Telegram Web Link
🌹የመስከረም_5_ግጻዌ

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_5_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ተሰሎንቄ 2
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹³ ስለዚህም የመልእክትን ቃል እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፥ በእውነት እንዳለ በእናንተ በምታምኑ ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት፥ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን።
¹⁴ እናንተ፥ ወንድሞች ሆይ፥ በይሁዳ የሚኖሩትን በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉትን የእግዚአብሔርን ማኅበሮች የምትመስሉ ሆናችኋልና፤ እነርሱ ከአይሁድ መከራ እንደ ተቀበሉ፥ እናንተ ደግሞ ያንን መከራ ከአገራችሁ ሰዎች ተቀብላችኋልና።
¹⁵ እነዚያም ጌታን ኢየሱስን ደግሞ ገደሉ ነቢያትንም እኛንም አሳደዱ፥ እግዚአብሔርንም ደስ አያሰኙም፥ ሰዎችንም ሁሉ ይቃወማሉ፥
¹⁶ ሁልጊዜ ኃጢአታቸውን ይፈጽሙ ዘንድ አሕዛብ እንዲድኑ እንዳንናገራቸው ይከለክሉናልና። ነገር ግን ቍጣው ወደ እነርሱ ፈጽሞ ደርሶአል።
¹⁷ እኛ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ በልብ ያይደለ ፊት ለፊት ለጥቂት ጊዜ አጥተናችሁ፥ በብዙ ናፍቆት ፊታችሁን ለማየት እጅግ ሞከርን፤
¹⁸ ወደ እናንተ ልንመጣ ወደን ነበርና፥ እኔ ጳውሎስም አንድና ሁለት ጊዜ፥ ሰይጣን ግን አዘገየን።
¹⁹ ተስፋችን ወይስ ደስታችን ወይስ የትምክህታችን አክሊል ማን ነው? በጌታችን በኢየሱስ ፊት በመምጣቱ እናንተ አይደላችሁምን?
²⁰ እናንተ ክብራችን ደስታችንም ናችሁና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² ወዳጆች ሆይ፥ በእናንተ መካከል እንደ እሳት ሊፈትናችሁ ስለሚሆነው መከራ ድንቅ ነገር እንደ መጣባችሁ አትደነቁ፤
¹³ ነገር ግን ክብሩ ሲገለጥ ደግሞ ሐሤት እያደረጋችሁ ደስ እንዲላችሁ፥ በክርስቶስ መከራ በምትካፈሉበት ልክ ደስ ይበላችሁ።
¹⁴ ስለ ክርስቶስ ስም ብትነቀፉ የክብር መንፈስ የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን ናችሁ።
¹⁵ ከእናንተ ማንም ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ክፉ አድራጊ እንደሚሆን ወይም በሌሎች ጒዳይ እንደሚገባ ሆኖ መከራን አይቀበል፤
¹⁶ ክርስቲያን እንደሚሆን ግን መከራን ቢቀበል ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር።
¹⁷ ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት ተነሥቶ የሚጀመርበት ጊዜ ደርሶአልና፤ አስቀድሞም በእኛ የሚጀመር ከሆነ ለእግዚአብሔር ወንጌል የማይታዘዙ መጨረሻቸው ምን ይሆን?
¹⁸ ጻድቅም በጭንቅ የሚድን ከሆነ ዓመፀኛውና ኃጢአተኛው ወዴት ይታይ ዘንድ አለው?
¹⁹ ስለዚህ ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መከራን የሚቀበሉ፥ መልካምን እያደረጉ ነፍሳቸውን ለታመነ ፈጣሪ አደራ ይስጡ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 16
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²² ሕዝቡም አብረው ተነሡባቸው፥ ገዢዎቹም ልብሳቸውን ገፈው በበትር ይመቱአቸው ዘንድ አዘዙ፤
²³ በብዙም ከደበደቡአቸው በኋላ ወደ ወኅኒ ጣሉአቸው፥ የወኅኒውንም ጠባቂ ተጠንቅቆ እንዲጠብቃቸው አዘዙት።
²⁴ እርሱም የዚህን ዓይነት ትእዛዝ ተቀብሎ ወደ ውስጠኛው ወኅኒ ጣላቸው፥ እግራቸውንም በግንድ አጣብቆ ጠረቃቸው።
²⁵ በመንፈቀ ሌሊት ግን ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩ እግዚአብሔርን በዜማ ያመሰግኑ ነበር፥ እስረኞቹም ያደምጡአቸው ነበር
²⁶ ድንገትም የወኅኒው መሠረት እስኪናወጥ ድረስ ታላቅ የምድር መንቀጥቀጥ ሆነ፤ በዚያን ጊዜም ደጆቹ ሁሉ ተከፈቱ የሁሉም እስራት ተፈታ።
²⁷ የወኅኒውም ጠባቂ ከእንቅልፉ ነቅቶ የወኅኒው ደጆች ተከፍተው ባየ ጊዜ፥ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ይገድል ዘንድ አስቦ ሰይፉን መዘዘ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_5_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ወቀተሉ ዕቤረ ወእጓለ ማውታ። ወቀተሉ ፈላሴ። ወይቤሉ ኢይሬኢ እግዚአብሔር"። መዝ. 93(94)፥6-7።

#ትርጉም፦ "ባልቴቲቱንና ድሀ አደጉን ገደሉ፥ ስደተኛውንም ገደሉ። #እግዚአብሔር አያይም፥ የያዕቆብ አምላክ አያስተውልም አሉ"። መዝ. 93(94)፥6-7።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_5_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 18
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²³ ስለዚህ መንግሥተ ሰማያት ባሮቹን ሊቈጣጠር የወደደን ንጉሥ ትመስላለች።
²⁴ መቈጣጠርም በጀመረ ጊዜ፥ እልፍ መክሊት ዕዳ ያለበትን አንድ ሰው ወደ እርሱ አመጡ።
²⁵ የሚከፍለውም ቢያጣ፥ እርሱና ሚስቱ ልጆቹም ያለውም ሁሉ እንዲሸጥና ዕዳው እንዲከፈል ጌታው አዘዘ።
²⁶ ስለዚህ ባሪያው ወድቆ ሰገደለትና፦ ጌታ ሆይ፥ ታገሠኝ፥ ሁሉንም እከፍልሃለሁ አለው።
²⁷ የዚያም ባሪያ ጌታ አዘነለትና ለቀቀው፥ ዕዳውንም ተወለት።
²⁸ ነገር ግን ያ ባሪያ ወጥቶ ከባልንጀሮቹ ከባሮቹ መቶ ዲናር ዕዳ ያለበትን አንዱን አገኘና፦ ዕዳህን ክፈለኝ ብሎ ያዘና አነቀው።
²⁹ ስለዚህ ባልንጀራው ባሪያ ወድቆ፦ ታገሠኝ፥ ሁሉንም እከፍልሃለሁ ብሎ ለመነው።
³⁰ እርሱም አልወደደም፥ ግን ሄዶ ዕዳውን እስኪከፍል ድረስ በወኅኒ አኖረው።
³¹ ባልንጀሮቹ የሆኑ ባሮችም ያደረገውን አይተው እጅግ አዘኑ፥ መጥተውም የሆነውን ሁሉ ለጌታቸው ገለጡ።
³² ከዚያ ወዲያ ጌታው ጠርቶ፦ አንተ ክፉ ባሪያ፥ ስለ ለመንኸኝ ያን ዕዳ ሁሉ ተውሁልህ፤
³³ እኔ እንደ ማርሁህ ባልንጀራህ የሆነውን ያን ባሪያ ልትምረው ለአንተስ አይገባህምን? አለው።
³⁴ ጌታውም ተቈጣና ዕዳውን ሁሉ እስኪከፍለው ድረስ ለሚሣቅዩት አሳልፎ ሰጠው።
³⁵ ከእናንተ እያንዳንዱ ወንድሙን ከልቡ ይቅር ካላለ፥ እንዲሁ ደግሞ የሰማዩ አባቴ ያደርግባችኋል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
🌹ሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ሠለስቱ_ምዕት_ቅዳሴ ነው። መልካም የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በዓል፣ የቅዱስ ኪራኮስ የእናቱ ቅድስት ሐና፣ የአባ ጳውሎስ ሰማዕትና የቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ ወልደ እልፍዮስ በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ንስሐ_ከኃጢያት_የሚያነጻ_ቅዱሳን_ሱራፌል_ከመንበረ_ሥላሴ_የወሰዱት_የእሳት_ፍም_ነው!

በእርሱ የኃጢያተኛው ኃጢያት ተወግዷልና #ንስሐም ኃጢያታችን የሚወገድበት ሰይጣንን የምናቃጥልበት እሳት ነው። ኢሳ.6÷4። #ንስሐ ከሕይወታችን ኃጢያትን የምናስወግድበት ብቻ ሳይሆን ከፍርድ መዝገብም ኃጢያታችንን የምናስፍቅበት ብቸኛ መንገድ ነው። #እግዚአብሔርም በነብዩ ኤርሚያስ አድሮ "በደላቸውን እምራቸዋለሁና ኃጢያታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስብምና"። ኤር.31÷34 በማለት የተናገረው ቀድሞ የሠራነውና በፍርድ መዝገብ የተጻፈው ኃጢያታችን የሚደመሰሰው በ #ንስሐ አማካኝነት መሆኑን ሲያስተምር ነው። #መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም በዘመነ ሥጋዌው " #ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንዲሁ ትጠፋላችሁ" በማለት ከፍርድ ለመዳን የሚቻለው በ #ንስሐ አማካኝነት ከኃጢያት በመለየት መሆኑን አስረድቷል። ሉቃ.13÷3

#ይቀጥላል.......
#ቃልኪዳን_የጥቅምት_5_አቡነ_ገብረ_መንፈስ_ቅዱስ

    #አንድ_አምላክ_በሆነ_በአብ#በወልድ#በመንፈስ_ቅዱስ ስም አሜን!

፩, የመነኮሳት አባት፣ ጽኑ ተጋዳይ፣ የባሕታውያን አለቃ በሆነ በአባታችን በገብረ መንፈስ ቅዱስ በዓል "ጥቅምት 5" ቀን የሚነበብ ቃልኪዳን ይህ ነው።

፪, ወደ ረጅም ተራራ ሲወጣ ከዕፀ አድኅኖ ጥላ ሥር በሺበት የተሸፈኑ በሦስት ሽማግሌዎች አምሳል " #ሥላሴ"ን አገኛቸው። በጀርባው አዝሎ ወደ ዝቋላ ተራራ አወጣቸው።  የ " #ሥላሴ" ስዕል ከተሳለባት ከዕፀ ሥርየት ሥር አስቀመጣቸው።

፫, ከዚህ በኃላ #ሥሉስ_ቅዱስ እስከ ሰባተኛው ሰማይ ድረስ አወጡት። ያክንት መረግድ በተባለ ዕንቁ የተሸለመች የሰማያዊት ኢየሩሳሌምን የሕንፃዋን ጌጥ ውበት አሳዩት። ከእነርሱም ተባረከ። የዝቋላና የምድረ ከብድ ኮከብ፣ ማር፣ እንኮይ አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስ÷ በ #ሥሉስ_ቅዱስ እጅ ያለውን #መስቀል ተሳለሙ። አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስ የኢትዮጵያ መብራት ነው።

፬, ወደ ምድር ከወረደ በኃላ የዐይኖቹ ሽፋሽፍት ሳይከደኑ ሰባት ወር ከ አምስት ቀን ኖረ። #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በወንጌል ከልብ በመነጨ ፍቅር የሚወደኝን እኔ በአእላፍ መላዕክት ፊት እወደዋለሁ። የጠላቶቹን የአጋንንትን መውደቅ አሳየዋለሁ ያለውን አስቦ እንዲህ ሆኖ ኖረ።(ዮሐ.14÷21)

፭, የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤልም መጥቶ፣ ጠላቶችህን አጋንንትን ታጠፋቸው ዘንድ ውረድ፣ ከፈጣሪህ ከ #እግዚአብሔር ዘንድ ኃይል ተሰቶሀልና አለው። ቃሉን አልሰማም፣ አልታዘዘለትምም፣ ክፉም ቢሆን በጎም ቢሆን አልመለሰለትም።

፮, ከዚህም በኃላ #መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ መጥቶ አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስን በደብረ ታቦር አምሳል ወደተጠራ ዝቋላ ኸደ ሚባል ቅዱስ ተራራ ና ውረድ አለው፣ እስከ 100 አመት ድረስ የአባታችን የገብረ መንፈስ ቅዱስ ደም የፈሰሰባት፣ በብርሃን ወደ ተሸለመች ባሕርም።

፯, እመቤታችን ድንግል #ማርያምም የአጋንንትን ጥፋት ታይ ዘንድ ከዚያ ባሕር ዳር ተቀመጠች። መልዐኩ ቅዱስ ራጉኤልም ከሠራዊቱ ጋር የመባርቅት ልብሶችን ለብሶ መጣ፣ ቅዱሳን ሚካኤልና ገብርኤል፣ የመላእክት ወገን ሁሉ የእሳት ነበልባል ለብሰው መጡ። ቦታው እስኪጠባቸው ድረስ ዙርያውን ከበቧት። መላእክት ጭፍቅ እንዳለች እንደሮማን ፍሬ ተጨናነቁ፣ የእግር ጫማ መረገጫ ያህል ቦታስ እንኳ አልተገኘም።

፰, ከመላእክት ብቻ በቀር ሁለመናዋ አይታይም ነበር፣ በእሳት ሰይፎች ታጥራ ነበር እንጂ። በውስጧ የነበሩትን አጋንንትን ሁሉ አጠፏቸው፣ ፍለጋቸውም አልተገኘም። በነፋስ ፊት እንዳለ ትቢያ ሆኑ፣ በበረሃ መካከል እንደሚነድ ጢስ ጠፉ፣ በአሸዋና ሙጫ እንደተደፈነች ጉድጓድም ሆኑ።

፱, የሰው ሥጋ የለበሰ ስራው ክፉ የሆነ፣ አንድ ጋኔን አምልጦ፣ አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስ የሚወደው ጽኑ ተጋዳይ በሚሆን በገዳማዊ አባ ፍሬ ቅዱስ በአት ትይዩ ባለችው አንዲት ገደል መካከል ተደበቀ። አባታችንም ያቺን ገደል ከሁለት ሰነጠቃት፣ አፏንም ከፈተች።

፲, በዚያች ገደል ላይ ወድቆ፣ ተጥሎ አገኘው፣ በመብረቅ መታው፣ በክፉ አሟሟትም ሞተ። ለእንስሳ ለአራዊት ሁሉ በሽታ እንዳይሆን በመሬት ውስጥ አልተቀበረም፣ ለመጪው ትውልድ ታላቅ ምልክት ይሆን ዘንድ የዋሻው ስንጥቅ እስከዛሬ አለ።

፲፩, ሕዝብ፣ አሕዛብ፣ ነገሥታት፣ መኳንንት፣ ሽማግሌውች፣ ሕጻናት፣ ደናግል፣ መነኮሳት፣ ልዩ ልዩ ልብስ የለበሱ፣ በሐር ልብስ ያጌጡ፣ የከበሩ ወንድች ሴትችም ያዩታል። በተሳሉ ደንጊያዎች አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስን እየደበደበ ሲያሰቃየው የነበረ የዚያ ጋኔን አጥንቶቹ፣ መላ ሰውነቱ ሁሉ ወድቆ ይታይ ነበር።

፲፪, አባታችን ይህንን ከፈጸመ በኃላ ከ #ጌታችን_ከመድኃኒታችን_ከኢየሱስ_ክርስቶስ ቃልኪዳን ተቀበለ፣ በአባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገድል የተቀደሰች ይህችን ገዳም የሚሳለሟት ደጅ የሚጠኗት ሁሉ በመንግስተ ሰማያት ተስፋ ያገኛሉ። ከሩቅም ከቅርብም የጻድቁን በዓል ለማክበር ወደ እርሷ የሚመጡትንም ኀጢያት አንዳላገኘው እንደ 40 እንደ 80 ቀን ሕጻን ይሆናሉ።

፲፫, እንደ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ፣ 70 ዘመን ሙሉ በሐዘን ፊቱ እንደጠቆረ በምሥጢር ባሕር እንደ ዋኘ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ይሆናሉ።

፲፬, ይህንን ሁሉ አስቦ ከአባታችን በዓላት ከፍ ባለች በከበረች በጥቅምት "5" ቀን የአባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስን በዓል ያከበረ ሁሉ፣ በሰው ሁሉ እንደታወቀች እንደ መጋቢት "5" ቀን የሚያያት የሚያከብራትንም ሁሉ #እግዚአብሔር_አብ ከአንተ ጋር የእሳትን ባሕር በግልጥ ይለፍ፣ የመለአከ ሞት የዲያብሎስን ፊት አያይም ብሎ ቃል ገባለት።

፲፭, ከዚህ በኃላ " #አብ_ወልድ_መንፈስ_ቅዱስ" ብርሃን በማይታይባት ባሕር ላይ ለሰው ሁሉ መድኃኒት ትሆን ዘንድ የምሕረት ጽዋ አፈሰሱባት።

፲፮, መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል መጥቶ ክብር ይግባውና የ #ጌታችን_የመድኃኒታችን_የኢየሱስ_ክርስቶስን ደም በባሕር ላይ ጨመረ።

፲፯, ሕንጻዋ ያማረ በ #ሥላሴ ስም የታነጸች አንዲት ቤተ መቅደስ አለች፣ የሕንጻዋ ውበትም ከፀሐይ ሰባት እጅ ያበራል። ያችንም ባሕር ቅዱሳን ይጠብቋታል። ሥጋቸውም ለአይን እንደሚያስደንቅ በምሥራቅ እንደሚወጣ እንደንጋት ኮከብ ይሆናል።

፲፰, ስማቸው የማይታወቅ ብዙ ስውራን ቅዱሳን መጥተው፣ ከገነት አፈር አምጥተው፣ እስከ ዘለዓለም ድረስ ከክፉ ነገር ምንም ምን በውስጧ እንዳይገባ በዝቋላ ገዳም ላይ በተኑት። የአባታችን የጻድቁ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጸሎትና በረከት በእኛ በገዳሙ ልጆችና በመላው ሕዝበ ክርስቲያን በሀገራችን በኢትዮጵያ ላይ ለዘለዓለሙ ጸንቶ ይኑር። አሜን!

#ምንጭ#ገድለ_ብፁዕ_ወቅዱስ_አቡነ_ገብረ_መንፈስ_ቅዱስ!
"ልጆቼ! የሚያሳፍር ነገር፣ የስንፍና ንግግር ወይም ዋዛ ፈዛዛ የማይገቡ ናቸውና በእኛ በክርስቲያኖች ዘንድ ከቶ አይሰሙ፡፡ እስኪ ንገሩኝ! የዋዛ ፈዛዛ ንግግር ጥቅሙ ምንድን ነው? እስኪ ንገሩኝ፤ አንድ ጫማ ሰፊ፣ ጫማ እየሰፋ በአንድ ጊዜ ሌላ ሥራ መሥራት ይችላልን? አይችልም፡፡ ከዋዛ ፈዛዛ የሚያሳፍር ንግግር ይወለዳል፡፡ የአሁኑ ጊዜ ደግሞ ለእኛ ለክርስቲያኖች ዋዛ ፈዛዛ የምንናገርበት ሳይኾን የንስሐችን ጊዜ ነው፡፡ እስኪ አሁንም ልጠይቃችሁና እናንተም መልሱልኝ! አንድ ቦክስ የሚጫወት ሰው ውድድሩን ችላ ብሎ ዋዛ ፈዛዛን ይናገራልን? እንዲህ የሚያደርግ ከኾነስ በተጋጣሚው በቀላሉ የሚሸነፍ አይደለምን? ታዲያ ባለጋራችን ዲያብሎስ‘ኮ የሚውጠውን ፈልጐ እንደሚያገሣ አንበሳ በዙርያችን ቁሟል፡፡ ጥርሱን እያንቀጫቀጨብን ነው፡፡ እኛን የሚጥልበት ወጥመድ በማዘጋጀት ላይ ነው፡፡ የደኅንነታችን መንገድ ላይ እሳት እየተነፈሰ ነው፡፡ ታዲያ ዲያብሎስ እንዲህ እኛን ለመጣል ሲተጋ እኛ ዋዛ ፈዛዛን፣ የሚያሳፍር ነገርን፣ የስንፍናንም ንግግር ስንናገር ቁጭ ልንል ይገባናልን?

የምወዳችሁ ልጆቼ! ጊዜው የምንተኛበት ጊዜ አይደለም፡፡ የተጋድሎ ጊዜ ነው እንጂ፡፡ ቅዱሳን ጊዜያቸውን እንደ ምን እንደሚያሳልፉት ማወቅ ትፈልጋላችሁን? እስኪ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስን አብረን እንስማው፤ እንዲህ ያለውን፡- “ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሠጽ እዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ”፤ … “በብዙ መከራና ከልብ ጭንቀት በብዙም እንባ ጽፌላችኋለሁ…”፡፡ … “የሚደክም ማን ነው፤ እኔ አልደክምምን? የሚሰናከል ማን ነው፤ እኔም አልናደድምን?”፤ “… በድንኳኑ ያለን እኛ ከብዶን እንቃትታለን”፡፡ ታዲያ እነ ቅዱስ ጳውሎስ ጊዜያቸውን እንዲህ ካሳለፉ፣ ኃጥአን የምንኾን እኛ ጊዜያችንን በሳቅና ስላቅ ልናጠፋ ይገባናልን? በክርስቶስ ፍቅር የማፈቅራችሁ ልጆቼ! በንግግሬ አትማረሩ፡፡

ጊዜው የተጋድሎ ጊዜ ነው፤ ታዲያ ስለ ምንድን ነው የዘፋኞችን መሣርያ አንሥተን ከዓለም ጋር የምንዘፍነው? በጦር ግንባር ያለ ወታደር ከጠላት ሊመጣ የሚችለውን ጥቃት ለመከላከል ከመዘጋጀት ይልቅ ጊዜውን በዋዛ ፈዛዛ ያጠፋልን? አያጠፋም፡፡ ታዲያ እኛም‘ኮ የክርስቶስ በጎ ወታደሮች ነን፡፡ ..."

(ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)
ፈረስ የሚጋልብ ሰው ልጓሙን በአግባቡ ካልያዘው በቀር ፈረሱም ጋላቢውም ይጎዳሉ፡፡ አንድ እባብ የነደፈው ሰው ባለመድኃኒቶችን አግኝቶ መርዙ ወደ ሰውነቱ ኹሉ እንዳይሰራጭ ካላደረገ በቀር ወደ ሞት ሊደርስ ይችላል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ አንድ ትንሽ ቁስል በጊዜው ጊዜ ካልታከሙት በቀር ሰፍቶና ተስፋፍቶ ትልቅ ቁስል ወደ መኾን ያድጋል፡፡

በእኛ በክርስቲያኖች ዘንድም እንደዚህ ነው፡፡ የኃጢአት ቁስል የሚሰፋው ችላ ሲባል ነው፡፡ ገና ትንሽ ነው በሚባልበት ደረጃ ካላራቅነው በቀር ነገ ከነገ ወዲያ ትልቅ ቁስለ ነፍስ ይኾናል፡፡

ተመልከቱ! ዛሬ ላለመቈጣት የሚታገል ሰው ነገ ሰዎችን የሚጎዳበት ዘዴን አይዘይድም፡፡ ሰዎችን የሚጎዳበት ዘዴ ካልዘየደም ብዙ ባልንጀሮች ይኖሩታል፡፡ ብዙ ባልንጀሮች ካሉት የሚጠላቸውም የሚጠሉትም ሰዎች አይኖሩም፡፡ ባልንጀራ እንጂ ጠላት የሌለው ሰውም የምግባር ኹሉ ፍጻሜ የኾነውን ፍቅር ገንዘብ ያደርጋል፡፡

ስለዚህ ተወዳጅ ሆይ! ወደዚህ ምግባር ታድግ ዘንድ ወደዚህ እንዳታድግ የሚያደርጉህን ጥቃቅን ኃጢአቶችን ከአንተ አርቅ፡፡ ሰፍቶ ተስፋፍቶ ነገ እንዳይቸግርህ ዛሬ በእንጭጩ እያለ ችላ አትበለው፡፡

ይሁዳ ገና የገንዘብ ፍቅር ደረጃ ላይ እያለ ራሱን ቢመረምርና ይህን ለማራቅ ቢጥር ኖሮ በኋላ ከተሰበሰበው ገንዘብ ወደ መስረቅ ባላደገ ነበር፡፡ ገና ከመጀመሪያው ደረጃ እያለ ችላ ባይል ኖሮ የኃጢአት ኹሉ ራስ የኾነው ኃጢአት ወደ መፈጸም ባልደረሰ ነበር፡፡

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንደዚህ ልናደርግ እንደሚገባን ሲያስተምረን ከዝሙት ብቻ እንድርቅ ሳይኾን የእርሱ ሥር የኾነውንና አይቶ መመኘትን ችላ ልንለው እንደማይገባን ነገረን (ማቴ.5፡28)፡፡ ኃጢአት ሥር ሰዳና ሰፍታ ከመቸገራችን በፊት በችግኝ ደረጃ ላይ እያለች ነቅለን መጣል ቀላል ነውና፡፡ 

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
#ጥቅምት_6

#አንድ_አምላክ_በሆነ_በአብ_በወልድ_በመንፈስ_ቅዱስ ስም
ጥቅምት ስድስት በዚህች ቀን እመ ሳሙኤል ነቢይ #ቅድስት_ነቢይት_ሐና ያረፈችበት፣ ቅዱስ አባት #አባ_ጰንጠሌዎን ያረፈበት፣ #ዕንባቆም_ነቢይ መታሰቢያው፣ የሀገረ አቴና ኤጲስቆጶስ #ቅዱስ_ዲዮናስዮስ በሰማዕትነት ያረፈበት እና የሴት ልጅ #ቅዱስ_ሄኖስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ነቢይት_ሐና

ጥቅምት ስድስት በዚህች ቀን የታላቁ ነቢይና ካህን የሳሙኤል እናት ቅድስት ነቢይት ሐና አረፈች።

ይችም ቅድስት ከሌዊ ነገድ ናት የታኅርም ልጅ ሕልቃና አገባት ፍናና የምትባልም ሌላ ሚስት አለችው እርሷም ወላድ በመሆኗ ቅድስት ሐና ልጅ ስለሌላት መካንም ስለሆነች ሁልጊዜ ትገዳደራት ነበር።

ሐና ግን ፈጽማ በማዘን አትበላም አትጠጣም ባሏ ሕልቃናም ያረጋጋታል ማረጋጋቱንም አልተቀበለችውም በሊቀ ካህናቱ በኤሊ ዘመንም ወደቤተ #እግዚአብሔር ወጣች እያለቀሰችና እያዘነች በ #እግዚአብሔር ፊት ጸለየች እንዲህም ብላ ስለትን ተሳለች አቤቱ ልጅ የሰጠኸኝ እንደሆነ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ለአንተ የሚያገለግል አደርገዋለሁ።

ካህኑ ኤሊም አያትና እርሷ የወይን ጠጅ ጠጥታ እንደ ሰከረች አሰበ እርሷ በዝምታ በልቧ ትጸልይ ነበርና በቊጣና በግሣጼ የወይን ጠጅ ጠጥተሽ ወደዚህ ወደ #እግዚአብሔር ቤት ለምን መጣሽ አሁን ሒጂ ስካርሺን በእንቅልፍ አስወግጂ አላት።

እርሷም እንዲህ አለችው የወይን ጠጅ ከቶ አልጠጣሁም ልጅ ያጣሁ በመሆኔ በልቤ አዝናለሁ እንጂ ካህን ኤሊም አጽናናት እንዲሁም ብሎ ባረካት የእስራኤል ፈጣሪ የለመንሽውን ይስጥሽ በሰላም ሒጂ በቃሉም አምና ወደ ቤቷ ገባች።

ከዚህም በኋላ ፀንሳ ወንድ ልጅን ወለደች ስሙንም ሳሙኤል ብላ ጠራችው። ጡትንም በአስጣለችው ጊዜ ወደ #እግዚአብሔር ቤት ይዛው ወጣች ወደ ካህን ኤሊም አቀረበችውና እንዲህ ብላ አስረዳችው ከአሁን በፊት ልጅን ይሰጠኝ ዘንድ ወደ #እግዚአብሔር ስጸልይና ስለምን ያየኸኝ ሴት ነኝ ልመናዬንም ሰምቶ ይህን ልጅ ሰጠኝ አሁንም በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ለ #እግዚአብሔር አገልጋይ ይሆን ዘንድ አመጣሁት።

ከዚህም በኋላ ቅድስት ሐና #እግዚአብሔርን አመሰገነችው። ልቤ በ #እግዚአብሔር አምኖ ጸና የሚለውን ጸሎትና ትንቢት እስከ መጨረሻው ተናገረች። ይቺም በዳዊት መዝሙር መጨረሻ ከሙሴ መኀልይ ቀጥላ ተጽፋለች።

ከዚህም በኋላ #እግዚአብሔርን አገልግላ በሰላም አረፈች።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት ሐና በጸሎቷ ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_ጰንጠሌዎን

ዳግመኛም በዚችም ቀን በዋሻ ውስጥ የሚኖር ቅዱስ አባት አባ ጰንጠሌዎን አረፈ። ይህም ቅዱስ በሮሜ አገር በንጉሥ ቀኝ ከሚቀመጡ ከከበሩ ሰዎች ወገን የተወለደ ነው ። በታናሽነቱም ጊዜ ወደ መነኰሳት ገዳም ወስደውት በበጎ ምክር ዕውቀትን እየተማረ በመጸለይና በመጾም በዚያ አደገ።

ከዚህም በኋላ ከቅዱሳን ከስምንቱ ባልንጀሮቹ ጋር ወደ ኢትዮጵያ በንጉሥ አልዓሜዳ ዘመን መጣ በአንድነትም ጥቂት ዘመናት ኑረው ከዚህም በኋላ እርስበርሳቸው ተለያዩ ቅዱስ ጰንጠሌዎንም ከታናሽ ተራራ ላይ ወጥቶ ርዝመቱ አምስት ክንድ አግድመቱ ሁለት ስፋቱ ሦስት ክንድ የሚሆን ዋሻ ለራሱ ሠራ ጠፈሩም አንድ ደንጊያ ነው ከጥቂት ቀዳዳ በቀር በር የለውም።

በውስጡም ሳይቀመጥ ሳይተኛ ያለመብልና ያለ መጠጥ አርባ አምስት ዓመት ኖረ ቆዳው ከዐጥንቱ እስከሚጣበቅ በዕንባ ብዛትም ቅንድቡ ተመለጠ። በሽተኞችን በማዳን የዕውሮችንም ዐይኖች በመግለጥ ብዙ ተአምራትን አደረገ።

በአንዲትም ቀን በማታ ጊዜ ዕንጨት ተከለ አሰከሚነጋ ድረስም አድጎ ትልቅ ዛፍ ሆነ ወዲያውም ደረቀና ደቀ መዝሙሩ ፈልጦ አነደደው ፍሙንም በልብሱ ቋጥሮ ለማዕጠንት ወሰደው።

የናግራንን አገር ያጠፋትን ምእመናኖችንም የገደላቸውን አይሁዳዊ ንጉሥ ሒዶ ሊወጋው ንጉሥ ካሌብ በአሰበ ጊዜ በጸሎቱ ይረዳው ዘንድ ይህን አባት ጰንጠሌዎንን ለመነው እርሱም በሥራው ሁሉ ላይ ችሎታ ያለው #እግዚአብሔር በጠላቶችህ ላይ ድል አድራጊነትን ሰጥቶህ በደኀና በፍቅር አንድነት ትመለሳለህ አለው።

ንጉሥ ቅዱስ ካሌብም ከናግራን ሀገር በደረሰ ጊዜ ከከሀዲው ንጉሥ ከፊንሐስ ጋር ተዋጋ ድል አድርጓቸውም ከሀድያንን ሁሉ እንደ ቅጠል እስቲረግፉ አጠፋቸው አባ ጰንጠሌዎንንም በጦርነቱ መካከል ጠላቶችን ሲአሳድዳቸው እንዳዩት ብዙዎች ምስክሮች ሆኑ።

ከዚህም በኋላ ንጉሥ ካሌብ ከድል አድራጊነት ጋር በተመለሰ ጊዜ መንግሥቱን ትቶ በዚህ አባት እጅ መነኰሰ ከዋሻ ውስጥም ገብቶ በጾምና በጸሎት እየተጋደለ ኖረ።

ይህም ቅዱስ አባ ጰንጠሌዎን ተጋድሎውን በፈጸመ ጊዜ ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ወደርሱ መጣ ስሙን ለሚጠራ መታሰቢያውን የሚያደርግ ገድሉንም ለሚጽፍ ቃል ኪዳን ሰጠው እንግዲህስ ድካም ይበቃሀል ዕረፍ ያን ጊዜም ዐጥንቶቹ ተነቃነቁ በፍቅር አንድነትም አረፈና በዚያ በዋሻው ውስጥ ተቀበረ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአቡነ ጰንጠሌዎን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዕንባቆም_ነቢይ

በዚችም ቀን የስሙ ትርጓሜ አዋቂ የሆነ የዕንባቆም ነቢይ መታሰቢያው ነው። ይህም ቅዱስ በአንዲት ዕለት እህሉን ለሚያጭዱለት ምሳቸውን አዘጋጅቶ ተሸክሞ ሲሔድ መልአክ ተገልጾለት ይህን መብል በባቢሎን አገር በአንበሶች ጕድጓድ ውስጥ ላለ ለነቢዩ ዳንኤል ውሰድ አለው።

ቅዱስ ዕንባቆምም ጌታዬ ሆይ ባቢሎንን አላየኋት ጉድጓዱንም አላውቀው አለው። የ #እግዚአብሔር መልአክም በራሱ ጠጉር ያዘው ምግቡን በእጁ እንደያዘ ወሰደውና ጉድጓዱ እንደተዘጋ አስገባው ምግቡንም ሰጥቶ መገበው ወዲያውኑ ዕንባቆምን ወደ ይሁዳ አገር መለሰው።

በአረጀና በሸመገለም ጊዜ የእስራኤል ልጆች ከተማረኩበት ተመልሰው ቤተ መቅደስን ሠሩ። ቅዱስ ዕንባቆምም ኢየሩሳሌም ደርሶ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ በታላቅ ደስታም ተቀበሉት ትንቢቱንም ሊሰሙ ወደርሱ ተሰበሰቡ አፉንም ከፍቶ በ #መንፈስ_ቅዱስ እንዲህ አለ።

አቤቱ ድምፅህን ሰማሁ ሰምቼም ፈራሁ ሥራህንም አይቼ አደነቅሁ አለ። ስለ #መድኃኒታችንም መውረድና በይሁዳ ክፍል በሆነች በቤተ ልሔም ስለመወለዱ ሲናገር የተመሰገነ #እግዚአብሔር ግን ከፋራን ተራራ ከቴማን ከይሁዳ አውራጃ ይመጣል ብሎ እስከ መጨረሻው ተናገረ ከነቢያት መጻሕፍትም ጋራ ደመርዋት።

ከዚህ በኋላ ከእስራኤል ልጆች አንዲት ሴት ወደርሱ መጣች እያለቀሰችም እንዲህ አለችው። ሁለት ልጆች ነበሩኝ ጣዖት እንዲአመልኩ ፈለጉአቸው እምቢ በአሉ ጊዜም ገድለው በጐዳና ላይ ጣሉአቸው። ተገድለው ወደ አሉበትም አብሮዋት ሔደ ነፍሳቸውንም ይመልስላቸው ዘንድ #እግዚአብሔርን ለመነው ልመናውንም ተቀበሎ በሕይወት አነሣቸው።

ዕረፍቱም በቀረበ ጊዜ ዘመዶቹን ጠራቸው። እንደሚሞትም ነገራቸውና አንዲት ሰዓት ያህል ወደላይ እየተመለከተ ተቀመጠ ። እነሆ እንደ ሰው ክንድ ያለች ታላቅ ክንድ የቤቱን ጣሪያ ሠንጥቃ ወረደች ወደ አፉም ተዘርግታ ነፍሱን ወሰደች ያን ጊዜም አረፈ።

በክርስቲያናዊ ንጉሥ በአንስጣስዮስ ዘመን እንዲህ ሆነ ገድሉን በአነበበ ጊዜ አድንቆ በግብጽ ደቡብ ቀርጣስ በሚባል ቦታ በስሙ ቤተ ክርስቲያን ተሠራለት።
#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በነብዩ ቅዱስ ዕንባቆም ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ኤጲስቆጶስ_ቅዱስ_ዲዮናስዮስ

በዚችም ቀን የሀገረ አቴና ኤጲስቆጶስ ቅዱስ ዲዮናስዮስ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም ቅዱስ በአቴና አገር በእውቀቱና በመራቀቁ የከበረና ከፍ ከፍ ያለ ነው። በአቴናው ከተማ በዐዋቂዎች የመሳፍንት አንድነት ከአማካሪዎች አንዱ እርሱ ነው።

ቅዱስ ሐዋርያ ጳውሎስም ወደዚያ በደረሰ ጊዜ ሃይማኖትን አስተምሮ የክርስትና ጥምቀትን አጥምቆ በአቴና አገር ኤጲስቆጶስ አድርጎ ሾመው።

ብዙ ድርሳናትንም ደረሰ ከእርሳቸውም አንዱ ክብር ይግባውና ስለ #መድኃኒታችን ስቅለት የደረሰው በዕለተ ዐርብ የሚነበብ አንዱ ነው።

የእምነቱም ምክንያት እንዲህ ነው ከዕለታት በአንዱ በፍልስፍናው ቤት ተቀምጦ ሳለ የአቴናም ፈላስፎች በእርሱ ዘንድ ተሰብስበው ነበር እርሱ ለሁሉም አለቃ ስለሆነ በዐርብ ቀንም ቀትር ሲሆን ፀሐይ ጨለመ ታላቅ ንውጽውታም ሆነ አሕዛብ ሁሉ ደንግጠው እጅግ ፈሩ ቅድስ ዲዩናስዩስንም በዓለም ውስጥ የሆነውን #ጌታችን ሆይ አስረዳን ብለው ጠየቁት።

አርሱም ፀሐይን ጨረቃንና ከዋክብትን መረመረ ጸጥ ብለው አገኛቸው ደግሞ ባሕሮችን ትልቁንም በዓለም ዙሪያ ያለውን የውቅያኖስን ባህር መረመረ እሱንም ጸጥ ብሎ አገኛው።

ከዚህም በኋላ አርስጣላባ የሚባል የፍልስፍና መጽሐፍን አንስቶ ሲመረምር በውስጡ እልመክኑን የሚል አገኘ ይህም ኀቡእ አምላክ ወረደ ወገኞቹም በእርሱ ላይ ተነስተው ሰቀሉት ማለት ነው በዚያችም ጊዜ ልብሱን ቀዶ ታላቅ ሀዘንን አዘነ ከበታቹ ምሁራን ያየውን ያስርዳቸው ዘንድ ለመኑት እርሱም ሁሉን ነገራቸው እነርሱም ይህን ሰምተው ታላቅ ፍርሃት ፈሩ።

ደቀ መዝሙሩ ኡሲፎስንም የሆነውን ሁሉ የዚያችንም ቀን ስሟን ሰዐቷን ወርዋን ዘመኑንም እንዲጽፍ አዘዘው ዳግመኛም በጣዖታቱ ቤቶች በደጃፋቸው እልመክኑን እያሉ እንዲጽፉ አዘዘ።

ከዐሥራ አራት ዓመትም በኋላ ቅዱስ ሐዋርያ ጳውሎስ ወደ አቴና አገረ መጣ ክብር ይግባውና የ #መድኃኒታችን_የኢየሱስ_ክርስቶስን መውረዱን ከእመቤታችን ከቅድስት #ድንግል_ማርያም ከስጋዋ ስጋ ከነፍሷ ነፍስን ነስቶ መወለዱን መከራ መቀበሉን መሰቀሉንና መሞቱን በሶስተኛው ቀን መነሳቱን ማረጉንም በሕያዋንና በሙታን ለምፍረድ ዳግመኛ መምጣቱን አስተማረ።

የአቴና ሰዎችም የሐዋርያዉን ስብከት በሰሙ ጊዜ እጅግ አደነቁ ወደ ዲዩናስዩስም ሩጠው እንዲህ ብለው ነገሩት አንድ ሰው ዛሬ ወደ አገራችን መጥቶ እኛ የማናውቀውን ወይም ከእኛ በፊት የነበሩ አባቶቻችን የማያውቁትን በአዲስ አምላክ ስም አስተማረን።

ቅዱስ ዲዮናስዮስም ልኮ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስን ወደርሱ አስመጥቶ በሀገራችን ውስጥ በአዲስ አምላክ ስም የምታስተምረው ምንድን ነው አለው።

ቅዱስ ጳውሎስም በአደባባያችሁ መካከል አልፌ ስሔድ በአማልክቶቻችሁ ቤቶች በደጃፋ ላይ እልመክኑን የሚል ጽሑፍ አየሁ ይህም የማይመረመር አምላክ ወረደ ማለት ነው እኔም ለእናንተ የምሰብከው ይህንኑ ነው ብሎ መለሰ።

በዚያንም ጊዜ ከዐሥራ አራት ዓመት በፊት ያጻፈውን ያን መጽሐፍ ያመጣው ዘንድ ኡሲፎስን አዘዘው ሁለተኛም ጊዜውንና ወራቱን ሐዋርያውን ጠየቀው እርሱም በመጋቢት ወር በሃያ ሰባት ዓርብ ቀን በስድስት ሰዓት ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርሶቶስ ያን ጊዜ እንደ ተሰቀለ ፀሐይም እንደ ጨለመ ምድርም እንደተናወጠች አስረዳው።

የአቴና ሰዎችም ይህን በስሙ ጊዜ ከቅዱስ ዲዮናስዮስ ጋር ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_በኢየሱስ_ክርስቶስ አመኑ የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው ዲዮናስዮስንም በእነርሱ ላይ ኤጲስቆጶስን አድርጎ ሾመው የቤተ ክርስቲያንንም ሥርዓት የተረጐመ እርሱ ነው።

ከዚህም በኋላ በባሕር አቅራቢያ ወደ አለ አገር በመሔድ በሐዋርያት ዘመን አስተማረ ብዙ ወገኖችንም ክብር ይግባውና በ #ጌታችንም አሳመነ ድንቆች የሆኑ ብዙዎች ተአምራትን አደረገ።

ከሀዲ ንጉሥ ጠማትያኖስም ይዞ ጽኑ ሥቃይን አሰቃየው ከዚያም የከበረች ራሱን በሰይፍ ቆረጠው የተቆረጠች ራሱንም በእጁ ይዞ ሁለት ምዕራፍ ያህል ጐዳና ተጓዘ ሁለተኛም የደቀ መዛሙርቱን የኡሲፎስንና የኡርያኖስን ራሳቸውን ቆረጠ የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ትድረሰን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሄኖስ

በዚችም ቀን የሴት ልጅ የ ቅዱስ ሄኖስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው የ #እግዚአብሔርንም ስም መጥራት የጀመረ ይህ ሄኖስ ነው። ሄኖስም መቶ ዘጠና ዓመት ኖረ ቃይናንም ወለደው ቃይናንንም ከወለደው በኋላ ሰባት መቶ አሥራ አምስት አመት ኖረ ወንዶች ልጆችንና ሴቶች ልጆችን ወለደ በቅዳሜ ቀንም አረፈ። መላ ዕድሜውም ዘጠኝ መቶ አምስት ነው።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት_6)
🌹#የጥቅምት_6_ግጻዌ🌹

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_6_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጢሞቴዎስ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁵ ብቻዋንም ኖራ በእውነት ባልቴት የምትሆን በእግዚአብሔር ተስፋ ታደርጋለች፥ ሌትና ቀንም በልመና በጸሎትም ጸንታ ትኖራለች፤
⁶ ቅምጥሊቱ ግን በሕይወትዋ ሳለች የሞተች ናት።
⁷ ያለ ነቀፋ እንዲሆኑ ይህን ደግሞ እዘዝ።
⁸ ነገር ግን ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፥ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው።
⁹ ባልቴት በመዝገብ ብትጻፍ ዕድሜዋ ከስድሳ ዓመት እንዳያንስ፥ የአንድም ባል ሚስት የነበረች እንድትሆን ያስፈልጋል፤
¹⁰ ልጆችን በማሳደግ እንግዶችንም በመቀበል፥ የቅዱሳንንም እግሮች በማጠብ፥ የተጨነቁትንም በመርዳት በጎንም ሥራ ሁሉ በመከተል፥ ይህን መልካም ሥራ በማድረግ የተመሰከረላት ልትሆን ይገባል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁹ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት።
¹⁰ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል ያጸናችሁማል ያበረታችሁማል።
¹¹ ለእርሱ ክብርና ኃይል እስከዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን።
¹² እየመከርኋችሁና የምትቆሙባት ጸጋ እውነትኛ የእግዚአብሔር ጸጋ እንድትሆን እየመሰከርሁላችሁ፥ የታመነ ወንድም እንደ ሆነ በቈጠርሁት በስልዋኖስ እጅ በአጭሩ ጽፌላችኋለሁ።
¹³ ከእናንተ ጋር ተመርጣ በባቢሎን ያለች ቤተ ክርስቲያን ልጄም ማርቆስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።
¹⁴ በፍቅር አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ። በክርስቶስ ላላችሁ ለሁላችሁ ሰላም ይሁን። አሜን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 17
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³⁰ እንግዲህ እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ አሁን በየቦታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል፤
³¹ ቀን ቀጥሮአልና፥ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤ ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሣቱ ሁሉን አረጋግጦአል።
³² የሙታንንም ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ እኵሌቶቹ አፌዙበት፥ እኵሌቶቹ ግን፦ ስለዚህ ነገር ሁለተኛ እንሰማሃለን አሉት።
³³ እንዲሁም ጳውሎስ ከመካከላቸው ወጣ።
³⁴ አንዳንዶች ወንዶች ግን ተባብረው አመኑ፤ ከእነርሱ ደግሞ በአርዮስፋጎስ ያለው የፍርድ ቤት ፈራጅ ዲዮናስዮስ ደማሪስ የሚሉአትም አንዲት ሴት ሌሎችም ከእነርሱ ጋር ነበሩ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_6_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇🌹

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
 "እበውእ ቤተከ ምስለ መባእየ። ወእሁብ ብጽዓትየ ዘነበብኩ በአፉየ። ዘእቤ በከናፍርየ አመ ምንዳቤየ"። መዝ 65(66)፥13-14

#ትርጉም፦ “ከሚቃጠል መሥዋዕት ጋር ወደ ቤትህ እገባለሁ፤ በመከራዬ ጊዜ በአፌ የተናገርሁትን ከንፈሮቼም ያሉትን ስእለቴን ለአንተ እፈጽማለሁ።” መዝ 65(66)፥13-14

ወይም👇

"ዘያነብራ ለመካን ውስተ ቤቱ። ወያስተፌሥሐ ለእመ ውሉድ። ዘያነብራ ለመካን ውስተ ቤቱ"። መዝ.112(113)÷9

#ትርጉም"፦ “መካኒቱን በቤት የሚያኖራት፥ ደስ የተሰኘችም የልጆች እናት የሚያደርጋት። ።” መዝ.113(113)፥9

ወይም👇

"ተቀሠፍኩ ወየብሰ ከመ ሣዕር ልብየ። እስመ ተረሥዐኒ በልአ እክል። እም ቃለ ገዐርየ ጠግዐ ሥጋየ ዲበ አዕፅምትየ"። መዝ.101(102)÷4-5

#ትርጉም፦ "እህል መብላት ተረስቶኛልና ተቀሠፍሁ ልቤም እንደ ሣር ደረቀ። ከጩኸቴ ድምፅ የተነሣ አጥንቶቼ ከሥጋዬ ጋር ተጣበቁ"። መዝ.101(102)÷4-5
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_6_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 10
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³² ስለዚህ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤
³³ በሰው ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ።
³⁴ በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም።
³⁵ ሰውን ከአባቱ፥ ሴት ልጅንም ከእናትዋ፥ ምራትንም ከአማትዋ እለያይ ዘንድ መጥቻለሁና፤
³⁶ ለሰውም ቤተ ሰዎቹ ጠላቶች ይሆኑበታል።
³⁷ ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ ከእኔ ይልቅም ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤
³⁸ መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም።
³⁹ ነፍሱን የሚያገኝ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም ስለ እኔ የሚያጠፋ ያገኛታል።
⁴⁰ እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።
⁴¹ ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል።
⁴² ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም።

ወይም👇

ሉቃስ 2
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³⁶ ከአሴር ወገንም የምትሆን የፋኑኤል ልጅ ሐና የምትባል አንዲት ነቢይት ነበረች፤ እርስዋም ከድንግልናዋ ጀምራ ከባልዋ ጋር ሰባት ዓመት ኖረች፤
³⁷ እርስዋም ሰማኒያ አራት ዓመት ያህል መበለት ሆና በጣም አርጅታ ነበር፤ በጾምና በጸሎትም ሌሊትና ቀን እያገለገለች ከመቅደስ አትለይም ነበር።
³⁸ በዚያችም ሰዓት ቀርባ እግዚአብሔርን አመሰገነች፤ የኢየሩሳሌምንም ቤዛ ለሚጠባበቁ ሁሉ ስለ እርሱ ትናገር ነበር።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️  🌹
የሚቀደው ቅዳሴ የ #እመቤታችን_የማርያም ነው። መልካም የነቢይት ቅድስት ሐና፣ የአባ ጰንጠሌዎን፣ የቅዱስ ዲዮናስዮስ፣ የቅዱስ ሄኖስ የዕረፍታቸው በዓልና የጾም ጊዜ። ለሁላችንም ይሁንልን። 🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ንስሐ_ከሚመጣው_የመጨረሻ_መከራና_ሐዘን_መዳኛ_ወይም_ማምለጫ_መንገድ_ነው!

የነነዌ ሰዎች ከኃጢያታቸው የተነሳ የ #እግዚአብሔር ቁጣ እንደመጣባቸው በነብዩ ዮናስ አማካኝነት በተሰበከላቸው ጊዜ ሊወርድ ከነበረው የእሳት ዝናብ ለመዳን የቻሉት በ #ንስሐ ለቅሶ ነው። ት.ዮናስ.3÷10። በነብዩ ኤርሚያስ "አሁንም መንገዳችሁንና ሥራችሁን አሳምሩ! የአምላካችሁንም የ #እግዚአብሔር ቃል ስሙ #እግዚአብሔር የተናገራችሁን ቁጣ ይተዋል" ኤር.26÷23 በማለት የተነገረው ስለዚህ ነው።

#ይቀጥላል.......
ጥቅምት 6 #ኢትዮጵያዊ_አቡነ_በጸሎተ_ሚካኤል_ሥጋው_ወደ_ጋስጫ_ገዳም_የፈለሰበት_ነው!

ይኸውም ከካህናት ወገን የሆነው አባቱ ማርቆስ ሲሆን እናቱ እግዚእ ክብራ ትባላለች፡፡ እግዚእ ክብራም ወደ ወላጆቿ በሄደች ጊዜ ‹‹ከመኳንንቶቹ ለአንዱ እናጋባታለን›› ብለው ወደ ባሏ ተመልሳ እንዳትሄድ ከለከሏት፡፡ ማርቆስም ስለዚህ ነገር አዝኖ ወደ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሄዶ ሚስቱን እንደከለከሉት ለአንድ መነኩሴ ነገረው፡፡ መነኩሴውም ሄዶ ቢጠይቃቸው ወላጆቿ ድጋሚ ለመነኩሴውም ከለከሉት፡፡ ማርቆስም እየተመላለሰ መነኩሴውን ቢያስቸግረው ይዞት ሄደ ነገር ግን ወላጆቿ ጥላቻቸውን አበዙባቸው፡፡ መነኩሴውም ‹‹ማርቆስንና ሚስቱን ለአንድ ቀን ብቻ ሁለቱን አንድ ላይ ላናግራቸው›› በማለት ይዟቸው አደረ፡፡ እርሱም በማደሪያው እንዲያድሩ ከነገራቸው በኋላ ‹‹በዚህች ሌሊት ሩካቤ ሥጋ ሳትፈጽሙ እንዳታድሩ›› አላቸው፡፡ ሁለቱም በመነኩሴው ቤት አድረው ሳለ ሌሊት መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ለማርቆስ ተገለጠለትና ‹‹ሚስትህ ወንድ ልጅ ትወልዳለች፣ በወለደችም ጊዜ ስሙን በጸሎተ ሚካኤል ትለዋለህ፣ ለቤተ ክርስቲያንም ዐምድ ይሆናል›› አለው፡፡ ማርቆስም ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ ከሚስቱ ጋር ተገናኘና አቡነ በጸሎተ ሚካኤል ተፀነሱ፡፡

እግዚእ ክብራ ከፀነሰች በኋላ ፊቷ እንደፀሐይ የሚያበራ ሆነ፡፡ የታመሙ ሰዎችም ሆዷን በነኩት ጊዜ ይፈወሱ ነበር፡፡ በወለደችም ጊዜ በቤቷ ውስጥ ቀስተ ደመና ተተክሎ ታየ ሲሆን አስቀድሞ መልአኩ ስሙን እንዳወጣለት ‹‹በጸሎተ ሚካኤል›› አሉት፡፡ አባቱም ካህን ነውና ምግባር ሃይማኖትን ጠንቅቆ እያስተማረ አሳደገው፡፡ በጸሎተ ሚካኤል ገና ሕፃን ሳለ መዝሙረ ዳዊትን፣ የነቢያት ጸሎትን በማዘውተር በጾም በጸሎት ሲጋደል ወላጆቹ ‹‹ይህ ሕፃን ልጃችን በረሃብ ይሞትብናል›› በማለት በግድ እየገረፉ እንዲመገብ ያስገድዱት ነበር፡፡ በግድ አፉን ይዘው ምግብ ከጨመሩበር በኋላ ‹‹ይኸው ጾምህን ፈታህ›› ሲሉት እርሱ ግን በሕፃን አንደበቱ ‹‹እኔ በፈቃዴ በአፌ ውስጥ ብጨምረው ጾሜን በሻርኩት ነበር፣ እናንተ በአፌ ውስጥ በግድ ከጨመራችሁት ግን ጾሜ አይሻርም›› እያላቸው እስከ ማታ ይጾም ነበር፡፡

ከዚህም በኋላ አባቱ ወደ ጳጳስ ዘንድ ወስዶ ዲቁና እንዲሾም አደረገው፡፡ ባደገም ጊዜ አባቱ ማርቆስ ሚስት ያጋባው ዘንድ ባሰበ ጊዜ አቡነ በጸሎተ ሚካኤል ሸሽቶ ወደ ገዳም ገባ፡፡ አበ ምኔቱም ከእርሱ ጋር አስቀምጦ የምንኩስናን ቀንበር ያሸክመው ዘንድ ብዙ ፈተነው፡፡

ወላጆቹም መጥተው አስገድደው ከገዳሙ ሊያወጡት ሲሉ እምቢ ቢላቸው እናቱ ዘመዷ ወደሆነው ንጉሡ ውድም ረአድ በመሄድ ስለ ልጇ ነገረችው፡፡ ንጉሡም ከወታደሮቹ ውስጥ በአለንጋ ይዞ የሚገርፍ ወታደር ላከላት፡፡ የተላከው ወታደርም በጸሎተ ሚካኤልን እየገረፈ በማስገደድ ከገዳም አውጥቶ ለወላጆቹ ሰጠው፡፡

አቡነ በጸሎተ ሚካኤልም በወላጆቹ ቤት ሳለ ወላጆቹን ‹‹እመነኩስ ዘንድ እስካልተዋችሁኝ ድረስ የቤታችሁን ምግብ አልበላም›› ብሎ ማለ፡፡ አባቱም ‹‹ምግብ ካልበላህ›› በማለት ጽኑ ድብደባ እየደበደበው ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ቆየ፡፡ አቡነ በጸሎተ ሚካኤልም ሦስቱንም ቀን እቤት ሳይገባ የቀን ፀሐይ ሐሩሩ የሌሊት ውርጭ ቅዝቃዜ እየተፈራረቀበት እቤትም ሳይገባ በደጅ ሆኖ በጾም በጸሎት ቆየ፡፡ በዚህም በአባቱ እጅ ሰማዕትነትን ተቀበለ፡፡ #ጌታንም ‹‹ለምድር ሰላምን ያመጣሁ አይምሰላችሁ ሰይፍን ነው እንጂ፡፡ የመጣሁትስ ሰውን ከአባቱ ልጅንም ከእናቷ ልለይ ነው›› ያለው ቃል በአባታችን ላይ ተፈጸመ፡፡ ማቴ 10፡34፡፡ አባቱ ማርቆስም ሥጋው እስኪያልቅ ድረስ በግርፋት ብዛት የልጁን ሀሳብ ለማስለወጥ ቢሞክርም እንዳልተሳካለት ሲያውቅ መልሶ ወደ ገዳሙ እንዲወስዱት አገልጋዮቹን ላካቸው፡፡ አበ ምኔቱም መምህር ሆኖ ያገለግል ዘንድ እንዲማር ሲነግረው ‹‹እኔ መነኩሴ መሆን እንጂ መምህር መሆን አልፈልግም›› በማለቱ ሳይስማሙ ቀሩና ወደ ሌላ ገዳም ወሰዱት፡፡ በዚያም እንዲሁ ሆነ፡፡ መልሰውም ወደ አባቱ ቤት ባመጡት ጊዜ ወላጆቹም ልጃቸው የምንኩስናን ሀሳቡን ይተወው ዘንድ ከአንድ ሴት ጋር ተማክረው በዝሙት እንድትጥለው ተነጋገሩ፡፡ ሴቷም ወደ በጸሎተ ሚካኤል ቀርባ በዝሙት ልትጥለው ብዙ ሞከረች፡፡ እርሱም ዐውቆ ‹‹ከእኔ ጋር አብረሽ መተኛት ደስ ካሰኘሽ እሺ ከእስራቴ ፍቺኝና እንተኛለን›› አላት፡፡ ይህንንም ያላት ከታሰረበት እንድትፈታውና እንዲያመልጥ ነው፣ እርሷ የእውነት መስሏት ደስ አላትና ሄዳ ለወላጆቹ አብሯት እንዲተኛ መስማማቱን ነገረቻቸው፡፡ ነገር ግን በዚያች ሌሊት አቡነ በጸሎተ ሚካኤል ማንም ሳያየው ተነሥቶ ከእናት አባቱ ቤት ወጥቶ ሄደ፡፡

ከዚህም በኋላ የ #እግዚአብሔር መንፈስ ወደ ደብረ ጎል አደረሰው፣ ይኸውም ቀሲስ አኖርዮስ በብቸኝነት ሸሽቶ የሚጋደልባት ደብረ ጽሙና ናት፡፡ አቡነ በጸሎተ ሚካኤልም በዚያ ከመነኮሰ በኋላ ጽኑውን የተጋድሎ ሕይወት መኖር ጀመረ፡፡ በጾም በጸሎት ሆኖ ቀን የጉልበት ሥራ ይሠራል ሌሊት ቆሞ ሲጸልይ ያድራል፡፡ 90 ሸክም የወይራ ፍልጥ እየፈለጠ ለቤተ ክርስቲያኑና ለአበ ምኔቱ ያመጣ ነበር፡፡ እንጨቱንም ሲቆርጥና ሲፈልጥ የብረት መቆፈሪያ ብቻ ይጠቀም ነበር እንጂ ስለታም የሆኑ ምሳርና መጥረቢያ አይጠቀምም ነበር፡፡ ምክንያቱም የወጣትነት ኃይሉና ሥጋው በእጅጉ ይደክም ዘንድ ነው፡፡ እንዲህም ሲሠራ ጾም፣ ጸሎት፣ ሥግደቱን አያስታጉልም ነበር፡፡ እስከ 4 ቀንም የሚጾምበት ጊዜ አለ፡፡ አቡነ በጸሎተ ሚካኤል በእንደዚህ ያለ ጽኑ ተጋድግሎ 13 ዓመት በድቁና ሲያገለግል ኖረ፡፡ ከዚህም በኋላ ሥጋውን ማድከም ቢሳነው ከእኩለ ቀን ጀምሮ ፀሐይ ስታቃጥል አለቱ ሲግል ጠብቆ ሄዶ አለቱ ላይ ይተኛል፣ ከግለቱም የተነሣ የሥጋው ቆዳ እስኪበስል ድረስ በአለቱ ላይ ይተኛል፡፡

አቡነ በጸሎተ ሚካኤልም ከዚህ በኋላ ቅስና ተሾመ፡፡ ወደ ዋሻም ገብቶ በዓቱን አጸና፡፡ ከምግባር ትሩፋቱ የተነሣ ሌሎች ቅዱሳን ሁሉ አቡነ በጸሎተ ሚካኤልን እንደ መልአክ ያዩት ነበር፡፡ እርሱም ከሰው ጋር ላለመገናኘት ብሎ በቁመቱ ልክ ጉድጓድ ቆፍሮ መጻሕፍቱን ብቻ ይዞ ከዚያ ገባ፡፡ ቅዱሳንም መጥተው ‹‹አንተንም ሌሎችንም የምትጠቅመው ከዚህ ጉድጓድ ውስጥተህ ብታስተምር ነው…›› እያሉ በብዙ ልመና ከጉድጓዱ አወጡት፡፡ ከዚህም በኋላ የተሰወረውን ሁሉ በግልጥ የሚያይ ሆነ፡፡ ብዙ አስደናቂ ተአምራትን እያደረገ ወንጌልን ያስተምራል፡፡ ወደ በዓቱም እየገባ በቀን 8ሺህ ስግደትን ይሰግዳል፡፡ ከስግደቱም ብዛት የተነሣ ምድሪቱ ጎድጉዳ እስከ ጉልበቱ ትውጠው ነበር፤ ከሰገደበትም ቦታ ወዙ መሬትን ጭቃ እስኪያደርጋት ድረስ እንደ ውኃ ይፈስ ነበር፡፡

ከመነኮሰበት ጊዜ ጀምሮ ተቀምጦ በእጁ ላይ አረፍ ይላል እንጂ በጎኑ ተኝቶ አያውቅም፡፡ #ጌታችንም ተገልጦለት ማደሪያው ከጴጥሮስና ከጳውሎስ ጋር መሆኑን ነግሮታል፡፡ አባታችን ወደተለያዩ ገዳማት በመሄድ የቅዱሳንን በረከት ተቀበለ፡፡ወደ ደብረ ዳሞ በመሄድ ከአቡነ አረጋዊ ጋር ተነጋገረ፣ ወደ አባ መጣዕ ቤት በመሄድ ከአባ ሊባኖስ ጋር ተነጋገረ፣ ወደ አባ ገብረ ናዝራዊ ገዳም በሄድም ከጻዲቁ ጋር ተነጋገረ፡፡ ከሰንበት በቀር እህል ባለመቅመስ 40 ቀንና 40 ሌሊት በመጾም ሱባኤ በያዘ ጊዜ #እግዚአብሔር የተለያዩ ምሥጢራትን ይገልጥለታል፡፡ በሄኖክ መጽሐፍ ላይ ተጽፎ ያለው የሰማይ ምሥጢር ሁሉ ተገለጠለት፡፡ የፀሐይ፣ የጨረቃ፣ የብርሃናት አፈጣጠራቸው፣ የንፋስ መስኮቶቸን ሁሉ በግልጥ ባየ ጊዜ ነቢዩ ሄኖክን ‹‹ሄኖክ ሆይ የራእይህ ምሥጢር እንደዚህ ብሩህ
ነውን? የምሥጢርህ መሰወር እንዲህ ግልጥ ነውን?›› ይለዋል፡፡ ዳግመኛም የነቢያት የትንቢታቸው ራእይ ይገለጥለት ዘንድ 40 ቀንና 40 ሌሊት በመጾም ሱባኤ በያዘ ጊዜ የመጻሕፍቶቻቸው ምሥጢር ይገለጥለታል፡፡

ከዚህም በኋላ አቡነ በጸሎተ ሚካኤል በመማለጃ (በጉቦ) ክህነት በሚሰጥ ጳጳስ ምክንያት በሐዋርያት ግዝት ዓለም ሁሉ በግዝት እንደሚኖር ተመለከተ፡፡ ወደ ጳጳሱ አባ ዮሐንስ ዘንድ ሄደና አገኘው፡፡ ጳጳሱም ‹‹ልጄ በጸሎተ ሚካኤል ደህና ነህን?›› አለው፡፡ አባታችንም ‹‹ደህና ነኝ›› ባለው ጊዜ ጳጳሱ ‹‹ስለምን መጣህ?›› አለው፡፡ አቡነ በጸሎተ ሚካኤልም ሰው ሁሉ ከአጠገባቸው እንዲርቅ ካደረገ በኋላ ጳጳሱን እንዲህ አለው፡- ‹‹ቅዱሳን ሐዋርያት በሲኖዶሳቸው መጽሐፍ ‹በመማለጃ ክህነትን የተቀበለና የሰጠ የተለየ የተወገዘ ነው› ያሉትን አልሰማህምን?›› አለው፡፡ ዳግመኛም ‹‹እጄን በጫንኩበት #መንፈስ_ቅዱስ ይወርድ ዘንድ ተናገሩ ብሎ በሐዋርያት እግር ሥር ወርቁን አምጥቶ ባፈሰሰው ጊዜ ሲሞን መሠርይን ጴጥሮስ እንዳወገዘው አልሰማህምን? ጴጥሮስም ‹ወርቅህና ብርህ ለጥፋት ይሁንህ፣ የ #እግዚአብሔር ጸጋ በወርቅ የምትገዛ ይመስልሃልን?› አለው፡፡ በመራራ መርዝ ተመርዘህ አይሃለሁና፡፡›› ሐዋ 8፡19፡፡ ‹‹አባቴ ሆይ የውኃ ምንጭ የፈሰሰ የደፈረሰ እንደሆነ የምፈሰውም ውኃ ሁሉ ይደፈርሳል፡፡ ምንጩ ንጹሕ ከሆነ ግን የውኃው ፈሳሽም ሁሉ የጠራ ይሆናል፡፡ አንተ በሐዋርያት ውግዘት ብትገባ ሁሉም የተወገዘ ይሆናል›› አለው፡፡ ጳጳሱም ተቆጥቶ ‹‹አንተ ከእኔ ተማር እንጂ ለእኔ መምህር ልትሆነኝ ትፈልጋለህ?›› በማለት ተናገረው፡፡ በወንጌል ላይ ‹‹እናንተ ግብዞች ጸሐፍትና ፈሪሳውያን መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምዘጉ ወዮላችሁ፣ እናንተ አትገቡም የሚገቡትንም ትከለክሏቸዋላችሁ›› ያለው የ #እግዚአብሔር ቃል በእርሱ ላይ ደረሰ፡፡ ማቴ 23፡14፡፡

ከዚህም በኋላ አቡነ በጸሎተ ሚካኤል ወደ ካህናተ ደብተራ በመሄድ ከንጉሡ ጋር ያገናኙት ዘንድ ጠየቃቸው፡፡ የቤተ መንግሥት ካህናትም ለንጉሡ ነግረውለት አስገቡት፡፡ አባታችንም ንጉሡን ‹‹መንግሥትህ በግዝት ጨለመች፣ ሐዋርያት ጥምቀትም ቢሆን ወይም ክህነት በመማለጃ (በጉቦ) የሚሰጥንና የሚቀበልን አስቀድመው ሐዋርያት አውግዘዋል›› አለው፡፡ ዳግመኛም ‹‹እነሆ ይህ ጳጳስ የሐዋርያትን ትእዛዝ ተላልፎ በጉቦ ክህነት ይሰጣል፣ ጳጳሱም በሐዋርያት ግዝት ከገባ በእጁ የተጠመቁና የተሾሙት ሁሉ የተወገዙ ይሆናሉ፣ እንደዚሁ ዓለሙ ሁሉ በውግዘት ውስጥ ይኖራል›› አሉው፡፡ ንጉሡም ሦስቱ አንድ ላይ ሆነው እንዲነጋገሩ ቀጠሮ ሰጠውና በሌላ ቀን ሦስቱም ተገናኙ፡፡ ጳጳሱም ለንጉሡ ‹‹ይህ በጸሎተ ሚካኤል እኔን ከሹመቴ አንተን ከመንግሥትህ ሊሽረን ይፈልጋል ስለዚህ ልጄ የምነግርህን ስማኝ አስረህ ወደ ትግራይ ይወስዱት ዘንድ እዘዝ›› አለው፡፡ ንጉሡም የጳጳሱት ክፉ የሀሰት ምክር በመስማት ‹‹ይሁን አንተ እንዳልከው ይሁን›› በማለት አቡነ በጸሎተ ሚካኤልን በጽኑ ማሠሪያ አስረው በግዞት ወደ ሳርድ ይወስዱት ዘንድ አዘዘ፡፡ ጭፍሮቹም እንደታዘዙት አደረጉና አባታችን በዚያ በግዞት ሁለት ዓመት ታስሮ ቆየ፡፡ ከዚያም ወደ ጽራይ ምድር ወሰዱትና ቆራር በተባለ ቦታ ለተሾመው ሰው ‹‹እንደ ንጉሡ ትእዛዝ ይህንን መነኩሴ እሰረው›› ብለው ሰጡት፡፡ የሀገሩ ሰዎችም አቡነ በጸሎተ ሚካኤልን እጅግ ወደዱትና ወደ ጽራር ሀገር ገዥ ሄደው እንዲፈታው ለምነው ከእስራቱ አስፈቱት፡፡ በሀገራቸውም ወንጌልን አስተምሮ ብዙ ተአምራት እያደረገላቸው ከቆየ በኋላ ወደ ልጁ ሳሙኤል ለመሄድ ተነሣ፡፡ ሲሄድም አቡነ ገብረ ናዝራዊ ጋር ደረሰና አብረው ሳሙኤል ጋር ደረሱ፡፡

አቡነ በጸሎተ ሚካኤል በቅዳሴ ጊዜ #ጌታችን በሕፃን ልጅ አምሳለ በመንበሩ ተቀምጦ ስለሚያየው ሁልጊዜ ሲቀድስ ያለቅሳል፡፡ አንድ ቀን አባታችንን ሲቀድስና ሕፃኑን በመንበሩ ላይ ሲሠዋው ወንድሞቹና ልጆቹ አይተውት በድንጋጤና በፍርሃት ሆነው አልቅሰዋል፡፡ የሕፃኑንም ሥጋ በፈተተው ጊዜ የአባታችን እጁ በለመለመ ሥጋ ይመላል፡፡ ቅዳሴውም ከተፈጸመ በኋላ ሁሉም መጥተው ቅዱስ_ሥጋና #ክቡር_ደሙን በፍርሃት ይቀበላሉ፡፡ ከእነርሱም ውስጥ አስቀድመው ስለ ሥጋወደሙ መለወጥ ጥርጣሬ የነበራቸው ሰዎች ስለነበሩ የእነርሱን ጥርጣሬ ዐውቆ አባታችን ቅዳሴውን ከፈጸመ በኋላ ‹‹ኅብስቱ የ #ክርስቶስ ሥጋ ወይኑም ደሙ መሆን ይችላልን እያላችሁ በልባችሁ ስታስቡ አይቻለሁና ይኸው ዛሬ በግልጽ እንዳያችሁት አማናዊ ሆኖ ይለወጣልና ተጠራጣሪ አትሁኑ›› ባላቸው ጊዜ እግሩ ሥር ወድቀው ‹‹አንተ ብፁዕ ነህ የተሸከመችህም ማኅፀን ብፅዕት ናት… ›› ብለው ይቅር እንዲላቸው ለመኑት፡፡ አባታችንም ወንጌልን አስተማራቸው፡፡ መነኮሳት ልጆቹ ሩቅ ቦታ እየሄዱ ውኃ በመቅዳት ቢቸገሩ ውኃን አፍልቆላቸዋል፡፡ ከዚህም በኋላ ሰዎቹ አንድ ነገር ልንነግርህ እንወዳለን አሉት፡፡ አቡነ በጸሎተ ሚካኤልም ንገሩኝ ባላቸው ጊዜ የአባቱን ሚስት ስላገባው ንጉሥ ነገሩትና ሄዶ እንዲያስተምረው እንዲገሠጸው ለመኑት፡፡ አባታችንም ‹‹በጽኑ ማሰሪያ ታስሬ በእስር ስለነበርሁ አልሰማሁም›› ካላቸው በኋላ ሄዶ ቢሰማው እንደሚመክረው ባይሰማውና ባይመለስ ግን እንደሚያወግዘው ነገራቸው፡፡ አባታችንም ልጆቹን አስከትሎ ወደ ንጉሡ ዘንድ ሄደ፡፡ አቡነ በጸሎተ ሚካኤል ‹‹ንጉሡ የአባቱን ሚስት በማግባቱ ሄደን ስንገሥጸው መከራ ቢያጸናብን ከሰማዕትነት ይቆጠርልናል›› ብሎ ሲነግራቸው ከሰማይ #መንፈስ_ቅዱስ ወርዶ በሁሉም በላያቸው ላይ ሲወርድ አባታችን በግልጽ ተመለከተ፡፡ በረኃብ በጥም ሆነው ከተጓዙ በኋላ ትግራይ ሰወን ከምትባል ሀገር ደረሱ ንጉሡ ከዚያ ነበረና፡፡ ንጉሡም ቅዱሳኑ መክረው ሊመልሱት ካልሆነም ሊያወግዙት መምጣታቸውን በሰማ ጊዜ ጭፍሮቹን ልኮ ቅዱሳኑን ወደ እርሱ እንዲያመጧቸው አዘዘ፡፡

ለማስፈራራትም ብዙ ጦረኛ ጭፍሮችንና የታሰሩ አስፈሪ አንበሶችን በፊቱ አቆመ፡፡ ቅዱሳኑንም ‹‹ስለምን ወደዚህ ከተማ መጥታችኋል?›› አላቸው፡፡ አቡነ በጸሎተ ሚካኤልም ‹‹እውነትን ስለማጽናት ከአንተ ጋር ለመነጋገር መጥተናል›› አሉት፡፡ ንጉሡም እሺ ንገሩን ባላቸው ጊዜ አባታችን የ #እግዚአብሔርን ትእዛዝ ስለጠበቁ ደጋግ ነገሥታት ከመጽሐፍ ቅዱስ በመጥቀስ ንጉሡን አስተማሩት፡፡

ትእዛዙንም ያልጠበቁትን አመፀኞችን እንደቀጣቸው ነገሩት፡፡ በመጨረሻም ‹‹የአባትህን ሚስት ሀፍረተ ሥጋ አትግለጥ፣ የአባትህ ሀፍረተ ሥጋ ነውና›› የሚለውን ኦሪት ዘሌ 18፡6 በመጥቀስ አስተማሩት፡፡ ዳግመኛም ‹‹ከአባቱ ሚስት ጋር የተኛ የአባቱን ሀፍረት ገልጧልና መሞትን ይሙት ሁለቱም በደለኞች ናቸውና›› የሚለውን የሙሴን ሕግና ሌላም ከሐዲስ ኪዳን እየጠቀሱ አስተማሩት፡፡ አባታችን ካስተማሩት በኋላም ‹‹የክርስቲያን ሚስቱ አንድ ብቻ ናት አንተ ግን ብዙ ሚስት አግብተህ የአባትህንም ሚስት አግብተሃልና ሕግ ተላልፈሃል›› አሉት፡፡ ንጉሡም ተምሮ ከመመለስ ይልቅ በታላቅ ቁጣ ሆኖ ቅዱሳኑን ይደበድቧቸው አዘዘ፡፡ ሲደብድቧቸውም ታላቅ ጩኸት ተነሣ፡፡ ለየብቻ አስረው ካሳደሯቸው በኋላ ንጉሡ ለየብቻ ወደ እርሱ እያስመጣ አናገራቸው፡፡ እያንዳንዳቸውንም በ7 ገራፊዎች በታላቅ ጅራፍ አስገረፋቸው፡፡ ደማቸውም እንደ ውኃ ምድር ላይ ፈሰሰ፡፡ ከደማቸውም እሳት ወጣና እስከ ሦስት ቀን ድረስ ወደላይ እየነደደ ቆየ፡፡ በዚህም ንጉሡ እጅግ ደንግጦ ብዙ ውኃ ከወንዝ እየቀዱ እሳቱን እንዲያጠፉ አዘዘ፡፡ የበዛ ውኃም ባፈሰሱበት ጊዜ የእሳቱ መጠን ይበልጥ ይጨምር ነበር፡፡
ዳግመኛም ብዙ ጨምረው ውኃ እየቀዱ ቢያፈሱበትም ማጥፋት እንዳልተቻላቸው ባየ ጊዜ ንጉሡ የወንዙን ውኃ በቦይ መልሰው እንዲያመጡ አዘዘ፡፡ ንግሥቲቱ ዛንመንገሣም ንጉሥ ዐምደ ጽዮንን ‹‹የ #እግዚአብሔርን ቁጣ አታስተውልምን›› ብላ ተናገረችው፡፡ ወዲያውም ነጭ የዝንብ መንጋ መጥቶ ⅝ ፈረሶችና በቅሎዎች ነከሳቸውና ሞቱ፡፡ ንጉሡም ፈርቶ በሌሊት ሸሽቶ ወጣ፡፡ ቅዱሳኑንም አንድ መውጫና መግቢያ ብቻ ባላት ደራ ወደምትባል ታላቅ ተራራ ቦታ አውጥተዋቸው እንዲያስሯቸው አደረገ፡፡

በዚያም የሚኖሩት አሕዛብ ስለሆኑ #ክርስቶስንም አያውቁም፣ ነፍሰ ገዳዮችም ነበሩ፡፡ ንጉሡም አቡነ በጸሎተ ሚካኤልንና ልጆቹን ይገድሏቸው ዘንድ ወደ እነርሱ መልእክት ይልክ ነበር፡፡ ነገር ግን አባታችን ወንጌልን ሰበከላቸውና አሳምኖ የ #ክርስቶስ ተከታዮች አደረጋቸው፡፡ እነርሱም ወደ ንጉሡ ሄደው ክርስቲያን እንደሆኑ ነገሩት፡፡

የአባታችን የተአምሩ ዜና በሀገሩ ሁሉ በተነገረ ጊዜ ንጉሡ ቅዱሳንን አሳደው ስሙ ዝዋይ ወደሚባል ታላቅ ባሕር ውስጥ ያገቧቸው ዘንድ አዘዘ፡፡ አባታችንና ልጆቹንም አረማዊያን ወዳሉበት ደሴት አስገቧቸው፡፡ ከብዙ ጊዜም በኋላ ከግዞት መልሰው በማውጣት በሴዋ አውራጃ እንዲያስተምሩ ፈቀደላቸው፡፡ ንጉሡም ናርእት የሚባሉ ሰዎችን በጦር ይወጋቸው ዘንድ ተነሣ፡፡ እነዚህም ሰዎች አስቀድመው በአቡነ በጸሎተ ሚካኤል ስብከት በ #ጌታችን ያመኑ ክርስቲያኖች ሆነዋል፡፡ ንጉሡም ድጋሚ አባታችንን አሠራቸውና ማስፈራራት ጀመረ፡፡ አቡነ በጸሎተ ሚካኤል ግን የንጉሡን ማስፈራራት በመናቅ ተናገሩት፡፡ እንዲህም አሉት፡- ‹‹በጦር ብታስወጋኝ ሕዝቅኤልን አስበዋለሁ፤ አንበሶች እንዲበሉኝ ብታዝ ዳንኤልን አስበዋለሁ፤ ወደ እሳት ውስጥ ብትጥለኝ አናንያን አዛርያንና ሚሳኤልን አስባቸዋለሁ፤ በእንጨት መቁረጫ መጋዝ እንዲቆርጡኝ ብታዝ ኢሳይያስን አስበዋለሁ፤ በድንጋይ እንዲወግሩኝ ብታዝ ኤርሚያስን አስበዋለሁ፤ በሰይፍ አንገቴንም እንቆርጡኝ ብታዝ በወንደሙ ፊሊጶስ ሚስት ምክንያት የገደለው የዘካርያስ ልጅ ዮሐንስ መጥምቅን አስበዋለሁ፤ ልዩ ልዩ መከራዎችን ብታጸናብኝም መከራ የተቀበሉትን ሐዋርያትንና ሰማዕታትን አስባቸዋለሁ›› ብለው ለንጉሡ መለሱለት፡፡ ንጉሡም ከዚህ በኋላ አባታችንን ‹‹ይቅር ይበሉኝ›› አላቸው፡፡ በአባታችን ምክር ብዙ የንጉሡ መኳንንቶችም ክፉ ሥራቸውን በመተው በ #ንስሓ ተመለሱ፡፡ ንጉሡም አንዲት ሚስቱን ለጭፍራው አሳልፎ ሰጥቶት ነበርና እርሷም አባታችንን ስታገኛቸው #ንስሓ ገባች፡፡ ንጉሡም ይህቺ የተዋት ሚስቱ #ንስሓ እንደገባች ሲሰማ ‹‹ዛሬ ሌሊት ከእርሷ ጋር ተኝቼ #ንስሓዋን አስተዋታልሁና ይዛችሁ አምጡልኝ›› ብሎ ጭፍሮቹን ላከ፡፡ አባታችንም ሴቲቱን በ #ንስሓዋ ወደዋት ነበርና አሁን ንጉሡ በእርሷ ላይ ሊያደርግ ያሰበውን ልጆቹ ነገሩት፡፡ አባታችንም ይህን ሲሰማ የቀረበውን ማዕድ ሳይቀምሱ አስነስቶ ሁሉም እንዲጸልዩ አዘዘና እርሱም ቆሞ መጸለይ ጀመረ፡፡ በዚያችም ሌሊት ወዲያው ንጉሡ ድንገት በጠና ታመመ፡፡ ያንጊዜም ንጉሡ ‹‹ይህ ድንገተኛ ሕመም የመጣብኝ አቡነ በበጸሎተ ሚካኤል ጸሎት ነው›› ብሎ ያችን ሴት ካመጡበት ቦታ እንዲመልሷት አዘዘ፡፡ ወደ አባታችንም ‹‹አባቴ ሆይ! ይቅር በለኝ፣ ይህ ሕመም ያገኘኝ በአንተ የተማጸነችውንና #ንስሐ የገባችውን ሴት በኃጢአት ላረክሳት ስላሰብኩ ነው፤ አሁንም ልጅቷን ወደነበረችብ መልሻታሁና አባቴ ሆይ ከዚህ በሽታዬ ከዳንኩ በሕግህ እኖራለሁ›› ብሎ መልእክተኛ ላከ፡፡ አባታችንም የቤተ መንግሥቱን ካህናተ ደብራዎች ወቀሳቸው፡፡ ‹‹ከእናንተ በቀር ይህን ንጉሥ የሚያስተው የለም ያለ ሥራው እያሞገሳችሁ በኃጢአት ላይ ኃጢአት እንዲሠራ የምታድርጉ እናንተ ናችሁ›› ብለው በተናገሯቸው ጊዜ ደብተራዎቹም ‹‹እኛም በሕግህ እንኖራለን ይቅር በለን፣ ጉሡንም ይቅር ብለህ ከመጣበት ደዌው ፈውሰው›› ብለው ለመኗቸው፡፡ አቡነ በጸሎተ ሚካኤልም ‹‹ንጉሡ ከኃጢአቱ ተመልሶ #ንስሓ እንደማይገባ እኔ ዐውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ሞቱ በእኔ ቃል ምክንያት እንዳይሆን #እግዚአብሔር ከበሽታው ይፈውሰው›› አሏቸው፡፡ ካህናቱም ‹‹ከደዌው በሚድን ነገር እንወስድለት ዘንድ የእግርህን ትቢያ ስጠን›› አሏቸው፡፡ አባታችንም ‹‹የእግሬን ትቢያ አልሰጣችሁም ነገር ግን ሂዱ ከደዌው ሁሉ ተፈውሶ ታገኙታላችሁ›› አሏቸው፡፡ ካህናቱም ወደ ቤተ መንግሥት በሄዱ ጊዜ ንጉሡን ከደዌው ፍጹም ተፈውሶ አገኙት፡፡ አንዲት ድንግል መነኩሲት ከክብር ያሳነሳት ርጉም የሆነ አንድን መነኩሴ አገኙትና አባታችን መክረው ገሥረው #ንስሓ ግባ አሉት፡፡ ነገር ግን እርሱ በወቅቱ እሺ ብሎ #ንስሓ ሳይገባ ቀረ እንዲያውም በአባታችን ላይ ክፉ ያስበ ጀመር፡፡

እንዲሁም ክህነት ሳይኖረው በውሸት ካህን ነኝ እያለ ሲቀድስ የነበረን አንዲን ዲያቆን አባታችን አግኝተው ‹‹የ #ክርስቶስን ሥጋ ቅዱሳን መላእክትስ እንኳን መንካት የማይቻላቸውን አንተ በውሸት ለመንካት እንዴት ደፈርክ….›› ብለው በመምከር #ንስሓ እንዲገባ አዘዙት፡፡ ነገር እነዚህ ሁለት ክፉ ሰዎች #ንስሓ ከመግባት ይልቅ በአባታችን ላይ ክፋትን ያስቡ ጀመር፡፡ ወደ ንጉሡም ዘንድ ሄደው ‹‹በጸሎተ ሚካኤል የሚባለው መነኩሴ ‹ፈርዖንና ሠራዊቱን በባሕር ያሰጠመው እንደዚሁ ሁሉ ይህንንም ንጉሥ ያስጥመው› እያለ ይረግምሃል›› ብለው አወሩለት፡፡ ንጉሡም ተቆጥቶ አባታችንን ከነልጆቻቸው አስረው ያመጧቸው ዘንድ አዘዘ፡፡ አስረው አምጥተውም በንጉሡ ፊት ኦቆሟቸው፡፡ ንጉሠም አባታችንን ‹‹ለምን ትረግመኛለህ›› ሲላቸው እሳቸውም ‹‹ጠላትህን ውደድ ያለንን የአምላክ ሕግ እንከተላለን እንጂ አንተንስ የረገመህ የለም፤ ጳውሎስም በምንኩስና ሥርዓት ሰይጣንንም እንኳ አትርገሙ ብሏል፡፡ ሰይጣንን እንኳ መርገም የሚከለክል ከሆነ ንጉሥን እንዴት ይረግሙታል›› አሉት፡፡ ንጉሡም የከሰሱትን ሁለቱን ሰዎች አምጥቶ ለአባታችን አሳቸው፡፡ እሳቸውም የእያንዳንዳቸውን ክፉ ሥራ ለንጉሡ ነገሩት፡፡ ንጉሡም ይርታ ጠይቆ አባታችንን በሰላም አሰናበታቸው፡፡

ከዚህ በኋላ ጠላት ዲያብሎስ በቅዱሳን ላይ ክፉ ሥራ ይሠራ ዘንድ በንጉሡ ልብ ክፉ ሀሳብን አስነሣ፡፡ ንጉሡም ‹‹እኔ በምገዛው አገር ሁሉ ያሉ ቅዱሳንን አምጧቸው›› ብሎ በሕዘቡ ሁሉ ትእዛዝ አስተላለፈ፡፡ ቅዱሳንንም ሁሉ ሰብስበው አመጧቸው፡፡ አቡነ ዘአማኑኤል ከልጆቹና ከአባታችን ከአቡነ በጸሎተ ሚካኤል ጋር ደረሰ፡፡ ንጉሡም በቁርባንና በጸሎት ከእኔ ጋር ተባበሩ (አንድ ሁኑ) የምትፈልጉትን ሁሉ አሟላላችኋለሁ፣ ከእኔ ጋር መተባበርን እምቢ ካላችሁ ግን ወደ እርሱ እሰዳችሁ ዘንድ ሊቀ ጳጳሱ አዘዋልና ወደ ግብጽ በረኃብና በጥም ትሄዳላችሁ በመንገድም ሰውን የሚገድሉ ሽፍቶች አሉ›› አላቸው፡፡ የአቡነ ዘአማኑኤል ደቀ መዛሙርት ግን ‹‹እኛ ከአንተ ጋር እንተባበራለን፣ ያዘዝከንን ሁሉ እንፈጽማለን›› ብለውት የሚሹትን ሁሉ ሰጥቷቸው በሰላም አሰናበታቸው፡፡

መምህራቸው አቡነ ዘአማኑኤል ግን ይህን አልፈልግም ብሎ ብቻውን ተሰደደ፡፡ ንጉሡም ወደ አቡነ በጸሎተ ሚካኤል መኳንንቱን በመላክ ከእርሱ ጋር እንዲተባበሩ ወርቅና ብሩን ላሞችንና ጥሪቶችን ሁሉ እንደሚሰጣቸው ካልሆነ ግን ወደ ኢሩሳሌም መንገድ እንደሚልካቸውና በመንገድም በሽፍቶች እንደሚገደሉ ነገራቸው፡፡ አባታችንም ‹‹ወርቅህና ብርህ ጥሪትህም ሁሉ ከአንተ ጋራ ለጥፋት ይሁንህ›› ብለው መለሱለት፡፡ ከልጆቹም ጋር አባታችንን በግዳጅ ወደ ንጉሡ ዘንድ ሲወስዷቸው የንጉሡን ምግብ እንዳይቀምሱ ተማምለው አንደኛው መነኩሴ የገንዘባቸው የገዙትን ጎመን
ተሸክሞ አብሯቸው ሄደ፡፡ ንጉሡም ባየው ጊዜ በጽኑ ጅራፍ እያስገረፈው እያለ ሕይወቱ በዚያው አለፈች፡፡ ከዚህም በኋላ ንጉሡ በግዞት ወደ አረማውያን መኖሪያ እየነዱ እንዲወስዷቸው አዘዘ፡፡

ወደ ግሎ ማክዳ ምድር እንዳደረሱት በዚያ ያሉ ቅዱሳን በደስታ ተቀበሉት፡፡ ስማቸውም ማርቆ፣ ክርስቶስ አምነ፣ አባ ሲኖዳና ማማስ ናቸው፡፡ ማማስም ለአባታችን ለጸሎት የሚሆነውን የድንጋይ ዋሻ አሳየው፡፡ አባታችንም ‹‹ይህች ዋሻ ለዘላለም ማረፊያዬ ናት›› ብሎ ውስጧን በድንጋይ ይወቅር ጀመር፡፡ በውስጧም አገልገሎቱን ፈጸመ፡፡ ወደ ቅዱሳኑ ወደ እነ አባ ማርቆስ፣ ክርስቶስ አምነ እና ሲኖዳ መጥተው የመቃብር ጉድጓድ እንዲቆፍሩ መልአክት ላከባቸው፡፡ በቀዳሚት ሰንበት ዕለትም ደቀ መዝሙሩ ዕንባቆም በአገኘውና ‹‹ነገ አባትህን ወደ መቃብር ትጥለዋለህ›› አለው፡፡

በማግሥቱም እሁድ ቀን ደቀ መዛሙርቱን ሁሉ ሲመክራቸው ዋለ፡፡ በመጨረሻም አንዱን ደቀ መዝሙሩን ብቻ አስከትሎ ወደ ዋሻዋ ግቶ በ4ቱም ማዕዘን ባረካት፡፡ ከዚህም በኋላ እጁንና እግሩን ዘርግቶ ነፍሱን በፈጣሪው እጅ አስረከበ፡፡ ነቢዩ ‹‹የጻዲቅ ሰው ሞቱ በ #እግዚአብሔር ፊት ክቡር ነው›› እንዳለ ያለ ምንም ጻዕር ዐረፈ፡፡ መዝ 115፡6፡፡

ደቀ መዛሙርቱም በመጡ ጊዜ ዐርፎ አገኙት፡፡ እነርሱም መሬት ላይ ወድቀው ‹‹አባት እንደሌላቸው እን ሙት ልጆች ለማን ትተወናለህ፣ በስውር የሠራነው ኃጢአትስ ማን ይነግረናል….›› እያሉ ጽኑ ልቅሶን አለቀሱ፡፡ አስቀደሞም እርሱ ደቀ መዛሙርቱ በስውር የሚሠሩትን ሥራ ሁሉ እርሱ በግልጽ እያየ ‹‹አንተ ይህን ሠርተሃልና #ንስሓ ግባ›› እያለ ይመክራቸው ነበርና፡፡ ልቅሶአቸውንም ከፈጸሙ በኋላ ራሱ በጠረባት የድንጋይ ዋሻ ውስጥ ቀበሩት፡፡ የሀገሪቱም ሰዎች ክፉዎች ናቸውና ከጊዜም በኋላ ደቀ መዛመርቱ የአባታችች ዐፅሙን አፍልሰው ወደ ሌላ ቦታ አስቀመጡት፡፡ እስከ ኢትዮጵያ ጳጳስ አባ ያዕቆብ መምጣት ድረስ ደብቀው አኖሩት፡፡ አባ ያዕቆብም የአባታችንን ዐፅም ያመጡለት ዘንድ አዘዘቸው፡፡ ከጊዜም በኋላ ዐፅሙን ወደ ጋስጫ አፍልሰውታል፡፡ ይኸውም ጋስጫ ከሊቁ አባታችን ከአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም ሥር የሚገኝ ነው፡፡ ዋሻ ቤተ መቅደሱም በግሩም አሠራር የተሠራ ነው፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጻድቁ አቡነ በጸሎተ ሚካኤል ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
2025/10/21 07:55:06
Back to Top
HTML Embed Code: