Telegram Web Link
ስሜት

ስሜት የብረት ድስት ነው፣ ሲጥዱት ቶሎ ይግላል፣ ሲያወርዱት ቶሎ ይቀዘቅዛል፤ እውነት የሸክላ ድስት ነው፣ ቶሎ አይግልም፣ ቶሎ አይበርድም። ስሜት የእንጀራ እናት ጡጦ ነው፣ እውነት ግን የሚያጠግብ የወተት ጋን ነው። ስሜት ችግኝ ነው፣ እውነት ግን የሚያስጠልል ዛፍ ነው። ስሜት መጣሁ ብሎ የሚሄድ የመስከረም ዝናብ ነው ፣ እውነት ግን የሚያጠግብ የነሐሴ ጠል ነው። ስሜት የአሁን ንጉሥ ነው፣ እውነት ግን ነገም የሚኖር ኃይል ነው። ስሜት የርችት መብራት ነው፣ እውነት ግን ግለቱ የሚጨምር የፀሐይ ብርሃን ነው። ስሜት ቀን ነው፣ ማታ ለመሆን ይቸኩላል፤ እውነት ሌሊት ነው፣ ወደ ቀን ይጓዛል። ስሜት ሁሉን የሚያረክስ ነው፣ እውነት ሁሉን የሚቀድስ ነው። ስሜት ሮጦ የሚደክም ነው፣ እውነት እያዘገመ የሚደርስ ነው። ስሜት ተሳዳቢ ነው፣ እውነት ግን አሸናፊ ነው። ስሜት እገሌ የሚል ጠቋሚ ነው ፣ እውነት ግን እኔ የሚል ተነሣሒ ነው። ስሜት ሰጥቶ የሚቆጭ ነው፣ እውነት ግን ሰጥቶ የሚደሰት ነው። ስሜት የእኔ ቃል የእግዜር ቃል የሚል ነው፣ እውነት ግን የእግዚአብሔርን የሚያስቀድም ነው። ስሜት ግልብ ነው ፣ እውነት ግን እውቀትን ያደላደለ ነው። ስሜት ቢሞትም ሰማዕት አያሰኝም፣ እውነት ግን የጽድቅ አክሊል አላት። ስሜት ኢየሱስ ጌታ ነው እያለ በሥራው ያዋርደዋል፣ እውነት ግን ክርስቶስን በሕይወቱ ያከብረዋል። ስሜት በሬ ይነዳል ፣ እውነት ግን ራሱን ይሰጣል።

ስሜት ግሎ ያጋግላል፣ እውነት ግን ሰምቶ ይጋግራል። ስሜት የቅጠል እሳት ነው፣ አያበስልም ኋላም አመድ የለውም ፤ እውነት ግን የሚያበስል ቀጥሎም የሚያሞቅ ፍም ያለው ነው። ስሜት ጊዜያዊ እብደት ነው፣ እውነት ግን መጥኖ መኖር ነው። ስሜት ተናግሮ የሚያስብ ነው፣ እውነት ግን አስቦ የሚናገር ነው። ስሜት ከውድቀቱ የሚማር ነው፣ እውነት ግን በነጻ የሚማር ነው። ስሜት ወደድሁ ሲል ያብዳል፣ እውነት ግን ፍቅር ለዘላለም መሆኑን ያምናል። ስሜት በአሳብ ይሰጥና ቆይቶ ይከለክላል፣ እውነት ግን “የእኔ ድጋፍ የሚያስፈልገው ለማን ነው ?” ይላል። ስሜት ጭብጨባ ምሱ ነው ፣ እውነት ግን ጭብጨባን የሚጠየፍ ነው። ስሜት ፍሬን የለውምና ይጋጫል፣ እውነት ግን ማብረጃ አለው። ስሜት ኃይል ሲሆን ራሴ መሪ ካልሆንሁ ይላል ፤ እውነት ግን “እግዚአብሔር ሆይ ምራኝ” ይላል። ስሜት ቊጣና ስድብ የሚባሉ ልጆች አሉት፣ እውነት ግን እውቀትና ተግባር የሚባሉ ልጆች አሉት።

ስሜት ከሚያደርገው የሚያወራው ይበዛል፣ እውነት ግን ሥራው ይናገር ብሎ ያከናውናል። ስሜት እንደ ማር ይጣፍጣል፣ ከደቂቃ በኋላ እንደ እሬት ይመራል፤ እውነት ግን መጀመሪያ መራራ ቀጥሎ ጣፋጭ ነው። ስሜት ሲሰበክ በመነንሁ ይላል፣ ቀጥሎ ይዘፍናል፤ እውነት ግን መስቀሉን ለመሸከም ጎንበስ ይላል። ስሜት አሁን አመስጋኝ አሁን ተራጋሚ ነው፣ እውነት ለሁለቱም አይቸኩልም። ስሜት ከነቆቡ የሚዘልል ነው፣ እውነት ግን ዓላማውን የሚያከብር ነው። ስሜት ልጅ ያደርጋል፣ እውነት ግን ትልቅ ያደርጋል። ስሜት ጦርነትን ይለኩሳል፣ ማብረድ ግን አይችልም፤ እውነት ግን ለሰላም ዋጋ ይሰጣል። ስሜት “ካፈርሁ አይመልሰኝ” ይላል፣ እውነት ግን ገና ለመታረም ይኖራል። ስሜት ተግሣጽ ጠላቱ ነው። እውነት ግን ምከሩኝ የሚል ነው። ስሜት እስኪገባ የሚቸኩል፣ ከገባ በኋላ ልውጣ የሚል ነው፤ እውነት ግን ዋጋውን ተምኖ የሚገባ፣ በትዕግሥትም ነገሩን የሚፈጽም ነው። ስሜት ራሳችንን የምንታዘብበት ነው፣ እውነት ግን ራሳችንን የምናርምበት ነው። 

ጌታ ሆይ በስሜት ሳይሆን በእውነት እንድመላለስ እርዳን።

ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
​​ረቢ ወዴት ትኖራለህ

ከመጥምቁ ዮሐንስ ተማሪዎች መካከል ሁለቱ "የእግዚአብሔር በግ እነሆ" የሚለውን የመምህራቸውን ስብከት ሰምተው ጌታን ተከተሉት::

"ኢየሱስም ዘወር ብሎ ሲከተሉትም አይቶ፦ ምን ትፈልጋላችሁ? አላቸው። እነርሱም፦ ረቢ፥ ወዴት ትኖራለህ? አሉት፤ መጥታችሁ እዩ፡ አላቸው። መጥተው የሚኖርበትን አዩ፥ በዚያም ቀን በእርሱ ዘንድ ዋሉ፤ አሥር ሰዓት ያህል ነበረ" ዮሐ. 1:37-39

ጌታን ተከትለው የሚኖርበትን ካዩት ደቀ መዛሙርት አንደኛው ስም እንድርያስ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የራሱን ስም በወንጌሉ ላይ እኔ የማይጽፈውና ቤተ ክርስቲያን ግን የራሱን ነገር ሲገልፅ በሚጠቀመው ቋንቋ የምታውቀው ወንጌላዊው ዮሐንስ ነበረ::

"ረቢ፥ ወዴት ትኖራለህ? አሉት፤ መጥታችሁ እዩ፡ አላቸው። መጥተው የሚኖርበትን አዩ" የሚለው ቃል በእርግጥ በጣም አስገራሚ ነው:: የክርስቶስን መኖሪያ ማየት መፈለጋቸው ፈልገው እንዳያጡት አድራሻውን ለማወቅ ካላቸው ጉጉት የተነሣ ነበረ::
ሆኖም ክርስቶስ በምድር ላይ ሲኖር ቋሚ አድራሻ አልነበረውም:: ራሱ እንደተናገረ :-ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም" (ማቴ. 8:20)

እነዚህ ሁለት ደቀ መዛሙርት የጠየቁት "ረቢ፥ ወዴት ትኖራለህ?" የሚለው ጥያቄ አድራሻ ከመጠየቅ ከፍ ያለ ጥልቅ ጥያቄ ነው:: ነቢያቱ "የጥበብ ሀገርዋ ወዴት ነው? ማደሪያዋስ ወዴት ነው?" ብለው የተጨነቁለት የጥበብ ክርስቶስ ማደሪያ የት እንደሆነ ማወቅ የነፍስ ዕረፍት ነውና ተራ ጥያቄ አይደለም?
ይህ ጥያቄ ዳዊት ለዓይኖቹ እንቅልፍ ለሽፋሽፍቶቹ ዕረፍት ያልሠጠበት "የያዕቆብ አምላክን ማደሪያ እስኪያገኝ ድረስ" የለመነበት ጥያቄ ነው::

ረቢ ወዴት ትኖራለህ? የሚለው ጥያቄ እንድርያስና ዮሐንስ በአንድ ቀን ብቻ የሚመለስ ጥያቄ መስሎአቸው አብረውት ሔደው አብረውት ዋሉ እንጂ የጌታ መኖሪያ ግን ያን ቀን የዋለበት ብቻ አይደለም::

ረቢ ወዴት ትኖራለህ?
"ብርሃንህንና እውነትህን ላክ፤ እነርሱ ይምሩኝ፥ ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያህ ይውሰዱኝ" መዝ. 43:3

ረቢ ወዴት ትኖራለህ?  "ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ ነህ፤ ወደ ሲኦልም ብወርድ፥ በዚያ አለህ። እንደ ንስር የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥ እስከ ባሕር መጨረሻም ብበርር፥  በዚያ እጅህ ትመራኛለች፥ ቀኝህም ትይዘኛለች" መዝ. 139:8 ለአድራሻ የሚያስቸግረው የረቢ መኖሪያው ብዙ ስለሆነ የት ትኖራለህ ለሚለው ጥያቄ መልሱ "መጥታችሁ እዩ" ብቻ ነው::

ረቢ ወዴት ትኖራለህ? ብለው ለጠየቁት ደቀ መዛሙርቱ ቦታውን ከመናገር ይልቅ  "መጥታችሁ እዩ" ያለው ጌታ እርሱን ጸንተው እስከተከተሉ ድረስ በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ አልፎም ከሞቱ በኋላ የሚያዩት ብዙ መኖሪያ ስላለው ነበር::

የረቢ መኖሪያው ብዙ ነው:: "የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል፡ ወደ እርሱም እንመጣለን፡ በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን" እንዳለ ቃሉን የሚጠብቅ ሰው ሰውነትም የእርሱ ማደሪያ ነው:: (ዮሐ. 14:23)

ረቢ ወዴት ትኖራለህ? " በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና" ስትል ሰምተንህ ነበር:: (ዮሐ. 14:2) የአንተ መኖሪያ መንግሥተ ሰማያት አይደለምን?  ቅዱስ ጳውሎስ "ልሔድ ከክርስቶስ ጋር ልኖር እናፍቃለሁ" ሲል እንደሰማነው እስከ ዐሥር ሰዓት ድረስ እንደመዋል ዐሥሩ መዓርጋት ላይ የደረሱ በጽድቅ መንገድ የሔዱ የሚያዩት ማደሪያህ መንግሥተ ሰማያት አይደለምን? መጥተን ለማየት "እናንተ የአባቴ ቡሩካን ወደ እኔ ኑ" እስክትለን በተስፋ እየጠበቅን አይደለምን?

ረቢ ወዴት ትኖራለህ? ካሉት ጠያቂዎች መካከል አንዱ ዮሐንስ መሆኑን ሳስብ ደግሞ ዮሐንስ ያያቸው የረቢ መኖሪያዎች ከገሊላ እስከ ታቦር ተራራ ፣ ከሊቶስጥራ እስከ ቀራንዮ ፣ ከወንጌል እስከ ራእይ እጅግ ብዙ እንደነበሩ ታየኝ::

"ወዴት ትኖራለህ?" ብሎ ጠይቆ ጌታን የተከተለው ዮሐንስ "መጥተህ እይ" በተባለው መሠረት የጌታን መኖሪያ የእርሱን ያህል ያየም ሰው የለም::

ዮሐንስ "ረቢ ወዴት ትኖራለህ?" ለሚል ጥያቄው ግን አንጀት የሚያርስ ልብ የሚያሳርፍ መልስ ያገኘው አርብ ዕለት መስቀሉ ሥር ነበር:: ወዴት ትኖራለህ? ላለው ዮሐንስ የዘጠኝ ወር ከተማውን የዘላለም ማረፊያውን "እነኋት እናትህ" ብሎ ሲሠጠው መጥቶ ካያቸው የረቢ መኖሪያዎች ሁሉ የምትበልጠውን መኖሪያ አየ:: "እግዚአብሔር ጽዮንን መርጦአታልና፥ ማደሪያውም ትሆነው ዘንድ ወድዶአታልና፥ እንዲህ ብሎ፦  ይህች ለዘላለም ማረፊያዬ ናት፤ መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ" ብሎ የመረጣትን ማደሪያ ከማየት በላይ ምን ክብር አለ? (መዝ. 132:13)

ዮሐንስ ይህችን የረቢ መኖሪያ ወዲያው ወደ ቤቱ ወሰዳት:: ዮሴፍ ሊወስዳት ስላልፈራ ምን እንዳገኘ ያውቃልና እርሱም ይህችን የዕንቁ ሳጥን ወደ ቤቱ ወስዶ ቢዝቁት የማያልቅ ጸጋን ተጎናጸፈ::

ጌታ እናቱን ለዮሐንስ መሥጠቱ የሁለት ድንግልናዎች ማስረጃ ሆነ:: የድንግል ማርያም ዘላለማዊ ድንግልናም የዮሐንስ ድንግልናም በጌታ ንግግር ታወቀ:: 

አንዳንዶች እንደሚመስላቸው ድንግል ማርያም ከጌታ ሌላ ልጆች ቢኖሩአት ኖሮ "እናቴን ከልጆችዋ ነጥለህ ወደ ቤትህ ውሰዳት" "አንቺም ልጆችሽን ይዘሽ ወደ ሰው ቤት ሒጂ" ብሎ ለዮሐንስ አይሠጣትም ነበር:: ድንግል ማርያም የአብን አንድያ ልጅ አንድያ ልጅዋ አድርጋለችና አምላክ ባደረበት ዙፋን ሌላ ፍጡር ያላስቀመጠች የአምላክ ብቸኛ ዙፋን ፣ እግዚአብሔርን አስገብታ በርዋን የዘጋች ዘላለማዊት ድንግል መሆንዋ ለዮሐንስ በመሠጠትዋ ታወቀ:: ዮሐንስም ቤት ንብረት የሌለው መናኝ ባይሆንና ሚስት ድስት ያለው ሰው ቢሆን ድንገት ወደ ቤቱ ይዞአት እንዲሔድ እናቱን ባልሠጠው ነበር::

የሰው ልጅ ድኅነት ታሪክ በሁለት "እነሆ"ዎች መሃል መከናወኑ እጅግ ይደንቃል:: የሰው መዳን የተጀመረው "እነሆኝ የጌታ ባሪያ" ብላ ራስዋን ለፈጣሪ በሠጠችው ድንግል ቃል ሲሆን የተጠናቀቀው ደግሞ "እነኋት እናትህ" ብሎ በደም በታጠበ አንደበቱ በነገረን የኑዛዜ ቃል ነው::

ረቢ ወዴት ትኖራለህ? ለእኛም አታሳየን ይሆን? እስከ ዐሥር ሰዓት መዋል ፣ ዐሠርቱን ትእዛዛትህን ፣ ዐሥሩን የቅድስና ደረጃዎችን መውጣት ላቃተን ለእኛስ መኖሪያህን ታሳየን ይሆን? መጥታችሁ እዩ የሚለውን ጥሪ ሰምተን ለማምጣት አቅም ላነሰን መጻጉዕዎች ፣ ዓይን ላጣን በርጤሜዎሶች ተነሡ እዩ ብለህ መኖሪያህን አታሳየን ይሆን? መቅደስህን እንመለከት ዘንድ ፣ መኖሪያህን መንግሥትህን እናያት ዘንድ ፣ ዮሐንስ ያያትን መኖሪያህ እናትህን እናይ ዘንድ እንመኛለን::

ረቢ ወዴት ትኖራለህ?

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
​​​​VALENTINE'S DAY

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኛ ቤዛ ሆኖ በፍቅሩ የገዛን እጃችንን ለጣኦት እንድንሰጥ አይደለም ብዙ ዋጋ የተከፈለብን እስከ ሞት እንከን በሌለው ፍቅሩ የወደደን መንግስቱን እንድንወርስ እንጂ እንድንጠፋ አይደለም።

የቫላንታይ ቀን ድብቅ እውነታ ስንቶቻችን እናውቃለን?  ይህን የቫላታይን ቀን (የፍቅረኛሞች ቀን) ብለን ስንቶቻችን ነን የምናከብረው ? ወይስ ሰው ስላከበረውና የስልጣኔ መገለጫ መስሎን ነው የምናከብረው ???

ከክርስቶስ ልደት በፊት በባቢሎን ፤ቤልዘቡል ፤በግሪክ ፓን ፤ ሮማ ሞሎቅ ፤ በላቲን ሳተርን ለሚባሉት ሰይጣኖች ያላገቡ ሴቶች ደም የሚፈስላቸው ቀይ ልብስ የሚለበስላቸው ጣኦቶች ናቸው ይህ ዛሬ ቫለንታይን ተብሎ የመጣው ማለት ነው።

የሚገርመው ደሞ ሴቶቹ በዚህ ቀን ለመደፈር ብለው እራቁታቸውን ጫካ መግባታቸው ነው በዚህ ቀን የተደፈረች እና ደሟን ያፈሰሰች ሴትም ሆነ ወንድ በጣኦቱ የተመረጠ እና የተባረከ ነው መባሉ ነው ይበልጥ ነገሩን ሰይጣናዊ የሚያደርገው።

ግሪክ አርኬዲያ ብለው በሚጠሩት አስቀያሚ ትርጉም ባለው ተራራቸው ላይ በዚህ ቀን ላይ ነው ያላገቡ ወንድ እና ሴቶቻቸውን ጣኦቱ ስር ወሲብ በመፈጸም ገላቸውን አርክሰው ለሰይጣን የሚገብሩት።

ይህ የሰይጣን ቀን ነው ክርስትና ይሄን ትከለክላለች ታወግዛለች። (ሁሉም ቀን የእግዚአብሔር ነው ግብሩ ነው የሰይጣን የሚያደርገው)

ኢየሱስ ክርስቶስ ከመውለዱ ከዘመናት በፊት አረማውያን ሮማውያኖች Feb 14 ማታ  እና ለ Feb 15 ንጋት አጥቢያ  የተኩላ አዱኚ ለሚሉት ሉፐርካልያ (luperkalya ) ጣኦት የሚዘጋች ክብረ በአል ነው፡፡   

ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ክርስትና ተቀብሎ እውነተኛ የጽድቅ ሃይማኖት መሆኑን በማውጁ ማንኛውም የጣኦት አምልኮ እንዲቀር ቢያስጠነቅቅም የተውሰኑ የሮማውያን ሰዎች ግን በአሉን ማክበር አልተውም።

እንዴት ይህ አረማዊ ባህል ቫለንታይን የሚል ሰያሜ ተሰጠው? ቫለንታይን የሚል ስም በሮማውያን ዘንድ የተለመደ ስያሜ ነው፡፡ ቫለንታይን የጥንታዊ ታዋቂው ሉፐርኩስ ጣኦት ነው።

ሉፐርኩስ በግሪካዎያን ፓን (pan) ተብሎ ሚጠራው ከወገቡ በታች በግ አናቱ ላይ ቀንድ ያለው ጣኦት ነው። በጥንታውያን አይሁድ ደግሞ ይህ ፓን ባል (baal) በሚል ስያሜ ይታወቃል።

ጥንታውያን ሮማውያን ከባቢሎናውያን የቀዱት አረማዊ የልብ (heart) ምልክት ይጠቁማሉ፡፡ በባቢሎናውያን ባል (bal) ልብ የሚል ፍች ነው ያለው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ይህ አረማዊ የልብ ምልክት ለቫለንታይን ቀን (የፍቅረኛሞች ቀን) የምንለው መግለጫነት እንጠቀምበታለን። ባል የባቢሎናውያን ጣኦት ነበር።

በዚህ የሃጥያት ቀን በትንቹ ይህ ይሆናል

1. በዚህ ቀን February 14 በብዙ የሚቆጠሩ እህቶቻችንን ክብረ ንጽህናቸውን (ድንግልናቸውን) ያጣሉ

2. በርካታ ወጣቶች በስካር ምክንያት በሚያሽከረክሩት መኪና ህይወታቸውን እና አካላቸውን ያጣሉ

3. በአለማችን ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የአልኮል መጠጥ ሽያጭ የሚከናወንበት ቀን ነው በአጠቃላይ የዝሙት እና ስካር መንፈስ የሚነግስበት በከፍተኛ ሁኔታ ሰይጣን በደም የሚረካበት ቀን ነው።

Valentine day ማለት ሰይጣን በጥልቅ እና ረቂቅ ሃሳብ ብዙዎችን የሚያጠምድበት ቀን ነው አስተውሉ ሰይጣን ከ7ሺህ አመት በላይ የክፋት ልምድ አለው።

እንግዲህ ምርጫው ያንተ/ቺ ነው :- የእግዚአብሔር ወይም የሰይጣን ልጅ መሆን???

" ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል፤ አንተም እውቀትን ጠልተሃልና እኔ ካህን እንዳትሆነኝ እጠላሃለሁ፤ የአምላክህንም ሕግ ረስተሃልና እኔ ደግሞ ልጆችህን እረሳለሁ። "
        (ትንቢተ ሆሴዕ 4 : 6)

እግዚአብሔር አምላክ ማስተዋሉን ያድለን።

ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
​​የተሠጠህን ቁጠር

ሔዋን ከዕባብ ጋር እየተነጋገረች ነው:: የመጀመሪያ ጥፋትዋ ካለደረጃዋ ወርዳ ከዕባብ ጋር ወዳጅነት መጀመርዋ ሳይሆን አይቀርም:: ዕባብ ደግሞ የሰይጣን አንደበት ነበረ::

ሰይጣን እንዲህ አላት :- በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን? አላት።
ልብ አድርጉ እግዚአብሔር "ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ" አላለም። የከለከለው አንዲት ዛፍ ነው። ሰይጣን ግን ሁሉን ተከልክላችሁዋል? ብሎ እንዳላዋቂ ጠየቀ:: ሰይጣን በመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሩን የከፈተው በውሸት ነበረ።

ዓላማው ከሔዋን መረጃ ለማግኘት አልነበረም። ሔዋን እስከዛሬ ያላሰበችውን ማሳሰብ ነበር። ብሉ ተብሎ ከተሠጣቸው ብዙ ሺህ ዛፍ ይልቅ የተከለከሉትን አንዲት ዛፍ አሳይቶአት ሔደ። ከዚያች ደቂቃ ጀምሮ ስላልተሠጣት ማሰብ ጀምራ ደስታዋን አጣች። የተከለከለችውን በልታ የተሠጣትን ብዙ ሥጦታ ከነሠጪው አጣች።

ወዳጄ የቀደመው እባብ ዛሬም መርዙን ይረጫል።

በሕይወታችን ከተሠጠን ብዙ ነገር ይልቅ ያልተሠጠንን ጥቂት ነገር እናስባለን:: ገንዘብ እንደሌለህ እያሰብክ ጤና እንዳለህ ትረሳለህ:: ጫማ እንደሌለህ እያሰብክ እግር እንዳለህ ትረሳለህ:: አልጋ እንደሌለህ እያሰብክ እንቅልፍ እንዳለህ ትረሳለህ።

ስለዚህ ውስጥህ ያለውን የዕባቡን ድምፅ  አትስማ ከሌለህ ይልቅ ያለህ ይበልጣልና የተሠጠህን ቁጠር።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል ( ፩ኛ .ቆሮ . ፲፭ ፥ ፴፫ )

ባልንጀርነት ማለት ተዋደደ ፣ ተስማማ፣ ተካከለ ማለት ሲሆን እኩያ፣ አምሳያ፣ ባልደረባ፣ ዘመደ፣ ጓደኛ፣ ጎረቤት፣ አቻ፣ ኅብረት፣  አንድነትና ትክክለኝነት ያለው ማንኛውም ነገር ነው።  ይህም  በሁለት ይከፈላል።

፩ኛ መልካም  ባልንጀራ ፦ ማለት ሕይወትህን ሕይወቱ፣ ድካምህ ድካሙ፣ ጎዶሎህን  ጎዶሎ፣ ደስታህን ደስታው፣ ክብርህን ክብሩ፣ ኀዘንህን ኀዘኑ፣ ስደትህን ስደቱ፣ መከራህን መከራው አድርጎ ከጎንህ የማይጠፋ ዘንበል ስትል ቀና ፣ ዘመም ስትል ደገፍ እያደረገ በምክርና በሐሳብ ካንተ ሳይለይ ምሥጢር የምታካፍለውንና የምትነግረውን ቆጥቦ የሚይዝ ፣በጥቂቱ የሚታመን በብዙ የልብህ መንግስት ውስጥ የሚሾም ማለት ነው።

ባልንጀራን መውደድ ትእዛዘ እግዚአብሔር እና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ነው ። ነገር ግን ባልጀራውን የማይወድ በጨለማ፣ በድንቁርና፣ በገሃነም ይኖራል፤  “ ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ” እንደተባለው (ዘሌ ፲፱ ፥ ፲፰ ) ለሰው ልጅ ሁሉ ሕግን የሰጠ አምላክ ሰዎች እርስ በእርሳቸው ተዋደው ቢኖሩ የመዋደድ በረከትን አንዱ ሌላውን ቢያጠፋ ደግሞ የኃጢአት ውጤት የሆነውን ቅጣት ያስተላልፋልና።

በአርአያ ሥላሴ የተፈጠረ የሰው  ልጅ  ሁሉ ማንንም ከማን ሳያበላልጥ እኩል በሆነ ፍቅር መመልከት ተገቢ በመሆኑ በዕድሜ፣ በዕውቀት፣ በሥራ ቦታ፣  በማኅበራዊ ኑሮ ሁሉ ባልንጀራ የሆነውን የሰው ዘር በመውደድ፣ ትእዛዝን በመፈጸም እና ለመፈንሳዊ በረከት በመሽቀዳደም መበርታት ያስፈልጋል ። ስለዚህ ባልንጀራን እንደ ራስህ አድርጎ መውደድን ፣ ራስን አሳልፎ እስከ መስጠት የሚደረስበት መሆኑን ማወቅ ተገቢ  ነው።

ጠቢቡ ሰለሞን እንዲህ አለ “ባልንጀራህን የሚንቅ እሱ በእግዚአብሔር ፊት ይበድላል።” (ምሳ ፲፬ ፥ ፳፩ )  በቅዱስ ወንጌል ታሪኩ የተጻፈለት ደጉ ሳምራዊ በመንገድ ላይ ወድቆ ያገኘውን ቁስለኛ አንስቶ መልካም ነገር ስለአደረገለት መልካም ባልንጀራ በማት ተጠቁሟል።( ሉቃ ፲ ፥ ፳፭ ) በሀገራችን ኢትዮጵያም ቅዱሳት መካናትን ለመሳለም የሚመጣውን ኅብረተሰብ ኢትዮጵያውያን እግር አጥበው፣ መኝታ ሰጥተው፣ ስንቅ ጨምረው የሚል ናቸው። ስለዚህ በደዌ ሥጋና  በረኀበ ሥጋ ማጥገብና መፈወስ ብቻ ሳይሆን በደዌ ነፍስ ተይዘው የሚቃትቱትን እና እርዳታ ለሚሹ ሁሉ ደርሶ ከቃለ እግዚአብሔር ተመግበው፣ በንስሐ ታክመው ጸጋና ረድኤት ተጎናጽፈው በመንፈሳዊ ሕይወት እንዲኖሩ ማድረግ ባልንጀራን መውደድ ነው።

፪ኛ ክፉ ባልንጀራ፦  የሰውን ልጅ የፈጠረ እግዚአብሔር ክፋት የሚስማማው ስላልሆነ የዋህነት፣ ቅንነትና በጎነት እንዲስማማ አድርጎ ቢፈጥርም በኃሚአት ምክንያት ክፋት ወደ ሰው ልጅ መጥቷል፤ ክፋት የማን ነው ቢባል ከዲያቢሎስ በመሆኑ ከበጎ ሥራችን ክፉ ሥራችን የሚበዛ ከሆነ ከእግዚአብሔር ሳይሆን ከሐሰት አባት ከዲያቢሎስ በግብር በመውሰድ የክፋት የኃጥያት ባሪያ እንሆናለን፤ የኃጥያት ደሞዝ ደሞ ሞት ነው። ( ሮሜ ፮ ፥ ፳፫ ) ስለዚህ የክፉ ሰዎች ደመወዝ ለጊዜው ቢመስልም መጨረሻው ሞት ነውና በዚህም ሰውች ገጽታን እየተመለከቱ ልቡናንና እንቅስቃሴውን ሳያውቁ ባስቀመጡት ክቡ ባልንጀራ የተጎዱ ብዙዎች ናቸውና ከክፉ ባልጀራ መራቅ አስፈላጊ ነው። ለማሳያ ያህል በጥቂቱ፦

ሀ‚ የሔዋንና የእባብ ባልንጀርነት፦ የሰዎች ሁሉ እናት የሆነችው ሔዋን እግዚአብሔር የነገራትን ባለ መስማት በእባብ ላይ ባደረው ዲያብሎስ ጋር ጓደኝነት በመጀመሯ እና ምክር በመስማቷ ከፈጣሪ ተጣላች፣ ልጅነቷን አጣች፣ ከገነት ተባረረች፣ በሞተ ሥጋ መርገመ ነፍስ ተፈረደባት። ዛሬም ብዙ ሰዎች በትምህርት ቤት፣ በመሥሪያ ቤት፣ በጎረቤት ሁሉ የጓደኛ ምርጫቸውን ካላስተካከሉ ይፈተናሉ፤ የነፍስም የሥጋም በሽተኛ ይሆናሉ፤ ከእግዚአብሔር የተቀበሉትን ጸጋ ያጣሉ። 

ለ‚ የአምኖንና የኢዮናዳብ ባልንጀርነት፦ የንጉሡ የዳዊት ልጅ አምኖን መንፈስ ዝሙት አድሮበት በእኅቱ በትዕማር በመጎዳቱ በዚህ ጊዜ ኢዮናዳብ የሚባለው ጓደኛው ክፉ ምክር መክረው፣ አምኖንም የክፉ ጓደኛውን ምክር ተቀብሎ በተግባር ፈጸመ። እኅቱን አስገድዶ ደፈረ፣ ከክብር አዋረደ፣ አባቱንም እግዚአብሔር አሳዘነ፣ በበጎ ምግባር እአያ መሆን ሲገባው በእንደዚህ ዓይነት መጥፎ ተግባር ሲጠቀስ ይኖራል። በዘመናችን ሰዎች ተቸገርኩ ብለው ሲያማክሩ ወደ መልካም መንገድ ከመምራት ይልቅ ያሰበውን ክፉ ሐሳብ ለማስፈጸም የኃጥያት መንገድ የሚጠርጉ ብዙዎች ናቸው።

በመሆኑም ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያስጠፋል ማለት እንደዚህ ያለው ነውና በዚህ ዓለም ስንኖር ወደንመ ሆነ ተገደን ከሰዎች ጋር ማኅበራዊ ሕይወት ይኖረናል፤ ይሁን እንጂ ከማን እና ምን ዓይነት የሕይወት ልምድ ካለው ጋር ነው የምንኖረው የሚለውን የማጤን ሥራ ልንሠራ ይገባል። ከክፉ ባልንጀርነት በመጠበቅ በመልካም ባልንጀርነት መጠቀም ያስፈልጋል ።

ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
ትሞታለህና ቤትህን አስተካክል

ንጉሥ ሕዝቅያስ በጠና ታምሞ ተኝቶአል::  ነቢዩ ኢሳይያስ ሊጠይቀው መጣ:: ሆኖም እንደ ልማዱ እግዚአብሔር ይማርህ አላለውም:: ለጆሮ የሚከብድ  ቃል ጥሎበት ወጣ:: "ትሞታለህና ቤትህን አስተካክል!"

ነቢዩ ይህንን ብሎት ከወጣ በኁላ ሕዝቅያስ ወደ ግድግዳው ዞሮ ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ:: አምላኩ በንግግር ብዛት የሚሰማ አምላክ አይደለምና ፊቱን ወደ መቅደሱ አቅጣጫ አዙሮ አለቀሰ:: 

ከጥቂት ደቂቃ በኁዋላ ነቢዩ ኢሳይያስ ሌላ መልእክት ይዞ ተመለሰ:: እግዚአብሔር እንዲህ ይላል :- ጸሎትህን ሰምቻለሁ ዕንባህን አይቻለሁ በዕድሜህ ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እጨምራለሁ" (ኢሳ 38:5)

ሕዝቅያስ ቤትህን አስተካክል ከተባለ በኁዋላ ፊቱን አዙሮ ከማልቀስ በቀር ምንም አላደረገም:: ሕዝቅያስ ሆይ ከአልጋህ ሳትወርድ ያስተካከልከው ቤት ምን ዓይነት ቤት ነው? ለባሪያዎችህ መመሪያ ሳትሠጥ የምታስተካክለው ቤትስ እንዴት ያለ ነው? በደቂቃዎች ውስጥ ትሞታለህ ከተባልክ በኁዋላ ዐሥራ አምስት ዓመት ያስጨመረልህ ምን ዓይነት ማስተካከያ አድርገህ ነው? ለእኛም ንገረንና ዕድሜ እናስጨምር::

ሕዝቅያስ ከአልጋው ሳይነሣ ያስተካከለው ቤቱ ልቡ ነበር። ልብህን ካስተካከልህ ቤትህ ይስተካከላል:: እግዚአብሔር እንደሆን ትሞታለህ ቢልህም መሞትህን አይፈልግም:: እርሱ ከኃጢአትህ እንጂ ካንተ ጋር ጸብ የለውም::

"በውኑ ኃጢአተኛ ይሞት ዘንድ እፈቅዳለሁን? ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ከመንገዱስ ይመለስና በሕይወት ይኖር ዘንድ አይደለምን?" ይላል መሐሪው (ሕዝ 18:23)

እርሱ ትሞታለህ የሚልህ መኖርህን ፈልጎ ነው:: አንዴ ብያለሁ ብሎ አይጨክንብህም:: በንስሓ ተመለስ እንጂ ምሬሃለሁ ለማለት ይቸኩላል:: አሁን ትሞታለህ ብዬው አሁን ትድናለህ ብለው ይንቀኛል ሳይል ተመልሶ ይምርሃል:: ኃጢአትህንም ወደ ጥልቁ ይጥለዋል:: በጎ እንድትሠራም ዕድሜ ይጨምርልሃል:: አንተ ብቻ ተመለስና አሁኑኑ ንስሓ ግባ::

ከበደል አልጋ ጋር ያጣበቀህን ፈተናም ድል መንሻው ጊዜ አሁን ነው:: ሕዝቅያስ በደቂቃ ዕንባ ምሕረት አግኝቶ ዕድሜ ካስጨመረ ቀን ሙሉ የሚያለቅስ ምን ያህል ዕድሜ ያገኝ ይሆን?

ወዳጄ አንተም ተነሣና በዚህች ዕለት ቤትህን አስተካክል:: እንደ ሕዝቅያስ ፈጣሪህ ይጠብቅሃል:: የተቀየምከውን ይቅር በል  የበደልከውን ካስ የሚበቀልህን የማይተኛ ጠላትህን ዲያቢሎስ ተበቀለው::

ከቁስልህ የምትፈወስበት ጊዜ እንደደረሰ ዕወቅ:: ልትላቀቀው እየፈለግህ ያቃተህ ክፉ ልማድ የለብህም:: እንደ ቅዱስ ጳውሎስ "የምፈልገውን መልካም ነገር አላደርግም የማልፈልገውን ክፉ ነገር ግን አደርጋለሁ:: ምንኛ ጎስቋላ ለዚህ ለሞት ከተሠጠ ሰውነት ማን ያድነኛል?" ብለህ ምርር እንድትል ያደረገህ ኃጢአት የለም? እንግዲያውስ እወቀው:: ከንስሓ በቀር መፍትሔ የለውም:: እንደ ሕዝቅያስ አሁኑኑ ቤትህን በንስሓ አስተካክል::

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
+ ንስሐ ግቡ +

የጌታቻን የኢየሱስ ክርስቶስ መጠመቅ አሰቀድሞ በዮሐንስ ለሀጥያት ስርየት ማጥመቅ መንገድ ጠራጊነት የተጀመረ ነው እርሱም እኔስ ለጠጅ ፡ ቢረሌን ፡ ለልብስ ፡ ገላን ፡ እንዲያጥቡለት ፡ ለሱ ፡ ጥምቀት በሚያበቃ ጥምቀት አጠምቃቹሀለው ይል ነበር እንዲሁም  እርሱ የሚያጠምቀው ጥምቀት ክርስቶስ ከሚያጠምቀው ጥምቀት  ልዩ መሆኑን ሲገልፅ "በመንፈስ : ቅዱስ : እሳትነት" ክፍውን : ሕሊና : ከበጎው : ሕሊና የሚለይበት ስልጣነ ክህነት ገንዘቡ የሚሆንለት በማለት ይገልፃል  ። ዮሐንስ  ትንቢት የተነገረለት ያለነቀፌታ ይኖሩ ከነበሩ በእግዚአብሔር ፈት ጻድቃን ከነበሩ ከካህኑ  ዘካርያስ እና ከኤልሳቤጥ የተወለደ ነው ። በሉቃ 8-11"

***
በእግዚአብሔር ፈት በቤተ መቅደስ ገብቶ የማጠን  ተራ  በመዓት አንድ ጊዜ  የደረሰበት ካህኑ ዘካርያስ በመሰዊያው ቀኝ የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦለት ታየው ።  ይህም  በዓመት አንዴ ሳይሆን  አንድ ጊዜ በፈሰሰ ደሙ አለምን የሚያድን አምላክ ሊወለድ መሆኑን ሲነግረው ነው  አንድም ካለመታዘዝ  ወደ መታዘዝ የሚመልስ ከጣኦት አምላኪነት ወደ እግዚአብሔር አምላኪነት የሚመልስ ልጅ ትወልዳለህ ሲለው ነው በተጨመሪም በቀኝ እጁ አምላክን የሚያጠምቅ ልጅ ትወልዳለህ እያለ መንገሩ ነው ("ጸያሔ ፍኖት" ርዕሰ ሊቃውንት አባ ገብረ ኪዳን ግርማ )  ።

ለዚህም ነበር በሰፈው ፈት ፃድቃን መስለው ይታዩ ለነበሩት በእግዚአብሔር ፈት  ፅድቃቸው ከተመሰከረላቸው ቤተሰብ የተገኘው ዮሐንስ እርሱ በጌታ ፈት ታላቅ የሆነ  ሉቃ 1፡15  በህሊና የተሰወረውን ክፍ ግብራቸውን ሳይፈራ እግዚአብሔር ገልጦለት  ይገስፃቸው ነበር ፈሪሳውያንን "መልካም ፍሬ የማያፈራ ይጣላል " ማቴ 3-10 እያለ  የነብያት ልጆች መሆናቸው ብቻ ንስሃ ካለመግባታቸው የሚመጣባቸውን ቅጣት እንደማያስመልጣቸው ክቡዳነ አእምሮ ለሆኑት ለእነርሱ  "ንስሀ ግቡ" እያለ ያስተምራቸው ነበር ።  ምንመካባቸው ብዙ የተከማቹ ሀብት ይዘን ሊሆን ይቻላል በዘመንድ ብዛት የእከሌ ዘመድ የእከሌ ዘር እያልን ምንመፃደቅባቸው በሰው ፈት ከሁሉ የተሻልን ለመምሰል የምናቀርባቸው ቁሶች ከመቃብር አይሻገሩም ያለን ግዙፍ ቤት  በሁሉ ፈት ለመመካት ይዘነው አንዞርም አንድ ቦታ  እንደተተከለ ይቀራል  የሰማይ መንግስት እንወርስ ዘንድ ዮሐንስ ዛሬም "እንግዲህ ለንስሐ የሚያበቃቹሁን በጎ ስራ ስሩ" ይለናል " ማቴ 3-8 

ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
የክርስትና ስም ለምን አስፈለገ ?

የክርስትና ስም ለምን ያስፈልጋል?
ጥቂት የማንባል ሰዎች ከነ መሰየሙም የክርስትና ስማችንንም የማናስታውስ ልንኖር እንችላለን፡፡ የክርስትና ስም አንድ የሚጠመቅ ሰው በሚያጠምቀው ካህን የሚሰጠው ወይም የሚጸድቅለት ስያሜ ነው፡፡ ይህንን ስም ቤ/ክ ዝም ብላ ለህጻናቱ የምትለጥፍ የሚመስላቸው ሰዎች ቀላል አይደሉም፡፡ በጥምቀት ግዜ ቤ/ክን ልጆቿን ስትቀበል እንዲሁ አይደለም ተገቢ ስም አውጥታ ከመንፈስ ቅዱስ በጥምቀት ዳግመኛ ወልዳ ቅበዐ ሜሮን ቀብታ የሚንከባከብ የክርስትና አባት እናት ሰይማ በመስቀሉ ቃል አስገብታ ቅዱስ ስጋና ደሙን መግባ ነው፡፡ የክርስትና ስም መጽሐፍ ቅዱሳዊ እና ክርስቲያናዊ ትውፊት አለው፡፡ ብዙ ነብያት እና ቅዱሳን ካላቸው መጠሪያ ሰም በተጨማሪ እራሱ አምላካችን አዳዲስ ስም ሲያወጣላቸው እናያለን ለምሳሌ፡-
አብራምን ☞ አብርሃም
ያዕቆብን ☞ እስራኤል
ስምዖንን ☞ ጴጥሮስ

ሳኦልን ☞ ጳውሎስ እያለ ሲጠራቸው ለምን በአዲስ ስም መጥራት እንደፈለገ አንዳች ነገር ልንገነዘብ ይገባል፡፡

#ዓላማውስ_ምንድን_ነው?

1. #ቋሚ የቅዱሳን መታሰቢያ እንዲሆን፡- በት.ኢሳ 56:5 አምላክ ለቅዱሳን የማይጠፋ ስም እና የዘለዓለም መታሰቢያ እንደሰጣቸው እናነባለን፡፡ስለዚህ በተለያዩ ቅዱሳን ላይ የነበረውን ፀጋ እና በረከት ለመካፈልና እንዲሁም እንደነሱ የበረታን እንድንሆን በስማቸው እንሰየማለን የጌታችንንም ስሙን ዘርፍ በማድረግ እንዲሁ እንጠቀምበታለን፡፡

2. #ለተጠማቂውም በረከት እንዲሆንለት፡-
በምሳ 10:6 የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው ይላል፡፡ ስለዚህ በስማቸው በመሰየም ከላይ እንደገለጽነው መታሰቢያቸውን እና በረከታቸውን ለመካፈል ሲረዳን ይህን ጸጋ ለማግኘት በቅዱሳን ስም በመሰየም የክርስትና ስም ይወጣልናል፡፡

3. #መጠሪያ ስም ነው፡-
በቀድሞው ስርአት የክርስትና ስም ለሁልጊዜውም መጠሪያ ነበር፡፡ ከግራኝ መሐመድ መነሳት አስቀድሞ የነበሩ ምዕመናን በክርስትና ስማቸው ነበር የሚጠሩት፡፡ነገር ግን መከራው ሲበዛባቸው ከርስታቸው ላለመሰደድ ሲሉ ተለዋጭ ስም በማውጣት መጠቀም ጀመሩ ከዛን ግዜ ጀምሮ ይህ ነገር እየተስፋፋ መጥቶ ከነ ጭራሹ ለመለወጥ በቃ፡፡

በተጨማሪም
☞ -የማይገባ የክርስትና ስም
በአምላክ ስም በቀጥታ መጠራት አይገባም ለምሳሌ፡- አማኑኤል፣ኤልሻዳይ፣ኢየሱስ እነዚህ ስሞች ለሠው ልጆች መጠናችን ስላልሆኑ መጠቀም የለብንም፡፡ በዚህ ምትክ ገብረ አምላክ፣ሣህለ ሥላሴ፣ፍቅርተ ክርስቶስ ፣ዘአማኑኤል በማለት መሰየም ይቻላል።
☞-በቅዱሳንም ስም በቀጥታ ወይም ዘርፍ እየተደረገለት መሰየም ይቻላል፡፡
ለምሳሌ፡- ዘማርያም፣ዘሚካኤል፣አጸደ ማርያም፣ ተክለ ሐይማኖት ወዘተ...

#ከዚህ ስርዓት ከሚገኘው በረከት ተሳታፊዎች እንድንሆን አምላካችን እግዚአብሔር ለሁላችንም ይርዳን።
       ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
          
​​የሰጠኸኝ ሴት

እግዚአብሔር አዳምን "አትብላ ካልሁህ ዛፍ በላህን?" ብሎ ጠየቀው። አዳምም:- ከእኔ ጋር እንድትሆን የሠጠኸኝ ሴት ከዛፉ ሠጠችኝና በላሁ አለ።

የሰጠኸኝ ሴት! በጣም ይገርማል። ሚስቴ አላለም። አዳምና ሔዋን የተገናኙ ቀን አዳም ያለውን አስታውሱ "ይህች አጥንት ከአጥንቴ ይህች ሥጋ ከሥጋዬ" ብሎአት ነበር:: ምንም እንክዋን አዳም ወላጆች ባይኖሩትም ሰው እናትና አባቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ብሎም ነበር። ራቁታቸውን ቢሆኑም አይተፋፈሩም ነበር::

አሁን በራቁቱ ብቻ ሳይሆን በሔዋንም አፈረባት:: እናትና አባቱን ይተዋል እንዳላለ ሔዋንን ራስዋን ተዋት። ከሚስቱ ጋር መተባበር ቀርቶ ክስ ጀመረ።

አካሌ አጥንቴ ሥጋዬ ማለቱ ቀረና የሠጠኸኝ ሴት አለ:: የጫጉላው ጊዜ አለፈና ከሚስትነትዋ ሴትነትዋ ብቻ ታየው።

በጋብቻ ብቻ አይደለም እግዚአብሔር የሠጠንን ነገር ሁሉ ቀድመን የራሳችን እናደርጋለን ነገሮች ሲበላሹ ግን ባለቤትነቱን ወደ እርሱ እንመልሰዋለን::

የሠጠኸኝ ሥራ
የሠጠኸኝ ወላጆች
የሠጠኸኝ ሰፈር
የሠጠኸኝ ሀገር
የሠጠኸኝ መሪ
የሠጠኸኝ ጉዋደኞች
የሠጠኸኝ ደካማ ሥጋ
የሠጠኸኝ ዓይን

ትናንት ሲሠጠን ዘምረን የተቀበልነውን ሥጦታ ዛሬ ለምሬት እንጠቅሰዋለን። የሠጠኸኝ የሠጠኸኝ .... ሠጠኝና በላሁ ብለን ቀርጥፈን ለበላነው ዕፀ በለስ ፈጣሪን እንከስሰዋለን::

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
          
ቅዱሳን ሰማዕታት

ሰማዕት ማለት ምስክር ማለት ሲሆን በሃይማኖት ምክንያት የተገደለ፣ መከራ የደረሰበት ሰማዕት ይባላል። (ሐዋ.22፡20) የመጀመሪያዎቹ የሐዲስ ኪዳን ሰማዕታት ሐዋርያትና አርድዕት ናቸው።

ቅዱሳን ሰማዕታት የሚባሉት “እግዚአብሔርን ካዱ ለጣዖት ስገዱ” ሲባሉ “እግዚአብሔርን አንክድም ለጣዖት አንሰግድም” በማለት በአላውያን ነገሥታት ፊት ቀርበው ሳያፍሩና ሳይፈሩ ስለጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የባህርይአምላክነት የመሰከሩ ናቸው። በዚህም ምክንያት ተዘርዝሮ የማያልቅ የመከራ ዓይነት ተቀብለው ለፈጣሪያቸው ክብር ሲሉ ደማቸውን ያፈሰሱ፣ አጥንታቸውን የከሰከሱ፣ ሕይወታቸውን ያጡ ናቸው።

በእሳት ተቃጥለዋል፣ በውኃ ተቀቅለዋል፣ በሰይፍ ተመትረዋል፣ በመጋዝ ተተርትረዋል፣ በመንኩራኩር ተፈጭተዋል (መንኩራኩር የሚባለው በዘመነ ሰማዕታት የነበረ ዘመናዊ የወፍጮ መሳሪያ ነው።)፣ እንደከብት ቆዳቸው ተገፏል፣ ወደጥልቅ ባህርተጥለዋል። በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ ከሃይማኖታቸው አላፈገለጉም፤ እንደውም “እኔ በእርሱ አምላክ አመልካለሁ” እንዲሉ አድርገዋቸዋል።

ዘመነ ሰማዕታት የሚባለው በአርማንያ 40 ዘመን ሲሆን ብዙ ቅዱሳን ሰማዕትነትን ተቀብለውበታል። ከኢትዮጵያም 1600 ክርስቲያኖች በቀን “ይህ ሰማዕትነት አያምልጠን” በማለት ሄደው ተሰውተዋል። በዘመኑ የነበሩት አረማውያን ነገሥተ ዲዮቅልጥያኖስ፣ መክስምያኖስ፣ ድርጣድስ፣ እለእስክንድሮስ፣ በኡልያኖስ፣ በፋርማህ እጅ የተሰዉ ነበሩ።

ማቴ.10፡28 “ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ።”

· ዕብ.11፡34 – 38 “የአንበሶችን አፍ ዘጉ፥ የእሳትን ኃይል አጠፉ፥ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፥ ከድካማቸው በረቱ፥ በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ፥ የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ።ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይበእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤ በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ተፈተኑ፥ በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ።”

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
          
#የካቲት_16
#ኪዳነ_ምሕረት (#የሰባቱ_ኪዳናት_ማሕተም)

የካቲት ዐሥራ ስድስት በዚችም ዕለት የክርስቲያን ወገኖች ሁሉም አማላክን ለወለደች ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓልን ያደርጋሉ። በዚች ዕለት መታሰቢያዋን ለሚያደርግ ስሟን ለሚጠራ ለድኆችና ለችግረኞች እስከ ቀዝቃዛ ውኃ ለሚሰጥ የክብር ባለቤት ከሆነ ከተወደደ ልጅዋ ከጌታችንና ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምሕረት ቃል ኪዳንን ተቀብላለችና።

ይህችም የከበረች እመቤታችን ልጅዋ ንጹሕ ሥጋዋን ተዋሕዶ ከብቻዋ ኃጢአት በቀር የሰውነትን ሥራ ፈጽሞ ስለእኛ መዳን ወዶ ያደረገውን መከራ ተቀብሎ ሙቶ ተነሥቶ ከዐረገና በአባቱ ዕሪና ከተቀመጠ በኋላ እርሷን እናቱን ማርያምን በደቀ መዝሙሩ ዮሐንስ ዘንድ ትቷት ነበር እነሆ ልጅሽ እርሱንም እነሆዋት እናትህ ብሎ አደራ እንዳስጠበቀው።

ከዚያንም ጊዜ ጀምራ እመቤታችን ማርያም ትጸልይ ዘንድ ያለ ማቋረጥ ወደ ልጅዋ መቃብር ሁል ጊዜ ስትሔድ ኖረች ይኸውም ጎልጎታ ነው።

አይሁድም በአዩዋት ጊዜ ቍጣንና ቅናትን ተመልተው በድንጊያ ሊወግሩዋት ወደዱ እግዚአብሔርም ከዓይናቸው ሠወራት ከዚህም በኋላ ዳግመኛ መጥታ በዚያ እንዳትጸልይ ተማክረው ከመቃብሩ ዘንድ ጠባቂዎችን አኖሩ እርሷ ግን በየዕለቱ መሔድን አላቋረጠችም ጠባቆችም አያይዋትም የልጅዋ የጌትነቱ መጋረጃ ሠውርዋታልና መላእክትም መጥተው ያገለግሏታል ጌታችንም ዘወትር ይጐበኛታል የምትሻውንም ይፈጽምላት ነበር።

ከዚህም በኋላ መላእክት ወደ ሰማይ አሳረጓትና የጻድቃንን ማደሪያዎች አሳዩዋት አብርሃም ይስሐቅ ያዕቆብም ወዳሉበት አደረሱዋት ከአዳም ጀምሮ እስከዚያ ዕለት በአካለ ነፍስ ያሉ አባቶች ሁሉ አንቺን ከሥጋችን ሥጋን ከዐፅማችን ዐፅምን ለፈጠረልን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን የአምላክ ልጅ ከአንቺ ሰው በመሆኑ በአንቺ ድህነት አግኝተናል ከጥፋትም የሕይወት ወደብ ሆነሽልናልና እያሉ ሰገዱላት።

ከዚያም ወደ ተወደደ ልጅዋ የእሳት መጋረጃ ወደተተከለበት ወደ ጌትነቱ ዙፉን አደረሷት ጌታችንም እጇን ይዞ ወደ ውስጠኛው መጋረጃ አስገብቶ ከጌትነቱ ዙፋን ላይ አውጥቶ ከእርሱ ጋር አስቀመጣት ያዘጋጀላትንም ዐይን ያላየው ጆሮ ያልሰማው በሰው ልቡና ያልታሰበ ተድላ ደስታን ሁሉ ነገራት።

ከጌትነቱ ዙፋንም በታች የእስራኤል ንጉሥ አባቷ ዳዊትን የነቢያትና የመላእክት ማኀበር እንደ ግድግዳ ከበውት በመሰንቆ ሲያመሰግን አየችው እንዲህም ይላል ልጄ ስሚ በጆሮሽም አድምጪ ወገንሽን የአባትሽንም ወገን ርሺ ንጉሥ ደም ግባትሽን ወዷልና እርሱም ጌታሽ ነውና።

ዳግመኛም የሥቃይን ቦታ ያሳዩዋት ዘንድ መላእክት ከዚያ ውሰዷት ለሰይጣንና ለሠራዊቱ በእርሱ ጐዳና ለሚጓዙ ሁሉ ወደተዘጋጀ ወደጨለማው ዳርቻ አደረሷት እመቤታችን ማርያምም ወዮልኝ ወደዚያ እንዳይመጡ ለሰው ልጆች ማን በነገራቸው አለች መልአኩም አመቤቴ ቡርክት ማርያም ሆይ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ይኖራልና ለአንቺም ከአንቺ በኋላም በቃል ኪዳንሽ ለሚታመኑ አትፍሪ አላት ከዚህም በኋላ ወደ ቦታዋ መለሷት።

ከዚያንም ጊዜ ጀምራ እመቤታችን ድንግል ማርያም ስለ ኋጥአን እጅግ እያዘነች ኖረች እንደ ዛሬይቱም የካቲት ዐሥራ ስድስ ቀን በጎልጎታ ቦታ ቁማ ወደ ልጇ እንዲህ ብላ ለመነች ልጄ ሆይ በእግዚአብሔር አባትህ በክርስቶስ ስምህ ከአንተ ጋርም ህልው በሆነ አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ አማፅንሃለሁ ዓለም ሁሉ ሊሸከምህ የማይችል ሲሆን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በተሸከመችህ ማሕፀኔ አማፅንሃለሁ ልጄ ሆይ ያለ ሕማም ያለ ድካም ከእኔ በመውጣትህ በመወለድህ በአሳደጉህ ጡቶቼ በሳሙህ ከንፈሮቼ በአቀፋህ እጆቼ ከአንተ ጋር በተመላለሱ እግሮቼ አማፅንሃለሁ ። በውስጡ በተኛህበት በረት በተጠቀለልክበት ጨርቅ አማፅንሃለሁ የምወድህ ልጄ ሆይ በልቡናዬ ያለውን ሁሉ ትፈጽም ዘንድ የልመናዬን ቃል ሰምተህ ወደእኔ ትመጣ ዘንድ ወዳንተ ፈጽሜ እማልድሃለሁ።

የብርሃን እናቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንዲህ ብላ በጸለየች ጊዜ እነሆ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወረደ ከእርሱም ጋር አእላፍት መላእክት አሉ በዙሪያውም ሁነው ያመሰግኑታል እርሱም እናቴ ማርያም ሆይ ምን ላድርግልሽ አላት እመቤታችንም ለተወዳጅ ልጅዋ እንዲህ ብላ መለሰችለት ልጄ ወዳጄ ሆይጌታዬና ፈጣሪዬ አለኝታዬና መጠጊያዬ በእናቴ ማሕፀንም ሳለሁ ባንተ ጸናሁ አንተም ጠበቅኸኝ ሁልጊዜም ስም አጠራሬ አንተ ነህ።

አሁንም ጸሎቴንና ልመናዬን ስማኝ ቃሌንም አድምጥ እኔ እናትህ እኔም አገልጋይህ የምለምንህ ይህ ነው መታሰቢያዬን ለሚያደርጉ በስሜ አቢያተ ክርስቲያን ለሚሠሩ ወይም የተራቆተውን ለሚያለብሱ የተራበውን ለሚያጠግቡ የተጠማውንም ለሚያጠጡ የታመመውን ለሚጐበኙ ያዘነውን ለሚያረጋጉ የተከዘውንም ደስ ለሚያሰኙ ወይም ምስጋናዬን ለሚጽፉ ልጆቹንም በስሜ ለሚሰይም በበዓሌም ቀን በማኅሌት ለሚያመሰግን አቤቱ ዐይን ያላየውን ጆሮ ያልሰማውን በሰውም ልቡና ያልታሰበውን በጎ ዋጋ ስጣቸው በአማላጅነቴም የሚታመነውን ሁሉ ከሲኦል ነጻ አድርገው ከአንተ ጋር የደረሰብኝን ረኃቡንና ጥማቱን መከራውን ሁሉ አስብ አለችው።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንዳልሽው ይሁንልሽ የሰጠሁሽም ቃል ኪዳን እንዳይታበል በራሴ ማልኩልሽ አላት።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእመቤታችን ድንግል ማርያም በጸሎቷ ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
          
#ዘወረደ
(የዐቢይ ጾም የመጀመሪያው ሳምንት )

የዐቢይ ጾም የመጀመሪያው ሳምንት ዘወረደ ይባላል፡፡

‹‹ዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ›› የሚልና ይህንን የመሳሰለ ጌታ እኛን ለማዳንና ፍቅሩን ሊገልጽልን ከሰማያት መውረዱን ከድንግል ማርያም የእኛን ሥጋ መዋሐዱን የሚያዘክር ምስጋና የሚቀርብበት ሳምንት ነው፡፡ ሌላም ስም አለው #ጾመ_ሕርቃል ይባላል፡፡ ይህ ጾም የጾም መግቢያ የመጀመሪያ ሳምንት የምንጾመው ጾም ሲሆን #ሕርቃል የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡

#ሕርቃል_ማን_ነው?
#ለምንስ_በስሙ_ተሰየመ?
በ614 ዓ.ም ኪርዮስ የተባለ የፋርስ ንጉሥ ኢየሩሳሌምን በመውረር ጥቃት አደረሰ፡፡ በዚህ ወቅት በኢየሩሳሌም ንግሥት ዕሌኒ በሠራችው ቤተመቅደስ ውስጥ ሲገባ ንግሥቷ በክብር አስቀምጣው የነበረው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል እንደ ፀሐይ ሲያበራ አገኘው፡፡ ቢነካው አቃጠለው ዲያቆናቱን አሸክሞ ሌላውን ንዋየ ቅድሳት ዘርፎ 60 ሺህ የሚደርሱትን አቁስሎ ገድሎ 3 ሺህ የሚሆኑትን ማርኮ ከተማዋንም ቃጥሎ ወደ ፋርስ ባቢሎን ይመለሳል፡፡ በዚህ ጊዜ ከጦርነቱ ያመለጡ በየዋሻው በየጉራንጉሩ ገብተው የተሸሸጉ ተሰብስበው ከ14 ዓመት በኋላ በ628 ጩኸታቸውንና የደረሰባቸውን በደል ለክርስቲያኑ የሮም ንጉሥ ሕርቃል ይነግሩታል። እርሱም ሐዋርያት ሰውን የገ*ደ*ለ እድሜውን በሙሉ ይጹም ስላሉ እንዴት ላድርገው አላቸው እኛ የአንተን እድሜ ተከፋፍለን እንጾማለን ብለው አንድ አንድ ሳምንት ደርሷቸው ጾሙን በሚገባ ጾመውታል፡፡

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልና የተማረኩ ክርስቲያኖችን ለመመለስ ሕርቃል ጦር መዝዞ በኪርዮስ ላይ ተነሳበት ድል ለሕርቃል ሆነና መስቀሉን ያለበትን አጥቶ ሲቸገር መስቀሉን ሲቀብርና ዲያቆናቱን ሲያስገድል በመስኮት ሆና ያየችው ከኢየሩሳሌም የተማረከች አንዲት ብላቴና አሳይታው አውጥቶ በልብሰ መንግሥቱ ጠቅልሎ ወደ ቁስጥንጥንያ ተመለሰ፡፡ የተማረኩት በሙሉ ነጻ ወጡ ይህን ለማሰብ ለማስታወስ በተጨማሪ በኃጢአት ላይ ድል እንድናገኝ መንፈሳዊ ጦር በውስጣችን እንዲበዛልን መስቀልህ ከምርኮ እንደተመለሰ እኛንም ከኃጢአት ምርኮ መልሰን ለሕርቃል ድል መንሳትንና በጠላቶቹ ላይ ኃይልን እንደሰጠኸው ለእኛም በኃጢአት ላይ ድል መንሳት መንፈሳዊ ኃይልን ስጠን እያልን እንጾመዋለን፡፡

በጌታ ጾም ላይ እንዲጾም የሆነበት ምክንያት ጾሙ የጌታ ጾም በሚጾምበት ወቅት ላይ ስለተጾመ ቤተክርስቲያናችን አብራ ደንግጋዋለች፡፡ እዚህ ላይ በዚያን ጊዜ ለሕርቃል ሕዝቡ ሱባኤ ይዞለታል፡፡ ዛሬም እኛ ለቤተክርስቲያን ያደረግነውን በማሰብ እግዚአብሔር አምላክ ለሕርቃል የሰጠውን በጠላቶቹ ላይ ድል መንሳትን ለእኛም እንዲሰጠን የምንጠይቅበት ስለሆነ የመጀመሪያውን ሳምንት በሕርቃል ሰይመን ጾሙን እንጾማለን፡፡ የእኛ ጠላት የጨለማ ገዥ የሆነው ዲያቢሎስ ነውና እሱን ደግሞ በጾም እንደምናሸንፈው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮናል፡፡

«#ዘወረደ» ማለትም በቀጥታ፣ ቃል በቃል ሲተረጐም «#የወረደ» ማለት ነው፡፡ ይህም በምስጢሩ አምላክ ወልደ አምላክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤዛ ዓለም በቅዱስ ፈቃዱ ሰው ሆኖ ከሰማየ ሰማያት፣ ከባሕርይ ልዕልናው በትሕትና ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱን የሚያመላክት፣ ይህም የሚታወስበት፣ የሚወሳበት የዐቢይ ጾም አንደኛው ሳምንት ነው፡፡ ዮሐ.3፥13፡፡

ሳምንቱ #ሙሴኒ ይባላል። ይህ የተባለበትም ምክንያት በዚሁ ሳምንት መጀመሪያ የሰኞ ዕዝል «ከመዝ ይቤ ሙሴ ፀዓቱ እምትእይንት» «ሙሴ ከከተማ መውጣቱ እንደዚህ ነው አለ» ስለሚል እንደዚሁም የዚሁ ዕለት ማለት የሰኞ አቡን «ሙሴኒ ይቤ በውስተ ኦሪት ምድር ሰናይት» እያለ የሙሴን ታሪክ ስለሚያጠቃቅስ ሳምንቱ ሙሴኒ ተባለ፡፡ ነቢያትም አርባ አርባ ቀን ጾመው ከአለፉ በኋላ የሙሴ ሕግና ትንቢተ ነቢያት ፈጻሚ የሆነው ምላካችን እንደ እነሱ 40 ቀንና 40 ሌሊት መጾሙን የሚያስታውስ ነው፡፡ /ዘፀ.24፥18፤ 1ኛ.ነገ.19፥8፤ ማቴ. 4፥1-4/፡፡
ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
          
​​​​ዐቢይ ጾም

ዐቢይ ለምን ተባለ ቢሉ ‹‹ዐበየ›› ማለት ከፍ አለ ማለት ሲሆን ከዚህም ግስ አቢይ የሚለው ቅጽል ይገኛል፡፡ ዐቢይ ማለት ከፍ ያለ ትልቅ ማለት ነው፡፡

ዐቢይ ጾም የተባለበት ምክንያት፡-

. ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ጾም ስለሆነ

. በቀኑ ቁጥር ከሌሎች አጽዋማት የሚበልጥ ስለሆነ

. ሦስቱ ታላላቅ የሰይጣን ፈተናዎች ማለትም 'ትዕቢት' 'ስስት' 'ፍቅረ ነዋይ' ድል የተመቱበት ስለሆነ ነው፡፡

በቤተክርስቲያን ስያሜ መሰረት በዐቢይ ጾም ውስጥ የሚውሉ ሰንበታት እያንዳንዳቸው መጠሪያ ስም ሲኖራቸው እነርሱም፡-

1. ዘወረደ
የዐቢይ ጾም የመጀመሪያው ሰንበት ሲሆን ይህም ቅድመ ዓለም የነበረ ዓለምን ፈጥሮ የሚኖር አልፋና ኦሜጋ ከሰማየ ሰማያት መውረዱንና ከእመቤታችን ከቅድስተ ቅዱሳን ከንጽሕተ ንጹሐን ከድንግል ማርያም መወለዱን የሚያመለክት ሥያሜ ነው፡፡

2. ቅድስት
ይህ የሁለተኛው ሰንበት ስያሜ ሲሆን የተባለበትም ምክንያት ስለ ዕለተ ሰንበት ቅድስና ስለሚያወሳ ነው፡፡ እንዲሁም ይህ ዕለት ዕለተ እግዚአብሔር የተባለች የሰንበት ክርስቲያን ቅድስናን ያመለክታል ምክንያቱም የዚች ዕለት ጌታ እርሱ ቅዱስ እግዚአብሔር ነውና ስለዚህም ዕለተ ሰንበት ቅድስት ተብላለች፡፡

3. ምኩራብ
ይህ የሦስተኛው ሰንበት ስያሜ ሲሆን በዚህ ሰንበት ጌታ በመዋዕለ ትምህርቱ በምኩራብ ገብቶ ማስተማሩ ይነገራል፡፡ እንዲሁም ይህች ዕለት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኩራብ ገብቶ እንዳስተማረ የሚታሰብበት ዕለት ነው፡፡ ምኩራብ ማለት የቤተ አይሁዳውያን የጸሎት ቤት ነው፡፡

4. መጻጉዕ
ይህ የአራተኛው ሰንበት መጠሪያ ሲሆን ይህም ዕለት ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድውያንን መፈወሱ እውራንን ማብራቱ ለምጻምን ማንጻቱ ሽባዎችን መተርተሩ የሚያነሳ መዝሙር የሚዘመርበት እንዲሁም እነዚህ ሁሉ ድንቅ ገቢራተ ታምራቶች የሚዘከሩበት ዕለት ነው፡፡

5. ደብረ ዘይት
ይህ የአምስተኛው ሰንበት መጠሪያ ሲሆን ይህም ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሆኖ ነገረ ምጽአቱን እንዳስተማረ የሚወሳበት ሰንበት ነው፡፡ ደብረ ዘይት ማለት ወይራ የበዛበት ተራራ ማለት ነው፡፡

6. ገብርኄር
ይህ የስድስተኛው ሳምንት ሰንበት ስያሜ ሲሆን ይህም ዕለት ለጌታው ታማኝና በጎ የሆነው ባርያ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ ተብሎ እንደተመሰገነ የሚነገርበት ዕለት ነው፡፡

7. ኒቆዲሞስ
ይህ የሰባተኛው ሰንበት ስያሜ ነው፡፡ ይህም ዕለት ኒቆዲሞስ የተባለው የአይሁድ መምህር በሌሊት ወደ ጌታው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እየመጣ ይማር እንደነበረ ይታሰብበታል በዚም ዕለት የኒቆዲሞስን ታሪክ የሚያስታውስ መዝሙር ይዘመርበታል፡፡

8. ሆሳዕና
ይህ የስምንተኛው ሳምንት ሰንበት መጠሪያ ሲሆን ይህም ዕለት በነቢዩ በዘካርያስ ላይ የተጻፈው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ጌታችም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያይቷ እና በውርንጭላይቷ ላይ ተቀምጦ ሆሳዕና በአርያም ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ ተብ እየተመሰገነ ወደ ቤተ መቅደስ መግባቱ የሚተሰብበት ዕለት ነው፡፡ ሆሳዕና ማለት ‹‹እባክህ አሁን አድን አሁን ባርከን›› ማለት ነው፡፡ በሰሙነ ሕማማት ጸሎተ ፍትሃት ጸሎተ አስተስርዮ ስለማይፈጸም ጸሎተ ፍትሃትና አስተስርዮ የሚደረገው በዚሁ ዕለት ነው::

   ጾሙን የበረከት ጾም ያድርግልን፡፡
ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
          
ቅዱስ ማርቆስ ወንጌላዊው እንደሚነግረን ጌታችን የተፈተነው በአርባኛው ቀን ብቻ ሳይሆን አርባውን ቀን በሰይጣን እየተፈተነ ነው የሰነበተው፡፡(ማር 1:13) መጻሕፍት በአርባኛው ቀን የተፈተናቸውን ፈተናዎች ብቻ ይዘው መገኘታቸው በሚበልጠው ለመናገር ነው እንጂ እነዚህን ብቻ ነው የተፈተነው ማለታቸው አይደለም፡፡ በፈተና የሚያልፉ ክርስቲያኖች በደል ሳይገኝበት ‹በነገር ሁሉ የተፈተነ› እና በድካማቸው የሚራራላቸው አምላክ እንዳላቸው አውቀው ይጽናኑ ዘንድ እርሱ በበጎ ለሚፈተኑ ሁሉ በኩር ሆነ፡፡ (ዕብ 4:15)

            ጌታ የተፈተነው ከተጠመቀ በኋላ ነበር፡፡ ይህ ለእኛ ምን ያስተምረናል? ምዕመናን ሁል ጊዜ የእግዚአብሔርን ኃይል ፣ልጅነትን በጥምቀት ከተቀበሉ በኋላ የሚያስተናግዱት የፈተና ሕይወት እንዳለ ነው፡፡ ሰይጣን ደስ የሚሰኝበት ምንም ዓይነት የጽድቅ ሥራ ባለመኖሩ ፣የፈተና ወጥመዱን የሚዘረጋው ፈቃዱን ለሚፈጽሙ ደካሞች ሳይሆን በጥምቀት የእግዚአብሔርን ልጅነት ላገኙ እና የዲያቢሎስን ክፋት በመልካም ተጋድሎ ለሚቃወሙት ጽኑዓን ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ‹ኃይልን የምንታጠቀው እኮ ለመዋጋት ነው እንጂ ለመቀመጥ አይደለም› ይለናል! እውነት ነው!፡፡ እግዚአብሔር በጥምቀት መንፈሳዊውን ኃይል የሚያስታጥቀን ከጠላት ዘንድ ፋታ የሌለው ውጊያ ስላለብን አይደለምን? ታዲያ ለምን ለፈተና ሁል ጊዜ እንግዶች እንሆናለን? 

            አምላካችን በወንጌል በምሳሌ እንዳስተማረው ኢየሩሳሌም ከተባለች ልዕልና ኢያሪኮ ወደ ተሰኘች ትሕትና አንድ ሰው የተባለ አዳም ሲወርድ በመንገድ አጋንንት አግኝተው ፈትነው ፣ልጅነቱን ቀምተው ፣በኃጢአት ቁስል አቁስለው በሞትና በሕይወት መካከል ጥለውት እንደሄዱ ፤ የአዳምና የሔዋንን እዳ ለመክፈል ሰው የሆነ ክርስቶስም ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ሲወርዱ በሚያገኙት የቆሮንቶስ በረሃ አዳምን ያቆሰሉትን አጋንንት ድል ነስቶለታል፡፡ (ሉቃ 10) 

           ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
          
+++ ልሸፈንላችሁ? +++

ሙሴ ከሲና ተራራ ወርዶ ከሕዝቡ ጋር ሲገናኝ የፊቱን ማንጸባረቅ አይተው "ተሸፈንልን" ያሉት ሕዝቡ ናቸው። እርሱ "ከእግዚአብሔር ጋር ስነጋገር ቆይቼ እኮ አሁን መውረዴ ነው? ምነው የፊቴ ብርሃን አስቸገራችሁ? ልሸፈንላችሁ እንዴ?" አላለም። እንዲያውም ቅዱስ መጽሐፍ "ሙሴም ከተራራው በወረደ ጊዜ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ተነጋገረ የፊቱ ቁርበት እንዳንጸባረቀ አላወቀም ነበር" ነው የሚለው።(ዘጸ 34፥29) ለቅዱሳን እግዚአብሔር በፊታቸው የሚሥለው የክብር ብርሃን እነርሱን ለሚመለከታቸው እንጂ ለራሳቸው አይታወቃቸውም። እውነተኞቹ ቅዱሳን  "ተሸፈኑልን" የሚባሉ እንጂ "ልሸፈንላችሁ" የሚሉ አይደሉም።

ጥቂት በጎ ሥራ ሠርተህ ጻድቅነትህን በግድ ለማሳየት አትሞክር። ሌሎች ተሸፈንልን ይበሉህ እንጂ፣ አንተ ራስህ "ልሸፈንላችሁ" እያልህ የዋሐንን አታስጨንቅ።

በአገራችን የሚታወቅ ተረት አለ። አንድ ጊዜ ትንኝ በሬ ቀንድ ላይ ቆመችና "ከብጄህ እንደ ሆነ ንገረኝና ልነሣልህ" አለችው። በሬውም "እንኳን ልትከብጅኝ መኖርሽንም አላወቅሁም" አላት።

"ጻድቃን እንደ ሆኑ በራሳቸው ለሚታመኑና ሌሎቹን ሁሉ በጣም ለሚንቁ ይህን ምሳሌ ነገራቸው"   ሉቃስ 18፥9
ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
          
ለቅዳሴ ያለንን ቦታ እንፈትሽ

እስቲ ቅዳሴ የምንቀርበትን ምክንያቶች እንፈትሻቸው ክርስቶስ በአካል ከሚገኝበት ቦታ ምን በልጦብን ነው የምንቀረው? ኳስ መጫወት ፣ ስፖርት መሥራት ፣ እንቅልፍ? እነዚህ ነገሮች በራሳቸው ጥሩ ቢኾኑም የጌታን ቦታ እየወሰዱ ከኾነ ግን ዝሙት ናቸው። ቅዱስ አውግስጢኖስ "አንድን ነገር የሙሽራውን የክርስቶስን ቦታ እስኪወስድ ድረስ የምንወድ ከኾነ በሙሽራችን ላይ የሚፈጸም ዝሙት ነው" ይለናል። ለአንድ ክርስቲያን በጌታ ቀን በዕለተ እሑድ ቅዳሴ ቀርቶ ሌላ ቦታ መዋል የሙሽራውን ድግስ አልፈልግም በማለት በሙሽራው ላይ የሚፈጸም አመጽ ነው! አሁን በምድራዊው የክርስቶስ ሠርግ ላይ ካልተገኘን እንዴት በሰማያዊው ሠርግ ላይ የመሳተፍ እድል አለን ብለን እናስባለን? ለቅዳሴ ፣ ለክርስቶስ ያለንን ቦታ እንፈትሽ።

መንፈሳዊ ሕይወት ላይ ጥሩ ነን ብለን እራሳችንን የምናስብ ሰዎችም ቢኾን ለቅዳሴው ያለንን ቦታ መልሰን እንፈትሽ፤ ስንት ጊዜ ነው ማኅሌት ተሳተፍን ብለን ቅዳሴው እየተጀመረ ረግጠን የወጣነው? ስንት ጊዜ ነው በጌታ ቀን ቅዳሴውን ትተን መንፈሳዊ ጉዞ ብለን የሔድነው? በቤተክርስቲያን ውስጥ የትኛውም አገልግሎት ሊቀር ይችላል ቅዳሴ ግን በፍጹም አይቀርም ቅዳሴ ለቤተክርስቲያን ሕይወቷ ነውና!

የታረደው በግ ደም እንዳይፋረደን በበጉ ሠርግ ላይ እንገኝ የሕይወትንም መድኃኒት እንቀበል!
ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
          
መቋሚያ
ብዙውን ከእንጨት የሚዘጋጅ እንደ በትር ዘለግ ያለ ከወደ ጫፉ መስቀል ቅርጽ ያለው ነው፤ በአሁኑ ጊዜ በአብዛኛው የ "ፐ" ቅርጽ ያለው አሊያም ድቡልቡል የሆነ ነው፤ ከወደ ጫፉ የሚደረገው ነገር የብር ፣የነሐስ ፣የወርቅ፣ የብረት፣ የቀንድ ና የእንጨት ሊሆን ይችላል

አገልግሎቱም
መደገፊያ ፣ መሞርኮዧ ና መዘመሚያ ሲሆን ይህም ከከበሮ እና ጸናጽል ጋር እንዲሁም ብቻውን ከማህሌት ላይ በዝማሜና በሽብሸባ ያገለግላል

ምስጢሩ
መቋሚያ የአዳም ተስፋና ከእመቤታችን ተወልዶ በዕጸ መስቀል ላይ የተሰቀለው የጌታችን የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው።

👉 አንድም መቋሚያ ያዕቆብ ትምህርተ መስቀል ያለበት በትር በፊቱ እያቆመ ይሰግድና ይጸልይ የነበረበት ምሳሌ ነው

👉ካህናት መቋሚያን በትከሻቸው አድርገው  ወዲህ ወዲያ ማለታቸው አይሁድ በዕለተ አርብ መስቀል አሸክመው ወደ ቀራንዮ መመውሰዳቸው

ዝማሜ ሚመሰለው በህማማተ ክርስቶስ ነው። መቋሚያው በመስቀል ይመሰላል።ካህናቱ መቋሚያቸው ከዜማ ጋር አስማምተው በዝማሜ ወቅት መቋሚያውን ወደ ግራ ወደ ቀኝ ማድረጋቸው አይሁድ ኢየሱስን አንዴ ወደግራ አንዴ ወደቀኝ ከነመስቀሉ ማንገላታታቸውን ለማስታወስ ነው። ከዛ ወደታች መሬቱን መምታታቸው ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ግርፋቱ ሲበዛበት መሬት ላይ መውደቁን ያሳያል።

ጽናጽል
ከብር ከነሐስ-ከሌላም ብረት የሚሰራ፤ እንዲሿሿ ከብረት ቅጠል የሚደረግበት ሲሆን አገልግሎቱም ለእግዚአብሔር ክብር ይዘመርበታል። ጽናጽል ከከበሮ ጋር አብር የሚሄድ የዜማ መሳሪያ ነው

የብረት ቅጠሎቹ ሲያንሱ 5 ሲበዙ 7 ይሆናሉ። 5 ሲሆን አምስቱ አዕማደ ሚስጢር 7 ሲሆን በሰባቱ ሰማያት ይመሰላል።

👉2 የብረት ዘንጎች(የብረት ቅጠሎቹን የሚይዙት) ላይ ከታችኛው ላይ 2 የብረት ቅጠሎች የሚኖሩ ሲሆን ይህም ጌታችን ልደቶች  ማለትም ቅድመ ዓለም ያለ እናት ከአብ ፤ ድህረ ዓለም ደግሞ ያለ አባት ከእመቤታችን መወለዱ ምሳሌ ነው

👉 የብረት ቅጠሎቹ 3 መሆን የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ነው

👉ድምጹ ያማረና መልካም መሆኑ በመላእክት ዜማ ይመሰላል (ሰብሕዎ በጽናጽል ዘሠናይ ቃሉ እንዲል መዝሙረኛው ዳዊት በመዝሙር 150)
👉ጽናጽል ወዲህ ወዲያ ማለቱ ጌታችን የመንገላታቱ ምሳሌ ነው

ከበሮ
ከእንጨት ተዘጋጅቶ በጠፍርና በቆዳ የሚለጎም የዜማ መሳሪያ ነው።

ለክብረ በዓል ለበዓል ለበዓለ ንግሥ ዕለት ለእግዚአብሔር ክብር የሚመታ የሚመዘመርበት ነው

በከበሮ ወበመዝሙር ይዜምሩ ሎቱ እንዲል መዝሙረኛው ዳዊት በመዝሙር 149

ምስጢሩ-
አፉ ሁለት ነው፤ ጠባብ እና ሰፊ
   ሰፊው- ቁመት ደረት ምሉዕ በኩለሄ/እግዚአብሔር በሁሉ ሙሉ መሆኑን ሲሆን

ጠባቡ- ደግሞ ወልድ በአጭር ቁመት መወሰኑን የሚያመለክት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው

እንጨቱ ከቆዳ የተለጎመበት ጠፍር- ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አይሁድ ስድስት ሺህ ስድስት መቶ ስልሳ ስድስት ጊዜ የገረፉበት የግርፋቱ (የገላው ሰንበር) ምሳሌ ነው

ከበሮ የሚለብሰው ሱቲ ጌታችን የለበሰው ቀይ ግምጃ ምሳሌ ነው

የከበሮ አመታት ምስጢር
መጀመሪያ ከበሮ ተቀምጦ ቀስ እየተባለ ነው የሚመታው።

👉በመሬት መመታቱ ጌታችን አይሁድ በመሬት እየጎተቱ መምታታቸውን
👉በግራ እና በቀኝ ሲመታ ከቀኝ ሲመታ ወደ ግራ ከግራ ሲመታ ወደ ቀኝ ማዘንበሉን ለማስታወስ ነው
👉ከበሮ በትከሻ ተደርጎ ሲመታ ከወደቀበት እንደመቱት ፤በፍጥነት ሲመታ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሊሰቀል ሲቃረብ በፍጥነት መምታታቸውን ያስታውሰናል

የማሕሌት ተወዛዋዦች

ዛሬ ለወጉ ማሕሌት አንቀርም ፣ ቸብቸቦ ይጀመራል ፣ ወጣቶች ከበሮውን ለማንሳት ሪከርድ በሚያሻሽል ፍጥነት የከበሮውን ገመድ ከጀርባቸው ያዋሕዱታል (እንዲያው ወጣቶች ስንል በእድሜ ማለታችን አይደለም ቆብ የደፉ መስቀል የጨበጡ ቀጣይ በምናየው መልኩ የሚሳተፉትንም የሚገልጽ ቃል ነው እንጅ ) : አፍታም ሳይቆይ እንደ አሎሎ ወርዋሪ መሽከርከር ይጀመራል : አንድ እጅ ተዘርግቶ እስክስታው ይቀልጣል: ሁለት እግር ከፍ እያለ መዝለል ይጀመራል : አሁን በአንደበት የሚነገረው ስብሐተ እግዚአብሔር ነው መሬት ላይ ደግሞ ኅብረ ብሔራዊ ጭፈራ ሁኗል : ነፍስ ምን እየተካሄደ እንዳለ ዘንግታለች : ስጋ ግን እየተንቀጠቀጠ ነው : የስሜት እሳት ተቀጣጥሏል : እሽሽሽሽሽሽ የሚል ማጀቢያ መሆኑ ነው ከአንደበት አትጠፋም : የሙቀቱ መጠን ከቁጥጥር እየወጣ ነው : ወደ ሴቶች ጉዞ ይጀመራል : አሁን ሴቶች በቅርበት እየተመለከቱ ነው ከበሮው ላይ ብትሩ ይበረታል : የዝላዩ ከፍታ ይጨምራል : ጿጿጿጿጿ የሚል የጽናጽል ድምጽ የሚያሰማ ቢኖርም ፈገግ ተብሎ ታልፎ ጭፈራው ይደራል : ሊቃውንቱ ቢናገሩም የተጠሉ ይሆናሉ : ነፍስ ከተኛች ቆይታለች ከዱካካዋ ልትነቃ አልቻለችም : ከጎን ከበሮ የሚመታው ጓደኛ በመቺው ትዕዛዝ አመታቱን እየቀረጸ ነው : Tik Tok ቀጣዩ የቪዲኦው መሰራጫ መድረክ ነው : የታይታ ክርስትና ! እንደ ፈሪሳውያን ሰው እንዲያይ ብሎ መዘመር ! ተቃራኒ ጾታ እያዩ መስፈንጠር ! በከበሮ ትዳር አይፈለግም ! መዝለል ፣ መሽከርከር ፣ መስፈንጠር፣ መንቀጥቀጥ ፣ እሽሽሽሽሽ ማለት ፣ ወደ ተቃራኒ ጾታ አንጋጦ መዞር ይቁሙ !

ሁለት እጅ ስላለህ እና መምታት ስለቻልክ ብቻ ከበሮ አትሸከም ምስጢሩን ተረዳ ያኔ ሲገባህ ዕንባህ ከዐይንህ ያለማቋረጥ ጉንጮችህን መወረጃ አድርጎ ሲጎርፍ ይታወቅሀል : ያኔ ልብህ እንጅ እግርህ አይዘልም : ያኔ የምትንቀጠቀጠው እግዚአብሔርን በመፍራት ይሆናል: ያኔ ስትዘል አፍአዊ ላብ ሳይሆን ሕሊናህ ይሆናል በተመስጦ የሚያልበው : ያኔ እንደ መላእክት የሰማይ የመቅደሱ በር እስኪከፈት እንዲዘምሩ አንተም የልቦናህ በር ተከፍቶ ለምስጋና ትታትራለህ ። አየኋት : አወቅኳት : ወደድኳት ብሎ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ የመላዕክትን ዝማሬ ሰምቶ መጦ ባቀናት ቤተክርስቲያን ምድራዊ ተወዛዋዦች ገብተናልና ወደ ልቦናችን እንመለስ ።

በወንዶች ብቻ የሚቆም ግብር አይደለም በአንስቶችም ተመሳሳይ ፍሬ አፍርቶ ተንዠርቅቆ እናገኘዋለን : በሰንበት ትምህርት ቤት እንዲሁ በአደባባይ በዓላት ቁጥራቸው ትቂት ያልሆኑ በከበሮ ላይ መከራ አጽንተው በመከራ ድር ተተብትበው ይኖራሉ : አንቲ ተቃራኒ ጾታሽ እንዲያይሽ ካልሆነ ምን ያሽከረክርሻል ? ምን ያዘልልሻል ? ወደ እነማን ፊትሽን ዙረሽስ ትመቻለሽ ? ወደፊት ወደ ኋላ ስትይ የክርስቶስን መገፋት ታስቢያለሽ ወይስ ወደፊት ሄደሽ ልብሽ የወደደውን ትፈቅጃለሽ ? ከንቱ ውዳሴን ሽተሽ በሰፈሩ የከበሮ አመታትሽ እንዲወራ ከሆነ እኅቴ ሆይ የገሀነም ደጃፍ ላይ ነሽና ሳትገቢ ተመለሽ! በአደባባይ ምድርን የሚያበራ እሳት ከማቀጣጠል በሕሊና መቅረዝ ትቂት መንፈሳዊ ማኅቶት ማብራት ይሻላል ! በእውነት እናስተውል ! እነ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት እኮ በዝማሬያቸው ሕሙም ይፈውሱ ነበር በእኛስ? ዘመርን ብለን እራሳችን ሕሙም ሆነን እንመለሳለን ! ወደ እነእንተና ለይቶልን በኅብረ ብሔራዊ ጭፈራ እግዚአብሔር ቢመለክ ምን ችግር አለው ብለን የኅብረት ዘፋኞች ከመሆናችን በፊት ለብው ! አምላከ ያሬድ ወዳዊት ወእዝራ የቀናውን መንፈስ ያድለን ! የቅዱሳኑ ዝማሬ ወላዲተ ቃል ድንግል ማርያም በረድኤት አትለየን።
ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
          
​​​​ቅድስት (የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት)

«ቅድስት» ማለት የዘይቤ ፍችው « የተቀደሰች የተለየች » ማለት ነው። ምስጢራዊ መልእክቱ ግን የምስጢረ አድኅኖት ታላላቅ ሥራውን ለመጀመር መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶሰ በገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ ከቆመ ሳያርፍ፣ ከዘረጋ ሳያጥፍ የጾማት የአርብዓው ቀንና ሌሊት ልዩ የሆነችና ክብርት ጾም የምትጀመርበትን ሁለተኛ ሳምንት ከልብ ያሳስበናል፡፡ ማቴ. 4-2

ቅድስት የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሰንበት ስያሜ ነው፡፡ ስያሜውም ከኢትዮያዊው የዜማ ሊቅ ከቅዱስ ያሬድ የተገኘ ነው። ከዚህ ሰንበት ዋዜማ ጀምሮ ስለ ዕለተ ሰንበት ቅድስና ይዘመራል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ሰንበቱን ስለ ቅድስና ልጆቿን ታስተምርበታለች ፡፡

በቅዳሴ ጊዜ የሚሰበከው ምስባክ ፤ የሚነበቡ መልዕክታት ፤የሐዋርያት ሥራ ና ወንጌል ስለ ቅድስት የሚያስተምሩ ናቸው፡፡

‹‹ቅዱስ›› ማለት ልዩ፤ ክቡር ማለት ነው፡፡እግዚአብሔር አምላካችን በባሕርዩ ቅዱስ ነው፡፡ ይህም ቅድስና ከማንም ያላገኘው የባሕርይ ገንዘቡ ነው። መጻሕፍትም የባሕርይ ቅድስናውን ተባብረው መስክረዋል፡፡ ባባሕርዩ ቅዱስ ስለሆነ ‹‹ቅዱስ፡ቅዱስ፡ቅዱስ›› እየተባለ ይመሰገናል፡፡ ( ኢሳ 6፡1-3፤40፡25 ራዕ 15፡4 ፤ 1ሳሙ2፡2-3፡፡) እኛም ቅዱስ ልጁ በሥጋ ተገልጦ እንዳስተማረን በየዕለት ጸሎታችን ‹‹ስምህ ይቀደስ›› እንለዋለን፡፡

የቅድስና ምንጭ ፡ ቅድስናን የሚሰጥ እርሱ ብቻ ነው፡፡ ‹‹ ቅዱስ ›› የሚለው ቃል ለሰዎች ፡ለመላእክት ፡ ለቦታ ፡ለዕቃ: ለዕለታት … ቢቀጸልም ቅድስናቸው በባሕርይው ቅዱስ ከሆነው ከእግዚአብሔር የተገኘ ነው፡፡ ይህም የጸጋ ቅድስና ይባላል፡፡

እግዚአብሔር ቅዱስ ስለሆነ በመልኩና በምሳሌው አክብሮ የፈጠረንን እኛም ቅዱሳን እንድንሆን ይፈለጋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ዳሩ ግን እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁን›› ተብሎ ስለተጻፈ የጠራቸው ቅዱስ እንደሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ ›› ያለንም ይህንን ሲያስተምረን ነው። ከመፈጠራችን አስቀድሞ መጠን በሌለው ፍቅር የወደደን እግዚአብሔር ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣን ፤ ለውርደት ሳይሆን ለክብር፤ ለርኩሰት ሳይሆን ለቅድስና፤ ለሞት ሳይሆን ለሕይወት ነው፡፡ የመፈጠራችንም ዓላማ በፊቱ በፍጹም ምግባርና ሃይማኖት በመመላለስ ከእርሱ ጋር እንድንኖር ነው፡፡ ብርሃን ከጨለማ፡ ጽድቅ ከኃጢአት፡ ጋር ኅብረት የለውምና ከእርሱ ጋር ለዘላለም ነግሰን ለመኖር በቅድስና መኖር ይጠበቅብናል፡፡

ቅድስናችን በኑሮአችን ሁሉ እንዲሆን ታዘናል (1ጴጥ1፡15)፡፡ ስለዚህ በተሰማራንበት የሥራ መስክ ፣ በማኅበራዊ ኑራአችን ፣በምንበላው ምግብ ፣በምንለብሰው ልብስ ፣ በንግግራችንና በመሳሰለው ሁሉ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኘውን በማድረግ እግዚአብሔርን በሚሞት ሥጋችን እናክብረው፡፡ ‹‹እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ የኃጢአትንም ጭንቀት ከእኛ አስወግደን በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግስት እንሩጥ፡፡

የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን እንከተለው፤ እርሱ ነውርን ንቆ ፣ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጧል ›› ተብሎ እንደተጻፈ ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ ተጋድሎ አድርገን ከኃጢአት ርቀት በቅድስና እንድንኖር ይገባናል (ዕብ 12፡1)።

ሥጋዊ ምኞታችንንና መሻታችንን ሰቅለን አሮጌው ሰዋችንን አስወግደን ንስሐ ገብተን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብለን በቅድስና እንድናኖር ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
          
+++ የጀማሪ ጠባይ +++

መንፈሳዊ ሕይወትን ገና ስትጀምረው ለፍጹምነት ጥቂት የቀረህ ያህል ይሰማሃል። አንተ ጋር ያለው ደስታ እና ሰላም ሌሎች ጋር የሌለ ይመስልሃል። በዚህች ሁከት በሞላባት ዓለም አንተ ብቻ ክርስቶስን እንዳገኘኸው ታስባለህ። የቀረው ሕዝበ አዳም እንዲሁ በከንቱ ሲርመሰመስ የሚውል ባካና ሆኖ ይታይሃል። ታዝንለታለህ፣ አይይይ ይህ ኃጢአተኛ ሕዝብ ምን ይሻለዋል? ትላለህ።

የእውነተኛ መንፈሳዊ እድገት መገለጫ ግን ይህ አይደለም። ሰው ወደ እግዚአብሔር እየቀረበ ሲመጣ ከሌላው ሰው ይልቅ የራሱ ጉድለት ይታየዋል። መንፈሳዊነት የሚገልጥልህ ሰዎችን ተመልክተህ የምትፈርድበትን ውጫዊ ዓይንህን ሳይሆን ራስህን አይተህ የምትወቅስበት የውስጥ ዓይንህን ነው። መንፈሳዊ ሕይወትህ ሲጎመራ "አይ ሰው" ሳይሆን "አይ እኔ!" ያሰኝሃል። አባ ማቴዎስም እንዲህ ይላል "ሰው የበለጠ ወደ እግዚአብሔር ሲቀርብ ይበልጥ ኃጢአተኛ መሆኑ እየታየው ይመጣል። ነቢዩ ኢሳይያስ እግዚአብሔርን ካየ በኋላ ከንፈሮቼ የረከሱብኝና የጠፋሁ ሰው ነኝ እንዳለ።"

ከብቃት ደርሰህ መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ ቢታዩህ እንኳን ሁሉ እንዳንተ ስለሚመስልህ እንደ ዮሐንስ ሐጺር "ሚካኤል ይበልጣል ወይስ ገብርኤል?"  እያልህ ከአጠገብህ የቆመውን ትጠይቃለህ እንጂ "አይይ አንተ እንኳን ገና አልበቃህም። ብዙ ይቀርሃል" ብለህ ወዳጅህን አታናንቅም። ይልቅ "ለእኔ ብቻ ገልጦ ለሌላው እንዲሰውር የሚያደርገው ምንም ቁም ነገር የለኝም" በማለት ከወንድምህ የተሻልህ እንዳልሆንክ በፍጹም ልብህ ታምናለህ።

ለመንፈሳዊ ሕይወት አዲስ ስትሆን ገና ጥቂት ጸልየህ፣ ጥቂት ጾመህ፣ ጥቂት መጽውተህ ሳለ ግን ሩጫህን ወደ መጨረሱ የተቃረብህ ይመስልሃል። ጉዞህን በግማሽ እርምጃ ከመጀመርህ ከፍጻሜው ላይ የደረስህ ያህል ይሰማሃል። "እኔን ምሰሉ" ማለት ያምርሃል። ነገር ግን መንፈሳዊ ሕይወት የቱንም ያህል ብትሮጥበት ሁል ጊዜ እንደ ጀማሪ የሚያደርግ ረጅም ጎዳና ነው። ሰማንያ ዓመት በገዳም ሲጋደል የነበረው አባ ሲሶይ ነፍሱ ከሥጋው ልትለይ በቀረበች ጊዜ ብዙ መነኮሳት በአልጋው ዙሪያ ከበውት ሳለ ቅዱሱ "አምላኬ ሆይ፣ እባክህ ለንስሐ የሚሆን ጥቂት ጊዜን ስጠኝ?" እያለ በልቅሶ ሲማጸን ሰሙት። በዚህ የተገረሙት መነኮሳቱ አባ ሲሶይን "አባታችን አንተ እድሜ ልክህን በንስሐ የኖርህ መምህረ ንስሐ ሆነህ ሳለ እንዴት አሁን ጥቂት የንስሐ ጊዜን ትለምናለህ?" ቢሉት፣ ቅዱሱም "ልጆቼ ይህን መንፈሳዊ ጥበብ (ንስሐን) ገና አሁን መጀመሬ ነው" አላቸው።

ጌታ ሆይ መንፈሳዊ ሕይወት እኖር ዘንድ አስጀምረኝ፤ ገና ጀማሪ ሳለሁ ደርሻለሁ ከማለትም ሰውረኝ። እንድቆም አትፍቀድልኝ፤ ወደ አንተ ሳበኝ፣ አሳድገኝ።

ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
          
2025/07/01 17:28:02
Back to Top
HTML Embed Code: