
+++ "እመቤታችን ከጌታ ዕርገት በኋላ" +++

መድኃኔዓለም ክርስቶስ በቅዱስ መስቀሉ ላይ ባፈሰሰው ክቡር ደሙ የመሠረታትን ቤተ ክርስቲያን ለሐዋርያቱ አደራ ሰጥቷል፡፡ በመጀመሪያው ምዕት ዓመት በነበረው የቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ የጌታ እናቱ እመቤታችን የነበራት ድርሻ ትልቅ ነበር፡፡ ከክርስቶስ ዕርገት በኋላ እመቤታችን በሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ቤት ሳለች፣ የሐዲስ ኪዳኗ ቤተ ክርስቲያን ራስ እና ፈጻሚ የሆነው ክርስቶስ የተገኘባትን እርሷን ለማየት ከሁሉም የዓለም ክፍላት የሚመጡ ሰዎች ብዙ ነበሩ፡፡ ድንግልም ወደ እርሷ የመጡትን ሁሉ እየባረከች፣ ያዘኑትንም እያጽናናች፣ በንስሓ ሕይወት እንዲኖሩ በመምከር ተስፋና ደስታን እየሞላች ትሸኛቸው ነበር፡፡ በርግጥም እግዚአብሔር ሰው ሆኖ በምድር ላይ ለመገለጡ፣ እንደ ሕፃናት ጥቂት በጥቂት ለማደጉና በመጨረሻም ለፈጸመው የቤዛነት ሥራው ሁሉ እናቱና አገልጋዩ ከምትሆን ከእመቤታችን የበለጠ ምስክር ከየት ሊመጣ? እርሷን ለማየት ባይጓጉ ነበር የሚደንቀን፡፡

ከሰባ ሁለቱ አርድዕት አንዱ የሆነው ቅዱስ ሉቃስም ወንጌሉን ሲጽፍ በሕይወቷ ውስጥ የተፈጸሙ እርሷ ብቻ የምታውቃቸውንና ብቻዋን ሆና የሰማቻቸውን እንደ ብሥራት ያሉ ታሪኮችን በመንገር እረድታዋለች፡፡ ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ በቃልም በመጽሐፍም አይሁድን ተከራክሮ ድል ባደረጋቸው ጊዜ፣ ተቆጥተው ድንጋይ ሲያነሡበትና ሲከቡት ከሩቅ በማየቷ የሰማዕትነት ሥራውን በጽናት ይፈጽም ዘንድ በጸሎቷ እንዳበረታችው በጥንታውያን የታሪክ መዛግብት ሰፍሮ እናገኛለን፡፡

እመቤታችንን የማየት ዕድል ካገኙት አንዱ የሆነው ቅዱስ ዲዮናስዮስ ዘአርዮስፋጎስ እርሷን ባየ ጊዜ ሐዋርያቱ ሰው መሆኗን ባይነግሩት ኖሮ አምላክ መስላው እንደ ነበር ጽፏል፡፡ የፊቷን ደም ግባትና ሰላም፣ በእርሷም ላይ ይንጸባረቅ የነበረውን የቅድስና ብርሃን አይቶ በልጇ የማያምን እንደ ሌለም መስክሯል፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ደቀ መዝሙርና የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳስ የነበረው ቅዱስ አግናጥዮስም ለመምህሩ (ቅዱስ ዮሐንስ) በላከለት መልእክት፣ ክርስቲያኖች በሚሳደዱበት በዚያ ዘመን የእግዚአብሔር እናቱ እመቤታችን በስደቱ ደስተኛ እንደ ሆነች፣ በመከራዎችም ውስጥ ሆና እንደማታጉረመርምና እርሷንም ይነቅፉ በነበሩ ሰዎች እንዳልተቆጣች ይናገራል፡፡

እመቤታችን በልጇ ሕይወት ውስጥ ወሳኝ ታሪኮች የተፈጸሙባቸውን ስፍራዎች መጎብኘት ትወድ ነበር፡፡ የልደቱን ነገር፣ የእረኞችና የመላክቱን ዝማሬ፣ የጥበበኞቹን ስጦታ አስባ ቤተልሔም ትሄዳለች፡፡ ከሁሉም በላይ ግን መከራ ወደ ተቀበለበት ስፍራ መሄድ ታዘወትራለች፡፡ በዚያም የተቀበላቸውን ሕማማት፣ የደረሰበትን ተዋርዶ እና መከዳቱን እያሰበች ታነባለች፡፡ ‹ይህ ልጄ የተገረፈበት፣ ይህ የእሾህ አክሊል የተቀዳጀበት፣ ይህ ደግሞ መስቀል ተሸክሞ የሄደበት፣ ይህ የተሰቀለበት ነው› ትላለች፡፡ ወደ መቃብሩ ስፍራ ስትመጣ ግን በልዩ ደስታ እየተሞላች ‹‹ይህ በሦስተኛው ቀን ከሞት የተነሣበት ቦታ ነው›› ትል ነበር፡፡

በተሰጣት ቃል ኪዳን እኛ ኃጥአን የሆንን ልጆቿን ታስምረን!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
ፍቅር ከበጎች አንዱ የነበረውን ጴጥሮስን ለውጣ እንደ ጌታ በምእመናን ላይ እረኛ አደረገችው። ፍቅርን ስላገኘ ጌታን መሰለ።

አረጋዊ መንፈሳዊ

ፍቅር ያለው ሁሉ አለው።
የኃጢአተኞች ተስፋ የሆነው መድኃኒታችን በኢያሪኮ ገብቶ ሲያልፍ፣ የቀራጮች አለቃ ባለጠጋው ዘኬዎስ ሊያየው ወድዶ ነበር። ነገር ግን አልቻለም። ያለማየቱንም ምክንያት ጸሐፊው ቅዱስ ሉቃስ ሲነግረን "ቁመቱም አጭር ነበረና ስለ ሕዝቡ ብዛት አቃተው" ይለናል።(ሉቃ 19፥3) ዘኬዎስ ጌታን ማየት ያልቻለው በእርሱ የቁመት ማጠር ላይ የሕዝቡ ብዛት ተጨምሮበት ነው። ታዲያ ለዚህ ችግር ጥሩ መፍትሔ የሚሆነው "እስኪ ዘወር በሉ" እያለ ከእያንዳንዱ ሰው ጋር መጣላት ሳይሆን፣ የራሱን ቁመት ማጠር የሚፈታበት ሌላ መንገድ መፈለግ ነው። ስለዚህም ከፊቱ ወዳለው የሾላ ዛፍ ሮጦ ወጣ። "ባለጠጋ ነኝ፤ በዚያ ላይ ትልቅ ሰው። ራሴን እንደ ትንሽ ልጅ እዚህ ዛፍ ላይ ሳንጠለጥል የሚያየኝስ ምን ይለኛል?" አላለም። ዘኬዎስ ስለ ክብሩና ስለ ሰው አስተያየት ቢጨነቅ ኖሮ "ሰው የሆነውን አምላክ" ማየትና በቤቱ ማስተናገድ ይቀርበት ነበር። ብዙዎቻችን እኛ ክርስቶስን ክርስቶስም እኛን ከሚያይበት የሾላ ዛፋችን "ንስሐ" የምንርቀው "ሰው ምን ይለኛል?" በሚል አጉል ጭንቀት ነው።

አሁን ዘኬዎስ ከሾላው ዛፍ ላይ ነው። የቁመቱን ማጠር ችግር ለመፍታት ባደረገው ጥረት ከአንድ ሰው ጋር ሳይጣላ ያለ ማንም ከልካይ የፈለገውን ክርስቶስ ለማየት በቃ። ጌታም ከበለሷ ተክል ፈልጎ ያጣውን ፍሬ አሁን ከሾላው ዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ አገኘው።(ማቴ 21፥19) ይህም በሾላው ዛፍ ላይ የተገኘው ፍሬ "የዘኬዎስ ተነሳሒ ልብ" ነው።

አንዳንድ ጊዜ መንፈሳዊ ሕይወትህን፣ ዓላማህን እንዳታይ ከፊትህ ቆመው የሚጋርዱህ ውጫዊ ነገሮች ይኖራሉ። "ዘወር በሉልኝ!" እያልክ ከእነርሱ ጋር አትጋጭ። "ለምን ትከልሉኛላችሁ?!" በማለትም በብስጭት አታጉረምርም። እንደ ዘኬዎስ የራስህ ችግር ላይ አተኩር። የውጭውን ነገር ማማረር ትተህ እጥረትህን የሚቀርፍልህ የምትወጣበት ዛፍ ፈልግ። እዚያው ሆነህ ለመንጠራራት አትሞክር። ችግርህ ከመንጠራራት በላይ ነው። አትታክት፣ እስኪ መጋፋት ተውና መሬቱን ልቀቅ አድርግ። ያን ጊዜ ከማንም ሳትጣላ ከምትፈልገው እና ከናፈቅኸው ነገር ጋር ያለ ምንም ከልካይ በግልጽ ትተያያለህ። ብቻ የሕዝቡን ብዛት ትተህ የራስህ ማጠር ላይ አተኩር።

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
ሥጋዊ ኃይልና ጉልበት በሕመም ይደክማል። ጽኑዕ ደዌ ብርቱ ክንድን ልምሾ ያደርጋል። የታጠከው የጉብዝና ኃይል በእድሜህ አመሻሽ ይፈታል። ደዌ የማያደክመው እድሜ የማያጠፋው ጉልበት "ኃይለ እግዚአብሔር" ነው። ብዙ ድንቅ ያደረጉና የዓለምን አስፈሪ ነገሮች የታገሉ ታላላቅ ቅዱሳንን ተመልከት። እንደ ቅዱስ ቂርቆስ ያሉ ሰውነታቸው ያልጸና ሕፃናትን፣ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ በራስ ምታት፣ በጎን ውጋትና በቁስል የሚሰቃዩ የደዌ ሰዎችን፣ ከአናብስት ጋር እንደ ተፋለመው ቅዱስ አግናጥዮስ ያሉ አረጋውያንን ታያለህ። የተሻለ እንዳገለግል ይህ ደዌ ቢርቅልኝ፣ ጉልበቴ ቢመለስልኝ አትበል። የሰውነትህ ድካም በአንተ የሚሠራውን የእግዚአብሔርን ኃይል ሊያስቆመው አይችልም። ዓለምን በወንጌል ያጠመቀው እና ከሁሉ ይልቅ የደከመው ሐዋርያ ታማሚው ጳውሎስ መሆኑን አትርሳ።

+++ "አቤቱ ጕልበቴ ሆይ፥ እወድድሃለሁ" መዝ 18፥1 +++

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
እንደ እድል ሆኖ ያደግኹት በመልአኩ ቤት ነው። ስለ እርሱ በቃል የማይገለጽ ልዩ ፍቅር አለኝ። በሄድኩበት ሁሉ ስሙ ሲጠራ ከሰማኹ አንዳች የደስታ ስሜት ሰውነቴን ውርር ያደርገዋል። "ሚካኤል" ብዬ ያልቀለለ ሸክም፣ ያልተመለሰ ጸሎት የለኝም። አንዳንዴ መልአኩ በጣም ቅርቤ ይመስለኛል። ደግሞ ስለ እርሱ ሳስብ ያሳዝነኛል። ለምን? እንጃ ግን ለእኔ ስለሚያዝንልኝ ይሆናል። ስለ እኔ የሚጨነቅ፣ የሚሳሳልኝ ይመስለኛል። ስለዚህ ያሳዝነኛል። ሚካኤል የዋህ፣ ትሑት፣ ሰውን ወዳጅ መልአክ ነው። ሁልጊዜ ሲዘመር ደስ የሚለኝ መዝሙር አለ:- ነዋ ሚካኤል መልአከክሙ
         ይስአል ለክሙ በእንተ ምሕረት
ትርጉም:- "እነሆ ሚካኤል መልአካችሁ ምሕረትን ይለምንላችሁ"

ሚካኤል መልአኬ፣ ሚካኤል መልአካችን!

ከታናሽነቴ ጀምሮ እኔን የመገበኝ፣ ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ነው!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
ኀዳር ቅዱስ ሚካኤል /2015 ዓ.ም.
አዲስ አበባ
[email protected]

ድረ-ገጹን ይጎብኙ
www.dnabel.com
+++ "በእኛ ውስጥ ያሉ አራዊት" +++

ምክንያታዊ ያልሆኑ (irrational) ዓሦችን ትገዛ ዘንድ ሥልጣን ተሰጥቶህ እንደ ነበር፣ እንዲሁ ምክንያታዊ ባልሆኑ ስሜቶችህም ላይ ገዢ ሆነሃል። "የምድር አራዊትንም ሁሉ ይግዙ" ስለተባለ በዚህም በእኔ ውስጥ ያሉት አራዊት ምንድር ናቸው? ትላለህ። በእርግጥም በሺዎች የሚቆጠሩና በዝተው የተጨናነቁ አራዊቶች በአንተ ውስጥ አሉ። ይህንንም ስልህ ንግግሬን ስሜትን እንደሚጎዳ ጽርፈት (ስድብ) አድርገህ አትውሰደው።

ትንሹ አውሬ "ቁጣ" በልብህ ውስጥ በጮኸ ጊዜ ከውሾች ይልቅ የከፋ አውሬ አልሆነም? ማንኛውም ያደፈጠ አውሬን ከመግራት አታላይ በሆነች ነፍስ የሚደረግን የተንኮል ማድፈጥ መግራት የበለጠ አስቸጋሪ አይደለምን? ትምክህተኝነት አውሬ አይደለምን? በስድብ የሰላስ ሰው እንደ ጊንጥ አይደለምን? በበቀል ጥም በስውር ሊያጠቃ የተሸሸገ ከእፉኝት ይልቅ አይከፋምን? ስስታም ሰውስ የሚስገበገብ ቀማኛ ተኩላ አይደለምን? በእኛ ውስጥ የሌለ እንደ ምን ያለ አውሬ ነው? ሴቶችን ባየ ጊዜ የሚቅለበለብስ የተቀለበ ፈረስ አይደለምን? መጽሐፍ ቅዱስ " እንደ ተቀለቡ ፈረሶች ሆኑ፤ እያንዳንዳቸውም ከባልንጀሮቻቸው ሚስቶች ኋላ አሽካኩ" ይላልና።(ኤር 5:8) ነቢዩ ሰዎቹ ከራሳቸው ጋር ካዛመዱት እኩይ ፍትወት የተነሣ ከሴቶቹ ጋር " ያሽካካሉ" አለ እንጂ "ይነጋገራሉ" አላለም። ስለዚህም በእኛ ውስጥ ብዙ አራዊት አሉ።

በውጪ ያሉትን እየገዛህ በውስጥህ ያሉትን ግን ያለ ገዢ ብትተዋቸው በእውነት የአራዊት ገዢ የምትሆን ይመስልሃል? ምክንያተኝነትህን ተጠቅመህ አንበሳን በመግዛትህና ግሳቱንም እንደ ተራ ጩኸት በመናቅህ፣ ነገር ግን ጥርስህን እያፏጨህና ወል የሌለው ድምጽ እያሰማህ በአንድ ጊዜ ተቆጥተህ ለማጥቃት የምትታገል አንተ በእውነት ገዢ ነህ? የሰው ልጅ በስሜቱ ሲገዛ (ሲነበብ ይጠብቃል)፣ ቁጣውም (ንዴቱ) ምክንያተኝነቱን ወደ ጎን ገፍታ ቦታ በማሳጣት በነፍሱ ላይ ስትሰለጥን ከማየት የበለጠ ምን አደገኛ ነገር አለ?

በእርግጥም አንተ የስሜቶች ፣የአራዊት ፣በደረታቸው የሚሳቡና በክንፋቸው የሚበሩ ፍጡራን ሁሉ ገዥ ሆነህ የተፈጠርህ ነህ። ቀላል የሆኑና በኅሊናህ ውስጥ የማይረጉ አየራዊ ሐሳቦች አይኑሩህ። በራሪ በሆኑ ነገሮችም ላይ ትገዛቸው ዘንድ ተሹመሃልና። …የፍጡራን ሁሉ ገዥ ትሆን ዘንድ በቅድሚያ በአንተ ውስጥ ያሉትን ሐሳቦች ግዛ። በእንስሳት ላይ የተሰጠን የገዢነት ሥልጣን የእኛ በሆኑት ነገሮች ላይም ገዢዎች እንድንሆን ያለማምደናል።

ቅዱስ ባስልዮስ ዘየዐቢ ስለ ሰው ተፈጥሮ ካስተማረበት ድርሳን የተወሰደ

ትርጉም : ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
ሰው ከሌሎች በምድር ካሉ ሕይወት ያላቸው ፍጥረታት የሚለየው ለባዊት ነፍስ (rational soul) ያለችው እና እግዚአብሔርን የመምሰል እድል የተሰጠው እንስሳ ሆኖ መፈጠሩ ነው። አምላኩ በምክንያታዊነት የሰላ፣ ውስብስብ ነገሮችን ማሰላሰል የሚችልበትን ትልቅ ማንነት ሰጥቶ ፈጥሮታል። "ማሰብ" ሰው በምድር ካሉ ፍጥረታት ሁሉ የሚለይበት አንደኛው መልኩ ነው። እግዚአብሔርም "ግዛ" የሚለውን የሥልጣን ማኅተም ያሳረፈው የሰው "ሐሳብ" ላይ ነው። ሰው ክንፍ ባይኖረውም በተሰጠው የማሰብ ጸጋ ሲሻው እንደ ንሥር ከፍ ብሎ በሰማይ ይበራል። ከፈለገም የብሱን ትቶ እንደ ዓሣ አንበሬ ወደ ጥልቁ ይወርዳል። "ሐሳብ" ትልቅ ነገር ነዋ!

ሰይጣን ደግሞ ይህን ትልቅ ጸጋ ሊያበላሽ ሲፈልግ ሰው ለሐሳቡ ከመጠን በላይ የተጋነነ ግምት እንዲሰጥ እና ያልሆነውን "ነኝ" እንዲል ያመቻቸዋል። ያ ሰው መንፈሳዊ ከሆነም እሬቱን ለመሸፈን እንደ ማር የሚጠቀመው እና እርሱን የሚያሞኝበት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አያጣም። እውነታው ግን በዚህ ተንኮሉ የሚያስብ አድርጎ የፈጠረውን አምላክ እንዳያስብ እና በራሱ ማስተዋል ላይ ብቻ እንዲደገፍ ያደርገዋል። "አእምሮህ ውስጥ የተሰወረ እምቅ ኃይል አለህ"፣ "ያሰብከውን ሁሉ ትሆናለህ"፣ "ብቻህን ትችላለህ"፣ "ማንም አያስቆምህም"፣ "አንተ ለራስህ ብቁ ነህ" የሚሉ መርዛማ ጥቅሶችን ኅሊናው ላይ ይረጭበታል። ወደ ፈጣሪው ቀና ብሎ ረድኣቱን የሚለምንበትን ትሕትና አሳጥቶ "ሐሳቡን" አምላኪ ያደርገዋል። ይህ ደግሞ ትልቅ መንፈሳዊ ውድቀት ነው።

ያልሆኑትን ነኝ ብሎ ማሰብና ያንን መስሎ ለመታየት መጣር በሰው ልጅ ምድራዊ ሕይወትም ላይ የሚያመጣው ኪሳራ ቀላል አይደለም። አንደኛ ሁል ጊዜ ብሆን ብሎ የሚያስበውን ነገር ለማስመሰል ሲጥር መሆን የሚችለው ላይ ሳይደርስ ጊዜውን በከንቱ ይፈጃል። ሁለተኛ ይህ "አስመሳይነቱ" ከሰው ጋር ያለውን ግንኙነትና አጠቃላይ ማኅበራዊ ኑሮውን ያውክበታል። ሽራፊ ሳንቲም ሳይኖረው ሚሊየነር ነኝ የሚል ሰው ቢራብ የሚያበላው፣ ቢታመም የሚያሳክመው፣ ቢወድቅ የሚያነሣውን በቀላሉ ለማግኘት ይቸገራል። "አለኝ" የሚለው አጉል አስተሳሰቡ የወንድሞቹን ሐዘኔታ ያነጥፍበታል።

ሰውነትን ያላገናዘበ "ያሰብኩትን ሁሉ ይሆናል" የሚለው የ"law of attraction" ጉዞ መጨረሻው ክፉ ነው። ተኝቶ ሲርበው አፉ ውስጥ የሌለውን ጡት እንደሚምግ ምስኪን ሕፃን ባልተጨበጠ ነገር የ"wish fulfillment" ቅዘት ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋል። በዚህ ሕልም ውስጥ ያለ ሰው ደግሞ መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር የሚጣጣም አስተሳሰብ ስለሌለው ፍጻሜው የአእምሮ ሕመምተኛ መሆን ነው።

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
👍1
በሕይወት ውስጥ መጀመሪያ ከፊት የሚመጡት ሰዎች "ሔዋንህ" ወይም "አዳምሽ" ላይሆኑ ይችላሉ። ልክ አዳም ከተፈጠረ በኋላ መጀመሪያ በእርሱ ፊት እንስሳትን እንዳገኘ እና ለእነርሱም የሚገባቸውን ስም እየሰጠ እንዳሰናበታቸው፣ አንተም አንዳንዴ በኑሮህ ቀድመህ የምታገኛቸው አካላት "ጎረቤት፣ የሥራ ባልደረባ፣ ጓደኛ" እያልክ ስም የምታወጣላቸው ብቻ ይሆናሉ። ለምን? "እንደ አንተ ያሉ (የሚመቹ) ረዳቶች" አይደሉማ። አዳም ለእንስሳት፣ ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ሁሉ ስም ካወጣላቸው በኋላ መጽሐፉ "ለአዳም እንደ እርሱ ያለ ረዳት አልተገኘለትም ነበር" ይላል።(ዘፍ 2፥20)

አዳም እንደ እርሱ ያለ ረዳት ከእንስሳቱ መካከል ፈልጎ በማጣቱ "በቃ የምን መኩራት ነው? ያሉት እነዚህ ስለሆኑ እኔን ባትመስል እንኳ ትንሽ ለእኔ የቀረበችውን ብመርጥ ይሻላል" አላለም። ከሌሎች ይልቅ በአካላዊ ቁመና ለእርሱ የምትቀርበውን ትልቅ ጦጣ (Chimpanzee) መርጦም ወደ ፈጣሪው በመውሰድ "እባክህ ጌታዬ፣ ለአንተ የሚሳንህ የለምና ትንሽ ጸጉሯን ብትቀንስ፣ ጅሯቷን ብታጠፋ እና ፊቷ አካባቢ ማስተካከያ ብታደርግላት እንደ እኔ ያለ ረዳት ትሆናለች" ብሎ ሲማጸን አናገኝም። ይህን ቢያደርግ ኖሮ አሁን የአዳምን ታሪክ የምናነብ ሰዎች ሁሉ በችኮላው እየተገረምን እንስቅበት ነበር። ምክንያቱም እግዚአብሔር ከጥቂት ቀን በኋላ አጥንቷ ከአጥንቱ፣ ሥጋዋ ከሥጋው የተፈጠረ ሔዋን የተባለች እጅግ ውብ ሚስት እንደሰጠው ስለምናውቅ።

ከአንተ ጋር በሃይማኖት፣ በአመለካከትና ይህን በመሳሰሉት ነገሮች ጨርሳ ልትገጥም የማትችል የማትመችህን ረዳት "ለአንተ ምን ይሳንሃል? አስተካክልልኝ" እያልክ ለምን ትታገላለህ። በፍጹም ስለማይሆንሽ ሰው ለምን የmodification ጥያቄ ታቀርቢያለሽ? ጥቂት ጊዜ ከታገስህ እግዚአብሔር ለአንተ የምትመችህን (compatible) ረዳት ያመጣልሃል። አሁን ግን ፊት ለፊት ያገኘሃት ጥሩ የሥራ ባልደረባ ወይም ጓደኛ እንጂ የምትመች ረዳትህ አይደለችም።

በሕይወት ውስጥ ቀድሞ የመጣ ሁሉ ባል ወይም ሚስት አይሆንም። መጽሐፍ ቅዱስም "ቢቻላችሁስ... ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ" ይላል እንጂ "ከሁሉ ጋር ተጋቡ" አላለንም።(ሮሜ 12፥18)

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
+++ "ክረምትን ለምን ፈራሁ?" +++

በጋና ክረምትን እያፈራረቀ የሰውን ልጅ ሁሉ የሚመግብ እግዚአብሔር ነው። በክረምት ገበሬው ይዘራል፣ እግዚአብሔር ደግሞ ከሰማይ ጠሉን ይልክለታል። በክረምቱ ጊዜ ተዘርቶ ያደገው ሰብል እንዲበስል ፈጣሪው የበጋውን ፀሐይ ያወጣለታል። ትጉሁ ገብሬም የደረሰውን አዝመራ ሊሰበስብ በበጋው ማጭዱን ይዞ ይታያል። ክረምት ለገበሬው የሥራ ጊዜ ነው።

ለእኔ ግን ክረምት ያስፈራኛል። እንዳልጽፍ እጆቼ በብርዱ ቆፈን ይያዛሉ፣ እንዳላነብ አይኖቼ በእንቅልፍ ሽፋሽፍት ይፈዝዛሉ። ማልጄ በቤቴ መስኮት የማያት ፀሐይ በደመና ስትሸፈን ቀኑ የጀመረ ሌሊቱም የነጋ አይመስለኝ። ከአልጋዬ ተነሥ ተነሥ አይለኝም። ውጪው ሲጨልም ቤቴም ይደበዝዝብኛል። ወጥቼ ሥራዬን እንዳልሠራ፣ ከወዳጆቼ ጋር ተገናኝቼ እንዳላወጋ ዝናቡ አላላውስ ይለኛል። ለእኔ ክረምት ያስፈራኛል።

ግን ለምን ክረምትን ፈራሁት? እንደ ገበሬው የዝናብን በረከት ማየት ስላቃተኝ ይሆን? ወይስ የምዘራው ዘር በእጄ ስለሌለ? እንዲጸድቅ የምፈልገው ተክል፣ ልምላሜውን ማየት የሚያጓጓኝ እጽ የለኝ ይሆን?

በሥራ እና በግል ጉዳዮቼ ተጠምጄ ከራቅኋቸው ከቤቸሰቦቼ ልብ ላይ የምዘራው ብዙ የፍቅር ዘርማ አለኝ። በሰዎች ሆታ እና ጩኸት ስከበብ የዘነጋሁት በመልካም ሰብእና እንዲጸድቅና እንዲለመልም የምፈልገው እኔነት አለኝ። ታዲያ ለራሴ የሚሆን በቂ ጊዜ አግኝቼ ውስጤን አርስ፣ እመረምርና አለሰልስ ዘንድ ክረምት የመጣው፣ ዝናቡስ የዘነበው ለእኔ ብሎ አይደል?

ለካ የብርዱ ቆፈን የበረታብኝ፣ የአይኖቼ ሽፋሽፍት በእንቅልፍ የደከሙብኝ ክረምትን ስለማልወደው ሳይሆን የክረምትን በረከት ማስተዋል ስላልቻልኩ ነው። ለካስ ክረምቱ የደበተኝ "ደግሞ ሊመጣ ነው" ብዬ ቀድሜ ስላወገዝኩትና ራሴን ለሥራ ስላላዘጋጀሁ ነው። ሰማዩ ሲደምን እና ዝናቡ አላስወጣ ብሎ ሲዘንብ በእኔ ውስጥ ያለችውን ፀሐይ ፈልጌ እንድገልጣት እድል እየሰጠኝ ነው። ክረምት የደረቀው እጽ መልሶ የሚያቆጠቁጥበት ብቻ ሳይሆን ያረጀውና ሊወድቅ ያዘመመው ውስጤ የሚታደስበትና የሚጠገንበት ጊዜ ነው። ለካስ ክረምት ለገበሬ ብቻ የመሰለኝ ስህተት ነው። ክረምት ለእኔም ነው!

(ክረምት ሲገባ እና ፀሐይ አዘውትራ መታየት ስታቆም ከዚህ ጋር ተያይዞ "Seasonal affective disorder" የተባለ ድባቴ ውስጥ ለሚገቡ ሁሉ መታሰቢያነት የተጻፈ)

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
ሰኔ 26፣ 2013 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

ቤተሰብ ይሁኑ

https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
+++ ማነው የሚያድነኝ +++

ለዚህ ለኃጢአት ሕግ ከተሰጠ
ከሕይወት መርገምን ከመረጠ
ለሞት ከተሰጠ ከንቱ ኑሮ
ማነው የሚያድነኝ ሞትን ሽሮ/2x/
ሥጋ በሥጋ ሕግ ይሰበኛል
መንፈስ በመንፈስ ሕግ ይመራኛል
ለየትኛው ጌታ ተገዝቼ
የቱን እመርጣለሁ አንዱን ትቼ
ኃጢአት እሰራና ይጨንቀኛል
አምላኬ ሲለየኝ ይሰማኛል
ጌታዬ ሲለየኝ ይሰማኛል

https://youtu.be/kjyAINE2D2I
2025/07/09 02:18:37
Back to Top
HTML Embed Code: