Telegram Web Link
የሱስ ነገር !!! የጉድ ሃገር
------------------

እንጂባራ ቆመን ይታየን ነበረ ሐይቁ ዘንገና
ዘንድሮ ግን ጠማን
መንገድ ቆፋሪዎች ፥ ….. ነጣጠሉንና
ካንባሰል ተራራ ፤ ከመስቀሉ ጫፍ ላይ
ኮረብቶች አየሉ ...
ከውቅሮ ነጃሺ ፥ ....ቂርቆስን እንዳንይ
፡፡፡፡፡
ሁሉ ወዶ ጠላ
ከጥንሡ ገንቦ ፥ አሽጎ አተላ
ንፋስ እየገባው ፥ በቅጡ ሳይፈላ
በሱስ አስተሳሰብ ፥ ሽታ ብቻ ሰክረን
እንደ ስጋ ለባሽ በዘር መታወቂያ በድኑንም ለየን
፡፡፡፡፡
ይህ ነው ዳር ድንበሩ
የሱሰኞች ተክል ፥ አፈር አልባ ሥሩ
ብረት እንደሚያቀልጥ…
እንደ ቆዳ ወናፍ ፥ እሳት እፍ እያሉ
ያርገበግቡናል
ባ'ንዲት እፍኝ ውሃ ማጥፋት እየቻሉ
፡፡፡፡፡
ተመልከት እንግዲ…
የሴራውን ስፋት ፥ የሱሰኛን ድንበር
የሞት ፍርድ አንግበህ ፥ ምትኖር በጉድ ሃገር
እንደ ቀበሌያችን… 
መታወቂያ ሳይሆን ፥ መቀበሪያ ደብተር
እንዲያመች ነጥሎ ፥ ለይቶ ለመስበር
መኪናም እንደሰው ፥ ይከፈላል በዘር
.
(ሚካኤል እንዳለ)
አንዱ "undo"
----------

አንዱ' የለም እንጂ አንዱ'ማ ቢኖር
ያለፈንን ሁሉ…
እያስተካከልን ፥ እንደግመው ነበር
ያለፈ ቢደገም አንዱ' እየተባል ፥ የሄደ ቢመጣ
አፍሮ ይሆን ነበር
ድጋሚ ተስሎ ይህ ሁሉ መላጣ
ቀና ባለ ነበር
ዘመን እንደ ኤሊ ያስረጀው ጎባጣ
፡፡፡፡፡
አንዱ' የለም እንጂ ፥ አንዱ'ማ ቢኖር
ጃርቶች የተከሉት የጎናችን እሾህ ይነቀል ነበር
እሾህ ተሸክሞ
እንደ ሀገር ታሞ
የኋላን እረስቶ ፥ ለሚጓዝ ከፊቱ
እየመላለሰ…
ያጠፋው ነበረ ፥ አንዱ' መዳኒቱ
፡፡፡፡፡
አንዱ' የለም እንጂ አንዱ'ማ ቢኖር
ስንቱን የቃል ግድፈት…
ከታሪክ ማህደር ፥ ..እንፈቀው ነበር
የሚያባላን ፊደል ፥ ፈቅፍቀን ከስር
፡፡፡፡
እነ ጠቅል ዋጤ
ለሆዳቸው ቅላት ሌላውን እርገጤ
ፈትለው ብዙ አሳር'እ
እንደ ሰርገኝ ጤፍ ፥ እንደ ጫካ ማር
አንዱ ቢኖር ኖሮ…
ታሪክን ቀይጠው ፥ አይጽፉም ነበር
፡፡፡፡፡
እረ አንዱ' ፈዋሹ ፥ አንዱ' ገራገሩ
ችግር ጠፍቶ ሰላም እንዲሆን ሃገሩ
እንደው ተለመነን ስማንማ እግዜሩ
ያለፉ ግድፈቶች ህዝብን ያሳከሩ
ኋላቸው ተፍቆ ፥ ባዲስ እንዲሰሩ
አንዱን ትከል በሰው ፥ እንደ ኮምፒተሩ
.
( ሚካኤል እንዳለ )
.
በቴሌግራም ከጥበብ እልፍኝ ይቋደሱ subscribe 👉 www.tg-me.com/mebacha
ቅጥረኝው ልቤ
-----------

ካንቺሆዬ ቅኝት ፥ ትካዜ አጠንፍፌ
ትዝታን ከባቲ ፥ ካንባሰል ቀፍፌ
ስለ ፍቅርሽ ሳስብ ፥ ከመጠን አልፌ
እራት'ኳ ቀርቦ...
ይጠፋኝ ጀመረ ፥ ምጎርስበት አፌ
.
የረጋ መሳዩን ፥ እንደ ንፁህ ኩሬ
ያን ለጋ ቅቤሽን ፥ ሳላየው አንጥሬ
ብክር ባጠጣሺኝ ፥ ቃላቶች ሰክሬ
ሆኜልሽ አረፍኩት...
በእጆቼ እምሄድ ፥ የምበላ በእግሬ
.
እንዳመጸ መንጋ ፥ አውራ እንደሌለው
አካሎቼ ሁሉ ፥ ስራ ተቀያይረው
በምላሴ አይቼ ፥ በአይኔ ምቀምሰው
ባፍንጫ ሰምቼ ፥ በጆሮ ማሸተው
ባንቺ ጥልፍ ሙያ...
በለማጅ እጆችሽ ፥ ጅምር ሽመና ነው
.
ህዋስ የተባለ
ያለጸጋው ገብቶ ፥ እንዳሻው ሲያበላሽ
ያለ ስራው ውሎ ፥ እንደ ህፃን ሲኳሽ
አደራ ያልበላ ፥ ያልዘለለ ድንበር
መክሊቱን አክባሪ ፥ ልቤ ብቻ ነበር
እን'ዳባት አደራ ፥ እንደ ሐገር ክብር
አምጥተሽ በላዩ ፥ የጣልሽውን ፍቅር
ከወዴት አስቀምጦ ፥ ስራውን ይቀይር ?
.
« ሚካኤል እንዳለ»

@menacha
@mebacha
@ethio_art
@ethio_art
አፈሩን ተይልኝ
----------

ቢያሰኝሽ አቀበት
ወደላይ ወደላይ ፥ ሽቅብ ዳገት ዳገት
እንዳ'ባይ ብቴጂ ፥ ባ'እድ ለማጠጣት
እኔም ምንጭ አላጣ…
ጥርኝም ውሃ አፍልቄ ፥ ጥሜን ምቆርጥበት
ይልቅ ለድካሜ
ለለፋው ቅልጥሜ
ለባከነው ህልሜ
እንድ ጺዮን አምባ
እንደ መፍቀሬ ሰብ ፥ የሶሎምን እንባ
እንደ አዜብ ጽንሰት ፥ ትውስታ ቢሆነኝ
ጠርገሽ አትውሰጂው ፥ አፈሩን ተይልኝ
ችግኙን መውደዴ...
ከስርሽን ተክዬው ፥ ከርሞ ቢይፀድቅልኝ
.
(ሚካኤል እንዳለ)
.
@ethio_art
@ethio_art
@mebacha
@mebacha
መለየት
-----

የለም ! የለም !
መለየት ሞት አይደለም
ሞትም መለየት አያክለው
መለየትም ሞትን አይመስለው
ትርጓሜያቸው ለየቅል ነው

አንቺም እኔም ጅረት ኾነን
ከራሳችን ምንጭ ፈልቀን
በራሳችን ፈለግ ፈስሰን
አገር ምድሩን አድርሰን
ሄደን ! ሄደን ! ሄደን ! ሄደን
ወርደን ! ወርደን ! ወርደን ! ወርደን !
ሞት በሚሉት ውቅያኖስ
አንድ ስንኾን ተዋሕደን
ተገናኘን 'ንጂ መች ጨርሰን ተለያየን

የለም ! የለም !
መራቅ መለየት አይደለም
ሰው በሰዎች ግዞት
ችግር መከራ ይዞት
አገር ቀዬውን ጥሎ
ስልቻውን በጫንቃው አዝሎ
ቅሉን ጨርቁን አንጠልጥሎ
ብቻውን ሄደ ብለው ሰፈርተኛው ተጃጅሎ
እርሱ በልቡ ሕንፃ በማይዘመው በማይፈርሰው
ከተጓዘ አኑሮ ሰው
አሁን ይኼ መለየት ነው ?

የለም የለም !
መለየት ይህ አይደለም
ትርጓሜያቸው እንቀይረው
ላ 'ንቺና ለ'ኔ ሌላ ነው
ከፊቴ ቁጭ ብለሽ
ከፊትሽ ቁጭ ብዬ
ክንድሽን ከአንገቴ ጥለሽ
ክንዴን ከአንገቴ ጥዬ
የምታወሪው ሳይገባኝ
የማወራሽ ሳይገባሽ
ለይስሙላ
ጥርስሺ ሲሥቅ ቻው ቻው ሲለኝ ቀልብሽ
ደህና ኹኚ ሲልሽ ዐይኔ
መለየት ይህ ነው ለ'ኔ፡፡

( በእውቀቱ ስዩም )
'' አባጂው ''
--------------
.
ቀድመው የቀረቡት
....ቀድመው እየራቁት
እንደተወለደ ፥ እንደ ቁራ ጫጩት
ገላው ተገላልጦ ፥ ከሙቀት ቢሸፍት
፡፡፡፡
በረዶ እየዛቁ
ከናጌብ ከጥልቁ
በቀዝቃዛ አንኳላ ፥ በቆርጣማ ኩስኩስት
ከጫንቃው ቢሰፍሩ ፥ አራቱ ነፋሳት
እያርገበገቡ ፥ ሆዱን ቢያላውሱት
፡፡፡፡
የተገፋ ልቡን
ቀልብ'ና ሐሳቡን
እንደ አራስ ህጻን ፥ እሹሩሩ ብሎ
መሻቱን ባ'ንቀልባ ፥ ህሊናው ላይ አዝሎ
እኪሱ ላይ ባልች ፥ ወጠጤ ቀልቀሎ
ሄዶ ከሸመታ ፥ ካስፓልቱ ዳር ውሎ
፡፡፡
በድቃቂ ንዋይ
ካለ ከመንገድ ላይ
አይነ ግቡ መርጦ ፥ ስሜት እንዳይገዛ
ኑሮ ሸመታዋን ፥ ......አለልክ አጡዛ
በድህነት ገመድ ፥ ብታስረው ሰቅዛ
ከሴት ተራ ርቆ…
ሸማ ተራ ሄደ ፥ ብርድ ልብስ ሊገዛ
፡፡፡
አዬ ጉድ ብቸኛው
ወዲ ደሞ አብያው
ሙቀት በ'ጀ ጠባብ ይመጣ ቢመስለው
ያለውን አንግቦ ፥ ጥንዱን ቢሸምተው
ብርዱን ለመሸወድ...
ድርብ የተልባ እግር ፥ ቢከምር ከጫንቃው
ውርጩ ተሸንፎ ፥ እኳንስ ሊሞቀው
ይንቀጠቀጥ ጀመር…
ከመሬት ላይ ውሃ ፥ እየላሰ ኩታው
.
እሱማ ምን ያርገው
በንግድ አለም ዘዬ ፥ በንዋይ ድለላ
በአሞሌ ሚዛን ፥ ...ክቡድ ልቡ ቀላ
አገኘሁኝ ብሎ ፥ ልኩን እንደሌላ
ቢሰነዝር እጁን ፥ የ'ድሉን ሊባላ
እንደ ድመት ጸጉር እንደ ጥጥ አለላ
እንደ ዱቄት ቅንጣት ፥ ከብናኝ አቅልላ
አለሜ ገፋችው…
በእፍታ ብቻ ፥ .........…እንደ'ፉዬ ገላ
.
አሁን ለመቆያ…
ከሸክም ቢላቀቅ ፥ ከጫንቃው ላይ ትቢያ
የ'ንቅጥቅጡ'ን ዘመን ፥ ቢሆነው መዝለቂያ
ለጊዜው…ለጊዜው
ምናልባት ቢበጀው
አንቺ ሸማ ፈታይ ፥ እባክሽ ቅበሪው
ውሃ አዘል ቁርጥማት..
አጥንቱ ሰንጥቆ ፥ ከሚያንገበግበው
ሙቀት ከውስጥ እንጂ
ከውጭ እንዳሎነ ፥ ደግሞም እንዲገባው
ከቡትት ሸከማም ፥ ..…ጥቂት እንዲቀለው
ያጠድቅሻልና…
ጥንዱን ጋቢ ገፈሽ ፥...…ነጠላን ''አባጂው''

.
« ሚካኤል እንዳለ »
.
በቴሌግራም ከጥበብ እልፍኝ ይቋደሱ
👉 www.tg-me.com/mebacha
ቆሞ ማነስ
--------
ንጹህ ከሚመስሉ ፥ ከንጹህ ለባሾች
ትልቅ ከሚመስሉ ፥ ከትልቅ ህጻኖች
ከሚያስቡት ቆመው ፥ ግእዛን ካላቸው
ዓለምን በመናቅ…
የጉንብስ የሚሄድ ፥.…ውሻ በለጣቸው
.
( ሚካኤል እንዳለ )

👉 @mebacha
👉 @ethio_art
በልደት ቀን መሞት
-------------

እረ ምታው ምታው
እንደ ሰርግ አታሞ ፥ አከታትለህ በለው
ወልዶ ሳያሳድግ ፥ አባት ያለው ማነው ?
ውስጡ ለረከሰ
ለውጥ ለለበሰ
ብላችሁ ንገሩት እኛስ አባት አለን ደሙን ያፈሰሰ
፡፡፡፡
.… . . . . . ..…እንደጉድ ታመናል
በኋላ ቀር ሰበብ…
የቆጥ እያሳዩ ፥ ጥበብ ያስጥሉናል
ጨዋታውን ወስደው...
ስር የለሹን በለስ ፥ ዛፉን ያስጌጡናል
፡፡፡፡
እስኪ እንጠይቀው
በበረት ተኝታ
ያስገኘች አምጣ
.................…እያለች በቦታው
የገና አባት ገናን መቼ ነው የወለደው ?
ሆኖብን ነው እንጂ ፥ እንቅብ በእንቅብ ላይ
አሜን ልማዳቻን ፥ ሲደፋብን ከላይ
፡፡፡፡
ወዲህም ሌላ ጉድ
አስገራሚ ትውልድ
በ ''እንትን'' ማሰር መፍታት ሆኖ የጾም ልማድ
እኛ መሞት ጀመርን ፥........….ጌታችን ሲወለድ
አዬ ጉ ኡ ኡ ኡ ኡ ኡ ድ.
.
(ሚካኤል እንዳለ)
.
እንኳን አደረሳቹ መልካም በዓል ለሁላችሁም እመኝለው፡፡
@mebacha
@mebacha
@mebacha
ያገባኛል
----------------
ባህል እንደ እሳት
አሽቶ በፈተነው ፥ በወርቅ እጇ በልቶ
ወንድ የሆን የለም ፥ በሴት እጅ አንስቶ
ታጥቀው አይጠብቁን
ወይ ......አላስታጠቁን
በባዶ ገላችን ፥ ከጅብ አጣበቁን
፡፡፡፡
የሱን ሴት ሰብስቦ ፥ አሞኘን ንጉሡ
ስላሎሎዳቸው ፣ ምነገባው እሱ
የእናትን ለቅሶ
ስቃይን ደርበሽ ፥ ታውቂያለሽ የልጅን
የሴት ሁሉ እራስ ፥ ማርያም ተለመኝን
፡፡፡፡
ያ ሽፍታ ላመሉ መውጫውን ቢረሳም
እንደ ክብሪት እንጨት ከሆዷ ተገኝቶ እራሷን ቢመታም
እሱ ቢነድ እንጂ እሷስ በሰማዩ ህይወትን አታጣም
.
( ሚካኤል እንዳለ )
.
ሰው በሌለበት ፥ የምትችል ማዳንን
እንደ ሶስቱ ህጻናት ፥ ከእሳት አውጣልን

@mebacha
@ethio_art
ያልተረዳ መርዶ
-----------
( ሚካኤል እንዳለ )
.
.
ደብቀው አክርመው ፥ ያልተረዳ መርዶ
ቤታችን አለቀ..
እንደ'ቧይ ካብ ግርጄ ፥….. ተንዶ ተንዶ
፡፡፡
ጥርስ ያለው አንበሳ
እንደ ድዳም ጠቦት ፥ በሬት ተወድውዶ
በከንፈር በምላስ ፥.. እጅጉን ተወዶ
ያ'ሳር ስጋ ሆነ…፥ ተውሾች ተላምዶ
፡፡፡
እረ አንቺ ሃገር
ጣራሽን ተማምኖ እንዴት ነው ሚታደር
በጭዱ ከለላ…
በምስጥ ተበልቶ ፥ እየሞተ ማገር
፡፡፡
እንደ ጎዶሎ ውሃ
እንደተወቀጠ ፥ ደርሶ እቦጭ እያሉ
ሃገሬ ሃገሬ ፥ …..…..ይሉሻል ላመሉ
እንደ ቄሱ ሐና…
ከላይ ጿሚ መስለው ፥ ከስር እየበሉ

@mebacha
@mebacha
@mebacha
መሬት ውረጂልኝ
------------
( ሚካኤል እንዳለ )
.
.
እሷ
ቀንህን 'ማበራ ፥ ፀሐይህ ነኝ አለች
ጠግቤ ሳላያት…
በአንድ ቀን ጉዞ ፥ ገብታ እየጨለመች
፡፡፡
ሲመሽም ጠብቃ
ከዋክብትን ታጥቃ
የማታህ መድመቂያ ፥ ጨረቃህ ነኝ አለች
ዘልቃ ሳታበራ…
ንጋት ላይ ደብዝዛ ፥ በቀኑ ተዋጠች
፡፡፡
.........እንዲህ በጄ ብላ
እሩቅ ባለ አካል ፣ እራሷን መስላ
በነግዕ መባቻ ፥ ፀሐዩ ሲወጣ
መዓልቱ አብቅቶ ፥ ውድቅቱ ሲመጣ
እየጠፉ ''አየሁህ''…
በሚለው ጨዋታ ፥ ብቅ ጥልቅ ያዘች
እንደ 'ፃይ ጨረቃ ፥ ጊዜ እየጠበቀች
፡፡፡
እኔ
. . .. . . . . ይልቅ ደስ እንዲለኝ
እንደ ሰማዩአ ላም ፥ አካል ከማይገኝ
ህዋ ላይ ተሰቅለሽ ፥ በርቀት ከምቶኝ
ምድር ውረጂና በመዳፌ ያለ መሬትን ሁኚልኝ
በሄድኩበት ሁሉ እጄን ስዘረጋ ገላሽን እንዳገኝ

@mebacha
@ethio_art
የደረሰ ትንቢት
---------
.
(ሚካኤል እንዳለ)
.
እንደ ሽሪሚሪ
እንዳለቀ ሱሪ
እምነት ከላይ ከላይ ፥ ስለተለበጠ
ፌጦና 'ነይ ሽንኩርት ፥ ከእግዜሩ በለጠ
አይ ጊዜ ቀላጁ
አውጥቶ አውራጁ
ጉልቤን አሰጋጁ
በአይን የማይታይ ቅንጣት አስከትሎ
ሃያል ሃገር ታየ ፥ እንደ ቅጠል ቀሎ
፡፡፡፡
ሲበሉ ስንበላ
የነሱን አግዝፈን የኛን ስንጠላ
አብረን ስንጎተት ከኋላ እንደ ጥላ
ሲሄዱ ሳንጠይቅ ፥ እንዲው ስንከተል
የቆጥ ላይ አንጋጠን የብብቱን ስንጥል
ሲስቁ ስንስቅ ሲዘሉ ስንዘል
ሲያብዱ አብረን አብደን
በቀደዱት ትቦ እንደ ጅረት ፈሰን
ሲያለቅሱ አልቀስን
የሆኑትን ሆነን
ለሃገር ለእምነት ጠበቃ እንዳልሆንን
በሥስት ቁር ደርቀን ማህተብ አላላን
ሃይማኖትን ሽጠን ፥ ቁራሽ ዳቦ በላን
የነብስን ዘንግተን ፥ የስጋን ሞት ፈራን
አምላክ እንደሌለው እነሱ ሲፈሩ አብረናቸው ፈራን
፡፡፡፡፡
አቋራጭ ነው ብለህ በማታውቀው ልማድ
እንደ ግንደ ቆርቁር ፥ ሺ 'ባሕል ለመናድ
ተጉዘሃልና ፥ በሄዱበት መንገድ
እነሱን መከተል ፥ በበሽታም ልመድ
፡፡፡፡
ጊዜ ለምዶ ሩጫ
አብዝቶብን ጩጫ 
ሲወቅጠን ሰብስቦ በአንድ ሙቀጫ
የቀደመው መንገድ ቢጠፋን አቅጣጫ
ጠበሉን እረስተን ቁርባኑን ዘንግተን ፥ ወ'ዳልኮል ሩጫ
ይልቅ አትፈትነው
የእግዜርን ቁጣ ታጥበህ ላታጸዳው
ምናልባት እራርቶ ቁጣውን ቢተወው
ከደጁ ተደፍተህ ፥ ይቅር ይቅር በለው
ከ'እጅህም በላይ የህሊናህን ቋት ራስህን ታጠበው
.
( ሚካኤል እንዳለ )
የመጻተኛ ምክር
---------

እከርማለው ብለህ ስራ እሞታለው ብለህ ኑር
አቋርጦህ እንዳ'ያልፍ ፥ ፈጣሪን አታማር
ለመቆየት እንጂ ፥ አትልፋ ለመኖር
ሞቶ መነሳትን ፥ ከስንዴ ዘር ተማር
፡፡፡፡
እግዜርን ከፊቱ
ሞግቶ በብርቱ
እንደ ቅዱስ ያቆብ ፥ ከሌለ መታገል
የበኩር ልጅነት ፥ አይገኝም አክሊል
፡፡፡፡
ጎንን የሚወቃ
ከ'ንቅልፍ የሚያነቃ
የሚያባንን እሾህ ፥ ከሌለህ ጠላትም 
ምን ጎበዝ ብትሆን ፥ ድል ማድረግ አይኖርም
፡፡፡፡
ጸጸት በዋለበት ሃጢያትህ አትቆይም
ፍቅር ባለችበት ትቢት ውላ አታድርም
ሁለቱን አጋምደህ እንደ ዘሃ ዘጌ
'ራስህን ዝቅ አርገህ ሳትሆን ባለጌ
እንደ መግደላዊት ተደፍተህ ከግርጌ
ስረይ ለነ በለው ስራህን አይቆጥርም
ያለፈን የሚያስብ እሱ ሰው አይደለም
፡፡፡
እውነት የምር የምር
እንደ ጴጥሮስ እንባ እንደ ቅድስት አስቴር
ከልብ ከለመኑት ፥ ተደፍተው ከምድር
ላጋንንትም ያዝናል ፥ እኳን ለሰው ፍጡር

( ሚካኤል እንዳለ )

@mebacha
@mebacha
ስማ ወዳጄ
--------
.
(ሚካኤል እንዳለ )
.
.
ከድሮም
ከወትሮም
ከኋላም
ከፊትም
ከአምናም ካቻምናም
በሁሉም በምንም ፥ አንድ ነህ እያሉት
እንደ ጴጥሮስ ዶሮ ደጋግመው ቢነግሩት
የሰው ልጅ ከልቡ ፥ መቼ ሰምቶ ያውቃል
ክፉ ቀን ሲመጣ..
አብሮ መኖር ሳይችል : አብሮ ይቀበራል

@mebacha
@ethio_art
አንቀብጥም
------------
#ሚካኤል እንዳለ
.
.
ይታየኛል ሰማይ
ይታየኛል ፀሐይ
ከሞት ጋር ቀጠሮ የለም ዘንድሮ ላይ
.
.
ክረምቱ ቢጀምር ፥ ቀድሞ ከክረምቱ
ቀን በጋውም ቢያጥር እረዝሞ ለሊቱ
ባይኖር ከእዳ ነፃ ፥ ተምሮ ተምሮ
አያልፍም አትበሉ ፥ ያልፋል ተዘክሮ
እንኳን የኛ እድሜ
ማቱሳላም አልፏል ሺ አመታትን ኖሮ
.
.
እንደው እንዲታወስ
የታወረን  ቁራ ፥ እንባውን የሚያብስ
የ'ንስሣቱን ገላ በጠጉር የሚያለብስ
ያለሰው  ንክኪ ፥  ያለ አንዳች ሃኪም
ከደዌ ከስቃይ ፥ አውአፍን የሚያክም
እስካለን ወጌሻ ፥ ያልልክ አንፈራም
እኳን የሰው ገላ
እርሱ ካልፈቀደ ፥ ድንቢጥም አቶድቅም
.
.
ቢሆንም አንቀብጥም 😷😷😷


@mebacha
@ethio_art
አንብቧቸው
-----------
#ሚካኤል_እንዳለ
.
.
ምድርን በብርሐን ፋና
ሰማይን በክንፍ በደመና
በእውቀት ያሰሱ የዳሱ
ንሥር ጋልበው እንደ ንፋስ የነፈሱ
እንደ ግዮን የማይነጥፉ
ከሐይቅ አድማስ የሚሰፉ
ከፀሐይ ደረት የሚገዝፉ
. . .
እንደ ዶሮ እውቀት ጭረው
ብራና አጥፈው ቀለም ቀልመው
የጥበብ አምድ መቅረዝ ተክለው
ሀሁ ዘርተው ቅኔ ለቅመው
ከፊደል ሆድ ቃላት አልበው
እንደ ወተት ጥበብ ግተው
. . .
አረም ነጭተው
እሾህ ነቅለው
አዝመራውን እያረሙ
ህሙም ሃሳብ የሚያክሙ
ውልቅ አዕምሮን የሚገጥሙ
መንሽ አንግበው ገለባውን የሚገልቡ
በላሜዳ ጥበብ ሰፌድ ፍሬ አብዝተው ሚመግቡ
ሥጋ ለበስ መፅሐፍ ናቸው 'ሚነበቡ
. . .
ለሚያቸው የኮሰሱ
ሲቀርቧቸው ጥበብ ፈትለው የለበሱ
ሁሉን አጥተው የሚኖሩ
ግን ሁሉንም የሚሰፍሩ
እንደ ኮኮብ እንደ ፀሐይ የሚያበሩ
. . .
ሳይሰለቹ ሳይታክቱ
ህመም ችለው ሳይቃትቱ
በደከመኝ ሳይረቱ
እንደ ህዋ እንደ ናጌብ ቢዘለቁ
ከገነት ሆድ የሚፈልቁ
እንደ ዳዊት ቢገልጧቸው የማያልቁ
. . .
አሉ በምድራቹ
ዞር በሉ በዙሪያቹ
ምዕራቡን ተዉትና እነሱን እዩ በአይናቹ
የፀሐይ መውጫ ምስራቁ ነው ሚበጃቹ
ፊደል አባት ስለሞሉ አሳዩአቸው ልጅ ሆናቹ
የዛሬን አያድርገውና የሚል ተረት ይታክታቹ
. . .
እኒህ ነበሩ
መንገድ አቅኚ ፋና ወጊ
የትውልዴን ኩክ ጠራጊ
እኒህ ነበሩ ቀለማችን
ውበት ሸማ ድምቀታችን
ብርሐን ቀጂ መርህ መንገድ አይኖቻችን
እኒህ ነበሩ ህይወት ሰጪ የእግዜር ትንፋሽ
በሄዱበት ሳንከተል ያረግናቸው አመድ አፋሽ
. . .
አሁን በዐይን ባናያቸው
እጅ አንስተን 'ባንዳሳቸው
ጊዜ ቆጥሮ ገቺ ዘመን ቢገታቸው
አፈር ቢሆን ያ ሥጋቸው
ሞቱ አንልም ህያው ናቸው
እስትንፋስ ቢቆምም ቅሉ ነፍስ አለውና ፊደላቸው
.
.
አንብቧቸው
! ! !
ብልኋ  እንቁራሪት
-----------

(ሚካኤል_እንዳለ)

አንዲት እንቁራሪት በኩሬ ውስጥ ያለች
የሚቃጠል መንደር ፥ ከሩቁ እያየች
ትፀልይ ጀመረ ፥ እንደዚህ እያለች
.
.
እባክህ ጌታዬ ይህን እሳት አጥፋው
ባለበት እንዲቆም ግዛቱን አታስፋው
ብላ ለፈጣሪ ፥ አዝና ስትናገር
ለካስ ካጠገቧ እባብ ቆሞ ነበር
እሱም በመገረም ፥ በጸሎቷ ነገር
የሽሙጥ እያየ እንዲህ ይላት ጀመር
.
.
እንደው ምን ትገርሚ እንደምን ትደንቂ
እሳቱ እንዲጠፋ ፥ ጌታን 'ምጠይቂ
እሱ 'ሚደድ እዛ እሩቅ ነው ካንቺ ዘንድ
በምን ደርሶብሽ ነው ያንቺን ቤት የሚያነድ ?
ደሞም ከውሃ ውስጥ ቁጭ ብለሽ ያለሽው
የማይደርስብሽን ፥ እሳት የምትፈሪው
እያለ በሹፈት ፥ ከልቡ ሳቀባት
ወደታች በንቀት አዘቅዝቆ እያያት
.
.
ይ'ን ጊዜ እቁራሪት እየተገረመች
በእባብ ጅልነት በጣም እያዘነች
እንዲት ትለው ጀመር ቀና ብላ እያየች
አዎ ትክክል ነህ ፥ እሳቱ እሩቅ ነው
እኔም ያለሁበት ዙሪያውን ውሀ ነው
ነገር ግን አስተውል እጅግ አትሳት
ቃጠሎውን ቶሎ ወዲያው ካላቆሙት
ከ'ኔ ዘንድ መ'ተው ነው ውሀ የሚቀዱት
.
.
እናም ያላወከው እውነታው ይሄ ነው
ምንም'ኳ እዚህ ብቀመጥ ከውሃው
እዛ እሩቅ ቢሆን መንደሩ 'ሚነደደው
ካልጠፋ በጊዜ ፥ አምላክ ካላቆመው
የ' ኔም ቤት ነውና ተዝቆ የሚያልቀው
.
.
ስለዚህ ወዳጄ አያጥቃህ ጅልነት
ቃጠሎው ባይደርስም እኔ ካልሁበት
እዛ ነዶ ነዶ ፥ እጅግ ከባሰበት
ባልዲ ተሸክመው ሲመጡ ለመቅዳት
ይከቱኛል ወስደው ፥ ከሚነደው እሳት
.
.
ይህን አውቄ ነው ከሩቁ መፍራቴ
አጥፋው በሚል ፀሎት ምድር መደፋቴ
የአቅሜን ያህል እነሱን መርዳቴ
ብላ ስትናገር ፥ እባብን ገረመው
ማየት ያልቻለውን ገልጣ ስታሳየው
.
.
እናም እሩቅ ያለ ከ' እኛ የማይደርስ
የሌላ ነው ያልነው ፥ እሳቱ ሲለኮስ
ስለማይቀር እዚ ፥ መምጣቱ ቀስ በቀስ
ትልቅ እገዛ ነው
የሰው ችግር አይቶ ፥ ለኔ ብሎ ማልቀስ
---
(ሚካኤል እንዳለ)
ሰኔ 1 , 2012 ዓ.ም
አ.አ አስኮ

መነሻ ሃሳብ - ዳኒኤል ክብረት
እድሜ ለኮሮና
ስንቱን አስተዋውቆ ያሳየናል ገና
'ርዕሱ ነው 😁
__________

( ሚካኤል_እንዳለ )

አንቺ ሥራ ዋይ ነሽ ማታ ገቢ እኔም
አላይሽ በቀኑ ፥ አታይኝም አንቺም
ጠዋት እንደወጣን ፥ እንደ ግንቦት ጀንበር
ማታ ነው 'ምንገባው ግጦሽ ተሰማርታ እንደዋለች ጊደር
እሱንም ለማደር !
.
.
የት ውዬ እንደመጣው ፥ በምንም አታውቂ
ያንቺን አትነግሪኝ ፥ የኔን አጠይቂ ?
ቀኑን ሙሉ ስንዞር
ውሃ እንደተጠማ እንደራበው ንሥር
ለወግ ያህል ነበር
የምንተያየው ስንገባ 'ባንድ በር
እሱንም ለማድር !
.
.
አመታትን ቆጥረን አብረን ብንኖርም
በአንድ ትሪ እንጂ አብረን አልበላንም
ገላችን የሚያርፈው
'ባንድ አልጋ ቢሆንም
ጎን ለጎን እንጂ ፥ አብረን አልተኛንም
ትዳር ይሄ አይደለም እስኪ እወቂያቸው
አብሮ መብላትና ባንድ ትሪ መብላት ልዩነት አላቸው
አብሮ መተኛትም ባንድ አልጋ ከማደር ለየቅል እያቸው
.
.
ያኔ ድሮ ድሮ
ከሥር ከመሰረት ካብሮነት ጅማሮ
ተቀንጭቦ ጊዜ ለማሳለፍ አብሮ
አንድነት ከሌለ
የሚያስተዋውቀን ፥ የጋርዮሽ ዓለም
አብሮ መኖር ከንቱ ለመተኛትማ ይገናኛል ሁሉም
.
.
ዛሬ ደዌ ሰፍቶ
ሳታውቂው አግብተሽ ሳያውቅሽ አግብቶ
እንደ እኔና እንዳንቺ ፥ ሁሉ ቀሳ ገብቶ
ጊዜ ሲያበጥረው ሲሰለቻች ሁሉም
ጠባያችን እርቃን ፥ አደባባይ ሲቆም
እንደ በጋ ሰማይ ፥ ሲገለጥ እውነቱ
በአንድ አብሮ ሲውል ፥ ሁሉ ሰው ከቤቱ
እድሜ ለበሽታ
ደፋሪው ሲበዛ ይተዋወቅ ጀመር ያገር 'ባል ከሚስቱ

@mebacha
@ethio_art
እህሉስ ተሰጠ እኔም ተቀበልኩኝ
እንግዲ ማን ይሆን ሰርቶ የሚያበላኝ
እያየ ጉልበቴን
እንኳንስ ለመቆም
ለቀመቀመጥ ደክሞኝ
ምናለ ከረዳ ፥ ቤቴ'ኳ ቢያደርሰኝ
እያሉ ሲያስቡ ፥ ሲተክዙ እርሶ
እሱ ቤቱ ገብቷል ፥ ዜናውን ጨርሶ
. . .
#ሚካኤል_እንዳለ
በሽታን አትሥጉ
ዘመኑ ሲደርስ ያበቃል በጊዜው
መቅሰፍትም አትፍሩ
ትዛዙን ፈጽሞ ፥ ይሄዳል ከቦታው
ቸነፈር ቢሆን
እንግዳ ነውና ቅርብ ነው ማደሪያው
---
ይልቅ ያለመድሎ ሚዛኑን ከያዝነው
ያለ ጊዜ ገደብ  ፥ መፍራትስ ሰውን ነው
ከበሽታ በላይ
ዘላለም ነውና ፥ ሲገል የሚኖረው
---
ስለዚህ ተፈጥሮ
እጇን ብታነሳ ፥ ብትመልስ ከዓለም
ደዌ ከምድራችን ፥ እርቆ ቢቆምም
ፈጣሪ ከቁጣው ፥ ህዝቡን ቢሰውርም
የሰው ልጅ እስካለ የሰው ሞት አይቆምም

ሚካኤል_እንዳለ

@ethio_art
@ethio_art
@mebacha
@mebacha
2024/05/10 20:39:56
Back to Top
HTML Embed Code: