Telegram Web Link
1ኛ ተሰሎንቄ 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³ የእግዚአብሔር ፈቃድ ከዝሙት ርቃችሁ እንድትቀደሱ ነው፤
⁴ ደግሞም እያንዳንዱ የገዛ ሰውነቱን በቅድስናና በክብር መያዝ እንዳለበት እንዲያውቅ ነው፤
⁵ ይህም እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ በፍትወተ ሥጋ ምኞት አይሁን።
⁶ በዚህም ነገር ማንም ተላልፎ ወንድሙን አያታል፤ ምክንያቱም ከዚህ በፊት እንደነገርናችሁና እንዳስጠነቀቅናችሁ ጌታ እንደ እነዚህ ያለውን ኀጢአት ሁሉ የሚፈጽሙትን ይበቀላል፤
⁷ እግዚአብሔር በቅድስና እንድንመላለስ እንጂ ለርኵሰት አልጠራንምና።
⁸ እንግዲህ ይህን ምክር ንቆ የማይቀበል፣ የናቀው ቅዱስ መንፈሱን የሰጣችሁን እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አይደለም።
“እግዚአብሔርን የሚፈሩት ሁሉ፥ በመንገዶቹም የሚሄዱ ምስጉኖች ናቸው።”
— መዝሙር 128፥1
የሕይወት ምክር

o አንድ ወጣኒ መናኝ አንድን ታላቅ አባት ጥሩ ሰው የሚባለው ምን የሚያደርግ ነው ብሎ ቢጠይቃቸው፤ እኚህ ትልቅ አባትም መልሰው ዘወትር ለኃጢአቱ የሚጨነቅና ይቅርታ የሚጠይቅ፤ ዘወትር በሥራና በትጋት የተጠመደ፤ ከመናገር ዝምታን ገንዘብ የሚያደርግ፤ ትእዛዛቱን የሚጠብቅና እራሱን ዝቅ የሚያደርግ ነው በማለት መለሱለት፡፡
o ዓሣ ከውኃ ወጥቶ ከቆየ ወዲያው እንደሚሞት ክርስቲያንም ከመንፈሳዊ ሕይወቱ ከወጣ እንደዚሁ ይሞታል፡፡ ዓሣው ቶሎ ተምልሶ ወደ ውኃው ሲገባ እንደሚድን ሰውም በንስሐ ቶሎ ሲመለስ እግዚአብሔር የይቅርታውን በር ይከፍትለታል፤ ስለዚህ ንስሐን እንደ ቀላል ነገር አትቁጠረው፤
o ከተሰወረ ፍቅር የተገለጠ ዘለፋ፣ ከጠላት መልካም ሐሳብ የወዳጅ ክፉ ምክር፣ ከራቀ ወንድም የቀረበ ወዳጅ ሳይሻል እንደማይቀር አትዘንጋ፤
o መልካም ሞት የመልካም ኑሮ ውጤት ነው፤
o ሳያልፍ የመጣ ክፉ ነገር የለምና እስኪያልፍ ታገሥ፤
o አንደበተ ትልቅ ውስጠ ቀላል እንዳትሆን ተጠንቀቅ
o በእግዚአብሔር እንጂ በደጋፊዎች አትተማመን በደጋፊዎች ከተማመንክ ከሰባራ ወንበር ላይ እንደተቀመጥክ ቁጠረው፤
o የሰይጣን ደህና ባይኖረውም፣ ብቻውን ካለ ሰይጣን ይልቅ በሰው ላይ ባደረ ሰይጣን ተጠንቀቅ፣ በሰው ላይ ያደረ ሰይጣን በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ስትለው ከሰውየው ጋር ተጣብቆ ያስቸግራልና፡፡
o ሰዎች በአንተ ላይ ምንም እንዳያወሩ ሥልጣን የለህምና፤ የሚሉህን እየሰማህ ስህተትህን አስተካክል፤

(አባ ሳሙኤል አዲሱ፣ መንፈሳዊ የሕይወት ምክር)
“ተአምራትን ማድረግ ትፈልጋላችሁን? እንኪያስ በዘፈን የደነቆረን ጀሮ መዝሙር እንዲሰማ አድርጉት፡፡ ሴትን በመመኘት የታወረው ዐይን ፈጣሪውን እንዲያይ አድርጉት፡፡ በስርቆት የሰለለ እጅ በምጽዋት እንዲዘረጋ አድርጉት፡፡ ወደ ኃጢአት ቤት በመሄድ ሽባ የሆነውን እግር ወደ እግዚአብሔር ቤት እንዲሮጥ አድርጉት፡፡ ሐሜትን በማውራት ዲዳ የሆነውን ከንፈር መልካም ንግግርን እንዲናገር አድርጉት፡፡ ከተአምራት ሁሉ የበለጠ ተአምር ይሄ ነው፡፡"

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
"ቅዱስ፣ ጥንቁቅ፣ ግልጽና ብልህ ሁን፡፡ እርጋታን የተላበሰ ሰብእና ይኑርህ፡፡ ደስተኛ ሁን፤ ሰላምታህ በፈገግታ የታጀበ ንጹህ ይሁን፡፡ ንግግርህ የታረመ አጭርና በጨው እንደተቀመመ ጣፋጭ ይሁን፡፡ ቃላቶችህ የተመጠኑ እና ጤናሞች ሁሉም የሚረዳቸው ይሁኑ፡፡

የጓደኛህን ምስጢር አትግለጥ፤ ለሚወዱህ ሁሉ የታመንክ ሁን፡፡ ወደ ጭቅጭቅ እና ንትርክ ከመግባት ራህን ጠብቅ፡፡ የሚሰሙህ ሁሉ እንዳይጠሉህ ወደ ጠብ አትግባ፡፡ ከሰይጣን በቀር ምንም ጠላት አይኑርህ፡፡

የሰዎችን ስህተት አትመራመር፤ የባልንጀራህ ኃጢአት አትግለጥ፡፡ የባልጀራህ ውድቀት ደጋግመህ አታውራ፡፡ በራስህ ኃጢአት ላይ ፍረድ እንጂ በሌሎች ላይ አትፍረድ ገዢያቸው አይደለህምና፡፡

ኃጢአትን በፈጸመ ሰው ላይ ወቀሳ አታብዛ አንተም ትበድላለህና፡፡ ነገር ግን ከኃጢአቱ ይመለስ ዘንድ ረዳትና መካሪ ሁነው፡፡ ከወደቀበትም የስህተት ሥራ እንዲወጣ አበርታው፡፡ ተስፋውን በእግዚአብሔር ላይ ቢያደርግ ኃጢአቱን ልክ በእሳት ፊት እንደወደቀ ገለባ ፈጥኖ እንደሚወገድለት ንገረው፡፡

ተፈጥሮ እንደ መጽሐፍ ፍጥረታት እንደ ጽላት ይሁኑህ። ከእነሱ ሕግጋትን ተማር፤ በተመስጦ ሆነህ በመጽሐፍ ያልሰፈሩትን ምስጢራት ተረዳ፡፡

እግዚአብሔርን ከሚፈራ በቀር ባለጸጋ የሆነ ሰው ማነው? የእውነት እውቀት ከጎደለው ሰው በላይ ፍጹም ደሃ የሆነ ማን ነው? ሁል ጊዜም እውነተኛ ፍቅራችን ጸንቶ ይቀጥል ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ፡፡ እርሱን ለምነው፡፡ ስለ ቸርነቱ ምስጋና አቅርብ፤ ምክሬን ፈጽሞ ቸል አትበል፡፡"

(ምክር ወተግሳጽ ዘቅዱስ ኤፍሬም)
ኦርቶዶክሳዊ የሕፃናት አስተዳደግ ማለት፥ ልጆቻችን እኛ አየናቸውም አላየናቸውም በሕሊናቸው ጓዳ በልቡናቸው ሰሌዳ ላይ መንግሥተ እግዚአብሔርን መቅረፅ ነው፡፡

ኦርቶዶክሳዊ የሕፃናት አስተዳደግ ማለት ስንጠራቸው አቤት ስናዛቸው ወዴት የሚሉንን ሳይኾን ትዕግሥትን፣ ቸርነትን፣ በጎነትን፣ እምነትን፣ የውሃትን፣ ራስን መግዛትን፥ በአጭር ቃል የመንፈስ ፍሬዎችን ገንዘብ ያደረጉ ልጆችን ማሳደግ ነው (ገላ.5፡22-24)፡፡

ኦርቶዶክሳዊ የሕፃናት አስተዳደግ ማለት፥ ልጆቻችን የገዛ ክብራቸውን እንዲያውቁና በዚያ መሠረት እንዲያድጉ - ይኸውም የእግዚአብሔር ልጆች፣ ክርስቶስን የሚመስሉ፣ በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል ቅዱሳን እንዲኾኑ አድርጎ ማሳደግ ነው (ዘፍ.1፡26)፡፡

ኦርቶዶክሳዊ የሕፃናት አስተዳደግ ማለት ልጆቻችን የእኛ ንብረት እንዲኾኑ ሳይኾን የእግዚአብሔር ልጆች እንዲኾኑ አድርጎ ማሳደግ ነው፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ እስራኤላውያንን ለክርስቶስ ያዘጋጃቸው እንደ ነበረ፥ እኛም በዚያ መንገድ ልጆቻችን የእግዚአብሔር ልጆቸ እንዲኾኑ ማዘጋጀት ነው፡፡

ኦርቶዶክሳዊ የሕፃናት አስተዳደግ ማለት የልጆቻችንን መጥፎ ጠባይ ከማራቅና እንዲታዘዙን ከማድረግ በላይ፥ እግዚአብሔርን በፍጹም ኃይላቸው እንዲወድዱ ማድረግ ነው፡፡ ቅዱሳንን እንዲያፈቅሩ፣ በቃል ኪዳናቸው ታምነው እነርሱን እንዲመስሉ ማድረግ ነው፡፡

ትንሿ ቤተ ክርስቲያን፣ ገጽ 507-508
ገብረ እግዚአብሔር ኪደ
@memhrochachn
"#እባክህን_ከእሳቱ_ላይ_አትውረድ"

አንድ ወንድም አባ ጴሜንን "ምከረኝ" ብሎ ጠየቀው። አባ ጴሜንም "ድስት በእሳት ላይ እያለ ምንም አይነት ተባይ ሊቀርበውና ሊያበላሸው አይችልም። ከእሳት ወጥቶ ሲቀዘቅዝ ግን ነፍሳት ሁሉ ለመግባትና ለማበላሸት ይቻላቸዋል። ክርስቲያንም ከመንፈሳዊ ተግባር ካልራቀ ጠላት የድቀት ምክንያት አያገኝበትም" አለው።

ወዳጄ ሆይ ሕይወት ቀዝቅዛብሃለችን? ከእሳቱ ወደ መሬት ወርደህ በርደሃልን? የሕያውነትህ ሙቀት እሳት በማጣት ተንዘፍዝፏልን? ድስት የተባለ ሰውነትህ ክረምት የሚያህል ጉድን ተሸክሟልን? ዙሪያ ገባህ ፀሐይ እንደማትወጣበት ምእራብ ጨለማን የሚጠራ ሆኗልን? ማንነትህ እሳት እንዳጣ ምግብ ጥቃቅን ነፍሳት በተባሉ ኃጢአቶች (ቁጣ፣ ቸልተኛነት፣ ስስት፣ አልታዘዝ ባይነት፣ ጭንቀት፣ ሁሉን የመናቅ ስሜት፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ...) ተወርሮ፣ መዓዛ ቅድስና ተለይቶት እጅ እጅ ብሏልን? ሞቅ የሚያደርገው አጥቶ በዓለማዊነት ሻግቷልን? የተባዮች መጫወቻ፣ የተውሳኮች መቀለጃ ሆኗልን? እንግዲያውስ በቶሎ ወደ እሳቱ ውጣ፡፡

ወዳጄ ሆይ ሃይማኖት በተባለችና ከሰማይ በወረደች ልዩ እሳት (ሉቃ.12፥49) ላይ ተቀምጠህ የድስትነትህን ሙቀት መልስ፡፡ እምነት፣ ተስፋና ፍቅር (1ቆሮ.13፥13) በተባሉ ሦስት ጉልቻዎች ላይ በምቾት ተጥደህ የሕይወትህን የኃጢአት ብርድ አስወግድ፡፡ ንስሐ በተባለች ነበልባል ውበትነት የክረምትህን ጽልመት በምስራቃዊ በጋነት ድል ንሳ፡፡ በሥጋ ወደሙ ፍምነት ድስት የተባለ ሰውነትህን በከዊነ እሳትነት ቀድስ፡፡ እባክህን በቶሎ ወደ እሳቱ ውጣ፡፡

ሃይማኖት የተባለ እሳትን ተባይ አይቀርበውም፡፡ እምነት ተስፋና ፍቅር የተሰኙ ጉልቻዎችን ተውሳኮች ሽቅብ አይወጡአቸውም፡፡ የነበልባለ ንስሐን ብርሃንና ሙቀት ነፍሳተ ጽልመት መቋቋም አይችሉም፡፡ ስለዚህ በእሳቱ ላይ እስካለህ ድረስ (በመንፈሳዊ ተግባራት እስከጠነከርክ ድረስ) አንተ ሁሌም ከተባይና ከነፍሳት ብልሽት (ከአጋንንት) የራቅክ ነህ፡፡

ወዳጄ እባክህን ከእሳቱ ላይ አትውረድ፡፡ እሳቱ በደንብ ይነድ ዘንድ ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት የተባሉ እንጨቶችንና ምጽዋት የተባለ ጋዝን መጨመርህን እንዳትዘነጋ፡፡ እንዲህ ከሆነ ዘንዳ ድስትነት ሁሌም የሞቀ ይሆናል፡፡ እጅ እጅ ከማለት፣ ከመሻገትና የተባይ መጫወቻ ከመሆን ትድናለህ፡፡

ወዳጄ ሆይ እባክህን ከእሳቱ ላይ አይትውረድ፡፡

በኃጢአት "እጅ እጅ '' ከማለትና በበደል ከመሻገት እግዚአብሔር ይሠውረን! አሜን!

(ሕሊና በለጠ ዘኆኅተብርሃን)
#ልብ_ብለው_ያንብቡ

#ቅዱስ_ጎርጎርዮስ_ዘእንዚናዙ ለንስሓ ልጁ በሰርጓ ቀን መገኘት ባለመቻሉ የላከላት ደብዳቤ

“ልጄ! ለሰርግሽ የነፍስ አባትሽ እኔ ጐርጐርዮስ ይህን ግጥም ስጦታ አድርጌ ልኬልሻለሁ፡፡ አባት ለሚወዳት ልጁ ሊሰጣት የሚችለው የተሻለው ምክርም ይህ እንደ ኾነ አምናለሁ፡፡

“ኦሎምፒያታ ሆይ፥ እውነተኛ ክርስቲያን ለመኾን ያለሽን ፍላጎት ዐውቃለሁና በደንብ አድምጪኝ! እውነተኛ ክርስቲያን እንዲሁ መኾንን የሚመኝ ብቻ ሳይኾን እንደዚያ ለመኾን ሊጥር ይገባዋል፡፡

“ከኹሉም በላይ፥ እግዚአብሔርን ልታከብሪውና ልትወጂው ይገባሻል፡፡ ከእርሱ ቀጥሎም በቅዱስ ወንጌል እንደ ታዘዘው እንደ ጌታችንና መድኃኒታችን [ኢየሱስ ክርስቶስ] አድርገሽ ባልሽን ልታከብሪውና ልትወጂው ይገባሻል፡፡ ስለዚህ እጠይቅሻለሁ! ጌታዋንና ፈጣሪዋን [ኢየሱስ ክርስቶስን] የማታከብርና የማትወድ ሴት በዚህ መንገድ ባልዋን እንዴት አድርጋ ልታከብረውና ልትወደው ትችላለች?

“በጋብቻሽ ውስጥ የትዳር አጋርሽ ይኾን ዘንድ እግዚአብሔር መርጦ ለሰጠሽ ባል ያለሽ መውደድ፣ ስሜትና ፍቅር እጅግ ኃያል ሊኾን ይገባዋል፡፡ ይህ ሰው አሁን የሕይወትሽ ዓይን፣ የልብሽም ደስታ ነውና፡፡

“እግዚአብሔርን እንደምትወጂው፥ ባልሽንም ያለ ቅድመ ኹኔታ ልታከብሪውና ልትወጂው ይገባሻል፡፡ አንቺ ሴት እንደ ኾንሽና ታላቅ የኾነ ዓላማና ግብ እንዳለሽ፥ ኾኖም ዓላማሽና ግብሽ የቤትሽ ራስ ሊኾን ከሚገባው ባልሽ የተለየ እንደ ኾነ ዕወቂ፤ ተረጂም፡፡ ባንቺ ዕድሜ ላይ ያሉት አንዳንዶች ኹለቱም ፆታዎች እኩል [ራስ ናቸው] ብለው የሚሰብኩትን አትስሚ፤ የጋብቻንም ግዴታ [ወይም ዋና ዓላማ] አስቢ፡፡ እነዚህን ግዴታዎች [ወይም ዓላማዎች] ስታውቂ የቤተሰብሽን ተግባራት ለማከናወን እንደ ምን ያለ ትዕግሥትና ጽናት እንደሚያስፈልግሽ ታውቂያለሽና፡፡ እንደ ሚስት እጅግ ጥንካሬን ገንዘብ የምታደርጊውም በዚህ መንገድ ነው፡፡

“ወንዶች እንዴት በቀላሉ የሚቈጡ መኾናቸውን በርግጥ ልታውቂ ይገባሻል፡፡ አይችሉም፤ ብዙ ጊዜም እንደ በረኻ አንበሳ ይኾናሉ፡፡ እንግዲህ ሚስት ጸንታ ልትቆምና የነፍስ ልዕልናዋን ልታሳይ የሚገባት በዚህች ቅጽበት ነው፡፡ አንበሳን የማስለመድ ሥራ መሥራት አለብሽ፡፡ አንበሳን የሚያስለምድ ሰው አንበሳ ሲያገሳ የሚያደርገው ምንድን ነው? ከየትኛውም ጊዜ በላይ ዝም ጸጥ ይላል፡፡ በጸጥታውና በርጋታውም የአንበሳውን ቊጣ ይቈጣጠራል፡፡ በርጋታና በለሆሳስ ኾኖ ያናግረዋል፤ ይደባብሰዋል፤ በቀስታ ያሻሸዋል፤ በጥቂት በጥቂቱም አንበሳው ቊጣውን ይተዋል፡፡

“ባልሽ ስሕተት ሲሠራ በፍጹም ልትነቅፊው፣ ልትንቂው ወይም ልታስነውሪው አይገባም፡፡ በተመሳሳይ መንገድ አንድ መሥራት ያለበትን ነገር ባይሠራና ከዚሁ የተነሣም ውጤቱ ደስ የማያሰኝ ቢኾን፣ ወይም እጅግ የምትፈልጊውና አግባብ ነው ብለሽ የምታስቢውን ባያደርግ እንኳን ባልሽን መናቅ ከአንቺ ልታርቂ ይገባል፡፡ ክፉዎች አጋንንት ዘወትር ቤታችሁን ለማፍረስና የጥንዶች መንፈሳዊ አንድነትን ለመበተን እንደሚሞክሩ ዕወቂ፡፡”

( #ከገብረ_እግዚአብሔር_ኪደ ከትንሿ ቤተክርስቲያን መጽሐፍ የተወሰደ)
“ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው።”
— ሮሜ 8፥6
ዝም ብላቹ አመስግኑት

አንዳንድ ሰዎች እግዚአብሔር ለማመስገን አንድ የተለየ ምክንያት ይፈልጋሉ፤ እንደነዚ አይነት ሰዎች የብርሀንን መልካምነት ለመናገር ጭለማ እስኪመጣ የሚጠብቁ ሰዎች ናቸው፤ ወዳጆቼ እግዚአብሔር ለማመስገን ምክንያት አትፈልጉ፣ ቢሆንላቹም ባይሆንላቹም፣ ቢሳካላቹም ባይሳካላቹም፣ ሁኔታዎች ቢመቻቹም ባይመቻቹም ጌታን ማመስገን አታቋርጡ፤ እግዚአብሔር 24 ሰዓት ካለ እንከን የሚያመሰግኑት መልአክቶች አሉት ቢሆንም ግን ከኛ ከልጆቹ የምስጋናን ቃል መቀበል ይፈልጋል፤ ስለዚህ እርሱ ምስጋናን ከኛ ከፈለገ አንደበቶቻችንን ለምስጋና እንክፈትለት።
@memhrochachn
የንጉሥ ሥልጣን በሥጋ ላይ ነው፤ የካህን ሥልጣን ግን በነፍስ ላይ ነው፡፡ ንጉሥ ይቅር ቢል የገንዘብን ዕዳ ነው፤ ካህን ይቅር ሲል ግን የበደል የኃጢአት ዕዳን ነው፡፡

ንጉሥ ያዝዛል፤ ካህን ግን ያስተምራል ይዘክራል፡፡ ንጉሥ ያስገድዳል፤ ካህን ግን ነጻ ፈቃድን ያያል፡፡

ንጉሥ ቁሳዊ የጦር ዕቃ መሣሪያ አለው፤ ካህን ግን ረቂቅ (መንፈሳዊ) የጦር ዕቃ መሣሪያ አለው፡፡ ንጉሥ የጦር ዕቃ መሣሪያውን ቢሰብቅ አንገዛም ብለው ባመፁት (እንዲሁም ከወራሪዎች ሥጋውያን ደማውያን) ላይ ነው፤ ካህን ግን ውጊያው ከጨለማ አበጋዞች ከአጋንንት ጋር ነው፡፡

ስለዚህ ሥልጣነ ክህነት ከሥልጣነ መንግሥት ይበልጣል፡፡ እንዲህም በመኾኑ ንጉሥ አንገቱን ለካህናት እጅ ያጎነብሳል፡፡

(ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ትንቢተ ኢሳይያስ፣ ድርሳን ፬ በተረጎመበት ድርሳኑ)
#የምንለወጠው_ምን_ስናደርግ_ነው?

በታመምህ ጊዜ ድካም ይሰማሃል፤ ብርታት ያንስሃል፤ ፊትህም ይገረጣል፡፡ የዕለት ተዕለት ሥራዎችህን በአግባቡ ማከናወን ይሳንሃል፡፡ በዚህ ጊዜም ሕመምህ ምን ያህል እንደ በረታ ሰዎች ያስተውላሉ፤ መታከም እንደሚገባህም ይነግሩሃል፡፡ ስለዚህ ወደ ሐኪም ትኼዳለህ፡፡ ወደ ሐኪም የምትኼደው ግን ሐኪሙ ምን እንዲያደርግልህ ነው? አሁን ለሚሰሙህ ስሜቶች የሚሽሩ መድኃኒቶችን እንዲሰጥህ ነው፡፡ ኾኖም ይሰ'ሙህ የነበሩ ስሜቶች ቢሻሉህም ሰውነትህ አሁንም እንደ ደከመ፣ ፊትህ እንደ ገረጣ ከቀረ፣ የዕለት ተዕለት ሥራዎችህንም በአግባቡ ማከናወን ከተሳነህ በተሰጠህ ሕክምና ደስተኛ ትኾናለህን? አትኾንም !

“እውነታው ምንድን ነው?” ስንል ወደ ሐኪሙ የኼድከው የበሽታህን ምንጭ ለመታከም ሳይኾን የበሽታህን ምልክቶች ለማስታገሥ ስለኾነ ነው፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ የበሽታህ መንሥኤ እስካልታከመ ድረስ የበሽታህ ምልክቶች ለጊዜው ቢታገሡም ቅሉ ፈጽመው ሊወገዱ እንደ ማይችሉ ሐኪሙ በደንብ ያውቃል፡፡

በክርስቶስ ክርስቲያን፣ በወልድ ውሉድ፣ በመንፈስ ቅዱስም መንፈሳውያን የተባልን እኛም እግዚአብሔር መንፈሳዊ በሽታችንን እንዲያስወግድልን እንሻለን፡፡ እንደ እውነታው ግን ብዙዎቻችን ወደ እግዚአብሔር ቀርበን እንዲያስወግድልን የምንሻው ምልክቶቹን ነው፡፡ ለምሳሌ ችግርን፣ ኀዘንን፣ ቀቢጸ ተስፋንና የመሳሰሉትን እንዲያርቅልን እንፈልጋለን፡፡

እግዚአብሔር ደግሞ ከዚህ በተቃራኒ የእነዚህ ምክንያት የኾነውንና ሥር የሰደደውን፣ ዋና ምክንያትም የኾነውን መንፈሳዊ በሽታችንን ሳይሽር እነዚህን ምልክቶች ሊያርቅልን አይፈልግም፡፡ ችግር የሚኾነውም ይህን ጊዜ ነው፡፡ ምልክቶቹን እንዲያርቅልን ስንደክም ወደ ውሳጤያችን ገብቶ የችግሩን ምንጭ ሊያርቅልን የሚችለውን የእግዚአብሔርን ጸጋ (ኃይልን) አጥብቀን እንቃወማለንና፡፡ በውሳጤያችን የተሸሸገውን በሽታ ማስወገድ አንፈልግም፡፡ አመለካከታችን እንዲለወጥ አንፈቅድም፡፡ እውነተኛ ለውጥ የሚመጣውና አማን በአማን የምንታከመው ግን የልባችንን ውሳጤ ለእግዚአብሔር ስንከፍትለትና እርሱም በዚያ በመረቀዘው ቁስላችን ላይ ጽኑ መድኃኒት ሲያስርልን ነው፡፡ እንዲለወጡ የምንፈልጋቸው ምልክቶች በእርግጥም የሚለወጡት ይህ በልባችን ውስጥ የተደበቀው መንፈሳዊ በሽታችን ሲጠፋ ነው፡፡

➛ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
➛ አምስቱ የንስሐ መንገዶች - ገጽ 69-70
እግዚአብሔር ሲቀጣን

"[አንድ] ሐኪም አእምሯቸውን የሳቱ ሰዎች ቢሰድቡት፥ ስድባቸውን ከቁም ነገር አይቆጥረውም፡፡ እንዲህ አእምሯቸውን እንዲስቱ ያደረጋቸውን ምክንያት ያስወግድላቸው ዘንድ ይተጋል እንጂ፡፡ 'ሰድበውኛል' ብሎ የራሱን ጥቅም አያይም፤ የሕሙማኑን እንጂ፡፡ በጥቂቱም ቢኾን ሻል ካላቸውና ራሳቸውን መግዛት የሚችሉ ከኾነም እጅግ ደስ ይሰኝባቸዋል፡፡ ውስጡ በፍጹም ሐሴት ይሞላል፡፡ መድኃኒት መስጠቱን በፊት ከሚያደርግላቸው ይልቅ ተግቶ ይሰጣቸዋል፡፡ 'ከዚህ በፊት ሰድበውኛልና ልበቀላቸው' ብሎ በፍጹም አያስብም፡፡ ይበልጥ እንዲጠቀሙና ወደ ቀድሞ ጤናቸው ይመለሱ ዘንድ ተግቶ ይሠራል እንጂ፡፡

"እግዚአብሔርም እንደዚህ ነው፡፡ ምንም እንኳን እጅግ ጥልቅ በኾነ ኃጢአት ውስጥ ብንወድቅም፥ ኹሉንም ነገር የሚያደርገው እኛን ከመቅጣት አንጻር አይደለም፤ የሚቀጣን ስለ ሠራነው የኃጢአት ዓይነት አይደለም፡፡ ከዚህ ሕመማችን እንድንፈወስ ብሎ ነው እንጂ፤ በዚሁ መንገድ ሊመለሱ ይችላሉ ብሎ በማሰብ ነው እንጂ፡፡"

ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ፥ ወደ ቴዎድሮስ፥ ገ. 36
ስለ እርሱ አንብቡ

እግዚአብሔር በአሳባቸሁ ውስጥ እንዲኖር ስለ እርሱ አብዝታችሁ አንብቡ። እርሱን ለማወቅ ስለ እርሱ አንብቡ። እርሱን ካላወቃችሁት እንዴት እርሱን ልትወዱት ትችላላችሁ?

ስለ እርሱ አንብቡ ስታነቡ ግን በሳይንሳዊ ወይም በፍልስፍና ጠባይ አታንብቡ ወይም ደግሞ ስለ እርሱ ጥናታዊ ጽሑፍ ወይም ትምህርት ለመስጠት አታንብቡ። ነገር ግን ወደ እርሱ ጥልቀት ለመግባት ወይም እርሱ ወደ እናንተ ጥልቀት እንዲገባ አንብቡ። ለነፍሳችሁ ውድ የሆኑትን የእርሱን ባሕርያት ለማወቅ ስትሉ አንብቡ ይህ እውቀት አሳባችሁ ከእርሱ ጋር እንዲጣበቅና ፍቅሩ ከእናንተ ልብ ጋር እንዲቀናጅ ያደርግላችኋልና። ስለ ስምምነቱ ስትሉም አንብቡ። ከወደዱት ሰዎች ጋር ስላለው ግንኙነት በጠላቶቹ ላይ ስላለው አቋም ስትሉ አንብቡ! በጽሑፎች ውስጥ ስለ እርሱ "ውበትህ ከሰው ልጆች ይልቅ ያምራል" [መዝ 44÷2] የሚለውን ቃል በማንበብ የእርሱን ውበት ታውቁ ዘንድ አንብቡ።

እግዚአብሔር ቸር እንደ ሆነ ቀምሳችሁ ታዩ ዘንድ ስለ እርሱ አንብቡ። ታዲያ ንባባችሁ ለልባችሁ ምግብ እንዲሆን እንጂ እንዲሁ ተራ ንባብ እንዲሆን አትፍቀዱ። ስለ እግዚአብሔር ብዙ ካነበባችሁ በእርሱ ዘንድ ያለውን ፍጹምነት በሙሉ ታገኛላችሁ። እርሱን ስለምትወዱትም በሰሎሞን መዝሙር ውስጥ ካለችው ድንግል ጋር አብራችሁ "እርሱ ፈጽሞ ያማረ ነው" [መኃ. 5÷16] ትላላችሁ።

ከወደዳችሁት ስለ እርሱ ማንበባችሁን ትቀጥላላችሁ። እግዚአብሔር ስለ እርሱ የሚያነቡትን ስለ እርሱ ዜና የሚጠይቁትን ከእርሱ ታሪኮች መካከል አንዱን ለማወቅ የሚናፍቁትንና እርሱን የሚያደንቁትን ሰዎች ይወዳቸዋል። ስለ እርሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ወይም ከአባቶች ብሒሎች ወይም ከቤተክርስቲያንና ከቅዱሳን ታሪክ ልታነቡ ትችላላችሁ። በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ የእግዚአብሔር እጅ ለመዳሰስ ስትሞክሩ በጥበቡ በኃይሉና በርኅራኄው ውስጥ እንደምትወዱት ታውቃላችሁ።

አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ
🌿"እግዚአብሔርን ከመፍራት ጋር ያለ ጥቂት ነገር ሁከት ካለበት ከብዙ መዝገብ ይሻላል።"

(ምሳሌ 15: 16)
የትዳር ዋና ዓላማ

አንዳንድ ትዳሮች ለባል፣ ለሚስት፣ ለልጆችና ለሌሎች ሰዎች በረከትን ይዘው ይመጣሉ፡፡ አንዳንድ ትዳሮች ደግሞ ይህን ይዘው አይመጡም፡፡ ይዘው ካለመምጣታቸውም በላይ ለባልም፣ ለሚስትም፣ ለልጆችም፣ ለሌሎች ሰዎችም ችግር ይኾናሉ፡፡

🌱ለመኾኑ የእነዚህ ትዳሮች ልዩነቱ ምን ላይ ነው?
የእነዚህ ትዳሮች ዋና ልዩነቱ ትዳሩን ግብ ባደረጉበት ዓላማ ላይ ነው፡፡ አንድ ወንድና አንዲት ሴት የሚጋቡት የሩካቤ ፍላጎታቸውን ለማርካት ወይም በቁሳዊ ነገር ለመረዳዳት ከኾነ ጋብቻቸው በረከት ይዞ አይመጣም፡፡ ጽድቅን ዓላማ አድርገው ከዚህ ዓለም ወደ ወዲያኛው ዓለም ለመጓዝ ለሚጋቡት ግን ትዳራቸው ለተጋቢዎቹ ብቻ ሳይኾን ለልጆቻቸውም ለሌሎች ሰዎችም ታላቅ የኾነ ደስታን ያመጣል፡፡

እግዚአብሔርም ጋብቻን የመሠረተው ለዚህ ነው - የምንኩስና ሕይወትን መምራት ለማይችሉ ሰዎች ጽድቅን ዓላማ አድርገው እንዲኖሩበት ! ! !

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
@memhrochachn
መምህራችን ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በላከው ሁለተኛ መልእክቱ ምዕራፍ 13 ውስጥ የጠቀሰልንን ሁልንም የፍቅር ዓይነቶች ተግባራዊ እናድርግ።

➡️"ፍቅር ሁልን ይታገሳል፣" ሰዎችን ሁሉ በትዕግስት ቻል።

➡️"ፍቅር አይቀናም፣" በሌሎች ላይ ላለመቅናት እንለማመድ።

➡️"ፍቅር ራሱን አያስመካም፣" አንድ ሰው ሌሎች ሰዎች ሊያገኙት በሚችሉት ነገር ላይ ሊመካባቸው አይገባም።

➡️"ፍቅር አይታበይም፣" እግዚአብሔር አምላክ ትዕቢተኞችን ስለሚቃውምና ለትሑታን ጸጋን ስለሚሰጥ ትዕቢት አደገኛ ማነቆ ነው።

➡️"ፍቅር ክፉ ነገር አያሳስብም፥" ሰውን የሚወድ ሰው በክፋት አይናገርም በትሕትና እንጂ ልክ ጣፋጭ ውኃ እንደሚያመነጭ ንጽህ ምንጭ።

➡️" ፍቅር ብቻየን ይድላኝ አይሰኝም፣" ሰዎች የሚወድ ሰው ራሱን ወዳድ አይደለም ሌሎችን ይወዳል እንጂ፡እርሱ ለእነርሱ መሥዋዕት ይሆናል ያለውን ሊሰጣቸውም ዝግጁ ነው ራስ ወዳድነት የብዙ ችግሮች ምክንያት ስለሆነ እርሱን ከእናንተ አርቁ።

➡️"ፍቅር አይበሳጭም፣" ብስጭት(ቁጣ) የእግዚአብሔርን ጽድቅ ስለማይሰራ አትበሳጩ።

➡️"ፍቅር ስለ ዓመፃ ደስ አይለውም፣" ሌሎች ሰዎችን የሚጎዳ ውድቀት አይመኝም። ሕሊናቸው ንጹህ ለሆኑ ሰዎች ሁሉም ነገር ንጹህ ነው። ንጹሓን ሰዎች ከራሳቸው ይልቅ ሌሎች ሰዎችን ያስቀዳማሉ።
➡️"ፍቅር ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል ፣"ፍቅር ያለው ሰው ሰዎች ስኬት ወይም ሀብት ወይም ደስታ ወይም ልጆች ወይም በሌሎች እግዚአብሔር በሚሰጣቸው በረከቶች ይደሰታል ።ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ ከምያለቅሱም ጋር አልቅሱ።"ሮሜ11፥15

➡️"ፍቅር ሁሉን ይታገሳል ፣" ታጋሽ ሰው ለመሆን ተለማመድ። እጅግ ከባድ የተባሉ ስሕተቶች ላይ ብትወድቅም እንኳን ቁጣህ ፈጥና አትቀጣጠል የሰዎችን ፍቅርና ክብር ታጣለህና። ለመታገስ የሚቻለው ለማፍቀር ሲቻል ነው። ስለዚህ ሁሉንም ነገሮች ሁሉንም ሁኔታዎችና ሁሉንም ሰዎች ያለ ምንም ማማረር ታገሡ።

➡️"ፍቅር ሁሉንም ያምናል፥" ፍቅር ቀላል ነው እንጂ አታላይ አይደለም ፍቅር ጠቢብና አርቆ አሳቢ ነው።ተስፋ የሚያደርገው ለሌሎች ሰዎች መልካምነት ነው ።

➡️" ፍቅር በሁሉ ይጸናል ፣" ከእርሱ ጋር የሕይወት አክሊል ስለሚመጣ ትዕግስትን ተለማመድ። ሌሎች ሰዎችን መቻልም ተለማመድ እነዚህ ሰዎች ችግር ፈጣሪዎች ቢሆንም እንኳ ይህን ስታደርግም ትዕግስትህ መልካም ነገር እንደሚያሰገኝልህ በማወቅ ይሁን።

➡️"ፍቅር ለዘላለም አይወድቅም ፥" የተለያዩ ፈተናዎችና መከራዎች ቢገጥሙም እውነተኛ ፍቅር ፈጽሞ አይወድቅም፡በማንኛውም ፈተና ፊት በጽናት ይቆማል እንጂ: -"ፍቅር እንደ ሞት የበረታች ናትና ፥........ብዙ ውኃ ፍቅርን ይጠፋት ዘንድ አይችልም ፈሳሾችም አያሰጥሟትም ሰው የቤቱን ሀብት ሁሉ ስለ ፍቅር ቢሰጥ ፈጽሞ ይንቁታል።"ምሳ 8፥6-7
ጸሎት ንሰሐና ተምስጦ
አቡነ ሺኖዳ ሳልሳዊ
ደካማነትህን አስታውስ፣ ያን ጊዜ በጣም ጠንቃቃ ትሆናለህ፣ ሊጎዱህ በሚችሉ በትምክህትና በውዳሴ ከንቱም አትሸነፍም።

📚የተሰጠህን በፍቅር የተሞላ የእግዚአብሔርን ቸርነት አስታውስ፣ ይህም በምስጋና የተሞላ ሕይወት እንድትመራ ያደርግሃል፡፡ በእግዚአብሔር ፍቅርና ሥራ ላይ ስትታመን ፍጹም የሆነ እምነት በልብህ እያደገ ይመጣል። ከእግዚአብሔር ጋር ያሳለፍከው ጊዜ ደግሞ በእምነት እንድትኖር ያበረታታሃል።

📚ሞት እንዳለ አስታውስ፣ እንዲሁ በዓለም ያለ ፈተናም እንደሚያልፍ "ሁሉ ከንቱ ነው፣ ነፋስንም እንደመከተል ነው።" መክ. 1፥14 ማለትን ትረዳለህ።

📚 በእግዚአብሔር ፊት መቆምህንና እርሱም እንደሚመለከትህ አስታውስ፣ ያኔ ኃጢአት አትሠራም እግዚአብሔርን ታየዋለህና።

📚 ስለ አንተ የፈሰሰውን የክርስቶስን ክቡር ደም አስታውስ። በዚህም ሕይወትህ ያለውን ዋጋ በእርግጥ ታውቃለህ፤ በዓይኖችህ ፊት የከበረ ይሆናል፣ ስለዚህም በከንቱ በመኖር አታጠፋውም፣ "በዋጋ ተገዝታችኋልና..." 1ቆሮ. 6፥20 እንዲል ቅዱስ ጳውሎስ።

📚በወላጆችህ እምነት በተጠመቅህባት ቦታ ለእግዚአብሔር የገባኸውን ቃል አስታውስ፤ ዲያብሎስን፣ ሥራዎቹን ሁሉ፣ ሐሳቦቹንና ጥበቡን፣ ኃይሉንም ትክድ ዘንድ።

📚 በዚህ ዓለም እንግዳ መሆንህንና ወደ ሰማያዊው ቤትህ እንደምትመለስ
ዘወትር አስታውስ። ያን ጊዜ በዚህ ዓለምና በደስታው ተስፋ ማድረግን ትተዋለህ።

📚በጠባቡ በር መጓዝ ወደ መንግሥተ ሰማያት እንደሚያደርስህ አስታውስ። ሰፊው ደጅ ፊት ለፊትህ ተከፍቶ ብታየው፣ አልፈኸው ሂድ ከእሱም ራቅ፣ በእርሱ የሄዱ እንዳሉ አልቀዋልና።

📚 የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ መሆንህን አስታውስ። በውስጥህ ያለውንም ቅዱሱን የእግዚአብሔር መንፈስ አታሳዝን። ዘወትርም ቅዱስ የእግዚአብሔር ማደሪያ ሁን።

አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ
ጾም ሙሽሪትን ትመስላለች፤ ሙሽሪትን በሠርግ አዳራሽ ኾነው የሚቀበሏት ሰዎች ቤቱን ያስጌጡታል፤ ይሸልሙታል፡፡ ወደ ሠርጉ አዳራሽ የሚገባውን ሰው የሠርግ ልብስ ለብሶ እንደኾነ፣ የቆሸሸ እንዳልኾነ አይተው ያስገቡታል፡፡ እኛም እንዲኽ ልንኾን ይገባናል ብዬ እነግራችኋለኹ፡፡ ልቡናችንን በማንጻት፣ ልል ዘሊል ከመኾን በመራቅ፣ የክፋት እርሾን በማስወገድ፣ ከጾም ጋር አብረው የሚመጡትን የሚያጅቧትን መልካም ምግባራትንም ለመቀበል የልቡናችንን ውሳጤ በመክፈት የምግባር እናት፣ የማስተዋል እንዲኹሉም ለሌሎች ምግባራት ኹሉ ንግሥት የምትኾን ጾምን ልንቀበላት ይገባናል ብዬ እነግራችኋለኹ፡፡ ይኽን ያደረግን እንደኾነ ታላቅ ሐሴት እናደርጋለን፤ ርሷም ቁስለ ነፍሳችንን ትፈውስልናለች፡፡ በሌላ አገላለጽ ብነግራችኁ ሐኪሞች በአንድ ታማሚ ሰውነት ውስጥ ያለውን ቆሻሻ፣ መርዘኛ ፈሳሽን ማስገድ ሲፈልጉ መጀመሪያ የሚያደርጉት ነገር ቢኖር ታማሚው ምግብ ከመውሰድ እንዲቈጠብ ነው፡፡ ታማሚው ለጊዜው ምግብን ከመብላት ካልተከለከለ ሓኪሞቹ የሚሰጡት መድኃኒት እንደተፈለገው ውጤት አይሰጥም፡፡ እኛም ቁስለ ነፍስ ቁስለ ሥጋ የምትፈውሰውን ጾም ስንቀበላት ከዚኽ በላይ ልንኾን ይገባናል ብዬ እነግራችኋለኹ፡፡ ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስን የምንሻ ከኾነ ልቡናችንን ንጹሕና ንቁ በማድረግ ልንወስዳት ይገባናል፡፡ እንዲኽ ካልኾነ ግን ከጥቅሟ ይልቅ ጉዳቷ ያመዝናል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

ጾመ ሐዋርያት (ሰኔ ጸም) ሰኔ 6/2014 ዓ.ም
(JUNE 13/2022 G.C) ይገባል፡፡

@memhrochachn
ሙሉ ገቢው ለደብረ አሚን ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ እድሳት የሚውል #የግዮን_ወንዝ የሚል አዲስ መጽሐፍ በቅርብ ቀን ከሙሽራው ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ ለገበያ ይቀርባል።
2024/05/15 02:31:40
Back to Top
HTML Embed Code: