Telegram Web Link
አባ ይፍቱኝ
(በእወቀቱ ስዩም)

ሲኦል አለ ሲሉኝ፥ የለም ብየ ክጀ
የባልቴት ተረት ነው፥ በማለት ቀልጀ
አውቄ በድፍረት፥ በድያለሁና
ያንጹኝ በንስሐ፥ ያንሱኝ በቀኖና
ሲኦል ከነጭፍራው፥ በጉም ተሸፍኖ
እንዴት ሳላየው ኖርኩ፥ ካጠገቤ ሆኖ?

አባ ይፍቱኝ
ሰይጣን ብሎ ነገር፥ የተጭበረበረ
ዋዛ ነው ቧልት ነው፥ ብየ አስብ ነበረ
ይሄው እውነት ሆኖ፥ ዋዛና ተረቱ
ባይኔ በብረቱ
ዲያብሎስን አየሁት፥ በሸሚዝ ዘንጦ
እልፍ ግዳይ ጥሎ፥ ቸብቸቦ ጨብጦ

አባ
ልክ እንደ ብርሌ፥ አጥንት ሲከሰከስ
አባይን አዋሽን፥ የሚያስንቅ ደም ሲፈስ
ለምለም ፍጥረት ሁላ፥ ወደ አመድ ሲመለስ
ልክ እንደ ጧፍ ሐውልት፥ ምስኪኖች ሲጋዩ
ምድጃው ዳር ሆነው፥ ይሄንን እያዩ
ገሃነም ከላይ ነው፥ ብለው መሳትዎ
እርስዎ እንደፈቱኝ፥ እግዚሃር ይፍታዎ፡፡

@zephilosophy
እኛን ኢትዮጵያውያንን ጠፍሮ የያዘን ምንድነው?
____
(የባህል አብዮትና መፈንቅለ-አስተሳሰብ እንደ መፍትሄ)

ፀሀፊ -አሰፋ ሀይሉ

ከሃያ ምናምን ዓመታት በፊት ከዩኒቨርሲቲ የመመረቂያ ጥናቴን የሠራሁት በFreedom of Association ላይ ነበረ።

ያ ጥናት በተለይ ሰዎች ፖለቲካዊ ማኅበሮችን የሚፈጥሩበትን ሂደትና በፓርቲ ምሥረታና እንቅስቃሴዎች ላይ ያሏቸውን ነፃነቶችና ገደቦች በዓለም ዙሪያና ባገራችንም across centuries ያሉትን አንኳር እውነቶች ለመዳሰስ የሞከርኩበት ጥናት ነበረ።

የኢትዮጵያችንን በተመለከተ ከእኔ በፊት ጉዳዩን ያጠኑ ጥቂት የውጭና ያገርውስጥ ምሁራን ነበሩ። የሚገርመኝ አንድ ነገር፣ የጥናቶቹ ሁሉ ግኝትና ድምዳሜ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በንጉሡም ዘመን፣ በወታደራዊው ደርግ ዘመንም ሆነ በኢህአዴግ ዘመን፣ (ሌላ ቀርቶ አሁንም ላይ) በአንድ ዓይነት ባህርይ የተቃኘ መሆኑ ነው።

በኢትዮጵያችን ለምን የmultiparty አስተሳሰብ አልዳበረም? ለምን የተቃውሞ ድምፅን ሰብሰብ ብሎ በማኅበር ተደራጅቶ ማሰማት፣ ለጋራ መብት በጋራ መቆም ለምንድነው ኢትዮጵያውያንን የሚያስፈራቸው? ምንድነው የያዘን? የሁሉም፣ የሁላችንም ጥያቄ ነው።

ዋና ታሪካዊ ምንጩ የእኛ የኢትዮጵያውያን አስተሳሰብ ወይም አመለካከት ነው የሚል ነው።

እኛ ኢትዮጵያውያን ሥር-የሰደደ የተገዢነት ስነልቦና ያለን ሕዝቦች ነን! አብረን በጋራ ተደራጅተን መብታችንን ከመጠየቅ የያዘን ነገሬ ጥልቅ የሆነ ሌላን ሰው የሚጠራጠር የወል ሰብዕናችን ነው።

ሥልጣን ካለው ኃይለኛ አካልና ከባለጊዜ ጋር ጫን አድርጎ አፍ መከፋፈት ለቅስፈት ይያርጋል የሚለው ዘመን ያፈጀ የፍርሃት ባህርያችን ነው። እጅግ ጥልቅ መሠረት ያለውና ከዘር ማንዘር የወረደ የአድርባይነት በሽታችን (ባህላችንም) ነው።

የራሳችንን መብት ለመጠየቅ መፍራት ብቻ አይደለም! ሌላውም ከኛ በአቅም ያነሰ ነው የምንለውን ሰውም መብቱን እንዲጠይቀን፣ አሊያም ተቃውሞውን እንዲተነፍስ አንፈቅድለትም።

በድሮ ዘመን ባርያና አሽከር፣ ወይ ጢሰኛ፣ ወይ የቤት ሠራተኛ፣ ወይም የበታች ሠራተኛ መብቴ ነው የሚለውን ወይም ቅር ያለውንና እንዲስተካከልለት የሚሻውን ነገር ከጠየቀን፣ እኛ ኢትዮጵያውያን በመጀመሪያ የሚመጣልን ሃሳብ፣ ጥጋብ ይዞት ነው የሚል ነው።

ተረቶቻችን፣ ምሣሌዎቻችን እና ስነልቦናችን ሁሉ ጥጋበኛን ያወግዛል። የመብት ጥያቄ ሁሉ ከትዕቢት የመነጨ፣ ከመታበይ የመጣ ይመስለናል። ጥጋቡን ሳላስተነፍስለት የቀረሁ እንደሆነ እኔን አያርገኝ እየተባለ ይዛታል! እውር ቢሸፍት እስከ ጓሮ ነው እየተባለ ይዘበታል።

በቅሎ ገመዷን በጠሰች በራሷ አሳጠረች እየተባለ ይሰለቃል። ይቺ ባቄላ ያደረች እንደሆን አትቆረጠምም ይባላል። ለአኩራፊ ቁርሱ ራቱ ይሆናል ይባልለታል።

አጓጉል የረዘመች የማሽላ ዛፍ፣ አንድም ለወፍ አሊያም ለወንጭፍ - እየተባለ ከሰው ተነጥሎ አጉል መንጠራራት ለመቀሰፍ እንደሚዳርግ ይሰበካል። አጉል መንፈራገጥ ለመላላጥ ይባላል፣ ቆማ* ሲጠግብ በትሩን ይወረውራል እየተባለ "ጥጋቡ" መሣለቂያ ይደረጋል።

ንጉሥ አይከሰስ፣ ሠማይ አይታረስ እንላለን። ወንዝ ቁልቁል እንጂ ሽቅብ አይፈስም እንላለን። ወደላይ አንጋጠህ ለበላዮችህ ምን ማድረግ እንዳለባቸው መንገር ድፍረት ነው። ብልግና ነው። ጥጋብ ነው።

እና ዝምታ ወርቅ መሆኑን እንሰበካለን። ዝም ባለ አፍ ዝንብ የማይገባ መሆኑን እንማራለን። በአፍ ይጠፉ በለፈለፉ እየተባለ ይተረታል። ሰው ያመነበትን አውጥቶ እንዳይናገር የሚያሠለጥን የዝጎች ባህል ነው ያለን። መከበር በከንፈር መሆኑን እናምናለን። ኢፍትሃዊነትን ከመጋፈጥ ይልቅ በአድርባይነት የምናገኛት ሽልማት ትናፍቀናለች!

በእነዚህ ከዘር ማንዘር ከወረስናቸው የፖለቲካ ውርዴዎች ይባብሎ ደግሞ፣ በኢትዮጵያችን የመንግሥትነት ሥልጣንን የያዙ ገዢዎች ሁሉ ደግሞ - እስካሁንም ድረስ -  በሥልጣናቸው ላይ ጥያቄ ያነሳባቸውን ማናቸውንም አካል የሚያስተናግዱት - እጅግ አስከፊውን ቅጣት በማከናነብ ነው!

ደፍሮ ሥልጣንን የተቃወመን ሰው ወይም የሰዎች ስብስብ፣ አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶ ሌሎች እንዳይነሱ መቀጣጫ ማድረግ ነው ለዘመናት የኖረና ያልለቀቀን ባህላችን። የተቃወመ ሰው የሚቀጣው የራሱን ፋንታ ብቻ አይደለም፣ የሌሎችንም ድርሻ ነው! ሌሎች እሱን አይተው አደብ ገዝተው መቀመጥ አለባቸው።

አፄ ዮሐንስ ያመፁባቸውን ወሎዬዎችና ጎጃሜዎች ወርረው፣ ጨፍጭፈው፣ ዘርፈው፣ አልበቃ ብሏቸው የየሰዉን እጅ ቆራርጠው ይመለሱ ነበር።

አፀ ቴዎድሮስ ሸዋ፣ ጎጃም፣ ወሎ፣ ራሱ ጎንደር ላይ ዘምተው ዘርፈው፣ አቃጥለው፣ ገድለው አላረካ ሲላቸው የሰውን እጅ ሁሉ ቆርጠው ጥለው ይመለሱ ነበረ።

ጎንደር ከተማዋ ሙሉዋን በታሪኳ ሶስት አራት ጊዜ ስትቃጠል፣ አንዴ ዮዲት ጉዲት፣ ግራኝ አህመድ፣ ደርቡሽ፣ እያለ በመጨረሻ ራሳቸው አፄ ቴዎድሮስ ናቸው ሌላ ቦታ ዘምቼ ስመለስ ከድታችሁ ጠበቃችሁኝ ብለው ከተማዋን ያቃጠሏት። ሌላ ቀርቶ እሳቸውን ለመቀበል አበባ ይዘው የወጡ ሴቶች አልቀሯቸውም!

በሃገራችን ሥልጣንን በተቃወሙ ላይ ከሠማይ የአውሮፕላን ጥቃት ማዝነብ የጀመሩት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ናቸው! ደርግ ቀጠለበት! ኢህአዴግ በሄሊኮፕተሮች ያጭድ ነበር ሶማሌ ድረስ ሄዶ።

ይሄኛው የብልፅግናው መንግሥትም በሥልጣኑ ላይ የተነሱበትን የገዛ ወገኖቹን በድሮንና ሔሊኮፕተር ያጭዳል! የዘር ውርስ ነው። የማይለቅ ውርዴያችን ነው የተቃወሙንን ያለምህረት መቅጣት!

ይህ ነገር የሚጀምረው በቤት ውስጥ ከህፃናት አስተዳደግ ጀምሮ ነው! በእኛ ሀገር እስከቅርብ ጊዜ ህፃን ልጅ ከነስሙ አሽከር ነው። ጩሎ ነው። ከቁምነገር የማይጣፍ ነው። እንዲከበር የሆነ ነገር ይዞ ወይ ሠርቶ ማሳየት አለበት። ...

አለበለዚያ በሌላ ሰው ቁጥጥር ስር ነው። የሚቸረው እንጂ የሚጠይቀው መብት የለውም። አለዚያ አይቀጡ ቅጣት ይጠብቀዋል። ሰጥ ለጥ ብሎ ለauthority መገዛትን የምንለማመደው በህፃንነታችን ነው። የታዛዥነት ዓመል የሚያሸልምበት፣ ማጉረምረም የሚያስኮረኩምበት አስተዳደግ ነው ያለን!

ልጅ ፊቱን አይበርደውም፣ ደሃ ሕዝብም አይርበውም! አሽከር መረገጥ አይቆረቁረውም! የምንኖረው በአገዛዞች መልካም ፈቃድ ነው እንጂ፣ እኛ የተገባን ባለመብቶች ሆነን አይደለም!...

እነዚህንና እነዚህን የመሠሉ ሥር የሰደዱ አስተሳሰቦቻችን ናቸው፣ ቢያንስ ያለፈውን በዓለም ሁሉ ንቃት ያላቸው ሕዝቦች በምድራቸው ማንበር የቻሉትን የመናገር፣ የመቃወም፣ የመፃፍ፣ የመሰብሰብ፣ ሠላማዊ ተቃውሞ የማድረግና ለፖለቲካ ወይም ለሥልጣን መያዝ ዓላማ ተሰባስቦ የመደራጀት መብታችንን ማስከበር እንዳንችል ቀፍድደው የያዙን።

በእነዚህ ሁሉ ላይ ደግሞ፣ ህዝቡ ራሱን censor እንዲያደርግ፣ ጥላውን እንኳ እንዳያምን፣ እርስበርሱ እንዳይተማመን የሚያደርጉ የመንግሥት የምሥጢር ወሬ አቀባዮችና ሠላዮች ደግሞ ተመድበውበታል።

ዛሬ አፍህን ከፍተህ በማግሥቱ የለህም! ሃሳቡን ሊያወያይህ የቀረበህ፣ ተናግሮ አናጋሪ ነው። ማንንም አታምንም። ስለሆነም ግፋ ቢል በዘመድ አዝማድና በቅርብ ቤተሰብ ትደራጃለህ።

ለዚህም ነው ባገራችን በ1900ዎቹ የታዩ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች በአብዛኛው በአንድ ቤተሰብ አባላት፣ በአንድ ወገን፣ በአንድ ብሔር፣ በአንድ ካዴት ሁሉ ሊሆኑ የበቁት። ማንም ስለማይታመንም፣ ባልንጀራ በየወንዙ ይማማላል። ሲጀመር እንጂ ሲጨረስ የሚታይ ህብረት የለም!
እጅግ ተጠራጣሪዎች፣ አማኝ የምንመስል እጅግ ኢ-አማኞች፣ አስመሳዮችም ሆነናል። እኛ ኢትዮጵያውያን በአገዛዞች ጭካኔና ያንን አሜን ብሎ በሚቀበለው ባህላችን የተነሳ በጊዜ ሃ ሂደት አውቀንም ይሁን ሳናውቀው፣ የእስስትነት ባህርይን ተላብሰናል።

በመልታይፖላር ፐርሰናሊቲ ዲስኦርደር የተጠቃ ትውልድ ታቅፈን ነው የቀረነው። ኢትዮጵያዊ በቤተክርስትያንና መስጊድ ሌላ ሰው ነው። በሥራ ቦታ ሌላ። በአደባባይ ሌላ። በጓዳ ሌላ። ብቻውን ሌላ። ከወዳጆቹ ጋር ሌላ። ከትዳር አጋሩ ጋር ሌላ። ...

በኛ ማኅበረሰብ አንድ ሰው አንድ ብቻ አይደለም። የማይጨበጥና እርስበርሱ የሚቃረን ብዙ ሰው ነው! ከአንበሣነት ወደ እስስትነት ራሳችንን በአዝጋሚ ለውጥ የቀየርን ሕዝቦች ነን ቢባል ማጋነን አይሆንም።

ይህ ሁሉ የእኛ ኢትዮጵያውያን የወል መለያ ባህርይ፣ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ለወጡ አፈሙዝ ለጨበጡ ኃይሎች ሁሉ፣ አመቺ ሆኖላቸዋል።

ለመጋለብ ያመቸ፣ ለመግዛት የተመቸ፣ ለመረገጥ የተዘጋጀ፣ ለመገረፍ ጀርባውን፣ ለመጫን ጫንቃውን ያደነደነ ህዝብ መሆኑን አገዛዞቹ አሳምረው ያውቃሉ። ጥቂቱን ጥቅም እያንጠባጠቡ፣ ሌላውን ጅራፍ እያወዛወዙ ይገዙታል።

ህዝቡም አንድ ገዢ አካል የመጨረሻ የማማረር ደረጃ ላይ ደርሶ ሆ ብሎ ካልተነሳ በቀር ይህ የመረገጥ እውነት፣ የአገዛዞች ሀሉ ባህርይ ነው ብሎ ተቀብሎታል።

የሐመር ሚስት ለአዲሷ ሚስት ባሏ የገረፋትን የጀርባዋን ጠባሳ እያሳየች፣ ባሌ ከአንቺ ይልቅ እኔን ነው የበለጠ የሚወደኝ እንደምትላት የመሠለ ነው!

ሚስቱን የሚማታው ቅናተኛ ባል ሚስቱን የሚወድ ነው! ይወደዳልም! መረገጥ ባህል ሲሆን በሁሉም የህይወት ዘርፍ ይንፀባረቃል!

ይህ ሁሉ አልበቃ ብሎ ደግሞ፣ በ20ኛው ክፍለዘመን በሀገራችን ሥልጣን ላይ የወጡ መንግሥቶች ራሳቸውን በህግ ሀገሩን ወደሚያስገብር አምባገነንነት ቀይረውታል።

ህጎች ሁሉ በሲስተም ዲዛይን የሚደረጉት የዜጎችን መብት ለመጠበቅ ሳይሆን፣ በይስሙላ የተረጋገጡ መብቶችን በሌላ ስልታዊ መንገድ ከዜጎች ላይ መቀማት የሚቻልበትን ሥርዓት በመዘርጋት ነው።

ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሁለት ጊዜ ህገመንግሥት አሻሽለዋል። ሶስተኛው ጅምር ረቂቅ ሆኖ ቀርቷል፣ በለውጡ ተቀድሞ ቀረ። በእነዚህ ሁሉ ውስጥ አንድም ጊዜ፣ ዜጎች ለፖለቲካ ዓላማ ተሰባስበው የፖለቲካ ፓርቲ የመመሥረትና በረላማዊ መንገድ የመንቀሳቀስ መብት አላቸው የሚል አንዲት ሰባራ አንቀፅ አልደነገጉም!

የሕዝብን መብት አስከብራለሁ ብሎ የመጣው የደርጉ ወታደራዊ መንግሥት፣ ለጊዜው በለውጡ ሰሞን አቅሙን እስኪያደራጅ በዝምታ ይመለከታቸው የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሁሉ በሚዘገንን አብዮታዊ በትር አንድ በአንድ ድራሻቸውን አጥፍቶታል።

በቀኃሥና በደርግ (በኢህዲሪ) ዘመን ለስሙም ቢሆን በኢትዮጵያችን በህገመንግሥት ለስሙ እንኳን የተረጋገጠው የዜጎች የመደራጀት መብት ለኢኮኖሚ ዓላማ ብቻ እስከሆነ ድረስ ነበር።

የሙያ ማኅበራትን (trade unionsን) መመሥረት ብቻ ለዜጎች ተፈቅዶ፣ ለፖለቲካ ዓላማ መደራጀት ግን ለገዢ መንግሥት ብቻ የተፈቀደ ነበር።

ንጉሡም በሞናርክ ርዕዮት ተመራሁ በማለት፣ ንጉሡን ገረሰስን ያሉትም አብዮተኞች በማርክሲዝም ተመራን በማለት - ሁለቱም የሕዝብን የተደራጀ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማፈን ቆርጠው የተነሱ በህግ የሚያስገብሩ አምባገነኖች ነበሩ!

ይሄ ታሪካችን ይገርማል! ምክንያቱም በጠባይና በርዕዮተዓለም፣ በሕዝባዊ መሠረትና በአባሎቻቸው ዓይነች ፍፁም የሚለያዩ አገዛዞች፣ ነገር ግን የሕዝብን የፖለቲካ ተቃውሞ በማፈን ላይ አንድ ሆነው መገኘታቸው ይገርማል። የኛን የኢትዮጵያውያንን የረግጠህ-ግዛው ውርዴ በዘመን ለውጥ አለመፈወስ የሚያረጋግጥም ነው!

በኢትዮጵያ 3ሺህ ዓመት የሀገረመንግሥት ታሪክ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያችን፣ ለይስሙላም ቢሆን ለፖለቲካ ዓላማ ተሰባስቦ ማኅበር የመመሥረትን፣ በሠላማዊ መንገድ የፖለቲካ ፓርቲ መሥርቶ የመንቀሳቀስን የዜጎች መብት በመጀመሪያ በሽግግር ወቅት ቻርተር፣ ቀጥሎም በህገመንግሥት ያሰፈረው የወያኔ-ኢህአዴግ መንግሥት ነው!

ለዚህ ታሪካዊ ተግባሩ ሊመሠገን ቢገባውም፣ በተግባር ግን ሥጋውን ሰጥቶ ቢላዋውን የመንሣት የተለመደ ጨዋታውን ይጫወት የነበረ አገዛዝ ነው። ከሌሎቹ ብዙም የተለየ የሚመሠገን ባህርይ አልነበረውም።

የመግዣ ሥልቱን አራቀቀው፣ እና ትያትራዊነቱን ጨመረው እንጂ፣ የዜጎችን የልዩነት የፖለቲካ ሃሳብን የመግለፅ መብት በህጎቹም ሎነ፣ በአፈና ተቋሞቹ በተግባር ሲጨፈልቅ የኖረ - እናም ለምሥጋና የማይመች - አምባገነን መንግሥት ሆኖ አልፏል! (አልፏል ስንል አርፏል እንዳይመስል፣ ስሙንና መልኩን ቀይሮ አሁንም አለ!)

ፅሑፌን ስደመድም፣ የአትዮጵያ ሕዝብ የመብት ጥያቄውን በተደራጀ መልክ እንዳያቀርብ፣ በመብት ጥያቄው እንዳይገፋበት፣  ዋናው አስሮ ያስቀመጠው ነገር፣ ባጠቃላይ፣ በመሠረታዊነት፣ ከሌላ የውጭ አካል የሚመጣ ነገር ሳይሆን፣ ሕዝቡ ራሱ ለመገዛት የተመቸ ሕዝብ ስለሆነ ነው!

የመንግሥቶቹ አፋኝነት በሁለተኛ ደረጃ የሚመጣ ጉዳይ ነው። አመቺ ለም መሬት ያገኘ ዘር በቀላሉ ይበቅላል። አመቺ ተገዢ ህዝብ ያገኘ መንግሥትም፣ በቀላሉ የተቃወሙትን የመውጊያ ቀንድ ያበቅላል።

በዚያም ላይ ገዢ ሆነው የሚመጡትም ከጃፓን ወይ ከፓፓዋ ጊኒ የመጡ ሰዎች አይደሉም። ከኛው መሐል የወጡ፣ በአስተሳሰብም፣ በስነልቦናም፣ በባህርይም እኛኑ የመሠሉ ሰዎች ናቸው! ገዢነትንና ተገዢነትን የሣሉበት መንገድ ከሌሎቻችን የተለየ አይደለም። ሥልጣን ላይ ሲወጡም የሚያሳዩት ባህርይ ያንኑ እኛ ውስጥ ያለውን ቢሆን የሚገርም ነገር የለውም!

ለማንኛውም ይህን ለዘመናት የተጣባንን የተገዢነት ስነልቦና በምንድነው መስበር የምንችለው? ምን ብናደርግ ከአፈና ቀንበር መውጣት እንችላለን? የሚለው ላይ መነጋገር፣ መወያየት፣ ራሳችንን መፈተሽና መቀበል፣ ....

ራሳችንን ለመለወጥ የግልና የጋራ እንቅስቃሴዎችን መጀመር፣ በህግ የታሠረ መንግሥትን ለመፍጠር መታገል፣ እኛ ባይኖረኅ ልጆቻችን ዘመናዊ ዕውቀት እንዲኖራቸው የቻልነውን ሁሉ መጣር... ለነገዬ የሚባሉ የቤትሥራዎች አይመስሉኝም!

ሕዝቡን የሚያስፈራራ ሳይሆን፣ ሕዝቡን የሚፈራ መንግሥት ለማምጣት የተገዢነት ቀንበራችንን ሰብረን ለመብቶቻችን በጋራ መነሳት ብንችል፣ ከዘር የወረደ የፖለቲካ ውርዴያችን ቢያንስ በኛ ላይ ማብቃት ይችላል!

በነገራችን ላይ፣ እኛ ነፃ ነን የምንለው ኢትዮጵያውያን ለአገዛዞች የመገዛት ስነልቦናችን፣ ከተቀሩት በቅኝግዛት ባርነት ሥር ከማቀቁት ሌሎች ሕዝቦች የተለየ አይደለም! እጅጉን ይመሳሰላል ብቻ ሳይሆን፣ almost አንድ ዓይነት symptoms ናቸው ያሉብን!

ታዲያ ብዙዎች ከቅኝተገዢነት ነፃ ከወጡ እኛም ከአፋኝ አገዛዞች የመብት አፈና ነፃ መውጣት እንችላለን ማለት ይመስለኛል።

በርግጥ ከቅኝገዢዎች መላቀቅ ቀላል ነው። ከቅኝተገዢነት አስተሳሰብ መላቀቅ ነው ከባድ ሆኖ የተገኘው። ብዙዎች ዛሬ ነፃ ወጥተው፣ ግን አሁንም ነፃ አልወጡም። አሁንም ሥሪታቸው የተቀረፀው ከተገዢነት ቁስ ውስጥ ነው።  እስካሁን ነፃ ወጣን የሚሉት ጨርሰው በመንፈስ ነፃ መውጣት ፈተና ሆኖባቸዋል!

እኛ ኢትዮጵያውያን ሙሉ መብት የተጎናፀፍን ዜጎች እንዳንሆን ጠፍሮ የያዘንን፣ የአካልም የመንፈስም እሥራት በጣጥሰን፣ እስስትነታችንን አውልቀን፣ ሙሉ ሰው፣ ሙሉ ዜጋ፣ ሙሉ አትዮጵያዊ፣ ሙሉ ጌቶች የምንሆንበትን ዘመን እናፍቃለሁ!

ተነሣ፣ ተራመድ፣ ክንድህን አበርታ!

ሰናይ ጊዜ!!

@zephilosophy
"ሥልጣን ያባልጋል፤ እውነት ነው፤ ፍጹማዊ ሥልጣን ደግሞ የባለጌ ባለጌ እንደሚያደርግ የሮማ ካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጎርጎሪያ ሶስተኛ የተናገሩት ሀሳብ ግሩም ምስክር ይሆናል᎓᎓ ነገር ግን፣ ይህም ታውቆ እንኳን ዛሬም እንደ ትላንቱ ሥልጣን የአያሌዎችን ልብ እያጓጓች፤ ልክፍት በሚመስል አስፈሪ ፍቅሯ እንደማግኔት ትስባቸዋለች:: ድሮም ሆነ ዘንድሮ የመንበር ጥማት ያው የመንበር ጥማት ነው፤ ከብዙዎች ልብ ተፍቆ አልወጣም:: ሥልጣን፣ ቢሰሩባትም ባይሰሩባትም እርካቧን የረገጠ፣ ኮርቻውን የተቆናጠጠ፣ መንበሯ ላይ የተደላደለ ሁሉ (ቢያንስ አብዛኛው) በሞቱ እንጂ በፈቃዱ ሊለያት የማይሻ ጦሰኛ ፍቅሯ ተቀፍድዶ ይኖራል፡፡ አፍቃሪዋም ዘመኑን ሁሉ ሲጨነቅና ሲጠበብ ዕድሜውን የሚገብርላት፣ የክብሩ ዘውድ፣ ወይም የመራራ ውርደቱ ፅዋ ትሆናለች።"

(ዲራአዝ፤ እርካብና መንበር)

@zephilosophy
እመ መከራ

ኢትዮጵያ እመ መከራ
የግዜር መመራመሪያው
የስቃይ ቤተ-ሙከራ
መውደቅማ ነበር ያባት
እንደ ያሬድ እስከ ሰባት
እንደ በላ ብላቴና
የእንክርዳድ ሙልሙል እንጎቻ
የትውልዴ እጣ ፋንታ
መውድቅ፥ መውድቅ፥ መውድቅ ብቻ!

በእውቀቱ ስዩም
📚የማለዳ ድባብ

@zephilosophy
ከምነቴ ጋር ቀረሁ

አውቃለሁ!
አታምኝም በማምነው
ያንደኛው ሰው መንገድ፣ ለሌላው ገደል ነው።
ቢቀና ጎዳናው፣ ቢወለወል አስፋልት
አብሮ ከማያልም፣ አብሮ መሄድ ልፋት
ያንደኛው ሰው እግር፣ ለሌላው እንቅፋት።

ባልጮህ ባደባባይ
ምኩራብ ባልገነባ፣ መዝሙር ባላሰማ
ከጥላየ በቀር፣ ባይኖረኝ ተከታይ
በቃል ወይ በዜማ
ተገልጦ ባይታይ
በልብ ተጠንስሶ፣ ባይን የሚገነፍል
እኔም እምነት አለኝ፣ ዋጋ የሚያስከፍል።

እምነት - ተስፋ - ፍቅር
መች ባንድ ላይ ሁኖ
ለሰው ልጅ ይሰጣል
በምነቱ የፀና፣ ድንገት ፍቅሩን ያጣል
ፍቅርሽን ሸኝቼው፣ ተስፋየን አባረርሁ
ከምነቴ ጋር ቀረሁ፡፡

በእውቀቱ ስዩም
📚አዳምኤል

@zephilosophy
Audio
የአለማችን ታላቁ ተጓዥ
ኢብን ባጡጣ
አዘጋጅ- ግሩም ተበጀ
ከሞሮኮ-ቱርክ
ክፍል-1
@zephilosophy
የማያኬቬሊ የተመረጡ አባባሎች

1.የአንድን መሪ ወይም ገዢ ብቃትና ችሎታ ለመገመት የመጀመሪያው መላ በዙሪያው ያሉ ሰዎችን መመልከት ነው።

2.አብዛኛው ሰው የሚያየው አለባበስህን ነው፡፡ ጥቂቶች ግን ትክክለኛ ማንነትህን ለማየት ልምድ አካብተዋል፡፡

3.ማዕረግ አይደለም ሰውን የሚያስከብረው፡፡ ሰው ነው ማዕረግን ማክበር ያለበት፡፡

4.የትኛውም ታላቅ ውጤት ያለምንም አደጋ ወይም ችግር ተሠርቶ አያውቅም፡፡

5.ከፍተኛ ፍላጎትና ፈቃደኝነት ባለበት ቦታ ሁሉ ችግሮች ትላልቅ መሆን አይችሉም።

6.ነፍስን ማንቀሳቀስ የሚችል ኃይል የሌለው ትንሽ እቅድ አታቅድ።

7.ሰዎች በሁለት መሠረታዊ ግፊቶች ይናጣሉ፡፡ ወይ በፍቅር አልያም በፍርሃት፡፡

8.ሰው መፈራትንም ሆነ መፈቀርን ሁለቱንም ማሳካት ካልቻለ መፈራት ከመፈቀር ይልቅ የተሻለ ስለሆነ እሱን ይምረጡ።

9.ይቅርታ የሚወጣው ደግነት ከተሞላው ነፍስ ነው፡፡

10.ሰዎች ምንም ዓይነት እርምጃ ለመውሰድ ከመወሰናቸው በፊት የሚጠብቃቸውን ፈተና እና አደጋ መመርመር አለባቸው ።ውሳኔያቸው ከመጀመሪያ ፍላጎታቸው ጋር የሚጣጣም ቢሆንም እንኳ ጉዳቱ ከጠቀሜታው ከበለጠ ሊተዉት ይገባል፡፡

@zephilosophy
አስተዋይ መሪ ኋላ በአጠቃላይ ሕዝቡን ወይም ሀገሩን ሁሉ አጣብቂኝ ውስጥ ሊከትቱ የሚችሉ መዘዞችን ሁልጊዜ ገና ከመነሻቸው አሽትቶ ማወቅ የሚችል ነው። ይህ መዘዞችን አስቀድሞ የማስተዋል ጸጋ የሌለው መሪ ለመሪነት የተሰጠ ሰው አይደለም። መሪው ይህ ጸጋ ኖረውም አልኖረውም ግን ሁልጊዜም ቢሆን ራሱን ልምድ ባላቸው ሙሁራኖችና አማካሪዎች መክበብ አለበት። ትክክለኛ መሪ የሁሉንም የካበተ ልምድ ያላቸው አዋቂዎች ምክርና አስተያየትን የሚጠይቅ፥ ነገር ግን ለማንም ሳይገዛ የራሱን የመጨረሻ ውሳኔ ማሳለፍ የሚችል የገዛ ራሱ ቆፍጣና ጌታ ሆኖ መገኘት አለበት፡፡

ኒኮሎ ማኪያቬሊ
@zephilosophy
በወንዶች አለም ውስጥ አንዲት ሴት

ዓለማየሁ ገላጋይ “መለያየት ሞት ነው”
በሚለው መፅሀፉ እንዲህ ይለናል

 "የአዲስ አበባ ወንድ የመልበሻ ቤት መስተዋት ሆኗል፡፡ ሴቶቹ በሱ ፊት ላይ አለባበሳቸውን ያያሉ፤ የአዲስ አበባ መንገዶች፣ ካፌዎች፣ ባሮች፣ ቢሮዎች፣ ሆቴሎች፣ የፀሎት ቤቶች … አለባበስ ማሳያ መድረኮች ሆነዋል፡፡
ወንዱ የጥሞና ጊዜ ተነፍጓል፡፡ ሲበላ፣ ሲጠጣ፣ ሲሰራ፣ ሲፀልይ፣ ታክሲ ሲጠብቅ … በሞዴሎች ተከቦ ነው፡፡ ህይወቱ የናይት ክለብ ውስጥ እስረኛ ሆናለች፡፡ ሲወለድ ሳውና ባዝ የገባ ሲሞት ይወጣል፡፡ ኑሮው በላብ መጠመቂያ ስፍራው ሆናለች፡፡ አይኑ ሸሽቶ የትም አይደርስም፡፡ እድሜ ልኩን መስክ መካከል እንደቆመ ሁሉ በአበባ ተሰላችቷል፡፡ …ትቢያ… ናፍቆታል፡፡
ሴቶች፤ የወንዶች አገልግሎት አቅራቢ ድርጅት ሆነዋል፡፡ አይኑን ያገለግላሉ፣ ልቡን ያገለግላሉ፣ ስሜቱን ያገለግላሉ … የሴቶች የመጨረሻ አማራጭ … የወንዶች ገበያ .. እንደሚፈልገው ሆኖ መገኘት ነው። ህይወታቸው በወንዶች ህልም የተፈበረከ ነው፡፡ ከሰው የሚጠበቀው ከዘንድሮ ሴቶች አይገኝም፡፡ ወንድ የሚፈልገውን ግን አያጣም። አይኑ፣ ጆሮው፣ አፍንጫው፣ ምላሱ … በሴቶች ትጋት ሥር ተጠምዶ ተደናቅፏል፡፡ አንዲት ሴት ከአንዲት አበባ ጋር በንፅፅር ቆማለች፡፡ የወንድ ቀልብ እንደ ንብ ሲጠመድላት ከማየት ውጭ ሌላ ህልም የላትም፡፡
እንግሊዛዊው ደራሲ ዲ.ኤች ላውረንስ ይሄንን ታዝቦ አንዲት የመረረች መጣጥፍ አቅርቦ ነበር፡፡ “Give her a pattern” ይላል ርእሱ “The real trouble about women is that they must always go on trying to adapt themselves to men’s theories of women, as they always have done.” ብሏል፡፡ (የሴቶች ዋነኛ ችግር ወንዶች ስለሴቶች የሚኖራቸውን ፅንሰ ሃሳብ አሟልተው ለመገኘት ሁልጊዜም መጣራቸው ነው)
የዘንድሮ ሴቶች ሴት የመሆን መብት የላቸውም፤ ወንድ የሚፈልገው አይነት ሴት እንጂ፡፡ ሴቶች የወንዶችን ህልም ለመተርጎም ህይወታቸውን የሚሰዉ ጭዳዎች ናቸው። በመሰልጠን ስም እራሳቸውን ለፆታ ባርነት አጋልጠዋል፡፡ ኧረ እንዳውም ከባርነት ወርደው ለአሻንጉሊትነት ተዳርገዋል፡፡ ሁኔታውን “Living Doll” ይለዋል Cliff Richard የተባለ አቀንቀቃኝ፡፡ … ህያው አሻንጉሊት … እንደማለት ነው፡፡ “I got myself a sleeping, walking, crying, talking Doll” (እራሴን የምትተኛ፣ የምትሄድ፣ የምታለቅስ፣ የምታወራ አሻንጉሊት ሆኜ አገኘሁት) የዘንድሮ ሴቶች ሰው መሆናቸው የሚረጋገጠው ስለሚተኙ፣ ስለሚሄዱ፣ ስለሚያለቅሱና ስለሚያወሩ ብቻ ነው፡፡ እንደ አበባ … ንብ.. መጥራት የህይወት ትርጉማቸው ሆኗል፡፡  "

@Zephilosophy
የመጀመሪያዋ ሴት "ሊልዝ"

የሔዋንን የሴት ቀዳሚነትነትን የማይቀበሉ ግለሰቦች ሊልዝ የሚልን ስም ሲያነሱ ይሰማል፡፡ ሊልዝ ከሔዋን በፊት የተፈጠረች ሴት ስትሆን፤ የአዳም የመጀመሪያዋ ሚስት ናትም ይሏታል፡፡ ሊልዝ ከሔዋን መቅደሟን በተመለከተ ከሚቀርቡት መከራከርያዎች መካከል ከመጽሐፍ ቅዱስ አንፃር የሚነሳውን ለማንሳት ያህል፡ አንደኛው በዘፍጥረት መጽሐፍ 1፡27 ላይ የተቀመጠውን ትረካ የሚመለከት ነው፤ ይህ ክፍል ፈጣሪ ወንድ እና ሴትን በአንድ ጊዜ እንደፈጠረ የሚናገር ሲሆን በዚህ ክፍል ላይ ከአዳም ጋር በተመሳሳይ ጊዜ የተፈጠረቸዋ ሴት ሔዋን ሳትሆን ሊልዝ ናት የሚል ድምዳሜ ይነሳል፡፡ ሌላኛው የኢሳያስ መጽሐፍ 34፡14” ነው፤ በዚህ ላይም የተገለጸቹ ሊልዝ መሆኗ አከራካሪ ኢይደለም ይሉናል የሔዋን ቀዳሚት ሴትነትን የማይቀበሉት፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ ባሻገር “Talmud”፣ “Kabbalah” እና “Alphabet of Ben Sira" ተብለው በሚጠሩ የሂብሪው መጽሐፍት ላይ ሊልዝ ስሟ በግልጽ ሰፍሮ ይገኛል፡፡እነዚህ መፅሀፎች የአዳም የመጀመሪያ ሚስት ሊሊዝ እንደሆነች፣ ኾኖም ከአዳም ጋር እኩል ነን አይደለንም በሚል ጭቅጭቅ ምክንያት እንደተለየችው ይተረካሉ፡፡

ሊልዝ ከገነት ከወጣች በኃላ የክፉ መናፍስት እናት በመሆን በሌሊት ህጻናት ገዳይ እና የሴሰኝነት ምንጭ ተደርጋ በአይሁዶች ዘንድ ዛሬም ድረስ ትወሰዳለች፡፡ በሌላ በኩል ስለ ሴቶች መብት እና እኩልነት አጥበቀው የሚከራከሩን ፌሚኒስቶች ሊልዝን የነጻነት እና የእኩልነት ምልክት አድርገው ይወስዷታል፡፡ ለዚህ ማሳያ በእስራኤል በሴቶች መብት እና እኩልነት ላይ ያተኮረ “Lilith” የሚል መጽሔት እንደሚገኝ መጥቀስ ይችላል፡፡ እንዲሁም ፌሚኒስት የሆኑ ጸሓፍት በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ ያለው የሰው አፈጣጠር ትረካ ዳግም መከለስ አለበት በማለት የተለያዩ ድርሳናትን ጽፈዋል፡፡ አብዛኞቹ መጽሐፍት የመጀመሪያዎቹ ሰዎች አፈጣጠር ትረካ መምስል ያለበት የሚሉት፦
"በመጀመሪያ እግዚአብሔር አዳም እና ሊልዝን ከአፈር አበጃቸው፡፡ የሕይወት እስትንፋስንም በአፍንጫቸው ተነፈሰባቸው፡፡ ሁለቱም ከተመሳሳይ ነገር ተፈጥረዋልና እኩል እና አቻ ነበሩ፡፡ እኩልነታቸውን ያልወደደው አዳም ታዲያ ወደ ፈጣሪ ቀርቦ ቅሬታውን አቀረበ፡፡ ፈጣሪም አዳምን ሰምቶ ሊልዝ አዳም እንደፈለገው የበታቹ እንድትሆን፣ ካለዚያ ከገነት እንደምትወጣ ነገራት፡፡ ሊልዝም ከአዳም በታች ከምትሆን ይልቅ  ከገነት መውጣትን መረጠች:: ፈጣሪም ይህን ባየ ጊዜ ለአዳም ሌላ ሴት መፍጠርን ወሰነ፡፡ ከአዳም ግራ ጎንም ሔዋንን ፈጠረ "
የሚል መልክ ያለው ነው::

@Zephilosophy
በእቅፍሽ ውስጥ ያለው ሰላም

በደጃፌ
ያዱኛ ጅረት ይፈስሳል
ሲዘረጋ መዳፌ
አልማዝ እፍሶ ያመለሳል።

ድህነትን አልቀድስም፤ ሀብታም መሆን አልጠላም
ግና ገንዘብ ኪስን እንጂ፣ የልብን ከፍተት አይሞላም
ከሁሉም ግን የሚልቀው፣ እቅፍሽ ውስጥ ያለው ሰላም።

በጉልምስና ዘመኔ፣ ወደ ልጅነት ተዛውሬ
የወይን ፅዋን ወርውሬ
እልፍ ጡቶችን ብጠባ
ካንዲት ሽንቁር ተመዝዤ፣ ሌላይቱ ውስጥ ብገባ
ብለዋውጥ ማህደር
ብቀያይር ሰገባ
ምን አገኘሁ? ምን አተረፍሁ? ምን ፈየድኩኝ? ምኔ ረባ?

ሥጋ በሥጋ ቢሞረድ፣ የደነዘ ነፍስ አይሰላም
ከሁሉም ግን የሚልቀው፣ እቅፍሽ ውስጥ ያለው ሰላም።

በእውቀቱ ስዩም
📖አዳምኤል
@zephilosophy
Silence

ለመግባባት እኮ ቃላት በቂ አይደሉም፡፡ ቃላት ይናገራሉ፤ ግን የሚናገሩት በከፊል ነው፡፡ ፀጥታ ግን በምልዓት ያግባባል፡፡እናም ቃላትን መጠቀም አደገኛ ጨዋታም ጭምር ነው፡፡ ምክንያቱም ትርጉሙ ከእኔ ጋር ሐሳብ ሊቃረንም የመቻሉ ነገር ሰፊ ነው፡፡ ቃሉ ብቻ ነው ከእናንተ ዘንድ የሚደርሰው፤ እናንተም የራሳችሁን ትርጓሜ፣ የራሳችሁን ቀለም ትሰጡታላችሁ፡፡ ለማለት የተፈለገውን ተመሳሳይ እውነትን አይዝም፡፡ የሚይዘው ሌላ ነገርን ነው፡፡ ቃሉ እናንተ ጋር ሲደርስ አንድ ከእውነተኛው ትርጓሜው በራቀ ሁኔታ ዝቅተኛ የሆነን ሌላ አንድምታ አንደማይዝ በምን እርግጠኛ መሆን ይቻላል፡፡ ቃሉ ሊይዝ የሚችለው የእናንተን ትርጉም እንጂ የእኔን ትልም አይደለም፡፡ ቋንቋን ማዛባት እኮ እጂግ ቀላል ነው፡፡ እንዲያውም ከባዱ ነገር ማዛባትን ማስወገድ ይመስለኛል፡፡
ፀጥታን ግን ማዛባት አትችሉም፡፡ ፀጥታን አንድም ትረዱታላችሁ አሊያም አትረዱትም፡፡ በቃ... ፀጥታን በተሳሳተ መንገድ መረዳት አትችሉም፡፡ ወሰኑ ፍፁም ነው፡፡ የዝንተዓለምን ያክል የራቀ.....
የትኛውም ሰው በቀን ውስጥ ቢያንስ የአንድ ሰዓት የጸጥታ ጊዜ ያሰፈልገዋል፡፡

ኦሾ

@zephilosophy
"የእውነት ጠቢብ ወደ ራሱ ጥበብ ቤት እንድትዘልቁ አይጠራችሁም ፤ ወደ ገዛ አዕምሮአችሁ ደጃፍ ይመሯችኋል እንጂ "
ካህሊል ጂብራን

በመቀጠልም አንድ መምህር ተናገረ፡- ‹‹ስለማስተማር ንገረን?››
አለውም::

እሱም አለ
‹‹ማንም ሰው ቢሆን ገና ድሮ በእውቀታችሁ መክፈቻ ንጋት ላይ በከፊል እያንቀላፋ ተጋድሞ ካለው በስተቀር ሌላ ምንም ነገር ሊገልጥላችሁ አይቻለውም...

‹‹በቤተመቅደሱ ጥላ ስር ከተከታዮቹ ጋር የሚንሽራሽረው መምህርም ከእምነቱ ጋር ከፍቅር ወጪ ጥበቡን ሊሰጣችሁ አይችልም፡፡ በእውነት ጠቢብ ከሆነም ወደ ራሱ ጥበብ ቤት እንድትዘልቁ አይጠራችሁም፡፡ ወደ ገዛ አዕምሯችሁ ደጃፍ ይመራችኋል እንጂ...

‹‹የክዋክብት ተመራማሪውም ስለ ህዋ ያለውን ግንዛቤ ይነግራችሁ ይሆናል፡፡ ግን ግንዛቤን ሊሰጣችሁ አይችልም...

‹‹ዘማሪውም በህዋ ላይ ያሉትን ዜማዎች ሁሉ ይዘምርላችሁ ይሆናል፤ ዜማውን ሊነግራችሁ ይችላል እንጂ ወደ እነዚያ ወሰኖች ሊያስኬዳችሁ አይችልም፡፡ የአንድ ሰው ዓይንስ ብርሃኖቹን ለሌላ ሰው ያሳልያልን

‹‹እናም ለየብቻ በእግዚአብሔር እውቀት ውስጥ እያንዳንዳችሁ እንደምትቆሙት ሁሉ ስለ እግዚአብሔር ባላችሁ እውቀትና ስለዓለም ባላችሁ ግንዛቤም ውስጥም ለየብቻችሁ መቆም ይገባችኋል፡፡››

@zephilosophy
የብልጥ ጀግና ትግል

እኔው በገዛ እጄ
የነብርን ቁጣ፣ የአናብስቱን ሞገስ
                       ለሀይልሽ አውሼ፤
ድልሽን አጣፈጥኩ ሽንፈቴን አርክሼ፡፡

ዘመኔን በሙሉ!
“በማረክሺኝ!” ፈሊጥ፣
“በተረታሁ!” ልማድ፣
“በሞትኩልሽ!” ተረት፤
ከገጽሽ ስዋጋ፣ ከገላሽ ስናረት᎓᎓
በአይንሽ ተወግቼ፣
በጥርስሽ ደምቼ፣
በከንፈርሽ ሞቼ፣
ይዘትሽን ባገዘፍኩ፣ ቅርጽሽን ባጎላሁ
                            በስሜት ፈርጄ፤
ድልሽን አገነንኩ ሽንፈቴን አክብጄ ፥

ግና!
የሁለትዮሽ መልኩ በአብሮነት ብራና፣
በአንዱ ቀለም ብቻ ደምቆ ይታይ ዘንድ
                                 አልተሳለምና፣
በአንዲት ፍትሃዊ ቀን፣
ሚዛናዊው ዳኛ ከውበት ቢያስታርቀን..

ያራቀኩት ቅርጽሽ፣
ያገዘፍኩት ምስልሽ፣
የቀባሁሽ ቀለም -በእውነታ ተፍቆ ፤
ሚዛንሽን አሳየኝ፣
አቅምሽን ነገረኝ – ልብሽ ከእጄ ወድቆ።

ደስ ሲል!!!
ልብሽን እጄ ላይ!
ጨፍልቄ ጨምቄ፣ አፍርጬ ጨልፌ፤
መቅኒዬን ከመቅኒሽ ለካሁ አንጠፍጥፌ፡፡

ዋውው!!!
ነፍሴ አሁን ገና ግዙፍ ሃቅ አዜመች፤
ለነገ መዝሙሯ አዲስ አዝማች ፃፈች፦

“ስንቱ የስሜት ሎሌ!
እንደዘበት ያልፋል -ለገጽ ተገዝቶ፣
                                 ሽፋን አገልግሎ፤
ብልህ ግን ይጥላል –ከተሰራው ሳይሆን
                                   ከስሪቱ ታግሎ!”

ወዳጄ!
በውድድር ሜዳ ማሸነፍ ስትቀምር፤
የትግልህን ጫፍ
ከውጤቱ ሣይሆን ከግብዓቱ ጀምር፡፡

ሃፊዝ
📖የመንፈስ ከፍታ

@zephilosophy
ባንዲት ቃል ይጫራል
በእውቀቱ ስዩም

ጉልቤው ባደባባይ፣ ድሃውን ሲበድል
ድምፅህን አጠብድል
ቃል፣ ሩምታ፣ ተኩስ
አውቆ የተዘጋ፣ ጆሮ የሚነድል
ባንዲት ቃል ይጫራል፣ ያንድ ዘመን ገድል፡፡

@zephilosophy
አንድ ዮጊ ባቡር ላይ ይሳፈራል፡፡ ሶስተኛ ደረጃ ባለው የባቡር ፉርጎ ውስጥም ተቀመጠ፡፡ ከዛም የያዘውን ሳጥን ጭንቅላቱ ላይ አስቀመጠ፡፡ ተንቀሳቃሽ አልጋውንና የመኝታ ልብሶቹን ደግሞ ሳጥኑ ላይ ደረበ፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ዣንጥላውን ደርቦ አስቀመጠ፡፡ በዚህ ግዜ አብረውት የነበሩት መንገደኞች፡- “ምን እያደረግክ ነው? ጓዝህን ወለሉ ላይ አስቀምጠህ ለምን በምቾት አትቀመጥም?” ሲሉ በመገረም ጠየቁት፡፡ ዮጊውም፡-

“የገዛሁት ቲኬት ለኔ ብቻ ነው! ባቡሩ ላይ ተጨማሪ ሸክም መጫን ሰናይ ምግባር እንዳልሆነ አስባለሁ፡፡ ስለዚህ ሸክሙን ጭንትላቴ ላይ መጫኑ ተገቢ ነው፡፡
ሲል መለሰላቸው፡፡

ሰዎቹም፡- “አብደሃል እንዴ? ጓዝህን ጭንቅላትህ ላይ ብትሸክመውም የክብደቱ ጫና የሚያርፈው እኮ ባቡሩ ላይ ነው፡፡ ታዲያ አላስፈላጊ ሸክም ጭንቅላትህ ላይ ለምን ትጭናላህ? ወለሉ ላይ አስቀምጠውና ፈታ ብለህ ተቀመጥ፡፡” አሉት፡፡

ከዛም ዮጊው፡-" ባቡሩ ውስጥ ያሉት ሰዎች አላዋቂዎች እንደሆኑ አስቤ ነበር። አሁን ግን ብልህ መሆናቸውን ተረድቻለሁ።” አለ። ሰዎቹ ግን የተናገረው እንዳልገባቸው ገለፁለት።

ከዛም ዮጊው፡- "በህይወት ውስጥ ብዙ ሰዎች ለአምላክ ሊተውት የሚገባቸውን ሽክም በጭንቅላታቸው ተሸክመው አይቻለሁ፡ ፡ እያንዳንዱ ሰው መላው አፅናፈ ሊሸከማቸው የሚችለውን የስጋትና የጭንቀት ተራሮች ጭንቅላቱ ላይ ተሸክሞ አይቻለሁ፡፡ ትማሩ ይሆናል በሚል ነበር ጓዜን ጭንቅላቴ ላይ የጫንኩት፡፡ እናንተ ግን ብልሆች ናችሁ፡፡ ነገር ግን ብልህነታችን እዚህ የባቡር ፉርጐ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ሁላችንም በህይወታችን ባቡር ውስጥ ተሳፍረን እየተጓዝን ነው፡፡ በዛ ግን ሁሉንም ጓዞቻችንን የምንጭነው ጭንቅላታችን ላይ ነው፡፡ ” ሲል መለሰላቸው።

@zephilosophy
"ስናዳሪ ምን ቢማር ምን ቢመራመር ከእውነት ተርታ እና ከፍትህ ከፍታ ስትፈልገው ብትውል ልታገኘው አትችልም። ለምን ? ቢባል አድራሻው ከሆዱ ስር ነውና። ስናዳሪ ማለት ሳይወለድ የሞተ፣ በስህተት ቢወለድ እንኩዋን ለከርሱ ምሎ፣ በወጣበት ህዝብ ላይ ተሸብልሎ፣ የገዛ ተዝካሩን በመንግስት እያስደገሰ የሚበላ ፍጡር ማለት ነው።"

‹ ዝናብም ጸሀይም በሌለበት ቀን፣ አምባገነን ደጋ ላይ ብቅ ሲል ስናዳሪ ታች ቆላ ላይ ሆኖ ጃንጥላ ይዘረጋለታል፡፡ ስናዳሪ በከርሱ፣ አምባገነን በኩርሲው ከመጡባቸው የማያጥፉት ቃል የማይክዱት ህዝብ የለም፡፡ ››

ምንዳርአለው ዘውዴ
📖የፍትህ ስርቅታ
ይህ ፁሁፍ ሰሞኑ ስናዳሪ መሆናቸውን ላረጋገጡት አርቲስቶችና ፖለቲከኞች መታሰቢያ ይሁንልኝ

@zephilosophy
2025/06/27 10:22:09
Back to Top
HTML Embed Code: