Telegram Web Link
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
                         †                         


❝ በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው። ❞

[ ፩ ዮሐ . ፩ ፥ ፱ ]



         †              †               †
▬▬▬▬ ▬▬▬▬▬ ▬▬▬▬
1
🕊

[ †  እንኳን ለተባረከ ወር ሐምሌ እና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፣ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

† እግዚአብሔርን ቸር የምንለው በባሕርዩ ፍጹም ቸር በመሆኑ ነው:: ይሕንን ደግሞ ለማረጋገጥ መቅመስ ይቻላል:: ይገባልም:: [መዝ.፴፫፥፯] ይሔው ደግሞ ያን ሁሉ ኃጢአታችንን ታግሶ ከወርኀ ሐምሌ አደረሰን:: ለዚሕ ቸርነቱ አምልኮ : ውዳሴና ስግደት ይገባዋል::
ለወርኀ ነሐሴ ደግሞ እንዲያደርሰን ልንማጸነው ይገባል::

🕊 † ቅዱስ አግናጥዮስ ሐዋርያዊ ሊቅ †  🕊

† ሐዋርያዊ ጳጳስና ሰማዕት ቅዱስ አግናጥዮስ ገና በልጅነቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ያየ : ራሱ ጌታችን ትንቢት የተናገረለት [ማቴ.፲፰፥፩] እና ከጌታ ዕርገት በኋላ ሐዋርያትን የተከተለ አባት ነው:: ጌታ ሲያርግ የአምስት ዓመት ሕፃን ሲሆን ከሰላሳ ስድስት ዓመታት በላይ ሐዋርያትንና ቤተ ክርስቲያንን አገልግሏል::

ዕድሜው ወደ አርባዎቹ ሲደርስ [ኢየሩሳሌም በጠፋችበት ዓመት - በ፸ ዓ/ም] እርሱ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ሆኖ ተሹሟል:: አስቀድሞ ከወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ እግር ምሥጢርና ፍቅርን ጠጥቷልና የተለየ ሰው ነበር:: ቅዱስ አግናጥዮስ ከአንጾኪያ እየተነሳ ምድረ እስያንም በወንጌል ዕርፈ መስቀል አርሷል::

በአካል ያልደረሰባቸውን በጦማር [በክታብ] አስተምሯል:: በአካሉ እንኳ ምንም በጾም በጸሎትና በብዙ ድካም የተቀጠቀጠ ቢሆን ግርማው የሚያስፈራ ነበር:: ከነገር ሁሉ በኋላ የወቅቱ ቄሣር ጠራብሎስ ይዞ አሰቃይቶ ለአንበሳ አስበልቶታል:: በዚህ ምክንያት "ምጥው ለአንበሳ-ለአንበሳ የተሰጠ" እየተባለ ይጠራል::


🕊  † አባ ብዮክ እና አባ ብንያሚን †  🕊

† እነዚህ ቅዱሳን የሥጋ ወንድማማቾች ናቸው:: ካህን አባታቸው በሚገባ ቢያሳድጋቸው እነሱም ገና በወጣትነት የሚደነቅ የክህነት አገልግሎትን ሰጥተዋል:: ሙሉ ሌሊት ለጸሎት : ሲነጋ ለኪዳን : በሠርክ ደግሞ ለቅዳሴ ይፋጠኑ ነበር:: ሁሌም በየቤቱ እየዞሩ የደከመውን ሲያበረቱ : የታመመውን ሲፈውሱ : ያዘነውን ሲያጽናኑ ውለው ትንሽ ቂጣ ለራት ይመገባሉ::

ሰውነታቸው በፍቅር ሽቱ የታሸ ነበርና ብዙዎችን መለወጥ ቻሉ:: አንዴ ቅዳሴ ሊገቡ ሲሉ "አባታችሁ ሊሞት ነው" ቢሏቸው "ሰማያዊው አባት ይቀድማል" ብለው ቀድሰዋል:: አባታቸውንም ቀብረውታል:: በመጨረሻ ግን አንድ ቀን ለመስዋዕት ብለው ያዘጋጁትን የበረከት ሕብስት እባብ በልቶባቸው አገኙ:: እንደ ምንም ፈልገው እባቡን ገደሉት::

ነገር ግን ያ የተባረከ ሕብስት በሆዱ ውስጥ ነበርና ምን ያድርጉት? ጌታን ስለ ማክበር ሊበሉት ፈልገው ጌታን ቢጠይቁት መልአኩ መጥቶ "ሰማዕትነት ሆኖ ይቆጠርላቹሃል" አላቸው:: ሁለቱ ወንድማማቾች ብዮክና ብንያሚን ፈጣሪያቸውን አመስግነው በሉት:: ምዕመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገቡ ሁለቱንም እንደተቃቀፉ ዐርፈው አገኟቸው:: መልካም እረኞቻቸው ናቸውና ከታላቅ ለቅሶ ጋር ቀብረዋቸዋል::

🕊 † ቅድስት ቅፍሮንያ ሰማዕት ወጻድቅት † 🕊

† ይህቺ ቅድስት እናታችን ደግሞ ገና በአሥራ ሁለት ዓመቷ ታላቅ እህቷን ተከትላ ገዳም ትገባለች:: በሚገርም ተጋድሎ በጥቂት ጊዜ አጋንንትን አሳፍራ መነኮሳይያትንም አስገርማቸዋለች:: ትጋቷ ግሩም ነበርና ስትታዘዝ : ስትጸልይና ስትሰግድ ያለ እንቅልፍና ምግብ ቀናት ያልፉ ነበር:: በዚህ የተቆጣ ሰይጣን አረማዊ መኮንንን ይዞባት መጣ::

ሌሎች ደናግል ሲያመልጡ እርሷ ለመከራ ተዘጋጅታ ጠበቀችው:: አዕምሮ የጎደለው መኮንኑም ክርስቶስን ካልካድሽ ብሎ ጽኑዕ ጽኑዕ መከራን አመጣባት:: በተጋድሎ ባለቀ አካሏ ሁሉንም ቻለች:: በዚህች ቀን ግን አንገቷን በሰይፍ አስቆርጧታል::

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የወዳጆቹን ትዕግስትና ጽናት ለእኛም ያድለን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::

🕊   † ቅዱስ ቶማስ    †    🕊

ዳግመኛ በዚህ ቀን ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ይታሰባል::
ይኸውም ከሕንድ አውራጃዎች በአንዱ ወንጌልን ሰብኮ እኩሎቹ ሲያምኑ እኩሎቹ እንቢ አሉ:: ቅዱስ ቶማስም ያመኑትን "ከጣዖት አምልኮና ከዝሙት ሽሹ" ብሎ መከራቸው::

ምክሩን ከሰሙት አንዱ በዚያው ምሽት ሊጠጣ ወደ መሸታ ቤት ይገባል:: ሰው ሁሉ ከወጣ በኋላ ባለ መሸተኛዋ ሴት እንደለመደችው አብረው እንዲተኙ ስትጠይቀው "እንዴት ሐዋርያው ከዝሙት ሽሹ እያለ እንዲህ ትይኛለሽ?" በሚል ሰይፍ አውጥቶ አንገቷን ቆረጣት::

እርሱ መልካም ያደረገ መስሎታል:: የሠራው ሥራ [መግደሉ] ግን አሕዛባዊ ግብር ነው:: በማግስቱ ቅዱስ ቶማስ ነገሩን ሰምቶ ሰዎችን ሰበሰበና "ይህንን የአውሬ ድርጊት የፈጸመ ማነው?" ሲል ጠየቀ:: ፈጻሚው ግን አልታወቅም በሚል ዝም አለ:: ወዲያው ቅዱሱ ሐዋርያ ዳቦ አንስቶ ቆረሰና "ለበረከት እያነሳችሁ ውሰዱ" አለ:: ሰውየው ተራውን ጠብቆ ሊያነሳ ሲል እጁ ሰለለች::

ሐዋርያው "ምነው ልጄ! ምን ሆንክ?" አለው:: እሱም እንዳላመለጠ ሲያውቅ እውነቱን ተናዘዘ:: ቅዱስ ቶማስ ግን ሕዝቡ ሁሉ እንደተሰበሰበ ያን ወጣት ገስጾ "አስከሬኑን አምጡልኝ" አለ::

የወጣቱን እጅ ፈውሶ "በል የገደልኩሽ እኔ:: የሚያስነሳሽ ግን ጌታየ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው:: ብለህ አንገቷን ቀጥለው" አለው:: እንዳለው ቢያደርግ የሞተችው አፈፍ ብላ ተነሳች:: ይህንን ተአምር ያዩ አሕዛብ አምነው ተጠምቀዋል::

††† ከሐዋርያው በረከት ይክፈለን::

🕊

[ † ሐምሌ ፩ [ 1 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ አግናጥዮስ ሐዋርያዊ ሰማዕት
፪. አበው ቅዱሳን ብዮክና ብንያሚን
፫. ቅድስት ቅፍሮንያ [ ሰማዕት ወጻድቅት ]
፬. ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
፭. አቡነ ገብረ መድኅን ጻድቅ
፮. አባ ክልዮስ ዘሮሜ

[ †  ወርኀዊ በዓላት ]

፩. ልደታ ለማርያም ድንግል እግዝእትነ
፪. ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፫. ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላእክት
፬. ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
፭. ቅዱስ ሚልኪ ትሩፈ ምግባር

" በዚያች ሰዓት ደቀ መዛሙርቱ ወደ ጌታ ኢየሱስ ቀርበው "በመንግስተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ይሆን?" አሉት:: ሕፃንም ጠርቶ በመካከላቸው አቆመ:: እንዲህም አለ :- "እውነት እላቹሃለሁ:: ካልተመለሳችሁ እንደ ሕፃናትም ካልሆናችሁ ወደ መንግስተ ሰማያት ከቶ አትገቡም:: እንግዲህ እንደዚህ ሕፃን ራሱን የሚያዋርድ ሁሉ በመንግስተ ሰማያት የሚበልጥ እርሱ ነው::" † [ማቴ. ፲፰፥፩]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
🙏2
#ወላዲተ__አምላክ

#ድንግል_ማርያም ወላዲተ አምላክ እነደሆነች ማመን #የኦርቶዶክሳዊነት መሠረት መለኪያ መስፈሪያ ጣምም ነው። ማንም ንጽሕተ ንጹሐን ቅድስተ ቅዱሳን #ድንግል_ማርያም ወላዲተ አምላክ እንደሆነች የማያምን ቢኖር #ከልዑል_እግዚአብሔር እቅፍ የወጣ ነው ሃይማኖትም የለውም"

#ቅዱስ_ጎርጎርዮስ_ነባቤ_መለኮት

              
#_ሰናይ__ቀን🙏

ለመቀላቀል 👇👇👇👇
@Enatachn_mareyam  
@Enatachn_mareyam
8🙏3
🕊

✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን።  ✞

[ ✞ እንኩዋን ለሐዋርያው ቅዱስ ታዴዎስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞ ]

🕊  †  ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ  †   🕊

ቅዱሳን ሐዋርያት አባቶቻችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በተከተሉበት ሰዓት እድሜአቸው በ፫ ደረጃ የተከፈለ እንደ ነበር የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ያሳያል::

¤ እንደ ዮሐንስ ወንጌላዊ ያሉት በ፳ ዎቹ ውስጥ:
¤ ቅዱስ ታዴዎስን የመሰሉት ደግሞ በ፴ ዎቹናና በ፵ ዎቹ ውስጥ የነበሩ ሲሆን
¤ እነ ቅዱስ ዼጥሮስ ደግሞ በ፶ ዎቹ ውስጥ የሚገኙ ነበሩ:: ደቀ መዛሙርቱ ከወጣቶችም: ከጐልማሶችም ከአረጋውያንም የተዋቀሩ ነበሩ ማለት ነው::

ቅዱስ ታዴዎስ በቀደመ ስሙ ልብድዮስ ይባል የነበረ ሲሆን በአንዳንድ መጻሕፍት ውስጥ [በተለይ በምሥራቅ ኦርቶዶክሶች] ስምዖን እና ይሁዳ እየተባለም ተጠርቷል::

ቅዱሱ ጌታችን ተከትሎ : -

¤ ከ፲፪ቱ አንዱ ሆኖ በፈጣሪው ተመርጦ:
¤ 3 ዓመት ከ፫ ወር ከጌታ እግር ተምሮ:
¤ በዕርገቱ ተባርኮ:
¤ በበዓለ ሃምሳም ፸፪ ልሳናትን ተቀብሎ:
¤ ሐዋርያት ዕጣ ሲጣጣሉ የበኩሉን አሕጉረ ስብከት ተካፍሎ ዓለምን ዙሯል::

ቅዱስ ታዴዎስ አንድ ቀን ከሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ዼጥሮስ ጋር ወደ አንዲት ሃገር ይገባሉ:: ታዲያ ለቀናት ያለ ምግብ ወንጌልን ሲሰብኩ ቆይተው ነበርና ደጐቹ ሐዋርያት ራባቸው:: ወደ ከተማዋ ሳይገቡ አንድ ሽማግሌ ሲያርስ አይተው ሰላምታን ሰጡትና "እባክህ እርቦናልና አብላን" አሉት:: እርሱም ምንም ወገኑ ከአሕዛብ ቢሆነ አሳዝነውት በሬዎቹን ሳይፈታ እየሮጠ ሄደ::

ያን ጊዜ ቅዱስ ታዴዎስ ሊቀ ሐዋርያትን "እርሱ እስኪመጣ ለምን አናርስም" አለው:: ፪ቱ ተነስተው ታዴዎስ ሞፈር: ዼጥሮስ ደግሞ ስንዴውን ያዘ:: ቅዱሳኑ እየዘሩ ያረሱት ሰውየው ምግብ ይዞ እስኪመጣ አድጐ: አፍርቶ: እሸት ሆኖ ቆየው::

ገበሬው የተደረገውን ተአምራት ባየ ጊዜ ደነገጠ:: ሊያመልካቸውም ወደደ:: እነርሱ ግን "እኛ የልዑል ባሮች ነን" ብለው በክርስቶስ ማመንን አስተማሩት:: "ልከተላችሁ" ቢላቸው "የለም! ከእሸቱ ይዘህ ወደ ከተማ ግባና ራት አዘጋጅልን:: እኛ እንመጣለን" አሉት::

እርሱ ወደ ቤቱ ሲመለስ አሕዛብ ነገሩን ተረዱ:: ተሠብሥበውም "እነዚህ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እሳትም ሰይፍም አይበግራቸውም" ብለው ወደ ከተማ እንዳይገቡ ከበሩ ላይ ራቁቷን የሆነች ዘማ አቆሙ::

ቅዱስ ታዴዎስ ገና ከርቀት ስላያት ቀና ብሎ ቅዱስ ሚካኤልን "እርዳን" አለው:: ሊቀ መላእክትም ድንገት ወርዶ ዘማዋን ሴት በጸጉሯ በዓየር ላይ ሰቀላት:: በከተማዋ ያሉ አሕዛብም ይህንና ሌሎች ተአምራትን አይተው ሁሉም በጌታችን አምነው ተጠመቁ:: ለሐዋርያቱም ሰገዱላቸው::

አንድ ቀን ግን አንድ ጐረምሳ ባለ ጠጋ ቅዱስ ታዴዎስ "ሀብት ንብረታችሁን መጽውቱ" ሲል ሰምቶት ዘሎ የሐዋርያውን ጉሮሮ አንቆ ከሞት አድርሶት ነበር:: ያን ጊዜ "ጌታየ! ለካ ሀብታም ከሚጸድቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል ያልክ ለዚህ ነው!" ብሏል:: ባለ ጠጋው "እንዴት ይሆናል?" ቢለው መርፌ አሠርቶ ግመሉን ከነ ባለቤቱ በሰው ሁሉ ፊት ፫ ጊዜ አሳልፎታል::

ያም ማለት ጌታችን እንዳለው "በሰው ዘንድ የማይቻለው በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል::" [ማር.፲፥፳፫]  በዚህ ምክንያትም ያ ክፉ ባለ ጸጋ ወደ ልቡናው ተመልሶ ከቅዱስ ታዴዎስ እግር ሥር ወደቀ:: ሐዋርያውም አለው "ሀብትህን ለነዳያን ስጥ:: ይህንንም በትር እንካና እየዞርክ ወንጌለ መንግስትን ስበክ::" ባለ ጸጋውም የተባለውን ሁሉ ፈጽሞ በክብር ዐርፏል::

ቅዱሳኑ ታዴዎስና ዼጥሮስ ግን በሃገሪቱ አብያተ ክርስቲያናትን አንጸው: ካህናትን ሹመው: ያቺን በዓየር ላይ የሰቀሏትን ዘማም የተባረከች መበለት አድርገው: በሌሎች አሕጉራት ወንጌልን ለማዳረስ ወጥተዋል::

ቅዱስ ታዴዎስም እስከ እርጅናው ድረስ ለወንጌል ሲተጋ ኑሯል:: ጌታችንም በየጊዜው በአካል እየተገለጸ አጽናንቶታል:: ከብዙ የድካምና የመከራ ዘመናት በሁዋላም በዚህች ቀን ዐርፏል::

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሱ ሐዋርያ በረከት ይክፈለን::

[ † ሐምሌ ፪ [ 2 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ [ከ፲፪ቱ ሐዋርያት]

[ † ወርኀዊ በዓላት ]

፩. ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
፪. ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
፫. ቅዱስ አቤል ጻድቅ
፬. ቅዱስ አባ ዻውሊ ገዳማዊ [ታላቁ]
፭. ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
፮. አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ

" ጌታ ኢየሱስም ዘወር ብሎ አይቶ ደቀ መዛሙርቱን "ገንዘብ ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግስት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል!" አላቸው:: ደቀ መዛሙርቱም እነዚህን ቃሎች አደነቁ:: ጌታ ኢየሱስም ደግሞ መልሶ "ልጆች ሆይ! በገንዘብ ለሚታመኑ ወደ እግዚአብሔር መንግስት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው! ባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግስት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል" አላቸው:: " [ማር.፲፥፳፫-፳፰]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
2025/07/08 21:56:44
Back to Top
HTML Embed Code: