Telegram Web Link
🌹#የጥቅምት_21_ግጻዌ🌹

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_21_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሮሜ 10
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁹ ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤
¹⁰ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና።
¹¹ መጽሐፍ፦ በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም ይላልና።
¹² በአይሁዳዊና በግሪክ ሰው መካከል ልዩነት የለምና፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፥ ለሚጠሩትም ሁሉ ባለ ጠጋ ነው፤
¹³ የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና።
¹⁴ እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ?
¹⁵ መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው ተብሎ እንደ ተጻፈ ካልተላኩ እንዴት ይሰብካሉ?
¹⁶ ነገር ግን ሁሉ ለምሥራቹ ቃል አልታዘዙም። ኢሳይያስ፦ ጌታ ሆይ፥ ምስክርነታችንን ማን አመነ? ብሎአልና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2ኛ ዮሐንስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁵ አሁንም፥ እመቤት ሆይ፥ እርስ በርሳችን እንድንዋደድ እለምንሻለሁ፤ ይህች ከመጀመሪያ በእኛ ዘንድ የነበረች ትእዛዝ ናት እንጂ አዲስ ትእዛዝን እንደምጽፍልሽ አይደለም።
⁶ እንደ ትእዛዛቱም እንሄድ ዘንድ ይህ ፍቅር ነው፤ ከመጀመሪያ እንደ ሰማችሁ፥ በእርስዋ ትሄዱ ዘንድ ትእዛዙ ይህች ናት።
⁷ ብዙ አሳቾች ወደ ዓለም ገብተዋልና እነርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የማያምኑ ናቸው፤ ይህ አሳቹና የክርስቶስ ተቃዋሚው ነው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 2
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁴ ነገር ግን ጴጥሮስ ከአሥራ አንዱ ጋር ቆመ፥ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ተናገራቸው፦ አይሁድ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁላችሁ፥ ይህ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፥ ቃሎቼንም አድምጡ።
¹⁵ ለእናንተ እንደ መሰላችሁ እነዚህ የሰከሩ አይደሉም፥ ከቀኑ ሦስተኛ ሰዓት ነውና፤
¹⁶ ነገር ግን ይህ በነቢዩ በኢዩኤል የተባለው ነው።
¹⁷ እግዚአብሔር ይላል፦ በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፥ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፥ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ፤
¹⁸ ደግሞም በዚያች ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ ትንቢትም ይናገራሉ።
¹⁹ ድንቆችን በላይ በሰማይ፥ ምልክቶችንም በታች በምድር እሰጣለሁ፤ ደምም እሳትም የጢስ ጭጋግም ይሆናል፤
²⁰ ታላቅ የሆነ የተሰማም የጌታ ቀን ሳይመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ።
²¹ የጌታን ስም የሚጠራም ሁሉ ይድናል።
²² የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ ይህን ቃል ስሙ፤ ራሳችሁ እንደምታውቁ፥ የናዝሬቱ ኢየሱስ እግዚአብሔር በመካከላችሁ በእርሱ በኩል ባደረገው ተአምራትና በድንቆች በምልክቶችም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእናንተ የተገለጠ ሰው ነበረ፤
²³ እርሱንም በእግዚአብሔር በተወሰነው አሳቡና በቀደመው እውቀቱ ተሰጥቶ በዓመፀኞች እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_21_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇🌹

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ወገሠጸ ነገሥተ በእንቲአሆሙ። ኢትግሥሡ መሲሐንየ። ወኢታኅሥሙ ዲበ ነቢያትየ። መዝ.104÷14-15

#ትርጉም፦ “የቀባኋቸውን አትዳስሱ፥ በነቢያቴም ክፉ አታድርጉ ብሎ፥ ሰው ግፍ ያደርግባቸው ዘንድ አልፈቀደም፥ ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ።” መዝ.104÷14-15
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_21_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዮሐንስ 11
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³⁸ ጌታችን ኢየሱስም በራሱ አዝኖ ወደ መቃብሩ መጣ፤ እርሱም ዋሻ ነበረ፤ ድንጋይም ተገጥሞበት ነበር።
³⁹ ጌታችን ኢየሱስ፦ ድንጋዩን አንሡ አለ። የሞተውም እኅት ማርታ፦ ጌታ ሆይ፥ ከሞተ አራት ቀን ሆኖታልና አሁን ይሸታል አለችው።
⁴⁰ ጌታችን ኢየሱስ፦ ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር እንድታዪ አልነገርሁሽምን? አላት።
⁴¹ ድንጋዩንም አነሡት፦ ጌታችን ኢየሱስም ዓይኖቹን ወደ ላይ አንሥቶ፦ አባት ሆይ፥ ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ።
⁴² ሁልጊዜም እንድትሰማኝ አወቅሁ፤ ነገር ግን አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ በዚህ ዙሪያ ስለ ቆሙት ሕዝብ ተናገርሁ አለ።
⁴³ ይህንም ብሎ በታላቅ ድምፅ፦ አልዓዛር ሆይ፥ ወደ ውጭ ና ብሎ ጮኸ።
⁴⁴ የሞተውም እጆቹና እግሮቹ በመግነዝ እንደ ተገነዙ ወጣ፤ ፊቱም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበር። ጌታችን ኢየሱስም፦ ፍቱትና ይሂድ ተዉት አላቸው።
⁴⁵ ስለዚህ ወደ ማርያም ከመጡት፥ ጌታችን ኢየሱስም ያደረገውን ካዩት ከአይሁድ ብዙዎች በእርሱ አመኑ፤
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ 🌹
  የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታችን #የማርያም_ቅዳሴ ነው። መልካም የ #እመቤታችን የተዓምር በዓል፣ የነብዩ ቅዱስ ኢዩኤል የዕረፍት በዓል፣ የቅዱስ አልዓዛር የሥጋው ፍልሰት፣ የቅዱስ አላኒቆስ የዕረፍት በዓል እና የጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።
🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነቢዩ_ኢዩኤል

በስመ #አብ_ወወልድ_ወመንፈስ_ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

#ኢዩኤል” ማለት “ #እግዚአብሔር አምላክ ነው” ማለት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱሳችን እንደምንመለከተውም “ኢዩኤል” የሚለው ስም በዕብራውያን የተለመደ መኾኑ ነው /፩ኛ ሳሙ.፰፡፪፣ ፩ኛ ዜና ፬፡፴፭፣ ፪ኛ ዜና ፳፱፡፲፪፣ ዕዝራ ፲፡፵፫/፡፡
አባቱ ባቱአል እናቱም መርሱላ ይባላሉ፡፡ የመጽሐፉ የአንድምታ ትርጓሜ መቅድም እንደሚናገረው ነገዱ ከነገደ ሮቤል ወገን ነው፡፡ ሌሎች ሊቃውንት ግን ኢዩኤል ከነገደ ይሁዳ ወገን እንደኾነ ይናገራሉ፡፡ ለዚኽ አባባላቸው እንደ ማስረጃ የሚያስቀምጡትም አንደኛ ኢዩኤል ይኖር የነበረው በኢየሩሳሌም መኾኑ፤ ኹለተኛ በመጽሐፉ ስለ ካህናት ማንሣቱ /፩፡፲፫/፤ ሦስተኛ ስለ ቤተ መቅደስ መናገሩ /፩፡፱/፣ እና ሌላም ሌላም በማለት ነው፡፡

በብዙ ሊቃውንት ዘንድ ነቢዩ ኢዩኤል የነበረበት ዘመን ላይ ልዩነት አለ፡፡ አንዳንዶቹ ከምርኮ በፊት ነበረ ሲሉ ሌሎች ደግሞ “አይደለም ከምርኮ በኋላ የነበረ ነው” ይላሉ፡፡ ኹለቱንም ወገኖች የሚያቀርቡትን ማስረጃ እናስቀምጥና አንባብያን የየትኞቹ አሳማኝ እንደኾነ ማየት ይችላሉ፡፡ አስቀድመንም “ከምርኮ በኋላ ነበረ” የሚሉትን እንመልከት፡፡ እነዚኽ ሊቃውንት ነቢዩ ኢዩኤል ከምርኮ በኋላ ነበረ ለማለት ያነሣሣቸው፡-
1.ነቢዩ ኢዩኤል በዘመኑ ስለ ነበረው ንጉሥ ሳይናገር ይልቁንም ስለ ካህናትና ስለ ሽማግሌዎች መናገሩ በእስራኤልና በይሁዳ ከምርኮ ከተመለሱ በኋላ ንጉሥ ስላልነበራቸው ነው፡፡

2.ነቢዩ ኢዩኤል ስለ ሰሜናዊው ግዛት ማለትም ስለ እስራኤል አለመናገሩና ስለ ይሁዳ ብቻ መናገሩ ዘመኑ ከምርኮ በኋላ መኾኑ ያመለክታል፡፡

3.ነቢዩ ኢዩኤል ከኢየሩሳሌም ውጪ በሰማርያ ስለ ነበሩ የአምልኮ ዐፀዶች ምንም አላለም፡፡ ስለ አምልኮተ ጣዖትና ስለ በኣልም ምንም አላለም፡፡ እነዚኽ ደግሞ ገንነው ይታዩ የነበረው ከምርኮ በፊትና በምርኮው ጊዜ እንጂ ከምርኮ በኋላ አይደለም፡፡

4.ነቢዩ ካህናቱን፡- “የ #እግዚአብሔር አገልጋዮች” ብሎ ጠርቷቸዋል /፩፡፲፫/፡፡ ይኽ ዓይነቱ አጠራር ደግሞ ከምርኮ በኋላ ባለው ጊዜ በጣም በተደጋጋሚ ይዘወተር የነበረ አባባል ነው፡፡

አኹን ደግሞ “ከምርኮ በፊት የነበረ ነው” የሚሉ ሊቃውንት ለትምህርታቸው እንደ ማስረጃ የሚያቀርቡትን እንመልከት፡-
1.ነቢዩ በጊዜው የነበረውን ንጉሥ ማን እንደኾነ አለመጥቀሱ ንጉሡ ገና ሕፃን ስለ ነበረ ሊኾን ይችላል፡፡ ይኸውም ኢዮአስ መንገሥ የዠመረው በሰባት ዓመቱ እንደነበረ ማለት ነው /፪ኛ ዜና.፳፬፡፩/፡፡ ሕፃን ከኾነ ደግሞ የሚነገረው ነገር ማመዛዘን ስለማይችል፡- “እገሌ ንጉሥ ሳለ እንዲኽ ያለ ትንቢት ተናገርኩ” ቢል ተቀባይነት የለውም፡፡ ወይም ደግሞ ነቢዩ የሚፈልገው የሕዝቡን የ #ንስሐ ሕይወት እንጂ የፖለቲካ ጉዳይ ስላልኾነ ነው፡፡

2. ነቢዩ ስለ አምልኮተ ጣዖት፣ ወይም ስለ በዓል አለመናገሩ የትንቢት መጽሐፉን ከምርኮ በኋላ መጻፉን አያመለክትም፡፡ ይልቁንም የስብከቱ መንገድ አንዱን አቅጣጫ ማለትም ስለ በዓልና ስለ አምልኮተ ጣዖት ሳይናገር #እግዚአብሔርን በንጹሕ ልቡና ማምለክ እንዳለባቸው መንገርን ስለ መረጠ ነው፡፡

3.ብዙ ነቢያት ለምሳሌ እነ ቅዱሳን ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ፣ ሕዝቅኤል እና አሞጽ ከትንቢተ ኢዩኤል መጽሐፍ ጠቅሰው ተናግረዋል፡፡ ስለዚኽ ነቢዩ ከእነዚኽ በፊት ነበረ ማለት ነው፡፡

4.ነቢዩ ኢዩኤል ምርኮ እንደሚኾን ተናገረ እንጂ እንደኾነ አልተናገረም /ኢዩ.፫፡፪-፫/፡፡ ይኽም ከምርኮ በፊት እንደ ነበረ ያስረዳል፡፡

5.ነቢዩ ግብጽ የይሁዳ ባላንጣ እንደኾነች ተናግሯል /፫፡፲፱/፡፡ ይኽም ከምርኮ በፊት እንጂ ከምርኮ በኋላ ሊኾን አይችልም፡፡ ከዚኽም በተጨማሪ ከምርኮ በፊት ስለነበሩ የይሁዳ ጠላቶች ማለትም ስለ ጢሮስ፣ ስለ ሲዶና፣ ስለ ፍልስጥኤማውያን /፫፡፬/፣ ስለ ኤዶምያስ /፫፡፲፱/ መናገሩ ነቢዩ ከምርኮ በፊት እንደነበረ ያሳያል፡፡

6. ነቢዩ ስለ ሰሜናዊው መንግሥት ማለትም ስለ እስራኤል አለመናገሩና ጠቅለል አድርጐ ስለ እስራኤል መናገሩ አንደኛ ኹለቱም ሕዝቦች አንድ በመኾናቸው /፪፡፳፯፣ ፫፡፲፮/፤ ኹለተኛው የነቢዩ አገልግሎት በይሁዳ ስለነበር፤ ሦስተኛውና ዋናው ደግሞ ነቢዩ በትንቢት መነጽር በአዲሲቱ እስራኤል (በቤተ ክርስቲያን) መለያየት እንደሌለና ኹሉም አንድ እንደሚኾኑ ሲናገር ነው፡፡

🌹 #ትንቢተ_ኢዩኤል 🌹

ምንም እንኳን ነቢዩ ኢዩኤል የይሁዳን ከተማ የሚወርራት አስፈሪውን የአንበጣ መንጋ ድምፅ ቢሰማም፤ ምንም እንኳን የአንበጦቹ መንጋ ሰማዩን ሲከድነው፣ ፀሐይቱ ስትጨልም፣ ኹሉም ጭጋጋም ኾኖ ቢመለከትም፤ ምንም እንኳን ዛፉ ኹሉ ደርቆ ምድሪቱ ምድረ በዳ ስትኾን ቢያይም ከዚያ ጀርባ የነበረችይቱን የ #እግዚአብሔር ጣትም ያይ ነበር፡፡ የ #እግዚአብሔር እጅ ይኽን ኹሉ እንዳደረገችና ሕዝቡን ለመቈንጠጥ ጥበብ ሰማያዊ መኾኑን ያስተውል ነበር፡፡

ነቢዩ ኢዩኤል፥ ሕዝቡ የአንበጦቹን ቋንቋ አላደምጥ ሲል የድርቁን ተግሳጽ አልሰማ ሲል በምርኮ እንደሚኼድ ቢመለከትም ይኽም የ #እግዚአብሔር ፈቃድ እንደነበረ በትንቢት አጉሊ መነጽር አይቷል፡፡ ደጋግሞ “የጨለማና የጭጋግ ቀን፣ የ #እግዚአብሔር ቀን” እያለ የጠራትም ይኽቺው የሕዝቡ የምርኮ ቀን ናት /፪፡፩-፫/፡፡

ምንም እንዲኽ ቢኾንም ግን #እግዚአብሔር ሕዝቡን ያለ አንዳች ተስፋ እንዳልተዋቸውም ጨምሮ ተናግሯል፤ መንፈሱን በሥጋ ለባሽ ኹሉ ላይ እንደሚያፈስና የሰው ልጆችን በሙሉ ለታላቂቱ የ #ጌታ ቀን እንደሚያዘጋጃቸው አብሮ ተናገረ እንጂ፡፡ በዚኽም #እግዚአብሔር ራሱ ረዳት እንደሚኾናቸውና ለክፉዎቹ የጨለማ ቀን እንደሚኾንባቸው ለመልካሞቹ ግን የብርሃን ቀን እንደሚኾንላቸው ተናገረ፡፡

መጽሐፉ በአጠቃላይ #እግዚአብሔር በሰው ልጆች ላይ ያለውን ዕቅድ የሚያስረዳ ነው፡፡ #እግዚአብሔር ሕዝቡን በተለያየ ቋንቋ (በአንበጦቹ፣ በድርቁ፣ በምርኮው …) ሲያናግራቸው አንዳች ነገር ከእነርሱ አልሰወረባቸውም፤ የክብሩ ተካፋይ ይኾኑ ዘንድ #መንፈስ_ቅዱስ ስንኳ ከመስጠት አልከለከላቸውም፡፡

ይኽ መጽሐፍ #መንፈስ_ቅዱስ በሥጋ ለባሽ ኹሉ ላይ እንደሚፈስ የሚያስረዳ መጽሐፍ ነው፡፡ ሌሎች ነቢያት ክብር ይግባውና #ጌታችንና_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በድንግና ተፀንሶ በድንግልና ተወልዶ የዓለምን ኃጢአት እንደሚያስወግድ ሲናገሩ ትንቢተ ኢዩኤል ግን ስለ ዓለም ኃጢአት ስለ ጽድቅም ስለ ፍርድም ዓለምን ስለሚወቅስ ስለ #መንፈስ_ቅዱስ አብዝቶ የሚናገር መጽሐፍ ነው /ዮሐ.፲፮፡፰/፡፡ ነቢዩ ኢዩኤል አብዝቶ የሚናገረው #ጌታችንና_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በደሙ የዋጃትን ቤተ ክርስቲያን በጽድቅና በቅድስና እንድትቀጥል ስለሚያድገው አጽናኝ #መንፈስ_ቅዱስ ነው፡፡ አብዝቶ የሚናገረው በረኻ የኾነውን የሰውን ልቡና ምድረ ገነት ወደመኾን ስለሚለውጠው #መንፈስ_ቅዱስ ነው፡፡

ነቢዩ የአንበጣ መንጋ ዘሩን፣ ዛፉን፣ ቅጠሉን ጨርሶት እርሻውም ኹሉ ደርቆ ምድረበዳ እንደኾነ መናገሩ ኃጢአት የተባለ አንበጣ “የ #እግዚአብሔር እርሻ፣ ወይን፣ በለስ፣ ሮማን፣ ተምር፣ እንኮይ፣ የምድር ዛፍ” የተባለውን የሰውን ልጅ ክብሩን እንዳሳጣው ሲናገር ነው /፩፡፲፪/፡፡ የኃጢአት እሳት፥ እርሻ የተባለውን ሰው እንደበላ (እንዳቃጠለ) አስቀድሞ መናገሩ ይኽን እርሻ ዳግም ወደ ገነት የሚመልስ ሌላ እሳት (ይኸውም #መንፈስ_ቅዱስ ነው) እንደሚያስፈልግ ይናገር ነበር፡፡
ሊቃውንት እንደሚናገሩት፡- “ምንም እንኳን ነቢዩ ኢዩኤል ደጋግሞ የ #ጌታ ቀን፣ የ #እግዚአብሔር ቀን እያለ ቢናገርም ይኽን መቼ እንደተናገረው፣ በእርሱ ዘመን የነበሩ ነገሥታትም እነማን እንደኾኑ አለመጥቀሱ መጽሐፉ ለትውልድ ኹሉ መጻፉን የሚያመለክት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ የ #ጌታ ቀን ብለን የምናውቃት የምጽአት ቀን መቼ እንደኾነች የሰው ልጅ በሙሉ እንዳያውቃትና ይልቁንም ዘወትር ዝግጁ ኾኖ እንዲኖር ከመሻት አንጻር ነው” ይላሉ፡፡

ምንም እንኳን እያንዳንዱ የ #እግዚአብሔር ነቢይ ሕዝቡ ከኃጢአት እንዲመለስ ለማድረግ #እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ሊያመጣ ያሰበውን ቁጣ ቢናገሩም በአጠቃላይ ግን የመሲሑን የማዳን ሥራ፣ የዳዊት ልጅ፣ መንፈሳዊው ንጉሥ፣ አገራትን ኹሉ ወደ አባቱ ዕቅፍ የሚያመጣውን መሲሕ በተዋሕዶ ከብሮ እንደሚመጣ በመናገር ነው፡፡ ሕዝቡ ከሚደርስባቸው ጊዜአዊ ችግር ተሸግረው ይኽን የመሲሑ ዘመን እንዲመለከቱ ያደረጉበት መንገድ ግን የተለያየ ነው፡፡ ቅዱሳን ኢሳይያስ፣ አሞጽና ሚክያስ #ንስሐ ላይ ትኩረት ያደርጋሉ፤ ቅዱሳን ዕዝራና ነህምያ የ #እግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና የኢየሩሳሌምን አጥር በማነፅ እንዲመለሱ ያደርጋሉ፤ ቅዱሳን ሕዝቅኤልና ኤርምያስ ደግሞ አፍአዊ በኾነ መንገድ ሳይኾን ልቡናቸውን ለውጠው ወደ #እግዚአብሔር መምጣት እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡ ነቢዩ ኢዩኤል ግን አፍአዊውን የኢየሩሳሌም ቅጥር፣ የቤተ መቅደሱን መታነፅ፣ የካህናቱን አኳኃን ቢመለከትም ስለ ውሳጣዊቷ ኢየሩሳሌም፣ ስለ ምስጢራዊው ቤተ መቅደስ፣ ስለ ልቡናም ጨምሮ ይናገራል፡፡ ነቢዩ፥ የ #እግዚአብሔር ሕዝብ ግላዊ በኾነ እይታ እንዲመለከት አይጋብዝም፤ የቤተ ክርስቲያን ሕዋስ እንደመኾኑ “እኛ” በሚል መንፈስ ይናገራል እንጂ፡፡ በደሉን የሠሩት በአንድ ላይ እንደመኾናቸው መመለስም ያለባቸው በአንድ ላይ መኾን እንዳለባቸው ይናገራል፡፡ አንዱ አንዱን እንዲረዳ ያበረታታል፡፡

ነቢዩ ኢዩኤል “የኦሪት ነቢይ” እየተባለ ይጠራል፤ ይኸውም ከአምስቱ የሙሴ መጻሕፍት ፳፭ ጊዜ ጠቅሶ ስለሚናገር ነው፡፡ ዳግመኛም ስለ #መንፈስ_ቅዱስ አብዝቶ ስለሚናገር“የ #ጰንጤ_ቆስጤ ነቢይ” ይባላል፡፡

🌹 #መጽሐፉን እንደሚከተለው መክፈል እንችላለን፡-

1. የአንበጣ መንጋ አገሩን እንደወረረ /ምዕ. ፩/፤
2. ጠላት መጥቶ እንደሚወራቸው /ምዕ. ፪፡፩-፳፯/፤
3. ርደተ #መንፈስ_ቅዱስ /ምዕ. ፪፡፳፰-፴፪/፤
4. ታላቂቱ የ #እግዚአብሔር ቀን /ምዕ. ፫/።

#ተመስጦ
ቸርና #ቅዱስ_እግዚአብሔር_ሆይ! ነቢዩ ኢዩኤል እንደተናገረ ኃጢአት እንደ አንበጣ መንጋ ኹለንተናችን ወረረው፡፡ የመንፈስ ፍሬ እንዳናፈራ የኃጢአት ኩብኩባ ልቡናችንን በላው፡፡ ገነት ልቡናችንንም ምድረበዳ አደረገው፡፡ የኃጢአት መንጋ መቅደስኽ ልቡናችንን አቆሸሸው፡፡ ደስታ ከእኛ ዘንድ ራቀ፡፡ የንጉሥ ልጆች ብንኾንም በገዛ ፈቃዳችን “ገብሩ ለዲያብሎስ፣ አመቱ ለዲያብሎስ” ተብለን ወደ ባርነት ኼድን፡፡ መዓዛ መለኮትኽ ከእኛ ዘንድ ራቀ፡፡ በረከትኽን አርቀን ፍርድን በላያችን ላይ ጨመርን፡፡ አንተም ከገነት እንድንወጣ አደረግከን፡፡
ቅዱስና ርኅሩኅ አባት ሆይ! ከገነት እንድንወጣ ማድረግኽ ግን የፍቅርኽ መገለጫ ነበር፡፡ ከገነት ስታወጣን ዕድፈታችንን አስወግደኽ ዳግም ወደ ጥንተ ተፈጥሮአችን ለመመለስ ነበርና ከፍቅርኽ የተነሣ ወጣን፡፡ ወዮ! ከቁንጥቻኽ ጋር አብሮ የሚታየው ፍቅርኽ እንደምን ይረቃል? እንደምን ይመጥቃል? ከቁንጥጫኽ ጀርባ ያለው የፍቅር እጅኽን ያየ ሰውም ንዑድ ክቡር ነው፡፡
#ቅዱስ_አባት_ሆይ! ስንወጣም እንደወጡ ይቅሩ አላልከንም፡፡ እንደቃልኽ ፈለግከን እንጂ፡፡ እንደ ፍቅርኽ በትከሻኽ ተሸከምከን እንጂ፡፡ ፍርዳችንን ተሸክመኽ ዳግም ልጆችኽ አደረግከን እንጂ፡፡ በቈሰለው ማንነታችን፣ በመረቀዘው ልቡናችን ላይ ዘይትን አፈሰስክልን፡፡ ቅድስናችን አንተው ራስኽ ኾንከን፡፡ ይኽም ሳይበቃ ቅድስናችንን እንዳናቆሽሽ መጽንዒ #መንፈስ_ቅዱስን ላክልን፡፡ በረኻው ልቡናችንንም ገነት ወደ መኾን መለስክልን፡፡
እኛ ግን የተደረገልንን ረስተን የኃጢአት አንበጣ የኃጢአት ኩብኩባና ደጎብያ እየጠራን እንገኛለን፡፡ #ቅዱስ_አባት_ሆይ! አንተ ግን አትተወን፡፡ #ቅዱስ_መንፈስኽን አትውሰድብን፡፡ ከምርኮ መልሰን፡፡ ደካሞች ነንና እርዳን፡፡ መሻት እንጂ ብርታቱ የለንምና ደግፈን፡፡ ለታላቂቱ ቀን የተዘጋጀን አድርገን፡፡ አሜን!!!

ዋቢ ድርሳናት፡- ➣የትንቢተ ኢዩኤል አንድምታ፤
➣የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት
🌹 "በስመ #አብ_ወወልድ_ወመንፈስ_ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። 🌹

#ጥቅምት ፳፩ (21) ቀን። እንኳን #ለኢትዮጵያዊው_ጻድቅ መሰቀልህን በቅዱሳት መጻሕፍት ሰማሁ ይኽን በዐይኔ አሳየኝ በማለት #መድኃኔዓለምን_ለጠየቁት_እሱም ለገለጸላቸው፤ የንጉሡን መልዕክተኞች ከንጉሡ ቤት እንገናኝ በማለት መልዕክተኞቹ ዘጠኝ ቀን ተጉዘው ሲደርሱ እሳቸው ቀድመዋቸው ንጉሡ ቤት ለተገኙት #አቡነ_ዐሥራተ_ወልድ_ለዕረፍታቸው በዓል #እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።

                              
🌹 #አቡነ_ዐሥራተ_ወልድ፦ በዳሞት አውራጃ ልዩ ስሟ እነሴ በምትባል ቦታ በዐፄ ሠርጸ ድንግል ዘመነ መንግሥት በ1584 ዓ.ም ተወለዱ። አባታቸው ፃማ #ክርስቶስ እናታቸው ጽጌ #ማርያም ይባላሉ። ኹለቱም በሕገ #እግዚአብሔር ጽንተው የሚኖሩ በሃይማኖት በምግባር የተመሰገኑ በተጋድሎ በትሩፋት የታወቁ ክርስቲያኖች ነበሩ ነገር ግን ልጅ ስላልነበራቸው እንደ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ የተባረከ ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ ሁልጊዜ #እግዚአብሔርን በጸሎት ይጠይቁ ነበር አምላክን የወለደች ክብርት #እመቤታችንንም ይማጸኗት ነበር።

ኹለቱም #እግዚአብሔርን የሚፈሩ በምድራዊ ሀብትም የበለጸጉ ነበሩ፤ ለድኖችና ለምስኪኖች አብዝተው ይመጸውቱ ስለነበር ከጾማቸው በኋላ ያለ ድኖችና ምስኪኖች ብቻቸውን አይመገቡም ነበር። #እግዚአብሔርም ጸሎት ልመናቸውን ተቀብሎ የተባረከ ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ ወደደ። ከዕለታትም በአንደኛው ቀን የ #እግዚአብሔር ሰው ለጽጌ #ማርያም ታይቶ "ዝናው በአራቱ ማዕዘን ኹሉ የሚደርስ በሕይወተ ሥጋ እያለ የብዙ ሰዎችን ነፍስ በጸሎቱ ከኃጢአት ወደ ጽድቅ የሚያወጣ ወደ ሰማይም ወጥቶ የ #ሥላሴን ምሥጢር የሚያይ የተባረከ ልጅን ትወልጂ ዘንድ አለሽና ደስ ይበልሽ" በማለት ካበሠራት በኋላ አቡነ ዐሥራተ ወልድ ሰኔ ሃያ ቀን ተወለዱ።

ጻድቁም በተወለዱ በስምንተኛ ቀናቸው "ለ #አብ ምስጋና ይገባል ለ #ወልድ ምስጋና ይገባል ለ #መንፈስ_ቅዱስ ምስጋና ይገባል" ብለው ፈጣሪያቸውን አመስግነዋል። እስከ ዐሥራ ኹለት ዓመታቸውም ድረስ ውኃ በመቅዳት ዕንጨት በመስበር ወላጆቻቸውን ካገለገሉ በኋላ ወላጆቻቸው ወደ ታላቁ ጻድቅ ወደ አቡነ ተጠምቀ መድኅን ዘንድ ወስደው እንዲያስተምሩላቸው አደራ ብለው ሰጧቸው።

አቡነ ተጠምቀ መድኅንም ዐሥራተ ወልድን ተቀብለው የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር ኹሉ አስተማሯቸው። በሚማሩበትም ጊዜ #መንፈስ_ቅዱስ በአፋቸው ያቀብላቸው ስለነበር አስቀድመው የተማሩ ይመስሉ ነበር። በሦስት ዓመትም ውስጥ መጻሕፍተ ብሉያትን መጻሕፍተ ሐዲሳትን መጻሕፍተ መነኰሳትን፣ አዋልድ መጻሕፍትንም ኹሉ ከነትርጓሜያቸው ከአቡነ ተጠምቀ መድኅን ተምረው #እግዚአብሔርም ከሐሰት መጻሕፍት ከሟርት ከጥንቆላ መጻሕፍት በቀር ያልገለጠላቸው የመጻሕፍት ምሥጢር የለም። የመላእክትንና የቅዱስ ያሬድንም ዜማ ገለጠላቸው።

ከዚኽም በኋላ አቡነ ዐሥራተ ወልድ ለመመንኰስ ወላጆቻቸውን አስፈቅደው ከመምህራን ጋር ወደ ታላቁ ገዳም ወደ ደብረ ዳሞ ሔደው በዚያም መነኰሳቱን እያገለገሉ ለ25 ዓመታት ያህል በተጋድሎ ከኖሩ በኋላ በዐፄ ፋሲል ዘመን መንግሥት በ40 ዓመታቸው በ1624 ዓም መንኰሱ። ከሊቀ ጳጳሱ ከአቡነ ሚካኤልም እጅ የቅስና ማዕረግ ተቀበሉ። ከዚኽም በኋላ ከመምህራቸው ከአቡነ ተጠምተ መድኅን ጋር ወደ ጋሾላና ጉሓን ገዳማት ሔደው ተጋድሏቸውን ጨምረው መጾም መጸለይን አበዙ። ወደ ተራራ ሔደው ዳዊት ሲያነቡ ያድራሉ፣ ምሥራቅም ዙረው አምስት መቶ ጊዜ ይሰግዳሉ፤ ወደ ምዕራብም ዙረው አምስት መቶ ጊዜ ይሰግዳሉ፤ ወደ ሰሜንም ዙረው አምስት መቶ ጊዜ ይሰግዳሉ ወደ ደቡብም ዙረው እምስት መቶ ጊዜ ይሰግዳሉ፤ እንዲህም እያደረጉ በየዕለቱ ኹለት ሺህ ይሰግዱ ነበር። ላባቸው እንደ ውኃ ፈስሶ ምድርን እስኪያርስ ድረስ ይሰግዳሉ፤ የቆሙበትም ምድር እንደ ጉድጓድ ይጎደጉዳል። እንደዚህ ባለ ታላቅ ተጋድሎ ጸንተው ብዙ ዘመን ኖሩ። የ #ጌታችንንም ዐርባ ጾም ምንም ሳይቀምሱ ዐርባውን ቀን ይጾሙ ነበር።

ከዚኸም በኋላ አቡነ ዐሥራት ወልድ ጃባ በሚባለው ቦታ ዐሥራ አንድ ዓመት በተጋድሎ ኖሩ። አባታችን ያከብሯት የነበረች ቅዱስ ሉቃስ የሣላት የክብርት #እመቤታችን ሥዕል በዚያ ነበረችና እርሷም ድንቅ ድንቅ ተኣምራትን ታደርግላቸው ነበር። ጃባ በምትባል ቦታም ዘወትር ታነጋግራቸው ነበር። በአንደኛውም ሌሊት ተኝተው ሳሉ አምላክን በድንግልና የወለደች ክብርት #እመቤታችን ተገልጣላቸው "ልጄ ወዳጅ ዐሥራተ ወልድ ሆይ! በጸሎትና በልመናህ የጃባ ሰዎች ኹሉ ይድናሉ፣ በቃልህ #ክርስቶስን አምነው በእጅህ #ቅዱስ_ሥጋውንና #ክቡር_ደሙን ይቀበላሉ" አለቻቸው።

ከዚኽም በኋላ የታዘዘ የ #እግዚአብሔር መልአክ ለኹለቱም ቅዱሳን ተገልጦላቸው አቡነ ተጠምቀ መድኅንን ወደ ጋዝጌ እና ወደ መተከል ሔደው የከበረች ወንጌልን እንዲያስተምሩ ሲያዛቸው አቡነ ዐሥራተ ወልድን ደግሞ ወደ ጫራ ምድር ሔደው በዚያ ወንጌልን ይሰብኩ ዘንድ አዘዛቸው። ኹለቱም ቅዱሳን እርስ በርሳቸው በመንፈሳዊ ሰላምታ እጅ ተነሣሥተው ለሐዋርያዊ አገልግሎት ተለያይተው ወደታዘዙባቸው ቦታዎች ሔዱ። አባታችን ዐሥራተ ወልድም እየጸለዩ ስምንት ዓመት ከስድስት ወር በርበር በምትባል በረሓ ውስጥ ሳሉ በአራቱም ማዕዝናት እየተዘዋወሩ በምሥራቅ አንድ ሽህ በምዕራብ አንድ ሺህ በሰሜን አንድ ሺህ በደቡብ አንድ ሺህ ጊዜ ይስግዱ ጀመር የክብር ባለቤት #ጌታችን_አምላካችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም በዚህ ጊዜ ተገልጦላቸው "ወዳጀ ዐሥራተ ወልድ ሆይ! ለምን ሥጋህን እንደዚህ አደከምህ" አላቸው አባታችንም " #ጌታ ሆይ! ኃይላቸውን በስግደት ቀንና ሌሊት በመትጋት የሚያደክሙ በመንግሥትህ አይደሰቱምን በዓለም የደከመ ለዘለዓለም ይድናል ጻድቃን ዳግመኛም በብዙ ድካምና መከራ ወደ #እግዚአብሔር መንግሥት እንገባ ዘንድ ይገባናል" እንዳለ በማለት መለሱ። #ጌታችን_መድኀኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ "ድካምህ በከንቱ አትቀርም በሰማያውያን መላእክት በተባረኩ ጻድቃን ድል በነሱ ሰማዕታት ንጹሐን በሚሆኑ ደናግል በፍጹማን መነኰሳት ፊት የድካምህን ዋጋ እሰጥሃለሁ። እንግዲህ ከዛሬ ጀምረህ ወደ አዘዝኩህ ቦታ ሒድ፤ "መንግሥተ ሰማያትም ቀርባለች" እያልህ የመንግሥትን ወንጌል አስተምር፣ ኃይሌ ከአንተ ጋር ይኖራልና" ብሎ አዘዛቸው።

#ጌታችን ይህን ሲነግራቸው አውሎ ነፋስ መጥቶ ጉርብ ወደ ምትባለው ዋሻ ወስዶ አደረሳቸው። በሥራ የሚኖሩ የሀገሩ ሰዎችም የአባታችን ዐሥራተ ወልድን መምጣት ሰምተው ተቆጥተው በአባታችን ላይ በጠላትነት ተነሡባቸው፣ ጋሻቸውንና ጦራቸውን ይዘው የመጡ ቢሆንም አባታችን ግን የከበረች የ #ክርስቶስን ወንጌል አስተምረው አሳምነው አጠመቋቸው። የጫራንም ሕዝብ አምስት ዓመት ካስተማሯቸው በኋላ ዳግመኛ የሻሽናን ሕዝብ ያስተምሯቸው ዘንድ የ #እግዚአብሔር መልአክ እየመራው ሻሽና አደረሳቸው። አባታችን በዚያም የሀገሩን ሕዝብ አስተምረው አጠመቁ።
የጎንደር ንጉሥ ጻድቁ ዮሐንስ የአባታችን ዐሥራተ ወልድን ቅድስናና ገድል በሰማ ጊዜ ወደ እርሱ ያመጧቸው ዘንድ መልእክተኞችን ላከ፤ መልእክተኞችም አባታችንን በሻሽና አገኟቸው፤ አባታችን ግን መልእክተኞቹን "ልጆቼ እኔ ኃጢአተኛ ስሆን ከጎንደር እስከ ሻሽና ንጉሡ ምን ብሎ ላካችሁ?" አሏቸው። ይኸንንም ተናግረው የንጉሥን ጭፍራ "ወደ እናንተ እስክመለስ ድረስ ከዚኸ ጠብቁ" ብለው ወደ ንጉሡ ዘንድ ከመሔዳቸው በፊት ወደ ጸሎት ቤት ገብተው ከዳዊት መዝሙር ጸለዩ። ጸሎታቸውንም ከፈጸሙ በኋላ አባታችን ወደ እነርሱ ተመልሰው "እኔ ሽማግሌ ሰው ነኝ ወደ ጎንደር ለመሔድ አልችልም" አሏቸው። እነርሱም "አባታችን ሆይ! አንተ ከእኛ ጋር ካልሔድህ ተመልሰን አንሔድም" አሉ። አባታችንም እጅግ አዝነው "ልጆቼ ሒዱ እኛ እርሰ በእርሳችን በንጉሡ ቤት እንገናኘለን አሏቸውና ተመልስው ሔዱ ተመልስው ከሔዱ በኋላ ወደ ንጉሡ ቤት ቢደርሱ አባታችንን ከንጉሡ ጋር ተቀምጠው አገኟቸው።

የንጉሡ መልእክተኞችም ለንጉሡ "እኛ ከሻሽና ከተነሣን እስከዚህ ዘጠኝ ቀናችን ነው ይኽ አባት የሚያስደንቅ ተአምር እያደረገ በየት አለፈን?" ብለው እጅግ ተገረሙ። ንጉሡም ይኽን ድንቅ ተኣምር በስማ ጊዜ ከአባታችን እግር ሥር ሰገደ አቡነ ዐሥራተ ወልድንም "አባቴ ሆይ አስተምረህ ላሳመንኽውና ለአጠመቅኽው ሕዝብ ታቦትን ወስደህ ቤተክርስቲያን ሥራ ከታቦታትም የወደዱኻውን ምረጥ"። በማለት ጠየቃቸው። ብፁዕ አባታችን ዐሥራተ ወልድም "በጣም የምወዳት እንደ ምግብ የምመገባት እንደ መጠጥ የምጠጣት እንደ ልብስ የምለብሳት፣ እንደ ምርጉዝ የምደገፋት በፍቅሯ የምረካባት የ #ኪዳነ_ምሕረት ታቦት ናትና እርሷን እወዳታለሁ" ብለው መረጡ፤ ንጉሡም ቃላቸውን ሰምቶ ታላቅ ደስታ ተደሰተ ፈቀደላቸውም።

ከዚኽም በኋላ አቡነ ዐሥራተ ወልድ ወደ ኢየሩሳሌም ሔደው በዚያ " #ጌታየ ሆይ መሰቀልህን በቅዱሳት መጻሕፍት ሰማሁ ይኽን በዐይኔ አሳየኝ" እያሉ አንድ ዓመት ቆመው ጸለዩ። የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም ለአባታችን ተገለጠላቸውና መጀመሪያ አይሁድ እንዴት እንደሰቀሉት የእሾኽ አክሊልን እንደአቀዳጁት፣ ጎኑን በጦር እንደተወጋ አሳያቸው። አቡነ ዐሥራተ ወልድም የ #ጌታችንን ስቅለት በተመለከቱ ጊዜ እጅግ ደንግጠው ወደቁ።

በዚያን ጊዜም #ጌታችን ወደ እርሳቸው መጥቶ "ልታይ የማትችለውን ዕለተ ዐርብ ለምን ለመንከኝ? እንግዲህ ተነሣና ወደ ሀገርህ ተመለስ የሰበሰብሃቸው መንጋዎችህ አንተን በማጣታቸው ተበትነዋልና" አላቸው። ከዚኽም በኋላ #ጌታችን ታላቅ የምሕረት ቃልኪዳን ገብቶላቸው በክብር ዐረገ። አባታችን ዐሥራተ ወልድም ከገዳማቸው ወጥተው ወደ ኢየሩሳሌም ሔደው አንድ ዓመት ከቆዩ በኋላ በትንሣኤ ዕለት #ቅዱስ_ሥጋውንና #ክቡር_ደሙን ተቀብለው በ #መንፈስ_ቅዱስ ኃይል ተመስጠው ካህናት ጸሎተ ቅዳሴውን ሳይጨርሱ ገዳማቸው ዙርዙር ኪዳነ ምሕረት ደረሱ።

ከዚኽም በኋላ አባታችን ጉርብ በምትባል ዋሻ ውስጥ በአድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን ቤተ ክርስቲያንን ሠርቶላቸው መቶ ዐሥር ዓመት ከኖሩና #ጌታችንም ታላቅ የምሕረት ቃልኪዳን ከገባላቸው በኋላ የጥቅምት ወር በባተ በሃያ አንድ ቀን ከዚኽ ዓለም ድካም በሰላም ዐርፈዋል። ከአባታችን ከአቡነ ዐሥራተ ወልድ #እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከት ያሳትፈን። በጸሎታቸው ይማረን!።
#ጥቅምት_22

#ቅዱስ_ሉቃስ_ወንጌላዊ
#አንድ_አምላክ_በሆነ_በአብ_በወልድ_በመንፈስ_ቅዱስ ስም
ጥቅምት ሃያ ሁለት በዚህች ቀን ብልህ ጥበበኛ የሆነ ቅዱስ ወንጌላዊ ሉቃስ በሰማዕትነት አረፈ።

በሀገረ አንጾኪያ ከአሕዛብ ወገን የተለወደው አይሁዳዊው ሉቃስ ከሰባ ሁለቱ አርድእት የተቆጠረ ባለ መድኃኒትና ወንጌልን የጻፈ ቅዱስ ሐዋርያ ነው፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በወንጌል ትርጓሜያቸው ስሙ ‹ዓቃቤ ሥራይ› ወይም ‹ባለ መድኃኒት› የሚል ትርጉም በውስጡ የያዘ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በላቲን ቋንቋ ‹ሉካስ› ማለት ‹ብርሃናማ፣ ብርሃን የያዘ› ማለት ነው፡፡ መጽሐፈ ስንክሳር ደግሞ ብልህና ጥበበኛ በማለት ይገልጸዋል፡፡

ቅዱስ ሉቃስ የሚመሰለው በገጸ ላህም ነው፡፡ ‹‹ፍሪዳ አምጡና እረዱ፤ ከእርሱ ጋር እየበላን ደስ ይበለን›› እያለ ምሳሌውን ይጽፋልና፡፡ (ሉቃ.፲፭፥፳፫) በጤግሮስም ወንዝ ይመሰላል፤ ጤግሮስ ፈለገ መዓር ወይም የመዓር ወንዝ ነው፤ ርስትነቱም ጸዊረ ነገር (ምሥጢር መሸከም) የሚቻላቸው ሰዎች ርስት ነው፡፡

ቅዱስ ሉቃስ በአቴና ሀገር በእስክንድሪያ ሕክምናን አጥንቷል፤ የሥነ ሥዕልም ችሎታ ነበረው፤ ይህን የሥዕል ችሎታውንም በወንጌሉና በሐዋርያት ሥራ መጻሕፍቱ ላይ በሥዕላዊ መልክ ገልጾታል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ትውፊት እንደሚናገረው እመቤታችን #ቅድስት_ድንግል_ማርያም ልጇን አቅፋ (ምስለ ፍቁር ወልዳ) ለመጀመርያ ጊዜ የሣለው እርሱ ነው፡፡ ሥዕሎቹም በኢትዮጵያ በተድባባ ማርያም፣ በደብረ ዘመዶ፣ በዋሸራና በጀብላ ይገኛሉ፡፡ ተመሳሳዩም በስፔን ቅድስት #ማርያም ካቴድራል እንደሚገኝ ይነገራል፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በሰዓታት ምስጋናው ‹‹ከወንጌላውያን አንዱ የሆነው ጠቢቡ ሉቃስ ለሣላት ሥዕልሽ ሰላምታ ይገባል›› በማለት አመስግኗል፡፡

ቅዱስ ሉቃስ #ጌታችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ከመረጠው በኋላ የቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙር በመሆን አገልግሏል፡፡ ቀድሞ ዓቃቤ ሥራይ ዘሥጋ (ሥጋዊ ሐኪም) ቢሆንም በኋላ ግን ዓቃቤ ሥራይ ዘነፍስ (መንፈሳዊ ሐኪም) እንደሆነ ሊቃውንቱ ይናገራሉ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለ እርሱ ሲመሰክር ‹‹የተወደደው ባለ መድኃኒቱ ሉቃስ ዴማስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል›› በማለት ገልጦታል፡፡ (ቆላ.፬፥፲፬) ቅዱስ ሉቃስ ተንሣኢ (ፈጣን) እየተባለም የሚጠራው ለስብከተ ወንጌል ስለሚፋጠን ነበር፤ በወንጌሉም አጻጻፍ ላይ ስለ ሕመማቸውና ድኅነት ስለሚያገኙበት ሁኔታ ገልጦ ጽፏል፤ ለዚህም ምሳሌ የሚሆኑት ታሪኮች የደጉ ሳሚራዊና ደም ይፈሳት ስለነበረችው ሴት ናቸው፡፡ (ሉቃ.፲፥፴‐፴፭፤፰፥፵፫) ሐዋርያው መበሥር ወይም ብሥራት ነጋሪ እየተባለም ይጠራል፤ ይህም ብሥራተ መልአክን ጽፏልና ነው፡፡ (ሉቃ.፩፥፩)

የቅዱስ ሉቃስ ወንጌል የተጻፈው በሀገር አኪይያ (ሮም) በጽርዕ (ግሪክ) ቋንቋ ነው፤ የሉቃስ ወንጌል ‹የአሕዛብ ወንጌል›፣ ‹ሰባኬ #መንፈስ_ቅዱስ›፣ ‹ሰባኬ ጸሎት›፣ ወንጌለ አንስት ተብሎም ይጠራል፡፡

፩. ‹የአሕዛብ ወንጌል› እየተባለ የሚጠራው ወንጌሉ የተጻፈው ለአሕዛብ በመሆኑ ነው፡፡

፪. ሰባኬ #መንፈስ_ቅዱስ የሚባለው ስለ #መንፈስ_ቅዱስ ደጋግሞ ስለሚናገር ነው፡፡

፫. ሰባኬ ጸሎት የተባለው ከሌሎች ወንጌላት የበለጠ ደጋግሞ የ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስን እና እመቤታችን ቅድስት ድንግል #ማርያምን ጸሎት ጽፏልና ነው፡፡

፬. ወንጌለ አንስት የሚባለው ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል #ማርያም፣ ስለ ቅድስት ኤልሳቤጥ፣ ስለ ማርያም እንተ እፍረት፣ ስለ ናይን እና ወዘተ በስፋት ስለሚናገር ነው፡፡

ወንጌሉን ከመጻፉ አስቀድሞም ቅዱስ ሉቃስ የቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙር ከመሆኑ በፊት የቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር እንደነበረ ትርጓሜ ወንጌል ላይ ተጽፎ ይገኛል፡፡ በአንጾኪያ ሀገር ቅዱስ ጳውሎስን ካገኘው በኋላም ሊቀ ሐዋርያው ሰማዕት እስከሆነበት ድረስ አገልግሎታል፡፡ ከሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ጋርም በነበረበት ጊዜም መቄዶንያ የምትባል ሀገር ከፍሎ እንዲስተምር እንደሰጠው በወንጌል ትርጓሜ ተገልዿል፡፡ ቅዱስ ሉቃስም በዚያ ሀገር ከ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ መፀነስ ጀምሮ፣ መዋዕለ ስብከቱን፣ የሠራውን ትሩፋትና ገቢረ ተአምሩን በሙሉ ለአሕዛቡ በነገራቸው ጊዜ ከኃጢያት ወደ ጽድቅ፣ ከአምልኮ ጣዖት ወደ አምልኮ #እግዚአብሔር ተመለሰው በማመን የክርስትና ጥምቀት ተጠምቀዋል፡፡ ለስብከት በሚጓዝበትም ወቅት ትምህርት ባልተዳረሰባቸው ስፍራ ሲያስተምር አንድ ታዖፊላ የተባለ የእስክንድርያ መኮንን ስብከቱን አድምጦ በማመን ‹ዜና ሐዋርያትን› (ገድለ ሐዋርያትን) እንዲጽፍለት በጠየቀው መሠረት ጽፎለታል፡፡ በዚህም ቅዱስ ሉቃስ የጻፋቸው መጻሕፍት ከወንጌሉና ከሐዋርያት ሥራ ጋር ሦስት ናቸው፡፡

ቅዱስ ሉቃስ የሕይወት ታሪኩ እንደሚገለጸው በድንግልና የኖረ ሐዋርያ ነው፤ ሐዋርያዊ አገልግሎቱንም የፈጸመው በአብዛኛው በግሪክ ነበር፡፡ ሐዋርያቱ ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ ካረፉ በኋላም በሮም ሀገር ማስተምር ቀጠለ፤ በቀናች ሃይማኖትም ይጸኑ ዘንድ ለምእመናን መልእክትን ይጽፍ ነበር፤ ስለዚህም ጣዖት አምላኪዎች ከአይሁድ ጋር በመስማማት በአንድ ምክር ሆነው በንጉሥ ኔሮን ፊት በመቆም ስለ ሐዋርያው ቅዱስ ሉቃስ እንዲህ ብለው ተናገሩ፤ ‹‹ይህ ሉቃስ በሥራይ ብዙ ሰዎችን ወደ ትምህርቱ አስገባቸው፡፡›› ንጉሥ ኔሮንም ወደ ፍርድ ዐደባባይ ሉቃስን እንዲያቀርቡት ባዘዘ ጊዜ ሐዋርያው ቅዱስ ሉቃስ ዕረፍቱ እንደ ደረሰ በ #መንፈስ_ቅዱስ ዐውቆ ወደ ባሕር ዳርቻ ሄደ፡፡ በዚያም ዓሣ የሚያጠምድ አንድ ሽማግሌ ሰው አግኝቶ መጻሕፍቱንና ደብዳቤዎችን እንደሰጠውና ‹‹ወደ #እግዚአብሔር መንገድ መርተው ያደርሱሀልና እነዚህን መጻሕፍት ጠብቃቸው›› በማለት እንደገነገረው መጽሐፈ ስንክሳር ይጠቅሳል፡፡

ከዚህም በኋላ በንጉሥ ኔሮን ፊትም ቀርቦ በቆመ ጊዜ ንጉሡ ‹‹በሥራይህ ሕዝቡን የምታስት እስከ መቼ ነው?›› ብሎ ጠየቀው፤ ቅዱስ ሉቃስም ‹‹እኔ ለሕያው #እግዚአብሔር ልጅ ለ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሐዋርያ ነኝ እንጂ ሥራየኛ አይደለሁም›› ብሎ መለሰለት፡፡ ንጉሥ ኔሮንም ሁለተኛ እንዲህ አለው፤ ‹‹እየጻፈች ሰዎችን የምታስት ይህች እጅህን እኔ እቆርጣታለሁ፤›› ይህንንም ብሎ የቀኝ እጁን እንዲቆርጡት አዘዘ፡፡ በቆረጡትም ጊዜ ‹‹ንጉሥ ሆይ እኛ የዚህን ዓለም ሞት እንደማንፈራ ዕወቅ፤ ነገር ግን የ #ጌታዬና የፈጣሪዬን ኃይሉን ታውቅ ዘንድ አሳይሃለሁ፤›› ይህንንም ብሎ የተቆረጠች የቀኝ እጁን በግራ እጁ አንሥቶ ከተቆረጠችበት ቦታዋ ላይ አገናኝቶ እንደ ቀድሞዋ ደኅነኛ አደረጋት፤ ከዚህም በኋላ ለያት፤ በዚያም የነበሩ አደነቁ፤ የሠራዊቱም አለቃና ሚስቱ ብዙዎችም ሰዎች ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አመኑ፤ ቁጥራቸውም ዐራት መቶ ሰባ ሰባት ነፍስ ሆነ፡፡ ንጉሡም ከቅዱስ ሉቃስ ጋር ራሶቻቸውን እንዲቆርጡ በማዘዙ ቆረጡአቸው፤ የምስክርነት አክሊልም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ፡፡ ቅዱስ ሉቃስ ያረፈው በ፹፬ ዓመቱ ነው፡፡

ከዚህም በኋላ ሥጋውን በማቅ አይበት ውስጥ አድርገው ወደ ባሕር ጣሉት፡፡ በ #እግዚአብሔር ፈቃድ ወደ አንድ ደሴት ደረሰ ምእመናንም አግኝተው ወስደው ገነዙት፤ በአማረ ቦታም አኖሩት፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን የወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ አማላጅነት፣ ተረዳኢነትና በረከት አይለየን፤ ለዘላለሙ አሜን!

(ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት_22)
🌹 #የጥቅምት_22_ግጻዌ 🌹

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_22_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ቆላስይስ 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² ከእናንተ የሆነ የክርስቶስ ባሪያ ኤጳፍራ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ በእግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉ ተረድታችሁና ፍጹማን ሆናችሁ እንድትቆሙ፥ ሁልጊዜ ስለ እናንተ በጸሎቱ ይጋደላል።
¹³ ስለ እናንተ በሎዶቅያም በኢያራ ከተማም ስላሉቱ እጅግ እንዲቀና እመሰክርለታለሁና።
¹⁴ የተወደደው ባለ መድኃኒቱ ሉቃስ ዴማስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።
¹⁵ በሎዶቅያ ላሉቱ ወንድሞችና ለንምፉን በቤቱም ላለች ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ አቅርቡልን።
¹⁶ ይህችም መልእክት በእናንተ ዘንድ ከተነበበች በኋላ፥ በሎዶቅያ ሰዎች ማኅበር ደግሞ እንድትነበብ አድርጉ፤ ከሎዶቅያም የምትገኘውን መልእክት እናንተ ደግሞ አንብቡ።
¹⁷ ለአክሪጳም፦ በጌታ የተቀበልኸውን አገልግሎት እንድትፈጽሙው ተጠንቀቅ በሉልኝ።
¹⁸ በገዛ እጄ የተጻፈ የእኔ የጳውሎስ ሰላምታ ይህ ነው። እስራቴን አስቡ። ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ዮሐንስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁴ ደስታችሁም እንዲፈጸም ይህን እንጽፍላችኋለን።
⁵ ከእርሱም የሰማናት ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት፦ እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም የምትል ይህች ናት።
⁶ ከእርሱ ጋር ኅብረት አለን ብንል በጨለማም ብንመላለስ እንዋሻለን እውነትንም አናደርግም፤
⁷ ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ በብርሃን ብንመላለስ ለእያንዳንዳችን ኅብረት አለን፥ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል።
⁸ ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም።
⁹ በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው።
¹⁰ ኃጢአትን አላደረግንም ብንል ሐሰተኛ እናደርገዋለን ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹-² ቴዎፍሎስ ሆይ፥ ኢየሱስ የመረጣቸውን ሐዋርያትን በመንፈስ ቅዱስ ካዘዛቸው በኋላ እስከ ዐረገበት ቀን ድረስ፥ ያደርገውና ያስተምረው ዘንድ ስለ ጀመረው ሁሉ መጀመሪያውን ነገር ጻፍሁ፤
³ ደግሞ አርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገር እየነገራቸው፥ በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ ራሱን አሳያቸው።
⁴ ከእነርሱም ጋር አብሮ ሳለ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ አዘዛቸው፥ ነገር ግን፦ ከእኔ የሰማችሁትን አብ የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቁ፤
⁵ ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና፥ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኃላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ አለ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_22_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇🌹

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"አልቦ ነገር ወአልቦ ነቢብ ዘኢተሰምዐ ቃሎሙ። ውስተ ኵሉ ምድር ወፅአ ነገሮሙ። ወእስከ አፅናፈ ዓለም በጽሐ ነቢቦሙ"። መዝ 18፥3-4።

#ትርጉም፦ "ነገር የለም መናገርም የለም፥ ድምፃቸውም አይሰማም። ድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ፥ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ"። መዝ 18፥3-4።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_22_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
“የከበርህ ቴዎፍሎስ ሆይ፥ ከመጀመሪያው በዓይን ያዩትና የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት እንዳስተላለፉልን፥ በኛ ዘንድ ስለ ተፈጸመው ነገር ብዙዎች ታሪክን በየተራው ለማዘጋጀት ስለ ሞከሩ፥ እኔ ደግሞ ስለ ተማርኸው ቃል እርግጡን እንድታውቅ በጥንቃቄ ሁሉን ከመጀመሪያው ተከትዬ በየተራው ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ።”— ሉቃስ 1፥1-4
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ 🌹
 የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱሳን_ሐዋርያት_ቅዳሴ ነው። መልካም የወንጌላዊው የቅዱስ ሉቃስ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ውራ_ኢየሱስ ገዳምን የመሠረቱትና #ጌታችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ከገነት ዕንጨቶች የተሠሩ ታቦታት አምጥቶ የሰጣቸው ታላቁ ጻድቅ #አቡነ_ዮሐንስ ዘውራ #ኢየሱስ ጥቅምት 22 ቀን ዕረፍታቸው ነው።

#አቡነ_ዮሐንስ_ዘውራ_ኢየሱስ፦ የአባታቸው ስም የማነ ብርሃን የእናታቸው ስም ሐመረ ወርቅ ይባላል።በመጀመሪያ እናታቸው ሐመረ ወርቅን ወላጆቿ ያለ ፈቃዷ ሊድሯት ሲሉ እርሷ ግን “ደብረ ሊባኖስ ሔጄ ከአባታችን ተክለ ሃይማኖትና ከሌሎቹም ቅዱሳን መቃብር ሳልባረክ አላገባም በማለት ነሐሴ 16 ቀን ወደ ደብረ ሊባኖስ ሔደች። በዚያም ሳለች አቡነ ተክለ ሃይማኖት በራእይ ተገለጡላትና የብርሃን ምሰሶ አሳይተዋት ይኸ ለአንቺና ለባልሽ ለየማነ ብርሃን ነው› አሏት። ይኽንንም ራእይ ለሰባት ቀን የገዳሙ አባቶችና አበ ምኔቱ አባ ዳንኤል አዩት። ከዚኸም በኋላ ባለጸጋውና ሃይማኖትን ከምግባር አስተባብሮ የያዘው የማነ ብርሃን ከዘርዐ ያዕቆብ ሀገር በ #እመቤታችን ትእዛዝ ወደ ደብረ ሊባኖስ ሲመጣ አበ ምኔቱ አባ ዳንኤል የማነ ብርሃንን እና ሐመረ ወርቅን ኹለቱ ተጋብተው የተባረከ ልጅ እንደሚወልዱ በራእይ ያዩትን ነገሯቸው፤ ከዚኽም በኋላ በአባታችን በተክለ ሃይማኖት የዕረፍታቸው በዓል ዕለት ነሐሴ 24 ቀን ተጋቡ። እነርሱም በሃይማኖት በምግባር #እግዚአብሔርን ደስ አሰኝተው ሲኖሩ #እግዚአብሔር ልጅ ሰጣቸውና አቡነ ዮሓንስ ነሐሴ 24 ቀን ተፀንሰው ግንቦት 24 ቀን ተወለዱ።

የፈለገ ብርሃን ናዳ #ማርያም እና የክብረ ደናግል ናዳ ቅዱስ ላሊበላ አንድነት ገዳም አበምኔት፣ የቅኔ፣ የትርጓሜ መጻሕፍት፤ የፍትሐ ነገሥት እና የባሕረ ሐሳብ መምህር የሆኑት ሊቀ ብርሃናት ቆሞስ ይባቤ በላይ ከግእዝ ወደ አማርኛ የተረገሙት የአቡነ ዮሐንስ ዘውራ ኢየሱስ ገድል እንደሚናገረው ጻድቁ በሰባት ዓመታቸው ይኸችን ዓለም ንቀው የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ኹለተኛ ልጅ ወደሆነው አባ ጸጋ ኢየሱስ ዘንድ ሔደው 5 ዓመት እየተማሩ ተቀምጠው በ12 ዓመታቸው መነኰሱ። ከዚኽም በኋላ አቡነ ዮሐንስ ወደ ዋልድባ በመሔድ አባቶችን ማገልገል ጀመሩ። መነኰሳቱም ሌሊትና ቀን እንዲገለግሏቸው በሥጋ ቍስል ሁለንተናው
ለተላና ለሸተተ ግብሩ ለከፋ ለአንድ መነኵሴ ሰጧቸው። በሽተኛውም መነኵሴ አቡነ ዮሐንስን ይረግማቸውል አንዳንድ ጊዜም ይደበድባቸው ነበር፣ ነገር ግን አቡነ ዮሐንስ በዚህ ከማዘን ይልቅ ደስ እያላቸው ያንን ሊቀርቡት የሚያሰቅቅ በሽተኛ በማገልገል ለዓመታት አስታመመ።

እንዲሁም የዋልድባ መነኰሳትን መኮሪታ በማብሰል፣ ቋርፍ በመጫር እና ዕንጨት በመልቀም፣ ውኃ በመቅዳት ገዳማውያንን ያገለግሉ ነበር። ከዕለታትም በአንደኛው ቀን በዋልድባ የሚኖር በክፉ በሽታ ተይዞ የሞተ አንድ መነኩሴ ሞቶ ሣለ ሽታውን ፈርተው መነኰሳቱ ለመገነዝ ፈሩ፡ ነገር ግን አበ ምኔቱ ለመገነዝ ወደ ውስጥ ሲገባ አቡነ ዮሐንስ አብረው ገቡ። አቡነ ዮሐንስም ወደሞተው መነኵሲ ቀርበው አቀፉት፣ በዚኸም ጊዜ ጥላቸው ቢያርፍበት ያ የሞተው መነኵሴ አፈፍ ብሎ ከሞት ተነሣና ከሞትሁ 3ኛ ቀኔ ነው አይቶ የጎበኘኝ የለም፣ ዛሬ ግን የ #እግዚአብሔር ሰው የገዳማት ኮከብ የቅድስት ውራ ገዳም መነኰሳት አባት፣ የማይጠልቅ ፀሓይ፣ የማይጠፋ ፋና ወደ ሰባቱ ሰማያት ወጥቶ ከ24ቱ ካህናተ ሰማይ ጋር የ #ሥላሴን ዙፋን የሚያጥን አባታችን ዮሐንስ ባቀፈኝ ጊዜ ነፍሴ ከሥጋዬ ጋር ፈጽማ ተዋሐደች፤ አምላክን የወለደች #እመቤታችን_ማርያምም ንዑድ ክቡር ቅዱስ በሆነ በዮሐንስ ጸሎት ከሞት አስነሥቶ ሕያው አደረገህ አለችኝ› ብሎ ተናገረ። ዳግመኛም #እመቤታችን አባ ዮሐንስን ወደ ኢየሩሳሌም ሔደው እርሳቸውን ሲጠብቁ የኖሩትን ሦስት ታቦታት ያመጡ ዘንድ አቡነ ዮሐንስን እንዳዘዘቻቸው ተናገረ። በዚኽም ጊዜ የዋልድባ መነኰሳትና የገዳሙ አለቃ ለፍላጎታችን አገልጋይና ታዛዥ አደረግንህ ይቅር በለን ብለው ከእግራቸው ሥር ወድቀው ለመኗቸው። አባታችንም ‹‹አባቶቼ ሆይ! እናንተ ይቅር በሉኝ፡ ይህ የሆነው ስለ እኔ አይደለም፡ ስለ ክብራችሁ ነው እንጂ አሏቸው። መነኰሳቱም በትሕትናቸው ተገርመው እያለቀሱ ወደ ኢየሩሳሌም ሸኟቸው። በዚኸም ጊዜ አባታችን ዕድያቸው ገና 19 ነበር።

አባታችን ዮሐንስም ጎልጎታ ደርሰው ከቅዱሳት ቦታዎች ተባርከው ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔዱ። በዚያም 500 ዓመት የኖረ ኹለተኛ እንጦንስ የተባለ አንድ ባሕታዊ ኣገኙ። #እመቤታችንም አባ እንጦንስን ታቦተ ኢየሱስን፣ ታቦተ ኪዳነ ምሕረትን እና ታቦተ ጽዮንን እያስጠበቀችው ይኖር ነበር። አባ እንጦንስም ኣቡነ ዮሐንስን ባገኛቸው ጊዜ በልቡ ተደስቶ በመንፈሱ ረክቶ በዐይኖቼ አንተን ያሳየኝ በጆሮዎቹም ቃልህን ያሰማኝ የአባቶቻችን አምላክ #እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን፤ እመቤታችን #ማርያም ከልጇ ከወዳጇ ከ #ኢየሱስ_ክርስቶስ ጋር በእጇ የሰጠችኝን ያስጠበቀችኝን እነዚኽን ታቦታት ተቀበለኝ›› ብለው ሦስቱን ጽላት ‹‹ወደ ሀገርህ ይዘህ ሒድ›› ብለው ሰጧቸው። አባታችን ዮሐንስም ‹‹…እኔ እርሱ አይደለሁም እንዴት አወከኝ?› ሲሏቸው አባ እንጦንስም ፈገግ ብለው ከሞተ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት የሆነውን ሰው በጸሎትህ ከሞት ካስነሣኸው በኋላ ከሀገርሀ ከኢትዮጵያ ከዋልድባ ገዳም ከተነሣኽ ዘጠኝ ወር ነው፤ ይኸንንም የ #እግዚአብሔር መላእክት ነገሩኝ መምጣቱን ተስፋ የምታደርገው ኢትዮጵያዊው ጻድቅ ከሀገሩ ዛሬ ተነሣ አሉኝ አሏቸው። አባታችን ዮሐንስም እመቤታችን #ማርያምን እንዴት አገኘሃት? አሏቸው። አባ እንጦንስም ከልጇ ከወዳጇ ጋር በብርሃን መርከብ ላይ ተቀምጣ መላእክት፣ ነቢያት፣ ሐዋርያት ጻድቃን፣ ሰማዕታት ሲከቧትና በክብር በምስጋና ሲሰግዱላት ግንቦት 21 ቀን በደብረ ምጥማቅ አገኘኋት አሏቸው። #እመቤታችንም ልጇን #ኢየሱስ_ክርስቶስን ፈቃድህን ለሚያደርጉ ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለዓለሙ ሁሉ የመዳን ተስፋ ስጠኝ አለችው። #ጌታችንም ያንጊዜ መላእክትን ከገነት ዕንጨትና ዕብነ በረድ፡ ከጎልጎታ መቃብሩና ከጌቴሴማኒ አፈር እንዲያመጡ አዘዛቸው። መላእክትም የታዘዙትን አምጥተው በሰጡት ጊዜ #ጌታችን ከገነት የመጡትን ዕንጨትና ዕብነ በረድ ሦስቱን ታቦታት አድረጋቸው በማለት አባ እንጦንስ ለአባ ዮሐንስ ነገሯቸው።

አቡነ ዮሐንስም ሦስቱን ጽላት ይዘው አንዲት እንደፀሓይ የምታበራ ድንጋይ እየመራቻቸው ሰኔ 12 ቀን ጎጃም ደረሱ። ድንጋዩዋንም መንገድ እንድትመራቸው የሰጣቸው #ጌታችን ነው። ከዚያም ውሮ ተብሎ የሚጠራ አንድ ባላባት ቤት ገብተው አድረው በሚገባ ተስተናግደው በቀጣዩ ቀን ድንጋዩዋ እየመራቻቸው ቅዱሳን ከነበሩበት ጫካ ወስዳ አገናኘቻቸው። ቅዱሳኑም ለአቡነ ዮሐንስ የጠበቅንልህን ይኸችን ቦታ ተረከበን የዘለዓለም ማረፊያህ ናትና› ብለው እነርሱ ወደ ኢየሩሳሌም ሔዱ። አባታችንም ታቦተ #ኢየሱስን በዚኽች ገዳም ተክለው ቦታዋን መጀመሪያ በተቀበላቸው ሰው በውሮ ስም "ውራ #ኢየሱስ ብለው ሰየሟት።

ከዘጠኝ ዓመትም በኋላ መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል እየመራቸው ወደ ጣና ወስዶ ዘጌ አደረሳቸውና ታላቋን ዑራ #ኪዳነ_ምሕረትን ተከለ።
ከዚያ ቀጥለው ታቦተ ጽዮንን አዴት አካባቢ ተከሉ። እነዚህን ሦስት ገዳማት አቅንተው ከኖሩ በኋላ መልካም የሆነውን ተጋድሏቸውን ፈጽመው ጥቅምት 22 ቀን ዐርብ በ9 ሰዓት ዐረፉ። ከማረፋቸውም በፊት #ጌታችን #እመቤታችንን#መላእክትን#ቅዱሳንን #ሰማዕታትን አስከትሎ መጥቶ “…ጸሎት አድርጎ መልክህን የደገመ እባብ አይነድፈውም፤ መብረቅ አይገድለውም የሚል ድንቅ የምሕረት ቃልኪዳን ገባላቸው። ዳግመኛም ስምህን የጠራውን መታሰቢያህን ያደረገውን፤ በበዓልህ ቀን ማኅሌት የቆመውን የገድልህን መጽሐፍ የጻፈውን ያጻፈውን ያነበበውን የሰማውን፣ እጅ መንሻ ለቤተ ክርስቲያን የሰጠውን እምርልሃለሁ፤ ልጆቹንም እስከ 15 ትውልድ እባርክልሃለሁ፤ በገዳምህ በውራ መብረቅ ነጎድጓድ፣ እባብ ሰውን አይገድልም የማይጸድቅ ሰው ወደ ገዳምህ አይመጣም" አላቸው።

አባታችንም ካረፉ በኋላ መነኰሳት ልጆቻቸው ሥጋቸውን ተሸክመው ከደብረ ጽዮን ኮቲ ተነሥተው ወደ ውራ #ኢየሱስ ለመውሰድ ሲጓዙ በበረሓ ሣሉ መሸባቸውና ፀሓይ ገባች፣ ወዲያውም ሰባት አንበሶች መጥተው እንዳይፈሯቸው መነኰሳቱን በሰው አንደበት ካናገሯቸው በኋላ የአቡነ ዮሓንስን ዐፅም ተሸክመው ሰባት ምዕራፍ ያህል ወሰዱት። ወቅቱ ቢመሽባቸውም በ #እግዚአብሔር ፈቃድ ፀሓይ ግን በተኣምራት ወጣችላቸውና ውራ #ኢየሱስ ገዳም በሰላም ደረሱ። ያንጊዜም ፀሓይ ገባች፤ አንበሶቹም እጅ ነሥተው ወደ ቦታቸው ተመለሱ።

አቡነ ዮሐንስ መላ ዘመናቸውን የማያዩ ዐይነ ሥውራንን እንዲያዩ፣ የማይሰሙ እንዲሰሙ፣ የማይራመዱ እንዲራመዱ በማድረግ፤ ሕሙማንን በመፈወስ፣ ሙታንን በማስነሣት በርካታ ተኣምራትን በማደረግ ወንጌልን በመስበክ ያገለገሉ ሲሆን ከዕረፍታቸውም በኋላ በርካታ ድንቅ ድንቅ ተኣምራትን አድርገዋል። ከተኣምራታቸውም አንዱ ይኸ ነው፡- ንዑድ ክቡር ልዩ በሚሆን በአባታችን ዮሐንስ የዕረፍታቸው ቀን ጥቅምት 22 ቀን አንድ ዐረማዊ እስላም ሰው ለተሳልቆና ለመዘባበት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ቈረበ። በአባታችን በዓል ዕለትም #ቅዱስ_ሥጋውንና #ክቡር_ደሙን ተቀብሎ ወጥቶ እየተቻኮለ ሔዶ ከእስላሞች መስጊድ ገብቶ በአባታችን በዮሐንስ በዓል ምክንያት የቆረበውን ቍርባን ተቀብሎ በወገኖቹ በከሃዲያኑ እስላሞች ፊት ተፋው። ወዲያውም የዚያ እስላም ሰው መላ ሰውነቱ አበጠ በንፋስ ገመድነትም ታንቆ ሰዎች እስኪያዩት ድረስ በሰማይና በምድር መካከል ተሰቀለ።

በተሰቀለበትም ቦታ ወፎችና አሞራዎች ይበሉት ጀመር፤ ሥጋውንም በሉት። በዚኽም ጊዜ ያ እስላም ድምፁን ከፍ አድርጎ ‹‹እኔ ንዑድ ክቡር ልዩ በሆነ በአባታችን በዮሐንስ አምላክ አምኛለሁ ብሎ መሰከረ። #እግዚኣብሔርም የገዳማት ኮከብ በሆነው በብፁዕ ዮሓንስ ልመናና ጸሎት ፈጽሞ ይቅር አለው። ከዚኽም በኋላ ለብቻው ቀኖና ገባ የቀኖና ሥርዓቱንም ጨርሶ #ንስሓ ገብቶ ከባለቤቱ ከልጆቹ ከቤተሰቦቹና ከዘመዶቹ ከጎረቤቱቹ ሁሉ ጋር የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቀ ስሙንም ገብረ ዮሐንስ አሉት ትርጓሜውም የዮሐንስ ባለሟል ማለት ነው።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአቡነ ዮሐንስ ጸሎት ይማረን የአቡነ ዮሐንስ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ ለዘላለሙ አሜን።
2025/10/31 20:14:10
Back to Top
HTML Embed Code: