Telegram Web Link
"ወር በገባ በ2 ፃድቁ ኢዮብ ነው::

       #አመሰጋኝ🙏
ኢዮብ- በጤናው አመሰጋኝ ነበር::
ኢዮብ-በበሸታውም አመሰጋኝ ነበር::
ኢዮብ-ሀብት እና ንብረት ሞልቶት አመሰጋኝ ነበር::
ኢዮብ-ልጆቹ አልቀውበትም አመሰጋኝ ነበር::
ኢዮብ-ሚሰቱ ከድታው አመሰጋኝ ነበር::
ኢዮብ-ዘመዶቹ ፊት ነሰተውት  አመሰጋኝ ነበር::
ኢዮብ-ቀን እና ሌሊት ተፈራርቀውበት ሲነጋ መቸ ነው  የሚመሸው ሲመሸ መቸ ነው የሚነጋው እያለ ሰውነቱን ትል እያፈላ አመሰጋኝ ነበር::
ኢዮብ-እንዴት  አደርክ ሲሉት  እግዚአብሔር ይመሰገን ነው የሚለው::
ታጋሸ እንደ ኢዮብ እንድንሆን ዘንድ ፈጣሪ ይርዳን በማግኘት እና በማጣት  አመሰጋኞች እንድንሆን ዘንድ አምላክ ማሰተዋሉን ያድለን::

የኢዮብን እምነትና ፅናት ትግሰት እንደ ኢዮብ ያድለን::🙏
🌹#አባ_ሕርያቆስ 🌹

☞ወር በገባ በ2 የእመቤታችን ወዳጅ የቅዳሴ ማርያም ደራሲ የአባ ሕርያቆስ ወርሐዊ መታሰቢያው ነው፡፡ ሕርያቆስ ማለት ኅሩይ ረቂቅ ፀሓይ ብርሃን ማለት ነው፡፡ሀገሩ በብህንሳ ነው፡፡ በ10'000 መነኮሳት ላይ ተሹሟል፡፡ግብረ ገብ ነውናሥርዐት ያጸናባቸዋል፡፡ ነገር ግን ያልተማረ ነውና ይንቁታል፡፡ እሱ ግን እንደ ጠሉኝልጥላቸው እንደ ናቁኝ ልናቃቸው ሳይል በፍቅር በትሕትና ጸንቶ ያስተምራቸውጀመረ፡

☞ከዕለታት አንድ ቀን በምን ምክንያት እንሻረው ብለው መከሩ፡፡ ቅዳሴ ቀድሰኽ
አቁረበን ብለን የሚያስቸግር ቅዳሴ ሰጥተን በዚህ ምክንያት እንሽረዋለን ብለው
ወሰኑ፡፡
☞እሱ ግን እንደ ቅዱስ ኤፍሬም የእመቤቴ ምስጋና እንደ ባሕር አሸዋ በዝቶልኝ
እንደ ልብስ ለብሼው እንደ ምግብ ተመግቤዎ እንደ ውሃ ጠጥቼው እያለ ይመኝ
ነበርና ሥርዐቱን ጨርሶ ፍሬ ቅዳሴ ሲደርስ ከሊቃውንት የሚያስቸግር እያሉ
ሲያወጡ ሲያወርዱ ጉሥዐ ልብየ ቃለ ሠናየ ብሎ ወይእዜኒ ንስብሖ እስከ
ሚለው ድረስ ሰተት አድርጎ ተናግሮታል፡፡
☞የሚጠሉትና የሚንቁት የነገሩትን አከናውኖ መናገር የማይችል ዛሬስ እንግዳ
ድርሰት እደርሳለኹ ብሎ እንዳገኘ ይቀባጥራል ብለው አቃለሉበት፡፡
☞የሚወዱትና የሚያከብሩት ደግሞ ከመንፈስ ቅዱስ ካልኾነ ከዕሩቅ ብእሲ
እንዲኽ ያለ ምስጢር አይገኝም በማለት ጽፈው ደጉሰው ከውሃ ቢጥሉትብራናው
ሳይፋቅ ከእሳትቢጥሉት ሳይቃጠል ወጣ፡፡ ከሕሙማን ላይ ቢጥሉት ድውይ
ፈወሰ፡፡ የበለጠ ደግሞ ሙት አስነሳ፡፡
☞ይህስ ደግ ድርሰት ነው ብለው ከቅዳሴ ድረስት መካከል 14ኛ አድርገው
ጠርዘውታል፡፡፡፡
☞አባ ሕርያቆስ ተሹሞ ሳለ ብዙ ድርሰት ብዘ ተግሣፅ ጽፏል፡፡ ከብዙም ቅዳሴ
ማርያምና ላሐ ማርያም ተጠቃሽ ናቸው፡፡
☞እመቤታችን ቅዱስ ኤፍሬምን ከሶርያ አንተ ውዳሴዬን አባ ሕርያቆስን ከብሕንሳ በደመና ነጥቃ  አንተ ቅዳሴን ንገሩት ብላ ቅዱስ ያሬድ በዜማ ደረሶላቸዋል፡፡
☞የቅዱስ አባ ሕርያቆስ ድርሰት የሆነው ከ14
ቅዳሴ አንዱ የሆነው" ቅዳሴ ማርያም" ብለው ሰየሙት፡፡
☞(ከመድብለ ታሪክ መጻሐፍ የተወሰደ)
☞ለአባ ሕርያቆስ፤ለቅዱስ ኤፍሬም፤ለቅዱስ ያሬድ፤ለአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
የተመነች ለእኛም ትለመነን፡፡ ማስተዋሉን ታድለን
🌹#አባ ጉባ ማለት📌

📌#ወር በገባ  በ2 ፃድቁ አባ ጉባ ከዘጠኙ ቅዱሳን አንድ ናቸው#አባ ጉባ🌹••• ጻድቁ የተወለዱት ታሕሳስ 29 ቀን በ336 ዓ/ም በመንፈቀ ሌሊት ነው:: አባታቸው ጌርሎስ : እናታቸው ቴዎዶክስያ ደጐች ነበሩ::አባ ጉባ ("ባ" ጠብቆ ይነበብ) በተወለዱ ቀን ጌታችን ከመላእክቱ ጋር በመውረዱ ቤታቸው ለ7 ቀናት በብርሃን ተሞልቶ ነበር:: ሕጻኑ ጉባም ፈጣሪያቸውን "ሃሌ ሉያ" ብለው አመስግነዋል::

በልጅነታቸው መጻሕፍትን አጥንተው : ወደ ገዳመ አስቄጥስ ገብተው መንነዋል:: ለበርካታ ዓመታት ከተጋደሉ በኋላ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል "ወደ ቅድስት ሃገር ኢትዮዽያ ሒድ" ብሏቸው ከ8ቱ ቅዱሳን ጋር ወደ ሃገራችን መጥተዋል:: በወቅቱ ዕድሜአቸው ከ140 በላይ ነበር::

ጻድቁ አባ ጉባ እንደመሰሎቻቸው በስብከተ ወንጌል : መጻሕፍትን በመተርጐም : ገዳማትን በማስፋፋትና አብያተ ክርስቲያናትን በማነጽ ቆይተዋል:: በተለይ ራማ ኪዳነ ምሕረት የእርሳቸው ናት ይባላል::

ጻድቁ ቅዳሴ ሲቀድሱ ከመሬት ከፍ ብለው ነበር:: ብዙ ጠበሎችን አፍልቀው ድውያንን ፈውሰዋል:: ሙታንንም አንስተዋል:: እመቤታችንም የብርሃን መስቀል ሰጥታቸዋለች:: ጻድቁ ከበርካታ የቅድስና ዘመናት በኋላ በዚህች ቀን ዐርፈው በገዳማቸው ተቀብረዋል::

በዘመኑ ትኩረት ካጡ ታላላቅ ገዳማት አንዱ ይሔው ትግራይ ውስጥ የሚገኘው የአባ ጉባ ገዳም ነው::

(በነገራችን ላይ "ጉባ" ማለት "አፈ-መዐር : ጥዑመ-ልሳን" ማለት ነው)

ቸሩ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ የጻድቃኑን በረከት ያድለን:: በጸሎታቸውም በደላችንን ይቅር ይበለን::
#መስከረም_2_ግጻዌ


✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_2_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ቆሮንቶስ 6
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ከእናንተ አንዱ ከባልንጀራው ጋር ሙግት ቢኖረው በቅዱሳን ፊት በመፋረድ ፋንታ በዓመፀኞች ፊት ሊፋረድ ይደፍራልን?
² ቅዱሳን በዓለም ላይ እንዲፈርዱ አታውቁምን? በዓለምስ ላይ ብትፈርዱ ከሁሉ ይልቅ ትንሽ ስለሚሆን ነገር ልትፈርዱ አትበቁምን?
³ የትዳር ጉዳይ ይቅርና በመላእክት እንኳ እንድንፈርድ አታውቁምን?
⁴ እንግዲህ ስለ ትዳር ጉዳይ የፍርድ ቤት ቢያስፈልጋችሁ በቤተ ክርስቲያን የተናቁትን ሰዎች ፈራጆች አድርጋችሁ ታስቀምጣላችሁን?
⁵ አሳፍራችሁ ዘንድ ይህን እላለሁ። እንደዚህ ነውን? በወንድሞች መካከል ሽማግሌ ሊሆን የሚችል አንድ አስተዋይ ሰው በእናንተ ዘንድ አይገኝምን?
⁶ ነገር ግን ወንድም ወንድሙን ይከሳል፥ ይህም በማያምኑ ፊት ይደረጋልን?
⁷ እንግዲህ ፈጽሞ የእርስ በርስ ሙግት እንዳለባችሁ በእናንተ ጉድለት ነው። ብትበደሉ አይሻልምን? ብትታለሉስ አይሻልምን?
⁸ ነገር ግን እናንተ ትበድላላችሁ ታታልሉማላችሁ፥ ያውም ወንድሞቻችሁን።
⁹ ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀራጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ
¹⁰ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ዮሐንስ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁰ የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ የተገለጡ ናቸው፤ ጽድቅን የማያደርግና ወንድሙን የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም።
¹¹ ከመጀመሪያ የሰማችኋት መልእክት፦ እርስ በርሳችን እንዋደድ የምትል ይህች ናትና፤
¹² ከክፉው እንደ ነበረ ወንድሙንም እንደ ገደለ እንደ ቃየል አይደለም፤ ስለ ምንስ ገደለው? የገዛ ሥራው ክፉ፥ የወንድሙም ሥራ ጽድቅ ስለ ነበረ ነው።
¹³ ወንድሞች ሆይ፥ ዓለም ቢጠላችሁ አትደነቁ።
¹⁴ እኛ ወንድሞችን የምንወድ ስለ ሆንን ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን፤ ወንድሙን የማይወድ በሞት ይኖራል።
¹⁵ ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ነፍሰ ገዳይም የሆነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንዳይኖር ታውቃላችሁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 13
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁴ ከመምጣቱ በፊት ዮሐንስ አስቀድሞ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የንስሐን ጥምቀት ሰብኮ ነበር።
²⁵ ዮሐንስም ሩጫውን ሲፈጽም ሳለ፦ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ታስባላችሁ? እኔስ እርሱን አይደለሁም፤ ነገር ግን እነሆ፥ የእግሩን ጫማ እፈታ ዘንድ ከማይገባኝ ከእኔ በኋላ ይመጣል ይል ነበር።
²⁶ እናንተ ወንድሞቻችን፥ የአብርሃም ዘር ልጆች ከእናንተ መካከልም እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሆይ፥ ለእናንተ የዚህ የመዳን ቃል ተላከ።
²⁷ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሰዎችና አለቆቻቸው እርሱንና በየሰንበቱ የሚነበቡትን የነቢያትን ድምፆች ስላላወቁ በፍርዳቸው ፈጽመዋልና፤
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_2_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
  "ወይርአዩ አሕዛብ በቅድመ አዕይንቲነ። በቀለ ደሞሙ ለአግብርቲከ ዘተክዕወ። ይባዕ ቅድሜከ ገዐሮሙ ለሙቁሓን"። መዝ.78፥10-11።

#ትርጉም፦ "አሕዛብ፦ አምላካቸው ወዴት ነው? እንዳይሉ፥ የፈሰሰውን የባሪያዎችህን ደም በቀል በዓይኖቻችን ፊት አሕዛብ ይወቁ።
የእስረኞች ጩኸት ወደ ፊትህ ይግባ፤ እንደ ክንድህም ታላቅነት ሊገደሉ የተፈረደባቸውን አድን"። መዝ.78፥10-11።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_2_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
  ማርቆስ 6
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁴ ስሙም ተገልጦአልና ንጉሡ ሄሮድስ በሰማ ጊዜ፦ መጥምቁ ዮሐንስ ከሙታን ተነሥቶአል ስለዚህም ኃይል በእርሱ ይደረጋል አለ።
¹⁵ ሌሎችም፦ ኤልያስ ነው አሉ፤ ሌሎችም፦ ከነቢያት እንደ አንዱ ነቢይ ነው አሉ።
¹⁶ ሄሮድስ ግን ሰምቶ፦ እኔ ራሱን ያስቈረጥሁት ዮሐንስ ይህ ነው እርሱ ከሙታን ተነሥቶአል አለ።
¹⁷ ሄሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን አግብቶ ነበርና በእርስዋ ምክንያት ራሱ ልኮ ዮሐንስን አስይዞ በወኅኒ አሳስሮት ነበር፤
¹⁸ ዮሐንስ ሄሮድስን፦ የወንድምህ ሚስት ለአንተ ልትሆን አልተፈቀደም ይለው ነበርና።
¹⁹ ሄሮድያዳ ግን ተቃውማው ልትገድለው ትፈልግ ነበር አልቻለችም፤
²⁰ ሄሮድስ ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው እንደ ሆነ አውቆ ይፈራውና ይጠባበቀው ነበር፤ እርሱንም ሰምቶ በብዙ ነገር ያመነታ ነበር፤
²¹ በደስታም ይሰማው ነበር። ሄሮድስም በተወለደበት ቀን ለመኳንንቱና ለሻለቆቹ ለገሊላም ሹማምንት ግብር ባደረገ ጊዜ ምቹ ቀን ሆነላትና
²² የሄሮድያዳ ልጅ ገብታ ስትዘፍን ሄሮድስንና ከእርሱ ጋር የተቀመጡትን ደስ አሰኘቻቸው። ንጉሡም ብላቴናይቱን፦ የምትወጂውን ሁሉ ለምኚኝ እሰጥሽማለሁ አላት፤
²³ የመንግሥቴ እኩሌታ ስንኳ ቢሆን የምትለምኚውን ሁሉ እሰጥሻለሁ ብሎ ማለላት።
²⁴ ወጥታም ለእናትዋ፦ ምን ልለምነው? አለች። እርስዋም፦ የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ አለች።
²⁵ ወዲያውም ፈጥና ወደ ንጉሡ ገብታ፦ የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በወጭት አሁን ልትሰጠኝ እወዳለሁ ብላ ለመነችው።
²⁶ ንጉሡም እጅግ አዝኖ ስለ መሐላው ከእርሱም ጋር ስለ ተቀመጡት ሊነሣት አልወደደም።
²⁷ ወዲያውም ንጉሡ ባለ ወግ ልኮ ራሱን እንዲያመጣ አዘዘው። ሄዶም በወኅኒ ራሱን ቈረጠ፥
²⁸ ራሱንም በወጭት አምጥቶ ለብላቴናይቱ ሰጣት፥ ብላቴናይቱም ለእናትዋ ሰጠች።
²⁹ ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው መጡ በድኑንም ወስደው ቀበሩት።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ 
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ዮሐንስ_ወልደ_ነጎድጓድ ቅዳሴ ነው። መልካም የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
††† መስከረም 3 ቀን የሚከበሩ የቅዱሳን በዓላት †††

እንኳን ለጻድቁ አባ ሙሴ እና አባ አንበስ ኢትዮጵያዊ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

† አባ ሙሴ ዘሲሐት †

† ገዳመ ሲሐት የሚባሉ ብዙ ቦታዎች አሉ:: ቅድሚያውን የሚይዘው ግን የግብጹ ነውና ዛሬ የዚህን ገዳም አንድ ቅዱስ እናስባለን:: ሕይወታቸውም በእጅጉ አስተማሪ ነው:: ቅዱሱ አባ ሙሴ ይባላሉ:: የ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ክርስቲያን ናቸው::

እኒህ ጻድቅ አንድ ነገር ከሌሎች ቅዱሳን ይለያቸዋል:: ከምግባርና ትሩፋት በቀር አንድም የእግዚአብሔር ቃል አያውቁም:: ዝም ብለው በየዋሕነት ይኖሩ ነበር እንጂ:: ተወልደው ባደጉበት በምድረ ግብጽ በቅን ሕይወት ኑረው በወጣትነታቸው ወደ ደብረ ሲሐት ገቡ::

በዚያም በብሕትውና ዘግተው በጾምና ጸሎት ተወስነው ለ45 ዓመታት ኖሩ:: እጅግ የዋሕ ሰው ናቸውና ከጸጋ (ከብቃት) ደረሱ:: ሰው በአካባቢው አልነበረምና አብረው የሚውሉት ከግሩማን አራዊት ጋር ነበር:: አራዊቱም ጻድቁን ያጫውቷቸው ይታዘዙላቸውም ነበር:: በፈንታው ደግሞ አባ ሙሴ በተአምራት ዝናብ ያዘንቡላቸው ምግብም ይሰጧቸው ነበር::

አባ ሙሴ ልብስ አልነበራቸውምና በቅጠል ይሸፈኑ ነበር:: የምግባቸው ነገርማ "በመጠነ ኦፍ" ይላል ትንሽ ድንቢጥ የምትበላውን ያህል ቀምሰው ጥርኝ ውሃም ተጐንጭተው ነበር የሚኖሩት:: በሁዋላ ግን እጅግ ከመብቃታቸው የተነሳ ዐይናቸውን ሲገልጡ 'ገነት' (የአትክልት ሥፍራ) ይታያቸው ነበር:: ከዚያም ለበረከት ቆርጠው ይበሉ ነበር::

ሰይጣን እርሳቸውን ይጥል ዘንድ እጅግ ቢጥርም አልተሳካለትም:: በስተ መጨረሻ ግን የሚጥልበት መንገድ ተከሰተለት:: ምንም ባለ መማራቸው ሊፈትናቸውም ተነሳ:: አንድ ቀን ከበአታቸው በር ላይ ከአራዊት ጋር ተቀምጠው ሳለ ሰይጣን ሽማግሌ መነኩሴ መስሎ እየተንገዳገደ መጣ::

አራዊቱ ደንግጠው ሲሸሹ እርሳቸው ግን ሳያማትቡ ሮጥ ብለው ደገፉት:: ወደ በዓታቸውም አስገቡት:: ማታ ላይ ሲጨዋወቱ "ማንነትዎን ይንገሩኝ" አላቸው:: ለአባ ሙሴ ሰይጣኑ የበቃ አባት መስሏቸዋልና የ45 ዓመታት ድንግልናዊ የተባሕትዎ ሕይወታቸውን ነገሩት::

እርሱም በፈንታው ሐሰቱን ቀጠለ:: "እኔ ግፍ እየሠራሁ በዓለም እኖር የነበርኩ ሰው ነኝ:: ነገር ግን ዓለምን ትቼ ላለፉት 40 ዓመታት በበርሃ በንስሃ ኑሬአለሁ:: ያም ሆኖ አንዲት ሴት ልጅ አለችኝና 'ማን ያገባታል' ብየ ስጨነቅ አንተ እንደምታገባት ተገለጠልኝ" አላቸው::

አባ ሙሴ ደንግጠው "እንዴት ድንግልናየንና ሕይወቴን ትቼ አገባለሁ?" ሲሉም ጠየቁ:: ሰይጣን ግን ቃለ እግዚአብሔር እንደማያውቁ ተረድቷልና "አንተ ከአብርሃም ከያዕቆብ ከዳዊት ትበልጣለህ? እነሱ አግብተው የለ!" ብሎ ቢገስጻቸው አንዳንዴ አለ መማር ክፉ ነውና አባ ሙሴ ሸብረክ አሉ ተረቱ::

ከዚያም ተያይዘው ጉዞ ወደ ዓለም ሆነ:: መንገድ ላይ ግን መነኩሴ ነኝ ያለው ሰይጣን ወደቀና የሞተ መሰለ:: አባ ሙሴ በእንባ ቀብረውት ሲሔዱ ተኖ ጠፋ:: አባ ሙሴ ቀና ሲሉ ሰይጣን በምትሐት የሠራውን ያማረ ግቢና ቆንጆ ሴት አዩ:: ወደ እሷ እቀርባለሁ ሲሉ አውሎ ንፋስ ማጅራታቸውን መትቶ ጣላቸው::

አባ ሙሴ ከወደቁበት ሲነሱ ያዩት ነገር ሁሉ ሰይጣናዊ ምትሐት መሆኑን አወቁ:: ወደ በአታቸው መጥተው ከገነት ፍሬ ቢቀምሱ ጸጋ እግዚአብሔር ተለይቷቸዋልና መራራ ሆነባቸው:: እያለቀሱ ከበዓታቸው ወጡ::

መንገድ ላይ ያው ሰይጣን ነጋዴ መስሎ "መንገድ ልምራዎት" ብሎ ምንም ከሌለበት በርሃ ላይ ጥሏቸው ተሰወረ:: የሚያደርጉት ጠፋባቸው:: ረሃቡ፣ ጥሙ ከፈጣሪ ጸጋ መለየቱ አቃጠላቸው:: አሁንም አንዲት ሴት መነኩሴ ድንገት መጥታ ወደ በዓቷ አስገባቻቸው::

የማይገባውን ድርጊት እናድርግ ብላ አባበለቻቸው:: ይባስ ብላ ወደ አይሁድ እምነት እንዲገቡ አሳመነቻቸው:: ወዲያውም ወደ ሌላ በርሃ ወስዳ "አወቅኸኝ?" አለቻቸው:: "የለም" አሏት:: እዚያው ላይ ተቀይራ ጋኔን መሆኗን አሳይታቸው ተሠወረች::

አባ ሙሴ በዚያው ሥፍራ በአንድ ጊዜ ሁሉንም አጡ:: አለቀሱ: ተንከባለሉ:: እንባቸው እንደ ዥረት ፈሰሰ:: ልቡናቸው ሊጠፋ ደረሰ:: ወደ ፊታቸው አፈር እየረጩ "ወየው" እያሉ ሲያለቅሱ ጌታችን መልአኩን ላከላቸው::

እንደ ቀድሞውም ፊት ለፊት ታይቶ አጽናናቸው:: "አይዞህ! ፈጣሪ እንባህንና ንስሃህን ተቀብሏል" ብሎ ወደ ስውራን ከተማ ወሰዳቸው:: በዚያም ለ7 ቀናት ቆይተው በዚህች ቀን ዐርፈዋል::አባ ሳሙኤልም ቀብሯቸዋል::

† አባ አንበስ ኢትዮጵያዊ †

† ጻድቁ የነበሩት በ13ኛው መቶ ክ/ዘመን ሲሆን የተወለዱት ትግራይ ውስጥ ነው:: ዛሬም ድረስ የብዙ ስውራን ቤት እንደ ሆነ የሚታወቀውን ደብረ ሐዘሎንም እርሳቸው እንደ መሠረቱት ይነገራል:: አባ አንበስ ከገዳማዊ ትሩፋታቸው ባሻገር በአንበሶቻቸው ይታወቁ ነበር::

የትም ቦታ ሲሔዱ በአንበሳ ጀርባ ላይ ነበር:: በእርግጥ አባቶቻችን ከዚህም በላይ ብዙ ድንቆችን ማድረግ ይችላሉ:: ምክንያቱም እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ነውና:: ጻድቁ የአቡነ ገብረ መንፈስቅዱስ የሳሙኤል ዘዋልድባና የአባ ብንያሚን ባልንጀራ ናቸው:: ዛሬ ደግሞ ዕረፍታቸው ነው::

† አምላከ ቅዱሳን የወዳጆቹን ፈተና አስቦ እኛን ከመከራ ይሰውረን:: በቃል ኪዳናቸው ይጠብቀን:: በረከታቸውንም ያብዛልን::

† መስከረም 3 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አባ ሙሴ ዘደብረ ሲሐት
2.አባ አንበስ ኢትዮጵያዊ
3.አበው ኤጲስ ቆጶሳት
4.አባ ዲዮናስዮስ
5.አባ ዲዮስቆሮስ ሰማዕት
6.ቅዱስ በትንከል ዲያቆን

† ወርኀዊ በዓላት
1.በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቅዱሳን ሊቃነ ካህናት አበው (ዘካርያስና ስምዖን)
4.አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ
5.አቡነ ዜና ማርቆስ
6.አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ዘደብረ በንኮል
7.ቅዱስ ቄርሎስ ሊቅ (ዓምደ ሃይማኖት)

† "በመጠን ኑሩ ንቁም ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይዞራልና:: በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት::"(1ጴጥ 5:8)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በአንተ ለሚያምኑ ሁሉ ምሕረትን ይለምን ዘንድ በሥልጣናት ላይ አለቃ አድርገህ መጋቤ ድንግል ሊቀ መላዕክት ቅዱስ ፋኑኤልብ የሾምከው የቅዱስ ፋኑኤል አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ሆይ እኔ ባሪያህን ስለ ወዳጅህ መጋቤ ድንግል ሊቀ መላዕክት ቅዱስ ፋኑኤል ብለህ ከሥጋና ነፍስ መከራ ሁሉ ሠውረኝ ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን ወአሜን.......
          *አባታችን ሆይ በሰማያት የምትኖር.....*
🌹ወር በገባ በ3 ታስበው የሚውሉት አባታችን አባ ሊባኖስ ያደረገው ተአምር፡፡ጸሎቱና በረከቱ ከሁላችን ከሕዝበ ክርስቲያን ጋር ይኑር ለዘአለዓለሙ አሜን፡፡
☞ከንጉስ ጭፍራዎች የታመመ ትከሻውም ከጉልበቱ ጋር እስከሚገናኝ የጎበጠ
አንድ ወታደር ነበር፡፡
☞ወደ አባታችን ወደ አባ ሊባኖስም ቦታ በፈረስ ጭነው አምጥተው አባታችን አባ ሊባኖስ በመስቀል ባርኮ ባፈለቀው በሕይወት ውሃ አጠመቁትና በክብር አባታችን በአባ ሊባኖስ መቃብር ውስጥ አስቀመጡት፡፡
☞ከዕለታት በአንድ ቀን ካህናቱ በማህሌት እያመሰገኑ ሳለ የዚያ በሽተኛ አጥንቶቹ ሲንቋቁ ከቤተክርስቲያን እንጨት የተሰበረ መስሏቸው ወደ ቤተክርሲቲያኑ ጠፈር ይመለክቱ ጀመር፡፡
☞ዳግመኛም ወደዚያ በሽተኛ ሮጠው ቢሄዱ ሁለተናዉ ተቃንቶ ድኖ አገኙት፡፡ከተኛበትም አነሱትና እግሩና ወገቡ ፀንቶለት ተቃንቶ በእግሩ ሄደ፡፡
☞አንድ ካህንም ወንድሜ ሆይ እንደምን ሆነህ ዳንክ ብሎ ጠየቀው እሱም ተኝቼ ሳለ አንድ ሰው በመነኩሴ ተመስሎ ወደ እኔ መጣና በመስቀል ምልክት በላዬ ላይአማተበ አጥንቼ ሁሉ እየተንቋቁ ጮኹ ይኸው ዛሬ እንደምታየኝ ተቃንቼ ድኜ አለሁ አለ፡፡
☞ያየና የሰማ ሁሉ እግዚአብሔር አመሰገኑ፡፡ለቅዱስ ለአባ ሊባኖስ ፈጽሞ ተገዙለት፡፡
☞ያም በሽተኛ አባታችን አባ ሊባኖስ በፀሉቱ ከአፈለቀው ከፀበሉ ይዞ ወደ ንጉሱ ወደ ሰይፈ አርዕድ ሄደ፡፡
☞በዚህ ምክንያት ንጉሱ ሰይፈ አርዕድ ወደደው ያን በሽተኛ ያየውም ሰው ሁሉ አደነቀ፡፡
☞ያም በሽተኛ ብዙ ገንዘብ ሁሉ ለአባ ሊባኖስ ቤተክርስቲያን አወረሰ፡፡ስሙም መጣዕ መሐሮ ተባለ፡፡
☞የአባታችን የአባ ሊባኖስ ጸሎት በረከታቸው ከሁላችን ከተዋህዶ ልጆች ጋር ይሁን፡፡
☞(ገድለ አባ ሊባኖስ)
2025/10/22 03:12:34
Back to Top
HTML Embed Code: