Telegram Web Link
#እናመሰግናለን| ሃይለየሱስ ሻወል
#hawassa| እናመሰግናለን!
አንድ ቀን በህዳሴ ቅ/መደበኛ ት/ቤት ለተማሪዎች ድጋፍ ስናደርግ ተዋወቅን። በጫወታችን በጎ ስራ የሚያስደስተው እንደሆነና በግሉ የሚደግፋቸው ልጆች እንዳሉ ነገረኝ። በእለቱም እሱ ለ8 ተማሪዎች ዩኒፎርም ያሰፋውን ለመስጠት ነበር የመጣው። በጣም ደስ አለኝ። ሃይለየሱስ ይህን በጎ ስራ ሲሰራ ቢቆይም ለማንም ነግሮ አልነበረምና ፈጣሪ ብቻ ያውቃል።
እኛም የምንሰራውን ስራ ተመልክቶ በርካቶች ቃል እንደሚገቡት እንደሚደግፈን ገለፀልኝ። አመስግኜ ተለያየን።
ባለፈው ለፍሬ ህክምና ድጋፍ ስንጠይቅ ለኔ ሳይነግረኝ ቤታቸው ድረስ በመሔድ ለአባቷ 2000 ብር ሰጥቶ ሄዷል። አባቷ አንድ የፖሊስ አባል የፍፁም ጓደኛ ነኝ ብሎ ብር ሰጥቶ ሄዷል ሲሉኝ ከተገናኘን ስለቆየ እሱ መሆኑ ባይመጣልኝም ለማመስገን እንኳ አላገኘሁትም ነበር።
በቅርቡ ደግሞ ለጋሽ ለማ ድጋፍ ስናደርግ ሰምቶ ደወለልኝ እኔም ላያቸው ፈልጋለሁ አለኝ። እነፍሬ ቤት ሄዶ ገንዘብ የሰጠው እሱ መሆኑን አላወኩም ነበርና እሽ አልኩት። ሰሞኑን ትንሽ ስራ ስለበዛብኝ ለመገናኘት አልቻልንምና ለጋሽ ለማ 1000 ብር ባካውንታቸው እንዳስገባ በኮሜንት ስር ደረሰኙን አስቀመጠልን። በጣም ደነቀኝ በእውነት። ይህ ወጣት የፖሊስ አባል ሆኖ ለወገኑ ከህይወት እስከ ኢኮኖሚ ድረስ ለመርዳት ያለው ቁርጠኝነት አስደመመኝ። ዛሬ ደግሞ በመንገድ ሳልፍ ጠራኝ። እንዳየሁት ዞሬ ተመለስኩና አገኘሁት። ለፍሬ ቤት ድረስ በመሔድ የሰጠው እሱ መሆኑን አወቅሁ።
ለተማሪዎችም የበኩሉን እንደሚያደርግ ሲገልፅልኝ ተደንቄ አመስግኜ ተለያየሁ። አፍታ ሳይቆይ ደወለና ሶስት ደርዘን ደብተር ከብዕር ጋር ገዝቶ አስረከበኝ! ሰውን ለመርዳት ልብ ካላቸው ቅን ሰዎች መሐከል ለየት ያለብኝ ሰዎች ያሉበት ድረስ በመሔድ ያለ ጉትጎታና ልመና ለመርዳት ዝግጁ ሆኖ ስላገኘሁት ታመሰግኑና ታበረታቱልኝ ዘንድ ለሌሎች አርዓያ ይሆን ዘንድ ባይፈልግም ለምኜ አቀረብኩት።
በወጣው ይተካ የ2016 የትምህርት ዘመን የተማሪ ልጄ አንድ ፓኮ ለአንድ ተማሪ ንቅናቄን ሻማ ለኩሷል እንድትቀላቀሉና ማንም ተማሪ በደብተርና ብዕር ምክንያት ከትምህርት ብርሃን እንዳይቀር የበኩላችንን ትውልድ ላይ እንስራ ለማለት እወዳለሁ ክበሩልኝ!
ሐዋሳ ሐምሌ 29/2015
#ለእርጅና_እጅ_ያልሰጡት_አባት| ኡኩሞ ኦሳንጎ
#hawassa|
በደርግ ዘመን ወጣት እያሉ ነው ወደ ሐዋሳ የገቡት። እድሜያቸው ወደ ዘጠና ተቃርቧል። የሚታወቁት አሮጌው ገበያ የእጅ ጋሪያቸውን ይዘው ለወጣት የሚከብድ ሸክም ሸክፈው በተባሉበት ታማኝ ሆነው ገበያተኛን ሲያገለግሉ ነው።
አሳቸው እንደሚሉት ባለትዳርና ለስራ ያልደረሰች (አራት አመት) ህፃን ልጃቸውን ለማስተዳደር፤ ኑሮን ለማሸነፍ መስራት ግድ ሆኖባቸው ያቅማቸውን በመታተር ላይ ናቸው።
በስተርጅና ይሄን ከባድ የጉልበት ስራ ካልሰሩ ቤተሰባቸው በረሃብ መቀጣቱና ለችግር መዳረጋቸው ስለማይቀር ይጣሩ እንጅ አሁን አቅም እየከዳቸው፣ ጤናም እየራቃቸው ቢሆንም ከመስራት ወደኋላ አላሉም። ቢደላማ መጦሪያቸው ነበር!
ከዚህ ቀደም ባለቤታቸው የቀን ስራ (የግንበኛ ረዳት) በመሆን ያቅሟን እየሰራች፣ እርሳቸውም ጋሪ እየገፉ የእለት ጉርሳቸውን ሲሸፍኑ ቢቆዩም አሁን ግን ባለቤታቸው ጤና ስላጡ የቤቱን ወጭ መሸፈን በእሳቸው ብቻ የተወሰነ ሆኗል። "እያቃተኝ ህመሜን ችዬ ..." ይላሉ ያሉበትን ሁኔታ ሲገልፁ።
የጋሽኡኩሞ እድሜ እየጨመረ ጤናም በመጥፋቱ ዛሬ እንደበፊቱ ጠንክረው ሰርተው የለት ወጭ ለመሸፈን አዳጋች ሆኖባቸው፤ አንዴ ሲያገኙ አንዴ ሲያጡ በችግር መኖር ከጀመሩ አመታት ተቆጥረዋል።
"እስከምሞት ስራ አላቆምም" የሚሉን አባታችን ወጣት ሆኖ ስራ የማይሰሩና የሚለምኑ ሲያዩ እንደሚቆጩ ያብራራሉ። "ምናለ አቅም ባይከዳኝ!" ይላሉ። እኛ አቅም ላጡ አቅም አንሆንም ወገን?!
ጋሽ ኡኩሞን በደምበኝነት ለረዠም አመታት የሚያውቋቸው ሲገልፁ ጥንካሬና ታታሪነት ብቻ ሳይሆን ታማኝነታቸው የበለጠ የሚያስመሰግናቸው እንደሆነ ተረድተናል። አቅም እያለ ከስራ ማጭበርበርና ልመናን ስራ ላደረጉ ሁሉ ከአባታችን ብዙ ሊማሩ ይገባል። ለዚህም አለን በማለት ከጎናቸው እንሁን።
ውድ የሐዋሳ ትዝታ ቤተሰቦች፣ እኝህን አባታችንን ለ ፊታችን አዲስ አመት አዲስ ሐይል እንሆናቸውና፣ በተቻለ መጠን ደግፈን ከከባዱ የጉልበት ስራ አላቀን ቀላል ጀብሎ እንኳን ሰርተው መኖር የሚችሉበትን እድል በመፍጠር የታታሪነታቸውን ዋጋ በመደገፍ እንድንረባረብላቸው የከበረ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
#መልካም_ዜና| ለሐዋሳና አካባሲዋ ነዋሪዎች
#hawassa| #መስማት_የተሳናቸው ት/ቤት
በከተማችን ብቸኛ የሆነው መስማት የተሳናቸውን ወገኖች በትምህርት ሲደግፍ የቆየው #ቪዥን_ግሎባል_ኢምፓወርመንት_ሐዋሳ በየትምህርት ቤቶች የሚገኙ የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ውስጥ መስማት የተሳናቸውን በርካታ ህፃናትና ታዳጊዎች በትምህርት ቁሳቁስ፣ እንዲሁም በሙያ ተማሪዎችን ያለምንም ክፍያ ሲደግፍ የቆየ ተቋም ሲሆን አሁን ደግሞ በቅድመ መደበኛ መስማት የተሳናቸውንና ሌሎች መደበኛ ተማሪዎችን ለማስተማር ፍቃድ አግኝቶ በምዝገባ ላይ ይገኛል።
የተቋሙ ዳይሬክተር አቶ ሐምሳሉ እንደገለፁት ተቋሙ መስማት የተሳናቸው ህፃናት በትምህርት ገበታቸው ባለመስማታቸው የሚገጥማቸውን ችግር መቅረፍ እና ማህበራዊ ተግባቦታቸውን ማሻሻልን በዋናነት ትኩረት አድርጎ እየሰራ ያለ ሲሆን፣ ከዚህ ጎን ለጎን ለወላጆችና ፍላጎቱ ላላቸው ሰዎች #የምልክት_ቋንቋ ስልጠናም ሲሰጥ ቆይቷል።
ከትምህርት ስራው በተጨማሪ በብቁ ባለሙያና ዘመናዊ የጆሮ ምርመራ /hearing test በማከናወን አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ እየሰራ ይገኛል።
ውድ የሐዋሳ ትዝታ ቤተሰቦች #visions_global_empowerment_hawassa በማህበረሰብ ድጋፍ የጎላ ተሳትፎም ያለው ሲሆን ለ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የሐዋሳ ትዝታ ለተማሪዎች የደብተርና ብዕር የማሰባሰብ መርሐ ግብር የበኩሉን ድጋፍ በማድረጉ በእናንተ ስም የከበረ ምስጋናችንን ለመግለፅ እንወዳለን።
ስለሆነም እርስዎ አልያም የሚያውቁት መስማት የተሳነው ወገን በአካባቢያችሁ ካለ ተቋሙን በቀጥታ (ቄራ ሜዳ በሚገኘው የተቋሙ ጊቢ) በመገኘት አልያም በመደወል የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እናሳውቃለን።
#የአዲስ_አመት_ስጦታ| ቃል በተግባር
#hawassa| የሚጋባ ደስታ😍
ወድ ቤተሰቦች ያለውን አካፍሎ በፍቅር መኖር ልምዱ የሆነው የሐዋሳ ህዝብ ፍሬዎች ከሆኑት #አለማየሁና #አሸናፊ (ቾምቤ) ጋር በጋራ በመሆን አቅም ላጡ፣ ቤት ዘግተው በአልን ለማሳለፍ ግድ ለሆነባቸው አባትና እናት አረጋውያን የሚጋባ ደስታን በስጦታዎች ፈጥረዋል።
በመጀመሪያው ዙር ዶሮ፣ ዘይትና ሽንኩርት እንዲሁም ገንዘብ ለ12 አረጋውያን አድርሰናል።
"ከፈጣሪ ጋር ትናንት ስጣላ ነበር... እግዜር ፀሎቴን ሳይውል ሳያድር መለሰልኝ"
ያሉት አንድ እናት በተደረገላቸው ስጦታ መደሰታቸውን ሲገልፁ በእንባ ታጅበው ነበር። በፊታቸው ደስታንና ፈገግታን የጫራችሁ እናንተ ውድ የሐዋሳ ጀግኖች የአባትና እናቶች ምርቃት በናንተ ይደር ለማለት እንወዳለን።
በእለቱ ከሐዋሳ ትዝታ አባላት እና የዘውትር ተሳታፊዎቻችን አንዱ የሆነው ወጣት #ሐይለየሱስ በቦታው በመገኘት ለአንዳንድ ወጭ የሚሆን በማለት የገንዘብ ስጦታ ለእናቶቹ በተጨማሪነት ሰጥቷቸዋል። እግዜር በወጣ ይተካ።
በተለይ አሌክስና ቾምቤ ሁለት ቤተሰቦች ቋሚ በየወሩ የ2000 ብር ድጋፍ እያደረጉ ሲሆን ከ70 ተማሪዎች በላይ ዩኒፎርምና የትምህርት ቁሳቁስ እንዲሁም የመምህር ደሞዝ ክፍያ በመፈፀም አጀብ የሚያሰኝ ከልብ የመነጨ ደግነታቸው ፈጣሪ ይባርካቸው ህልማችሁ ይሳካ ድመቁ ለማለት እንወዳለን።
በተጨማሪ የሐዋሳ ትዝታ ማስተባበሪያ ቢሮ የሚገኝብ መሐል ክፍለከተማ ጵ/ቤት ጎን በሚገኘው ቤተልሄም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ም/ር መምህር የሆኑት ወ/ሮ ምህረት በመገኘት ስጦታውን በክብር እንግድነት ስላበረከቱልን እንዲሁም ለመልካም ስራ ሁሌም ተባባሪ በመሆናችሁ የት/ቤቱን አስተዳደር ከልብ እናመሰግናለን።
ሁለተኛው ስጦታችን ደግሞ ከቤት መውጣት ለማይችሉ #ታማሚና #አስታማሚ እናትና አባቶች ቤት ለቤት ያደረግነውን ጉብኝት ይዘን እንቀርባለን።
ውድ ቤተሰብ ለመልካምነት ጊዜው አይረፍድምና መስጠት ባንችል እንኳ የሰጡትን ታበረታቱልን፣ ታመሰግኑልን ዘንድ በአክብሮት እንጨይቃለን!
መልካም አዲስ አመት!😍😍
የፍቅር የሰላምና የአንድነት አርበኞች!
2025/10/22 22:32:11
Back to Top
HTML Embed Code: