Telegram Web Link
🕊

†  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ
አምላክ፡፡ አሜን፡፡  †

[  † ግንቦት ፳፪ [ 22 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  †   ]


🕊   †  ቅዱስ እንድራኒቆስ   †  🕊

ቅዱስ ወብጹእ እንድራኒቆስ ሐዋርያ ትውልዱ ነገዱ ከቤተ እሥራኤል ሲሆን ከ፸፪ [72] ቱ አርድእት አንዱ ነው:: ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱ ፻፳ [120] ቤተሰቦቹን ሲመርጥ እርሱን ከአርድእት ጋር ደምሮ አስተምሮታል::

ሰብዐው አርድእት በጌታችን ተልከው አጋንንት ሲገዙላቸው ከእነርሱ አንዱ ቅዱስ እንድራኒቆስ ነበር:: ይሕ የተፈጸመ ገና መድኃኔ ዓለም ከመሰቀሉ በፊት ነው:: [ሉቃ.፲፥፩-፳] (10:1-20)

ቅዱሱ ከጌታችን ዕርገት በኋላ ከሐዋርያት ጋር ለ፲ [10] ቀናት በሱባኤ ሰንብቶ የመንፈስ ቅዱስን ሐብት ተቀብሏል:: እንደ ባልንጀሮቹም ወደ ዓለም ወጥቶ የወንጌል የምሥራችን ሰብኳል:: በተለይ ከቅዱስ ዻውሎስ ጋር ለበርካታ ዓመታት አምላኩን አገልግሏል:: ቅዱስ ዻውሎስም በቆረንቶስ እያለ ቅዱስ እንድራኒቆስ በሮም ያስተምር ነበር:: ለዛም ነው በሮሜ መልዕክቱ ፲፮፥፯ [16:7] ላይ "እንድራኒቆስን ሰላም በሉ" ያለው::

ቅዱስ ዻውሎስ በሰማዕትነት ካረፈ በኋላ ከቅዱስ ዮልዮስ ጋር ሆነው የአህዛብን ልቡና በወንጌል አብርተዋል:: እጅግ ብዙ መከራ ደርሶባቸዋል:: ከእግዚአብሔር በተሰጣቸው ትዕግስት ድል ነሥተዋል:: በዚሕም በርካታ የጣኦት ቤቶችን አፍርሰው አብያተ ክርስታያናትን አንጸዋል:: በአሕዛብም ፊት ድንቅ ድንቅ ተአምራትን አሳይተዋል::

ቅዱስ እንድራኒቆስ ብዙ መከራን ቢቀበልም አንገቱን ይቆረጥ ዘንድ የጌታ ፈቃዱ አልነበረምና ጥቂት ታሞ በዚሕች ቀን አርፏል:: ባልንጀራው [ሐዋርያው] ቅዱስ ዮልዮስ በክብር ገንዞ ቀብሮታል::

  †   🕊   ቅዱስ ያዕቆብ    🕊   †  

ዳግመኛ በዚሕ ቀን ጻድቅና ተአማኒ [ታማኝ] የተባለ የምሥራቅ ሰው ቅዱስ ያዕቆብ መታሠቢያ ይደረግለታል::

ቅዱስ ያዕቆብ ቁስጥንጥንያ አካባቢ በርሃ ውስጥ ይኖር የነበረ አባት ነው:: ከቅድሰና ሕይወቱ ባሻገር በደፋርነቱ [ ጥብዐቱ ] ይታወቃል:: በ፫፻፵ [ 340 ] ዎቹ ዓ/ም ታናሹ ቆስጠንጢኖስ አርዮሳዊ በሆነ ጊዜ ይሔ አባት በይፋ ገስጾታል:: በዚህም ምክንያት መከራ ተቀብሏል: ታስሯል: ተገርፏል:: እግዚአብሔርም መናፍቁን ንጉሥ ለጦርነት በወጣበት ቀስፎታል::

የአባቶቻችን አምላክ ልዑለ ባሕርይ ክርስቶስ ጸጋ ክብራቸውን ያድለን::

[  †  ግንቦት ፳፪  [ 22 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት   ]

፩. ቅዱስ እንድራኒቆስ ሐዋርያ [ከ፸፪ [72] ቱ አርድእት]
፪. ቅዱስ ያዕቆብ ምሥራቃዊ [ለክርስቶስ የታመነ]

[   †  ወርኃዊ በዓላት    ]

፩፡ ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት
፪፡ ቅዱስ ደቅስዮስ
፫፡ ቅዱስ ዮልዮስ ሰማዕት
፬፡ ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ
፭፡ አባ እንጦንስ አበ መነኮሳት
፮፡ አባ ጳውሊ የዋህ

" ስለ እናንተ ብዙ ለደከመች ለማርያ ሰላምታ አቅርቡልኝ:: በሐዋርያት መካከል ስመ ጥሩዎች ለሆኑ: ደግሞም ክርስቶስን በማመን ለቀደሙኝ: አብረውኝም ለታሰሩ ለዘመዶቼ ለአንድራኒቆንና ለዮልያን [እንድራኒቆስና ዮልዮስ] ሰላምታ አቅርቡልኝ:: " + [ሮሜ.፲፮፥፮] (16:6)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
🕊

[ † እንኩዋን ለቅዱሳን ሐዋርያት ዮልዮስና አፍሮዲጡ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ † ]


🕊 † ዮልዮስ ወአፍሮዲጡ ሐዋርያት †  🕊

ቅዱሳን ሐዋርያትና አርድእት በቁጥር ፹፬ [84] ቢሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ታሪኩ በዝርዝር የተጻፈለት ቅዱስ ዻውሎስ ነው:: የሌሎቹ አልፎ አልፎ የተጠቀሰ ሲሆን ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ግን የት እንደ ደረሱም አልተጻፈም::

በዚሕ ምክንያት ወደድንም ጠላንም አዋልድ መጻሕፍትን መጠቀማችን አይቀርም:: ምክንያቱም "ሑሩ ወመሐሩ" ያላቸው ሁሉንም ሐዋርያትና አርድእት ነውና::

የቅዱሳን ሐዋርያትን ሕይወት ከያዙ ቅዱሳት መጻሕፍት መካከል በቀዳሚነት ዜና ሐዋርያትና ገድለ ሐዋርያት የሚጠቀሱ ሲሆን ስንክሳራችንም አልፎ አልፎ ያወሳቸዋል:: በዚሕም መሠረት ዛሬ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከ72ቱ አርድእት የሚቆጠሩትን ቅዱስ ዮልዮስንና ቅዱስ አፍሮዲጡን ታከብራለች::

ሁለቱም ከጌታችን እግር ሥር ለ፫ [3] ዓመታት ተምረው: በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው: ከባልንጀሮቻቸው ሐዋርያት ጋር ለወንጌል አገልግሎት ሃገራትን ዙረዋል:: በሐዋርያት ሲኖዶስም ዽዽስናን ተሹመዋል::

በአገልግሎት በነበሩባቸው የእስያና አውሮዻ ሃገራት አእላፍ ነፍሳትን ወደ ሕይወት ሲማርኩ ግፍን በአኮቴት ተቀብለዋል:: ከጌታቸውም የማይጠፋ የሕይወት አክሊልን ተቀዳጅተዋል::

በተለይ ቅዱስ ዮልዮስ ከቅዱስ ዻውሎስ ጋር መከራን በመቀበሉ በሮሜ መልዕክቱ ፲፮፥፯ [16:7] ላይ አወድሶታል:: ከቅዱስ እንድራኒቆስ ጋርም በጣም ይዋደዱ ነበርና ትናንት እርሱን ገንዞ ቀብሮ በእንባ ወደ ጌታው ፀለየ:: ጌታችንም በማግስቱ [ማለትም ዛሬ] አሳርፎታል::

አምላከ ቅዱሳን ከሐዋርያቱ ትጋትና በረከት ያድለን::

🕊

[ † ግንቦት ፳፫ [ 23 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ ዮልዮስ [ዮልያን] ሐዋርያ [ከ፸፪ [72] ቱ አርድእት]
፪. ቅዱስ አፍሮዲጡ ሐዋርያ [ከ፸፪ [72] ቱ አርድእት]
፫. ቅዱሱ ሕጻን ሰማዕት [በዘመነ ሰማዕታት ገና የ፪ [2] ወር ሕጻን ቢሆንም ጌታችን አፉን ከፍቶለት ክርስቲያን ነኝ በማለቱ ከእናቱ ጋር ተሠይፏል]
፬. አባ አንስያ ሰማዕት
፭. ቅዱስ ታኦድራጦስ

[ †  ወርኀዊ በዓላት ]

፩. ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት
፪. ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
፫. ቅዱስ ሰሎሞን ንጉሠ እስራኤል
፬. አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
፭. አባ ሳሙኤል
፮. አባ ስምዖን
፯. አባ ገብርኤል

" ስለ እናንተ ብዙ ለደከመች ለማርያ ሰላምታ አቅርቡልኝ:: በሐዋርያት መካከል ስመ ጥሩዎች ለሆኑ: ደግሞም ክርስቶስን በማመን ለቀደሙኝ: አብረውኝም ለታሰሩ ለዘመዶቼ ለአንድራኒቆንና ለዮልያን [እንድራኒቆስና ዮልዮስ] ሰላምታ አቅርቡልኝ:: " [ ሮሜ.፲፮፥፮ ] (16:6)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
🕊

[ † እንኩዋን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ የስደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ † ]

የአርያም ንግሥት: የፍጥረታት ሁሉ እመቤት ድንግል ማርያም የባሕርይ አምላክ ልጇን አዝላ በዚህች ቀን ወደ ምድረ ግብፅ ወርዳለች::

በወንጌል ላይ [ማቴ.፪፥፩-፲፰] (2:1-18) እንደተጻፈው ጌታችን በተወለደ በ፪ [2] ዓመቱ የጥበብ ሰዎች [ሰብአ ሰገል] ወደ ቤተ ልሔም መጥተው ሰግደውለት: ወርቅ እጣን ከርቤውን ገበሩ: አገቡለት::

ንጉሥ ተወልዷል መባሉን የሰማ ሔሮድስ መቶ አርባ አራት ሺህ 144,000 ሕጻናትን ሲፈጅ በቅዱስ ገብርኤል ትዕዛዝ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፩ [1] አምላክ ልጇን አዝላ: በአንዲት አህያ ጥቂት ስንቅ ቁዋጥራ: ከዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር ስደት ወጣች::

ከገሊላ ተነስታ በጭንቅ በመከራ: በረሃብና በጥም: በሐዘንና በድካም: በላበትና በእንባ ተጉዛ በዚሕች ቀን ምድረ ግብፅ ገብታለች::

- የአምላክ እናቱ

- እሳትን አዝላ በብርድ ተንገላታለች::
- ለእኛ የሕይወት እንጀራን ተሸክማ እርሷ ተራበች::
- የሕይወትን ውሃ ተሸክማ ተጠማች::
- የሕይወት ልብስን ተሸክማ ተራቆተች::
- የሕይወት ፍስሐን ተሸክማ አዘነች::
- እመ አምላክ ተራበች: ተጠማች: ታረዘች: ደከመች: አዘነች: አለቀሰች: እግሯ ደማ: ተንገላታች::

ለሚገባው ይሕ ሁሉ የተደረገው ለእኛ ድኅነት ነው:: በእውነት ይህንን እያወቀ ለድንግል ማርያም ክብር የማይሰጥ ሰይጣን ብቻ ነው:: አራዊት: ዕፀዋትና ድንጋዮች እንኩዋ ለአመላክ እናት ክብር ይሰጣሉ::

አረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍና ቅዱስ ሰሎሜ ደግሞ የክብር ክብር ይገባቸዋል:: ከአምላክ እናት ከድንግል ማርያምና ከቸር ልጇ ጋር መከራ መቀበልን መርጠዋልና::

መድኃኔ ዓለም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ተሰደደ? ለምንስ ስደቱን ወደ ግብፅና ኢትዮዽያ አደረገ?

፩. ትንቢቱን ይፈጽም ዘንድ:: በፈጣን ደመና ወደ ግብፅ እንደሚወርድ ተነግሯልና [ኢሳ.፲፱፥፩ 19:1, ዕን.፫፥፯ 3:7]

፪. ምሳሌውን ለመፈጸም:: የሥጋ አባቶቹ እነ አብርሃም: ያዕቆብ [እሥራኤል]: ኤርምያስ ወደዚያው ተሰደዋልና::

፫. ከግብፅ ጣዖት አምልኮን ያጠፋ ዘንድ:: [ኢሳ.፲፱፥፩] (19:1)

፬. የግብፅና የኢትዮዽያ ገዳማትን ይቀድስ ዘንድ::

፭. ሰው መሆኑ በአማን እንጂ ምትሐት እንዳልሆነ ለማጠየቅ:: ሰው ባይሆን ኑሮ አይሰደድም ነበርና:: ሔሮድስ ቢያገኘው ደግሞ ሊገድለው አይችልም:: ያለ ፈቃዱና ያለ ዕለተ ዐርብ ደሙ አይፈስምና::

፮. ስደትን ለሰማዕታት ባርኮ ለመስጠት:: እና

፯. የአዳምን ስደት በስደቱ ለመካስ ነው::

ቸሩ መድኃኔ ዓለም የድንግል እናቱን ስደት አስቦ ከመንግስተ ሰማያት ስደት ይሠውረን:: ከስደቱ በረከትም ያድለን::

🕊

[ † ግንቦት ፳፬  [ 24 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ ዕንባቆም ነቢይ
፪. ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊና ቅድስት ሰሎሜ
፫. ቅዱስ አብቁልታ ሰማዕት
፬. ቅዱስ አልዓዛር ካህን [የአሮን ልጅ]

[ † ወርኀዊ በዓላት ]

፩. ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
፪. ቅዱስ አጋቢጦስ [ጻድቅ ኤዺስቆዾስ]
፫. ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
፬. ቅዱስ ሙሴ ፀሊም
፭. ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
፮. ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
፯. "፳፬ 24ቱ" ካኅናተ ሰማይ [ሱራፌል]
፰. አቡነ ዘዮሐንስ ጻድቅ [ኢትዮዽያዊ]

" ዘንዶውም ሴቲቱ በወለደች ጊዜ ሕጻኑዋን እንዲበላ ልትወልድ ባላት ሴት ፊት ቆመ:: አሕዛብንም ሁሉ በብረት ዘንግ ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ልጅ: ወንድ ልጅ ወለደች:: ልጇም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ:: ሴቲቱም ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን በዚያ እንዲመግቧት በእግዚአብሔር ተዘጋጅቶላት ወደ ነበረው ሥፍራ ወደ በረሃ ሸሸች:: " [ራዕይ.፲፪፥፬-፯] (12:4-7)

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
🕊

[ † እንኳን ለእናታችን ቅድስት ሰሎሜ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል እና ለበዓለ ቅዱስ ሜሮን በሰላም አደረሳችሁ † ]

🕊   ቅድስት ሰሎሜ   🕊

የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ ከመረጣቸው ፴፮ [36] ቱ ቅዱሳት አንስት የቅድስት ሰሎሜን ያሕል ያገለገለ: ክብርም የተቀበለ የለም:: ከእመቤታችን ቀጥሎ ከጽንሰቱ እስከ ዕርገቱ ያልተለየች ብቸኛዋ ሰው ናትና::

ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:- ቅድስት ሰሎሜ ከነገደ አሮን በሚመዘዝ የዘር ሐረግ እናቷ ማርያም ትባል ነበር:: አባቷ ደግሞ ክቡር አረጋዊ ቅዱስ ዮሴፍ ነው:: ቅድስት ሰሎሜና እመቤታችን የእህትማማች ልጆች ናቸው::

ቅድስት ኤልሳቤጥም ዝምድናዋ ተመሳሳይ ነው:: የ ፫ [3] ቱ እናቶች [ሐና: ማርያምና ሶፍያ] የማጣትና የሔርሜላ ልጆች በመሆናቸው እህታማቾች ናቸው::

"ጥቂት ነገሮች ስለ እናታችን ቅድስት ሰሎሜ "
፩. የአረጋዊ ዮሴፍ ልጆችን [ወንድሞቿን] እንደሚገባ አሳድጋለች::

፪. ጌታችን በተወለደ ጊዜ በቤተ ልሔም ነበረች:: የእመቤታችን መውለድ እንደ ሌሎች ሴቶች መስሏት ድንግልን ስለ ነካች እጆቿ ተቃጥለዋል:: ምሕረት ጠይቃ ጌታን ስትዳስሰው ግን ተፈወሰች::

፫. እመ ብርሃን ስደት ስትወጣ ቅድስት ሰሎሜ "ባንቺ የደረሰ በኔም ይድረስ" ብላት አብራ ተሰዳለች:: ረሐቧን ተርባለች:: ጥሟን ተጠምታለች:: በሐዘኗ አዝናለች:: አብራት አልቅሳለች:: ለ፫ [3] ዓመታት ከ፮ [6] ወራት ያን ሁሉ ጭንቅ አብራ ተካፍላለች::
ድንግል እመቤታችን እሾህ ሲወጋት ታወጣላት: እንቅፋት ሲመታት ደሟን ትጠርግላት ነበር:: ባለቤቱ አድሏታልና ጌታችንን አንዴ በጎኗ ታቅፈው: አንዴም በጀርባዋ ታዝለው: አንዳንዴም ትስመው ነበር::

"መለኮትን ማቀፍ: ማዘልና መሳም ምን ይደንቅ! ለቅድስት እናታችን አንክሮና ምስጋና በጸጋ ይገባል!"

ከስደት ከተመለሱ በሁዋላም ለ፳፭ [25] ዓመታት ከጌታና ከድንግል ማርያም ጋር ኑራለች: አገልግላቸዋለችም:: ጌታችን ተጠምቆ ማስተማር ሲጀምርም ተከተለችው:: እርሱም ከ፴፮ [36] ቱ ቅዱሳት አንስት ደምሯታል:: ለ፫ [3] ዓመታት ከ፮ [6] ወራት ከዋለበት ውላ: ካደረበት አድራ ተምራለች:: እንደሚገባም አገልግላለች::

አምላክ ሲሰቃይ ከጐኑ: ሲሰቀልም ከእግረ መስቀሉ ነበረች:: ብርሃነ ትንሳኤውም ከተገለጠላቸው ቅዱሳት አንስት አንዷ ናት:: ከመድኃኔ ዓለም ዕርገት በሁዋላ መንፈስ ቅዱስን ተቀብላ በሐዋርያት ዘመን የነበረችውን ቤተ ክርስቲያን አገልግላለች::

እድሜዋ ምን ቢገፋ ለወንጌልና ለማዕድ ተግባር ተግታለች:: ወገኖቿ አይሁድ ብዙ አሰቃይተዋት በዚህች ዕለት በመልካም ዕረፍት ወደ ፈጣሪዋ ሔዳለች::

🕊   ቅብዐ ሜሮን   🕊

ዳግመኛ በዚሕ ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛ የምንከብርበትን ቅብዐ ሜሮን አፍልቆልናል::

በስደቱ ጊዜ ጌታችን በምድረ ግብፅ ደክሟቸው ካረፉበት ቦታ ላይ የዮሴፍ በትርን ቆራርጦ: በኪነ ጥበቡ ውሃ አፍልቆ: አጠጥቶ: ትልልቅ ዛፎች አደረጋቸው:: እዛውም ላይ ቅብዐ ሜሮንን አፈለቀ:: ቅብዐ በለሶንም ይሏቸዋል::
በሁዋላም የጌታችን ወዙ በታጠበ ጊዜ ተቀላቅሎበታል:: ዛሬ እኛም: ንዋየ ቅድሳትም የምንከብረው በዚሁ ቅዱስ ቅብዐት ነው::

አምላካችን እግዚአብሔር በቅድስት ሰሎሜ ላይ ያሳደረውን ጸጋ በእኛም ላይ ያሳድርልን::

🕊

[ † ግንቦት ፳፭ [ 25 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. እናታችን ቅድስት ሰሎሜ [ከ ፵፮ [36] ቱ ቅዱሳት አንስት]
፪. ታላቁ አባ ሔሮዳ ሰማዕት
፫. ፴ ሺህ "30,000" ሰማዕታት [የአባ ሔሮዳ ማሕበር]
፬. ቅዱስ አብቁልታ ሰማዕት
፭. ቅዱስ ቅብዐ ሜሮን

[ † ወርሐዊ በዓላት ]

፩. ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
፪. ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
፫. ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
፬. ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
፭. አቡነ አቢብ [አባ ቡላ]
፮. ቅዱስ አባ አቡፋና ጻድቅ

" ሰንበትም ካለፈ በሁዋላ መግደላዊት ማርያም: የያዕቆብም እናት ማርያም: ሰሎሜም መጥተው ሊቀቡት ሽቱ ገዙ:: ከሳምንቱም በፊተኛው ቀን እጅግ በማለዳ ፀሐይ ከወጣ በሁዋላ ወደ መቃብር መጡ . . . ወደ መቃብርም ገብተው ነጭ ልብስ የተጐናጸፈ ጐልማሳ በቀኝ በኩል አዩና ደነገጡ:: እርሱ ግን አትደንግጡ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ትፈልጋላችሁ:: ተነስቷል: በዚህ የለም . . . አላቸው:: " [ማር.፲፮፥፩-፰] (16:1-8)

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
2024/06/16 06:40:40
Back to Top
HTML Embed Code: