Telegram Web Link
TIKVAH-ETHIOPIA
“ ... 1,500 ካ/ሜ ግሪን ኤርያውን 12 ወጣቶች መጥተው አጠሩት ” - ቅሬታ አቅራቢዎች በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፤ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 አካባቢ በሚገኘውና በ1979 ዓ/ም ለ “ አዲስ አበባ 100ኛ ዓመት ቤት ሥራ ማኀበር ” ተሰጥቶ ነበር የተባለ 1500 ካ/ሜ መሬት የመከነ ማስረጃ ባቀረቡ ሰዎች መታጠሩን ማኅበሩ ገለጸ። ቦታው በ1979 ዓ/ም ለማኀበሩ ከተሰጠ ጊዜ…
#Update

በአዲስ አበባ ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ወረዳ 1 ጀርመን አደባባይ አካባቢ የሚገኘውና በ1979 ዓ/ም ለ “ አዲስ አበባ 100ኛ ዓመት ቤት ሥራ ማኀበር ” ተሰጥቶ ነበር የተባለ 1,500 ካ/ሜ መናፈሻ መሬት የመከነ ማስረጃ ባቀረቡ ሰዎች መታጠሩን ማኀበሩ መግለጹን መረጃ አጋርተናችሁ ነበር።

ከዚያ ወዲህ ምን ተፈጠረ ?

የማኀበሩ አባላት ትላንት (ዓርብ ሚያዚያ 18 ቀን 2016 ዓ/ም) ከምሽቱ 3 ገደማ በሰጡት ቃል፣ “ ጨለማን ተገን አድርገው የግንባታ እቃዎች አስገብተዋል ” ብለዋል።

“ ደንቦች ቢባል፣ ሰላምና ጸጥታ ቢባል ምንም ሊፈይድልን አልቻለም። አሁን ለሕይወታችን ሁሉ እየፈራን ነው። የ70 ዓመት አረጋዊ ገፍትረው ጣሉ አታስገቡም ብሎ ሲከለክላቸው ” ሲሉም ወቅሰዋል።

የጸጥታ አካላት መፍትሄ እንዲሰጧቸው ቢጠይቁም ፈቃደኛ እንዳልሆኑላቸው ገልጸው፣ “ የለፋንበት፣ ወጪ ያወጣንበት ቦታ ነው። ኃላፊነት የጎደለው ነገር እየተሰራ ነው ” ብለዋል።

ታጠረ የተባለው ግሪን ኤሪያ ጀርመን አደባባይ አካባቢ የተባበሩት ነዳጅ ማደያ ወደ ውስጥ 300 ሜትር ገባ ብሎ መሆኑን አመላክተዋል።

ለቅሬታው ምላሽ እንዲሰጡ የጠየቅናቸው አንድ የደንብ ማስከበር አካል፣ ጉዳዩን በዝርዝር ከሰሙ በኋላ ምላሽ ለመስጠት የማይመች ቦታ ላይ እንደሆኑና ከቆይታ በኋላ እንዲደወል ቢጠይቁም ፣ በድጋሚ ሲደወል ስልክ ለማንሳት ፈቃደኛ አልሆኑም።

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
#ICS

የሕዝብ ተ/ም/ቤት የሕግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ፤ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎትን የ9 ወር አፈጻጸም ትላንት ገምግሟል።

ኮሚቴው ከዚህ ግምገማ በፊት ማለትም ሚያዚያ 3/2016 ላይ #ድንገተኛ ምልከታ አድርጎ ነበር።

ቋሚ ኮሚቴው ምን አለ ?

- ምንም እንኳ የተጀመሩ ሥራዎች ጥሩና ተስፋ ሰጪ ቢሆኑም በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ችግሮችን እና የተገልጋይን ቅሬታ መፍታት አልተቻለም።

- ተገልጋዮች አገልግሎት ለማግኘት ብለው በሚደርስባቸው እንግልትና ስቃይ ምክንያት በተቋሙ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ቅሬታ እንደሚያቀርቡ በድንገተኛ ምልከታ መመልከት ተችሏል።

- በዋና መ/ ቤቱ ተገልጋይ በተቋሙ ሠራተኞች ፦
➡️ #መሰደብ
➡️ #መመናጨቅ
➡️ #መገፍተር_ጭምር የሚደርስበት በመሆኑ ተገልጋይ በሥነ ምግባር መስተናገድ አለበት።

- በአዲስ አበባ " ካሳንቺስ አካባቢ " የሚገኘዉ የውጪ ዜጎች አገልግሎት ተቋም የሚሰጠው አገልግሎት ኢትዮጵያን የማይመጥን፣ ምቹ ያልሆነ እና የንጽህና ጉድለት ያለው ነው። ይህ መታረም አለበት።

- ዋናው መስሪያ ቤት ለአገልግሎት ምቹ ያልሆነ፣ ሕንፃው የቆየ እና አስፈላጊዉን የማሻሻያ ጥገና ያላገኘ ነው። ሕንፃው ከተቋሙ አገልግሎት አሰጣጥ ባህሪ ጋር የማይጣጣም ስሪት ያለው ነው።

- በዋና መስሪያ ቤት ያለው መጨናነቅ እንዲቀንስ በአዲስ አበባ ከተማ ከአምስት ያላነሱ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች እንዲከፈቱ የመፍትሔ ሃሳብ ቢሰጥም አልተፈጸመም። በተለይ በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ የማስፋፋት ሥራዎች መሠራት አለበት።

- የደላላ ሰንሰለት በመለየት ማቋረጥ ያስፈልጋል።

- አሁንም ከደላሎች ጋር የሚመሳጠሩ የተቋሙ #ሠራተኞች በመኖራቸው ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አለበት።

- የሠራተኛ ባጅ አለመኖሩም ሊታሰብበት ይገባል።

በምክር ቤቱ የተገኙት የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ለተነሱት ጉዳዮች ምላሽ ሰጥተዋል።

ያንብቡ ፦ https://telegra.ph/EPA-04-27-2 #EPA

@tikvahethiopia
" ኑሮ ውድነቱ መፍትሄ ይሻል። መፍትሄ እንሻለን " - የኢሰማኮ ፕሬዝዳንት ካሳሁን ፎሎ 

የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ የስራ ግብር እንዲቀነስ ፤ የዝቅተኛ ደመወዝ ወለል የሚወስን የደመወዝ ቦርድ እንዲቋቋም እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።

የኢሰማኮ ፕሬዝዳንት ካሳሁን ፎሎ ከኑሮ ውድነቱ አንፃር የዘገየው የሰራተኞች ዝቅተኛ የደሞዝ ወለል እና የግብር ቅነሳ ምላሽ ማግኘት እንዳለበት ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልፀዋል።

" አሁንም #በቀን_አንድ_ጊዜ ብቻ በልቶ ለመዋል የሚቸገር ሰራተኛ ነው ያለው " ያሉት አቶ ካሳሁን ሰራተኛው ካለው ገቢ አንፃር ችግሩ የሰፋ እንደሆነ አስረድተዋል።

እነዚህ ጥያቄዎች #በአዎንታዊ_መልኩ መታየት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

አቶ ካሳሁን " ዝቅተኛ የደሞዝ ወለል በሚመለከት ስራና ክህሎት ሚኒስቴር የዝቅተኛ የደሞዝ ወለል የሚወስን ቦርድ የሚቋቋምበት ደምብ ላይ ጥናት ማድረጋቸውን በቅርቡ አሳውቀውናል " ሲሉ ተናግረዋል።

የኑሮ ውድነት በጣም አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ ሰራተኛው ችግር ውስጥ መግባቱን የጠቆሙት ፕሬዝዳንቱ " ትክክለኛ ግብር ከፋይ ሰራተኛው ነው። ለመንግስት ቀኝ እጁ በሚከፍለው ግብር ሰራተኛው ነው። የግብር ቅነሳው አንድ እና ሁለት የለውም ዘግይቷል " ሲሉ ጠቁመዋል።

አቶ ካሳሁን ፤ ሚያዚያ 23 ቀን በኢትዮጵያ ለ49ኛ ጊዜ በሚከበረው ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ቀን (ሜይዴይ) አዳራሽ ውስጥ እንደሚከበር ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አሳውቀዋል።

" አሁንም ቢሆን ባልተመለሱልን ጉዳዮች ላይ ነው የምንወያየው። የቀኑ መሪ ቃል ' ለሰላም እና ለኑሮ ውድነት መፍትሄ እንሻለን ' የሚል ነው  ብለዋል።

" የሰላም ችግር አለ። ሰራተኞች በአንዳንድ ቦታዎች ይታገታሉ ፣ ይሞታሉ " ያሉት አቶ ካሳሁን ፎሎ ፤ " ይሄ እስከ መቼ ይቀጥላል ? ማንኛውም ማህበረሰብ ላይ እንደሚደርሰው ጉዳት ሁሉ ሰራተኛውም ላይ እየደረሰ ነው ፤ ስለዚህ ለሰላም መፍትሄ መምጣት አለበት " ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
" የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በተመረጡ ከተሞች በኦንላይን ይሰጣል " - ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ

የ2016 ዓ.ም 12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና በተመረጡ ከተሞች በኦንላይን እንደሚሰጥ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ፤ " ፈተናው ሙሉ በሙሉ በኦንላይን ለመስጠት ባይቻልም በክልሎች በተመረጡ ከተሞች ለመስጠት እየተሠራ ነው " ብለዋል።

" በሁሉም ክልሎች ያሉ የተመረጡ ተማሪዎች በኦንላይን ፈተናቸውን ይወስዳሉ " ሲሉ አሳውቀዋል።

ቀሪዎቹ ደግሞ በተለመደው አግባብ ፈተናቸውን እንደሚወስዱ ገልጸዋል።

የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር እሸቱ ከበደ በበኩላቸው ፤ " ፈተናው በኦንላይን ለመሥጠት የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ ነው " ብለዋል።

ተፈታኝ ተማሪዎች በሙከራ ፈተና እንዲለማመዱ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የአሰልጣኞች ስልጠና በመስጠት ተማሪዎች ተደጋጋሚ ስልጠና እንደሚሰጣቸው አመልክተዋል።

ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ የአሰልጣኞች ስልጠና መስጠት ይጀመራል ብለዋል።

#MoE

@tikvahethiopia
#ጥንቃቄ🚨

" ማህበረሰቡ ያለበትን #የቤት_እጦት እና ፍላጎት በመገንዘብ ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ከኢትዮ - ቴሌኮም ጋር በመተባበር 100 ሚሊዮን ብር መድቦ እየሰራ ነው " እየተባለ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚሰራጨው መረጃ ፍጹም #ሀሰተኛ ነው።

በማህበራዊ ሚዲያው የሚዘዋወረው መልዕክት አጭበርባሪዎች ህብረተሰቡን #ለማጭበርበር የፈጠሩት ነው።

" ሼር ብቻ እያደረጋችሁ የቤት ባለዕድለኛ ሆኑ ፣ ተሸለሙ " የሚሉት መልዕክቶች በሁለቱም ተቋማት እውቅና የሌላቸው የአጭበርባሪዎች ስራ ናቸው።

" ቤት ታገኛላችሁ ሼር አድርጉ " እንዲህ የሚባል ነገር የለም።

ውድ የቲክቫህ ቤተሰቦቻችን ፤ መሰል #በውሸት የተሞሉ የማጭበርበሪያ ስልቶችን እንድትጠነቀቁ ከዚህ ቀደም በዛ ያሉ መልዕክቶች ተለዋውጠናል ፤ በቂ እውቀትም አላችሁ።

ምናልባት እንዲህ ያለን ሀሰተኛ መልዕክት አምኖ የሚጭበረበር ወዳጅ ዘመንድ እንዳይኖራችሁ አስገንዝቧቸው።

#TikvahFamily

@tikvahethiopia
#ሆሣዕና

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የ2016 ዓ/ም ሆሣዕና በዓል አስመልክተው በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ተገኝተው ትምህርት፣ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጥተዋል።

ቅዱስነታቸው ፤ የዛሬው የሆሣዕና በዓል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ የሚቀድሙት እና የሚከተሉት ህዝብ በተለይ አእሩግ እና ሕጻናት " ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም ሚመጣ የተባረከ ነው ፤ ሆሣዕና በአርያም " በማለት ጌታችንን መቀበላቸው የሚታወስበት በዓል መሆኑን አስረድተዋል።

ቅዱስ ፓትርያርኩ ሰሙነ ህማማትንም  አስመልክተው ለመላው ምዕመናን አባታዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ቅዱስነታቸው ፦

" ሰሙነ ሕማማትን እግዚአብሔር አምላክ በሰላም አስጀምሮ እንዲያስፈጽመን ለብርሃነ ትንሳዔው እንዲያበቃን እግዚአብሔር አምላካችንን እንለምነዋለን።

ሰሙነ ሕማማትን ሁላችንም በየአካባቢያችን ባለው ቤተክርስቲያን ተገኝተን ሰሞነ ሕማማትን ፣ ስግደቱን ፣ ጸሎቱን፣ ልመናውን በሕብረት ወደ እግዚአብሔር አምላካችን እንጸልያለን።

በጸሎታችን ደግሞ ያለውን ችግር ሁሉ እንዲያስወግድልን ፦
- #ሰላሙን
- #ፍቅሩን
- #አንድነቱን እንዲሰጠን የሁላችንም ጸሎትና ምኞት ነውና እግዚአብሔር አምላካችን ከዚያ ያድርሰን ሰሙነ ሕማማቱን በሰላም ያስፈጽመን። "

#TikvahEthiopiaFamilyAddisAbaba

@tikvahethiopia
2024/05/14 00:15:10
Back to Top
HTML Embed Code: