Telegram Web Link
ከመላእክት ጋር አብረን የምንዘምርበትን የዜማ ሥርዓት ለሠራልን፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ የወረደውን የምስጋና ማዕድ ለእኛ እንደሚገባ አድርጎ ላደረሰ ታማኝ መጋቢ፣ ለዘማሪው፣ ለተርጓሚው፣ ለባለ ቅኔው ለቅዱስ ያሬድ ማኅሌታይ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሰን።

-የአንደበት አመጽ ጸጋን አስገፍፎ እንዴት የመልአክነትን ክብር እንደሚያሳጣ በሳጥናኤል አየን!

-የአንደበት ፍሬ እንዴት እንደሚያከብር እና ምድራዊ መልአክ እንደሚያደርግ ደግሞ በቅዱስ ያሬድ ማኅሌታይ ተመለከትን!

አቤቱ የያሬድን ልሳን ስጠኝ!

ዲያቆን አቤል ካሣሁን
[email protected]
https://www.tg-me.com/Dnabel
የፊታችን ረቡዕ ሌሊት 11፡00 ሰዓት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ትምህርት ስለምንጀምር በየትኛውም ዓለም የምትኖሩ እና መማር ፈቃዳችሁ የሆነ ሁሉ ከታች የተቀመጠውን የZoom link በመጠቀም ልትቀላቀሉን ትችላላችሁ::

“ብዙ ምርኮ እንዳገኘ በቃልህ ደስ አለኝ” መዝ 119:162

https://us02web.zoom.us/j/81873667259?pwd=R2ZGVWVEamhLZU5aVk1PeXhxcGFrdz09
አጭር ግን ቶሎ እጅ የሚያሰበስብ ቃል ነው። ቅዳሴ ላይ በሰማሁት ቁጥር ሁሌ “እንዴት ሆኜ አይቶኝ ይሆን?” እንድል የሚያደርገኝ ጉልበታም ንግግር ነው።

“እግዚአብሔር ያያል!”
ረቡዕ ግንቦት 21 ሌሊት 11 ሰዓት (በኢ/ያ አቆጣጠር) ሁለተኛ ክፍል ትምህርታችንን እንቀጥላለን። ትምህርቱ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ላላችሁ ሁሉ ክፍት ነው። ባለፈው ሳምንት ያሳያችሁን ሰዓት አጠባበቅ እና ትጋት በዚህም ሳምንት አይለይዎ!

“እንዲህም የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ ደግሞ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ” 2ኛ ጴጥ3:15

https://us02web.zoom.us/j/81873667259?pwd=R2ZGVWVEamhLZU5aVk1PeXhxcGFrdz09
የቅዱስ ኤፍሬም ድርሳናት ፍሬ

በትውልድ እንግሊዛዊው እና ለብዙ ዘመናት የፕሮቴስታንቲዝም አንዱ ቅርንጫፍ በሆነው የአንግሊካን እምነት ውስጥ የቆየው ዕውቁ ሊቅ ሰባስትያን ብሮክ ቅዳሜ ግንቦት 18 (May 25) በሶርያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥምቀተ ክርስትና ተፈጽሞለት በቅብዓ ሜሮን ከብሮ ዋለ።

ሰባስትያን በኦርቶዶክሱ ዓለም በሶርያ የሚገኙ ጥንታዊ የሆኑ የነ ቅዱስ ኤፍሬም ድርሳናትን ከጥልቅ ሐተታዎች ጋር በመተርጎም እና የሶርያን ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ሕይወት በማጥናት በሰፊው ይታወቃል። በዚህ ዙሪያ የሠራቸው እና ያሳተማቸው የጥናት እንዲሁም ትርጉም መጻሕፍት ዝርዝር ብቻ ወደ ሠላሳ ገጽ ይሆናሉ። የሶርያም ቤተ ክርስቲያንም ለዚህ ድካሙ የቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ሜዳልያ (Medal of St. Ephrem the Syrian) የተባለውን በክብር አበርክታለታለች።

እነዚያን ወርቅ የሆኑ አጥንት ድረስ ዘልቀው የሚወጉ የማር ኤፍሬምን ድርሳናት ከውጭ (በሃይማኖት) ሆኖ መተርጎሙ ሁሌ ያሳዝነኝ ነበር። ታምሞ ግን የሚድንበትን መድኃኒት ተሸክሞ እንደሚቸገር ምስኪን ሰው አድርጌም አስበው ነበር። ድርሳናቱ መቼ ነው ወደሚድንበት መርከብ እየመሩ የሚያስገቡት ብዬ ብዙ ጊዜ እጠይቅ ነበር።

ያለፈው ቅዳሜ ግን ይህን ኀዘን የሚሽር የምሥራች ሰማሁ። ለካስ ቅዱሱ የቀጠረለት ቀን ነበር?! ይኸው የኤፍሬም ቀለም የበላውን (ያቃጠለውን) ምሁር ከኦርቶዶክሳዊው ካህን ስር በትሕትና በርከክ ብሎ አየሁት።

ይህ መመለስ የቅዱሱ ምልጃ እና በቅዱስ ኤፍሬም ድርሳን ያለቀሱ የብዙ የዋሃን ምእመናን እንባ ውጤት ነው።

የአበው ድርሳን አሁንም በሥራ ላይ ነው!!!

ዲያቆን አቤል ካሣሁን
[email protected]
"አርእይኒ ገጸ ዚአኪ ማርያም ምእረ፤ ዘኢይሰምዖ ካልዕ እንግርኪ ነገረ"
"ማርያም ሆይ፣ ለሌላው የማልነግረውን ነገር እነግርሽ ዘንድ አንድ ጊዜ ፊትሽን አሳይኝ"

መልክአ ማርያም

እንኳን ለበዓለ ደብረ ምጥማቅ በሰላም አደረሳችሁ!
ረቡዕ ግንቦት 28 ሌሊት 11 ሰዓት (በኢ/ያ አቆጣጠር) ሦስተኛ ክፍል ትምህርታችንን እንቀጥላለን። ትምህርቱ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ላላችሁ ሁሉ ክፍት ነው።


“ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ” ዕብ 1:1


ከታች ባስቀመጥነው የzoom link በመጠቀም ይቀላቀሉን!

https://us02web.zoom.us/j/81873667259?pwd=R2ZGVWVEamhLZU5aVk1PeXhxcGFrdz09
ክቡራን፣
ሌሊት ጀምሮ በተፈጠረው የመብራት መቋረጥ ምክንያት ለመግባት ባለመቻሌ ትልቅ ይቅርታ እጠይቃለሁ። በዚሁ ሳምንት የዛሬውን ትምህርት የምናካክስበት አንድ ቀን የምናመቻች መሆኑን በትሕትና እገልጻለሁ። ቸር ያገናኘን።
+++ "ስንሞት ያመናል እንዴ?" +++

ሕፃናት መጠየቅ ይወዳሉ። አንዴ መጠየቅ ከጀመሩ በኋላ ደግሞ ከእነርሱ የሚወጣው "ለምን ሆነ?" የሚለው የጥያቄ ዝናብ እንዲህ በቀላሉ ቶሎ የሚያባራ አይደለም። እኛም በእነዚህ ጥያቄዎቻቸው ቶሎ ተሰላችተን ወይም ተበሳጭተን ይሆናል። ይሁን እንጂ ጉዳዩ ግን የሕፃናቱ አዲስ አእምሮ ራሱን የሚያሳድግበትና የነገ ማንነታቸውን የሚቀርጽበት ወሳኝ ሂደት ነው። የነገ ወጣቶችን ማንነት የሚቀርጹት ዛሬ "ለምን?" እያሉ ለሚጠይቁ ሕፃናት የምንመልሳቸው መልሶች ናቸው። ስለዚህ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባናል።

በጠና የታመመ ሕፃን ልጅ ያላት አንዲት እናት ነበረች። ይህች እናት በምትችለው ሁሉ ልጇን አሳክማና ተንከባክባ ለማዳን ብትጥርም፣ ይህ ልፋቷ ግን ሊሳካላት አልቻለም። ልጇን የያዘው በሽታ መድኃኒት ስላልነበረው ወደ ሞት አፋፍ አቅርቦታል። ታዲያ አንድ ቀን ሕፃኑ ልጅ እናቱን እንዲህ ሲል ጠየቃት :- "እናቴ፣ መሞት ምን ይመስላል? ስንሞት ያመናል እንዴ?"

በእናትየው ዓይኖች እንባዎች ሞሉ። ፊቷም በኃዘን ደፈረሰ። የረሳችው ነገር ያለ ይመስል "ቆይ መጣኹ" ብላ ሮጣ ከክፍሉ ወጣች። ብቻዋን ስቅስቅ ብላ አለቀሰች። ልጇ የጠየቃትን ጥያቄ መመለስ እንዳለባት ብታውቅም ለዚህ ለጋ አእምሮ እንዴት አድርጋ መልስ እንደምትሰጥ ግራ ገብቷታል። እንደ ምንም ራሷን አረጋግታና ጥበቡን እንዲሰጣት ወደ ፈጣሪዋ ተማጽና ተመልሳ ወደ ልጇ ክፍል ገባች።

ሕፃኑ መልሱን በጉጉት ይጠብቃል። እናትየውም የውስጧን ኃዘን ለመሰወር ለይምሰል ፈገግ ብላ እንዲህ አለችው "ልጄ፣ ታስታውሳለህ አንድ ጊዜ ጎረቤት ያለ ጓደኛህ ቤት ሄደህ ስትጫወት አምሽተህ ስለደከመህ በዚያው እንቅልፍ ወስዶህ ነበር። ከዚያም በማግስቱ ግን ስትነቃ ራስህ ያገኘኸው በመኖሪያ ቤታችን ውስጥ ስለሆነ 'እንዴት እዚህ መጣኹ?' እያልክ ስትጠይቀኝ ነበር። እኔም አባት ወደዚያ መጥቶ በጥንካራ ክንዶቹ ተሸክሞህ የአንተ ወደ ሆነው ቤትህ እንዳመጣህ ነግሬሃለኹ። አስታወስክ?"

ልጅየው :- "አዎን እናቴ"

እናትየው ቀጠለች :- "የኔ ልጅ፣ ሞትም እንደዚሁ ነው። እኛ መኖሪያችን ባልሆነች በዚህ ዓለም ሆነን እናንቀላፋለን። የሰማይ አባታችን እግዚአብሔር ደግሞ ብርቱ በሆኑ እጆቹ አቅፎ ወደ ሰማይ ይወስደናል። ከዚያም ነግቶ እንደ ገና ስንነቃ ራሳችንን በገዛ አባታችን ቤት ውስጥ እናገኘዋለን" አለችው።

እውነት ነው! ሞት ለክርስቲያኖች ሁሉ የሚኖረው ትርጉም ይህ ነው። ከእግዚአብሔር ተልከን ወደዚህ ዓለም እንደ መጣን ወደ እርሱ መመለሳችን ደግሞ የማይቀር ነው። ሞት ማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ "ድንኳን" ብሎ ከገለጸው ከጊዜያዊው መቆያችን ወደ እውነተኛው መኖሪያ አገራችን መሸጋገር ነው።

በ2ኛው ክፍለ ዘመን የነበረው ግሪካዊው ፈላስፋ አርስጣደስ በጊዜው አዲስ ሃይማኖት ስለሆነበት ስለ ክርስትና እና ይህ የክርስትና እምነት በሞት ላይ ስላለው እሳቤ ለአንድ ወዳጁ በጻፈለት ደብዳቤ ላይ እንዲህ የሚል ንግግር አስፍሮ ነበር። "ከክርስቲያኖቹ ውስጥ አንድ ጻድቅ የሆነ ሰው ከዚህ ዓለም በሞት ቢለይ ምእመናኑ ደስ ይሰኛሉ። ለፈጣሪያቸውም ምስጋናን ያቀርባሉ። ያም ሰው ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላ ቅርብ ሥፍራ የተሸጋገረ ይመስል ሰውነቱን በመዝሙራትና በምስጋና አጅበው ይሸኙታል" ይላል። ክርስትና እንዲህ ነዋ!

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም ክርስቲያኖች በሞት ላይ ሊኖራቸው ስለሚገባ እይታ ሲናገር "ከእኛ መካከል አንድ ሰው በሞተ ጊዜ፣ የማያምነው ሬሳ ሲያይ ክርስቲያኑ ግን ያንቀላፋ ሰውነት ይመለከታል። ያላመነው "የሞተው ሰው ሄደ" ይላል። በርግጥ በዚህ እኛም እንስማማለን። ነገር ግን ወደ የት እንደሚሄድም እናውቃለን። የሚሄደው ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ጴጥሮስ እንዲሁም ሌሎች የቅዱሳን ማኅበር ወደ አሉበት ነው። በኋላም ተስፋ መቁረጥ ባለበት እንባ ሳይሆን፣ በክብርና በማንጸባረቅ እንደሚነሣ እናስባለን!"

+++ "ለባሪያዎችህ ሞት የለባቸውም ፍልሰት እንጂ" +++



ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
ረቡዕ ሰኔ 5 ሌሊት 11 ሰዓት (በኢ/ያ አቆጣጠር) ሦስተኛ ክፍል ትምህርታችንን እንቀጥላለን። ትምህርቱ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ላላችሁ ሁሉ ክፍት ነው።

ባለፈው ሳምንት በመብራት መቋረጥ ምክንያት ተፈጥሮ ስለ ነበረው መታጎል ይቅርታ እንጠይቃለን። የነገውን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ልክ አጥቢያ 11:00 ላይ እንጀምራለን።


“ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ” ዕብ 1:1


ከታች ባስቀመጥነው የzoom link በመጠቀም ይቀላቀሉን!

https://us02web.zoom.us/j/81873667259?pwd=R2ZGVWVEamhLZU5aVk1PeXhxcGFrdz09
እንደ እድል ሆኖ ያደግኹት በመልአኩ ቤት ነው። ስለ እርሱ በቃል የማይገለጽ ልዩ ፍቅር አለኝ። በሄድኩበት ሁሉ ስሙ ሲጠራ ከሰማኹ አንዳች የደስታ ስሜት ሰውነቴን ውርር ያደርገዋል። "ሚካኤል" ብዬ ያልቀለለ ሸክም፣ ያልተመለሰ ጸሎት የለኝም። አንዳንዴ መልአኩ በጣም ቅርቤ ይመስለኛል። ደግሞ ስለ እርሱ ሳስብ ያሳዝነኛል። ለምን? እንጃ ግን ለእኔ ስለሚያዝንልኝ ይሆናል። ስለ እኔ የሚጨነቅ፣ የሚሳሳልኝ ይመስለኛል። ስለዚህ ያሳዝነኛል። ሚካኤል የዋህ፣ ትሑት፣ ሰውን ወዳጅ መልአክ ነው። ሁልጊዜ ሲዘመር ደስ የሚለኝ መዝሙር አለ:- ነዋ ሚካኤል መልአከክሙ
         ይስአል ለክሙ በእንተ ምሕረት
ትርጉም:- "እነሆ ሚካኤል መልአካችሁ ምሕረትን ይለምንላችሁ"

ሚካኤል መልአኬ፣ ሚካኤል መልአካችን!

ከታናሽነቴ ጀምሮ እኔን የመገበኝ፣ ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ነው!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
አዲስ አበባ
[email protected]

ድረ-ገጹን ይጎብኙ
www.dnabel.com
ነገ ረቡዕ ልናደርግ የነበረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ትምህርት ቀኑ ሰኔ 12 ዓመታዊ የቅዱስ ሚካኤል በዓል በመሆኑ ወደ ቀጣይ ሳምንት ተሸጋግሯል። ስለዚህ በዓሉን ከማታው ማኅሌት ጀምረን በቅዳሴ እና በዑደት እያከበርን ከበረከቱ ተሳታፊ እንሁን። ቀጣይ ሳምንት እንደ አምላካችን ቸርነት በዕብራውያን መልእክት ሐተታ 4ኛ ክፍል ትምህርት እንገናኛለን።

"ከልጅነት ጀምሮ እኔን የመገበኝ፥ ከክፋ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ ሚካኤል ነው"
+++"እውነትም የመከር በዓል"+++

ጌታችን ከትንሣኤው በኋላ በጋራም በተናጠልም ለሐዋርያቱ እየታያቸው የትንሣኤውን አማናዊነትና ‹ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ነገር እየነገራቸው› አርባ ቀን ቆይቷል፡፡(ሐዋ 1:3) በአርባኛውም ቀን ሲያርግ ‹የሚያጸና፣ የሚያነጻ እና የሚያጽናና መንፈስ ቅዱስን› እንደሚልክላቸው ተስፋን ሰጣቸው፡፡ ነገር ግን ከላይ ኃይልን እስከሚቀበሉባት ቀን ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ እንዲቆዩ አዘዛቸው፡፡ (ሉቃ 24፡49-51) ሐዋርያቱም ከጌታ ዕርገት በኋላ በጽዮን አዳራሽ (ጽርሐ ጽዮን) ውስጥ በአንድ ልብ ሆነው በጸሎት ይተጉ ጀመር፡፡

   ለሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ የወረደበት ቀን ማለት አይሁድ በዓመት ውስጥ ከሚያከብሯቸው ታላላቅ በዓላት መካከል አንዱ የሆነውን ‹በዓለ ሃምሳ› የሚውልበት ዕለት ነበር፡፡ ይህም በዓል አይሁድ ፋሲካቸውን ካከበሩ ከሰባት ሳምንታት በኋላ ባለው ሰንበት ማግስት (በእሁድ፣ በ50ኛው ቀን) ስለሚከበር ‹‹ጰንጠቆስጤ››/‹‹በዓለ ሃምሳ›› ተብሎ ይጠራል፡፡ በዚህም ቀን እስራኤላውያን አርሰው ካመረቱት ላይ አዲሱን የእህል ቁርባን ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡበትም ዕለት ስለሆነ በሌላ ስያሜ ‹የመከር በዓል› ተብሎ ይጠራል፡፡ በተጨማሪም የእስራኤል መስፍን የነበረው ሊቀ ነቢያት ሙሴ በሲና ተራራ ከአምላኩ ዘንድ ሕገ ኦሪት መቀበሉንም የሚያስቡበት ቀን ነው፡፡

  በተለያዩ የዓለም ክፍላት የሚኖሩ አይሁድ ከያሉበት አገር ተጉዘው በመምጣት የፋሲካንና የመቅደስ መታደስ በዓላትን በኢየሩሳሌም ተሰብስበው ለማክበር ይቸገሩ ነበር፡፡ የችግሩም ምክንያት እነዚህ በዓላት በሚውሉበት ወቅት ያለው የአየር ጠባይ በጣም አስቸጋሪና ነፋሱም ማዕበል የሚቀሰቅስ በመሆኑ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በዚሁ ጊዜ ወደ ኢጣልያ ለመሄድ በመርከብ በተሳፈረ ጊዜ ስላጋጠመው እንግልትና ስቃይ በሐዋርያት ሥራ ላይ ተጽፏል፡፡(ሐዋ 27፡9) እርሱ ራሱም በመንገዱ መካከል አብረውት ይጓዙ የነበሩትን ሰዎች ‹‹እናንተ ሰዎች ሆይ ይህ ጉዞ በጥፋትና በብዙ ጉዳት እንዲሆን አያለሁ፤ ጥፋቱም በገዛ ሕይወታችን ነው እንጂ በጭነቱና በመርከቡ ብቻ አይደለም›› ሲል ጉዞውን ለጥቂት ጊዜ እንዲያዘገዩት መክሯቸው ነበር፡፡ በዓለ ሃምሳ ግን የመጀመሪያዎቹ የፀደይና የመከር ወቅት ላይ ስለሚውል የአየሩ ሁኔታ ለመርከብ ጉዞ የተመቸ ነው፡፡ ስለዚህም የፋሲካና የመቅደስ መታደስ በዓላት ላይ በኢየሩሳሌም መገኘት ያልቻሉ አይሁድ ሁሉ በጉጉት የሚጠባበቁትና ወደ ቅድስቲቱ ከተማ በመግባት ተሰብስበው የሚያከብሩት ታላቅ በዓል ነው፡፡

  "በዓለ ሃምሳ" የሚለው መጠሪያ አስቀድመን እንደ ተናገርነው በኦሪቱ ለሚከበረው በዓል መታወቂያነት የሚያገለግል ስያሜ ቢሆንም፣ የጌታ ሐዋርያትም መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉት ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ በተነሣ በሃምሳኛው ቀን በመሆኑ ለሐዲስ ኪዳኑም ታላቅ በዓል መጠሪያነት ቢውል የሚያውክ አይሆንም፡፡ ይሁን እንጂ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህንን ቀን ‹በዓለ ጰራቅሊጦስ› ስትል ለሐዋርያት በወረደው ቅዱስ መንፈስ ልዩ ስም ትጠራዋለች፡፡ ‹‹ጰራቅሊጦስ›› የሚለው የግሪክ ቃል ሲሆን ‹‹መጽንዒ፣ መንጽሒ››/‹‹የሚያጸና፣ የሚያነጻ›› የሚል ትርጉም አለው፡፡

  ወደ ቀደመ ነገራችን እንመስና ሐዋርያቱ በጽርሐ ጽዮን ተሰብስበው ሲጸልዩ ሳሉ ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምጽ መጣ፣ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው፡፡(ሐዋ 2፡2) በዚህ ክፍል ይህን ታሪክ የሚጽፍልን ቅዱስ ሉቃስ የመንፈስ ቅዱስ መውረድ ‹ድንገት› እንደ ሆነ ይነግረናል፡፡ ለመሆኑ ‹ድንገት› ሲል ምን ለማለት ፈልጎ ነው? ጸሐፊው ቅዱስ ሉቃስ ‹ድንገት› የሚለውን ቃል የተጠቀመው ነገሩ በሰው ቀጠሮ ሳይሆን ‹በእግዚአብሔር ጊዜ› የተፈጸመ መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ ሐዋርያት አጽናኙ መንፈስ እንደሚላክላቸው ቢነገራቸውም በየትኛው ቀን ግን እንደሚወርድ የሚያውቁት ነገር አልነበረም፡፡ ስለዚህም ‹ድንገት› የሚለው ቃል ሐዋርያቱ ቀኑን ፈጽመው አለማወቃቸውን ያሳያል፡፡ ሁል ጊዜ ጸጋን የሚሰጠው እግዚአብሔር ስለሆነ የሚሰጥበት ቀነ ቀጠሮ በሰጪው እንጂ በተቀባዩ አይወሰንም፡፡ ስለዚህ የተቀባዩ ሰው ድርሻ ሳይዝል ተስፋም ሳይቆርጥ የአምላኩን የሥራ ቀን በትዕግሥት መጠባበቅ ነው፡፡

  የዓውሎ ነፋሱም ድምፅ ልክ ኤልያስ የምድሩን መናወጥና እሳቱን ሲመለከት በመጎናጸፊያው ተሸፍኖ ከዋሻው በመውጣት እግዚአብሔርን ለማናገር ራሱን እንዳዘጋጀ፣ ሐዋርያቱም የመንፈስ ቅዱስን መውረድ እንዲያስተውሉና ለዚያም ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ የተሰማ የማንቂያ ድምፅ ነው፡፡(1ኛ ነገ 19፡12) በተጨማሪም ድምፅ ‹ኃይልን› ያመለክታል፡፡ ስለዚህ እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ የተሰማው ድምጽ ሐዋርያቱ ከመንፈስ ቅዱስ ኃይል መቀበላቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ እዚህ ላይ ጌታችን በዮርዳኖስ ወንዝ ከተጠመቀ በኋላ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በእርሱ ላይ ሲያርፍ ያሰማው አንዳች ድምፅ አለመኖሩን ልብ ይሏል፡፡(ማቴ 3፡16) ይህም እርሱ ለደካሞች ጽንዕ የሚሆን እንጂ እንደ ፍጡር ኃይል የሚቀበል አለመሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡

አስቀድሞ መድኃኒታችን ለኒቆዲሞስ ‹‹ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል›› ሲል እንዳስተማረው፣ በዚህች ቀን በነፋስ የተመሰለ መንፈስ ቅዱስ በወደዳቸው በሐዋርያት ሰውነት ያድር ዘንድ ወደ ጽርሐ ጽዮን ነፈሰ(መጣ፣ ወረደ)፡፡ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ መንፈስ ቅዱስን ከነፋሳትም መርጦ ከደቡብ አቅጣጫ በሚነፍሰው ነፋስ ይመስለዋል፡፡ ብዙ ጊዜ ከሰሜኑ የሚነሣው ነፋስ ቀዝቃዛና ሰብል የሚያጠፋ በመሆኑ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚኖሩ ገበሬዎች ይፈሩታል፡፡ ከደቡብ አቅጣጫ የሚነፍሰው ነፋስ ግን ከምድር ወገብ የሚወጣውን ሞቃታማ አየር ይዞ ስለሚነፍስ የተዘራውን ሰብል ያበስለዋል፡፡ በዚህም ገበሬዎቹ ደስ ይሰኙበታል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ መንፈሳዊ ብስለትን የሚሰጠው መንፈስ ቅዱስ ልክ በደቡብ እንደሚነፍሰውና ሰብሎችን እንደሚያበስለው ያለ ተወዳጅ ነፋስ ነው ይላል፡፡

  ቀጥሎም ለሐዋርያቱ እንደ እሳት የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፡፡ በያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው፡፡ በሁሉም ላይ መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፡፡ አስተውሉ በዚህ አንድ ታሪክ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ በእሳትም በነፋስም ተመስሎ ሲቀርብ እናገኛለን፡፡ ታዲያ መንፈስ ቅዱስ የተመሰለባቸው ምሳሌዎች መብዛታቸው ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ እንዳብራራው የመንፈስ ቅዱስ ባሕርይ በምልዓት የማይታወቅ መሆኑን ያመለክታል፡፡

እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን በእሳት መመሰል አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በዕብራውያን መልእክቱ ‹‹አምላካችን በእውነት የሚያጠፋ እሳት ነውና›› ሲል ስለ እርሱ ተናግሯል፡፡(ዕብ 12፡29) መንፈስ ቅዱስ በእሳት መመሰሉ፣ ከከርሰ ምድር መዓድናትን የሚያወጣ ባለሙያ ከመሬት ቆፍሮ ያወጣውን መዓድን ከትቢያው የሚለየው በእሳት እንደ ሆነ እንዲሁ፣ መንፈስ ቅዱስም ነፍሳችንን ትቢያ ከተባለ ኃጢአት ሁሉ ለይቶ ያነጻታልና በእሳት ተመሰለ፡፡ ይህንንም በተመለከተ ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ‹‹የእስራኤልም ብርሃን እንደ እሳት፣ ቅዱሱም እንደ ነበልባል ይሆናል፡፡ እሾኹንና ኩርንችቱን በአንድ ቀን ያቃጥላል›› ሲል ይናገራል።(ኢሳ 10፡17) አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫም በመጽሐፈ ምሥጢሩ ለሐዋርያቱ በሃምሳኛው ቀን በእሳት አምሳል የወረደው መንፈስ ቅዱስ ‹‹ሥጋቸውን ሳይሆን የኃጢአታቸውን እሾኽ አቃጠለ›› በማለት ይገልጻል፡፡
እነዚያ እንደ እሳት ላንቃ የተከፋፈሉት ልሳኖች ከመታየትም አልፈው በሐዋርያቱ ላይ መቀመጣቸው፣ ደቀ መዛሙርቱ የሚያዩት ነገር ሁሉ ቅዠት ወይም ምናባዊ ሳይሆን እውነተኛ የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ መሆኑን እንዲገነዘቡ ነው፡፡ ከዚያም በኋላ በሁሉም ላይ መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፡፡ የእግዚአብሔርን ልጅ በረገጡና አመጽ ወዳድ በነበሩት አይሁድ ቅንዓትና ቁጣ ሲሞላ፣ የሰላም ልጆች በነበሩት ሐዋርያት ግን መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፡፡ ስለዚህም መንፈስ ቅዱስ ይናገሩ ዘንድ (በየአቅማቸው) እንደ ሰጣቸው በሌሎች ቋንቋዎች ይናገሩ ጀመር፡፡

  እግዚአብሔር አሕዛብ ያለ ሐዋርያት ስብከት በሥላሴ ማመን እንደማይችሉ፣ ሐዋርያትም ያለ መንፈስ ቅዱስ መውረድ በየአገሩ ቋንቋዎች ሁሉ መስበክ እንደማይችሉ ዐወቀ፡፡ ስለዚህም በሰናዖር ሜዳ የተበተኑትን የዓለምን ቋንቋዎች በሐዋርያት አንደበት ሰብስቦ ያኖር ዘንድ ቅዱስ መንፈሱን ላከ፡፡ የተላከውም መንፈስ ያለ አንድ ቋንቋ የማይናገረውን የሐዋርያቱን አንደበት በቅጽበት አሰለጠነው። በእውነት እንደ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ያለ አስማሪ ማን ነው?!በዚህችም እለት ሐዋርያቱ በዓለም ሁሉ ቋንቋዎች ተሞልተው ከእርሷ የወጡባት የጽዮን አዳራሽ (ጽርሐ ጽዮን) እንደ ምን ያለች ናት?! መንፈስ ቅዱስ ከዚያም በፊት ከዚያም በኋላ ታይታ የማትታወቅ ልዩ ትምህርት ቤት አደረጋት፡፡

ሐዋርያቱም በመንፈስ ቅዱስ ተሟሙቀው በሰበኩት በመጀመሪያ ዕለት ስበከት ብዙዎችን አሳምነው አጠመቁ። በዚህ የመከር በዓል አይሁድ ከአዲሱ እህል ለእግዚአብሔር ቁርባን ሲያቀርቡ፣ ሐዋርያቱ ግን የክርስቶስ አካል ለሆነችው ለሐዲሲቷ ቤተ ክርስቲያን ከእህል ቁርባን ይልቅ የሚወደዱ ምእመናንን ስጦታ አድርገው አቀረቡ። በአይሁድ የመከር በዓል ቀን በሐዋርያቱ በተሰጠ ትምህርት የእግዚአብሔር እርሻ የሆኑ ምዕመናን በዝተው አብበው ተገኙ። እውነትም የመከር በዓል!!!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
ረቡዕ ሰኔ 19 አጥቢያ 11 ሰዓት (በኢ/ያ አቆጣጠር) አራተኛ ክፍል ትምህርታችንን እንቀጥላለን። ትምህርቱ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ላላችሁ ሁሉ ክፍት ነው።


“ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ” ዕብ 1:1


ከታች ባስቀመጥነው የzoom link በመጠቀም ይቀላቀሉን!

https://us02web.zoom.us/j/81873667259?pwd=R2ZGVWVEamhLZU5aVk1PeXhxcGFrdz09
ሰይጣን መንፈሳዊ ሕይወትን ለመኖር ወስነህ ስትጀምር በእነዚህ ሁለት ሐሳቦች ይዋጋሃል።

1. አንተ ለዚህ ሕይወት እንደማትሆን እና መቼም እንደማትለወጥ ሹክ ይልሃል። ይህን የሚያደርገው ተስፋ ቆርጠህ የያዝከውን ሩጫ እንድታቆም ነው። የሚገርመው ግን መለወጥ ባትጀምር ኖሮ ሰይጣን “አልተለወጥህም” አይልህም።

2. ገና ከመጀመርህ የደረስህ እና ለመፈጸም ጥቂት የቀረህ አስመስሎ ያሳይሃል። ብዙ ርቀህ እንደ ሄድህ አስበህ ልክ እንደ ጥንቸሏ ተዘናግተህ እንድትተኛ እና የጽድቅ ነገር ሁሉ ጠላት የሆነው ትዕቢት እስረኛ እንድትሆን ያደርግሃል። አሁንም ሰይጣን “ደርሰሃል” እያለ ሲክብህ ገና እግርህን ለማንሣት የምትጣጣር እንደ ሆንህ አቅምህን በደንብ ያውቀዋል።

ጀማሪ ስትሆን ሰይጣን “አትችልም” ብሎ ተስፋ በማስቆረጥ ወይም “ደርሰሃል” እያለ ያለ ልክ በማመስገን ወጥመዱ ውስጥ ሊጥልህ ይሞክራል።

“በሰይጣን እንዳንታለል፤ የእርሱን አሳብ አንስተውምና” 2ኛ ቆሮ 2:11

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
ረቡዕ ሰኔ 26 አጥቢያ 11 ሰዓት (በኢ/ያ አቆጣጠር) አምስተኛ ክፍል ትምህርታችንን እንቀጥላለን። ትምህርቱ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ላላችሁ ሁሉ ክፍት ነው።


“ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን” ዕብ 1:2


ከታች ባስቀመጥነው የzoom link በመጠቀም ይቀላቀሉን!

https://us02web.zoom.us/j/81873667259?pwd=R2ZGVWVEamhLZU5aVk1PeXhxcGFrdz09
2025/07/05 20:21:05
Back to Top
HTML Embed Code: