Telegram Web Link
🌿🌾 #ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ🌾🌿

እውነተኛ ፈተና አንድና አንድ ብቻ ነው ፣ እርሱም ኃጢአት ነው፡፡

አንተ የራስን ድርሻ ተወጥተ ስትጨርስ እግዚአብሔር የራሱን ድርሻ ይወጣል፡፡

መውደቅ አዳማዊ ነው ወድቆ አለመነሳት ግን ዲያብሎሳዊ ነው፡፡

ከውኃ እንዴት እንወለዳለን የሚል ሰው ካለ እንዴት ከአፈር ተወለድን ብዬ እጠይቀዋለው፡፡"

ደጋግመህ ኃጢአት ብትሠራም ደጋግመህ ንስሐ ግባ፡፡ ቤተክርስቲያን ሐኪም ቤት እንጂ ፍርድ ቤት አይደለችምና፡፡”

ትዕቢት የነበረንን መልካም ምግባር ሁሉ የሚያሳምም ደግሞም የሚገድል ክፋ ደዌ ነው፡፡

ከእግዚአብሔር ጋር ታረቅ ፤ ከዚያም ሰማይና ምድር ከአንተ ጋር ይታረቃሉ

ዕውቀት የሚባለው የገዛ ራስን ሲያውቁ ነው፡፡ ራስን አለማወቅ ከለየለት ዕብደት እጅግ የከፋ ነውና፡፡ ምክንያቱም የለየለት ዕብደት የሚባለው ሳይወዱና ሳይፈቅዱ የሚመጣ በሽታ ሲኾን ራስን አለማወቅ ግን ወደውና ፈቅደው የሚያብዱት ዕብደት ነው፡፡

ሰዎች ከፍቅር በላይ በየትኛውም ዓይነት መንገድ ከክፋታቸው ልንመልሳቸው አንችልም፡፡ ፍቅር ሰዎች ከአውሬነታቸው መልሳ ሰዎች እንድሆኑ የምታደርግ ታላቅ መምህርት ናት፡፡

የበለስ ቅጠል ሰፊና ደስ የምታሰኝ ናት፤ ወደ ጥፋት የምትወስደው የኃጢአት መንገድም ሰፊ በር ናት፡፡ የበለስ ፍሬ ሲበሏትና ሲያላምጧት ጣፋጭ ናት፤ ኃጢአትም ሲሠሯት ደስ ታሰኛለች፡፡ ከሠሯት በኋላ ግን (እንደ በለሲቱ) መከራን ታመጣለች፡፡ በሚሠሯት ጊዜ ጣፋጭ ከሠሯት በኋላ ግን መራር ናትና እርሷን ከመሥራት ሽሽ፡፡

•••✞✞✞•••✞✞✞•••✞✞✞•••
✞ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያንን አስተምሮና ስርዓት የጠበቁ የተለያዩ መርሃ ግብሮች በየቀኑ ወደ እርስዎ ይቀርባሉ፡፡ ለወዳጅዎ #Share በመድረግ የበረከት ተካፋይ ያድርጓቸው ✞
╭══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╮
https://www.tg-me.com/EOTC2921
╰══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╯
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ✞✞✞
✞✞✞ ጥር 18 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ✞✞✞
+" #ቅዱስ_ጊዮርጊስ_ልዳዊ "
✞✞✞ መጽሐፈ ገድሉ እንደሚለው የሰማዕታት አለቃቸው: አንድም ሞገሳቸው ታላቅና ክቡር ሰማዕት ቅዱስ
ጊዮርጊስ ከ7 ዓመታት ስቃይ በኋላ ተሰይፏል:: ይህስ ጥንተ ነገሩ እንደምን ነው ቢሉ:-
+ቅዱሱ የተወለደው ከአባቱ ዘረንቶስ (አንስጣስዮስ) እና ከእናቱ ቴዎብስታ የድሮው ፋርስ ግዛት ፍልስጥኤም
(ልዳ) ውስጥ ነው:: የተባረኩ ወላጆቹ ክርስትናን ጠንቅቀው አስተምረውት አባቱ ይሞታል::
+ቅዱስ ጊዮርጊስ 20 ዓመት ሲሞላው የአባቱን ስልጣን እጅ ለማድረግ ሲሔድ የቢሩት (የአሁኗ ቤይሩት-ሊባኖስ)
ሰዎች ዘንዶ/ደራጎን ሲያመልኩ አገኛቸው:: እርሱ ግን የከተማውን ሕዝብ አስተምሮ: አሳምኖ: ደራጎኑንም
በፈጣሪው ኃይል ገድሎ መንገዱን ቀጥሏል::
+ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ዱድያኖስና 70 ነገሥታት ዘንድ ሲደርስ ክርስቶስ ተክዶ ለጣዖት ይሠገድ ነበር:: በዚያች
ሰዓት ድንግል እመቤታችን ወደ ሰማዕቱ መጥታ መከራውንና ክብሩን ነገረችው:: እርሱም በክርስቶስ ስም መሞት
ምርጫው ነበርና ከእመቤታችን ተባርኮ ወደ ምስክርነት አደባባይ (ዐውደ
ስምዕ) ደረሰ::
+ከዚያም ለተከታታይ 7 ዓመታት ብዙ ጸዋትወ መከራዎችን ተቀበለ:: 3 ጊዜ ሙቶ ተነሳ:: ከሰው ልጅ የተፈጥሮ ትዕግስት በላይ የሆነ ስቃይን ስለ ቀናች ሃይማኖት ሲል በመቀበሉ የሰማዕታት አለቃቸው: ፀሐይና የንጋት ኮከብ በሚል
ይጠራል:: "ተውላጠ ጻማሁ ወሕማሙ:
ዘተለዐለ ሞገሰ ስሙ" እንዲል መጽሐፍ::
+ከ7 ዓመታት መከራ በኋላም ከብዙ ተዓምራት ጋር ተሰይፎ ደም: ውሃና ወተት ከአንገቱ ፈሷል:: 7 አክሊላትም
ወርደውለታል::
+" ዝርወተ ዓጽሙ "+
+ይህቺ ዕለት ለሰማዕቱ 'ዝርወተ አጽሙ' ትባላለች:: በቁሙ 'አጥንቱ የተበተነበት' እንደ ማለት ነው:: ቅዱስ ጊዮርጊስን ለዘመናት በብዙ ስቃያት ሲያስጨንቁት ኖረው በጽናቱ አሸነፋቸው:: 70 ነገሥታትን ከነ ሠራዊታቸው ከማሳፈሩ
ባሻገርም በርካታ (በመቶ ሺ የሚቆጠሩ) አሕዛብን ማርኮ ለሰማዕትነት አበቃ::
+በዚህ የተበሳጨ ዱድያኖስም ኮከበ ፋርስ ቅዱስ ጊዮርጊስን እንዲቆራርጡት አዘዘ:: ወታደሮቹም ቅዱሱን
ቆራርጠው: በብረት ምጣድ ላይ ጠበሱት:: ያለ ርሕራሔም አካሉን አሳረሩት:: ቀጥለውም ፈጭተው አመድ አደረጉት::
+በአካባቢው ወደ ነበረው ትልቅ ተራራ ጫፍ (ደብረ ይድራስ) ወጥተውም በነፋስ በተኑት:: "ሐረድዎ ወገመድዎ: ወዘረዉ ሥጋሁ ከመ ዓመድ" እንዲል:: (ምቅናይ)
+እነርሱ ይህንን ፈጽመው ዘወር ሲሉ ግን የቅዱሱ ዓጽም ባረፈባቸው ዛፎች: ቅጠሎችና ድንጋዮች ሁሉ "ቅዱስ
ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት" የሚል ጽሑፍ ተገኘ:: ስለዚህም ይህቺ ዕለት
ቅዱሱ አለቅነትን የተሾመባት ናት ማለት ነው::
+ወዲያው ግን ኃያል ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተበተነበት ተነስቶ ወታደሮችን አገኛቸውና "በክርስቶስ እመኑ" ብሎ:
አስደንቆ ወደ ሕይወት መራቸው:: 70ው ነገሥታት ግን አፈሩ::
+" ቅዱስ ባኮስ ጃንደረባው "+
+'ጃንደረባ' የሚለው ቃል በግዕዙ 'ሕጽው' ተብሏል:: ይህ ስም በቤተ ክርስቲያን የተለመደ እንጂ እንግዳ አይደለም:: መድኃኒታችን እንዳለው በተፈጥሮ የሆኑ: ሰዎች እንዲያ
ያደረጉዋቸውና ራሳቸውን ስለ ጽድቅ ጃንደረባ ያደረጉ ብዙዎች ናቸውና::
+ኢትዮዽያዊው ጃንደረባ ቅዱስ ባኮስም (አንዳንዴ አቤላክ / አቤሜሌክም ይባላል):-
*በ1ኛው መቶ ክ/ዘመን በሃገራችን ኢትዮዽያ ተወልዶ ያደገ
*ነገሥታቱንና ሃገሩን በሙያው ያገለገለ
*በተለይ ከ34 እስከ 46 ዓ/ም ለነገሠችው ንግሥት ሕንደኬ ገርስሞት በገንዘብ ሚንስትርነት ያገለገለ
*በገንዘቧ ላይ ሁሉ አዛዥ (ታማኝ) የነበረ
*ጃንደረባ በመሆኑ ለንግሥቲቱና ቤተሰቧ ቅርብ የነበረ
*መጻሕፍትን የሚያነብና የሚመረምር
*ዘወትር ወደ ኢየሩሳሌም እየሔደ ከቅዱሳት መካናት የሚሳለም በጐ ሰው ነበር::
+በግብረ ሐዋርያት ምዕ. 8:26 ላይ እንደ ተጠቀሰው
ቅዱሱ ከኢየሩሳሌም ለፋሲካና ለእሸት በዓል ነበር የሔደው::
ሲመለስ መንፈስ ቅዱስ ከፊልዾስ ጋር በጋዛ አገናኝቶታል:: በዚያም ምሥጢረ ክርስትናን ተምሮ: በክርስቶስ
አምላክነትና አዳኝነት አምኖ ተጠምቁዋል::
+ክርስትናን ለኢትዮዽያ በ34 ዓ/ም አምጥቷል:: "ጃንደረባው ለወገኖቹ ሐዋርያ ሆነ" ሲል ቅዱስ ዮሐንስ
አፈ ወርቅ እንደ ተናገረው ወደ ሃገራችን ተመልሶ: ስለ ክርስቶስ ሰብኮ በርካቶችን አሳምኗል::
+ቀጥሎም ሃብቱን ንቆ (መንኖ): ከኢትዮዽያ እስከ ሕንድ
ወንጌልን ሰብኮ በዚህች ዕለት በሰማዕትነት ዐርፏል::
(ተሰውሯል የሚሉም አሉ)
<< በእውነት ለቅዱስ ባኮስ ክብር ይገባል:: >>
+" ቅዱስ ያዕቆብ ዘንጽቢን "+
+ይህ ቅዱስ ሰው:--
*እጅግ የተመሠከረለት ሊቅ
*በፍጹም ትሕርምት የኖረ ገዳማዊ
*በርካቶችን ወደ ክርስትና ያመጣ ሐዋርያዊ
*ለአእላፍ ምዕመናን እረኛ የሆነ የንጽቢን (ሶርያ) ዻዻስ
*ለጀሮ ድንቅ የሆኑ ተአምራትን የሠራ ገባሬ መንክራት
*ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊን ጨምሮ በርካታ ሊቃውንትን ያፈራ ታላቅ መምሕር
*ለክርስቶስና ለእመቤታችን ታጥቆ የተገዛ የፍቅር ሰው
*እጣቶቹ እንደ ፋና የሚያበሩለት ማኅቶት
*ራሱን ዝቅ አድርጐ በቆሸሸ ልብስ የሚኖር የትህትና ሰው ነው::
+በ325 (318) ዓ/ም: በኒቅያ 318ቱ ሊቃውንት ሲሰበሰቡና አርዮስን ሲያወግዙ እርሱ አንዱ ነበር::
በሥፍራውም ሙት አስነስቶ ሕዝቡን አስደምሟል:: በዚያም የቤተ ክርስቲያንን
ሥርዓት ሠርቶ ወደ ሃገሩ ተመልሶ በቅድስና ኑሮ በዚህች ቀን
ዐርፎ በክብር ተቀብሯል::
+"+ ደናግል ማርያ ወማርታ +"+
+በዘመነ ሐዋርያት በተመሳሳይ 'እንተ ዕፍረት-ባለ ሽቱ' ተብለው የሚጠሩ 2 እናቶች ነበሩ:: 2ቱም ስማቸው
ማርያም ስለ ነበር ለመለየት እንዲያመች አንደኛዋን 'ማርያም ኃጥዕት-
ከኃጢአት የተመለሰች': 2ኛዋን ደግሞ 'ማርያም እኅተ አልዓዛር-በቢታንያ የነበረችው ብለው አበው ይጠሯቸዋል::
+በሉቃስ ወንጌል ላይ የምትገኘው ከኃጢአት ሕይወት የተመለሰችው ስትሆን በዮሐንስ ወንጌል 12:1 ላይ
ያለችው የአልዓዛር እህት (ድንግሊቱ) ናት:: ዛሬም የምናስባት ይህቺውን
እናታችን ነው::
+ቅድስት ማርያም መድኃኒታችን ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ በሚያስተመርበት ዘመን በቢታንያ አካባቢ ትኖር የነበረች ድንግል ወጣት ናት:: ወላጆች ባልነበረበት ቤት ውስጥ
ታላቆቿ አልዓዛርና ማርታ አሳድገዋታል::
+በቤተሰብ ደረጃ እንግዳን ይቀበሉ ነበርና ጌታችን ወደዳቸው::
አልዓዛርን ከ72ቱ አርድእት: ማርያምና ማርታን ደግሞ ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት ቆጥሯቸዋል:: ወንድማቸው አልዓዛር በታመመ ጊዜ ወደ ጌታ ልከው ነበር::
+ያለ ጊዜው የማይሠራ ጌታ ባይመጣ አልዓዛር ሞተ:: በ4ኛው ቀን አምላክ ሲመጣ ቅድስት ማርያም በጌታ ፊት
ሰግዳ "እግዚእየ ሶበሰ ኀሎከ ዝየ እምኢሞተ እሑየ-አንተ በዚህ
በኖርክስ ወንድሜ ባልሞተ ነበር" ብላ አለቀሰች:: (ዮሐ.11)
+ጌታም ስታለቅስ ባያት ጊዜ አምላክነቱ አራርቶት አለቀሰ:: ወዲያውም በስልጣነ ቃሉ አዞ አልዓዛርን
አስነሳው:: ከፋሲካ (ጌታ ከመሰቀሉ 6 ቀናት) በፊትም ቅዱሳኑ ለጌታ ግብር
አገቡ:: እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ታደመላቸው:: (ዮሐ. 12:1)
+በዚያም አልዓዛር ከጌታ ጐን ሲቀመጥ: ቅድስት ማርያም ከጌታ ሥር ተንበርክካ: ናርዶስ የሚሉትን የ300 ዲናር ሽቱ
በጌታ ላይ አፈሰሰች:: መዓዛ መለኮቱና ሽቱው ሲገናኝ "መልዐ መዓዛሁ" እንዲል ምስጥ የሚያደርግ ሽታ ቤቱን ሞላው::
+
🌾#ይህ_ነው_ጊዮርጊስ🌾

ይህ ነው ጊዮርጊስ ከሰማእታት አንዱ /፪/
መጣ እንዲረዳን እንዲያፅናናን /፪/
🌾#ቅዱስ_ጊዮርጊስ_አበርታኝና🌾

ቅዱስ ጊዮርጊስ አበርታኝና
እኔም እንዳንተ በሐይማኖት ልጽና(፪)

የፈረሱ ኮከብ የልዳው ፀሐይ
ሊቀ ሰማዕት ታማኝ አገልጋይ
እጅግ ድንቅ ነው ገደልህ ታምራትህ
ከሞት ያስጥላል ምልጃና ጸሎትህ

#አዝ---❖---❖---❖---
ለዘንደው እራት ግብር የተጣሉ
ምልጃ የሚያሻችው በግፍ የታሰሩ
የተጨነቁ ፍጥረታት አሉና
ስበክላቸው የድህነት ዜና

#አዝ---❖---❖---❖---
የበረት ጫማ ሰይፍና እሳቱ
ቢፈራረቅም ፀንቷል ለሐይማኖቱ
የሚነበብ ነው ህይወቱ መጽሐፉ
የሚያበረታ ልብ የሚያሳርፍ

#አዝ---❖---❖---❖---
ዝሏል ጉልበቴ በዚህ አለም ፈተና
ቅዱስ ጊዮርጊስ ፈጥነህ ወደኔ ና
አፅናኝ ደግፈኝ አቁመኝ በእምነት
ጎጆየን ይሙላው ያንተ በረከት

#አዝ---❖---❖---❖---
ለዘንደው እራት ግብር የተጣሉ
ምልጃ የሚያሻቸው በግፍ የታሰሩ
የተጨነቁ ፍጥረታት አሉና
ስበክላቸው የድህነት ዜና
#የእመቤታችን_በዓለ_ዕረፍት
🌾🌾🌾🙏🙏🙏🌾🌾🌾
✞✞✞ #አስተርእዮ_ማርያም ✞✞✞

በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
ጥር 21 የእመቤታችንን በዓለ ዕረፍት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በታላቅ ድምቀት ታከብራለች። የቅድስት ድንግል ማርያም መላ ዕድሜዋ 64 ሲኾን ይኸውም በእናት ባባቷ ቤት 3 ዓመት፤ በቤተ መቅደስ 12 ዓመት፤ ጌታን ፀንሳ በቤተ ዮሴፍ 9ወር ከ5 ቀን፤ ከልጇ ጋር 33 ዓመት ከ3 ወር ከቆየች በኋላ፤ ዓለምን ለማዳን በዕለተ ዓርብ በመስቀል በተሰቀለ ጊዜም የሚወድዳት እናቱን ለሚወድደው ደቀ መዝሙር ለዮሐንስ “እነኋት እናትኽ” በማለት አደራ በመስጠት በዮሐንስ በኩል ለሚወድደን ለእኛ የአደራ ልጆቿ እንድንኾንና የአደራ እናታችን እንድትኾን ታላቅ ስጦታን በቀራንዮ በእግረ መስቀል ሥር ሰጠን (ዮሐ ፲፱፥፳፮‐፳፯)፡፡

በዚኽም መሠረት ሐዋርያትም ከአምላካቸው የተሰጠቻቸው የአምላካቸውን እናት ይዘው ሲጸልዩ መንፈስ ቅዱስ ወርዶ ፸፪ት ቋንቋ ገልጾላቸው ታላቅ መንፈሳዊ ኀይልን ሰጣቸው (የሐዋ ፩፥፲፬)፤ ዮሐንስም በእናትነት የተቀበላት ቅድስት ድንግል ማርያምን በቤቱ 15 ዓመት አኑሯታል፡፡

ከዚያም ልጇ ክርስቶስ ለእናቱ ተገልጾ ከኀላፊው ዓለም ወደ ማያልፈው ሰማያዊዉ ዓለም ሊወስዳት እንደኾነ ነገራት፤ ርሷም ይኽነን ለሐዋርያት ነገረቻቸው፤ እነርሱም “አይቴ ተሐውሪ እግዝእትነ” (እመቤታችን ወዴት ትኼጃለሽ) ብለው ሲጠይቋት “ኀበ ጸውአኒ ወልድየ” (ልጄ ወደጠራኝ) በማለት ወደዚያኛው ዓለም የመኼጃዋ ጊዜ እንደደረሰ ነገረቻቸው፤ ይኽነን ሰምተው “ወበከዩ ኲሎሙ ሐዋርያት” ይላል ሐዋርያት በእጅጉ ዐዘኑ አለቀሱ፡፡

ያን ጊዜ ቅዱሳን መላእክት ተገልጸው ሐዋርያትን ማዕጠንታቸውን ይዘው ደስ አሰኝተው እንዲሸኝዋት እንጂ እንዳያዝኑ እንዳያለቅሱ በመንገር አረጋጓቸው፤ ቁጥሩ ከ72 ቱ አርድዕት የኾነው ቅዱስ ኢቮዲደስ እንደጻፈው የእመቤታችን ዕረፍቷ ሲደርስ ጌታ ተገልጾ እናቱን እንዲኽ አላት:-

"ዛሬ ለዘጠኝ ወራት በምድር ላይ መኖሪያዬ ኾና የቆየችውን ድንግል እናቴን የምቀበልበት እና ከእኔ ጋር ወደ ሰማያት ሰማያዊ ቦታዎች ይዤያት በመውሰድ ለመልካሙ አባቴ በስጦታ የማስረክባት ቀን ነው፣ ዳዊትም እንኳን “በኋላዋ ደናግሉን ለንጉሥ ይወስዳሉ፤ ባልንጀሮችዋንም ወደ አንተ ያቀርባሉ” (መዝ ፵፬፥፲፬) እንዳለ።

ጌታም በመለኮታዊዉ እና ግሩም ድምፁ የኔ ውድ እናት ሆይ ተነሥተሽ ወደ እኔ ነዪ (መሓ ፪፥፲)፤ የነፍሴ ደስታ የኾንሽ ወደ እኔ ነዪ (መሓ፪፥፲፫) አላት፤ አንቺ ከቄዳር ልጆችም በላይ ውብ ቆንዦ ነሽ (መሓ ፩፥፭)፤ አንቺ የተመረጥሽ ጎጆ ሆይ የመልካማ ርግብ መኖርያ ነሽ፤ አንቺ የተመረጥሽ የአትክልት ስፍራ ያለምንም ዘር እና የወንድ ሩካቤ መልካሙን ፍሬ ያፈራሽ (መሓ ፬፥፲፪)።

አንቺ የወርቅ መሶብ ሆይ መናው እውነተኛው መና እኔ እንኳን የተሰወርኹብሽ (ዘፀ ፲፮፥፴፫-፴፬)፤ አንቺ ስዉር ቅርስ እውነተኛው ብርሃን የተሰወረብሽ እና ከአንቺም ውስጥ ወጥቶ በመገለጽ በሰው ልጆች ላይ የተትረፈረፈ ሀብት ያስገኘላቸው፡፡

ተነሥተሽ ወደ እኔ ነዪ የእኔ ውብ ርግብ ሆይ (መሓ ፮፥፱) የእኔ ቅድስት መርዐት (መሓ ፬፥፰)፣ የእኔ ንጽሕት መስክ፣ ከእኔ ጋር ወደ አትክልት ስፍራው እወስድሻለኊ (መዝ ፸፩፥፮) ከርቤ እና ጣፋጭ ቅመማ ቅመሜን እደረድርልሻለኊ (መሓ ፬፥፲፬) ከበታችሽም እንድታርፊበት ያማረውን ምንጣፍ አነጥፍልሻለኊ፤ ማርያም እናቴ ሆይ አንቺ የተባረክሽ ነሽ ወደ ምድር ወልደሽ አምጥተሽኛልና፡፡

እኔ ኹሉን መጋቢ የኾንኹትን ያጠቡ ጡቶሽን የተባረኩ ናቸው፡፡ እንዲኹም በከፍታ ቦታዎች ወደሚገኙ ሰማያዊ ስፍራዎች ወስጄሽ በአባቴ በመልካም ነገሮች እመግብሻለኊ፡፡ እስከዚያው በጉልበትሽ ላይ ያስቀመጥሺኝ ድንግል እናቴ ማርያም ሆይ በኪሩቤል ሠረገላ ላይ በማኖር ከእኔና ከቸሩ አባቴ ጋር ወደ ሰማያት እወስድሻለኊ፡፡

በመጠቅለያ ጨርቆች እንደጠቀለልሽኝ ኹሉ የእኔ ድንግል እናት ማርያም ሆይ በወለድሽኝ ዕለት በከብቶች በረት ከላም እና አህያ ጋር በአንድ ላይ ከብበውኝ እንዳኖርሽኝ ኹሉ (ኢሳ ፩፥፫፤ ሉቃ ፪፥፯)፤ እኔ ደግሞ ዛሬ ከእኔ ጋር ከሰማያት ባመጣዋቸው በሰማይ መጐናጸፊያ ሰውነትሽን እጠቀልለዋለኊ፤ ከዚያም ከሕይወት ዛፍ ሥር አስቀምጠዋለኊ፣ ኪሩቤልም በሰይፈ ነበልባላቸው እንዲጠብቁት አደርጋለኊ (ዘፍ ፫፥፳፬)፡፡

የተባረከችውን ነፍስሽን የሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም መንበር በተሸፈነችበት መሸፈኛዎች እንድትሸፈን አደርጋለኊ፡፡ እኔን በሚያሳድድበት ጊዜ ሥርዓት አልባውን ሄሮድስ በመፍራት ወደ ግብጽ ምድር እንደተሰደድሽው ኹሉ (ማቴ ፪፥፲፫-፲፰)፤ መላእክቶቼ ኹልጊዜም በክንፎቻቸው እያጠሉብሽ እና መልካም ዝማሬያቸውን እንዲዘምሩልሽ አደርጋለኊ አላት፡፡

ከዚያም ጥር 21 እሑድ ዕለት በልጇ ፈቃድ በመዐዛ ገነት፣ በመዝሙረ ዳዊት፣ በይባቤ መላእክት የእመቤታችን ነፍሷ ከሥጋዋ ተለየች፤ ጌታም እንደ በረዶ ጸዐዳ የኾነውን የድንግል ማርያምን ነፍስ በዕቅፉ ውስጥ እንደያዘ ለነፍሷ የከበረ ሰላምታውን ሰጥቶ ባማረው ሸማ ጠቅልሏት ለሊቀ መልአኩ ለቅዱስ ሚካኤል በብርሃናማ ክንፎቹ እንዲሸከማት ሰጠው።

ከዚያም ልጇ “የእኔ እናት ማርያም ሆይ እግዚአብሔርን (እኔን) የሳምሽባቸው ከናፍሮችሽ የተባረኩ ናቸው፤ ወደ ምድር ሲመለከት መሠረቶቿ እንዲናጉና እንዲሸበሩ ለማድረግ የሚችለውን ከኀሊውን ልጅሽንና አምላክሽን (እኔን) ያየሽባቸው ዐይኖችሽ የተባረኩ ናቸው፤ ከሰማያት ነዋሪዎች ጋር በመላእክት ቋንቋዎች ስነጋገር የሰማሽባቸው ዦሮዎችሽ የተባረኩ ናቸው።

አንቺ ሆይ በቃሉ ኀይል ምድርን የተሸከማትን የተሸከሙት የኖርኹባቸው ታናናሾች ክንዶችሽ የተባረኩ ናቸው፡፡ የእኔ ድንግል እናት ማርያም ሆይ ፍጥረትን ኹሉ የምመግበውን የመገቡት እና ያጠቡት ጡቶችሽ የተባረኩ ናቸው፡፡ በኀያሉ ዙፋን ላይ በክብር የምቀመጠውን እኔን በፍቅር ያስቀመጡኝ ጉልበቶችሽ የተባረኩ ናቸው፡፡ ለዘጠኝ ወራት የተሸከሙኝ ማሕፀኖችሽም የተባረኩ ናቸው፡፡ በመለኮታዊነቴ ብርሃን ብሩሃት የኾኑት ሥጋሽና ነፍስሽ የተባረኩ ናቸው” አላት::

ሐዋርያት በታላቅ ግርማ በአምላክ እናት ሥጋ ፊት ምስጋናን እያሰሙ ዝማሬን እየዘመሩ ሥጋዋን እጅ እየነሡ ጌቴሴማኒ ሊቀብሯት ሲኼዱ አይሁድ አይተው ለምቀኝነት አያርፉምና ቀድሞ ልጇ ሞተ፣ ተነሣ፣ ዐረገ እያሉ እያስተማሩ ኖሩ ከመቃብሩም ተአምራት ይደረጋል፤ አሁን ደግሞ ርሷ ሞተች፣ ተነሣች፣ ዐረገች ብለው ሊያስተምሩ አይደል፤ “ንዑ ናውዒ ሥጋሃ ለማርያም ምስለ ዓራታ” በማለት በምቀኝነት ተነሡባቸው፤ ታውፋንያ የሚባል ከአይሁድ ወገን በድፍረት የአልጋዋን አጎበር ሊነካ ሲሞክር ቅዱስ ገብርኤል በሰይፈ እሳት ቀጣው፡፡

ያን ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስ በዕለተ ዐርብ ከአምላኩ በስጦታ የተሰጠችውን የአምላክ እናትን ሥጋዋን በድፍረት ሊነኩ መምጣታቸውን አይቶ “ይቤ ዮሐንስ ወኢይገድፍ ምዕቅብናየ ወዘንተ ብሂሎ ወድቀ በላዕሌሃ” ይላል (ዐደራዬን አላፈርስም፤ ከርሷ ጋር እሞታለኊ በማለት ይኽነን ተናግሮ በላይዋ ላይ ወደቀ፡፡ ከዚያም “ወወረዱ ሚካኤል ወገብርኤል እምሰማይ በዐቢይ ግርማ” ይላል ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል በታላቅ ግርማ ወርደው የቅድስት ድንግል ማርያምን ሥጋዋንና ቅዱስ ዮሐንስን በደመና ነጥቀው በገነት በሕይወት ዛፍ ሥር አኖሯት፡፡

ወዲያውኑ “ወአምጽኡ ሎቱ ማዕጠንተ ወርቅ” ይላል የወርቅ ማዕጠንት ለዮሐንስ አምጥተውለት፤ “ወዕጥን ሥጋሃ ለማርያም መዓልተ ወሌሊተ” ይላል የቅድስት ድንግል የከበ
ረ ሥጋዋን በመዓልትና በሌሊት ዕጠን አሉት፤ ዮሐንስም ይኽነን ክብር በመቀበሉ ደስ ብሎት ሥጋዋን እያጠነ “ወፍና ሠርክ ያመጽዕ ሎቱ ራጉኤል መልአክ ኅብስተ ሰማይ” ይላል ሰርክ ሲኾን ራጉኤል መልአክ ሰማያዊ ኅብስት ሰማያዊ መጠጥ እያመጣለት ያን እየተመገበ በገነት ቆይቷል፡፡
[የአምላክ እናት ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ ከማያልቀው በረከትሽ አብዝተሽ አሳድሪብን]
በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
፡ ፡ ፡ ፡ ፡
፡ ፡ ፡ ፡ ፡
፡ ፡ ፡ ፡ ፡
✞✞✞ #አስተርእዮ_ማርያም ✞✞✞
፡ ፡ ፡ ፡ ፡ ፡ ፡ ፡ ፡ ፡ ፡

ወር በገባ በ21ኛው ቀን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን የምናስብት ቀን ነው፡፡ ለመሆኑ ምክንያቱ ምንድር ነው?
:
ምክንያቱ የእመቤታችንን በዓለ እረፍት የምናስብት በመሆኑ ነው፡፡ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ሞትና ትንሣኤ በነገረ ማርያም አበው እንደሚያስረዱት ዕረፍቷ በጥር 21
እሑድ ነው ።
:
#ጥር_21 አስተርእዮ ማርያም ይባላል፡፡ አስተርእዮ ማለት መታየት፣ መገለጥ ማለት ነው። ቃሉ አስተርአየ ታየ፡ ተገለጠ
ከሚለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ነው። ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስክርስቶስ በገባው ቃል ኪዳን መሠረት በሥጋ
የተገለጠበት(የታየበት) ፣አንድነት ሦስትነቱም የተገለጠበት ወቅት
በመሆኑ ከልደት በዓል እስከ ጥር መጨረሻ በሙሉ ዘመነ አስተርእዮ በመባል ይታወቃል። የእመቤታችን በዓለ ዕረፍት በዘመነ አስተርእዮ ውስጥ ስለሚከበር “አስተርእዮ ማርያም” ተብሏል።

የኃጥአንን ለቅሶና ሐዘን አይተሽ ስለእነርሱ ድኅነት(መዳን) ዕረፍትሽን በሀሴት የተቀበልሽ እመቤታችን ሆይ ሐዋርያት በሱባዔ ትንሣዔሽን ለማየት በቅተዋልና እኛም በዓለ ዕረፍትሽን
አክብረን ልጅሽ በሰጠሽ ቃል ኪዳን በቀኙ እንቆም ዘንድ ለምኝልን🙏አሜን🙏
Audio
🌾#እናቴ_እመቤቴ🌾
https://www.tg-me.com/EOTC2921

እናቴ እመቤቴ የማትጠፊው ከአፌ /፪/
በረከቴ አንቺ ነሽ የመስቀል ስር ትርፌ /፪/
አምላኬ ሸልሞኝ ለዘለአለም ያዝኩሽ
ጌታን የማይብሽ ብሌኔ አደረኩሽ

በልቤ ላይ ይፍሰስ የፍቅርሽ ጸዳሉ
የሚጣፍጥ ስምሽ መድኃኒት ለሁሉ
ተወዳጁን ልጅሽ ጸጋውን ያብዛልኝ
እድሜ እስኪፈጸም ለክብርሽ እንድቀኝ
#አዝ
ነፍሴ እንዳትጎዳ እንዳትቀር ባክና
ብርታት ሆኖልኛል የስምሽ ምስጋና
እኖራለው ገና ንኢ ንኢ ስልሽ
ክብሬ ነሽ ጌጤ ነሽ ከአፍ የማልነጥልሽ
#አዝ
ሲነጋም ጠራሁሽ ሲመሽም ጠራሁሽ
ስዕልሽ ፊት ቆሜ ሰአሊ ለነ እያልኩሽ
አሜን የምልብሽ መነጋገሪያዬ
የአማኑኤል እናት አንቺ ነሽ ቋንቋዬ
#አዝ
መች በስጋ ጥበብ ሰው ላንቺ ይቀኛል
ከአምላክ ካልተላከ ከፊትሽ ይቆማል
አንቺን ማመስገኔ አንቺን ማወደሴ
በልቡ ያሰበሽ ፈቅዶ ነው ሥላሴ
#አዝ
ብዙ ተቀብዬ ጥቂት አልዘምርም
ለእናትነት ፍቅርሽ ከቶ ዝም አልልም
እኔን በእደ ፍቁርሽ የምትባርኪ
ኦ ምልይተ ጸጋ ድንግል ሰላም እለኪ
#አዝ
🎤ሊቀ መዘምራን ቴዎድሮስ ዮሴፍ
††† #እንኳን_ለአባታችን_ለቅዱስ_አቡነ_ተክለ_ሃይማኖት_ዓመታዊ_በዓል_በሰላም_አደረሳችሁ_አደረሰን። †††
††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
አሜን! †††
††† ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ሐዋርያዊ †††
††† ልደት †††
††† መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራልና ተክለ ሃይማኖትን
የወለዱት ደጋጉ: ጸጋ ዘአብ ካህኑና እግዚእ ኃረያ ናቸው::
እርሱ በክህነቱ: እርሷ በደግነቷ: በምጽዋቷ ጸንተው ቢኖሩ
እግዚአብሔር ጣፋጭ ፍሬን ሰጥቷቸዋል::
በዳሞቱ ገዢ በሞተለሚ አደጋ ቢደርስባቸው ቅዱስ
ሚካኤል: ጸጋ ዘአብን ከሞት: እግዚእ ኃረያን ከትድምርተ
አረሚ (ከአረማዊ ጋብቻ) አድኗቸዋል:: በኋላም የቅዱሱን
መወለድ አብስሯቸዋል::
ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የተጸነሱት መጋቢት 24 ቀን
በ1206 ዓ/ም ሲሆን የተወለዱት ደግሞ ታኅሣሥ 24 ቀን
በ1207 ዓ/ም ነው:: በተወለዱበት ቀንም ብዙ ተአምራት
ተገልጸዋል:: ቤታቸውም በበረከት ሞልቷል::
††† ዕድገት †††
የጻድቁ የመጀመሪያ ስማቸው "ፍሥሃ ጽዮን" ይሰኛል::
ይሕንን ስም ይዘው: አባታቸው ጸጋ ዘአብን ተከትለው
አድገዋል:: በተለይ ቅዱሳት መጻሕፍትን (ብሉያት:
ሐዲሳትን) ተምረዋል:: በሥጋዊው ጐዳናም ብርቱ አዳኝ
እንደ ነበሩ ይነገራል:: ዲቁናም ከወቅቱ ጳጳስ አባ ጌርሎስ
ተቀብለዋል::
††† መጠራት †††
አንድ ቀን ፍሥሃ ጽዮን ለአደን ወጥቶ ሲያነጣጥር ድንገት
ከሰማይ አስደንጋጭ ድምጽ ተሰማ:: የክብር ባለቤት
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አእላፍ መላእክት እያመሰገኑት
በሚካኤል ክንፍ ተቀምጦ ወረደ::
የወጣቱን አዳኝ ፍርሃቱን አርቆ ጌታችን ተናገረ:: "ከዛሬ
ጀምሮ ስምህ ተክለ ሃይማኖት (ተክለ ሥላሴ) ይሁን::
ከዚህ በኋላ አራዊትን ሳይሆን ነፍሳትን ታድናለህ:: ዘወትር
ካንተ ጋር ነኝ" ብሎ በግርማ ዐረገ:: ቅዱስ ተክለ
ሃይማኖት ከዚህ ጊዜ በኋላ ሰዓትን አላጠፉም::
ንብረታቸውን ለነዳያን በትነው በትር ብቻ ይዘው ቤታቸው
እንደ ተከፈተ ወደ ምናኔ ወጡ::
††† አገልግሎት †††
ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከጳጳሱ ቅስና ተቀብለው የወንጌል
አገልግሎትን ጀመሩ:: በመጀመሪያ ስብከታቸው እዚያው
ሽዋ (ጽላልሽ) አካባቢ ብቻ በ10ሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን
አሳምነው አጠመቁ:: ያን ጊዜ ኢትዮጵያ 2 መልክ ነበራት::
1ኛ. ዮዲት (ጉዲት) በፈጠረችው ጣጣና በእስላሞች
ተጽዕኖ ወደ ደቡብ አካባቢ ያለው ነዋሪ አንድም ሃይማኖቱን
ክዷል: ወይም በባዕድ አምልኮ ተጠምዷል::
2ኛው ደግሞ በዛግዌ ነገሥታት ጥረት ክርስትናና ምናኔ
ተነቃቅቶ ነበር::
ግማሹ ሃገር በጨለመበት ወቅት የደረሱት ሐዲስ ሐዋርያ
አባ ተክለ ሃይማኖት በወጣት ጉልበታቸውና በኃይለ
መንፈስ ቅዱስ ብዙ ቦታዎችን አደረሱ:: ሕዝቡን:
መሣፍንቱን ወደ ሃይማኖት መልሰው: ማርያኖችን
(ጠንቋዮችን) አጥፍተዋል::
††† ገዳማዊ ሕይወት †††
††† ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት በወንጌል ብርሃን ኢትዮጵያን
ከማብራታቸው ባለፈ ገዳማዊ ሕይወትንም አስፋፍተዋል::
እርሳቸው ከሁሉ የተሻሉ ሳሉም በ3 ገዳማት በረድዕነት
አገልግለዋል::
እነዚህም በአቡነ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም ለ12 ዓመታት:
በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ ገዳም ለ7 ዓመታት: በደብረ
ዳሞ ከአቡነ ዮሐኒ ጋር ለ7 ዓመታት: በአጠቃላይ ለ26
ዓመታት አገልግለዋል::
በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ከመነኮሱ በኋላም ወደ ምድረ ሽዋ
(ዞረሬ) ተመልሰው በአንዲት በዓት ውስጥ ለ22 ዓመታት
ቆመው ጸልየዋል:: በተሰበረ እግራቸውም 6 ጦሮችን
በግራና በቀኝ ተክለው ለ7 ዓመታት ጸልየዋል::
††† ስድስት ክንፍ †††
ኢትዮጵያዊው ጻድቅና ሐዋርያ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት
ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው ከቅዱሳት መካናት
ተባርከዋል:: ጻድቁ ምድረ እሥራኤል የገቡት በየመንገዱ
መንፈሳዊ ዘርን እየዘሩ: እያስተማሩና እያሳመኑ ነበር::
ከወቅቱ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤል ጋርም ተገናኝተው
ቡራኬን ተሰጣጥተዋል:: ዋናው ጉዳይ ግን ከዚህ በኋላ
ነው:: ጻድቁ እመቤታችንና ጌታችን ከጽንሰታቸው እስከ
ዕርገታቸው የረገጧቸውን ቦታዎች ሲመለከቱ በፍጹም
ተደሞ እንባቸው ይፈስ ነበር::
ምክንያቱም እግዚአብሔር ስላበቃቸው ተክለ ሃይማኖት
የሚያዩት ቦታውን አልነበረም:: በገሃድ:-
*በቤተ መቅደስ ብስራቱን
*በቤተ ልሔም ልደቱን
*በቤተ ዮሴፍ ግዝረቱን
*በፈለገ ዮርዳኖስ ጥምቀቱን
*በቤተ አልዓዛር ተአምራቱን ይመለከቱ ነበር::
የጉብኝታቸው የመጨረሻ ክፍል ወደ ሆነው ቀራንዮ
ደርሰው ጌታቸውን እንደ ተሰቀለ ሆኖ ቢመለከቱት
ከዓይናቸው ይፈስ የነበረው ቁጡ እንባ መልኩን ቀየረና
ዓይናቸው ጠፋ::
በዚያች ቅጽበት ስም አጠራሯ የከበረ እመቤታችን ድንግል
ማርያም ፈጥና ደርሳ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ወደ ሰማይ
አሳረገቻቸው::
††† በዚያም:-
*የብርሃን ዐይን ተቀብለው
*6 ክንፍ አብቅለው
*የወርቅ ካባ ላንቃ ለብሰው
*ማዕጠንተ ወርቁን ይዘው
*ከ24ቱ ካህናተ ሰማይም ተደምረው
*ሥላሴን በአንድነቱና ሦስትነቱ ተመልክተው
*"ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ ይደሉ" ብለው መንበረ
ጸባኦትን አጥነው ወደ መሬት ተመልሰዋል::
††† ተአምራት †††
የቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ተአምራት እንደ ሰማይ ከዋክብት
የበዛ ነው::
*ሙት አንስተዋል
*ድውያንን ፈውሰዋል
*አጋንንትን አሳደዋል
*እሳትን ጨብጠዋል
*በክንፍ በረዋል
*ደመናን ዙፋን አድርገዋል::
ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው ደብረ ሊባኖስን
መሥርተዋል:: በዚያም ሴትና ወንድ መነኮሳት እንደ
ሕጻናት አብረው ኑረዋል:: በዘመናቸው ሰይጣን
ታሥሯልና::
††† ዕረፍት †††
††† ጻድቅ: ሰማዕትና ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ብርሃን
ሆነው: መከራን በብዙ ተቀብለው: እልፍ አእላፍ ፍሬን
አፍርተው: በተወለዱ በ99 ዓመት: ከ8 ወር: ከ1 ቀናቸው
ነሐሴ 24 ቀን በ1306 ዓ/ም ዐርፈዋል:: ጌታ: ድንግል
ማርያምና ቅዱሳን ከሰማይ ወርደው ተቀብለዋቸዋል:: 10
ትውልድ የሚያስምር ቃል ኪዳንም ተቀብለዋል::
††† በዚህ ዕለት አባታችን ተክለ ሃይማኖት ለ22 ዓመታት
የቆሙበት ቀኝ እግራቸው መሠበሩንና በአንድ እግራቸው
ለ7 ዓመታት ቆመው መጸለያቸውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን
ታስባለች::
††† ጥር 24 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1አቡነ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት
2.ቅድስት ማርያ ግብጻዊት
3.ታላቁ አባ ቢፋ
4.አባ አብሳዲ ቀሲስ
5.ቅዱሳን ጻድቃነ ሐውዚን
††† ወርኀዊ በዓላት
1.አቡነ ዘዮሐንስ (ዘክብራን ገብርኤል-ጣና)
2.ቅድስት እናታችን ክርስቶስ ሠምራ
3.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ
4.ቅዱስ ሙሴ ጸሊም
5.ቅዱስ አጋቢጦስ
6.ሃያ አራቱ ካህናተ ሠማይ
††† "በድካም : አብዝቼ በመገረፍ : አብዝቼ በመታሠር :
አትርፌ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ:: በድካምና በጥረት :
ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት : በራብና በጥም : ብዙ
ጊዜም በመጦም : በብርድና በራቁትነት ነበርሁ . . .
የቀረውን ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ
የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው::" †††
(፪ቆሮ ፲፩፥፳፫)
††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
✞✞✞ #እንኳን_ለታላቁ_ሰማዕት_ቅዱስ_መርቆሬዎስ_ዓመታዊ_የተአምር_በዓል_በሰላም_አደረሳችሁ_አደረሰን።✞✞✞

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††
††† ቅዱስ መርቆሬዎስ ኃያል †††
††† ለክርስትና ሃይማኖት የሚከፈል ትልቁ ዋጋ ሰማዕትነት ነውና ቤተ ክርስቲያን ለምስክሮቿ ሰማዕታት ልዩ ክብር አላት:: ከኮከብ ኮከብ እንዲበልጥ ሁሉ ከሰማዕታትም ቅዱስ ጊዮርጊስን እና ቅዱስ መርቆሬዎስን የመሰሉት ደግሞ ክብራቸው በእጅጉ የላቀ ነው::
ቅዱስ መርቆሬዎስን ብዙ ጊዜ ሊቃውንት "ካልዕ (ሁለተኛው) ሊቀ ሰማዕታት" ሲሉ ይገልጹታል:: ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
በ2ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ ከሮም ግዛቶች በአንዱ (አስሌጥ) ከአባቱና ከሚስቱ ጋር የሚኖር "አሮስ" የሚሉት ሰው ይኖር ነበር:: ሚስቱ ደም ግባት የሠመረላት: እርሱም ደግነት ያለው ሰው ቢሆኑም የሚያመልኩት ግን ጣዖትን ነበር::
አንድ ቀን አሮስ ሚስቱን ከቤት ትቶ ለአደን ከአባቱ ጋር ወጣ:: እንደ ልማዳቸው ወጥመዱን አስተካክለው ተደበቁ:: የወጥመዱ ደወል ሲያቃጭል: "እንስሳ ተያዘልን" ብለው ሲሯሯጡ ዐይናቸው ያየው ነገር በድንጋጤ እንዲፈዙ አደረጋቸው:: 2 ገጻተ ከለባት በወጥመዱ ውስጥ ተይዘው ነበር::
እነዚህ ፍጡራን ሰዎች ናቸው:: ግን ባልታወቀ የተፈጥሮ አጋጣሚ እንደዚህ እንደ ሆኑ ይታመናል:: ግን እጅግ ግዙፍ: ከአንገታቸው በላይ እንደ ውሻ: ወገባቸው እንደ ሰው: ጉልበታቸው እንደ አንበሳ ሲሆን ታችኛው እግራቸው የጋለ የናስ ብረት ነው የሚመስል::
እነዚህን ፍጡራን ሰማያዊ ካልሆነ ምድራዊ ፍጡር አይችላቸውም:: አንበሳና ነብርን እንኩዋ እንደ ጨርቅ በጣጥሰው ይጥሏቸው እንደ ነበር ይነገራል:: ዐይናቸው እንደ እሳት ይነድ ስለ ነበር ማንም ትክ ብሎ ሊያያቸው አይችልም:: ምሥጢራቸውን ግን የሚያውቀው የፈጠራቸው አምላክ ነው::
ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና:- አሮስና አባቱ ባዩአቸው ጊዜ ደንግጠው ወደቁ:: ገጻተ ከለባቱ የብረት ወጥመዱን እንደ ክር በጣጥሰው የአሮስን አባት በቅጽበት በሉት:: አሮስን ሊበሉት ሲሉ ግን ድንገት ቅዱስ መልአክ ወርዶ በእሳት ሰይፍ አጠራቸው::
"ከእርሱ የሚወጣ ቅዱስ ፍሬ አለና እንዳትነኩት" አላቸው:: ወዲያውም መልአኩ ያንን ኃይለኝነታቸውን አጠፋው:: በዚህ ጊዜ 2ቱም ወደ አሮስ ሒደው ሰገዱለት:: አሮስም ወደ ቤቱ ወስዶም ደበቃቸውና የሆነውን ሁሉ ለሚስቱ ነገራት::
ጥቂት ቆይታም ጸንሳ ወለደች:: ልጃቸውን ፒሉፓዴር (ፒሉፓተር) ሲሉ ስም አወጡለት:: ትርጉሙም "መፍቀሬ አብ - የአብ ወዳጅ" ማለት ነው:: ከዚያም አሮስ ሚስቱን : ልጁንና 2ቱን ገጻተ ከለባት ይዞ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሒዶ ተጠመቀ::
አበው ካህናት እሱን "ኖኅ" : ሚስቱን "ታቦት" : ልጁን ደግሞ "መርቆሬዎስ" ሲሉ ሰየሟቸው:: መርቆሬዎስ ማለትም "ገብረ ኢየሱስ ክርስቶስ - የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ" እንደ ማለት ነው::
ከዚያም ደስ እያላቸው: ክርስቶስን እያመለኩ: ነዳያንን እያሰቡ: ልጃቸውን መርቆሬዎስን አሳደጉ:: ነገር ግን የገጻተ ከለባት ወሬ በመሰማቱ ንጉሡ "ካላመጣሃቸው" አለው:: ኖኅ ጸልዮ ወደ ኃይለኝነታቸው መልሷቸው ስለነበር ፊታቸው ገና ሲገለጥ ብዙ አሕዛብ በድንጋጤ ሞቱ::
ንጉሡም ስለ ፈራ ኖኅን የጦር መኮንን አደረገው:: በጦርነት ጊዜም ገጻተ ከለባቱ ኃይላቸው ስለሚመለስ ተሸንፎ አያውቅም ነበር:: አንድ ጊዜ ግን 2ቱን ገጻተ ከለባት ንጉሡ አታሎ ወሰዳቸው:: ሃይማኖታቸውን ሊያስክዳቸው ሲል "እንቢ" በማለታቸው አንዱ ሲገደል ሌላኛው አምልጦ ጠፋ::
በዚያ ወራትም ኖኅ ለጦርነት ወጥቶ ተማረከ:: ንጉሡ ደግሞ ታቦትን "ላግባሽ" ስላላት የ5 ዓመት ልጇን ቅዱስ መርቆሬዎስን ይዛ ተሰደደች:: በስደት ጥቂት እንደ ቆየች ግን ባሏን ኖኅን አየችው::
እርሷ ብታውቀውም እርሱ ዘንግቷት ነበር:: በሁዋላ ግን በሕጻኑ መርቆሬዎስ አማካኝነት ማስታወስ በመቻሉ ደስ አላቸው:: በዚያው በሮም ዙሪያ ሳሉም አንዱ ገጸ ከልብ መጥቶ አገኛቸው:: በዚህም ምክንያት በስደት ሃገርም መኮንን ሆኖ ተሾመ::
በዚያም ቤተ ክርስቲያንን አንጾ: ቤቱን ቤተ ነዳያን አድርጐ ኖኅ ለዓመታት ኖረ:: ቅዱስ መርቆሬዎስ ወጣት ሲሆንም ወላጆቹ ታቦትና ኖኅ ዐረፉ:: እርሱ ከባልንጀራው ገጸ ከልብ ጋር ሆኖ በጾምና ጸሎት ሲኖር ስለ አባቱ ፈንታ የጦር መሪ አደረጉት::
በጦርነትም እጅግ ኃያል: በሰው ዘንድም ፍጹም ተወዳጅ: የጾምና የጸሎት ሰው ሆነ:: ያን ጊዜ ግን ዳክዮስ ንጉሡ ክርስቶስን በመካዱ ምዕመናን ላይ ሞት ታወጀ:: በጊዜው ደግሞ የበርበር ሰዎች በሮም መንግስት ላይ ጦርነትን በማንሳታቸው ዳኬዎስና ቅዱስ መርቆሬዎስ ለጦርነት ወጡ::
ነገር ግን በርበሮች እንደ አሸዋ ፈሰው ብዛታቸውን ሲያይ ንጉሡ ደነገጠ:: ለማግስቱ ቀጠሮ ተይዞ ቅዱስ መርቆሬዎስ ሲጸልይ ቅዱስ ገብርኤል ወርዶ ሰይፍ ሰጠው::
በማግስቱም "ምን ይሻላል?" ሲባል ቅዱስ መርቆሬዎስ "እኔ የክርስቶስ ባሪያ ነኝና ብቻየን እቋቋማቸዋለሁ" ቢል ሳቁበት::
እርሱ ግን በጥቁር ፈረሱ (አብሮት ያደገ ነው) ተጭኖ በርበሮችን "ጠብ ይቅርባችሁ: በሰላም ሒዱ" ቢላቸው ተሳለቁበት:: ያን ጊዜም ጸሎት አድርሶ የመልአኩን ሰይፍ ሲመዘው ብዙዎቹ ወደቁ:: ከበርበሮችም ለወሬ ነጋሪነት እንኩዋ የተረፈ አልነበረም::
ነገሩ በሮም ሲሰማ ታላቅ ሐሴት ሆነ:: ዳሩ ግን ከሃዲው ዳኬዎስ "ድሉ የጣዖቶቼ የነ አዽሎን ነው" በማለቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ ሲያዝን አደረ::
በ3ኛው ቀንም "ለጣዖት ሠዋ" የሚል ትዕዛዝ ከንጉሡ ዘንድ መጣ:: ቅዱሱ ግን ወደ አደባባይ ሔደ:: የክብር ልብሱንና መታጠቂያውን አውልቆ በንጉሡ ፊት ወረወረው::
"ሃብትከ ወክብርከ ይኩንከ ለኃጉል:: ሊተሰ ክብርየ ክርስቶስ ውዕቱ:: (ለእኔስ ክብሬ ክርስቶስ ነውና ንብረትህ ለጥፋት ይሁንህ)" ሲልም ንጉሡን በአደባባይ ዘለፈው:: ዳኬዎስም በቁጣ እሳት አስነድዶ: የብረት አልጋውንም አግሎ ቅዱስ መርቆሬዎስን በዚያ ላይ አስተኛው::
ያም አልበቃ:: ወታደሮች እየተፈራረቁ ሲደበድቡት ደሙ ፈሶ እሳቱን አጠፋው:: ለዚያ ነው ሊቃውንት:-
"አመ አንደዱ ላእሌከ ውሉደ መርገም::
እምቅሡፍ አባልከ እንተ ውኅዘ ደም::
አርአያ ዝናም ብዙኅ አጥፍኦ ለፍህም::" ያሉት::
ከዚያም ወስደው ወኅኒ ቤት ውስጥ ጣሉት:: ክርስቶስን ያስክደው ዘንድ በረሃብ: በግርፋት: በእሳት: በስለትም አሰቃየው:: በመጨረሻ ግን አሰቃይተው እንዲገድሉት ወደ እስያ ሰደደው:: በስፍራውም ብዙ አሰቃይተው ኅዳር 25 ቀን አንገቱን ሰይፈውታል::
እርሱ ካረፈ በሁዋላም የተባረከ ፈረሱ ለዓመታት ወንጌልን ሰብኩዋል:: አረማውያንንም ከአፉ በወጣ እሳት አጥፍቷል:: ተአምረኛውና ኃያሉ ሰማዕት ቅዱስ መርቆሬዎስ በ200 ዓ/ም እንደ ተወለደ: በ220 ዓ/ም መከራ መቀበል እንደ ጀመረና በ225 ዓ/ም ሰማዕት እንደሆነ ይታመናል::
ሰማዕቱ በዚህች ዕለት : በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ክርስቲያኖችን ያሰቃይና ይገድል የነበረውን ዑልያኖስን ያጠፋበት መታሠቢያ ይከበራል::
የቅዱሱ ክብር ታላቅ ነው!
††† አምላከ ቅዱስ መርቆሬዎስ በከበረ ቃል ኪዳኑ ይጠብቀን:: ከርስቱም አያናውጠን:: ከበረከቱም ይክፈለን::
ቸሩ እግዚአብሔር እድሜ ለንስሃ ዘመን ለፍሥሃ አይንሳን::
††† ጥር 25 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕተ ሮሜ
2.ቅዱሳን ባስልዮስና ጎርጎርዮስ
3.ብፁዕ አባ ዼጥሮስ ጽሙድ (ለምጽዋት ራሱን የሸጠ አባት)
4.ቅዱስ ሰብስትያኖስ ሰማዕት
5.ቅዱስ አስኪላ
ሰማዕት
††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
2.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
3.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
4.አቡነ አቢብ
5.አባ አቡፋና
††† "የሚበልጠውን ትንሳኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ:: ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ:: በድንጋይ ተወግረው ሞቱ:: ተፈተኑ: በመጋዝ ተሰነጠቁ: በሰይፍ ተገድለው ሞቱ:: ሁሉን እያጡ: መከራን እየተቀበሉ: እየተጨነቁ: የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ:: ዓለም አልተገባቸውምና . . . " †††
(ዕብ. 11:35)
††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
2025/10/24 17:26:20
Back to Top
HTML Embed Code: