Telegram Web Link
#ጉምቱ_ስፖርተኛ| ጋሽ ከማል አህመድ
#hawassa| ባለውለታ 3ኛ ዙር ከ 30
     አንዳንድ ሰዎች አሉ ያሰቡት ሚሳካላቸው፣ የነኩት ሚባረክላቸው፣ ያየህ ይውደድህ ተብለው የተመረቁ፤ ከእነዚያ መካከል አንዱ ጋሽ ከማል ናቸው ብል ማጋነን አይሆንብኝም፡፡ ጋሽ ከማል ስፖርቱ መቼ ከደማቸው ጋር እንደተዋሃደ አያውቁትም ብቻ ራሳቸውን ሲያውቁ ከኳስ ጋር ናቸው፡፡

የሁሉ ወዳጅ ናቸው፡፡ ቀልድም ያውቁበታል፡፡ ቁምነገራቸውም በግልጽ ሚታይ ነው፡፡ ከትንሹም ከትልቁም ጋር መግባባትን ያውቁበታል፡፡ የሰውም መውደድ አላቸው፤ እሳቸውም እንዲሁ ተግባቢና ቀለል ያሉ ሰው ናቸው፡፡  እስቲ በስራ ዘመናቸው ምን አከናወኑ እንመልከት፡፡

• በአሰልጣኝነት ደረጃ ኤ ላይሰንስ፣
• ከ1966 – 1970 የአዲስ አበባ ምስራቃዊት ሄዋን ክለብ አሰልጣኝ፣
• ከ1971 – 1980 የእርሻ ጣቢያ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ፣
• ከ1981 – 1988 የአዲስ አበባ የአግሮ ኢንዱስትሪ መንግስት እርሻ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ፣
• ከ1988 – 1993 የሀዋሳ ከነማ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ፣
• በ1994 የወንጂ ስኳር ፋብሪካ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ፣
• በ1995 የደብረ ብርሃን ብርድልብስ ፋብሪካ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ፣
• ከ1996 -2003 የሀዋሳ ከነማ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ፣
• ከ2004 – 2005 የኒያላ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ፣
• በ2006 የወላይታ ዲቻ እግር ኳስ ክለብ አማካሪ፣
• በ2007 የአዲስ አበባ ውሀ ስራዎች እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ፣
• በ1999 ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ፣
• በ2000 የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ፣
• በ2001 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ በሴካፋ ውድድር፣
• ሀዋሳ ከተማ ብቻ ለ13 ዓመታት በማሰልጠን 3 ጊዜ የዋንጫ ባለቤት፣
• በ1996 እና 1999 የኮከብ አሰልጣኝ በመሆን ተሸላሚ፣
• ከ50 ዓመታት በላይ በአሰልጣኝነት ያገለገሉ አንጋፋ አሰልጣኝ ናቸው፡፡
በእሳቸው የአሰልጣኝነት የህይወት ጉዞ በርካታ የእግር ኳስ ተጫዋቾችን በማፍራት ለዘርፉ አስተዋፅኦ ካበረከቱት በዋናነት ይጠቀሳሉ። ስለ አንጋፋው አሰልጣኝ ጋሽ ከማል ከዚህ ቀደም የሐዋሳ ማዘጋጃ ቤት ካሳተመው መፅሔት መረጃውን አቀረብኩ እንጂ ያልተነገረላቸው ብዙ ስራዎች እንደሰሩ ይታወቅልኝ፡፡
  

ጋሽ ከማል አሁን “ከማል አካዳሚ” ካምፕ በመክፈት ከ260 በላይ ታዳጊዎች በማሰባሰብ እግር ኳስ ማሰልጠኛ ከፍተው እየሰለጠኑ ይገኛሉ፡፡

አሁን እሳቸው ከስራው ጋር በተያያዘ ረዥም ጊዜ ከመቆም ጋር ተያይዞ አንድ እግራቸው ስለሚታመሙ እንደቀድሞው ተሯርጠው መስራት ባይችሉም ከአቶ መለሰ ከበደ ጋር በመሆን ድርጅቱን በመቆጣጠርና በማማከር ስራዎችን በመስራት የሚወዱትን ሙያ በማስቀጠል ላይ ይገኛሉ፡፡

ጋሽ ከማል ባለትዳርና የአንዲት ሴት፣ የሁለት ወንዶች አባት ሲሆኑ 5 የልጅ ልጅ አሏቸው፡፡ ጋሼ በኑሮአቸው ባለፉበት መንገድና አሁን የደረሱበትን መንገድ እያስታወሱ ፈጣሪን ያመሰግናሉ፡፡ ያሰቡትንም እንዳሳኩ ይሰማቸዋል፡፡

ወደመኖሪያ ቤታቸው በሄድንበት ወቅት እጅግ በጣም ደስተኛ ነበሩ፡፡ ይሄ ለእኔ ከገንዘብ በላይ ነው በጣም ደስ ብሎኛሎ በማለት የአባትነታቸውን መርቀውን ተመለስን፡፡ ለአባታችን ረዥም እድሜን ከጤና ጋር ተመኘን፡፡

ጋሽ ከማል አሁን መጽሐፍ ጽፈው አጠናቀዋል፡፡ መጽሐፉ ለሕትመት ዝግጁ ሆኖ ህትመት ብቻ ይቀረዋል፡፡ አባታችን ህልማቸው ተሳክቶላቸው ዳግም ለመገናኘት ያብቃን፡፡
( countdown 3 of 30 round one) ለዚህ በጎ ስራ ለተባበራችሁ ውድ ቤተሰቦች (ፍቅሩና ጓደኞቹ) ከልብ የመነጨ ምስጋናችን ይድረሳችሁ።

@በሐና በቀለ
የፍቅር የሰላምና የአንድነት አርበኞች
(ከላይ የተጠቀሰው ቁጥር ከ30 ሶስተኛ ዙር ላይ መድረሳችንን ብቻ የሚገልፅ ነው)
#ዝግጅት_አንድ| ቃል በተግባር
#hawassa| የገና ስጦታ 1

    ውድ ቤተሰቦች እንኳን አደረሳችሁ! ከሰሞኑ እንዳስተዋወቅናችሁ የመጀመሪያውን የስጦታ መርሐ ግብር  አከናውነናል።  ዝግጅቱም በተሳካና በእናት አባቶች ምርቃት ደምቆ ተከናውኗል። ለስጦታ የተዘጋጀው የቅርጫ፣ የዘይት፣ የሽንኩርትና የዳቦ ዱቄት ሲሆን በአለማየሁ፣ ቾምቤና ቤተሰቦቹ ስፓንሰርነት በሐዋሳ ትዝታ ማህበራዊ ሚዲያ አስተባባሪነት የቀረበ ዝግጅት ነው።
    አቶ ከለማየሁና ቤተሰቦቹ ለመልካም ነገር የተሰጡ፣ እውቀት፣ ገንዘብና ጊዜያቸውን ሳይሰስቱ በየአመቱ እስከ መቶ ሺህ ብር የሚጠጋ በጀት መድበው ለምስኪኖች ድጋፍ በማድረግ ይታወቃሉ። በተጨማሪም በቋሚነት የሚደግፏቸው ወገኖችም አሉ።
     መሐል ክ/ከተማ ቤተልሔም አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ግቢ በእለተ ቅዳሜ (ዋዜማ) በአቅማቸው ድጋፍ የሚፈልጉ፣ በእድሜ የገፉና ጧሪ የሌላቸው 24 ወገኖች የስጦታው ተጠቃሚ ሆነዋል። ወገኖቹ የተመረጡት ከከተማዋ ከተለያየ ሰፈር እና በተለያየ ሰዎች ጥቆማ ሲሆን ስጦታውን በማግኘታቸው በአባትና እናት ወግ መርቀዋል አመስግነዋልም።
    በስጦታው ወቅት ከተገኙት እንግዶች መሐከል መ/ር መሐሪ አንዱ ሲሆኑ ይህን በጎ ስራ የሰሩትን ቤተሰቦች ከማመስገን ባለፈ ለዝግጅቱ ስኬት አብረውን ውድ ጊዜና ጉልበታቸውን ሰውተው በመተባበራቸው ከፍተኛ ምስጋናችንን ለማቅረብ እንወዳለን።
   መልካምነት ይከፍላል።
የፍቅር የሰላምና የአንድነት አርበኞች!
ታህሳስ 27/2016
#አንጋፋዋ_ሾፌር| ወ/ሮ ወይኒቱ ከበደ
#hawassa| በልጅ ወግ አክብረናል

በቢሮ ደረጃ የሴት ሾፌር ብርቅ በነበረበት ዘመን እሳቸው ግን ኧረ እናንተ እድሉን ስጡኝ እንጂ ምን ገዶኝ በሚገባ ኃላፊነቴን እወጣለሁ በማለት ከ30 ዓመታት በላይ በሹፍርና አገልግለዋል፡፡

ወ/ሮ ወይኒቱ ከበደ ባሌ ክ/ሀገር የተወለዱ ሲሆን የ10 ዓመት ልጅ እያሉ ነው ወደሀዋሳ አክስታቸው ቤት የመጡት፡፡ በ19 ዓመታቸው የተዳሩት ወ/ሮ ወይኒቱ ቦረና ከዚያም ያቤሎ ከባለቤታቸው ጋር እየኖሩ ባሉበት ወቅት በጊዜው በነበረው ጦርነት 2 ልጆቻቸውን ይዘው ወደሀዋሳ ከተማ ተመለሱ፡፡

በ1970 ዓ.ም የአሁኑ ግብርና ኮሌጅ በፊት አዋሳ እርሻ ኮሌጅ በሚባልበት ወቅት በ21 ዓመታቸው ኮሌጁ እንጀራ ጋጋሪ ማስታወቂያ አውጥቶ ስለነበር ተወዳድረው ገቡ፡፡ ነገር ግን ብዙም በስራው አልዘለቁበትም፤ ሁለት ወር ከሰሩ በኋላ ይህቺ ወጣት ልጅ በአግባቡ እንጀራ እየጋገረች አይደለም ብለው የተማሪ ምገባ ክፍል በመስተንግዶነት እንዲሰሩ ተደረገ፡፡

ከዚያም የሴቶች ጥበቃ ተፈልጐ ስለነበር ወደዚያ በመዛወር ለ3 ወራት ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር  ወታደራዊ ትምህርት በመውሰድ መሣሪያ መፍታት፣ መግጠም ተምረው ሲመለሱ ጥበቃና ፍታሽ ሆነው አገልግለዋል፡፡ 

በኋላ ግን ይላሉ ወ/ሮ ወይኒቱ 1986 ዓ.ም እኔ እና 15 ወንዶች ሹፍርና እንድንሰለጥን መስሪያ ቤቱ ባመቻቸልን ዕድል ስልጠናውን ጨርሰን ላይሰንስ ይዘን ተመለስን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ 3ኛ መንጃ ፈቃድ ድረስም መስሪያ ቤቱ አስተምሮኛል፡፡ ከዚያም የኮሌጁ ትራንስፖርትና ገራዥ ክፍል ከጥበቃ ተዛወርኩ፡፡ በጊዜው የነበሩ ፕሮፌሰር ዝናቡ ገ/ማሪያም እና ፕሮፌሰር አድማሱ ፀጋዬ ሌሎችም ጥሩ ዶክተሮችና ሰራተኞች ነበሩ እኔ እንድማርና እዚህ ደረጃ እንድደርስ ትልቅ  አጽተዋፅኦ አድርገውልኛል ይላሉ፡፡

ከስልጠናው በኋላ ነገሮች አልጋ በአልጋ አልሆኑልኝም፡፡ በቢሮ ደረጃ የሴት ሾፌር ተቀጥራም ሰርታም ስለማታውቅ ከወንዶቹ እኩል ሰልጥኜ ብመጣም መኪና ሊሰጡኝና ወደስራ ሊያሰማሩኝ ፈቃደኛ ስላልነበሩ ያለስራ 10 ዓመታትን ተቀመጥኩ፡፡

ከዚያ ግን በስምሪት ክፍሉ የነበሩ ሀላፊ መኪና ይሰጣትና ሻሸመኔ ደርሳ ትመለስ ብለው አዘዙና አንድ ታዛቢ ሹፌር ተመደበልኝ፡፡ ትንሽዋን ቴዮታ ሰጡኝና ሻሸመኔ፣ አርሲ ኔጌሌ፣ ቱላ፣ ይርጋዓለም ደርሼ ስመለስ ይርጋዓለም ከሄደች በንሳ ደርሳ ትመለስ ተባልኩ፡፡

በሹፍርና የመስራት ፍላጎቱም ስለነበረኝ ከዚያ በተጨማሪ ተከልክዬ የተቀመጥኩበት እልሁም ተጨምሮበት ስራዬን በጥንቃቄና በትጋት እሰራ ነበር፡፡

ኋላ ብቃቴን ስለተመለከቱ የምርምር ስራን የሚሰሩ ባለሙያዎችን፣ አስተማሪዎችንና ዶክተሮችን ይዤ ወላይታ ሶዶ እና አርባምንጭ አድርሻቸው መለስኳቸው፡፡    

አሁን የእኔ ጊዜ መጣ ብል ማጋነን አይሆንብኝም፡፡ ከዚያም ፒካፕ መኪና ሰጡኝ፤ ቀጠሉና ላንድክሩዘር ብቻ እንዲህ እንዲያ እያልኩ የተገኘነው መኪያ እየቀያየርኩ ሀገራችንን ከጫፍ እስከ ጫፍ ማዳረስ ጀመርኩ፡፡ በሹፍርና ህይወቴ ብዙ የኢትዮጵያ ሃገራትን አይቻለሁ፡፡ በዚያ ደግሞ ትልቅ ኩራት ይሰማኛል፡፡

ወ/ሮ ወይኒቱ ሲናገሩ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በጣም ታላላቅ ሰዎች ብዙ ምሁራን ያሉበት ቤት ነው ያንን ቤት በጣም እወደዋለሁ፡፡ ብዙ ያየሁበት ጊቢ ነው፡፡ ልጅነቴን ያስታውሰኛል፡፡

ከለሊሉ 9 ሰዓት ከወንዶች እኩል በመነሳት የተማሪዎችን ምግብ የሚያበስሉ ሰራተኞችን ከየቤታቸው በመሰብሰብ 12 ሰዓት ወደቤት እመለስ ነበር፡፡ ከዚያም  ቀን እንዲሁ መምህራኖችን በማመላለስ ሰርቻለሁ፡፡

ነገር ግን ስራው እየተደራረበ ድካም ሲበዛብኝ የቅርብ የስራ ኃላፊ የሆነውን ግለሰብ የለሊቱ ስራ እንዳልተመቸኝ ባሳውቅም በወቅቱ ድካሜን ተረድቶ ቅሬታዬን ስላልተቀበለ አንድም ቀን በዚህ መልኩ ስራዬን እለቃለሁ ብዬ ባላሰብኩት ሰዓት 5 ዓመት ለጡረታ ሲቀረኝ የምወደውን ሞያና ዩኒቨርስቲ ለመልቀቅ ተገደዱ፡፡

እኛ ወ/ሮ ወይኒቱ እቤት በሄድንበት ወቅት ጋቢ ስናለብሳቸውና ለሴቶች ተምሳሌት ኖት ስላገለገሉን እናመሰግናለን ስንል በጉንጫቸው የሚወርደውን እምባ እየጠራረጉ ለካስ መስራቴን ለሕዝብ መድከሜን የሚያውቅልኝ ትውል አለ አመሰግናለሁ ነበር ያሉን፡፡

ሆኖም ግን የጡረታ መብታቸውን ካስከበሩ በኋላ መሪ ለቆ ወደቤት መግባት ለእኔ ከባድ ነበር የሚሉት ታታሪዋ ሾፌር ኦዲት ቢሮ ለ11 ወራት እንዲሁም አሁን የመድሐኒት አቅራቢ አገልግሎት ሀዋሳ ቅርንጫ በሾፌርነት 9 ዓመት ያገለገሉ ሲሆን አሁንም በስራ ላይ ናቸው፡፡

በመጨረሻም የመድሐኒት አቅራቢ አገልግሎት ሀዋሳ ቅርንጫፍ ኃላፊ ለሆኑት አቶ ዘመን ለገሰን የከበረ ምስጋና አቅርቢልኝ እሱ መልካምና የልጅ አዋቂ ነው ብለዋል፡፡ እንዲሁም መስሪያ ቤቱ ላሉ ሰራተኞች ስለሁሉም ነገር አመሰግናለሁ የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

አሁን ወ/ሮ ወይኒቱ 68 ዓመት ሆኗቸዋል፤ ባለትዳር እና የ2 ሴቶችና የ4 ወንዶች በአጠቃላይ የ6 ልጆች እንዲሁም 10 የልጅ ልጆችን አይተዋል፡፡
 
እኛም ታታሪዋን ሾፌር ለብዙ ሴቶች እህቶቻችን ተምሳሌት ነዎትና በድጋሚ  እያመሰገንን ቀሪ ዘመንዎን አምላክ ይባርክልዎት ማለት ወደድን፡፡

በሐና በቀለ
የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ!
የፍቅር የሰላምና የአንድነት አርበኞች!
#awassa
2025/10/21 11:10:45
Back to Top
HTML Embed Code: