Telegram Web Link
ጎተራ አካባቢ ሊፈርስ መሆኑ ተሰማ

በአዲስ አበባ ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ውስጥ የሚገኘውና በተለምዶ ጎተራ ተብሎ የሚጠራው ሰፈር ሊፈርስ መሆኑን ዘሪፖርተር እንግሊዘኛ ጋዜጣ ዛሬ ባቀረበው ዘገባ አስታውቋል፡፡ ‹‹አዲስ ቱሞሮው›› በሚል ፕሮጀክት የከተማው አስተዳደር ለሚያስገነባው ልዩ የኢኮኖሚ መንደር አካባቢውን ለማፍረስ መታቀዱንም አስረድቷል፡፡

ፕሮጀክቱ በአዲስ አበባ ከንነቲባ አዳነች አቤቤና በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የሚመራ እንደሆነ የጠቀሰው ዘገባው የከተማው አስተዳደር መንደሩን ለመገንባት ከቻይናው የኮሚኒኬሽንና ኮንትራክሽን ድርጅት ጋር ስምምነት መፈፀሙን አስታውቋል፡፡ መንደሩ የንግድ፣ የፋይናንስ፣ የትምህርት፣ የባህልና ሰማይ ጠቀስ የመኖሪያ ህንፃዎች እንደሚኖሩት መገለፁን ያስረዳው ዘገባው በመሆኑም በጎተራ አካባቢ በሚገኝ ሰፊ መሬት ላይ ለመስራት እንደታሰበ ጠቅሷል፡፡ የአዲስ ቱሞሮው መንደር ግንባታ በቢሊዮን የሚቆጠር ብር እንደሚፈጅ አስረድቶም ከዚህም በላይ በጎተራ አካባቢ የሚኖሩ በርካቶችን እንዲፈናቀሉ እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኮሪደር ልማትና በጫካ ፕሮጀክት ፕሮጀክቶች አማካኝነት በመቶ ሺ የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተፈናቅለው ወደተለያዩ አካባቢዎች እንዲሰፍሩ የተደረገ ሲሆን በዚህኛው ፕሮጀክትም በርካታ ነዋሪዎች ተመሳሳይ እጣ እንደሚገጥማቸውም አስታውቋል፡፡
👍2
በሰይፉ የዩትዩብ ቻናል ሲተላለፍ የነበረው የመቄዶንያ የገቢ ማሰባሰብያ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ ተጠናቀቀ፡፡

ከየካቲት 01 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በሰይፉ በኢቢኤስ እና በሰይፉ ሾው ዩቲዩብ ቻናል ላይ እየተደረገ በቆየው የቀጥታ ስርጭት የገቢ ማሰባሰብያ መርሃ ግብር ላይ የመጀመሪያው ዙር የገቢ ማሰባሰብ የቀጥታ ስርጭት ግቡን በማሳካት ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ በይፋ ተጠናቀቀ፡፡

መቄዶንያ የአረጋዊያን እና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል  በአዲስ አበባ እያስገነባ ለሚገኘው የአረጋውያን መኖሪያና ዘመናዊ ሆስፒታል አጠቃላይ የፊኒሺንግ ስራውን ለማጠናቀቅ 5 ቢሊዮን ብር  እንደሚያስፈልግ በመግለፅ ከየካቲት 01 ቀን 2017  ጀምሮ የመጀመሪያ ዙር የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት 1 ቢሊየን ብር ለማሰባሰብ ዕቅድ በመያዝ በseifu on ebs እና በ Seifu Show ዩቱብ ቻናል ላይ በመጀመር ላለፉት ሶስት ወራት (90 ቀናት) በቆየው ገቢ ማሰባሰብ ፕሮግራም ላይ የታሰበውን እቅድ በማሳካት አጠቃላይ በገንዘብ እና በአይነት ከ 1 ቢሊየን ብር በላይ በማሰባሰብ በሰይፉ ዩቱዩብ ቻናል የተደረገው የመጀመሪያ ዙር የገቢ ማሰባሰብ ግንቦት 01 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ ተጠናቋል፡፡

ይህ የገቢ ማሰባሰብ ፕሮግራም የተካሄደበት Seifu on EBS እና Seifu Show ዩቱዩብ ቻናል በቀጥታ ስርጭትና በማስታወቂያ ገቢ የተገኘ ብር 4,032,585.63 ለመቄዶኒያ ገቢ የተደረገ ሲሆን በመዝጊያ ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት የመቄዶንያ የአረጋዊያን እና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል መስራች የክብር ዶክተር ቢኒያም በለጠ ላለፉት ሶስት ወራት ሲደረግ በቆየው ዝግጅት ላይ የተሳተፉትን በሙሉ በማመስገን ለዚህ ዝግጅት ዋናውን ሚና ሃላፊነት በመውሰድ የ1 ቢሊየን ብር ግብ እንዲሳካ ላደረገው ለሰይፉ ፋንታሁን ምስጋና በማቅረብ የምስጋና የምስክር ወረቀት የተበረከተ ሲሆን እንዲሁም በመቄዶኒያ በሚገኙ ተረጂዎች በእጅ ጥበብ የተሰራ ጋቢ ለሰይፉ ፋንታሁን እና ለአርቲስት ይገረም ደጀኔ ያለበሱ ሲሆን በአረጋውያኑ ምርቃት በመታጀብም በሰይፉ ፋንታሁን ምስል የተቀረፀ ምስለ ቅርፅ በስጦታ አበርክተዋል፡፡

በዚህ  በሰይፉ በኢቢኤስ እና በሰይፉ ሾው ዩቲዩብ ቻናል በቀጥታ ስርጭት ላለፉት ሶስት ወራት በዘለቀው እና ለተመካቾች በደረሰ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር  ፣ ከተለያዩ የሀይማኖት ተቋማት የመጡ መምህራን፣ የኪነ ጥበብ ሰዎች ፤ የተለያዩ የመንግስት እና የግል ተቋማት ፤ ባንኮች እና የሚዲያ ባለሞያዎች መድረኩን በማድመቅ ልግስና በመስጠት እና ለጋሾችን በማበረታታት አብረውን ቆይተዋል። አሁንም በመቄዶንያ ዩቱዩብ ቻናል የቀጥታ ስርጭት የገቢ ማሰባሰቢያ እንደቀጠለ ነው ተብሏል።
👍1
በስልኩ ምክንያት አንገቱን ማንሳት ያቃተው የ25 ዓመቱ ጃፓናዊ

ለቀናት የሞባይል ስክሪን ማየትን በመልመዱ ይህ ወጣት "የወደቀ ጭንቅላት ሲንድሮም" ተብሎ በሚታወቅ በሽታ ተይዟል።

ከባድ የአንገት ህመም፣ ምግብን መዋጥ ፣መቸገር ፈጣን የክብደት መቀነስ እንዲሁም ከጭንቅላቱ ጀርባ ላይ እብጠት አጋጥሞት ነበር።

አንገቱን ወደነበረበት መመለስ የቻሉት የአከርካሪ አጥንቱን በሚጠግኑ ብሎኖች አማካኝነት ብቻ ነበር።
🥰1
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከዛሬ ጀምሮ የወሰዳቸው የለውጥ እርምጃዎች ……

1. ለአስመጪዎች የቅድመ ክፍያ (አድቫንስ ፐይመንት) መጠንን ከ5 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ወደ 50 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ከፍ ተደርጓል።

2. ለውጭ ሀገር ተጓዦች የሚፈቀደውን የውጭ ምንዛሪ ጥሬ ገንዘብ መጠን 10 ሺህ የአሜሪካ ዶላር፣ ለንግድ ሥራ መንገደኞች ደግሞ 15 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ሆኗል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ የውጭ ምንዛሪ የባንክ ሂሳብ ያላቸው ግለሰቦች ከሂሳባቸው ላይ በካርድ መጠቀም የሚችሉት የውጭ ምንዛሪ መጠን ከ10 በመቶ ወደ 20 በመቶ ከፍ እንዲል ሆኗል፡፡

3. የባንኮችን የውጭ ምንዛሪ ክፍያዎችን ሥርዓት ለማስያዝ በማሰብ ባንኮች ከገቢ ንግድ፣ ከአገልግሎት ክፍያ ወይም ከጥሬ ገንዘብ ጋር በተያያዘ ለውጭ ምንዛሪ አገልግሎት የሚያስከፍሏቸው ማናቸውም አስተዳደራዊ ወጪዎችና ክፍያዎች ከግንቦት 18፣ 2017 ጀምሮ ከ4 በመቶ እንዳይበልጡ ተወስኗል፡፡
👍1
የምርጫ ቦርድ ዕጩ አባላት መልማይ ኮሚቴ ስድስት ዕጩ አባላትን ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የስራ አመራር ቦርድ እጩ አባላት መልማይ ኮሚቴ በዛሬው ዕለት ስድስት ዕጩ አባላትን ይፋ አድርጓል፡፡

የመልማይ ኮሚቴው ሰብሳቢ ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንደገለፁት፤ ከሚያዚያ 1 ቀን 2017 ጀምሮ ለተከታታይ 21 ቀናት በስልክ፣ በፖስታ እና በኢሜል ከቀረቡት 168 ተጠቋሚዎች በሦስት የማጣሪያ ምዕራፎች ስድስት ዕጩ አባላት ተለይተዋል።

በዚሁ መሰረት ኮሚቴው አቶ ተስፋዬ ነዋይ፣ አቶ ተክሊት ይመስል፣ ወይዘሮ ነሲም አሊ፣ ወይዘሮ ዳሮ ጀዋል፣ ወይዘሮ ፍሬህይወት ግርማ እና ዶክተር ያሬድ ሀይለማርያምን በዕጩነት መርጧል፡፡

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዕጩ አባላት መልማይ ኮሚቴው የመረጣቸውን ስድስት አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚልክና ለቦታው የሚፈለጉት የመጨረሻዎቹ ሦስት ሰዎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚለዩ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሲሚንቶ ምርት 20 ሚሊዮን ቶን ደረሰ

የማዕድን ሚኒስትሩ ሀብታሙ ተገኝ የነባር ፋብሪካዎችን ምርታማነት በማሳደግና አዳዲሶችን ወደ ሥራ በማስገባት ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ ለጎረቤት ሀገራት ሲሚንቶ ማቅረብ የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ ነው ብለዋል።

አክለውም አራት የድንጋይ ከሰል ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ወደ ሥራ በማስገባት የሲሚንቶ አምራቾችን አቅም የማሳደግ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የግብዓት አቅርቦት ምላሽ ለመስጠት በብረት፣ እምነ በረድ፣ ሲሚንቶና ሌሎች መስኮች እደገቶች እየተመዘገቡ እንደሆነም ተናግረዋል።

በድሬዳዋ ከተማ የተገነባው የፓዮኔር ሲሚንቶ ማኑፋክቸሪንግ ማስፋፊያ ፕሮጀክት በትናትናው እለት በፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ተመርቆ ተከፍቷል፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔትያናሁ ሃማስ ታጋቾችን በሙሉ ለቆ ትጥቁን የሚፈታ ከሆነ ሀገራቸው በጋዛ የጀመረችውን ዘመቻ ልታቆም እንደምትችል አስታወቁ።

ኔትያናሁ ይህን ያሉት እንግሊዝ ፣ ፈረንሳይ እና ካናዳ እስራኤል በጋዛ የጀመረችውን አዲሱን ዘመቻ እንድታቆም ማስጠንቀቂያ ከሰጡ በኋላ ነው።

የብሪታንያው ጠቅላይ ሚንስትር ኪር ስታርመር ፣ የፈረንሳዩ ፕሬዚደንት ኢማኑኤል ማክሮን እና የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ማርክ ካኒ እስራኤል በጋዛ ሰርጥ የጀመረችውን አዲሱን ዘመቻዋን ካላቆመች ማዕቀብ ሊጥሉ እንደሚችሉ በጋራ ባወጡት መግለጫ አስጠንቅዋል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔትያናሁ ለመሪዎቹ በሰጡት ምላሽ ግን "ምዕራባዉያን የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን መንገድ ተከትለው እስራኤልን ቢደግፉ ይሻላል" ብለዋል።

እስራኤል በጋዛ ሰርጥ የጀመረችውን ዘመቻ ለማቆምም "ሐማስ የቀሩ ታጋቾችን ከለቀቀ፣ ትጥቁን ከፈታ እና መሪዎቹ ጋዛን ለቀው የሚሰደዱ ከሆነ ብቻ ነው " ፤ ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል ለኢራን ሲሰልሉ ነበር ያለቻቸው ሁለት ዜጎቿን በቁጥጥር ስር ማዋሏን አስታዉቃለች።

የእስራኤል የደህንነት ባለስልጣናት እንዳሉት ሁለቱ የ24 ዓመት ዕድሜ እንዳላቸው የተነገረላቸው እስራኤላዉያን ወጣቶች ከኢራን ተልዕኮ ተቀብለው በእስራኤል ምድር ሲሰልሉ ነበር ።

በጣቶቹ በተለይ በደቡባዊ እስራኤል በሚገኙት የክፋር አሂም ማህበረሰብ ውስጥ የእስራኤሉን የመከላከያ ሚኒስቴር እስራኤል ካትስን ስም የማጥላላት ክስም ቀርቦባቸዋል።

ወጣቶቹ ከኢራን ባለስልጣናት ተሰጣቸው በተባለው ተልዕኮ መሰረት በማህበረሰቡ ውስጥ በቀጥታ የቪዲዮ ስርጭት ሚኒስትሩን ሲሳደቡ እና ሲያጥላሉ ተደርሶባቸዋል ነው የተባለው።

በቅጥጥር ስር ስለዋሉ ወጣቶች እና ስለቀረበባት ክስ ግን ኢራን ያለችው ነገር የለም።
የአውሮፓ ህብረት በሶሪያ ላይ ተጥለው የነበሩ ማዕቀቦችን ማንሳቱን አስታወቀ

ህብረቱ ከጦርነት ማግስት ላይ የምትገኘው ሶሪያ ማገገም እንድትችል በሚል ከዚህ ቀደም የጣላቸውን ሁሉንም ኢኮኖሚያዊ ማዕቀቦች ማንሳቱን አስታውቋል።

ይህ የአውሮፓ ህብረት ውሳኔ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባሳለፍነው ሳምንት በሀገሪቱ ላይ የጣሉትን ማዕቀብ እንደሚያነሱ ማስታወቃቸውን ተከትሎ የመጣ ነው ተብሏል።

የሶሪያ አዲሱ መሪ አሕመድ አልሻራ ሶሪያን ዳግም ለመገንባት ኢኮኖሚያዊ ማዕቀቦች እንዲነሱላቸው ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

ማዕቀቡን ለማንሳት የተደረሰው መግባባት ከዓለም ስርዓተ የተገፉትን የሶርያን ባንኮችን ያማከለ ሊሆን እንደሚገባ የህብረቱ ዲፕሎማቶች ለሮይተርስ ተናግረዋል።

የቀድሞ የአሳድ አስተዳደር ላይ ተጥለው የነበሩ ማዕቀቦች ይቀጥላሉ ተብሏል ።

አዲሱ የሶሪያ አስተዳደርም ቃሉን ማክበር ካልቻለ እና መብት ማስከበር ካልቻለ ማዕቀቦቹ ዳግም ሊጣሉ እንደሚችሉ ተነግሯል።
👍1
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፤ የጉባኤ አባላቶቹን ይፋ አድርጓል

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ላለፉት አስራ አራት ዓመታት ሰባት የሃይማኖት ተቋማትን በአባልነት በማቀፍ ሲሰራ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
ሆኖም ጉባኤው በቅርቡ ባደረገው የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ የአባል የሃይማኖት

ተቋማቱን ፍላጎት፣ ጉባኤው የደረሰበትን የእድገት ደረጃ እና ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታውን በማገናዘብ የጉባኤውን መተዳደሪያ ደንብ ለሶስተኛ ጊዜ በማሻሻል የአሰራር እና የአደረጃጀት ማስተካከያ ማድረጉን አስታውቋል።
በዚህም መሰረት፦

1ኛ/ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፤

2ኛ/ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፤

3ኛ/ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፤

4ኛ/ የኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል እና

5ኛ/ የኢትዮጵያ የሰባተኛው ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን የጉባኤው አባል እንዲሆኑ

ማድረጉን የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ አስታውቋል።
የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ የትግራይ ክልልን ጎበኙ

የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ዛሬ ወደ ትግራይ ክልል አቅንተው ከተለያዩ የክልሉ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል። በአምባሳደሩ ጉብኝት ወቅት የጸጥታ፣ ፖለቲካዊ፣ ሰብዓዊ ጉዳዮች፣ የፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት አተገባበርና ቀጠናዊ ጉዳዮች በውይይቱ ዋነኛ ትኩረት ነበሩ።

ከክልሉ አመራሮች ጋር የተደረገ ውይይት
አምባሳደር ማሲንጋ ከሕወሓት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል፣ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት አማኑኤል አሠፋ እና ከጸጥታ ኃይሎች ከፍተኛ አዛዦች ጋር ሰፊ ውይይት አድርገዋል።

የውይይቱ ዋና ዓላማ በክልሉ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ መገምገም እና ለዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት የሚረዱ መፍትሄዎችን መፈለግ እንደነበር ተገልጿል።

የሽሬ የተፈናቃዮች መጠለያ ጉብኝት

አምባሳደሩ በጉብኝታቸው ወቅት የሽሬውን የተፈናቃዮች መጠለያ ጎብኝተዋል። ከአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ጋር በሽሬ የተፈናቃዮች መጠለያ ከተፈናቃዮች ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ዕርዳታ መስጠት ዘላቂ መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል እና መፍትሄው ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው መመለስ እንደሆነ የክልሉ ዜና ምንጮች ዘግበዋል።

አምባሳደሩ፣ ተፈናቃዮቹ ወደ ቀያቸው ተመልሰው ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው መረዳታቸውን ተናግረዋል።

ይህ የአምባሳደሩ ጉብኝት በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ በቅርበት ለመመልከት እና ለአሜሪካ መንግስት ተጨማሪ መረጃዎችን ለማቅረብ ያለመ እንደሆነ ይጠበቃል።
👍1
ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የድንበር ፀጥታን ለማጠናከር ተወያዩ

ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የቀጠናውን መረጋጋት ለማጠናከር፣ ትብብርን ለማስፋት እና በድንበር ላይ የጋራ የፀጥታ ጥረቶችን ለማጎልበት ያለመ የከፍተኛ ደረጃ የሁለትዮሽ ውይይት በድንበር ከተማዋ ጋቢሌይ አካሂደዋል።

የልኡካን ቡድኖች

ውይይቱ በሁለቱም ወገኖች ከፍተኛ ባለስልጣናት የተመራ ሲሆን፤ የኢትዮጵያን ልኡክ የመከላከያ ሰራዊት ስምሪት ኃላፊ ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው፣ የሶማሌ ክልል ፖሊስ አዛዥ ጄኔራል አብዲ አሊ ሲያድ እና የምስራቅ እዥ ምክትል አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ፍቃዱ ተሳትፈዋል።

በሶማሊላንድ በኩል ደግሞ የሶማሊላንድ ብሔራዊ ጦር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ኒምካን ዩሱፍ እና የሶማሊላንድ ፖሊስ ኃይል አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል አብዲራህማን አብዲላሂ ሀሰን ከከፍተኛ ወታደራዊ እና የፖሊስ መኮንኖች ጋር በመሆን ተገኝተዋል።

የውይይቱ ትኩረት

ሆርን ዲፕሎማት እንደዘገበው፣ የፀጥታ ውይይቱ ቅድሚያ በሚሰጣቸው የጋራ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲሆን ይህም የጋራ አሠራሮችንና የመረጃ ትብብርን ማጠናከር እና ሰላማዊ ድንበር ተሻጋሪ ግንኙነቶችን መደገፍን ያካትታል።

በተጨማሪም ሁለቱም ልኡካን ሰላምን ለማጽናት እና ሊከሰቱ የሚችሉ የፀጥታ ስጋቶችን ለመከላከል ቀጣይነት ያለው ስትራቴጂካዊ ትብብር ያለውን ጠቀሜታ አፅንዖት ሰጥተዋል።

በሁለቱ አካላት መካከል ያለውን መተማመን እና የአሠራር ዝግጁነት ለማጠናከር መደበኛ ስብሰባዎች አስፈላጊ መሆኑ ላይ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል። ቀጣዩ ዙር ውይይት በሶማሊላንድ ዋና ከተማ ሀርጌሳ ለማካሄድ ቀጠሮ ተይዟል።
የትግራይና ኦሮሚያ ጤና ማህበራት ለጤና ባለሙያዎች ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ጠየቁ

የጤና ባለሙያዎች የጀመሩት የስራ ማቆም አድማ ስምንተኛ ቀኑን በያዘበት በአሁኑ ወቅት፣ የትግራይ እና ኦሮሚያ ክልሎች ጤና ማህበራት መንግስት ለጤና ባለሙያዎች ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ጠየቁ።

የትግራይ ህክምና ማህበር ያቀረበው አቤቱታ

የትግራይ ህክምና ማህበር ግንቦት 10 ቀን 2017 ዓ.ም. (ሜይ 18፣ 2025) ለጤና ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ፣ መንግሥት ለጤና ባለሙያዎች ጥያቄና መብት ተገቢውን ትኩረትና ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የጤና ባለሙያዎችን ጥያቄ በመጣስ ተገቢ ያልሆነ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አስታውቋል።

ማህበሩ እነዚህ የታሰሩ የሞያ አጋሮቻቸው እንዲፈቱ አስፈላጊውን ጫና እንዲደረግ ሲል ለጤና ሚኒስቴር አሳስቧል። በተጨማሪም፣ ሁሉም የሞያ ማህበራት እና ጤና ባለሙያዎች ችግሮቹን ለመፍታት ግልጽና ሁሉን ያሳተፈ ውይይት እንዲደረግ ጠይቋል።

የኦሮሚያ ሐኪሞች ማኅበር ድጋፍ

በተመሳሳይ፣ የኦሮሚያ ሐኪሞች ማኅበር ትናንት ግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም. (ሜይ 19፣ 2025) ባወጣው መግለጫ፣ "የጤና ባለሙያው የሚገባውን ለመስጠት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ አይፈቅድም ቢባል እንኳን እየተራበ እንዳያገለግል፣ እየተጠማ እንዳይማር፣ እየታመመ ማስታገሻ እንዳያጣ የሚያደርግ የኑሮ ሁኔታ እንዲፈጠርለት ሲታገል ቆይቷል" ሲል አውግዟል። ማህበሩ አሁን ላይ በጤና ባለሙያዎቹ እየተነሱ የሚገኙ ጥያቄዎችን እንደሚደግፍ ገልጾ፣ እየተፈጠረ ያለው ሁኔታ ተባብሶ ጉዳት ከማስከተሉ በፊት ውይይቶች እንዲደረጉና እርምጃዎች እንዲወሰዱ ጠይቋል።

የጤና ባለሙያዎች የስራ ማቆም አድማ በአገሪቱ የጤና አገልግሎት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ቀጥሏል።
1
2025/07/10 08:48:41
Back to Top
HTML Embed Code: