Telegram Web Link
🕊

†   🕊   በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡   🕊   †

❖ እንኳን አደረሳችሁ ❖

ግንቦት ፯ [ 7 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት


🕊 †  ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ †  🕊

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከሐዋርያት ቀጥሎ የቅዱስ አትናቴዎስን ያሕል ስለ ሃይማኖት የተዋጋ ቅዱስ ፈልጐ ማግኘት አይቻልም::

†  ቅዱስ አትናቴዎስ ማን ነው ?

ቅዱስ አትናቴዎስ በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት በዘመነ ሰማዕታት መጠናቀቂያ በ፫፻ [300] አካባቢ ፪፻፺፮ (296) እስክንድርያ ግብፅ ውስጥ ነው የተወለደው:: ወላጆቹ አረማውያን በመሆናቸው ክርስትናን አልተማረም ነበር::

ሕጻን እያለ ለጭዋታ ከቤቱ ሲወጣ የክርስቲያን ልጆች ሃይማኖታዊ ጨዋታ ሲጫወቱ ተመለከተ:: ሊቀላቀላቸው ቢፈልግም ክርስቲያን ባለመሆኑ ከለከሉት:: አትናቴዎስም ክርስቲያን ልሁንና አጫውቱኝ ብሏቸው እሺ ስላሉት ሕጻናቱ ዕጣ ተጣጣሉ::

ላንዱ ቄስ: ላንዱም ዲያቆን መሆን ሲደርሳቸው ለአትናቴዎስ ፓትርያርክ መሆን ስለ ደረሰው ሌሎቹ ሕጻናት ይሰግዱለት ጀመር:: በአጋጣሚ ሕጻናቱ ይሕንን ሁሉ ሲያደርጉ የወቅቱ ፓትርያርክ ቅዱስ እለ እስክንድሮስ በመገረም ያያቸው ነበርና ለሕጻኑ አትናቴዎስ ትንቢት ተናገረለት::

ከዚያም የአትናቴዎስ አባቱ ሲሞት ሊቀ ዻዻሳቱ ከእናቱ ወስዶ አጥምቆ: የሚገባውን መንፈሳዊ ትምሕርት ሁሉ በልቡናው ላይ ቀረጸበት:: ከዚሕ በኋላ ዲቁናን ሹሞ አስተምር አለው:: ምንም ሕጻን ቢሆንም ከሊቅነቱ: ከአመላለሱና ከአንደበቱ ጣፋጭነት የተነሳ የሰማው ሁሉ ይደነቅ ነበር:: ጸጋ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ አድራለችና::

ቅዱስ አትናቴዎስ ሊቀ ዲቁና በተሾመ ወራት አርዮስ ቤተ ክርስቲያንን በመረበሹ ኒቅያ ላይ ፫፻፲፰ [318] ቱ ሊቃውንት ሲሰበሰቡ ጸሐፊ አድርገው ሾሙት:: በጊዜውም በዕድሜ የስንት ጊዜ ትልቁ የሚሆነውን አርዮስን ተከራክሮ ምላሽ አሳጣው::

†  ቅዱስ

አትናቴዎስ ከሊቃውንቱ ጋር ሆኖ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ: እግዚአብሔር መሆኑን በአደባባይ መሠከረ:: ጸሎተ ሃይማኖትንም ያረቀቀው እርሱ ነው::

ከዚሕ በኋላ የእስክንድርያ [የግብፅ] ፳ [20] ኛ ፓትርያርክ ሆኖ ተሾመ:: ቤተ ክርስቲያንን በመልካም እረኝነት ለ፵፰ [48] ዓመታት ሲመግብ ብዙ መከራዎችን ተቀበለ:: ለ፭ [5] ጊዜ ከመንበሩ አፈናቅለው ወደ በርሃ ሲያግዙት በስደት ከ፲፭ [15] ዓመታት በላይ አሳልፏል::

በተሰደደባቸው ቦታዎች መከራን እየተቀበለ ያላመኑትን አሳምኗል:: በጎቹ እንዳይባዝኑበት ደግሞ በጦማር [በደብዳቤ] ይጠብቃቸው ነበር:: ዛሬ በሃይማኖተ አበው የምናገኘው ቃለ ሃይማኖት በዚሕ ዘመን የተጻፈ ነው::

በወቅቱ የነበረው ንጉሥ [ትንሹ ቆስጠንጢኖስ] የአባቱን [ታላቁ ቆስጠንጢኖስን] ዕረፍት ተከትሎ ነገሠ::

ወዲያውም አርዮሳዊ መናፍቅ ሆነ:: ሃይማኖታቸው የቀና አባቶችንም ያሳድድ ገባ:: ከአበው ቅዱሳን መካከል ግንየዚህ መከራ ቀዳሚው ገፈት ቀማሽ ታላቁ ሊቅ ቅዱስ አንትናቴዎስ ነበር::

በተለይ አንድ ጊዜ ንጉሡ ቅዱሱን ወደ በርሃ አግዞ: መናፍቅ ዻዻስ በግብጽ ሹሞ: ብዙ ክርስቲያኖችን በግፍ ሲያስገድል: ቅዱሱን ለ፮ [6] ዓመታት አሰቃየው:: የወገኖቹ [የልጆቹን] ስቃይ የሰማው ቅዱስ አትናቴዎስ ግን በድፍረት ወደ ቤተ መንግስት ገብቶ ተናገረው::

፪ [2] አማራጭን አቅርቦ "ወይ ግደለኝና እንደ አባቶቼ ሰማዕት ልሁን: ካልሆነ ግን ወደ መንጐቼ [ምዕመናን] መልሰኝ" አለው:: መናፍቁ ንጉሥም ቢገድለው ብጥብጥ እንደሚነሳ ስለሚያውቅ በስልት ሊያጠፋው ወሰነ::

ቀዛፊ: መቅዘፊያ: ምግብና ውሃ በሌላት ጀልባ ውስጥ ከቶም ሜዲትራኒያን ባሕር ውስጥ ጣለው:: ድንገት ግን ከሰማይ ጌታችን መላእክቱን አስከትሎ ወረደ::

ሚካኤልና ገብርኤል ባሕሩን እየቀዘፍ: ሌሎች መላእክት እየመገቡት በዚህች ቀን እስክንድርያ [ግብጽ] አድርሰውት ተሠውረዋል:: ሕዝቡም በታላቅ ሐሴት እየዘመሩ አባታቸውን ተቀብለውታል::

ሐዋርያዊው ቅዱስ ስለ ኦርቶዶክስ ተዋግቶ: ብዙ ስቃይንም ተቀብሎ በ፫፻፹፫ [373] ዓ/ም አካባቢ አርፏል:: ቤተ ክስርቲያን ፦
- "ሊቀ ሊቃውንት:
- ርዕሰ ሊቃውንት:
- የቤተ ክርስቲያን
- [ የምዕመናን ] ሐኪም [ Doctor of the Church ]:
- ሐዋርያዊ" ብላ ታከብረዋለች::

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሊቁ በረከት አይለየን:: በምልጃውም ሃይማኖታችንን ይጠብቅልን::

🕊

[ † ግንቦት ፯ [ 7 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
፪. የባሕታውያን አለቃ ታላቁ አባ ሲኖዳ [ጽንሰቱ]
፫. ቅዱስ ዮሐንስ ጻድቅ [ሃብቱን: ንብረቱን: ልብሱን
ሳይቀር መጽውቶ ራቁቱን የተገኘ ደግ ሰው ነው]
፬. አባ ሐርስዮስ ገዳማዊ

[ †  ወርሐዊ በዓላት ]

፩. ሥሉስ ቅዱስ [አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ]
፪. አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
፫. አባ ሲኖዳ [የባሕታውያን አለቃ]
፬. አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
፭. አባ ባውላ ገዳማዊ
፮. ቅዱስ አግናጥዮስ [ለአንበሳ የተሰጠ]

" ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብጹዐን ናቸው:: መንግስተ ሰማያት የእነርሱ ናትና:: ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብጹዓን ናችሁ:: ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ:: ሐሴትም አድርጉ:: ከእናንተ በፊት የነበሩ ነቢያትን እንዲሁ አሳደዋቸዋልና። " [ማቴ.፭፥፲] (5:10)


[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
🕊

[  † እንኳን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥንተ በዓለ ዕርገት እና ለጻድቁ አባ ዳንኤል ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †   ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †


 †  🕊   ዕርገተ እግዚእ   🕊  †  

† ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዓለ ዕርገትን ፪ [2] ጊዜ ታከብራለች:: አንዱ "ጥንተ በዓል" : ሁለተኛው ደግሞ "የቀመር በዓል" ይሠኛል:: ጥንተ በዓል ማለት ጌታችን በትክክል ያረገበትን ቀን ያመለክታል::

የክብር ባለቤት መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በኪነ ጥበቡ [በሕማሙ : በሞቱ] ዓለምን አድኖ: ፵ [40] ቀን ለሐዋርያቱ መጽሐፈ ኪዳንን: ትምሕርተ ኅቡዓትን አስተምሯቸዋል::

በ፵ [40] ኛው ቀን ፻፳ [120] ውን ቤተሰብ ይዟቸው ወደ ቢታንያ ወጣ:: በዚያም እስከ ሊቀ ዽዽስና ድረስ ሾሟቸው : ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡም አዟቸው የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ጠብቁ ብሏቸዋል:: እየባረካቸው በተዋሐደው ሥጋ ወደ ሰማያዊ ዙፋኑ አርጓል::

ሰማያት: ምድር: ደመናት: ነፋሳት: መባርቅትና መላእክት: ፍጥረት በሙሉ አመስግኗል:: አይሁድ መናፍቃን ዕርገቱን ምትሐት ነው እንዳይሉ: ጌታችን ትንሳኤውን አማናዊ እንደሆነ ለማስረዳት በ፵ [40] ኛው ቀን ዐረገ::

አንድም ራስ ባለበት ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ሊኖሩ ይገባልና ጌታችን ዕርገቱን በገሃድ አደረገው:: "ዐርገ እግዚእ ከመ ያለቡ ዕርገተ ጻድቃን ንጹሐን" እንዲል::

† ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ::
ወእግዚእነ በቃለ ቀርን::
ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ:: † [መዝ.፵፮፥፮] (46:6)


🕊  †  ታላቁ አባ ዳንኤል  †  🕊

† ይህ ቅዱስ አባት ስም አጠራሩ ክቡር ነው:: በሁሉ ነገሩ የተቀደሰ የገዳማውያን መብራትም ነው:: ከተረፈ ንጹሕ ሕይወቱ ጣዕመ መንግስተ ሰማያትን አይቷልና:: አባ ዳንኤል በትውልድ ግብጻዊ ሲሆን ዓለምን ንቆ [መንኖ] ገዳም የገባው ገና በወጣትነቱ ነው::

ጊዜውም ዘመነ ጻድቃን [በ፭ [5] ኛው መቶ ክ/ዘመን] ነበር:: በገዳመ አስቄጥስ እና በደብረ ሲሐት ይታወቃል:: ታላቋ መካነ ቅዱሳን ገዳመ ሲሐት ዛሬም ድረስ በስሙ የምትጠራ ሲሆን ለዚህም ምክንያቱ እጅግ ለብዙ ዘመናት በውስጧ ተጋድሎ ፍሬ ስላፈራባት : ደቀ መዛሙርትን በቅድስና ስለ ወለደባት ነው::

ስለዚህም ዛሬም ድረስ "አባ ዳንኤል ዘደብረ ሲሐት" ተብሎ ሲጠራ ይኖራል:: ሌላኛው ስሙ ደግሞ "ዘገዳመ አስቄጥስ" ይሰኛል:: ገዳመ አስቄጥስ የታላቁ ቅዱስ መቃርስ ርስት ሲሆን በዓለም በስፋትም : ብዙ ቅዱሳንን በማፍራትም አንደኛ የሆነ ገዳም ነው::

በዚህ ገዳም ላይ አበ ምኔት ሆኖ የሚሾሙ አበው ሁሌም የብቃት መዓርግ ላይ የደረሱ ሲሆኑ ክብራቸው ከፓትርያርክ በላይ ነው:: አባ ዳንኤልም ከብዙ የቅድስና ዓመታት በኋላ በአስቄጥስ ገዳም አበ ምኔት ሆኖ ተሹሞ እልፍ አእላፍ መነኮሳትን በጽድቅ መንገድ መርቷል::

ቅዱሱ ከትጋቱ የተነሳ ለምግብና ለእንቅልፍ ጊዜ አልነበረውም:: ቀን ቀን መነኮሳቱን ሲናዝዝ : ድውያንን ሲፈውስ : ሥርዓተ ገዳምን ሲቆጣጠር ይውላል:: ልክ ሲመሽ ጭው ወዳለውና ስውራን ወደ ሚገኙበት በርሃ ይወጣል::

በዚያም ሙሉውን ሌሊት የተሰወሩ አባቶችን ሲፈልግ ያድር ነበር:: በዚህም ምክንያት የብዙ ስውራንን ገድል የጻፈ ሲሆን ባረፉ ጊዜም ገንዞ በመቅበር በረከታቸውን ተሳትፏል:: ታላቅ ሙያንም ፈጽሟል::

እርሱ ገንዞ ቀብሮ : ዜናቸውን ከጻፈላቸው ሥውራን ቅዱሳንም እንደ አብነት እሥራኤላዊቷን ቅድስት ዓመተ ክርስቶስን [ለ፴፰ [38] ዓመት ራቁቷን በሥውር የኖረች] እና ቅድስት በጥሪቃ ንግሥትን [መንግስቷን ትታ በሥውር የኖረች ናት] መጥቀስ እንችላለን::

ከዚህ ባለፈም አባ ዳንኤል በሰው ዘንድ የተናቁትንም ማክበርን ያውቅበታል:: ለምሳሌ በሴቶች ገዳም እብድ ናት ተብላ በበር የተጣለችውን ቅድስት አናሲማን : በእስክንድርያ ከተማ ሊቀ ዻዻሳቱ ሳይቀር "እብድ ነው" ብለው የናቁትን ቅዱስ ምሕርካን: እብድ ሳይሆኑ ራሳቸውን የሠወሩ ቅዱሳን መሆናቸውን ገልጧል::

አባ ዳንኤል ሐዋርያዊም ነበር:: በጊዜው ጦማረ ልዮን የሚባል የኑፋቄ ደብዳቤ ይላክ ነበርና ለዚህ ኬልቄዶናዊ ኑፋቄ በትጋት ምላሽ ይሰጥ ነበር:: አንድ ቀንም በንጉሥ ትዕዛዝ ኑፋቄው በእርሱ ገዳም ሊነበብ ሲል ቅዱሱ ከወታደሩ ቀምቶ ስለ ቀደደው ለሞት እስኪደርስ ደብድበውታል::

ጻድቁ አባ ዳንኤል አንዴ አውሎጊስ የሚባልድሃ ድንጋይ ጠርቦ እንግዳ ሲቀበል ተመልክቶ "ጌታ ሆይ! ይህንን ደግ ሰው ለምን ድሃ አደረከው?" ሲል በፈጣሪ ሥራ ገባ::

ጌታም እንደ ወትሮው በገሃድ ተገልጦ "በነፍስህ ትዋሰዋለህ?" አለው:: "አዎ ጌታየ" ስላለው ጌታችን ለአውሎጊስ ሃብትን ሰጠው:: ግን ወዲያው የጦር አለቃና ጨካኝ ሰው ሆነ::

ጻድቁ ወሬውን ሰምቶ ሊጠይቅ ቢሔድ የአውሎጊስ ወታደሮች ደበደቡት:: ጌታችንም አባ ዳንኤልን ወደ ፍርድ ዙፋኑ አቅርቦ "ወዳጄን መልስልኝ" አለው:: እመ ብርሃን ግን ቀርባ የልጇን እግር ሳመች::

"ልጄ ሆይ ማር!" አለችው:: ጌታም "እሺ" ብሎ ጻድቁን ወደ በአቱ: አውሎጊስን ወደ ቀደመ ግብሩ መለሳቸው:: የአባ ዳንኤል ድንቁ ብዙ ነው::

ሌላው ቢቀር ሽፍታ አባ ዳንኤልን መስሎ ወደ ደናግል ገዳም ሊዘርፍ : በማታለል ገባ:: ደናግሉም ጻድቁ መስሏቸው እግሩን አጥበው ዐይነ ስውሯን ቢቀቧት ዐይኗ በርቷል:: ሽፍታውም ደንግጦ ንስሃ ገብቷል:: አባ ዳንኤል ግን ተጋድሎውን ፈጽሞ በዚህች ቀን ዐርፏል::

† በተረፈው ግን ከቅድስና ሕይወቱ ባሻገር :-

፩. በገዳመ አስቄጥስ [ግብጽ] አበ ምኔት ሆኖ ተሹሞ ባሳየው ትጋት::
፪. በሃይማኖት ጠበቃነቱ በደረሰበት ድብደባና ስደት::
፫. ብዙ የበርሃ ቅዱሳንን በየበአታቸው እየዞረ በመቅበሩ::
፬. የብዙ ስውራን ቅዱሳንን ዜና ሕይወት በመሰብሰቡ::
፭. በየጊዜው በእግዚአብሔር ኃይል ይፈጽማቸው በነበሩ ተአምራት:: እና
፮. ለድንግል እመቤታችን ማርያም በነበረው ልዩ ፍቅር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታከብረዋለች::

† ቸር አምላክ ክርስቶስ ከዕርገቱና ከጻድቁ በረከት አይለየን::

🕊

[  † ግንቦት ፰ [ 8 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱሳን የጌታ ቤተሰብ [፻፳ (120) ው]
፪. ቅዱስ አባ ዳንኤል ጻድቅ
፫. ቅዱስ ዮሐንስ ሰማዕት
፬. ቅዱስ መክሲሞስ መስተጋድል
፭. አቡነ ዮሐኒ ዘደብረ ዳሞ [አቡነ ተክለ ሃይማኖትንና አቡነ ኢየሱስ ሞዐን ለምንኩስና ያበቁ]

[    † ወርሐዊ በዓላት    ]

፩. ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
፪. ኪሩቤል [ አርባዕቱ እንስሳ ]
፫. አባ ብሶይ [ ቢሾይ ]
፬. አቡነ ኪሮስ
፭. አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን
፮. ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ [ከ፲፪ [12] ቱ ሐዋርያት]

" እስከ ቢታንያም አወጣቸው:: እጆቹንም አንስቶ ባረካቸው:: ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ:: ወደ ሰማይም ዐረገ:: እነርሱም ሰገዱለትና በብዙ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ:: ዘወትርም እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እየባረኩ በመቅደስ ኖሩ:: " † [ሉቃ.፳፬፥፶-፶፫] [24:50-53]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
🕊

[ † እንኳን ለእናታችን ቅድስት እሌኒ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †


🕊  †   እሌኒ ንግሥት   †   🕊

† ቅድስት እሌኒ የታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ እናቱና እግዚአብሔር ለበጐ አገልግሎት የጠራት ቡርክት ሴት [ንግሥት] ናት::

ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ :-

የቅድስቲቱ ሃገረ ሙላዷ ሮሃ [ሶርያ] አካባቢ ነው:: ነገዷ ከእሥራኤል ዝርዋን እንደሆነም ይነገራል:: ጣልያኖች "Helena" : በእንግሊዝኛው "Helen" ይሏታል:: እኛ ደግሞ "እሌኒ" እንላታለን:: ትርጓሜው "ጥሩ ምንጭ" : አንድም "ውብና ደግ ሴት" ማለት ነው::

ቅድስት እሌኒ በመልካም ክርስትና አድጋ እንደ ቤተ ክርስቲያን መተርጉማን ተርቢኖስ የሚባል ነጋዴ አግብታ ነበር:: ወቅቱም ዘመነ ሰማዕታት ነበር:: በማይሆን ነገር ጠርጥሮ ባሕር ላይ ጥሏት ንጉሥ ቁንስጣ አግኝቷታል:: እርሱም የበራንጥያ [የኋላዋ ቁስጥንጥንያ] ንጉሥ ነበር::

ቅድስት እሌኒ ከቁንስጣ የተባረከ ልጅን ወለደች:: ቆስጠንጢኖስ አለችው:: በልቡናው ፍቅርን : ርሕራሄን : መልካምነትን እየዘራች አሳደገችው:: ቅዱሱ አባቱ በሞተ ጊዜ ተተክቶ ነገሠ::

ቅድስት እሌኒንም ንግሥት አደረጋት:: ያንን የአርባ ዓመት ግፍ በአዋጅ አስቀርቶ ለክርስቲያኖች ነፃነትን : ክብርን በይፋ ሰጠ:: አንድ : ሁለት ብለን የማንቆጥረውን ውለታ ለምዕመናን ዋለ:: ከነዚህ መልካም ምግባራቱ ጀርባ ታዲያ ቅድስት እናቱ ነበረች::

ቅድስት እሌኒ ጾምን : ጸሎትን ከማዘውተሯ ባሻገር አጽመ ሰማዕታትን ትሰበስብ : አብያተ ክርስቲያንን ታሳንጽ : ለነዳያንም ትራራ ነበር:: በኢየሩሳሌምና አካባቢው ብቻ ከሰማንያ በላይ አብያተ መቃድስ አሳንጻለች:: እነዚህንም በወርቅና በእንቁ ለብጣቸዋለች::

በዘመኗ መጨረሻም የጌታችንን ቅዱስ ዕፀ መስቀል ከተቀበረበት አውጥታ ለዓለም በረከትን አስገኝታለች::

እናታችን ቅድስት እሌኒ እንዲህ በቅድስና ተመላልሳ በሰማንያ ዓመቷ በ፫፻፴ [330] ዎቹ አካባቢ ዐርፋለች:: ቤተ ክርስቲያናችንም ስለ ቅድስናዋና ውለታዋ በዓል ሠርታ : ታቦት ቀርፃ ስታከብራት ትኖራለች::

† ከቅድስት እናታችን ምልጃና በረከት አምላካችን ያድለን::

🕊

[ †  ግንቦት ፱ [ 9 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅድስት እሌኒ ንግሥት
፪. ቅዱስ ስልዋኖስ

[ † ወርኀዊ በዓላት ]

፩. አባ በርሱማ ሶርያዊ [ለሶርያ መነኮሳት ሁሉ አባት]
፪. አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ [ኢትዮጵያዊ]
፫. ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ቅዱሳን ሊቃውንት [ርቱዐነ ሃይማኖት ዘኒቅያ]
፬. የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን
፭. አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ [ኢትዮጵያዊ]
፮. ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ [ዓለመ ብፁዐንን ያየ አባት]

" ነገር ግን ለበጐ ነገር ጥበበኞች : ለክፉትም የዋሆች እንድትሆኑ እወዳለሁ:: የሰላምም አምላክ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ፈጥኖ ይቀጠቅጠዋል:: የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን:: " † [ሮሜ. ፲፮፥፲፱]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
#ቅዱስ_ያዕቆብ ዘሥሩግ እንዲህ አለ:-

#በቅድስና_ውበት ስለተሞላችው ንጽሕት ትሕት እናገር ዘንድ አንደበቴ ብቁ አይደለም፡፡ ... የተራ ቀለማት
መዋሐድ ለማይመጥኗት ለዚህች እጅግ ክብርት እንዴት ያለ ሥዕልን ልሣል? ውበትዋ ከእኔ መጠበብ በላይ ነው ፤ አእምሮዬም እንዲሥላት አልፈቅድለትም፡፡

#የድንግል_ማርያምን ክብርዋን ከመግለጥ ፀሐይን ከነብርሃንዋና ከነሙቀትዋ መሣል ይቀልላል፡፡ ምናልባት የፀሐይ ጨረር በሥዕል ሊቀመጥ ይችል ይሆናል፡፡ ስለ እርስዋ የሚነገረውን ነገር ግን አሟልቶ ለመስበክ አይቻልም፡፡

እርስዋን ከነማን ጋር መመደብ ይቻላል? ከደናግል ጋር? ከቅዱሳን ጋር? ከንጹሐን ጋር? ካገቡ ሴቶች ጋር? ከእናቶች ጋር? ከአገልጋዮች ጋር? እነሆ የድንግልናን ማኅተም ከወተት ጋር የያዘ ሰውነትዋን እዩ! መውለድዋንም ከታተመ ማኅፀንዋ ጋር እዩ! ከደናግል መካከል ናት ስል ሕፃን ይዛ ስታጠባ አያታለሁ! ከዮሴፍ ጋር ትኖራለች ስል በጋብቻ ቃልኪዳን እንዳልታሠረች አያለሁ!

#ስለ_እርስዋ እንድናገር ፍቅር ያስገድደኛል ፤
የክብርዋ ከፍታ ግን ያስቸግረኛል፡፡ ከቶ ምን ባደርግ
ይሻለኛል? ስለ እርስዋ ለመናገር ብቁ እንዳልሆንሁ
በግልፅ እናገራለሁ፡፡ ከፍቅር የተነሣ ግን ተመልሼ
መናገር ያምረኛል፡፡...

ሱራፌል ከእሳቱ የሚሸሸጉለትን የእርሱን ከንፈሮች በቡሩካን ከነፈሮችዋ የሳመች እርስዋ የተባረከች ናት! ዓለማት ሕይወትን የጠጡበትን ምንጭ እርሱን ያጠባች እርስዋ የተባረከች ነች’

(የብርሃን እናት ገፅ 352)


             #_ሰናይ__ቀን🙏

ለመቀላቀል 👇👇👇👇
@Enatachn_mareyam  
@Enatachn_mareyam
🕊

[ † እንኳን ለቅዱሳን ሠለስቱ ደቂቅ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †


🕊  † ቅዱሳን ሠለስቱ ደቂቅ  †  🕊

† አናንያ : አዛርያና ሚሳኤልን እንዲያው በቀድሞው አጠራር ሠለስቱ ደቂቅ [ሦስቱ ሕጻናት] እንላቸዋለን እንጂ ለእኛስ በእድሜም : በጸጋም : በትሩፋትም አባቶቻችን ናቸው::

ቅዱሳኑ የወቅቱ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአቄም ልጆች ናቸው:: ናቡከደነጾር ኢየሩሳሌምን አቃጥሎ ሕዝቡን ሲማርክ አብረው ተማርከው ባቢሎን ወርደዋል::

ንጉሡ ከምርኮ ወጣቶች ለቤተ መንግስት ሲመርጥ ሦስቱ ቅዱሳንና ዳንኤል ተመርጠው የምቾት ሕይወት ተዘጋጅቶላቸው ነበር:: ነገር ግን በምግብና በአምልኮ ከአሕዛብ ጋር መተባበርን አልፈለጉምና ምርጫቸው ጾምና ጸሎት ከቆሎ ጋር ሆነ:: ምንም እንኳ በቤተ መንግስት ውስጥ ቢኖሩ : ምንም የነገሥታት ልጆች ቢሆኑ ለእነርሱ ከእግዚአብሔር ፍቅር የተሻለ አልነበረምና በጥሬ ቆሎ ተወስነው ኖሩ::

አምላካቸው ከሃሊ ነውና በውበትም ሆነ በጥበብ በባቢሎን ምድር ከነርሱ የሚደርስ አልተገኘም:: ንጉሡም በባቢሎንና በአውራጃዋ ላይ ሾማቸው:: ስማቸውንም በአማልክቱ ስም ሲድራቅ : ሚሳቅና አብደናጐ አላቸው::

ከነገር ሁሉ በኋላ አሕዛብ ቀንተውባቸዋልና የክፋት አዋጅን አሳወጁ:: ናቡከደነጾር ፷ [60] ክንድ ቁመት ያለውን የወርቅ ምስል አቁሞ "ስገዱ" ቢላቸው አይሆንም በማለታቸው ተቃጥለው እንዲሞቱ እሳት ተፈረደባቸው:: ነበልባሉ ከጉድጓዱ ወደ ላይ ፵፱ [49] ክንድ ቢነድም ቅንጣት ያህል ፍርሃት አልጎበኛቸውም::

ወደ እሳቱም ሲጥሏቸው መልዐከ አድኅኖ ቅዱስ ገብርኤል ደርሶ አዳናቸው:: ከሆነው ነገር የተነሳ አሕዛብ አፈሩ:: ናቡከደነጾር ግን ከዙፋኑ ተነስቶ የቅዱሳኑን አምላክ እግዚአብሔርን ባረከ::

ከዚያች ቀን በኋላ አናንያ : አዛርያና ሚሳኤል በአት አጽንተው : በጾምና በጸሎት ተወስነው ኑረዋል:: ነፍሳቸው ከሥጋቸው ስትለይ ታላቅ ንውጽውጽታ ሆኗል:: ቅዱስ ዳንኤልና ናቡከደነጾር ተሯሩጠው ቢሄዱ ሦስቱም በአንድነት ዐርፈው ተገኝተዋል:: ንጉሡ በእጅጉ ይወዳቸው ነበርና በወርቅ በተለበጠ ሳጥን ቀብሯቸዋል:: ስሞት ከመካከላቸው ቅበሩኝ በማለቱ ዛሬ ድረስ ለበቁ አባቶች የአራቱ መቃብር ባቢሎን ውስጥ ይታያል::

ቅዱሳን አናንያ : አዛርያና ሚሳኤል [ሲድራቅ : ሚሳቅና አብደናጐ] ያረፉት ግንቦት ፲ [10] ቀን ሲሆን ዘመኑም ከክርስቶስ ፭፻ [500] ዓመት በፊት ነው::

† አምላካቸው ከእሳት ባወጣቸው ቀንም :-
"ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ::
ስቡሕኒ ውዕቱ ወልዑልኒ ውዕቱ ለዓለም::" የሚለውን ምስጋና ፈጣሪ ገልጾላቸው ደርሰውታል:: [በእሳቱ ውስጥ ሆነው ተናግረውታል::]

ድርሰታቸው ፪ [2] ወገን ሲሆን ባለ ስድስት አንቀጹ ምስጋናቸው ከ፮፻ [600] ዓመት በኋላ ክርስቶስ እንደሚወለድ የሚያሳይ ነው:: ሌላኛውና ፴፫ [33] አንቀጾች ያሉት ምስጋናቸው ደግሞ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም ለ፴፫ [33] ዓመታት እንደሚመላለስ ያጠይቃል::

ቅዱሳን ሠለስቱ ደቂቅ ካረፉ ከ፱፻ [900] ዓመታት በኋላ [ማለትም ከክርስቶስ ልደት በ፬፻ [400] ዓመታት] ታላቁ ቅዱስ ቴዎፍሎስ ቤተ ክርስቲያንን አንጾላቸው ነበርና አጽማቸውን ሊያገኝ ተመኘ::

ወዳጁን ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ጠርቶ "አባ! አጽመ ቅዱሳንን ባቢሎን ወርደህ አምጣልኝ?" አለው:: ቅዱሱ ሐጺር ዮሐንስም በደመና ተጭኖ ባቢሎን ገባ:: በቅዱሳኑ መቃብር ፊትም ሰግዶ አለቀሰ:: ሠለስቱ ደቂቅም "ወዳጃችን! ምን ሆንክ?" አሉት::

ቅዱሱም መልሶ "ወደ ግብጽ እንሒድ:: አባ ቴዎፍሎስ ይፈልጋቹሃል" አላቸው:: እነሱም "ለቅዱሱ ቴዎፍሎስ እንዲህ በለው:: እግዚአብሔር ዋጋህን ይክፈልህ:: ግን አጽማችን እስከ ዓለም ፍጻሜ ባቢሎንን አይለቅም:: ለክብርህ ግን እንመጣለን::"

"ለምልክትም ይሆን ዘንድ መብራት ሳታበራ በሌሊት ጠብቀን በለው" ብለው ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ባርከው ሸኙት:: ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርም መጥቶ መልእክቱን አደረሰ:: በዕለተ ቅዳሴ ቤታቸው ቅዱሳን:- ቴዎፍሎስ : ቄርሎስ : ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርና ሌሎችም ከምዕመናን ጋር በጨለማ ሳሉ ቤተ ክርስቲያኑ ቦግ ብሎ በራ::

እጅግ የሚደነቅ ብርሃንም ከበባቸው:: በብርሃኑ መካከል ሠለስቱ ደቂቅ ሲያልፉ በጐ መዓዛ ሸተተ:: ሕዝቡም በደስታና በዝማሬ የቅዱሳኑን ቅዳሴ ቤት አክብሯል::

† በረከታቸው ይደርብን::

🕊

[ † ግንቦት ፲ [ 10 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ሠለስቱ ደቂቅ ቅዱሳን [አናንያ : አዛርያና ሚሳኤል]
፪. ቅዱስ አብርሃም ጸራቢ [ሰማዕት]
፫. አባ ሚካኤል ገዳማዊ
፬. አባ ይስሐቅ ግብጻዊ

[ †  ወርሐዊ በዓላት ]

፩. ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ
፪. ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሃገረ ሜራ
፫. ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ጻድቅ ንጉሥ
፬. አቡነ መልክዐ ክርስቶስ
፭. ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ [ወልደ እልፍዮስ]
፮. ቅድስት ዕሌኒ ንግስት
፯. ቅዱስ ዕፀ መስቀል

† " ናቡከደነፆርም መልሶ:- መልአኩን የላከ : ከአምላካቸውም በቀር ማንንም አምላክ እንዳያመልኩ ለእርሱም እንዳይሰግዱ ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡትን : የንጉሡንም ቃል የተላለፉትን : በእርሱ የታመኑትን ባርያዎቹን ያዳነ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብደናጎም አምላክ ይባረክ:: " † [ዳን.፫፥፳፰] (3:28)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
#እንካ_ሰላምታ_

🙎‍♂ እንካ ሰላምታ፦
👉👨‍🔧ምን አይነት ሰላምታ?
🙎‍♂
#በፀሎት
👉👨‍🔧 ምን አለ በፀሎት?
🙎‍♂ምህረቱ በበዛ በእግዚአብሔር ቸርነት፣
ከሳጥናኤል ቀንበር ወጣን ከባርነት።

👨‍🔧አንካ ሰላታ
👉🙎‍♂ ምን አይነት ሰላምታ?
👨‍🔧
#በጦፍ
👉🙎‍♂ምን አለ በጦበጦፍ?
👨‍🔧 ንጹህ ደም ለማፍሰስ ጠላቴ ሲሰለፍ፣
ለራሱ ታዘዘ ለእኛ የመጣው ሰይፍ

🙎‍♂እንካ ሰላታ፦
👨‍🔧ምን አይነት ሰላምታ?
🙎‍♂
#በከበሮ
👨‍🔧ምን አለ በከበሮ?
🙎‍♂ ጥበበኛው ሰይጣን በጥበብ ተሽሮ፣
ሲኦል ስትማረክ ተመልሷል አፍሮ።

👨‍🔧እንካ ሰላምታ፦
🙎‍♂ምን አይነት ሰላምታ?
👨‍🔧
#በወይን
🙎‍♂ምን አለ በወይን?
👨‍🔧በቀራኒዮ መስቀል የፈሰሰለትን፣
የሰው ልጅ ካልበላ ስጋውን እና ደሙን፣
ያን! ሰማያዊ ቤት አይወርስም ርስቱን።

🙎‍♂ እንካ ሰላምታ፦
👨‍🔧ምን አይነት ሰላምታ?
🙎‍♂
#በስግደት
👨‍🔧ምን አለ በስግደት?
🙎‍♂ጉንብስ ቀና ስንል በመንፈስ በእምነት፣
እንደ ሰም ቀለጠ የሳጥናኤል ጉልበት።

👨‍🔧እንካ ሰላምታ፦
🙎‍♂ ምን አይነት ሰላምታ?
👨‍🔧
#በበገና
🙎‍♂ምን አለ በበገና?
👨‍🔧ለናዝሬቱ ኢየሱስ እናቅርብ ምስጋና፣
ከባርነት ቀንበር አውጥቶናልና።

እንኩ ሰላምታ
በምንታ
#በሰማይ_በምድር
ምን አለ በሰማይ በምድር
ከአለም ትሰፋለች የአምላክ እናት
#ድንግል_ማርያም

             #_ሰናይ__ቀን🙏

ለመቀላቀል 👇👇👇👇
@Enatachn_mareyam  
@Enatachn_mareyam
2024/05/18 13:38:56
Back to Top
HTML Embed Code: