Telegram Web Link
+++ የማያሳፍር ተስፋ +++

ክርስቲያኖች በራሳቸው ማስተዋል ወይም በሀብታቸው አይደገፉም። እንደ እነርሱ ተሰባሪ በሆነ ሰው ላይም ተስፋቸውን አያደርጉም። የክርስቲያን ተስፋው “የተስፋ አምላክ” ክርስቶስ ነው።(ሮሜ 15፥13) ክርስቶስን ለምን ተስፋ እናደርጋለን? “ሁሉ በእርሱ ስለሆነ፤ ከሆነውም አንዳች እንኳን ያለ እርሱ የሆነ” ስለሌለ፣ ኃይልና ችሎታ በእጁ ስለሆነ፣ ያጎበጠንን ሸክም አራግፎ ሊያሳርፈን “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ።” ብሎ ስለ ጠራን፣ ወደ ጠራን አምላክ ቀና እንላለን።(ዮሐ 1፥3፣ 2ኛ ዜና 20፥6፣ ማቴ 11፥28) እርሱን ተስፋ ብናደርግ እንደ ሰው አይለወጥብንም። እስከ ሽበት እንኳን ተሸክሞን አይሰለቸንም።(ኢሳ 46፥4) ነፍሱን እስኪሰጥ ስለወደደን፣ በብዙ ሕማም በእጁ መዳፍ ላይ ስለቀረጸን ፍቅሩ ቀዝቅዞ ጨርሶ ሊረሳን አይችልም።(ኢሳ 49፥16)

"ኢሰማዕነ ወኢርኢነ ወኢነገሩነ አበዊነ ከመ ቦ ባዕድ አምላክ ዘእንበሌከ"

"ከአንተ በቀር ሌላ አምላክ እንዳለ አባቶቻችን አልነገሩንም። እኛም አልሰማንም፤ አላየንምም!"

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
ሊቀ ሊቃውንት ስምዓኮነ መልአክ ከአበው ኅሊና ሳይወጡ በራሳቸው ተመርሖ ልቡና ያጠረውን አርዝመው የረዘመውን አሳጥረው የሚተረጉሙ፣ ሁልጊዜ አዳዲስ ምሥጢራት የሚገኝባቸው “ስፍሐ አእምሮ” የተሰጣቸው ታላቅ ሊቅ ናቸው። መጻሕፍትን የሚመረምሩበት ጠንቃቃ ዓይኖቻቸው እጅግ ያስቀናሉ። እንደ የኔታ ስምዓኮነ ዓይነት መምህራን በታሪክ የሚነገርላቸው ከአፄ አድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን በፊት የተነሡ በግእዝ የሚራቀቁ (የራሳውን አንድምታ እስከ ማዘጋጀት የደረሱ) ሊቃውንት እንደ ነበሩን የሚያስረግጡልን ሕያው ምስክሮች ናቸው።

https://youtu.be/Fm86VvBXf48?si=PxV4ZZ9vqno5VugI
🌟🌟🌟በገና አባት የተሸፈነ ቅዱስ አባት🌟🌟🌟

+++ቅዱስ ኒቆላዎስ ገባሬ መንክራት (St.Nicholas the wonder worker)+++

ቅዱስ ኒቆላዎስ (St.Nicholas-Santa Claus) በሮማ መንግስት ዘመን በኤዥያ ውስጥ በምትገኝ ሜራ በምትባል አገር (የአሁኗ ቱርክ) ግሪካዊ ከሆኑ ክርስቲያን ቤተሰቦቹ ተወለደ፡፡ የዚህም ቅዱስ እናቱ ጦና (Tona) አባቱ ኤጲፋንዮስ ይባላሉ፡፡ እኒህም እግዚአብሔርን የሚፈሩና ባለጠጎችም ነበሩ፡፡ ነገር ግን ከሞቱ በኋላ ንብረታቸውን የሚያወርሱት፣ ለልባቸውም ደስታን የሚመግብ ልጅ አልነበራቸውም፡፡ ዕድሜያቸው እየገፋ በመምጣቱም ምክንያት በተስፋ መቁረጥ ተከበው ይኖሩ ነበር፡፡ በልብ መታሰቡ በቃል መነገሩ ከፍ ከፍ ያለ አምላክ በእርጅና ዘመናቸው ልክ ጻድቁ ዘካርያስና ሚስቱ ኤልሳቤጥን እንደጎበኘ እነርሱንም በቸርነቱ ጎበኛው፡፡ ቅዱስ የሆነም ልጅን ሰጣቸው፡፡ ይህም ልጅ ገና ታናሽ ሳለ መንፈሰ እግዚአብሔር የሞላበት ነበር፡፡ ዕድሜውም ለትምህርት በደረሰ ጊዜ ዕውቀትና ጥበብን ይቀስም ዘንድ ወደ መምህራን የተላከ ቢሆንም፣ ከመምህሩ ከተማረው ይልቅ ከመንፈስ ቅዱስ የተረዳው ይበልጥ ነበር፡፡

መሠረታዊ የሆኑትን የቤተ ክርስቲያንን ትምህርቶች በልጅነቱ ተምሮ በማጠናቀቁ በዲቁና መዓርግ ተሾመ፡፡ በኋላም የአጎቱ ልጅ አበምኔት በሆነበት በአንዱ ገዳም አርዑተ ምንኩስናን (የምንኩስናን ቆብ) ጭኖ የቅድስና እና የትሕርምት ሕይወትን ኖሯል፡፡ በአሥራ ዘጠኝ ዓመቱም የቆሞስነትን መዓርግ አግኝቷል፡፡

ለዚህም ቅዱስ አባት እግዚአብሔር ተአምር እና ድንቅን የማድረግ ፤ሕሙማንንም የመፈወስ ታላቅ ጸጋ ሰጥቶታል፡፡

#ለጋስ (የስጦታ) አባት

በሜራ ከተማ የሚኖር ቀድሞ ባለጠጋ የነበረ በኋላ ግን ሃብት ንብረቱን ያጣ አንድ ሰው ነበረ፡፡ በድህነቱ ምክንያት ሊድራቸው ያልቻለ ሦስት ዕድሜያቸው ለጋብቻ የደረሱ ሴቶች ልጆች ነበሩት፡፡ ሰይጣንም እነዚህን ልጆቹን በዝሙት ሥራ ገንዘብ እየሰበሰቡ ሕይወታቸውን እንዲመሩ ያደርጋቸው ዘንድ ክፉ ሐሳብን በሕሊናው አመጣበት፡፡ እግዚአብሔርም በዚህ ሰው ልቡና ውስጥ ሰይጣን የተከለበትን ክፉ ሐሳብ እና ምን ሊያደርግ እንደተነሣሣ ለቅዱስ ኒቆላዎስ ገለጠለት፡፡

ቅዱስ ኒቆላዎስም የእናት የአባቱ ገንዘብ ከሆነው ላይ መቶ ዲናር ወስዶ በስልቻ (sack) ጠቅልሎ ማንም ሳያየው በምሽት ወደዚያ ደሃ ሰው ቤት በመሄድ በመስኮት በኩል ወረወረለት፡፡ ያም ደሃ ከየት እንደመጣ ያላወቀውን 100 ዲናር በቤቱ ባገኘ ጊዜ ተደነቀ አምላኩንም አመሰገነ፡፡ ያሰበውንም ክፉ ሐሳብ ተወ። በገንዘብ እጦት ምክንያትም ከትዳር የዘገየችውን የመጀመሪያ ልጁን ዳረ፡፡ በሌላም ቀን ቅዱስ ኒቆላዎስ ሁለተኛ ልጁን መዳር ይችል ዘንድ፣ አሁንም ተጨማሪ መቶ ዲናር ገንዘብ በጥቅል ስልቻ አድርጎ በመስኮቱ በኩል ወረወረለት፡፡ ይህንንም ገንዘብ ዳግመኛ በቤቱ ያገኘው ደሃ ሰው እንዲህ ያለውን ቸርነት በስውር የሚያደርገው ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ አይቶ ያውቅ ዘንድ ጉጉት አደረበት፡፡ ቤቱንም በንቃት መከታተል ጀመረ፡፡

ቅዱስ ኒቆላዎስም እንደ ለመደው ለሦስተኛ ጊዜ መቶውን ዲናር የያዘውን ስልቻ በመስኮት ሲወረውር ወዲያው ተዘጋጅቶ ይጠብቀው የነበረው ሰው ፈጥኖ በሩጫ ከቤቱ ወጣ። ሊያየው ይመኘው የነበረ ያንንም ቸር ሰው ሊቀ ጳጳሱ ኒቆላዎስ ሆኖ አገኘው፡፡ ከእግሩ ስርም ተደፍቶ ልጆቹን ከድህነት እና ከኃጢአት ሕይወት ስለታደገለት ሊያመሰግነው ቢሞክርም ቅዱስ ኒቆላዎስ ግን ምስጋናውን እምቢ አለ፡፡ ይህን ሐሳብ በልቡ ያኖረ እግዚአብሔርንም ያመሰግን ዘንድ ለመነው፡፡

ከዚህ ታሪክ በተጨማሪም ለሕፃናት እና ለተቸገሩ ሰዎች ያደረገው ልግስና የብዙ ብዙ ነው። ለዚህም ይመስላል በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት መታሰቢያውን በልግስና የሚያከብሩት።

በአጠቃላይ ይህ ቅዱስ አባት በዘመነ ዲዮቅልጥያኖስ ስለ እምነቱ ብዙ ስቃይ እና እስራት ደርሶበታል፡፡ ፋታ በማይሰጥ መከራ እና ግርፋት ውስጥ እያለ የራሱን ሕመም ከማዳመጥ ይልቅ በውጪ ላሉ ለልጆቹ ምዕመናን የሚያበረታታ እና በእምነታቸው እንዲጸኑ የሚያደርግ መልእክትን ይጽፍላቸው ነበር፡፡ ቅዱስ ኒቆላዎስ በ325 ዓ.ም ለአውግዞተ አርዮስ ከተበሰቡት 318ቱ ሊቃውንት መካከል አንዱ የነበረ የዚህች ኦርቶዶክሳዊት እምነት ባለውለታ ነው፡፡ ከአርባ ዓመታት በላይ በሊቀ ጵጵስና መንበር በጎቹን ከነጣቂ ተኩላ እየጠበቀ ቤተ ክርስቲያንን ካገለገለ በኋላ በሰማንያ ዓመቱ አርፏል፡፡

(ቅዱስ ኒቆላዎስ በእኛ (በኢትዮጽያ) የስንክሳር መጽሐፍ ላይ የእረፍቱ መታሰቢያ የሚያዝያ ወር በገባ በአስራ አምስተኛው ቀን እንደሆነ ተመዝግቧል፡፡ ኒቆላዎስም ማለት ‹መዋኤ ሕዝብ - ሕዝብን የሚያሸንፍ› ማለት ነው።)

የልደት በዓል እግዚአብሔር አብ ልጁን ለዓለም የሰጠበት በመሆኑ ‹የሥጦታ በዓል› በመባል ይጠራል፡፡ ይህንንም በማሰብ ለድሆች በመራራት ለተቸገሩት ቸርነት በማድረግ እናከብረው ዘንድ ምሳሌ እንዲሆነን ቅዱስ ኒቆላዎስን እናስባለን፡፡ ምንም ዓለም አፈ ታሪክ አድርጋ ብታወራውም፣ የዚህንም ቅዱስ ማንነት እንዳይታወቅ በፈጠረቻቸው ተረቶች ብታጠለሸውም እኛ ግን የ‹ገና አባት› ብላ ከሰየመቻቸው የፈጠራ ሰው ጀርባ እውነተኛ የሆነውን ይህን ቅዱስ አባት እናስበዋለን፡፡

+++++ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ እኛ ኃጢአተኞቹንም በዚህ ጻድቅ ሰው ጸሎት ይማረን!!!+++

ምንጭ:– -መጽሐፈ ስንክሳር
-Coptic synaxarium

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ3ኛው ክፍለ ዘመን የነበረ አንድ የሚያስገርመኝ ዜኖ የሚባል ፈላስፋ ነበር። ይህም ሰው ከዕለታት በአንዱ ቀን ከትምህርት ቤት ወደ ቤቱ ሲመለስ ድንገት ወደቀና ጣቱ ክፉኛ ተጎዳ። ከዚያም ከወደቀበት ሳይነሣ በእጆቹ መሬቱን እየመታ “እየመጣሁ ነውና እኔን ለመጥራት መድከምህ ከንቱ ነው” ሲል የአንድ ባለ ቅኔን ንግግር ተናግሮ እዚያው ራሱን አፍኖ ገደለ።

አትላንቲክ ውቅያኖስ አካባቢ የሚኖሩ Celts የሚባሉ ወገኖችም ነበሩ። እነዚህ ሰዎች ሞትን መፍራትን እንደ ትልቅ ውርደት አድርገው ስለሚያስቡ ትልልቅ ጥፋት የሚያመጡ ነገሮችን ሳይቀር ፊት ለፊት ይጋፈጡ ነበር። ለምሳሌ ቤቱ ሊያፈርስ ቢያዘምባቸው ወይም ግድግዳው ሊናድ ቢንደረደርባቸው ሮጠው ከዚህ አደጋ ለማምለጥ አይሞክሩም። በውቅያኖስም ውስጥ ሆነው ማዕበል ቢቀሰቀስ ወደ ኋላ አያፈገፍጉም። እንዲያውም ወጀቡ እስኪያልፍ ባሉበት ሳይንቀሳቀሱ ይቆማሉ። ሞትን ፈርተው ሸሹ እንዳይባሉ እነዚህን አስፈሪ ነገሮች ያደርጋሉ።

“ሕይወት” እግዚአብሔር የሰጠን ትልቁ ስጦታ ነው። እርሱ በቀጠረው ጊዜ እስኪጠራን ድረስ አለመታገስ የዚህን ስጦታ ዋጋ አለመረዳት ነው። እውነተኛ ጀብድ በዚህ አስቸጋሪ ዓለም ሊያጋጥሙ የሚችሉትን ፈተናዎች ሁሉ ታግሎ ለማሸነፍ እስከ መጨረሻዋ ሕቅታ ድረስ መፋለም እንጂ ቀድሞ ሩጫ ማቋረጥ አይደለም። አንድ ክርስቲያን ሞትን እንደማይፈራ ማሳየት ያለበት “ሕያው የሚያደርገውን” የክርስቶስን ሥጋ እና ደም በመቀበል እንጂ ራሱን ለሞት በማጋለጥ መሆን የለበትም።

“ማምሻም ዕድሜ ነው” እንደሚባለው አይደለም በወጣትነት በሽምግልና ዘመን የቀረች ጥቂት ቀን እንኳ ታሳሳለች። ምክንያቱም ከመሰንበት ንስሐ መግባት፣ መጸጸት፣ መመለስ፣ የኋላውን ትቶ የፊትን ለመያዝ መዘርጋት አለና።


ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
ከአሥርቱ መዓርጋተ መላእክት ውስጥ አንደኞቹ አርባብ ይሰኛሉ። ረበበ ማለት ጋረደ፣ ሸፈነ ማለት ሲሆን አርባብ ማለት የሚጋርዱ፣ የሚሸፍኑ የሚል ትርጉምን ይሰጣል፡፡ እነዚህም መላእክት የእግዚአብሔርን መንበር በክንፎቻቸው ስለሚሸፍኑ እና ስለሚጋርዱ ይህን ስያሜ አግኝተዋል። ዳግመኛም ዘወትር ከሚወረወረው የሰይጣን ፍላጻ (ጦር) ያመልጡ ዘንድ ለሰው ልጆች ሁሉ ሽፋን ከለላ ስለሚሆኑ ስለዚህ አገልግሎታቸው አርባብ/"የሚጋርዱ" ተብለው ይጠራሉ። የእነዚህም የመላእክት ሠራዊት አለቃቸው ሠለስቱ ደቂቅን ሰይጣን በናቡከደነጾር ልብ አድሮ ካነደደው እሳት ጋርዶ፣ ሸፍኖ ያዳናቸው ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡

ቅዱስ ገብርኤል በተለይ ልጅ ወደሚወልዱ ደጋግ ቅዱሳን አበው እና ቅዱሳት እማት ‹አብሣሬ ጽንስ›/‹ጽንስን የሚያበሥር› ሆኖ በመላክ በተደጋጋሚ በመጽሐፍ ስሙ የተጠቀሰ መልአክ ነው፡፡ ለማኑሄ እና ለሚስቱ ሶምሶን የተባለ ኃያል ሰው እንደሚወልዱ፣ ለሊቀ ካህናቱ ዘካርያስ ዮሐንስ መጥምቅን የመሰለ ደገኛ ልጅ እንደሚወልድ፣ ክብር ይግባትና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ በማኅጸኗ እንደሚቀረጽ ያበሠረ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ነውና ‹መልአከ መበሥር› በመባል ይጠራል፡፡(መሳ 13፥4 ፣ሉቃ 1፥13 ፣ሉቃ 1፥26)

በተጨማሪም አዲስ እና ደስ የሚያሰኘውን የአምላክን መወለድ ዜና ብሥራትም በመናገሩ እና በሐዲስ ኪዳንም ስሙ ተደጋግሞ በመነሣቱ ምክንያት ‹መጋቤ ሐዲስ› በመባል ይታወቃል፡፡ ለብፁዕ ዳንኤልም ዕውቀት እና ማስተዋል የሰጠው ጥበብንም ያስተማረው መልአክ ቅዱስ ገብርኤል መሆኑን ይኸው ነቢይ በመጽሐፉ ምስክርነትን ይሰጣል፡፡(ዳን 8፥15)

የአምላክን ሰው ሆኖ ወደዚህች ምድር መምጣት ያበሰረው ቅዱስ ገብርኤል እንደሆነ ሁሉ ፤ ‹ልደት እና ዕርገት በአንድ መልአክ ተበሠሩ› በሚለው በቅዱስ አትናቴዎስ ዘእስክንድርያ ትምህርት ደግሞ የአምላክን ወደ ሰማይ ማረግም ለሰማያውያን መላእክት ‹መኳንንት ደጆቻችሁን ክፈቱ› ሲል ዳግመኛ ያበሠረው ይኸው መልአክ መሆኑ ተጠቅሶ እናገኛለን፡፡

እንኳን አደረሳችሁ!!!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
በኃጢአት የጎሰቆለው አዳም የሚታደስበትን ዜና ሊያበስር መልአኩ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፤

ንጹሕ ለሆነው ሙሽራ የተገባች አዳራሽ ትሆነው ዘንድ መመረጧን ሊያበሥራት መልአኩ ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፤

ከኃጢአት ንጹሕ የሆነው መልአክ በደል ወዳልተገኘባት ንጽሕት ድንግል ተላከ፤

የፀሐየ ጽድቅን መምጣት ያበሥር ዘንድ ብርሃናዊው መልአክ ተላከ፤

በአባቱ እቅፍ ያለው አንድያ ልጅ በእናቱም እቅፍ እንደሚሆን ያበሥር ዘንድ መልአኩ ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፤

እንኳን ለበዓለ ብሥራት በሰላም አደረሰን!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
ከግርግሙ ማን ይቀራል?

የምድር ነገሥታት ሰማያዊውን ንጉሥ ለማምለክ ሊመጡ ይገባል። ወታደሮችም ሠራዊትን ሁሉ በአፉ እስትንፋስ ያጸናውን ጌታ ለማገልገል ሊቀርቡ ያስፈልጋል። ሴቶችም ኀዘናቸውን ወደ ደስታ ይለውጥ ዘንድ ከሴት የተወለደውን ያዩ ዘንድ ሊመጡ ይገባል። ሕፃናትም ከሚጠቡ እና ከሕፃናት አፍ ምስጋናን ያዘጋጅ ዘንድ ሕፃን የሆነውን ይመለከቱ ዘንድ ሊመጡ ያስፈልጋል። እረኞችም ነፍሱን ስለ በጎቹ የሚያኖር መልካሙን እረኛ ለማየት ይመጡ ዘንድ ይገባል። ባሮችም የባርነት ቀንበራቸውን ሰብሮ በነጻነት ያከብራቸው ዘንድ የባሪያውን መልክ የነሣውን ሕፃን ያዩ ዘንድ መምጣት ይገባቸዋል። ዓሣ አጥማጆቹም የቃሉን መረብ አስይዞ ሰው አጥማጅ የሚያደርጋቸውን ወንድ ልጅ ለማየት ይቀርቡ ዘንድ ይገባቸዋል። ቀረጥ ሰብሳቢዎችም ከቀራጮች መካከል ወንጌላዊ አድርጎ የሚመርጠውን ጌታ ለማየት ሊመጡ ይገባቸዋል። ዘማውያን ቅዱሳት እግሮቹን በዘማውያን እንባ እንዲታጠብ የሚሰጠውን የፍቅር አምላክ ለማየት ይቀርቡ ዘንድ ይገባል። ኃጥአን ሁሉ የዓለምን ኃጢአት የሚሸከመውን የእግዚአብሔር በግ ለማየት ሊመጡ ይገባል።

#ዛሬ ከቀኑ 10፡00 ሰዓት በአእላፋት ዝማሬ እንገናኝ!

https://www.tg-me.com/Dnabel
"በልዑል መጠጊያ የሚኖር ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል። እግዚአብሔርን፡— አንተ መታመኛዬ ነህ፡ እለዋለሁ፤ አምላኬና መሸሸጊያዬ ነው፥ በእርሱም እታመናለሁ። እርሱ ከአዳኝ ወጥመድ ከሚያስደነግጥም ነገር ያድንሃልና። በላባዎቹ ይጋርድሃል፥ በክንፎቹም በታች ትተማመናለህ፤ እውነት እንደ ጋሻ ይከብብሃል። ከሌሊት ግርማ፥ በቀን ከሚበርር ፍላጻ፥ በጨለማ ከሚሄድ ክፉ ነገር፥ ከአደጋና ከቀትር ጋኔን አትፈራም። በአጠገብህ ሺህ በቀኝህም አሥር ሺህ ይወድቃሉ፤ ወደ አንተ ግን አይቀርብም። በዓይኖችህ ብቻ ትመለከታለህ፥ የኃጥኣንንም ብድራት ታያለህ። አቤቱ፥ አንተ ተስፋዬ ነህና፤ ልዑልን መጠጊያህ አደረግህ። ክፉ ነገር ወደ አንተ አይቀርብም፥ መቅሠፍትም ወደ ቤትህ አይገባም።
በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፤ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል። በተኵላና በእባብ ላይ ትጫማለህ፤ አንበሳውንና ዘንዶውን ትረግጣለህ። በእኔ ተማምኖአልና አስጥለዋለሁ፤ ስሜንም አውቆአልና እጋርደዋለሁ። ይጠራኛል እመልስለትማለሁ፥ በመከራውም ጊዜ ከእርሱ ጋራ እሆናለሁ፤ አድነዋለሁ አከብረውማለሁ። ረጅምን ዕድሜ አጠግበዋለሁ፥ ማዳኔንም አሳየዋለሁ።"

                መዝሙር 91

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
የቀደሙት ሰዎች በሰናዖር ከምድር እስከ ሰማይ፣ እስከ አምላክ ማደሪያ የሚደርስ ግንብ ሊሠሩና ስማቸውን ሊያስጠሩ ተነሡ። ነገር ግን በትዕቢታቸው ጠፉ። እነዚህ የባቢሎን ሰዎች ምንኛ ችኩሎች ሆኑ?! ጥቂት ዘመን ቢታገሱ ኖሮ ራሱ አምላክ ከእነርሱ እንደ አንዱ ሰው ሆኖ በግርግም ተኝቶ ያገኙት አልነበር?!

እነዚህ የሰናዖር ሰዎች ትንሽ ቢታገሱ ኖሮ ከምድር ወደ ሰማይ መሻገሪያ የምትሆን በእግዚአብሔር እጅ የታነጸች ታላቋን የብርሃን ድልድይ ድንግል ማርያምን ያገኙዋት ነበር። በዚህችም የብርሃን ድልድይ (መሰላል) እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ የሰው ልጆች ሁሉ ስም እንደ ተጠራ አይተው ደስ ይሰኙ ነበር።

====

አቤቱ ጾም፣ ጸሎት፣ መንፈሳዊ ትሩፋቶቻችን የአንተ ረድኤት የሌለባቸው በትዕቢት ያቆምናቸው የሰናዖር ግንቦች አይሁኑብን። እንዲህም ከሆኑ፣ በሥራዬ እያለ ልባችን እንዳይኮራ፣ ዓይናችንም ወደታች እያየ ወዳጆቹን እንዳይንቅ ወደ አንተ የማያደርሱንን እነዚህን የሐሰት ግንቦች አፍርስልን። በእነርሱም ፈንታ በትሕትና እና በፍቅር ያጌጡ ውብ ግንቦችን እናንጽ ዘንድ ረድኤትህን ላክልን።

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
https://www.tg-me.com/Dnabel
https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
ሰው አያከብርህም?

ሰው ሲሰድብህ ትናደዳለህ? የሚያዋርድ እና አንገት የሚያስደፋ ነገር ቢያደርግብህስ በቁጣ ትገነፍላለህ? ግን አንድ ጊዜ ቆም ብለህ እስኪ ራስህን ጠይቅ? ከአንተ በላይ አንተን የሰደበ፣ ከአንተ በላይ አንተን ያዋረደ እና አንገት የሚያስደፋ ነገር ያደረገብህ አለ? ከአንተ በላይ አንተነትህን ዋጋ ቢስ ያደረገ ማን ነው? አንተ አይደለህ?

አንተው መልስ!

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደሚለው ለሰው ጠላቱ ማንም አይደለም፤ ራሱ ነው። የሕይወትን ዛፍ ቸል ብሎ ወደ እጸ በለስ የሚሮጠው፣ የብርሃኑን ልብሱን ጥሎ ቅጠል ማገልደም የሚያምረው፣ ከወንድሙ ጋር በሰላም ከመኖር ይልቅ ደሙን አፍስሶ ዚቅበዘበዝ መኖር የሚመርጠው ሰው ራሱ ነው።

ሌላውን ከመውቀስህ በፊት መጀመሪያ አንተ ራስህን ታከብራለህ? በአንተ ዘንድ የአንተነትህ ዋጋው ስንት ነው? ከልብስ ይልቅ ሰውነትህን ከመብልስ በፊት ነፍስህን ታስቀድማለህ? አንተ ራስህን በክፋት እና በበደል እንዲህ እያጎሳቆልክ “ማንም አያከብረኝም” እንዴት ትላለህ?

ዲያቆን አቤል ካሣሁን
[email protected]
ሰሞኑን በሎሳንጀለስ ከተነሣው ሰደድ እሳት ጋር ተያይዞ በየማኅበራዊ ድረ ገጹ ሲዘዋወር የቆየ አንድ ፎቶ ነበር። ለነገሩ ቤቱ ነው እንጂ አንድ ፎቶዎቹ ግን ሦስት ዓይነት ነበሩ። ከፎቶዎቹም ጋር ተያይዞ “ይህ ቤት በሎሳንጀለስ የሚኖር የክርስቲያን ቤት ሲሆን የእሳት ወላፈን ሳይነካው በእግዚአብሔር ጥበቃ የተረፈ ነው”የሚሉ ያልተረጋገጡ ዘገባዎች በስፋት ሲዘገቡ ሰንብተዋል።

ነገር ግን ከሦስቱ የቤት ፎቶዎች ሁለቱ በ2023 ዓ.ም. አውስትራሊያ ላይ ተፈጥሮ ከነበረው ሰደድ እሳት የተረፈ የአንድ ቤት ምስል ሲሆኑ፣ ሦስተኛው (የተቃጠሉ ቤቶች መካከል ያለው) ደግሞ በAI ቴክኖሎጂ አማካኝነት የተፈበረከ ፎቶ ነው።

እግዚአብሔር ከሚነድ እሳት ሊያድን እንደሚችል መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ባያድንም ግን እግዚአብሔርነቱ ጥርጥር ውስጥ የሚገባ አይደለም። የውሸት ፎቶ እየፈበረኩ እንዲህ ዓይነት ዜና መንዛት ግን ሃይማኖት እና ሃይማኖተኝነትን ያዋርድ እንደ ሆነ እንጂ አያስከብርም።

ዲያቆን አቤል ካሳሁን

https://www.snopes.com/news/2025/01/14/la-fires-home-god-saved/
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
መቼ ላግባ?

እንኳን ለቃና ዘገሊላ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!
🌸🐝 የንብ ዓይን ይኑርህ🌸🐝

አንዳንድ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ የተሳሳቱ ነገሮች እንደሚያዩ እና ያም እንደሚያሳዝናቸው ይነግሩኛል። እኔም ለእነዚህ ሰዎች ይህን እላቸዋለሁ:-

ዝምብን አግኝታችሁ “እዚህ አካባቢ አበባ አይተሻል?” ብትሏት፡- “ስለ አበቦቹ እንኳን የማውቀው ነገር የለም። ባይሆን እዚያ ጋር የምታየው ክምር ላይ የፈለግኸውን ቁሻሻ ልታገኝ ትችላለህ” ብላ ልትመልስልህ እና ንጹሕ ያልሆኑ ብዙ የቆሻሻ ዓይነቶችን ልትዘረዝርልህ ትችላለች።

ንብን አግኝተህ ደግሞ “እዚህ አካባቢ የተጣሉ ቆሻሾች አይተሽ ይሆን?” ብለህ ብትጠይቃት፣ “ቆሻሻ ነገሮች? ኸረ እኔ ምንም አላየሁም። ይህ ቦታ እኮ ልዩ ልዩ መዓዛ ባላቸው አበቦች የተሞላ ነው” ስትል ልትመልስልህ እና በአትክልቱ ስፍራ ያሉትን አበቦች አንድ በአንድ ልታስቆጥርህ ትችላለች።

አየህ! ዝምብ የቆሸሹ ነገሮች የት ሊገኙ እንደሚችሉ ብቻ ስታውቅ፣ ንብ ግን ውብ የሆኑ አበቦች መኖሪያ ወዴት እንደሆነ ታውቃለች።

አሁን ላይ እንደ ተረዳሁት ከሆነ አንዳንድ ሰዎች ንብን ሲመስሉ ሌሎች ደግሞ ዝንብን ይመስላሉ። ዝንብን የሚመስሉት በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ክፉን ነገር ብቻ እያሻተቱ የሚፈልጉ እና ሐሳባቸውም በዚያ የሚዋጥባቸው ናቸው። እነዚህ ሰዎች የትም ቦታ ቢሆን ጥሩ ነገር አይታያቸውም።

ንቧን የሚመስሉት ግን በሚያዩዋቸው ነገሮች ሁሉ ውስጥ ጥሩን ነገር ያስተውላሉ።

ትርጉም፡ ዲያቆን አቤል ካሣሁን
ምንጭ፡ St. Paisios of Mt. Athos, "Good and Evil Thoughts”
2025/06/30 22:22:32
Back to Top
HTML Embed Code: