Telegram Web Link
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
                            †                             

[ ዋይ ዜማ ዘሰማዕኩ ]


" ዋይ ዜማ ዘሰማዕኩ እመላእክት ቅዱሳን "

[ ከሰማይ ከቅዱሳን መላእክት የሚያስደንቅ ዜማ ሰማሁ። ]

[ ቅዱስ ያሬድ ]


" በአባቶችሽ ፈንታ ልጆች ተወለዱልሽ::" [መዝ.፵፬፥፲፪]


†                       †                        †
💖                    🕊                     💖
🕊

[ † እንኳን ለታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

 🕊 † ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ †  🕊

† ቅዱስ ያሬድ :- ከእግዚአብሔር ያገኘነው አባታችን : ክብራችን : ሞገሳችን ነውና በምን እንመስለዋለን ?

- አንደበቱ ጣፋጭ [ጥዑም]::
- ልቡናው የቅድስና ማሕደር::
- ሕሊናው የምሥጢራት ሠረገላ ነው::
- እስከ አርያም ተነጥቆ የማይፈጸም ምሥጢርን የተመገበ ማን እንደርሱ!

ሊቀ ሊቃውንት እዝራ ሐዲስ እንደሚሉት:- "ቅዱስ ያሬድ ለኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከራስ ጸጉሯ እስከ እግር ጥፍሯ : ሙሉ አካሏ ነው::"

🕊 † የሊቁ ዜና ሕይወት በጥቂቱ †  🕊 

† ቅዱስ ያሬድ የተወለደው በ፭፻፭ [505] ዓ/ም አክሱም አካባቢ ሲሆን እናቱ ክርስቲና [ታኡክልያ] አባቱ ደግሞ ይስሐቅ [አብድዩ] ይባላሉ:: ሊቁ በሕጻንነቱ ምሥጢር [ትምሕርት] አልገባው ብሎ ይቸገር ነበር:: ትምሕርት እንቢ ያለው ሰነፍ ስለ ነበር አይደለም:: በጥበበ እግዚአብሔር እንጂ::

ምን ትምሕርት ባይገባው ጾምና ጸሎትን ያዘወትር ነበር:: ልቡናው ደግሞ በእመቤታችንና በልጇ ፍቅር የታሠረ ነበር:: አንድ ቀን ግን መምሕሩ የነገሩት ቀለም አልያዝሕ አለው:: ሲፈትኑትም ባለመመለሱ ተገረፈ::

ዱላው በጣም ስለ ተሰማው ቅዱሱ ከመምሕሩ ኮብልሎ ማይ ኪራሕ አካባቢ ሲደርስ ደክሞት አርፎ እግዚአብሔር ትጋትንና ተስፋ አለመቁረጥን ከትል አስተማረው:: ትሏ ስድስት ጊዜ ወድቃ በሰባተኛው ፍሬዋን ስትበላት ተመልክቷልና::

ከዚህ በኋላ ቅዱስ ያሬድ ወደ መምሕሩ ተመልሶ : ይቅርታ ጠይቆ ትምሕርት ጀመረ:: ሊቁም ትጋትንና ጸሎትን ከሰጊድ ጋር አበዛ:: እግዚአብሔር ደግሞ በድንግል እናቱ አማካኝነት የምሥጢር ጽዋን አጠጣው::

ካህኑ ያሬድ እንዲያ አልገባህ ያለው ምስጢር ተገልጦለት በጥቂት ጊዜ ብሉይ ከሐዲስ ወሰነ:: በምሥጢር ባሕርም ይዋኝ ጀመር::

ያን ጊዜ ሰማያዊ ዜማ አልተገለጠም ነበርና በጸሎት ላይ ሳለ ተደሞ መጣበት:: ሦስት መላእክት በሦስት ወፎች አምሳል መጥተው አነጋገሩት:: ድንገትም ነጥቀው ወደ ሰማያት : ወደ ልዑላኑ መላእክት ዘንድ አደረሱት:: ሊቁ በሰማያት ልዩ ምሥጢር : ልዩ ምስጋናና ልዩ ዜማን አዳመጠ:: ይሕንን ምስጋና ብዙ ቅዱሳን ቢሰሙትም ቅዱስ ያሬድ ግን ይዞት እንዲወርድ ተፈቀደለት::

ሊቁ ወደ ምድር ተመልሶ በታላቅ ተመስጦ አክሱም ጽዮን ውስጥ በሃሌታ አመሰገነ:: ሕዝቡና ንጉሡም ከጣዕሙ የተነሳ አደነቁ:: ቅዱስ ያሬድ ለተወሰነ ጊዜ በአክሱምና ደብረ ዳሞ ሲያገለግል ቆይቶ : ከመሬት ክንድ ከስንዝር ከፍ ብሎ ለእመቤታችን አንቀጸ ብርሃንን ደርሶላት ከሃገሩ ወጣ::

† ቅዱስ ያሬድ በቀሪ የሕይወቱ ዘመናት :-

፩. አምስት ያሕል መጻሕፍትን ጽፏል::
፪. በጣና ቂርቆስ : በዙር አባና በሌሎችም ቦታዎች ወንበር ዘርግቶ ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርቷል::
፫. በሰሜን ተራሮች አካባቢ በትጋሃ መላእክትና በተባሕትዎ ኑሯል::

† በ ፭፻፸፮ (፭፻፸፩) 576 (571) ዓ/ም በተወለደ በ፸፩ [71] ዓመቱ በዚህች ቀን ተሰውሯል::

† አባቶቻችን :-

- ጥዑመ ልሳን
- ንሕብ
- ሊቀ ሊቃውንት
- የሱራፌል አምሳያ
- የቤተ ክርስቲያን እንዚራ
- ካህነ ስብሐት
- መዘምር ዘበድርሳን
- ማኅሌታይ
- ልዑለ ስብከት እያሉ ይጠሩታል::

† የቅዱሱ ጸሎትና በረከት ሃገራችንን ከክፉው ሁሉ ይጠብቅልን::

🕊

[ †  ግንቦት ፲፩ [ 11 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ ያሬድ ካህን ወማኅሌታይ
፪. አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ
፫. ቅዱሳን ክርስቲናና ይስሐቅ [ የቅዱስ ያሬድ ወላጆች ]
፬. ቅድስት ታውክልያ እናታችን [ ንግሥናን ንቃ ሰማዕት የሆነች ]
፭. ቅድስት ኤፎምያ ሰማዕት
፮. ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
፯. ቅድስት አናሲማ ገዳማዊት
፰. አባ በፍኑትዮስ ገዳማዊ
፱. አባ አሴር ሰማዕት [ ኢትዮዽያዊ ]
፲. አባ በኪሞስ ጻድቅ

[ †  ወርሐዊ በዓላት ]

፩. ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት
፪. ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
፫. ብፁዐን ኢያቄም እና ሐና

" እንዲህ ያለው ሰው ከአሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ:: እንዲህ ያለውንም ሰው አውቃለሁ:: በሥጋ እንደ ሆነ ወይም ያለ ሥጋ እንደሆነ አላውቅም:: እግዚአብሔር ያውቃል:: ወደ ገነት ተነጠቀ:: ሰውም ሊናገር የማይገባውን: የማይነገረውን ቃል ሰማ :: " † [፪ቆሮ.፲፪፥፪-፭] (12:2-5)

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
ሰላም ለአጽፋረ እግርከ ከዋክብተ ጽባሕ ጽዱላት ። እስከ ምዕራብ እግር አብርሃ መልዕልተ አጻብዕ ሰማያት ። አድህነነ በጸሎትከ እም እለት አኪት። ወባልሀነ እምኩሉ መንሱት።

#ትርጉም ፦ የሚያበሩ የንጋት ከዋክብት ለኾኑ ጥፍሮችህ ሰላምታ ይገባል፤በጣቶችኽ ሰማያት እስከ ምዕራብ ድረስ ይበራሉና፤ቅዱስ ያሬድ ከሞት በፊት እንደተሰወርኽ በጸሎትኽ ከክፉ ቀን አድነን፤ከፈተናም ሁሉ ሰዉረን።

የኢትዪጵያ ሞገስ ግርማ
የኦርቶዶክስ የክብር አርማ
ስሙ በአለም የተሰማ
ቅዱስ ያሬድ ባለዜማ

እንኳን ለቅዱስ ያሬድ አመታዊ ክብረ
በአል በሰላም አደረሳችሁ


#መልካም_ዕለተ_ሰንበት 🙏

አጫጭር ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶች
•➢ 👇 ለማግኘት // 👇

@Enatachn_mareyam
@Enatachn_mareyam
                        †                        

🕊  💖        ሰ ላ ም ታ        💖  🕊

❝ ክርስቶስ ተንስአ እሙታን
▸ በዐቢይ ኃይል ወስልጣን ፤
አሠሮ ለሰጣን
▸ አግዐዞ ለአዳም ፤
ሰላም
▸ እምይእዜሰ ፤
ኮነ
▸ ፍስሐ ወሰላም ❞

🕊

❝ ክርስቶስ በታላቅ ኃይልና ስልጣን ከሙታን ተነሳ ፤ ሰይጣንን አሰረው ፤ አዳምንም ነጻ አወጣው ፤ ስለዚህም ከእንግዲህ ወዲህ ፍፁም ሰላም እና ደስታ ሆነ። ❞

▬▬▬▬▬▬   †    ▬▬▬▬▬▬

[ ❝ ይህች ዕለት የተቀደች ናት ❞ ]

  ዛቲ ዕለት ቅድስት ይእቲ ለውሉደ  ሰብእ  መድኀኒት ..."

ይህች ዕለት የተቀደች ናት ። ለሰው ልጆችም  መድሃኒት ናት።በየጊዜውና በየሰአቱ መሪ ትሁነን። እግዚአብሔር ሰንበትን ቀደሰ።

ሁልጊዜ መሀሪ ሰውን ወዳጅ ክርስቶስ የዓለም ንጉሥ ሕዝቡን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው ሰንበትን በእውነት አክብሩ። መዋደድን ገንዘብ አድርጉ። ሰንበትን አክብሩ ጽድቅንም ስሩ። ነቀዝ የማይበላውን የማያረጀውን የማይጠፋውን ሰማያዊ መዝገብ [ሃብት] አከማቹ። ❞

[    ቅዱስ ያሬድ    ]


[ †  🕊  ክብርት ሰንበት  🕊 † ]

†                       †                         †
💖                    🕊                     💖
                        †                        

🕊  💖    ቅዱስ ያሬድ    💖  🕊

[ ግንቦት ፲፩ [ 11 ] የቅዱስ ያሬድ ዓመታዊ በዓል ]

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ አባቱ አብዩድ [ ይሥሐቅ ] እናቱ ክርስቲና [ ታውክልያ ] ሲባሉ የተወለደውም በ፭፻፭ ዓ.ም. በአክሱም ነው፡፡ ሰባት ዓመት ሲመላው አባቱ ስላረፈ፤ እናቱ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እንዲያስተምረው ለአባ ጌዴዎን ሰጠችው፡፡

ነገር ግን ማጥናት ስላልቻለ አባ ጌዴዎን ይቈጣው ነበርና ሸሽቶ ከዱር ውስጥ ገባ ፤ ከዐዘኑም ብዛት የተነሣ በዛፍ ሥር ተጠልሎ ሳለ አንዲት ታናሽ ትል ከዛፍ እኩሌታ ደርሶ ሲወድቅ ሲነሣ በመጨረሻም በጭንቅ ከዛፉ ላይ ሲወጣ በማየቱ እግዚአብሔር በዚኽች ታናሽ ፍጥረት እንዳስተማረው በመረዳት ይቅርታ ጠይቆ ወደ መምህሩ ተመልሷል፡፡

❝ ወእምዝ ሶበ ሰአለ ኀበ እግዚአብሔር በብካይ ብዙኅ ተርኅወ ልቡናሁ ወተምህረ በሐጺር ዕለት መጻሕፍተ ብሉይ ወሐዲስ❞ ይላል ከዚኽ በኋላ ቅዱስ ያሬድ ወደ እግዚአብሔር በለመነ ጊዜ ልቡናው ብሩህ ኾኖለት በዐጭር ጊዜ ውስጥ የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ተምሮ በመጨረስ ዲቁናን ተሾመ ፤ እስከ ርሱ ዘመን በማነብነብ እንጂ በከፍተኛ ድምፅ የመዝሙር ማሕሌት አልነበረም ፤ እግዚአብሔርም ለዚኽ አባት የመላእክትን ዝማሬ ሊያሳየው ስለወደደ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እስከ ሦስተኛው ሰማይ እንደተነጠቀ ኹሉ ሊቁም ተነጥቆ የኻያ አራቱ ካህናተ ሰማይን የምስጋና ዝማሬ ሰምቶ ተመለሰ፡፡

ቅዱስ ያሬድ ከአርያም ወርዶ ወደ ምድር እንደ ደረሰ ወደ አክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ፦ ❝ ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ ቀዳሚሃ ለጽዮን ሰማየ ሣረረ ወበዳግም አርአዮ ለሙሴ ዘከመ ይገብር ግብራ ለደብተራ ❞

[ ለአብ ምስጋና ይገባል ፣ ለወልድም ምስጋና ይገባል ፣ ለመንፈስ ቅዱስም ምስጋና ይገባል፡፡ ከጽዮን አስቀድሞ ሰማይን ፈጠረ ዳግመኛም ለሙሴ የድንኳኑን ሥራ እንዴት እንደሚሠራ አሳየው ] ሲል ዘምሮ ይቺኑ መዝሙር ከሰማይ መላእክት አገኘኹት ፣ በማለት "አርያም" በሚል ሥያሜ ጠርቷታል፡፡

ይኽነኑ ድርሳነ ዜማ የጻድቁ ካሌብ ልጅ ንጉሥ ገብረ መስቀል በሰማ ጊዜ ጫማውን ሳይጫማ ንግሥቲቱም ደንገጡሮቿን አጃቢዎቿን ሳታስከትል መኳንንቱ ፣ ካህናቱና መምህራኑ እነሱን ተከትለው እየተጣደፉ ወደ ዐደባባዩ በመኼድ በተመስጦ ሲሰሙት ውለዋል፡፡

ቅዱስ ያሬድ ዐምስት የዜማ መጻሕፍትን የደረሰ ሲኾን እነርሱም ፦

፩ኛ ] ድጓ  
፪ኛ ] ጾመ ድጓ
፫ኛ ] ምዕራፍ
፬ኛ ] ዝማሬ
፭ኛ ] መዋሥዕት ናቸው፡፡

እነዚኽንም ታላላቅ ድርሰቶቹን በሦስት የዜማ ስልቶች ማለት በግእዝ ፣ በዕዝል ፣ በአራራይ አዘጋጅቷቸዋል፡፡ ❝ ወአሐተ ዕለተ እንዘ ይዜምር ያሬድ ቀዊሞ ታሕተ እገሪሁ ለንጉሥ ገብረ መስቀል ወእንዘ ያጸምዕ ንጉሥ ቃሎ ለያሬድ ተከለ በትረ ኀጺን ውስተ መከየደ እግሩ ለያሬድ❞ ይላል ፤ ከዕለታት ባንዳቸው ቅዱስ ያሬድ በተመስጦ ልዑል እግዚብሔርን በዝማሬ ሲያመሰግን ንጉሥ ገብረ መስቀል ሳያውቁት ልባቸው በጣዕመ ዜማው በመመሰጡ የብረት ዘንጉን በቅዱስ ያሬድ እግር ላይ ተክለውታል፤ ከእግሩም ብዙ ደም ቢፈስስም ቅዱስ ያሬድ ግን ማሕሌቱን እስከሚፈጽም ድረስ ምንም አልሰማውም ነበር፡፡

ንጉሡም የደሙን መፍሰስ አይቶ ደንግጦ ቅዱስ ያሬድን ❝ የደምኽ ዋጋ የፈለግኸውን ንገረኝ ❞ አለው ፤ ቅዱስ ያሬድም ተምኔቱ ወደ ገዳም መኼድ እንደኾነ ነገረው ፤ ያን ጊዜ ንጉሡ እያዘነ አሰናብቶታል፡፡

❝ ወእምዝ ቦአ ያሬድ ውስተ ቤተ ክርስቲያን ወቆመ ቅድመ ታቦተ ጽዮን ❞ ይላል ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ በታቦተ ጽዮን ፊት በመቆም የአንቀጸ ብርሃንን ምስጋና ከመዠመሪያው እስከ መጨረሻው በተናገረ ጊዜ በእግዚአብሔር ኀይል ክንድ ያኽል ከምድር ከፍ ከፍ አለ።

ከዚኽ በኋላ ወደ ሰሜን ተራራዎች ወደ ገዳም ሲኼድ የአኲስም ጽዮን ካህናት እስከ ተከዜ ወንዝ ድረስ ሸኙት ርሱም እጅግ ባማረ ጣዕመ ዜማ ድምፁን ከፍ አድርጎ ❝ ሰላም እግዚአብሔር ኲሉ ባቲ ተሃሉ ወትረ ምስለ ኲልክሙ ❞ [ በኹሉ ላይ ጸንታ የምትኖር የእግዚአብሔር ሰላም ዘወትር ከኹላችኊ ጋር ትኑር ] ብሎ የስንብት መዝሙርን ዘመረ ፤ ካህናቱም ይኽነን ቃል ሰምተው መሪር እንባን አለቀሱና ተሰነባበቱ፡፡

በትርጓሜ ቅዳሴ ማርያም መቅድም ላይ እንደምናነብበው ቅዱስ ያሬድ ማይ ኪራህ በተባለው ቦታ ተሰውሮ ጸዋትወ ዜማን ሲያስተምር እመቤታችን ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬምን የብህንሳውን አባ ሕርያቆስን በአካለ ነፍስ እንዲመጡ አድርጋ ኤፍሬም ውዳሴዬን ፤ ሕርያቆስ ቅዳሴዬን ነግራችኹት ቅዱስ ያሬድ በዜማ ይድረስልኝ ብላ ነግረውት በዜማ ደርሶታል ፤ ይኽም ሊታወቅ ሥረይ በቅዳሴ ማርያም ይበዛል፡፡

ርሱም ጸዋትወ ዜማን ለደቀ መዛሙርቱ እያስተማረ መላእክት ዘወትር እየጐበኙት በጾም በጸሎት ተወስኖ በተጋድሎ ለኻያ ኹለት ዓመት ጸንቶ ኖረ፤ በመጨረሻም ጌታችንም ለቅዱስ ያሬድ ተገልጾለት ፦

❝ ኦ ፍቁርየ ቀዳሚኒ በከመ ሰመርኩ ትርአይ ሥርዐተ ስብሐተ መላእክት ዘበሰማያት ወአስተኀለፍከ ዘንተ ማሕሌተ ዲበ ምድር ... ❞

[ ወዳጄ ሆይ ቀድሞ በሰማይ ያለ የመላእክትን ሥርዐተ ማሕሌት እንድታይና ወደ ምድርም አስተላልፈኽ ይኽነኑ ዜማ እንድትመሠርት እንደ ወደድኊ ኹሉ እኔ ዳግም ተመልሼ በምመጣበት ጊዜ ከካህናተ ሰማይና ሄሮድስ ደማቸውን ካፈሰሰው ሕፃናት ጋር በደብረ ጽዮን ትዘምር ዘንድ ሰማያዊ የክብር አክሊልና የብርሃን ልብስ ተዘጋጅቶልኻል። ] ብሎት ቃል ኪዳንን ሰጥቶት ጌታ በክብር ዐረገ፡፡ የቅዱስ ያሬድ መታሰቢያውም ግንቦት ዐሥራ አንድ ነው፡፡

ሊቁ አርከ ሥሉስም የቅዱስ ያሬድን ነገር በአርኬው ላይ ፦

❝ ሰላም ለያሬድ ስብሐተ መላእክት ለሕዋጼ
እንተ አዕረገ በልቡ ኅሊና መንፈስ ረዋጼ
ለትምህርተ መጽሐፍ ገብአ እምኀበ ኮነ ነፋጼ
በብዙኅ ጻማ ዘአልቦ ሑጻጼ
መልዕልተ ጒንደ ዖም ነጺሮ እንዘ የዐርግ ዕጼ❞

[ የመላእክትን ምስጋና ለመጐብኘት ከመንፈስ ቅዱስ የሚሰጥ ፈጣን ዐሳብን ወደ ልቡናው ያሳረገ ለኾነ ፤ ጒድለት በሌለበት በብዙ ድካምም ወደ ዛፍ ግንድ ጫፍ ላይ ትል ሲወጣ ተመልክቶ፤ ኰብልሎ ከኼደበት መጻሕፍትን ለመማር የተመለሰ ለኾነ ለያሬድ ሰላምታ ይገባል። ] በማለት ሊቁ ማሕሌታይን አመስግኖታል፡፡

ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በተአምኆ ቅዱሳን መጽሐፉ ላይ ማኅቶተ ቤተ ክርስቲያን ሊቁ ቅዱስ ያሬድን ሲያወድስ ፦

❝ ሰላም ለያሬድ ቀሲስ ዘጽጉብ እክለ መንፈስ ቅዱስ ፤
ዘአስተጋብአ ምድራሳተ እምኲሎሙ መጻሕፍት
ወአሰርገዋ በሐዋዝ ስብሐት ወበጥዑም ማሕሌት
ለብሔረ ኢትዮጵያ በስብሐት ሃሌ ሉያ
ዘከዐወ ቃለ መለኮት ዲቤሃ
ከመ አስራበ ወርቅ ንጹሐ፡፡ ❞

[ የመንፈስ ቅዱስን ምግብን የጠገበ ፤ ከመጻሕፍት ኹሉ ትርጓሜያተ ድርሰትን ያሰባሰበ ፤ ሃሌ ሉያ በሚል ምስጋና የኢትዮጵያ ሀገርን በጥዑም ማሕሌትና በሚያምር ምስጋና ያስጌጠ፤ የመለኮት ቃልን በላይዋ ላይ እንደ ንጹሕ የወርቅ ሻሻቴ ያፈሰሰ ለኾነ ለካህኑ ያሬድ ሰላምታ ይገባል ] ይለዋል፡፡

[ በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ ]


†                       †                         †
💖                    🕊                     💖
Forwarded from አብሰራ ገብርኤል ለማርያም (ባሕራን)
🕊


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ
አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡

🕊   †  እንኳን አደረሳችሁ  †   🕊 

🕊   ግንቦት ፲፪ [ 12 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት


[ † 🕊 ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ 🕊 † ]

ለቤተ ክርስቲያን የብርሃን ምሰሶ ስለሆነላት ስለ ታላቁ ሐዋርያዊ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ምን እላለሁ? ምንስ እናገራለሁ? እንደ እኔ ያለ ኃጥእ: ለባሴ ሥጋና ገባሬ ንስሃ ስለሱ ሊናገር አይቻለውምና:: አባቶቻችን እንደ ነገሩን ስለ አፈ ወርቅ ለመናገር አፈ ወርቅ መሆን ያስፈልጋል:: ግን እስኪ በቅዱሱ አባት ምልጃ ጥቂት ልሞክር::

🕊  ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ማን ነው?  🕊

ነገዱ ከሶርያ: የተወለደው በ፫፻፵፯ [347] ዓ/ም በእስክንድርያ ሲሆን አባቱ አስፋኒዶስ እናቱ ደግሞ አትናስያ ይባላሉ:: እነርሱ ደግ ቢሆኑ ይህንን እንቁ ልጅ እግዚአብሔር ሰጣቸው:: ዮሐንስ ለክርስቲያን እንደሚገባ በትምሕርትና በጥበብ አደገ:: ገና በሕጻንነቱ ወደ ግሪክ ሔዶ የዘመኑን ሳይንስ [ፍልስፍና] ከአፉ እስከ ገደፉ ተምሮ ተመልሷል::

ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅን ለየት ከሚያደርጉት ነገሮችም አንዱ ይሔው ነው:: በዘመናዊም ሆነ በመንፈሳዊ ትምሕርት ይህ ቀረህ የማይሉት ሊቅ የሆነው ገና በ፲፭ [ 15 ] ዓመቱ ነበር:: በ፪ [ 2 ] ወገን የተሳለ ሰይፍ በመሆኑ ስንኳን በሕይወተ ሥጋ እያለ ዛሬም ለንፉቃን ትልቅ የራስ ምታት ነው::

ቅዱሱ ገና በ፲፮ [ 16 ] ዓመቱ ሃብት: ንብረት: ውበት: ክብርና እውቀት የሞላለት ቢሆንም ያለውን ሁሉ ለነዳያን ሰጥቶ መጻሕፍትን ብቻ ሰብስቦ ከባልንጀራው ቅዱስ ባስልዮስ ጋር በርሃ ገባ:: ሰውነቱን በጾምና በጸሎት እየቀጣ በበርሃ ሲኖር ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስና ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ዼጥሮስ ወደ እርሱ መጡ:: ሊቀ ሐዋርያት የመንግስተ ሰማያትን መክፈቻ ስልጣን ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ ወንጌሉን ሰጥተው ተሰወሩት::

ከዚህች እለት በኋላ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ባሕረ ምስጢራት ሆነ:: ብሉይ ከሐዲስ: ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ራዕየ ዮሐንስ ድረስ በአንድምታ ትርጉዋሜ ተነተናቸው:: በተለይ ሐዲስ ኪዳንን እየመላለሰ አመሰጠረው:: ቅዱስ ሕሊናው ሳይታክት: ንጹሕ እጆቹ ሳይዝሉ የጻፋቸው ድርሳናት: መልዕክታትና ትርጉዋሜያት ቢቆጠሩ አሥር ሺህ ሞሉ:: በእውነት ለዚህ አንክሮ ይገባል! የሚገርመው ይህን ሁሉ ሲሰራ እድሜው ገና ለጋ: ማዕርጉም ዲቁና ነበር::

ከዚህ በኋላ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ቅስና ተሹሞ
በስብከተ ወንጌል ብዙ ቦታዎችን አዳረሰ:: በቅድስናው ወደውታልና የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ አድርገው ሾሙት:: አፈ ወርቅ ሲናገርም ሆነ ሲያስተምር እንኳን የሚያወራ ኮሽ የሚል የለም:: ከጣዕመ ትምሕርቱ የተነሳ ሕዝቡ በተደሞ ይሰሙት ነበር::

ሲያስተምር ምድራዊው ሰው ይቅርና ልዑላኑ መላእክት ተሰብስበው ያደንቁት ነበር:: አንዴም እመቤታችን በሕዝብ መካከል " አፈ-ወርቅ" ብላ ጠርታዋለች:: ለዛም ነው አፈ-ወርቅ የሚባለው:: ቅዱሱ በሥልጣነ ቃሉ መልዐከ ሞትን ገስፆ ፲ [10] ዓመት አቁሞታል::

ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ለሰው ፊት አያደላም:: በርሱ ዘንድ ንጉሥና ደሃ ነዳይ እኩል ነው:: ለሞት ያበቃውም ይሔው ነበር:: ምክንያቱም የወቅቱ ንግስት አውዶክስያ ያንዲት ድሃ መበለትን መሬት ቀምታ አልመልስም በማለቷ መክሮ አወገዛት:: እርሷ ግን ከኃጥአንና መናፍቃን ጋር መክራ ፪ [2] ጊዜ አጋዘችው::

በተሰደደበት ፍሬ አፍርቶ: አስተምሮና አሳምኖ በ፬፻፯ [407] ዓ/ም አርፏል:: ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ሳይጠግቡት እንደናፈቁት በ፷ [60] ዓመቱ አጡት:: በወቅቱ ታላቅ ሐዘንና ለቅሶ ተደረገ::

አንድ ቀን የዘመኑ ደግ ንጉሥ አርቃድዮስ ግብር አገባ [ግብዣ አዘጋጀ]:: በዚያች ሌሊት ደግሞ ቅዱሱ ሊቅ ታጥቆ ሲጸልይ ሳለ: አባ ማርዳሪ የሚባል ጻድቅ ደግሞ ከሰማይ ፲፪ [12] ቱ ሊቃነ መላእክት [እነ ቅዱስ ሚካኤል] በግርማ ሲወርዱ ተመለከተ::

ደንግጦ "ወዴት ናችሁ ጌቶቼ" ቢላቸው "ቁስጥንጥንያ: ወደ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እንሔዳለን:: እርሱ እመቤታችንን እንደሚያመሰግናት ጌታ ነግሮናልና" አሉት:: "እባካችሁ እኔም የአፈ ወርቅ ምስጋናው እንገለጥልኝ መርቁኝ" አላቸው:: ሊቃነ መላእክቱም መርቀውት ጐዳናቸውን ቀጠሉ::

በማግስቱ በቤተ መንግስት ውስጥ ሊቃውንቱ: መሳፍንቱ: ዻዻሳቱ: ሕዝቡ ሁሉ ተሰብስበው ከድግሱ በሉ:: ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ግን በመንበሩ ተቀምጦ ነበር እንጂ አልበላም:: ድግሱ ሲጠናቀቅ ንጉሡ አርቃድዮስ ሊቁን "ጥያቄ አለኝ" ብሎ በጉባኤ መካከል ጠየቀው::

"ምነው ወንጌላዊ ማቴዎስ 'ኢያዕመራ ዮሴፍ እስከ አመ ወለደት ወለደ ዘበኩራ-የበኩር ልጇን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም' ማለቱ [ማቴ.፩፥፳፭] (1:25) ስለ ምን ነው?" ቢለው ቅዱሱ ተነስቶ: በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ይተረጉምለት ጀመር::

"ድንግል ማርያም ንጹሕ ብርሌን ትመስላለች:: ብርሌ የተለያየ ቀለም ያለው ፈሳሽ ቢያስገቡበት ቀለሙ አብሮ ይቀያየራል:: እመቤታችንም ጌታን ጸንሳለችና ሕብረ መለኮቱ ሲለዋወጥ መልኳ አብሮ ሲለዋወጥ እያየ ዮሴፍ ይደነግጥ ነበር::

'እርሷ ማን ናት? በማሕጸኗ ያለውስ ማን ነው' እያለ ይጨነቅ ነበር:: ጌታን ከወለደች በኋላ ግን አንድ ሕብረ መልክ ሆናለችና:: አስቀድሞ ማን እንደ ነበረች አላወቀም::

አሁን ግን እርሷም ወላዲተ አምላክ: ልጇም አምላክ ዘበአማን መሆኗን አወቀ ማለት ነው" እያለ ሲተረጉም ሰምተው ሁሉም ሲያደንቁ: በዚያ የነበረች ስዕለ አድኅኖ "አፈ ወርቅ! ልሳነ ወርቅ! አፈ በረከት!" ስትል ተናገረች::

ያን ጊዜ አርቃድዮስ የወርቅ ልሳን በሊቁና በስዕሏ ላይ አደረገ:: አፈ ወርቅ ግን ባጭር ታጥቆ "እሰግድ ለኪ ! እሰግድ ለኪ ! ወእዌድሰኪ . . ." ብሎ ዛሬ በተአምረ ማርያም የምናውቀውን ምስጋና ሰተት አድርጐ አደረሰላት:: ይህንን ምስጋናም ሊቃነ መላእክቱ ሰምተው እያደነቁ ወደ ሰማይ ወጥተዋል::

ሊቁ ባረፈ በ፴፭ [35] ዓመቱ: በትንሹ ቴዎዶስዮስ ዘመን: ሥጋው ፈልሷል:: ወደ ቁስጥንጥንያ ሲደርስም ከናፍቆት የተነሳ ታላቅ ዝማሬና እንባ ተደርጓል:: አፈ ወርቅም ቀና ብሎ ሕዝቡን
ባርኳል::

ቅዱሱ ሲጠራ እንዲሕ ነው :-

- ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
- አፈ በረከት
- አፈ መዐር [ማር]
- አፈ ሶከር [ስኳር]
- አፈ አፈው [ሽቱ]
- ልሳነ ወርቅ
- የዓለም ሁሉ መምሕር
- ርዕሰ ሊቃውንት
- ዓምደ ብርሃን [የብርሃን ምሰሶ]
- ሐዲስ ዳንኤል
- ሊቀ ዻዻሳት ዘበርትዕ [እውነተኛው]
- መምሕር ወመገስጽ ዘኢያደሉ ለገጽ
- ጥዑመ ቃል - - -

እግዚአብሔር ከቅዱሱ በረከት አብዝቶ: አብዝቶ: አብዝቶ ይክፈለን::

ዳግመኛ በዚህ ቀን ታላቁ ጻድቅ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሥጋቸው ፈልሷል:: ይሕ የተደረገው ጻድቁ ከረፉ ከ፶፮ [56] ዓመታት በኋላ ነው:: በዕለቱም ድንቅ ድንቅ ተአምራት ተፈጽመዋል::

እናታችን ርሕርሕቷ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ደግሞ በዚሕ ቀን ስሟን ለጠራና መታሠቢያዋን ላደረገ የምሕረት ቃል ኪዳን ተቀብላለች::

ቸር አምላካቸው ከሁለቱም ብሩሃን ቅዱሳኑ ክብር ያድለን::

🕊
Forwarded from አብሰራ ገብርኤል ለማርያም (ባሕራን)
[  †  ግንቦት ፲፪ [ 12 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ [ የዓለም ሁሉ መምሕር ]
፪. አቡነ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ጻድቅ [ ፍልሠታቸው ]
፫. ቅድስት እናታችን ክርስቶስ ሠምራ [ ቃል ኪዳን
የተቀበለችበት ]
፬. አባ አብርሃም ዘደብረ ሊባኖስ
፭. ቅዱስ ዕንባቆም ነቢይ
፮. እስክንድር ንጉሠ ኢትዮዽያ
፯. ቅዱስ መስቀል [ የተአምር በዓሉ ]
፰. አባታችን ያሬድ [ የማቱሳላ አባት ]
፱. ቅዱስ ሚናስ ዲያቆን

[ † ወርኃዊ በዓላት ]

፩. ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት
፪. ቅዱስ ድሜጥሮስ
፫. ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
፬. ቅዱስ ቴዎድሮስ በናድሌዎስ
፭. አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ
፮. ቅዱስ ላሊበላ
፯. ቅድስት መስቀል ክብራ

" እናንተ የምድር ጨው ናችሁ . . . እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ:: በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትም:: መብራትንም አብርተው በዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያናሩታል:: በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል:: መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ። " [ማቴ.፭፥፲፫-፲፮] (5:13-16)

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
2024/06/16 20:43:34
Back to Top
HTML Embed Code: