Telegram Web Link
🌹#የጥቅምት_7_ግጻዌ🌹

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_7_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2ኛ ቆሮ 11
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²³ እንደ እብድ ሰው እላለሁ፤ እኔ እበልጣለሁ፤ በድካም አብዝቼ፥ በመገረፍ አብዝቼ፥ በመታሰር አትርፌ፥ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ።
²⁴ አይሁድ አንድ ሲጎድል አርባ ግርፋት አምስት ጊዜ ገረፉኝ።
²⁵ ሦስት ጊዜ በበትር ተመታሁ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወገርሁ፤ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረ፤ ሌሊትና ቀን በባሕር ውስጥ ኖርሁ።
²⁶ ብዙ ጊዜ በመንገድ ሄድሁ፤ በወንዝ ፍርሃት፥ በወንበዴዎች ፍርሃት፥ በወገኔ በኩል ፍርሃት፥ በአሕዛብ በኩል ፍርሃት፥ በከተማ ፍርሃት፥ በምድረ በዳ ፍርሃት፥ በባሕር ፍርሃት፥ በውሸተኞች ወንድሞች በኩል ፍርሃት ነበረብኝ፤
²⁷ በድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት፥ በራብና በጥም ብዙ ጊዜም በመጦም፥ በብርድና በራቁትነት ነበርሁ።
²⁸ የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር፥ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው።
²⁹ የሚደክም ማን ነው፥ እኔም አልደክምምን? የሚሰናከል ማን ነው፥ እኔም አልናደድምን?
³⁰ ትምክህት የሚያስፈልግ ከሆነ፥ ከድካሜ በሚሆነው ነገር እመካለሁ።
³¹ ለዘላለም የተባረከ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት እንዳልዋሽ ያውቃል።
³² በደማስቆ አርስጦስዮስ ከተባለ ንጉሥ በታች የሆነ የሕዝብ ገዥ ሊይዘኝ እየወደደ የደማስቆ ሰዎችን ከተማ ያስጠብቅ ነበር፥
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ያዕቆብ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና።
¹³ ማንም ሲፈተን፦ በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም።
¹⁴ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል።
¹⁵ ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች።
¹⁶ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ አትሳቱ።
¹⁷ በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፥ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 21
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² ይህንም በሰማን ጊዜ እኛም በዚያ የሚኖሩትም ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ ለመንነው።
¹³ ጳውሎስ ግን መልሶ፦ እያለቀሳችሁ ልቤንም እየሰበራችሁ ምን ማድረጋችሁ ነው? እኔ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞት እንኳ ተሰናድቼአለሁ እንጂ ለእስራት ብቻ አይደለም አለ።
¹⁴ ምክርንም ሊቀበል እምቢ ባለ ጊዜ፦ የጌታ ፈቃድ ይሁን ብለን ዝም አልን።
¹⁵ ከዚህም ቀን በኋላ ተዘጋጅተን ወደ ኢየሩሳሌም ወጣን።
¹⁶ በቂሣርያም ከነበሩ ደቀ መዛሙርት አንዳንዶች ደግሞ ከእኛ ጋር መጡ፥ እነርሱም ወደምናድርበት ወደ ቀደመው ደቀ መዝሙር ወደ ቆጵሮሱ ምናሶን ወደሚሉት ቤት መሩን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_7_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ጸርሑ ጻድቃን ወእግዚአብሔር ሰምዖሙ። ወእምኵሉ ምንዳቤሆሙ አድኅኖሙ። ቅሩብ እግዚአብሔር ለየዋሃነ ልብ"። መዝ 33፥17-18።

#ትርጉም፦ "ጻድቃን ጮኹ፥ #እግዚአብሔርም ሰማቸው ከመከራቸውም ሁሉ አዳናቸው። #እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፥ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል"። መዝ 33፥17-18።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_7_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 19
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁵ ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው እጅግ ተገረሙና፦ እንኪያስ ማን ሊድን ይችላል? አሉ።
²⁶ ጌታችን ኢየሱስም እነርሱን ተመልክቶ፦ ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል አላቸው።
²⁷ በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ፦ እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፤ እንኪያስ ምን እናገኝ ይሆን? አለው።
²⁸ ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ እውነት እላችኋለሁ፥ እናንተስ የተከተላችሁኝ፥ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ፥ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ።
²⁹ ስለ ስሜም ቤቶችን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል የዘላለምንም ሕይወት ይወርሳል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
🌹
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ሠለስቱ_ምዕት_ቅዳሴ ነው። መልካም የአባ ባውላ የዕረፍት በዓልና የጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።
🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ንስሐ_እግዚአብሔር_የሰውን_ኃጢያት_ይቅር_የሚልበትና_ከኃጢያት_ውጤት_የሚያድንበት_መሣሪያ_ነው!

የሰው ኃጢያት ቢበዛም #እግዚአብሔር ፈቃዱ ሰው ሁሉ ከሞተ ነፍስ እንዲድን ነው። ከልዑል መንበሩ ስቦ ሰው ያደረገው-- የሰውን ባሕርይ ገንዘብ አድርጎ በመሞት ሞትን ለማጥፋት ያስወሰነው ለሰው ያለው ፍቅር ነው። ከዚህ ታላቅ ፍቅሩ የተነሣ ለሰው ድኅነት #ንስሐን ሰጠ። ስለዚህ ነው #ንስሐ_እግዚአብሔር በኃጢያት የወደቁ ሰዎችን ከኃጢያታቸው ለማንጻት፣ ያጡትን ውስጣዊ ሰላም ለመስጠትና በኃጢያት ምክንያት ወደ አጡት የቀደመ ክብራቸው እንዲመለሱ የተሰጠ አምላካዊ ጸጋ ነው የተባለው።

#ይቀጥላል.....
"መለወጥ የምትፈልግ ነፍስን በተመለከተ አባ ዮሐንስ እንዲህ አለ፦ በአንዲት ከተማ ውስጥ ብዙ ወዳጆች የነበሯት አንዲት አመንዝራ ሴት ነበረች። ከገዢዎች አንዱ ቀረባትና "መልካም ሴት ለመሆን ቃል ጊቢልኝና አገባሻለሁ" አላት። እርሷም ቃል ገባችለትና ተጋቡ። ወደ ቤቱም ወሰዳት። የቀድሞ አፍቃሪዎቿ ያቺን ሴት ፈለጓት፤ እርስ በእርሳቸውም "ያ ልዑል ወደ ቤቱ ወስዷታል፤ ወደ ቤቱ ብንሄድ ይቀጣናል። ነገር ግን በጓሮ በኩል እንሂድ ለእሷም እናፏጭላት የፉጨቱን ድምፅ ስትሰማ ከደርቡ ወርዳ ወደኛ ትመጣለች፣ በዚህም ያለ ችግር እናገኛታለን" ተባባሉ። ወደ ቤቷም ጓሮ ተጉዘው ያፏጩ ጀመር። እርሷ ግን የፉጨቱን ድምፅ ስትሰማ ጆሮዎቿን ደፈነች። ወደ ውስጣዊው እልፍኝም ገባች። በሩንም ጥርቅም አድርጋ ዘጋች።

➣ ይህቺ ሴት የእኛ የነፍስ ምሳሌ ናት፣
➣ ወደ እልፍኙ የተባለው ዘለዓለማዊ ቤት ነው፣
➣ እነዚያ የሚያፏጩት ክፉዎች አጋንንት ናቸው፣ ነገር ግን ነፍስ ሁልጊዜም በ #ክርስቶስ አምባነት ትሸሸጋቸዋለች።

#ቅዱስ_ዮሐንስ_ሐጺር
#ለእራኃቲክሙ

#አብ_ወልድ_መንፈስ_ቅዱስ_ሆይ ዓለምን እንደ እንቁላል ለያዘ መለኮታዊ መዳፋችሁ ሰላምታ ይገባል።

#ሥሉስ_ቅዱስ_ሆይ ቅድመ ዓለም የነበራችሁ ዛሬም ያላችሁ ለዘለዓለሙም በአንድነት በሦስትነት ጸንታችሁ የምትኖሩ፤ እናንተ ብቻ ናችሁና። ኤልያስ ከእርሻ የአንዱን ትልም የሚያረካ ዝናምን ለማዝነም ቢከለከለኝም እንኳ እናንተ ግን በልቡናዬ እርሻ ላይ ሰላም ዝናማችሁን አዝንሙልኝ።

#መልክዐ_ቅድስት_ሥላሴ
#የሥላሴ የሐዲስ ሥርዓት ዘመን ከመመስረቱ በፊት በብሉይ ዘመን ሕግ የታወቀ ነው።

ስለዚህ ከነብያት ወገን የፈጠረህና ያጸናህም እሱ #አብ ነው ሲሉ የተናገሩ አሉ።

ስለ #ወልድም ሕፃን ተወለደልን ወልድም ለኩነተ ሥጋ ተሰጠልን በማለት የተናገሩ አሉ።

ዳግመኛም ለ #መንፈስ_ቅዱስ #መንፈስ_ቅዱስ በጽድቅ ጎዳና ይምራኝ ሲሉ የተናገሩ አሉ።

እነሆ የ #ሥላሴ ስም ቅድመ ዓለም እንደነበረና እስከ ዘለዓለም የሚኖር መሆኑ ታወቀ ተረዳ።
👍2
"ከቤተ ክርስቲያን የሚበልጥ ብርቱ (ጠንካራ) ምንም የለም። ይህችውም ከሰማይ ከፍ ያለች ከምድርም ይልቅ የሰፋች ናት። አታረጅም ነገር ግን ዘወትር ታበራለች።"…

"ቤተ ክርስቲያን በዘመናት ሁሉ ትሰፋለች። መታሰቢያዋም የሚጠፋ (የሚሞት) አይደለም።"…

"ቤተ ክርስቲያን በስንቶች ውጊያ ተደርጎባት ነበር? አልተሸነፈችም እንጂ። የተዋጓት አላውያን፣ የጦር መሪዎች፣ ነገሥታቱስ ምን ያህል ናቸው? የተማሩና ኃይልን የተሞሉ ጎበዞች ሐዲሲቷን ቤተ ክርስቲያን በብዙ ጎዳናዎች ተዋግተዋት ነበር። ሊነቅሏት ግን አልቻሉም። ነገር ግን እርሷን የተዋጉ ጥቂቶች ለዝምታና ቶሎም ለመረሳት ተላልፈው ተሰጥተዋል። የወጓት ቤተ ክርስቲያን ግን ከሰማይ በላይ ከፍ ከፍ ብላለች። ቤተ ክርስቲያንን ድል ከማድረግስ ፀሐይን ማጥፋት (ማጨለም) ይቀላል። ሰው ሆይ! ከቤተ ክርስቲያን የሚበልጥ ኃያል ምንም የለም። ከሰው ብትጣላ ወይ ታሸንፋለህ አልያም ትሸነፋለህ። ቤተ ክርቲያንን ግን ብትጣላ፣ ታሸነፍ ዘንድ የሚቻልህ አይደለም። እግዚአብሔር ከሁሉ ይልቅ ኃያል ነውና። እግዚአብሔር መስርቷታል፣ እንግዲህ ማን ሊነቀንቃት ይችላል? "

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
(በዲያቆን አቤል ካሳሁን የተተረጎመ)
እመቤቴ የተመረጥሽ ድንግል ማርያም ሆይ በዕብራይስጥ ማሪሃም የተባልሽ አምላክ ካንቺ ጋራ በመሰደዱ በግብፅ መከራሽ እማልድሻለሁ፡፡ መንገድ በመሄድ የድካምሽ አሳብ በልጅሽ ፊት ይቁም ስለ ኃጢአቴ መማለጃ ይሆን ዘንድ፡፡

በምድረ ግብፅ ያገኘሽ የረኃብና የጽምዕ ሐሳብ በበኩር ልጅሽ ፊት ይቁም ስለ ኃጢአቴ ማቃለያ ይሆን ዘንድ፡፡ ካይንሽ የፈሰሰው የዕንባ ጎርፍ በፊትሽ የተንጠባጠበው በልጅሽ በወዳጀሽ ፊትም የወረደው፡፡ አሁንም ደግሞ በልጅሽ በወዳጅሽ ፊት ይቁም ስለ ኃጢአቴ ማዘከሪያ ይሆን ዘንድ፡፡

የሠራሁትን ኃጢአት ባስበው ልቡናዬ እጅግ ደነገጠብኝ፡፡ አእምሮ ሳለኝ አለል ዘለል እያልኩ በጽርዓት መኖሬን ባሰብሁት ጊዜ ልቡናዬ እጅግ ደነገጠ፡፡ የኃጢአቴን ብዛት በተቆጣጠርሁ ጊዜ ልቡናዬ እጅግ ደነገጠ አንድ ሰዓት ስንኳን ኃጢአት ለመስራት አላቋረጥኩም፡፡

በሰውና መላእክት ጉባኤ መካከል ራቁቴን መቆሜን አሰብሁ፡፡ በዓይነ ልቡናዬ እመለከት ዘንድ ወዲህና ወዲያ ተመላለስሁ፡፡ ምናልባት የሚረዳኝ ባገኝ፡፡ ከዚህ እጅግ የሚያስፈራው ከሠራሁት ኃጢአት ፍዳ የተነሣ ምናልባት የሚዋሰኝ ባገኝ ብዬ፡፡ ነገር ግን በማማለድ እኔን ለማዳን የምትቸይውን አንቺን አማላጅ አገኘሁ፡፡ ዘወትርም ከኔ እንዳትርቂ ዐወቅሁ፡፡

እንዲህ በፍቅር ያዝሁሽ በጣቶቼ አይደለም በሃይማኖት ያዝሁሽ በመዳሰስ አይደለም በእደ ሕሊና ያዝሁሽ በእደ ሥጋ አይደለም፡፡ እደ ሕሊናየን ግን የሰው ኃይለኝነት ሊያስተወው አይችልምና፡፡ የሰይፍ ስለትም ሊቆርጠው አይችልም፡፡

ልትደገፊኝ ያዝሁሽ ልትጥይኝ ግን አይደለም ወደ ላይ ከፍ ከፍ ልታደርጊኝ ያዝሁሽ ወደ ታች ልታወርጅኝ ግን አይደለም፡፡ ለዘለዓለሙ ያዝሁሽ ለዕድሜ ልክ ብቻ አይደለም፡፡ እናቴ ሆይ ነፍሴ ባንቺ ዘንድ ትክበር ስለቸርነትሽም እመቤቴ ነሽ፡፡ ስለ ፍቅርሽ የታመንሽ ስለ ልጅሽም የመድኃኒት ቀንድ ሆይ አስቢኝ እንደ ወደቅሁም እቀር ዘንድ አትርሺኝ፡፡

(በአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ - የማክሰኞ አርጋኖን)
ትንሿ ቤተክርስቲያን በኦርቶዶክሳዊ ቤተሰብ

ባለትዳሮች በቤታቸው ውስጥ ማድረግ ያለባቸው ቤተ ክርስቲያን መጥተው ያዩትን ነው፡፡ ለምሳሌ፦

👉 ቤተክርስቲያን ውስጥ የጠዋትና የሰርክ ጸሎት እንዳለ ኹሉ እነዚህ ባለ ትዳሮችም የጠዋትና የሰርክ ጸሎት በቤታቸው ውስጥ ሊኖራቸው ይገባል፡፡

👉 በቤተክርስቲያን ያለው የኅብረትና የአንድነት ጸሎት እንደ ኾነ ኹሉ፥ ባልና ሚስት ልጆችም ሳይለያዩ አብረው መጸለይ አለባቸው፡፡

👉 በቤተክርስቲያን ውስጥ ከቅዳሴ በኋላ ትምህርተ ወንጌል እንዳለ ኹሉ፥ ባልና ሚስትም እራት ከበሉ በኋላ ቃለ እግዚአብሔር ሊማማሩ ይገባቸዋል፡፡

👉 በቤተክርስቲያን ውስጥ ራሳቸውን ገዝተው የሚኖሩ ትጉሃን መነኰሳት እንዳሉ ኹሉ፥ ባልና ሚስትም ይህን ትግሃትና ምስጋና ወደ ቤታቸው ይዘዉት ሊኼዱ ይገባቸዋል፡፡

👉 ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማታ ላይ ኅብስቱን አበርክቶ ሕዝቡን ከመገባቸው በኋላ ወዲያው ወደ መኝታ እንዲኼዱ እንዳላደረገ ኹሉ፥ ባልና ሚስትም ወደ መኝታቸው ከመኼዳቸው በፊት የቀን ውሎአቸውን መገምገም አለባቸው፡፡

👉 ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሌሊት ሌሊት ሲጸልይ ያድር እንደ ነበረ ኹሉ፥ ባልና ሚስትም ሌሊት ላይ ነቅተው መጸለይ ይገባቸዋል፡፡ ሕፃናት ካሉም አብረዋቸው እንዲነሡ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡

👉 በቤተክርስቲያን ጾም እንደሚታወጅ ኹሉ፥ ባልና ሚስትም በቤተ ክርስቲያን ከሚታወጀው ጾም በተጨማሪ ከንስሐ አባቶቻቸው ጋር ተመካክረው በፈቃዳቸው ሊጾሙ ይገባቸዋል፡፡

👉 በቤተክርስቲያን ውስጥ እንዳለው፥ ባልና ሚስትም የቤታቸውን ግድግዳ፣ መስኮትና በር በመስቀል ሊያስጌጡት ይገባቸዋል፡፡ ማማተብ በማይችሉ ልጆቻቸው ግንባርም አድገው ራሳቸው ማማተብ እስኪችሉ ድረስ እነርሱ ያማትቡላቸው፡፡ ቅዱሳት ሥዕላትም በቤታቸው ውስጥ ሊኖሩ ይገባል፡፡

ቤታቸው ትንሿ ቤተ ክርስቲያን የምትኾነው በዚህ መንገድ ነው፡፡

(ኦርቶዶክሳዊ ቤተሰብ በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ገጽ 60 - 61)
#ጥቅምት_8

#አንድ_አምላክ_በሆነ_በአብ_በወልድ_በመንፈስ_ቅዱስ ስም
ጥቅምት ስምንት በዚች ቀን ታላቁ አባት #አባ_አጋቶን መታሰቢያው ነው፣ ሽማግሌው #አባ_መጥራ በሰማዕትነት አረፈ፣ በላይኛው ግብጽ ከሚኖሩ ሰዎች ወገን የሆነ ቅዱስ አባት #አባ_ሖር መታሰቢያው ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_አጋቶን_ባህታዊ

ዳግመኛም በዚህ ቀን ታላቁ አባት አባ አጋቶን መታሰቢያው ነው፡፡ ይህን ቅዱስ ታላቅ ጻድቅ ገዳማዊና የ #እግዚአብሔር ሰው ሲሆን አንደበቱን ከክፋት ይከለክል ዘንድ ለ30 ዓመታት ድንጋይ ጐርሶ ኖሯል። ይህንን ቅዱስ ሊቃውንት ሲገልጹት "ክምረ ክምር ጽድቁ እስከ አስተርአየ" ይሉታል። ትእግስቱ ደግነቱ አርምሞው ትሩፋቱ ከመነገር በላይ ነው። በነበረበት በ4ኛው መቶ ክ/ዘመንም እንደ ኮከብ ያበራ ታላቅ አባት ነው።

ታላቁ ገዳማዊ አባት አጋቶን የታላቁ መቃርዮስ የመንፈስ ልጅ ነው። ገዳመ አስቄጥስ እልፍ አእላፍ ቅዱሳንን ስታፈራ ይህ አባት ቅድሚያውን ይይዛል። ምንም በብዛት የሚታወቀው በአርምሞው (በዝምታው) ቢሆንም ባለ ብዙ ትሩፋት አባት ነው። የሚገርመው የቀደሙ አባቶቻችን የፈለገውን ያህል መናኝ ቢሆኑም የሰው ጥገኛ መሆንን አይፈልጉም። "ሊሠራ የማይወድ አይብላ" የሚለውን መለኮታዊ ትዕዛዝ መሠረት አድርገው ከተጋድሎ በተረፈቻቸው ሰዓት ሥራ ይሠራሉ። አንዳንዶቹ እንደሚመስላቸው ምናኔ ሥራ መፍታት አይደለምና ሰሌን ዕንቅብ ሠፌድ የመሳሰለውን ይሠፋሉ። ታላቁ አባ አጋቶንም በአንደበቱ ድንጋይ ጐርሶ በእግሮቹ ቀጥ ብሎ ቆሞ እንቅቦችን ይሠፋ ነበር። ቅዱሱ የሰፋውን ወደ ገበያ ይዞ ይወጣል በጠየቁትም ዋጋ ሽጦት አንዲት ቂጣ ይገዛል። የተረፈውን ገንዘብ ግን እዚያው ለነዳያን አካፍሎት ይመጣል እንጂ ወደ ገዳሙ አይመልሰውም።

አንድ ቀን እንደልማዱ የሠፋቸውን እንቅቦች ተሸክሞ ወደ ገበያ ሲሔድ መንገድ ላይ አንድ የኔ ቢጤ ወድቆ ያገኛል። እንደ ደረሰም ስመ #እግዚአብሔር ጠርቶ ይለምነዋል። አባ አጋቶን ከእንቅቦቹ ውጪ ምንም ነገር አልነበረውምና "እንቅቡን እንካ" አለው። ነዳዩ ግን ወይ የሚበላ ካልሆነም ገንዘብ እንደሚፈልግ ይነግረዋል። ወዲያው ደግሞ "የምትሠጠኝ ነገር ከሌለህ ለምን ወደ ገበያ ተሸክመህ አትወስደኝም?" አለው። የነዳዩ አካል እጅግ የቆሳሰለ በመሆኑ እንኩዋን ሊሸከሙት ሊያዩትም የሚከብድ ነበር። ጻድቁ ግን ደስ እያለው ያለማመንታት አንስቶ ተሸከመው። ከረጅም መንገድ በኋላ ከገበያ በመድረሳቸው አውርዶ ከጐኑ አስቀመጠው። ያ ነዳይ አላፊ አግዳሚውን ሁሉ ቢለምንም የሚዘከረው አጣ። አባ አጋቶን አንዷን እንቅብ ሲሸጥ "ስጠኝ?" ይለዋል። ጻድቁም ይሠጠዋል። እንዲህ "ስጠኝ" እያለ የእንቅቦችን ዋጋ ያ ነዳይ ወሰደበት። አባ አጋቶን ግን ምንም ቂጣ ባይገዛም በሆነው ነገር አልተከፋምና ሊሔድ ሲነሳ ነዳዩ "ወደ ቦታየ ተሸክመህ መልሰኝ" አለው። አባቶቻችን ትእግስታቸው ጥግ የለውምና ጐንበስ ብሎ በፍቅር አንስቶት አዘሎት ሔደ። ካነሳበት ቦታ ላይ ሲደርሱ ይወርድለት ዘንድ ጻድቁ ቆመ። ነዳዩ ግን አልወርድም አለ። ትንሽ ቆይቶ ግን ለቀቀው ሊያየው ዞር ቢል መሬት ላይ የለም። ቀና ሲል ግን ያየውን ነገር ማመን አልቻለምና ደንግጦ በግንባሩ ተደፋ። ነዳይ መስሎ እንዲያ ሲፈትነው የነበረው ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ነበርና ክንፎቹን ዘርግቶ በብርሃን ተከቦ በግርማ ታየው ከወደቀበትም አነሳው። "ወዳጄ አጋቶን ፍሬህ ትእግስትህ ደግነትህ ግሩም ነውና ዘወትር ካንተ ጋር ነኝ" ብሎት ተሰወረው፤ ጻድቁም በደስታ ወደ በዓቱ ሔደ። አባ አጋቶን ተረፈ ዘመኑን በአርምሞ ኑሮ ዐርፏል።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጻድቁ አባ አጋቶን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ይደርብን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_መጥራ_አረጋዊ (ሰማዕት)

ጥቅምት ስምንት በዚች ቀን ሽማግሌው አባ መጥራ በሰማዕትነት አረፈ። ከእርሱም ጋር ብዙዎች ሰዎች በሰማዕትነት አረፉ። ይህም ቅዱስ ከእስክንድርያ አገር አማኒ ክርስቲያን ነው። ከሀዲ ንጉሥ ዳኬዎስ በነገሠ ጊዜ የጣዖትን አምልኮ አቁሞ የክርስቲያንን ወገኖች አሠቃያቸው።

ትእዛዙም ወደ እስክንድርያ አገር ደርሶ ሰዎቿን ሁሉንም አሠቃያቸው የብዙዎች ምእመናንንም ደማቸውን አፈሰሰ። ያን ጊዜ ክርስቲያን እንደ ሆነ ቅዱስ መጥራን በመኰንኑ ዘንድ ወነጀሉት፤ መኰንኑም ወደርሱ አስቀረበው እርሱም ብቻውን እውነተኛ አምላክ እንደ ሆነ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ ክርስቶስ ታመነ።

መኰንኑም ለአማልክት ስገድ እኔም ብዙ ገንዘብን እሰጥሃለሁ ታላቅ ክብርንም አከብርሃለሁ አለው። እርሱም ቃል ኪዳኑን አልተቀበለም ኪዳንህና ገንዘብህ ካንተ ጋራ ወደ ጥፋት ይሒድ አለው እንጂ። መኰንኑም በእርሱ ላይ ተቆጥቶ እኔ በጽኑዕ ሥቃይ እቀጣሃለሁ አለው።

ቅዱስ መጥራም ፈርቶ ከበጎ ምክሩ አልተመለሰም እንዲህም አለው እንጂ እኔ ሰማይና ምድርን ለፈጠረ ለሕያው #እግዚአብሔር እሰግዳለሁ። ለረከሱ ጣዖታት ከደንጊያና ከዕንጨት ለተሠሩ ለማያዩ ለማይሰሙ ለማይናገሩ ለማያሸቱ ለማይንቀሳቀሱ እንሰግድ ዘንድ እንዴት ይገባል አለው።

መኰንኑም በሰማ ጊዜ አፈረ። ጽኑ ግርፋትንም እንዲገርፉት አዘዘ። ከዚህም በኋላ በክንዱ ሰቀሉት በደረቀች ሽመልም ጎኖቹን ሠነጠቁ ቀደዱትም ክብር ይግባውና #ጌታ_ኢየሱስም አዳነው። ያለ ጥፋትም በጤንነት አስነሣው መኰንኑም ማሠቃየቱን በሰለቸ ጊዜ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ። ከከተማውም አውጥተው የከበረች ራሱን ቆረጡ። ሌሎች ብዙዎች ሰማዕታትንም ከእርሱ ጋር ራሶቻቸውን ቆረጡ። የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ሰማዕታት በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_ሖር

ዳግመኛም በዚችም ቀን በላይኛው ግብጽ ከሚኖሩ ሰዎች ወገን የሆነ ቅዱስ አባት አባ ሖር መታሰቢያው ነው።

ደግነት ያለው መነኰስ በመሆን ጽኑዕ ገድልን ተጋደለ በአምልኮቱና በተጋድሎው ከቅዱሳን ሁሉ ተለይቶ በብዙዎች ላይ ከፍ ከፍ አለ ለብቻ መኖርን ስለወደደ ወደ በረሀ ወጥቶ በገድል ተጠምዶ ብዙ ዘመናት ኖረ። የበጎ ሥራ ጠላት የሆነ ሰይጣንም ቀንቶበት በግልጥ ታየውና በበረሀ ውስጥ ግን አንተ ድል ትነሣናለህ በዚህ ሰው የለምና ጽኑ ኃይለኛ ከሆንክ ወደ እስክንድርያ ከተማ ና ብሎ ተናገረው።

አባ ሖርም ይህን በሰማ ጊዜ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን ኃይል ተማምኖ ወደ እስክንድርያ ከተማ ሒዶ ለእሥረኞችና ለችግረኞች ደካሞች ውኃ የሚቀዳ ሆነ በአንዲት ዕለት ሦስት ፈረሶች በከተማው ውስጥ እየዘለሉ ሲያልፉ አንዱ ፈረስ አንዱን ሕፃን ረገጠውና ወዲያውኑ ሞተ ሰይጣንም በሰዎች ልብ አደረና ይህን ሕፃን ያለዚህ አረጋዊ መነኵሴ የገደለው የለም ብለው አሰቡ አባ ሖርም መጣና ሕፃኑን አንሥቶ ታቀፈው በልቡም በመጸለይ ክብር ይግባውና ወደ #እግዚአብሔር ማለደ በ #መስቀል ምልክትም በላዩ አማተበ የሕፃኑም ነፍስ ተመለሰች ድኖም ተነሣ ለአባቱም ሰጠው ወደ ከተማ ውጭ ሸሽቶ በመሔድ ወደ በዓቱ ገባ ፈልገውም አላገኙትም ጽድቅንና ትሩፋትንም በመሥራት ብዙ ዘመናት በገድል ተጠምዶ ኖረ።
የሚሞትበት ጊዜ ሲቀርብ ብዙዎች ቅዱሳንን ሲጠሩት አያቸው እጅግም ደስ አለው ልጆቹንም ሰብስቦ በምንኲስና ሥርዓት ጸንተው ትሩፋትን እንዲሠሩ አዘዛቸው ክብር ይግባውና ወደ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም እርሱ እንደሚሔድ ነገራቸው እነርሱም እጅግ አዘኑ ጥቂት ቀንም ታሞ ነፍሱን በ #እግዚአብሔር እጅ ሰጠ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኅ_ጥቅምት_8 እና #ከገድላት_አንደበት)
🌹#የጥቅምት_8_ግጻዌ

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_8_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ፊልጵስዩስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁹ ወደ ፊትም ደግሞ ደስ ይለኛል፤ ይህ በጸሎታችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ መሰጠት ለመዳኔ እንዲሆንልኝ አውቃለሁና፥
²⁰ ይህ ናፍቆቴ ተስፋዬም ነውና፤ በአንድ ነገር እንኳ አላፍርም ነገር ግን በሕይወት ብኖር ወይም ብሞት፥ ክርስቶስ በግልጥነት ሁሉ እንደ ወትሮው አሁን ደግሞ በስጋዬ ይከብራል።
²¹ ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና።
²² ነገር ግን በስጋ መኖር ለእኔ የሥራ ፍሬ ቢሆን፥ ምን እንድመርጥ ኣላስታውቅም።
²³ በእነዚህም በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፥ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤
²⁴ ነገር ግን በሥጋ መኖሬ ስለ እናንተ እጅግ የሚያስፈልግ ነው።
²⁵-²⁶ ይህንንም ተረድቼ፥ በእናንተ ዘንድ እንደ ገና ስለ መሆኔ፥ በእኔ መመካታችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ይበዛ ዘንድ፥ በእምነት ታድጉና ደስ ይላችሁ ዘንድ እንድኖር ከሁላችሁም ጋር እንድቈይ አውቃለሁ።
²⁷ ይሁን እንጂ፥ መጥቼ ባያችሁ ወይም ብርቅ፥ በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብራችሁ እየተጋደላችሁ፥ በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ ስለ ኑሮአችሁ እሰማ ዘንድ፥ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ።
²⁸ በአንድም ነገር እንኳ በተቃዋሚዎች አትደንግጡ፤ ይህም ለእነርሱ የጥፋት፥ ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው፥ ይህም ከእግዚአብሔር ነው፤
²⁹ ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም፤
³⁰ በእኔ ያያችሁት አሁንም በእኔ እንዳለ የምትሰሙት፥ ያው መጋደል ደርሶባችኋልና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ያዕቆብ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²-³ ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት
⁴ ትዕግሥትም ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም።
⁵ ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለእርሱም ይሰጠዋል።
⁶ ነገር ግን በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላልና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 14
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁹ አይሁድ ግን ከአንጾኪያና ከኢቆንዮን መጡ፤ ሕዝቡንም አባብለው ጳውሎስን ወገሩ የሞተም መስሎአቸው ከከተማ ወደ ውጭ ጐተቱት።
²⁰ ደቀ መዛሙርት ግን ከበውት ሳሉ፥ ተነስቶ ወደ ከተማ ገባ። በነገውም ከበርናባስ ጋር ወደ ደርቤን ወጣ።
²¹-²² በዚያችም ከተማ ወንጌልን ሰብከው እጅግ ደቀ መዛሙርትን ካደረጉ በኋላ፥ የደቀ መዛሙርትን ልብ እያጸኑ በሃይማኖትም ጸንተው እንዲኖሩ እየመከሩና፦ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል እያሉ፥ ወደ ልስጥራን ወደ ኢቆንዮንም ወደ አንጾኪያም ተመለሱ።
²³ በየቤተ ክርስቲያኑም ሽማግሌዎችን ከሾሙላቸው በኋላ ጦመውም ከጸለዩ በኋላ፥ ላመኑበት ለጌታ አደራ ሰጡአቸው።
²⁴ በጲስድያም አልፈው ወደ ጵንፍልያ መጡ፥
²⁵ በጴርጌንም ቃሉን ከተናገሩ በኋላ ወደ አጣልያ ወረዱ፥
²⁶ ከዚያም ስለ ፈጸሙት ሥራ ለእግዚአብሔር ጸጋ አደራ ወደ ተሰጡበት ወደ አንጾኪያ በመርከብ ሄዱ።
²⁷ በደረሱም ጊዜ ቤተ ክርስቲያኑን ሰብስበው እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ያደረገውን ሁሉ ለአሕዛብም የሃይማኖትን ደጅ እንደ ከፈተላቸው ተናገሩ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_8_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇🌹

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"እግዚአብሔር ኢያስተጼንሶሙ እምበረከቱ ለእለ የሐውሩ በየውሀት። እግዚኦ አምላከ ኃያላን። ብፁዕ ብእሲ ዘተወከለ ኪያከ"። መዝ 83፥11-12።

#ትርጉም፦ " #እግዚአብሔር አምላክ ምሕረትንና እውነትን ስለ ወደደ፥ ሞገስንና ክብርን ይሰጣል፤ #እግዚአብሔር በቅንነት የሚሄዱትን ከመልካም ነገር አያሳጣቸውም። የሠራዊት አምላክ ሆይ፥ በአንተ የታመነ ሰው ምስጉን ነው"። መዝ 83፥11-12።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_8_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሉቃስ 21
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² ከዚህም ሁሉ በፊት እጃቸውን በላያችሁ ይጭናሉ ያሳድዱአችሁማል፤ ስለ ስሜም ወደ ምኵራብና ወደ ወኅኒ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ ወደ ነገሥታትና ወደ ገዥዎችም ይወስዱአችኋል፤
¹³ ይህም ለምስክርነት ይሆንላችኋል።
¹⁴ ስለዚህ እንዴት እንድትመልሱ አስቀድማችሁ እንዳታስቡ በልባችሁ አኑሩት፤
¹⁵ ወደረኞቻችሁ ሁሉ ሊቃወሙና ሊከራከሩ የማይችሉትን አፍና ጥበብ እሰጣችኋለሁና።
¹⁶ ወላጆችም ስንኳ ወንድሞችም ዘመዶችም ወዳጆችም አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ ከእናንተም አንዳንዱን ይገድላሉ፤
¹⁷ በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ።
¹⁸ ከራሳችሁም አንዲት ጠጉር ስንኳ አትጠፋም፤
¹⁹ በመታገሣችሁም ነፍሳችሁን ታገኛላችሁ።
²⁰ ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ 🌹
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ባስልዮስ_ቅዳሴ ነው። መልካም በዓልና የጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን። 🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ንስሐ_ከሰዎች_ጋር_ለመታረቅ_የተዘረጋ_የእግዚአብሔር_እጅ_ነው!

#ንስሐ በኃጢያት ምክንያት ከ #ፈጣሪው ጋር ለመገናኘት ያልቻለው የሰው ልጅ ከ #ፈጣሪው ጋር እንዲገናኝ #እግዚአብሔር የከፈተው የሕይወት መንገድ ነው። #ንስሐ_እግዚአብሔር የሰውን የቀደመ ኃጢያት ይቅር የሚልበትና የሚያጥብበት መንፈሳዊ ሳሙና ነው። ሰው በ #ንስሐ የታጠበ እንደሆነ ከበረዶ ይልቅ ይነጻል መዝ.50። #ንስሐ በኃጢያት ምክንያት የፈረሰው (የተናደው) የሰው መንፈሳዊ ተስፋ ዳግመኛ የሚገነባበት መሣሪያ ነው። #ንስሐ የምሕረት፣ የይቅርታ፣ የሕይወት በር ነው። #ንስሐ ሰውንና መላእክትን፤ መሬትንና መንግስተ ሰማያትን የሚያገናኝ ረቂቅ መንፈሳዊ ድልድይም ነው። ለዚህ ነው #ንስሐ ከሰዎች ጋር ለመታረቅ የተዘረጋ የ #እግዚአብሔር እጅ ነው የተባለው።

#ይቀጥላል.......
#ጥቅምት_9

#አንድ_አምላክ_በሆነ_በአብ_በወልድ_በመንፈስ_ቅዱስ ስም
ጥቅምት ዘጠኝ በዚህች ዕለት #የአባ_ሊዋርዮስ እና #የአቡነ_አትናስዮስ እረፍታቸው ነው፣ በዲዮቅልጢያኖ ዘመን የመጀመሪያ የሆነው ሰማዕት #ቅዱስ_እስጢፋኖስ_ዘአንጾኪያ በሰማዕትነት አረፈ፤ #ሐዋርያው_ቅዱስ_ቶማስ በሕንድ አገር ድንቅ ተአምር ያደረገበትም ዕለት ነው ዳግመኛም ኢትዮጵያዊው ጻድቁ #አቡነ_መዝገበ_ሥላሴ እረፍታቸው ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሊቀ_ጳጳሳት_ቅዱስ_ሊዋርዮስ

ጥቅምት 9 በዚች ቀን ቅዱስ አባት የሮሜ አገር ሊቀ ጳጳሳት ሊዋርዮስ አረፈ። ይህም ዕውነተኛ ደግ ንጹሕ የሆነ ሰው በታናሽነቱ መንኲሶ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እየተማረ በቤተክርስቲያን ግቢ አደገ። በሮሜ አገርም በሐዋርያት አለቃ በጴጥሮስ ወንበር ላይ ሊቀ ጳጳሳት ሊሆን መርጠው ሾሙት።

በጎ መንገድንም በመጓዝ #እግዚአብሔርን አገለገለው ሕዝቡን አዘውትሮ ያስተምራቸው ነበርና ከ #እግዚአብሔርም ሕግና ትእዛዝ የተላለፉትን መክሮ ገሥጾ ወደ #እግዚአብሔር ሕግ ይመልሳቸው ነበርና። ታናሹ ቁስጠንጢኖስም በሞተ ጊዜ ከሀ*ዲው ዑልያኖስ ነገሠ #እግዚአብሔርም እስከ አጠፋው ድረስ የክርስቲያንን ወገኖች አሠቃያቸው።

ይህም ዑልያኖስ ለቈስጠንጢኖስ የአባቱ እኅት ልጅ ነው መንግሥትንም በያዘ ጊዜ የጣዖታትን ቤቶች በመክፈት የክርስቲያንን ወገኖች ሁሉ አሠቃያቸው። ይህ አባት ሊዋርዮስም ከሮሜ አገር ወደ ቂሣርያ መጣ ከቅዱስ ባስልዮስም ጋር ተገናኘ። ከታላቅ ስሕተቱና ከክህ*ደቱ መክረው ይመልሱት ዘንድ ወደ ንጉሥ ዑልያኖስ ለመሔድ ሁለቱ ተስማሙ። እነርሱ ከታናሽነታቸው ጀምረው እየተማሩ ከእርሱ ጋር በአንድነት ያደጉ ናቸውና።

ከዚህም በኋላ ተነሥተው ሔዱ ንጉሥ ዑልያኖስም ወዳለበት ደርሰው ከፊቱ ቆሙ ከስሕተቱም በሚመልሱበት ሊናገሩት ወደው ሳለ እርሱ ቀድሞ በ ክብር ይግባውና #ጌታችን ላይ በመሣለቅ ክብር ይግባውና የጠራቢውን ልጅ ወዴት ተዋችሁት አላቸው። ቅዱስ ባስልዮስም አንተን በሲኦል ይቀብሩህ ዘንድ ሣጥን ሊሠራልህ ተውነው ብሎ መለሰለት። በዚያንም ጊዜ በእነርሱ ላይ ተቆጥቶ በወህኒ ቤት እንዲያሥሰሯቸው አዘዘ።

በዚያም የቅዱስ መርቆሬዎስን ሥዕሉን አግኝተው በፊቱ እያለቀሱ የ #ክርስቶስ ምስክር ሆይ በክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ ላይ የዚህን ከሀዲ መሣለቁን አትሰማምን ብለው ጸለዩ ይህንንም ሲጸልዩ ያን ጊዜ አንቀላፉ። አባ ሊዋርዮስም በእንቅልፉ ውስጥ ሳለ ቅዱስ መርቆሬዎስን ሰማይና ምድርን በፈጠረ በሕያው ፈጣሪዬ ላይ እንዲሣለቅ ይህን ከሀዲ በሕይወት አልተወውም ሲል በሕልሙ አየው።

ከእንቅልፉ ነቅቶ ያየውን ለቅዱስ ባስልዮስ ነገረው በዚያንም ጊዜ ሥዕሉን ከቦታው አጡት እርሱ ዑልያኖስ ወዳለበት ሒዶአልና በጦርም ወግቶ ገደለው ወደ ቦታውም ተመልሶ ተሰቀለ ከጦሩ አንደበትም ደም ይንጠፈጠፍ ነበር።

እሊህ ቅዱሳንም ይህን ድንቅ ሥራ በአዩ ጊዜ መፈራትንና ባለሟልነትን የተመላህ የ #ኢየሱስ_ክርስቶስ ምስክር ሆይ ዑልያኖስን ገደልከውን አሉ ። ያን ጊዜ አዎን እንደሚል ሥዕሉ ዘንበል አለ እሊህም ቅዱሳን ሊዋርዮስና ባስልዮስ ደስ አላቸው።

ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስን የሚያምን ዩማንዮስ ነገሠ እሊህንም ቅዱሳን ከእሥር ቤት አወጣቸውና ወደየቦታቸው ተመለሱ። ይህም አባት ሊዋርዮስ አርዮሳውያንን እጅግ ይጣላቸው ነበር። ከክርስቲያን ወገኖችም ለይቶ ያሳድዳቸዋል።

መልካም ጒዞውንም ከፈጸመ በኋላ #እግዚአብሔርን አገልግሎ በሰላም አረፈ። የሹመቱም ዘመን ሰባት ዓመት ነው።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን አበው ጸሎት ይማረን በረከታቸውም
ይደርብን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሊቀ_ጳጳሳት_ቅዱስ_አትናስዮስ

በዚችም ቀን ዳግመኛ የከበረ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት አባ አትናስዮስ አረፈ ። ይህም ቅዱስ ከታናሽነቱ ጀምሮ መነኰሰ ባሕታዊም ሁኖ የሚያገለግል ቅን ትሑት በበጎ ሥራ ሁሉ ፍጹም ሆነ ።

ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤልም ከአረፈ በኋላ ኤጲስቆጶሳት ሁሉም ተሰበሰቡ ይህንንም አባት ሊቀ ጵጵስና ይሾሙት ዘንድ መረጡት ። ፈጥኖም እንዲመጣና ከእነርሱ ጋር ይህን አባት እንዲሾም ወደ ሀገረ ሰልቅ ሊቀ ጳጳስ ወደ አባ እልመፍርያን ላኩ እርሱ ግን መምጣትን ዘገየ። እነርሱም ኃምሳ ቀኖች ያህል ጠብቀው አባ አትናስዮስን ሹመውት ወደየሀገረ ስብከታቸው ተመለሱ። ከዚህም በኋላ በላኩበት መሠረት ሊቀ ጳጳስ አባ እልመፍርያን መጣ ወደ ሶርያም ድንበር ሀገረ ዓምድ ደርሶ ከአንድ ጳጳስ ጋር ተገናኘ። ያም ጳጳስ እርሱ ከመምጣት በዘገየ ጊዜ አባ አትናስዮስን እንደ ሾሙት ነገረው በሰማም ጊዜ እጅግ ተቆጣ እንዲህም አለ በእኛና በእናንተ መካከል ያለውን ሕግ እንዲህ ትሽራላችሁን ይህንንም ብሎ በቊርባንም ቢሆን ወይም በማዕጠንት የአባ አትናስዮስን ስም የሚጠራውን ሁሉ አውግዞ ወደ ሀገሩ ተመለሰ።

አባ አትናስዮስም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ ረዳቱንም ጠርቶ እንዲህ አለው ልቤ ትባርክህ ትመርቅህ ዘንድ ታዘዝልኝ ሕዝቡ የፈለጉኝ እንደሆነ በዋሻ ሱባዔ ውስጥ ነው በላቸው እኔ ወደ አንድ ቦታ ሔጄ አንድ ዓመት ያህል እቆያለሁና አንተም ሊሆን በሚገባ ሥራ ሁሉ እዘዛቸው በእኔም ፈንታ እሠር ፍታ ረዳቱም እሺ አለው ።

ከዚህም በኋላ አባ አትናስዮስ የድኃ ልብስ ለብሶ በሥውር ወጣ በእግሩም ሒዶ ወደ ሀገረ ሰልቅ ደረሰ ። የሊቀ ጳጳስ አባ እልመፍርያንን ደጅ አንኳኳ በረኛውም ምን ትሻለህ አለው ከአባት ሊቀ ጳጳስ ቡራኬ እሻለሁ ብሎ መለሰለት ነግሮለትም አስገባው አባ እልመፍርያን አንተ ከወዴት ነህ አለው ። እርሱም ከሶርያ አገር ነኝ የዕለት ሲሳይና ልብስ አጥቼ መጣሁ በጥላህም ሥር ሁኜ ላገለግል እሻለሁ ብሎ መለሰ ።

ሁለተኛም ቄስ ነህን ወይስ ዲያቆን አለው እርሱም አይደለሁም አለ ሹሙንም ጠርቶ ከመነኰሳቱ ጋር እንዲአኖረው አዘዘው ።

አባ አትናስዮስም የሊቀ ጳጳሱን የቤት ውስጥ ሥራ የፈረሶችንና የበቅሎዎችን ፍግ እስከሚጠርግ የሚሠራ ሆነ ይፈጫል ውኃ ይቀዳል እንጀራ ይጋግራል ወጥ ይሠራል ምንም ምን ሥራ አይቀረውም። እንዲሁም ለመነኰሳቱ ቤቶቻቸውን ይጠርግላቸዋል ውሀንም ይቀዳላቸዋል እሳትንም ያነድላቸዋል እጅግም ስለ ወደዱት እንደ ሰማያዊ መልአክ አስመሰሉት።

ከዚህም በኋላ አትናስዮስን ዲቁና ይሾመው ዘንድ ሊቀ ጳጳሱን መነኰሳቱ ማለዱት በእሑድም ቀን አባ እልመፍርያን ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ዲቁና ሊሾመው አባ አትናስዮስን ጠራው እርሱም አልቅሶ አባቴ ሆይ ተወኝ እኔ ድኃ ነኝና አለው ባልተወውም ጊዜ አባቴ ይቅርታ አድርግልኝ ይህስ ዲቁና አለኝ አለው። ሊቀ ጳጳሱም ከትዕግሥቱና ከትሕትናው የተነሣ አደነቀ በዲቁናም እንዲአገለግል አዘዘው በዲቁና እያገለገለ ሰባት ወር ኖረ።

ሊቀ ጳጳሱም አዋቂነቱን አይቶ ቅስና ሊሾመው ወደደ በእሑድ ቀንም ወደ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ጠርቶ #መንፈስ_ቅዱስ ቅስና ሊሾምህ ጠርቶሃል አለው አባ አትናስዮስም ሰምቶ አለቀሰ እንዲተወውም ማለደው። ባልተወውም ጊዜ አባቴ ይቅር በለኝ እኔ ቄስ ነኝ አለ መነኰሳቱም ሁሉ አደነቁ በእርሱም ደስ አላቸው።
አባ እልመፍርያንም አስተዋይነቱን የአንደበቱን ጣዕም የተደራረበ አገልግሎቱንም ተመልክቶ ጳጳስዋ ለሞተባት ለአንዲት አገር ጵጵስና ሊሾመው ወደደ። ጳጳሳትንና ኤጲስቆጶሳትን ቀሳውስትንና ዲያቆናትንም በእሑድ ቀን ሰበሰባቸው አባ አትናስዮስንም አቅርበው እንዲህ አሉት ለዕገሌ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ልትሆን ዛሬ #መንፈስ_ቅዱስ ጠርቶሃል አሉት። እርሱም ሰምቶ አለቀሰ እንዲተዉትም አልቅሶ አማላቸው እንደማይተውትም በአወቀ ጊዜ እርሱ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት አትናስዮስ እንደሆነ ነገራቸው የአመጣጡንም ምሥጢር ገለጸላቸው።

በዚያን ጊዜ አባ አልመፍርያን ደነገጠ አክሊሉንም ከራሱ ላይ አውልቆ በምድር ላይ ወደቀ ለረጅም ጊዜ እንደ ሞተ ሆነ በተነሣም ጊዜ እንዲህ ብሎ ጮኸ ወንድሞቼ የማደርገውን እስቲ ንገሩኝ ዛሬ እሳት ከሰማይ ወርዶ እንዳያቃጥለኝ ምድርም አፍዋን ከፍታ እንዳትውጠኝ እፈራለሁና ጌታዬ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት አትናስዮስ ውኃ እየቀዳ የፈረሶችና የበቅሎዎች ጉድፍ እየጠረገ በቤቴ ውስጥ እንደ ባርያ ሊአገለግል አግባብ ነውን ወዮልኝ ወዮልኝ።

ጳጳሳቱና የተሰበሰቡት ሁሉ በሰሙ ጊዜ ከእግሩ በታች ወድቀው ሰገዱለት እጆቹንና እግሮቹንም ሳሙ ሊቀ ጳጳሱም ያማሩ የክህነት ልብሶችን ያለብሱት ዘንድ መስቀሎችንና አርዌ ብርቱን ያመጡ ዘንድ በመንበር ላይም ያስቀመጡት ዘንድ አዘዘ።

ከዚያም በኋላ ጳጳሳቱ ከመንበሩ ጋር ተሸከሙት ሦስት ጊዜ አክዮስ አክዮስ አክዮስ እያሉ ይህም ይገባዋል ማለት ነው ቤተ ክርስቲያኑን አዙረው ወደ መቅደስ አስገቡት ።

ከዚህም በኋላ መቀደሻ ልብስ ለብሶ መሥዋዕቱን አክብሮ ቀድሶ አቈረባቸው እነርሱንም ሀገራቸውንም ባረከ ለዚያችም አገር ምንኛ መጠን የሌለው ደስታ ሆነ ተባለ ።

በማግሥቱም አባ እልመፍርያን ተነሥቶ በቅሎ አስመጣ ለጒዞ የሚያሻውን ሁሉ አዘጋጀ አባ አትናስዮስንም በበቅሎ አስቀምጦ እርሱ በእግሩ ተከተለው ጳጳሳቱና ኤጲስቆጶሳቱ ሁሉም ከአባ እልመፍርያን ጋር አጅበዉ ወደ አንጾኪያ አገር ወሰዱት አባት አትናስዮስም አባ እልመፍርያንን አንተም በበቅሎ ላይ ተቀመጥና በአንድነት እንሒድ አለው። አባ እልመፍርያንም ጌታዬ ለእኔ አይገባኝም አንተ በእግርህ ወደ አገሬ እንደመጣህ እንዲሁ እኔም በእግሬ ወደ አገርህ አደርስሃለሁ አለው።

የአንጾኪያ አገር ጳጳሳትም የሊቀ ጳጳሳት አትናስዮስን መምጣት በሰሙ ጊዜ ከሕዝብ ሁሉ ጋር ሊቀበሉት ወጡ በታላቅም ክብር ተቀብለው ወደሹመቱ መንበር አስገቡት። ለአባ እልመፍርያንም ሁለተኛ ወንበር አድርገው በክብር አስቀመጡት በዚያችም ቀን ፈጽሞ ደስ አላቸው ተሰናብተውትም ወደ ሀገራቸው በፍቅር አንድነት ተመለሱ። ይህም አባት አትናስዮስ በጎ አኗኗርን ኖረ መንጋውንም በትክክል በእውነት ጠበቀ በጎ ጒዞውንም ፈጽሞ በሰላም አረፈ ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አባ አትናቴዎስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_እስጢፋኖስ_ካልዕ

በዚችም ቀን በከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስ ዘመን በአንጾኪያ አገር የሰማዕታት መጀመሪያ ሁኖ ሌላው እስጢፋኖስ በሰማዕትነት አረፈ ።

ይህም የፋሲለደስ ወንድም ለሆነ የኒቆምዮስ ልጅ ነው በወገንም የከበረ ነው አባቱም ከአንጾኪያ ታላላቆች ወገን ሁኖ በወርቅ በብር በወንድ ባሮች በሴት ባሮች እጅግ የበለጸገ ነው ክብር ይግባውና #ክርስቶስንም እጅግ ይፈራዋል ይወደዋልም ለድኆችና ለችግረኞች አብዝቶ ይመጸውታል በሰው ሁሉ ዘንድ ተወዳጅ ነው ።

ይህንንም ቅዱስ እስጢፋኖስን በወለዱት ጊዜ በበጎ ተግሣጽ በምክር አሳደጉት በጀመሪያም የዳዊትን መዝሙር ከዚያም የብሉይና የሐዲስ መጻሕፍትን የ #መንፈስ_ቅዱስ ዕውቀት በላዩ እስቲመላ ድረስ አስተማሩት ።

ሁለተኛም ሥጋዊ ጥበብ ፈረስ መጋለብን ጦር መወርወርን በፍላፃ መንደፍን በቅዱስ ፋሲለደስ ቤት ሁኖ ከቅዱሳን ፊቅጦርና ገላውዴዎስ ጋር ተማረ ለፋሲለደስ የወንድሙ ልጅ ነውና ስለዚህም የፋሲለደስ ልጅ ይባላል ።

ዘመዶቹም ሁሉ #እግዚአብሔርን የሚፈሩ ናቸው በሕጉ በትእዛዙ በአምልኮቱ ሁሉ የጸኑ ናቸው ። ከውስጣቸውም ክብር ይግባውና ከ #ክርስቶስ የፍቅር ትኲሳት ልቡን የሚያቀዘቅዝ ወደ ቀኝ ቢሆን ወደ ግራም ፈቀቅ የሚል የለም ።

#ጌታችንም ለእርሱ ያላቸውን የፍቅራቸውን ጽናት በአየ ጊዜ ዓለም ሳይፈጠር ያዘጋጀላቸውን መንግሥቱን ሊአወርሳቸው ወደደ ። ከዚህም በኋላ የግብጽ አገር ወደ ሆነ የፍየል ጠባቂ በጦርነት ምክንያት ወደ መለመሉት ስሙ አግሪጳዳ ወደ ሚባል ሰው ሰይጣን መጥቶ አደረበት ወደ አንጾኪያም በደረሰ ጊዜ የመንግሥት ፈረሶች ባልደራስ አደረጉት ።

የአንጾኪያም ንጉሥ በሞተ ጊዜ መንበሩ ከንጉሥ ተራቆተ በአንዲት ዕለትም የንጉሡ ሴት ልጅ በቤቷ ደርብ ስትመላለስ ሲዘፍን አየችው እርሱም ለፈረሶች ክራርና መሰንቆ ሲመታላቸው እንደሚዘፍን ሰው ሁነው ያሽካኩ ነበር ። ስለዚህ ወደደችውና ባል አድርጋ አነገሠችው ስሙንም ዲዮቅልጥያኖስ ብላ ሰየመችው ።

ያን ጊዜ በዘመኑ ለተደረገ ዓመፅና ግፍ ወዮ ምን ዓይነት ዓመፅና ግፍ ነው ። ክብር ይግባውና #ክርስቶስን ከካደው በኋላ ጣዖታትን አመለከ በ #ክርስቶስም ያመነውን ሁሉ ገደለ እንደ ነጣቂዎች አራዊትም የሰውን ሥጋ የሚበላ ደማቸውንም የሚጠጣ ሆነ ። የተመረጡ የመንግሥት ልጆችን ሁሉ እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች በተናቸው ከእነርሱ ውስጥ በችንካሮች ቸንክሮ የገደላቸው አሉ በማረጃ አርዶ የገደላቸው በጦር ወግቶ በእሳትም አቃጥሎ የገደላቸው አሉ አሥሮ አፋቸውንም በልጓም ለጉሞ ወደ ግብጽ አገሮች እስከ ሰደዳቸው ድረስ ልቅሶና ዋይታም በአንጾኪያ አገር እስከመላ ድረስም ባል ስለ ሚስቱ ሚስትም ስለ ባልዋ እናትና አባት ስለ ልጆቻቸው ልጆችም ስለ ወላጆቻቸው ሰዎችም ሁሉ ስለ ወገኖቻቸው የቅዱሳን ሰማዕታትም ሥጋቸው በሀገሩ ጥጋጥግ የወደቀ ሆነ ። ለጠባቂዎች ገንዘብ ሰጥተው በሥውር ወስደው ከሚቀብሩአቸው በቀር ቀባሪ የላቸውም ።

ይህም ቅዱስ እስጢፋኖስ የምስክርነት አክሊልን ይሰጠው ዘንድ ወደ #እግዚአብሔር ሲጸልይ ኖረ ።

የመጀመሪያዪቱ ቀን ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ በግዛቱ ውስጥ ላሉ አገሮች ሁሉ አብያተ ክርስቲያናት እንዲዘጉ የጣዖት ቤቶች እንዲከፈቱና እንዲአመልኳቸው እነርሱ በጦርነት ውስጥ ድል አድራጊነትን ይሰጡናልና ይህንንም ትእዛዝ የሚቃወምና እምቢ የሚል ቢኖር ንብረቱ ይወረስ በየአይነቱ በሆነ ሥቃይ ይሠቃይ ርኅራኄ በሌለው አሟሟት እስኪሞት ብሎ የሚያዝ የአዋጅ ደብዳቤ ጻፈ ።

የመንግሥቱን ታላላቆች ሁሉ ሕዝቡንም ታላቁንም ታናሹንም ሰበሰባቸው ። ይቺ የረከሰች ደብዳቤም በተሰበሰቡት ፊት ትነበብ ዘንድ አዘዘ ቅዱስ እስጢፋኖስም በሰማ ጊዜ ስለ ቀናች ሃይማኖት በ #ክርስቶስ ፍቅር እሳትነት ልቡ ነደደ ።

ዲዮቅልጥያኖስንም ተመለከተው እንደ ኢምንትም አደረገው። እንዲህም አለው ንጉሥ ሆይ አጵሎንን ያመልኩ ዘንድ የምታዝ ይቺን የረከሰች ደብዳቤ በመጻፍህ የምታሳየው ይህ ዓመፅ ምንድን ነው ይህንንም ሁሉ ያጠፋው ዘንድ ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አለ ይህንንም ብሎ ይችን የረከሰች ጽሑፍ በያዘ ወታደር ላይ ተወርውሮ ነጠቀውና ቀደዳት በጣጥሶም ጣላት ።
ንጉሡም ቅዱስ እስጢፋኖስን ይህ የምትሠራው ምንድር ነው ለራስህ ጥፋትን አምጥተሃልና አለው ከዚህም በኋላ ሰይፉን መዝዞ መታውና ከሁለት ከፈለው የቅዱስ እስጢፍኖስም ራስ ለረጅም ጊዜ በንጉሥ ፊት ሁና በክርስቲያን ወገኞች ላይ የሚደረገውን ሁሉ ግፍ ዳግመኛም በስተኋላ በንጉሡ ላይ የሚመጠበትን ዐይኖቹ እንደሚታወሩ ምጽዋትንም እንደሚመጸወት ከዚያም በኋላ እንደሚጠፋ ተናገረች።

ከዳተኛ ንጉሥ ሄሮድስን የምጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ራስ እንደ ዘለፈችው የቅድስ እስጢፋኖስም ራስ ዲዮቅልጥያኖስን ስትዘልፈው ያዩዋት ዘንድ ብዙ ሕዝቦች የሚመጡ ሆኑ ሄሮድስና ዲዮቅልጥያኖስ አንድ ጠባይ ናቸውና በከፋች ሥራቸውም አይለያዩም።

ሴቶች ከወለዱአቸው የሚመስለው የሌለ የልዑል ነቢይ የሆነ ጻድቅ ሰውን ሄሮድስ በገደለው ጊዜ ዝሙቱ እንዳይገለጽ ሽቶ ነበር ስለዚህም ተልቶ ተበላሽቶ እስኪሞት ሚስቱንም ምድር እስከ ዋጠቻት ልጅዋም እስከ አበደች ድረስ ጉስቍልና አገኘው የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ራስም ዝሙቱን ግልጽ አድርጋ ዘለፈችው።

ይህም ጐስቋላ ዲዮቅልጥያኖስ የረከሱ የጣዖታትን አምልኮ ሊገልጥ የማይደበቅ የሕያው #እግዚአብሔርን አምልኮ ሊደብቅ ወዶ የቅዱስ እስጢፍኖስን ራስ ቆረጠ የቅዱስ እስጢፍኖስ ራስ ግን ዘለፈችው አማልክቶቹም የርኩሳን አጋንንት ማደሪያዎች እንደ ሆኑ ገለጠች አሳፈረችውም ።

በምድርም ውስጥ እንዲደፍኑዋት አዘዘ ። እርሷም በምድር ውስጥ ተደፍና ሳለች ዝም አላለችም ሦስት ቀን ያህል አብዝታ እየተናገረች ትዘልፈው ነበር ሕዝቡም ሁሉ ይሰሟታል እጅግም አፈረ ከእርሳስም ሣጥን ውስጥ እንዲጨምሯትና ሣጥኑን አሽገው ከጥልቅ ባሕር ውስጥ እንዲጥሉት አዘዘ በዚያንም ጊዜ የ #እግዚአብሔር መልአክ ወረደ ሣጥኑንም ከባሕር አውጥቶ በባሕሩ ዳር አኖረው ።

እናቱም ሥጋውን እየፈለገች በ #እግዚአብሔር ፈቃድ ከዚያ ደረሰች አግኝታውም ዘመን እስቲያልፍ በሥውር ቦታ አኖረችው በፊቱም መብራት አኖረች የመከራውም ወራት ከአለፈ በኋላ ያማረች ቤተ ክርስቲያን ተሠራችለት ከእርሱም ታላላቅ ድንቆች ተአምራት ተገለጡ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ እስጢፋኖስ ሰማዕት ጸሎት ይማረን በረከቱም ይደርብን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ቶማስ_ሐዋርያ

በዚችም ቀን በሕንድ አገር ቅዱስ ሐዋርያ ቶማስ ላደረገው ድንቅ ተአምር መታሰቢያ ሆነ ።

ይህም እንዲህ ነው ሐዋርያ ቅዱስ ቶማስ እንደ ባሪያ ተሽጦ ወደ ሕንድ አገር ከአበኒስ ጋር በገባ ጊዜ አበኒስ ወደ ንጉሥ ጎንዶፎር አቀረበውና ሐናፂ እንደሆነም ለንጉሡ ነገረው ንጉሡም ስለሚችለው ሙያው ሐዋርያውን ጠየቀው ቅዱስ ሐዋርያ ቶማስም እንዲህ ብሎ ለንጉሥ መለሰለት እኔ የጥርብ ሥራን ሁሉ ቀንበሮችን ሚዛኖችን ሠረገላዎችን መርከቦችን በግንብ ሥራም ቤተ መንግሥትን እሠራለሁ ንጉሡም እጅግ ደስ አለው ።

ቤተ መንግሥቱንም እንዲሠራለት ከሚሻው ቦታ ወሰደውና በምን ወር ትሠራለህ አለው ሐዋርያውም ከኅዳር መባቻ ጀምሬ በሚያዝያ ወር እጨርሳለሁ አለው ። ንጉሡም አድንቆ ሕንፃ ሁሉ በበጋ ይታነፃል አንተ ግን እንዴት በክረምት ወር ታንፃለህ አለ ሐዋርያም ስለዚህ ነገር ችግር የለም አለ ።

ከዚህም በኋላ ንጉሡ ለራሱና ከእርሱ ጋር ለሚሠሩ ሠራተኞች የሚሆን ብዙ ገንዘብን ሰጠው ቅዱስ ሐዋርያ ቶማስም ተቀብሎ ሔደ ። የንጉሥን ለንጉሥ እሰጣለሁ እያለ ለድኆችና ለምስኪኖች መጸወተው ዳግመኛም የቤተ መንግሥቱ ግድግዳው ተፈጽሞ ጣሪያው ቀርቷል ብሎ ወደ ንጉሡ ላከ ። ያን ጊዜም ንጉሥ ብዙ ገንዘብ ላከለት ሐዋርያውም ተቀብሎ እንደ ልማዱ መጸወተው ።

ከዚህም በኋላ ንጉሡ በመጣ ጊዜ ስለ ቤተ መንግሥቱ ሕንፃ ጠየቀ ምንም የተሠራ ነገር አላገኘም ነገር ግን ገንዘቡ ለድኆች ምጽዋት ሁኖ እንደተበተነ ሰማ ። እጅግም ተቆጣ በሚገለውም ነገር እስቲመክር ድረስ ሐዋርያ ቅዱስ ቶማስን ከአመጣው ከአበኒስ ጋር አሠረው ።

በዚያችም ሌሊት የንጉሡ ወንድም ጋዶን በደንገት ታመመና ሞተ ቅዱሳን መላእክትም ነፍሱን ወስደው ተመሳሳይ የሌለው በወርቅና በዕንቍ የተሠራ ቤተ መንግሥትን አሳዩዋት ። ጋዶንም መላእክትን ይህ ቤተ መንግሥት የማነው አላቸው መላእክትም ለጋዶን ሐዋርያ ቶማስ ለንጉሥ ጎልዶፎር የሠራለት ነው አሉት ከዚህም በኋላ ጋዶን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ ያየውንም ሁሉ ለወንድሙ ለንጉሥ ጎልዶፎር ነገረው ። በዚያንም ጊዜ ወደ እሥር ቤት ሮጡ ቅዱስ ሐዋርያ ቶማስንም አበኒስንም ከወህኒ ቤት አወጡአቸው ። ለሐዋርያውም ሰገዱለት የሀገር ሰዎችም ሁሉ ከንጉሥ ጎልዶፎር ጋር አመኑ በ #አብ#ወልድ#መንፈስ_ቅዱስ ስም ተጠመቁ የ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስንም_ቅዱስ_ሥጋውንና_ክቡር_ደሙን አቀበላቸው ። ከዚህም በኋላ ባረካቸውና ከእርሳቸው ዘንድ ወጥቶ ወደ ሌላ ቦታ ሔደ ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ይደርብን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_መዝገበ_ሥላሴ_ጻድቅ

አቡነ መዝገበ ሥላሴ በታሪካዊነቱና በያዛቸው ድንቅ ድንቅ ቅርሶች ከሚታወቀውና ኢትዮጵያዊውን ሀሳበ ዘመን በመቀመር ከሚታወቀው ከእውነተኛው የብህትውና ቦታ ከደብረ ገሪዛን ቅድስት #ማርያም ጉንዳጉንዶ ገዳም የተገኙ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ እነ አቡነ አበከረዙንን ጨምሮ የባሕረ ሐሳብ ፍልስፍናና የሥነ ጽሑፍ ማዕከል ከሆነው ከዚህ ገዳም የወጡ ገድል ተጽፎላቸው፣ ታቦት በስማቸው የተቀረጸላቸው ከ17 በላይ ታላላቅ ቅዱሳን አሉ፡፡ አቡነ መዝገበ ሥላሴም ከእነዚህ የበቁ ቅዱሳን ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡ አባታቸው ሀብተ ጽዮን እናታቸው ማርያም ሞገሳ ሲባሉ እነርሱም በ #እግዚአብሔር ፊት ቅኖች ነበሩ፡፡

ማርያም ሞገሳ ዕለት ዕለት አምሃ(ስጦታ) እየያዘች ወደ ቤተ ክርስቲያን እየሄደች ስትጸልይ በአንደኛው ዕለት የታዘዘ መልአክ መጥቶ ‹‹በ #እግዚአብሔር ፊት ሞገስ ያገኘና የተባረከ ልጅ ትወልጃለሽ›› ብሎ አበሰራት፡፡እርሷም ‹‹ከማኅፀኔ እንደፀሐይ የሚያበራ ልጅ ሲወጣ አየሁ›› አለች፡፡ በዚህም መሠረት አቡነ መዝገበ #ሥላሴ በምሥራቃዊ ትግራይ ዞን በገላውዴዎስ ዘመነ መንግሥት በ1532 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ በ40ኛ ቀናቸውም ሲጠመቁ ሰጊድለ #አብ ተባሉ፡፡ ሰጊድለ #አብ ከዕለታት በአንደኛው ቀን የ #እግዚአብሔር መልአክ ከእናታቸው እቅፍ ውስጥ ነጥቆ ወስዶ ደብረ ከስዋ (ደብረ ገሪዛን) ጉንዳጉንዶ ቅድስት #ማርያም ገዳም አደረሳቸው፡፡ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑም ካስገባቸው በኋላ በውስጥ የነበሩትን ንዋያት ሁሉ እያሳየ ‹‹አንተ ሕፃን ሆይ! ዕወቅ ይህ የምታየው ሁሉ የአንተ ነው፣ ትጠብቀውም ዘንድ #እግዚአብሔር ሰጥቶሃል፡፡ ደግሞም የ #ክርስቶስን በጎች ትጠብቅ ዘንድ ተሰጥቶሃልና ፈጽሞ ደስ ይበልህ›› አላቸውና ፈጥኖ ወደ እናታቸው እቅፍ መለሳቸው፡፡ ዕድሜአቸውም ለትምህርት ሲደርስ ወደ ጉንዳጉንዶ ተመልሰው የሁሉንም መጻሕፍትን ምሥጢር ጠንቅቀው ተማሩ፡፡ በገዳሙም የምንኩስናን ሥራ እየሠሩ በተጋድሎ ኖሩ፡፡ ክብርት #እመቤታችንም ተገልጻላቸው ‹‹ልጄ በተፈቀደልህ ተጋድሎ አሰልጥኖሃልና ጨክን፣ በርታ እኔም ከአንተ አልለይም›› አለቻው፡፡ ከመነኮሱም በኋላ ስማቸው ‹‹አቡነ መዝገበ #ሥላሴ›› ተባሉ፡፡
አቡነ መዝገበ #ሥላሴ ስብከተ ወንጌልን በመላ ሀገራችን በማስፋፋት ብዙ የደከሙ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ‹‹የሐዋርያት አምሳል›› ተብለዋል፡፡ የገዳሙ አበምኔት ሲያርፉ መነኮሳቱ በፈቃደ #እግዚአብሔር አቡነ መዝገበ #ሥላሴን ይዘው በግድ አበምኔትነት ሾሟቸው፡፡ እሳቸውም ከተሾሙ በኋላ በመላ ሀገራችን ተዘዋውረው ወንጌልን ሰብከዋል፡፡ ብዙ ድውያንን ፈውሰዋል፣ ሙታንን አንሥተዋል፡፡ በዓታቸውንም በማጽናት በጸሎት ተወስነው የዐይኖቻቸው ቅንድቦች እስኪላጡ ድረስ ጉንጮቻቸውም እስኪቀሉ ድረስ በጸሎት ይተጉ ነበር፡፡ 40 ቀንና 40 ሌሊትም ይጾማሉ፡፡ ስግደታቸውም በቀንና በሌሊት ያለ እረፍት እንደመንኮራኩር ፈጣን ሆነ፡፡ ወዛቸውና ዕንባቸው አንድ ላይ ተቀላቅሎ እንደጅረት እስኪፈስ ድረስ በጭንቅ ተጋድሎ እንደኖሩ ገድላቸው ይናገራል፡፡ #እመቤታችንም ብዙ ጊዜ እየተገለጠችላቸው ከህመማቸው እየፈወሰች ታበረታቸው ነበር፡፡ ከዕለታትም በአንደኛው ቀን አቡነ መዝገበ #ሥላሴ ራእይ ተመለከቱ፡፡ እነሆም ውበታቸው የሚያስገርም፣ መልካቸውም የሚያስደንቅ፣ የምስጋና ነፀብራቅ የከበባቸው፣ የራሳቸው ፀጉር ነጭ የሆነ ሦስት ወፎችን ተመለከቱ፡፡ አባታችንም አንድ ጊዜ ሦስት ሌላ ጊዜ ደግሞ አንድ ሲሆኑ ተመልክተው ፈጽሞ አደነቁ፡፡ እንዲህ እያደነቁ ሳለ #እግዚአብሔር በቃሉ ጠርቶ ካነጋገራቸው በኋላ ብዙ ምሥጢራትን ነገራቸው፡፡ ለመረጣቸው ቅዱሳን እንዲህ መገለጥ ለ #እግዚአብሔር ልማዱ ነውና ለአባታችን ለአዳም፣ ለሄኖክ፣ ለኖኅ፣ ለአብርሃም በልዩ ልዩ ህብር ተገልጧል፡፡ ኦ.ዘፍ 3፡10፣ 5፡24፣ 6፡13፣ 18፡1 ፡፡ ለሕዝቅኤልም በኮበር ወንዝ፣ ለዳንኤል በሱሳ ግንብ፣ ለኢሳይያስ ሱራፌል እያመሰገኑት ተገልጦላቸዋል፡፡ ሕዝ 1፡1፣ ዳን 8፡1-3፣ ኢሳ 6፡1-3፡፡

አቡነ መዝገበ #ሥላሴ በዘመን ደረጃ በኋለኛው ዘመን የተነሡ አባት ይሁኑ እንጂ በሰጡት ሐዋርያዊ አገልግሎትና ገንዘብ ባደረጉት የተጋድሎ ጽናት የከበሩ ቅዱሳን ሐዋርያትን መስለዋቸዋል፡፡ የታዘዘ መልአክ ወደ መንግሥተ ሰማያት ነጥቆ ወስዶ ማደሪያቸውን አሳይቷቸው መልሶ ወደ ምድር ካመጣቸው በኋላ የዕረፍታቸው ጊዜ እንደደረሰ ነገራቸው፡፡ ‹‹በሰኔ ወር ታርፋለህ›› ቢላቸው ‹‹በሰኔማ ልጆቼ ተዝካሬን ማድረግ አይችሉም›› አሉት፡፡ መልአኩም መልሶ ‹‹ዕረፍትህ በሐምሌ ይሁን›› ቢላቸው ጻድቁ አሁንም ‹‹አይሆንም›› ብለው ተከራከሩ፡፡ በነሐሴም እንደዚያው ሆነ፡፡ መልአኩም መስከረምን አሳልፎ በጥቅምት እንደሚያርፉ ነግሯቸው ዐረገ፡፡ ከዚህም በኋላ ለስም አጠራሩ ምስጋና ይግባውና #ጌታችን ቅድስት እናቱን፣ መላእክትን፣ ቅዱሳን ጻድቃን ሰማዕታትን ሁሉ አስከትሎ መጥቶ ‹‹አንተ የዓሥራ አንደኛው ሰዓት ቅጥረኛ ወዳጄ ሆይ! (ከቅዱሳን ሁሉ በኋላ የተነሣህ-ማቴ 20፡1-5) የምስራች እነግርህ ዘንድ የድካምህም ዋጋ እሰጥህ ዘንድ መጥቻለሁ፡፡ እነሆ ከጠዋት ጀምሮ ከደከሙት ጋር አንድ አድርጌሃለሁ፡፡ ከአንተም ጋር ቃልኪዳን ገብቻለሁ፣ ስምህን በእምነት የጠራ፣ መታሰቢያህን ያደረገ፣ በጸሎትህም የታመነ እስከ ሰማንያ ሺህ ስድስት መቶ (80,600) ነፍሳት ዓሥራት ይሁኑህ…›› በማለት ቃልኪዳን ከገባላቸው በኋላ ወደ ሰማያት ዐረገ፡፡ በዚያን ጊዜም አቡነ መዝገበ #ሥላሴ ፊታቸው እንደፀሐይ አበራና ጥቅምት 9 ቀን ከሌሊቱ በ6 ሰዓት እንደመልካም እንቅልፍ ዐረፉ፡፡ መላ ዘመናቸው 115 ሲሆን የደብረ ገሪዛን ጉንዳጉንዶ ቅድስት #ማርያም ገዳም አበምኔት ሆነው ከመሾማቸው በፊት 62 ዓመት፣ ከተሾሙበት ጊዜ እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው ድረስ 53 ዓመት ነው፡፡ መካነ መቃብራቸው እዚያው የደብረ ገሪዛን ጉንዳጉንዶ ቅድስት #ማርያም ገዳም ይገኛል፡፡

በጉንዳጉንዶና አዲግራት በሚገኘው ገዳማቸው ውስጥ በስማቸው የፈለቁ ብዙ ፈዋሽ ጠበሎች አሉ፡፡ አዲግራት የሚገኘው ገዳማቸው ውስጥ ያለው ጠበል የትኛውንም በሽታ በአስቸኳይ ፈውስ በመስጠት ይታወቃል፡፡ ተጠማቂው ሰው የማይድንም ከሆነ ቶሎ ይሞታል እንጂ ከ7 ቀን በላይ አይቆይም፡፡ ጻድቁ ብዙ የተጋደሉበት ይህ ገዳም በግራኝ አህመድ ዘመን 44 ጽላቶች ተሰውረውበታል፡፡ ዮዲት ጉዲትም ልታገኘው ያልቻለችው ታላቅ ገዳም ነው፡፡ በአንድ ወቅት ከሃዲያን አሕዛብ ጦረኞች ወደ ገዳሙ ሲወጡ በተአምራት ወደ ፅድ ዛፍነት ተለውጠዋል፡፡ ፅዶቹ አሁንም ድረስ በገዳሙ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ፅዶቹን በእሳት አቃጥለው ከሰል ቢያደርጓቸው ደም ሆነው ይፈሳሉ እንጂ ፈጽሞ ከሰል መሆን አይችሉም።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት_9 #ከገድላት_አንደበት)
2025/10/21 21:24:18
Back to Top
HTML Embed Code: