Telegram Web Link
ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደሆነ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከኣንድ ፈጠረ፤ የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ደረጃ መደባላቸው፤ ቢሆንም ከእያንዳንዳችን የራቀ ኣይደለም›› (የሐ. ሥራ. ፲፯÷፳፮)፤
ፈጣሬ ፍጥረታት እግዚአብሔር ትዕይንተ ዓለምንና በውስጡ የሚገኙ ፍጥረታትን የፈጠረ ኣምላክ ነው፤ እግዚአብሔር የፈጠራቸው ፍጥረታት የሚታዩና የማይታዩ ተብለው በጥቅል በቅዱስ መጽሓፍ ተገልጸዋል፤ የሰው ልጅ ከፍጥረታት መካከል ሆኖ ከኣንድ ወገን የተገኘ እንደሆነ በዚህ ጥቅስ ተጽፎኣል፤

የሰው ልጅ ከፍጥረታት ሁሉ የተለየ ክብርና ደረጃ እንዳለው በቅዱስ መጽሓፍ በተደጋጋሚ ተገልጾኣል፤ ልዩ የሚያደርገውም ከኣፈጣጠሩ ጀምሮ ነው፤
ሰው ልዩ ፍጡር መሆኑን ከሚገለጽባቸው መካከል እግዚአብሔር በሦስትነቱ “ሰውን በኣርኣያችንና በኣምሳላችን እንፍጠር” በሚል ልዩ ኣገላለጽ መፈጠሩ፣ ኣፈጣጠሩም በእግዚአሔር መልክና ኣምሳል መሆኑ፣ በእግዚአብሔር እፍታ ሕያው ነፍስ እንዲኖረው መደረጉ፣ በሥልጣንም የፍጥረታት ሁሉ የበላይ ሆኖ መሾሙ ከሌሎች ፍጥረታት ልዩ ያደርገዋል፡፡
ከዚህ ኣንጻር ሰው በዚህ ዓለምም ሆነ በወዲያኛው ዓለም ከፍጥረታት ሁሉ በላይ ነው፤ የሁሉም ገዥ ነው፤ በተለይም በዚህ ዓለም ከሰው በላይ ሆኖ የፍጡራን ገዥ የሆነ ፍጡር እንደሌለ ሁላችንም የምናየውና የምናውቀው ነው፤
በላይኛው ዓለምም ቢሆን መላእክትን ጨምሮ ሰማይና ምድርን ከነግሣንግሡ እየገዛ ያለው ሰው የሆነ ጌታ ነው፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ የፍጥረት ገዥ ነው፤ እሱ ሰብእናችንን በፍጹም ተዋሕዶ የተዋሓደ በመሆኑ ሰብእናችን በተዋሕዶተ ቃል ኣምላክ ሆኖ የፍጥረታት ሁሉ ገዥ ሆኖኣልና ነው፤
ቅዱስ መጽሓፍም “ወተኰነኑ ሎቱ መላእክት ወሥልጣናት ወኵሉ ኃይል፡- መላእክት፣ ሥልጠናትና ኃይል ሁሉ ተገዙለት” በማለት ይህንን ያረጋግጣል፤ ይህ እግዚአብሔር ለኛ ለሰዎች ያጐናጸፈን ግሩምና ኣስደናቂ ጸጋ ነው፤ ለዚህም ነው “ወሰብእ ይከብር እምኵሉ ፍጥረት፡- ሰው ከፍጥረት ሁሉ ይከብራል” ተብሎ የሚዘመረው፤
•  የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ኢትዮጵያውንና ኢትዮጵያውያት!
እኛ ሰዎች የእግዚአብሔር ክብር መገለጫ ሆነን እንድንኖር በእግዚአብሔር ስንፈጠር በሕይወት እንድንኖር ነው፤ እግዚአብሔር በምድር ላይ በሕይወት ይኖሩ ዘንድ ሰውን ከኣንድ ፈጠረ የሚለው መጽሓፍ ቅዱሳዊ ኣስተምህሮም ይህንን ያመለክታል፤
ሰዎች በምድር ላይ በሕይወት እንዲኖሩ የተፈጠሩ ሆነው እያለ በሕይወት እንዳይኖሩ ማድረግ ከፈቃደ እግዚአብሔር ጋር መጋጨትን ያስከትላል፤በዘመናችን ዓለማችንን እየፈተነ ያለው ተቀዳሚ ፈተና ሰዎች በሕይወት እንዳይኖሩ የማድረግ ዝንባሌ ነው፤
እንደዚህ ዓይነቱ ዝንባሌ በዓለም ባይኖር ኖሮ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቈጠሩ ድሆች ባሉበት ዓለም ለሰው ልጅ ሕይወት ማጥፊያ የሚሆን መሳሪያ ለማምረት ኁልቈ መሣፍርት የሌለው ገንዘብ ኣይወጣም ነበር፤
ይህ ክፉ የዓለም ዝንባሌ እንደ ክፋት ብቻ ሳይሆን እንደ ሞኝነትም የሚያሳይብን ነው፤ማንኛችንም ሰዎች ‹‹ሰው ማጥፋት ይሻላል ወይስ ማዳን›› ተብለን ብንጠየቅ መልሳችን ምን እንደሚሆን ይታወቃል፤
ነገር ግን ኣንፈጽመውም፣ ሞኝነት የሚያሰኘውም እዚህ ላይ ነው፤ የሚጠቅመንንና የመሰከርንለትን ትተን የሚጐዳንንና፣ ያልመሰከርንለትን እንፈጽማለንና ነው፤
ስለሆነም በሕይወት እንዲኖር የተፈጠረውን ሰው በሕይወት የመኖር መብቱን ከመንፈግ መቆጠብ የኣዲሱ ዓመት ትልቁ ኣጀንዳ ኣድርገን ብንወስድ ለሁላችንም ይበጀናልና እንቀበለው እንላለን፤
•  የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን! ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት!
ሰው በሕይወት እንዲኖር በእግዚአብሔር ሲፈጠር እግዚአብሔርን የሚፈልግበትና የሚያገኝበትን ዕድሜና ዘመንም እንደተሰጠው ከተጠቀሰው ክፍለ ንባብ እንገነዘባለን፤ መቼም እግዚአብሔር ሁሉን የፈጠረ በስራ ለስራ እንደሆነ የምንስተው ኣይሆንም፤ እግዚአብሔር ዕድሜና ዘመን ለሰዎች ሲሰጥ ሊሰራበት ነው፤ ስራውም መንፈሳዊና ዓለማዊ ነው፤ ተደምሮ ሲታይ ደግሞ ለሰው ጥቅም የሚውል ነው፤
እኛ ሰዎች በተሰጠን ዕድሜና ዘመን በመንፈሳዊው ስራችን እግዚአብሔርን ፈልገን እንድናገኝ ተፈጥረናል፤ እሱን ማግኘት የማይቻል የሚመስለን ካለንም እሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ ኣይደለም ተብለናልና በመንፈስ ከፈለግነው በመንፈስ እንደምናገኘው መጽሓፉ ያስረዳናል፤ስለሆነም በተሰጠን ዘመን ይህንን ስራ መስራት ይኖርብናል፤
በሌላ በኩል ለኑሮኣችን የሚያስፈልገንን ፍጆታ በበቂ ሁኔታ እንድናገኝ ላባችንን ኣንጠፍጥፈን መስራት ይገባናል፤ ይህም ከሰራን ያለጥርጥር የምናገኘው ነው፤ ሁለቱም የጐደሉብን በኛ ኣስተሳሰብ፣ ኣሰራርና ኣጠቃቀም እንጂ እግዚአብሔር ሳይፈቅድልን ቀርቶ ወይም ነፍጎን ኣይደለም፤ እግዚአብሔር የሰጠን ምድር በልዩ ልዩ ሀብተ ጸጋ የተሞላች እንደሆነች፣ የምንረግጠው መሬትም ወደ ሀብት መቀየር እንደሚቻል የተረጋገጠ ነው፤
ነገር ግን እኛ በምንራመድበት በእግራችን ሥር ያለውን ሀብት ትተን በሩቅ ያለውን ስንመለከት ሁሉን ያጣን ሆነን በችግር ወድቀን እንገኛለን፤ በተለይም እኛ ኢትዮጵያውያን በኣሁኑ ጊዜ እየተፈታተነን ያለው ይኸው የተሳሳተ እሳቤ ነው፤
ኢትዮጵያ የሁላችንም ኢትዮጵያውያን ኣድርገን በማመን በእኩልነት፣ በኣንድነትና በስምምነት ከመጠቀም ይልቅ ያ የኔ ነው ያም የኔ ነው በሚል ኣባባል ምን ያህል ዋጋ እየተከፈለ እንደሆነ እያየን ነው፤ ይህ ግለኝነት ያየለበት ኣስተሳሰብ ገታ ኣድርገን በእኩልነትና በኣብሮነት የሚያሳድገንን ኣስተሳሰብ በእጅጉ ይጠቅመናል፤ ይህንንም የኣዲሱን ዓመት ምርጥ እሳቤ ኣድርገን ብንወስድ የተሻለ መግባቢያ ሊሆን ይችላል፤ ኣዲሱ ዓመት በኣዲስ እሳቤ ካላጀብነው ኣዲስ ሊሆን ኣይችልምና ነው፤ ስለሆነም ኣዲሱን ዓመት መልካም በሆነ ኣዲስ ኣሳብ ፣እግዚአብሔርንና ሰውን በሚያገናኝ ቅዱስ ተግባር፣ በልማት፣ በሰላም፣ በፍቅር፣ በዕርቅና በስምምነት እንድንቀበለው ወቅታዊ ጥሪያችን ነው፤
በመጨረሻም ኣዲሱ ዓመት ለሀገር ሰላምና ልማት፣ ለሕዝቦች ኣንድነትና ስምምነት እንደዚሁም ኣለመግባባትን በፍትሕና  በዕርቅ ለመፍታት ከልብ የምንተጋበት መልካም የስኬት ዘመን እንዲሆንልን እንጸልይ፣ በዚህም መላ ሕዝባችን ጠንክሮ እንዲሰራ ለመላ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ሁሉ ኣባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፤
እግዚአብሔር ኣምላካችን ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ኣሜን

  አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣
                                 
       መስከረም 1 ቀን 2018 ዓ.ም
            አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ

ምንጭ:- የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
44🙏6
Media is too big
VIEW IN TELEGRAM
እንኳን  አደረሳችሁ!
ማኅበረ ቅዱሳን ለሚያስገነባው የልህቀት ማእከል ድጋፍ የሚውል የበረከት ዕቁብ ይሳተፉ! አንድ ዕጣ በወር 500ብር ብቻ።
ለመሳተፍ-https://forms.gle/jkjeZnNBunzKHvp69
ለበለጠ መረጃ-0966636363 ይደውሉ።
ማኅበረ ቅዱሳን።-https://forms.gle/jkjeZnNBunzKHvp69
ለበለጠ መረጃ-0966636363 ይደውሉ።
ማኅበረ ቅዱሳን።
15👍11
ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚገቡ ተማሪዎች አደራ የመስጠት መርሐ ግብር ተካሄደ

መስከረም ፭ /፳፻፲፰ ዓ.ም

ማኅበረ ቅዱሳን ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጋር በመተባበር በ2017 ዓ.ም የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ተፈትነው ውጤት በመጠባበቅ ላይ ለሚገኙ ተማሪዎች አደራ የመስጠት መርሐ ግብር በትናንትናው ዕለት መስከረም 4 ቀን 2018 ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነት በጽርሐ ተዋህዶ ተካሄዷል።

በመርሐ ግብሩ የከፋ ሸካ ቤንች ማጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የሰዋሰው ብርሃን የቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ኃላፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ዶክተር ሙሉጌታ ስዩም የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራር ጉባኤ አባል፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የአራዳና ጉለሌ ክፍለ ከተማ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ሰብሳቢ አቶ ኤልያስ አበበ፣ የደብረ ይድራስ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢና የአዋሽ ካፒታል ባንክ ፕሬዝዳንት በትረ ትጉሃን ዲያቆን ዶ/ር አንዱዓለም ኃይሉ ፣ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ተገኝተዋል።

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የአራዳና ጉለሌ ክፍለ ከተማ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ሰብሳቢ አቶ ኤልያስ አበበ የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን ስለ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት አደረጃጀት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ሰብሳቢው አክለውም ተማሪዎች ዩንቨርስቲ በሚኖራቸው ቆይታ ግቢ ጉባኤን እንዲሳተፉ ያሳሰቡ ሲሆን በዚህም ማኅበረ ቅዱሳን እና አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ኅብረት አብረው እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
17👏1🤔1
ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ዶክተር ሙሉጌታ ስዩም የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራር ጉባኤ አባል በበኩላቸው ”እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ ሐሳቡንም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንደሚደረግ እናውቃለን” (ሮሜ ፰፥፳፰) የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል መነሻ በማድረግ ትምህርት ያስተማሩ ሲሆን ተማሪዎች በውጤታቸው መሠረት በመንግሥትና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲሁም በኮሌጆች ቢመደቡም በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ነውና ይህንን ለበጎ እንደተደረገ በማመንና በመቀበል በተመደቡበት በየትኛውም ሥፍራ በኦርዶክሳዊ መንገድ ሕይወታቸውን መምራት እንዲችሉ ተናግረዋል።

በኩረ ትጉሃን ዲያቆን ዶ/ር አንዱዓለም ኃይሉ የደብረ ይድራስ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢና የአዋሽ ካፒታል ባንክ ፕሬዝዳንት ተማሪዎች ወደ ዩንቨርስቲ በሚገቡበት ወቅት ሊገጥማቸው የሚችለውን ነገሮችና የአገልግሎት ምቹ ሁኔታዎች በተመለከተ ልምዳቸውን ያካፈሉ ሲሆን ተማሪዎች በዓለማዊም ሆነ በመንፈሳዊ ትምህርታቸው በርትተው መሥራት እንዲችሉ መልእክት አስተላልፈዋል።


አቶ አምደሥላሴ ሙሉጌታ በማኅበረ ቅዱሳን የሕዝብ ግንኙነትና ትብብር አገልግሎት የቅድመ ግቢ ጉባኤ ኃላፊ ማኅበረ ቅዱሳን ከሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጋር በጋራ በመሆን በርካታ ሥራዎችን መሥራታቸውን ገልጸው ተማሪዎች በቀለም ትምህርት ውጤታማ እንዲሆኑ፣ በመንፈሳዊ ሕይወት ራሳቸውን ጠብቀው በግቢ ጉባኤ አገልግሎት እንዲሳተፉና የተዘጋጀላቸውን ኮርሶች አጠናቀው እንዲወጡ አሳስበዋል።

በመጨረሻም የከፋ ሸካ ቤንች ማጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የሰዋሰው ብርሃን የቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ኃላፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክትና አባታዊ ቡራኬ ሰጥተዋል።👇👇👇👇👇👇👇
የማኅበረ ቅዱሳን የማኅበራዊ ሚዲያ አውታሮች ይቀላቀሉ
ቴሌግራም፡- http://www.tg-me.com/mkpublicrelation
የማኅበረ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎት፡- http://www.facebook.com/eotcmkidusan/
ድረገጽ፡- http://www.eotcmk.org
ዩ ቲዩብ፡- http://www.youtube.com/user/EOTCMK
:- https://www.youtube.com/@-zemawetibebzmk7905
27
2025/09/15 20:01:09
Back to Top
HTML Embed Code: