Telegram Web Link
በደቡብ ማእከላት ማስተባበሪያ አዘጋጅነት በወላይታ ሀገረስብከት በሚገኘው ካህናት ማሠልጠኛ  ለስድስት  ተከታታይ ቀናት  ሲሰጥ የቆየው የደረጃ ሁለት ተተኪ አመራር ሥልጠና  መጠናቀቁ ተገለጸ።

ሰኔ ፲፬/፳፻፲፯ ዓ.ም

በማኅበረ ቅዱሳን ደቡብ ማእከላት ማስተባበሪያ አዘጋጅነት ከተለያዩ የመንግስት ዩኒቨርሲቲ ለተዉጣጡ ለግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ለስድስት  ተከታታይ ቀናት  እየተሰጠ የቆየው የደረጃ ሁለት ተተኪ አመራር   ሥልጠናና ውይይት በዛሬው ዕለት ብፁዕ  አቡነ ይስሐቅ የወላይታ ሀገረስብከት ሊቀጳጳስ በተገኙበት  የማጠቃለያ መርሐ ግብር በርእሰ አድባራት ወገዳማት ደብረ መንክራት አቡነ ተክለሃይማኖት አንድነት  ገዳም መከናወኑ ተገልጿል ።

ሠልጣኞች  ከአርባ ምንጭ ፣ ከወላይታ ፣ ከጂንካ  ፣ከሆሳዕና ማእከላት የተወጣጡ ቁጥራቸው ከ50  በላይ እንደሆኑ ተጠቁሟል ።

የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የመሪነት ሚና ትላንት፣ ዛሬና ነገ ፣ ኦርቶዶክሳዊነት ሕይወቱና ክህሎቱ ፣የአኃት አብያተ ክርስቲያናት ተሞክሮ፣ ሴኩላሪዝም ከኦርቶዶክስ እሳቤና ኑሮ አንጻርና ሌሎች ሥልጠናዎች እንደሰጠም ተመላክቷል።

በዛሬው ዕለት በተካሄደው  በማጠቃለያ መርሐግብር የወላይታ ሀገረስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ  " የተካሄደው ሥልጠና እጅግ ጠቃሚ የሆነና ሊበረታታ የሚገባው መሆኑን ጠቅሰው   " የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው በማለት ሠልጣኞች በተሰጠው ሥልጠና  እግዚአብሔርን በመፍራት፣ ሕይወታቸውን በመምራት፣   መክሊታቸውን በማትረፍ በሚሄዱበት ሁሉ ቅድስት  ቤተ ክርስቲያንን፣ ወላጆቻቸውንና አገራቸውን እንዲያገለግሉ የአደራ መልእክትና አባታዊ ቡራኬ ሰጥተዋል።
በማኅበረ ቅዱሳን መቱ ማእከል በሁለት ግቢ ጉባኤያት ያስተማራቸውን ተማሪዎች ማስመረቁ ተገለጸ።

ሰኔ ፲፮ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም

በማኅበረ ቅዱሳን መቱ ማእከል በመቱ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤ እና በጥምር ግቢ ጉባኤ ሲያስተምራቸው የቆዩ ከ500 በላይ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎችን ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም በቦቶ ደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ማስመረቁ ተገልጿል።

በማኅበረ ቅዱሳን የመቱ ማእከል ሰብሳቢ መ/ር ጌትነት ሰይፉ እንደገለጹት ተመራቂዎች ከግቢ ወጥተው ወደ ተለያዩ ቦታዎች ሲሄዱ ቤተ ክርስቲያን የመሪነት ሚናዋን እንድትወጣ በሚችሉት ሁሉ የቤተ ክርስቲያንን መዋቅር ማገዝ ይገባል ብለዋል።

በመጨረሻም ተመራቂዎች በአባቶች ቡራኬና የአደራ መስቀል ተቀብለዋል።
ዓለም ዓቀፍ የግቢ ጉባኤ ምሩቃን መርሐ ግብር መከናወኑ ተገለጸ

ሰኔ ፲፮/፳፻፲፯ ዓ.ም

በማኅበረ ቅዱሳን የሕዝብ ግንኙነትና ትብብር አገልግሎት አዘጋጅነት ዓለም ዓቀፍ የግቢ ጉባኤ ምሩቃን መርሐ ግብር በትናትናው ዕለት ሰኔ 15 ቀን 2017 ዓ.ም መካሄዱ ተገልጿል።

በጉባኤው ከተለያዩ ግቢ ጉባኤያት የተዉጣጡ ከ300 በላይ ተሳታፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የመርሐ ግብሩ ዓላማ የሚመረቁ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ተልእኮ ተኮር አገልግሎት ይዘው የሚሠሩበትን ዕድል ማሳደግና ከግቢ ጉባኤ በኃላ ወደ ቤተክርስቲያን መዋቅር ገብተው እንዲያገለግሉ ለማስቻል የተዘጋጀ እንደሆነ ተጠቁሟል።

በዕለቱ የልምድ ልውውጥ፣ መዝሙር የተከናወነ ሲሆን ትምህርተ ወንጌል በመጋቤ ሐዲስ መምህር እንዳልካቸው መሰጠቱ ተመላክቷል።
በመርሐ ግብሩ ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ተገኝተው ያላቸውን ልምድ እና ተሞክሯቸውን ለወጣቶች ያጋሩ ሲሆን “ከልጅነቴ ጀምሮ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በፈሪሐ እግዚአብሔር ያደግሁ መሆኔ ለስኬቴ መሰረት ነው ብለዋል።

የሁለት ኦሎምፒክ የድል ወርቆቼን የሰጠሁት ለእንጦጦ ኪዳነ ምህረት ነው ያሉት አትሌቱ በየወሩም እንደማይቀሩና እሷ ለእኔ ብዙ ነገሬ ናት ብለዋል።

እኔ በሰከንድ ሚሊዮኖችን እንዳገኘሁ ሁሉ በሰከንድም ብዙ ሚሊዮን የሚያወጣ ሀብት አጥቻለሁ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጋር በመሆኔ ሁሌም አሸንፋለሁ ሲሉም ገልጸዋል።


ሻለቃ ኃይሌ በመርሐ ግብሩ ወጣቶች እግዚአብሔርን በማመን የትኛውንም መሰናክል በቀላሉ ማለፍ፣ጠንካራ የማሸነፍ ስሜት ሊኖራቸው እንደሚገባ ከልምዳቸው ተነስተው በመግለጽ በተለይ ከሥራ ፈጠራ እና ከባሕል አንጻር ጽናትና ብርታትን ለማግኘት ከፊት ይልቅ አሁን መጠንከር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
አትሌቱ አክለውም በተሰማራችሁበት የሥራ መስክ ታማኝ መሆንና ሥነ ምግባር መላበስ እንደሚገባ አመላክተዋል።


በመጨረሻም የማኅበረ ቅዱሳን ሚዲያ ማእከልን ጎብኝተዋል።
2025/06/30 15:57:10
Back to Top
HTML Embed Code: