Telegram Web Link
የኤፌሶን ጉባኤ

ክፍል ሁለት

በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

5፥72 እነሆ በአሏህ የሚያጋራው ሰው አሏህ በእርሱ ላይ ገነትን በእርግጥ እርም አደረገ፥ መኖሪያውም እሳት ናት፡፡ ለበዳዮችም ምንም ረዳቶች የሏቸውም፡፡ إِنَّهُ مَن يُشْرِكْ بِاللَّهِ فَقَدْ حَرَّمَ اللَّهُ عَلَيْهِ الْجَنَّةَ وَمَأْوَاهُ النَّارُ ۖ وَمَا لِلظَّالِمِينَ مِنْ أَنصَارٍ

"ፍጹም" ማለት በነገረ ክርስቶስ ዐውድ "ሙሉ"fully" ማለት ነው፥ ከ 330 እስከ 390 ድኅረ ልደት ይኖር የነበረው ዲዮደር ዘጠርሴስ"Diodorus of Tarsus" እና ከ 350 እስከ 428 ድኅረ ልደት ይኖር የነበረው ቴዎደር ዘሞፓሲስቲያ"Theodore of Mopsuestia" ኢየሱስን "ሙሉ አምላክ እና ሙሉ ሰው ነው፥ ሁለት አካል ነው" የሚል ትምህርት ነበራቸው። ስለዚህ ትምህርት አትናቴዎስ ዘእስክንድርያ እንዲህ ይላል፦
ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 23 ቁጥር 21
"ይህም የማይገባ የማይጠቅም ክህደት ነው፥ ፍጡርን ከፈጣሪ ጋር አቆራኝተዋልና። ተገዥን ከገዥ አንድ አድርገዋልና፥ ካልተፈጠሩ አካላት ጋር "ልዩ አራተኛ አካል" ብለዋልና"።

የቆስጠንጢኒያው ኤጲስ ቆጶስ ንስጥሮስ በተመሳሳይ የመለኮት አካል እና የሰው አካል ጥምረት "ሱንዴሴይስ" σῠ́νδεσῐς ሲባል ትርጉሙ መስተጻምር"conjuction" ማለት ነው፥ ይህንን "መስተጻምር" የሚለውን ቃል ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ ይጠቀምበት ነበር። ንስጥሮስ ድንግል ማርያም ማኅፀን ውስጥ የተፈጠረውን ፍጡር "የአምላክ ተሸካሚ" "ጸዋኤ አምላክ"bearer of God" በማለት "ቴዎፎሮስ" θεόφορος ይለው ነበር፥ "ቴዎስ" Θεός ማለት "አምላክ" ማለት ሲሆን "ፎሮስ" φορος ማለት "ተሸካሚ" ማለት ነው። ማርያምን ደግሞ "የክርስቶስ እናት" በማለት "ኽሪስቶቶኮስ" Χριστοτόκος ይላት ነበር፥ "ኽሪስቶስ" χριστός ማለት "የተቀባ" ማለት ሲሆን "ቶኮስ" τόκος ማለት ደግሞ "ወላጅ" "እናት" ማለት ነው። እንደ ንስጥሮስ ትምህርት "ኢየሱስ በመለኮት የአብ ልጅ ነው፥ በትስብእት የማርያም ልጅ ነው" የሚል ነው፥ ንስጥሮስ "ኢየሱስ በአባቱ አምላክ ነው፥ በእናቱ ሰው ነው" ብሎ ያምን ነበር።

ከእርሱ በተቃራኒው የእስክንድርያው ኤጲስ ቆጶስ ቄርሎስ የመለኮት አካል እና የሰው አካል ሕብረት"Hypostatic union" በግሪኩ "ሄኖሲስ ካት ሒፓስታሲን" ἕνωσις καθ᾽ ὑπόστασιν ይለዋል። ቄርሎስ ዘእስክንድርያ ማርያምን "የአምላክ እናት" በማለት "ቴዎቶኮስ" Θεότόκος ይላት ነበር፥ "ቴዎስ" Θεός ማለት "አምላክ" ማለት ሲሆን "ቶኮስ" τόκος ማለት ደግሞ "ወላጅ" "እናት" ማለት ነው።

ከድጡ ወደ ማጡ የሆነውን ይህንን ውዝግብ ለመፍታት እና "የውርስ ኃጢአት የለም እና ሰው ለሰው የሚሞትበት ምክንያት የለም፥ ሰው ለሚሠራው ሥራ በአላፍትና የሚጠየቀው እራሱ ነው" በማለት ሙግቱን ያቀረበውን ቢላርግዮስን ለማውገዝ 431 ድኅረ ልደት በንጉሥ ደኃራይ ቴዎዶስዮስ ሊቀ መንበርነት የኤፌሶን ጉባኤ 200 ኤጲጵ ቆጶሳት ከመላው ዓለም ተሰብስበው ማርያም "የአምላክ እናት ናት" "ኢየሱስ ፍጡርም ፈጣሪ ነው" የሚል ስብጥር ውሳኔ ወሰኑ፦
ሃይማኖተ-አበው ምዕራፍ 124 ቁጥር 19
"ለሊሁ ፍጡር ወለሊሁ ፈጣሪ"

ትርጉም፦ "እርሱ ፍጡር ነው፥ እርሱ ፈጣሪ ነው" ማለት ነው። እንደ ክርስትናው ትምህርት ቅድመ ተዋሕዶ ወይም ቅድመ ተሠግዎት ድንግል ማርያም ማሕፀን ውስጥ የተፈጠረ ፍጡር አለ፥ ይህንን ዕሩቅ ብእሲ "መለኮትን ያዋሓደው አዋሐጅ አብ ሲሆን፣ ተዋሐጅ ከአብ የተገኘው መለኮታዊ አካል ሲሆን፣ ተወሐጅ ደግሞ ያለ ዘርአ ብእሲ የተፈጠረው ሰብአዊ አካል ነው" የሚል ነው። "ሰው እና አምላክ አንድ ሆነዋል" ማለት "ለማኝ እና ተለማኝ፣ አምላኪ እና ተመላኪ፣ ፍጡር እና ፍጣሪ አንድ ሆነዋል" ማለት ነው። መለኮት "ክብሬን ለሌላ አልሰጥም" እያለ ማርያም ማሕፀን ውስጥ የተፈጠረ ዕሩቅ ብእሲ መለኮት በማድረግ ክብሩን ማጋራት ተገቢ አይደለም፦
ኢሳይያስ 42፥8 እኔ ያህዌህ ነኝ፤ ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፥ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም።

"ዕሩቅ ብእሲ" ማለት "ፍጡር ሰው" ማለት ነው። ማንን እንስማ "ክብሬን ለሌላ አልሰጥም" የሚለውን መለኮትን ወይስ የኤፌሶንን ጉባኤ? "መለኮት ሰውነትን አምላክ አደረገው" የሚል ትምህርት በመለኮት ላይ የተቃጣ ክፉኛ ትምህርት ነው፦
ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 31 ቁጥር 18
"ሥጋ አምላክነትን የማይመረመር ጌትነትን አገኘ"
መጽሐፈ ምሥጢር ምዕራፍ 21 ቁጥር 14
"ሰውነት በመለኮት አምላክ ሆነ"

አክባሪ መለኮት ተከባሪ(ከባሪ) ሰውን በአምላክነት ለማክበር ከፍጡር ጋር አንድ ሆነ ማለትስ ሕሊና ይቀበለዋልን? "ከእኔ ሌላ ሌሎች አማልክት አታምልክ" እያለ በእጅ አዙር ፍጡር ፈጥሮ "ፍጡር አምልክ" የሚልበት አንዳች ቁብ እና ምክንያት የለውም፦
ዘጸአት 20፥3 ኢታምልክ አማልክተ ወኢምንተኒ ዘእንበሌየ።

ትርጉም፦ "ከእኔ ሌላ ሌሎች አማልክት አታምልክ" ማለት ነው። ያለ ዘርአ ብእሲ ማለትም ያለ ወንድ ሩካቤ ወይም ያለ ፍትወት የተፈጠው መሢሑ ያስተማረው "ጌታዬን እና ጌታችሁን አሏህን አምልኩ" የሚል ነው፦
5፥72 አል መሢሕም አለ፡- «የእስራኤል ልጆች ሆይ! ጌታዬን እና ጌታችሁን አሏህን አምልኩ»። وَقَالَ الْمَسِيحُ يَا بَنِي إِسْرَائِيلَ اعْبُدُوا اللَّهَ رَبِّي وَرَبَّكُمْ

በአምላክነቱ ሰውነት በሌለበት በአሏህ ላይ ፍጡርን የሚያጋራ ሰው አሏህ በአጋሪው ላይ ገነትን በእርግጥ እርም አደረገ፥ መኖሪያውም እሳት ናት፡፡ ለበዳዮችም ምንም ረዳቶች የሏቸውም፦
5፥72 እነሆ በአሏህ የሚያጋራው ሰው አሏህ በእርሱ ላይ ገነትን በእርግጥ እርም አደረገ፥ መኖሪያውም እሳት ናት፡፡ ለበዳዮችም ምንም ረዳቶች የሏቸውም፡፡ إِنَّهُ مَن يُشْرِكْ بِاللَّهِ فَقَدْ حَرَّمَ اللَّهُ عَلَيْهِ الْجَنَّةَ وَمَأْوَاهُ النَّارُ ۖ وَمَا لِلظَّالِمِينَ مِنْ أَنصَارٍ

በግሪክ ዐረማዊ ትምህርት "ቴ አንትሮፖስ" θε άνθρωπος ማለት "አምላክ ወሰብእ" "አምላክ እና ሰው" ማለት ነው፥ ፈጣሪን በፍጡር ልክ ፍጡርን በፈጣሪ ልክ ለክቶ ያስቀመጠ ትምህርት ይህ የፓጋን ትምህርት ነው። የሚያጅበው በኤፌሶን ቦታ "የአምላክ እናት" ተብላ የምትትጠራ "አርጤምስ" የተባለች ጣዖት ነበረች፥ በዛው በኤፌሶን ቦታ ማርያምን "የአምላክ እናት" በማለት ማጽደቁ ያጋጣሚ ጉዳይ አይደለም። ለነገሩ "የአምላክ እናት" ተብለው የሚጠሩ ጣዖታት በሮም "ዲያና" በግብፅ "አይስስ" ነበሩ።
አምላካችን አሏህ ከዚህ ከሚቀደድ እና ከሚቀረደድ ውስብስብ ትምህርት ነጻ ያውጣችሁ! እኛንም ወለም ዘለም እና ውልፍጥ ዝልፍጥ በሌለው በተውሒድ ትምህርት ያጽናን! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://www.tg-me.com/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
ኢየሱስ ጌታ ነውን?

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

5፥117 በእርሱ ያዘዝከኝን ቃል "ጌታዬን እና ጌታችሁን አሏህን አምልኩ" ማለትን እንጂ ለእነርሱ ሌላ አላልኩም፡፡ مَا قُلْتُ لَهُمْ إِلَّا مَا أَمَرْتَنِي بِهِ أَنِ اعْبُدُوا اللَّهَ رَبِّي وَرَبَّكُمْ

በየመንገዱ፣ በገበያ ቦታ፣ በመስክ ውይይት በተለይ ፕሮቴስታንት "ኢየሱስ ጌታ ነው" በማለት ሲሰብኩ ይታያል፥ ቅሉ ግን "ኢየሱስ ጌታ ነው" ወይም "ኢየሱስ ጌታ አይደለም" ለማለት ቅድሚያ "ጌታ" ሲባል ምን ማለት ነው? የሚለውን ጥያቄ መልስ ያሻል። ለምሳሌ፦ ሣራ ለአብርሃም፦ "ጌታ" ብላ እየጠራችው ታዘዘችለት፦
1 ጴጥሮስ 3፥6 እንዲሁም ሣራ ለአብርሃም፦ "ጌታ" ብላ እየጠራችው ታዘዘችለት። ὡς Σάρρα ὑπήκουσεν τῷ Ἀβραάμ, κύριον αὐτὸν καλοῦσα·

እዚህ አንቀጽ ላይ "ጌታ" ለሚለው የገባው ቃል "ኩሪዮስ" κύριος ሲሆን ጳውሎስ ኢየሱስን "ጌታ" ለሚልበት የሚጠቀመው ቃል ይህንኑ ነው፥ ስለዚህ ሳራ አብርሃምን "ጌታ" ስትል "የዓለማቱ ጌታ" ማለቷ ሳይሆን እልቅና እና ክብርን ካሳየ በጳውሎስ እሳቤ "ኢየሱስ ጌታ ነው" ሲባል በዚህ ስሌት እንረዳዋለን። ምክንያቱም የኢየሱስ ጌትነት በመደረግ ላይ የተመሠረተ መነሾ እና ጅማሮ ያለው ስለሆነ የባሕርይ ጌትነት በፍጹም አይደለም፦
የሐዋርያት ሥራ 2፥36 ኢየሱስን አምላክ ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ። ἀσφαλῶς οὖν γινωσκέτω πᾶς οἶκος Ἰσραὴλ ὅτι καὶ Κύριον αὐτὸν καὶ Χριστὸν ἐποίησεν ὁ Θεός, τοῦτον τὸν Ἰησοῦν.

እዚህ አንቀጽ ላይ "አምላክ" ባለቤት ሲሆን "ኢየሱስ" ተሳቢ ነው፥ በባለቤት እና በተሳቢ መካከል "እንዳደረገው" የሚል ተሻጋሪ ግሥ አለ። ጌታ አድራጊው አንዱ አምላክ ሲሆን ጌታ ተደራጊው ኢየሱስ ነው፥ አምላክ ኢየሱስን ጌታ ካረደገው የኢየሱስ ጌትነት መነሾ እና ጅማሮ ያለው ስለሆነ እና ጌታ ከመደረጉ በፊት በባዶነት ስለሚቀደም ጌትነቱ ሥልጣን እና ሹመት ያሳያል። ምክንያቱም "እንዳደረገው" ለሚለው የገባው ቃል "ኤፓዬሴን" ἐποίησεν ሲሆን ከዚህ በፊት ያልሆነ ወደ መሆን በመደረግ ለመጣ ነገር በግሪክ ኮይኔ ይጠቀምበታል፦
ዘፍጥረት 45፥9 "አምላክ" በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ "ጌታ" አደረገኝ። ἐποίησέ με ὁ Θεὸς κύριον πάσης γῆς Αἰγύπτου·

የግሪክ ሰፕቱአጀንት ዮሴፍ "አደረገኝ" ላለበት የተጠቀመበት ቃል "ኤፓዬሴ" ἐποίησέ እንደሆነ ልብ አድርግ! አምላክ ዮሴፍን ጌታ ማድረጉ ሥልጣን እና ሹመት ያሳያል ከተባለ እንግዲያውስ አምላክ ኢየሱስን ጌታ ማድረጉ ሥልጣን እና ሹመት ወይም እልቅና እና ማዕረግን ያሳያል። "አዶናይ" אֲדֹנָ֥י ማለት "ጌታዬ" ማለት ነው፥ መሢሑ በትንቢት መነጽር ያህዌህን "ጌታዬ" ብሎታል፦
ኢሳይያስ 61፥1 "የ-"ጌታዬ" የያህዌህ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች የምሥራችን እሰብክ ዘንድ ያህዌህ ቀብቶኛልና። ר֛וּחַ אֲדֹנָ֥י יְהוִ֖ה עָלָ֑י יַ֡עַן מָשַׁח֩ יְהוָ֨ה אֹתִ֜י לְבַשֵּׂ֣ר עֲנָוִ֗ים

እዚህ አንቀጽ ላይ "አዶናይ" אֲדֹנָ֥י ማለት "ጌታዬ" ማለት ከሆነ ኢየሱስ አምላኩን "ጌታዬ" ማለቱ በራሱ የሚገዛለት ጌታ እንዳለው አመላካች ነው። ኢየሱስ በትንቢት መነጽር የፈጠረው ጌታ እንዳለው ተናግሯል፦
ምሳሌ 8፥22 "ጌታ" በቀድሞ ተግባሩ "ፈጠረኝ"። κύριος ἔκτισέν με ἀρχὴν ὁδῶν αὐτοῦ εἰς ἔργα αὐτοῦ

በግሪክ ሰፕቱአጀንት እዚህ አንቀጽ ላይ "ፈጠረኝ" ለሚለው የገባው ቃል "ኤክቲሴን ሜ" ἔκτισέν με ሲሆን፣ በዕብራይስጥ ማሶሬት "ቃናኒ" קָ֭נָנִי ሲሆን፣ በግዕዝ ደግሞ "ፈጠረኒ" ነው፥ ቀደምት የቤተክርስቲያን አበው ምሳሌ 8፥22 ላይ "ፈጠረኝ" የሚለው ኢየሱስ እንደሆነ ያለምንም ልዩነት በወጥ ፍሰት አብራርተዋል። ኢየሱስን የፈጠረ ጌታ ጌትነቱ የባሕርይ ሲሆን የዓለማቱ ጌታ ነው፥ በጌትነቱ ላይ ባርነት የሌለበት ይህ ጌታ ኢየሱስን "ባሪያዬ" ይለዋል፦
ኢሳይያስ 42፥1 እነሆ ደግፌ የያዝሁት ባሪያዬ፤ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ምርጤ፤ በእርሱ ላይ መንፈሴን አድርጌአለሁ፥ እርሱም ለአሕዛብ ፍርድን ያወጣል። הֵ֤ן עַבְדִּי֙ אֶתְמָךְ־בֹּ֔ו בְּחִירִ֖י רָצְתָ֣ה נַפְשִׁ֑י נָתַ֤תִּי רוּחִי֙ עָלָ֔יו מִשְׁפָּ֖ט לַגֹּויִ֥ם יֹוצִֽיא׃

በጌትነቱ ላይ ባርነት ያለበት ኢየሱስ የባሕርይ ጌታ አለመሆኑን ይህ ጥቅስ በቂ አስረጅ ነበር። ማርያም እና ዮሴፍ ኢየሱስ በጌታው ፊት ሊያቆሙት ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት፦
ሉቃስ 2፥24 "በጌታ ፊት ሊያቆሙት"፥ በጌታም ሕግ፦ “ሁለት ዋሊያ ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች፡” እንደ ተባለ፥ መሥዋዕት ሊያቀርቡ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት።

"በጌታ ፊት ሊያቆሙት" የሚለው ይሰመርበት! የተወሰደው ኢየሱስ እና ጌታው በማንነት ሆነ በምንነት ሁለት ለየቅል የሆኑ ሃልዎት ናቸው፥ "የባሕርይ ጌታ" ማለት ጌትነቱ በራሱ የተብቃቃ እና ጌትነቱ የራሱ ገንዘቡ የሆነ ማለት ነው። ኢየሱስ ከአሏህ የተሰጠው ተልእኮ "ጌታዬን እና ጌታችሁን አሏህን አምልኩ" የሚል ነበር፦
5፥117 በእርሱ ያዘዝከኝን ቃል "ጌታዬን እና ጌታችሁን አሏህን አምልኩ" ማለትን እንጂ ለእነርሱ ሌላ አላልኩም፡፡ مَا قُلْتُ لَهُمْ إِلَّا مَا أَمَرْتَنِي بِهِ أَنِ اعْبُدُوا اللَّهَ رَبِّي وَرَبَّكُمْ

እንግዲህ ኢየሱስ ጌታ ካለው፣ ለጌታው ባሪያ ከሆነ፣ ጌትነቱ በመደረግ ላይ የተመሠረተ መነሻ እና ጅማሮ ካለው እንግዲያውስ በጌትነቱ ባርነት የሌለበትን የባሕርይ ጌታ አሏህን በብቸኝነት አምልኩ! እንደ ኢየሱስ ለጌታችን ባሪያ መሆን ምንኛ መታደል ነው? ስለዚህ የኢየሱስን ጌታ እንድታመልኩ ጥሪያችን ነው። ጌታችን አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://www.tg-me.com/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
መጣጥፋችንን በእንግሊዝኛ ከፈለጋችሁ ይህንን ሊንክ አስፈንጥሩ! https://www.tg-me.com/wahidenglish
ዕሩቅ ብእሲ

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

3፥47 ፦ "ጌታዬ ሆይ! ሰው ያልነካኝ ስኾን ለኔ እንዴት ልጅ ይኖረኛል? አለች፡፡ "ነገሩ እንዳልሽው ነው፡፡ አሏህ የሚሻውን ይፈጥራል፡፡ አንዳችን በሻ ጊዜ ለእርሱ ኹን ይለዋል፤ ወዲውኑም ይኾናል" አላት፡፡ قَالَتْ رَبِّ أَنَّىٰ يَكُونُ لِى وَلَدٌۭ وَلَمْ يَمْسَسْنِى بَشَرٌۭ ۖ قَالَ كَذَٰلِكِ ٱللَّهُ يَخْلُقُ مَا يَشَآءُ ۚ إِذَا قَضَىٰٓ أَمْرًۭا فَإِنَّمَا يَقُولُ لَهُۥ كُن فَيَكُونُ

በግዕዝ "ዕሩቅ" ማለት "ብቻ" ማለት ነው፥ "ብእሲ" ማለት "ተባዕት ሰው" "ወንድ" "ጎልማሳ" ማለት ሲሆን "ብእሲት" ማለት ደግሞ "አንስታይ ሰው" "ሴት" "ጎልማሲት" ማለት ነው። በጥቅሉ "ዕሩቅ ብእሲ" ማለት "ሰው ብቻ" ማለት ሲሆን በዐበይት ክርስትና ኢየሱስ የመለኮት ማንነት እና ምንነት ከመዋሐዱ በፊት የነበረው የሰው ማንነት እና ምንነት "ዕሩቅ ብእሲ" ይባላል፦
ሉቃስ 1፥31 እነሆም ትፀንሻለሽ "ወንድ ልጅም" ትወልጃለሽ፥ ስሙንም "ኢየሱስ" ትዪዋለሽ።

"ወንድ" የሥጋ መደብ እና የአንስታይ አንቀጽ ሲሆን የሚገረዝ ወንድ ነው፥ "ትፀንሻለሽ" የሚለው በራሱ ፅንስ ፍጡር መሆኑን አመላካች ነው። ቄርሎስ ዘእስክንድርያ ኢየሱስ "ፍጡር" እንደሚባል ተናግሯል፦
ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 124 ቁጥር 19
“ከሴት በሥጋ ስለተወለደ "ፍጡር" እንላለን”።

ዐማርኛ ላይ "ሰው" ብለው ቢያስቀምጥም ግዕዙ “ንብሎ "ፍጡረ" እስመ ውእቱ ተወልደ በሥጋ እምብእሲት” በማለት አስቀምጦታል፥ "ፍጡረ" ማለት "ፍጡር" ማለት ነው። በአንድ ወቅት "ኢየሱስ ፍጡር ነው" ብዬ ይህንን ጥቅስ ስጠቅስ "ፍጡር አይልም፥ ወሒድ ዋሽቷል" በማለት የኦርቶዶክስ መምህራን ሲወርፉኝ ከርመው በኃላ ላይ ሃማኖተ አበውን በግዕዝ ሲመረምሩ ብዙ ቦታ ኢየሱስ ፍጡር መሆኑን ሲረዱ "ፍጡር ነው" የሚሉ የኦርቶዶክስ መምህራን "ፍጡር አይባልም" ከሚሉ የኦርቶዶክስ መምህራን እስከ ዛሬ እየተወዛገቡ ነው። አል ሐምዱ ሊላህ የሙሥሊም ዐቃቢያን የኦርቶዶክስ መምህራንን ዓይናቸውን ገለጡላቸው፥ ይህ ውዝግብ ለብዙዎች መሥለም ምክንያት እየሆነ ነው። ኤጲፋኒዮስ ዘቆጵሮስ ኢየሱስ የተፈጠረ ሰው መሆኑን ፍንትው አርጎ ተናግሯል፦
ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 56 ቁጥር 20
"ተፈጠረ" መባሉ ሰው በመሆኑ ምሥጢር ይፈጸማል"።

ኤጲፋኒዮስ ዘቆጵሮስ በተጨማሪም ኢየሱስ የተፈጠረ ሰው እንደሆነ ቁልጭ አርጎ ተናግሯል፦
ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 56 ቁጥር 21
"ሰው ስለሆነ "ፍጡር" ቢባል ወዲህ በር ተባለ"።

ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ በተመሳሳይ “ሥጋ ስለሆነ ፍጡር ይባላል” ብሏል፦
ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 35 ቁጥር 6
“ሥጋ ስለሆነ ፍጡር ይባላል”።

ግዕዙ “ወዓዲመ ይትበሀል ፍጡረ በእንተ ዘኮነ ሥጋ” በማለት አስቀምጦታል። ኢየሱስ በትንቢት መነጽር "ከማኅፀን ጀምሮ "የሠራኝ" በማለት እግዚአብሔር እርሱን እንደፈጠረው ይናገራል፦
ኢሳይያስ 49፥5 ያዕቆብን ወደ እርሱ እንድመልስ እስራኤልንም ወደ እርሱ እንድሰበስብ ባሪያ እሆነው ዘንድ ከማኅፀን ጀምሮ "የሠራኝ" እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡—

ቄርሎስ ዘእስክንድርያ ኢሳይያስ 49፥5 ያለውን ጥቅስ ይዞ የኢየሱስ ፍጡርነት እንቅጩን ፍርጥ አርጎ ተናግሯል፦
ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 76 ቁጥር 19
“ዳግመኛም መድኅን ክርስቶስ ከድንግል ስለመወለዱ በኢሳይያስ አፍ “ብዙ ሥራ እሠራ ዘንድ የያዕቆብንም ወገን አጸና ዘንድ አስራኤልንም አንድ አደርግ ዘንድ "በድንግል ማኅፀን ተፈጠርኩ" አለ”።

ዐማርኛው ላይ "ተፀነስኩ" ቢሉትም ግዕዙ ግን "ተፈጥረ" ይለዋል፥ "ተፈጥረ" ማለት "ተፈጠርኩኝ" ማለት ነው። ነገሩ ፅንስ ፍጡር ነውና ቄርሎስ ዘእስክንድርያ በመቀጠል ኢየሱስ "በማሕጸን "የፈጠረኝ" እግዚአብሔር" ማለቱን አጽንዖት ሰጥቶ ተናግሯል፦
ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ ምዕራፍ 76 ቁጥር 21
“ዳግመኛም የያዕቆብን ወገን አንድ ለማድረግ፤ እስራኤልን ለማዳን አገልጋይ እሆነው ዘንድ "በማሕጸን "የፈጠረኝ" እግዚአብሔር" እርሱ ይወደኛልና”።
ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 124 ቁጥር 25
"በእውነት ሰው እንደመሆኑ "እግዚአብሔር ፈጠረኝ" ይላል"።
ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 124 ቁጥር 26
"ሰው ፍጡር ነውና ስለዚህ እርሱ ሰው ስለሆነ "እግዚአብሔር ፈጠረኝ" ይላል"።

እንግዲህ ኢየሱስ "እግዚአብሔር ፈጠረኝ" ካለ ማኅፀን ውስጥ የተሠራ ነገር አምላክ ካልሆነ የተሠራውን ሰው ማምለክ ባዕድ አምልኮ ነው፦
ኢሳይያስ 43፥10 ከእኔ በፊት "አምላክ አልተሠራም" ከእኔም በኋላ አይሆንም።

ፈጣሪ "አምላክ አልተሠራም" እያለ "ፈጣሪ ፍጡር ሆነ" "ፈጣሪ ተፈጠረ" "ማኅፀን ውስጥ ከተፈጠረው ዕሩቅ ብእሲ ጋር ፈጣሪ አንድ ሆነ" የሚል ትምህርት ምንኛ ክፉ ትምህርት ነው? ሳውርዮስ ዘአንጾኪያ "ፍጡር ከፈጣሪ ጋር አንድ ሆነ" የሚል ተስተምህሮት አለው፦
ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 112 ቁጥር 32
"ፍጡር ከፈጣሪው ጋር አንድ ሆነ"።

"ፈጣሪ እና ፍጡር አንድ ሆነ" የሚል ትምህርት "ወሕደቱል ዉጁድ" وَحْدَة الوُجُود ሲባል በኢሥላም ኢንካር የተደረገ ነው። ከዚያ ይልቅ ዒሣ መሢሑ መርየም ማኅፀን ውስጥ የተፈጠረ ፍጡር እና በምንነቱ ሰው ብቻ ነው፦
3፥47 ፦ "ጌታዬ ሆይ! ሰው ያልነካኝ ስኾን ለኔ እንዴት ልጅ ይኖረኛል? አለች፡፡ "ነገሩ እንዳልሽው ነው፡፡ አሏህ የሚሻውን ይፈጥራል፡፡ አንዳችን በሻ ጊዜ ለእርሱ ኹን ይለዋል፤ ወዲውኑም ይኾናል" አላት፡፡ قَالَتْ رَبِّ أَنَّىٰ يَكُونُ لِى وَلَدٌۭ وَلَمْ يَمْسَسْنِى بَشَرٌۭ ۖ قَالَ كَذَٰلِكِ ٱللَّهُ يَخْلُقُ مَا يَشَآءُ ۚ إِذَا قَضَىٰٓ أَمْرًۭا فَإِنَّمَا يَقُولُ لَهُۥ كُن فَيَكُونُ

ይህንን ዕሩቅ ብእሲ የምታመልኩ በንስሓ ወደ አሏህ እንድትመጡ በታላቅ ትህትና እንጠይቃለን። አምላካችን አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://www.tg-me.com/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
የነቢያችን"ﷺ" ሥርወ ግንድ

በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

53፥56 ይህ ከፊተኞቹ አስጠንቃቂዎች የሆነ አስጠንቃቂ ነው። هَـٰذَا نَذِيرٌ مِّنَ النُّذُرِ الْأُولَىٰ

ኢብራሂም እና ልጁ ኢሥማዒል፦ «ጌታችን ሆይ! ከእኛ ተቀበል፡፡ አንተ ሰሚው እና ዐዋቂው አንተ ነህና» በማለት አሏህ ተማጽነዋል፦
2፥127 ኢብራሂም እና ኢሥማዒልም «ጌታችን ሆይ! ከእኛ ተቀበል፡፡ አንተ ሰሚው እና ዐዋቂው አንተ ነህና» የሚሉ ሲኾኑ ከቤቱ መሠረቶቹን ከፍ ባደረጉ ጊዜ አስታውስ፡፡ وَإِذْ يَرْفَعُ إِبْرَٰهِـۧمُ ٱلْقَوَاعِدَ مِنَ ٱلْبَيْتِ وَإِسْمَٰعِيلُ رَبَّنَا تَقَبَّلْ مِنَّآ ۖ إِنَّكَ أَنتَ ٱلسَّمِيعُ ٱلْعَلِيمُ

ኢብራሂም እና ኢሥማዒል በመቀጠል፦ "ለአንተ ታዛዦችም አድርገን፡፡ ከዘሮቻችንም ለአንተ ታዛዦች ሕዝቦችን አድርግ" በማለት አሏህ ለምነዋል፦
2፥128 «ጌታችን ሆይ! ለአንተ ታዛዦችም አድርገን፡፡ ከዘሮቻችንም ለአንተ ታዛዦች ሕዝቦችን አድርግ፡፡ ሕግጋታችንንም አሳውቀን፡፡ በእኛም ላይ ተመለስን፤ አንተ ጸጸትን ተቀባዩ ሩኅሩኅ አንተ ብቻ ነህና፡፡» رَبَّنَا وَاجْعَلْنَا مُسْلِمَيْنِ لَكَ وَمِن ذُرِّيَّتِنَا أُمَّةً مُّسْلِمَةً لَّكَ وَأَرِنَا مَنَاسِكَنَا وَتُبْ عَلَيْنَا ۖ إِنَّكَ أَنتَ التَّوَّابُ الرَّحِيمُ

እዚህ አንቀጽ ላይ "ታዛዦችም" ተብሎ የተቀመጠው ቃል "ሙሥሊመይኒ" مُسْلِمَيْنِ ሲሆን "ሙሰና" مُثَنًّى ማለትም "ሁለትዮሽ"dual" ነው፥ እነዚህ ሁለቱ ኢብራሂም እና ኢሥማዒል ናቸው። "ዘሮቻችን" ሲሉ ደግሞ የሁለቱም ዝርዮች እንጂ ኢሥሐቅን እና የዕቁብን አያካትትም፥ ምክንያቱም ኢሥሐቅ የኢሥማዒል ወንድም እንዲሁ የዕቁብ የኢሥማዒል የወንድም ልጅ እንጂ የኢሥማዒል ዝርዮቹ በፍጹም አይደሉም። በቀጣይ ዐውደ ንባብ ከኢብራሂም እና ከኢሥማዒል ዘር መልእክተኛ እንዲላክ ሁለቱም አበው ተማጽነዋል፦
2፥129 «ጌታችን ሆይ! "በውስጣቸውም ከእነርሱ የኾነን መልእክተኛ በእነርሱ ላይ አንቀጾችህን የሚያነብላቸውን መጽሐፍን እና ጥበብንም የሚያስተምራቸውን ከክህደት የሚያጠራቸውንም ላክ፤ አንተ አሸናፊው ጥበበኛው አንተ ብቻ ነህና» የሚሉም ሲኾኑ፡፡ رَبَّنَا وَابْعَثْ فِيهِمْ رَسُولًا مِّنْهُمْ يَتْلُو عَلَيْهِمْ آيَاتِكَ وَيُعَلِّمُهُمُ الْكِتَابَ وَالْحِكْمَةَ وَيُزَكِّيهِمْ ۚ إِنَّكَ أَنتَ الْعَزِيزُ الْحَكِيم

"ከእነርሱ" የሚለው ኃይለ ቃል ይሰመርበት! "ከ" የሚለው መስተዋድድ መነሻ የሆነት "እነርሱ" የሚለው ተሳቢ ተውላጠ ስም "ዘሮቻችን" የሚለውን ተክቶ የመጣ ነው፥ "ሚንሁም" مِّنْهُمْ የሚለው ወሳኝ ቃል ከኢብራሂም እና ከኢሥማዒል ዘር የሚመጣ መልእክተኛ እንዳለ አመላካች ነው። "አንቀጾችህን የሚያነብላቸውን መጽሐፍን እና ጥበብንም የሚያስተምራቸውን ከክህደት የሚያጠራቸውን" በተባለው መሠረት ዘመኑ ሲደርስ አምላካችን አሏህ ነቢያችንን"ﷺ" ከዚህ ሥርወ ግንድ"offspring" ልኳል፦
2፥151 "በውስጣችሁ ከእናንተው የኾነን በእናንተ ላይ አንቀጾቻችንን የሚያነብላችሁና የሚያጠራችሁ፣ መጽሐፍን እና ጥበብንም የሚያስተምራችሁ፣ ታውቁት ያልነበራችሁትንም ነገር የሚያሳውቃችሁ የኾነን መልእክተኛ እንደላክን" ጸጋን ሞላንላችሁ፡፡ كَمَا أَرْسَلْنَا فِيكُمْ رَسُولًا مِّنكُمْ يَتْلُو عَلَيْكُمْ آيَاتِنَا وَيُزَكِّيكُمْ وَيُعَلِّمُكُمُ الْكِتَابَ وَالْحِكْمَةَ وَيُعَلِّمُكُم مَّا لَمْ تَكُونُوا تَعْلَمُونَ

"ከእናንተ" የሚለው ኃይለ ቃል ይሰመርበት! "ከ" የሚለው መስተዋድድ መነሻ የሆነት "እናንተ" የሚለው ሁለተኛ መደብ ተሳቢ ተውላጠ ስም "ዘሮቻችን" የሚለውን ተክቶ የመጣ ነው፥ "ሚንኩም" مِّنكُمْ የሚለው ወሳኝ ቃል ከኢብራሂም እና ከኢሥማዒል ዘር የመጡትን መልእክተኛ ነቢያችንን"ﷺ" አመላካች ነው፦
62፥2 እርሱ ያ በመሃይሞቹ ውስጥ አንቀጾቹን በእነርሱ ላይ የሚያነብላቸው፣ ከማጋራት የሚያጠራቸውም፣ መጽሐፍን እና ጥበብን የሚያስተምራቸውም የኾነን መልእክተኛም ከእነርሱ ውስጥ የላከ ነው፡፡ هُوَ الَّذِي بَعَثَ فِي الْأُمِّيِّينَ رَسُولًا مِّنْهُمْ يَتْلُو عَلَيْهِمْ آيَاتِهِ وَيُزَكِّيهِمْ وَيُعَلِّمُهُمُ الْكِتَابَ وَالْحِكْمَةَ

ኢብራሂም እና ኢሥማዒል ፊተኞቹ አስጠንቃቂዎች ሲሆኑ ከፊተኞቹ አስጠንቃቂዎች የሆነ አስጠንቃቂ
አንቀጾችን የሚያነብላቸውን መጽሐፍን እና ጥበብንም የሚያስተምራቸውን ከክህደት የሚያጠራቸውን ተወዳጁ ነቢያችን"ﷺ" ተልከዋል፦
53፥56 ይህ ከፊተኞቹ አስጠንቃቂዎች የሆነ አስጠንቃቂ ነው። هَـٰذَا نَذِيرٌ مِّنَ النُّذُرِ الْأُولَىٰ

ነቢያችንም"ﷺ" በሐዲስ ከኢብራሂም እና ከኢሥማዒል ሥርወ ግንድ እንደመጡ አበክረው እና አዘክረው ተናግረዋል፦
ጃምዒይ አት ተርሚዚይ መጽሐፍ 49, ሐዲስ 3964
ዋሲላህ ኢብኑል አሥቃዕ እንደተረከው፦ "የአሏህ መልእክተኛም"ﷺ" እንዲህ አሉ፦ "አሏህ ከኢብራሂም ልጅ ኢሥማዒልን መረጠ፣ ከኢሥማዒል ትውልድ የኪናናን ሥርወ ግንድ መረጠ፣ ከኪናናህ ሥርወ ግንድ ቁረይሽን መረጠ፣ ከቁረይሽ የሃሺምን ሥርወ ግንድ መረጠ፣ ከሃሺም ሥርወ ግንድ እኔን መረጠ"። عَنْ وَاثِلَةَ بْنِ الأَسْقَعِ، رضى الله عنه قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم ‏ "‏ إِنَّ اللَّهَ اصْطَفَى مِنْ وَلَدِ إِبْرَاهِيمَ إِسْمَاعِيلَ وَاصْطَفَى مِنْ وَلَدِ إِسْمَاعِيلَ بَنِي كِنَانَةَ وَاصْطَفَى مِنْ بَنِي كِنَانَةَ قُرَيْشًا وَاصْطَفَى مِنْ قُرَيْشٍ بَنِي هَاشِمٍ وَاصْطَفَانِي مِنْ بَنِي هَاشِمٍ

ሚሽነሪዎች ሆይ! የእናንተ ጉዳይ መላ ቅጡ፣ ውጥን ቅጡ እና ቅጥ አንባሩ የጠፋበት ጊዜ ነው። ዲኑል ኢሥላምን ለማጠልሸት የማትቆፍሩት ጉድጓድ፣ የማትፈነቅሉት ድንጋይ፣ የማትደረምሱት መሬት የለም፥ ቅሉ እና ጥቅሉ ግን ስለማይሳካላችሁ ይህ የሐቅ ብርሃን የልብ ፍልጠት፣ የራስ ምታት፣ የሆድ ቁርጠት፣ የጎን ውጋት እና የእግር ቁርጥማት ነው። አምላካችን አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://www.tg-me.com/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
አቃኒም

በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

22፥69 አሏህ በትንሣኤ ቀን በዚያ በእርሱ ትለያዩበት በነበራችሁት ሁሉ በመካከላችሁ ይፈርዳል፡፡ اللَّهُ يَحْكُمُ بَيْنَكُمْ يَوْمَ الْقِيَامَةِ فِيمَا كُنتُمْ فِيهِ تَخْتَلِفُونَ

፨ "ፊሲስ" φύσις ማለት "ባሕርይ" "ምንነት" "ኑባሬ" "ህላዌ" ማለት ነው፥ "ኡሲያ" οὐσία የሚለው ቃል በተመሳሳይ "ኑባሬ" "ህላዌ" "ባሕርይ" "ምንነት" ማለት ነው።
፨ "ሒፓስታቲስ" ὑπόστασις ማለት እንደ ዐውዱ "ባሕርይ" "አካል" ማለት ሲሆን በኤፌሶን ጉባኤ ዐውድ ግን "እኔነት" "ማንነት" "አካል"person" የሚለውን የሚያሲዝ ነው፥ "ሒፓስታቲስ" ὑπόστασις በተለይ "እኔ" የሚለውን ውሳጣዊ ማንነትን ያመለክታል። "ፕሮሶፓን" πρόσωπον በተመሳሳይ "እኔነት" "ማንነት" "አካል"person" ማለት ነው፥ "ፕሮሶፓን" πρόσωπον በተለይ መለያ ውጫዊ ማንነትን ያመለክታል።

"ሒፓስታቲስ" በዐረቢኛ "ኡቅኑም" أُقْنُوم ሲሆን በዐረማይስጥ ደግሞ "ቅኖማ" ܩܢܽܘܡܳܐ ነው። በግዕዝ የተቀመጠው "አቃኒም" የሚለው ቃል "ኡቅኑም" أُقْنُوم ከሚለው የዐረቢኛ ቃል የመጣ ሲሆን "አካል" "እኔነት" "ማንነት"identity" የሚለውን ታሳቢ ያደረገ ነው፥ "ቴዎ ሎጎስ" ወይም "ነባቤ መለኮት" በሚል ማዕረግ የሚጠራው ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ "አቃኒም" ሲል "አካል"individual" የሚለውን ዋቢ አርጎ ነው፦
ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 13 ቁጥር 6
"የእግዚአብሔር አቃኒም ስሞች ናቸው፥ ስሞችም አቃኒም ናቸው። የአቃኒም ትርጓሜው በገጽ እና በመልክ ፍጹማን የሚሆኑ፤ ባለመለወጥ ጸንተው የሚኖሩ አካላት ማለት ነውና"።

ሥላሴአዊያን ማለትም የሥላሴ አማንያን"trinitarian" አብን፣ ወልድን እና መንፈስ ቅዱስን "አካላዊ ስሞች"hypostatic names" የሚሉት ለዛ ነው። ስለዚህ የቤተክርስቲያን አበው "ከሁለት አካል አንድ አካል ሆነ" ሲሉ "ከሁለት "ሒፓስታቲስ" ὑπόστασις አንድ "ሒፓስታቲስ" ὑπόστασις ሆነ" ማለታቸው ነው፦
ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 73 ቁጥር 3
"እርሱ ወልድ ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ሆነ"።
ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 94 ቁጥር 13
"ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ከሁለት አካል አንድ አካል እንደሆነ እርሱን እናውቃለን"።

በኤፌሶን ጉባኤ ዐውድ ግን "አካል" ሲባል "እኔ" የሚል "ማንነት" ነው፥ የሰው አካል "እኔ" የሚል "ማንነት" እንጂ ቁርበት ወይም ቅርፊት"shell" ብቻ እንዳልሆነ ሁሉ "ከሁለት አካል አንድ አካል ሆነ" ሲሉ "ከሁለት ማንነት አንድ ማንነት ሆነ" እንዲሁ "ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ሆነ" ሲሉ "ከሁለት ምንነት አንድ ምንነት ሆነ" ማለታቸው ነው። ቄርሎስ እና ጀሌዎቹ "የሰው ባሕርይ ከመለኮት ባሕርይ የሰው አካል ከመለኮት አካል ጋር በመገናዘብ"exchange" አንድ ሆነ" ሲሉ ንስጥሮስ እና ጀሌዎቹ ደግሞ "የሰው ባሕርይ ከመለኮት ባሕርይ የሰው አካል ከመለኮት አካል ጋር ተቆራኘ፣ ተጣመረ እንጂ አንድ አልሆነም" ይላሉ። የቀጰዶቅያ አበው መካከል ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ ጉዳዩን እንዲህ ይገልጸዋል፦
ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 13 ቁጥር 8
"በመለኮት የአካል አራተኛ የባሕርይ ሁለተኛ ሆኖ የተጨመረ አይደለም"።

ንስጥሮስ "የአብ ልጅ አካል እና የማርያም ልጅ አካል አንድ አልሆኑም" ሲል በሥላሴ ሦስት አካላት ላይ አራተኛ አካል በሦስቱ አንድ ባሕርይ ላይ ሁለተኛ የሰው ባሕርይ ጨመረ፥ አትናቴዎስ ዘእስክንድርያ ጉዳዩን እንዲህ ይገልጸዋል፦
ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 31 ቁጥር 16
"አእምሮ በማጣታቸውም ለሥላሴ ባሕርይ ሁለተኛ፥ ለአካል አራተኛ እንዳለ ተናገሩ"።
ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 23 ቁጥር 20
"የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አካል አንድ ነው" ስለ ማለት ፈንታ "ሁለት አካል፣ ሁለት ባሕርይ፣ ሁለት ገጽ" ብለው አመኑ፥ በሦስት አካላት ስለ ማመን ፈንታም ሊያምኑበት ሊያስተምሩበት በማይገባ ሥራ "አራተኛ" ብለው አመኑ"።

"አራተኛ" የተባለው ከማርያም የተገኘው ማንነት እና እኔነት ነው፥ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ "አንድ አካል አንድ ባሕርይ" ሲል "ከሁለት ማንነት አንድ ማንነት፥ ከሁለት ምንነት አንድ ምንነት" ማለቱ ነው፦
ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 35 ቁጥር 2
"ክርስቶስ ማለት ፈጣሪ እና ፍጡር፥ አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመሆን አንድ ሆነ ማለት ነው"።
ከኤፌሶን ጉባኤ በኃላ ሁለቱን ልጆች ማለትም ከአብ የተገኘው ልጅ እና ከማርያም የተገኘው ልጅ የማገጣጠሙ ሂደት ላይ ትልቅ ውዝግብ ተፈጥሯል፥ የክርስቶስ አካላዊነት"personhood" ጥያቄ "ኤንሒፓስታሲያ" እና "አንሒፓስታሲያ" የሚባሉ ሁለት ሌላ ጎራ ፈጥሯል። እነዚህ ጎራ እስቲ እንመልከት!

፨ "ክርስቶስ ከማርያም የሰው ባሕርይ"human nature" ብቻ ሳይሆን የሰው አካል"human person" ነስቷል" የሚሉ የክርስትና ነገረ መለኮት ምሁራን በላቲን "ኤንሒፓስታሲያ"enhypostasia" ይባላሉ። ይህ የላቲኑ ቃል "ኤን ሒፓስታቲስ" ἐν ὑπόστασις ከሚል ግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን "በ አካል" ማለት ነው፥ ኤን" ἐν ማለት አውንታዊ ሲሆን በ"in" ማለት ነው።

"ኢየሱስ ሙሉ መለኮትነት"full divinity" እና ሙሉ ሰብአዊነት"full humanity" አለው" ከተባለ ሰብአዊነቱ ላይ አካል ጎሎታል ማለት ትርጉም አይሰጥም፥ አንድ መሉ ሰው የሰው አካል"human person" እና የሰው ባሕርይ"human nature" ካለው ኢየሱስም ከሰውነት የጎደለው ምንም ነገር ከሌለ "ኢየሱስ ሰው ነው" ሲባል የሰው ባሕርይ እና የሰው አካል ያለው ሙሉ ሰው ነው።

በ381 ድኅረ ልደት በቆስጠንጢኒያ ጉባኤ ላይ የተወገዘው አቡሊናርዮስ፦ "ኢየሱስ ሥጋ እንጂ ነፍስ የለውም፥ በነፍስ ፋንታ መለኮት ተተክቷል" የሚል ትምህርት ነበረው፥ አንድ ሰው ማንነት ከሌለው ሕያዊት፣ ነባቢት እና ልባዊት ነፍስ እንዴት ይኖረዋል? "ኢየሱስ ምንነት እንጂ ማንነት የለውም" ማለት በተዘዋዋሪ "ኢየሱስ ሥጋ እንጂ ነፍስ የለውም" ማለት ነው።

፨ ከዚህ በተቃራኒው "ክርስቶስ ከማርያም የሰው ባሕርይ"human nature" እንጂ የሰው አካል"human person" አልነሳም" የሚሉ የክርስትና ነገረ መለኮት ምሁራን በላቲን "አንሒፓስታሲያ"anhypostasia" ይባላሉ። ይህ የላቲኑ ቃል "አን ሒፓስታቲስ" ἀν ὑπόστασις ከሚል የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን "ኢ አካል" ማለት ነው፥ አን" ἀν ማለት አፍራሽ ሲሆን ኢ"not" ማለት ነው።

የአን ሒፓስታሲስ"Anhypostasis" እሳቤ በዋነኝነት ከ 485 እስከ 543 ድኅረ ልደት ይኖር የነበረው የሊዮንቲየስ ዘባዛንታየም"Leontius of Byzantium" እሳቤ ነው፥ "ኢየሱስ ከማርያም ባሕርይን እንጂ አካልን አልነሳም" የሚል ትምህርት አካል የባሕርይ መገለጫ እንዲሁ ባሕርይ የአካል መሠረት መሆኑን በቅጡ ያልተረዳ አሊያም የሥነ ኑባሬ ሙግትን በአግባቡ ያላጠና ትምህርት ነው። "መሠረቱን ነስቶ መገለጫው ተወ" ማለት ጤናማ ነውን? አንድ ሰውስ ያለ ማንነት በምንነት ብቻ ፍጹም(ሙሉ) ሰው ይባላልን? ሙሉ መለኮት ማለት ማንነት እና ምንነት ከሆነ ሙሉ ትስብእት ማለት ማንነት እና ምንነት ነው።

"ኢየሱስ የሰው ምንነት እንጂ የሰው ማንነት የለውም" የሚል ትምህርት የምሥራቅ ኦርቶዶክስ"eastern Orthodox"፣ የካቶሊክ እና የፕሮቴስታንት አቋም ሲሆን በተቃራኒው በጽብሓውያን ኦርቶዶክስ"Oriental Orthodox" ዘንድ አዲሱ አቡሊናርዮሳዊ ምንፍቅና"neo-apollinarianism heresy" ነው። "አምላክነት"Godhead" ያለ ማንነት ሙሉ አምላክ ካልተሰኘ "ሰብአዊነት"manhood" ያለ ማንነት ሙሉ ሰው እንዴት ይሰኛል? እንግዲህ አምላካችን አሏህ ስለ ዒሣ ምንነት እና ማንነት በቁርኣን የነገረን ቃል እውነተኛ ቃል ነው፦
19፥34 ይህ የመርየም ልጅ ዒሣ ነው፡፡ ያ “በ”እርሱ የሚከራከሩበት እውነተኛ ቃል ነው፡፡ ذَٰلِكَ عِيسَى ٱبْنُ مَرْيَمَ ۚ قَوْلَ ٱلْحَقِّ ٱلَّذِى فِيهِ يَمْتَرُونَ

“የምተሩነ” يَمْتَرُونَ ማለት “የሚከራከሩበት” ማለት ሲሆን በታሪክ ውስጥ ብዙ ሰዎች በዒሣ ምንነት እና ማንነት ቢከራከሩበትም አሏህ ስለ ዒሣ የነገረን ግን እውነተኛ ንግግር ነው፥ “ሂ” هِ ማለትም “እርሱ” የተባለው ዒሣ ሲሆን “እርሱ” በሚለው መነሻ ቅጥያ ላይ “ፊ” فِي የሚል መስተዋድድ ሲኖር “ስለ”about” በሚል የመጣ ነው። አምላካችን አሏህ በትንሣኤ ቀን በዚያ በእርሱ ትለያዩበት በነበራችሁት ሁሉ በመካከላችሁ ይፈርዳል፦
22፥69 አሏህ በትንሣኤ ቀን በዚያ በእርሱ ትለያዩበት በነበራችሁት ሁሉ በመካከላችሁ ይፈርዳል፡፡ اللَّهُ يَحْكُمُ بَيْنَكُمْ يَوْمَ الْقِيَامَةِ فِيمَا كُنتُمْ فِيهِ تَخْتَلِفُونَ

አምላካችን አሏህ በዒሣ ዙሪያ የምትወዛገቡትን ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://www.tg-me.com/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
አሥ ሠላሙ ዐለይኩም ወራሕመቱላሂ ወበረካቱሁ

ያ ጀመዓህ! "የተደበቀው እውነት" የሚለው ስድስተኛው መጽሐፌ በኦሮሚኛ ቋንቋ በገበያ ላይ ውሏል። "የተደበቀው እውነት" የሚያውጠነጥነው ስለ ተወዳጁ ነቢያችን"ﷺ" መምጣት በተውራት እና በኢንጂል ተነግሮ የመጽሐፉ ሰዎች ይህንን እውነት እንዴት እንደደበቁት የሚገልጥ እና የሚያጋልጥ ነው። ዝርዝሩን መጽሐፉ ላይ ያንብቡ እና ለሌሎች የሂዳያህ ሠበብ እንዲሆን አስነብቡ!

የሙሥሊሙ ቁጥር ኦሮሚያ ውስጥ ትልቅ ነው፥ ይህንን ትልቅ ቁጥር ለማክፈር ሚሽነሪዎች ጠብ እርግፍ በሚሉበት ሰዓት የንጽጽር ሥራዎች በኦሮምኛ ማኅበራችን ጀምሯል።
መጽሐፉን መርካቶ አንዋር መሥጂድ ኢሥላማዊ መጻሕፍት መደብር ውስጥ ያገኙታል፥ የበለጠ መረጃ ለማግኘት +251920781016 ዐብዱ ብለው ይደውሉ!

መጽሐፉ ለኦሮምኛ ተናጋሪዎች ተደራሽነት እንዲኖረው ባለው የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ሼር በማድረግ ሠበቡል ሂዳያህ ይሁኑ!

ወጀዛኩሙላህ ኸይራ!

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://www.tg-me.com/Wahidcom
የማይተኛ አምላክ

በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

2፥255 አሏህ ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም፡፡ ሕያው ራሱን ቻይ ነው፡፡ ማንገላጀትም እንቅልፍም አትይዘውም፡፡ اللَّهُ لَا إِلَـٰهَ إِلَّا هُوَ الْحَيُّ الْقَيُّومُ ۚ لَا تَأْخُذُهُ سِنَةٌ وَلَا نَوْمٌ

አምላካችን አሏህ ስለ ራሱ ኑባሬ በሦስተኛ መደብ ሲናገር፦ "ማንገላጀትም እንቅልፍም አትይዘውም" በማለት እንቅልፍ በእርሱ ጥበቃ ላይ እንደሌለበት ይናገራል፦
2፥255 አሏህ ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም፡፡ ሕያው ራሱን ቻይ ነው፡፡ ማንገላጀትም እንቅልፍም አትይዘውም፡፡ اللَّهُ لَا إِلَـٰهَ إِلَّا هُوَ الْحَيُّ الْقَيُّومُ ۚ لَا تَأْخُذُهُ سِنَةٌ وَلَا نَوْمٌ
ሡነን ኢብኑ ማጃህ መጽሐፍ 1 ሐዲስ 196
አቢ ሙሣ እንደተረከው፦ "የአሏህ መልክተኛም"ﷺ" እንዲህ አሉ፦ "አሏህ አይተኛም፥ መተኛትም ለእርሱ ተገቢው አይደለም"። عَنْ أَبِي مُوسَى، قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ ـ صلى الله عليه وسلم ـ ‏"‏ إِنَّ اللَّهَ لاَ يَنَامُ وَلاَ يَنْبَغِي لَهُ أَنْ يَنَامَ

አጽናፈ ዐለማትን የፈጠረ አንድ አምላክ ይቅርና እኔ በእጄ ላይ በብርጭቆ ሻይ ይዤ አይደለም ባንቀላፋ ባንገላጅጅ በእጄ የያስኩት ሻይ ይደፋል፥ ያ ከዐርሽ በላይ ያለው አንድ አምላክ ፍጥረትን ሲቆጣጠር እና ሲጠብቅ ማንገላጀትም እንቅልፍም የለበትም። መንገላጀት ከእንቅልፍ በፊት ያለው የሰመመን ሁኔታ ነው፥ "ሢናህ" سِنَة ማለት "መንገላጀት" ማለት ሲሆን "ነውም" نَوْم ደግሞ "እንቅልፍ" ማለት ነው። በባይብል ቢሆን አንዱ አምላክ አይተኛም አያንቀላፋም፦
መዝሙር 121፥4 እነሆ እስራኤልን የሚጠብቅ አይንገላጅም አይተኛምም። הִנֵּ֣ה לֹֽא־יָ֭נוּם וְלֹ֣א יִישָׁ֑ן ומֵ֗ר יִשְׂרָאֵֽל׃

ከማይንገላጀው እና ከማይተኛው አንዱ አምላክ በተቃራኒው ኢየሱስ ከልጅነቱ እስከ ዕውቀቱ የሚተኛ ምንነት ነው፦
ሉቃስ 2፥12 ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም "ተኝቶ" ታገኛላችሁ።
ሉቃስ 2፥16 ፈጥነውም መጡ ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግም "ተኝቶ" አገኙ።
ማርቆስ 4፥38 እርሱም በስተኋላዋ ትራስ ተንተርሶ "ተኝቶ" ነበር፥ አንቅተውም። መምህር ሆይ፥ ስንጠፋ አይገድህምን? አሉት።

ግርግም ማለት ከብቶች የሚመገቡበት አሸንዳ ነው፥ ሕፃኑ ኢየሱስ በጨቅላነቱ በግርግም ተኝቶ ነበር። ካደገ በኃላ ደግሞ ተኝቶ ሐዋርያት ሲቀሰቅሱት ነበር፥ ፍጡር በፍጡር መቀስቀስ የተተለመደ ነው። እንቅልፍ ሰውነታችን በሽታ የመከላከል ዐቅሙን በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል፣ የበላነውን ምግብ ከሰውነታችን ጋር በቀላሉ ውሕደት ይፈጥራል፣ አካላችን እረፍት በማግኘት ኃይልን ያሰባስባል፣ የአእምሮ የማስታወስ ብቃትን ያጎለብታል፥ ኢየሱስ የተኛበት ምክንያት ይህንን ጥቅም ለማግኘት ነው።

ኢየሱስ የሚተኛ እና የሚያንቀላፋ ከሆነ አንዱ አምላክ የማይተኛ እና የማያንቀላፋ ከሆነ የሚተኛ እና የሚያንቀላፋ ኢየሱስ የማይተኛውን እና የማያንቀላፋውን አንዱን አምላክ በምን ዓይነት መልኩ እንዴት አድርጎ ሊሆን ይችላል? ከ 185 እስከ 254 ድኅረ ልደት ይኖር የነበረ አርጌንስ ዘእስክንድርያ "መተኛት ለፈጣሪ ተገቢ አይደለም" ብሏል፦
"መተኛት ለፈጣሪ ተገቢ አይደለም፥ መተኛት የሰው ድካም ነው"።
On First Principles, Book 1, Chapter 6, Section 4

ከ 354 እስከ 430 ድኅረ ልደት ይኖር የነበረ አውግስጢኖስ ዘሂፓ አንዱ አምላክ በባሕርይ ላይ እንቅልፍ እንደሌለው እንዲህ ይናገራል፦
"አምላክ የእንቅስቃሴ ሁሉ እና የሕይወት ምንጭ ነው፥ ስለዚህ ለእንቅልፍ ሊገዛ አይችልም"።
The City of God, Book 11, Chapter 24

ከ 1225 እስከ 1274 ድኅረ ልደት ይኖር የነበረ ቶማስ አኳነስ እንቅልፍ የድካም ምልክት እንደሆነ እና እንቅልፍ የአምላክ ባሕርይ እንዳልሆነ አስረግጦ ተናግሯል፦
"እንቅልፍ የድካም ምልክት ነው፥ ስለዚህ እንቅልፍ ለአምላክ ሊባል አይችልም"።
Summa Theologica, Part 1 Question 9, Article 1

ኢየሱስ ሲተኛ የሚጠብቀው አምላክ ያ የማይተኛው እና የማያንቀላፋው ነው፦
ኢሳይያስ 42፥6 እኔ ያህዌህ በጽድቅ ጠርቼሃለሁ፥ እጅህንም እይዛለሁ "እጠብቅህማለሁ"።

ለመልእክተኛነት ጠሪው አንዱ አምላክ ያህዌህ ሲሆን ተጠሪው ደግሞ መሢሑ ነው፥ አምላኩ ኢየሱስን "እጠብቅህማለሁ" ሲል መሢሑ ሲተኛ የማይተኛው አምላክ ይጠብቀዋል። ያህዌህ በሁለተኛ መደብ መሢሑን "እጅህንም እይዛለሁ" ሲል ደግፎ ስለያዘው ነው፦
ኢሳይያስ 42፥1 እነሆ ደግፌ የያዝሁት ባሪያዬ፤ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ምርጤ፤ በእርሱ ላይ መንፈሴን አድርጌአለሁ።

መሢሑ ሁሉን የሚችል አምላክ ሳይሆን ሁሉን በሚችል አምላክ እጅ የተያዘ እና ሁሉን የሚችል አምላክ ደግፎ የያዘው ባርያው ነው። ክርስቲያኖች ሆይ! የሚተኛ እና የሚያንቀላፋ ፍጡር ማምለክ ትታችሁ የማይተኛውን አምላክ እንድታመልኩ ጥሪያችን ነው። በጥበቃው ላይ እንቅልፍ የሌለበት አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://www.tg-me.com/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
ዲን መሠረት ነው፣ አኽላቅ ግድግዳ ነው፣ ጣሪያው(ግቡ) ጀነት ነው። 

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://www.tg-me.com/Wahidcom
የማይሞት አምላክ

በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

25፥58 በዚያም በማይሞተው ሕያው አምላክ ላይ ተመካ፡፡ وَتَوَكَّلْ عَلَى الْحَيِّ الَّذِي لَا يَمُوتُ

አምላካችን አሏህ ስለ እርሱ ኑባሬ በሦስተኛ መደብ ሲናገር፦ "የማይሞተው ሕያው አምላክ" በማለት መዋቲነት በእርሱ ሕያውነት ላይ እንደሌለበት ይናገራል፦
25፥58 በዚያም በማይሞተው ሕያው አምላክ ላይ ተመካ፡፡ وَتَوَكَّلْ عَلَى الْحَيِّ الَّذِي لَا يَمُوتُ

በባይብልም ቢሆን አንድ ሰው እንኳ ያላየው አንዱ አምላክ ብቻ የማይሞት ነው፥ ይህም የማይሞት ብቻውን አምላክ የሚሆን ነው፦
1ኛ ጢሞቴዎስ 6፥16 እርሱ ብቻ "የማይሞት ነው"፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል፤ አንድ ሰው እንኳ አላየውም ሊያይም አይቻለውም።
1ኛ ጢሞቴዎስ 1፥17 ብቻውን አምላክ ለሚሆን "ለማይሞተው" ለማይታየውም ለዘመናት ንጉሥ ምስጋናና ክብር እስከ ዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን። Τῷ δὲ Βασιλεῖ τῶν αἰώνων, ἀφθάρτῳ ἀοράτῳ μόνῳ Θεῷ, τιμὴ καὶ δόξα εἰς τοὺς αἰῶνας τῶν αἰώνων· ἀμήν.

የማይታየው ይህ ብቻውን ያለ አምላክ የማይሞት"immortal" ከሆነ ኢየሱስ ከእርሱ በተቃራኒው ሟች ነው። እንደ ጳውሎስ ትምህርት "አንዱ" ሞተ ሲባል "አንዱ አምላክ" ማለቱ ሳይሆን "አንዱ ሰው" ሞተ ማለቱ ነው፦
2ኛ ቆሮንቶስ 5፥14 "አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ"።
ሮሜ 5፥15 "በአንዱ ሰው" በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የሆነው ስጦታ ከዚያ ይልቅ ለብዙዎች በዛ። and the gift by grace, which is by one man, Jesus Christ, hath abounded unto many.

የሚያሞት አንድ አምላክ ከሞተ ፍጥረትን ማን ሊቆጣጠራት ነው? እርሱስ ሲሞት ማን ሊያሞተው ነው? ፈጣሪ በፍጥረቱ ተገደለ ማለትስ ስሜት ይሰጣልን? የሚያሞት እና ሕያው የሚያደርግ አሏህ ከሚሉት ነገር ጥራት ይገባው! ኢየሱስ ሟች ከሆነ አንዱ አምላክ የማይሞት ከሆነ የሚሞተው ኢየሱስ የማይሞተውን አንዱን አምላክ በምን ዓይነት መልኩ እንዴት አድርጎ ሊሆን ይችላል? ከአንዱ በቀር ማንም አምላክ የለም፥ ይህ አንዱ አምላክ አይሞትም፦
1ኛ ቆሮንቶስ 8፥4 ከአንዱም በቀር ማንም አምላክ እንደሌለ እናውቃለን።
ዕንባቆም 1፥12 የተቀደስህ አምላኬ ያህዌህ ሆይ! አንተ ከዘላለም ጀምሮ አልነበርህምን? አንተ አትሞትም"። הֲלֹ֧וא אַתָּ֣ה מִקֶּ֗דֶם יְהוָ֧ה אֱלֹהַ֛י קְדֹשִׁ֖י לֹ֣א נָמ֑וּת

"አታህ" אַתָּ֣ה ማለት "አንተ" ማለት ሲሆን "ሎ ናሙት" לֹ֣א נָמ֑וּת ማለት "አትሞትም"not die" ማለት ነው፥ "አትሞትም"you will not die" በሚል ብዙ መተርጉማን አስቀምጠዋል፦
1.Christian Standard Bible
Are you not from eternity, LORD my God? My Holy One, you will not die.

2. New International Version
LORD, are you not from everlasting? My God, my Holy One, you will never die.

3. Holman Christian Standard Bible
Are You not from eternity, Yahweh my God? My Holy One, You will not die.

4. NET Bible
LORD, you have been active from ancient times; my sovereign God, you are immortal.

5. New Revised Standard Version
Are you not from of old, O LORD my God, my Holy One? You shall not die.

በተቃራኒው "እኛ አንሞትም"We shall not die" በማለት ያስቀመጡ መተርጉማን ቢኖሩም ሰው ሆኖ የማይሞት እንደሌለ ከሚታወቀው ሥነ ኑባሬአዊ እውነታ ጋር ይጣረሳል። የማይሞት አንድ አምላክ አለ፥ በአንድ አምላክ እና በሰዎች መካከል መልእክት የሚያስተላልፍ መካከለኛ ሟች ሰው አለ፦
1ኛ ጢሞቴዎስ 2፥5 አንድ አምላክ አለና፥ በአምላክ እና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። εἷς γὰρ Θεός, εἷς καὶ μεσίτης Θεοῦ καὶ ἀνθρώπων, ἄνθρωπος Χριστὸς Ἰησοῦς,

መሢሑ የማይሞት ሕያው አምላክ ሳይሆን የማይሞት ሕያው አምላክ ከሞት የሚያስነሳው ሟች ፍጡር ነው። ዮስጦስ ሰማዕቱ አምላክ ብቻ ያልተወለደ እና የማይሞት እንዲሁ ከእርሱ በኋላ ያሉት ነገሮች ሁሉ የተፈጠሩ እና የሚሞቱ መሆናቸውን ተናግሯል፦
"አምላክ ብቻ ያልተወለደ እና የማይሞት ነውና፥ ስለዚህም እርሱ አምላክ ነው። ነገር ግን ከእርሱ በኋላ ያሉት ነገሮች ሁሉ የተፈጠሩ እና የሚሞቱ ናቸው"።
Dialogue with Trypho (Justin Martyr) > Chapter 5

ክርስቲያኖች ሆይ! የሚሞት ፍጡር ማምለክ ትታችሁ የማይሞተውን ሕያው አምላክ እንድታመልኩ ጥሪያችን ነው። በሕያውነቱ ሞት የሌለበት አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://www.tg-me.com/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
የማይመገብ አምላክ

በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

6፥14 «ሰማያትን እና ምድርን ፈጣሪ ከኾነው አሏህ እርሱ የሚመግብ እና የማይመገብ ሲኾን ሌላን አምላክ እይዛለሁን?» በላቸው፡፡ قُلْ أَغَيْرَ اللَّهِ أَتَّخِذُ وَلِيًّا فَاطِرِ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ وَهُوَ يُطْعِمُ وَلَا يُطْعَمُ

አምላካችን አሏህ ጂንን እና ሰውን የፈጠረበት ዓላማ እርሱን በብቸኝነት እንዲያመልኩት ነው፦
51፥56 ጂንን እና ሰውን ሊያመልኩኝ እንጂ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም፡፡ وَمَا خَلَقْتُ الْجِنَّ وَالْإِنسَ إِلَّا لِيَعْبُدُونِ

አሏህ ከፈጠራቸው ከጂን ሆነ ከሰው ምንም ሲሳይ አይፈልግም፥ ሊመግቡትን አይሻም። በእርሱ መጋቢነት መመገብ የሚባል ባሕርይ የለውም፦
51፥57 ከእነርሱም ምንም ሲሳይ አልፈልግም፡፡ ሊመግቡኝም አልሻም፡፡ مَا أُرِيدُ مِنْهُم مِّن رِّزْقٍ وَمَا أُرِيدُ أَن يُطْعِمُونِ
6፥14 «ሰማያትን እና ምድርን ፈጣሪ ከኾነው አሏህ እርሱ የሚመግብ እና የማይመገብ ሲኾን ሌላን አምላክ እይዛለሁን?» በላቸው፡፡ قُلْ أَغَيْرَ اللَّهِ أَتَّخِذُ وَلِيًّا فَاطِرِ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ وَهُوَ يُطْعِمُ وَلَا يُطْعَمُ

"አሏህ እርሱ የሚመግብ እና የማይመገብ ሲኾን" የሚለው ይሰመርበት! ከአሏህ በተቃራኒው መሢሑ ኢየሱስ የእርሱ መልእክተኛ ሲሆን የተገኘባት እናቱ መርየም ደግሞ ጻዲቅ ሴት ናት፦
5፥75 የመርየም ልጅ አል መሢሕ ከበፊቱ መልእክተኞች በእርግጥ ያለፉ የኾነ መልእክተኛ እንጅ ሌላ አይደለም፡፡ እናቱም በጣም እውነተኛ ናት፡፡ مَّا الْمَسِيحُ ابْنُ مَرْيَمَ إِلَّا رَسُولٌ قَدْ خَلَتْ مِن قَبْلِهِ الرُّسُلُ وَأُمُّهُ صِدِّيقَةٌ

መርየም ሆነ ልጇ መሢሑ ሁለቱም ምግብን የሚመገቡ ነበሩ፦
5፥75 ሁለቱም ምግብን የሚመገቡ ነበሩ፥ አንቀጾችን ለእነርሱ (ለከሓዲዎች) እንዴት እንደምናብራራ ተመልከት! ከዚያም ከእውነት እንዴት እንደሚመለሱ ተመልከት፡፡ كَانَا يَأْكُلَانِ الطَّعَامَ ۗ انظُرْ كَيْفَ نُبَيِّنُ لَهُمُ الْآيَاتِ ثُمَّ انظُرْ أَنَّىٰ يُؤْفَكُونَ

መሢሑ ምግብ የሚመገብ ከሆነ የመሢሑ ፈጣሪ አሏህ ምግብ የማይመገብ ከሆነ የሚመገብ ፍጡር መሢሑ የማይመገበውን አንዱን አምላክ አሏህን በምን ዓይነት መልኩ እንዴት አድርጎ ሊሆን ይችላል?
በባይብልም ቢሆን ፍጥረትን የሚመግብ አንዱ አምላክ የሚበላ እና የሚጠጣ ምንነት በፍጹም አይደለም፦
መዝሙር 50፥13 የፍሪዳውን ሥጋ እበላለሁን? የፍየሉንስ ደም እጠጣለሁን?

የፍሪዳውን ሥጋ እበላለሁን? የፍየሉንስ ደም እጠጣለሁን? የሚለው መጠይቅ ምጸት "አልበላም አልጠጣም" የሚል መልእክት አለው። ይህ የማይበላ እና የማይጠጣ አንድ አምላክ ከሚበላ እና ከሚጠጣ ሰው በሰዋስው ተነጥሎ ተቀምጧል፦
ዮሐንስ 13፥31 ከወጣም በኋላ ኢየሱስ እንዲ አለ፦ “አሁን የሰው ልጅ ከበረ አምላክም ሰለ እርሱ ከበረ። Ὅτε οὖν ἐξῆλθεν, λέγει Ἰησοῦς Νῦν ἐδοξάσθη ὁ Υἱὸς τοῦ ἀνθρώπου, καὶ ὁ Θεὸς ἐδοξάσθη ἐν αὐτῷ·

"የሰው ልጅ" እና "አምላክ" ሁለት የተለያዩ ምንነት እና ማንነት ስለ ሆኑ አምላክ አክባሪ ባለቤት የሰው ልጅ ኢየሱስ ተከባሪ ተሳቢ ነው፦
ዮሐንስ 13፥32 አምላክ ስለ እርሱ የከበረ ከሆነ፥ አምላክ ደግሞ እርሱን ራሱን ያከብረዋል። ወዲያውም ያከብረዋል። εἰ ὁ Θεὸς ἐδοξάσθη ἐν αὐτῷ, καὶ ὁ Θεὸς δοξάσει αὐτὸν ἐν αὑτῷ, καὶ εὐθὺς δοξάσει αὐτόν.

"የሰው ልጅ" በሚል ቃል ውስጥ "ሰው" የተባለችው ድንግል ማርያም ስትሆን የእርሷ ልጅ ፍጡር ስለሆነ የመራብ እና የመጠማት እንዲሁ የመብላት እና የመጠጣት ባሕርይ አለው፥ ኢየሱስ ምግብ እየበላ እና መጠጥ እየጠጣ የመጣ ነው፦
ማቴዎስ 11፥19 "የሰው ልጅ” እየበላ እና እየጠጣ መጣ።

የመብላት እና የመጠጣት ባሕርይ ያለው ሰው የመጸዳዳት እና የመሽናት ባሕርይ አለው፥ ወደ አፉ የበላውን እና የጠጣውን ደግሞ በሌላ መልኩ ከሰውነት ያስወግዳል፦
ማቴዎስ 15፥17 ወደ አፍ የሚገባ ሁሉ ወደ ሆድ አልፎ ወደ እዳሪ እንዲጣል አትመለከቱምን?

ኢየሱስ መጸዳጃ ቤት ሲጸዳዳ ሰው መጥቶ ቢያንኳኳበት "ሰው አለ" እንጂ "አምላክ አለ" ወይም "ሰውም አምላክ" አለ አይልም። እንግዲህ መሢሑ የማይመገብ አምላክ ሳይሆን በፈጣሪ ሲሳይ ተመጋቢ ፍጡር ነው። ክርስቲያኖች ሆይ! እንደ እናንተ የሚመገብ ፍጡር ማምለክ ትታችሁ የማይመገበውን መጋቢ አምላክ እንድታመልኩ ጥሪያችን ነው። በመጋቢነት ላይ ተመጋቢነት የሌለበት አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://www.tg-me.com/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
የገደለ ይገደል!

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

42፥40 የመጥፎም ነገር ዋጋ ብጤዋ መጥፎ ናት፡፡ وَجَزَاءُ سَيِّئَةٍ سَيِّئَةٌ مِّثْلُهَا

“ዘንብ” ذَنب ማለት “ኃጢአት” ማለት ነው፥ በሥነ ኃጢአት ጥናት”hamartiology” ውስጥ "ኃጢአት” ማለት "አሏህ ያዘዘውን መልካም ነገር አለማድረግ፥ የከለከለውን ክፉ ነገር ማድረግ" ማለት ነው። ኃጢአት “ከባኢሩ አዝ ዘንብ” كَبَائِر الْذَنب እና “ሶጋኢሩ አዝ ዘንብ” صَغَائِر الْذَنب ተብለው ለሁለት ይከፈላሉ፥ “ከባኢር” كَبَائِر ማለት “ዐብይ” “ታላቅ” ማለት ሲሆን “ሶጋኢር” صَغَائِر ማለት ደግሞ “ንዑስ” “ትንሽ” ማለት ነው። ከዐበይት ኃጢአቶች መካከል አንዱ ነፍስን ያለ ሕግ መግደል ነው፦
ኢማም ቡኻርይ መጽሐፍ 83, ሐዲስ 53
ዐብደሏህ ኢብኑ ዐምሪው እንደተረከው፦ “ነቢዩም”ﷺ” አሉ፦ ”ዐበይት ኃጢአቶች በአሏህ ላይ ማሻረክ፣ ወላጆችን አለማክበር፣ ነፍስን መግደል እና የውሸት መሓላ ናቸው”። عَنْ عَبْدِ اللَّهِ بْنِ عَمْرٍو، عَنِ النَّبِيِّ صلى الله عليه وسلم قَالَ ‏ “‏ الْكَبَائِرُ الإِشْرَاكُ بِاللَّهِ، وَعُقُوقُ الْوَالِدَيْنِ، وَقَتْلُ النَّفْسِ، وَالْيَمِينُ الْغَمُوسُ ‏”‌‏.‏

"ቀትሉ አን-ነፍሥ" قَتْلُ النَّفْس የሚለው ቃል ይሰመርበት! አምላካችን አሏህ ነፍስን መግደል ሐራም አርጓል፦
17፥33 ”ያቺንም አላህ እርም ያረጋትን ነፍስ ያለ ሕግ አትግደሉ”፡፡ وَلَا تَقْتُلُوا النَّفْسَ الَّتِي حَرَّمَ اللَّهُ إِلَّا بِالْحَقِّ

“እርም ያረጋት” ለሚለው የገባው ቃል “ሐረመ” حَرَّمَ መሆኑ አንባቢ ልብ ይለዋል። “ሐራም” حَرَام የሚለው ቃል እራሱ “ሐረመ” حَرَّمَ ማለትም “ከለከለ” ከሚል ሥርወ ቃል የመጣ ሲሆን “የተከለከለ” ማለት ነው። እንደውም ያለጥፋት አንድን ሰው መግደል ሰዎችን ሁሉ እንደገደለ ነው፦
5፥32 ”በዚህ ምክንያት በእስራኤል ልጆች ላይ እነሆ ያለ ነፍስ መግደል ወይም በምድር ላይ ያለማጥፋት ካልሆነ በስተቀር ነፍስን የገደለ ሰው ሰዎቹን ሁሉ እንደገደለ ነው፥ ሕያው ያደረጋትም ሰው ሰዎቹን ሁሉ ሕያው እንዳደረገ ነው” ማለትን ጻፍን፡፡ مِنْ أَجْلِ ذَٰلِكَ كَتَبْنَا عَلَىٰ بَنِي إِسْرَائِيلَ أَنَّهُ مَن قَتَلَ نَفْسًا بِغَيْرِ نَفْسٍ أَوْ فَسَادٍ فِي الْأَرْضِ فَكَأَنَّمَا قَتَلَ النَّاسَ جَمِيعًا وَمَنْ أَحْيَاهَا فَكَأَنَّمَا أَحْيَا النَّاسَ جَمِيعًا

አንድን ነፍስ ያለ ሕግ መግደል እርሱ አግብቶ ቤተሰብ፣ ነገድ፣ ጎሳ፣ አገር እያለ ሕዝብ የሚሆንበትን የተፈጥሮ ዐላማና ዒላማ መቅጨት ስለሆነ ነፍስ ያለ ሕግ የገደለ ሰዎቹን ሁሉ እንደገደለ ነው። ቅሉ ግን ወሰን አልፈው የሚገሉትን ሰዎች መግደል ቂሷስ ነው፥ "ቂሷስ" قِصَاص የሚለው ቃል "ቋሶ" قَاصَّ ማለትም "አመሳሰለ" ከሚል ሥርወ ቃል የመጣ ሲሆን "ማመሳሰል" ማለት ነው፦
2፥179 ባለ አእምሮዎች ሆይ! ለእናንተም በማመሳሰል ሕግ ውስጥ ሕይወት አለላችሁ፡፡ ትጠነቀቁ ዘንድ ገዳይን መግደል ተደነገገላችሁ፡፡ وَلَكُمْ فِي الْقِصَاصِ حَيَاةٌ يَا أُولِي الْأَلْبَابِ لَعَلَّكُمْ تَتَّقُونَ

እዚህ አንቀጽ ላይ "ማመሳሰል" ለሚለው ቃል የገባው "ቂሷስ" قِصَاص መሆኑ ልብ አድርግ! ሰው ጤናማ ሕይወት ይኖር ዘንድ አምላካችን አሏህ ቂሷስን ደንግጓል፥ በቂሷስ ነፍስ ያጠፋ ነፍሱ ይጠፋል። "ያለ ሕግ አትግደሉ" ሲል በሕግ መሠረት የገደለ ይገደላል፥ መጥፎ ለሠሩ ሠዎች መጥፎ ቅጣት መቅጣት ቂሷስ ነው። የአሏህ መጽሐፍ ጭብጡ ቂሷስ ነው፦
42፥40 የመጥፎም ነገር ዋጋ ብጤዋ መጥፎ ናት፡፡ وَجَزَاءُ سَيِّئَةٍ سَيِّئَةٌ مِّثْلُهَا
ኢማም ቡኻርይ መጽሐፍ 65, ሐዲስ 26
አነሥ እንደተረከው፦ “ነቢዩም"ﷺ" እንዲህ አሉ፦ "የአሏህ መጽሐፍ ቂሷስ ነው"። أَنَّ أَنَسًا، حَدَّثَهُمْ عَنِ النَّبِيِّ صلى الله عليه وسلم قَالَ ‏ “‏ كِتَابُ اللَّهِ الْقِصَاصُ ‏”‌‏.‏

በባይብልስ? ነቁ እና በቁ የተባሉ መምህራን "መጽሐፋችን ይቅርባይነት እንጂ ግደሉ አይልም" እያሉ ይቀጥፋሉ። እኛም እንደ ፍጥርጥራቸው እና እንደ ፍጥምጥማቸው ሳንል በባይብል የገደለ እንደሚገደል እንሞግታለን፦
ዘሌዋውያን 24፥17 ሰውንም እስኪሞት ድረስ የሚመታ ፈጽሞ ይገደል።

"ይህ ብሉይ ኪዳን ላይ ነው" ብለው ማንቃረሩን ሲያያዙት ቀፍድደን ወደ አዲስ ኪዳን በማምጣት ኢየሱስ ሲመጣ ደግሞ ሕጉ ጠብቆ እና አጥብቆ የሞት ፍርድ የሚገባው የገደለ ብቻ ሳይሆን በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ የሞት ፍርድ እንደሚገባው አበክሮ እና አዘክሮ መናገሩን እናስረዳለን፦
ማቴዎስ 5፥21-22 ለቀደሙት፦ አትግደል እንደ ተባለ ሰምታችኋል፤ የገደለም ሁሉ ፍርድ ይገባዋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል።

"የገደለም ሁሉ ፍርድ ይገባዋል" ማለት በዘሌዋውያን 24፥17 "ፈጽሞ ይገደል" የሚለው ከሆነ "በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል" ሲል "ፍርድ ይገባዋል" ማለት "ፈጽሞ ይገደላል" ማለት ነው። አጥር እና ቅጥር በማድረግ "ብሉይ ኪዳን ላይ ነው" ለሚሉን ኢየሱስ እንቅጩን ፍርጥ አርጎ፦ "በሰይፍ የሚገድል ማንም ቢኖር ራሱ በሰይፍ እንዲገደል ይገባዋል" ማለቱን እናረዳቸዋለን፦
ራእይ 13፥10 "በሰይፍ የሚገድል ማንም ቢኖር ራሱ በሰይፍ እንዲገደል ይገባዋል"።

"በሰይፍ የሚገድል ማንም ቢኖር ራሱ በሰይፍ እንዲገደል ይገባዋል" የሚለው መልእክት በዮሐንስ፣ በመልአኩ፣ በኢየሱስ ከአምላክ የመጣ መልእክት ነው። ራእይ 1፥1 ተመልከት! በአዲስ ኪዳን ባለ ሥልጣኖች በአምላክ የተሾሙ እና በመልካም ነገር ለሕዝብ የቆሙ የአምላክ አገልጋዮች ናቸው፥ ሰይፍ የሚታጠቁት አምባሻ ሊቆርጡበት ሳይሆን ሕገ ወጥን አንገቱን እንዲቀሉበት ነው፦
ሮሜ 13፥1 ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በአምላክ የተሾሙ ናቸው።
ሮሜ 13፥4 ለመልካም ነገር ለአንተ የአምላክ አገልጋይ ነውና። በከንቱ ግን ሰይፍ አይታጠቅምና ክፉ ብታደርግ ፍራ፤ ቍጣውን ለማሳየት ክፉ አድራጊውን የሚበቀል የአምላክ አገልጋይ ነውና።

የምን ከዘፋኙ በላይ መወዛወዝ ነው? ባለ ሥልጣኖች ክፉ አድራጊውን የሚበቀሉ የአምላክ አገልጋዮች ከሆኑ እንግዲያውስ የገደለውን በታጠቀው ሰይፍ መቅጣት አዲስ ኪዳናዊ ትምህርት መሆኑን ስናራውጣቸው እና ስናቆራጥጣቸው መግቢያቸው ምን ይሆን? አሏህ ሂዳያህ ይስጣቸው! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://www.tg-me.com/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
ወሒድ የዕቅበተ ኢሥላም መጣጥፍት"Wahid Articles of Islamic Apologetics"
Video
ስቅለተ ዐርብ

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

4፥157 ጥርጣሬን ከመከተል በስተቀር በእርሱ ነገር ምንም ዕውቀት የላቸውም፡፡ በእርግጥም አልገደሉትም፡፡ مَا لَهُم بِهِ مِنْ عِلْمٍ إِلَّا اتِّبَاعَ الظَّنِّ ۚ وَمَا قَتَلُوهُ يَقِينًا

ክርቲያኖች እራሳቸውን የሚያስጠጉበት ጳውሎስ ኢየሱስ በተቀበረ "በሦስተኛው ቀን ተነሣ" ይለናል፦
1ኛ ቆሮንቶስ 15፥3 መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፥ ተቀበረም፥ መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ፥ that he was buried and that he was raised on the third day according to the Scriptures.

ሦስቱ ቀን የሚጀምረው ከተቀበረበት ከሆነ በምድር ልብ ማለትም በመቃብር ውስጥ ሦስት ቀን እና ሦስት ሌሊት እንደሚሆን ይናገራል፦
ማቴዎስ ወንጌል 12፥40 ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ፥ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል።

ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት በመቃብር ያለውን ጊዜ የሚሸፍን መሆኑን ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ያ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወደ መቃብር የገባው ደግሞ በምሽት ነው፦
ማርቆስ 15፥42-46 አሁንም "በመሸ ጊዜ" የሰንበት ዋዜማ የሆነ የማዘጋጀት ቀን ስለ ነበረ።

"በመሸ ጊዜ" የሚለው ኃይለ ቃል ይሰመርበት! አይሁድ የሚያከብሩት በዓል ከ 12 ሰዓት በኃላ የነገው ነው፥ ያ በዓል የሚጀመረውም ሌሊቱ ከምሽቱ 12 ነው። ምሽት የሌሊት መጀመሪያ ነው፦
ዘጸአት 12፥18 በመጀመሪያውም ወር በአሥራ አራተኛው ቀን "በመሸ ጊዜ" ከወሩም እስከ ሀያ አንድ ቀን በመሸ ጊዜ የቂጣ እንጀራ ትበላላችሁ።
ማቴዎስ 26፥20 "በመሸም ጊዜ" ከአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ።
ማርቆስ 1፥32 "ፀሐይም ገብቶ በመሸ ጊዜ"፥ የታመሙትንና አጋንንት ያደረባቸውን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤

"ፀሐይም ገብቶ በመሸ ጊዜ" የሚለው ይሰመርበት! ምሽት ማለት የፀሐይ መግባት ነው። እንግዲህ ከዚህ ከሰንበት ማለት ከቅዳሜ ዋዜማ ምሽቱ የቅዳሜ ከሆነ ከዚያ ጀምራችሁ ቁጠሩት! ሰኞ ማታ ለማክሰኞ ዋዜማ ላይ ይመጣል፥ ያ ማለት ሥስት ቀን እና ሦስት ሌሊት አይሞላም። አንድ የቅዳሜ ሌሊት እና አንድ የእሑድ ሌሊት ሲሆን ሁለት ሌሊት ይሆናል፥ አንድ የቅዳሜ መዓልት(ቀን) ብቻ ይተርፋል። በጥቅሉ ሁለት ሌሊት እና አንድ መዓልት እንጂ ሦስት ሌሊት እና ሦስት መዓልት አይሞላም፦
ዮሐንስ 20፥1 ከሳምንቱም በፊተኛው ቀን መግደላዊት ማርያም ገና ጨለማ ሳለ ማለዳ ወደ መቃብር መጣች ድንጋዩም ከመቃብሩ ተፈንቅሎ አየች።

በአይሁድ የሳምንቱም ፊተኛው ቀን እሑድ ሲሆን እሑድ እጅግ በማለዳ ፀሐይ ሳትወጣ ጨለማ ሳለ ከመቃብር ተነሳ ካለ ሦስት ሌሊት እና ሦስት መዓልት አይሞላም። ይህ የገባው የፕሮቴስታንት መምህር ሀብታሙ ታደሰ "ኢየሱስ የሞተው ረቡዕ ነው" በማለት ከእሑድ ወደ ኃላ በመቁጠር ሦስት ሌሊት እና ሦስት መዓልት የሚለውን ለማስታረቅ ሞክሯል። ቅሉ እና ጥቅሉ ግን ቤተክርስቲያን ሆነች የቤተክርስቲያን አበው "ረቡዕ" የሚለውን ሳይሆን "ዓርብ" የሚለውን ስላስቀመጡ ስቅለት የሚባል በዓል በዓመት አንድ ጊዜ ዓርብ ቀን ያከብራሉ፦
ዲድስቅልያ 30፥25 ዓርብ ቀን ሰቀሉት፥ ተሰቅሎ በሞተ በሦስተኛው ቀን ተነሣ።

ዲድስቅልያ"didache" የጥንት ጽሑፍ ነው። እሩቅ ሳንሄድ የ 1980 አዲስ ትርጉም ኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ እና ፕሮቴስታንት የተሳተፉበት የትርጉም ሥራ ሲሆን የሸንጎ አማካሪ የሆነ ዮሴፍ በዓለት በተዋቀረ መቃብር የቀበረው ዓርብ ማታ እንደሆነ ተጽፏል፦
ሉቃስ 23፥54 ይህንንም ያደረገው "ዓርብ" ማታ ለሰንበት ዝግጅት በሚደረግበት ጊዜ ነው።

የ 1993 አዲሱ መደበኛ ትርጉም ሉቃስ 23፥54 ጥቅስን በሚያብራራበት የግርጌ ማብራሪያ ላይ "የመዘጋጀት ቀን ለሰንበት ቀን የሚያስፈልግ ማንኛውም ነገር የሚሰናዳበት ቀን ሲሆን ቀኑም ዓርብ ነው" በማለት እንቅጩን አስቀምጧል። ከመነሻው ሰንበት ቅዳሜ ከሆነ የሰንበት ዋዜማ ዐርብ ነው፦
ማርቆስ 15፥42 አሁንም በመሸ ጊዜ የሰንበት ዋዜማ የሆነ የማዘጋጀት ቀን ስለ ነበረ፥ የከበረ አማካሪ የሆነ የአርማትያስ ዮሴፍ መጣ።

"የሰንበት ዋዜማ" የሚለው ይሰመርበት! የማርቆስ 15፥42 የትርጓሜ መጽሐፍ አንድምታው፦ "ዓርብ ሲመሽ ያን ጊዜም የሰንበት መግቢያ ነበር" በማለት ፍርጥ አርጎ አስቀምጦታል። ገና ለገና ከሙሥሊም ሙግት ለማምለጥ ታሪክን እና ትውፊትን ጥሶ እና በርጥሶ "የተሰቀለው ረቡዕ ነው" ብሎ መጨነቅ እና መጨናነቅ ለምን አስፈለገ? ጥርጣሬን ከመከተል በስተቀር በኢየሱስ ነገር ምንም ዕውቀት የላቸውም፡፡ በእርግጥም አልገደሉትም፦
4፥157 ጥርጣሬን ከመከተል በስተቀር በእርሱ ነገር ምንም ዕውቀት የላቸውም፡፡ በእርግጥም አልገደሉትም፡፡ مَا لَهُم بِهِ مِنْ عِلْمٍ إِلَّا اتِّبَاعَ الظَّنِّ ۚ وَمَا قَتَلُوهُ يَقِينًا

አሏህ ሂዳያህ ይስጣቸው! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://www.tg-me.com/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
ሞናርኪያውያን

ክፍል አንድ

በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

28፥53 በእነርሱ ላይ በሚነበብላቸውም ጊዜ «በእርሱ አምነናል፡፡ እርሱ ከጌታችን የኾነ እውነት ነው፡፡ "እኛ ከእርሱ በፊት ሙሥሊሞች ነበርን» ይላሉ፡፡ وَإِذَا يُتْلَىٰ عَلَيْهِمْ قَالُوا آمَنَّا بِهِ إِنَّهُ الْحَقُّ مِن رَّبِّنَا إِنَّا كُنَّا مِن قَبْلِهِ مُسْلِمِينَ

"ሞናርኪያ" የሚለው ቃል "ሞናርኺያ" μοναρχίᾱ ከሚል ግሪክ ኮይኔ ቃል የመጣ ነው፥ "ሞናርኺያ" μοναρχίᾱ የሚለው ቃል "ሞኖስ" μόνος እና "አርኾስ" ἀρχός ከሚል ሁለት ቃላት ውቅር ነው። "ሞኖስ" μόνος ማለት "ብቻ" ማለት ሲሆን "አርኾስ" ἀρχός ማለት ደግሞ "ገዥ" ማለት ነው፥ በጥቅሉ "ሞናርኺያ" μοναρχίᾱ ማለት "ብቸኛ ገዥነት" ማለት ነው። "አንድ አምላክ አብ ብቻ ነው" የሚል አቋም ያላቸው የጥንት አሐዳውያን "ሞናርኪያውያን" ሲባሉ "የኢየሱስ አምላክ አንዱ አምላክ ነው" የሚል ይህ አቋም የኢየሱስም አቋም ነው፦
ዮሐንስ 17፥3 እውነተኛ አምላክ ብቻህን የሆንህ አንተን እና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት። αὕτη δέ ἐστιν ἡ αἰώνιος ζωή, ἵνα γινώσκωσιν σὲ τὸν μόνον ἀληθινὸν θεὸν καὶ ὃν ἀπέστειλας Ἰησοῦν Χριστόν.

"ሴ ቶን ሞኖን አሌቲኖን ቴዎን" σὲ τὸν μόνον ἀληθινὸν θεὸν ማለት "እውነተኛ አምላክ ብቻህን የሆንህ አንተን" ማለት ነው፥ ለዚያ ነው የኦርቶዶክስ፣ የካቶሊክ እና የፕሮቴስታንት ሊቃውንት የተሳተፉበት የ 1980 አዲስ ትርጉም፦ "ብቻህን እውነተኛ አምላክ የሆንከው አንተን" ብሎ በቅጡ ያስቀመጠው። "ሞኖን" μόνον" ማለት "ብቻ" ማለት ሲሆን ይህም ቅጽል እየገለጸ ያለው ከፊቱ "ሴ" σὲ ማለትም "አንተ" የተባለውን ማንነት ነው፥ ይህም ማንነት አብ ሲሆን አብ ብቻውን እውነተኛ አምላክ ነው።

"ሞኖቴይዝም"monotheism" የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል እራሱ "ሞኖስ" μόνος እና "ቴዎስ" θεός ከሚሉ ሁለት ቃላት የተዋቀረ ነው፥ "ሞኖስ" μόνος ማለት "ብቸኛ" ማለት ሲሆን "ቴዎስ" θεός ደግሞ "አምላክ" ማለት ነው። በጥቅሉ "ሞኖ ቴዎስ" μόνο θεός ማለት "አንድ ብቸኛ አምላክ" ማለት ሲሆን ይህም አንድ አምላክ ኢየሱስን የላከ ነው። ጳውሎስም ብዙ ቦታ አብን ብቸኛ አምላክ አርጎ ያስቀምጣል፦
ሮሜ 16፥27 "ብቻውን" ጥበብ ላለው "ለ-"አምላክ" "በ-"ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን! አሜን። μόνῳ σοφῷ Θεῷ, διὰ Ἰησοῦ Χριστοῦ, ᾧ ἡ δόξα εἰς τοὺς αἰῶνας τῶν αἰώνων· ἀμήν.
1 ጢሞቴዎስ 1፥17 "ብቻውን" አምላክ ለሚሆን ለማይሞተው፣ ለማይታየው፣ ለዘመናት ንጉሥ ምስጋናና ክብር እስከ ዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን። Τῷ δὲ Βασιλεῖ τῶν αἰώνων, ἀφθάρτῳ ἀοράτῳ μόνῳ Θεῷ, τιμὴ καὶ δόξα εἰς τοὺς αἰῶνας τῶν αἰώνων· ἀμήν.
1 ጢሞቴዎስ 6፥16 እርሱ ብቻ የማይሞት ነው፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል፤ አንድ ሰው እንኳ አላየውም ሊያይም አይቻለውም፤ ለእርሱ ክብርና የዘላለም ኃይል ይሁን፤ አሜን። ὁ μόνος ἔχων ἀθανασίαν, φῶς οἰκῶν ἀπρόσιτον, ὃν εἶδεν οὐδεὶς ἀνθρώπων οὐδὲ ἰδεῖν δύναται· ᾧ τιμὴ καὶ κράτος αἰώνιον· ἀμήν.
1 ጢሞቴዎስ 6፥15 ያንም መገለጡን በራሱ ጊዜ ብፁዕና "ብቻውን የሆነ ገዥ" የነገሥታት ንጉሥ እና የጌቶች ጌታ ያሳያል። ἣν καιροῖς ἰδίοις δείξει ὁ μακάριος καὶ μόνος Δυνάστης, ὁ Βασιλεὺς τῶν βασιλευόντων καὶ Κύριος τῶν κυριευόντων,

1 ጢሞቴዎስ 6፥16 ላይ "እርሱ" የሚለው ተውላጠ ስም 1 ጢሞቴዎስ 6፥15 ላይ "ብቻውን የሆነ ገዥ" የተባለውን ማንነት ተክቶ የመጣ ነው፥ ስለዚህ "እርሱ ብቻ የማይሞት ነው፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል፤ አንድ ሰው እንኳ አላየውም ሊያይም አይቻለውም" የተባለው አብ ሲሆን ይህም "ብቻውን የሆነ ገዥ" ነው። ብቻውን ለሆነ አምላክ ክብር፣ ግርማ፣ ኃይል እና ሥልጣን በኢየሱስ አማካኝነት ይቀርብለታል፦
ይሁዳ 1፥25 "ብቻውን "ለ-ሆነ አምላክ እና መድኃኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለምም ድረስ በጌታችን "በ-"ኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኃይልም ሥልጣንም ይሁን፤ አሜን። μόνῳ Θεῷ Σωτῆρι ἡμῶν διὰ Ἰησοῦ Χριστοῦ τοῦ Κυρίου ἡμῶν δόξα μεγαλωσύνη κράτος καὶ ἐξουσία πρὸ παντὸς τοῦ αἰῶνος καὶ νῦν καὶ εἰς πάντας τοὺς αἰῶνας· ἀμήν.
አምላካችን አሏህ በዒሣ ቀዳማይ ተከታዮች ልቦች ውሰጥ መለዘብን እና እዝነትን አድርጎ ሳለ የአሏህን ውዴታ ለመፈለግ ምንኩስና ፈጠሩ፥ ነገር ግን አዲስ የፈጠሩዋትንም ምንኩስናን በእነርሱ ላይ አልደነገገም። ከእነርሱም ብዙዎቹ አመጸኞች ሲሆኑ ጥቂት አሓዳውያን በቁርኣን ላመኑት ምንዳቸውን ሰጣቸው፦
57፥27 ከእነርሱም ለእነዚያ ላመኑት ምንዳቸውን ሰጠናቸው፥ ከእነርሱም ብዙዎቹ አመጸኞች ናቸው፡፡ فَـَٔاتَيْنَا ٱلَّذِينَ ءَامَنُوا۟ مِنْهُمْ أَجْرَهُمْ ۖ وَكَثِيرٌۭ مِّنْهُمْ فَٰسِقُونَ

እነዛ ጥቂት አሓዳውያን ቁርኣን በወረደበት ጊዛ በቁርኣን አምነዋል፥ ቁርኣን በእነርሱ ላይ በሚነበብላቸውም ጊዜ «በቁርኣን አምነናል፡፡ ቁርኣን ከጌታችን የኾነ እውነት ነው፡፡ "እኛ ከቁርኣን በፊት ሙሥሊሞች ነበርን» ይላሉ፦
28፥52 እነዚያ ከእርሱ በፊት መጽሐፍን የሰጠናቸው እነርሱ "በእርሱ ያምናሉ"፡፡ الَّذِينَ آتَيْنَاهُمُ الْكِتَابَ مِن قَبْلِهِ هُم بِهِ يُؤْمِنُونَ
28፥53 በእነርሱ ላይ በሚነበብላቸውም ጊዜ «በእርሱ አምነናል፡፡ እርሱ ከጌታችን የኾነ እውነት ነው፡፡ "እኛ ከእርሱ በፊት ሙሥሊሞች ነበርን» ይላሉ፡፡ وَإِذَا يُتْلَىٰ عَلَيْهِمْ قَالُوا آمَنَّا بِهِ إِنَّهُ الْحَقُّ مِن رَّبِّنَا إِنَّا كُنَّا مِن قَبْلِهِ مُسْلِمِينَ

"እኛ ከእርሱ በፊት ሙሥሊሞች ነበርን" የሚለው ይሰመርበት! "ሙሥሊም” مُسْلِم ማለት "አንዱን አምላክ በብቸኝነት አምላኪ፣ ተገዢ፣ ታዛዥ" ማለት ነው፥ እዚህ አንቀጽ ላይ "ሙሥሊሞች" ለሚል የገባው ቃል "ሙሥሊሚን" مُسْلِمِين ሲሆን "ሙሥሊም" مُسْلِم ለሚለው ብዙ ቁጥር ነው። ወደ ተወዳጁ ነቢያችን"ﷺ" የመጣው ወሕይ ጭብጡ እና አንኳር መልእክቱ "አምላካችሁ አንድ አምላክ ብቻ ነው" የሚል ነው፦
6፥19 «እርሱ አንድ አምላክ ብቻ ነው፡፡ እኔም ከምታጋሩት ነገር ንጹሕ ነኝ» በላቸው፡፡ قُلْ إِنَّمَا هُوَ إِلَٰهٌۭ وَٰحِدٌۭ وَإِنَّنِى بَرِىٓءٌۭ مِّمَّا تُشْرِكُونَ
21፤108 «ያ ወደ እኔ የሚወረደው፦ "አምላካችሁ አንድ አምላክ ብቻ ነው" ማለት ነው፥ ታዲያ እናንተ ፍጹም “ታዛዦች” ናችሁን?» በላቸው፡፡ قُلْ إِنَّمَا يُوحَىٰٓ إِلَىَّ أَنَّمَآ إِلَٰهُكُمْ إِلَٰهٌۭ وَٰحِدٌۭ ۖ فَهَلْ أَنتُم مُّسْلِمُونَ

እዚህ አንቀጽ ላይ “ታዛዦች” ተብሎ የተቀመጠው ቃል "ሙሥሊሚን" مُسْلِمِين እንደሆነ ልብ አድርግ! "አንድ" ለሚለው ቃል የገባው ቃል “ዋሒድ” وَٰحِد ነው፥ "አሏህ አንድ ነው" ብሎ የሚያምን አማኝ “ሙዋሒድ” مُوَٰحِد ሲባል የአንድ አምላክ አስተምህሮቱ ደግሞ "ተውሒድ" تَوْحِيد ይባላል። ከእነርሱም ብዙዎቹ ከቀጥተኛው መንገድ ከተውሒድ ወጥተው በሥላሴ በማመን የተሳሳቱ ናቸው፥ ቅሉ ግን ጥቂት ያልተሳሳቱ የኢየሱስ ተከታዮች ነበሩ፦
1፥7 የእነዚያን በእነርሱ ላይ በጎ የዋልክላቸውን፥ በእነርሱ ላይ ያልተቆጣህባቸውን እና ያልተሳሳቱትን ሰዎች መንገድ ምራን" በሉ፡፡ صِرَاطَ الَّذِينَ أَنْعَمْتَ عَلَيْهِمْ غَيْرِ الْمَغْضُوبِ عَلَيْهِمْ وَلَا الضَّالِّينَ
ጃምዒ አት ቲርሚዚይ መጽሐፍ 47 ሐዲስ 3212
ዐዲይ ኢብኑ ሓቲም እንደተረከው ነብዩም”ﷺ” አሉ፦ "አይሁዳውያን የተቆጣባቸው ናቸው፥ ክርስቲያኖች የተሳቱተት ናቸው"። عَنْ عَدِيِّ بْنِ حَاتِمٍ، عَنِ النَّبِيِّ صلى الله عليه وسلم قَالَ ‏ “‏ الْيَهُودُ مَغْضُوبٌ عَلَيْهِمْ وَالنَّصَارَى ضُلاَّلٌ ‏”‏ ‏.‏

ከክርስቲያኖች ጥቂት ያልተሳሳቱ ሙዋሒዲን የሄዱበትን መንገድ "ምራን" ብለን እንቀራለን። ታዲያ ሞናርኪያውያን በታሪክ ውስጥ ምን ሆኑ? አሁን ላይ የት አሉ? ኢንሻላህ ይቀጥላል.....

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://www.tg-me.com/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
قَالَ إِنِّي عَبْدُ اللَّهِ آتَانِيَ الْكِتَابَ وَجَعَلَنِي نَبِيًّا
وَجَعَلَنِي مُبَارَكًا أَيْنَ مَا كُنتُ وَأَوْصَانِي بِالصَّلَاةِ وَالزَّكَاةِ مَا دُمْتُ حَيًّا
وَبَرًّا بِوَالِدَتِي وَلَمْ يَجْعَلْنِي جَبَّارًا شَقِيًّا
وَالسَّلَامُ عَلَيَّ يَوْمَ وُلِدتُّ وَيَوْمَ أَمُوتُ وَيَوْمَ أُبْعَثُ حَيًّا
ሞናርኪያውያን

ክፍል ሁለት

በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

5፥14 ከእነዚያም "እኛ ነሷራ ነን" ካሉት የጠበቀ ቃል ኪዳናቸውን ያዝን፡፡ በእርሱም ከታዘዙበት ነገር ፈንታን ተውት፡፡ وَمِنَ الَّذِينَ قَالُوا إِنَّا نَصَارَىٰ أَخَذْنَا مِيثَاقَهُمْ فَنَسُوا حَظًّا مِّمَّا ذُكِّرُوا بِهِ فَأَغْرَيْنَا

የኢየሱስ ቀዳማይ ተከታዮች ሐዋርያት ሙሥሊሞች ነበሩ፦
3፥52 ዒሣ ከእነርሱ ክህደት በተሰማውም ጊዜ፡- «ወደ አሏህ ረዳቶቼ እነማን ናቸው?» አለ፥ ሐዋርያትም፡- «እኛ የአሏህ ረዳቶች ነን፤ በአሏህ አምነናል፥ እኛም ትክክለኛ ታዛዦች መኾናችንን መስክር» አሉ፡፡ فَلَمَّآ أَحَسَّ عِيسَىٰ مِنْهُمُ ٱلْكُفْرَ قَالَ مَنْ أَنصَارِىٓ إِلَى ٱللَّهِ ۖ قَالَ ٱلْحَوَارِيُّونَ نَحْنُ أَنصَارُ ٱللَّهِ ءَامَنَّا بِٱللَّهِ وَٱشْهَدْ بِأَنَّا مُسْلِمُونَ

እዚህ አንቀጽ ላይ "ታዛዦች" ለሚል የገባው ቃል "ሙሥሊሙን" مُسْلِمُون ሲሆን "ሙሥሊም" مُسْلِم ለሚለው ብዙ ቁጥር ነው፥ "ነሲር" نَصِير ማለት "ረዳት" ማለት ሲሆን የነሲር ብዙ ቁጥር ደግሞ "አንሷር" أَنصَار ነው። "ነስራኒይ" نَصْرَانِيّ ገላጭ ቅጽል ሲሆን "ረዳት" ማለት ነው፥ የነስራኒይ ብዙ ቁጥር "ነሷራ" نَصَارَىٰ ሲሆን "ረዳቶች" ማለት ነው፦
5፥14 ከእነዚያም "እኛ ነሷራ ነን" ካሉት የጠበቀ ቃል ኪዳናቸውን ያዝን፡፡ በእርሱም ከታዘዙበት ነገር ፈንታን ተውት፡፡ وَمِنَ الَّذِينَ قَالُوا إِنَّا نَصَارَىٰ أَخَذْنَا مِيثَاقَهُمْ فَنَسُوا حَظًّا مِّمَّا ذُكِّرُوا بِهِ فَأَغْرَيْنَا

አምላካችን አሏህ "እኛ የአሏህ ረዳቶች ነን" ካሉት ከሐዋርያት ጋር የያዘው የጠበቀ ቃል ኪዳን «በእኔ እና በመልእክተኛዬ እመኑ» የሚል ነው፥ እነርሱም "አመንን፥ እኛ ሙሥሊሞች መኾናችንን መስክር" አሉ፦
5፥111 ወደ ሐዋርያትም «በእኔ እና በመልእክተኛዬ እመኑ» በማለት ባዘዝኩ ጊዜ አስታውስ፡፡ وَإِذْ أَوْحَيْتُ إِلَى الْحَوَارِيِّينَ أَنْ آمِنُوا بِي وَبِرَسُولِي
5፥111 «አመንን፥ እኛ ሙሥሊሞች መኾናችንን መስክር» አሉ፡፡ قَالُوا آمَنَّا وَاشْهَدْ بِأَنَّنَا مُسْلِمُونَ

እዚህ አንቀጽ ላይ "ሙሥሊሞች" ለሚል የገባው ቃል "ሙሥሊሙን" مُسْلِمُون መሆኑን ልብ አድርግ! ነገር ግን ከሐዋርያት ኅልፈት በኃላ የተነሱት ሰዎች የታዘዙበትን ተውሒድ ተውት፥ በአሏህ ላይ ወሰን አልፈው አምላክን "አንድም ሦስትም ነው" በማለት አስተማሩ።
ከ 180 እስከ 313 ድኅረ ልደት በዓለም ዐቀፍ ደረጃ "ታላቂቱ ቤተክርስቲያን"Great Church" ተብላ በሮም መንግሥት መቀመጫ ያደረገች ታላቂቱ ቤተክርስቲያን በአበው ተዋቅራ ተደራጀች፥ ይህቺ ሴት በሮም መንግሥት ላይ ተቀምጣ በቅዱሳን ደም እና በኢየሱስ ምስክሮች ደም ሰክራ ታይታለች፦
ራእይ 17፥6 ሴቲቱም በቅዱሳን ደም እና በኢየሱስ ምስክሮች ደም ሰክራ አየኋት።

በታሪክ ውስጥ "ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው" የሚለውን ታላቁን እና ፊተኛውን የአምላክ ትእዛዝ የሚጠብቁትን የኢየሱስ ምስክር ያላቸው አሐዳውያንን ቤተ ክርስቲያን ደማቸውን በማፍሰስ ገላለች።
በ 200 እስከ 275 ድኅረ ልደት ይኖር የነበረውን ጳውሎስ ዘሳምሳጢ"Paul of Samosata" የሳምሳጢ ኤጲስቆጶስ በግዝት እና በግዞት አሰቃይታለች። ሞናርኪያውያን "ኢየሱስ በምንነት ሰው ብቻ ነው፣ ምንነቱ ከማርያም ይጀምራል፣ ከማርያም በፊት በቃል ደረጃ እንጂ በህልውና የለም። በማንነቱ ነቢይ፣ መልእክተኛ፣ መሢሕ ነው፥ የአብ ልጅ የተባለው በግብር እንጂ በባሕርይ ስላልሆነ ልጅነቱ የማደጎ ልጅነት"Adoption" ነው" የሚል አቋም ነበራቸው፦
2ኛ ሳሙኤል 7፥12 ከወገብህ የሚወጣውን ዘርህን ከአንተ በኋላ አስነሣለሁ፥
2ኛ ሳሙኤል 7፥14 እኔም አባት እሆነዋለሁ፥ እርሱም ልጅ ይሆነኛል።

ከወገብ የሚወጣ ዘር ፍጡር ነው፥ ከወገብ ለሚወጣ ዘር አምላክ "አባት እሆነዋለሁ" ሲል የሚወጣው ዘር ደግሞ "ልጅ ይሆነኛል" ስላለ ልጅነቱ የማደጎ ልጅነት የሚል አቋም አላቸው። እነዚህ ሞናርኪያውያን "ጠንካራ ሞናርኪያውያን"dynamic monarchian" ሲባሉ ነገር ግን በ 260 ድኅረ ልደት ሰባልስዮስ ዘሊቢያ"Sabellius of Libya" ሞናርኪያ የነበረ ሲሆን ሮም ሄዶ ከተማረ በኃላ "ኩነት"mode of existence" የተባለውን ትምህርት አስተማረ፦
መጽሐፈ ምሥጢር ምዕራፍ 5 ቁጥር 4
"ሰብልያኖስ "አብ እንደ ሰው፣ ወልድ እንደ አንደበቱ ንግግር፣ መንፈስ ቅዱስ እንደ አፉ እስትንፋስ ናቸው" አለ። ስለዚህ አንድ ገጽ ናቸው" አለ።

"አንድ ሰው አንድ ገጽ(ማንነት) ኖሮት ዋናው ልብ ሲኖረው ከልቡ ቃል እና ከአፉ እስትንፋስ እንደሚወጣ አንድ አምላክ አብ ከራሱ የሚወጣ ቃል ወልድ እስትንፋሱ መንፈስ ቅዱስ ይባላል" የሚል አቋም ያላቸው የሰባልዮስ ተከታዮች "ኩነታዊ ሞናርኪያውያን"Modalistic monarchian" ይባላሉ። ሰባልዮስ ይህንን አቋም ሊያራምድ የቻለው ሮም ውስጥ "አማልክት ከአንዱ አምላክ "ብናኝ"Aeon" እየሆኑ ይወጣሉ" የሚል የኤዎን እሳቤ አዙሮት ነው። ይህ የመኳኳን ኩነት አብን ካርዲያስ ምንጭ፣ ወልድን ሎጎስ፣ መንፈስ ቅዱስን ኑውማቶስ በማድረግ ተኳኩነት"Modalism" ነው፥ "ካርዲያስ" καρδίας ማለት "ልብ" ማለት ነው፣ "ሎጎስ" λόγος ማለት "ቃል" ማለት ነው፣ "ኑውማቶስ" ማለት "እስትንፋስ" ማለት ነው።
2025/07/10 11:07:57
Back to Top
HTML Embed Code: