Telegram Web Link
🌾✞ "ሰዎች የሚያብዱትና አንደነሱ ያላበደ ሰዉ ሲያዬ እንደኛ ስላልሆንህ አብደሀል የሚሉበት ዘመን ይመጣል።"ቅዱስ እንጦንስ

🌾✞ "መካሪ አያስፈልገኝም የማለትን ያህል ታላቅ ትዕቢት የለ።" ቅዱስ ባስልዮስ

🌾✞ "የክርስቲያኖች መሳሪያ በእጃቸው ሰይፍ መታጠቅ ሳይሆን እጃቸውን ወደላይ ለፀሎት መዘርጋት ነዉ።" ቅዱስ አትናቴዎስ ዘእስክንድርያ
#መጥምቀ_መለኮት_ቅዱስ_ዮሐንስ

📖ሰኔ ፴
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
እንኳን ለነቢዩ ለሰማዕቱ ለካህኑ ለሐዋርያው ለመጥምቀ መለኮት ለተወለደበት (ለልደት) በዓልና በሕንደኬ ካሉ ደሴቶቸ በአንዲቱ ውስጥ ለሚኖር ለገድለኛ ለሆነ ለአባ ጌራን ለዕረፍት መታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከቅዱሳን ማርያና፣ ከማርታ፣ ከመነኰስ ገብረ ክርስቶስ ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን

✝️✝️✝️
የዕለቱ አንገርጋሪ ግእዝ ዜማ፦ ሃሌ ሉያ "ሰምዑ አዝማዲሃ ወሰብአ ቤታ። እስመ አዕበየ እግዚአብሔር ሣህሎ ላዕሌሃ። ወተፈሥሁ ፍሥሃ ፈድፋደ። ወፈቀዱ ይስምይዎ በስመ አቡሁ ዘካርያስ። ወትቤ እሙ ዮሐንስሃ ይሰመይ"። ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በድጓው ላይ።

✝️✝️✝️
ነቢይ፣ ሰማዕትና ሐዋርያ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ልደት፦ ይህም በእናቱ ማኅፀን ውስጥ ሳለ ለእግዚአብሔር ልጅ የሰገደው ነው። ይህም በመድኅን ክርስቶስ ራስ ላይ እጁን ጭኖ በውኃ ያጠምቀው ዘንድ የተገባው ነው።

በቅዱስ ወንጌል እንደ ተነገረ ወንድ ልጅን ትወልድ ዘንድ የኤልሳቤጥ የፅንሷ ወራት በተፈጸመ ጊዜ ወንድ ልጅን ወለደች። ዘመዶቿና ጎረቤቶቿ እግዚአብሔር ቸርነቱን እንዳበዛላት በሰሙ ጊዜ ስለርስዋ ደስ አላቸው። በስምንተኛውም ቀን ሊገዝሩት መጡ በአባቱ ስም ዘካርያስ ብለው ጠሩት። እናቱ ግን "አይሆንም ዮሐንስ ይባል" አለች። "ከዘመዶችሽ ስሙ እንዲህ የሚባል የለም" አሏት።

አባቱንም ጠቅሰው "ማን ሊባል ትወዳለህ" አሉት። እርሱም ብራና ለምኖ ስሙ "ዮሐንስ ይባል" ብሎ ጻፈ። ሁሉም አደነቁ። ያን ጊዜም አንደበቱ ከድዳነት ተፈትቶለት ተናገረ እግዚአብሔርንም ፈጽሞ አመሰገነው። ስለ ልጁና ስለ መድኃኒታችን መምጣት ልጁ ዮሐንስም የልዑል ነቢይ እንደሚባልና በእግዚአብሔርም ፊት እንደሚሔድ ትንቢት ተናገረ።

ሰብአ ሰገልም መጥተው ከሔዱ በኋላ ሄሮድስ ሕፃናትን በገደላቸው ጊዜ ስለ ሕፃናትን በገደላቸው ጊዜ ስለ ሕፃኑ ዮሐንስ ለሄሮድስ ነገሩት እንዲገድሉትም ጭፍሮችን ላከ ጭፍሮችም ወደ አባቱ ዘካርያስ መጡ ሕፃኑንም ከእርሱ ፈለጉት አባቱም አንሥቶ በትከሻዎቹ ተሸክሞ ወደ ቤተ መቅደስ ከእርሱ ጋራ እንዲሔዱና ሕፃኑን ከዚያ እንዲወስዱት ወታደሮችን ለመናቸው።

ከዚህም በኋላ ሕፃኑን በመሠዊያው ጠርዝ ላይ አኖረውና "ከዚህ ራሳችሁ ተቀብላችሁ ውሰዱት" አላቸው ወዲያውኑ የእግዚአብሔር መልአክ ነጥቆ ወደ በረሀ ወሰደው። ጭፍሮችም ባላገኙት ጊዜ አባቱ ዘካርያስን ገደሉት። ሕፃኑ ግን አድጎ ለእስራኤል እስከተገለጠበት ጊዜ ድረስ በበረሀ ውስጥ ኖረ።

"የእግዚአብሔርን መንገድ ጥረጉ ጥርጊያውንም አስተካክሉ እያለ በምድረ በዳ የሚጮህ የዐዋጅ ነጋሪ ድምጽ እነሆ" ብሎ ኢያሳያስ የተናገረለት ይህ ነው። ሚልክያስም ስለርሱ እንዲህ አለ "በፊትህ ጎዳናዬን አስተካክሎ የሚጠርግ መልአክተኛዬን እኔ እሰዳለሁ"።

ራሱ መድኃኒታችንም ስርሱ ሲናገር "ሴቶች ከወለዱአቸው መጥምቁ ዮሐንስን የሚበልጠው የለም" ብሏል። ይህ የእግዚአብሔር ልጅ በአጠመቀውና የማትዳሠሥ ራሱን በዳሠሠው ጊዜ "የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት" የሚል የአብን ቃል ሰምቷልና።

ዳግመኛም ክብር ይግባውና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ራስ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወርዶ ሲቀመጥ አየ። እኛንም መድኃኒታችን እንዲምረንና ይቅር እንዲለን በአማላጅነቱ እያመን መታሰቢያውን እናድርግ የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስ በረከቱም እኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✝️✝️✝️
ገድለኛው የሆነ አባ ጌራን፦ ይህም ቅዱስ በሕንደኬ ካሉ ደሴቶች በአንዲቱ ውስጥ የሚኖር ነው። እርሱም እግዚአብሔርን የሚፈራና የሚወደው ጾምና ጸሎትንም የሚወድ ነበር። ወደ እግዚአብሔርም የሚለምነውን ሁሉ ይሰማው ነበር። በጸሎቱም ከዚያች አገር ንዳድ፣ አባር፣ ድርቅ፣ በጠላት መማረክ፣ የደም መፍሰስና የመርከቦች መሥጠም ተወገደ የፈለገውንም ሁሉ በጸሎቱ ያገኝ ነበር።

ሰይጣንም ስለዚህ ስለ ተሰጠው ጸጋ ቀናበት በዕንቊ ያጌጠ ነገሥታትን ልብስ በለበሰች መልከ መልካም ሴት አምሳልም ታየው እርሷም ብቻዋን ትንጎራደድ ነበር። በአያትም ጊዜ ወደርሷ ሒዶ ሥራዋን ጠየቃት እርሷም እንዲህ አለችው "የንጉሥ ሰርስባን ልጅ ነኝ እኅቴ ከአባቷ ባሮች ጋራ በአመነዘረች ጊዜ ሁላችንንም ሊገድለን ፈለገ። ስለዚህ ፈርቼ በሌሊት ወጣሁ ወደዚች በረሀም መጣሁ ቅዱሱን ሰው አንተን በማግኘቴም እድለኛ ነኝ" አለችው። እርሱም "ወደ እኔ የሚመጡ ሰዎች እንዳያዩሽ ወደዚያች የዐለት ዋሻ ሒጂ" አላት።

በሌሊትም ከአራዊት የተነሣ እንደፈራ ሰው እየጮኸች መጥታ "የዱር አራዊት እንዳይበሉኝ ክፈትልኝ" አለችው። እርሱም ከፈተላትና ገባች በጎኑም ተኝታ ደረቱን አቀፈችው ልቡን ወደ ፍቅርዋ እስከ አዘነበለችው ድረስ ነገሯን አለሰለሰችለት። ያን ጊዜ ያደረበት የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ተለየው ከእርሷም ጋራ ተኝቶ ኃጢአት እደሚሠራ ሆነ። ከስህተት ስካርም በነቃ ጊዜ በጠላት ሰይጣን ተንኰል ተሸንፎ እንደ በደለ አወቀ።

ከዚህም በኋላ ከሰይጣን ተንኰል የተነሣ ያገኘውን ሁሉ በሥጋውም ኃጢአት እንደሠራ ጻፈ። ከዚህ በኋላም ከደሴቱ ተራራ ድንጊያ አንሥቶ እስከሚሞት ድረስ ራሱንና ደረቱን እየደበደበ ኖረ። ነፍሱም ድና ወደ ዘላለም ሕይወት በጌታ ቸርነት ገባች።

ከዚህም በኋላ እንደ ልማዳቸው ከእርሱ ቡራኬ ሊቀበሉ ሰዎች መጥተው አላገኙትም በፈለጉትም ጊዜ ተኝቶ አገኙትና ያንቀላፋ መስሏቸው ጀምሩ ግን ሞቶ አገኙት አለቀሱለት ተሳለሙት ገንዘውም ቀበሩት።

ከዚህም በኋላ ሞቱ በጠላት ሰይጣን ተንኮል ምክንያት ስለመሆኑ የጻፈውን አገኙ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ጻድቃንና ሰማዕታት ጸሎት መንፈሳውያን በሆኑ በቅዱሳን መላእክትም አማላጅነት ይልቁንም አምላክን በወለደች በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጸሎቷና በአማላጅነቷ ከሰይጣን ወጥመድ ያድነን።

የተባረ የሰኔ ወር በእግዚአብሔር ቸርነት ተፈጸመ አሜን። ምንጭ፦ የሰኔ 30ስንክሳር።

✝️✝️✝️
"ሰላም ለዮሐንስ ግፋዕ ወቅቱል ንጹሕ ወቅዱስ ወስቡሕ ላእክ ወነቢይ ወሰማዕት ድንግል ካህን ጸያሒ ወሰባኪ መጥምቀ እግዚኡ"። ትርጉም፦ ጌታውን ያጠመቀና ሰባኪ፤ መንገድ ጠራጊ፣ ካህን ድንግል ሰማዕት፣ ነቢይና አገልጋይ፤ ምስጉን ቅዱስና ንጹሕ፤ ተገፍቶ የተገደለ ለኾነ ለቅዱስ ዮሐንስ ሰላምታ ይገባል። ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በተአምኆ ቅዱሳን ላይ።

✝️✝️✝️
የዕለቱ የማኅሌት ምስባክ፦ "አሜሃ ይቤሉ አሕዛብ። አዕበየ ገቢረ ሎሙ እግዚአብሔር። ወኮነ ፍሡሓነ። መዝ 125፥2፥3። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 1፥76-ፍ.ም።

✝️✝️✝️
የዕለቱ የቅዳሴ ምስባክ፦ "ወተወከልኩከ እንዘ ሀሎኩ ውስተ አጥባተ እምየ። ላዕሌከ ተገደፍኩ እማኅፀን። እምከርሠ እምየ አንተ አምላኪየ"። መዝ 21፥9-10። የሚነበቡት መልዕክታት ሮሜ 7፥14-ፍ.ም፣ 1ኛ ዮሐ 3፥7-10 እና የሐዋ ሥራ 19፥1-21። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 1፥57-80። የሚቀደሰው ቅዳሴ የወልደ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ቅዳሴ ነው። መልካም የመጥምቀ መለኮት የልደት በዓልና የጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።
╭══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╮
https://www.tg-me.com/EOTC2921
╰══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╯‌‌
#ቅዱስ_ጳውሎስና_ቅዱስ_ጴጥሮስ
📖ሐምሌ ፭

ሐምሌ አምስት በዚች ቀን የክቡራንና የዐበይት አባቶቻችን ሐዋርያት #የቅዱስ_ጴጥሮስ እና #የቅዱስ_ጳውሎስ የሰማዕትነታቸው መታሰቢያ ነው።

በዚህች ዕለት ስለክርስቶስ የተገፋ፣ ስለክርስቶስ የተወገረ፣ ስለክርስቶስ የተሰደደ፣ ስለክርስቶስ የታሰረ፣ ስለክርስቶስ ከአለም ሃሳብና መሻቷ የተለየ፣ ስለክርስቶስ ራሱን የለየ፣ ስለክርስቶስ ምእመናን ያነፀ፣ ስለክርስቶስ መልካምን መልእክት የፃፈ #ቅዱስ_ጳውሎስ ሰማዕት ሆነ። ነገር ግን በስጋ ሞተ በመንፈስ ግን ህያው ነው፤ የፅድቅን አክሊል ተቀበለ ከክርስቶስ ጋር መኖርን እንደናፈቀ አገኛት፤ ከእልፍ አእላፋት ቅዱሳን ማህበር ተቀላቀለ ከመላእክት ምስጋና ተጋራ በስጋ ህይወቱ ከእውቀት ከፍሎ እንዳወቀ በሰማያዊው ኑሮ በእጅጉ የበለጠ እውቀትን ተቸረ። በማይጠወልግ፣ በማይደርቅ፣ በማይዝል፣ ፍሬያማም በሆነ ክርስቶስ ግንድነት ላይ ቅርንጫፍ ሆኖ ተሰርቷልና በስጋ ኑሮው በድካም ዝለት ጠውልጎ እንደነበረ የሚጠወልግ አይደለም፤ በማስተማር ብዛት ጉሮሮው እንደደረቀ አሁን የሚደርቅ አይደለም፤ በብርቱ ክንድ ላይ በምቾት አለና የሚዝልም አይደለም፤ ክፉወች ሮማውያን ግን ቅዱስ ጳውሎስን ገደልን አሉ። አይሁድም እፎይ ጳውሎስ ሞተ አሉ። ቅዱስ ጳውሎስ ግን የናፈቀው ክርስቶስ ጋር ሊኖር ወደ ዘለዓለማዊው ህይወት ሄደ፤ ራሱን ህያው መስዋእት አድርጎ በክርስቶስ ፊት እንደ ንፁህ መገበሪያ ስንዴ ተፈጨ፤ አይሁድ በጳውሎስ መሞት ድል ያደረጉ ይመስላቸዋል ነገር ግን የፅድቅን አክሊል በራሱ ላይ አድርጎ ከፀሃይ ይልቅ እያበራ በሰማይ ሆኖ ቅዱስ ጳውሎስ አለ በማይደርቅ ግንድ ላይ የተተከለ ቅዱስ ጳውሎስ ፍሬ በሙላት የያዘ የለመለመ ቅርንጫፍ ሆኖ አለ በቅድስና በተዋበ የክርስቶስ አካል መካከል መልካም ብልት ሆኖ አለ

አይሁድ ግን ቅዱስ ጳውሎስን ገደልን አሉ በሰይፍ አንገቱን ቆርጠው በስጋ ገድለውታልና አላዋቂ አይሁድ ከሮማውያን ጋር አብረው ጳውሎስን ገደልን አሉ፤ እርሱ ግን ከአፈር በተበጀ ስጋ ሞት ቢሞት በእግዚአብሔር እስትንፋስ ስለተሰጠች ነፍስ ህያው ነው

ዳግመኛም በብርሃኑ ብርሃንን በጨውነቱ መጣፈጥን በመድሃኒቱ መፈወስን የሰጣቸው ተወዳጅ የሐዋርያት አለቃ #ቅዱስ_ጴጥሮስን አይሁድ ቁልቁል ሊሰቅሉት ወደ ሮም አደባባይ ከወዳጁ ከጳውሎስ ጋር አጣደፉት፤ ጴጥሮስ ግን በትምህርቱ ብርሃን ጨለማቸውን ገፍፎላቸው፣ በእምነት መድሃኒት ሙታናቸውን አንስቶላቸው፣ ጎባጣቸውን አንቅቶላቸው አንካሳወቻቸውን አፅንቶላቸው ክፉ ጠላት ዲያብሎስንም አባርሮላቸው ነበር አይሁድ ግን ከወዳጃቸው ጴጥሮስ ይልቅ ጠላቶቻቸውን ሮማውያን ጋር አብረው አንድም ከወዳጃቸው ከክርስቶስ ይልቅ ከጠላታቸው ዲያቢሎስ ጋር አብረው ቅዱስ ጴጥሮስን እንደጌታውና መምህሩ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሊሰቅሉት ወደሮም አደባባይ አፋጠኑት። የማይጠፋውን ፋና ሊያጠፉ የማይደበዝዘውን ብርሃን ሊያደበዝዙ የማይሞት የክርስቶስን ልጅ ሊገድሉ በገሃነም ደጆች የማትናወጥ ክርስትናን ሊያናውጡ አይሁዳውያን የክርስቲያኖች ዋና ያሉትን ቅዱስ ጴጥሮስን በብዙ ስቃይ አንገላቱት፤ ተወዳጅ ሐዋርያ ቅዱስ ጴጥሮስ ግን የስጋ ሞቱ ዕረፍቱ እንደሆነ እጅግ አስቀድሞ አውቆ ነበር የአይሁድ ማሰቃየት ወደ ክርስቶስ የፀጋ ግምጃ ቤት እንደሚያደርሰው አውቆ ነበር የአይሁድ መጨከን ወደ ክርስቶስ አማናዊ ፍቅር እንደሚመራው አውቆ ነበር፤ “ገደልንህ” አሉት። እርሱ ግን “ወደ ዘለዓለማዊ ህይወት ክርስቶስ ገፋችሁኝ” አላቸው። “ክርስቲያኖችን ጨረስን” አሉት እርሱ ግን “የእኛ ሞት የክርስቲያኖች ዘር ነው” አላቸው፤ “አንተ ርጉም” አሉት እርሱ ግን “የክርስቶስ ምህረት በእናንተ ላይ ይሁን” ሲል በፍቅር ፀለየላቸው

እነሆ አባቶቻችን እነሆ ዋኖቻችን በክፋት በአንዳች እንኳን የሚከሰሱበት ምክንያት አልተገኘም በቀማኝነትም ማንም እነሱን ሊከስ የሚችል የለም ነገር ግን የሚሰድቧቸውን መረቁ ለሚያሳድዷቸው ፀለዩ ለተራቡት ምግብን ለተጠሙት መጠጥን አቀበሉ ድሆችን ተንከባከቡ ድውዮችን ፈወሱ የጨለማን ክፋት በፍቅር ብርሃን አረከሱ የዲያብሎስን ጭካኔ በክርስቶስ ርህራሄ ሰበሩ፡፡ እነሆ አባቶቻችን አስቀድመው ክርስቶስን አይተው ነበርና ክርስቶስን በትምህርቱ በተአምራቱ በሞቱም መሰሉት

እንኳን ለቅዱስ ጴጥሮስና ለቅዱስ ጳውሎስ አመታዊ መታሰቢያ እለት አደረሰን፡፡ በረከታቸው ይደርብን። አሜን!!
ምንጭ፦ ቤተ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
╭══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╮
https://www.tg-me.com/EOTC2921
╰══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╯‌‌
*NEW* "የአምላክ አቃቤ ሕግ"| "Ye Amlak Akabe Heg"
ማኅቶት ቲዩብ - Mahtot Tube
✞✞✞ #የአምላክ_አቃቤ_ሕግ ✞✞✞
https://www.tg-me.com/EOTC2921

ገባሬ መንክራት በግብሩ ያወቅነው፣
የእግሮቹ ትቢያ የአራዊት ስንቅ ነው፣
ገብረ መንፈስ ቅዱስ የአምላክ አቃቤ ህግ፣
የኢትዮጵያ ዋስ ነው ፈጥኖ የሚታደግ፡፡
#አዝ•••••••✞✞✞•••••••
ፀሐይ /2/ የምድራችን ፀሐይ፣
በገድሉ ያበራል እስከ ጥልቁ ቀላይ፣
የመላዕክት ወዳጅ /2/ ገብረ ህይወት ሰማይ፡፡
#አዝ•••••••✞✞✞•••••••
መብረቅ/2/ ሰረገላው መብረቅ፣
የቃል ኪዳኑ ወንዝ ቢጠጣ የማይደርቅ፣
የፍጥረቱ ደስታ/2/ ገብረ ህይወት ጻድቅ።
#አዝ•••••••✞✞✞•••••••
ኮከብ/2/ ክብረ ገዳም ኮከብ፣
አለምን የሚያስንቅ መዓዛው የሚስብ፣
አልክ ስሉስ ቅዱስ/2/ ገብረ ህይወት ኪሩ።
#አዝ•••••••✞✞✞•••••••
ስሒን/2/ ፄና ልብሱ ስሒን፣
የነፍስን አዳራሽ በገድል የሚሸፍን፣
የሚነበብ መጽሐፍ/2/ ገብረ ህይወት ድርሳን።
#አዝ•••••••✞✞✞•••••••
መቅረዝ/2/ የማህቶት መቅረዝ፣
ምድረ ከብድ ዝቋላን ያለመለመ ወንዝ፣
የዝግቲው ፈዋሽ/2/ ገብረ ህይወት ምርኩዝ፡፡{➋}
#አዝ•••••••✞✞✞•••••••
https://www.tg-me.com/EOTC2921
👍1
🌾✝️ #ልብህን_ስጣቸው ✝️🌾

"ለሰዎች የምትሰጠው ምንም ነገር ከሌለህ፤
ሞቅ ያለ ፈገግታ እና ደግ ቃል ስጣቸው፣
ፍቅር ስጣቸው፣
ርህራሄን ስጣቸው፣
የማበረታቻ ቃል ስጧቸው;
ልብህንም ስጣቸው።"

📖አቡነ ሺኖዳ ሳልሳዊ ፫ኛው የግብፅና የአሌክሳንድሪያ ሊቀ ጳጳሳት፤ በረከታቸው ይደርብን🙏
#የሊቀ_መላእክት_የቅዱስ_ገብርኤልና_የቅዱስ_ቂርቆስ_በዓል🍇🌾

❖ሐምሌ ፲፱ ዕለት የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል አምላካቸው ክርስቶስን
አንክድም በማለታቸው የፈላ ጋን ውስጥ የተወረወሩት ቅዱስ ቂርቆስና እናቱን
ቅድስት ኢየሉጣ ተራድቶ ያዳነበት በዓል ነው።
❖ ይኸውም የቅድስት ኢየሉጣን ልጅ ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ከሐዲው መኰንኑ
ይዞ “ስምኽ ማነው” ብሎ በጠየቀው ጊዜ “ነቅዕ ዘእምዐዘቅት ንጹሕ ወእማይ
ዘኢይማስን ክርስቲያን ስምየ” (ከንጹሕ ዐዘቅትና ከማይለወጥ ከማይጠፋ ውሃ
የተገኘ ስሜ ክርስቲያን ነው ሞክሼ ስም ከፈለግኽ ደግሞ እናቴ የሠየመችኝ
ቂርቆስ ነው) በማለት ክርስትናው መመኪያው የኾነው ይኽ ቅዱስ ሕፃን
መለሰለት፡፡
❖ መኰንኑም ለአማልክት ከሠዋኽ ስታድግ እሾምኻለኊ ክርስቶስን ካድ ቢለው ቅዱስ ቂርቆስ ግን “የሰይጣን መልእክተኛ ለእውነትም ጠላቷ የኾንኽ ከእኔ ራቅ” አለው፡፡ መኰንኑም ይኽነን ሰምቶ በመቈጣት የቅዱስ ቂርቆስ ደሙ እንደ ውሃ እስኪፈስስ ድረስ እንዲጨምቁት እና ጨውና ሰናፍጭ በኹለቱ የአፍንጮቹ ቀዳዳዎች እንዲጨመሩ ቢያደርግበት፤ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የጠነከረው ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ግን “ትእዛዝኽ ለጒረሮዬ ጣፋጭ ኾነ ከማርና ከሥኳርም ለአፌ ጣመኝ” እያለ አምላኩ ክርስቶስን አመሰገነ፡፡
❖ መኰንኑ በዚኽ ሳያበቃ እናትና ልጇ በክፉ አሟሟት እንዲሞቱ በማሰብ
የረዘሙና የተሳሉ በእሳትም እንደ ፍም የጋሉ ዐሥራ አራት የብረት ችንካሮች
እንዲመጡ አስደርጎ ሰባቱ በእናቱ አካላት፤ ሰባቱ በሕፃኑ ሰውነት ላይ እንዲሰካ ቢያስደርግም በጌታችን ትእዛዝ ግለቱ ጠፍቶ እንደ በረዶ በመቀዝቀዝ ምንም ምን ጒዳት ሳያደርስባቸው ቀረ፡፡
❖ ከዚያም ወደ ወኅኒ ቤት እንዲገቡና እንዲዘጋባቸው አደረገ፤ ከዚያም ሕፃኑና
እናቱ የሚሠቃዩበት ታላቅ መንኰራኲር ለ፵ ቀናት ተሠርቶ ካለቀ በኋላ ኹለቱንም
በደራቁ ራሳቸውን ላጭተው የእሳት ፍሕምን በላያቸው ላይ ቢያደርጉም
የእግዚአብሔር መልአክ ሥቃዮቹን ኹሉ ከእነርሱ አራቀላቸው፡፡
❖ የሕፃኑ ምላስ እንዲቈረጥ አዝዞ ቢያስቈርጠውም ጌታችን ምላሱን
መልሶለታል፡፡ “ወአዘዘ ካዕበ ያፍልሑ ማየ ውስተ ጽሕርት ዐቢይ ወይደይዎሙ
ለሕፃን ቂርቆስ ወለእሙ ኢየሉጣ” ይላል በታላቅ ጋን ውሃ አፍልተው ሕፃኑንና
እናቱን እንዲጨምሯቸው ሲያዝዝ ከሚፍለቀለቀው ውሃ ድምፅ የተነሣ ለጊዜው እናቱ ፍርሀት ሥጋዊ ቢያገኛትም ልጇም ወደ ጌታችን በጸለየላት ጊዜ ፍርሃቱ ርቆላት ከልጇ ጋር ስትገባ መልአከ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ወርዶ ውሃውን
አቀዝቅዞ ሐምሌ ፲፱ አውጥቷቸዋል፡፡
❖ በመጨረሻም የሰማዕትነትን አክሊል የሚያገኝባት ጊዜ ሲደርስ ጌታችን
ተገልጾለት ስሙን ለሚጠራ ኹሉ ቃል ኪዳንን ከሰጠው በኋላ ሥጋኽን በኤልያስ ሠረገላ ላይ አኖርልኻለኊ አለው፤ ይኽነን በሰማ ጊዜ በእጅጉ ተደሰተ፤ ከዚኽም በኋላ ጥር ፲፭ በሌሊቱ እኲሌታ ከእናቱ ጋር አንገቱ ተቈረጠ የሰማዕትነትን ክብር ተቀዳጅተዋል።
❖ ጥር ፲፮ ደግሞ የቅዱስ ቂርቆስ ማኅበር የኾኑ ዐሥራ አንድ ሺሕ አራት
በሰማዕትነት ዐልፈዋል፡፡ ሊቁ አርከ ሥሉስም የቅዱስ ቂርቆስን ተጋድሎ በማዘከር፡-
“እግዚአብሔር ሤመ ረድኤቶ ለንእስናከ ዐቃቤ
ወስምዖ መጥበቤ
ፍትወ ምግባር ቂርቆስ ወምዑዘ ኂሩት እምከርቤ
ለዘተጽዕረ በምንዳቤ ወለዘቈስለ በጥብጣቤ
ለአባልከ ሰላም እቤ”
(እግዚአብሔር ረድኤቱን ለታናሽነትኽ ጠባቂን አስቀመጠ፤ ብልኅ የሚያደርግ
ምስክርነቱንም፤ ምግባርኽ ያማረ በጎነትኽ ከከርቤ ይልቅ የሚሸት ቂርቆስ፤
በመከራ የተቸገረ በግርፊያ የቈሰለ ለኾነ ሰውነትኽ ሰላም እላለኊ) እያለ ሕፃኑን ሰማዕት ያወድሳል፡፡
❖ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም በመጽሐፉ፦
“ሰላም ለቂርቆስ ወሬዛ በመንፈስ
በልደት ንዑስ፤
ንጹሕ ከመ ዕጣን
ወፍሡሕ ከመ ወይን”፡፡
(በልደተ ሥጋ ታናሽ በመንፈስ ጐልማሳ፤ እንደ ዕጣን ንጹሕ እንደ ወይንም
አስደሳች ለኾነ ለቂርቆስ ሰላምታ ይገባል)
❖“ሰላም ለሰማዕታት እለ ምስሌሁ ፭፼ ወ፬፻፤ ፬፼ ወ፪፻፲ወ፬”፡፡
(ከርሱ ጋር ያሉ ፭፼ ከ፬፻፤ ፬፼ከ፪፻፲፬ ሰማዕታት ሰላምታ ይገባቸዋል) በማለት
አመስግኗል፨
ከመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
🙏✞[የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት የቅዱስ ቂርቆስ የእናቱ የኢየሉጣ፤ ስለአምላካቸው ስለ ክርስቶስ ፍቅር አንገታቸው በሰይፍ የተቆረጡት
የሰማዕታት በረከት ይደርብን።]✞🙏

✞የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያንን አስተምሮና ስርዓት የጠበቁ የተለያዩ መርሃ ግብሮች በየቀኑ ወደናንተ ይቀርባሉ፡፡ ለወዳጅዎ #Share በመድረግ የበረከት ተካፋይ እናድርጋቸው✞
╭══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╮
@EOTC2921
@Orthodox2921
╰══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╯
“… ያችኛይቱ ሔዋን ከአዳም ተገኝታ የተሠራችና አዳም ወደ እርስዋ እያየ ‘ይህች አጥንት ከአጥንቴ ይህች ሥጋ ከሥጋዬ ናት’ የሚላት ናት፡፡

ይህችኛይቱ ሔዋን ድንግል ማርያም ግን ከአዳም ጎን የተገኘች ሳትሆን አዳምዋ ክርስቶስ ሥጋው በጅራፍ ግርፋት ሲቆስልና አጥንቶቹ ሲቆጠሩ በጭንቀት እያየች ‘ይህ አጥንት ከአጥንቴ ነው ፤ ይህ ሥጋም ከሥጋዬ ነው’ የምትል ሔዋን ናት፡፡

የቀደመችዋ ሔዋን አዳምዋ በእርስዋ ምክንያት ጠፍቶ ‘አዳም ሆይ ወዴት ነህ?’ ተብሎ ሲፈለግ በዛፎች መካከል ሆኖ ከአባቱ ከእግዚአብሔር ‘ፈርቼ ተሸሸግሁ’ የሚል አዳም ነበረ::

ሁለተኛይቱ ሔዋን ድንግል ግን አዳምዋን ፍለጋ የምትጨነቅና ወዴት ነህ? ስትለው አዳምዋ ‘በአባቴ ቤት እኖር ዘንድ እንዲገባኝ አታውቁምን’ ብሎ የሚመልስላት ከአባቱ እቅፍ ያልተለየ አዳም እናት ናት፡፡

ለድንግል ማርያም ክርስቶስ ከእርስዋ የተገኘ አዳምዋ ብቻ ሳይሆን በቀናተኞቹ ቃየኖች አይሁድ በግፍ የተገደለባት አቤልዋም ጭምር ነው፡፡ ልዩነቱ የአቤል ደም ወንድሙን የሚከስስ ደም ሲሆን የእርስዋ ልጅ የክርስቶስ ደም ግን ‘ከአቤል ደም ይልቅ የሚሻለውን የሚናገር’ ‘ከኃጢአት ሁሉ የሚያነጻ ደም’ ነው"

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
የብርሃን እናት ገጽ 100

ሥዕል :- ሠዓሊ ዮሐንስ ዳኜ የብርሃን እናትን የገጽ ሽፋን ከጥንታዊ የብራና ሥዕላት ጋር አጣጥሞ እንደሠራው

*እመ ኲሎሙ ሕያዋን ቢል ይቀናል
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
አሜን

✍️"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"
📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

ቀናችንን በጸሎት እንጀምር


✥••┈┈┈••●◉ ✞ ◉●••┈┈┈••✥
ልጄ ሆይ፤ ዋዘኛና ቀልደኛ አትሁን
✥••┈┈┈••●◉ ✞ ◉●••┈┈┈••✥

❖ በመከራ ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ የምታዝንና የምትራራ ሁን፤ በድኃ ላይ አትጨክን፤ ርስቱንና ቤቱንም በምክንያት አትውሰድበት፤ ለመጨረስም የማትችለውን ነገር አትጀምር፡፡

❖ ልጄ ሆይ፤ በልተህ ስትጠግብ ረኃብን፤ ስትበለጥግ ድኅነትን፤ ስትሾም ሽረትን፤ ሌላውንም ይህን የመሰለውን ሁሉ አትርሳ፡፡

❖ ልጄ ሆይ፤ ለሞተው ወዳጅህ ከማልቀስ ይልቅ በሕይወቱ ሳለ የክፋት ሥራ ለሚሠራ ወዳጅህ አልቅስለት፡፡

❖ ልጄ ሆይ፤ ባለ ጠጋ ሰው ሁሉ ይደግፈዋል፤ ድኃ ሲወድቅ ግን ሰው ሁሉ ወዲያው ይገፋዋል፤ ባለ ጠጋ ሲከሰስ በሸንጎ የተቀመጠው ሁሉ ይሟገትለታል፤ ድሀ ሲከሰስ ግን በሸንጎ የተቀመጠው ሁሉ ይፈርድበታል፡፡

❖ መልካም ዳኛ በመካከላቸው የተቀመጠ እንደ ሆነ ግን ፍርዱ እንደ ፀሐይ ያበራለታል፤ ስለዚህ በምትኖርበት ሀገር መልካም ዳኛ አያጥፋብህ፡፡

❖ ልጄ ሆይ፤ በማናቸውም ነገር ቢሆን ሞት አይቀርም፤ ነገር ግን በሰው እጅ ከመውደቅ በእግዚአብሔር እጅ መውደቅ ይሻላል፡፡

❖ ለአፍህ መሐላ አታልምደው፤ እግዚአብሔር ስሙን ከንቱ ያደረገውን ሳይቀስፈው አይቀርምና ስሙን በከንቱ አትጥራ፡፡

❖ ልጄ ሆይ፤ የምትሠራውን ሥራ ሁሉ ሰው ቢያየው ቢሰማውም አይጎዳኝም ብለህ እንደ ሆነ ነው እንጂ አይታይብኝም፤ አይሰማብኝም ብለህ አትሥራው፤ አንተ ምንም ተሰውረህ ብትሠራው ከተሠራ በኋላ መታየቱና መሰማቱ አይቀርም፡፡

❖ ልጄ ሆይ፤ አንተ አስቀድመህ በሰው ላይ አትነሣ፤ ሰው በአንተ ላይ ቢነሣብህ ግን እንዳትሸነፍ ጠንክረህ መክት፤ እምነትህንም በእግዚአብሔር ላይ አድርግ፡፡

❖ ልጄ ሆይ፤ ሰው ሳይኖር ብቻህን ከሴት ጋር አትነጋገር፤ ባሏ አለመኖሩን በደጅ ጠይቀህ ከደጅ ተመለስ እንጂ ወደ ቤት አትግባ፡፡

❖ ሰው ሳይኖር ብቻህን ከሴት ጋር የተነጋገርህ እንደ ሆነ ግን፤ ምንም ሌላ ምስጢር ባይኖራችሁ በመነጋገራችሁ ብቻ መጠርጠር አይቀርም።

❖ ልጄ ሆይ፤ በጌታህም ቤት ቢሆን በሌላም ስፍራ ቢሆን ገንዘብ ወይም ሌላ እቃ ወድቆ ብታገኝ አታንሣ፤ ብታነሣውም መልሰህ ለጌታህ ወይም ለዳኛ ስጥ እንጂ ሰውረህ አታስቀር፡፡

❖ ልጄ ሆይ፤ በፍፁም ልብህ ለማትወደው ሰው ቤትህንና የቤትህን ዕቃ አታሳይ፡፡

❖ ልጄ ሆይ፤ ንፁሕ አለመሆንህን እግዚአብሔር ያውቃልና በእርሱ ፊት ንፁሕ ነኝ አትበል፤ በንጉሥ ፊትም ብልህ ነኝ አትበል፤ የብልሃት ሥራ ሠርተህ አሳየኝ ያለህ እንደ ሆነ ታፍራለህና፡፡

❖ ልጄ ሆይ፤ ጠላት በዛብኝ፤ ምቀኛ አሴረብኝ ብለህ እጅግ አትጨነቅ፤ በዓለም የሚኖር ፍጥረት ሁሉ ጠላትና ምቀኛ አለበት እንጂ ባንተ ብቻ አይደለም፡፡

❖ ከዚሁም በጥቂቱ እጽፍልሃለሁ፤ በፍየል ነብር፤ በበግ ተኩላ፤ በአህያ ጅብ፤ በላም አንበሳ፤ በአይጥ ድመት፤ በዶሮ ጭልፊት አለባቸው፡፡ ይህንንም የመሰለ ብዙ አለ፤ ሰውም እርስ በርሱ እንዲሁ ነው፡፡

❖ ስለዚህ የሚመጣብህን ነገር ሁሉ በትእግሥት ሆነህ ተቀበለው፤ በመጨረሻው ግን ሁሉ አላፊ ነውና ጠላቶችህ ሁሉ ያልፋሉ ወይም አንተ አስቀድመህ ታልፍና ከዚህ ዓለም መከራና ጭንቀት ታርፋለህ፡፡

❖ ልጄ ሆይ፤ እስቲ ያለፉትን ሰዎች ሁሉ አስባቸው፤ እነዚያ ሁሉ ጀግኖች ሁሉም መሬት ሆነዋል፤ እነዚያ ሁሉ ዓለመኞች፤ እነዚያ ሁሉ ቀልደኞችና ፌዘኞች፤ እነዚያ ሁሉ ግፈኞች፤ እነዚያ ሁሉ በድኃ ላይ የሚስቁና የሚሳለቁ ሁሉም መሬት ሆነዋል፡፡

❖ እነዚያ ሁሉ ድሆች ሲበደሉ፣ ሲያዝኑ፣ ሲያለቅሱ ካንዱ ሀገር ወደ ሌላው ሀገር ሲሰደዱ፣ ሲራቡ፣ ሲጠሙ፣ ሲታረዙ የነበሩ መሬት ሆነዋል፤ ስንት ሰዎች የነበሩ ይመስልሃል የድኃ እንባ ሲፈስ የወንዝ ውኃ የሚፈስ የሚመስላቸው ስንት ሰዎች ነበሩ፡፡

❖ ድኃ ሲጮህ ውሻ የሚመስላቸው ስንት ሰዎች ነበሩ፤ ድኃ ታስሮ ወይም በሌላ ጭንቅ ነገር ተይዞ ሲሞት የወፍ ግልገል የሚሞት የሚመስላቸው ስንት ሰዎች ነበሩ፤ ጉልበት ካለን ብለው በደካሞች ላይ ያሰቡትን ሁሉ የሚሠሩ ስንት ሰዎች ነበሩ፡፡

❖ ሰውን ለማጥፋት እጅግ የሚጥሩ ሰውን ካላጠፉ እንቅልፍ የማይወስዳቸው ስንት ሰዎች ነበሩ፤ ነገር ግን ከዚህ ቀድሞ የነበሩት ሁሉም መሬት ሆነዋል፤ ከመሬት የተገኘ ሁሉ መሬት ስለ ሆነ ወደ መሬትም የማይመለስ ስለሌለ እኛም ነገ እንደዚያው እንሆናለን፤ ስለዚህ በማናቸውም ምክንያት የሰው ደስታውና አዘኑ እጅግ አጭር መሆኑን በጣም እወቅው፡፡

❖ ልጄ ሆይ፤ ቀን በሥራህ ላይ፤ ሌሊት በአልጋህ ላይ፤ የሚጠብቅህ እግዚአብሔር ነውና ማታ ስትተኛ፤ ጧት ስትነሣ እግዚአብሔርን አምላክህን መለመንና ማመስገን አትተው፡፡

📌ምንጭ
✍️ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ፤ ለልጃቸው ለፈቃደ ሥላሴ የፃፉት ምክር)


✍️"ልብህን በእርጋታ አኑረው፤ የሁሉም መጨረሻ እና የሁሉም አገልጋይ ለመሆን በጣም ትጋ ለከንቱ ንግግር ዘገምተኛና ሰነፍ ሁን፤ ነገር ግን የቅዱሳት መጻህፍትን ቃል በማወቅ በመስማት ድኅነትን የሚሰጡ ናቸውና ብልህ ሁን"
📚ታላቁ ባስልዮስ ዘቂሳሪያ

✍️ "በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ በእግዚአብሔርም እውቀት እያደጋችሁ፥
ለጌታ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናለን"
📖ቆላስይስ 1፥10-11

✞ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያንን አስተምሮና ስርዓት የጠበቁ የተለያዩ መርሃ ግብሮች በየቀኑ ወደ እርስዎ ይቀርባሉ፡፡ ለወዳጅዎ #Share በመድረግ የበረከት ተካፋይ ያድርጓቸው ✞
╭══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╮
https://www.tg-me.com/EOTC2921
╰══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╯
🌾#ጾመ_ፍልሰታ🌾

✞ "ፍልሰታ" የሚለው ቃል "ፈለሰ፣ ተሰደደ፣ ተጓዘ" ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን እመቤታችንም ከጌቴ ሴማኒ ወደ ገነት መፍለሷን በኃላም በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረችበት መነሳቷን ለማመልከት አስቀድሞ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት "ተንሥእ እግዚኦ ውስተ እረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅደስከ"(አቤቱ ወደ እረፍትህ ተነስ አንተና የመቅደስህ ታቦትም) መዝ ፻፴፩፥፲ በማለት ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት የእመቤታችንን ምልጃዋን ትንሣኤዋን አስቀድሞ በትንቢቱ ተናግሮ ነበር።
www.tg-me.com/EOTC2921
✞ የፍልሰታ ጾምም ሁሌ በየአመቱ ከነሐሴ ፩ እስከ ፲፭ ቀን ይሆናል። በነገረ ማርያም እንደተጻፈው ጥር ፳፩ ቀን አርፋ በ፷፬ ዓመት እድሜዋ በ፵፱ ዓ/ም አይሁድ ለምቀኝነት አያርፋም ነበርና ቀድሞ ልጅዋን ተነሣ አረገ እያሉ ሲያውኩን ኖረዋል አሁን ደግሞ እሷን ተነሣች አረገች እያሉ ሊያውኩን አይደለምን? "ንዑ ናውዒ ሥጋሃ ለማርያም ምስለ ዓራታ"(ኑ የማርያምን ሥጋ በእሳት እናቃጥለው) ብለው ተነሱ። ከመካከላቸውም አንድ ታውፋንያ የሚባል ጎበዝ ከሐዋርያት እጅ ለመንጠቅ የአልጋውን ሸንኮር መያዣ ሲይዝ ቅዱስ ገብርኤል በእሳት ሰይፍ እጆቹን ቆረጣቸው። እጆቹም በአልጋው ሸንኮር ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ። ታውፋንያም ወደ ሐዋርያት ዞሮ በድያለሁ ይቅር በሉኝ ብሎ ቢማፀን፤ የምሕረት እናት የሆነች እመቤታችን አይኖቹዋን ገልጣ ቅዱስ ጴጥሮስን እጆቹን መልስለት ብላው እጆቹንም እንደ ነበሩ መልሶለት ተፈውሷል።
✞ ያን ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስ በዕለተ ዐርብ ከአምላኩ በስጦታ የተሰጠችውን የአምላክ እናትን ሥጋዋን በድፍረት ሊነኩ መምጣታቸውን አይቶ ዐደራዬን አላፈርስም፤ ከርሷ ጋር እሞታለኊ በማለት ይኽነን ተናግሮ በላይዋ ላይ ወደቀ። ከዚያም ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል በታላቅ ግርማ ወርደው የቅድስት ድንግል ማርያምን ሥጋዋንና ቅዱስ ዮሐንስን በደመና ነጥቀው በገነት በሕይወት ዛፍ ሥር አኖሯት፡፡ ወዲያውኑ የወርቅ ማዕጠንት ለዮሐንስ አምጥተውለት፤ የቅድስት ድንግል የከበረ ሥጋዋን በመዓልትና በሌሊት ዕጠን አሉት፤ ዮሐንስም ይኽነን ክብር በመቀበሉ ደስ ብሎት ሥጋዋን እያጠነ ሰርክ ሲኾን ራጉኤል መልአክ ሰማያዊ ኅብስት ሰማያዊ መጠጥ እያመጣለት ያን እየተመገበ በገነት ቆይቷል፡፡ ኋላም በጌታ ፈቃድ ከተቀሩት ሐዋርያት ጋር ተገናኘ። ሐዋርያትም የእመቤታችንን ነገር እንደምን እንደኾነ ሲጠይቁት ርሱም በገነት ያየውን ነገር ነገራቸው፤ ሐዋርያትም ይኽነን ታላቅ ምስጢር ዮሐንስ አይቶ እኛ ሳናይ ብለው ሥጋዋን አግኝተው ይቀብሩት ዘንድ በአረፈች በስምንተኛው ወር ነሐሴ ፩ ሱባኤ ጀመሩ ነሐሴ ፲፬ ቀን በኹለተኛው ሱባኤ ጌታ የእናቱን ሥጋ አምጥቶ ሰጥቷቸው በምኅላና በደስታ በጌቴሴማኒ አሳረፋት።
✞ ከዚህም በኃላ በሦስተኛው ቀን ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ በተወደደች ዕለት ነሐሴ ፲፮ ሰባቱ ሊቃነ መላእክት ምድርን ይጠሯት ዘንድ አዘዛቸው እነርሱም ምድርን “ይኤዝዘኪ እግዚእነ ከመ ታውጽኢ ሥጋሃ ለእሙ ቅድስት” (ጌታችን የንጽሕት እናቱን ሥጋ ታወጪ ዘንድ ያዝሻል) አሏት፤ ያን ጊዜ ልጇ “ንዒ ኀቤየ ወላዲትየ ከመ አዕርጊ ውስተ መንግሥተ ሰማያት”(ወደ መንግሥተ ሰማያት አሳርግሽ ዘንድ እናቴ ወደኔ ነዪ) አላት፤ በልጇም ሥልጣን የቅድስት ድንግል ማርያም ነፍሷና ሥጋዋ ተዋሐዱ፤ በነሐሴ ፲፮ ዕለትም እመቤታችን ከሞት ተነሣች፡፡ ቅዱሳን መላእክትም ከሰማይ በታላቅ ግርማ ወረዱ፤ ነቢዩ ዳዊትም "ንግሥቲቱ ወርቀ ዘቦ ግምጃ ደርባ ደራርባ በቀኝኽ ትቆማለች" እያለ ይዘምርላት ነበር፤ አየሩ ኹሉ በቅዱሳን መላእክት ተመላ፤ እጅግ የሚያስደንቅ መዐዛ አካባቢን ዐወደው። በታላቅ ክብርም በመላእክት ታጅባ ወደ ሰማይ ስታርግ፤ ጥሪው ከሰዱቃውያን ትውልዱ ሕንዳዊ የሆነው ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለስ ሰማዩ ኹሉ በቅዱሳን መላእክት ተመልቶ የአምላክ እናት በክብር ስታርግ ተመለከተ፤ ያን ጊዜ ነገሩ ረቆበት ምን ይኾን እያለ ሲል ቅዱሳን መላእክት የእመቤታችን ዕርገት እንደኾነና እጅ እንዲነሣ ነገሩት፡፡ ቅዱስ ቶማስም ትንሣኤዋን ከእርሱ ሰውራ ያደረገች መሥሎት፤ “ከቶ ምን አርጌ ይኾን፤ ቀድሞ የልጇን ትንሣኤ ሳላይ ቀረኊ ዛሬ ደግሞ የርሷን ትንሣኤ ሳላይ ልቅር?” ብሎ ከደመና ተወርውሮ ሊወድቅ ወደደ።
http://www.tg-me.com/EOTC2921
✞ እመቤታችንም “አይዞኽ አትዘን እነሱ ሞቴን አይተዋል እንጂ ዕርገቴን አላዩም። አኹንም እመቤታችን ተነሣች፤ ዐረገች ብለኽ ንገራቸው” ብላ ለቀሩት ሐዋርያት ምልክት የሚሆን ሰበን ወይም መግነዟን ሰጥታው ተለያዩ። እርሱም በደስታ ተመልቶ ሐዋርያት ያሉበት በመኼድ የእመቤታችን ነገር እንደምን ኾነ ብሎ ጠየቃቸው፤ እመቤታችን ሞተች ቀበርናት አሉት፤ “መቼ ሞተች?” አላቸው በጥር አሉት፤ “መቼ ቀበራችኋት?” አላቸው በነሐሴ አሉ፤ ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር ተዉ ይኽ ነገር እንዴት ይኾናል? አላቸው፤ ቅዱስ ጴጥሮስም ቶማስን ቀድሞ የልጇን ትንሣኤ አላምን ብለኽ የጌታን ጐን የዳሰሰ እጅኽ ተቃጥሎ ነበር፤ አኹን ደግሞ እኛ ብንነግርኽ አላምን ትላለኽ ብሎ፤ መቆፈሪያ ይዞ ኼዶ ይቆፍር ጀመር፤ እርሱም የያዘውን ይዟልና ጸጥ ብሎ ይሰማቸዋል፤ ቈፍረው ሲያጧት ደነገጡ፤ ቶማስም አይዟችኊ አትደንግጡ እመቤታችን እኮ በመላእክት ምስጋና ወደ ሰማይ አረገች ብሎ ሰበኑን አሳያቸው፤ እነርሱም ለበረከት ሰበኑን
ተካፍለውታል፡፡ ዛሬም ሐዋርያዊት የኾነችው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ይኽነን በማሰብ ዛሬም ቀዳሽ ዲያቆኑ ከመስቀል ሥር ከመፆሩ ጋር የሚይዘው መቀነት መሳይ ጨርቅ የእመቤታችን የሰበኗ ወይም የመግነዝዋ ምሳሌ ነው።
✞ ከዚህም በኃላ በዓመቱ ሁሉም ሐዋርያት ተሰባስበው ቶማስ ትንሣኤሽን አይቶ እኛ ሳናይ ብለው በድጋሚ ሱባኤ ከነሐሴ ፩ እስከ ፲፬ ቢጾሙ ጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ነፍሷን ከስጋዋ አዋህዶ ትንሣኤዋንም ዕርገቷንም አሳይቷቸዋል። ክብር ይግባውና ጌታችን በደመና ነጥቆ ወስዶ ሥርዓተ ቊርባንን ፈጽሞላቸው፤ ስለ እናቱ ዕርገት በዓለሙ ኹሉ ዙረው እንዲያስተምሩ አዝዟቸዋል፡፡ እነርሱም
ዓለምን ዞረው ወንጌልን ሲያስተምሩ የእመቤታችንን ትንሣኤና ዕርገትም ሰብከዋል አስተምረዋል፡፡ እኛም ከበረከቷ ለመሳተፍ በመላው ዓለም የምንገኝ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ የሆንን ሁሉ ከሕፃን እስከ አዋቂ ድረስ በፍቅርና በዕምነት የምንጾመው የሱባዔ ጾም ነው።
✞ እመቤታችን ከእናቷ ማሕፀን ዠምራ በመንፈስ ቅዱስ የተጠበቀች አዳማዊ ኀጢአት ያላገኛት፣ ኀጢአት አልባ የኾነች እንዲያውም አዳምና ሔዋን ከእርግማን በፊት ከነበራቸው ንጽሕና የበለጠ ንጽሕናን ገንዘብ ያደረገች ስትኾን ክብር ይግባውና አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ይኽነን ንጹሕ ሥጋዋንና ነፍሷን በመንሣት በተዋሐደው ሥጋ በመስቀል ተሰቅሎ፤ ሦስት መዓልትና ሌሊት በከርሠ መቃብር ዐድሮ፤ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ሞትንና ኀጢአትን ድል ነሥቷልና፤ አማናዊት ታቦቱ እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያምም በልጇ ሥልጣን በሦስተኛው ቀን ተነሥታለች። "በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝ ትቆማለች።"(መዝ ፵፬፥፱)፡፡

✞የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያንን አስተምሮና ስርዓት የጠበቁ የተለያዩ መርሃ ግብሮች በየቀኑ ወደናንተ ይቀርባሉ፡፡ ለወዳጅዎ #Share በመድረግ የበረከት ተካፋይ ያድርጓቸው✞
╭══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╮
@EOTC2921
╰══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╯
​​🌾#መልክአ_ፍልሰታ🌾
https://www.tg-me.com/EOTC2921
✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ
አሃዱ አምላክ አሜን ✞

#ለፍልሰተ_ሥጋኪ
#እመቤቴ_ማርያም_ሆይ
ሕያዊት ከምትሆን ነፍስሽ ጋር በፍጹም ተዋህዶ ለተከናወነው ፍልሰተ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል፡፡
#ድንግል_እመቤቴ_ሆይ
አንቺ ወለተ ማቲ የተባልሽ በነፍስ በስጋ በውስጥ በአፍአ አማናዊት ድንግል ነሽ እኮን ብልሆችና አዋቂዎች የአፌዝን ወርቅ አሳፍረው የሚጓዙብሽ ሰሎሜናዊት የተርሴስ መርከብ አንቺ ነሽ፡፡

#ለፍልሰተ_ሥጋኪ
#እመቤቴ_ማርያም_ሆይ
ኅዘንን ወደሚረሱበት ትካዜን ወደማያስቡበት የተረጋጋ ፍጹም ደስታ ወዳለበት ለተጓዘው ፍልሰተ ስጋሽ ሰላምታ ይገባል፡፡
#ድንግል_እመቤቴ_ሆይ
ቅድመ አለም በአምላክ ልቡና ታስበሽ ያለሽ ነሽ እኮን፡፡ እንግዲህ በፍልሰትሽ በፍጹም ደስታ ዛሬ ደስ ተሰኝቻለሁ ነገር ግን ፊትሽን የማየው መቼ ይሆን፡፡

#ለፍልሰተ_ሥጋኪ
#እመቤቴ_ማርያም_ሆይ
በሰው ልብ የማይታሰበውን ግርማ ሞገስን የተላበሰ ጸጋ ክብርን ለተጎናጸፈ ፍልሰተ ስጋሽ ሰላምታ ይገባል፡፡
#ድንግል_እመቤቴ_ሆይ
ሥጋሽ ዕንቈ ባሕርይ ነው፡፡ ስለዚህም በደመና ሲያርግ በተመለከተ ጊዜ ሞት በፍጹም ኃፍረት አፈረ፡፡

#ለፍልሰተ_ሥጋኪ
#እመቤቴ_ማርያም_ሆይ
ከባረካ ልጅ ከኄኖክ ፍልሰት ከፍ ከፍ አድርጎ እግዚአብሔር አክብሮ ለባረካት ፍልሰተ ስጋሽ ሰላምታ ይገባል፡፡
#ድንግል_እመቤቴ_ሆይ
ከብርሃናት ሁሉ የምትበልጭ ብርህትና አስደሳች ነሽ እኮን ስለዚህም የብዙ ብዙ የሚሆኑ የሰማይ መላእክት በአንቺ ምክንያት በሰማያዊት አዳራሽ ታላቅ ደስታን ያደርጋሉ፡፡

#ለፍልሰተ_ሥጋኪ
#እመቤቴ_ማርያም_ሆይ
ክብሩ ባለሟልነቱ ለማይገሰስ የምስጋናው ባሕር (ባሕርይ) ለማይጎድል ፍልሰተ ስጋሽ ሰላምታ ይገባል፡፡
#ድንግል_እመቤቴ_ሆይ
የእግዚአብሔር የልዩ ምስጋናው አዳራሽ ነሽ እኮን ስለዚህ በፍልሰትሽ ጊዜ አንቺን የተቀበሉ መላእክት ማርያምስ በሰማይም በምድርም የከበረች ነች ተባባሉ፡፡

#ለፍልሰተ_ሥጋኪ
#እመቤቴ_ማርያም_ሆይ
ከጌታ ወዳጅ ከያዕቆብ ፍልሰት ይልቅ ክብር ምስጋና ለተገባው ፍልሰተ ስጋሽ ሰላምታ ይገባል፡፡
#ድንግል_እመቤቴ_ሆይ
ቀናንሞ የተባለ ሽቱ ነሽ። የልዩ ሽቱ አይነትም መገኛ ነሽ፡፡ ስለዚህም ብርሀን ለብሰው በብርሃን ነፀብራቅ ተጎናጽፈው የፍልሰትሽን በዓል መላእክት ያከብራሉ፡፡

#ለፍልሰተ_ሥጋኪ
#እመቤቴ_ማርያም_ሆይ
ከፀሐይና ከጨረቃ ሥነ ጸዳል ይልቅ ፈጽሞ ለሚያበራውና ፍጹም ምስጋና ለተገባው ፍልሰተ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል፡፡
#ድንግል_እመቤቴ_ሆይ
ሁሉን ከሚያስደስትና የደስታ መገኛ ከሚሆን ልጅሽና ያለ አንቺ የሞትን ማሰሪያ በጣጥሶ የሲኦልን ደጃፍ ሰባብሮ ነፍሳትን ከዲያብሎስ የባርነት አገዛዝ ነጻ ያወጣ ማንም የለም፡፡

#ለፍልሰተ_ሥጋኪ
#እመቤቴ_ማርያም_ሆይ
ሱራፊ መልአክ እየጠበቃት በኪሩቤል ከተማ ትኖር ዘንድ ከዚህ ከአላፊውና ከጨለማው ዓለም ለተዛወረችው ፍልሰተ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል፡፡
#ድንግል_እመቤቴ_ሆይ
ከጥቅምት ወር የጽጌ የአበባ ሽታ ይልቅ የመዓዛሽ ጣዕም እጅግ የጣፈጠ ነው፡፡እነሆ በስህተት ባሕር ልሰጥም ተቃርቤአለሁና በንጽሕናሽ በቅድስናሽ መርከብ አሳፍረሽ እኔን አገልጋይሽን አሻግሪኝ፡፡

#ለፍልሰተ_ሥጋኪ
#እመቤቴ_ማርያም_ሆይ
በቅድስተ ቅዱሰን ቆሞ የነግሁን መስዋዕት ሲያሳርግ የካህናቱን አለቃ ለአስደነቀው ፍልሰተ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል፡፡
#ድንግል_እመቤቴ_ሆይ
አምላክ ያተመው የፍልሰትሽ ግርማ ሞገስ ያን የቂም በቀል መልአክና የክፉ መጨረሻ የሆነ መልዐከ ሞት ምንኛ አሰቃየው ምንኛ መከራውን አሳየው እሰይ እሰይ።

#ለፍልሰተ_ሥጋኪ
#እመቤቴ_ማርያም_ሆይ
የይቅርታው ክናድ ለዘላለሙ ጸንቶ ለሚኖረውና የኃይለኞች ኃይለኛ ለሚሆን ፍልሰተ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል።
#ድንግል_እመቤቴ_ሆይ
መታሰቢያሽ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለዘላለም ሲታሰብ ይኖራል። በምድር ላይ ለሚኖሩ ኃጥአን ሁሉ አማልደሽ ምህረት የምታስገኝ ነሽና እመቤቴ ሆይ የተባረክሽ የክርስቶስ አካሉን ነሽ፡፡

፲፩ #ለፍልሰተ_ሥጋኪ
#እመቤቴ_ማርያም_ሆይ
ለተመረጡት ልጆች እናት ትሆኛቸው ዘንድ ምጡቅ በሆነ በብርሀን ሰረገላ ለመጠቀ ፍልሰተ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል።
#ድንግል_እመቤቴ_ሆይ
ብዙዎች ወገኖች በሁለት ድሪም በአስፈላጊው ጊዜ በትጋትና በመፋጠን ወገንን እንደሚዋጁ እኔን አገልጋይሽን በይቅርታሽ ወርቅ ዋጅተሽ ገንዘብ አድርጊኝ፡፡

፲፪ #ለፍልሰተ_ሥጋኪ
#እመቤቴ_ማርያም_ሆይ
እግዚአብሔር ለተዋሐዳትና ስነ ስርአቷንም ለተካፈላት ፍልሰተ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል
#ድንግል_እመቤቴ_ሆይ
በፍልሰትሽ ጊዜ በምድረ ይሁዳና በኢየሩሳሌም አደባባይ የተርሴስና የደስያት ነገስታት ለመታሰቢያሽ መዓዛቸው የጣፈጠ ሽቶና ልዩ ልዩ እጅ መንሻዎች ይዘው ቀረቡ፡፡

፲፫ #ለፍልሰተ_ሥጋኪ
#እመቤቴ_ማርያም_ሆይ
ከሴሎ ነቢይ ከኤልያስ ፍልሰት ይልቅ እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ላደረገው ፍልሰተ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል፡፡
#ድንግል_እመቤቴ_ሆይ
ሁሉን እንዳውሬ የሚያድን ሞት ተከትሎኝ የኔ በተድላ ደስታ መኖር ምኔም ስለአይደለ በአውሎ ነፋስ ክንፍ ጠልፈሽ ጻድቅ ካለበት ቦታ ወስደሽ ከዚያ አድርሽኝ።

፲፬ #ለፍልሰተ_ሥጋኪ
#እመቤቴ_ማርያም_ሆይ
ተጠባቢዋና መጋቢዋ እግዚአብሔር የሆነ ወደ አማረችውና ወደ ተደላደለችው ሀገር ለፈለሰው ፍልሰተ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል፡፡
#ድንግል_እመቤቴ_ሆይ
መሪር ከሆነ የሞት አገዛዝ ነፃ አውጪኝ የሰማይና የምድር ንግሥት ሆይ አንቺ እኮ ከፈቀድሽ ኃጥኡን ባሪያ ነፃ ማውጣት አይሳንሽም ፡፡

፲፭ #ለትንሣኤ_ሥጋኪ
#እመቤቴ_ማርያም_ሆይ
ሕያው ባሕርዩን በውስጧ ሰውሮ ለተነሳባት የክርስቶስ ትንሳኤ መንትያ ለሆነች ትንሣኤ ስጋሽ ሰላምታ ይገባል፡፡
#ድንግል_እመቤቴ_ሆይ
በዚያች በቁርጥ ቀን የፍርድ ምርመራ በተደረገ ጊዜ ምድርም አደራዋን በመለሰች ጊዜ አንቺ የኤፍራታ ርግብ ሆይ በክንፈ ረድኤትሽ ሠውሪኝ በጥላሽም ሥር ሸሽገሽ አድኚኝ፡፡

፲፮ #ለዕርገተ_ሥጋ
#እመቤቴ_ማርያም_ሆይ
አንቺን ለሚያመሰግኑ ቅዱሳን ሰዎች ሁሉ የዕርገታቸው መመሪያ ለሆነ ዕርገተ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል፡፡
#ድንግል_እመቤቴ_ሆይ
የሊቀ ካህናቱ የካህኑ የአሮን የሽልማቱ ጌጥ ነሽ እኮን በአንደበታችን የሚነገረው የምስጋናሽ ፍሬ ሁሉ በውስጥም በውጭም ላለው ልብስሽ ላይ በስዕል መልክ ተቀርጾ ይኑር፡፡

፲፯ #ስብሐት_ለኪ
#እመቤቴ_ማርያም_ሆይ
በሥጋዊ በደማዊ አንደበት ሁሉ ለአንቺ ምስጋና ይገባል፡፡ በመላእክትም አንደበት ያለማቋረጥ ለአንቺ ምስጋና ይገባል፡፡
#ድንግል_እመቤቴ_ሆይ
የደብተራ ኦሪት ቃል ኪዳን የተጻፈብሽ የሕግ ታቦት ላንቺ ሰላምታ ይገባል፡፡እንደዚሁም ለኔ ለአገልጋይሽ ለ........ የክብር ጌጥ ወይም ሽልማት ሆኖኝ ይኖር ዘንድ የልዩ ችሮታሽን የነጭ ሐር ልብስ አጎናጽፊኝ፡፡
ይልቁንም በሥጋ በነፍስ ጥበቃሽ አይለየኝ፡፡ አሜን።
---✞ #አቡነ_ዘበሰማያት ✞---

✞የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያንን አስተምሮና ስርዓት የጠበቁ የተለያዩ መርሃ ግብሮች በየቀኑ ወደ እርስዎ ይቀርባሉ፡፡ ለወዳጅዎ #Share በመድረግ የበረከት ተካፋይ ያድርጓቸው✞
╭══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╮
@EOTC2921
╰══•|❀:๑✞♡✞๑:❀|•══╯
ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ @EOTC2921.pdf
15.6 MB
#ውዳሴ_ማርያም_ትርጓሜ
ቅዱስ ኤፍሬም የደረሰው

✍️የኢትዮጵያ ሊቃውንት እንደ ተረጎሙት
2025/07/08 15:33:03
Back to Top
HTML Embed Code: