Telegram Web Link
[ዓለምን እያነጋገረው ስላለው ስለ 2024 YR4 አስትሮይድ ዐጭር መረጃ]
✍️ በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ከፍተኛ የሕዋ ዓለት (አስቴሮይድ) እየመጣ እንደኾነ በመሠራጨቱ ብዙዎች ይኽ የሚሠራጨው መረጃ እውነት ነው ወይስ አይደለም? የሚሉ ብዙ መልእክቶች በውስጥ መሥመር በመላካቸው ትክክለኛው መረጃን ለማጋራት ወደድኹ።

👉 አስትሮይድ 2024 YR4፣ በ100 እና 300 ጫማ (40 እና 90 ሜትር) ስፋት መካከል ያለ ሲኾን በተመራማሪዎች የታየው እ.ኤ.አ በታኅሳስ 27፣ 2024 ዓ.ም. ላይ ነበረ።

👉 በሃዋይ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ፈለክ ተመራማሪ የሆኑት ጆን ቶኒ ለሳይንቲፊክ አሜሪካዊ እንደተናገሩት ምድር ላይ ቢወድቅ ፍንዳታው ከ10 ሜጋቶን ቦምብ ጋር እኩል ሊሆን ይችላል። ወይም ከሄሮሺማ ላይ ከወደቀው ቦምብ 500 ዕጥፍ እንደማለት ነው። በሦስት ወይም በአራት ኪሎ ሜትር ውስጥ ያለው ነገር ሁሉ ይቃጠላል። ምናልባት እስከ 10 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ነገር ሁሉ ይሰባብራል›› ብሏል።

👉 አስትሮይድ 2024 YR4 ምድርን ሊመታ የሚችልበት እድል በ1.3% አለ፣ በናሳ ስሌት መሠረት ይኽ የሚከሰተው ግን አሁን ሳይኾን እ.ኤ.አ በታኅሳስ 22, 2032 ማለትም በኢትዮጵያ አቆጣጠር ረቡዕ ታኅሣሥ 13/ በ2025 ዓመተ ምሕረት ከ8 ዓመት በኋላ ነው።

👉 ምናልባት ምድር ላይ ቢወድቅ ምሥራቃዊ የፓስፊክ ውቅያኖስ፣ ሰሜናዊው የደቡብ አሜሪካ ክፍል ፣ አትላንቲክ ውቅያኖስ ፣ አፍሪካ ፣ የአረቢያ ባሕር ፣ ደቡብ እስያ ይገመታል።

👉 መልካሙ ዜና ግን 2024 YR4 በደኅና በዚህ ቀን በምድር ላይ በሰላም የማለፍ እድሉ 99% ያህል ነው። 1.3% የመጋጨት እድሉ ትንሽ ሊመስል ቢችልም፣ ለሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ግን በቁም ነገር እንዲያስቡበት ከበቂ በላይ ነው።

👉 እንደውም ከ8 ዓመት በኋላ ከሚመጣው አስትሮይድ 2024 YR4 ይልቅ አስትሮይድ 99942 አፖፊስ በመባል የሚታወቀው 1,200 ጫማ (370 ሜትር) ስፋት ያለው፣ በትልቅነቱ ምክንያት “ከተማ አውዳሚ” ተብሎ የተመደበ ሲኾን እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በሚያዝያ 13, 2029 በእኛ አቆጣጠር ደግሞ ዐርብ ሚያዝያ 5/ 2021 ዓ.ም መሬትን በ19,400 ማይሎች ወይም 31,200 ኪሎሜትር ያልፋል። ይህም ከጂዮስቴሽነሪ ሳተላይቶች ይልቅ በመቅረብ ሲኾን በዐይን የመታየት ዕድል ይኖረዋል።

👉 በጊዜው አፖፊስም ቢሆን ከመሬት ጋር የመጋጨት እድሉ 2.7% ብቻ ነው። እንደ ጎርጎርዮሳዊያኑ አቆጣጠር በ2029፣ ቀጥሎ በ2036 ከዚያም በ2068 ላይ አፓፊስ በዑደት እንደሚመለስ ታውቋል። ቢኾንም 2.7% እንደ ቀላል የሚቆጠር አይደለም (ስለ አስትሮይድ አፓፊስ አንድሮሜዳ ቁጥር 2 መጽሐፍን ያንብቡ)።

👉አደጋን ካሰብን እ.ኤ.አ. በ1908 የቱንጉስካ ክስተት ሲሆን ከ30-50 ሜትር የሚደርስ ሜትየር በሳይቤሪያ ላይ ፈንድቶ በ770 ስክዌር ማይል የሚገኙ 80 ሚሊዮን ዛፎችን እንዳወደመ የሚታወቅ ነው።

👉 እ.ኤ.አ የካቲት 15፣ 2013 ሩሲያ ቼልያቢንስክን የመታው ሜትየር መጠኑ (ከ17 እስከ 20 ሜትሮች ወይም ከ56 እስከ 66 ጫማ) በዲያሜትር ይገመታል። በክስተቱም 1,500 የሚያህሉ ሰዎችን አቁስሎ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሕንፃዎች ላይ ጉዳት አድርሶ ነበረ። አስትሮይድ 2024 YR4 ግን በዲያሜትር ከ40 ሜትር እስከ 90 ሜትር (ከ130 ጫማ እስከ 300 ጫማ አካባቢ) መካከል ነው።

👉 በቼልያቢንስክ ላይ የተለቀቀው ኃይል ወደ 500 ኪሎ ቶን TNT ተመሣሣል ተብሎ ይገመታል—ከሂሮሺማ አቶሚክ ቦምብ በ30 እጥፍ ይበልጣል። 2024 YR4 ቢመታ ከ8 እስከ 10 ሜጋ ቶን ያህል ሊሆን ይችላል ሲሉ በአሪዞና ዩኒቨርሲቲ የካታሊና ስካይ ጥናት ዳይሬክተር የሆኑት ካርሰን ፉልስ ተናግረዋል። ከእንደዚህ ዓይነት ተጽእኖ የሚፈነዳ ሞገድ የብዙ ማይል ራዲየስ ይኖረዋል።

👉 እንዲህ ዓይነት ክስተት ለአብዛኛው አስፈሪ ቢኾንም ለከዋክብት ተመራማሪዎች ግን በቅርበት ለማጥናትና ለማየት ምቹ ስለሚኾኑ ታላቅ ዕድል ነውና እንደ መልካም ዜናም ይታያል። በመጨረሻም ሰማይን ማየት፣ ሰማይን መመልከት እንውደድ እንልመድ በማለት ስለ ሰማያዊ አካላት የተጻፉትን
አንድሮሜዳ ቁጥር 1 እና 2/ ማዛሮትን እንድታነቡ በመጋበዝ ጽሑፌን አበቃኹ።
✍️ መጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ (የ29 መጻሕፍት ጸሐፊ)
በጥበብ እንድመቅ
እጅግ ድንቅና እርስዎን ወደ ጥበብ ከፍታ የሚያደርሶት በብዙ ምስጢር የተመላው "የግእዝ ቀመረ ፊደል" (Geez Gematria) የኦንላይን ትምህርት
👉 በዶክተር ሮዳስ ታደሰ ሊጀመር ነው።
👉 በዶክተር ጌትነት ፈለቀ (ሥነ ፈለክ)

💥 ትምህርቱ፦ ቅዳሜ ለ1 ሰዓት ተኩል

💥 ሰዓት፦ ከምሽቱ 3 ሰዓት በኢትዮጵያ አቆጣጠር
👉 1 PM EST (NY) Time
👉 10 AM PST (LA) Time

💥 የመጀመሪያው ሴሚስተር የካቲት 22 (March 1) - ግንቦት 23 (May 31)

💥 ለበለጠ መረጃ (ለምዝገባ) በሰሜን አሜሪካ ላሉ፦
(202) 643-3620  ይደውሉ።

በሀገር ውስጥ ላሉ ስልክ፦  0911827336 ወይም 0925354271

👉 ለምዝገባ በውጪ ላሉ፦

🔥 *Considering the high volume of future Students who have expressed interest to take these Online Courses, we are happily  extending some discounts to our future students*

🔥 *If you are applying from out side of Ethiopia, PLEASE use the links shown below. Each link Registers you to the corresponding course, or courses.*

👉 *1. This Link gives you a $30 Discount  for Qemere Geez I  [Geez Gematria]*

https://square.link/u/L21tk5AM

👉 *2. This Link gives you a $30 Discount for Sine-Felek I  [Astronomy]*

https://square.link/u/eOBVh9L1

👉 *3. This Link gives an additional $90 Discount for those who are taking both Courses*

https://square.link/u/1IfOhLnQ

👉 በሕይወት ዘመንዎ ከጥበብ ጋር የሚገናኙባት ዕለት ምርጥ ናት። ይመዝገቡ ለጥበብ ወዳጆችም ሼር ያድርጉ።
[የካቲት 5 (February 12) በዓሏ የሚታሰብላት ሉቃስ የሣላት ከጒንጯ ደም የሚፈስሳት ተአምር አድራጊዋ የእመቤታችን ሥዕል እጅግ አስደናቂ ታሪክ (መነበብ የሚገባው)]
በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
የዚኽች አስደናቂ ሥዕልን ድንቅ ታሪክ ከመጻፌ በፊት ለወንጌል አገልግሎት ከ8 ዓመት በፊት ወደ ኖርዌ በኼድኊ ጊዜ ከጒንጮቿ ላይ ደም የሚፈስሳት ኾና የምትታየው ኹላችንም የምናውቃት የእመቤታችንን የታተመች ሥዕሏን በአንድ ወንድም ቤት ውስጥ በክብር ባማረ መልኩ ተቀምጣ አይቼ በመደነቅ፤ ሥዕሏን ከየት እንደገዛት ጠየቅኹት።

እርሱም በኖርዌ የዕቃ መሸጫ አጠገብ ወድቃ አግኝቶት ቶሎ ብሎ በገንዘቡ ገዝቷት፤ ቤቱ ወስዶ መብራት አብርቶ፤ ሽቱ ረጭቶ በክብር ባስቀመጣት ጊዜ ሌሊቱን ኹሉ እጅግ ዕጹብ ድንቅ የሚያሰኝ የዕጣን ሽታ ሲሸተውና የማዕጠንትና የምስጋና ድምፅ ሲሰማ እንዳደረ ነገረኝ። እኔም ልዑል እግዚአብሔርን በማመስገንና የተቀደሰ ሥዕሏን በመሳለም፤ ጉንጮቿ ላይ ያለውን ታሪክ ታውቀዋለህ? ብዬ በጠየኩት ጊዜ ቀዩ ነገር በአጋጣሚ ከሥዕሉ ጋር ዐብሮ የተሣለ እንደመሰለው ብቻ ነገረኝ።

እኔም በቤተ ክርስቲያን ታሪክ በተለይ በቅዱሳት ሥዕላት ትውፊት የሚነገረውን የሥዕሏን ታሪክና ያደረገችውን ተአምር ይልቁኑ ስትሣል ጉንጯ ላይ ለምን የደም ነጠብጣብ እንደሚደረግ ነገርኩት፡፡ ልጁ የገዛት ሥዕል ግን ዋናዋ የጥንቷ ናት ማለቴ ሳይኾን ያው አኹን የምንጠቀምባት ፖስት ያደረግኳት ዓይነት በዚያች በዋናዋ አምሳል የታተመችውንና የምትሸጠውን ሥዕል እንደኾነች ለማስታወቅ እፈልጋለኊ።

ይኽን በጥንት ጊዜ የነበራትን የተቀደሰ ታሪክ ለኹሉም መጻፍ እንዳለብኝ ለራሴ ቃል ገብቼ ነበርና እነሆ ጊዜው ገጥሞልኝ በየካቲት 4 በመላው ዓለም በዓሏ የሚታሰብላትን ታሪኳን በበዓሏ ዕለት እነሆ ብያለኊ፡፡

ስለዚኽች ድንቅ ተአምር አባ ጽጌ ድንግል አስቀድሞ በማሕሌተ ጽጌ ላይ እንዲኽ ብሏት ነበር፡-

“ሥዕልኪ ማርያም ጸገየት ሥጋዌ
ከመ ዕፀ ገነት ትጸጊ ጽጌያተ ለሥርጋዌ
ሣሕለ ተአምርኪ እኩን ለትውልደ ትውልድ ዜናዌ
ቅብዕኒ ሐፈ ሥዕልኪ ወፈውስኒ እምደዌ
እስመ በኅምዙ አቊሰለኒ አርዌ”

(የገነት ዛፍ አበቦችን ለሽልማት እንደምታብብ ማርያም ሥዕልሽ ግዘፍን አበበች (ሥጋን የለበሰች መስላ ታየች)፤ የተአምርሽን ዜና ለልጅ ልጅ የምነግር እኾን ዘንድ የሥዕልሽን ወዝ ቀቢኝ፤ ከበሽታም አድኚኝ፤ አባብ አውሬ በመርዙ በኀጢአት አቊስሎኛልና) በማለት ተማፅኗታል፡፡

ይኸውም ከ829-842 ዓ.ም. በቤዛንታይን የነገሠው ንጉሥ ቴዎፍሎስ በቅዱሳት ሥዕላት ላይ በክፋት ተነሳሥቶ ዐዋጅ በማወጁ ወታደሮቹ በርሱ ትእዛዝ በእያንዳንዱ ቤት እየዞሩ ቅዱሳት ሥዕላትን ለማጥፋት ፍተሻ ያደርጉ ነበር፤ በኒቅያ ከተማ አቅራቢያ አንዲት የተቀደሰች ሴት ነበረች፤ ቅዱስ ሉቃስ የሣላት የአምላክ እናት የቅድስት ድንግል ማርያም ውብ ሥዕሏን በቤቷ ውስጥ ደብቃ በማኖር በሥዕሏ ፊት መብራትን እያበራች ከልጇ እንድታማልዳት ትማፀን ነበር፡፡

የከሓዲው ንጉሥ ወታደሮቹም የአምላክ እናት ሥዕል በቤቷ እንዳለች በማወቃቸው ወደ ቤቷ በድንገት ዘልቀው ገቡ፤ ከመካላቸውም አንዱ ወታደር የእመቤታችንን ሥዕሏን በያዘው ጦር ጒንጯ ላይ ወጋት፡፡ ኾኖም ግን በእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ ይኽ ክፉ ሥራው በተአምር ተተክቶ፤ ከተወጋው ከአምላክ እናት ፊት ላይ ደም ይፈስስ ጀመር፡፡

ይኽን ግሩምና ድንቅ ተአምር ባዩ ጊዜ ወታደሮቹ ደንግጠው ሸሽተዋል፤ ሴቲቱም ይኽነን ድንቅ ተአምር ባየች ጊዜ ሌሊቱን ሙሉ በሥዕሏ ፊት መብራትን አብርታ በአምላክ እናት በቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ፊት ስትጸልይ ዐደረች፤ በነጋታውም በእግዚአብሔር ፈቃድ ከጒንጮቿ ደም የፈሰሳትን የአምላክ እናት ሥዕሏን በባሕሩ ላይ እንድታስቀምጥ ታዘዘችና አስቀመጠቻት።

ሥዕሏም በባሕሩ ላይ በመንሳፈፍ በማዕበሉ እየተነዳች ያለምንም መስጠምና መርጠብ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ጉዞዋን አድርጋ ወደ አቶስ ደረሰች፡፡ ጊዜያቶች ካለፉ በኋላ ከዕለታት በአንዳቸው ምሽት በአቶስ ተራራ የአይቬሮን ገዳም መነኮሳት የብርሃን ምሰሶ በባሕሩ ላይ ተተክሎ እንደ ፀሓይ ሲያበራ ተመለከቱ፡፡

ይኽም ተአምር ለተካታታይ ቀናቶች በመቀጠላቸው በዚያ የተቀደሰ ተራራ በምናኔ ያሉ አባቶች ኹሉ በአንድ ላይ ተሰባስበው በማድነቅ የብርሃን ምሰሶ ወደተተከለበት የአምላክ እናት ሥዕል በላዩ ላይ ወደ ተንሳፈፈበት ወደ ባሕሩ በመውረድ ወደ ሥዕሏ ለመጠጋት ቢሞክሩም ሥዕሏ ወደ ኋላዋ እየተመለሰች ሊያነሷት አልተቻላቸውም፡፡

በዚያው የአይቮሪዮን ገዳም ረድእ (የጉልበት አገልጋይ) ኾኖ የሚኖር አባ ገብርኤል Gabriel the Iberian የተባለው መነኩሴ ብቻ ሥዕሏን ከባሕር ውስጥ ማንሣት የሚችል እንደኾነ የአምላክ እናት ለመነኮሳቱ ገለጠችላቸው፤ በተመሳሳይም ለአባ ገብርኤል እመቤታችን ተገልጣለት “ወደ ባሕሩ ኺድ፤ ማዕበሉንም ሳትፈራ በባሕሩ ውስጥ በእምነት ተጓዝ፤ እናም ኹሉም ለዚኽ አንተ ላለኽበት ገዳም ያለኝን ፍቅርና ርኅራኄ ምስክር እንዲኾኑ፤ ሥዕሌን ከባሕር አውጣ” በማለት ነገረችው፡፡

ከዚያም በአቶስ ተራራ ያሉት መናንያን ኹሉ አባ ገብርኤልን ይዘው ልብሰ ተክህኖ ለብሰው፣ እያመሰገኑ፤ በማዕጠንታቸው ዕጣን እያጠኑ የብርሃን ምሰሶ ወደተተከለበት የአምላክ እናት ሥዕል ወዳለበት ወደ ባሕሩ ኼዱ፤ አባ ገብርኤልም በደረቅ መሬት እንደሚጓዝ ያለምንም ፍርሃት ወደ ባሕሩ ውስጥ በመግባት በናፍቆት ኾኖ የአምላክ እናት የቅድስት ድንግል ማርያምን ሥዕሏን በደረቱ ታቅፎ ተሳለማትና ወደ ባሕር ዳርቻ ይዟት ወጣ፤ እነርሱም በደስታ ኾነው እጅ ነሷት፡፡

ከዚያም ማግሰኞ በጠዋቱ ሥዕሏ ባረፈበት ቦታ ላይ በሚያመሰግኑበት ጊዜ ቀዝቃዛና ጣፋጭ ውሃ ከምድር ላይ ፈለቀላቸው፡፡ ከዚያም የእመቤታችንን ሥዕሏን በታላቅ ክብር በምስጋና ይዘው በመኼድ ወደ ቤተ መቅደስ አግብተው በመንበሩ ላይ አስቀመጧት፡፡

ነገር ግን በነጋታው መነኮሳቱ ወደ ቤተ መቅደስ ገብተው መብራት ሲያበሩ የእመቤታችን ሥዕሏን ባስቀመጡበት ቦታ አላገኟትም፤ ይልቁኑ በመግቢያው በር ባለው ግድግዳ ላይ ተሰቅላ አገኟት፤ እነርሱም መልሰው በቦታዋ ላይ ቢያኖሯትም ተመልሳ በገዳሙ መግቢያ ላይ ተሰቅላ ያገኟት ነበር።

ከዚያም እመቤታችን ለአባ ገብርኤል ተገልጻለት “ለወንድሞች እንዲኽ ብለኽ ንገራቸው፤ ከዚኽ በኋላ ሥዕሌን ማግባት የለባቸውም፤ የእኔስ ፈቃድ በእናንተ ልጠበቅ ሳይኾን እኔን በምልጃዬ ጥላ በዚኽም ዓለም በወዲያኛውም ዓለም ልጋርዳችኊ እንጂ፤ ሥዕሌን በገዳሙ በምታዩበት ጊዜ ኹሉ የልጄ ምሕረትና ጸጋ ከእናንተ አይቋረጥም” አለችው፡፡

በዚህ ምክንያት ሥዕሏ በነገረ መለኮት ሊቃውንት "አቃቢተ ኆኅት" (ደጃፍን የምትጠብቅ) Όδηγήτρια Panagia Portaitissa ("She who resides by the door" or "Keeper of the gate" ትባላለች።

መነኮሳቱም ይኽነን ሰምተው በእጅጉ በመደሰት ለአምላክ እናት ለእመቤታችን ክብር በገዳሙ በር አጠገብ አነስ ያለች ቤተ ክርስቲያን ሠርተው ገባሪተ ተአምራት ወመንክራት (ድንቅ ተአምር አድራጊዋን) የአምላክ እናት የቅድስት ድንግል ማርያምን ሥዕሏን ወደ ውስጥ አገቧት፤ የተቀደሰች የሥዕሏ መጠሪያም “የአይቬሮኗ የአምላክ እናት” (the Iviron Theotokos) ስትባል በግሪክ “ፓርታኢቲሳ” Παναγία Πορταΐτισσα; ትባላለች። ዛሬም የተቀደሰ ሥዕሏ በግሪክ በአቶስ ተራራ ላይ በሚገኘው በአይቬሮን ገዳም ውስጥ
ትገኛለች።

ከዚያም አካቲስት በሚባል ለአምላክ እናት በተደረሰ ምስጋና "ለጻድቃን የገነትን ደጆች የምትከፍት የተባረክሽ በር ጠባቂ ሆይ ደስ ይበልሽ።" የሚል ምስጋና ተደርሶላታል።

ከዚያም በአይቬሮን ገዳም ያለችው የእመቤታችን ሥዕል ድንቅ ተአምር በዓለም ኹሉ ላይ ከተሰማ በኋላ በረከቷን ለማግኘት ክርስቲያኖች ወደዚያች ገዳም መኼድን ጀመሩ፤ ይኽ የተቀደሰ ሥዕሏና ታሪኳም ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለሙ ኹሉ ላይ ተሰማ፤ ምእመናንም ይህንን ሥዕሏን በመላው ዓለም በማሣል መማፀን ጀመሩ። ዛሬም በዚህች ሥዕል ምእመናን ይማፀኑበታል፡፡ የዚኽችን የተቀደሰ ታሪክ የያዙ በርካታ ቅዱሳት ሥዕላት ኦንላይን ላይ ስላሉ ጉግል በማድረግ ማየት ትችላላችኹ፡፡ በዚኹ አጋጣሚ በኢትዮጵያ ሰበታ ጌቴሴማኒ ማርያም ገዳም በጼዴንያ ማርያም በክብር የተቀመጠች ሥዕሏን ለመመልከት ችያለሁ። አኹን ፓስት ያደረኳትን የእመቤታችንን ሥዕል አቶስ አይቬሮን ገዳም ያለችውን ሥዕል ስካን በማስደረግ በስጦታ የላከችልኝን ዶክተር ራሔል ዓለሙን አመሰግናለኹ፡፡

በተጨማሪም በኢትዮጵያ ዐይናቸው ማየት አቁሞ የነበሩት ወይዘሮ አልማዝ ስለዚኽች የተቀደሰች ሥዕል ታሪክ ልጆቻቸው ሲያነቡላቸዎ ሥዕሏን ፕሪንት እንዲያደርጉላቸው በመናገር ዐይናቸው ላይ ማደረጉት ጊዜ የጠፋ ዐይናቸው በርቶላቸው ይኽንን ምስክርነታቸውን በእንጦጦ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ገዳምና በሰአሊተ ምሕረት ደብረ ምጥማቅ ማርያም ወክርስቶስ ሠምራ ቤተ ክርስቲያን በነበረን የእመቤታችን ጉባኤ የተቀደሰ ሥዕሏን አጅበን ተባርከንበታል። እርሳቸውም በዐውደ ምሕረት ላይ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
https://youtu.be/ppsVn-IAFH8?si=v1vf25ywm043cnYx

ለአባ ገብርኤል የተለመነች እና በረከቷን እንዳሳደረችበት ዛሬም በረከቷ ምንም ሳንይዝ ባዷችንን ጥለነው በምንሄደው በዚኽ ኃላፊ ጠፊ ዓለምና፤ በማያልፈውም በወዲያኛውም ዓለምም እንዳይለየኝ በመማፀን አባ ጽጌ ድንግል ስለዚኽች ሥዕል በማሕሌተ ጽጌ ላይ ባመሰገናት ምስጋና፦

“ቦ አመ ትትረከብ ምስለ ቃለ ነገር ጥዑም
ወቦ አመ ትትረአይ በለቢሰ አባል ልምሉም
ሥዕልኪ ማርያም ጽጌ ተአምር አዳም
ወአመ ዘበጣ በሰይፍ አይሁዳዊ ርጉም
እምኔሃ አንጸፍጸፈ ደም”

(ሥዕልሽ ቃልን ደስ ከሚያሰኝ ነገር ጋራ የምትገኝበት ጊዜ አለ፤ የለመለመ አካልንም ለብሳ የምትታይበት ጊዜ አለ፤ ማርያም ሥዕልሽ የተአምር አበባ ናት፤ ርጉም አይሁዳዊ በሰይፍ በመታት ጊዜ ከርሷ ሥዕል ደም ተንጠባጠበ) በማለት አመሰግናታለሁ፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስለ ቅዱሳት ሥዕላት ክብር ዘወትር በምታቀርበው የመልክአ ሥዕል ምስጋና ስለዚኽች ሥዕል ክብር፦
"ሰላም ለሥዕልኪ ቦ ጊዜ ዘትትናገር
ወቦ ጊዜ ዘትክዑ ደመ ተአምር"
(አንዳንድ ጊዜ የምትናገር፤ አንዳንድ ጊዜ የተአምር ደምን ለምታፈስ ሥዕልሽ ሰላምታ ይገባል) በማለት ውዳሴ ታቀርባለች።

በመጨረሻም በጽሑፌ የአምላክ እናት ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ በምልጃሽ እና በቃል ኪዳንሽ የማይጠገበው በረከትሽን ዕጽፍ ድርብ አድርገሽ አሳድርቢን በማለት "በኢትዮጵያ ወግብጽ ወሶርያ በአንጾኪያ ወሮም
ለሥዕላትኪ ዘሀለዋ ማርያም ሰላም"
(በኢትዮጵያና በግብጽ፤ በሶርያ በአንጾኪያና በሮም ላሉ ሥዕሎችሽ ማርያም ሆይ ሰላም እላለሁ) በማለት በሊቁ ሰላምታ ለከበረ ሥዕሏ የአክብሮት ሰላምታ በማቅረብ ጽሑፌን አበቃለሁ።

እስቲ እናንተም በተቻላችኊ መጠን በተሰማችኊ ልክ አመስግኗት። እመቤታችንም በዓለም ላይ ከፈሰሰው መቅሠፍት በቃል ኪዳኗ ትጠብቀን።

(ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ) በድጋሚ ፓስት የተደረገ
እንደሚታወቀው የየካቲት ሙሉ ጨረቀ ከ6:35 PM ወይም በኢትዮጵያ ሰዓት ከ12:35 በኋላ ዛሬ ረቡዕ ትወጣለችና ከያላችሁበት ሀገር በምሽት የምታነሡትን ፎቶ https://www.tg-me.com/+xN518gdGKvswNzE0
ላይ መላክ ትችላላችሁ።
(ዶክተር ሮዳስ ታደሰ)
Forwarded from Zemenai
እንደምን ከረማችሁ የግዕዝ ቀመር ቤተሰቦች ::
እህቶቻችን እግዚአብሔር ይስጥልን በእዉነት ሁሌም በመሪነት በመቆም ለምታገለግሉን ::

የእኔ የግዕዝ ቀመር ግንዛቤ እንደገለጻችሁት ከፊደል በላይ ነው :: ግዕዝ ቀመር የራሱ ዓለም ያለው ሆኖ ነው የተሰማኝ :: ወደ ግዕዝ ዓለም ስገባ ይችን ዓለም ትቼ በፊደላቱ ዉስጥ በመንሸራሸር ታሪክ አነባለሁ :: ግዕዝ ሕይወት ያለው መሳሪያ ነው ብል ማጋነን አይሆንም። ግዕዝ የፍቅርም ቋንቋ ሆኖ ነው ያገኘሁት :: ልጄን የተማርኩትን ላካፍለው ስሞክር ለእኔ የበለጠ የሚገለጽልኝ ነገር አለ :: አንዳንድ ጊዜ በመገረም ፣ በመደንገጥ ቆም ብዬ አስበዋለሁ ። የግዕዝ ቀመር በጣም ኃይል ያለው በመሆኑ ራስን ለበለጠ ደረጃ ማዘጋጃትም ያስፈልጋል :: ዘመኑ የነፋስ ዘመን በመሆኑ የመጀመሪያውን ክፍል ብቻ ነው የውስድኩት እናም recording'ኦቹን ሁሌ ቃል በቃል ነው ደጋግሜ የምሰማው ::
መምህራችንን መጋቢ ሐዲስ ዶ/ር ሮዳስን ቸሩ አምላካችን ይጠብቅልን :: የአገልግሎት ዘመኑንም ይባርክልን ::
ትላንት ከመላው ዓለም የሙሉ ጨረቃ ፎቶ የላካችሁልኝን በእጅጉ አመሰግናለሁ እጅግ በእናንተ ደስ ብሎኛል። ሰማይን መመልከት ከፍታ ነው።
የሚቀጥለው የመጋቢት ወር ሙሉ ጨረቃ ግን በተለየ መልኩ ደም መስላ የምትታይበት ክስተት ስለሚሆን ቀርጾ ለማስቀረት ሆነ ለመመልከት ከአሁኑ በጉጉት የምንጠብቀው ይሆናል።
(ዶክተር ሮዳስ ታደሰ)
ዛሬ ኀሙስ ከምሽቱ 3 ሰዓት (9 PM) ላይ Manyazewal Eshetu Youtube ላይ ኒኮላ ቴስላ
"If you want to find the secrets of the universe, think in terms of energy, frequency, and vibration."
(የአጽናፈ ዓለምን ምስጢር ለማግኘት ከፈለክ በኃይል፣ ድግግሞሽ (ዝውተራ) እና ንዝረት በኩል ዐስብ) ብሎ በተናገረው አስደናቂ አባባል እጅግ ምርጥ ፓድካስት ይኖረኛልና በሰዓቱ ይህ ምርጥ መርሐ ግብር አያምልጦት።
ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
[እግዝእትነ ማርያምን ለዚኽ አማላጅ የለኝም ዐጼ ምኒልክ በአምላክ እናት ስም ያደረጉት የክተት ዐዋጅና ቀደምት ነገሥታት ለአምላክ እናት ያላቸው ፍቅር]
በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ [በየካቲት 23፤ 2010 ዓ.ም. ከሌሊቱ 6 ሰዓት ተጽፎ በድጋሚ አሁን ፓስት የተደረገ]
በምንኖርበት ምድር ካሉ ሀገራት ሁሉ ስናወዳድር ለእመቤታችን ጥልቅ ፍቅር የነበራቸው ነገሥታት የነበሩባት ታላቋ ሀገር ኢትዮጵያን በቀዳሚነት እናገኛታለን፨ በኢትዮጵያ ነገሥታት ሢመት እመቤታችን በስደቷ ከልጇ ጋር የተገኘችበት ጣና ቂርቆስን ጨምሮ አክሱም ጽዮን ማርያም፣ ተድባበ ማርያም፣ መርጡለ ማርያም ተጠቃሽ ናቸው።

ይኸውም ከ3000 ዓመት በፊት የአማናዊት ታቦት የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ የኾነችው ታቦተ ጽዮን ወደ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ በቀዳማዊ ምኒልክ በኩል እንድትመጣ እግዚአብሔር ስለፈቀደልን፤ የአማናዊት ታቦት የእናቱ የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌዋን አስቀድሞ በኢትዮጵያ ሀገር ላይ አስቀመጠ፨ ለታቦቲቱ መምጣት ቀዳማዊ ምኒልክ ተጠቃሽ ነው።

ከቅድስት ድንግል ማርያም በቤተልሔም አምላካችን ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ወርቅ፣ ዕጣን፣ ከርቤ ይዘው እመቤታችንን ከልጇ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በዐይናቸው ካዩ ከነገሥታት ሰብአ ሰገል ውስጥ ኢትዮጵያውያን እንደነበሩ እነ ዳዊት በመዝ 71 (72)፥10፤ እነ ኢሳይያስ በትንቢቱ ምዕ 60፥1-6 ሲናገሩ ብዙ የታሪክና የነገረ መለኮት ሊቃውንት ጽፈዋል፨ https://youtu.be/Am5xFV51AtA

ይኽ የቅድስት ድንግል ማርያም የቃል ኪዳኗ በረከት በዚች ሀገር ላይ አለና በኢትዮጵያ ሀገራችን የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን በኹለቱ ወንድማማቾች ነገሥታት በአብርሃ እና በአጽብሐ ከ1680 ዓመት በፊት በ330 ዓ.ም. ላይ በአክሱም ላይ ሲያሠሯት በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ስም ሲኾን በዚያን ጊዜ ስትሠራ ባለ 12 መቅደስ ኾና በወርቅና በዕንቁ ያጌጠች ነበረች፨ በዚኽም ወንድማማቾች ነገሥታት አብርሃ ወአጽብሐ ለአምላክ እናት ያላቸውን ታላቅ ፍቅር ገልጸዋል።

አብርሃ እና አጽብሐ በ331 ዓ.ም. በቅድስት ድንግል ማርያም ስም በጎጃም ደግሞ ርእሰ ርኡሳንን መርጡለ ማርያምን ያነጹ ሲኾን "ወእምድኅረዝ ፈቀዱ አብርሃ ወአጽብሐ ከመ ይሕንጹ መቅደስ በህየ ወሐነጹ ማኅደረ ሠናይተ ወገብሩ አረፋቲሃ ዘወርቅ ወዘብሩር ... ወሰመይዋ ለይእቲ መቅደስ መርጡለ ማርያም ” (ከዚኽ በኋላ ነገሥታቱ አብርሃና አጽብሐ በዚያ ቦታ ቤተ መቅደስን ይሠሩ ዘንድ ወደዱ። ያማረች ማደሪያን ሠሩ። ግንቧን በወርቅ በብር ሠሩ። ... መቅደሷንም መርጡለ ማርያም ብለው ጠሯት) ይላል።

ከ515-529 ዓ.ም. የነገሠው ዐጼ ገብረ መስቀል ሲኾን በርሱ ጊዜ የነበሩት ከ9ኙ ቅዱሳን አንዱ አቡነ አረጋዊ ነበሩ። ከሊቁ ማሕሌታይ ቅዱስ ያሬድ ጋር ንጉሡ ዐጼ ገብረ መስቀል ደብረ ዳሞ ድረስ በመውጣት ለእመቤታችን ካለው ጥልቅ ፍቅር የተነሣ በተራራዋ ላይ እጅግ የምታስደንቅ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያንን አሠራ።

ቅዱስ ያሬድም ዐጼ ገብረ መስቀል ያሠራትን ይኽችን የእመቤታችን ድንቅ ቤተ ክርስቲያን ተመልክቶ "ዖድክዋ ዖድክዋ ወርኢኩ ሥነ ሕንጼሃ" (ዞርኳት ዟርኳት ያማረ የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኗን ውበት አየሁ) እያለ ዘምሯል፨

እመቤታችንን በፍጹም ልባቸው ያፈቅሩ ከነበሩት ነገሥታት መኻከል አንዱ ከቋጥኝ ደንጊያ ከዐለት ዓለም የሚደነቅባቸውን አብያተ ክርስቲያንን ያነጸው ከ1157-1197 ዓ.ም. ለ40 ዓመታት የነገሠው ዐጼ ላሊበላ ነው። ንጉሡ ለእመቤታችን ከነበረው ከፍቅሩ ጽናት የተነሣ ከሌሎች ኹሉ አስበልጦ የእመቤታችንን መቅደስ እጅግ ውብ አድርጎ በብሩህ ቀለማት በቅዱሳት ሥዕላት አስጊጦ በ12 ዐምዶች ያነጻት ሲኾን በውበቷ ተወዳዳሪ የላትም፨

እመቤታችንን ይወዱ ከነበሩ ቀደምት የኢትዮጵያ ነገሥታት ከ1365-1395 ዓ.ም. የነገሡት ዐጼ ዳዊት በጣም የሚታወቁ ሲኾን ለቅድስት ድንግል ማርያም ካላቸው ጥልቅ ፍቅር በመነሣት የእመቤታችንን ተአምር ከዐረብኛ ወደ ግእዝ ቋንቋ ካስተረጎሙ በኋላ በወርቅ ቀለም እንዲጻፍ አድርገዋል፨

ንጉሥ ዳዊት የእመቤታችን ፍቅር ውስጣቸው ድረስ ጠልቆ በመግባቱ ተአምሯ በወርቅ ቀለም በሚጻፍ ጊዜ ንጉሠ ነገሥት ዐጼ ዳዊት ዕንባቸውን ከቀለሙ ጋር እንዲቀላቀል በማድረግ ለመጀመሪያ ጊዜ ዕንባቸውን ከቀለሙ ጋር ጨምረው የእመቤታችን ተአምርን ያጻፉ የምድራችን የመጀመሪያው ንጉሥ ነበሩ ማለት ይቻላል፨

የእመቤታችን ፍቅር በእጅጉ የበዛላቸው ሌላው ንጉሥ የዐጼ ዳዊት ልጅ ዐጼ ዘርዐ ያዕቆብ ሲኾኑ በግብጽ የምትገኘው የእመቤታችን የደብረ ምጥማቅ ቤተ ክርስቲያን በግብጹ ንጉሥ ባርስባይ በግፍ መፍረሷን የግብጽ ፓትርያርክ አቡነ ዮሐንስ ፲፩ኛ ዐጼ ዘርዐ ያዕቆብ ለእመቤታችን ያለውን ጥልቅ ፍቅር ስለሚያውቁ ለርሳቸው ደብዳቤን በጻፉ ጊዜ ዐዝነው ካይሮ በፈረሰችው በእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን ስም ተጒለት ውስጥ አሠሩ፤ ከዚኽ ተነሥተው ዛሬ ድረስ በጻድቃኔ ደብረ ምጥማቅ ማርያም እመቤታችንን "የዘርዐ ያዕቆብ እመቤት" ይሏታል።

ብሔራውያን ሊቃውንት አባታቸው ዐጼ ዳዊት እመቤታችንን ከመውደድ የተነሣ መልክአ ማርያምን “ለዝክረ ስምኪ” ከሚለው ዠምሮ “ለገቦኪ” እስከሚለው እስከ ኹለተኛው ቤት “በከመ ዳዊት ይዜኑ” እስከሚለው ደርሰው ሲያቆሙ ፤ ልጃቸው ዐጤ ዘርዐ ያዕቆብ ደግሞ “ማርያም ድንግል ለያዕቆብ ሞገሰ ሥኑ” በማለት ቀጥለው እስከ መጨረሻው እንደፈጸሙት ይናገራሉ ፡፡ ሌሎች ሊቃውንት ደግሞ ንጉሡ ዐጼ ናዖድም እንደጻፈላት የሚገልጹ መምህራን አሉ፨ በዚኹ አጋጣሚ ሦስት የተለያዩ ዓይነቶች የመልክአ ማርያም መጻሕፍት ሲኖሩ እኔም ከአምላክ እናት በረከት ለማግኘት "መልክአ ማርያም ቀዳሚት፣ መልክአ ማርያም ካልዒት፣ መልክአ ማርያም ሣልሲት ሙሉ ትርጓሜያቸውን አዘጋጅቼ ለአንባብያን እንደቀረቡ መጽሐፉን ያነበቡ ያውቃሉ።

በአምላክ እናት ፍቅር ልባቸው በመቃጠሉ ዐጼ ዘርዐ ያዕቆብ በኹሉም አብያተ ክርስቲያናትን በእሑድ እና በበዓላት የእመቤታችን ተአምር እንዲነበብ ሲያደርጉ፤ ልክ እንደ አባታቸው እንደ ዐጼ ዳዊት የእመቤታችንን የተአምር መጽሐፍ ለተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ሲያጽፉ ዕንባቸው ከመጻፊያው ቀለም ጋር እንዲደባለቅላቸው ለጸሐፊዎቹ በመንገር ዕንባቸውን በማፍሰስ ታማልዳቸው ዘንድ ይማፀኗት ነበር፨

ከ1500-1532 ዓ.ም. የነገሡት ዐጼ ልብነ ድንግል የቀደሙት ነገሥታትን ሕይወት በመከተል ለቅድስት ድንግል ማርያም ካላቸው ጥልቅ ፍቅር በመነሣት በመጽሐፈ ሰዓታት ላይ የሚገኘውን "ለኖኅ ሐመሩና ስብሐተ ፍቁር ዘማርያም የሚለውን ድንቅ የምስጋና ድርሰት ለእመቤታችን ደርሰውላታል።

ሌላዋ በጣም የእመቤታችን ፍቅር በልባቸው ያደረባቸው ከ1723-1748 ዓ.ም. የነገሡት የዐጼ በካፋ ሚስት እቴጌ ምንትዋብ ሲኾኑ የእመቤታችን የስደቷና ቁስቋም የመቀመጧን ነገር ኹሌ የሚያስቡ ንግሥት ነበሩ፤ እመቤቴ ልጇን ይዛ ከሀገሯ ወጣ ብላ ቁስቋም እንደቆየች እኔም ከከተማው ወጣ ብዬ መቀመጥ እሻለሁ ብለው 5ት ኪሎ ሜትር ከከተማ ርቀው በአንድ ሺሕ የኢትዮጵያ የግንባታ ጠበብት የእመቤታችን የመንበረ ፀሓይ ቁስቋም ቤተ ክርስቲያንን ሲያሠሩ 500ው ቆመው ስሕተቶችን በመንገር ያስገነቡ ነበር።
ንግሥት ምንትዋብ የእመቤታችንን ስደት በማሰብ ዕንባቸውን ያፈሱ የነበሩ ንግሥት ሲኾኑ የእመቤታችን ስደቷን አስበው የፈቃድ ጾም የኾነውን ጾመ ጽጌን መጾም የጀመሩ ንግሥት ርሳቸው እንደነበሩ ሊቁ ዶክተር ሥርግው በመዝገበ ቃላታቸው ላይ ይገልጻሉ።

እመቤታችንን በፍጹም ልባቸው ይወዱ የነበሩት ታላቁ ንጉሥ ዐጼ ምኒልክ ሲኾኑ ከሚስታቸው ከእቴጌ ጣይቱ ጋር በመኾን በእመቤታችን ፍቅር እንጦጦ ማርያምን ካሠሩ በኋላ ለቅዳሴ ቤቷ ብዙ ሺሕ ሰንጋዎችን ያሳረዱ ሲኾን ጠጁ በገንዳ እንዲመላ በማድረግ ፍቅራቸውን ገልጠው ነበር። በበዓሉ ሰማዩ ጠቁሮ ሊዘንብ ሲል እመቤታችን ከልጇ እንድታማልዳቸው "ይድረስ ለድንግል ማርያም" የሚል ደብዳቤ ጽፈው የእመቤታችን መንበር ላይ እንዲቀመጥ ሲያደርጉ ወዲያው ዝናብን የቋጠረው ደመና ተበትኖ ፀሐይ በመውጣት ድንቅ ተአምር እንደተደረገ የታሪክ ምሁራን ይመሰክራሉ።

ኢትዮጵያን ለመውረር ወራሪው ጣሊያን ወደ ሀገራችን በከባድ መሣሪያ ታግዞ በዕብሪት ሲመጣ ንጉሡ የክተት ዐዋጅን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሲያውጁ የዐዋጃቸው ማተሚያ ኹሌም በፍቅር የሚወዷት እመቤታችንን በመጥቀስ "እግዝእትነ ማርያምን ለዚኽ አማላጅ የለኝም" በማለት ነበር ክተት ያወጁት።

በክተት ዐዋጅ ስሟን የጠሯት አፍጣኒተ ረድኤት የኾነችው የእመቤታችንን ታቦትና የፍጡነ ረድኤት የቅዱስ ጊዮርጊስን ታቦት አስይዘው በመኼድ ጨረቃ ሙሉ ኾና በታየችበት የካቲት 23 በ1888 ዓ.ም. የጣሊያንን ጦር በመደምሰስ እጅግ አስደናቂ ድልን በአህጉሪቱ በአፍሪካ በማስመዝገብ ለመላው የአፍሪካ ሕዝቦች የነጻነት ጮራ ዋና ወጊ በመኾን፤ መላው አፍሪካ የተጫነበትን የቅኝ ግዛት ቀንበርን ሰባብሮ እንዲጥል መርህ ኾነውታል፤ በእውነት ስሟን የጠሯት ወላዲተ አምላክ አላሳፈረቻቸውም።
https://youtu.be/owQnvzufsN0

ይኽ ፍቅራቸው በልጃቸው በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዐልፎ በአታ ለማርያምንና ሌሎች በእመቤታችን ስም የተሠየሙ አሠርተው፤ በሚያልፍ ዐጭር የሹመት ዘመናቸው የማያልፍ ታላቅ ሥራ ሠርተው ዋጋን ወደሚከፍለው ወደ ልዑል እግዚአብሔር ተጠርተው ኼደዋል፨

[በመጨረሻም ጽሑፌን ዐጼ ምኒልክን በቃል ኪዳኗ የተራዳችውን እመቤታችንን፤ በፈጣን ተራዳኢነቱ ያልተለያቸው ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስን አስቀድሞ በ530 ዓ.ም. ባመሰገነው በቅዱስ ያሬድ ቃል አበቃለሁ፦
"ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወላዕሌነ ይኩን ምሕረት በጸሎተ ጊዮርጊስ ዐቢይ ሰማዕት ወማርያም ወላዲተ አምላክ" [በሰማያት ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይኹን በታላቁ ሰማዕት በጊዮርጊስና አምላክን በወለደች በእመቤታችን ጸሎት የእግዚአብሔር ምሕረት በእኛ ላይ ይኹን] [ቅዱስ ያሬድ]
[በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ] [በድጋሚ ፓስት አረኩት]
YouTube Channel https://www.youtube.com/channel/UCFKnpmDyWe3LQ_9Gx3TMnAg
2025/07/06 04:57:33
Back to Top
HTML Embed Code: