እራት በዚህ መልኩ ተሰናድቷል

ስለ ጌታ ልደት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ምን አሉ?

    እራት- ፪ [27/04/15]

👉 "በማሕጸን ሕጻናትን የሚፈጥራቸው እርሱ ሕጻን ሆነ። ብርሃንን የሚጎናጸፍ እርሱን በጨርቅ ጠቀለሉት። እንደ ምስኪን በድሃ ቤት አደረ። እንደ ንጉሥ እጅ መንሻን ያመጡለት ዘንድ ሐዋርያትን ላከ። ላም ጌታውን እንዲያውቅ የሚያደርገው እርሱ በበረት ተኛ እንደ ሕጻን አደገ።" [ቅዳሴ ዘዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ]

👉 "አቤቱ ጌታ ሆይ ምሕረትህ በየቀኑ የሚሆን ከሆነ በዚህች ልዩ በሆነችዋ በዛሬዋ ቀን ምንኛ ይበዛ! ቀናት ሁሉ ከዚህች ከምታንጸባርቀዋ ቀንህ በረከትን ያገኛሉና ሁሉም በዓላት ከዚህች ቀን ውበትና ጌጣቸውን ያገኛሉ። አቤቱ በዚህች የይቅርታህ ቸርነት የተደረገባትን ዕለት አብዛልን። ጌታ ሆይ ይህቺን ቀን ከቀናት ሁሉ አብልጠን እናከብራት ዘንድ እርዳን" [ድርሳነ ኤፍሬም ገጽ.135]

👉 "ምን እላለሁ? ምንስ እናገራለሁ? ከዘመን በፊት የነበረ እርሱ ትንሽ ሕጻን ሆኗልና እኔ ፈጽሜ አደንቃለሁ። ከሰማየ ሰማያት በላይ የሚሆን በዘላለማዊ ዙፋን የሚኖር እርሱ በበረት ተጣለ ከሥጋዌ ቀድሞ አይዳሰስ የነበረ አንድ እርሱ በምድራዊያን እጅ ተዳሰሰ። ኃጢአትን የሚያስተሠርይ እርሱን በጨርቅ ጠቀለሉት::" [ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ]
እንደምን አደራችሁ?

የዛሬው ቁርስ በዚህ መልኩ ተሰናድቷል።

ስለ ጌታችን ልደት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ምን አሉ?

     3ኛ ቀን - ቁርስ ፫ [28/04/15]

👉 "ሰማይ ይስማ ምድርም ታድምጥ የሰማይም መሠረቶች ይደንግጡ። በአባቱ ፈቃድ ወረደ። በማርያም ዘንድ እንግዳ ሆነ። እግዚአብሔር በንጹህ ድንግልናዋ ተወለደ:: በእንስሳት በረት ተጨመረ። የንግሡንም እጅ መንሻ ተቀበለ ከእናቱ ጡት ምግብን እየለመነ እንደ ሕጻናት አለቀሰ። " የዲዮስቆሮስ ቅዳሴ

👉 "ወልድም ኃጢአት እንደበዛች ባየ ጊዜ በማይነገር በማይመረመር ግብር ወርዶ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ማሕጸን አደረ። ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀንም በማህጸኗ ተወሰነ። በርሷ አድሮ ሊዋሐደው የፈጠረውን ፍጹም ሥጋን በአብ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ከእርሷ ነሳ። ... የምናምንበት ሃይማኖታችን ይህ ነው። በሐሰት አልተወለደም በእውነት በሥጋ ተወለደ እንጂ። በሐሰት አልታመም በእውነት በሥጋ ታመመ እንጂ።" [ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ አትናቴዎስ]

👉 "እርሱ የቋንቋዎች ሁሉ ባለቤት ሲሆን ከማርያም አንደበት እንደሌለው ሕጻን ተወለደ።  እርሱ ከዓለማትና ፍጥረታት ሁሉ በፊት የነበረ ሲሆን የዮሴፍ ልጅ ተባለ። ሰማያዊ የሆነ እርሱ ግን የጥበቦች ሁሉ ጥበብ የሆነ ለሁሉ የሚበቃ ጥበብ አለ። [ቅዱስ ኤፍሬም]
ለዛሬ የማይረሳ አጭር የምሳ መልዕክትም አለን
አጭር የምሳ መልዕክት

ጌታችን ሲወለድ በጎችን ይጠብቁ የነበሩት እረኞች በዚያ ሌሊት በጎችን የመጠበቃቸው ምክንያት ለኦሪት መስዋዕት ሊቀርቡ የሚያስፈልጉ ስለሆኑ አውሬ እንዳይበላቸው  ነው። ለኦሪት መስዋዕት የሚሆኑትን በጎች በሚጠብቁበት በዚያች ሌሊት ግን የሐዲስ ኪዳኑ መሥዋዕት እውነተኛው [አማናዊው] በግ  ኢየሱስ ክርስቶስ ተወለደ።

ተወዳጆች ሆይ! እኛስ ጌታ በተወለደበት በዚህ ዕለት ስንቶቻችን ነን ሕይወት የማናገኝባቸውን በጎቻችን እየጠበቅን እየተንከባከብን ያለነው? በዓሉን በጭፈራ በዝሙት በስካር ለማክበር ያቀድን ስንቶቻችን ነን? ዛሬም የጌታን ልደት አስበን ከመላዕክት ጋር እንድንዘምር ቤተ ክርስቲያን ኑ ልጆቼ ብላ ትጠራናለች።

በቤተ ክርስቲያን ተገኝታችሁ በምትሰሙትና በምታዩት ሁሉ ደስ ተሰኝታችሁ እንደ እረኞቹ እግዚአብሔርን እያመሰገናችሁ ትመለሳላችሁ!

"እረኞችም እንደ ተባለላቸው ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ ተመለሱ።" ሉቃ.2:20

አደራ የጌታን ልደት እንድንዘነጋ በሚያደርግ የዘፈን የስካር የጭፈራ የዝሙት በሆነው የሰይጣን ወጥመድ ውስጥ አንውደቅ!
       
       "የሚሰማ ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ" ማር.4:23

ለሌሎችም እንዲዳረስ Share አድርጉ።
እንደምን አመሻችሁ?

የዛሬው እራት በዚህ መልኩ ተሰናድቷል


እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳችሁ አደረሰን!

3ኛ ቀን- እራት ፫  [28/04/15]

👉 "ከአብ የማይለይ ረጅም ፈትል ሰማይና ምድርን የፈጠርህ በፈቃድህ ከሰማይ ወረድህ የድንግል ማሕጸን ወሰነህ የድሆች ልጅ ትንሽ ብላቴና ገሊላዊት አቀፈችህ ነፍሷን አከበርህ ስጋዋንም አነጻህ አጸናሃት ባንተ አልደነገጠችም። በቤተልሔም ተወለድህ እንደ ሰውም ታየህ።" የያዕቆብ ዘሥሩግ ቅዳሴ

👉 "የዛሬዋ ዕለት እግዚአብሔር በሥጋ የተወለደባት እለት ናት። በዚህችን ዕለት በዘመዶች ሞት፣ በበሽታ፣ በሀብቱ መጥፋት የሚያዝን፣ የሚያለቅስ ሰው በሰማያት ደስታ የለውም። በወንድሙ ቂም የያዘ፣ የተጣላ በዚህችም ዕለት ይቅር ያላለ ይህ ዐሥራ አራት እልፍ ከአራት ሺህ ሕጻናትን የገደለ የሄሮድስ ወንድም ነው። በዚያች ዕለት ሰላምን ለማድረግና ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ግን ከሄሮድስ የሸሸ ክርስቶስን ይመስለዋል። በዚህችን ዕለት ርኅራኄን፣ ምጽዋትን የሚያደርግ እጣው ከሰብአ ሰገል ጋር ይሆናል።" [ርቱዓ ሃይማኖት ገጽ.42]

👉 "እርሱ በአብ ዕሪና ሳለ በድንግል ማሕጸን ተወሰነ። ከእርሷም ተወለደ። በእናቱ ክንድ ላይ ሳለ በነፋስ ክንፍ ይመላለስ ነበር። መላዕክትም ይሰግዱለት ነበር። " ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ኤራቅልስ


አዘጋጅ:-  ተክለ ማርያም [ጅማ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት]
እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሰን!

በጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ተመስጦ [Contemplation On Nativity Of Our Lord and Savior Jesus christ]
       
        ክፍል- ፩

👉 በጌታችን የልደት በዓል ሰማያዊው ንጉስ እኛን ለማዳን የወረደበት የአምላካችንን ትሕትናውንና ፍቅሩን ያየንበት ነው። ይህን የአምላካችንን ፍቅር ትሕትና ሰው ሆነን ካላሳየን በዓሉን ማክበራችን ምሉዕ አይሆንም። ባልንጀራችንን ጠልተን ቂም በቀል ቋጥረን ቅናት ትዕቢት ተሸክመን ስለ ፍቅር አምላክ መምህረ ትህትና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት መናገር ራስን ማሞኘት ይሆንብናል።

👉 ልክ ሰብዓ ሰገል በጌታችን ልደት ቀርበው ስጦታዎችን እንዳቀረቡለት በንስሐ የተሰበረ ልባችንን ቸርነቱን ዘንግተን በበደል ላይ በደል ጨምረን በማሳዘናችን በመጸጸት የእንባ መባን ማቅረብ ይገባናል።  ዳግመኛም ሰብዓ ሰገል ቀድሞ በመጡበት መንገድ ሳይሆን በሌላ መንገድ ወደ ሀገራቸው እንደ ተመለሱ [ማቴ.2:12] በኃጢአት እግዚአብሔርን በማሳዘን የመጣንበትን መንገድ ትተን በሌላይቱ ቅድስናን በምትሰጠው የንስሐ መንገድ ልንመለስ ይገባናል።

👉 በዓለ ልደቱን ስናከብር በመርገም በኃጢዓት በፍዳ በጉስቁልና ተይዘን በነበርንበት ዘመን በመኃሪነቱ ጌታችን ወደ ምድር መጥቷል አማኑኤል በሚል ስመ ስጋዌ ተዛምዶናል። እኛም ከአምላካችን መኃሪነትና ፍቅር ተምረን እግዚአብሔር ከኛ ጋር እንደሆነ ሁሉ እኛም ሰው ከሌላቸው ከደካሞች ከነዳያን ጋር ልንሆን ነገረ ልደቱን በሕይወታችን ጭምር ማሰብ ይገባናል። 

👉 ስለ በዓሉ ስናስብ የአንድ ቀን ሁነት ወይም ክስተት ብቻ ሆኖ የምናልፈው አይደለም የልደቱን ነገር እመቤታችን በልቡናዋ ትጠብቀው ነበር በማለት ወንጌሉ እንደሚነግረን እኛም የጌታችንን በዓላት ስናስብ ዛሬ በተመስጦ ነገ ደግሞ በሌላ ማንነት  ሳይሆን ዘውትር በልቡናችን እያሰብን ልንኖር ያስፈልጋል።

ክፍል -፪ ይቀጥላል...
Contemplation on The Nativity of Our Lord and Savior Jesus Christ

ክፍል ሁለት

👉 በልደቱ ጊዜ ሁለት አካላት ጌታችንን አግኝተዋል የመጀመሪያዎቹ ሰብዓ ሰገል ሲሆኑ ሁለተኛዎቹ ደግሞ የበጎቹ እረኞች ናቸው። እኚህ የበጎች እረኞች የተባሉት ሰዎች የሚያግዱት በጎችን ነው፡። በዚያች ሌሊት በጎችን ለማገድ ያደረጋቸው ምክንያት በጎቹ ለኦሪት መስዋዕትነት የሚቀርቡ ስለሆነ በአውሬ እንዳይበሉ በእረኞች ይጠበቁ ነበር። ለኦሪቱ መስዋዕት የሚሆኑትን እረኞች በሌሊት ሲጠብቁ  አማናዊው በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ተወለደ። እኛስ አማናዊው በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ተወልዶ የድሮ በጎቻችንን ለመሰዋት የድሮ በግ ዝሙት ዳንኪራ ዘፈን ውስጥ ያለን ስንቶቻችን ነን?

👉 እረኞች የጌታችንን ልደት ለመስማት ከ ሰብዓሰገል የቀደሙ ሆነዋል። ሰብዓ ሰገል ባለ ዕውቀት ባለ ጥበብ ናቸው ረጅም ጉዞን ካደረጉ በኋላ ነው ጌታችንን ያገኙት ለርሱ ስጦታንም ያቀረቡት ምንም የማያውቁት የዋሃን የሆኑት የሆኑት እረኞች ግን የጌታችንን ልደት በቅርብ ርቀት ነው የተረዱት። ይህ የሚያስተምረን ሌላው ነገር ቢኖር ወደ እግዚአብሔር ለመድረስ ሁለት መንገዶች ያሳየናል የመጀመሪው ልክ እንደ ሰብዓ ሰገል ረጅሙና አድካሚው በጥበብና በእውቀት የሚገኘው መንገድ የተጓዙ ሲሆኑ ሁለተኛው ደግሞ ያልተማሩ ነገር ግን የዋሀን የሆኑት እረኞች የተጓዙበት የትህትና እና የየዋህነት መንገድ ነው። እግዚአብሔርን በቀላሉ ለማግኘት የየዋኅነትን የትህትናን መንገድ መከተል ይገባል ሲል ነው።

👉 ጌታችን የተወለደባት ቤቴልሔም ሌላው ጉዳይ ነው። ። በቤቴልሔም እንስሳት ለጌታችን እስትንፋስን ገብረውለታል። ሰው ግን ጌታችንን እያሳደደ ነበር። ሰው ያሳደደውን አምላክ እንስሳት እስትንፋስ ገበሩለት። መላዕክት መጥተው አመሰገኑ ብስራትን አደረጉ መላዕክት ሰው ሰላም በማግኘቱ ደስ ይሰኛሉ። ለኛ ብሎ የመጣውን አምላክ መላዕክት ደስ ሲሰኙበት ለኛ ብሎ የመጣውን አምላክ ግን ከልደቱ አንስቶ እስከ ሞቱ ድረስ ያሳደደው ሰው ነው። የጌታችን ፍቅር በምን ይገለጣል? ላድነው ብመጣ አሳደደኝ ብሎ ሰውን ከመውደድ ያልተመለሰ አምላካችን እንደምን ያለ ነው?

👉 የጌታችን ትዕግስት የተገለጠበት ሌላው ጉዳይ ጌታችን አምላክ ሆኖ ሳለ ወዲያው ልደግ በቅጽበት ልደግ አላለም ወንጌል በጥቂት በጥቂቱ አደገ አለን። 9 ወር በማህጸን ቆየ። ቅዱስ ኤፍሬም ይህን ይዞ  አትሰላቹ ደካማ አትሁኑ ጌታችን ለመወለድ አምላክ ሆኖ ሳለ ዘጠኝ ወርን በማህጸን ታግሶ የለምን? በክፉዎች አይሁድ መሃል 30 ዓመት ቆይቶ የለምን? በማለት ይናገራል።

ተክለ ማርያም [ጅማ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት]
ጥያቄ:- ቅዱሳንን_አማልዱን ማለት _መናፍስት_ጠሪነት_ነውን_ነውን?

መልስ

#1ኛ. ተቃዋሚዎች የሞቱትን መጥራት መናፍስት ጠሪነት ነው። በህይወተ ስጋ የተለዩ ቅዱሳንንም መጥራት አማልዱን እርዱን ማለት ያው መናፍስት ጠሪነት ነው በማለት ይናገራሉ፡፡ በመጀመርያ የተሳሳተ ሎጂክን ተጠቅመው ለመናገር መጀመራቸው ውጤቱንም [ድምዳሜያቸውን] የተሳሳተ ያደርግባቸዋል፡፡
ለምሳሌ፦
👉 በጋብቻ (Marriage) ውስጥ የግብረ ስጋ ግንኙነት አለ::
👉 በአስገድዶ መድፈር (Rape) ውስጥም የግብረ ስጋ ግንኙነት አለ፡፡

ከዚህ ተነስተን ጋብቻ ማለት አስገድዶ መድፈር ነው ወደ ሚል ድምዳሜ መድረስ ጤናማነት አይደለም፡፡ መናፍስት ጠሪዎች ከሞቱ ሰዎች ጋር መነጋገርን ከቅዱሳን አማላጅነት ጋር የሚቀላቅሉም ተቃዋሚዎች አካሄዳቸው ተገቢ አለመሆኑን ሊያውቁ ይገባል፡፡

#2ኛ. ግኖስቲኮች የተባሉ በመጀመርያዎቹ ክፍለ ዘመናት የተነሱ መናፍቃን  የሚታየውን ግዙፉን ዓለም የፈጠረው ታሕታዊውና ክፉው አምላክ ነው ይሉ ነበር፡፡ ረቂቁንና የማይታየውን አምላክ የፈጠረው ሉዓላዊውና ደጉ አምላክ ነው በማለት ያስተምሩ ነበር፡፡  ሥጋ ግዙፍ ነገር ሁሉ በክፉ አምላክ የተፈጠሩ ናቸው ብለው ስለሚያምኑ ሥጋን የኃጢአትና የርኩሰት ምንጭ ነው ይላሉ፡፡ ሰው በመባል የሚታወቀውና ሰብአዊ ክብርም ያለው ነፍስ እንጂ ሥጋ አይደለም በማለት ያስተምራሉ፡፡ ከዚህም የተነሳ በዚህ ዓለም መዋለድ መራባት ኃጢአት ማብዛት ነው በዚህ ፋንታ ከዚህ ለመራቅና ነፍስና ሥጋን ለመለያየት የሚያበቃ ትኅርምት በቀኖናቸው ያዛሉ፡፡ [የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በአለም መድረክ ገጽ. 58: አባ ጎርጎርዮስ] ስለዚህም አብዝተው የመጾማቸው ስጋቸውን የማድከማቸው አላማም ይህ ነበር፡፡ እኛ ክርስቲያኖች ግን ስንጾም ፈቃደ ስጋን ለፈቃደ ነፍስ ለማስገዛት እንጂ እንደ ግኖስቲኮች ሥጋ ከክፉ አምላክ የተገኘ ነውና ስጋን መጉዳት ይገባል በሚል መርሕ አይደለም፡፡ ከጌታ ከነቢያት ከሐዋርያት የተማርን እኛ ምንጾመው ስለ ጽድቅ ሰይጣንን ድል ለመንሳት በቅድስና ለማደግ ነው፡፡ ታዲያ ግኖስቲኮችም ስለ ጾሙ እኛም ክርስቲያኖች ስለጾምን መጾም ግኖስቲካዊነት ነው ያስብላልን?  እናስተውል፡፡ ግኖስቲኮች መጾምና የክርስቲያኖች ጾም ከምግብ ስለ ተከለከሉ ብቻ አንድ ነው ሊባል እንደማይችል ሁሉ ወደ በሕይወተ ስጋ ወደ ተለዩ ቅዱሳን መጸለይም መናፍስት ጠሪነት ነው አያስብልም፡፡

#3ኛ. በኖኅ ዘመን የነበረውን የጥፋት ውሃ አስመልክቶ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ባሉ በሌሎች አረማውያን ዘንድ ሌላ ታሪክ ተሰጥቶት እንደነበር እንመለከታለን፡፡ ለምሳሌ ያህል፦ በግሪኮች ዘንድ ጁፒተር የተባለው ጣዖት (The God Jupiter) ጻድቁ ዲኦካልዮንን (Deocalion) ከሚስቱና ከመላው ቤተሰቡ ጋር ወደ መርከብ እንዲገባ አዘዘው፡፡ መረከቡ ፓርታሱስ በተባለ ተራራ ላይ ባረፈ ጊዜ ርግብ ዝናሙ ማቆሙን ነገረችው፡፡እርሱም የምስጋና መስዋዕት ለመሰዋት ከመርከቡ ወጣ፡፡ (መድሎተ ጽድቅ ገጽ 427-428፤ Genesis Fr. Tadros Y. Malaty page 80-81) ተብሎ ይተረካል፡፡ ታዲያ ታሪኩ ተመሳሰለ ተብሎ በመጽሐፍ ቅዱስ የተዘገበው የኖኅ ታሪክ ከአረማውያን ነው የመጣው ሊባል ነውን? የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪክ ከግሪክ Mythology ጋር እያመሳሰሉ እንደሚጽፉት አላዋቂዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነተኛነት ልንጠራጠር ወይስ የአረማውያንን ትምህርት ከአማናዊው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር ልናመሳስል ነውን?  እንደዚሁ ሁሉ የቅዱሳንን አማላጅነትን ከመናፍስት ጠሪነት ጋር ለማመሳሰል የሚጥሩ ሰዎችም የቅዱሳን ምልጃን ከመናፍስት ጠሪነት የመጣ ነው ለማለት  የሄዱበት መንገድ ተገቢ አለመሆኑን ይወቁ፡፡

#በመጨረሻም በህይወተ ስጋ ከተለዩ ቅዱሳን ጋር መነጋገር መጸለይም ሆነ መገናኘት መናፍስት ጠሪነት ከተባለ በታቦር ተራራ ላይ "እነሆም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው፡፡" ማቴ.17:3 ፤ "ኤልያስና ሙሴም ታዩአቸው፡፡ ከኢየሱስም ጋር ይነጋገሩ ነበር፡፡" ማር. 9:4  በማለት ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከብዙ አመታት በፊት በህይወተ ስጋ ከተለየው ከሙሴ ጋር መነጋገሩ ስህተት ነበር ሊሉ ነውን? ወይስ በተራራው ላይ የነበረው ንግግር መናፍስት ጠሪነት ነው ሊባል ነው? ማስተዋሉን ያድልልን!

ተክለ ማርያም [ጅማ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት]
በምስጢረ ጥምቀት ላይ ጥያቄዎች

ጥያቄ:- ተቃዋሚዎች ያላመነ ይፈረድበታል እንጂ ያልተጠመቀ ይፈረድበታል አይልምና ለመዳን መጠመቅ አያስፈልግም ይላሉ

መልስ:-ጥምቀት ለመዳን የማያስፈልግ ቢሆን ኖሮ ያመነ ብቻ ይድናል በተባለ ነበር። ወንጌሉ ግን በግልጽ ያመነ  ብቻ ሳይሆን "ያመነ የተጠመቀም" በማለት ነው የሚገልጸው።
በመጀመርያ ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ስንመለከት ከቁጥር. 15 ላይ ጌታችን ለደቀመዛሙርቱ ወንጌልን ለፍጥረት እንዲሰብኩ ካዘዛቸው በኋላ ነው የተናገረው። ቅዱስ ጳውሎስም "እንግዲያስ እምነት ከመስማት  ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው።" ሮሜ. 10:17 እንዳለ አንድ ሰው ለማመን የእግዚአብሔርን ቃል መማር መስማት አለበት። ለዚህም ነው "ያመነ የተጠመቀ ይድናል" ከማለቱ በፊት ጌታችን ወንጌልን  ለፍጥረት ስበኩ ብሎ ያዘዛቸው። ማር. 16:15:: ጌታችን ያመነ ብቻ አይደለም ያለው "ያመነ የተጠመቀም ይድናል" ነው ያለው:: ስለዚህ በመጀመርያ እምነትን ብቻ እንዳላለ እናስተውል። ቀጥሎ ያላመነ
ይፈረድበታል ያለው ማመን ለሁሉ መሰረት በመሆኑ እንጂ ጥምቀት የማያድን [ለመዳን የማያስፈልግ] ስለሆነ አይደለም። ያላመነ ሰው ስለ መጠመቅ ሊያወራ አይችልምና ወንጌልን ስበኩ ብሎ የላካቸው የሐዋርያትን ቃል ሰምቶ ለማመን ያልበቃን ሲገልጽ ስለዚህ ያላመነ ይፈረድበታል አለ። በቅዱስ ጴጥሮስ
ስብከት ልባቸው ተነክቶ ካመኑ በኋላ ሕዝቡ የጠየቁት ጥያቄ "ምን እናድርግ?" የሐዋ.2:37 የሚል ነው። ቅዱስ ጴጥሮስም "ኃጢአታችሁ ይሰረይ ዘንድ ተጠመቁ በማለት ነው ያዘዛቸው። የሐዋ. 2:38:: ስለዚህ
አንድ ለማመን የደረሰ ሙሉ የሆነ ሰው ከመጠመቁ በፊት ማመን ይቀድማልና ነው። ያላመነ ሰው ግን እንዴት ብሎ ይጠመቃል ስለዚህ ነው ያላመነ ይፈረድበታል ያለው። ማመን መሠረት ነውና። መጠመቅ ከውሃና ከመንፈስ መወለድ እንደሚያድን ጌታችንም "እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ከውኃና
ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግስት ሊያይ አይችልም::" ዮሐ. 3:5 ብሏል:: ስለዚህም በጥምቀት ከውሃና ከመንፈስ በመወለድ የእግዚአብሔር ልጅ መሆን ለመዳን የሚያስፈልግ ነው ማለት ነው። ቅዱስ ጴጥሮስም "ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል።" 1ኛ ጴጥ.3:21 በማለት ጥምቀት እንደሚያድን በግልጥ ቃል ነግሮናል።

ይቀጥላል...

ተክለማርያም [ጅማ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት]
"ያመነ የተጠመቀም ይድናል" ተብሏልና "ያመነ" ብሎ ስለሚጀምር እምነት ይቀድማል ከዚያም ጥምቀት ይከተላል የሚሉ  ሕፃናትም ለማመን አልበቁምና ማጥመቅ አይገባም የሚሉ አሉ

[የሕጻናት ጥምቀት- Paedobaptism]

👉 በመጀመርያ በራሳቸው ቅደም ተከተል አበጅተው እምነት ይቀድማል ካሉ በማቴ 28:19  ላይ "እንግዲህ ሂዱ አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኀቸው ያዘዝኀችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኀቸው ደቀ መዛሙርቴ አድርጓቸው፡፡" ላይ እያጠመቃችኀቸው ካለ በኋላ  ነውና አስተምሩ የሚለው እዚህ ላይ ደግሞ ጥምቀት ሲቀድም እንመለከታለን፡፡ ታድያ መጽሐፍ ቅዱስ ርስ በርሱ ይጣረሳል? አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስን ለራስ  እንዲመች አድርጎ የመጥቀስ ስህተት የፈጠረው እንጂ። ለማመን ያልደረሱ ህፃናት በቤተሰብ እምነት ይጠመቃሉ፡፡ በቤተ ክርስቲያንም ነገረ ሐይማኖትን እንዲያውቁ በመንፈሳዊ ጉዞ በክርስትና ሕይወት እንዲጓዙ ሲባል ኃላፊነት የሚወስድ የክርስትና አባት [God father] ይሰጣል፡፡  በመጽሐፍ ቅዱስ እንደምንመለከተው እምነት ተሸጋጋሪ ነው፡፡ የአባት እምነት ለልጅ ሲጠቅም እንመለከታለን፡፡ ለዚህም የመቶ አለቃውና (ማቴ 8:8-10ን ተመልከቱ) የከነናዊቷን ሴት ታሪክ (ማቴ 15:22-28ን ተመልከቱ) ማስታወስ ይበቃል፡፡ በአባት እምነት ልጁ ሲድን ሲፈወስ እንመለከታለን፡፡ በከነናዊቷ ሴትም እምነት ልጇ ስትድን እንመለከታለን፡፡ በአንዱ እምነት ሌላው ሲፈወስ ሲድን እንመለከታለን፡፡ እምነት ተሸጋጋሪ ነውና፡፡ [መርሐ ጽድቅ ባሕለ ኃይማኖት፤ ሊቀ መዘምራን ሞገስ ዕቁበ ጊዮርጊስ] ስለዚህ በቤተሰብ እምነት ልጅን ማጥመቅ ይገባል፡፡

ጌታ በወንጌል ለኒቆዲሞስ " ሰው ዳግመኛ ከካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግስት ሊያይ አይችልም" ዮሐ 3:3 ብሎታል። በጥምቀት ዳግም መወለድ ለድኅነት ያስፈልጋል፡፡ ድኅነት ደግሞ ለአዋቂ ብቻ የተሰጠ ሳይሆን ለህፃናትም ጭምር ነው እንጂ፡፡

👉 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ
- በሐዋ 16 :15 "እርሷም ከቤተሰቦቿ ጋር ከተጠመቀች በኋላ..."
- ሐዋ 16:33 "ያን ጊዜም እርሱ ከቤተሰቦቹ ጋር ተጠመቀ" ልድያ ከቤተሰቦቿ ጋር እንደተጠመቀች:  የወኅኒ ጠባቂውም ከነቤተሰቦቹ እንደተጠመቀ ይነግረናል፡፡ ህፃናት ደግሞ የቤተሰብ አካል ናቸው፡፡  "ከነቤተሰቦቹ" ተባለ እንጂ ከህፃናት በቀር አልተባለም፡፡ ይህም የህፃናትን ጥምቀት እንዲገባ ያስተምረናል፡፡

👉 በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ቃል ኪዳን በገባው መሰረት የእግዚአብሔር ሕዝብ የሚባሉት ይገዘሩ ነበር። ግዝረቱም በተወለዱ በ8ኛው ቀን ይፈጸማል። ምንም የማያውቁት ሕጻናት ተገዝረው የእግዚአብሔር ወገን መሆንን ያገኛሉ አይከለከሉምም። ይህ ግዝረት ለጥምቀት ምሳሌ ነው። ቆላ.2:11-12:: ስለዚህ ለማመን ያልደረሱትን ሕጻናትን ማጥመቅ ይገባል። እስራኤል ዘሥጋ ባሕሩ ተከፍሎላቸው የመሻገራቸው ነገር የጥምቀት ምሳሌ ነው። 1ኛ ቆሮ 10:2። ባሕሩ ተከፍሎላቸው የተሻገሩት አዋቂዎች ብቻ አልነበሩም ሕጻናትም ነበሩ። በምሳሌው ይህን ከተማርን በአማናዊው ጥምቀት ደግሞ ሕጻናትን ጭምር ማጥመቅ እንደሚገባ ያስተምረናል።

ተክለ ማርያም [ጅማ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት]

ይቀጥላል...
ጥያቄ :- ጌታችን በወንጌል "ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግስት ሊያይ አይችልም።" ዮሐ. 3:5 ያለው ምሳሌያዊ እንጂ  ጥምቀትን አይደለም የሚሉ አሉ፦

መልስ

👉 ውሃና ከመንፈስ መወለድ የተባለው በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጅ መሆንንና ለመዳን የሚያስፈልግ መሆኑን የሚያመለክት ነው። እግዚአብሔር የሰጠንን ጸጋ ለመቀበል በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጆች ሆነን ካልተወለድን በስተቀር  ከእናት ከአባት በተወለድነው ተፈጥሮአዊና ሥጋዊ ልደት መንፈሳዊና ሰማያዊ የሆነውን የእግዚአብሔርን መንግስት ለመውረስ አንችልም።

ሐዋርያትና ከሐዋርያት የተማሩ ቅዱሳን ሊቃውንት ያስተማሩት በጥምቀት ዳግም ልደት መንግስቱን መወረስ የሚያስችል ምስጢር እንደሆነ ነው።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ጥምቀት መንግስተ ሰማያት የሚያስወርስ ምስጢር እንደሆነ ሲገልጽ "ለማያምኑት አልቅሱላቸው የጥምቀትን ማሕተም ሳያገኙ ለሞቱት አልቅሱላቸው። እነርሱ ከመንግስተ ሰማያት ውጪ ናቸውና ልናለቅስላቸው ይገባናል። ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ  በስተቀር ወደ እግዚአብሔር መንግስት ሊገባ አይችልም" ተብሏልና።" [ትርጓሜ ፊልጵስዩስ
ክፍለ ትምሕርት 3]

ቅዱስ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌምም "ማንም ሰው ካልተጠመቀ በቀር መዳንን አያገኝም፣ በውኃ ሳይሆን በደማቸው ከተጠመቁ ከሰማዕታት በስተቀር። ጌታችን ዓለምን በመስቀሉ ባዳነ ጊዜ ጎኑን ተወጋ ያን ጊዜም ደምና ውኃ ከጎኑ አፈለቀልን። ይህም በሰላም ጊዜ የሚኖሩ ሰዎች በውኃ ይጠመቁ ዘንድ በስደትና በመከራ ጊዜ የሚኖሩ ሰዎች ደግሞ በደማቸው ይጠመቁ ዘንድ ነው።..."።[ በእንተ ጥምቀት ትምሕርት 3 ቁ.10] ብሏል።"

👉 ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ ወደ እግዚአብሔር መንግስት ሊገባ አይችልም" የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ይዘው ውኃው የተባለው ጥምቀት ሳይሆን በተቃዋሚዎች ዘንድ አንዳንዶቹ ውኃው ምልክት (symbolic) ነው ሌሎቹ  የእምነት ማጽኛ ነው ሌሎቹም የእግዚአብሔር ቃል ነው  የእምነት መመስከሪያ [አንዳንዶቹም ውኃ የተባለው ምሳሌያዊ ሲሆን መንፈስ ቅዱስን ያመለክታል ይላሉ።] በማለት ይተረጉማሉ።

ማስረጃ 1:-ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ በመድሎተ ጽድቅ መጽሐፉ ይህን አስመልክቶ "በተቃዋሚዎች ዘንድ ርስ በርሳቸው እንኳ ይህ ሁሉ የአረዳድ ልዩነት የተፈጠረው ግን ሁሉም አንብቦ መተርጎም ይችላል በሚል የተሳሳተ ትምህርታቸው የተነሳ ነው። ይህን የጻፈልን የወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር የነበረው የቅዱስ ፖሊካርፕስ ደቀ መዝሙር ቅዱስ ሄሬኔዎስ "እኛ በኃጢአት ምክንያት አካላችን የተቆማመጠብን እንደመሆናችን የእግዚአብሔርን ስም በመጥራትና በተቀደሰው ውኃ በመጠመቅ ከክፉ በደሎቻችን ሁሉ እንነጻለን፤ አዲስ እንደተወለዱ ሕጻናትም በመንፈሳዊ ልደት ዳግመኛ እንወለዳለን ራሱ ጌታችንም እንዲህ ብሎ እንደተናገረ፦ "እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም።" ዮሐ 3:5 (ቅሬታት፣ 34)

ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ደቀ መዝሙሩን ቅዱስ ፖሊካርፕስን ያስተማረው እንደዚህ ነበር። ቅዱስ ሄሬኔዎስም ከመምህሩ ከቅዱስ  ፖሊካርፕስ እግር ሥር ቁጭ ብሎ የተማረው ይህንኑ ነበር፣ በተግባር ያየውም እንደዚህ ነበር። ስለዚህ ቅዱስ ሄሬኔዎስም ሆነ ሌሎቹ ክርስቲያኖች ሁሉ የተረዱት ጌታችን በውኃ መጠመቅ ለዳግመኛ ልደትና መንግሥተ ሰማያት አስፈላጊ ነው ያለ መሆኑን ነው።በኒቂያውና በቁስጥንጥንያው የእምነት መግለጫ አንቀጽ ላይም "ኃጢአት በሚሠረይባት በአንዲት ጥምቀት እናምናለን።" ተብሎ የተገለጸው ከእነርሱ በፊት ከነበሩ አባቶችና እነዚያም ከሐዋርያት፣ ሐዋርያት ደግሞ ከጌታ የተቀበሉት አተረጓጎምና አረዳድ ነው። ከዚህ የቤተ ክርስቲያናዊ አረዳድ የወጡና መጽሐፍ ቅዱስን በራሳችን መንገድ እንተረጉመዋለን የሚሉ ፕሮቴስታንቶች ግን ከዚህ ተቃራኒ የሆነ ነገር ይዘው ብቅ በማለት አንዳቸው ትክክለኛው ይኸኛው ነው፣ ሌላቸው ደግሞ እርሱ ሳይሆን እንደዚህ ነው እያሉ ሁሉም የራሳቸውን ግምት በሰዎች ላይ ለመጫን ይደክማሉ። (መድሎተ ጽድቅ ቅጽ 2. ገጽ 99)


ይቀጥላል...

ተክለ ማርያም [ሐመረ ኖኅ ጅማ ኪዳነ ምሕረት]
ከላይ እንደተገለጸው ተቃዋሚዎች "ውኃ" የተባለው ምሳሌያዊ እንጂ በቀጥታ አካላዊውን ውኃ አይደለም በማለት ተቃውሞን ያቀርባሉ። ውኃ ለመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ሆኖ "በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል ብሎ ጮኸ። ይህ ግን በርሱ የሚያምኑት ሊቀበሉት ስላላቸው ስለ መንፈስ ተናገረ" ዮሐ. 7:38-39 ቀርቧል። ዳግመኛም "ውሃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑንስ ብታውቂ አንቺ ትለምኚው ነበርሽ የሕይወትም ውኃ ይሰጥሽ ነበር አላት..." ዮሐ. 4:10-14 ውሃ በምሳሌያዊ መልኩ ተገልጿልና "ከውሃና ከመንፈስ ያልተወለደ..." ሲልም ውኃ" የተባለው ቀጥታ ውኃ ለማለት  ሳይሆን ምሳሌያዊ ነው መንፈስ ቅዱስን ወይም ጌታን ነው የሚያመለክተው ይላሉ

ማስረጃ 2:-  በዮሐ. 3:5 ላይ "ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግስት ሊገባ አይችልም።" የተባለው በውኃ ስለሚፈፀመው ጥምቀት እንጅ በምሳሌነት መንፈስ ቅዱስን ለማለት የተጠቀሰ አይደለም።

ይህን ለመረዳት ጌታችን ይህን ለኒቆዲሞስ ሲነግረው "ውኃ" የተባለው በውኃ ስለሚፈጸመው ጥምቀት  ውጪ  ሌላ ትርጉም ቢኖረው ኖሮ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ  አብራርቶ በጻፈልን ነበር። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌሉን ሲጽፍ የተሳሳቱ ወይም ግራ የሚያጋቡ ሃሳቦች ሲኖሩ አስተካክሎ አርሞ ያልፋል እንጂ እንዲሁ አይተወውም። "...እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተ መቅደስ ይል ነበር" ዮሐ. 2:19-21፤ "...ስለ አብ እንደ ነገራቸው አላስተዋሉም።" ዮሐ.8:25-27 "እንቅልፍ ስለመተኛት የተናገረ መስሏቸው ነበር" ዮሐ. 11፡13:: "የአትክልት ጠባቂ መስሏት ነበር" (ዮሐ. 21፡33)  በማለት አብራርቶ ስሕተትም ካለ አርሞ የሚጽፍ ሐዋርያ ነው።

ስለዚህም ከላይ 'ውኃ' የተባለው "መንፈስ ቅዱስ" ቢሆን ኖሮ በዮሐ. 7:37-39 ላይ እንደሰፈረው አብራርቶ ይጽፍልን ነበር።
በዮሐ. 7:38 ላይ "የሕይወት ውሃ"  የተባለው መንፈስ ቅዱስ መሆኑን አብራርቶ ገልጾ ነበርና።

ማስረጃ 3:-
በዮሐ. 3:5 ላይም የተጻፈው በቀጥታ በውኃ ስለሚፈጸመው ጥምቀት ባይሆን ኖር አብራርቶ ይገልጸው ነበር። "በውኃና በመንፈስ"  የተባለው በቀጥታ በውኃ ስለመጠመቅ እንጂ ስለ መንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ሆኖ አለመቅረቡን ለመረዳት:-

1ኛ.  በዮሐ. 4:10-14 እና በዮሐ. 7:38-39 ላይ የሕይወት ውኃ (living water) እያለ ሲናገር በዮሐ. 3:5 ላይ ግን "ውኃ" በማለት ብቻ ነው የተባለው። ስለ መንፈስ ቅዱስ ሲናገር የሕይወት ውሃ እያለ ሲገልጸው በዮሐ.3:5 ላይ ደግሞ "ውኃ" ብቻ በማለት ምሳሌያዊ እንዳልሆነ ያስረዳናል።

2ኛ. በዮሐ. 4:10-14 እና በዮሐ. 7:37-39 ላይ በውኃና በሕይወት ውኃ (living water) መካከል በማነጻጸር ሲያስቀምጥ በዮሐ. 3:5 ግን እያነጻጸረ አልገለጸም ምክንያቱም "በውኃና በመንፈስ" በማለት የተገለጸው ምሳሌያዊ ሳይሆን በቀጥታ በውኃ ጥምቀት የሚፈጸመውን የሚያመለክት ነውና።

3ኛ. "በውኃና በመንፈስ" የተባለው ላይ "ውኃ" የተባለው ዮሐ. 7:38-39 ላይ "የሕይወት ውኃ" ተብሎ እንደተገለጸው መንፈስ ቅዱስን ለማመልከት ቢሆን ኖሮ "እና" በሚል አያያዥ ቃል ባልተጠቀመ ነበር። ምክንያቱም ውኃ የተባለው መንፈስ ቅዱስ ቢሆን ኖሮ "በውኃና በመንፈስ" በማለት አይገልጽም ነበር። ድግግምሽ ይሆናልና። ይልቁኑ በውሃና በመንፈስ የተባለው በጥምቀት የመንፈስ ቅዱስ ልጅነትን የምናገኝበትን የሚያመለክት ቃል ነው።


ተክለ ማርያም [ጅማ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት]
ጥያቄ:_ ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በላከው ክታቡ "...በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ።" ኤፌ.5:26::    እንዲሁም ቅዱስ ጴጥሮስ "ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም። በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ።" 1ኛ ጴጥ.1:23   ሐዋርያው ያዕቆብም "ለፍጥረቱ የበኩራት ዓይነት እንድሆን በእውነት ቃል አስቦ ወለደን።" ያዕ.1:18 በማለት በቃሉ እንደምንድን አስተምሯል። ስለዚህም የምንድነው በቃሉ እንጂ በውኃ ጥምቀት አይደለምና ለምን እንጠመቃለን? የሚሉ አሉ፦

መልስ


👉 የጥምቀት ትርጉም በግሪኩም ሆነ በግዕዙ አንድ ነው። መንከር ወይም ውሃ ውስጥ መጥለቅ ማለት ነው። ከቃሉ ትርጉም እንኳ ስንነሳ ጥምቀት ሊከናወን የሚችለው በውኃ በመጠመቅ ነው። በውኃ ተጠምቆ ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና ለማግኘት ደግሞ አስቀድሞ ማመን ያስፈልጋል። ለማሳመን ደግሞ ማስተማር ግዴታ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ሮሜ.10:15 እንዳለው የእግዚአብሔርን ቃል ማስተማር ለሁሉመ መሰረታዊና አስፈላጊ ነው። ስለዚህ ቃሉ ሕይወትን የሚሰጥ ለጽድቅ የሚያበቃ መሆኑን ማንም አይክድም። ዳሩ ግን የቃል ጥምቀት (ቃሉን ሰምቶ በመንፈስ መለወጡ) መታጠብ እንጂ የውኃ ጥምቀት አያስፈልግም ማለት አይደለም።

👉 "በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳ [He might sanctify and cleanse it with the washing of water by the word..." በሚለው አነጋገር የውኃ ጥምቀት እንዳለ በግልጽ ተቀምጧል። ጥምቀት ማለት ውኃ ውስጥ ገብቶ መነከር ማለት ከሆነ በውኃ መታጠብ ማለት የሚያመለክተው መጠመቅን ነው።  ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው በውኃ ተጠምቆ  የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቶ ይነጻል ይቀደሳል። "በውኃ መታጠብ ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት በሚለው ውስጥ ለመጠመቁ ምክንያት ወይም ወደ ጥምቀት የመራው ቃሉ (ስብከቱ) እንደሆነ With the washing of water by the word በማለት ገልጦታል። by the word የሚለው ለመጠመቅ በቃሉ አምነው መቅረባቸውን ያመለክታል። ቅዱስ ጳውሎስ ማመን ከመስማት መስማትም ከእግዚአብሔር ቃል እንዳለ። በውኃ መታጠብ የተባለው ግን ቃሉ ነው ከተባለ ቃሉን እያለ መድገሙ ለምን አስፈለገ? ይህም ማለት  "በቃሉ ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት" እንደማለት ያለ ነው።

👉 "...ለፍጥረቱ የበኩራት ዓይነት እንድንሆን በእውነት ቃል አስቦ ወለደን" የሚለውም ተከታይ ተቀዳሚ የሌለው የአብ የባሕሪይ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሥልጣኑ ምንም ምን የሚያመልጥ ከቃሉ የሚወጣ (የሚዛነፍ) የሌለ "ያመነ የተጠመቀ ይድናል" ባለው ቃል መሰረት ወዶ ፈቅዶ ወልዶናልና "ለፍጥረቱ በኩራት እንድንሆን" ማለትም መጀመርያ ልጅነትን ያገኙት ሐዋርያት በመሆናቸው ራሱን ከወንድሞቹ ከሐዋርያት አግብቶ መናገሩ ነው። እስከ ምጽአት ድረስ ለሚነሱ ሁሉ አበው ሐዋርያት አብነት ይሆናሉና። እንግዲህ እምነት ከመስማት መስማትም ከቃሉ ነው። ለሁሉም መሰረቱ ቃለ እግዚአብሔር ነው። በእግዚአብሔር ቃል ሁሉም ይከናወናል። ጥምቀቱ ቁርባኑ መልካም ምግባሩ ከእግዚአብሔር ቃል ውጪ የሚሆን አይደለምና።  በእውነት ቃል ወለደን የሚለውም አነጋገር ጥምቀትን የሚሽር አይደለም።

👉 ቅዱስ ጴጥሮስ በማይጠፋ የእግዚአብሔር ቃል ተወለዳችሁ ሲል ያዕቆብ ደግሞ "በእውነት ቃል አስቦ ወለደን" ብሎ ሲናገር  እምነት የሚለውን ቃል አልተጠቀሙምና ለዳግም ልደት እምነት አያስፈልግም ሊባል ነውን? አንልም። ይልቁኑ ' ቃል' ብሎ ሲናገር በውስጡ ማመንንም አካቶ እንደሆነ እንረዳለን እንጂ። እምነት ቃል በቃል ስላልተጠቀሰ  "በእውነት ቃል አስቦ ወለደን" የሚለው የሚያምነውን የማያምነውንም ያጠቃልላል ልንል ነውን? እምነት ሳይጠቀስ ስለ ዳግም ልደት ይናገራል ልንል ነውን? በነዚህ ጥቅሶችም ጥምቀት የሚለው ስላልተጠቀሰ ብቻ የለም ተብሎ አይነገርም። ይልቁኑ ሐዋርያቱ የቃሉን የስብከተ ወንጌሉን ለዳግም ልደት ያለውን አስፈላጊነት ጠቀሱ እንላለን እንጂ። በቃሉ (በስብከተ ወንጌል) ሰው ወደ ማመን አምኖም ወደ መጠመቅ ይደርሳልና። "በውሃ መታጠብ ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት" ሲባልም "እምነት" የሚለው ቃል አልተጠቀሰም። ታዲያ ስላልተጠቀሰ እምነት አያስፈልግም እንበልን?
(መራሔ ድኅነት፤ Comparative theology)

ተክለ ማርያም  [ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት]
ጥያቄ :- ሰላም እንዴት ናችሁ?
ጥያቄ ለመጠየቅ ነበር መናፍቃን እኛ ኦርቶዶክሳውያንን አንዲት ጥምቀት ተብሎ ተጽፎ ለምን በየዓመቱ ትጠመቃላችሁ? ብለው ይጠይቃሉ ቢያብራሩልን።

መልስ

👉 ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በሚለው መጽሐፋቸው የዚህን ጥያቄ መነሻና ምላሹን እንዲህ ብለው ጽፈዋል። "የጠበሉን መረጨት አይተው በቀድሞ ዘመን ወደ ሀገራችን መጥተው የነበሩ ኢየሱሳውያን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ታጠምቃለች ብለው ጽፈዋል። ነገር ግን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በያመቱ ይህን የምትፈጽመው ጌታችን ለእኛ ብሎ ያሳየውን ትህትና ለመመስከር ለምዕመናን በረከተ ጥምቀትን ለማሳተፍ እንጂ የተጠመቁትን ምዕመናን እየመላለሰች በየዓመቱ አታጠምቅም። ጥምቀት አሐቲ [አንዲት] መሆኗን ታውቃለችና። [የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ታሪክ ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ገጽ.126]

ዲያቆን ብርሃኑ አድማስም በዓላት በሚለው መጽሐፉ በጥምቀት የምንጠመቀው ለሥርየተ ኃጢአት ጭምር መሆኑን ሲገልጽ እንዲህ ብሎአል።   "የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያንም  ለዚሁ አንጽሖተ ማይ (ውሃውን ለመቀደስ) እና ምእመናኑም በጥምቀት (በልጅነት) የቀደመ ኃጢአታቸው የተሠረየላቸውን ያህል በዚህ ዕለትም የሠሩት ኃጢአት ይሠረይላቸዋል ትላለች። [በዓላት፤ ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ ገጽ ገጽ.71] ስለዚህም በረከተ ጥምቀቱን ለምዕመናን በማድረስ ማሳተፍና ሥርየተ ኃጢአትን መስጠት እንጂ  መላልሶ ማጥመቅ አይደለም። ልጅነት አንድ ጊዜ ብቻ ነውና።

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ልጅነትን የምታሰጠዋ ጥምቀት አንዲት ናት። ኤፌ.{ 4:5። ልጅነትን የምታሰጠዋ ጥምቀት አንዲት ናት አትደገምም። በጸሎተ ሐይማኖት ላይም "ኃጢአት በሚሰረይባት በአንዲት ጥምቀት እናምናለን" ይላል።  ጥምቀት ከምናከብራቸው ከጌታችን ዓበይት በዓላት አንዱ ነው። ጌታችን በቅዱስ ዮሐንስ ሊጠመቅ መሄዱን የምናስብበት በዓል ነው ከጌታችን ጥምቀትም በረከትን የምንሳተፍበት በዓል ነው። ጥምቀት ሊደገም ይቅርና ይህን የጌታን ጥምቀትን በማሰብ የምናከብረውን በዓል ለማክበር መብቱ እንኳ ያላቸው ከማሕጸነ ዮርዳኖስ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ በጥምቀት የሥላሴ ልጅነትን ያገኙ ክርስቲያኖች ናቸው። ስለዚህ በረከተ ጥምቀትን ለመሳተፍ እንጂ ልጅነት የምታሰጠዋ ጥምቀት የምትደገም ሆና አይደለም።

ጌታችን በወንጌል " የክርስቶስ ስለ ሆናችሁ በስሜ ጽዋ ውኃ የሚያጠጣችሁ ሁሉ፥ ዋጋው እንዳይጠፋበት እውነት እላችኋለሁ።" ማር.9:41 እንደተናገረ ስሙን አስበን የምናደርጋቸው የምንዘክራቸው የጌታን ዓበይትና ንዑሳን በዓላትን ማሰብ መዘከር ስለ እርሱም ብሎ ነዳያንን በምሕረት መጎብኘት ዋጋ የማያሳጣ ተግባር ነው።


ተክለ ማርያም [ጅማ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት]
ጥያቄ:- ታቦት በአዲስ ኪዳን እንዴት ነው? ለምን  ይሰገዳል?

መልስ

ታቦት በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር በምህረት በሚገለጥበት ጊዜ ዙፋኑ ነው፡፡  ከክርስትና በፊት የብሉይ ኪዳን አገር የነበረችው ኢትዮጵያ በክርስትና ጊዜም ከብሉይ ኪዳንም ያገኘቻቸውን ጠቃሚ ነገሮች በክርስትና መንፈስ እየተረጎመች ትጠቀምባቸዋለች፡፡
ከብሉይ ኪዳን የወሰደቻቸው አንዱ ጽላተ ኪዳን ታቦተ ህጉ ነው፡፡ የደብተራ ኦሪት ጽላት እግዚአብሔር በደመና ተከናንቦ ሙሴንና አሮንን የሚነጋግርበት ለእስራኤል ልጆችም በረድኤት የሚገለጥበት ዙፋን ነበር፡፡ በአዲስ ኪዳን ታቦት ግን የአምላክ ስጋና ደም የሚፈተትበት ስጋዬን የበላ ደሜን የጠጣ የዘላለም ህይወት አለው፡፡ ስጋዬን ብሉ ደሜን ጠጡ እያለ ያመኑትን ሁሉ የሚጠራበት የምህረት ምስዋዕ ነው፡፡ ክብርና ሰግደትም ለዚህ ይደረግለታል፡፡

👉 በርግጥ የሐዲስ ኪዳን ታቦት ከብሉይ ኪዳን ታቦት የሚለይበት መንገድ አለው። በሐዲስ ኪዳን ታቦት የሚባለው የብሉይን ታቦትና ጽላት አንድ አድርጎ የያዘ ይመስላል። በብሉይ ጽላት ላይ  የተጻፉት ቃላትም አልተጻፉበትም። ምክንያቱም በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ቀዳማዊ እንደተገለጸው ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የሚችል ጻሕልና ጽዋ የሚያስቀምጥ እንዲሆን ተወስኗል። በላዩም አልፋ ወኦ፤ ቤጣ ፤ የውጣ የሚባሉ አስማተ መለኮት (የአምላክ ስሞች) በአራቱ ማዕዘን ይቀረጽበታል። በመካከል ሥነ ስቅለት ይቀረጽበታል። "ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ታቦተ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ተብሎ ይጻፍበታል። ኪሩቤል መንበረ ጸባዖትን እንደተሸከሙ ይሳልበታል። ከዚያም የቅዱሱ ስም ይቀረጽበታል። እስከ 15ኛው ምእተ ዓመት ከላይ ቅድስት ሥላሴ
ዝቅ ብሎ እመቤታችን ወደ ላይ አንገቷን በማቅናት ከታች ደግሞ ቅዱሱን ወደ እመቤታችን አቅንተው ይቀረጹ ነበር። ከላይ ታቦቱ ጻሕል ጽዋ እንዲያስቀምጥ ሆኖ የሚሰራው መሰዊያ ሆኖ ስለሚያገለግል ነው። ቅዱስ ጳውሎስ በዕብ.13:10 ላይ "መሠዊያ አለን" ያለው ታቦቱን እንደሆነ   ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ተርጉሞታል። "ታቦት ነበረን" አላለምና ታቦት አለን ያለው በዘመነ ሐዲስ በመሆኑ መሠዊያ በሐዲስ ኪዳን ለመኖሩ ያስረዳል ብሏል... ከዚህ አንጻር የታቦቱ አገልግሎት ለመሠዊያ ነው። መሠዊያ አለን እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ ያለ መሠዊያ የምትኖር ቤተ ክርስቲያን የለችም።
[ሁለቱ ኪዳናት ገጽ.310-311፤ መሪጌታ ሐየሎምና ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ]

👉 ከኢትዮጵያ ውጪ ያሉ እህት አብያተ ክርስቲያናት (Oriental Churches) ታቦት የተለመደ ህግ ነው፡፡ ስጋ ወደሙን የሚፈትቱት በታቦቱ ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ፦ ግብፃውያን ታቦቱን "ሉህ" ይሉታል፡፡ ጽላት ሰሌዳ ማለት ነው፡፡ ያለሱ ስጋ ወደሙ አይፈተትም፡፡ የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት የሚባሉት "የግሪክ፣ የሩሲያ የሩማንያና" የሌሎችም ወደ ክርስትና የተመለሱት ከአረማዊነት ስለሆነ የታቦትን ምስጢር አያውቁም፡፡ በታቦቱ ፈንታ ከመንበር የማይነሳ እንደ ታቦት የሚከበር የጌታ የስቅለቱ ወይም የግንዘቱ ስዕል ያለበት የነጭ ሐር መጎናጸፊያ አላቸው፡፡ ያለሱ ስጋውን ደሙን አይፈትቱም፡፡ ይህን በጽርዕ "አንዲሚንሲዮን" ይሉታል፡፡ "ህየንተ ታቦት" ማለት ነው፡፡ የሮማ ካቶሊኮች "ሜንሳ " "MENSA" ይሉታል፡፡ ጠረጴዛ ማለት ነው፡፡ [የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፡ አባ ጎርጎርዮስ ገጽ108-110]

👉 ስለዚህም የክርስቶስ ሥጋና ደም የሚፈተትበት ስለሆነ ክብርና ስግደት ይገባዋል። ዳግመኛም የኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተጻፈበት ስለሆነ ስለ ስሙ ስግደት ለማቅረብ በታቦት ፊት እንሰግዳለን። ቅዱስ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች በላከው መልዕክቱ  "፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥፤ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።" ፊልጵ.2:10-11 እንዳለ በታቦቱ ፊት እንሰግዳለን።


ተክለ ማርያም [ጅማ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት]
#መልካም_ዜና_በተለይ_ለወጣቶች_በሙሉ#

#መጽሔተ_ወራዙት_ዘኦርቶዶክስ#የተሰኘ_መጽሐፍ_በቅርብ_ወደ_እጃችሁ_ይደርሳል።

ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች የቅድስት ቤተ ክርስቲያን የወደፊት ተስፋዎች ናቸው። ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን በሙሉ በጥንቃቄ መጠበቅና ወደ አምላኳ መምራት የኹል ጊዜ ሥራዋ መኾኑ የታወቀ ነው። በተለይም ደግሞ ወጣት ልጆቿን የዚህ ዓለም ርካሽ ሐሳብ ከቤተ ክርስቲያናዊ (Ecclestical life) እንዳያጎድላቸው፥ ከቀድሞ የበለጠ መሥራት አለባት። በጥሩ መሠረት ላይ ያልቆሙ ወጣቶች ስንኳንስ የሌላው ቀርቶ የራሷ የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ይኾናሉና። በዚህም መሠረታዊ ምክንያት ቤተ ክርስቲያን ክርስቶሳዊት መኾኗ በጉልህ ይታወቅ ዘንድ ወጣቶቿን በመንፈሳዊ ሕይወትም ኾነ በቤተ ክርስቲያናዊ መረዳት ተግታ መሥራት አለባት።

ወጣቶች የምድራዊቷን ቤተ ክርስቲያን (Earthly Church) አባል ስለ ኾኑ፥ በንስሐ ሳሙን እየታጠቡ፥ ከክርስቶስ ሥጋና ደም እየተሳተፉ፥ በቅድስና ሕይወት እንዲኖሩ ማድረግ የቤተ ክርስቲያን እረኞች የተባሉ የካህናት ዋና ሥራ መኾን አለበት። ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ያሉ አካላትም ቢኾኑ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ብልጫ በዋነኛነት የሚያዩት ከወጣት ልጆቿ ነውና። ስለዚህ በዚህ ጉዳይ በተለይም በዚህ የኃጢአት እሳት በተለያየ መንገድ በሚቀጣጠልበት ዘመን፥ ኦርቶዶክሳዊ የኾነ የወጣትነት አኗኗርን የሚመለከቱ ብዙ ሥራዎች ያስፈልጉናል። ወጣትነት በብዙ መንገድ ሊጠበቅ የሚገባው የሕይወት ክፍል ስለ ኾነ፥ በእያንዳንዱ የወጣትነት የሕይወት ክፍል ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን የሚፈቱ ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮዎች ለወጣቱ በእጅጉ ያስፈልጋሉ። ይህ "የኦርቶዶክሳዊ ወጣቶች መስታወት" የተሰኘው መጽሐፍ በዋነኛነት በወጣቶች ሕይወት ዙሪያ የሚከሰቱ ነገሮችን መሠረት አድርጎ፥ በተለያዩ ጉዳዮች ቤተ ክርስቲያናዊ አስተምህሮዎችን ለማሳየት የተሞከረበት መጽሐፍ ነው። በመስታወት ፊት ቆመን ፊታችንን ስንመለከት በላያችን ላይ ያለውን ቆሻሻ ማስወገድ እንደምንችል ኹሉ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የአስተምህሮ መስታወት ፊት ስንቆምም፡ በውስጣችን ያሉ የኃጢአት ቆሻሻዎችን ማስወገድ እንችላለን፡፡ ይህ መጽሐፍ በወጣትነት ሕይወታችን ኦርቶዶክሳዊውን አኗኗር ገንዘብ አድርገን ጣዕም ያለው ኦርቶዶክሳዊ ሕይወት እንድንኖር በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትምህርት መስታወትነት  ያሳየናል፡፡ የተዘጋጀበት ዋና ዓላማውም ይህ ነውና፡፡
 
በዚህ መጽሐፍ ስምንት ክፍሎች ያሉት ሲኾን የመጀመሪያው ክፍል ወጣትነት ምን እንደ ኾነ፣ መልካም ወጣት መኾንስ እንዴት ወይም መልካም ወጣት ማለት በራሱ ምን ዓይነት እንደ ኾነ በዝርዝር ተገልጾበታል። ኹለተኛው ክፍል ደግሞ "ፍቅር" ምን እንደ ኾነ የሚያብራራ ነው። እውነተኛ ፍቅር ከተሳሳተ ፍቅር የሚለየው በምን በምን እንደ ኾነ፣ አንድ ሰው በእውነተኛ ፍቅር ውስጥ መኾኑን እንዴት ማወቅ እንደሚችል እንዲሁም የፍቅር ቀን የሚባለው ምን እንደ ኾነ ተብራርቶበታል። በክፍል ሦስት ደግሞ ኦርቶዶክሳዊውን የአለባበስ ሥርዓት እና በዚያ ዙሪያ ያሉ ሐሳቦችን ለማብራራት የተሞከረበት ሲኾን፥ "ሴት የወንድን ልብስ አትልበስ" ከሚለው አንሥቶ ጌጣጌጦች መጠቀም፣ እንዲሁም በሰውነት ላይ መነቀስን ጨምሮ የተብራራበት ክፍል ነው። አራተኛው ክፍል የመጽሐፉ ሰፊ ክፍል ነው። ይኸውም ስለ ሱስ ምንነት እና መፍትሔዎችን የያዘ ነው። እንግዲህ በዚህ ክፍል ውስጥ በወጣትነት ሕይወት ውስጥ እጅግ በጣም ፈታኝ የኾኑ የሱስ ዓይነቶች ተዘርዝረዋል፥ ከእነዚያ ሱሶችም መውጫ መንገዶች በዝርዝር ተቀምጧል። ለምሳሌ ጫት፣ ሲጋራ፣ ማኅበራዊ ሚዲያ፣ ትዕይንተ ግብረ ዝሙት፣ ግብረ አውናን፣ ሰዶማዊነት፣ ... የመሳሰሉት ሌሎች ከሱስ ጋር ተያያዥነት ያሏቸው ጉዳዮች ተብራርተዋል። በክፍል አምስት ደግሞ በሴቶች የሚከሰተው የወር አበባን በተመለከተ እና በወንዶች የሚከሰተውን ዝንየትን በተመለከተ ኦርቶዶክሳዊው ትምህርት ምንድን ነው የሚል የተተነተነበት ክፍል ነው። ክፍል ስድስት ዓለማዊነት ምን እንደ ኾነ፥ የትኩረት አቅጣጫውም ምን ምን ላይ እንደ ኾነ ተገልጿል። በሰባተኛው ክፍል ውስጥ ደግሞ ሕልምን በተመለከተ ኦርቶዶክሳዊው አረዳድ ምን እንደ ኾነ ተብራርቷል፡፡ የዚህ መጽሐፍ የመጨረሻው ክፍል ደግሞ ወጣቶች መልካም ይኾኑ ዘንድ ይጠቅሟቸዋል ተብለው የታሰቡ ትምህርታዊ ስብከቶች የተዘረዘሩበት ክፍል ነው።

#ወጣቶች_ሆይ_መጽሐፉ_በመከራ_ስለታተመ_ገዝቶ_ማንበብን_ግድብታደርጉ_መልካም_ነው። ስለ ምታነቡትና አስተያየታችሁንም ስለ ምትሰጡኝ ከወዲሁ ምስጋናዬን አቀርባለሁኝ።
ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንና ካህናት በሙሉ ፆመ ነነዌን ጥቁር በመልበስ እንድታሳልፉ ቅዱስ ሲኖዶስ አዟል!!

⚜️⚜️⚜️⚜️⚜️⚜️⚜️⚜️⚜️⚜️⚜️⚜️⚜️⚜️⚜️⚜️⚜️

ጥር ፳፮ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም (ጅማ፤ ኢትዮጵያ)
@የጅማ ሀገረ ስብከት መገናኛ ብዙኃን!!

ጾመ ነነዌን ምክንያት በማድረግ ጥቁር ልብስ ብቻ በመልበስ በጾምና በጸሎት ምሕላ በመያዝ ከቤተ ክርስቲያን ዓውደ ምህረት በመገኘት ወደ እግዚአብሔር ጾም፣ ጸሎትና ምሕላ እንድታቀርቡ ሲል ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን አስተላለፈ፡፡
2024/05/12 05:06:47
Back to Top
HTML Embed Code: