Telegram Web Link
+++ለአባ የትናንቱ+++

ያለ ማወቅ ፅልመት አገሩን ሲወርሰዉ
ማን ነበር ትዉሉዱን በወንጌል ያረሰዉ?
አባ ተክለ ሃይማኖት አባ የትናንቱ
ትዝ አለኝ ተጋድሎዉ ዉል አለኝ ሕይዎቱ
በቆላ በደጋ የተንከራተትኸዉ
የሃይማኖት ተክል ዞረህ የተከልኸዉ
የኢትዮጵያ ፀሐይ አባ ተክለ አብ
እስቲ መለስ ብዬ ገድልህን ላስብ
የክህደት ጨለማ ባንተ ሲርቅ
የሃይማኖት ብርሃን ሲያንፀባርቅ
በቀንና ሌሊት ከላይ ታች ዞረህ
ሕዝቡን አደረስከዉ አስተምረህ መክረህ

ስንት ነበር አባ የጉዞ አበልህ?
ያረፍህበት ስፍራ የተዘጋጀልህ
የት ነበር መኝታዉ ጎን ማሳረፊያህ
ንገረኝ እባክህ ማን ነበር የሸኘህ

እሳት አባቴ ሆይ እኔ አመድ ልጅህ
በዘመኔ ቋንቋ እስቲ ልጠይቅህ?

ምንጭ ደንገጡሯ እመቤት ከሚለዉ
የዲያቆን ሄኖክ መፅሃፍ
በገነት ያሉ ሦስት አስደናቂ ነገሮች

አንድ አባት ወደ ገነት ከገባ በሁዋላ ለሌላ አባት በሕልም እንዲህ ሲል ነገረው

ወደ ገነት በገባሁ ጊዜ ሦስት ነገሮች አስደነቁኝ
የመጀመሪያው ገነት ውስጥ ይገኛሉ ብዬ ፈጽሞ የማልጠብቃቸውን በእኔ ዓይን ኃጢአተኞች የሆኑ ሰዎችን በገነት ውስጥ ማግኘቴ ነው::
ሁለተኛው በገነት እንደሚኖሩ በእርግጠኝነት የምገምታቸውን ጻድቃን መስለው የታዩኝን ሰዎች በገነት ውስጥ አለማግኘቴ ነው::

ከሁሉም በላይ ያስደነቀኝ ግን እንደ እኔ ዓይነቱን እጅግ ኃጢአተኛ ሰው በገነት ውስጥ ማግኘቴ ነው" አለ::

"ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፡— እውነት እላችኋለሁ፥ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል" ማቴ 21:31

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ታኅሣሥ 24 2012 ዓ ም
አዲስ አበባ
+ ጌታ የተወለደው የት ነው? +

የገና ዋዜማ የት ልትሔድ አሰብህ? ምሽቱንስ የት ልታሳልፍ ነው? የትኛው ሆቴል? የትኛው የሙዚቃ ድግስ? "የገናን በዓል አስመልክቶ የተዘጋጀ ልዩ የሙዚቃ ድግስ" ላይ ጌታ የለም:: ባለ ልደቱ ጌታ የት ነው ያለው? አድራሻው ከጠፋብህ የተወለደ ዕለት የሆነውን ልንገርህ!

የተወለደውን ክርስቶስ ለማየት ብዙ ሀገራትን አልፈው ተጉዘው የመጡት ሰብአ ሰገል በኮከብ ተመርተው ነበር::
ለእስራኤላውያን እረኞች በታሪካቸው ውስጥ በሚያውቁአቸውና በለመዱአቸው መላእክት ልደቱን የገለጠው አምላክ ኮከብ ሲቆጥሩና ሲጠነቁሉ ለኖሩት ሰብአ ሰገል ደግሞ በሚያውቁት ኮከብ መራቸው::
ሕጻኑ ክርስቶስ ገና ከመወለዱ ብዙ እንደ ጣዖት የሚመለኩ ነገሮችን ድል አድራጊ መሆኑን አሳየ::

በሲና በረሃ እስራኤል ጥጃን አምላክ ብለው በወርቅ ጣዖት ሠርተው ነበር:: በቤተልሔም ጥጃ ትንፋሹን ለክርስቶስ በመገበር አምላኬ እርሱ ነው ሲል መሰከረለት:: በሬም ገዢውን አወቀ ሕዝቤ ግን አላወቀኝም የሚለው ተፈጸመ:: ከዋክብትንና ፀሐይን ያመልኩ የነበሩን የዞረዳሸት (ዞራስትራኒዝም) ፍልስፍናን የሚያምኑ ሰብአ ሰገልም በሚያመልኩት ኮከብ ፈጣሪያቸውን አገኙ:: ቅዱስ ኤፍሬም እንዳለው "የሚያመልኳት ፀሐይም በሰብአ ሰገል ጉልበት ለፈጣሪዋ ሰገደች"

ኮከብ የሚወጣበት ጊዜ በዚያን ቀን የሰውን ዕጣ ፈንታ ይወስናል ብለው የሚያምኑም ብዙዎች ናቸው:: ይህ የሆነው በኮከቤ ምክንያት ነው! ኮከባችን አይገጥምም የሚባባሉ ብዙዎች ናቸው:: ይህ ሁሉ ባዕድ አምልኮ ነው:: ኤሳውና ያዕቆብ መንትዮች ናቸው:: የተወለዱት በአንድ ቀን ነው:: እነርሱ በተወለዱ ቀን የወጣው ኮከብም አንድ ነው:: "ኮከባቸው" አንድ ሆኖ ሳለ ምነው ነገራቸው ሁሉ አልገጥም አለ? ኮከባቸው ይገጥማል ምነው እነርሱ አልገጠሙም? ስለዚህ ሐሰት ነው::

የተወለደው ንጉሥ ግን ኮከቡ ዕጣ ፈንታውን የሚወስነው ሳይሆን ከዋክብትን በየስማቸው የሚጠራቸው በቁጥር የሚያውቃቸው ጌታ ነው:: እንደ ዮሴፍ 11 ከዋክብት ሐዋርያቱ ከይሁዳ በቀር የሰገዱለት እናቱ ማርያምም እንደ ያዕቆብ በልብዋ እያሰበች የተደነቀችበት የከዋክብት ጌታ የጨረቃ ንጉሥ የፀሐዮች ሁሉ ፀሐይ ነው እርሱ::

ሰብአ ሰገል መሪያቸው የነበረውን ኮከብ ሲያጡት ወደ ሔሮድስ መጡና "የተወለደው ንጉሥ ወዴት ነው?" አሉ::
እውነትም ጠቢባን ናቸው:: መንገድ ከጠፋብን : መሪ ኮከብ ካጣን ልደቱን የፈለግንበት እናክብር አላሉም:: የተወለደው ወዴት ነው? ብለው ቤተ መንግሥት ሔደው ጠየቁ:: ጥሩ በዓል ለማክበር ከቤተ መንግሥት የተሻለ ሥፍራ የለም:: በቤተ መንግሥት ራት እየበሉ ጮማ እየቆረጡ በዘፈን ታጅበው በዓሉን ማክበር ይችላሉ:: እነርሱ ግን የትም ቢሆን ንጉሡን ሳናገኝ አንቆይም:: እሱ የሌለበት ቦታ ቤተ መንግሥትም ቢሆን ልደቱን አናከብርም:: አይ ሰብአ ሰገል! ይህንን ዘመን መጥተው ቢያዩ ምን ይላሉ?

ወዳጄ አንተ የጌታን ልደት የት ታከብራለህ? መቼም
ልደት የሚከበረው ባለ ልደቱ ባለበት ሥፍራ ነው:: በእውነት የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? በጭፈራ ቤት ነውን? በመጠጥ ቤት ነውን? የት ነው ያለው ብለህ ጠይቀሃል?

"የሚመራኝ ኮከብ የለም" ትል ይሆናል:: ምንም ቢሆን ግን ሕፃኑ በሌለበት ልደቱን ለማክበር መወሰን የለብህም:: ምንም ያሸበረቁ ሥፍራዎች ቢኖሩም እንዳትታለል:: የሔሮድስ ቤተመንግሥት ውበት የግብዣው ስፋት አታልሎህ የተወለደውን ንጉሥ እንዳያስረሳህ ተጠንቀቅ:: እሱ ከሌለበት ያማረ ሥፍራ ይልቅ እሱ ያለበት በረት ይሻልሃል:: እሱ ያልመረጠውን ሥፍራ መርጠህ ከመንገድ አትቅር:: "የተወለደው የአይሁድ ወዴት ነው" ብለህ ጠይቅ::

እሱ ደሃ ሆኖ ባለጠጋ የሚያደርግህን ንጉሥ በሚያልፍ ደስታ አትጣው:: በስካር በዝሙት በጭፈራ በሔሮድስ ቤተ መንግሥት ቀልጠህ ቀርተህ የተወለደውን ሕፃን ሳታየው አትቅር:: እሱ በተወለደባት ሌሊት አንተ ስትሞት አትደር:: እመነኝ የተወለደው ይሻልሃል ከሞቱት ጋር ጊዜህን አታጥፋ::

ሰብአ ሰገል "የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው?" ብለው ለአይሁድ ንጉሥ ሔሮድስ ጠየቁት:: የአህያ ውኃ ጠጪው ሔሮድስ ክው ብሎ ቢደነግጥም ፈገግ ብሎ ላጣራላችሁ ቆይ ብሎ አቆያቸው:: መጽሐፍ አዋቂዎቹን ጸሐፍት ፈሪሳውያን ተጠሩ:: እነ ሊቄ መለሱ:: "እንደተነገረው ትንቢት ከሆነማ" አሉ ኩፍፍፍስ ብለው
"በይሁዳ ቤተልሔም ነው" ብለው የተወለደውን ንጉሥ አድራሻ ተናገሩ:: ሔሮድስ ከነተንኮሉ ለሰብአ ሰገል መልእክቱን አደረሰ:: ሰብአ ሰገልም ሔደው ለንጉሡ ሰግደው እጅ መንሻ አቀረቡ::

ሔሮድስን ትተን እስቲ የጸሐፍቱን ነገር ትንሽ እናስተውለው:: የተወለደውን ጌታ አድራሻ ጠቁመው ለሰብአ ሰገል መንገድ የመሩ እነርሱ ግን መንገድና እውነት ሕይወትም የሆነው ጌታ የተሰወረባቸውን የታወሩ መሪዎች በሽተኛ ሐኪሞች የተራቡ መጋቢዎችን እስቲ ልብ እንበላቸው:: "ጥሩምባ ነፊ ቀብር አይገኝም" ማለትስ አይሁድ ናቸው::

ሌላውን ወደ ጌታ እየመራ እርሱ ከጌታው የራቀ : የእርሱን ቃል ሰምተው ሰዎች ሲድኑ እርሱ በኃጢአት ቁስል የተወረሰ ስንት አይሁድ እለ? ቅዱስ አምብሮስ እንዳለው የኖህ መርከብ ሲሠራ ሚስማርና መዶሻ እያቀበለ የሠራ ነገር ግን ከጥፋት ውኃ ያልዳነ ስንት በየቤቱ አለ::

እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል ማለት ቀላል ነው:: እንደተጻፈው መኖር ግን ከባድ ነው:: ከመጽሐፍ ጥቅስ ማውጣት ቀላል ነው የሚጠቀስ ሕይወት መኖር ግን ከባድ ነው:: ወዳጄ ለብዙ ሰብአ ሰገሎች ስለተወለደው ንጉሥ ነግረሃል:: በአንተ ሕይወት ውስጥስ "የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው?" ወይስ በአንተ ሕይወት ገና አልተወለደም? ወይስ እንደ እንግዶች ማደሪያ ቦታ የለም ብለህ መልሰኸዋል? ኸረ እኔ እንኩዋን የቆሸሸ ሕይወት ነው ያለኝ እሱ በእኔ አያድርም አትበል? እንደ በረት ብትሸት እንደ እንስሳ እየኖርህ ቢሆንም አትፍራ እርሱ አይጠየፍህም? ወደ ልብህ መለስ ብለህ እንዲህ ብለህ ራስህን ጠይቅ "በእኔ ሕይወት ውስጥ የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው?"

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ታኅሣሥ 27 2012 ዓ ም
ሻሸመኔ ኢትዮጵያ
ተሻሽሎ የተጻፈ

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ጸልዩ! በኮሜንት መስጫው ሥር "ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ" (ኤፌ 4:29)
የመንፈስ ቅዱስ በገና የሆነ ቅዱስ ኤፍሬም ስለ ጌታ ልደት ከደረሰው ዝማሬ መካከል እንዲህ አለ

★ ★ ★

ዮሴፍ እግዚአብሔር ወልድን እንደ ሕፃንነቱ አቀፈው ፣ እንደ አምላክነቱም አገለገለው። በመሐሪነቱ እጅግ ደስ አለው በፈራጅነቱ ግን እጅግ ፈራው።

እንዲህ ሲል:

የልዑልን ልጅ ለእኔ እንደ ልጅ ይሆን ዘንድ ማን ሠጠኝ? እናትህ በጸነሰች ጊዜ ተቆጥቼ ነበር ፣ በስውር ልተዋትም አስቤ ነበር። በማኅፀንዋ ውስጥ ከድህነቴ ሊያወጣኝና ባለጠጋ ሊያደርገኝ የሚችል የተሰወረ ሀብት እንዳለ አላወቅሁም ነበር። ከእኔ ዘር የሚሆን ዳዊትስ አክሊል የደፋ ንጉሥ ነበር ፣ እኔ ግን የተናቀ ደሃ ሆንሁ። እንደርሱ ንጉሥ በመሆን ፈንታ አናጢ ሆንኩ። አሁን ግን እነሆ አክሊል ወደ ቤቴ መጣ ፣ የአክሊላት ሁሉ ጌታ በእቅፌ ነውና!

★ ★ ★

ድንግል ማርያም ሕፃኑን እያባበለች በመደነቅ ቃል ነደደች
እንዲህ ስትል
"ድንግሊቱን እጸንስ ዘንድ የሰጠኝ ማን ነው?
ይህንን አንድ ሲሆን የበዛ ፣ ታናሽ ሲሆን ታላቅ የሆነ ፣ ከእኔ ጋር ሲሆን በሁሉ የሞላ ሕፃን የሠጠኝ ማን ነው?
....
በእኔ [ማኅጸን] ውስጥ እያለህ ከእኔም ውጪ በሁሉ ቦታ ነበርህ ፣ በወለድሁህ ጊዜም ረቂቅ አምላክነትነህም ከእኔ ውስጥ አልወጣም። በእኔ ውስጥ ነህ ፣ ከእኔም ውጪ ነህ! ይህ ነገር ለእኔ ለእናትህን ያስደነቀኛል።

የሚታየው ሰውነህን በፊቴ ባየሁ ጊዜ የማይታየው አምላክነትህን በሕሊናዬ አየዋለሁ። ቅዱስ ሆይ በሚታየው ሰውነትህ ውስጥ አዳምን አየዋለሁ ፣ በማይታየው መለኮትህ ውስጥ ደግሞ በአንተ ሕልው ሆኖ የሚኖረውን እግዚአብሔር አብን አየዋለሁ።

አንተ ምንጭ ሆይ ለአንተ ለማጠጣት የጡቶችን ምንጭ እንዴት ልከፍታቸው ይቻለኛል? ሁሉን ከገበታህ የምትመግብ ሆይ እኔ አንተን ልመግብህ እንዴት ይቻለኛል? የክብርን ነጸብራቅ የተጎናፀፍከው ሆይ እንደምን በጨርቅ ልጠቀልልህ እችላለሁ?

ምን ብሎ እንደሚጠራህ አንደበቴ አያውቅም። አእላፋት ስሞች ለአንተ አይበቁህም ፣ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ስትሆን የሰው ልጅ ነህና ፣ የዳዊት ልጅ ስትሆን የማርያም ልጅ ነህና!

ልጄ ሆይ ከእኔ ጋር ሆነህ ሳለ ከሰው ልጆች ሁሉ ጋር በመሆንህ አልቀናም። ለሚያምንብህ አምላክ ነህ ፣ ለሚያገለግልህ ጌታ ነህ ፣ ለሚወድህም ሁሉን ያንተ ታደርገው ዘንድ ወንድም ነህ!"

የአንደበቶች ሁሉ ጌታን አንደበት እንደሌለው ያደረገው ምን ይሆን? ልጄ ሆይ አንተን በድንግልና መፅነሴን ክፉ ሰዎች እየዘለፉ ነው።
ቅዱስ ሆይ ለእናትህ አንደበት ሁነኝ ፣ አንተን ከማን እንደፀነስሁህ ይረዱ ዘንድ ተአምርህን አሳይ።

ሁሉን የምትወድደው ሆይ ስለ አንተ ብዬ የተጠላሁ ሆንሁ ፣ ለሰው ልጆች መሸሸጊያ የሆንህ አንተን በመፅነሴ መከራን ተቀበልሁ።
አቤቱ በዮናስ ላይ እንደተቆጣ ባሕር በእናትህ ላይ ተቆጥቷል።
ሔሮድስ የተባለ ማዕበል የባሕርን ጌታ ሊይዝህ ፈልጓል። የእናትህ ፈጣሪዋ ሆይ ወዴት እንደምሸሽ ንገረኝ"

💥💥💥💥💥💥

ጌታችን ስለተወለደባት ምሽት ደግሞ ቅዱስ ኤፍሬም አንዲህ አለ....

‹‹ይህች ምሽት ንጹሕ የሆነውና እኛን ሊያነጻን የመጣው (አምላክ) የተገለጠባት ንጽሕት ምሽት ናት፡፡

ጆሮአችን ንጹሕ ይሁን ፤ ዓይኖቻችንም ወደ ንጹሕ ነገር ይመልከቱ ፤ የልባችን ስሜት ቅዱስ ይሁን! ንግግራችንም አክብሮትን ይሞላ!

ይህች ምሽት የዕርቅ ምሽት ናት ፤ ስለዚህ ማንም ሰው ወንድሙን ተቆጥቶ እንዳያስቀይም!

ይህች ምሽት ለዓለም ሁሉ ሰላምን ያስገኘች ምሽት ስለሆነች ማንም ሰው አይሸበርባት፡፡
ይህች ምሽት የደግነት ምሽት ስለሆነች ማንም ሰው ክፉ አይሁን!
ይህች ምሽት የትሕትና ምሽት ናትና ማንም ሰው
እንዳይታበይባት!
ይህች ምሽት የደስታችን ቀን ስለሆነች የበደሉንን
አንበቀልባት!

የበጎ ፈቃድ ቀን ናትና የጭካኔ ቀን አናድርጋት!
የጸጥታ ቀን ናትና በቁጣ የምንነድባት ቀን አናድርጋት!

ዛሬ እግዚአብሔር ወደ ኃጢአተኞች የመጣበት ቀን ነው ፤ ስለዚህ ጻድቅ ሰው በኃጢአተኞች ላይ አይኩራባቸው!

ዛሬ እጅግ ባለጠጋ የሆነው አምላክ ስለ እኛ ደሃ የሆነበት ቀን ነው፤ ስለዚህ ሀብታም ሰው ድሆችን ወደ ገበታው ይጥራቸው፡፡

ዛሬ ያልጠየቅነውን ሥጦታ የተቀበልንበት ዕለት ነው፡፡ ስለዚህ እጆቻቸውን ዘርግተው እየጮኹ ለሚለምኑን ሰዎች የእርዳታ እጃችንን እንዘርጋ!

የዛሬዋ ዕለት ለጸሎቶቻችን የሰማያትን በር ከፍታልናለች ፤ እኛም ይቅርታን ለሚጠይቁን ሰዎች በራችንን እንክፈት!

ዛሬ አምላክ የሰውነትን ማኅተም በራሱ ላይ አተመ ፤ ሰውም የአምላክነትን ማኅተም ተጎናጸፈ!››

ታኅሣሥ 26 2013 ዓ ም
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ጸልዩ!

ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like, Subscribe እና Share ያድርጉ :-

የፌስቡክ ገጽ :- https://www.facebook.com/officialHenokhaile/
የቴሌግራም ቻናል : https://www.tg-me.com/deaconhenokhaile
የዩቲዩብ ገጽ: https://www.youtube.com/channel/UCOaVsWC05aUjeqIEW3fWj7g
+ የሕዝብ ቆጠራ መዝገብ +

ጌታችን በቤተልሔም ለመወለዱ ምክንያት የሆነው ለሕዝብ ቆጠራ ሲሉ ወደ ይሁዳ አውራጃ በመምጣታቸው ነበር:: ለቆጠራ መጥተው ከመቆጠራቸው በፊት ጌታችን ተወለደ:: ወደ ናዝሬት ከመመለሳቸው በፊት ግን ሁለት ሆነው ሊቆጠሩ የመጡበትን የሕዝብ ቆጠራ ሦስት ሆነው አድርገው ተቆጥረዋል::

እባካችሁ ያንን የቆጠራ መዝገብ ያለበትን ቦታ የምታውቁ የሮማውያን ታሪክ መርማሪዎች ካላችሁ ብትነግሩኝ ደስ ይለኛል:: ደግሞ የሕዝብ ቆጠራ መዝገብ ምን ያደርግልሃል? ካላችሁ መዝገቡ ይገኝ እንጂ እኔ ግን የምፈልገው አንድ ስም አለ:: ከብዙ የይሁዳ ተወላጆች ስም መካከል ሰሎሜ ዮሴፍ ማርያም ከሚሉ ስሞች አጠገብ አንድ ዓለም የዳነበት ስም በሕዝብ ቆጠራው መዝገብ ሥር ተጽፎአል::

ጉልበት ሁሉ የሚሰግድለት ስም : ከሰማይ በታች እንድንበት ዘንድ የተሠጠን ስም : ከስም በላይ የሆነ ስም : ቅዱስ ገብርኤል በክብር ይዞት የወረደና ለድንግሊቱ የነገራት ስም : አጋንንት ሲሰሙት የሚንቀጠቀጡለት ስም : ሙታንን የሚያስነሣ ድውያንን የሚፈውስ ስም በዚያ የሕዝብ ቆጠራ መዝገብ ላይ እንደዋዛ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል::

ኢየሱስ ✍🏽

አንተ የሕዝብ ቆጠራ ሠራተኛ ሆይ ይህንን ስም እዚያ መዝገብ ላይ ስትጽፈው ብዕርህ አልተሰበረም ወይ? ቀለሙስ አልሸሸም ወይ? እጆችህስ አልተንቀጠቀጡም ወይ?

ጌታችን በዚያ መዝገብ ላይ ተጻፈ:: በዚያ መዝገብ ከጌታ ጋር የተጻፉት ንጽሕት ድንግልና ጻድቁ ዮሴፍ ብቻ አልነበሩም:: በዚያች ግዛት ያሉ ሰዎች ሁሉ አብረው ተጽፈዋል:: ጥሩ ሰዎች ክፉ ሰዎች ወንጀለኞች ነፍሰ ገዳዮች ሰካራሞች አመንዝሮች በዚያ መዝገብ ላይ ስማቸው ተጽፎአል::

ክርስቶስም ገና ከመወለዱ ከኃጢአተኞች ጋር ተቆጠረ:: በሕይወት ዘመኑ የኃጢአተኞች ወዳጅ የሚል ቅጽል ስም የወጣለት ጌታ በዕለተ አርብም በግራና ቀኙ ከወንበዴዎች ጋር አብሮ የተሰቀለው ጌታ አሁንም በልደቱ ጊዜ "ከዓመፀኞች ጋር ተቆጠረ" (ኢሳ 53:12)

እኛን ከቅዱሳን ጋር ሊደምረን እሱ ከኃጢአተኞች ጋር ተቆጠረ:: እኛን "ስማችሁ በሰማይ ስለተጻፈ ደስ ይበላችሁ" ለማለት እርሱ በምድር መዝገብ ላይ ተጻፈ::

ወዳጄ ክርስቶስ ስለ አንተ ሲል ከኃጢአተኞች ጋር ተቆጠረ:: አንተ ስለ እርሱ ከንጹሐን ጋር ተቆጠርለት:: በተወለደበት ጊዜ ከሰካራሞችና ዘራፊዎች ስም ዝርዝር ጋር ለአንተ ሲል አብሮ ተቆጠረ:: እስቲ አንተ ልደቱን አስበህ ከሚሰክሩት ሰዎች ስም ዝርዝር ውስጥ ውጣ:: ከዘራፊዎችም መካከል ተለይ:: ክርስቶስ ወደ አንድ ነገር የሚገባው የሚገቡትን ሊያወጣ ነው:: ወደ ሞት የገባው ሙታንን ሊያወጣ ነው:: ወደ ሲኦል የወረደው ነፍሳትን ከሲኦል ሊያወጣ ነው:: ወደ ሮማውያን የሕዝብ ቆጠራ የኃጢአተኞች መዝገብ ስሙ የገባውም የሁላችንን በደል ተሸክሞ እኛን ከዚያ መዝገብ ሊያስወጣን ነው::

"ስማችሁ ግን በሰማያት ሰለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ"
ሉቃ 10:20

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ታኅሣሥ 28 2013 ዓ ም

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ጸልዩ!

ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like, Subscribe እና Share ያድርጉ :-

የፌስቡክ ገጽ :- https://www.facebook.com/officialHenokhaile/
የቴሌግራም ቻናል : https://www.tg-me.com/deaconhenokhaile
የዩቲዩብ ገጽ: https://www.youtube.com/channel/UCOaVsWC05aUjeqIEW3fWj7g
ነቢዩ ኢሳይያስ ‘ስሙም ድንቅ!’ ብሎ እንደተናገረው የታተመችው ደብዳቤ ድንግል ማርያም የታቀፈችው ማድነቅ እንጂ ማወቅ የማይቻል ሕፃንን ነበር፡፡

እኛ የሰው ልጆች የጠበቅነው ፈራጅና ተበቃይ ፣ በእጆቹ ሰይፍን የያዘ ንጉሥን ነበር፡፡ እርሱ ግን የመጣው ሕፃን ሆኖ ነበር፡፡ እንደ ኃያል ገዢ ስንጠብቀው ‘ከእናቱ ጡት ወተትን እየለመነ እንደ ሕፃናት አለቀሰ’

የሰው ልጆች ራሳችንን ከእግዚአብሔር ጋር በማስተካከል ለሠራነው በደል ቅጣትን ልንሰማ ለተጠያቂነት ዝግጁ ሆነን ጠበቅነው፡፡ እርሱ ግን ፍቅራችንንና እንክብካቤያችንን ፣ ደግነታችንን የሚጠይቅ ፣ መታቀፍን የሚሻ ሕፃን ሆኖ እጆቹን ወደ እኛ ዘረጋ፡፡

እኛ መቼም በእግዚአብሔር ላይ ኖሮን የማያውቀውን እምነት እግዚአብሔር በእኛ ላይ አሳየ፡፡ የእኛ ኩራትና ትዕቢት ሳያግደው ራሱን ዝቅ በማድረግ ወደ እኛ ወረደ፡፡

በዚህ ሕፃን ዓለም ሁሉ ተደነቀ ፤ ሁሉም ከጠበቀው በላይ የሆነ ነገርን አገኘ፡፡

መካኒቱ ኤልሳቤጥ ወለደች ፣

ዲዳው ዘካርያስ ትንቢት ተናገረ ፣

ድንግሊቱ እናት ሆነች ፤

እረኞች ከመላእክት ጋር ቆመው ወግ አወጉ ፤

የከብቶች በረት ቤተ መንግሥት ሆነ ፣

እንስሳት የወለደችን እናት ከብርድ ለመከለል ከበቧት ፣

ከዋክብት መንገድ መሪ ሆኑ ፣

ነገሥታት በድሆች ቤት እጅ መንሻ አቀረቡ ፤

አረጋዊው ስምዖን ሞትን መፍራት አቆመ ፤

ኃያሉ ንጉሥ ሔሮድስ ሁለት ዓመት ያላለፉ ጨቅላ ሕፃናትን እንደ ኃያላን ወታደሮች ፈራቸው፡፡

ይህ ሕፃን ያላመጣው ድንቅ ነገር አልነበረም!

የብርሃን እናት ገጽ 275
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ታኅሣሥ 29 2015 ዓ.ም.
ይህችን መዝሙር ለእናንተ ጻፉ (ዘዳ 31:19)

የልደት ሰሞን የምንሰማት ዜማዋ ያማረ አንዲት መዝሙር አለች :-

"እንደ ዮሴፍ ወይ እንደ ሰሎሜ በሆንን
ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም  ኢየሩሳሌም
    በሆንን አምላክ ሲወለድ ባየን"

የሚል መዝሙር ነው:: በጣም ደስ የሚያሰኝ ሃሳብ ያለው ቢሆንም ትንሽ የሚከነክን ጂኦግራፊያዊ ችግር አለው::

እንደሚታወቀው ጌታ የተወለደው ከኢየሩሳሌም 10 ኪሎ ሜትር በምትርቀው በቤተልሔም ነው:: ምንም ቅርብ ቢሆንም ምንም እንኩዋን ሁለቱም የይሁዳ ግዛቶች ቢሆኑም ምንም እንኩዋን ኢየሩሳሌም ብሎ ጠቅላላውን መጥራት የተለመደ ቢሆንም ነገር ግን ጌታ በተወለደ ምሽት ኢየሩሳሌም የተገኘ ሰው እንደዮሴፍና ሰሎሜ አምላክ ሲወለድ አያይም:: በዛሬው አስተዳደራዊ ክልል ደግሞ ከሆነ ደግሞ መዝሙሩ የበለጠ ይበላሽና "ጌታ በፍልስጤም ሲወለድ ምነው እኔ እስራኤል ውስጥ በሆንሁ" እንደማለት ይሆናል::

ይህን የመሰለ መዝሙር ታዲያ ምን እናድርገው ካልን ዜማው ሳይሰብር እንዲህ መዘመር ይቻላል :

"እንደ ዮሴፍ ወይ እንደ ሰሎሜ በሆንን
በቤተልሔም በቤተልሔም በቤተልሔም
    በሆንን አምላክ ሲወለድ ባየን"

ከዚያ ውጪ በጌታ ልደት ሌሊት በቤተ ክርስቲያን የሚያሳልፍ ሁሉ በጌታ ልደት እንደተገኘ ነው:: "እመቦ ዘአክበረ ልደተ እግዚእ ይከውን ክብሩ ከመ ሰብአ ሰገል" (የጌታን ልደት የሚያከብር ቢኖር ክብሩ እንደ ሰብአ ሰገል ክብር ይሆናል) ይላል ሊቁ::
የእኛ ቤተ ክርስቲያን የገና ሰሞን የሚሠራና በዓሉ ሲያልፍ የሚፈርስ የቤተልሔም ግርግም ሳይሆን ለሁልጊዜ ቋሚ የሆነ አገልግሎት የሚፈጸምበት ቤተልሔም ያላት ቤተክርስቲያን ናት:: ወደ ቤተክርስቲያን ሒድ : ፊትህን ወደ ምሥራቅ መለስ ካደረግህ ቤተልሔምን ታያታለህ:: "የነቢያት ሀገራቸው ቤተልሔም ሆይ ደስ ይበልሽ" ብለህ ጌታ የተወለደበትን ሥፍራ ተሳለም::

በልደቱ በዓል ቀን ወደ ሌላ ሥፍራ አትሒድ:: የጌታ ልደት በዲያቢሎስ ጭፈራ ቤት አይከበርም:: በእንግዶች ማደሪያ ሔደህ ልደቱን ለማክበር እንዳትሞክር:: እርሱ ያለው ቤተልሔም ነው:: ልደቱን በዝማሬ ካከበርህ ደስ ይለዋል ትልቅ ሽልማትን ይሠጥሃል::

ቅዱስ ኤፍሬም እንዲህ ይላል :-

"ሄሮድስ ልደቱን ላከበረችለት ልጅ ደስ ተሰኝቶ ክፋትን የተሞላ ሥጦታን ይኸውም የመጥምቁን አንገት በወጪት ሠጥቶአት ነበር::  ክፉው ሄሮድስ ይህን ካደረገ ርኅሩኁ ክርስቶስ ልደቱን የሚያከብሩ ሰዎችን ምን ያህል በጎ ሽልማትን ይሸልማቸው ይሆን?"

ዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ
ጥቁር ውኃ : ኢትዮጵያ
ታኅሣሥ 25 2012 ዓ ም
+ እነሆ ልጅሽ +

‹‹አልቦ ዘመድ ጊዜ ተዋርዶ
ወይከውን ባዕደ ጊዜ ተዋርዶ ዘመድ
እመሰ ይትሌዓል በንብረተ ሥጋ ማዕድ
ጥቀ ዘመዱ ወጥቀ ነገድ
ባዕድ ይዛመድ እምኀበ አልቦ ትውልድ ፤
ወእምኀበ አልቦ ትውልድ
ሶበሂ ተሰአልዎ ለሐዋርያ አይሁድ
ኀደገ ፈጣሪሁ ወቆመ ምስለ ባዕድ
ዘመድሰ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ
ኢተፈልጠ ምስለ እሙ እስከነ መቃብረ ይወርድ››

የአፄ ዳዊት የፍትሐ ነገሥት አውጪ መምህር የነበሩት መምህር ኤርምያስ የተባሉ ኢትዮጵያዊ ሊቅ የተቀኝዋት ጥንታዊት ቅኔ ናት፡፡ የቅኔዋን ሃሳብ ሳላስቀር ለአማርኛ አንባቢዎች እንደሚከተለው ወደ ግጥም ለውጫታለሁ፡፡

በመዋረድ ቀን የለም ዘመድ
ዘመድ እንኳን ቀን ሲጎድል ይሆን የለም ወይ ባዕድ? የሥጋ ኑሮህ ሲሟላ ሲትረፈረፍልህ ማዕድ
ከነገድህ ያልሆነው ፤ ከዘርህ የማይወለድ
የሚዛመድህ ብዙ ነው ፤ ባዳም ይሆንሃል ዘመድ
ቀን ሲጎድል ግን እንዲህ ነው
ሐዋርያውን ቢጠይቁት አላውቀውም ብሎ ካደ ፈጣሪውን ተወና ከባዕድ ጋር ተዛመደ
ዘመድስ ዮሐንስ ነው የነጎድጓድ ልጅ ብርቱ
መቃብር እስኪወርድ ድረስ አልተለየም ከእናቱ

ዮሐንስ ‹ኢየሱስ ይወደው የነበረ ሐዋርያ› ነው፡፡ ምንም እንኳን የክርስቶስ ፍቅር እንደ ፀሐይ ብርሃን ለሁሉም እኩል የሚያበራ ቢሆንም የፀሐይ ብርሃን ወደ ቤታችን ውስጥ ዘልቆ ሊያበራ የሚችለው በርና መስኮታችንን በከፈትንበት መጠን እንደሆነ ሁሉ ዮሐንስም ለጌታው ፍቅር ከሌሎች በላይ የልቡን መስኮት ወለል አድርጎ ስለከፈተ የፍቅሩ ብርሃን በእርሱ ላይ ጎልቶ አብርቷልና ‹ኢየሱስ የሚወደው ደቀ መዝሙር› ሆነ፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ከዓሥራ ሁለቱ አንዱ ቢሆንም ሐሙስ ማታ እረኛው ሲመታ ከተበተኑት በጎች ጋር አብሮ አልሸሸም፡፡ ‹ከእርሱ ጋር እንሞት ዘንድ እንሒድ› ሲሉ የነበሩት እነ ቶማስ ፣ አልለይህም ሲሉ
የነበሩት እነ ጴጥሮስ ሲሸሹ ዮሐንስ ግን ጌታውን እስከመስቀል ድረስ ተከተለ፡፡

ጌታችን በክብር እየተመላለሰ ፣ ሕሙማንን እየፈወሰ ፣ ዓሣና እንጀራ አበርክቶ እየመገበ ፣ በሕጻናት ዝማሬ እየታጀበ በነበረበት ወቅት ከእርሱ ጋር ወዳጅ መሆን ብዙም አያስቸግርም ነበር፡፡ በተዋረደበትና በተሰቀለበት በዕለተ ዓርብ ከእርሱ ጋር መሆን ግን እውነተኛ ወዳጅነት ነው፡፡

ጌታችን ‹‹ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል›› ብሎ በተናገረበት ምሽት ‹ጌታ ሆይ እኔ እሆንን?› ብለው ሐዋርያት ሲጠይቁ ዮሐንስ ግን ወደ ጌታው ደረት ተጠግቶ ‹ጌታ ሆይ አሳልፎ የሚሠጥህ ማን ነው?› ብሎ ነበር፡፡

ዮሐንስ ከጌታ ደረት ላይ መጠጋቱ በሊቃውንቱ ዘንድ እጅግ ብዙ ትርጉም ያለው ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ‹‹ከደረቱ ተጠጋ የሚለውን
ቃል ስትሰሙ ጌታው እንዲህ እንዲቀርበው እንዴት ፈቀደለት ብላችሁ አስባችሁ ይሆን? የዚህ ድርጊት ምክንያቱ ግን ፍቅር ነው፡፡ ‹የሚወደው ደቀመዝሙር ወደ ደረቱ ተጠጋ› በማለት የገለጠውም ለዚህ ነው፡፡ ወደ ደረቱ መጠጋቱ አሳልፎ ይሰጠኛል የሚለው ክስ እርሱን እንደማይመለከተው እርግጠኛ መሆኑን ያሳያል›› ሲል ቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያ ደግሞ ‹‹እግዚአብሔርን ለሚያዩ ሰዎች የተዘጋጀ የክብር ሥፍራ ከደረቱ መጠጋት ነው›› ይላል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ወደ ጌታ ደረት መጠጋቱ በእርግጥም ትልቅ ክብር ነው፡፡ መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድስ እንኳን የለም ፤ ‹በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው› እንደሚል የማናየውን እግዚአብሔር በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ‹እኔና አብ አንድ ነን ፤ አብን ያየ እኔን አየ› ብሎ ተርኮልን ነበር፡፡ እግዚአብሔር ወልድን ደግሞ ከኢየሱስ እቅፍ የተጠጋው ቅዱስ ዮሐንስ ‹በመጀመሪያ ቃል ነበረ ... ቃልም
ሥጋ ሆነ› ብሎ ሊተርክልን የቻለው ከጌታ ደረት በመጠጋቱ ነው፡፡ ሊቁ ‹‹ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ደረት እስካልተጠጋና ከኢየሱስም ዘንድ ማርያምን እናት አድርጎ ካልተቀበለ ሰው በቀር ወንጌልን ሊረዳ የሚችል የለም›› ይላል፡፡ ‘‘No one can apprehend the meaning of it [the Gospel] except he have lain on Jesus’s breast and received from Jesus Mary to be his mother also’’ /Origin of Alexandria, Commentary on the Gospel of John book 1.6/

በእርግጥም ቅዱስ ዮሐንስ ‹ነባቤ መለኮት› (The Theologian) እስከመባል የደረሰው ፣ መላእክት እንኳን ሳይቀሩ ነገረ እግዚአብሔርን ከእርሱ ሊማሩ የሚመኙለትና ሲሰግድላቸው እንኳን አንተ ከእኔ በምን ታንሳለህ ‹አብሬህ ባሪያ ነኝ› እስከማለት ደርሰው የሚያከብሩት ሰው ሊሆን የቻለው ከጌታ ደረት በመጠጋቱና ድንግል ማርያምንም እንደ እናት በመቀበሉ ነው፡፡ የጌታውን እናት ከተቀበላት በኋላ ድንግሊቱ ‹በልብዋ ትጠብቀው ነበር› የተባለላትን ምሥጢር ሁሉ ብትነግረው ከሐዋርያት ሁሉ በላይ
የመጠቀ ፣ ነገረ መለኮትን በጥልቀት የጻፈ መጋቤ ምሥጢር ለመሆን በቃ፡፡

ጌታውን እጅግ ይወድ የነበረው ቅዱስ ዮሐንስ በዕለተ ዓርብ የጌታችንን መከራውን ባየ ጊዜ በኀዘን እጅግ ተሰቃይቶ ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ በድርሰቱ ‹‹በአንጻረ መስቀል ቀዊሞ ዮሐንስ በከየ ፤ እንዘ ይብል ወይልየ ወይልየ ፤ አማዑተ ከርሱ ከመ ነደ እሳት ውዕየ›› (በመስቀሉ አንጻር ቆሞ ዮሐንስ ወይ ለእኔ ወይ ለእኔ እያለ አለቀሰ ፤ አንጀቱም እንደ እሳት ነበልባል ተቃጠለ) በማለት እንደገለጸው እንደ ኢየሩሳሌም ሴቶች ጮኾ በማይወጣለት የወንድ ልጅ ለቅሶ ቅዱስ ዮሐንስ ስለጌታው መከራ በምድር ላይ በቆየበት ዘመን ሁሉ ያልተለየውን ጥልቅ ኀዘን አዝኗል፡፡

ጌታችን ለዚህ በኀዘን ባሕር ለሚዋኝ ደቀ መዝሙሩ ምንም የማጽናኛ ቃል አልተናገረውም ፤ እስከ መስቀል ድረስ ለመከተሉም ሌላ ሽልማት አልሰጠውም፡፡ ‹እናትህ እነኋት› አለው፡፡ በእርግጥም ላዘነ ሰው ከኀዘን የምታረጋጋ ድንግል ማርያምን ከመስጠት በላይ ምንም ማጽናኛ አለ? ለዚህ ሐዋርያ በምድር ላይ የቀረች ሀብቱን ድንግል ማርያምን ከማውረስ በላይ ምን ሥጦታ ሊሰጠው ይችላል? ‹‹እንዴት ያለ ክብር ነው? ሐዋርያውን እንዴት ባለ ክብር አከበረው? ነፍሱን ከሥጋው በለየበት በዚያች ሰዓት እናቱን እንዲጠብቅ ለደቀ መዝሙሩ ሰጠው››

በመስቀሉ ሥር የዮሐንስ ወላጅ እናቱ ማርያም ባውፍልያ እዚያው ቆማ ነበር፡፡ ጌታችን ግን የሥጋ እናት ላለው ዮሐንስ ሌላ መንፈሳዊት እናት ሰጠው፡፡ የሥጋ እናቱ ማርያም ባውፍልያ የምትለምነውን ሳታውቅ ‹በግራና በቀኝ አስቀምጥልኝ› ብላ ለልጆችዋ ሞትን የምትለምን እናት ነበረችና
ለዮሐንስ ሌላ እናት ያስፈልገዋል፡፡ (ማቴ. ፳፥፳፩)

‹‹ሰአሊት ለነፍሳቲነ ሕይወተ ኦ ጸጋዊተ ምሕረት ለእለ የአምኑ በጸሎታ›› ‹‹ለነፍሳችን ሕይወትን የምትለምን በጸሎትዋ ለሚያምኑ ምሕረትን የምታሠጥ›› እናት ያስፈልገዋልና እመቤታችን
‹እነኋት እናትህ› ብሎ ሰጠው፡፡ አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት ድንግል ማርያም ሌሎች ልጆች ቢኖሩአት ኖሮ ከልጆችዋ ነጥሎ ለደቀ መዝሙሩ ውሰዳት ብሎ ባልሠጣት ነበር::
ስለዚህ ያ ደቀ መዝሙር ‹ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ወደ ቤቱ ወሰዳት› ወደ ቤቱ ሲባል ትቶት ጌታን ወደተከተለው መኖሪያ ቤቱ ብቻ ከመሰለን የዋሆች ነን፡፡ ‹እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን›› ሲል የቤቴ ጣሪያና ግድግዳ እግዚአብሔርን ያመልካል ማለት ሳይሆን ሕይወቴ ፣ ሁለንተናዬ ፣ ቤተሰቤ ሁሉ ያመልከዋል ማለት አይደለምን? ‹ትሞታለህና ቤትህን አስተካክል› ማለት ሕይወትህን አስተካክል ማለት አይደለምን? ‹ወደ ቤቱ ወሰዳት› ማለትም ወደ ሕይወቱ ወደማንነቱ ወደ ልቡ ወሰዳት ማለት ነው፡፡

ጌታችን ለሚወደው ሐዋርያ የሚወዳት እናቱን ፣ ከደረቱ ለተጠጋው ሐዋርያ ከደረትዋ አስጠግታ ያሳደገችውን እናቱን ፣ እስከ መስቀል ለተከተለው ሐዋርያ እስከ መስቀሉ ያልተለየችውን እናቱን ሰጠው፡፡ ለእርስዋም ‹እነሆ ልጅሽ› አላት፡፡
‹‹እነሆ ልጅሽ አላት እንጂ እነሆ ይህም ሰው [በተጨማሪ እንደ] ልጅሽ ይሁን አላላትም፡፡

የተናገረው ‹ፀንሰሽ የወለድሽው ኢየሱስ
ራሱ እነሆ› ነው፡፡ በእርግጥ ማንም ሰው ወደ ፍጹምነት ሲመጣ እርሱ በሕይወት አይኖርም ፤ ክርስቶስ ግን በእርሱ ውስጥ ይኖራል (ገላ. ፪፥፳) ክርስቶስ በዮሐንስ ውስጥ ስለሚኖርም [እንደ ልጅ ይሁንሽ በማለት ፈንታ] ‹እነሆ ክርስቶስ ልጅሽ› አላት››248 ይህም ዮሐንስ ራሱን የክርስቶስ ማደሪያ አድርጎ በመሥጠቱ ጌታችን ‹እኔ በዮሐንስ ውስጥ አለሁና እነሆ ልጅሽ› አላት፡፡

ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ‹እነሆ ልጅሽ› የሚለውን ቃል ይዞ ለድንግል እንዲህ ይላታል ፡-

‹‹ክርስቶስ የሚታየውን ወተት ከአንቺ ደረት ተጠግቶ ጠጥቶ ነበር ፤ ዮሐንስ ደግሞ የተሰወሩ ምስጢራትን ከእርሱ ደረት ተጠግቶ ጠጥቷል፡፡ ክርስቶስ ወደ አንቺ እቅፍ በመተማመን እንደተጠጋ ዮሐንስም ወደ ክርስቶስ እቅፍ በመተማመን ተጠግቷል፡፡ ልጅሽ ድምፁን እንደምትናፍቂ ስላወቀ ለአንቺ መጽናኛ ይሆንሽ ዘንድ በገናውን [ዮሐንስ] ሰጠሽ››

ጌታችን በመስቀል ላይም ሆኖ ለዮሐንስ የነበረው ፍቅር አላቋረጠም ፤ አባ ጊዮርጊስ ‹‹በመስቀሉ ግንድ ላይ ደሙ በፈሰሰ ጊዜ በሕማሙ ጊዜ እንኳን የዮሐንስን ፍቅር አላጎደለም›› እንዳለው ‹‹በመስቀል ላይ የአይሁድን ሽሙጥ በተቀበለ ጊዜ እንኳን ‹እነሆ ልጅሽ› ብሎ ለእናቱ አደራ አድርጎ ሰጠው›› እንጂ ፍቅሩን አልቀነሰበትም፡፡ ‹ጌታ ይወደው ለነበረው ደቀ መዝሙር› ምን አደረገለት? የፍቅሩ መግለጫ ምንድን ነው? የሚል ቢኖር የፍቅሩ መግለጫ ‹እነኋት እናትህ› የሚል ሥጦታ ነበር፡፡

እመቤታችን ጌታ ለሚወደው ሰው የሚሠጣት ሥጦታ ናት፡፡ እርስዋን እንደ እናት ለመቀበልም እንደ ዮሐንስ መሆን ያስፈልጋል፡፡ የዓሣ ማጥመጃ መረቡን ጥሎ ሁሉን ነገር ትቶ ጌታውን የተከተለ ፣ ስለ ጌታው ክብር ከማንም በላይ በቅናት የተቃጠለ ፣ በጌታው የተወደደ ‹‹ፍቅረ ዮሐንስ ኢያንተገ በጊዜ ሕማሙ ፤ ነዋ ወልድኪ ይቤላ ለእሙ›› ‹‹ዝንጓጔ መስቀል አመ ተወፈየ ፤ ነዋ ወልድኪ ይቤላ ለእሙ›› (መጽሐፈ ሰዓታት ዘሌሊት ገጽ ፷)


ወደ ክርስቶስ ወደ ደረቱ የተጠጋ ፣ በታማኝነት እስከ መስቀሉ የተከተለ ካልሆነ በቀር የእርስዋ እናትነት ለማን ሊገባው ይችላል?

ለዚህ ክብር የማይገባ ፣ ከመስቀሉ አጠገብ መቆም ተስኖት የራቀ ሰው ግን የእመቤታችን እናትነትዋ አይዋጥለትም ፤ ጭራሽ ‹እነኋት እናትህ ያለው ለዮሐንስ ነው እንጂ ለእኛ ነው ወይ?› እያለ አፉን ሞልቶ ይከራከራል፡፡ እንዲህ የምትል ወንድሜ! እንዲህ በማለትህስ እውነት ተናገርህ እንጂ አልተሳሳትክም፡፡ በእርግጥም የእርስዋ እናትነት ለአንተ አይደለም ፤ እንደ ዮሐንስ ላሉት ብቻ ነው፡፡ እርስዋን እናቴ ለማለት ገና ሁሉን ትቶ መከተል ፣ የምሥጢር ሐዋርያ መሆን ፣ ወደ ደብረ ታቦር ወጥቶ የጌታን ክብር መመልከት ፣ ወደ ጌታ ደረት መጠጋት ፣ እስከ መስቀሉ ድረስ መከተል ይቀርሃል፡፡ ለእናቱ ፍቅር ማጣትህ ከክርስቶስ ደረት ያለመጠጋትህና ኢየሱስ የሚወደው ደቀ መዝሙር ያለመሆንህ ማሳያ ነው፡፡ ድንግል ማርያምን እንኳን እንደ ዮሐንስ በእናትነት ለመቀበል ቀርቶ ‹ጸጋን የሞላብሽ ሆይ ደስ ይበልሽ› ለማለት እንኳን እንደ መልአኩ ገብርኤል ‹በእግዚአብሔር ፊት መቆም› ያስፈልጋል፡፡


እናትነትዋን ፈልገው ፣ ፍቅርዋ እንደ ውኃ ጠምቷቸው ዓለምን ጥለው የመነኑ ስንት አሉ መሰለህ? ‹ድንግል ሆይ ወደ እኔ ነይ› እያሉ ሰዓታት የሚቆሙ ፣ እግርዋ የረገጠውን ፣ ጥላዋ ያረፈበትን የሚልሱ ስንት ዮሐንሶች አሉ መሰለህ? እግዚአብሔር የተቀመጠባትን መሰላል ሊያዩአት ናፍቀው ድንጋይ የተንተራሱ ስንት ያዕቆቦች በየምድረ በዳው አሉ መሰለህ? አንተ ግን ጭራሽ ‹እናቴ አትባልም› ትላለህ፡፡

እውነትህን ነው እርስዋ ለትሑታን እንጂ ለትዕቢተኞች እናት አይደለችም፡፡ ሥጦታን
ለመቀበል እኮ አቅም ያስፈልጋል፡፡ የሚቀበልበት ጫንቃ ‹ከተሰጠው በቀርም ሊቀበል የሚችል ማንም የለም› ጌታህ ‹እናትህ እነኋት› ሲልህ የምትሰማው አንተ እንደ ዮሐንስ መሆን ስትችል ነው፡፡ ከዚያም በኋላ ነው ወደ ቤትህ ልትወስዳት የምትችለው፡፡ ይህንን ሁሉ መንገድ ካልተጓዝህ ግን እናትነትዋ ለአንተ አይታይህም፡፡

ጌታችን በዕለተ ዓርብ እናቱን ‹እነኋት› ብሎ የሰጠው ፈርተው ለሸሹት ሳይሆን ፍርሃትን አሸንፎ ለቆመው ለዮሐንስ ነበር፡፡ ለሌሎቹ እናትነትዋ የደረሳቸውም በንስሓ ከተመለሱ በኋላ ነው፡፡ እርስዋ ‹የአሸናፊዎች የሰማዕታት እናት› (እመ ሰማዕታት መዋዕያን) ናት እንጂ እናትነትዋ ፈርተው ለሚክዱት አይደለም፡፡ ለአስቆሮቱ ይሁዳ ‹እናትህ እነኋት› ብሎ አልሰጠውም፡፡ የእርስዋ እናትነት በገንዘብ ለሚታለሉ ዘራፊዎች አይገባም፡፡ ወዳጄ ሆይ እስቲ አስበው እንደ ይሁዳ እየሸጥከው እንዴት ‹እናትህ እነኋት› ብሎ ይሥጥህ? ዮሐንስ እርስዋን ወደ ቤቱ ወስዶ የፈሰሰለት የመለኮት ምሥጢር ሁሉ በአንተ ደጅ ግን አያልፍም፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር የዘጠኝ ወር ማደሪያ ቤቱን ለወንበዴዎች አይሠጥም ፤ ቤቱማ የጸሎት ቤት ትባላለች እንጂ የወንበዴዎች ዋሻ አይደለችም፡፡

እመቤታችን ‹እነሆ ልጅሽ› የሚለውን የልጅዋን የመስቀል ላይ የአደራ ቃል ለመፈጸም ከዮሐንስና ከመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ያልተለየች የቤተ ክርስቲያን እናት ነበረች፡፡ ሐዋርያት በአጠቃላይ
ከመቶ ሃያ ቤተሰቦች ጋር ሆነው በጸሎት ስለመትጋታቸው በተጻፈበት ሥፍራ ቅዱስ ሉቃስ ‹‹ከኢየሱስም እናት ከማርያም ጋር ሆነው በጸሎት ይተጉ ነበር›› ብሎ በስም የጠቀሳት እመቤታችን ለቤተ ክርስቲያን ራስ ለክርስቶስ እናቱ እንደሆነች ሁሉ ለአካሉ ለቤተ ክርስቲያንም እናትነትዋ
አለመቋረጡን ያሳየናል፡፡

በሃምሳኛው ቀን መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያቱ
ላይ ሲወርድም እመቤታችን ከመካከላቸው ነበረች፡፡ በነገረ መለኮት ሊቃውንት ከጰራቅሊጦስ በፊት የተደረገ ጰራቅሊጦስ ወይም መቅድመ
ጰንጤቆስጤ ተብሎ በሚጠራው የገብርኤል ብሥራት በሰማችበት ዕለት መንፈስ ቅዱስ ይጸልልሻል የተባለችው ድንግል በዚያች ዕለት የተገኘችው ከሐዋርያት ጋር ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ልትቀበል አልነበረም፡፡( ‘Annunciation is a kind of premature Pentecost’ Fr. George Florovksy Artoszois)
ሐዋርያት በተሠጣቸው ክህነት በሰዎች ላይ እጅ እየጫኑ መንፈስ ቅዱስ ሲያሳድሩ ፣ ከሐዋርያት በኋላ የተነሡ ቀሳውስትም በቅብዐ ሜሮን በክርስቲያኖች ላይ መንፈስ ቅዱስን ሲያሳድሩ ድንግል ማርያም ግን እጅዋን ሳትጭን ፣ ሜሮን ሳትቀባ በሰላምታዋ ድምፅ ብቻ መንፈስ ቅዱስን በኤልሳቤጥ ላይ ያሳደረች ናትና የእርስዋ በሐዋርያት መካከል መገኘት የልጅዋን ‹እነሆ ልጅሽ› የሚል አደራ ለመወጣት ነበር፡፡
እስከ ሕይወትዋ ፍጻሜ ድረስ አደራ ተብሎ ከተሠጣት ልጅዋ ከዮሐንስ አልተለየችም፡፡

ልጅዋን ይዛ ከሄሮድስ ለመሸሽ ወደ ግብፅ እንደተሰደደች ሁሉ የአደራ ልጅዋን ዮሐንስን ይዛም ከሌላ ሄሮድስ ሸሽታለች፡፡ ‹‹በዚያን ዘመን ንጉሥ ሄሮድስ መከራ ያጸናባቸው ዘንድ ከቤተ ክርስቲያኑ በአንዳንዶች ላይ እጁን ጫነባቸው፡፡ የዮሐንስንም ወንድም ያዕቆብን በሰይፍ ገደለው፡፡ አይሁድንም ደስ እንዳሰኛቸው አይቶ ጨምሮ ጴጥሮስን ደግሞ ያዘው›› (ሐዋ. ፲፪፥፩‐፪) በዚህን ጊዜ እመቤታችን ከዚህኛውም ሄሮድስ ለመሸሽ የአደራ ልጅዋን ዮሐንስን ተከትላ ወደ ኤፌሶን ተሰድዳለች፡፡


ለመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች የእመቤታችን በመካከላቸው መሆን ታላቅ ደስታ ነበር፡፡ እርስዋን ለማየትም ብዙዎች ይጓጉ ነበር፡፡ የተአምረ ማርያም መቅድም ‹የድንግል ማርያም መልክዋ እንደ አምላክ መልክ ነው ፤ የአምላክን መልክ ይመስላል› እንደሚለው በሥጋ አባት የሌለውን መድኃኔ ዓለም የወለደችዋን እናት ማየት ማለት በምድር ላይ ጌታን የሚመስል መልክ ያላትን ብቸኛ ሴት ማየት ነውና ብዙዎች ‹ለፊትዋ ይማልሉ› ነበር፡፡ ግሪካዊው ቅዱስ ዲዮናስዮስ ዘአርዮስፋጎስ ወደ ኢየሩሳሌም ሔዶ ከጎበኛት በኋላ ‹‹ሐዋርያት ባይነግሩኝ ኖሮ ባየኋት ጊዜ ፍጡር ናት ብዬ ለማመን ተቸግሬ ነበር›› ሲል ቅዱስ አግናጥዮስ ደግሞ ‹‹እርስዋን አይቶ በልጅዋ አምላክነት የማያምን ሰው የለም›› ብሏል፡፡

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ጥር ዮሐንስ 2015 ዓ.ም.
ከሕማማት መጽሐፍ የተወሰደ
በልጆች አስተዳደግን የመንፈሳዊ አገልግሎት መስመር አድርገው ከሚሠሩ ሰዎች መካከል መምህር አቤል ሰሎሞን አንዱ ነው:: በሥነ ልቡና ባለሙያነቱና በሃይማኖት መምህርነቱ የሚታወቀው መ/ር አቤል ከዚህ ቀደም በልጆች አስተዳደግ ላይ የሚያተኩሩ መጻሕፍትንና ጥናታዊ ጽሑፎችን ለቤተ ክርስቲያን ያበረከተ ጸሐፊ ሲሆን የኔታ ጥዑም የተሰኘው የልጆች ተወዳጅ መርሐ ግብርም እንዲሁ የሚጠቀስ ነው:: አሁን ደግሞ ባማረ ስቱድዮና ቀረጻ ልጆቻችን የተሰኘ ይህንን ቻናል ይዞልን መጥቶአል::

ሰብስክራይብ እያደርግን ለእኛም ለልጆቻችን ትልቅ ውለታ እንሥራ

https://youtu.be/h9-MkH3lYAM
#የምወደው_ልጄ_ይህ_ነው!!

በጥምቀት በዓል በታላቅ ፍቅር ሲያመሰግኑ በነበሩት ወጣቶች አንጻር የሚከተለው #ተግሳጽ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጣ- "የምወደው ልጄ ይህ ነው!"
<< የምወደው ልጄ ይህ ነው! ባንተስ ደስ የምለኝ መቼ ነው?? >>
( በዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ)

በእርግጥ ያንተን ያህል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ መውጣት አይችልም፤ ኦሪት ዘፍጥረት የቱ ጋር እንደሆነ, ዜና መዋእልም የት እንደሚገኝ አያውቅም። ምናልባት ከራእይ ዮሐንስ ሀይለ ቃል ለማንበብ መዝ.ዳዊት ላይ ገልጦ ይዳክር ይሆናል፤ ምንም ምስጥር አያውቅም፤ ለአንድምታው,ለትርጓመውም እንግዳ ይሆናል፤ መላእክት ጻድቃን ሰማዕታትን አይለይም።

ጊዮርጊስ ሰማዕቱን ከመላእክት አንዱ አድርጎ ያስበዋል፤ ለየትኛውም ሃይማኖታዊ ጥያቄ መልስ መስጠት አይችልም፤ ዛሬም የእርሱ ጥያቄ ዓሣ ፆም አለው ወይስ የለውም ? የምል ልሆን ይችላል፤ በማህሌት እና በሰዓታት በቅዳሴና በወረብ መካከል ያለው ልዩነት አይገባውም! ለእርሱ በቤ/ክን ውስጥ የሚሰማ ዜማ ሁሉ ቅዳሴ ነው፤ ስለ ስርዓተ ቤ/ክን ምንም አያውቅም በእርሱ አስተሳሰብ በፆም ቀን ፀበል መጠጣት ፆሙን አያፈርስም፤ የምያማትበውም አንተ በምታውቀውና በምታብራራው ሥርዓት ሳይሆን እጅን በማወዛወዝ ልሆን ይችላል፤ የሰንበት ት/ቤትን ተከታታይ ት/ት አልተማረም ፤ በጉባኤ አባልነትም አልተመዘገበም፤ በየትኛውም ምድብ አያገለግልም፤ ከየተኛው መንፈሳዊ ት/ቤት አልተመረቀም፤ ይሁንና የምወደው ልጄ ይህ ነው።

የሚዘምረው መዝሙርም ሥርዓተ ቤ/ክን ያልጠበቀ ነው፤ ሽብሸባውም እንዲሁ፤ አለባበሱም ብዙ ጉድለት አለበት፤ ነጠላውን እንደዋዛ ይጠመጥመዋል እንጅ በትምህርተ መስቀል አያደርግም፤ አረማመዱም የምንፈሳዊ ሰው አይደለም ፀጉሩን የተንጨባረረ እና የተጠቀለለ ነው፤ የምውልበት ሥፍራ መልካም ላይሆን ይችላል፤ በሰው ሁሉ የተጠላ የተተፋ፤ ይሁን ግን ልንገርህ -የምወደው ልጄ ይህ ነው።

አናንያ ሆይ < የሳኦልን ክፉ አትንገረኝ ፤ የእርሱን የቀደመ ጭካኔውንና በሰው ዘንድ ያለውን ክፉ ስም አትንገረኝ፤ ጌታ ሆይ መጥፎ ነው >እያልክ አትወትውተኝ ሁሉንም አውቀዋለሁ፤ ነገር ግን ካንተ ይልቅ የሚሰማኝ የምፈራኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው።

አንተ በቤቴ ኖረህ ሳትሰማኝ ቃሌንና ትእዛዜን ተለማምደህ ቸል ብለህ ስትኖር፣ የተናገርኩትን ትእዛዝ ቸል ሳይል የምፈፅም የእኔ ምርጥ እቃ- የምወደው ልጄ ይህ ነው።
አንተ የለመድከውን አንተ የተዳፈርከውን መቅደሴን በሩቅ እያየ የምፈራ የምንቀጠቅጥ ሳነሳው የምነሳ ሳስቀምጠው የምቀመጥ ምርጥ እቃዬ -የምወደው ልጄ ይህ ነው።

እርግጥ ነው ዜማ አያውቅም እኔን ግን ያውቀኛል፤ ምንም ጥቅስ አልያዘም ትህትናን ግን ይዙዋል፤ የቅዳሴን ተሰጦ አይመልስም እኔ ስጠራው ግን ይመልስልኛል: እኔ ግን ይፈራኛል: ስለ ስሜ ስተጋ አይታክትም፤ ስለ ክብሬ ሲንከራተት አልተማረረም፤ ያንተን ቸልተኛውን ትእዛዝና ተገሳፅ በትህትና ተቀበለ እንጅ እኔን አክብሮ አከበረህ እንጅ ለታቦት ማለፍያ መንገድ ስደለድል፤ ቆሻሻ ሲዝቅ አፈር ሲሸከም ካንተ ያገኘውን ጥቅስ በየመንገዱ ሲሰቅል ድንጋይ ሲሸከም በፊቱ ላይ ደስታን እንጅ አንዳች ምሬት አላየሁበትም። ስሜታዊ ሆኖ ነው: ስላልበሰለ ነው አትበለኝ የቤቴ ቅናት የምትበላው ለእኔ የታመነ የምወደው ልጄ ይህ ነው።

ስሜታዊ መሆንስ እንዳንተ ማንቀላፋት ነው፤ መብሰልስ ቸልተኝነት ነው ስምኦን ሆይ ስለሱ አንዳች ክፉ አትንገረኝ ኃጥአተኛ ነው እንድህ አድርጓል አትበለኝ አንተ ያልሠራሀውን አልሠራም እኔ ያየሁትን ክፋቱን አይደለም፤ በንስሐ በትህትና ማጎንበሱን ነው። ለክብሩ ሳይሳሳ በእንባ እግሮቼን አጥቧል ምንጣፍ አንጥፎ ሳር ጎዝጉዞ በአደባባይ ከፊቴ ስደፋ ያን ጊዜ ነው የልጄን ልብ ያየሁት:: ስለሱ አንዳች ክፉ አትንገረኝ - የምወደው ልጄ ይህ ነው።

አንተ መዘመር ሰልችቶሃል ፤ ማጨብጨብም ደክሞሃል፤ እርሱ ግን ስያመሰግን ብውል ብያድር አይጠግብም። ምናልባት ጀማሪ ስለሆነ ነው ትል ይሆናል፤ አንተ ፈፃሚ ስለሆንክ ነው የተሰላቸህው? አንተ መዝሙር ምታጠናው ከበሮ ለመምታት ብቻ ይሆናል ፤እርሱ ግን በባዶ እጁ በማመስገኑ ደስተኛ ነው። አንተ እንዴት እንደምሸበሸብ እያወክ ታበላሸዋለህ ፤ እርሱ ግን ላገኘው ሁሉ እንዲህ ነው የሚሸበሸበው እያለ ይጨነቃል፤ ልክ ነህ ጀማሪ ነው፥ ስሜታዊ ነው፤ ያልበሰለ ነው ፤ ነገር ግን የምወደው ልጄ ይህ ነው። ባንተ ደስ አልተሰኘሁም፤ በተማርኸው መጠን አልኖርክም በዘራሀው መጠን አላፈራህም፤ ስለ ቅናቱ በእርሱ ደስ የምለኝ - የምወደው ልጄ ይህ ነው። ባንተስ ደስ የምለኝ መቼ ነው????????????

ይህን የእግዚአብሔር ተግሳጽ ከመቀበል ጋር አንድ መልእክት ይቀራል:: እነዚህ ወጣቶች ቀድሞም በቃለ እግዚአብሔር ተኮትኩቶው አላደጉም:: ምንም በጥሩ ምግባር ባይታወቁም በልባቸው ግን እንደ እሳት የሚንቀለቀል ሃይማኖት አላቸው:: ፈሪሃ እግዚአብሔር አላቸው::

እኛ ወደ እነርሱ ባንሄድ እነሱ ግን ወደኛ መጥተዋል:: ሌላ ምን እንላለን:: ነብዩ <መንፈሱ ሰብስባቸዋልና ከነዚህ አንድ አትጠፋም > እንዳለ ያለ ቀሽቃሽ የሰበሰባቸው የእግዚአብሔር መንፈስ እንዲጠብቃቸው እንዲያጸናቸው እንመኛለን:: በጎች ኑረው በረት ጠበባ አይባልምና ቤተ ክርስቲያንም መዋቅሯን አጠናክራ እንደምትቀበላቸው ተስፋ እናደርጋለን::

ለወጣቶቹ ግን < ምንነው ለጥምቀት ብቻ > ከሚል ምክር ጋር አንድ ቃለ ሐዋርያ እንጥቀስ::
" እግዚአብሔር፥ ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው፥ ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለም። " ዕብራውያን 6፥10

ወጣት ሆይ! አንብበህ ስታበቃ ተገሳፁ ላንተ እንደሆነ አስተውል!! "እኛስ ለታቦት ሥራ አለብን" ብለው እራሳቸውን ዝቅ ያደረጉ ወንድሞችህ "የምወደው ልጄ ይህ ነው" ተብለዋል። አንተም ከእነርሱ ተማርና የምወደው ልጄ አንተ ነህ ለመባል ያብቃህ!
[ጸሐፊ :- ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
የምወደው ልጄ ይህነው !
+++ የኒቆዲሞስ ክርስትና +++

ኒቆዲሞስ የሚለው ስም በዮሐንስ ወንጌል ብቻ ከተጻፉ ስሞች መካከል አንዱ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ የዚህን ሰው ስም ባነሣበት ሥፍራ ሁሉ ‹አስቀድሞ በሌሊት የመጣው› የምትል ቅጽል ያስቀድማል፡፡ ይህ ሰው የአይሁድ አለቃ ነው፡፡ በሀብቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያለ ባለጸጋ ፣ በሹመቱ የአይሁድ ሸንጎ /synagogue/ አባል ፣ በትምህርቱ ደግሞ ጌታችን ራሱ እንደመሰከረለት ‹የእስራኤል መምህር› የሆነና አዋቂ ነው፡፡

የአይሁድ አለቃ ፣ የእስራኤል መምህር ኒቆዲሞስ ጌታችን ራሱ ለብቻቸው በቃል ምልልስ እያናገረ ጥያቄያቸውን እየመለሰ ካስተማራቸው ጥቂት ዕድለኛ ሰዎች አንዱም ነው፡፡ ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅነት ያገኘንበትን ምሥጢረ ጥምቀት በጥልቀት እና በዝርዝር የተማረው የመጀመሪያው ሰውም ኒቆዲሞስ ነው፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ጌታችን ጥምቀትን በተግባር ሲመሠርት የዓይን ምስክር እንደነበረ ሁሉ ጥምቀት በትምህርት ስትመሠረት ደግሞ የዓይን ምስክሩ ኒቆዲሞስ ነው፡፡

በትምህርቱ መካከልም ባቀረበው ጥያቄ ‹ከውኃና ከመንፈስ ዳግመኛ ስለ መወለድ› ጌታችን በምሳሌ አድርጎ ያስተማረው ሲሆን አላምን ብሎ ‹እንዴት ሊሆን ይችላል?› ብሎ ሲከራከር ደግሞ ገሥጾታል፡፡ ዛሬም ድረስ ኒቆዲሞስ መልስ ከተሠጣቸው በኋላ የሚነታረኩ ተከራካሪዎች ምሳሌ ሆኖ በሊቃውንት ይጠቀሳል፡፡ እመቤታችን ድንግል ማርያምን የቅዱስ ገብርኤልን ብሥራት በሙሉ ልብ በመቀበሏ በምናመሰግናት ጊዜም ‹እንደ ዘካርያስ ሳትጠራጠሪ እንደ ኒቆዲሞስ ሳትከራከሪ ቃሉን የተቀበልሽ› እያልን መሆኑ ይህን እውነታ ያጎላዋል፡፡

ኒቆዲሞስ ወደ ክርስትና ከመጣበት መንገድ ጀምረን በዮሐንስ ወንጌል ስንከተለው ቀስ በቀስ እያደገ የመጣ የመንፈሳዊነት ደረጃን እናገኛለን፡፡ የኒቆዲሞስ ክርስትና እንደ ወጣኒ (ጀማሪ) እንደ ማዕከላዊና እንደ ፍጹም በሦስት ደረጃዎች ላይ የሚታይ ሕይወት ሆኖ በዮሐንስ ወንጌል ላይ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ እንደሚከተለው እንመልከተው፡፡

ወጣኒው (ጀማሪው) ኒቆዲሞስ

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፋሲካ በዓል በኢየሩሳሌም ሳለ ያደረገውን ተአምር ተመልክተው ብዙ ሰዎች በስሙ አምነው ነበር፡፡ ያ ወቅት ጌታችን በቃና ዘገሊላ ሠርግ ቤት ውኃን ወይን ያደረገበትና ፣ በቤተ መቅደስ ይሸጡ ይለውጡ የነበሩትን ገሥጾ ያስወጣበት ነበር፡፡ ይህንን ምልክት ተከትለው ካመኑበት ብዙ ሰዎች አንዱ ታዲያ ኒቆዲሞስ ነበር፡፡

ይህ ሰው በጌታችን ቢያምንም ባመነበት ወቅት እምነቱን በልቡ ብቻ ይዞ አቆይቶ ነበር፡፡ ከዚያም በአሳቻ ሰዓት በማታ ወደ ጌታችን መጣና ‹መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን› አለው፡፡

ኒቆዲሞስ ጌታችንን እግዚአብሔር በረድኤቱ ተአምራትን እንዲያደርጉ ከሚያስችላቸው ጻድቃን እና ነቢያት ለይቶ አላየውም ነበር፡፡ ንግግሩም ከእርሱ ጋር ምልክቱን አይተው አምነው ከነበሩት ሰዎች ቁጥር መሆኑን በሚያሳይ መንገድ ‹እናውቃለን› የሚል የብዙዎች ወኪልነት ንግግር ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ነበር እንግዲህ አምላካችን በዝርዝር ያስተማረው፡፡

ኒቆዲሞስን እንዲህ በሌሊት ያስመጣው ምንድር ነበር? ክርስቶስን በቀን በአደባባይ ሊያናግረው አይችልም ነበር? እሱ እንደሆነ በሔደበት መንገድ የሚለቀቅለት የአይሁድ አለቃ ነውና ጌታችንን ለማግኘት ሰዎች አገዱኝ ሊል አይችልም፡፡

ይህ እንግዲህ የኒቆዲሞስ የመጀመሪያው የክርስትና ደረጃ ነበር፡፡ እሱ አምላካችንን ስላደረገው ተአምር ሊያደንቀው ፈልጓል ‹እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው› ብሎ አመስግኖታል ፤ ሊከተለው ግን አልፈለገም፡፡ ሌላው ቀርቶ ከጌታችን ጋር ሆኖ ሰዎች እንዲያዩት አልፈለገም፡፡

የጌታ ተከታይ ፣ ደቀመዝሙር ሆኖ መታሰብ አልፈለገም ፣ ጉዳዩ ክብሩን የሚነካበት መሰለው፡፡ የተማረ ነውና ‹ገና ይማራል እንዴ› ብለው እንዳይንቁት ለክብሩ ሳሳ ፣ በዚያ ላይ ደግሞ ጌታችን በአይሁድ ሹማምንት ዓይን የተናቀ ነበር፡፡ እርሱ ‹ግንበኞች እንደናቁት ድንጋይ› ነበር፡፡

‹‹የተናቀ ከሰውም የተጠላ፥ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው ሰውም ፊቱን እንደሚሰውርበት የተናቀ ነው፥ እኛም አላከበርነውም።›› ይላል ነቢዩ፡፡ /ኢሳ. ፶፫፥፫/ ታዲያ የእርሱ ደቀ መዝሙር ሆኖ መታየት በዚያን ወቅት የሚያስከብር ነገር አልነበረም፡፡ ስለዚህ ፈራ ተባ እያለ በጨለማ መጣ፡፡

ወደ ክርስቲያናዊ ሕይወት የሚመጣ ሰው አንዱ ፈተናው ይኼ ነው፡፡ ክርስትናችን በሰዎች ፊት የታወቀ እንዲሆን ፈቃደኞች የማንሆን ብዙዎች ነን፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሰው ተብሎ ላለመታየት የሚሸሹ ብዙዎች ናቸው፡፡

ማዕተብ ማድረግ ፣ በቤተ ክርስቲያን አጠገብ ሲያልፉ መሳለም ፣ በአበው ትውፊት ጽዋዕ መጠጣት ወዘተ ማድረግ የሚከብዳቸው የሚጨነቁና የሚያፍሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ በሚሠሩበት መሥሪያ ቤት አካባቢ ስለ ሃይማኖታቸው ባይታወቅ የሚመርጡ፣ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሔዳቸው ባይሰማ ደስ የሚላቸው ኒቆዲሞሶች ብዙኃን ናቸው፡፡

የኒቆዲሞስ ችግር በክርስትናው ማፈሩ ብቻ አልነበረም፡፡ ክርስትና የሚያመጣበትን መዘዝ መፍራቱም ጭምር ነው፡፡ አይሁድ ‹‹እርሱ ክርስቶስ ነው ብሎ የሚመሰክር ቢኖር ከምኩራብ ይውጣ›› የሚል ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር፡፡ (ዮሐ. ፱፥፳፪) በዚህ ሕግ ምክንያት በጌታችን አምነው እንኳን ስለ እርሱ ለመመስከር የሚፈሩ ብዙዎች ነበሩ፡፡ ‹‹ከዚህም ጋር ከአለቆች ደግሞ ብዙዎች በእርሱ አመኑ፤ ነገር ግን ከምኵራብ እንዳያስወጡአቸው በፈሪሳውያን ምክንያት አልመሰከሩለትም፤ ከእግዚአብሔር ክብር ይልቅ የሰውን ክብር ወደዋልና።›› (ዮሐ. ፲፪፥፵፪)

ኒቆዲሞስ ወደ ጌታ መጥቶ መማሩ እንዲታወቅ ያልፈለገውም ለዚህ ነበር፡፡ ለክርስትናው ምንም ዓይነት ዋጋ ለመክፈል ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ ለማድነቅ እንጂ መከራን ለመቀበል አልተዘጋጀም፡፡ ይህ ዓይነቱ ችግር ሌላው የክርስቲያናዊ ሕይወት ፈተና ነው፡፡ ሐዋርያው የክርስትናችንን ዓላማ ሲገልጥ ‹‹ስለ እርሱ ደግሞ መከራን ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም፡፡›› ብሏል፡፡ (ፊል. ፩፥፳፱) ብዙዎቻችን ክርስትናችንን እንፈልገዋለን ፤ ሆኖም በክርስትናችን ምክንያት ቅንጣት መከራ እንኳን እንዲነካን አንፈልግም፡፡

በእግዚአብሔር በማመን ውስጥ ፈተናም አለ፡፡ ራሳችንን በእውነት ክርስቲያን ነኝ ብለን ለመጠየቅ ብንፈልግ አብረን መጠየቅ ያለብን በእውነት መከራ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ ወይ ማለት ጋር ነው፡፡ በእግዚአብሔር በማመናችን ምክንያት ምን የከፈልነው ዋጋ አለ? ለእርሱ ብለን የተውነው ነገር ምንድን ነው? ለእሱስ ብለን ያጣነው ነገር ይኖር ይሆን? ምንም ነገር ከሌለ ክርስትናችን ገና ያልጠነከረ ነው ማለት ነው፡፡

ማዕከላዊው ኒቆዲሞስ

ፈሪሳዊያንና የካህናት አለቆች ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይዘውት እንዲመጡ ሎሌዎች ላኩአቸው፡፡ እነዚህ ሎሌዎች ጌታችንን ይዘው እንዲመጡ ቢላኩም በጌታችን ጣዕመ ትምህርት ተደንቀው ተመስጠው ሲማሩ ውለው ባዶ እጃቸውን ተመለሱ፡፡
አይሁድ ‹ያላመጣችሁት ስለ ምንድን ነው?›› ብለው ቢጠይቋቸው ‹‹እንደዚህ ሰው ከቶ ማንም ተናግሮ አያውቅም›› ብለው መለሱ፡፡ ይህን ጊዜ አይሁድ ተቆጥተው ሎሌዎቹን ‹‹እናንተ ደግሞ ሳታችሁ? ከአለቆች ወይም ከፈሪሳውያን መካከል በእርሱ ያመነ ሰው የለም፡፡ ሕዝቡም ያመነበት ሕግ የማያውቅ ርጉም ስለሆነ ነው›› ብለው ገሠጹአቸው፡፡ እናንተ ያመናችሁት ባለማወቃችሁ ነው ፤ ከእኛ ከአዋቂዎቹ ማን በእሱ አመነ? ብለው ሊያሸማቅቋቸው ሞከሩ፡፡

ይህን ሁሉ ሲሆን የማታው ተማሪ የአይሁድ መምህር ኒቆዲሞስ እዚያ ቆሞ ነበር፡፡ ከአለቆች መካከል በጌታ ያመነ የለም ሲባል እየሰማ ነው፡፡ አሁን ክርስትናው ልትፈተን ነው፡፡ ደፍሮ እኔ አምኜአለሁ ብሎ መናገር ባይችልም ፈራ ተባ እያለ እንዲህ አለ ‹‹ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን? አላቸው።›› እነሱ በተናገሩት ብቻ ለምን ትፈርዳላችሁ? እሱን ሳትሰሙ መፍረድ ተገቢ ነው ወይ? ማለቱ ነበር፡፡

አይሁድ እንደ ሎሌዎቹ ሁሉ ኒቆዲሞስን ማቃለል እንዳይችሉ የተከበረ መምህር ሆነባቸው፡፡ ስለዚህ ‹‹አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንዳይነሣ መርምርና እይ አሉት። እያንዳንዱም ወደ ቤቱ ሄደ።›› ጌታችን ከገሊላ ናዝሬት መምጣቱን በመጥቀስ መሲህ ከገሊላ አይነሣም ብለው ሊያስተባብሉ ሞከሩ፡፡ ይህ ግራ መጋባት በሐዋርያው ናትናኤልም የታየ ነበር እርሱ ‹‹ከናዝሬት መልካም ነገር ይወጣልን?›› ብሎ የጠየቀው መሲሁ ከይሁዳ ቤተ ልሔም እንደሚነሣ የተነገረውን ትንቢት በማየት ነበር፡፡

ጌታችን የተወለደው ከቤተ ልሔም ነው ያደገው ግን በገሊላ ናዝሬት በመሆኑ ነው ይኼ ሁሉ ውዥንብር፡፡ ኒቆዲሞስ ክርስትናውን በሌሊት ፈርቶ ጀመረ፡፡ አሁን ሙሉ በሙሉ ክርስቲያን ነኝ ብሎ መመስከርና መግለጥ ባይችልም ቢያንስ አይሁድ ከአለቆች ማን በእርሱ አመነ? ብለው ሲዘብቱ ቢያንስ ድምፁን ለማሰማት ሞከረ፡፡ በጥያቄ አስጨንቆም በዚያች ዕለት ስብሰባውን በተነው፡፡

ፍጹማዊው ኒቆዲሞስ

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል መከራ ዓለምን የማዳን ሥራውን ፈጸመ፡፡ በዚህ የመከራ ወቅት በዋለበት የዋሉ ባደረበት ያደሩ ደቀ መዛሙርቱ ከዮሐንስ በቀር በፍርሃት ተበተኑ፡፡ ነፍሱን ከሥጋው ተለይቶ ከመስቀሉ ሲወርድም አንድም ሐዋርያ አብሮት አልነበረም፡፡ በዚህ ወቅት ኒቆዲሞስ እንደ ቀድሞው ሌሊት እስኪሆን አልጠበቀም፡፡ መቶ ንጥር የሚያህል የከርቤና የእሬት ቅልቅል ይዞ መጣ ከአርማትያው ዮሴፍ ጋር ሆነው የጌታችንን ሥጋ ወሰዱ፡፡ እንደ አይሁድ የአገናነዝ ልማድ ከሽቱ ጋር በተልባ እግር ልብስ ከፈኑት፡፡

ሲገንዙት እያለቀሱ ነበር ‹‹ሞትከኑ መንሥኤሆሙ ለሙታን ፤ ደከምከኑ መጽንኤሆሙ ለድኩማን›› ‹‹ሙታንን የምታስነሣ ሆይ ሞትክን? ደካሞችን የምታጸናቸው ሆይ ደከምክን?›› እያሉ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ጌታችን በመለኮቱ ሕያው እንደመሆኑ አነጋገራቸው፡፡ በነገራቸው መሠረት ‹‹ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት…›› የሚለውን በኪዳን ወቅት የምናደርሰውን ዓለም አቀፋዊ ጸሎት እያደረሱ ገነዙት፡፡

ኒቆዲሞስ ሲፈራ ፣ ቀስ እያለ ሲናገር የነበረውን ክርስትናውን በአደባባይ ገለጠ፡፡ ‹‹ልቡ ለጻድቅ ውኩል ከመ አንበሳ›› ‹‹ጻድቅ ግን እንደ አንበሳ ሳይፈራ ይኖራል ›› እንዲል ጠቢቡ በጌታ የደረሰ መከራ ቢደርስብኝ ሳይል ሥጋውን ተሸክሞ ገነዘ፡፡ ከምኩራብ ያስወጡኛል ብሎ የፈራው ኒቆዲሞስ ቤተ ክርስቲያን እንዳለች ስለተረዳ በድፍረት ክርስትናውን መሰከረ፡፡ ከሦስቱ የኒቆዲሞስ ክርስትና ደረጃዎች እኛ በየትኛው ላይ ነን? ስለ ሃይማኖታችንስ በየትኛው ደረጃ እንመሰክራለን፡፡ በጨለማ ነው? ፈራ ተባ እያልን ነው ? ወይንስ ያለ ፍርሃት?

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
[email protected]
"ውኃ ሽቅብ አይፈስስም" የሚል አባባል አለ:: ዛሬ ግን ውኃ ሽቅብ ፈሰሰ:: ፈጣሪም በውኃ ተጠመቀ::

ዛሬ ውኃ በውኃ ተጠመቀ:: "የሕይወት ውኃ እኔ ነኝ" ያለው ጌታ በዮርዳኖስ ውኃ ተጠመቀ::

ዮርዳኖስ የንዕማንን ለምፅ ያነፃ ወንዝ ነበር:: ዛሬ ሊጠመቅ ወደ እርሱ የወረደው ግን "ንጻ" ብሎ ለምፃምን በቃሉ የሚያነጻ ጌታ ነበር:: ለጌታም ጌታ አለው:: ዮርዳኖስ አፍ የላትም እንጂ ንጹሑ ጌታ ወደ እርስዋ ሲገባ እርስዋ ንዕማን ሆና "ጌታዬ ሆይ አንጻኝ" ልትል ምንም አልቀራት::

"አንቺ ባሕር የሸሸሽ፥ አንቺም ዮርዳኖስ ወደ ኋላሽ የተመለስሽ፥ ምን ሆናችኋል?" መዝ 113:5 እንዳለ ነቢዩ ዛሬ የመጣባት እንግዳ እንደ ንዕማን የሚነጻ ሳይሆን ከዮርዳኖስ ውኃ ይልቅ ግን እርሱ ንጹሕ ነበር::

ዮርዳኖስ በኢያሱ ዘመን የሊቀ ካህናቱ እግር ሲረግጠው የተከፈለ ወንዝ ነበር:: በኤልያስና በኤልሳዕ መጎናጸፊያም ሁለት ጊዜ ተከፍሎ ነበር::

ዛሬ የሐዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት ክርስቶስ ወደ ዮርዳኖስ ሲወርድ የዮርዳኖስ ልብ በፍርሃት ተከፈለ:: በዕለተ ሰኑይ ውኃን ለሦስት ከፍሎ ሐኖስ ጠፈር ውቅያኖስ ያደረገው አምላክ ወደ እርስዋ ሲመጣ ትንሽዋ የዮርዳኖስ ወንዝ ተጨነቀች:: በውኃ ላይ ሰፍፎ የነበረው መንፈስ ቅዱስ በርግ አምሳል ሲመጣባት ዮርዳኖስ ይኼን ሁሉ መሸከም አትችልምና ተጨነቀች::

"አቤቱ፥ ውሆች አዩህ፥ ውሆችም አይተውህ ፈሩ፤ ጥልቆች ተነዋወጡ፥ ውኆችም ጮኹ" መዝ. 77:16

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ጥምቀት 2014 ዓ.ም.
አዲስ አበባ
ፎቶ :- በዮርዳኖስ ወንዝ

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ጸልዩ! በኮሜንት መስጫው ሥር ዋጋን በምድር የሚያስቀር ውዳሴም ሆነ "ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ" (ኤፌ 4:29)

ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like, Subscribe እና Share ያድርጉ :-

የፌስቡክ ገጽ :- https://www.facebook.com/officialHenokhaile/
የቴሌግራም ቻናል : https://www.tg-me.com/deaconhenokhaile
የዩቲዩብ ገጽ: https://www.youtube.com/channel/UCOaVsWC05aUjeqIEW3fWj7g
+ አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? +

ልጅ እናቱን ‹አንቺ ሴት› ብሎ መጥራት በእኛ ሀገር ባሕልና በብዙ ቋንቋዎች ባሕል ፈጽሞ ያልተለመደ ነገር ነው፡፡ በተለይ በአደባባይ ሲሆን ይከብዳል:: ጌታ እናቱን ካልጠፋ ስም ለምን እንዲህ ብሎ ጠራት?

አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽ አከራካሪ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ የሚዳኘው በተጻፈበት ቋንቋ (Source language) እንጂ በተተረጎመበት ቋንቋ ባሕል አይደለም፡፡ ይህ አነጋገር በአይሁድ ዘንድ እና የዮሐንስ ወንጌል ላይ በተጻፈበት በግሪክ ቋንቋ የሚሠጠው ትርጉም በእኛ ዘንድ ካለው ትርጉም የተለየ ነው፡፡

በግሪኩ ‹‹አንቺ ሴት›› (gune = woman") ተብሎ የሚጻፍ ሲሆን ጌታችን እመቤታችንን ‹‹አንቺ ሴት›› ብሎ በጠራበት ሥፍራ ግን በግሪኩ ‹አንቺ ሴት› የሚለው ንባብ የተጻፈው ‹አንቺ ሴት ሆይ› (gynai "Dear woman") በሚል የአክብሮት አጻጻፍ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አነጋገር ደግሞ ነገሥታት ለንግሥቶቻቸው በሚጽፉአቸው ደብዳቤዎችም ላይ ጭምር ይጻፍ የነበረ እንደሆነ የቋንቋው ባለቤቶች የሆኑት ግሪካውያን አገናዝበው ጽፈዋል፡፡ ለምሳሌ አውግስጦስ የተባለው ንጉሥ ለግብፃዊቷ ንግሥት ለክሊዮፓትራ በጻፈው ደብዳቤ ላይ የተጠቀመው ቃል የግሪኩን ‹gynai› /ጋይናይ /አንቺ ሴት ሆይ/ የሚለውን የአክብሮት አጠራር እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡

ጌታችን በቃና ሰርግ ቤት ‹አንቺ ሴት› ብሎ የተናገረው ንግግር የቁጣ አነጋገር ነው የሚሉ ሰዎችን ሃሳብ እንዳንቀበል የሚያደርገን ሌላው ምክንያት ደግሞ ጌታችን ‹አንቺ ሴት› የሚለውን አጠራር ለእናቱ የተናገረው በቃና ሰርግ ቤት ብቻ አለመሆኑ ነው፡፡ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እያለ በመጨረሻው ሰዓት ከመስቀሉ ሥር ቆማ መከራውን እያየች በጽኑ ኀዘን ላይ እያለች ‹‹አንቺ ሴት እነሆ ልጅሽ›› በማለት ዮሐንስን ለእርስዋ እርስዋን ለዮሐንስ ሠጥቷል፡፡

በልጅና በእናት መካከል ባለው ሥነ ልቡናዊ ትስስር ምክንያት ለእናት የልጅዋን ስቃይ ቆሞ መመልከት እጅግ ከባድ ስቃይን ያስከትልባታል፡፡ እመቤታችን እያንዳንዱ ችንካር በተወደደ ልጅዋ እጅ ውስጥ ሲቸነከር ልብዋ በኀዘን ይቸነከር ነበር፡፡ ታዲያ ‹አንቺ ሴት› የሚለው አነጋገር የቁጣ አነጋገር ከሆነ ጌታችን በመስቀል ላይ ሆኖ ‹በነፍስዋ የኀዘን ሰይፍ እያለፈባት› ያለችውን እናቱን እንዴት ይቆጣል?

በሰርግ ቤት ውስጥስ ስለጠየቀችው ተቆጣ ይባል ፤ በመስቀል ሥር የልጅዋን ስቃይ በዝምታ ስትመለከት የነበረችን እናት ልጅዋ በስቃዩ መካከል ትንፋሹን ሰብስቦ ‹‹ተቆጣት›› ብሎ ሊነገር እንዴት ይችላል? በስተግራው የተሰቀለው ወንበዴ ‹አንተስ ክርስቶስ አይደለህም› ብሎ ሲሰድበው መልስ ያልሠጠ ‹ከቁጣ የራቀ› አምላክ በእርሱ ስቃይ እየተሰቃየች ያለችውን እናቱን እንዴት ይቆጣል? (ሉቃ. ፳፫፥፴፱) ይህ ፈጽሞ የማይታሰብ ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጽሐፍ ቅዱስ ከእናቱ ጋር በተነጋገረበት ስፍራ ‹እናቴ› ብሎ በመጥራት ወይም ‹ማርያም› በማለት ፈንታ ‹አንቺ ሴት› የሚለውን አጠራር መጠቀሙ እመቤታችን በኦሪት ዘፍጥረት በተጠራችበት ስም ለመጥራት እና እርስዋ ትንቢት የተነገረላት ዳግሚት ሔዋን ፣ ጌታችንም የዕባቡን ራስ የሚቀጠቅጠው ዘርዋ መሆኑን የሚያስረዳን ነው፡፡

በሊቃውንት ዘንድ የወንጌል መቅድም (Protevangelium / Protogospel) ወይም ‹የመጀመሪያው የነገረ ሥጋዌ ትንቢት› በመባል የሚታወቀው ‹‹በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ።›› የሚለው ትንቢት በእርስዋ መፈጸሙን ከምንረዳበት መንገድ አንዱ ጌታችን ‹አንቺ ሴት› ብሎ በመጥራቱ ነው፡፡ (ዘፍ. ፫፥፲፭)

በዕለተ አርብ በዕባብ የተመሰለው ዲያቢሎስ የጌታችንን ‹ሰኮና› በአይሁድ አድሮ ሲቀጠቅጥ ዋለ፡፡ ‹ዘርዋ› የተባለው ጌታም የዕባቡን ራስ እንዲሁ በመስቀሉ ቀጠቀጠው፡፡ በዚህ ወቅት እናቱን ደግሞ ‹አንቺ ሴት› ብሎ ጠራትና በትንቢቱ ላይ ያለችው ‹ሴቲቱ› እርስዋ መሆንዋን አስረዳን፡፡

የጻፈውን መተርጎም ልማዱ የሆነው ዮሐንስም ይህንን ጉዳይ የበለጠ ግልጽ በሚያደርግ ሁኔታ የሴቲቱን ፣ የልጅዋን እና የቀደመውን ዕባብ ማንነት በአንድ ምእራፍ ላይ አብራርቶ በራእዩ ጽፎልናል፡፡ ‹‹ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች። ... ዘንዶውም (እርሱም የቀደመው ዕባብ) በሴቲቱ ላይ ተቈጥቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ›› በማለት የዘፍጥረቱን ትንቢት በመተርጎም ሴቲቱ በእርግጥም ‹አሕዛብን በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ወንድ ልጅ የወለደችው› እመቤታችን መሆንዋን አስረድቶአል፡፡ (መዝ. ፪፥፱) ስለዚህ ጌታ ‹አንቺ ሴት› ማለቱ ጾታን ለማመልከት ብቻ ሳይሆን እመቤታችን የትንቢቱ ፍጻሜ መሆንዋን የሚያስረዳ የክብር አነጋገር ነው፡፡ (ራእ. ፲፪፥፩-፲፰)

እንዲሁም ለአዳም ሔዋን በተሠጠችው ጊዜ ‹‹ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል።›› ማለቱ (ዘፍ. ፪፥፳፫) ሴት የሚለውን ቃል ትርጉም ጾታን ከመግለጽ በላይ ‹ሥጋሽ ከሥጋዬ አጥንትሽም ከአጥንቴ› የሚል የእኔነት ትርጉም ያለው መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ልዩነቱ የመጀመሪያው አዳም ከጎኑ ሔዋንን ያስገኘ ሲሆን ሁለተኛው አዳም ግን ከሁለተኛዋ ሔዋን የተገኘ ነው፡፡ ሆኖም ሁለተኛው አዳምም ከጎኑ በፈሰሰው ውኃ የሁላችንን እናት ጥምቀትን (ቤተ ክርስቲያንን) አስገኝቷል፡፡

- ከአንቺ ጋር ምን አለኝ

‹‹ከአንተ / ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?› የሚለው አነጋገር በመጽሐፍ ቅዱስ በብሉይ ኪዳን ስድስት ቦታ ፣ በሐዲስ ኪዳን ደግሞ በአምስት ቦታዎች ተጽፎ የምናገኘው አነጋገር ነው፡፡ ይህ ዐረፍተ ነገር በየተጻፈባቸው አገባቦች (contexts) ሁለት ዓይነት ትርጉም የሚሠጥ ሆኖ ይገኛል፡፡ የመጀመሪያው አገባብ አለመግባባትን የሚገልጽ አነጋገር ሲሆን ፤ ሁለተኛው አገባብ ደግሞ አክብሮትን ወይም ሰላም ጠያቂነትን የሚያሳይ አነጋገር ነው፡፡

አለመስማማትን የሚያሳይ የተግሣጽ ንግግር ሆኖ የምናገኘው በነቢዩ ኤልሳዕ ታሪክ ነው፡፡ የእስራኤል ንጉሥ ኢዮራም ከይሁዳ ንጉሥ ከኢዮሳፍጥ ጋር ወደ ነቢዩ ኤልሳዕ መፍትሔ ለመጠየቅ መጥቶ ነበር፡፡ ኢዮራም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገርን አድርጎ ስለነበር ኤልሳዕ ‹‹እኔ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? ወደ አባትህና ወደ እናትህ ነቢያት ሂድ›› ብሎ መልሶለት ነበር፡፡ ኢዮራም ኤልሳዕን ለማነጋገር ሲሞክርም ኤልሳዕ በቁጣው ጸንቶ ‹‹አብሮህ ያለውን የይሁዳን ንጉሥ ባላፍር ኖሮ አንተን ባልተመለከትሁና ባላየሁ ነበር፡፡›› ብሎታል፡፡ (፪ነገሥ. ፫፥፲፫)

በዚህ ታሪክ ውስጥ በግልጽ ‹ከአንተ ጋር ምን አለኝ?› የሚለው ቃል ‹ከአንተ ጋር ምን ኅብረት አለኝ?› በሚል አገባብ ተቀምጧል፡፡ በተመሳሳይም እግዚአብሔር የጢሮስ ፣ የሲዶናና የፍልስጤም ግዛትን በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ ስላደረሱት በደል እንደሚፋረዳቸው በተናገረበት አንቀጽ ‹‹ከእናንተ ጋር ለእኔ ምን አለኝ? በውኑ ብድራትን ትመልሱልኛላችሁን? ፈጥኜ ብድራታችሁን በእናንተው ላይ እመልሳለሁ›› በማለት ተናግሯል፡፡ በዚህም ስፍራ እንዲሁ ይህ አነጋገር ከቁጣ ጋር ተነግሮ ይገኛል፡፡ (ኢዮ. ፫፥፬)
ሁለተኛው አገባብ ደግሞ ‹ከአንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ?› የሚል ትርጉም የሚሠጠው አገባብ ነው፡፡ ንጉሥ ዳዊት ለእርሱ የተቆረቆሩ የጽሩያ ልጆች የሰደበውን ሳሚን ‹እንምታው ፣ እንግደለው› ሲሉ ‹‹እናንተ የጽሩያ ልጆች፥ እኔ ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? እግዚአብሔር፦ ዳዊትን ስደበው ብሎ አዝዞታልና ይርገመኝ ለምንስ እንዲህ ታደርጋለህ? የሚለው ማን ነው?›› ብሎ ከልክሎአቸዋል፡፡ (፪ሳሙ. ፲፮፥፲) ተሳዳቢው ሳሚ መጥቶ ከእግሩ ሥር ተደፍቶ ይቅርታ ሲጠይቅም ዳግመኛ ‹‹እግዚአብሔር የቀባውን ሰድቦአልና ሞት ይገባዋል›› አሉ፡፡

ይህን ጊዜ ዳዊት ‹እናንተ የጽሩያ ልጆች፥ እኔ ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? ዛሬ ስለ ምን ጠላቶች ትሆኑብኛላችሁ? ዛሬስ በእስራኤል ዘንድ ሰው ሊሞት ይገባልን? ዛሬስ በእስራኤል ላይ እንደ ነገሥሁ አላወቅሁምን?›› (፪ሳሙ. ፲፱፥፳፪)
በእነዚህ የንጉሡ ንግግሮች ውስጥ ‹ከእናንተ ጋር ምን አለኝ?› የሚለው ቃል በአክብሮት የተነገረ ባይሆንም መልእክቱ ግን ‹ምን ጠብ አለኝ› ማለት መሆኑን ከአገባቡ መረዳት ይቻላል፡፡ ምናልባት የመጨረሻው አገባብ ቁጣ ያዘለ ቢመስልም እንኳን እየተናገረ ያለው ለእርሱ ከእርሱ በላይ ለተቆረቆሩት ታማኝ ወታደሮቹ ጋር መሆኑን መርሳት የለብንም፡፡ እርሱም ‹ከእናንተ ጋር ምን አለኝ?› ያለውን ‹ለምን ጠላቶች ትሆኑብኛላችሁ?› ብሎ በማብራራት የንግግሩ ፍሬ ሃሳብ ‹ከእናንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ› እንደሆነ አሳይቶአል፡፡

ሌላው ማሳያ ደግሞ የግብፅ ንጉሥ ኒካዑ ንግግር ነው፡፡ ኒካዑ ካልተዋጋሁህ ብሎ ለመጣበት ለኢዮስያስ ፡- ‹‹የይሁዳ ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? በምዋጋበት በሌላ ቤት ላይ ነው እንጂ በአንተ ላይ ዛሬ አልመጣሁም እግዚአብሔርም እንድቸኵል አዝዞኛል ከእኔ ጋር ያለው እግዚአብሔር እንዳያጠፋህ ይህን በእርሱ ላይ ከማድረግ ተመለስ ብሎ መልእክተኞችን ላከበት።›› (፪ዜና ፴፭፥፳፩) ይህ አነጋገር በትሕትና እና ‹ሆይ› በሚል የአክብሮት አጠራር የቀረበ ነው፡፡ በግልጽ ‹ልዋጋ የተነሣሁት ከሌላ ጋር ነው ፤ ከአንተ ጋር ምን ጠብ አለኝና ነው የምዋጋው!› ነው ያለው፡፡ በእውነቱ ‹ከአንተ ጋር ምን አለኝ?› ማለት ‹ከአንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ?› ማለት መሆኑን ለማስረዳት ከዚህም የተሻለና ግልጽ ታሪክ የለም፡፡ ምክንያቱም ኢዮስያስ የተነሣው ለጠብ ነው፡፡ ኒካዑም በአክብሮት የነገረው ‹ከአንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ?› ብሎ ነው፡፡

እንደተጨማሪ ማሳያ የምናገኘው ደግሞ የእግዚአብሔር ሰው ኤልያስን በቤትዋ የተቀበለችው የሰራፕታዋ መበለት የተናገረችው ነው፡፡ ይህች ሴት ኤልያስ በቤትዋ በመገኘቱ በቤትዋ ያለው ምግብ ተባርኮ በረሃብ ዘመን እየተመገቡ ከከረሙ በኋላ ልጅዋ በጠና ታመመ፡፡ ይህን ጊዜ ሴቲቱ ወደ ኤልያስ ቀርባ ፡-

‹‹የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? ኃጢአቴንስ ታሳስብ ዘንድ፥ ልጄንስ ትገድል ዘንድ ወደ እኔ መጥተሃልን? አለችው።›› (፩ነገሥ.፲፯፥፲፰)
ይህች ሴት ለነቢዩ በአክብሮት ያለችው ‹ከአንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ?› ነው፡፡ የቁጣና የተግሣፅ ንግግር ነው እንዳይባል መቼም ‹‹የእግዚአብሔር ሰው ሆይ...›› ብሎ የሚጀምር ቁጣ የለም፡፡ እንዲያውም በአንድ ሰው ስንቆጣ ማዕረጉን ትተን እንናገራለን እንጂ ማዕረግ ጠብቆ ቁጣ የለም፡፡

ወደ ሐዲስ ኪዳን ስንመጣ ‹ከአንተ ጋር ምን አለኝ?› የሚለውን ቃል የተናገሩት ዛሬ በወዳጆቻቸው አድረው ‹ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ማለት ስድብ ነው› እያሉ የሚበጠብጡን አጋንንት ናቸው፡፡ ከአዋቂ ጋር እንደ አዋቂ ፤ ካላዋቂ ጋር እንደ አላዋቂ ሆኖ ማደናቆር የአጋንንት ልማድ ነውና እነሱ በሚገባ ትርጉሙን ተረድተው እየተንቀጠቀጡ ለጌታ የተናገሩትን የአክብሮት አነጋገር ለእመቤታችን ሲሆን ትርጉሙ ሌላ ነው እያሉ ያውካሉ፡፡
‹‹እነሆም። ኢየሱስ ሆይ፥ የእግዚአብሔር ልጅ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ጊዜው ሳይደርስ ልትሣቅየን ወደዚህ መጣህን? እያሉ ጮኹ።›› (ማቴ. ፰፥፳፱)

‹‹እርሱም፦ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄአለሁ፥ የእግዚአብሔር ቅዱሱ ብሎ ጮኸ።›› (ማር. ፩፥፳፬)

‹‹የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? እንዳታሠቃየኝ በእግዚአብሔር አምልሃለሁ አለ፤›› (ማር. ፭፥፯)

‹‹ ተው፥ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄሃለሁ፥ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱሱ አለ።›› (ሉቃ. ፬፥፴፬)
‹‹ኢየሱስንም ባየ ጊዜ ጮኾ በፊቱ ተደፋ በታላቅ ድምፅም። የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? እንዳትሣቀየኝ እለምንሃለሁ አለ›› (ሉቃ. ፰፥፳፰)

ምንም እንኳን አጋንንትን እንደ ማስረጃ በመጥቀስ ክብር ባንሠጣቸውም ‹የጠላት ምስክርነት የታመነ ነው› እንዲል (ትምህርተ ኅቡዓት/ትር.) የአጋንንቱ ንግግር ‹ከአንተ ጋር ምን አለኝ› የሚለው ቃል በአክብሮት ሊነገር የሚችል ‹ምን ጠብ አለኝ› የሚል ትርጓሜ ያለው መሆኑን በግልጽ ያስረዳል፡፡

ምክንያቱም ‹ከአንተ ጋር ምን አለን› ከማለታቸው ጋር ‹ኢየሱስ ሆይ ፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ ፣ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ ፣ የእግዚአብሔር ቅዱሱ› የሚል የአክብሮት ንግግር ተናግረዋል፡፡ ከዚያም ‹እንዳታሠቃየኝ እለምንሃለሁ› የሚል ልመና ተከተለ፡፡ ልመናውም ከእግሩ ሥር እስከ መደፋት ድረስ የደረሰ ነበር፡፡ መቼም ከእግር ሥር ተደፍቶ የቁጣ ንግግር መናገር የማይታሰብ ነው፡፡

በአጠቃላይ ከላይ ባየነው የአገባብ ዝርዝር ‹ከአንተ ጋር ምን አለኝ?› ለሚለው ንግግር የሚያመዝነው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጉም ‹ከአንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ› የሚል ነው፡፡ በቃና ዘገሊላ ሰርግ ቤት ጌታችን ለእናቱ የተናገረው ‹ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?› የሚለው አነጋገርም ከአገባቡ እንደምንረዳው ሌሎች ስለ እርሱ በፍርሃት የተናገሩትን የአክብሮት የተነገረ ሲሆን ትርጉሙም ‹የጠየቅሽኝን እንዳላደርግልሽ የሚከለከለኝ ከአንቺ ጋር ምን ጠብ አለኝ?› የሚል ነው፡፡ ይህን የሚያስረዳን መልሱ የእምቢታ ቢሆን ኖሮ አንደኛ እመቤታችን ልመናዋን ቀጥላ ‹እባክህን ልጄ ሆይ› ብላ ለማሳመን ትሞክር ይሆናል እንጂ ‹የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ› ብላ ለአገልጋዮቹ በልበ ሙሉነትና በእርግጠኝነት ትእዛዝ ልትሠጥ አትችልም ነበር፡፡

ሁለተኛ ደግሞ ጌታችን ከዚያ በኋላ ጋኖቹን ሙሉ ብሎ ተአምራቱን አያደርግም ነበር፡፡ እንዲያውም ጌታችን ‹ከአንቺ ጋር ምን አለኝ ጊዜዬ ገና አልደረሰም› ያላት በቁጣና በእንቢታ ከሆነ ለአገልጋዮቹ ‹የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ› ብላ መናገርዋ የበለጠ ቁጣውን የሚያነድ ነበር የሚሆነው፡፡ ለእርስዋ እንቢ እያላት ቁጣውን ከምንም ሳትቆጥር ሌሎች ሰዎችን ማዘዝዋ የበለጠ አያስቆጣም ወይ ሊባል ይችላል? ይህ ሁሉ የሚያሳየን ጌታችን አንዳች የቁጣ ንግግር አለመናገሩን ነው፡፡

አባ ጊዮርጊስም የጌታችን መልስ የጠብ ሳይሆን እንዲያውም የጥልቅ ፍቅር መሆኑን ሲገልጽ ‹‹በልቡ ውስጥ ለተከማቸ ፍቅሯ በሚሻል /በሚመጥን/ ነገር መለሰላት›› ‹‹ወአውስኣ ዘከመ ይኄይስ ለዘዝጉብ ፍቅረ ዚኣሃ ውስተ ልቡ›› ብሏል፡፡ (መጽሐፈ ምሥጢር) ስለዚህ ‹ከአንቺ ጋር ምን አለኝ› የሚለውን ንግግር የቁጣ ንግግር አድርጎ መተርጎም ጥቅሱን ከአገባቡ የወጣ ጥቅስ (Text out of context) ያደርገዋል፡

+ ጌታችን እናቱን ተቆጥቷት ይሆንን? +
2025/07/14 03:08:08
Back to Top
HTML Embed Code: