Telegram Web Link
እሺ ብትሉ…

ልጆቼ! እስኪ ምላሴን ላሰናብትባችሁና እናንተም በትዕግሥት አድምጡኝ! የቤት ሠራተኛ አላችሁ እንበል፡፡ ይህቺ የቤት ሠራተኛችሁ የለበሰችውንና በወጥ፣ በአመድ እንዲሁም በሌላ ቆሻሻ እድፍ ያለ ልብሷን ትለብሱ ዘንድ ትፈቅዳላችሁን? በእርግጠኝነት አትፈቅዱም፡፡ ግን የብዙዎቻችን ሰውነት ከዚህ ልብስ በላይ መቆሸሽዋስ ታውቃላችሁን?

ልጆቼ! ንግግሬ በጣም እንደሚያሳምም አውቃለሁ፤ ግን ምን ላድርግ? የተስተካከለ ሕይወት ቢኖረን እንዲህ የምናገር ይመስላችኋልን? በፍጹም! አንድ የቆሰለ የሰውነት ክፍል ቢኖራችሁ ሐኪሙ ይህን ቁስላችሁ በጣቱ ሳይነካካ ማከም ይችላልን? አይችልም! እኔም እንዲህ ቁስላችሁን ካልነካካሁት በስተቀር ማከም አልችልም፡፡ ለነገሩ ሰው ሰውነትህን አትንካ ማለት ይቻላልን አይቻልም! ታድያ እኔና እንናተ እኮ አንድ አካል ነን፡፡ በክርስቶስ አንድ ኾነን የለምን? እንግዲያውስ ንግግሬን አትጥሉት፤ ክፉ ግብራችሁን እንጂ፡፡

ችግሩ ከማን ነው ከእኛው ወይስ ከቆሻሻው? አንድ ወደ ትዕይንት (ቲያትር) ቤት የሄደ ወጣት ገላዋን ገላልጣ የምትተውን ተዋናይትን አይቶ ዝሙትን መፈጸም የማያስብ ማን ነው? ደጋግሞ የዝሙት ዘፈንን የሚሰማ ሰው ዝሙትን ከመፈጸም መቋቋም እችላለሁ የሚል ማን ነው? ቀኑን ሙሉ የዝሙት ጽሑፎችን ሲያነብ የሚውል ሰው ዝሙትን ከመፈጸም መጠበቅ እችላለሁ የሚል ማን ነው?

ልጆቼ! ትዕይንቱን እያየነው፣ ዘፈኑን እየዘፈንነው፣ መጽሐፉንም እያነበብነው ኾኖም ግን መፍትሔ ካላገኘንበት ችግሩ እየባሰ የሚሄድ አይደለምን? እኛ ፈቃደኞች ከኾንን ግን መፍትሔው በሥጋችን ላይ ካለው ደዌ በላይ በጣም ቀላል ነው፡፡ ምክንያቱም የሥጋችን ቁስል ሐኪም፣ መድኃኒት፣ ጊዜ ያስፈልጓል፡፡ የነፍሳችንን ቁስል ግን ፈቃድ በቂ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔርን የማያውቁ አሕዛብ ከእኛ በላይ በንጽሕና ሲኖሩ ሳይ በጣም አፍራለሁ፡፡ እንግዲያውስ ልጆቼ እንመለስ፡፡ ያቆሸሹንን ነገሮች እንጣላቸው፤ እንቁረጣቸው፤ እናስወግዳቸው፡፡ ሰነፎች አንሁን፡፡

ውሳኔው የእኛው ነው፡፡ መጽሐፍ ሲናገር “እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ እምቢ ብትሉ ግን ብታምፁም ሰይፍ ይበላችኋል” ይላል /ኢሳ.1፡19-20/፡፡ ስለዚህ ሁሉም ነገር በእኛ እሺታና እምቢታ የተወሰነ ነው ማለት ነው፡፡ የምንኮነነውም የምንመሰገነውም በዚሁ መሠረት ነው ማለት ነው፡፡ መድኃኒዓለም በመንግሥቱ በመጣ ጊዜ ኑ እናንተ የአባቴ ብሩካን ከሚላቸው ጋር በቸርነቱ ይደምረን አሜን፡፡

ምንጭ፦ ሰማዕትነት አያምልጣችሁ መጽሐፍ በ ገብረ እግዚአብሔር ኪደ
የሰውን ልጅ በሩህሩህነት አሸንፈው። ቀናተኛውን በመልካምነትህ እንዲደነቅ አድርገው፤ ሁሉንም ሰው ውደድ ነገር ግን ከሁሉም ሰው ጋር ርቀትህን ጠብቀህ ኑር።

አባ እንጦንስ
#ሰሙነ_ሕማማት

ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ሰሙነ ሕማማት የጾመ ሁዳዴ የመጨረሻው ሳምንት፤ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕማም የሚታሰብበት፤ ካህናትና ምእመናን በአጸደ ቤተክርስቲያን ተሰብስበው የሕማሙን ነገር የሚያወሳውን ዜማ የሚያዜሙበት፤ ግብረ ሕማም በመባል የሚታወቀውን መጽፍ የሚያነቡበትና የሚሰሙበት፤ በነግህ፣ በሠልስት፣ በስድስት፣ በተሰዓት /ዘጠኝ /ሰዓት፣ በሰርክ /በዐስራ አንድ/ ሰዓት እየመላለሱ የሚሰግዱበትና የሚጸለዩበት ልዩ ሳምንት ነው ከሆሳዕና ማግስት እስከ ትንሳኤ።

በዚህ ሳምንት በተለይ ካህናት ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ ምክንያቱም ጌታችን የደረሰበትን መከራና ስቃይ እንዲሁም የሰው ልጅ ፭ ሺ ፭ መቶ ዘመን በጨለማ ግዞት ይኖር እንደነበር ለማዘከርም ጭምር ነው። የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መከራና ሕማም በጽኑ እንድናስበው ያስተማሩን ሐዋርያት ናቸው። ለእነርሱም የነገራቸው ደግሞ ራሱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

ሰሙነ ሕማማት የጌታችንን ሕማማት ከማሰብ ጋር በየዕለቱ በርካታ ድርጊቶች መፈጸማቸውን የምናስታውስበት ሳምንት ነው፦

#ሰኞ
#መርገመ_በለስ_የተፈጸመበት_ሰኞ_ይባላል
በዚህ ዕለት ጌታችን ከቢታኒያ ሲወጣ ተራበ ቅጠል ያለባትን በለስ ተመልክቶ ወደ በለሲቱ ቢቀርብ ከቅጠል በቀር ምንም ነገር ባለማግኘቱ “ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ምንም ካንቺ ፍሬ አይበላ” ማር ፲፩፥፲፬ በማለት ስለረገማት መርገመ በለስ የተፈጸመበት ሰኞ ይባላል።

#አንጽሖተ_ቤተ_መቅደስ_ይባላል፡-
ጌታ ወደ ቤተመቅደስ ሄዶ በቤተመቅደሱ የሚሸጡትን እና የሚለውጡትን “ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች” ማቴ ፳፩፥፲፫ በማለት ከቤተመቅደስ ገርፎ አስወጥቷቸዋልና።

#ማክሰኞ
#የጥያቄ_ቀን_ይባላል
ሰኞ ዕለት በቤተመቅደስ ሲሸጡ እና ሲለውጡ የነበሩትን ሁሉ እየገረፈ በማባረሩ ምክንያት ለሰው ልጅ ሹመትንና ስልጣንን የሰጠ ጌታ “በምን ስልጣን ይህንን ታደርጋለህ?” ማቴ ፳፩፥ ፳፫ ተብሎ በፈሪሳውያን ተጠይቋልና የጥያቄ ቀን ይባላል።

#የትምህርት_ቀን_ይባላል፡-
በዚህ ዕለት በቤተመቅደስ ረጅም ትምህርት ስላስተማረም የትምህርት ቀን ይባላል። ሉቃ ፳፩ ፥፳፰ ፣ ማር ፲፪፥፪።

#ረቡዕ
#ምክረ_አይሁድ_ይባላል
ረቡዕ እለት የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው የመከሩበትና ውሳኔ ያሳለፉበት ቀን በመሆኑ ምክረ አይሁድ ይባላል። ወቅቱ የፋሲካን በዓል የሚያከብሩበት ቀን በመሆኑ እና ብዙ ህዝብም ጌታን ይከተለው ስለነበር ሁከት እንዳይነሳ ስጋት ነበራቸው ። ነገር ግን ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ስለነገራቸው ሉቃ ፳፪፥፩-፮ ጭንቀታቸው ተወግዶ በጌታ መያዝ ተስማምተዋል።

#የመልካም_መዓዛ_ቀንም_ይባላል፡-
ጌታችን በዚህ ዕለት በለምጻሙ በሰምዖን ቤት ተቀምጦ ሳለ መላ ሕይወቷን ለዝሙት አስገዝታ ትኖር የነበረችው ማርያም እንተ እፍረት/ባለሽቶዋ ማርያም/ ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ የአልባጥሮስ ሽቱ አምጥታ በራሱ ላይ በማርከፍከፍ ስለቀባቸው ማቴ ፳፮፥፮-፯ የመዓዛ ቀን ይባላል።

#የእንባ_ቀን_ይባላል፡-
ባለሽቱዋ ሴት (ማርያም እንተ እፍረት) ኃጢአቷን ይቅር እንዲላት እየለመነች በእግሩ ስር ተደፍታ በእንባዋ እግሩን አርሳለችና ማር ፲፬፥፱ የእንባ ቀን ይባላል።

#ሐሙስ
#ጸሎተ_ሐሙስ_ይባላል
ጌታችን ለአይሁድ ተላልፎ ከመሰጠቱ በፊት በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ ሲጸልይ በማደሩ ማቴ ፳፮፥፴፮ ጸሎተ ሐሙስ ይባላል።ጌታችን የደቀመዛሙርቱን እግር በፍጹም ትህትና ዝቅ ብሎ ያጠበበት ዕለት በመሆኑም ዮሐ ፲፫፥፫-፲፩ ሕጽበተ ሐሙስ ይባላል።

#የምስጢር_ቀን_ይባላል፡-
ከሰባቱ ምስጢራት አንዱ የቅዱስ ቁርባን ምስጢር ማቴ፳፮፥፳፮-፳፱ በዚህ ዕለት ተፈጽሟልና የምስጢር ቀን ይባላል።

#የሐዲስ_ኪዳን_ሐሙስ_ይባላል፡-
መሥዋዕተ ኦሪት /በእንስሳት ደም የሚቀርብ መሥዋዕት/ቀርቶ ለአለም ድኅነት ራሱን ያቀረበበት ቀን በመሆኑ ሉቃ ፳፪፥፳ የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል።

#የነጻነት_ሐሙስ_ይባላል፡-
ለኃጢአትና ለዲያቢሎስ ባሪያ ሆኖ መኖር ማብቃቱን እንዲሁም የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለሆነም ዮሐ ፲፭፥ ፲፭ የነጻነት ሐሙስ ይባላል።

#ዓርብ
#የስቅለት_ዓርብ_ይባላል
ጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ቤዛ ሆኖ በመልዕልተ መስቀል ላይ ተሰቅሎ የዋለበት ዕለት ነውና ማቴ ፳፯፥፴፭ የስቅለት ዓርብ ይባላል።

#መልካሙ_ዓርብ_ይባላል፡-
ከጌታ ስቅለት በፊት በተለይም በሮማውያን ህግ የወንጀለኛ መቅጫ ምልክት የነበረውን መስቀል ጌታችን በደሙ ቀድሶ የምህረት፣ የሕይወት አርማ፣ የዲያቢሎስ ድል መንሻ ስላደረገው፤ በሞቱ መልካሙን ሕይወት ስላገኘን መልካሙ ዓርብ ይባላል።

#ቅዳሜ
#ቀዳም_ስዑር_ትባላለች
ይህች እለት ከድሮ በተለየ መልኩ የጌታችንን መከራ በማሰብ በጾም ታስባ ስለምትውል የተሻረች ቅዳሜ ይባላል።

#ለምለም_ቅዳሜ_ይባላል፡-
ካህናቱ ለምእመናን ለምለም ቀጤማ የሚያድሉበት ዕለት በመሆኑም ለምለም ቅዳሜ ይባላል። ምዕመናንም ይህንን ለምለም ቀጤማ እስከ ትንሣኤ ለሊት በራሳቸው ላይ ያስሩታል።

#ቅዱስ_ቅዳሜ_ይባላል፡-
ቅዱስ የሆነው እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን አከናውኖ ያረፈበት ቀን ሲሆን በዘመነ ሐዲስ ደግሞ የማዳን ስራውን ሁሉ ፈጽሞ በሥጋው በመቃብር ሲያርፍ በነፍሱ ወደ ሲኦል ወርዶ ሲኦልን በርብሮ ባዶዋን ሲያስቀራት በዚያ የነበሩትን ነፍሳት የዘላለም ዕረፍትን ያወረሰበት ዕለት ስለሆነ ቅዱስ ቅዳሜ ይባላል።

(ስምዐ ጽድቅ  መጋቢት ፳፻፪ ዓ.ም)
🍂  ሰኞ  #ማዕዶት

  ዐደወ = ተሻገረ    
ማዕዶት = መሻገር
                          
     ዛሬ ሰኞ የፋሲካ ማግስት ማዕዶት የሚል ስያሜ በቤተ-ክርስቲያን ተሰጥቶታል ትርጓሜውም መሻገር ማለት ነው። እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ነጻ የወጡበትን ቀን ነው ፋሲካ ብለው  የሚያከብሩት እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት በቅዱስ ሚካኤል አማላጅነት ባሕረ ኤርትራን ከፍለው እስራኤላውያን ተሻግረው ፈርኦንን ከነሰራዊቱ አስጥመው ወደ ዘለአለማዊ እረፍት ምድር ከነዓን ገብተዋል ይኽ ምሳሌ ነው ሙሴ የክርስቶስ በትር የመስቀል ባሕረ ኤርትራ የሲኦል ፈርኦን እና ሰራዊቱ የዲያብሎስ እስራኤላውያን የምዕመናን ምሳሌ ናቸው ክርስቶስ በመስቀል ተሰቅሎ ሲኦልን ከፍቶ አዳምን እና ልጆቹን አሻግሮ ዲያቢሎስን በሲኦል አስጥሞ ምዕመናንንበተድላ ገነት በምስጋናና በእልልታ አኑሯቸዋል።  በዚያምጊዜ የእስራኤል ልጆች ይህንን መዝሙር ለእግዚአብሔር  ዘምረዋል እንዲህም ብለው ተናግረዋል ።

#በክብር_ከፍ_ከፍ_ብሎአልና_ለእግዚአብሔር_እዘምራለው

#ፈረሱንና_ፈረሰኛውን_በባሕር_ጣለ
    .
    .
    .
የፈርዖንን ሰረገሎች ሠራዊቱንም በባሕር ጣላቸው።
                 ( ዘጸ 15 ፥ 1 , 4 )
  

👉 በመንገድም ይጠብቃቸውም ዘንድ መጋቤ ብሉይ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ይራዳቸው ነበር። ( ዘጸ 23 ፥ 19 )

🍀 ይህንንም በዓል የፋሲካ ( የመሻገር ) በዓል ብለው በየአመቱ ያከብሩ ነበር እሥራኤላውያን።

ከግብጽ ነጻ ቢወጡ ፤
ፈርኦን ከሠራዊቱ በባሕር በሲጥም ፣
የኤርትራን ባሕር ተሻግረው ከነዓን ቢገቡም፤
  #ዘላለማዊ_ዕረፍትን_ግን_አላገኙም
የሲኦልን ባሕር አልተሻገሩም ፤
ከዲያብሎስም አገዛዝ ነጻ አልወጡም።


   🍂    +    +     +     +   +   🍂

ዘመኑ ሲደርስ በመጀመሪያው ፋሲካ በምሳሌ የተገለጸው
    
  #አማናዊው_ፋሲካችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ
+          እውነተኛውን መሻገር አሻገረን። 
+         ከሞት ወደ ሕይወት ፣
+          ከኃጢአት ወደ ጽድቅ ፣   
+     ከጨለማ ወደ ብርሃን መለሰን ።

     ከግብጽ ከመሻገራቸው አስቀድሞ ስለ ታረደው ስለ ፋሲካው በግ አማናዊው ፋሲካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ ታርዶ ከሲኦል አንደ ተሻገርን ቅዱስ ጳውሎስ እንዲል አለ።
" #ፋሲካችን_ክርስቶስ_ታርዷልና"
        ( 1ኛ ቆሮ  5 ፥ 7 )

🙏 ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል
                 ድል መንሣትን
      ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን 🙏
            ( 1ኛ  ቆሮ 15 ፥ 55 - 57 )
ማክሰኞ ቶማስ

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ትንሣኤው ሐዋርያት ተሰብስበው በነበረበት በዝግ ቤት ገብቶ ሲገለጽላቸው ሐዋርያው ቶማስ ከእነርሱ ጋር አልነበረም፡፡ ሐዋርያትም የጌታችንን ከሙታን ተለይቶ መነሣት ቢነግሩት ‹‹እኔ ሳላይ አላምንም›› አላቸው፡፡ በሚቀጥለው ሳምንትም ጌታችን ቶማስ በተገኘበት በድጋሜ  ተገለጠላቸው፡፡ ጌታችንም ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስን ‹‹ጣትህን ወደዚህ አምጣና በጎኔ አግባው፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን›› ብሎ በጦር የተወጋ ጎኑን ፥ በችንካር  የተቸነከረ እጁንና እግሩን እንዲዳስሰው በማድረግ ትንሣኤውን  አረጋገጠለት፡፡ ቶማስም ሲዳስሰው እጅ ከእሳት እንደገባ ጅማት ስለተኮማተረ ‹‹ጌታዬ አምላኬም›› ብሎ መሰከረ፡፡  በኋላ ግን ፈውሶታል፤ ኢየሱስም ‹‹ስለ አየኸኝ አምነሀል ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዐን ናቸው›› አለው፡፡  ምንም አንኳን ድርጊቱ የተፈጸመው በዳግም ትንሣኤ ቢሆንም የሐዋርያው መታሰቢያ ሆኖ ዕለተ ማክሰኞ ‹ቶማስ› ተብሎ ተሰይሟል፡፡ (ዮሐ. ፳ ፥ ፳፬ -፴)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
#ክፉ_አሳብ

ልጆቼ! ከመጀመሪያውኑ ክፉ አሳብ ባታስቡ መልካም ነው፡፡ ካሰባችሁ ግን ቢያንስ አትናገሩት፡፡ በዚያው በሕሊናችሁ ውስጥ እያለ ዝም አሰኙት፤ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላም ወዳለመኖር ይኼዳል፡፡

እኛ ሰዎች ነን፡፡ በመኾኑም ብዙውን ጊዜ ክፉ፣ ያልተገቡና ጸያፍ ነገሮችን እናስባለን፡፡ ነገር ግን ቢያንስ እነዚህን አሳቦች አንናገራቸው፤ ቢያንስ ወደ ቃል አንለውጣቸው፡፡ ወደ ውጭ እንዳይወጡ አምቀን እንያዛቸው፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ እየከሰሙና እየደከሙ እየጠፉም ይኼዳሉ፡፡ አንድን እንስሳ ወደ ጉድጓድ ብትጥሉትና ጉድጓዱንም በመክደኛ ብትከድኑት ያ ወደ ጕድጓድ የጣላችሁት እንስሳ የሚተነፍሰውን አየር አጥቶ ይሞታል፡፡ ምናልባት ጥቂት ቀዳዳ ካገኘ ግን በዚያች ቀዳዳ በምትገባው አየር በሕይወት መቆየት ይችላል፡፡ ሲጨንቀውም እናንተን ክፉኛ ለመጉዳት ይዝታል፤ ከወጣም በኋላ ይጎዳችኋል፡፡ ልክ እንደዚሁ እናንተም በልቡናችሁ የተመላለሰውን ኩላሊታችሁ ያጤሰውን ክፉ አሳብ መውጫ ቀዳዳ እንዳይኖረው አድርጋችሁ ብትከድኑት (ብታፍኑት) ይሞታል፤ ከመኖር ወዳለመኖር ይለወጣል፡፡ በአንደበታችሁ በመናገር ጥቂት ቀዳዳ ከከፈታችሁለትና እንደ እንስሳው እንዲተነፍስ ከፈቀዳችሁለት ግን ክፉው አሳብ ክፉ ግብርን ይወልዳል፡፡ ያቆጠቁጣል፡፡ በአሳብ ሳለ ከጎዳችሁ በላይም በገቢር ተወልዶና ተለውጦ ክፉኛ ይጎዳችኋል፡፡

(#የክርስቲያኖች_መከራ #በቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ ገጽ 7➛በገብረ እግዚአብሔር ኪደ የተተረጎመ)
ከትንሣኤ እስከ ዳግም ትንሣኤ ያሉት ዕለታት ስያሜያቸውና ታሪካዊ አመጣጣቸው


ረቡዕ "አልዓዛር"

አልዓዛር ክርስቶስ ያስነሣው የማርያምና የማርታ ወንድም ነው፤ የስሙም ትርጓሜ እግዚአብሔር ረድቷል ማለት ነው፤ (ዮሐ. ፲፩፥፯-፵፰)፤ አልዓዛር የሞተው መጋቢት ፲፯ ነበር፡፡ እህቶቹም ክርስቶስ እንዲመጣ መልእክት ልከውበት ነበር፤ ክርስቶስ ግን በ፬ኛው ቀን ማለትም  መጋቢት ፳ መጥቶ ከሞት አስነሥቶታል፤(ዮሐ.፲፩፥፵፬)፡፡ ፋሲካውንም በወዳጁ በአልዓዛር ቤት ያከብር ዘንድ  ከቀደ መዛሙርቱ ጴጥሮስንና ዮሐንስን አስቀድሞ ላከ፤ ከዚያም በአልዓዛር ቤት ሆኖ የሐዲስ ኪዳንን ሥርዓት ምሥጢረ ቁርባንን ሰርቶ ለደቀ መዛሙርቱ አሳያቸው፤ አልዓዛር ከተነሣ በኋላ በሐዋርያት ኤጲስ ቆጶስነት ተሸሞ ፵ ዓመት አገልግሎ ግንቦት ፳፯ ቀን ዐርፏል (ስንክሳር ግንቦት ፳፯)፡፡


(ምንጭ:-መዝሙረ ማኅሌት ወቅዳሴ፤ ሥርዓተ አምልኮ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፤ የዮሐንስ ወንጌል አንድምታ፤ ምዕ. ፳፥፳፬)
እንኳን በሰላም አደረሳችሁ
<<ዮም ፍስሀ ኮነ በእንተ ልደታ ለማርያም>>
ግንቦት1 ይቺ ቀን ምን ያህል የተወደደችና የተመረጠች ናት ለድህነታችን መሰረት የተጣለበት ድንቅ ቀን!
እመቤታችን ሆይ ልደትሽ ልደታችን ነውና በደስታ እናከብረዋለን፡፡

ቅድሰት እናታችን በረድኤቷ አትለየን!!
ማንም ኋለኛ ነኝ ብሎ ተስፋ አይቁረጥ
(በቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ)

ከመጀመርያ ጀምሮ መልካም ነገርን መምረጥ ክፉ አይደለም፤ በመልካምነት አለመቀጠል ግን ብዙ ወቀሳን ያመጣል፡፡ የብዙ ሰዎች ክፉ መሆን በዚሁ የሚመደብ ነው፤ ብዙዎች ሕይወታቸውን በመልካም ጀምረው በኋላ ግን በክፋት መርዝ ተጠምቀው ሲሰክሩ ተመልክቻለሁና፡፡
እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ፡፡ ምንም እንኳን አሁን ወደ ክፋት ጥልቅ ወርዳችሁ ቢሆንም “ከዚሁ ተመልሰን መነሣት አይቻለንም፤ መለወጥም አይሆንልንም” በማለት ተስፋ የምትቈርጡ አትሁኑ፡፡እናንተ ስትፈቅዱ እግዚአብሔርም ሲረዳችሁ ከክፋት ዐዘቅት መውጣት በእጅጉ ቀላል ነውና፡፡ ከሁሉም በላይ አመንዝራ ተብላ በከተማው ዘንድ ትታወቅ የነበረችውን ሴት በመልካምነቷ እንዴት እንደምትወደስ አልሰማችሁምን? እየነገርኳችሁ ያለሁት በዮሐንስ ወንጌል ላይ ስለተጠቀሰችው ሴት አይደለም፡፡ በእኛ ዘመን ስላለችውና ፍኒሳ ከተባለችው ጋጠ ወጥ ከተማ ስለተገኘችው ሴት እንጂ፡፡ ይህች ሴት አስቀድማ በመካከላችን በአመንዝራነቷ ትታወቅ ነበር፡፡
በክብር ቦታ ሁሉ የመጀመርያን ስፍራ የምትይዝ ሴት ነበረች፤ ስሟ በሀገሩ ሁሉ የገነነ ነበር፤ በእኛ ከተማ ብቻ ሳይሆን በሲልስያ እና በቀጰዶቅያም ጭምር እንጂ፡፡ ይህች ሴት ብዙ ከተሞችን አፍርሳለች፤ የብዙ ወላጅ አልባ ሕፃናትን ንብረት በልታለች፡፡ ብዙዎችም “መተተኛ ናት” ይሏታል፤ ውበቷን ብቻ ሳይሆን መድኃኒትም ጭምር ትጠቀም ነበርና፡፡ ከዚሁ የተነሣ በአንዱ ቀን የንግሥቲቱን ልጅ እስከ ማማለል ደርሳለች፡፡ ጭካኔዋ የክፉ ክፉ ነበር፡፡
ከዕለታት በአንዲቱ ቀን ግን ማመን እስኪያቅተኝ ድረስ ሆኖም ግን በዓይኔ ፍጹም ተለውጣ ራሷን በእግዚአብሔር የጸጋው ዙፋን ፊት ድፍት አድርጋ ስታለቅስ አየኋት፡፡ አሁን የቀድሞ ክፉ ሥራዎቿን ሁሉ እርግፍ አድርጋ ትታለች፤ በእርሷ ላይ ከነበሩት
የአጋንንት ጭፍራ ተፋትታ አሁን የክርስቶስ ሙሽሪት ሆናለች፡፡
በእውነት ከእርሷ የሚከፋ ሰው በዐይኔ አላየሁም፡፡ በኋላ ግን ራሷን ከእንደዚህ ዓይነቱ ክፉ ሥራ ከለከለች፡፡ ከዚህ በፊት ስትለብሳቸው የነበሩት የምንዝር ጌጦች ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡ አሁን ግን እነዚህ ሁሉ በእርሷ ዘንድ ቦታ የላቸውም፡፡ እነዚህን ሁሉ አወላልቃ ጥላ ለእግዚአብሔር በሚገባ የማቅ ልብስ ለብሳ ራሷን የክርስቶስ ደቀ መዝሙር አድርጋለች፡፡ ይህችን ሴት ወደ ቀድሞ ሕይወቷ ለመመለስ የሀገሪቱ መኳንንት ከዙፋናቸው ወርደው ለምነዋት ነበር፤ ወታደሮች ትጥቃቸውን ታጥቀው በመምጣት አስፈራርተው ሊወስዷት ሞክረው ነበር፡፡ ሆኖም ግን ወደ ቀድሞ ሕይወቷ ሊመልሷት አልተቻላቸውም፤ ከተቀበሏት ደናግላን በዓት ሊያስወጧት አልተቻላቸውም፡፡ ይህች ሴት ከዚያ አስነዋሪ ሕይወቷ ተመልሳ ለቅዱስ ቁርባን በቅታለች፤ ለእግዚአብሔር ጸጋ የተገባ ሆና ተገኝታለች፤ ኃጢአቷን ሁሉ በጸጋው አጥባለች፤ ከተጠመቀች በኋላ ራሷን መግዛት ችላለች፡፡ ይህች ሴት የቀድሞ ሕይወቷን፣ ገላዋን ለብዙ ወዳጆቿ ያሳየችበትን ሕይወት “የእስር ቤት ሕይወት” ብላ ትጠራዋለች፡፡ በእውነት “ኋለኞች ፊተኞች ይሆናሉ፤ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ” የሚለው የከበረው የጌታ ቃል በእርሷ ሲፈጸም አየነው፤ መለወጥ ከፈለግን እኛን ማሰናከል የሚቻለው ኃይል እንደሌለ አወቅን ተረዳን፡፡
እንግዲያስ ተወዳጆች ሆይ! ተስፋ በመቁረጥ በኃጢአት ዐዘቅት ሰምጠን የምንቀር አንሁን፡፡ ከእኛ መካከል በጽድቅ በረሀነት የሚኖር ማንም አይገኝ፡፡ ፊተኛ ነኝ የሚልም ከቶ አይኑር፤ ብዙ አመንዝሮች እርሱን አልፈዉት ሊሄዱ ይችላሉና፡፡ ማንምም ኋለኛ ነኝ ብሎ ተስፋ አይቁረጥ፤ ከልቡ ከተጸጸተና ከተመለሰ ፊተኛ መሆን ይቻለዋልና፡፡
የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላል፡- “ይህም ሁሉ ካደረገች በኋላ ወደ እኔ ትመለሳለች ብዬ ነበር፡፡ ነገር ግን አልተመለሰችም፡፡ አታላይ እኅትዋም ይሁዳ አየች” /ኤር.3፡7/፡፡
ወደ እግዚአብሔር ስንመለስ የቀድሞ ኃጢአታችንን
አያስበውም፤ እግዚአብሔር እግዚአብሔር እንጂ ሰው አይደለምና፡፡ በእውነት እርሱ በቀድሞ ኃጢአታችን የሚወቅሰን አይደለም፡፡ እርሱ እንደ ሰው አይደለምና፡- “እስከ አሁኑ ሰዓት ወዴት ነበርክ?” የሚለን አይደለም፡፡ ብቻ እኛ እንመለስ እንጂ እርሱ እንዲህ ያለ አምላክ አይደለም፡፡
ይህን እንደናደርግ ሰውን በመውደድ ሰው የሆነው ክርስቶስ ይርዳን አሜን!!
"ሰይጣንም የአንቺን ምስጋና ወሬ ሲሰማ በብስጭት ጥርሱን ያፏጫል፤ የምስጋናሽ ወሬ በእርሱ ዘንድ መራጃ ነውና እራሱን ይቆርጠዋል፡፡ ከስምሽ አጠራር የተነሣ መብረቅ በኃይል ሲጮህ እንደ ሰማ ሁሉ ይደነግጣል፡፡ አንቺ ከተወለድሽ ጀምሮ ፈጽሞ ዕረፍት አላገኘም፡፡ በአንቺ ታመመ በልጅሽም ተጨነቀ በአንድ ልጅሽ መስቀል ሥቃይ አገኘው፡፡ ከፍጡራን ወገኖች ሁሉ ይልቅ ሰይጣን አንቺን ይጠላል፡፡"

#አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋስጫ
''እግዚአብሔር የሚጠይቅህ ጥቂት ነው የሚሠጥህ ግን ብዙ ነው!''

(ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)
ከእለታት አንድ ቀን አንድ አባት ወደ አባታችን አባ መቃርዮስ በኣት ሄደና "አባቴ ሆይ ድኅነትን አገኝ ዘንድ ምን ላድርግ?" ሲል ጥያቄ አቀረበላቸው። አባታችንም እንዲህ በማለት አሉት።
"ወደ መቃብር ሂድና ሙታንን ሰድበሃቸው ና" አሉት። ይህ አባትም የተባለውን አድርጎ ተመለሰ። አባታችንም "ምን አሉህ?" ሲሉ ጠየቁት። ሰውየዉም "ምንም አልመለሱልኝም" ሲል መለሰ። አባ መቃርዮስም "አሁን ደግሞ ሂድና ሙታንን አመስግናቸው" አሉት። ሄዶም አመሰገናቸው። "አሁንስ ምን አሉህ" ሲል በድጋሚ ጠየቁት። ሰውዬም "ምንም አልመለሱልኝም" ሲል መለሰ። አባታችን አባ መቃርዮስም: "ስትሰድባቸው ፤ስታመሰግናቸው እና  ስታወድሳቸው ምንም አልመለሱም፤ አንተም ለነፍስህ ድህነትን ከፈለግህ እንደሞተ ሰው ሆነህ ኑር። ሰዎች ክፉ ቢያደርጉብህም፣ ቢያመሰግኑህም ምንም አይሰማህ" አሉት።
​​በስመአብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ከጌታችን ትንሣኤ በኋላ ያሉት ዕለታት ስያሜ

አሁደ፦

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ በተነሳ በስምንተኛው ቀን በዕለተ እሁድ ደቀ መዛርሙርቱ አይሁድን ፈርተው በተሰበሰቡበት ዝግ ቤቶ "ሰላም ለእናንተ ይሁን"ሌሎች ዳግም ስለ ተገለጠ  ዳግማይ ትንሳኤተብሏል ።

ሁለተኛ_ለምን_ተገለጠ?ተብሏል
💧◦ለሐዋርያው ቶማስ ትንሳኤውን ለማሳመን ።
የጌታችን ትንሳኤ ቶማስ ስለ ተጠራጠረ ጌታችን ቶማስ በተገኘበት ዝግ ቤት ተገልጦ ለቶማስ ና ወደኔ የተቸነከረውን እጄና ጉኔን ዳስስ ብሎታል ።
ቶማስም የተቸነከረው እጁን አይቶ የተወጋውን ጉኑ በእጁ ዳስሶ የጌታችን ትንሳኤ አምኗል ።ሃገረ ስብከቱም በሕንድ ስለ ነበረ ተጋድሎውም የፈጸመው እንዲሁም ሰማዕትነት የተቀበለው በሕንድ ነው ።
ያቺ የጌታችንን ጎን የነካች (የዳሰሰች)እጅ ሳትበሰብስ ከታቦት ጋር በመንበሩ ላይ ተቀምጣለች ።እስካሁን ድረስ የሕንድ ሊቀ ጳጳስ ሲሾም በዛች እጅ ተመርጦና ተባርኮ እንደሚሾም አንዳንድ ሊቃውንት ይናገራሉ ።

💧◦ሰንበትን ሊያጸናልን ።
የአይሁድ ሰንበት፣እግዚአብሔር ሃያ ሁለትኘ ፍጥረታትን ፈጥሮ ያረፈባትና እረፉባት ብሎ ያዘዘን ሰንበት ቀዳም(ቅዳሜ)ናት ።

በሐዲስ ኪዳንም ጌታችን የተጸነሰባት ፣ከሙታን መካከል የተነሳባት፣አንዲሁም ደግሞ ለማጽናት ሁለተኛ የተገለጠባት(ዳግማይ ትንሳኤ)፣መንፈስ ቅዱስ የወረደባትና ሐዋርያት ከመጀመርያዋቹ ክርስቲያኖች ጋር በኅብረት ሆነው መንፈሳዊ ስራዋች የሚሰሩባት ቀን ዕለተ እሁድ ነበረች ።ቤተ ክርስቲያናችን ለቅዳሜ ቀዳሚት ሰንበት ለእሁድ ደግሞ ሰንበተ ክርስቲያን እያለች ለሁለቱም ቀናት እኩል ታከብራቸዋለች
።ጌታችንም ይቺ ቀን እረፍትነቷን ለማጽናት ሁለተኛ የተገለጠባት ቀን ናት ።እረፍት ስንልም ስራችንን ትተን ቁጭ ብለን (ተኝተን)የምናሳልፈው ማለት አይደለም ።እንደውም ከማንም ቀን በላይ አብዝተን መንፈሳዊ ስራዎች የምንሰራባቸው ቀናት ናቸው እንጂ ።
💧◦ምትሐት አለመሆኑ ለማስረዳት።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምትሐት እንዳልሆነና ቀድሞ የተዋሃደው ሥጋና መለኮት ፣ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑ ለማስረዳት ለሁለተኛ ጊዜ ተገልጦላቸዋል ።

በዝግ ቤት መግባቱ ደግሞ መለኮት እንዳልተለየውና ሥጋ ብቻው እንዳልሆነ ለማስረዳት ነው ።
"ብጹዓን እለ እንዘ ኢይሬእዩ የአምኑ"
(ዮሐ20:29)
አንድም
ዳግም ማለት ሁለተኛ ማለት ነው፡፡ ጌታ ሁለት ጊዜ አልተነሳም ፡፡ ዳግም የተባለው የትንሳኤው ስርዓት አና ቃለ እግዚአብሔር በዚህ ቀን ስለሚደገም ነው፡፡አንድም መነሳቱን ለአሥራ አንዱ ደቀመዛሙርት እንበለ ቶማስ ቢገልጥላቸው አምነው ለቶማስ ቢነግሩት የተቸነከሩ እግሮቹንና እጆቹን ካላየሁ ጣቴን በተወጋ ጎኑ ካላገባሁ
አላምንም ብሎ ነበርና በሳምንቱ ያምን ዘንድ ቶማስ ባለበት
ለሁለተኛ ጊዜ ተገለጠላቸው፡፡ ዮሐ ፳፥፳፮-ፍም

ቤተክርስቲያን ይህንን መገለጥ ዳግም ትንሳኤ ትለዋለች፡፡

፪፦ ፈጸምነ ይባላል
ይህ ስያሜ ደግሞ የፋሲካን በዓል አከበርን ስርዓቱን ዛሬ ፈጸምን ለማለት ነው፡፡
፫፦ አግብኦት ግብር ይባላል።
በዮሐ ፲፯፥፩ ጀምሮ በተገለጠው፡መፅሀፍ ቅዱሳዊ ቃል መሠረት ጌታ " አባ ወአቡየ ግብረ ዘወሀብከኒ ፈጸምኩ" ያለውን መዘምራን በቅዳሴ ማጠቃለያ አካባቢ ስለሚዘምሩበት ነው፡፡

ቶማስ ለምን ተጠራጠረ ?
መጠራጠሩ ስለ ሁለት ነገር ነው፡፡
፩፦ሰዱቃዊ ስለነበረ፡፡ ሰዱቃውያን ደግሞ ትንሳኤ ሙታን የለም ብለው የሚጠራጠሩ ናቸውና ሳላይ አላምንም ብሎ
፪፦ ሌሎች ሐዋርያት ትንሳኤውን ሲሰብኩ ተነስቶ አይተነዋል ሲሉ እርሱ ደግሞ መነሳቱን ሰምቻለሁ ብሎ ማስተማር ስለሌለበት ለማየት ሳላይ አላምንም አለ።

ጌታ የተገለጠላቸው ደጆች ተዘግተው ሳሉ ነበር ፡፡ ዮሐ ፳፥፳፮ ገብቶ ሰላም አላችሁ አስታረቅኀችሁ አላቸው።

በተዘጋው ቤት እንዴት ገባ ?ተብሏል
💧ኤልሻዳይ ስለሆነ ፡፡ ዘፍ 17፥1 ሳራ ማሕጸኗ ተዘግቶ መውለድ ባልቻለች ጊዜ ልጅ የሰጣት ኤልሻዳይ ነው፡፡ ።

ሀና ፣ ኤልሳቤጥ ሌሎችም እንዲሁ፡፡ ሉቃ 1፥ 37 እስመ አልቦ ነገር ዘይሰአኖ ለእግዚአብሔር ፡፡ እንዲል ረቂቅ መለኮት ሥጋን እንደተዋሃደ ለማጠየቅ ፦ በተዘጋ ቤት ገባ፡፡

ዛሬም ደጆች ቢዘጉም ጌታ ይመጣል፡፡ብዙ ሰዎች በሕመም ተይዘው የመዳን ደጃቸው ተዘግቶ ሳለ ጌታ የመጣው ዮሐ
5፥3-12 ነፍሳት በዲያብሎስ ቁራኝነት ተይዘው ገነት ተዘግታ ሳለ ኢየሱስ መጥቶ የለ ? ሉቃ 2፥9

💧እስራኤላውያን የግብጽ ባርነት ቢያይልባቸው የነጻነት ደጃቸው ቢዘጋባቸውም ጌታ መጥቶ አድኗቸው የለ ? ዘጸ 3፥1-8

ሲወጡስ ከፊት ቀይ ባህር ከኀላ ፈርኦን ከቀኝና ግራ ገደልና ዳገት ቢገጥማቸውም አምላክ ደርሶላቸው የለ ? ዘጸ14፥1

💧ለሶስና (መ ሶስ 1፥1-23) ከውግረት አድኗት የለ?

💧ለአይሁድ / ዕብራውያን/ መ አስ 1-10 ሐማ ያሳወጀውን የሞት ፍርድ ቀይሮላቸው የለ?

💧ለሶስቱ ሕጻናት ት ዳን 3፥17 ከእሳት አውጥቷቸው የለ ?

💧ለሞተው አላዛር ዮሐ 11፥1-48 ከሞት አንስቶት የለ ?

ስለዚህ ሁሉን ቻዩ ጌታ ምን ደጅ ቢዘጋ መክፈት ይችላልና እንመነው ፡፡ እርሱን አምኖ ተስፋ ሚያደርግ አያፍርም መዝ 24፥3 ተብሎ ተጽፏልና ፡፡

ስለ ማይነገር ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን
«ወደ እግዚአብሔር የምንጸልየው፥ መረጃ ወይም መመሪያ ልንሰጠው ሳይሆን፥ ወደ እርሱ እንድንቀርብና ከእርሱ ጋር ኅብረት ያለን እንድንሆን ነው።»
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
❖ ቻይ እና ትዕግስተኛ የሆነ ሰው ይጸልያል ስለሚሰጠውም የእግዚአብሔር መልስ አይጨነቅም፤ እግዚአብሔር ጸሎቱን እንደሚሰማው እርግጠኛ ነው፤ ሁሉም ነገር በእግዚአብሔር ጥበብና ፈቃድ እንደሚሆን በተገቢው ጊዜና መንገድ መልስ እንደሚሰጠው በማመን ለእግዚአብሔር ፍቅር ይተዋል፤ አንዳንድ ሰዎች ይህ መሰል ትዕግሥት የላቸውም፤ እግዚአብሔርን መውቀስ እና ከእርሱ ስሕተት መፈለግ እንጂ መጠባበቅ አይችሉም፤ እርሱን ይወነጅሉታል እርሱ ግን እጅግ ይታገሳቸዋል ወቀሳቸውንም ይሸከማል፤ እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔር ለእነርሱ እንደሚሰራ ማመን አለባቸው።

አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ
እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች ናቸው፥ ሰባትንም ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፈዋለች፦
   ፩ኛ. ትዕቢተኛ ዓይን፥
   ፪ኛ. ሐሰተኛ ምላስ፥
   ፫ኛ. ንጹሕን ደም የምታፈስስ እጅ፥
   ፬ኛ. ክፉ አሳብን የሚያበቅል ልብ፥
   ፭ኛ. ወደ ክፉ የምትሮጥ እግር፥
   ፮ኛ. በሐሰት የሚናገር ሐሰተኛ ምስክር
   ፯ኛ. በወንድማማች መካከልም ጠብን የሚዘራ።

ምሳሌ 6÷16-19
#ከሐልዮ_ኃጢአት_መጠበቅ

ሰይጣን ነቅዓ ሐልዮን መጠበቅ ላልቻለ ወጣት በቀጣይ እርሱን የሚወጋበት ኹለተኛው ጦር ሐልዮ ኃጢአት ነው። “የሐልዮ ኃጢኣት ምን ትጎዳለች?” እያለ እንዲያስብ ያደርገዋል። በሐልዮ ኃጢአት ያዝለዋል። ይኸውም ደቂቀ ሴት ደቂቀ ቃኤልን ከመስማት አልፈው እንዲመለከቷቸው በማድረግ በዝሙት ፍላጻ እንደነደፋቸው ነው። ስለዚህ የተለያዩ ነገሮችን እንዲመለከት ያደርገዋል። ለምሳሌ ራስን በራስ ስለ ማጎሳቆል፣ ወይም ስለ ምስለ ሩካቤ፣ ወይም ስለሚያውቃት ሴት በዝሙት ሕሊና እንዲያስብ ያደርገዋል። ጓደኞቹ የተናገሩትን ነገር ወይም በመጽሔት ያነበበውን ወይም በተለያየ መንገድ ሲወራ የሰማውን “ይህ ምን ያረክሳል?” እያለ በሕሊናው እንዲያመላልሰው ያደርገዋል።

እንደዚህ በሚኾንበት ጊዜ በየትኛውም ቀን ቢሰግድ ፆሩ ይመለስለታል። አንድ ወንድሜ እንደ ነገረኝ፡ እንደዚህ ያለ ፆር ሲመጣበት በሩካቤ አካሉ አከባቢ ካለው ፀጕር የተወሰነውን ይነጫል። በጣም ያማል። በዚያ ሰዓትም ከፆሩ ይልቅ ሕመሙ ስለሚበልጥ ፆሩን ከማሰብ ይመለሳል። ሕሊናው አድርገኝ አድርገኝ ብሎ እንዳይገፋፋው፣ ነጉዶ የመጣውን ፆሩን በተግባር ለመፈጸም ሰይጣንን እንዳይታዘዘው ያደርገዋል። እንደ ነደ እሳት የሚያቃጥለውን የፍትወትን ፆር እንዳያስነሣበት ይከልለዋል።

የሐልዮ ኃጢኣት በተነሣ ጊዜ "ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ” እንደ ተባለው፥ ለዚህ ከሚዳርጉን ነገሮች (ቦታ፣ ኹኔታ) መራቅ የመጀመሪያው እርምጃ ነው። “ይህ አሳብ የእኔ አይደለም” ብሎ ለመሸሽም የሐልዮ ኃጢአት የምታመጣውን መከራ የሚነግረን መምህር ወይም አበ ነፍስ ማግኘት እጅግ አስፈላጊ ነው (2ኛ ጢሞ.2፥22)። መካሪ መምህር ሳናገኝ ቀርተን ካዋልናትና ካሳደርናት ለሰይጣነ ፍትወት እጅ እንደ መስጠትና ወድቀን ወደ ቀጣዩ ደረጃ ወደ ገቢር ልናልፍ እንችላለንና። ከክፉ አሳብ መራቁ ብቻውን በቂ አይደለም። ክቡር ዳዊት “ከክፉ ሽሽ” ካለ በኋላ በዚያ ሳያቆም ጨምሮ “መልካምንም አድርግ" ይላልና (መዝ.33፥14)። እርስ በእርሳቸው የተያያዙ ናቸው። ስለዚህ አንዲት ሴት ጥሩ ልብሷን ተሸላልማ ተጊያጊጣ እየተኩነሰነሰች ስትሔድ አይቶ ፈላስፋው ዲዮጋንስ ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሰዎች "ከዚች ክፉ ወጥመድ ሽሹ" እንዳላቸው ሸሽቶ ወደ በጎ ሥራ ፊትን ማዞር ይገባል። ከወደቁ በኋላ ከመጠበብ ሳይወድቁ መጠንቀቅ ይሻላልና።

በሌላ መልኩ ደግሞ ተፈጥሮ ስለኾነ እነዚያ ስሜቶች ለምን መጡ ማለት አይቻልም። ስሜቶቹን ግን መቀደስ ስለሚቻል ከክፉ ሸሽቶ መልካም በማድረግ መቀደስ ይቻላል። አንድ ፈረስን የሚጋልብ ሰው፥ ፈረሱ ወደ ገደል ቢያመራ ጋላቢው የሚያደርገው ልጓሙን ማጥበቅ ብቻ አይደለም፤ ፈረሱ በትክክለኛው መንገድ እንዲሔድም ይመራዋል እንጂ። ስለዚህ እንደዚህ ዓይነት ስሜቶች ሲመጡብን ከመራቅ ባሻገር ወዲያው መንፈሳዊ ተግባር ማከናወንም አስፈላጊ ነው። ጸሎት ሊኾን ይችላል፤ ስግደት ሊኾን ይችላል፤ መጽሐፍ ማንበብ ሊኾን ይችላል፣ መንፈሳዊ አባት ጋር መደወል ሊኾን ይችላል።

ከበረኻ አባቶች ከተሰጡት ምክሮች አንዱ እንዲህ የሚል ነው፦“ሌላ እኁም ከሰይጣነ ዝሙት ጋር ይጋደል ነበር። በሌሊት ተነሥቶም ከአረጋውያኑ ወደ አንዱ መጥቶ ስለ ሕሊናው ነገረው። አረጋዊውም ይታገሥ ዘንድ መከረው። በዚህ መንገድ እገዛ አግኝቶም ወደ በዓቱ ተመለሰ። ለኹለተኛ ጊዜም ወደ አረጋዊው መጥቶም እርዳታ አግኝቶ ወደ በዓቱ ተመለሰ። ውጊያው ለሦስተኛ ጊዜ ሲመጣበትም እንደገና  በሌሊት ወደዚያ አረጋዊ ሔደ። አረጋዊውም ወጣቱን አላሳዘነውም፤ እንደሚጠቅመው መክሮ ዘክሮ ነገረው እንጂ፤ እንዲህ ሲል፡- ምንም ዕድል እንዳትሰጠው። ሰይጣነ ዝሙት በፈተነህ በማናቸውም ሰዓት ወደ እኔ ና። ከዚያም ታጋልጠዋለህ። ስታጋልጠው ሸሽቶ ይሔዳል። ሰይጣነ ዝሙት እነዚህን አሳቦች የሚደብቃቸውንና የማይገልጣቸውን ሰው ያህል የሚፈትነው የለምና።" ያ እኁም በዚያች ሌሊት እርዳታ ፈልጎ ዓሥራ አንድ ጊዜ ወደ አረጋዊው እየተመላለሰ አሳቦቹን ተቃወማቸው። አረጋዊውም ሰይጣነ ዝሙቱ ከእርሱ እንደ ራቀ ነገረው። ነገር ግን ወደ በዓቱ በተመለሰ ጊዜ ውጊያው እንደ ገና መጣበት። ከብዙ ጊዜ ምልልስ በኋላም ያ እኁ አረጋዊውን:- አባ! ቸርነትህ ይደረግልኝ፡ እንዴት አድርጌ መኖር እንዳለብኝ ምከረኝ አለው። አረጋዊውም፡- ልጄ ፥ በርታ! እግዚአብሔር ፈቃዱ ከኾነ የእኔ ሕሊና ወደ አንተ ይመጣል። ከዚያም በኋላ ንጹሕ ሕሊና ይዘህ ትሔዳለህ እንጂ ከእንግዲህ ወዲህ በዚህ አትፈተንም' አለው። ይህን ብሎ ሲጨርስም እግዚአብሔር ሰይጣነ ዝሙቱን እስከ ወዲያኛው ከዚያ እኁ አራቀለት።”

ስለዚህ ሰይጣነ ዝሙት መጥቶ ሲያሳስበን ወይም በሌላ መንገድ ያየነውንና የሰማነውን በሕሊናችን እንድናመላልሰው በሚፈልግበት ጊዜ ምንም ሳንሰለችና ዕድል ሳንሰጥ ወደ አበ ነፍሳችን መሮጥ እንዳለብን ያስረዳል። አበ ነፍሶችም በትዕግሥት ልጆቻቸውን የመርዳት መንፈሳዊ ግዴታ አለባቸው። ወላጆቻችንም ሊያግዙን ይችላሉ።

የሐልዮ ኃጢአት በእኛ ላይ እንዲነግሥ ከሚያደርጉ ነገሮች ኣንዱ ለብቻና ሥራ ፈት መኾን ነው። ሥራ ፈትተን ለብቻችን ስንኾን ሰይጣን መጥቶ ያንን ኃጢአት በደንብ እንድናስብበት፣ ተግብረው ተግበረው ይለናል። ልክ ለሔዋን በለስን የምታስጎመጅ አድርጎ እንዳሳያት፥ በእኛም የማስተዋል ሕሊናችንን አጣምሞ ከዚያ ኃጢአት ስለምናገኘው ደስታ ያሳስበናል። “ሥራ ያጣ መነኩሴ ቆቡን ቀድዶ ይሰፋል” የተባለው መነኰሴ ሥራ ላለመፍታትና ከሓልዮ ኃጢኣት ለመራቅ ሲል ይህን ስለሚያደርግ ነው። ስለዚህ ዝም ብለን መቀመጥ አይገባንም። ይልቅስ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በመሳተፍ፣ ሌሎች በጎ ሥራዎችንም በመሥራት እንጠመድ።

በዚህ ከተጎዱት ሰዎች መካከል አንዱ ነቢዩ ዳዊት ነው። ነቢዩ ዳዊት ወጣት ኾኖ በጎችን በሚጠብቅበት፣ ለሳኦል ጋሻ ጃግሬው ኾኖ በገና እየደረደረ በሚያገለግልበት፣ ሳኦል በምቀኝነት ተነሥቶበት በሚያሳድደው፣ ወደ ንግሥናው መጥቶ መንግሥቱ እስከ ተደላደለ ጊዜ ድረስ በዝሙት አልወደቀም ነበር። መንግሥቱ ተደላድሎ ከተመሠረተ፣ ክብሩ ከጨመረ በኋላ ግን ሥራ ፈትቶ በሰገነት ላይ ሲመላለስ የኦሪዮን ሚስት ቤርሳቤህን ስትታጠብ ተመለከታት። ቅዱስ ኤፍሬም ሶሪያዊ፡- “ሰውነት ሥራ ሲፈታ፥ ሕሊናም ሥራ ይፈታል” እንዳለው፥ ንጉሥ ዳዊት ሥራ ፈትቶ ስለ ነበረም በቀላሉ በነቅዓ ሐልዮ ሳያበቃ ስለ እርሷ በማሰብ ወደ ሐልዮ ኃጢኣት ገባ። ስለዚህም “መልእክተኞች ልኮ አስመጣት፣ ወደ እርሱም ገባች፥ ከርኩሰትዋም ነጽታ ነበርና ከእርስዋ ጋር ተኛ" (2ኛ ሳሙ.11፥4)።

በመኾኑም ራሳችንን ሰይጣን ወደ ሕሊናችን የሚያስገባውን የሐልዮ ኃጢአትን ከላይ በጠቀስናቸው መንገዶች በማራቅ፥ ንጽሕናችንን ጠብቀን ከሴት ከወንድ ርቀን እስከ ጋብቻ ድረስ መጽናት ይኖርብናል።

አንዳንድ ጊዜ በሕልማችን ሩካቤ ስንፈጽም ልናይ እንችላለን። በዚህ ጊዜ እኛ ራሳችን ቀን ላይ ያሰብነው አሳብ አለመኾኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። በቀን ያሰብነው ሌሊት ቀጥሎ ከኾነ ከአበ ነፍስ ጋር ተነጋግሮ አሳቡን ማራቅ፣ ከዚያ ውጭ ግን ወጣቶች በመኾናችንና “ፒቱታሪ” የተባለው ዕጢ የዘር ፈሳሽ ማመንጨቱና አንዳንድ ጊዜ በራሱ ተስፈንጥሮ ስለሚወጣ በዚህ መነሻነት ወደ ሌላ ኣሳብ እንዳንሔድ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።

(ገብረ እግዚአብሔር ኪደ  ከተጻፈው #ትንሿ_ቤተክርስቲያን መጽሐፍ - ገጽ 161-163)
"ቅዱስ፣ ጥንቁቅ፣ ግልጽና ብልህ ሁን፡፡ እርጋታን የተላበሰ ሰብእና ይኑርህ፡፡ ደስተኛ ሁን፤ ሰላምታህ በፈገግታ የታጀበ ንጹህ ይሁን፡፡ ንግግርህ የታረመ አጭርና በጨው እንደተቀመመ ጣፋጭ ይሁን፡፡ ቃላቶችህ የተመጠኑ እና ጤናሞች ሁሉም የሚረዳቸው ይሁኑ፡፡

የጓደኛህን ምስጢር አትግለጥ፤ ለሚወዱህ ሁሉ የታመንክ ሁን፡፡ ወደ ጭቅጭቅ እና ንትርክ ከመግባት ራህን ጠብቅ፡፡ የሚሰሙህ ሁሉ እንዳይጠሉህ ወደ ጠብ አትግባ፡፡ ከሰይጣን በቀር ምንም ጠላት አይኑርህ፡፡

የሰዎችን ስህተት አትመራመር፤ የባልንጀራህ ኃጢአት አትግለጥ፡፡ የባልጀራህ ውድቀት ደጋግመህ አታውራ፡፡ በራስህ ኃጢአት ላይ ፍረድ እንጂ በሌሎች ላይ አትፍረድ ገዢያቸው አይደለህምና፡፡

ኃጢአትን በፈጸመ ሰው ላይ ወቀሳ አታብዛ አንተም ትበድላለህና፡፡ ነገር ግን ከኃጢአቱ ይመለስ ዘንድ ረዳትና መካሪ ሁነው፡፡ ከወደቀበትም የስህተት ሥራ እንዲወጣ አበርታው፡፡ ተስፋውን በእግዚአብሔር ላይ ቢያደርግ ኃጢአቱን ልክ በእሳት ፊት እንደወደቀ ገለባ ፈጥኖ እንደሚወገድለት ንገረው፡፡

ተፈጥሮ እንደ መጽሐፍ ፍጥረታት እንደ ጽላት ይሁኑህ። ከእነሱ ሕግጋትን ተማር፤ በተመስጦ ሆነህ በመጽሐፍ ያልሰፈሩትን ምስጢራት ተረዳ፡፡

እግዚአብሔርን ከሚፈራ በቀር ባለጸጋ የሆነ ሰው ማነው? የእውነት እውቀት ከጎደለው ሰው በላይ ፍጹም ደሃ የሆነ ማን ነው? ሁል ጊዜም እውነተኛ ፍቅራችን ጸንቶ ይቀጥል ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ፡፡ እርሱን ለምነው፡፡ ስለ ቸርነቱ ምስጋና አቅርብ፤ ምክሬን ፈጽሞ ቸል አትበል፡፡"

(ምክር ወተግሳጽ ዘቅዱስ ኤፍሬም )
አንድ አረጋዊ እንዲህ አሉ ፦”ልጆቼ ሆይ፦ ራሳችሁን መለወጥ ሳትችሉ የሌላን ሰው ነፍስ ማዳን ወይንም ሰወችን መርዳት አትችሉም፤ ነፍሳችሁ በልዩ ልዩ ምስቅልቅል ውስጥ ሆናም የሌላውን ሰው መንፈሳዊነት ስርአት ማስያዝ አይቻላችሁም፤ እናንተ ራሳችሁ የውስጥ ሰላም ከሌላችሁ ለሌሎች ሰላምን ማስገኘት አትችሉም ፤ ብዙውን ጊዜ የሰወችን በኛ ምክንያት ለበጎ ነገር መነሳሳትና ነፍሳቸውም ወደ እግዚአብሄር መቅረብ የምናየው ወደ በጎ ይቀርቡ ዘንድ በአፍ በምንነግራቸው ነገር ሳይሆን በእኛ ላይ በተግባር በሚገለጥ የመንፈስ ፀጋና ስጦታ ነው፡፡ ሌሎች ሰወችም ህይወታቸው ለበጎ ነገር እንዲነሳሳና እንዲለወጥ በእኛ ህይወት ሲማሩ እኛ እንኳን ላናየውና ላንረዳው እንችላለን፡፡"
2024/05/31 03:18:17
Back to Top
HTML Embed Code: