Telegram Web Link
ዛሬ በሰሜን ወሎ ማረሚያ ቤቶች በወልድያ ማረሚያ ቤት የወልድያ ከተማ አስዳደር ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ጥበባት አክሊለ ብርሃን በተገኙበት ከስብከተ ወንጌል አገልሎት በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ስጦታውን ለታራሚዎች ኮሚቴ አስረክበናል።
58🙏12👍3👌1
ስለ ጌጠኛ ልብስ - ፪

....እኅቴ ሆይ! ራስሽን መሸላለም ብትፈልጊ እንዲህ አጊጪ፡፡
ከዚያም ከምረረ ገሃነም ትድኛለሽ፡፡ ባልሽንም ከማዘን ከመቆርቆር ትታደጊዋለሽ፡፡

ባልሽ እጅግ ደስ የሚሰኘው እንዲህ ስታጌጪ ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙ ወንዶች ሚስቶቻቸው “ሥጋችንን እናጊጥ” ሲሉአቸው ደስ አይላቸውም፡፡ እንዲህ በሚያዘወትሩ ሚስቶቻቸውም ያፍራሉ፡፡ ከክብረ ሥጋ ይልቅ ክብረ ነፍስን የምታስቀድሙ ከኾነ ግን ገንዘብ ስጡን ስለማትሉአቸው ሰጠናቸው ብለው ከመታበይ ይድናሉ፡፡ እኔ እበልጥ የሚል ስሜታቸው ይወገዳል፡፡ ምድራዊ ወርቅን እንደማትፈልጊና ለዚያ መግዣ የሚኾን ገንዘብ ሳትጠይቂው ሲመለከት እጅግ ቁጡ ቢኾንም አጊጠሸ ከሚያከብርሽ በላይ ሳታጌጪ ያከብርሻል፡፡ አንቺም የእርሱ ተገዢ አትኾኚም፡፡ የሰው ተገዢ የምንኾነው ከዚያ ሰው ብዙ [ምድራዊ] ነገርን የምንሻ ከኾነ ነውና፡፡ በዚህ ዓለም አላፊና ጠፊ ነገር ግድም እንደሌለን ሲያውቅ ግን ያ ሰው እኛ ላይ የሚሠለጥንበት ምክንያት የለውም፡፡ በመኾኑም እንደዚህ ስትኾኚ ባልሽን የምትታዘዢው ጊዜአዊ ነገር ስለ ሰጠሸ ሳይኾን እግዚአብሔርን ፈርተሸ እንደ ኾነ ይገነዘባል፡፡ ከዚህ በኋላ አንድ ነገር ስላደረገልሽ ብታመሰግኚው እንኳን የሰጠሽው ክብር ስላደረገው ነገር እንዳልኾነ ይረዳል፡፡ አንቺ በምላሹ የሰጠሽው ነገር ትንሽ ቢኾንም ትንሽ ነው ብሎ አይቈጥረዉም፡፡ ወይም አይበሳጭም፡፡

በብዙ ወርቅ መሸላለምና ጌጠኛ ልብስን ለብሶ በአደባባይ ከመዞር በላይ ምን ስንፍና አለ? በአደባባይስ ብዙ ባልደነቀኝ፤ እንዲህ ተሸላልማ ወደ ቤተ ክርስቲያን የምትመጣ ግን እጅግ ሰነፍ ናት፡፡ “በሽሩባና በወርቅ ወይም በዕንቁ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸላለሙ” የሚለውን ቃል መስማት ሲገባት እንዲኽ አጊጣና ተሸላልማ የምትመጣው ምን ለማድረግ ነው? (1ኛ ጢሞ.2፥9)፡፡ አንቺ ሴት እስኪ ንገሪኝ! ምን ለማድረግ ነው የመጣሽው? ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር ጠብ ክርክር ለመግጠም ነውን? እልፍ ጊዜ እንዲህ አትልበሺ ብሎ ቢነግርሽም ንቀሽው አጥቅተሺው መምጣትሽ ምን ለማድረግ ነው? ወይስ ቅዱስ ጳውሎስን መስለን እንዲህ የምናስተምረው መምህራን ትምህርቱን በከንቱ እንዳስተማርን ዐይተን እንድናፍር ሽተሸ ነው? እኮ ንገሪኝ! አንድ እነዚህን የቅዱስ ጳውሎስ ቃላት የሰማ ኢአማኒ ባል “በወርቅ ወይም በዕንቁ ወይም በከበረ ልብስ አይሸላለሙ” የሚለውን የሐዋርያው ቃል ለመስማት ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመኼድ የምትዘጋጀውን ክርስቲያን ሚስቱ ራስዋን በብዙ እንደምትሸላልም፣ ጌጠኛ ልብስን እንደምታደርግ ቢያያት ምንድን ነው የሚለው? “ባለቤቴ ምን እየሠራች ነው? በመስታወቱ ፊት ይህን ያህል ሰዓት መቆየቷ ስለ ምንድን ነው? ይህን ያህል ወርቅ መልበስዋ ለምንድን ነው? መኼድ ያሰበችው ወዴት ነው? ወደ ቤተ ክርስቲያን ነውን? ምን ለማድረግ? በወርቅ ወይም በዕንቁ ወይም በከበረ ልብስ አይሸላለሙ የሚለውን ቃል ለመስማት ነውን?” እያለ ብዙ አይዘብትምን? ብዙስ አይሳለቅምን? ሃይማኖታችንስ ስላቅና ማታለል እንደ ኾነች አያስብምን?

ይቀጥላል...

(የክርስቲያን መከራ እና ሌሎች ቅዱስ ዮሐንስ_አፈወርቅ እንደአስተማረው ገጽ 47-55➛ገብረ እግዚአብሔር ኪደ የተረጎመው)
61🙏19😍3👍2
"ለቤተ መቅደስህ ተክል ያደረግኸኝ፡፡ አቤቱ ሆይ የውጭ ተክል አታድርገኝ፡፡ የጽድቅ ተክል አድርገኝ፡፡ የኃጢአት አይደለም፡፡ የዕውነት ተክል አድርገኝ የሐሰት አይደለም የፍቅር ተክል አድርገኝ የጥል አይደለም፡፡

የመጻሕፍት መጀመሪያ የምትሆን ኦሪት ደመና የምትጋርደኝ፡፡ ከቅዱስ ወንጌል ፈሳሽ የምጠጣ ከጎንህ ከፈሰሰው ደም የምረካ ልሁን፡፡ በእናትህ በድንግል ጸሎት የሃይማኖት አበባ ላብብ፡፡ የጽድቅ ፍሬን ላፍራ ከቅዱሳንህ ሐዋርያትም ከቃላቸው ፍሬ የተነሣ እስከ ዘለዓለሙ ድረስ የተባረከ የወይን ቦታ ልባል የጽድቅን ፍሬ የሚያስቀረውንም የኃጢአት እሾህ ጠምዝዘው ከደጁም አሜከላውን አረሙንም ሙጃውንም ንቀለው፡፡ አቤቱ ከኔም አርቀው ሥርዓትህን የሚሠሩትን ያበባቸውን ፍጻሜ እንዳፈራ አድርገኝ"

ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
96🙏24💯4
በማረሚያ ቤት ውስጥ ለሚገኙ የሕግታራሚዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ስጦታ ተበረከተ።

መስከረም 11/2018 ዓ.ም (ሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሚዲያ)

በሰሜን ወሎ መንበረ ጵጵስና ሀገረ ስብከት የወልድያ ከተማ አስተዳደር ቤተክህነት የስብከተ ወንጌል ክፍል 50 መጽሐፍ ቅዱስ ለሰሜን ወሎ ማረሚያ ቤት የሕግ ታራሚዎች በስጦታ አበርክቷል።

በዛሬው ዕለት በከተማ አስተዳደር ቤተክህነቱ የስብከተ ወንጌል ክፍል የ2018 ዓ.ም የመጀመሪያ ልዩ ጉባኤ ከታራሚዎች ጋር ያከናወነ ሲሆን ዋና ሥራ አስኪያጁ መጋቢ ጥበባት አክሊለ ብርሃን ተመስገን ትምህርተ ወንጌል ሰጥተው መጻሕፍቱንም አስረክበዋል።

በከተማ አስተዳደር ቤተክህነቱ የስብከተ ወንጌል ክፍል ኀላፊ መ/ር ቡሩክ ተስፋዬ አስተባባሪነት ከበጎ አድራጊዎች በተሰበሰበ የገንዘብ ድጋፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ስጦታ የተበረከተ ሲሆን በቀጣይም የልዩ ጉባኤያት አገልግሎቱና የመጻሕፍት ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።

መጻሕፍቱ ሰሎሞን አያሌው ከቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የቴሌግራም ቻናል ቤተሰቦች፣ ቀሲስ ሠምረ ሞላ ከንስሐ ልጆቻቸውና ከሌሎች በጎ ፈቃደኞች በተሰበሰበ ከ70 ሺህ ብር በላይ ወጪ የተገዙ ናቸው።

የመጻሕፍት ስጦታውን የተረከቡት የማረሚያ ቤቱ አስተባባሪዎችና ታራሚዎች የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው በማረሚያ ቤት ሰፊ ጊዜ ቢኖራቸውም የመጻሕፍት ዋጋ ውድ በመሆኑ ገዝተው ለማንበብ ይቸገሩ እንደነበር ገልጸዋል።

ታራሚዎቹ እንዲህ ያለው ድጋፍ ለወደፊትም ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

#የሰሜን_ወሎ_ሀገረ_ስብከት_የማኅበራዊ_ሚዲያ_አማራጮችን_ይወዳጁ_ለሌሎችም_ያጋሩ
~ቴሌግራም፡ https://www.tg-me.com/NWDnews
~ዩቲዩብ፡ https://youtube.com/c/NorthWolloDioceseMedia
~ድረገጽ፡ https://eotc-nw.org
~ፌስቡክ፡https://www.facebook.com/EOTCNWD?mibextid=ZbWK
~ https://www.tiktok.com/@eotc.north?_t=ZM-8ukkHRXMOYg&_r=1
34😍1
"በመንፈሳዊው መንገድ ላይ የምትጓዙ ከሆነ እንዳትወድቁ በራሳችሁ አትደሰቱ። ትዕቢትን የምንፈራው እድገታችንን እንዳያቆመው ብቻ ሳይሆን እንዳይጥለንም ነው። መጽሐፍ ይህን አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ይላል፦"ትዕቢት ጥፋትን ኩሩ መንፈስም ውድቀትን ይቀድማል።" ምሳ 16፥18..."

(መንፈሳዊው መንገድ - በአቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ)
88🙏22😍2
ስለ ጌጠኛ ልብስ - ፫

ስለዚህ እማልዳችኋለሁ! ጌጠኛ ልብስን ለወታደራዊ ሰልፈኞች፣ ለተውኔት ቤቶች፣ ልብስን ለሚሸጡ እንተውላቸው፡፡ ትዕቢት እና ውዳሴ ከንቱ በሌለበት በምግባር በትሩፋት እናጊጥ እንጂ በእኛ ውስጥ ያለውን የእግዚአብሔር መልክ በእነዚህ ጌጦች አንሸፍነው፡፡

እኅቴ ሆይ! ከወንዶች ክብርን ማግኘት ሽተሽ እንደ ኾነ በዚህ ታገኚዋለሽና የክርስቶስን መልክ አትሸፍኚው፡፡ ምክንያቱም እኛ ወንዶች ባለ ጠጋ ሴት ብዙ ብታጌጥ አይደንቀንም፡፡ የሚደንቀን ባለ ጠጋ ኾና ሳለ ዕርቃኗን ለመሸፈን ብቻ ብላ ተርታ ልብስን ለብሳ ስትኼድ ብንመለከት ነው፡፡ እኛ ብቻ አይደለንም፤ ጻድቃን ኹሉ የሚያደንቋት ዘማውያን የሚጠሏት ይህቺን ሴት ነው፡፡ ጌጠኛ ልብስን እንዲሁም ወርቅን የሚያደርጉ ሴቶች ብዙ ናቸው፡፡ አንዲቱን ልብለጣት ብትል ሌላኛዋ ነገ ሌላ ጌጥ ይዛ ስለምትመጣ ትበልጣታለች፡፡ በመኾኑም ኹሉንም ልብለጣቸው ስትል እንደ ንግሥቲቱ የወይራ ጉንጉን በራስዋ ላይ ልታደርግ ትችላለች፡፡ ነገር ግን እጅግ የምታስደንቀውና ከእነዚህ ሴቶች ኹሉ (ከንግሥቲቱም ጭምር) ይልቅ እጅግ ያጌጠችው ተርታ ልብስ የለበሰችዋ ናት፡፡ ከእነዚህ ኹሉ ሴቶች ይልቅ እጅግ የከበረችውም እርስዋ ናት፡፡

ነገር ግን ይህንን የምናገረው ባል ለሌላቸው እና ለባለጠጎች ሴቶች ብቻ አይደለም፤ ባል ላላቸው ሴቶችም ጭምር ነው እንጂ፡፡

ተርታ ልብስን ብለብስ ባለቤቴን ደስ ላሰኘው አልችልም” ትዪኝ እንደ ኾነም እንዲህ ብዬ እመልስልሻለሁ፡- “እንዲህ የምታጌጪው ባልሽን ደስ ለማሰኘት አይደለም፤ ልብስ በሌላቸው ድኾች ሴቶች ልትመኪ ወደሽ ነው እንጂ፡፡ ልቡናቸውን በቅንአት እንደ ሰም ታቀልጪ ዘንድ ሽተሸ ነው እንጂ፡፡ በድኽነታቸው እንዲያማርሩና ኀዘናቸውን ልትጨምሪባቸው ፈልገሽ ነው እንጂ፡፡” አንቺ ሴት! በአንቺ ምክንያት እግዚአብሔርን ይሰድቡ ዘንድ ምን ያህል ምክንያት እንደኾንሻቸው ታስተውያለሽን? “ስለ ምን ድኾች ኾንን? እግዚአብሔር ድኾችን አይወድም፡፡ ድኽነትን የሚያመጣባቸው ለማይወዳቸው ሰዎች ነው” እንዲሉ እንደምታደርጊያቸው ትገነዘቢያለሽን? አዎ! ጌጠኛ ልብስ የማድረግሽ ዓላማ ባልሽን ደስ ለማሰኘት አይደለም፡፡ ባልሽን ደስ የማሰኘት ዓላማ ቢኖርሽ ኖሮስ ከቤትሽ ስትወጪ ያደረግሽውን ወርቅና ዕንቁ እንዲሁም ጌጠኛ ልብስሽን ከቤትሽ ስትገቢ ፈጥነሽ ባላወለቅሺው ነበር፡፡ ስለዚህ ባልሽን ደስ ማሰኘት የምትፈልጊ ከኾነ ሌላ ብዙ መንገድ አለ፡፡ በትሕትናሽ፣ በየውኀትሽና በርኅራኄሽ ባልሽን ደስ አሰኚው፡፡

ይቀጥላል...

(የክርስቲያን መከራ እና ሌሎች ቅዱስ ዮሐንስ_አፈወርቅ እንደአስተማረው ገጽ 47-55➛ገብረ እግዚአብሔር ኪደ የተረጎመው)
80🙏19💯5🎉1🕊1
ስለ ጌጠኛ ልብስ - ፬

....አንቺ ሴት እመኚኝ!
ባልሽ ምንም ያህል ዕውቀት የሌለው ቢኾን እንኳን እንዲህ እንደነገርኩሽ ብታጌጪ ቅዱስ እንዲኾን ማድረግ ይቻልሻል፡፡ ምንም ያህል ትምክሕተኛ፣ ትዕቢተኛ እንዲሁም አባካኝ ቢኾንም ከዚህ የተለየ እንዲኾን ማድረግ ይቻልሻል፡፡ አንቺ እንደምታስቢው ባልሽን ደስ ለማሰኘት ብለሽ በአፍአ ብዙ ብታጌጪ ግን ከእነዚህ ክፉ ምግባራት የተለየ እንዲኾን ማድረግ አይቻልሽም፡፡

የምናገረው ነገር ለጊዜው ላይገባሽ ይችላል፡፡ እንዲህ እንደነገርኩሽ በማድረጋቸው ባላቸውን ደስ ያሰኙት ግን ያውቁታል፡፡ ልዩ ልዩ ጌጣጌጦችን አድርጋችሁ ራሳችሁን ብታቆነጃጁ ግን ባለቤታችሁ ዘማዊ ከኾነ ከእናንተ ይልቅ በተሻለ ጌጥ ወዳጌጠችው ይኼዳል፡፡ ባልሽ ንጹህ ከኾነ ግን ጌጠኛ ልብስ በመልበስ ደስ አታሰኚውም፤ በበጎ ምግባርሽ ነው እንጂ፡፡ እንደዉም እንዲህ እርሱን ደስ አሰኘዋለሁ ባልሽው ተግባር ይበልጥ እንደምታሳዝኚው በእውነት እነግርሻለሁ፡፡ ከእግዚአብሔር ይልቅ ይህን ዓለም እንደምትወጂ ያስባልና፡፡ ምንም ያህል በጎ ሕሊና ቢኖረዉም መናገር አፍሮ በልቡ ይጠረጥርሻል፡፡ ቅናተኛ እንዲኾን ታደርጊዋለሽ፡፡ እንዲህ በማድረግሽ ከእርሱ ማግኘት የነበረብሽን ደስታ ታጫለሽ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ ትፋቻለሽ፡፡

ምናልባት በምናገረው ነገር ተበሳጭታችሁ “ለወንዶች አግዞ ሴቶች እንዳያጌጡ ይቃወማል” ልትሉኝ ትችላላችሁ፡፡ ነገር ግን አይደለም፡፡ ወንድ ስለኾንኩኝ ለወንዶች አድልቼ አይደለም፡፡ እንዲህ አድርጌ የምናገረው እናንተው ራሳችሁ ትዳራችሁን እንዳታፈርሱ ብዬ ነው እንጂ፡፡ ከአላፊና ጠፊ ግብር እንድለያችሁ ብዬ ነው እንጂ፡፡

አምራችሁ አጊጣችሁ መታየትን ትወዳላችሁን? እኔም እግዚአብሔር በሚወደውና ሰማያዊው ንጉሥ በመረጠው መንገድ ታጌጡ ዘንድ እወዳለሁ (መዝ.45፡11)፡፡

ይቀጥላል...

(የክርስቲያን መከራ እና ሌሎች ቅዱስ ዮሐንስ_አፈወርቅ እንደአስተማረው ገጽ 47-55➛ገብረ እግዚአብሔር ኪደ የተረጎመው)
93🙏20💯3🕊1
ስለ ጌጠኛ ልብስ - የመጨረሻ

እኅቴ ሆይ! እስኪ ንገሪኝ፤ የትኛው ትመርጫለሽ? እግዚአብሔር እንዲወድሽ ነውን ወይስ ሰው ይወድሽ ዘንድ ነው? በምግባር በትሩፋት ብታጌጪ እግዚአብሔር ይወድሻል፡፡ ጌጠኛ ልብስን ብትወጂ ግን ዘማውያን ይወዱሻል፤ እግዚአብሔርም ይጠላሻል፡፡ እግዚአብሔር የሚወደው ጌጠኛ ልብስን ሳይኾን ጌጠኛ ነፍስን ነውና፡፡ ዘማውያን ግን ጌጠኛ ነፍስን ሳይኾን ጌጠኛ አፍአዊ ሰውነትን ይወዳሉ፡፡

እናንተ ሴቶች ሆይ! እንግዲህ ከወንዶች ይልቅ እናንተን እንደወደድኳችሁ፣ በእውነተኛው ትሩፋት ታጌጡ ዘንድ እንደምደክም፣ ዘማውያን ከሚወዷችሁ እግዚአብሔር እንዲወዳችሁ እንደምተጋ አስተዋላችሁን?

እግዚአብሔር የሚወዳት ሴትስ ምን ትመስላለች? መላእክትን ትመስላለች፡፡ አንድ ምድራዊ ንጉሥ የሚወዳት ሴት ከኹሉም ይልቅ ደስተኛ ከኾነች ልዑል እግዚአብሔር ፈጽሞ የሚወዳት’ማ ክብሯ እንደ ምን ይበዛ ይኾን? ዓለሙን ኹሉ እስከ ምጽአት ድረስ ስትገዢ ብትኖሪ ይህን ክብር የሚተካከል የለም ብዬ በእውነት ያለ ሐሰት እነግርሻለሁ፡፡

እንግዲያው ተወዳጆች ሆይ! ማለፍ መለወጥ በሌለባት በመንግሥተ ሰማያት ጸጋንና ክብርን እናገኝ ዘንድ በምግባር በትሩፋት እናጊጥ፡፡ በዚህ ዓለም የሚኖረን ውበትና ጌጥ ድንገት ታይቶ የሚጠፋ ነው፡፡ የማይቻል ቢኾንም ምንም በሽታ፣ ኀዘን፣ ብስጭት፣ ይህም የመሳሰለ ኹሉ ባያገኘን እንኳን የዚህ ዓለም ውበትና ጌጥ ሃያ ዓመት ነው፡፡ በወዲያኛው ዓለም የሚሰጠው የሚገኘው ክብር ግን በዝቶ ሲሰጥ ይኖራል እንጂ መቼም ቢኾን መች አያልፍም፡፡ አይለወጥም፡፡ እርጅና የለምና ቆዳው አይጨማደድም፡፡ ደዌ ሥጋ ደዌ ነፍስ አያገኘውም፡፡ ኀዘን አያወይበውም፡፡ በዚያ የምናገኘው ክብር፣ ውበት፣ ጌጥ ከዚህ ኹሉ የተለየ ነው፡፡ በዚህ ዓለም የምናገኘው ክብርና ውበት ግን የሚጠፋው ገና ከመምጣቱ ነው፡፡ ቢመጣ እንኳን አድናቂዎቹ ብዙ አይደሉም፡፡ ትሩፋትን ጌጥ ያደረጉ ሰዎች አያደንቁትም፡፡ የሚያደንቁት አመንዝሮች ናቸው፡፡

ስለዚህ ከዚህ ዓለም ከኾነው ክብር ልንለይ ይገባናል፡፡ መንግሥተ ሰማያትን እንወርስ ዘንድ ልንፈልገው የሚገባን ትሩፋትን ነው፡፡

(የክርስቲያን መከራ እና ሌሎች ቅዱስ ዮሐንስ_አፈወርቅ እንደአስተማረው ገጽ 47-55➛ገብረ እግዚአብሔር ኪደ የተረጎመው)
83😍22🙏16👍5🕊1🏆1
2025/10/20 15:44:11
Back to Top
HTML Embed Code: