Telegram Web Link
ደብረ ታቦር ማእከል  106 የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤ ተማሪዎችን ማስመረቁ ተገለጸ፡፡

ሰኔ ፲፮/፳፻፲፯ ዓ.ም

በማኅበረ ቅዱሳን ደብረ ታቦር ማእከል ከ4 እስከ 5 ዓመት ሲያስተምራቸው የነበሩ 106 የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤ ተማሪዎችን  ሰኔ 15 ቀን 2017 ዓ.ም ማስመረቁ ተገልጿል።

በማኅበረ ቅዱሳን የደብረ ታቦር ማእከል  ሰብሳቢ የሆኑት ዲ/ን ዶ/ር ለማ ጉልላት  እንደገለጹት ጠቢቡ ሰሎሞን በተግሣጹ ‘’በለሱን የጠበቀ ፍሬውን ይበላል’’ እንዳለ ከብዙ የልፋት ዓመታት በኋላ የድካማችሁን ፍሬ ላያችሁበት ለዚህች ዕለት ልዑል እግዚአብሔር እንኳን በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ ብለዋል፡፡

ሰብሳቢው አክለውም ‘’ጢሞቴዎስ ሆይ የተሰጠህን አደራ ጠብቅ‘’ ብሎ አባቱ ቅዱስ ጳውሎስ የመከረውን ምክር ተቀብሎ ለአደራ እንደበቃው እንደ ጢሞቴዎስ እናንተም በዚህ የመከራ ወጀብ መካከል የወላጆቻችሁን ምክር፣ የአገራችሁንና የቤተ ክርስቲያናችሁን አደራ ጠብቃችሁ ለዚህ የምረቃ ክብር በመብቃታችሁ እግዚአብሔርንና እርሱ ያከበራቸውን ሁሉ ልናመሰግን ይገባናል በማለት ተናግረዋል።

አያይዘው ለተመራቂዎቹ ባስተላለፉት መልእክት በቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት መዋቅራት ማለትም በሰበካ ጉባኤ፣ በሰንበት ትምህርት ቤት፣ በማኅበረ ቅዱሳን መዋቅር በመግባት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በገንዘባችሁ፣ በጉልበታችሁ እና በዕውቀታችሁ በማገልገል፣ በእውነተኛ ትምህርቷ ጸንታችሁ በመኖር በዘር እና በቋንቋ ለተፈተኑ የቤተ ክርስቲያን አካላት አርአያ እንድትሆኑ፣ በመንፈሳዊ ሕይወታችሁ ዕድገት ለማሳየት እንድትተጉ እና ችግሮቿን ለመፍታት ከጎኗ እንድትሆኑ ሲሉ አሳስበዋል፡፡

በመጨረሻም የአደራ መስቀል በመስጠት መርሐ ግብሩ ተጠናቋል፡፡
ሐረር ማእከል በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ሐረር ጤና እና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ግቢ ጉባኤ የህክምናና የጤና ተማሪዎች ማስመረቁ ተጠቆመ

ሰኔ 15/2017 ዓ.ም

በማኅበረ ቅዱሳን ሐረር ማእከል ግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ዋና ክፍል ሥር ከሚገኙ አምስት ግቢ ጉባኤያት መካከል አንዱ የሆነው  የሐረማያ ዩኒቨርስቲ ጤናና ሕክምና ሳይንስ ኮሌጅ ግቢ ጉባኤ ተማሪዎችን በሐረር መካነ ሥላሴ ካቴድራል ሰኔ 15 ቀን 2017 ዓ.ም አስመርቋል።

በምርቃ መርሐ ግብሩ የሐረር መካነ ሥላሴ ካቴድራል አስተዳዳሪ፣ ካህናት አባቶች፣  የማኅበረ ቅዱሳን ሐረር ማእከል ግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ዋና ክፍል አባላት፣ የማኅበረ ቅዱሳን ሐረር ማእከል አባላት፣ተመራቂ ተማሪዎች እና ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት ተካሂዷል።

የማኅበረ ቅዱሳን ሐረር ማእከል ተመራቂ ተማሪዎች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መዋቅሯን ጠብቀው እንዲያገለግሉ ፣ በኢኮኖሚያዊ ፣ፖለቲካዊ፣ማኅበራዊ አገልግሎት ንቁ ተሳታፊ ሆነው ያስተማራቸውን ማኅበረሰብ  በእኩልነት እና በታማኝነት እንዲያገለግሉ መልእክት አስተላልፏል።

በካቴድራሉ አስተዳዳሪ መልአከ ሰላም ጥበቡ የአደራ መስቀል ለተማራቂ ተማሪዎች ያበረከቱ ሲሆን  በግቢ ጉባኤውና በክፍላት ሲያገለግሉ ለቆዩ የስጦታ መርሐ ግብር ተከናውኗል::
በማኅበረ ቅዱሳን የአሶሳ ማእከል 574 የግቢ ጉባኤ ተማሪዎችን ማስመረቁ ተጠቆመ

ሰኔ ፲፯/፳፻፲፯ ዓ.ም

በማኅበረ ቅዱሳን አሶሳማእከል በአሶሳ ዩንቨርስቲና በአሶሳ ከተማ መንግስት ና ግል ኮሌጆች በመደበኛ ግቢ ጉባኤያት ከዓለማዊ ትምህርታቸዉ ጎን ለጎን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ሲያስተምራቸዉ የነበሩ 574 ተማሪዎችን ሰኔ 15 ቀን 2017 ዓ.ም አስመርቋል።

በምርቃት መርሐ ግብሩ ትምህርተ ወንጌል በመምህራን እና ወረብ በተመራቂ ተማሪዎች ቀርቦ የአደራ መስቀል ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።
ሀዋሳ ማእከል በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ዋናው ግቢ፣ ግብርና ኮሌጅና ሪፈራል ግቢ ሲያስተምራቸው የነበሩ 250 ተማሪዎችን አስመረቀ፡፡

ሰኔ ፲፯/፳፻፲፯ ዓ.ም

የማኅበረ ቅዱሳ ሀዋሳ ማእከል በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ዋናው ግቢ፣ ግብርና ኮሌጅና ሪፈራል ግቢ ሲያስተምራቸው የነበሩ 250 ተማሪዎችን ሀዋሳ ደብረ ምጥማቅ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አስመርቋል።

በማኅበ ቅዱሳን ደቡብ ማእከላት ማስተባበርያ ጽ/ቤት ኃላፊ ቀሲስ እንጅነር አሰፋ ቦረና እንደገለጹት ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ ዕውቅና አግኝቶ ከተመሠረተ ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ በኀላፊነት የተሰጡትን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎችን በግቢ ጉባኤያት የማስተባበር፣ የማስተማር አገልግሎቱን ትናንትም ዛሬም እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

“ቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ የመሪነት ሚናዋን ስትወጣ ማየት” የሚለውን የማኅበሩን ርእይ እውን ለማድረግ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኦርቶዶክሳውያን ተመራቂ ተማሪዎች እንዲመጣ የፈለገው ውጤት በእናንተ ሕይወት ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግና የቤተ ክርስቲያንን ችግሮች ለመፍታት የመፍትሔው አካል ከመሆን አንጻር ከምሩቃን የምንጠብቀው አደራ ቀላል የሚባል አይደለም በማለት ተመራቂዎች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበዋል።

የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ስብሐት ቀሲስ ኪነ ጥበብ ያለው ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
በተጨማሪም በአብነት እና በአስኳላው ትምህርት የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የሽልማት ስነ ስርዓት ተካሂዷል።
2025/07/01 11:46:28
Back to Top
HTML Embed Code: