Telegram Web Link
ይህ ማማረር ሳይሆን ትዝብት ነው...

በአገራችን ካሉ ግዙፍ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች መካከል ከአንዱጋ ስለ የዙፋን ልፊያ የቃለመጠይቅ ቀጠሮ ነበረን። እንዳላረፍድ ስላስጠነቀቁኝ በጊዜ ከቤቴ ወጣሁ። የቀጠሮችን እለት "በጊዜ ተገኝልኝ" ብሎኝ ነበር አስተባባሪው።... በጊዜ ተገኝ ካለኝ ከ30 ደቂቃ በኋላ ቀጠሮ መሰረዙን ነገረኝ።
የሚጠበቅ ነው!

ሰሞኑን ስለዙፋን ልፊያ ልናወራ ከአንድ ሬዲዮ ጣቢያ ጋር ቀጠሮ ነበረን። እሱም ተሰረዘ። አልገረመኝም።

የኛ አገር ሚዲያ ባህሪ አስቸጋሪ ነው። ሎቢ ማድረግ ይፈልጋል። "መጽሐፍ ፅፌያለሁና እንግዳ አድርጉኝ" እንድትሏቸው ይፈልጋሉ። ራስን ማሻሻጥ ላይ ጎበዝ ያልሆነ ስለስራው አይወራለትም።

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ስለ ዙፋን ልፊያ ለማውራት ቀጠሮ ከሰጡኝ በኋላ ቀጠሯቸውን የሰረዙ የዩቲዩብ ፥ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ሚዲያዎች አሉ።... የጠበቅኩት ነው። ገና የመጽሐፉን ርዕስ ሲያዩ "ይሄ ነገር..." ያሉኝ ብዙ ናቸው። አልፈርድባቸውም።

ማማረር አልፈልግም። ግን ደግሞ የተጋነነ ፍርሃት ትክክል አይመስለኝም።

ለማንኛውም ከዚህ በኋላ የዙፋን ልፊያን ለማስተዋወቅ የተሻለው ቦታ ማህበራዊ ገፅ ይመስለኛል።

መጽሐፉን ያነበባችሁ ሰዎች ሪቪው ብትፅፉ ደስ ይለኛል።

አቅም ያላችሁ ደግሞ መጽሐፉን ለሰዎች በስጦታ ብትሰጡ ሸጋ ነው።

ለምሳሌ ወንድማችን ቢላል ከዚህ ለ35 ሰዎች ዮሴፍ ኢየሱስ ወርቅ ደግሞ ለ10 ሰዎች የዙፋን ልፊያን ስጦታ ሰጥተዋል።

መጽሐፉን አምስትም አስርም እየገዙ ስጦታ መስጠት እኔን ማበረታታት ነው። ደግሞ ማንበብ የሚፈልጉ እንዲያነቡት ማገዝ ነው።
👍7
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
ቴዎድሮስ ፀጋዬ 🤝 የዙፋን ልፊያ

"ለሌሎችም አረአያ እንዲሆን ብዬ ነው የዙፋን ልፊያን የማነሳው"
👍2
‹‹... ‹ተደፈርኩኝ› ብዬ ለማዘን አቅም የለኝም፡፡ የመጣሁት ስለልጄ ወደፊት በመጨነቄ ነው››

‹‹ልጅሽን ምን አገኘው?››

‹‹የአራት ዓመት ልጅ አለኝ፡፡ ስለ እርሱ ተጨንቄ መ ሞ ቴ ነው፡፡ ጦርነቱ ሲጀምር ሕግ ጠፍቶ ስርዓት አልበኝነት ነገሠ››

አዛውንቱ የሚያውቁትን እውነት ደግመው እየሰሙ ነው፡፡ የእርስ በእርሰ ጦርነቱ ከጀመረ በኋላ የሐገሪቱ ሕግ ሕገ-ወጥነት እንደሆነ አስተውለዋል፡፡ የሐይማኖት አባቶች ጆሮ ሲነፈጉ፣ የእምነት ተቋማት አቅም ሲያጡ፣ የመብራት ከተማ አባቶች መደመጥ የማይችሉ ሲሆኑ፣ ሸንጎው መዘባበቻ ሲደረግ፣ ሥነ-ምግባር ለጉልበት ሲገብር፣ ሕግ ለአመፅ ሲሰግድ አይተዋል፡፡

‹‹ጉልበተኞች ባሌን አገቱት›› አለች ሕይወት

‹‹ጉልበተኞች ባሌን ካገቱተ በኋላ ማስለቀቂያ ገንዘብ ጠየቁኝ፡፡ የጠየቁኝን ያህል ገንዘብ ዘር ማንዘሮቼ ኖሯቸው አያውቅም፡፡ የማደርገው ግራ ቢገባኝ የልጄን አባት ለማስለቀቅ ለልመና ወጣሁ፡፡ የሆነብኝን እየተናገርኹ የመብራትን ሕዝብ ለመንኹ፡፡ህዝቡ አላሳፈረኝም ነበር፤ አጋቾቹ ግን አሳፈሩኝ፡፡ ገንዘቡን ከተቀበሉኝ በኋላ ባሌን ይለቁልኛል ብዬ ብጠብቅም እነርሱ ግን ‹ገንዘቡን የከፈልሽው የሰጠንሽን ቀነ ገደብ አሳልፈሽ ነው› ብለው ባሌን ገ ደ ሉ ት››

አዛውንቱ ‹የመብራታዊያን አባት› በመሆናቸው ሲደሰቱ ኖረዋል፡፡ ‹‹ፈጣሪ ስለወደደኝ መረጠኝ›› ይሉ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ በኋላ ግን ደስታቸው በምሬት ተተክቷል፡፡ ‹ምነው ባልተመረጥኩ› ማለት ጀምረዋል፡፡ የእርስ በእርስ ጦርነቱ ከጀመረ በኋላ በየዕለቱ ብዙ ሀዘን ይሰማሉ፡፡ ጫንቃቸው መቋቋም ከሚችለው የበለጠ የመከራ ታሪክ ያደምጣሉ፡፡

‹‹አባቴ ፈርቻለሁ›› አለች ሕይወት

‹‹እንደምሞት ታውቆኛል፡፡ ባሌ ከሞተ በኋላ ልጄን ለማሳደግ ብዙ ለፋሁ፡፡ እድሜ ለዐጦ ርነ ቱ ስራ ማግኘት በባዶ ሆድ ወደተራራ መሮጥ ሆነብኝ፡፡ ቢቸግረኝ ልመና ጀመርኩ፡፡ ጦ ር ነ ቱ ኩራቴን ወስዶብኛል፣ ክብሬን ቀምቶኛል፡፡ ልመናን ብቻ ሳይሆን ተገዶ መደፈርን በፀጋ መቀበል ቻልኩበት፡፡ ከአንድም ሦስቴ ተደፈርኩ፡፡ በህብረት ተፈራረቁብኝ፡፡ መደፈርን ይሄ ጦርነት ለሁሉም ሴቶች ያመጣው መርገም እንደሆነ ስላመንኩ ህመሜን ቻልኩት››

ህይወት እየተናገረች አዛውንቱ ወደ ውስጥ አለቀሱ፡፡

የጦርነት እሳት ከተለኮሰበት ቀን ጀምሮ የሴቶች ማሕጸን ጦር ሜዳ መሆኑ ያንገበግባቸዋል፡፡ ‹ሴት ስትጠቃ ሐገር ትጠቃለች› ይላሉ አዛውንቱ፡፡

‹ሴት የቤተሰብ ማገር ናት፡፡ የተጠቃች ሴት ለመንፈስ ህመም ተጋላጭ ትሆናለች፡፡ ሥነ-ልነቦናዋ ይታመማል፣ የአዕምሮ ጠባሳ ይፈጠርባታል፡፡ ሥነ-ልቦናዋ የተጎዳ ሴት ቤተሰብ ስትመሠርት ቤተሰብዋ ለህመም ተጋላጭ ይሆናል፣ የታመመ ቤተሰብ የታመመ ልጅ ይፈጥራል፣ መንፈሱ የታመመ ልጅ የሐገር ስጋት ነው› ይላሉ አዛውንቱ፡፡
‹የሰለጠነ ሕዝብ ለደካሞች ይሟገታል፡፡ ጉልበተኛ ወንድ ደካመዋን ሴት ሲያጠቃ ጠበቃ መሆን ማህበረሰባዊ ግዴታ ነው› ይላሉ አዛውንቱ፡፡

‹ጉልበተኞች ደካሞችን ሲያጠቁ ዝም ማለት ሐገር እንድትፈርስ መፍቀድ ነው፡፡ ወንድ ሴትን ሲያጠቃ ዝም የሚል ሰው ጉልበተኛው ደካማን እንዲያጠቃ ፈቅዷል፡፡ ይህ ማለት ሀብታም ድሃን እንዲበድል፣ በቁጥር ብዙ የሆነ ጥቂት የሆኑትን እንዲያጠቃ፣ ስልጣን ያለው ስልጣን አልባው ላይ እንዲሰለጥን መፍቀድ ነው፡፡ ጉልበተኛ ጉልበት የለሽን ሲያጠቃ ስርዓት አልበኝነት ይፈጠራል፡፡ ስርዓት አልበኝነት ደግሞ ሐገር ያፈርሳል› ይላሉ አዛውንቱ፡፡

‹አስገድዶ የሚደፍር ወንድ ማህበራዊ ግኑኝነት ላይ ጥቃትን ይፈፅማል፡፡ እርስ በእርስ እንዳንተማመን የሚያደርግ መርዝን ይረጫል፡፡ ማህበራዊ ግኑኝነትን ያላላዋል› ይላሉ አዛውንቱ

‹አስገድዶ ደፋሪ፣ ወንድነት ላይ ጭምር ጥቃት አድራሽ ነው፡፡ ደፋሪዎች ሌሎች ወንዶች እንደ አውሬ እንዲታዩ ያደርጋሉ፡፡ ወንዶች ጠባቂዎች ተደርገው መቆጠር ሲገባቸው እንደስጋት እንዲታሰቡ ሰበብ ይሆናሉ› ይላሉ አዛውንቱ፡፡

‹‹አባቴ›› አለች ሕይወት እንባዋን እየጠረገች

‹‹እያደመጥኩሽ ነው፤ ቀጥይ ልጄ››

‹‹በልመናው ብዙ አልቆየሁኝም፡፡ ሁሉም ህዝብ ለማኝ ሆኗል፡፡ ትላንት ለተቸገሩት ይረዱ የነበሩ ዛሬ እርዳታ ፈላጊ ሆነዋል፡፡ ቸርነትን ለማድረግ ይዘረጋ የነበር እጅ ለእርዳታ ፍለጋ ሲዘረጋ አየን፡፡ ለማኙ ሲበዛ ልጄን ለምኜ ማብላት ቸገረኝ፡፡ ያኔ ገላ ሽያጭ መፍትሄ መሰለኝ፡፡ ከልመና ወደ ሽርመጥና ገባሁ፡፡ … እድሜ ለጦርነቱ አቻዎቼ በመደዳ ሴተኛ አዳሪ እየሆኑ ነው፡፡ ስህተት እና ትክክሉ ድንበሩ ጠፍቶብናል፡፡ ለእኔና ቢጤዎቼ ትክክል ማለት ራስን በሕይወት ማቆየት ሆኗል››

አዛውንቱ ጦርነቱ የተጀመረበትን ቀን ረገሙ፡፡ በሐገሪቱ ምን እየተደረገ እንዳለ የማያውቁ ሚስኪኖች በጦርነቱ የተነሳ የተጫነባቸውን የመከራ ቀንበር አስበው ጦርነቱ የጀመረበትን ቀን ረገሙት፡፡

‹‹አባቴ ሰሞኑን የምሞት ይመስለኛል፡፡ የስኳር ህመም እያሰቃየኝ ነው፡፡ መድሀኒት የለኝም፡፡ መድሀኒት መግዣ አላጣሁም፤ ያጣሁት መድሀኒት ነው፡፡ ሁለቱ ተዋጊዎች በዙሪያችን መፋለም ከጀመሩ በኋላ ወደ ከተማችን መሠረታዊ ነገሮችን ማስገባት ከባድ ሆኖብን መክረሙን ያውቁታል፡፡በዚህ የተነሳ በከተማችን መድሀኒት ጠፍቷል፡፡ የምሞት እየመሰለኝ ስለልጄ ፈራሁኝ አባቴ››

አዛውንቱ እንባቸውን ለመገደብ ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸው ቆይተው የነበረ ቢሆንም ተሸነፉ፣ ለእንባቸው ተረቱ፡፡ አንገታቸውን አቀርቅረው አለቀሱ፡፡

የለቅሷቸው ሰበብ ጉዳቷ ብቻ አልነበረም፡፡ በየዕለቱ ብዙ ሰቆቃ ያደምጣሉ፣ ችግር ሲያደምጡ ነግቶ ይመሻል...

ያስለቀሳቸው የሕይወት ስሜት ነው፡፡

በፊታቸው ሆና ብሶቷን የምትናገርው ምስኪን ሴት ገፅታ ላይ የተመለከቱት ስሜት አስነባቸው፡፡ ‹‹ሀዘኗ ከህመሟ አይነፃፀርም፡፡ ማዘን በሚገባት መጠን እንዳታዝን ያደረጋት መከራን መለማመዷ ነው›› ብለው ሲያስቡ አለቀሱ፡፡

‹‹መከራን እንደመልመድ ያለ መከራ ከወዴት ይገኛል?››

#የዙፋን_ልፊያ

መጽሐፉን ያላነበባችሁ አንብቡ፥ ያነበባችሁ ሃሳባችሁን አጋሩ።


@Tfanos
4
የአንባቢ አስተያየት

መጽሐፍህን አንብቤ ጨረስኩት። በስራ መደራረብ ምክንያት ለንባብ ጊዜ አላገኘሁም ነበርና፡ ትላንት ነው የጀመርኩት። ጀምሮ ለማቆም ይከብዳል። እያንዳንዱ ገፀ ባህሪ የሚወክለው ስብእና (ፖለቲካችን፥ ኋላ ቀር እምነታችን፥ የስነ አይምሮ በሽታ/ጠባሳ፥ ..) መማር ለሚፈልግ ብዙ ዕውቀት ይሰጣል።

በውስን ገፆች ብዙ subject ያካተተ ድንቅ መጽሐፍ ነው የጻፍከው፡ ጥልቅ አንባቢ መሆንክን ተረድቻለሁ ("አንተ ከተረዳኸኝማ ምኑን አንባቢ ሆንኩት" እንዳትለኝ አደራ 😊)።

ወቅታዊ ሁኔታ ስጋት ጥሎብን ለመናገር ምንፈራቸውን አሁናዊ እውነታዎችና የወደ ፊት ስጋቶች poetic በኾነ መንገድ ከትበህ voice of the voiceless ስለሆንከን ከልብ አመሰግናለሁ። የጻፍክበት ዓላማ ከግብ እንዲደርስ እመኛለሁ።

በርታ!

አስተያየቱን ያጋራን Henisha Henishom ነው።

#የዙፋን_ልፊያ

መጽሐፉን ያላነበባችሁ አንብቡ፥ ያነበባችሁ ሃሳባቾሁን አጋሩ
5🔥1
ለልደቱ አያሌው

ከአክብሮት ጋር

#የዙፋን_ልፊያ 🤝
"ወንድ ልጅ ከሃያዎቹ በኋላ ያለው ህይወት ከአትሌቲኮ ማድሪድ ጋር መጫወትን ይመስላል?"

... አትሌቲኮ ግብ ካስቆጠረ በኋላ ከነሱጋ መጋጠም...


@Tfanos
አትሌቲኮ ተከላካይ ቡድን ነው። አንዴ ግብ ቀድሞ ካስቆጠረ በኋላ ፈፅሞ ይከላከላል። አትሌቲኮ ላይ ግብ ማስቆጠር ከባዱ ስራ ነው
👏4
የአንባቢ አስተያየት

ትዝታን ማን ፈጠረዉ?

የተሰበረ ልብ ያላቸዉ ሰዎች በጥሩም ይሁን በመጥፎ ጊዜ ፥ ትዝታቸውን ማን ፈጠረው?

መጥፎ ትዝታ በሰዉ ልጅ ላይ አሳርፎ ከሚያልፍ ነገር መካከል ዋነኛው ጦርነት ነው። ጦርነት ብዙ ሊባልለት የሚገባ ቢሆንም ዝምታን መርጠናል። ስለ ጉዳዮ በምሬት የያነሱትም ይፈረጃሉ። እንደ ፓለቲካኛ እና የአንድ ወገን ደጋፊ ተድርገው ይቆጠራሉ።

የጦርነት አጀንዳ በፅንፈኝነት ሰበብ ተደባብሶ ያልፋል። አንዳንዴ ደግሞ "ጦርነት ዛሬ ነዉ ወይ የተጀመረዉ? ምነዉ አዲስ ሆነባችሁ?" አይነት የስላቅ ጥያቄ ይነሳል።
እይታችን ምንም ሆነ ምን ጦርነት disaster ነዉ።

የዙፋን ልፊያ የጦርነትን ጅራፍ በmass ሳይሆን በነጠላ ያስቃኛል። እያንዳንዳችን ልብ ላይ ያረፈዉን ጅራፍ ያስታዉሰናል።

የዙፋን ልፊያን ሳነብ ጦርነቶ እንዴት ሰባሪ እንደሆነ ተረድቻለሁ። መጽሐፉን እያነበብኩት ከ 2 ገፅ ማለፍ ያቅተኝ ነበር። ብዙ ጊዜ ሰዉነቴ ሲቆጣ ፥ ሲከፋኝ ፥ ግፋ ሲልም ጉሮሮዬ ላይ ማላቀዉ ነገር ሲመረኝ እና ሳለቅስ እራሴን አግኝቼዋለሁ።

ለእኔ ለአንዲት ድሃ ሴት ጦርነት የሚያመጣዉን ዉድመት ተስፋአብ ብዙ ቃላት ሳያባክን ገልፆልኛል። የጦርነትን ግፍ፣ የግብዝነትን ጥግ ማወቅ እና መጠንቀቅ ከፈለጋችሁ የዙፋን ልፊያን አንብቡት

አስተያየቷን ያጋራችን አርሴማ ረታ ናት

የዙፋን ልፊያን ያላነበባቾሁ አንብቡ ፥ ያነበባችሁ ሃሳባችሁን አካፍሉ

@Tfanos
3
ለአሜሪካ አንባቢዎች ፥

"የዙፋን ልፊያ" ን ማንበብ የምትፈልጉ ፥ በአሜሪካ የምትኖሩ ሰዎች ጥቂት ኮፒ ተልኳል። መጽሐፉን የምትፈልጉ ፃፉልኝ

@Jtesfaab
2
አሜሪካ ያላችሁ
እስኪ እንያችሁ

የዙፋን ልፊያ ውቂያኖስ አቋርጣ ፥ አሜሪካ ደርሳለች።

መጽሐፍ ወደ አሜሪካ መላክ እጅግ አስቸጋሪ ነው። ፖስታ ቤት ውድ ገንዘብ ያስከፍላል። ከጥቂት ኮፒ በላይ መላክ ክልክል ነው። በእርግጥ እዚህ ሐገር የመጽሐፍ ስራ አደንዛዥ እፅ ማዘዋወርን ይመስል ተግዳሮት ይበዛበታል።

ቢሆንም ጥቂት ኮፒ ለአሜሪካ አንባቢ ተልኳል።

በአሜሪካ ያላችሁ ፥ የዙፋን ልፊያን ማንበብ የምትፈልጉ ልታናግሩኝ ትችላላችሁ።

የተላከው ሳያልቅ የራሳችሁን ኮፒ አስቀሩ።


መጽሐፉን የምትፈልጉ @Jtesfaab ላይ ፃፉልኝ
ዘሪቱ ከብዙ ወንድጋ ተኝቻለሁ ብላለች?

ብዙ ሰው የዘሪቱን መጽሐፍ ያነበበ አይመስለኝም። ያነበበ ሰው መጽሐፉ ላይ በሌለ ሃሳብ አይዘምትባትም።

መጽሐፉን አንብቤዋለሁ።ዘሪቱ "ከብዙ ሰውጋ ተኝቻለሁ" አላለችም። አዎ አላለችም።

ዘሪቱ በ ዝ ሙ ት ሀጢያት ወድቃ እንደምታውቅ በግልፅ ፅፋለች። ሃጢያቷን የገለፀችው ስለ እግዚአብሔር ፀጋ ለማስረዳት ነው። "በሰው ፊት እንዳፃዲቅ በምቆጠርበት ፥ እኔም ራሴን እንደ ፃዲቅ በምቆጥርበት ወቅት ወደቅኹ" አለች።

ሰዎች በመውደቅ ጭምር ከራሳቸው እንደ አዲስ ይተዋወቃሉ። ከራስ መተዋወቅ ደካማ እና ሃጢያተኛ መሆንን መገንዘብ ነው። ሃጢያተኝነቱን የተረዳ የእግዚአብሔርን ምሕረት እና ፀጋ ይረዳል። ዘሪቱ መጽሐፍ ላይ ያለውም ይሄው ነው።

ይልቅ ዘሪቱ ስለ ውድቀቷ የፃፈችው ላይ መጠነኛ ቅሬታ አለኝ። ውድቀቷ የእግዚአብሔርን ፀጋ እንድታውቅ እንደረዳት ግልፅ ቢሆንም ጉዳዩ በተሻለ ጥልቀት መብራራት ነበረበት።

የህይወት ታሪክን ከማንበብ ጥቅሞች መካከል አንዱ ከሌላው የህይወት ጉዞ መማር ነው።

ደካሞች ነን። ከኛጋ ድካም የሚጋራን ሰው የህይወት መንገድ ማወቅ ይረዳናል። ዘሪቱ ስለ ውድቀቷ ስትፅፍ በተሻለ ጥልቀት ብትፅፍ ጥሩ ነበር።

ለውድቀቷ የዳረጓትን ገፊ ምክኒያቶች ፥ አስቻይ ሁኔታዎች ፥ ስነልቦናን ወዘተ ብትነግረን ሌሎቻችን ለምን እንደምንወድቅ እንድንገነዘብ ይረዳን ይሆናል።

ከችግሩ ነፃ ስትወጣም እንዴት ባለ መንገድ ነፃ እንደወጣች በተሻለ ጥልቀት ብታስረዳን ጥሩ ነበር።

ዘሪቱ በ ዝ ሙ ት የወደቀችባቸውን አጋጣሚዎች በግልፅ ፅፋለች። ነገር ግን ከብዙ ወንድ ጋ ተኝቻለሁ አላለችም። ይልቅ "ይሄ /መወደቋ/ የሁልጊዜ ተግባሬ ሳይሆን አልፎ አልፎ የሚፈትነኝ ድካሜ ነው" ብላለች።

Via ተስፋኣብ ተሾመ

@Tfanos
4👍4
ፕሮቴስታንት ላይ የሚወረወር እያንዳንዱ የጥላቻ ቀስት እኔንም ይ ወ ጋ ኛ ል። ለፕሮቴስታንት የታቀደ ጥ ላ ቻ ወለድ ጦ ር ሳይወጋኝ አያልፍም። ለወገኖቼ የተወረወረ ድን ጋ ይ እኔን ማግኘቱ አይቀርም።

ወገኖቼን አትንኩ!

ቸርች መሄድ ካቆምኩ አመታት ተቆጥረዋል። በማውቀውና በማላውቀው ምክኒያት ህብረት ማድረግ አቁሜያለሁ። ከፀልይኩ ብዙ አመቴ ነው። አንዳንዴ የተማርኩትን ሀይማኖታዊ ትምህርት እጠረጥራለሁ። የእምነቴ መስመር ከወገኖቼ እምነት መስመር ከተለየ ቆየ። አንዳንዴ ከሀይማኖት ወገኖቼ የተበጠስኩ ያህል ይሰማኛል። ቢሆኑም ወገኖቼ ናቸው። ሲነኩ ያመኛል። በነገር ቀስት ሲ ወ ጉ ልቤ ይደማል። የሚወረወርባቸው ድ ን ጋ ይ እኔም ይሰብረኛል።

ወገኖቼን አትንኩ!

እኔ ዘንድ በጎ ፍሬ ካለ ዘሩን የዘራችው ያደግኩባት ቃለ ህይወት ቤተ ክርስቲያን ናት። ምናልባት አንዳች ጥሩ ነገር ካለኝ ያንን ጥሩ ነገር ያገኘሁት ከቸርች መጋቢዎቼ ነው። የፓስተር አበበ ፈረንጅ የደህንነት ትምህርት ፥ የፓስተር ሀብቴ አሰፋ የደቀ-መዝሙርነትና የአገልግሎት ትምህርት ፥ የመምህሬ ሙልዬ የልጅነት ትምህርት ፥ የወንጌላዊ በላይ ቦርኩ ምክሮች ናቸው የሰሩኝ። እኔን የሰራኝ የፕሮቴስታንት ትምህርት ነው።

ወገኖቼን አትንኩ!

ከትምህርት ጋር የተዋወቅኩት በቃለ-ህይወት በኩል ነው። ፊደል ያስቆጠሩኝ ፥ የሂሳብ ስሌቶችን ያስተማሩኝ ፥ ማንበብ ያለማመዱኝ የቸርች መምህራን ናቸው።
ወንጌላዊ ስምኦን ፥ መምህር አለማየሁ ፥ ወንጌላዊ ተሻገር... ወዘተ እንዴት ረሳቸዋለሁ?

ወገኖቼን አትንኩ!

ትዝታዬን ከፕሮቴስታንት መነጠል አልችልም። ያለ ፕሮቴስታንት ወገኖቼ ምንም ነኝ። ሰው ያደረጉኝ እነሱ ናቸው። ፍቅር አስተምረውኛል።
ልጅ ሆኜ የተረት መጻሕፍት አላነበብኩም። ይልቅ ለሕፃናት የተዘጋጀ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክን አነብ ነበር። ከፍ ስል ወንጌላዊ ተስፋዬ "የሰው ልብ" የሚል መጽሐፍ አስነበበኝ። ያኔ እድሜዬ 11 ነበር። ቀጥሎ ደግሞ ወንጌላዊ ወርቅነህ መንፈሳዊ መጽሔቶችን አስተዋወቀኝ።
ሴኩላር መጻሕፍት ያገኘሁት ዘግይቼ ነው። ከዛ በፊት አነባቸው የነበሩት መጻሕፍት የነበረው የነዶክተር መለሰ ወጉን መጻፍት ነበር። በእርግጥ አይገባኝም ነበር።

ወገኖቼን አትንኩ

ፕሮቴስታንት ማለት ትዝታዬ ነው። ማንም ትዝታዬ ላይ ሲዘባበት ደስ አይለኝም። ፕሮቴስታንት ከእውቀት ጋር መተዋወቂያ በር ሆኖኛል። ፕሮቴስታንት ስነልቦናዬን ቀርፆኛል። ፕሮቴስታንት ብዙ ነገሬ ነው።
ኪነ-ጥበብን የተዋወቅኩት በቸርች በኩል ነው። ድራማ መፃፍ ፥ መግጠም ፥ ልብወለድ መድረስን የተማርኩት በቸርች በኩል ነው።

ልጆች ሆነን ድ ን ጋ ይ ይወረወርብን ነበር። እንሰደብ ነበር። ዛሬም እንደትላንቱ ማድረግ የሚፈልጉ እንዳሉ አውቃለሁ። እነሱን "እንከባበር" ማለት ያስፈልጋል።

ወገኖቼን አትንኩ!

ግማሽ አካሌ ፥ ትዝታዬ ፥ ቤተሰቦቼ ፥ ገጠመኞቼ ሁሉ ከፕሮቴስታንት ጋር የተሳሰረ ነው። ስለዚህ ወገኖቼ ላይ የሚሰነዘር ጥ ላ ቻ ወለድ ቀስት ልቤን ያደማዋል።

ወገኖቼን አትንኩ! እነሱን ስትነኩ "እኔም ከእነሱ እንደ አንዱ ነኝ" ብዬ እመጣለሁ


@Tfanos
13👍2👎2
ያየሰው ሽመልስ ፥ ስለ ዙፋን ልፊያ መጽሐፍ!

የዙፋን ልፊያን አነበብኩ

መፅሀፍ ቅዱሳዊው አፃፃፍ ድንቅ ነው። በመጀመሪያዎቹ ገፆች ላይ የጀመርከው አፃፃፍ መፅሀፈ መክብብን የማነብ እስኪመስለኝ ሰቅዞኝ ነበር።

(እስከመጨረሻው ብታዘልቀው ያ አፃፃፍ መፅሐፍ ቅዱስ ሊትሬቸሩ ሃያል እንደሆነ የምትመሰክር ተጨማሪ ሰው ያደርግህ ነበር። የበዓሉ ግርማ ፀጋዬ ሃይለማርያም ''መፅሐፍ ቅዱስን የምወደው በሊትሬቸሩ ነው" ይላት ነበር ለሮማን። አለማየሁ ገላጋይ አንዱን መፅሀፍ ሙሉውን የፃፈው እንደ መሀልየ መሀልየ ዘሰለሞን ነው።( የተጠላው እንዳልተጠለን መሰለኝ)። የዙፋን ልፊያ በዚያ ቅርፅ መቅረብ ጀምራ ከጥቂት ገፆች በኋላ እየረሳችው ትሄዳለች)

በውነቱ ቅርፁ ድንቅ ነው። የታሪክ አቀራረቡና አመራረጡ አስገራሚ ነው። የመረጣቸው ሰዎችና እንስሳት ይደንቃሉ። (በመጽሐፉ የተጠቀሰውን ው ሻ ው ን "መቻል" የመሰለ አስር ታማኝ ሰው ብናገኝ አገራችን ኮሽ የሚል ነገር የሚሰማባት አይመስለኝም። ችግሩ ጡቱ ነው። የሕይወት ጡ ት። ያጋድለናል)!

መብራት የምትባል በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የምትኖር ከተማ፣ "አልፈርስም" የሚል ተረት አላትና አልፈርስም ስትል ኖራ ትንኮታኮት ዘንድ ድ ን ቁር ና ሚናው ትልቅ ሆኗል። ሰላም ጠልነት፣ነግበኔ አለማለት አገርን ያፈርሳል። የሚተዋወቁ ሹሞች፣ የማይተዋወቀውን ሰው ፀባቸውን የማያውቀውን ወገን አጫረሱት። አንዱ ሕዝብ ወደ ሌላው ሕዝቡ እንዳይሄድ አደረጉት። የሴቶችን ገላ ጦርሜዳ አደረጉት! ያላደረጉት የለም!

poor them!

"እንዲህ ያለ ነገር በኢትዮጵያ ውስጥ ለመፃፍ ማሰብህ አስገርሞኛል" ማለት አለብኝ። ስለ ሰላም አስፈላጊነት ፣ ስለ ጦርነት ጎጂነት መፃፍና መናገር ሲያሰቅልና ሲያስወነጅል ያየን ትውልዶች ነን። ሰላም ይሻላል ብሎ መናገር ሰዎችን ለስደትና ለሞት የዳረገ ፖሊሲ መሆኑን ያየን ምስክሮች ነን።

ጀነራልና ፕሬዚዳንት ተጣሉ ተብሎ የሚጎዳውን የሚጨፈለቀውን የሳር ዓይነትና ብዛት በየገፁ ላይ መተረክ? ተቻለ እንዴ?

የመብራት ከተማ ሰዎች መብራታቸውን ሲያወድሙ፣ አገራቸውን ሲያፈርሱ ጠቆም ማድረግ ተቻለ እንዴ?

አንተ ግን ቻልክበት

መፍትሄው ግን ይሄው ነው። ሰው የሚሞትበትን ፣ አገር የሚወድምበትን ጦርነት "war is always unjust" እያልን መፃፍ፥ መናገር፤ ለዚህም ሲባል የሚመጣውን ቀራኒዮ መቀበል! ቢያንስ ትራስህ በወቀሳ ሲነዘንዝህ አታድርም! እንደ መ ን ጋ ው፣እንደ ጀኔራሉ፣ እንደ ፕሬዚዳንቱ አለመሆን... በእጄ ደ ም አለ ብሎ አለመሳቀቅ...ሰው ለሚሞትበት ነገር አንድ ግራም ጉልበት አለማዋጣት...የሕይወት ስንቅና መርህ መሆን አለበት!

በተቀረ

ጦርነት ነጋዴዎች አሉት፤ ሀብት የሚዝቁ አንድ ሰው በሞተ ቁጥር አስር ሺህ ዶላር የሚዝቁ፣ አንድ ጥይት በተተኮሰ ፍጥነት ሀብታቸው የሚተኮስ...! የዙፋን ልፊያ ላይ ተረስተዋል።

እንደገና በተቀረ...

ስለ እስር፣ ስለ መታሰር፣ በዘር መርጦ በመልክ አይቶ ስለማጎር የመብራት ከተማ ሰዎች አይመለከታቸውም?

ብርትት በልልኝ! ደጋግመህ ይሄን ጉዳይ ብትፅፈው የግራ እጅ ጣት የማይሞላ አሀዝ ካላቸው የትውልዳችን የሰላም ሰባኪያን ውስጥ መሆንህ ነው።

ስለተሰጠኝ privilege አመስጋኝ ነኝ።

በዘመናችን ውድ ምርቃት ልሰናበትህ!

ውለህ ግባ!


@Tfanos
👏3👍2
ማስታወሻ ፥ አሜሪካን ሐገር ያላችሁና መጽሐፉን የምትፈልጉ ለአሜሪካ ገበያ ከሚያከፋፍለው Yoseph Yeyesuswork ማግኘት ትችላላችሁ

@Jtesfaab ብትፅፉልኝ አድራሻውን እሰጣችኋለሁ

ማስታወሻ ሁለት ፥ መጽሐፉን ማንበብ እየፈለጉ እጅ ላጠራቸው ስፖንሰር መሆን የምትፈልጉ በውስጥ @Jtesfaab ፃፉልኝ

ማስታወሻ ሦስት ፥ መጽሐፉን ያነበባችሁ ሪቪው ፃፉ
2025/10/25 03:55:15
Back to Top
HTML Embed Code: