Telegram Web Link
ሰኔ 21  ሰኔ ጐልጐታ ወሕንፀተ ቤተክርስቲያን
እንኳን ለእናታችን ለእመቤታችን ለቅድስተ ቅዱሳን ለድንግል ማርያም ሰኔ ጐልጐታና ሕንፀተ ቤተ ክርስቲያን (ለመጀመሪያ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ለታነጸበት) ክብረ በዓል በሰላምና በጤና አደረሰን አደረሳችሁ፡፡

‹‹ሰኔ ጐልጐታ ፤
ችግር የምትፈታታ፡፡››

ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያም በዚህች  ቀን (ሰኔ 21) ልጇን ወዳጇን ጐልጐታ በሚባል ቦታ ላይ እንባዋ እንደ ጅረት እስኪፈስ ድረስ ለኃጥአን ምሕረትን ለምናዋለች:: ጌታችንም ‹‹ስምሽን የጠራውን፤ በቃል ኪዳንሽ ያመነውን ሁሉ እምርልሻለሁ፡፡›› ብሎ ቃል ኪዳን ሰጥቷታል፡፡ ሰኔ ጐልጐታን ተመልከት

✤✤ ሕንፀተ ቤተ ክርስቲያን፤

ሰኔ 21 ከእመቤታችን #33ቱ በዓላት አንዱ ሲኾን፤ ሕንጸተ ቤተክርስቲያን ይባላል፡፡ በሐዲስ ኪዳን የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን በአምላክ እናት ስም የታነጸችው በዚሁ እለት በሰኔ 20 ቀን ነው፡፡
አናጺውም ደግሞ እራሱ ባለቤቱ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን፤ ቦታው በፊልጵስዩስ ነው፤ ቤተክርስቲያኗ የተሰየመችው ደግሞ በእመቤታችን ስም ነው፤ ጥንተ ነገሩስ (ታሪኩ) እንደምን ነው ቢሉ፤
ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና አምላካችን መደኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ‹‹ሑሩ ወመሐሩ ኵሎ አሕዛበ፤ አሕዛብን ሁሉ ሒዱና አስተምሩ፡፡›› /ማቴ. 28፥19/ ባላቸው ቃል መሠረት ሐዋርያት በወንጌል ያርሷት ዘንድ በዕጣ ተካፍለዋታል::

የሰው ልጅ ድኅነቱ የሚፈጸመው ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ሲቀበል ነውና (ዮሐ. 6፥ 56) አበው ሐዋርያት ቊርባንን በተመረጡ ሰዎች ቤት እያዘጋጁ ቀድሰው  ያቆርቡ ነበር:: በመጀመሪያ በጽርሐ ጽዮን፣ቀጥሎም በተለያዩ ሰዎች ቤት እንዲህ ይከናወን ነበር፡፡ ለጸሎት ሥራ ደግሞ አንዳንዴ ምኵራበ አይሁድን ይጠቀሙ ነበር:: እየቆየ ሲሔድ ግን ከአሕዛብ ያመኑ ሰዎች ቊጥር እጅጉን በመብዛቱ /በተለይ ቅዱስ ዻውሎስ ያሳመናቸው ለጸሎት እያሉ ወደ ጣዖት ቤት መግባት አመጡ::/ በዚህ ምክንያት መምህራን ሕዝቡን ‹‹ካመናችሁ በኋላ እንዴት ወደ ጣዖት ቤት ትገባላችሁ?›› ቢሏቸው ‹‹እኛ ምን እናድርግ! የምንጸልይበት ቤት የለን››ሲሉ መለሱላቸው:: ነገሩ ሲያያዝ ከደጋጉ ሐዋርያት ዻውሎስና በርናባስ ደረሰ:: ወዲያውኑ አንዳንድ ወንድሞች ቤት ‹‹ለምን አናንጽም?›› ብለው ነበር:: ቅዱስ ዻውሎስ ግን ‹‹ሊቀ ሐዋርያቱ ሳይፈቅድ አይሆንም›› አለ:: (ለዚህ ነው ዛሬም ሊቀ ዻዻስ ካልፈቀደ ቤተክርስቲያን የማይታነጸው፡፡) ከዚያ ቅዱሳን ዻውሎስና በርናባስ ሐዋርያቱ ወዳሉበት ሔደው ነገሩን ለቅዱስ ዼጥሮስ አስረዱ:: ሊቀ ሐዋርያቱ ቅዱስ #ዼጥሮስም ‹‹የጌታችን ፈቃዱመኾኑን እናውቅ ዘንድ ተያይዘን ሱባዔ እንግባ›› ብሎ አዋጅ ነገረ::

በዓለም ያሉ ክርስቲያኖች ሁሉ በአንድ ልብ ሱባዔ ገቡ:: በሱባዔያቸው መጨረሻም ክብር ይግባውና ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኪሩቤል ጀርባ ላይ ሆኖ እልፍ አእላፍ መላአክትን አስከትሎ በግርማ ወደ እነርሱ ወረደ፤እመቤታችን በቀኙ ነበረች፡፡ ኹሉንም ሐዋርያት በሩቅም በቅርብም ያሉትን ደቀ መዛሙርቱን በደመና ጠቅሶ ፊልጵስዩስ በሚባል ሃገር ሰበሰባቸው፡፡ ከዚያም በስተምሥራቅ ከከተማ ወጣ ወዳለ ሥፍራ ወሰዳቸው፡፡

በዚያም ተራርቀው የነበሩ 3 ደንጊያዎች ነበሩ፡፡ 3ቱንም ድንጋዮችን በተአምራት አቀራርቦ አንሥቶ ጎተታቸው፡፡ ድንጋዮቹም እንደሰም ተለጠጡ፣ እንደ ግድግዳም ሆኑ፡፡ ቁመቱን ወርዱን መጥኖ ለሐዋርያቱ ሰጣቸው፡፡
እነርሱም እሳት እንዳየው ሰም በእጃቸው እየለመለሙ (እየሳቡ) ቁመቱን 24፥ ወርዱን 12 ክንድ አድርገው ዕጽብት፥ ግርምት የምትኾን 3 ክፍል ያላትን የመጀመሪያዋን ቤተክርስቲያን በ52 ዓ/ም ሰኔ 20 ቀን አነጹ፡፡
ዳግመኛም የብርሃን ምሰሶ ወረደ፤ ጌታችንም በሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም አምሳያ አድርጎ አነጻት፤ ሁለንተናዋም ተጠናቀቀ፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ለሐዋርያቱ ‹‹እንግዲህ እናንተም እንዲህ አድርጋችሁ ሥሩ፡፡›› ብሏቸው ዐረገ፡፡

✜ በማግስቱ ሰኔ 21 ዕለት ደግሞ ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አእላፍ መላእክትን፣ ሰማያውያን ቅዱሳንን እና እናቱን ቅድስት ድንግል ማርያምን ይዞ ወረደ:: ሐዋርያቱ አብዛኞቹ እዛው ሲጸልዩ አድረው ነበርና ጌታችን ከቅዳሴው በፊት 2 ነገሮችን አሳየ፤ አስቀድሞ ቤተክርስቲያኗን በድንግል እናቱ ስም አክብሮ ሥርዐተ ቤተክርስቲያንን አሳየ:: ቀጥሎ ደግሞ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስን ከመካከል አቁሞ ‹‹አርሳይሮስ›› ሲል ሾመው:: ይኼውም የዓለም ሁሉ ሊቀ ዻዻሳት (ፓትርያርክ) ማለት ነው:: በዚህ ጊዜ ቅዱሳን መላእክት ‹ ‹‹አክስዮስ››(አክዮስ)እያሉ 3 ጊዜ አሰምተው ጮሁ:: አክዮስ ማለት በግዕዙ ‹‹ይደልዎ›› በአማርኛው ደግሞ ‹‹ይገባዋል፤ ያስምርለት›› እንደ ማለት ነው::

ጌታችን ይህን ከከወነ በኋላ ይቀድስ ዘንድ ጀመረ:: አማናዊት ማኅደሩን ድንግል ማርያምን መንበር አድርጎ፣ ቅዱስ ጴጥሮስ እንደ ተራዳኢ ካህን ቆሞ፣ ቅዱስ እስጢፋኖስ ሠራኢ ዲያቆን ኾኖ፣ ሐዋርያት ድንግልን ከበው፣ መላእክተ ብርሃን በክብራቸው ቆመው ጌታችን ቀድሶ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለወዳጆቹ አቀበለ::
በዚያች ዕለት በፍጡር አንደበት ተከናውኖ ሊነገር የማይችል ደስታ ተደረገ:: ከቅዳሴ በኋላ ጌታችን ሐዋርያትን አዘዛቸው:: ‹‹ከዚህ ቀን ጀምሮ በመላው ዓለም በእናቴ በማርያም ስም አብያተ ክርስቲያናትን አንጹ፤ ይህችን  እለት የሚያከብራትን አከብረዋለሁ::›› ብሏቸው ከድንግል እናቱና ከመላእክቱ ጋር ዐረገ::

✤✤ ሥርዐተ ማኅሌቱ እንደየደብራችሁ ይትበሃል ትጠሙበበት ዘንድ የሁለቱንም (የላይ ቤት የግምጃ ቤትና የታች ቤት የበአታን) አብነት አስቀምጠንላችኋል፤ በቢጫ የተቀለመው የላይ ቤት (የግምጃ ቤት) አብነትን ለምትከተሉ አድባራት ሲኾን፤ ሰማያዊ የተቀለመው ደግሞ የታች ቤትን (የበዓታን) የአቋቋም ይትበሃል ለምትጠቀሙ ሲኾን፤ ሁለቱም የላይ ቤቱና ያየታች ቤቱ የሚተባበሩበት ላይ ደግሞ ዘግምጃ ቤት ወዘበዓታ ብለን በፈዛዛ ጥቁር አስቀምጠንላችኋል፡፡ መልካም ማኅሌት፨

ኦ አበው ወእማት አኃው ወአኃት ኢትርስዑነ በጸሎተክሙ (በዘጸለይክዋ በዝንቱ ሥርዐተ ማኅሌት) ለትምህርተ ቤትነ ቀ.ደ.ሰ.መድኀኔዓለም ወደ.ት.ቅ.ገብርኤል ፍኖተ ሕይወት፡፡
✼ የድንግል እመቤታችን ልመናዋ ክብሯ፣ ጣዕመ ፍቅሯና በረከቷ በሁላችን ላይ ይደርብን::
@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
2025/06/27 16:43:23
Back to Top
HTML Embed Code: