Telegram Web Link
🌼🌼🌼እንኳን አደረሳችሁ 🌼🌼🌼
🌼🌼🌼እንኳን አደረሳችሁ 🌼🌼🌼
✞✞✞ በእንተ ቅዱሳን ✞✞✞
Photo
🌼🌼🌼በአዲስ ዓመት አዲስ ሰው🌼🌼🌼

🌻✞ከቅዱስ አባታችን አዳም ጀምሮ ብዙ ትውልድ በዚህች ምድር ላይ ተመላልሷል፡፡ ወጥቷል ወርዷል አልፏል፡፡ ዘመን ሲያልፍ ዘመን ሲተካ ሰው ሲያልፍ ሰው ሲተካ፡ ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡

🌻ነቢየ እግዚአሔር ዳዊት በመዝሙሩ « ሰብዕሰ ከመ ሣዕር መዋዕሊሁ - ሰውስ ዘመኑ እንደ ሣር ነው እንደ ዱር አበባ እንዲሁ ያብባል፡፡ ነፋስ በነፈሰበት ጊዜ ያልፋል » መዝ.102/103፡ 15፡16 ብሏል፡፡ ይህም ቃል በአዳም ልጆች ሁሉ ላይ ሲሠራ ኖሮ ከአሁኑ ትውልድ ደርሷል፡፡ ቋሚ የቆየ የሚመስለው የአሁኑ ዘመን ሰው ግን ሊያስተውለው የሚገባ አንድ ዐቢይ ቁም ነገር አለ፡፡ ይኸውም ከእርሱ በፊት የነበረው ትውልድ ቦታውን ለአሁኑ እንደለቀቀ ሁሉ ይኸኛውም ትውልድ በበኩሉ ኃላፊ መሆኑ ነው፡፡ ታዲያ አሮጊው ዘመን አልፎ አዲሱ ዘመን ሲተካ ክርስቲያኖች አዲሱን ዘመን በምን ዓይነት መንፈስ ነው የምንቀበለው?

🌼ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ መልስ የሚሆነን ነገር በመጀመሪያ ክታቡ ላይ ጽፎልን እናገኘዋልን፡፡

🌻✞« የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁ በት፡ በመዳራት እና በሥጋ ምኞት፣ በስካርም፣ በዘፈንም ፣ያለልክም በመጠጣት፣ ነውርም ባለበት፣ በጣዎት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና »1ጴጥ.4፡3፡፡✞

🌺ባለፈው ዓመት ሕግ እንደ ሌላቸው አሕዛብ ያለ ሕግ የተመላለስንበት ያ የኃጢአት ሕይወት ዛሬ በንስሐ ተወግዶ በፍጹም ተለውጠን አዲስ ሰው የምንሆንበት ጊዜ ነው፡፡ ዳግም በሮሜ ምዕ 6 ላይ በስፋት አስተምሮናል ፤ መክሮናል ፤ ገስጾናል :: በክርስቶስ ክርስቲያን የተሰኘን ሁላችን በስካርና በዝሙት ፣ በስርቆት እና በቅሚያ ፣ በመግደልና በምቀኝነት ፣ በቅንዓትና በቂመኛነት ፤ በተንኮልና በመባከን ያሳለፍነውን ሕይወት ትተን አዲስ ሰው የምንሆንበት ዘመን ሊሆን ይገባል ፤ ያስፈልጋል ፡፡

🌼🌼🌼የቀን መቁጠሪያው 2013 ኛውን የምሕረት ዓመት አስቆጥሮናል እኛም በግላችን በዚህ ምድር ላይ ብዙ የምሕረት ዓመታትን አሳልፈናል፡፡ በእውነት ግን ካሳለፍናቸው የምሕረት ዓመታት በስንቶቹ ተምረንባቸው ይሆን? በምሕረት ዓመታት የብርሃንን /የጽድቅን/ ሥራ ትተን የጨለማን /የኃጢያትን/ ሥራ ብቻ ስንሠራ አሳልፈን ከሆነ ግን አዲሱ ዓመት ይህንን ትተን ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት ፣ ወደ ቅዱሳን አሰረ ፍኖት የምናቀናት ፣ ወደ ጽድቅ ሥራ የምንመለስበት ፣ ወደ ብርሃን የምወጣበት የምሕረት ዓመት ሊሆን ይገባዋል፡፡ ላይአችን ርግብ ውስጣችን ዕባብ የነበረበት ፣ በሰው ፊት ጻድቅ በእግዚአብሔር ፊት ግን ኃጥእ የሆንበት ፣ ሃይማኖታችንን በገንዘብ የለወጥንበት ፣ በማንኛውም መንገድ እግዚአብሔርን ያስከፋንበት ያ ያለፈው ዘመን አክትሞ መጪው ጊዜ አዲስ ሰው የምንሆንበት ሊሆን ይገባል፡፡


🌼✞ አዲስ ሰው መሆን ✞🌼

🌼ንሰሐ መግባት ነው ፤
🌼ምሥጢራትን መካፈል ነው ፤
🌼‹‹ የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ ›› የሚለውን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ቅዱስ ቃል መስማት ነው ፤
🌼ወደ በጎ ምግባር መመለስ ፤ 🌼ለመልካም ሥራ መነሳሳት መፋጠን ነው ፤
🌼ያለፈ ዘመንን ክፉ ሥራ መተው ነው ፤
🌼የመንፈስ ፍሬያትን ማፍራት ነው፡፡ «የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ የውኃት፣ ራስን መግዛት ነው፡፡» ገላ.5-22 ፤
🌼ትሩፋትን መታጠቅ ነው ፤
🌼ራስን መግዛት ነው ፤
🌼ቃሉን በተግባር መኖር ነው ፤
🌼ትዕዛዙን እና ሕጉን ወደ ማክበር መመለስ ነው ፤፤

🌻እነሆ የመዳን ቀን አሁን ነው እና ኃጢአታችን በንስሐ ውኃ የምንታጠብበት ፣ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ በቆረሰልን ሥጋው ባፈሰሰልን ደሙ የምንታተምበት ፣ ኃጢአተኛ የነበረውን ሰውነታችንን ለእግዚአብሔር ሕግ የምናስገዛበት የምሕረት ዓመት እንዲሆን እራሳችንን እንቀድስ በአዲስ ዓመት አዲስ ሰው እንሁን ፤ ይህን ያላደረግን እንደሆነ ዘመን መቊጠራችን ዓመት ማሳለፋች በኃጢአት ላይ ኃጢአትን ፤ በጥፋት ላይ ጥፋትን እንድንደርብ ከማድረግ ውጪ ፋይዳ ፡ ረብ ፡ ጥቅም የለውም ፡፡ በአዲስ ዓመት አዲስ ሰው መሆንን ከፈለግንና ለማረጋገጥም ከሻን ትላንት በአንደበታችን ሰዎችን ክፉ በመናገር ያስቀየምን ፣ የሰረቅን ፣የዋሸን ፣ የገደልን ፣ የሰው ንብረት ያለ አግባብ የወሰድን ፣ በሀሜትና በዝሙት ኀጢአት የወደቅን ፣ የምዋርት ፣ የጥልና የክርክር መንፈስ ያለብን ፣ . . . ወዘተ ሰዎች ሁሉ ይህ ሁሉ ራሳችንን ከሚጎዳ በስተቀር ምንም የማይጠቅመን መሆኑን ተገንዝበን ንስሐ ልንገባ ከእግዚአብሔር ጋር ልንታረቅ ይገባናል፡፡🌻

🌼🌼✞ለዚህም የሰላም የፍቅር የምሕረት የቸርነት የኂሩት አምላክ እግዚአብሔር ይርዳን✞🌼🌼

✞አሜን✞

🙏መልካም በዓል ይሁንላችሁ 🙏

ዲያቆን ኃይለ ማርያም ደመና
የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ስለ ዘመን አቆጣጠር ከጻፉት ሊቃውንት መካከል የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ዲሜጥሮስ አንዱ ነው።
በ3ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ የተነሳው ሊቁ ዲሜጥሮስ የመጀመሪያውን የዘመን አቆጣጠር ከሐዲስ ኪዳን በዓላት እና አጽዋማት ጋር አስማምቶ የመሰረተና ባሕረ ሐሳብ የተባለውን መጽሐፍ የደረሰ አባት ነው።
ዲሜጥሮስ ማለት መስታወት ማለት ነው። በመስታወት በዓይን ያለ ጉድፍ እንዲታይ እርሱም በዓላት አጽዋማትን አጉልቶ አምልቶ ያሳያልና። ባሕረ ሐሳብ ማለት በውስጡ እንደ ባሕረ ጥልቀት ያላቸው ጉዳዮች ያሉበት የዘመን ቁጥር ማለት ነው። ስለዚህ ባሕረ ሐሳብ ሲባል የአመታት የወራት የሳምንታት የዕለታትና የደቂቃዎች ልክ የሚታወቅበት የዘመን መቁጠሪያ መሣርያ ማለት ነው። መርሐ ዕውርም ይባላል። በዓላትና አፅዋማት የሚውሉበትን ዕለት ወደ ማወቅ መርቶ ያደርሳልና።
ቅ. ዲሜጥሮስ ድግ ታጥቶ እርፍ አርቆ ተክል አጽድቆ ይኖር የነበረ ገበሬ ነበር። ሚስቱም ልዕልተ ወይን ትባላለች። እናትና አባቷ ሙተውባት ከእርሱ ቤተሰቦች ጋር ያደገች የአጎቱ ልጅ ናት። ነገር ግን እርሱም እርሷም ሳይፈልጉ አጋብተዋቸዋል። እናት አባቱም የአጎቱን ልጅ ማጋባታቸው ዘመኑ ምዕመናን ያነሱበት አሕዛብ የበዙበት ዘመን ነበርና ለእርሱ የምትሆን ሚስት ባለማግኘታቸው ሕንጻ ሃይማኖት ከሚፈርስ ሕንጻ ሥጋ ይፍረስ ብለው ዝምድና እያላቸው አጋብተው ሥርዓተ መርዓዊና መርዓት ያድርሱ ብለው ከጫጉላ አስገቡአቸው ነገር ግን ልዕልተ ወይን ወንድሜ አንተም ነገሩን ሽተኸው ነውን? አለችው እርሱም የግድ ቢሉኝ ጊዜ ነው እንጂ ፈልጌው እንዳልሆነ እግዚአብሔር ያውቃል። አሁንም የተለያየን ከሆነ እኔንም አንችንም ለሌላ ያጋቡናልና በአንድ ላይ ንፅህናችንን ጠብቀን መኖር እንችላለን ተባብለው በአንድ አልጋ እየተኙ አንድ ልብስ እየለበሱ 48 ዘመን በንጽህና ኑረዋል። ይኸውም እንዲታወቅ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ግራ ክንፉን ለሷ ቀኝ ክንፉን ለሱ አልብሷቸው ያድር ነበር። ከዕለታት በአንድ ቀን ቅ ዲሜጥሮስ ከአትክልት ቦታ ገብቶ ያለ ጊዜው ያፈራ የወይን ዘለላ አግኝቶ ለልዕልተ ወይን ሰጣት እርሷም ይህንን ወስደህ ለሊቀ ጳጳሱ ሰጥተህ በረከት ተቀበልበት ብላ በንጹህ ሙዳይ አድርጋ ሰጠችው። በዘመኑ የነበረው የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ ዮልያኖስ ይባል ነበር። አርጅቶ የሚሞትበት ጊዜ ቀርቦ ነበርና መልአኩ ከአንተ ቀጥሎ የሚሾመው የለ ጊዜው ያፈራ የወይን ዘለላ ይዞ የሚመጣ ሠው ነው ብሎ ነግሮት ስለ ነበር ዲሜጥሮስ አምጥቶ ሲሰጠው ሕዝቡን ሰብስቦ ከኔ ቀጥሎ የሚሾመው እርሱ ነው ብሎ ነግ
ሮአቸው አርፎአል። ሕዝቡም ሊቀ ጳጳስ ዮሊያኖስ ቀብረው ተመልሰው አባታችን ከኔ ቀጥሎ የሚሾመው እርሱ ነው ብሎናልና ተሾምልን አሉት ። እርሱም ይህ ለእኔ አይገባኝም እጅግ ታናሽ ነኝና ልሾም አይገባኝም ቢልም ህዝቡ

አስገድደው አሾሙት። እርሱም ተሹሞ ብዙ መንፈሳዊ ስራዎችን ከመስራቱ በተጨማሪ የሕዝቡ ኃጢአት እየተገለፀለት አንተ በቅተሃል ቁረብ አንተ አልበቃህም አትቁረብ እያለ የሚከለክላቸው ሆነ። ሕዝቡም ተቆጥተው ያጉረመርሙ ጀመር በዚህ ጊዜ መልአኩ ተገልጦ ሕዝቡ በሃሜት እየተጎዱ ነውና በአንተና በሚስትህ መካከል ያለውን ነገር ግለፅላቸው አለው። እሳት አስነድዶ ሚስቱን ከመቅዋመ አንስት አስጠርቶ ፍሙን በእጁ እየዘገነ ወደ ሚስቱ ልብስ እየጨመረ ሄደሽ ለህዝቡ አሳይ አላት። አሷም ፍሙን በልብሷ ይዛ ልብሷ ሳይቃጠል እሷም ሳትቃጠል እየዞረች ለሕዝቡ አሳይታለች ። ከዚህ በኋላ ሕዝቡም ተዓምሩን በማየታቸው አባታችን በከንቱ አምተንሃልና ይቅር በለን አሉት።ቅዱስ ዲሜጥሮስም "ይፍታህ ይኅድግ ያንጽህ ወይቀድስ ብሎ ናዝዟቸዋል። ኑዛዜ የተጀመረው ከዚያ ወዲህ ነው።
የቀድሞ ሰዎች ዐቢይ ጾምን የጥምቀት ማግስት ይጀምሩ ነበር። ሕማማቱንም አዘግይተው መጋቢት ያደርጉ ነበር። በዚህ የተነሳ የዓቢይ ጾም የጥምቀትን ሳኒታ መነሻ አድርጎ ስለሚጀመር ሰኞን ደብረ ዘይት ሆሳዕና ትንሳኤ ጰራቅሊጦስ እሁድን ሳይጠብቁ ይውሉ ነበር። በዚህ ቅ. ዲሜጥሮስ ጾመ ነነዌ ዓቢይ ጾም ሆሳዕና ትንሳኤ ጰራቅሊጦስ እሁድ እንዲሆን። ርክበ ካህናት ጾመ ድኅነት ረቡዕ ስቅለት አርብ ዕርገት ከሀሙስ ባይወጣ እያለ ሲመኝ ይኖር ነበር። መልአኩ ተገልጦ ነገር በማሰብ ብቻ ይሆናልን? ሱባኤ ገብተህ ይገለፅልሃል አለው።በመዓልት ሰባት ሱባዔ ከሌሊቱ ሃያ ሦስት ሱባዔ ገብተህ ይገለጽልሃል። ይህን በ30 በ30 ገድፈህ በተረፈው ታገኘዋለህ ብሎታል በዚህም መሠረት የመዓልቱ 7×7=49 ይህ በ30 ሲገደፍ 49÷30 አንድ ደርሶ 19 ይቀራል ይህ 19 ጥንተ መጥቅዕ ተባለ የቀኑ 7 ያነሰበት ምክንያት የታመመ ሲጠይቅ የተጣላ ሲያስታርቅ የሌሊቱ 23ቱን አንድ እያለ 7 ጊዜ ይሰግድ ነበር። 23×7 = 161 ይህን በአምስት ሰላሳ ብንገድፈው 161-(5×30)= 11 ይተርፋል ይህን አበቅቴ በለው ብሎታል። አበቅቴና መጥቅዕ ቢደምሩት 30 ይሆናል። ይህን አዘጋጅቶ ጽፎ ለ4ቱ ሊቃነ ጳጳሳት ቢልክላቸው እነርሱም ቀድሞ ሐዋርያት ካስተማሩት ትምህርት ጋር ስለገጠመላቸው ደስ ብሏቸው ተቀብለውታል።
የ2013 ዓ/ም የአጿማትና የበዓላት ማውጫ ቀመር
"ዓመተ ዓለም"
ዓመተ ዓለም:- የዓመተ ምህረትና የዓመተ ኩነኔ/ፍዳ/ ድምር ውጤት ነው። በቁጥር ስናሰላው
2013+5500=7513 ይሆናል።
"ወንጌላዊውን ለማግኘት"
ዓመተ ዓለምን ለአራት በማካፈል መጠነ ራብዒትን እናገኛለን ይኸውም
7513÷4=1878 ይሆናል።ተውሳክ/ቀሪ/ 1 ይሆናል
1878 የዘንድሮ መጠነ ራብዒት ነው
በመቀጠልም ቀሪውን ለማወቅ
7512-4×1878 ውጤቱ 1 ይሆናል
ቀሪው 1ከሆነ ዘመኑ ዘመነ ማቴዎስ
ቀሪው 2ከሆነ ዘመኑ ዘመነ ማርቆስ
ቀሪው 3ከሆነ ዘመኑ ዘመነ ሉቃስ
ቀሪው4ወይም0 ከሆነ " ዮሐንስ ነው
# ስለዚህ የ2013 ቀሪ 1 ነው።ስለሆነም ዘመኑ ማቴዎስ ነው።
በዓመቱ የሚሾመው ወንጌላዊ ማቴዎስ ነው።
"መባቻ"
* መባቻ ማለት መስከረም አንድ የሚውልበት ቀን ማለት ነው። መባቻን ለማግኘት
ዓመተ ዓለምን ከመጠነ ራብዒት ጋር ደምረን ለሰባቱ እለታት እናካፍላለን።
7513+1878÷7 ውጤቱ 1341 ደርሶ ቀሪ "4" ይሆናል
*ቀሪው 0 ከሆነ መባቻ ሰኞ
*ቀሪው 1 ከሆነ መባቻ ማክሰኞ
*ቀሪው 2 ከሆነ መባቻ ረቡዕ
*ቀሪው 3 ከሆነ መባቻ ሐሙስ
*ቀሪው 4 ከሆነ መባቻ አርብ
*ቀሪው 5 ከሆነ መባቻ ቅዳሜ
*በመግደፍ ቀሪው 6 ከሆነ መባቻ እሁድ ይሆናል።
# በመሆኑም ቀሪው "4" ስለሆነ ዘንድሮ መባቻ "አርብ" ይሆናል
"መደብ"
መደብን ለማግኘት ዓመተ ዓለምን በ19 እንገድፋለን።
7513÷19= 395 ደርሶ ቀሪ 8 ነው
ስለዚህ መደብ 8 ይሆናል።
"ወንበር"
ወንበርን ለማግኘት ከመደብ አንድን ለዘመን መቀነስ/መተው/ ነው።
8-1=7 ስለዚህ ወንበር "7" ይሆናል
"አበቅቴ"
አበቅቴን ለማግኘት ወንበርን በጥንተ አበቅቴ አባዝተን በ30 ገድፈን እናገኛለን። ይኸውም ወንበር 7 ነው
ጥንተ አበቅቴ 11 ነው።
# 7×11=77
77÷30= 2ደርሶ ቀሪ "17" በመሆኑ
የዘንድሮ አበቅቴ "17" ነው።
"መጥቅዕ"
መጥቅዕን ለማግኘት ወንበርን በጥንተ መጥቅዕ አባዝተን በ30 በመግደፍ እናገኛለን።
# 7×19=133
#133÷30= 4 ደረሶ ቀሪ "13" ይሆናል።የዘንድሮ መጥቅዕ"13" ነው
ማሳሰቢያ:- አበቅቴና መጥቅዕ ተደምረው ከ3
0 አይበልጥም አያንስምም ። ሁሌ 30 ይሆናል።
ለምሳሌ
የዘንድሮን ብንደምረው 30 ይሆናል።
#17+13=30
$ መጥቅዕ "13" ስለሆነ ከ14 ያንሳል። ስለዚህ ጥቅምት ላይ ያርፋል።
በመሆኑም መጥቅዕ ከ14 በታች ስለሆነ ከጥቅምት ጀምረን እንቆጥራለን።
ጥቅምት "1" እሁድ ሲሆን ከእሁድ እሁድ"8" ሰኞ 9 ማክሰኞ 10 እሮብ 11 ሐሙስ 12 አርብ 13 ይሆናል ። የእለታት ተውሳካቸው ከቅዳሜ ይጀምራል።
የቅዳሜ ተውሳክ "8"
የእሁድ ተውሳክ "7"
የሰኞ ተውሳክ "6"
የማክሰኞ ተውሳክ "5"
የረቡዕ ተውሳክ "4"
የሐሙስ ተውሳክ "3"
የአርብ ተውሳክ "2" ነው።
የእለቱ ተውሳክ ከታወቀ በኋላ ጾመ ነነዌ መቼ እንደሚገባ ለማግኘት
መጥቅዕንና የዕለቱን ተውሳክ በመደመር ከ30 በላይ ከሆነ በ30 በመግደፍ እናገኛለን።
ዘንድሮ መጥቅዕ 13 ስለሆነ አርብ ዕለት ይውላል ስለዚህ የአርብ ተውሳክ 2 ስለሆነ 13+2=15
ስለሆነም ዘንድሮ ጾመ ነነዌ የካቲት 15 ቀን ይገባል።
ከዚህ በማስከተል የአጽዋማትንና በዓላትን ተውሳካቸው እናወጣለን
$ከጾመ ነነዌ እስከ ዐቢይ ጾም 14 ቀኖች አሉ ስለዚህ የዐቢይ ጾም ተውሳክ 14 ነው።
$ከጾመ ነነዌ እስከ ደብረ ዘይት 41 ቀኖች አሉ 41÷30 = 1ደርሶ ቀሪ11ይሆናል። ስለዚህ የደብረ ዘይት ተውሳክ 11 ነው።
$ ከነነዌ እስከ ሆሳዕና 62 ቀኖች አሉ
62÷30= 2 ደርሶ ቀሪው 2 ይሆናል።
የሆሳዕና ተውሳክ 2 ነው
$ ከነነዌ እስከ ስቅለት 67 ቀኖች አሉ
67÷30=2ደርሶ ቀሪ 7 ይሆናል
7 የስቅለት ተውሳክ ነው።
$ከነነዌ እስከ ትንሳኤ 69 ቀኖች አሉ
69÷30=2ደርሶ ቀሪ 9 ይሆናል።
9 የትንሳኤ ተውሳክ ነው።
$ከነነዌ እስከ ርክበ ካህናት 93 ቀኖች አሉ 93÷30= 3ደርሶ ቀሪው 3 ይሆናል 3 የርክበ ካህናት ተውሳክ ነው።
$ ከነነዌ እስከ ዕርገት 108 ቀኖች አሉ 108÷30= 3ደርሶ ቀሪ 18 ይሆናል።የዕርገት ተውሳክ 18 ነው
$ከነነዌ እስከ ጰራቅሊጦስ 118 ቀናት አሉ 118÷30 =3ደርሶ ቀሪ 28 ይሆናል የጰራቅሊጦስ ተውሳክ 28 ነው።
$ ከነነዌ እስከ ጾመ ሐዋርያት 119 ቀኖች አሉ 119÷30= 3 ደርሶ ቀሪ 29 ይሆናል።29 የጾመ ሐዋርያት ተውሳክ ነው።
$ከነነዌ እስከ ጾመ ድኅነት 121 ቀኖች አሉ 121÷30=4ደርሶ ቀሪ 1ይሆናል። 1 የጾመ ድኅነት ተውሳክ ነው።
@ ከዚህ በመነሳት አጽዋማትንና በዓላትን ተውሳኮቻቸውን ከነነዌ ጋር እየደመርን እናገኛለን።
#የዐቢይ ጾም ተውሳክ 14 ስለሆነ ከ15 ጋር ስንደምር 29 ይሆናል ዐቢይ ጾም የካቲት 29 የገባል።
# የደብረ ዘይት ተውሳክ 11 ስለሆነ ከ15 ጋር ብንደምረው 26 ይሆናል። 26 ከ30 ስለሚያንና በየካቲት ስላለፈ መጋቢት 26 እሁድ ደብረ ዘይት ይውላል።
# የሆሳዕና ተውሳክ 2 ስለሆነ ከ15 ጋር ስንደምረው 17 ይሆናል ከ30 ስለሚያንስና በመጋቢት ስላለፍን በሚያዝያ 17 እሁድ በዓለ ሆሳዕና ይውላል።
#የስቅለት ተውሳክ 7 ነው።
7+15=22 ሲሆን ዘንድሮ ሚያዝያ 22 አርብ ስቅለት ይሆናል #የትንሳኤ ተውሳክ 9 ነው።
9+15= 24 ሲሆን ሚያዝያ 24 በዓለ ትንሳኤ ይሆናል።
#የርክበ ካህናት ተውሳክ 3 ነው
3+15= 18 ሲሆን 18ትን በሚያዝያ ስላለፍን ግንቦት 18 ርክበ ካህናት ይሆናል።
# የዕርገት ተውሳክ 18 ነው
18+15=33ሲሆን 33በ30 ስንገድፈው 3 ይቀራል ዘንድሮ ሰኔ 3 በዕለተ ሐሙስ እርገት ይሆናል።
#የጰራቅሊጦስ ተውሳኩ 28 ነው
28+15=43 ሲሆን 43ን በ30 ስንገድፍ 13 ይቀራል ሰኔ13 እሁድ በዓለ ጰራቅሊጦስ ይሆናል።
#ጾመ ሐዋርያት ተውሳኩ 29 ነው።
29+15=44
44÷30 = 1 ደርሶ ቀሪው 14 ስለሆነ
ሰኔ 14 ጾመ ሐዋርያት ይገባል።
#ጾመ ድኅነት ተውሳኩ 1 ነው።
1+15= 16 ስለሆነ ሰኔ16 ጾመ ድኅነት ይገባል።
< ትኩረት>
@ ጾመ ነነዌ: አብይ ጾም እና ጾመ ሐዋርያት ከሰኞ አይወጣም።
@ ደብረ ዘይት : ሆሳእና : ትንሳኤ እና ጰራቅሊጦስ ከእሁድ አይወጣል።
@ በዓለ ዕርገት ከሐሙስ አይወጣም ።
@ በዓለ ስቅለት ከአርብ አይወጣም
@ርክበ ካህናት እና ጾመ ድኅነት ከረቡዕ አይወጣም::
እንግዲህ የ2013 ዓም የአጿማትና የበዓላት ማውጫ ቀመር ይህን ይመስላል
ዮሐንስ ተሻረ ማቴዎስ ተሾመ /3/
አነሳስቶ ላስጀመረን አስጀምሮ ላስፈጸመን ለልዑል እግዚአብሔር ክብርና ምስጋና ይግባው። ለዘለዓለሙ አሜን
ከመስከረም እስከ ጳጉሜ የተሰየሙት ወሮቻችን ስያሜያቸውን ከየት እንዳገኙ ያውቃሉ? እስኪ የሚከተለውን ይመልከቱ፡፡
🌸✥◉❖◉✥🌸
፩. የወሩ ስም - መስከረም
የግእዝ ሥርወ ቃሉ - መሴ እና ከረም
ትርጉም - መሴ-አለፈ ፣ ክረምቱ መሸ ፤ከረም- ክረምት፤ ክረምት አለፈ።
፪. የወሩ ስም - ጥቅምት
የግእዝ ሥርወ ቃሉ - ጠቀመ
ትርጉም - ሠራ፤ ጠቃሚ ጊዜ።
፫. የወሩ ስም - ኅዳር
የግእዝ ሥርወ ቃሉ - ኀደረ
ትርጉም - አደረ-ሰው በወርኃ አዝመራ ማሳ ውስጥ ለጥበቃ ማደሩን ይገልፃል።
፬. የወሩ ስም - ታኅሳስ
የግእዝ ሥርወ ቃሉ - ኀሠሠ
ትርጉም - መረመረ- በመኸር ወቅት የሰብል ምርመራን ያመለክታል ፤ ሰብዐ ሰገል በታኅሳስ ወር የተወለደውን ጌታችንን ማሰሳቸውን ፣ መፈለጋቸውንም ያመለክታል።
፭. የወሩ ስም - ጥር
የግእዝ ሥርወ ቃሉ - ነጠረ ፣ አጥረየ
ትርጉም - ነጠረ - ጠረረ- ብልጭ አለ፤ ነጻ፤ የፀሐይን ግለት ወቅት ያሳያል ፤ አጥረየ - ገዛ (ከብቱም ምርቱም የሚሸጥበት የሚገዛበት ወቅት)
፮. የወሩ ስም - የካቲት
የግእዝ ሥርወ ቃሉ - ከተተ ፣ ከቲት
ትርጉም - መክተቻ (እኅልን ወደ ጎተራ)
፯. የወሩ ስም - መጋቢት
የግእዝ ሥርወ ቃሉ - መገበ
ትርጉም - በቁሙ የሚመግብ (በጎተራ የተከተተው የሚበላበት)
፰. የወሩ ስም - ሚያዝያ
የግእዝ ሥርወ ቃሉ - መሐዘ
ትርጉም - ጎለመሰ ጎበዘ ሚስት ፈለገ (ወርኀ ሠርግ መሆኑን ሲያጠይቅ)
፱. የወሩ ስም - ግንቦት
የግእዝ ሥርወ ቃሉ - ገነበ
ትርጉም - ገነባ፤ ሠራ፤ ቆፈረ፤ ሰረሰረ (ለእርሻ የመሬቱን መዘጋጀት ያሳያል)
፲. የወሩ ስም - ሰኔ
የግእዝ ሥርወ ቃሉ - ሰነየ
ትርጉም - አማረ (አዝርዕቱ)
፲፩. የወሩ ስም - ሐምሌ
የግእዝ ሥርወ ቃሉ - ሐመለ
ትርጉም - ለመለመ ፣ ሐመልማል ሆነ ፣ ለቀመ (ለጎመን)
፲፪. የወሩ ስም - ነሐሴ
የግእዝ ሥርወ ቃሉ - አናሕስየ
ትርጉም - አቀለለ፤ ተወ (የክረምቱን እያደር መቅለልን ያሳያል)
፲፫. የወሩ ስም - ጳጉሜ/ን
ሥርወ ቃሉ - ኤጳጉሚኖስ (ግሪክ)
ትርጉም - ተጨማሪ ማለት ነው፡፡
🌸✥◉❖◉✥🌸
❖ የኢትዮጵያ የዓመቱ ወራት ሥፍረ ሰዓት በቤተክርስቲያናችን ❖
፩. መስከረም .. የቀኑ ርዝመት ..12
የሌሊቱ ርዝመት ..12
፪. ጥቅምት ..የቀኑ ርዝመት ..11
የሌሊቱ ርዝመት ..13
፫. ህዳር ..የቀኑ ርዝመት ..10
የሌሊቱ ርዝመት ..14
፬. ታህሣሥ ..የቀኑ ርዝመት .. 09
የሌሊቱ ርዝመት ..15
፭. ጥር ...የቀኑ ርዝመት ..10
የሌሊቱ ርዝመት ..14
፮. የካቲት .. የቀኑ ርዝመት ..11
የሌሊቱ ርዝመት..13
፯. መጋቢት.. የቀኑ ርዝመት..12
የሌሊቱ ርዝመት..12
፰. ሚያዝያ.. የቀኑ ርዝመት.. 13
የሌሊቱ ርዝመት ..11
፱. ግንቦት .. የቀኑ ርዝመት ..14
የሌሊቱ ርዝመት ..10
፲. ሰኔ .. የቀኑ ርዝመት ..15
የሌሊቱ ርዝመት ..09
፲፩. ሐምሌ .. የቀኑ ርዝመት ..14
የሌሊቱ ርዝመት ..10
፲፪. ነሐሴ .. የቀኑ ርዝመት ..13
የሌሊቱ ርዝመት..11
🌸✥◉❖◉✥🌸
እንኳን ለ2013 ዓ.ም አዲስ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ!!!
🌸✥◉❖◉✥🌸
#መስከረም_አስር - #ጼዴንያ_ማርያም

እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታላቅ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!!!

" ሰላም ለሥዕልኪ እንተ ሠዓላ በእዱ፡፡ ሉቃስ ጠቢብ እምወንጌላውያን አሐዱ፡፡ አመ ተቀብዑ ማርያም እምሐፈ ሥዕልኪ ቅብዐ ናርዱ፡፡ "(#መልክዐ_ስዕል)

#እመቤታችን ድንግል ማርያምን የምትወድና በሚቻላትም ሁሉ የምታገለግላት፣ ቤቷንም ለእንግዳ ማደሪያ ያደረገች አንዲት ማርታ የምትባል ሴት ነበረች፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን አባ ቴዎድሮስ የሚባሉ ኢትዮጵያዊ መነኮስ ከእርሷ ዘንድ በእንግድነት አድረው በማግሥቱ ከቤቷ ሲወጡ ማርታ የሚሔዱበትን አገር በጠየቀቻቸው ጊዜ እርሳቸውም ወደ ኢየሩሳሌም ሔደው ቅዱሳት መካናትን እንደሚሳለሙ ነገሯት፡፡

#ማርታም ከእርሷ ገንዘብ ወስደው የእመቤታችንን ሥዕል ገዝተው ይዘውላት እንዲመጡ ለመነቻቸው፡፡ መነኵሴውም በራሳቸው ገንዘብ ሥዕሉን ገዝተው እንደሚያመጡላት ቃል ገቡላት፡፡

#አባ_ቴዎድሮስ ኢየሩሳሌም ደርሰው ቅዱሳት መካናትን ከተሳለሙ በኋላ ሥዕሏን ሳይገዙ ወደ አገራቸው ለመመለስ ጉዞ ጀመሩ፡፡ ያን ጊዜም ‹‹ሥዕል መግዛትን ለምን ረሳህ?›› የሚል የሚያስደነግጥ ቃልን ሰምተው ተመልሰው መልኳ ያማረና የተወደደ የእመቤታችን ማርያምን ሥዕል ገዝተው በሐርና በንጹሕ ልብስ ጠቅልለው ይዘው እየተጓዙ ሳሉ ከሚያስፈራ ዱር ውስጥ ሲደርሱ ወንበዴዎች ተነሱባቸው፡፡ሊሸሹ ሲሉም ‹‹#መንገድህን_ሒድ››የሚል ቃል ከሥዕሏ ወጣ መነኵሴውም መንገዳቸውን በሰላም ተጓዙ፡፡
ሁለተኛም #አንበሳ ሊበላቸው በተነሣባቸው ጊዜ ከዚያች ሥዕል የሚያሥፈራ ድምፅ ወጥቶ አንበሳውን አባረረላቸው፡፡

#አባ_ቴዎድሮስ ይህን ኹሉ ድንቅ ተአምር ባዩ ጊዜም ያቺን ሥዕል ለማርታ ከመስጠት ይልቅ ወደ አገራቸው ሊወስዷት ወደዱ፡፡ በመርከብ ተሳፍረው በሌላ አቅጣጫ ሲሔዱም ታላቅ ነፋስ ተነሥቶ ወደ ማርታ አገር ወደ ጼዴንያ ወሰዳቸው፡፡ ከመርከብም ወርደው ከብዙ እንግዶች ጋር ወደዚያች መበለት ቤት ደረሱ፡፡ ነገር ግን ማንነታቸውን ለማርታ አልገለጡላትም ፤ እርሷም አላወቀቻቸውም ነበር፡፡

#በማግሥቱም ተሠውረው ወደ አገራቸው ሊሔዱ ሲሉ የቅፅሩ ደጃፍ ጠፍቶባቸው ሲፈልጉ ዋሉ በመሸባቸው ጊዜም ወደ ማደሪያቸው ተመለሱ፡፡ ማታ ማታ በሩን ያዩታል፤ ነግቶ መሔድን ሲሹ ግን የበሩ መንገድ ይሠወርባቸዋል፡፡ እንዲህም ኾነው እስከ ሦስት ቀን ድረስ ቆዩ፡፡ ማርታም ‹‹አባቴ ሆይ አእምሮህ ተነክቷልን? ስትቅበዘበዝ አይሃለሁና ምን ኾነህ ነው?›› ሰትል ጠየቀቻችው፡፡ እርሳቸውም ከእመቤታችን ሥዕል የተደረገውን ተአምር ሁሉ ነገሯት፤ ራሳቸውንም ገለጡላትና ሥዕሏን ሰጧት፡፡ እርሷም #የእመቤታችንን_ሥዕል ተቀብላ የተጠቀለለችበትን ልብስ በፈታችው ጊዜ ወዝ ከሥዕሊቱ ሲንጠፈጠፍ አገኘች፡፡ ከደስታዋ ብዛት የተነሣም የአባ ቴዎድሮስን እጃቸውንና እግራቸውን ሳመች፡፡
#ሥዕሏም_ቅዱስ_ሉቃስ_የሳላት_ነበረች፡፡
ከዚህም በኋላ ያቺን ሥዕል ወደ ጸሎት ቤቷ ወስዳ በታላቅ ክብር አኖረቻት፡፡ ማንም እንዳይዳስሳትም የነሐስ መስኮትን ሠራችላት፡፡
በቀንና በሌሊትም የሚያበሩ መቅረዞችን በፊቷ ሰቀለች፤ ከመቅረዞች ውጭም የሐር መጋረጃን ጋረደች፡፡ ከሥዕሊቱ በታችም እየተንጠፈጠፈ የሚወርደው የወዝ ቅባት የሚጠራቀምበት ከዕብነ በረድ የተሠራ ወጭት አኖረች፡፡ እኒያ መነኰስም እስከሚሞቱበት ቀን ድረስ የእመቤታችን ድንግል ማርያምን ሥዕል እያገለገሉ ኖሩ፡፡

#የአገሩ_ሊቀ_ጳጳስም የእመቤታችን ሥዕል ሥጋ የለበሰች ሆና ባገኙና ተአምሯንም በተመለከቱ ጊዜ ከዚህ አምላካዊ ግብር የተነሣ አደነቁ፡፡ #ከሥዕሏ_ከሚንጠባጠበው_ቅባት ቀድተው ለበረከት ሲካፈሉም ወዲያውኑ በወጭቱ ውስጥ መላ፡፡ ሥዕሊቱን ወደ ሌላ ቦታም ሊወስዷት በፈለጉ ጊዜም ንውጽውጽታ ሆኖ ብዙዎች በድንጋጤ ወደቁ፡፡ ሥዕሊቱም እስከ ዛሬ ድረስ በዚያች አገር #በጼዴንያ ትገኛለች፡፡
‹‹እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው›› ተብሎ እንደ ተጻፈ መዝ.67፥35 እግዚአብሔር አምላካችን በልዩ ልዩ መንገድ ለሰው ልጅ ተአምራቱን ይገልጣል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግቦ እንደምናገኘው እግዚአብሔር ከዓለት ላይ ውኃ እያፈለቀ ሕዝቡን ያጠጣል፡፡

#ከግዑዝ_ዓለት ውስጥ ውኃ የሚያፈልቅ አምላክ ከሥጋዋ ሥጋ፤ ከነፍሷ ነፍስ ተዋሕዶ ካከበራት ከቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ወዝ እንዲፈስ ቢያደርግ ምን ይሳነዋል? እንደዚሁም ቅዱሳን ሐዋርያት በቃላቸውም፣ በልብሳቸውም፣ በጥላቸውም ሙታንን በማስነሣት፤ ሕሙማንን በመፈወስ ተአምራትን ያደርጉ ነበር፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ጴጥሮስ በጥላው፤ ቅዱስ ጳውሎስም በልብሱ ቅዳጅ ያደርጓቸው የነበሩ ተአምራትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሐዋርያት ከእግዚአብሔር ዘንድ በተሰጣቸው ጸጋ በልብሳቸውና በሰውነታቸው ጥላ ተአምራትን ማድረግ እንደ ተቻላቸው ኹሉ አምላክን በማኅፀኗ የተሸከመችው ወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያምም በሥዕሏ ወዝ ብዙ ሕሙማንን መፈወስ ይቻላታል፡፡ ከቅዱሳን ልብስና ጥላ የእርሷ ሥዕል ይከብራልና፡፡

#በየዓመቱም መስከረም 10 ቀን ቤተ ክርስቲያናችን ከእመቤታችን 33ቱ በዓላት ውስጥ አንዱ አድርጋ በታላቅ ድምቀት ታከብረዋለች፡፡
የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፤ የልጇ፣ የወዳጇ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቸርነት አይለየን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
✞✞✞ በእንተ ቅዱሳን ✞✞✞
Photo
# የቅዱስ_ሶፍሮኒ_ጸሎት !
ዘላለማዊ ጌታና የሁሉ ፈጣሪ በማይሻር መልካምነትህ
ወደዚህ ሕይወት ጠርተኸኝ የጥምቀትን ጸጋ እና የመንፈስ
ቅዱስን ማኅተም ስጦታ ሰጠኸኝ ፡፡ ፊትህን የመፈለግ
መሻትን በውስጤ አኖርክ ፡፡ ጸሎቴን ስማ!
አቤቱ ያለ አንተ ሕይወት ፣ ብርሃን ፣ ደስታ፣ ኃይል ፣
ጥንካሬ ፣ ጥበብ የለኝም ፡፡ ከዓመፃዬ የተነሳ ዓይኖቼን
ወደ አንተ ለማንሳት አልደፍርም ፡፡ ነገር ግን
"አምናችሁም በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ"
ያልከውን አንተን እታዘዛለሁ። (ማቴ 21: 22)። እውነት
እውነት እላችኋለሁ፥ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ
ይሰጣችኋል። እስከ አሁን በስሜ ምንም አልለመናችሁም፤
ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን ለምኑ ትቀበሉማላችሁ። (ዮሐ
16፥23-24) ብለአል። ስለዚህ አሁን ወደ አንተ
ለመቅረብ ደፈርኩ፡፡ ከሥጋና ከመንፈስ እድፍ ሁሉ አንጻኝ
፡፡ በትክክል እንድፀልይ አስተምረኝ፡፡ ለማይገባኝ
አገልጋይህ ለእኔ የሰጠኸውን ቀን ባርክ፡፡ በበረከትህ
ኃይል ሁልጊዜ በእምነት ፣ በተስፋና ፍቅር ፣ በትሕትና ፣
በትዕግሥት ፣ በገርነት ፣ በሰላም ፣ በንጽህና ፣ በታናሽነት
፣ በድፍረት እና በጥበብ የምናገረውንና የምሰራውን
በንጹህ መንፈስ ለአንተ ክብር እንድሠራ አድርገኝ።
ሁልጊዜ ህልው እና መገኘትህን አስታውቀኝ ፡፡ ጌታ
አምላክ ሆይ በማይለዋወጥ ቸርነትህ ፈቃድህን አሳየኝና
ያለ ኃጢአት በፊትህ እንድጓዝ አድርገኝ፡፡ አቤቱ ልቦች ሁሉ
የተከፈቱልህ ፤ የምፈልገውን እና የሚያስፈልገኝን
ታውቃለህ። ዓይነ ስውርነቴን እና ድንቁርናዬን ታውቃለህ፡፡
የእኔን ድካም እና በደል ታውቃለህ፡፡ የእኔ ህመም እና
ጭንቀት ከአንተ የተሰወረ አይደለም፡፡ ስለዚህ
እለምንሃለሁ ጸሎቴን ስማኝ የምሄድበትን መንገድ
በመንፈስ ቅዱስ ኃይልህ አስተምረኝ፡፡ ጠማማነቴ በሌላ
መንገድ አይምራኝ። አቤቱ አትተወኝ ይልቅ ወደ መንገድህ
መልሰኝ፡፡
ጌታ ሆይ በፍቅርህ ኃይል መልካም የሆነውን አጥብቄ
እንድይዝ እርዳኝ ። ነፍስን ከሚያቆሽሽ ከማንኛውም ቃልና
ድርጊት ሁሉ ፣ በፊትህም ከማይደሰት እና በዙሪያዬ ላሉት
ሰዎችን ከምጎዳበት ከማንኛውም ስሜቶቼ ጠብቀኝ፡፡ ምን
ማለት እንዳለብኝ እና እንዴት እንደምናገር አስተምረኝ ፡፡
ዝምታዬ ቅዱስ ፈቃድህ ከሆነ ዝም እንድል እና መልስ
እንዳልሰጥ እርዳኝ። ሌሎች ሰዎችን እንዳልጎዳና
እንዳልሰብር በሰላም መንፈስ ዝም እንድል አነቃቃኝ
አበረታታኝ ፡፡ በትእዛዛትህ መንገድ አቁመኝ ፣ እስከ
መጨረሻ እስትንፋሴ ድረስ ከመንግሥትህ የብርሃን ህግ
እንዳልለይ እርዳኝ። አቤቱ ወደ አንተ እጸልያለሁ ማረኝ ፡፡
በመከራና በጭንቀት ጊዜ አድነኝ የማዳንህም መንገድ
ከእኔ አትሰውር፡፡ በሞኝነቴ እግዚአብሔር ሆይ ስለ ብዙ
እና ታላላቅ ነገሮች እለምንሃለሁ ፡፡ ግን እኔ ሁል ጊዜ
ክፋቴን ፣ ኃጢአቴን ፣ በደሌን አስባለሁ ማረኝ! በሞኝነቴ
ትምክህት ከአንተ ፊትም አትጣለኝ ፡፡ ከሰው ሁሉ ይልቅ
ኃጥህ የሆንኩ እኔ እንደ ትዕዛዝህ አንተን በፍጹም ልቤ ፣
በፍጹም ነፍሴ ፣ በፍጹም አሳቤ ፣ በፍጹም ኃይሌ
እንድወድህ የምችልበትን ጉልበትና ጸጋህን ስጠኝ።
ጌታ ሆይ ፣ በመንፈስ ቅዱስ መልካሙን ማስተዋልን
ስጠኝ፤ መሠረታዊውን ነገር አስተምረኝ ፡፡ ከመሞቴ በፊት
እውነትን አሳውቀኝ ፡፡ ለኃጢአቶቼ ከልቤ ንስሃ ሳልገባ
አትውሰደኝ። አዕምሮዬ በክፋት ታውሮ አትውሰደኝ ፡፡
ሕይወቴን ለማጠናቀቅ በደረስኩ ጊዜ ነፍሴን በፊትህ
እንድትመጣ እንዳዘጋጃት ማስጠንቀቂያ ስጠኝ ፡፡ ጌታ
ሆይ በዚያ አስደናቂ ሰዓት ከእኔ ጋር ሁን መድኃኒቴ
ደስታዬ በጸጋህ መዳኔን አረጋግጠኝ።
በምስጢር ከሰራሇቸው ኃጢአቶች አንጻኝ ፡፡ ከተሰወረ
በደል እጠበኝ፡፡ በፍርድ ወንበርህ ፊት እንዳላፍር መልስን
ስጠኝ፡፡
ትርጉም ፡ ብስራት ገብርኤል
[ምንጭ ፦ Orthodox Mistry Prayer at
Daybreak by St. Sophrony of Essex]
"ሰይጣን የማይነካው ዕቃ "

በአንድ ሐገር ድንገት የአንድ" ጠንቋይ ዝና ከዳር ዳር ተሰማ ። ሰውዬው የማያሳየው ምትሐት የለም። አንበሳ ላለ አንበሳ፣ ነብር ላለ ነብር፣ የሞተ ዘመዴን ላለ የሞተ ዘመዱን፣ የጠፋብኝን ዕቃ ከቤት ፈልገህ አምጣልኝ ላለ ዕቃውን ያመጣለታል። እንደሚታወቀው አጋንንት ከክብራቸው የተዋረዱ መላእክት ናቸው። መላእክት ደግሞ በፈለጉት ሁኔታ መገለጥ ይችላሉ። ይህ ጠንቋይ የሚሰጣቸውን ገጸ ባሕርይ ተቀብለው አንዴ አንበሳ፣ አንዴ ነብር፣ አንዴ ሰው እየሆኑ የሚተውኑት እንግዲህ አጋንንቱ ነበሩ።
የበዚህ ጠንቋይ ዝና ወደ ንጉሱ ደረሰ። ንጉሱ ደግሞ ክርስቲያን ቢሆንም ከመጸሐፍ ቅዱስ ይልቅ እንዲህ ያለ ተአምር እዚህ ቦታ ተፈጸመ ሲባል ለማየተት የሚሮጥ ሰው ነበር። ተአምር የሚወድ ሰው ደግሞ ክርስቲያንም ቢሆን ሰይጣን በሚሰራው ምትሐት መታለሉ የማይቀር ነው። ስለዚህ ይህ ንጉስ የተማረውን መጽሐፍ ቅዱስ ዘንግቶ በጠንቋዩ ምትሐት አመነ።
ይህንን የሰሙ የንጉሱ ንስሐ አባት ነገሩን ሰምተው ወደ ቤተ መንግሥት ሲሮጡ ደረሱ። ሲደርሱ ንጉሡ ከቁም ነገር አልቆጠራቸውም። እሱ የጠንቋይ ትርዒት ማየት ቀጠለ።
"እስቲ አሁን ደግሞ እእእ ነጭ ፈረስ አምጣልኝ" ማለቱን ቀጠለ
በነገሩ ያዘኑት "ኧረ ንጉሥ ሆይ ይተዉ፡ ይህ እኮ የሰይጣን ምትሐት ነው "
ብለው ሊያስረዱት ሲሉ በቁጣ አስቆማቸው።
ተአምር የሚከተል ሰው መቼስ ቢነግሩት አይሰማም። ጭራሽ እንዲያው ለንስሐ አባቱ እንዲህ አላቸው።
" የሰይጣን ስራ ነው አትበሉ፤ ቅናት ነው ይኼማ,,,, ይልቅ እርስዎም የሚፈልጉትን ነገር ይጠይቁት ያምጣልዎት!"አላቸው።
ጠንቋዩ «የፈለጉትን ላምጣልውት,,,,,ምን ይፈልጋሉ,,,, " የሞተ ዘመድ አለዎት,,,,, ወይስ ከቤትዎ,,,, » አላቸው በኩራት።
ካህኑ ውስጣቸው በመንፈሳዊ ቅናት ተቃጠለ። « እንግዲያውስ የፈለኩትን ማምጣት ከቻልህ ወደ ቤተ መቅደስ ሔደህ ልብሰ ተክህኖዬ ውስጥ መስቀል አለ እርሱን ይዘህልኝ ና » አሉት።
ይህን ግዜ ጠንቋዩ ገና ድግምቱን ሲጀምር አጋንንቱ እላዩ ላይ ሰፍረው ጣሉት።
በካህኑ ፊት ወደቀ። ሰይጣን ምንም ነገር ማምጣት ይችል ይሆናል። መስቀሉን ግን ማምጣት አይችልም። አባቶቻችን ሰይጣን እንኳን መስቀል ቀርቶ መስቀለኛ መንገድም አይወድም ይላሉ።
የጌታችን ቅዱስ መስቀል ሆይ ቅዱስ ዳዊት እንዳለ «ብከ ንወግዖሙ ለኩሎሙ ጸርነ»
«በአንተ ጠላቶቻችንን እንወጋቸዋለን!

ከዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ከሰማዕታቱ በረከት ይክፈለን

መስከረም 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ከሰኔ 22 ቀን 2012ዓ.ም. ሌሊት ጀምሮ በተከታታይ ለሁለትና ሦስት ቀናት በምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት በአረመኔዎች ሰማዕትነትን የተቀበሉ ክርስቲያኖች መታሰቢያ መሆኑን ሀገረ ስብከቱ አስታውቆ እንደነበር ይታወቃል።
ሰማዕታቱን ለመዘከርም ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ቦታው አምርተዋል። ቤተ ክርስቲያን ልጆቿ በክርስቲያኖዊ ጥብዓት ሰማዕትነትን ሲቀበሉ በተግባራቸው ብትኮራም አሁንም መከራ ላይ የማጥናትና ለሟች ወገኖች አለኝታ በመሆን ከሰማዕታቱ በረከት እንዲካፈሉ ልጆቿን ተግታ ማስተማርም ይኖርባታል። የሟች ወገኖቻችንን ቀሪ ዘመዶች መርሳት ከገዳዮች ጋር መተባበር መሆኑን ክርስቲያኖች መረዳት ይኖርብናል።
መንግሥትን ፍትሕ ተዳፍና እንዳትቀር የምንወተውተውን ያህል ክርስቲያኖችም በመከራ ውስጥ ያሉትን ወገኖቻችንን በማጽናትና የተጎዱትን በመደገፍ አይዟችሁ ባይ ወገን እንዳላቸው በተግባር መግለጥ ይኖርብናል። በክርስቲያኖች የደረሰውን መከራ ሳናዛንፍ ለዓለሙ ሁሉ ማሳወቅ ተገቢ የመሆኑን ያህል ምግብ፣ ልብስ፣ መጠለያና ቋሚ መተዳደሪያ በማጣት ክርስቲያን በመሆናቸው ብቻ በደረሰባቸው መሪር ኀዘን ተስፋ እንዳይቆርጡ መደገፍም የክርስቲያኖች ተግባር መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል። መከራውን ለመቋቋም መተባበርና አንድ አሳብ መሆንም ዘመኑ የሚጠይቀን ግዴታ ነው። ዘመኑን መሻገር የምንችልበትን ተግባር መፈጸም ብቻ ሳይሆን ዘመኑን ዋጅተን የቤተ ክርስቲያንን ብርሃንነት መግለጥም ክርስቲያናዊ ኃላፊነታችን ነው።




@mkpublicrelation የተወሰደ
ፎቶ ከማኅበራዊ ሚዲያ
አባ ሕርያቆስ
(ዲ. ሕሊና በለለጠ)
+++++++++
ጥቅምት ኹለት የአባታችን የአባ ሕርያቆስ ዕረፍቱ ነው፡፡ አባ ሕርያቆስ ከጽድቅ ሕይወቱ ባሻገር ለእመቤታችን ባለው ፍቅርና በደረሰው የቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ የሚታወቅ ታላቅ አባት ነው፡፡ በ1994 ዓ.ም. ትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት ያሳተመው (አዲስ አበባ) ስንክሳር የጥቅምት ኹለቱ ንባብ “ወበዛቲ ዕለት … ተዝካሮሙ ለሕርያቆስ ወቴክላ ሰማዕት በረከቶሙ ተሀሉ ምስሌነ ለዓለመ ዓለም አሜን” (ትርጉም- በዚህችም ቀን ደግሞ የሕርያቆስና የሰማዕት ቴክላ መታሰቢያቸው ነው በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን፡፡) ከማለት በስተቀር የሚገልፀው ነገር የለም፡፡ ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜን የመሳሰሉት መጻሕፍት ግን ስለ ጻድቁ በጥቂቱ ያትታሉ፡፡

-----የስሙ ትርጓሜ

ሕርያቆስ/ ኅርያቆስ ማለት (የቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ) እንደሚገልጠው ኅሩይ/ምርጥ/ ማለት ነው፤ ለሹመት መርጠውታልና ምርጥ ተባለ፡፡
አንድም ረቂቅ ማለት ነው፤ ምሥጢረ ሥላሴን ከኹሉ ይልቅ አምልቶ አስፍቶ ይናገራልና፡፡
አንድም ፀሐይ ማለት ነው፤ አብ ፀሐይ ወልድ ፀሐይ መንፈስ ቅዱስ ፀሐይ እያለ ጽፏልና፡፡
አንድም ብርሃን ማለት ነው፤ የምእመናንን ልቡና በትምህርቱ ብሩህ ያደርጋልና፡፡ ዘአብርሃ መንበረ ማርቆስ በብርሃን እንዲል፡፡
አንድም ንህብ ማለት ነው፤ ንህብ የማይቀስመው አበባ የለም፣ እርሱም የማይጠቅሰው ሊቅ የለምና፡፡

--------ሹመት

ሐዋርያት ስለ ሹመት በሠሩት ቀኖና የተማረና ግብረ ገብ የኾነ እንዲሾም አዝዘዋል፡፡ ኹለቱንም ያስተባበረ ባይኖር ግብረ ገብ የኾነ ነገር ግን ያልተማረ እንዲሾም ሥርዓቱ ያዛል፡፡ ትምህርቱን በጊዜ ሂደት ያመጣዋልና፡፡ በዚኽም መሠረት አባ ሕርያቆስ ያልተማረ ቢኾንም በምግባሩ የተመሠከረለት ግብረ ገብ በመኾኑ ተሾመ፡፡ በዚኽ ሹመትና ሥርዓትን የሚያፀና በመኾኑ ግን በክፋት የሚቀኑበት ብዙዎች ነበሩ፡፡ ያልተማረ በመኾኑም ይንቁታል፡፡ ዕለት ዕለትም አዋርደውት ከሹመቱ ለማስሻር ይጥሩ ነበር፡፡ እርሱ ግን “ወእቀውም ዮም በትሕትና ወበፍቅር” እንዲል እንደጠሉኝ ልጥላቸው እንደናቁኝ ልናቃቸው ሳይል በፍቅርና በትሕትና ጸንቶ ያስተምራቸው ነበር፡፡

--------የዕውቀት መገለጥ/የቅዳሴ ማርያም ድርሰት

አባ ሕርያቆስ ተምኔቱ እንደ ቅዱስ ኤፍሬም ነው፡፡ የእመቤታችን ምስጋና እንደ ባሕር አሸዋ እንደ ሰማይ ኮከብ በዝቶልኝ፣ እንደ ምግብ ተመግቤው፣ እንደ መጠጥ ጠጥቼው፣ እንደ ልብስ ለብሼው እያለ ይመኝ ነበር፡፡
በእርሱ የሚቀኑበት ተንኮለኞች ከዕለታት በአንዱ ቀን በምን ምክንያት እንሻረው ብለው ተማክረው ቀድሶ ማቁረብ አይችልምና ቀድሰህ አቁርበን ብለን በዚህ ምክንያት እንሻረው ብለው ተስማሙና እንዲቀድስ አደረጉት፡፡
አባ ሕርያቆስም ሥርዓቱን ጨርሶ ከፍሬ ቅዳሴው ሲደርስ ተንኮለኞቹ “ከሊቃውንት ቅዳሴ የሚያስቸግረውን እናውጣለት” እያሉ ሲያወጡ ሲያወርዱ የለመኗትን የማትነሳ የነገሯትን የማትረሳ እመቤት ገልጻለት “ጎሥዓ ልብየ ቃለ ሠናየ” ብሎ “ወይእዜኒ ንሰብሖ” እስኪል ድረስ ሰተት አድርጎ ተናግሮታል፡፡
የሚንቁትና የሚጠሉት ሰዎች “ ይኽ የነገሩትን ቀለም እንኳን አከናውኖ መናገር የማይቻለው ዛሬስ እንግዳ ድርሰት እደርሳለሁ ብሎ ያገኘ ያጣውን ይቀባጥር ጀመረ!” ብለው አደነቁበት፤ የሚወዱትና የሚያከብሩት ግን “ከመንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እንዲኽ ያለ ምሥጢር ከእሩቅ ብእሲ ይገኛልን” ብለው አደነቁለት፡፡ ወዲያውም ጽፈን ደጉሰን ልማድ እንያዘው ብለው ወሰኑ፡፡ ተንኮለኞቹ ግን ይኽንንም ስለተቃወሙ እንደ ሀገራችን ልማድ እንያዘው በሚል ተስማሙ፡፡ በሀገራቸው ልማድ እንግዳ ድርሰት የተደረሰ እንደኾነ ጽፈው ደጉሰው ከእሳት ይጥሉታል፣ ከእሳት ሳይቃጠል የወጣ እንደኾነ ከውሃ ይጥሉታል፣ ከውሃ ሳይርስ የወጣ እንደኾነ ከሕሙም ላይ ይጥሉታል፣ ድውይ የፈወሰ እንደኾነ ደገኛ ድርሰት ነው ብለው ይይዙታል፡፡

ይኽንንም የአባ ሕርያቆስን ድርሰት ጽፈው ደጉሰው ከእሳት ላይ ጣሉት ከእሳት ሳይቃጠል ወጣ፤ ከውሃ ጣሉት ሳይርስ ወጣ፤ ከሕሙም ላይ ጣሉት ድውይ ፈወሰ፣ ይልቁንም ሙት አስነሣ፡፡ ከዚኽ በኋላ ደገኛ ድርሰት ነው ብለው ጽፈው ደጉሰው ያዙት፡፡ በጥራዝም (ከ13ቱ ቅዳሴያት ጋር) 14ኛ አድርገው ጠርዘውታል፡፡

የተቀደሰው ከ33ቱ የእመቤታችን በዓላት በአንዱ ቀን ነው፡፡ የቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ አባ ሕርያቆስ ምሥጢር ባይገለጥለት ኖሮ በዕለቱ ቅዳሴ ሐዋርያትን ወይም ቅዳሴ እግዚእን ይቀድስ እንደነበር ይጠቁመናል፡፡ ቅዳሴ እግዚእ “እምድንግል ተወሊዶ ከመ ፈቃደከ ይፈጽም” ብሎ ድንግልን ያነሣታልና፡፡
አባ ሕርያቆስ ተሹሞ ሳለ ብዙ ድርሳን እንደደረሰና ብዙ ተግሳጽ እንደጻፈ የቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ ይገልጻል፡፡

---------ከቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊና ከቅዱስ ያሬድ ኢትዮጵያዊ ጋር

ቅዱስ ያሬድ ማይ ኪራህ መደበይ ታብር በሚባል ቦታ ይኖር ነበር፡፡ እመቤታችን ኤፍሬምን ከሶርያ አባ ሕርያቆስን ከብህንሳ በደመና ጠቅሳ ያሬድ ካለበት ቦታ አመጣቻቸውና “አንተ(ኤፍሬም) ውዳሴዬን አንተ(ሕርያቆስ) ቅዳሴዬን ነግራችሁት እርሱ(ያሬድ) በዜማ ያድርስ” ብላቸው፣ እነርሱም ለቅዱስ ያሬድ ነግረውት በዜማ አድርሶታል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ከዚኽ ጋር አያይዞ የቀሩትን 13ቱን ቅዳሴያት ኹሉ በዜማ ደርሷል፡፡

--------እመቤታችን የምትወደው ምስጋና

አንድ ባሕታዊ እመቤታችንን “ከምስጋናሽ ኹሉ ማንን ትወጃለሽ?” ብሎ ቢጠይቃት “ልጄ ዳዊትን፣ አቡነ ዘበሰማያትን ቢደግሙለት እንዲወድ እኔም ውዳሴዬን ቅዳሴዬን ቢደግሙልኝ እወዳለሁ” ብላዋለች፡፡

----------.ብህንሳ የት ናት?

ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ ስለ ብህንሳ የሚከተለውን ብሏል፡-
“ብህንሳ ቅድመ ትሰመይ አርጋድያ ወድኅረ መኑፍ ይላል፡፡ ብዙ ጊዜ ስመ ተፋልሶ አግኝቷታል፡፡ በፊት አርጋድያ ኋላም መኑፍ ተብላለች፤ ዛሬም ብህንሳ ትባላለች፤ ሴትና ወንድ ያልተለየባት ገዳም ናት እንደ ዘጌ እንደ ቆራጣ እንደ ቀንጠፋሜ፤”

ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ የባሕር ማዶ ድርሰት መኾኑን በሚጠቁም መልኩ ቅዱስ ያሬድ ከባሕር ወዲኽ እንዳመጣልንና ከተከዜ ወዲኽ ደግሞ ሳሙኤል ትውልደ ጌዴዎን ዘገበዘ አክሱም እንዳመጣው ይገልጻል፡፡ ስለዚህ ቢንያስ እንደ ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ ኢትዮጵያ ውስጥ አይደለችም።

Kyriakos of bhainsa ስለተባለ ሰው Wikipedia ቢገልጽም ዝርዝር መረጃን አላገኘሁም። Bhainsa የምትባል ከተማ ግን በሕንድ እንምደትገኝ ይገልጻል።

በዚኽ ዙሪያ ጥናት ያደረጋችኹ ወይም ተጨማሪ ያነበባችሁና የተማራችሁ እስኪ ሐሳባችሁን ወዲኽ በሉ፤ ፍላጎቱ፣ አቅሙና ጽናቱ ያላችሁም በጥልቅ መርምሩና ግለጡልን፡፡

የአባታችን የአባ ሕርያቆስ ምልጃ አይለየን፤ እመቤታችን ፍቅሯን በረከቷንና የምስጋናዋን ምሥጢር በልቡናችን ታሳድርልን ዘንድ በረድዔቱ ይባርከን፡፡

ጥቅምት 2፣ 2007 ዓ.ም.
+ የሰጠኸኝ ሴት +

እግዚአብሔር አዳምን "አትብላ ካልሁህ ዛፍ በላህን?" ብሎ ጠየቀው:: አዳምም :- ከእኔ ጋር እንድትሆን የሠጠኸኝ ሴት ከዛፉ ሠጠችኝና በላሁ አለ::

የሰጠኸኝ ሴት! በጣም ይገርማል:: ሚስቴ አላለም::
አዳምና ሔዋን የተገናኙ ቀን አዳም ያለውን አስታውሱ
"ይህች አጥንት ከአጥንቴ
ይህች ሥጋ ከሥጋዬ" ብሎአት ነበር::
ምንም እንክዋን አዳም ወላጆች ባይኖሩትም ሰው እናትና አባቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ብሎም ነበር::
ራቁታቸውን ቢሆኑም አይተፋፈሩም ነበር::

አሁን በራቁቱ ብቻ ሳይሆን በሔዋንም አፈረባት::
እናትና አባቱን ይተዋል እንዳላለ ሔዋንን ራስዋን ተዋት::
ከሚስቱ ጋር መተባበር ቀርቶ ክስ ጀመረ::

አካሌ አጥንቴ ሥጋዬ ማለቱ ቀረና የሠጠኸኝ ሴት አለ::
የጫጉላው ጊዜ አለፈና ከሚስትነትዋ ሴትነትዋ ብቻ ታየው::

በጋብቻ ብቻ አይደለም እግዚአብሔር የሠጠንን ነገር
ሁሉ ቀድመን የራሳችን እናደርጋለን ነገሮች ሲበላሹ ግን ባለቤትነቱን ወደ እርሱ እንመልሰዋለን::

የሠጠኸኝ ሥራ
የሠጠኸኝ ወላጆች
የሠጠኸኝ ሰፈር
የሠጠኸኝ ሀገር
የሠጠኸኝ መሪ
የሠጠኸኝ ጉዋደኞች
የሠጠኸኝ ደካማ ሥጋ
የሠጠኸኝ ዓይን

ትናንት ሲሠጠን ዘምረን የተቀበልነውን ሥጦታ ዛሬ ለምሬት እንጠቅሰዋለን:: የሠጠኸኝ የሠጠኸኝ .... ሠጠኝና በላሁ ብለን ቀርጥፈን ለበላነው ዕፀ በለስ ፈጣሪን እንከስሰዋለን::

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
እመቤታችን ተወለደች ማለት ጌታ ሊወለድ 15 ዓመት ቀረው ማለት ነው:: እግዚአብሔር ከሴት የተወለደ ልጁን ሊልክ የዘመኑ ፍጻሜ ቀረበ ማለት ነበር። እግዚአብሔር ሃና እና ኢያቄምን ሳይወልዱ ያዘገያቸውም ለዚህ ታላቅ ክብር እንዲበቁ ነበር።
ቀድመው ልጅ ቢወልዱ ኖሮ ይህችን የፍጥረት ደስታ የሆነች ልጅ አይወልዱም ነበር:: የእርስዋ የልደት ቀን የፍጥረት ደስታ ቀን ነው::

ክርስቶስ ፀሐይ ከሆነ የዛሬው ዕለት ሰማይዋ የተዘረጋችበት ዕለት ነው።

ክርስቶስ የሕይወት ውኃ ከሆነ ዛሬ ምንጭዋ የፈለቀችበት ዕለት ነው።

ክርስቶስ መድኃኒት ከሆነ ዛሬ የመድኃኒቱ ሙዳይ የተገኘችበት ዕለት ነው::

ወንጌል በመጥምቁ ዮሐንስ መወለድ ብዙዎች ደስ ይላቸዋል ይላል። በእመቤታችን መወለድ ምን ያህል ሰዎች ደስ ይላቸው ይሆን? የእመቤታችን ልደት በብዙ ሀገራት ብሔራዊ በዓል ሆኖ ይከበራል።

እኛም በሊባኖስ ተራሮች (አድባረ ሊባኖስ) መወለድዋን በማሰብ ከደጅ ወጥተን ቅድም አያቶችዋ በጨረቃ ተመስላ በህልማቸው ያዩአትን የጨረቃችንን (በግሪኩ ሶልያና) ልደት ጨረቃን እያየን እናከብራለን። የልደትዋ ቀን ልደታችን ነው!

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ግንቦት ልደታ 2012 ዓ ም
2024/06/03 04:46:07
Back to Top
HTML Embed Code: