Telegram Web Link
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ - ‌🇴‌🇷‌🇹‌🇭‌🇴‌🇩‌🇴‌🇽 ‌🇹‌🇪‌🇼‌🇦‌🇭‌🇩‌🇴
Photo
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ከኢትዮጵያ ኦርቶደክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ አዋጅ
በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረው አስቸኳይ ምልዐተ ጉባኤ በኢትዮጵያ የኦሮሚያ እና የብሔር ብሔረሰቦች ቅዱስ ሲኖዶስ በሚል በሕገ ወጥነት በቀድሞ ስማቸው አባ ሳዊሮስ የተባሉ ግለሰብ መሪነት ይህ መግለጫ እስከተሰጠበት ቀን ድረስ በተለያዩ ክልሎች እና የፌዴራል መንግሥት በሚመራቸው ቦታዎች ውስጥ በሚገኙ የቤተ ክርስቲያኗ አህጉረ ስብከት የሆኑትን ሥርዓተ አምልኮዋን የምትፈጽምባቸው በየመዋቅሩ የሚገኙ አስተዳደር ቢሮዎችን ከሕግ አግባብ ውጭ የቤተ ክርስቲያኗ እምነት ተከታይ ያልሆኑ ግለሰቦችን በማካተት በመንግሥት ልዩ ኃይል ድጋፍ በመውረር እና በመስበር የሕግ አግባብነት በሌላቸው እንዲሁም መብት እና ጥቅም ሳይኖራቸው በማሸግ ቤተ ክርስቲያን ላይ ወረራ እየተፈጸመባት የሚገኝ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ለመረዳት ችሏል፡፡
መንግሥትም ሰላም እና ደህንነትን ከማስጠበቅ ባለፈ የሕይወት እና የአካል ደህንነት መብትን እንዲሁም የመንቀሳቀስ መብትን በመገደብ ያለአግባብ ታግተው መቆየታቸውን ከሊቃነ ጳጳሳት ውስጥ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስን ከዚህ ቀደም መግለጻችን የሚታወቅ ሲሆን ከዚህ ድርጊታቸውም ሳይታቀቡ በጥር 26 ቀን 2015 ዓ.ም ከምሽቱ 3፡30 አካባቢ የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑትን ብጹዕ አቡነ ያሬድን በሕገ ወጥ መልኩ የዜግነት መብታቸው ተጥሶ በደረቅ ሌሊት በማሰር እና በማዋከብ ከሀገረ ስብከታቸው ለቀው እንዲወጡ የተደረጉ ሲሆን እንዲሁም የተለያዩ አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳትን ወደየ አህጉረ ስብከታቸው እንዳይሄዱ ማስፈራሪያ በመላክ የቤተ ክርስቲያችንን ክብር እና ልዕልና እጅጉን የሚጎዳ እና አሳዛኝ ድርጊት እየተፈጸመባት ይገኛል፡፡ በተጨማሪም የየሀገረ ስብከት ሥራ አኪያጆችንና ሠራተኞችን፤ አገልጋይ ካህናትንና ምእመናን በሕገ ወጥ መልኩ በማሰር እንደ መንግሥት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ባለመወጣቱ ቤተ ክርስቲያናችን እጅጉን አዝናለች፡፡
ከዚህም አልፎ መንግሥትም በቤተ ክርስቲያችን በኩል በተደጋጋሚ የተሰጠውን ማሳሰቢያ ችላ በማለቱ ምክንያት በምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት በሻሸመኔ ከተማ ሕገ ወጦቹ መንግሥትን ተገን በማድረግ የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በደብረ ስብሐት ቅዱስ ሚካኤል አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በሕገ ወጥ መልኩ ወረራ ለመፈጸም ባደረጉት እንቅስቃሴ ቤተ ክርስቲያንችንን ለመጠበቅ በወጡ ምእመናን ላይ ፖሊስ በወሰደው እርምጃ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ የአደባባይ የግድያ ወንጀል ተፈጽሟል፡፡ ሌሎች በቁጥር ያልታወቁ ምእመናንም ላይ ከፍተኛ እና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
ይህንንም ሕገ ወጥ ተግባር በተመለከተ ተገቢውን ሕጋዊ የሰላም እና የደህንነት ከለላ እንዲያደርጉ ለሚመለከታቸው የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት በተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ቤተ ክርስቲያናችን ብትሰጥም ይህንን ማሳሰቢያ ወደጎን በመተው መንግሥት ሕገ ወጡን ቡድን በመደገፍ እና በማስፈጸም ከላይ የተገለጹትን አሳዛኝ ድርጊቶች በይፋ በአደባባይ ፈጽሟል፡፡
ስለሆነም የኢትዮጵያ ኦርቶደክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በጠራው አስቸኳይ ጉባዔ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አስተላልፏል፡፡
1. በብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት እና የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች፤ የክፍል ኃላፊዎች፤ ካህናት፤ አገልጋዮች እና ምእመናን ላይ የተፈጸመውንና እና እየተፈጸመ ያለውን ሕገ ወጥ እስር እና ወከባ ቅዱስ ሲኖዶስ በፅኑ አውግዟል፤
2. በጥር 27 ቀን 2015 ዓ.ም በምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት በሻሸመኔ ከተማ በደብረ ስብሐት ቅዱስ ሚካኤል አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን፤ ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ የወጡት ምዕመናን ላይ ጭካኔ በተሞላ ሁኔታ የተፈጸመው ሕገ ወጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና የተፈጸመው አሰቃቂ የሞት ድርጊትን ፍጹም ታወግዛለች፤ ተገቢውን ሲኖዶሳዊ እና ሃይማኖታዊ ጸሎት በማድረግ በሁሉም አጥቢያ ሥርዓተ ፍትሐት እንዲፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤
3. ቅዱስ ሲኖዶስ በጥር 26 ቀን 2015 ዓ.ም ባስተላለፈው ውሳኔ እና በሰጠው መግለጫ መላው የቤተ ክርስቲያኒቱ ተከታዮች ጾመ ነነዌን ሙሉ የሱባዔ ጊዜ በማድረግ ጥቁር ልብስ ያለውን ትርጓሜ በመግለጥ እንድንሰነብት መግለጫ መሰጠቱ ይታወሳል፡፡
3.1. ለዚህም ዝርዝር አፈጻጸም መመሪያ ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ከጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት 3 ቀናት በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የምትገኙ ማናቸውም ካህናት እና ምዕመናን ሙሉ ጥቁር ልብስ በመልበስ በየአብያተ ክርስቲያናት እና በገዳማት ያለውን ሥርዓተ ጸሎት እንድትመሩ እና እንድትከታተሉ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤
3.2. በየትኛውም እንቅስቃሴ ይህንን ጥቁር ልብስ በመልበስ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ንቁ በመሆን እንድትፈጽሙ፤ ሆኖም ግን ቅዱስ ሲኖዶስ ይህንን ዓለም አቀፍ የጸሎትና የምህላ መርሐ ግብር ካወጀበት ቀን በኃላ በተለያዩ ከተሞች የጥቁር ልብስን ሆነ ተብሎ ከገበያ እንዲወጣ እየተደረገ መሆኑን በመረዳታችን ምዕመናን ያላችሁን ተመሳሳይ አልባሳት በመጠቀም የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔን በእንቅስቃሴያችሁ ሁሉ እንድትፈጽሙ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤
3.3. በነዚህ ቀናት ውስጥ አገልግሎቱ በድምጽ ማጉያ እንዲከናወን እና የሙሉ ጊዜ ሆኖ በሰባቱ የጸሎት ሰዓታት እየተጠበቀ በተመሳሳይ ሰዓታት ለአምስት ደቂቃ ያህል በማያቋርጥ ደወል በመደወል የማስተጋባት ሥራ እንዲሠራ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤
3.4. ይህንንም የየአህጉረ ስብከት፤ የወረዳ ቤተ ክህነት እና የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሰበካ ጉባኤያት በመከታተል እንድታስፈጽሙ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
3.5. የአኃት አብያተ ክርስቲያናት፤ የኦርቶዶክስ ዓለም፤ እውነቱን የምታውቁና የምትደግፉ ማናቸውም ኃይማኖታዊም ሆነ ማህበራዊ ተቋማት እና ግለሰቦች የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ጥሪ በመደገፍ በአንድነት ትቆሙ ዘንድ ጥሪያችንን እናስተላፋለን፡፡
4. በነዚህ የጸሎትና የምሕላ ጊዜያት የደነደኑ ልቦች ወደ ልቦናቸው ተመልሰው የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥሪ ሰምተው የማይፈጽሙ እንደሆነ
4.1. በየካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናት እና ምእመናን ከጠዋቱ 11፡00 ጀምሮ በየአጥብያቸው በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት እስከ ጠዋቱ 1፡30 ድረስ ሥርዓተ ቅዳሴው ከተፈጸመ በኃላ ከጠዋቱ 2፡00 ላይ ሁሉም ገዳማት፣ አድባራት እና አብያተ ክርስቲያናት በተመሳሳይ ሰዓት ደወል በመደወል ምእመናን በሙሉ እስከ ጠዋቱ 2፡30 ድረስ እንዲሰባሰቡ በማድረግ ከየአጥቢያው በመነሳት የጥምቀተ ባህር ወይም የመስቀል አደባባይ ላይ ታቦተ ሕጉን በማክበር፤ በማጀብ በዝማሬ እና በምህላ በአንድ ቦታ በመሰባሰብ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
4.2. የዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ዝርዝር አፈጻጸም መመሪያን በተመለከተ በአጭር ጊዜ ውስጥ የምናሳውቃችሁ መሆኑን አውቃችሁ ዝግጅት እንድታደርጉ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፡፡
5. ማንኛውም የመንግሥት የጸጥታ ኃይል ቤተ ክርስቲያን ያዘዘችውን ሰላማዊ ጥያቄ በሚከወንበት ማንኛውም የአገልግሎት ጊዜ ተግባራቱ ሰላማዊ መሆናቸውን በመገንዘብ ተገቢውን ጥበቃ የማድረግ ግዴታ እንዳለበት አውቆ እንዲያስፈጽም ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፤
. በደወል የተጠሩ ደወሎቻችን
🔔᳀᯼͟͞ ͟͞ ͟͞ ̸͟͞ ͟͞ ͟͞ ͟͞ ̸͞͝ ͟͞᳀͟͞ ͟͞ ̸͟͞ ͟͞ ͟͞ ͞ ͟͞ ̸ ͟͞ ͟͞᯼᳀🔔

"ወይደምጽ ድምጸ መጥቅዕ ወኲሉ ዘሰምዓ ይደነግፅ ⇨ ደወል [ረቂቅ ነጋሪት] ይሰማል : የሰማውም ሁሉ ይደነግጣል" 【ዕዝራ ሱቱኤል ፬፥፳፫】

በትናንቱ የቅዱስ ሲኖዶስ አዋጅ ውሥጥ እንዲህ የሚል "ሲኖዲቆን" ተቀምጧል

🖤 "በሰባቱ የጸሎት ሰዓታት እየተጠበቀ በተመሳሳይ ሰዓታት ለአምስት ደቂቃ ያህል በማያቋርጥ ደወል በመደወል የማስተጋባት ሥራ እንዲሠራ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤" 🖤

መደወሉ ከሰይጣን ማሳት እንድናመልጥ ፣ ከጠላት ወጥመድ እንድንወጣ ፣ ከገቢረ ኃጢኣት እንድንለይ ፣ ከድካም ሀኬት እንድንበረታ… እንደ ጴጥሮስ ዶሮ ልብን ለመመለስ የሚደወል ነው። እንደ ቃጭል ወይም መረዋ አነስተኛው ደወል ቃለ ዓዋዲ ተብሎ የመጠራቱ ምክንያት ይህ ነው።

በምሕላና በእግዚኦታ ጊዜ ደወል እንዲደወል ቤተክርስቲያን የምታውጀው በምሳሌነቱ ⇨ ከመስቀሉ አጠገብ ያልተለዩ የክርስቶስን መከራ አይተው ያለቀሱ የእመቤታችንና የቅዱሱን ሐዋርያ ዮሐንስ ወንጌላዊ የልቅሶ ድምፅ በማሰብ ነው። ዛሬም የጌታቸውን መንገድ ለሚከተሉ በእውነተኛ ምስክርነት ሕይወታቸው በግፍ ለሚያልፍ እንደቅጠል ለሚረግፍ ሰማዕታት መታሰቢያ እንዲሆን ይደወላል።

ደወል የራቁትን ያቀርባል የተበተኑትን ይሰበስባል ለዚህም ነው በዓላትና አጽዋማትን ሰብስቦ የሚነግረን የባሕረ ሐሳቡ ማውጫ ጥንተ መጥቅዕ የሚባለው!

የአጽዋማትና በዓላት በየዓመቱ መመላለስ መሪ የሆነ መባጃ ሐመሩንም የዓመቱን መጥቅዕ እና የመጥቅዕን ዕለተ ተውሳክ በመደመር እናገኘዋለን።

ለሐመሩ (ለመርከቡ) እና ለመጥቅዑ (ለደወሉ) መነሻ በኩፋ ፮፥፳፯ የተነገረው የኖኅ መርከብና ደወል ነው።

ኖኅ መርከቡን ከጥፋት ማምለጫ እንዲሆነው ሲያሰናዳ ቁመቱ ሦስት ክንድ፣ ስፋቱ አንድ ክንድ አድርጎ ደወል እንደሠራና በየዕለቱ በነግህ ለጸሎት፣ በቀትር ለምግብ፣ በሰርክ ለማሰናበት ሦስት ጊዜ እየደወለ ይጠቀምበት እንደነበር በመጽሐፈ ቀሌምንጦስ ምዕራፍ ፫ ከቁጥር ፷፪ ጀምሮ ተዘግቦልናል።

"ኖኅም… ሦስት ክንድ ርዝማኔና አንድ ክንድ ጉድን ያለው ደወል ከሊባኖስ ዕንጨት ሠራ። መርከቡን በሚሠራበት ጊዜ ሁልጊዜ ጧት ጧት ለሥራ እንዲሠበሰቡ ደወል ይደውላል። ቀትር ሲሆን ምሳ ለመብላት እንዲሰበሰቡ ይደውላል ቀኑ አልፎ ምሽት ሲሆን ወደየቤታቸው እንዲገቡ ይደውላል። መርከቡን ለምን እንደሚሠራው ጠያቂ ቢነሳበት እግዚአብሔር የጥፋት ውሃን ይህቺን የረከሰች ምድር ለማጠብ እንደሚያዘንምና። በዚሁም ምክንያት ራሱን ሚስቱን ልጆቹንና ሚስቶቻቸውን ለማዳን መርከብን እንዲሠራ መታዘዙን ይገልፅለታል።"

የደውሉም አገልግሎት እንዲህ እያለ ከኖኅ እስከ ሙሴ ደርሷል። ሙሴም ማኅበሩን መሰብሰቢያ የብር መለከቶችን አዘጋጅቶ እንደነበር መጽሐፍ ይነግረናል
“ሁለት የብር መለከቶች አጠፍጥፈህ ለአንተ አድርግ ማኅበሩን ለመጥራት ከሰፈራቸውም ለማስጓዝ ይሁኑልህ።” 【ዘኁ ፲፥፪】

እኛም ይህን ምሳሌ ይዘን በቤተክርስቲያናችን ለመንፈሳዊ አገልግሎት እንጠቀምበታለን። በተለይ እንደኖኅ ዘመን የሥራ ደወል ከጥፋት ለማምለጥ የምንሠራውን ይህን መርከብ የሆነ ሰውነታችንን ሕንፃ ሥላሴ አካላችንን በንሰሐና በቁርባን እንድናበጃጀው ደወሉ ያለማቋረጥ ሲመታ እንሰማለን።
አገልግሎቱም ሌሊት የተኙትን በመቀስቀስ ለሰዓታትና ለማኅሌት እንዲተጉ ፲፭ ጊዜ ይደወላል፤ በነግህ በ፫ ሠዓት ለዋዜማ ቁመት ፲፪ ጊዜ ይደወላል፤ በሰርክ ለቅዳሴ መግቢያ ፫ ጊዜ ይደወላል፤ በጻዑ ንዑሰ ክርስቲያን ጊዜ ፫ ጊዜ ይደወላል፤ በእግዚኦታ ጊዜ ፯ ጊዜ ይደወላል፤ በድርገት ጊዜ ፭ ጊዜ ይደወላል።

ምሳሌውም የቀርነ መለከት ሲሆን ፲፭ ጊዜ መደወሉ የ፲፭ቱ ነቢያት ምሳሌ ነው፤ ፲፪ ጊዜ መደወሉ የ፲፪ቱ ሐዋርያት ምሳሌ ነው፤ ሌሊት መደወሉ ነቢያት በዘመነ ጽልመት መኖራቸው ምሳሌ ነው፤ በሰርክ መደወሉ ብርሃን የተባለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመገለጹ ምሳሌ ነው።

በሥርዓተ ቅዳሴው ላይ ብቻ ለ፭ ምክንያቶች ሲደወል እንሰማለን፤ ምሳሌውን ከነምክንያቱ እንመልከት

፩】. የተጋብኦ ደወል
✦━━━━━━━
ካህናትና ምእመናን ለልዩ ልዩ አገልግሎት ወደ ቤተክርስቲያን እንዲሰበሰቡ የሚጠራ የቤተ ክርስቲያን በሮች ከመከፈታቸው በፊት የሚደወል ነው።

ምሳሌነቱ፦
✔️ የትንቢተ ነቢያት ነው:: ደውሉ ካህናትና ምእመናንን ቀስቅሶ ለአገልግሎት /ለጸሎት/ እንደሚዘጋጅ፤ ነቢያትም የሕዝቡን ልብ እየቀሰቀሱ፤ ከአምልኮተ ጣኦት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር እየመለሱ፤ ለአዲስ ኪዳን አገልግሎት እንዲዘጋጁ ያደርጉ እንደነበር ያሳያል።

፪】.የቅዳሴ መግቢያ ደወል
✦━━━━━━━━━━
ይህ ደወል ካህናት መሥዋዕቱን አክብረው ከቤተልሔም ወደ መቅደስ ሲጓዙ የሚደወል ነው፡፡

ምሳሌነቱ፦
✔️ የብሥራተ ገብርኤል ነው፤ አንድም ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ እነሆ የዓለሙን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ (ዮሐ ፩፥፪፱፡፡) በማለት የጮኸው /የተናገረው/ ድምፅ ነው።

፫】. የወንጌል ደወል
✦━━━━━━━
ይህ ደወል “ፃኡ” በሚባልበት የቅዳሴ ክፍል መካከል የሚደወል ነው።

ምሳሌነቱ፦
✔️ የስብከተ ዮሐንስ፣ የሐዋርያትና የሰብአ አርድዕት ልቅሶ ነው። (ሉቃ፫፥፫‐፯፡፡) ይህ ደወል ከተደወለ በኋላ ያለው የቅዳሴ ክፍል ፍሬ ቅዳሴ ይባላል:: ይህም መሥዋዕተ ወንጌል የሆነው የክርስቶስ ሥጋውና ደሙ የሚቀርብበት ነው:: ደወሉ ሐዋርያትና አርድእት ቅዱሳት አንስትም ጌታችን በተሰቀለ ጊዜ ያዘኑትን ሐዘን፥ ያለቅሱትንም ለቅሶ፣ ያፈሰሱትንም ዕንባ የሚያስታውስ ነው።

፬】.የእግዚኦታ ደወል
✦━━━━━━━
በቅዳሴ ጊዜ መጨረሻ አካባቢ ካህናትና ምእመናን በቅብብሎሽ /በማስተዘዘል /፵፩፥ ፵፩/ ጊዜ እግዚኦታ ያደርሳሉ:: በዚህን ጊዜ ከላይ የገለጽነው ደወል ይደወላል::

ምሳሌነቱ፦
✔️ ከመስቀሉ አጠገብ ያልተለዩ የክርስቶስን መከራ አይተው ያለቀሱ የእመቤታችንና የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ የልቅሶ ድምፅ ነው:: /ዮሐ ፲፱፥፳፭‐፳፰፡፡/

፭】.የድርገት ደወል
✦━━━━━━━
ሥጋ ወደሙ ለቆራብያን ሊሰጥ (ሊታደል) ልዑካኑ ከመቅደስ ወደ ቅድስት ሲወጡ የሚደወል ነው።

ምሳሌነቱ፦
✔️ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ በገነዙት ጊዜ ያለቀሱት ልቅሶ ነው:: አንድም የሐዋርያትና የሰብአ አርድእት ትምህርት ነው:: ዮሴፍና ኒቆዲሞስ የጌታችንን ሥጋ በገነዙበት ጊዜ እያለቅሱ ነፍስ የተለየውን፣ መለኮት የተዋሐደውን የጌታችንን ሥጋ ገንዘው ባዲስ መቃብር “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር…” ብለው እንዳኖሩት፤ ካህናትም በቅዳሴ ጊዜ ነፍስ የተለየውን መለኮት ያልተለየውን (የተዋሐደውን) የክርስቶስን ሥጋና ደም እንዲያቀብሉ ደወል ይደወላል:: ሐዋርያትና ሰብአ አርድእት ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ወንጌልን በመላው ዓለም አስተምረዋል፤ ሰብከዋል። ዞረው ማስተማራቸውንና በስብከታቸው የሰው ልጆች ሁሉ ከሞት ወደ ሕይወት መሸጋገራቸውን ለማሰብና ምእምናንም ዛሬ በደወሉ ድምፅ የዘለዓለም ሕይወት ወደሚያገኙበት፥ የክርስቶስ ሥጋና ደም እንደሚቀርቡ ለማመልከት ነው::

ደወሉ ትናንት ሁከት በነገሡባቸው ቦታዎች ምእመናንን ለክብር ወደ ምድራዊቷ ቤተመቅደስ ብቻ ሳይሆን ወደሰማይ ማደርያ ወደ ዘልዓለማዊው መኖርያ ጠርቷል። ጉባኤ ጳጳሳቱም "ተገቢውን ሲኖዶሳዊ እና ሃይማኖታዊ ጸሎት በማድረግ በሁሉም አጥቢያ ሥርዓተ ፍትሐት እንዲፈጸምላቸው" ትዕዛዝ አስተላልፏል።
ደወል የጠራቸው ደውሎቻችንን በዚህ የሰማይ አክሊል ዋጋ መንገድ እንድንከተላቸው የበቃን ሁላችንን ያድርገን !

✒️ በቴዎድሮስ በለጠ ጥር አማኑኤል ፳፻፲፭ ዓ.ም. 】

☞ የቤተክርስቲያንን ድል አድራጊነት የሰማዕቱን ክብር የሚገልጥ ይህን ሥዕል ለላከልኝ ሠዓሊ ኃይለማርያም ሽመልስ ምስጋናዬ ላቅ ያለ ነው!
«እኔን ብትጥሉኝ ሀገሩ ሰላም ይሆናል!»
°°°°°°°━✦•✧༒✧•✦━°°°°°°°
በደወሉ ተቀስቅሰን ነቅተን ይሆን?

ዮናስ ሆይ "ምንት ያነውመከ?"
↳ “ ምነው ተኝተሃል? እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ያስበን እንደ ሆነ ተነሥተህ አምላክህን ጥራ” እንጂ (ቁ. ፮)

ያ… ከእግዚአብሔር ርቆ እግዚአብሔርም ርቆት ምሕረት እያባረረ መዓት የሚጠራ ዮናስማ እኛ ነን።

ዛሬ ላይ የደረሰብንና የደረስንበትን ጥፋት በማጤን ብናየው ሌሎቹ ስተውና አሳስተው የመጣ ሳይሆን እኛው ባለማዕተቦቹ አጥፍተንና ጠፍተን ያመጣነው ለመሆኑ እንደ ነቢዩ ዮናስ በላያችን የወጣብን ዕጣ ያሳብቃል፤

ከሁሉ በተለየ እግዚአብሔርን አውቃለሁ በእግዚአብሔርም እታወቃለሁ የምንል ግን በሁከቱ መኃል ከጾምና ከጸሎት ርቀን ተኝተንና ነፋስ በሚጠራ ወጀቡን በሚያጠነክር ዘመቻ ተጠምዶ ወደ ውሥጠኛው የጎጥ ⇨ የዘር ⇨ የነገድ ⇨ የዜግነት ክፍል ወርደን ከባድ እንቅልፍ ጥሎናል!

በአንቂ ስብከትና በአነቃቂ ንግግር (motivational speech & Inspirational sermon) ከተኛንበት ነቅተናል የምንል ዮናሶች ሆይ ከእንቅልፋችን ስንላቀቅ ምን ብለን ምን አድርገን ይሆን?

◆ ዮናስን ቀስቅሰው ፭ ጥያቄ ጠይቀውታል “ ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት እንዳገኘን እባክህ ንገረን፤ ሥራህ ምንድር ነው? ከወዴትስ መጣህ? አገርህስ ወዴት ነው? ወይስ ከማን ወገን ነህ? አሉት።” 【 ዮና ፲፥፰】

ከ፭ቱ ለ፬ቱ ምላሽ ሠጠ አንዱን ግን አልፎታል ፦ ሊቃውንቱ “አይቴ ብሔርከ ላሉት ግን አይመልስም” ይላሉ።

ያኛው ዮናስ ዮናስ "ባህርና የብሱን የፈጠረ የሰማይን አምላክ እግዚአብሔርን አመልካለሁ …" ይላል እንጂ እንደዚህኛው ዮናስ ጠቅላይ ቤተክህነቱን በጎጥ እሳት ፣ ቅዱስ ሲኖዶሱንም በዘር ምድጃ ላይ ጥዶ «የዚህን ሀገር፣ የዛኛውን ሰፈር የዚህን መንደር እግዚአብሔር ነው የማመልከው» አላለም። (ቁ ፱)

◆ ያኛው ዮናስ ስለችችሩ ምንጭ "አነ አእመርኩ ከመ በእንቲአየ መጽአክሙ ዝንቱ ማዕበል ዐቢይ ⇨ ይህ ታላቅ ማዕበል በእኔ ምክንያት እንዳገኛችሁ አውቃለሁ … " አለ እንጂ እንደዚህኛው ዮናስ «ይህማ የመጣብን በነእንትና ስውር አጀንዳ ፣ በእነ እገሌ ሤራ ፣ በነ እገሊት ሸፍጥ… ነው» አላለም (ቁ ፲፪)

◆ ያኛው ዮናስ ስለመፍትኼው "ንስኡኒ ወወርዉኒ ውስተ ባህር ወየኀድገክሙ ⇨ (እኔኑ) አንሥታችሁ ወደ ባሕር ጣሉኝ፥ ባሕሩም ጸጥ ይልላችኋል" አለ እንጂ እንደዚህኛው ዮናስ «በሌሎች ድካምና ስንፍና በእናንተ በደልና ኃጢዓት ይህ ሁሉ በመምጣቱ እነርሱ ቢወገዱ እናንተ ብትጠፉ ችግሩ ተወግዶ መከራው ጠፍቶ መረጋጋት ይሰፍናል» አላለም (ቁ ፲፪)

ብቻ ከዚያኛው ዮናስ ይልቅ ይኼኛው ዮናሶች እጅግ እናሳዝናለን! በጎጥሸ እሳት በዘር ምድጃ ላይ እንደተኛን ነው የምንሰበከው ፣ ዛሬም የሸዋና የጎጃም ሲኖዶስ እያልን ነው የምንጾመው 😢

ሰው ከዚህ አደንዛዥ የዘረኝነት እንቅልፍ ሳይነቃ ፣ ከዚህ ከፋፋይ የጎጥ ቅዠት ሳይባንን ቢጾምና ቢጸልይ ፣ ቢሰበክና ቢማር ፣ ቢሰብክና ቢያስተምር … ጥቅሙ ምንድነው? የተነገረውን አድምጦ እንዴት በልቡ ሊያኖረው ይቻለዋል?

እስኪ መጀመሪያ የተኛ ይንቃ ⇨የነቃ ደግሞ ይማር ⇨ ከዚያ የተማረ ደግሞ ይሰበክ ።

ጠቢቡም ቀዳሚ ሊሆን ስለሚገባው ተግባር እንዲህ ይላል

" አንቅሆ እምዐቢይ ንዋም ለዘይነውም !"
【የተኛ ሰውን ከጽኑ እንቅልፍ ቀስቅሰው】ከዚያ አስተምረህ ከስንፍና ለየው ስንፍናውን በእውቀት ሲረታው ከስሜት ርቆ ይሰበክልሃል። ያለዚያስ?

… ያለዚያማ

"ዘይነግሮ ለአብድ ከመ ዘይነግሮ ለድቁስ ፤ ወሶበ አኅለቀ ነጊሮቶ ይብለከ ምንተ ትቤ ? ⇨ ለሰነፍ ሰው የሚነግር (የሚሰብክ) ሰው ለተኛ ሰው እንደሚነግር ሰው ነው ነግረኸው ከጨረስህ በኋላ ምን ተናገርህ? (ምን ነበር ያልከው?) ይልሃል።" 【ሲራ· ፳፪ ፥፰】

አያሌ «የማኅበረሰብእ አንቂዎች» እየተፈራረቁ በአግባቡ እንዳንተኛ እያባነኑንና በአግባቡ እንዳንነቃ እያቃዡን ከእምነት አጣልተው ወይ ኑሯችንን ሳናልም ወይ ደግሞ ሕልማችንን ሳንኖር እንድንዳክር ጋርደውናል።

አዝማሪው
«የተኛን ቀስቅሶ በማርዳት የለፋ
መች ቀብር ይሄዳል ጡሩምባ ሚነፋ?» ብሏል

"ጥሩምባ ነፊ ቀብር አይሔድም" እያሉ ቀስቃሾቹ ተኝተው፣ አንቂዎቹም ፈዘው ቢገኙ ተያይዞ ማለቅ ነው። ብቻ የነቃ ቀስቃሽ ከደብሩ ፡ ያረዳ አልቃሽ ከቀብሩ ብናይ ሸጋ ነበር።

ከመአቱ እንዲመለስ መቅሰፍቱንም እንዲያስወግድልን የምንችል ነነዌን ከጥፋት መንገድ እናውጣት ካልቻልን ራሳችን ከነነዌ እንውጣ፤ የሆነለት ሌላውን ከጥፋት ለይቶ ለማዳን ይድከም ያልሆነለት ስለራሱ ነፍስ ከመጥፋት ተለይቶ ከነነዌ ይውጣ።

"ነብዩ ዮናስ የተናገረው ነገር ያለውድ በግድ ይደረጋልና ልጄ አሁንም ከነነዌ ውጣ።" 【ጦቢ ፲፬፥፰】

ቴዎድሮስ በለጠ ጥር ፳፱ ነነዌ ፳፻፲፭ ዓ.ም.
አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ.pdf
250.6 KB
ከሀይማኖት ጋር ተያይዞ ባለው ወቅታዊ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ላይ ከኢሰመጉ የተሰጠ መግለጫ

የኢሰመጉ አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ-ጥር 30/2015 ዓ.ም
አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ 
 
ከሀይማኖት ጋር ተያይዞ ባለው ወቅታዊ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ላይ  ከኢሰመጉ የተሰጠ መግለጫ 
      ጥር 30/2015 ዓ.ም

መግቢያ፡ 
ኢሰመጉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ጋር ተያይዘው የሚነሱ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳዮችን ሲከታተል የቆየ ሲሆን ከእዚህም ጋር ተያይዞ እሁድ ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ሲኖዶስ እውቅና ባልተሰጣቸው ሶስት ሊቃነ ጳጳሳት አማካኝነት 26 ኤጲስ ቆጶሳት የተሾሙ ሲሆን ይህንንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ህገ-ወጥ ያለውን ድርጊት ተከትሎ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በዋናነት በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ አብያተክርስቲያናት ውስጥ ከቅዱስ ሲኖዶሱ እውቅና ያልተሰጣቸው አዲስ የተሾሙ ኤጲስ ቆጶሳት ወደ አብያተክርስቲያናት በመንግስት የጸጥታ አካላት ጭምር ታጅበው በመግባታቸው እና ምዕመኑ ይህንን ባለመቀበሉ ምክንያት በተፈጠሩ ግጭቶች በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ተፈጽመዋል፡፡ ለማሳያነት  በሻሸመኔ ከተማ ከመንግስት የጸጥታ አካላት በተተኮሱ ጥይቶች የሰዎች ህይወት ማለፉን፣ የአካል ጉዳት መድረሱን እንዲሁም በያቤሎ አካባቢ በቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ላይ ጭምር እስራት፣ ማዋከብ እና ድብደባ መፈጸሙን እና በተለያዩ አካባቢዎች ይህንን አካሄድ በተቃወሙ የእምነቱ ተከታዮች ላይ እና የቤተክርሲቲያኒቱ አገልጋዮች ላይ ድብደባዎች እንደተፈጸሙ፣ ቤት ሰብሮ በመግባት የህግ ስነስርዓትን ያልተከተሉ እስራቶች እንደተከናወኑ እና በርካታ ቁጥር ያለቸው ሰዎችም በብዛት እየታሰሩ መሆኑን ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡

በተጨማሪም ከቅዱስ ሲኖዶሱ በተላለፈ መልእክት መሰረት ጥቁር ልብስ የለበሱ ሰዎችን በአንዳንድ አካባቢዎች እስራት፣ እንግልት እና መዋከብ እየተፈጸመባቸው እንደሆነና ይህንንም ድርጊት አንዳንድ ተቋማት እና ድርጅቶች በተመሳሳይ መልኩ እየፈጸሙት መሆኑን ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡ ስለሆነም ይህ ጉዳይ ወደየማይሆን አቅጣጫ በመሄድ ተባብሶ ከፍተኛ የሰውና የንብረት ጥፋቶችን ከማስከተሉ በፊት የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉና የበኩላቸውን ሀላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

ኢሰመጉ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ በደረሱ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ላይ ተጨማሪ የምርመራ ስራዎችን በመስራት ዝርዝር ዘገባ የሚያዘጋጅ መሆኑን ከወዲሁ ይገልጻል

ተያያዥ የህግ ድንጋጌዎች፡

የኢፌዲሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ 27 የሀይማኖት ነጻነት መብትን የያዘ ሲሆን በአንቀጽ 11(3) ላይ መንግስት በሀይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ  እና ሀይማኖትም በመንግስት ጉዳይ ላይ ጣልቃ እንደማይገባ ይደነግጋል፡፡ የእዚህ ንዑስ አንቀጽ ዋነኛ አላማ ከህገ መንግስቱ ማብራሪያ መረዳት እንደሚቻለው ሀይማኖትን ከመንግስት ጣልቃ ገብነት እና ከፖለቲካ ጫና ነጻ እንዲሆን በማድረግ የዜጎችን የእምነት ነጻነት ላለመገደብ ሲሆን መንግስት በሀይማኖት ተቋማት መንፈሳዊ ስራ ላይ ጣልቃ መግባት እንደሌለበት ይገልጻል፡፡ በተጨማሪም መንግስት የማህበረሰቡን ደህንነት እና ሰላማዊ መስተጋብር የማስከበር እንዲሁም የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለበት ከህገ-መንግስቱ አንቀጽ 13 እና ከህገ መንግስቱ ማብራሪያ አገላለጽ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህም መብት በአፍሪካ ቻርተር የግለሰቦች እና ህዝቦች መብቶች አንቀጽ 8 ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡

የሰብዓዊ መብቶች ዓለም አቀፍ መግለጫ እና የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃልኪዳን አንቀጽ 18 ላይ ማንኛውም ሰው የሀሳብ፣ የህሊናና የሀይማኖት ነጻነት እንዳለው ይደነግጋሉ፡፡

የኢሰመጉ ጥሪ፡ 
 ሀይማኖት የማህበራዊ መስተጋብር አንዱ ክፍልና መብት በመሆኑ መንግስት የማህበረሰቡን ሰላማዊ እንቅስቃሴ የማስጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት  በመረዳት የፌደራል እና የክልል መንግስታት የዜጎችን ደህንነት እንዲያስከብር፣

 የፌደራል መንግስት እንዲሁም የክልል መንግስታት እና በዋናነት ችግሮች እየተፈጠሩበት ያለው  የኦሮሚያ ክልል መንግስት የጸጥታ አካላት  በቤተክርስቲያን እውቅና ያልተሰጣቸውን ኤጲስ ቆጶሳት በተለያዩ አብያተክርስቲያናት መመደብ አግባብ አይደለም በማለት የተቃወሙ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ላይ የሚፈጽሙትን ከህግ አግባብ ውጪ የሆነ ግድያ፣ አካል ማቁሰል፣ ድብደባ እና እስር እንዲያቆሙ እንዲሁም ከቅዱስ ሲኖዶስ በተላለፈው መልእክት መሰረት ጥቁር ልብስ የለበሱ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ እስሮች እና ድብደባዎችን እንዲያስቆም፣ ከህግ  አግባብ ውጪ ግድያ፣ እስራት፣ ደብደባ እና ሌሎችም የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች የፈጸሙ የጸጥታ አካላትን መንግስት በህግ ተጠያቂ  እንዲያደርግና ይህንንም ለህዝብ ይፋ እንዲያደርግ እንዲሁም ጉዳዩ መፍትሄ እንዳያገኝና ወደ ግጭት እንዲቀየር ለማድረግ ነገሮችን ወደ ሌላ አቅጣጫ የሚስቡ አካላት ሁሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ኢሰመጉ በዚህ አጋጣሚ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
Forwarded from ተεพ๑δr๑ร (አግናጥዮስ)𝕿𝖊𝖜𝖔𝖉𝖗𝖔𝖘 𝕭𝖊𝖑𝖊𝖙𝖊 𝕸𝖊𝖓𝖌𝖎𝖘𝖙𝖚 Ignatius Theophoros (Ἰγνάτιος Θεοφόρος)
🖤 ኑ ለቅሶ እንድረስ ⚫️▪️▪️
°°°°°°°°°°°°°°°
ያሳደገችኝ ደብር ተቀመጠች አሉኝ ለቅሶ
ውለታዋ ተረስቶ ክብር ማዕረጓ ተድሶ
በትእቢት ተረማመደ ቅጥር ጊቢዋን ጥሶ

ማር ይዘንባል ማር ነበር ዜማ ቅኝቷ
ስጋጃው በደም ራሰ ጥይት ዘነበ በቤቷ

ሰንደቃላማ ነበረ "የዘለለ–ዕለት" ውበቷ
ኑ እንድረሳት ለቅሶ ማቅ ለብሷል ጉልላቷ
.
.
.
ኑ እንላቀስ … ያልሰማ ይስማ መርዶ
ደብራችን አንብታለች መጋረጃዋ ተቀዶ
.
.
.

ፊደል ቀራጭ ስንዱዬ እኔን ልጅሽ ፊደል ጠፋኝ
ሀ ብለሽ ያስቆጠርሽው ሆ ብሎ ፊትሽ ደፋኝ
በጸአዳ ግምጃሽ ፈንታ ከልሽን ሳየው ከፋኝ
.
.
.
ለምጣዱ ሲባል ትለፍ ብለን ነበር አይጧ
ሰስተንላት ነገን ፈርተን ይሔ ቀን እንዳይመጣ
.
.
.
ብንጠፋ ብናጠፋ ከደጀ ሰላም ብንርቅም
የተስፋ ርስታችን ናት ‘ተዋህዶን’ አንለቅም
አንድ ፓትርይርክ (አንድ መንበር) አንድ ሲኖዶስ…
ከአንዲት ‘ቤተስኪያን’ ወዲያ አቻ ክብር አላውቅም
ልጄ በካህን እንጂ በአቶ አይጠመቅም!

✒️ ምሥራቅ ተረፈ

ተውሳክ ዘዚአየ (የእኔ ጭማሪ)

በመግደላቸው ሳያፍሩ የይቅርታ ቃል ሳይመልሱ
ጥቁር አውልቁ ይሉናል ጭራሽ ለቅሶ አትድረሱ

የሚያድግ ልጅ ከጠላ ፡ ሟች አረጋዊ ከረገመ
ያኔ ነው የሞት ጥላ ያጠላው ፡ ብርሃን ተስፋ የጨለመ
ዘውድ አንበሳው የተደፋ ፡ ዙፋን እሳቱ የከሰመ

አቢይ ማዕበል ተነስቶ ፡ የተርሴስ መርከብ ቢናወጥ
ዮናስ ከባህር ቢጣል ፡ ተላልፎ ለሞት ቢሰጥ
አየሁ … ትንቢት ሲሻር ፡ ካውሬው መንጋጋ ሲያመልጥ
እንባው መአት ሲገድብ ፡ ልቅሶው አለቱን ሲያቀልጥ
ተዋህዶ ሳትከፈል ነነዌም ሳትገለበጥ !
… አየሁ!

https://youtu.be/FEMGkYsesdQ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ - ‌🇴‌🇷‌🇹‌🇭‌🇴‌🇩‌🇴‌🇽 ‌🇹‌🇪‌🇼‌🇦‌🇭‌🇩‌🇴
Photo
በስመ አብ፤ ወወልድ፤ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ከጥር ፳፱ እስከ የካቲት ፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ለ ፫ ተከታታይ ቀናት በመላው ዓለም የታወጀው የነነዌ ፆም እና ምሕላ መጠናቀቅን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ::
++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++
በትንቢተ ዮናስ በሰፊው እንደተጠቀሰው የነነዌ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት ላይ ስለአመጹ እና ግብራቸውም በእግዚአብሔር ፊት አጸያፊ በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር ዮናስን “ተነስተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፤ ክፋታቸውም ወደ ፊቴ ወጥቷልና በእርስዋ ላይ ስበክ” በማለት አዘዘው፡፡ ትንቢተ ዮናስ ምዕ ፩ ቁጥር ፪ ዮናስም ድምፁን ከፍ አድርጎ ለነነዌ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ሲሰብክ “የነነዌ ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፤ ለጾም አዋጅ ነገሩ፤ ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ፡፡ ወሬውም ወደ ነነዌ ንጉሥ ደረሰ፤ እርሱም ከዙፋኑ ተነስቶ መጎናጸፊያውን አወለቀ ማቅም ለበሰ፤ በአመድም ላይ ተቀመጠ፡፡ አዋጅም አስነገረ፤ በነነዌ ውስጥ የንጉሡንና የመኳንንቱን ትእዛዝ አሳወጀ፤ እንዲህም አለ ሰዎችና እንስሶች፤ ላሞችና በጎች አንዳችን አይቅመሱ፣ አይሰማሩ፣ ውኃንም አይጠጡ፤ ሰዎችና እንስሶችም በማቅ ይከደኑ፣ ወደ እግዚአብሔርም በብርቱ ጩኸት ይጩኹ፤ ሰዎችም ሁሉ ከክፉ መንገዳቸውና በእጃቸው ካለው ግፍ ይመለሱ፡፡ እኛ እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ተመልሶ ይጸጸት እንደሆነ ማን ያውቃል፡፡ እግዚአብሔርም ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሥራቸውንም አየ፤ እግዚአብሔርም ያደርግባቸው ዘንድ በተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም” ትንቢተ ዮናስ ፫፡ ፭-፲

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ይህን የነነዌ ሰዎች ፆም መነሻ በማድረግ የነነዌ ሰዎችን በምሕረቱ የጎበኘ አምላክ እኛንም በምሕረቱ ይቅር ይለን ዘንድ በየዓመቱ በአዋጅ በመፆም አምላካችንን ስንማጸንበት ኖረናል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባዔ በጥር ፳፮ ቀን ፳፻፲፭ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በወሰነው መሠረት የካቲት ፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም የተጠናቀቀው የነነዌ ፆምና ምሕላ ልዩ በሆነ በመንፈሳዊ የንስሐ ጸሎት በሰላም ተጠናቋል፡፡

በምሕላውም ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ጀምሮ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤ ካህናት፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ አገልጋዮች እና ምእመናን እንደነነዌ ሰዎች ጥቁር ለብሰን ጠዋትና ማታ በጸሎት ፤ በምሕላ፤ ቀን በቅዳሴ እንዲሁም በሰባቱ የጸሎት ጊዜያት ፈጣሪያችንን ስንለምን እና ስንማጸን የቆየንበት ምክንያት በቤተክርስቲያናችን ላይ የመጣው ፈተና እጅግ በጣም ከባድ በመሆኑ ነው፡፡

በዚህ የጾምና የንስሐ ወቅት ምእመናን ልጆቻችን የአባቶቻችሁን ጥሪ ሰምታችሁ፤ የሹመኞችን ማዋክብና እስር ሳትፈሩ ጥቁር ለብሳችሁ ጠዋትና ማታ በጾምና በምሕላ፣ ቀን በቅዳሴ በቤተክርስቲያን ቅጥር እየተገኛችሁ ለአምላካችን ያቀረባችሁትን ጸሎት እና ምሕላ እግዚአብሔር ሰምቶ ለችግራችን መፍትሄ፣ ለሀገራችን ሰላምን እንደሚሰጠን እምነታችን ጽኑ ነው፡፡ እናንተም ምእመናን የቤተ ክርስቲያንን ጥሪ ሰምታችሁ ለሃይማኖታችሁ፣ ለሀገራችሁ አንድነትና ሰላም ያላችሁን ጥልቅ ፍቅር ስለገለፃችሁም ያገኘነው መንፈሳዊ ብርታት ሳንገልፅላችሁ አናልፍም፡፡

በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በእናታችን በቅድስት ድንግል ማርያም እና በቅዱሳን አማላጅነት፣ በመላእክት ተራዳኢነት በፍፁም ፍቅርና አንድነት የያዝነውን ጸሎት እና ምሕላ አጠናቀናል፡፡ ችግራችንን ለአምላካችን በለቅሶ እና በጩኸት ነግረናል፡፡ ከዚህ በኋላ መከራው ቢጸና፣ የመከራው ጊዜ እንኳን ቢረዝም እግዚአብሔር በመከራ ውስጥ ሊያፀናን እና ሊያበረታታን አስቦ በመሆኑ በፍፁም አንናወጽም፡፡ ከእነኚህ መከራዎች በኃላም ታሪክን ጽፈን ሃይማኖታችንን ጠብቀን እና አስጠብቀን በመንፈሳዊ ጽናት እና ተጋድሎ እንሻገራለን፡፡

ጥቃቱ የቤተ ክርስቲያንን እውነት በካዱና በእውነተኛዋ ቤተ ክርስቲያን መካከል ነው፡፡ ይህም የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሃይማኖት፤ ቀኖና እና አስተዳደራዊ ሕግጋትን ጥሰው ሕገወጥ የጳጳሳት ሢመት በመደረጉ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ቅዱስ ሲኖዶስ በሕገ ቤተ ክርስቲያንና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት በጥር ፲፰ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ይህን ጥሰት የፈፀሙትን ግለሰቦች አውግዛ ከቤተ ክርስቲያን ኅብረት የለየቻቸው ቢሆንም ጉዳዩ ከግለሰቦቹ በላይ በመንግሥት ስልጣን ላይ ባሉና ጽንፈኛ በሆኑ ፖለቲከኞች እንዲሁም የሌላ እምነት ተከታዮች ጭምር የሚደገፍ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያንን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈላት ይገኛል፡፡

እየተፈጸመ ያለው ድርጊት በሰማያዊ መንፈሳዊ ዓለምና በምድራዊ ሥጋዊ ዓለም መካከል ስለሆነ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥም የቤተ ክርስቲያን ክብርና ተቋማዊ ልዕልና ተደፍሯል፡፡ የቤተክርስቲያን ቅጥሮች መሣሪያ በያዙ አካላትና በመንግሥት የጸጥታ መዋቅር በኃይልና በጉልበት ተወሯል፡፡ ሊቃነ ጳጳሳት አባቶች ለብዙ ዓመታት ከኖሩበት አህጉረ ስብከት ያለአንዳች የሕግ መሠረት በጸጥታ መዋቅሮች ተባረዋል፡፡ በነጻነት የመንቀሳቀስ መብቶቻቸው ተገድቦም በግዞት ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ተደርገዋል፡፡ ወደ አህጉረ ስብከታቸውም ተመልሰው መግባት እንዳይችሉ እቀባ ተደርጎባቸዋል፡፡ ካህናት አባቶች እና ምእመናንም ያለአንዳች የሕግ መሠረት በየእስር ቤቱ ያለበቂ ምክንያት በሕገወጥ መንገድ ታጉረዋል፡፡ በጸጥታ ኃይል ከመጠን በላይ ከመደብደባቸው የተነሳ የሞት፣ የከባድ እና ቀላል አካል ጉዳት እንዲደርስባቸው ምክንያት ሆኗል፡፡ በአጠቃላይም በመንግሥት ኃይሎች ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈፅሞባቸዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያን ይህ ሁሉ በደል ቢፈጸምባትም ናዛዜ ሕዙናን የሆነው አምላካችን ለቤተ ክርስቲያናችን እና ለሀገራችን መፍትሔ እንዲያመጣልን፣ መንግሥትም ወደ ልቡ ተመልሶ ቤተክርስቲያንን እንዲያከብርና እንዲጠብቅ በሚል ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ይህን ጾም የነነዌ ሰዎች እንዳደረጉት ጥቁር ለብሰን በፍፁም ኃዘን ወደ አምላካችን እንድንጮህ ቅዱስ ሲኖዶስ ትእዛዝ ባስተላለፈበት ማግስት በሻሸመኔ ደብረ ስብሐት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ሕገወጡን ቡድን በኃይል ለማስገባት በመንግሥት የጸጥታ መዋቅሮች በተወሰደ አሰቃቂ እርምጃ እስከ አሁን በደረሰን መረጃ ቁጥራቸው ከ፴ በላይ የሚሆኑ ካህናትን እና አገልጋዮችን ጨምሮ የቤተ ክርስቲያናችን ልጆች ቅጥሯ አይደፈርም፣ ቤተክርስቲያን በተወገዙ ግለሰቦች አትረክስም በሚል ለሃይማኖታቸው ሰማእትነትን ተቀብለዋል፡፡ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ልጆቿም በደረሰባቸው ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት ምክንያት በሕክምና ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ሁሉ በደል በኋላም እስከ አሁን ድረስ የሞቱትን በአግባቡ መቅበርና የተጎዱትን በበቂ ሁኔታ ማሳከም ሳንችል ቀርተናል፡፡ እነዚህ ሰማዕታት በዚህ ኃጢያት በበዛበት ዘመን ለቤተክርስቲያን እስከሞት ድረስ በመታመን ለቤተ ክርስቲያንና ለምእመናን የጽናት ተምሳሌት በመሆናቸው ቤተክርስቲያን ስትዘክራቸው ትኖራለች፡፡ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያን በልጆቿ ላይ እየደረሰ ባለው ሞት፤ እርዛት፤ እስራት እና መልከ ብዙ በሆነው መከራ ብታዝንም ለክርስትና እውነተኛነት ምስክሮች የሆኑ አዳዲስ ቅዱሳን ሰማእታትን በማግኘቷም እጅግ ደስ ትሰኛለች፡፡
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ - ‌🇴‌🇷‌🇹‌🇭‌🇴‌🇩‌🇴‌🇽 ‌🇹‌🇪‌🇼‌🇦‌🇭‌🇩‌🇴
Photo
ጾሙ ከተጀመረም በኋላ ሕዝቡ ወደ አምላኩ እንዳይጮህ እና እንዳይጸልይ ለማወክ የሕዝብ አስተዳዳሪ ሆነው የተሾሙ የመንግሥት ሹማምንት ሊያገለግሉት ኃላፊነት የተቀበሉበትን የሀገሪቱን ሕግ ጥሰው ምእመናን ልጆቻችን ጥቁር ለብሰው ወደ መሥሪያ ቤት እንዳይገቡና በመንግሥት ቢሮዎችም አገልግሎት እንዳያገኙ በተለይም በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እና አንዳንድ በፌዴራል እና በከተማ መስተዳድር ቢሮዎች ጥቁር የለበሱ እና በሀዘን ላይ ያሉ ልጆቻችንን በማሠር ሲያንገላቱ በዓይናቸው ያዩ ምስክሮች አረጋግጠውልናል፡፡ በዚህም ሹማምንት ስልጣናቸውን ቤተ ክርስቲያንን ለማጥቃት እየተጠቀሙበት መሆኑን እና ለቤተ ክርስቲያናችንም ሆነ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ከፍተኛ ንቀት እና ጥላቻ ያላቸው መሆኑን ተረድተናል፡፡

ይህ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየደረሰ ያለው መከራና በደል በዚህ ዘመን በጉልህ የሚጠቀስ የቤተ ክርስቲያን የስደትና የመከራ ጊዜ ነው፡፡ ይህ የቤተ ክርስቲያን የስደትና የመከራ ጊዜ በቤተ ክርስቲያኒቱ የታሪክ መዝገብ እና በመጽሐፈ ስንክሳር ተመዝግቦ ይቀመጣል፡፡ ለትውልድም ይተላለፋል፡፡ ይህ የፈተና ዘመን ያልፋል፤ ነገር ግን በዚህ ታሪክ ውስጥ ከእውነት ጎን የቆማችሁ ስማችሁ በታሪክ እና በወርቅ ቀለም ሲፃፍ በቤተክርስቲያን ላይ መከራ ያበዛችሁ ክፉ ታሪካችሁን ዛሬ በእጃችሁ ጽፋችሁ አልፋችኋል፡፡

በዚህ አጋጣሚ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውጭ ሌሎች የክልል ርዕሳን መስተዳድሮችና ከተሞች በተለይም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፤ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት፤ የሲዳማ ክልላዊ መንግስት፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት፤ የሱማሌ ክልላዊ መንግሥት፤ የቤንሻንጉል ክልላዊ መንግሥት፣ የሐረሪ ክልላዊ መንግሥት፣ የአፋርና ጋምቤላ ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት፤ በጎፋ ዞን የሳውላ ከተማ እና ሌሎች ስማቸውን ያልጠቀስናቸው መንግሥታዊ ተቋማት የቤተ ክርስቲያናችንን ጥሪ በመከተል በአግባቡ ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር የወሰዳችሁ ፍትሐዊ እና ሕጋዊ መፍትሔዎችን እናደንቃለን፣ በቤተ ክርስቲያንም ስም እናመሰግናለን፡፡ እንዲሁም ሀዘናችሁ ሀዘናችን ነው ብላችሁ ከጎናችን የተሰለፋችሁ አኃት አብያተ ክርስቲያናት፤ የሃይማኖት ተቋማት፣ ድርጅቶች እና ጉባኤያት፤ የእስልምና እምነት ተከታዮች፤ በእምነት የማትመስሉን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ስላደረጋችሁልንና ስለምታደርጉልን እርዳታና ትብብር በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም እናመሰግናለን፡፡
ጸሎተ ምሕላውን ስናውጅ መንግሥት ሕግ አክብሮ እንዲያስከብር፣ የቤተክርስቲያኒቱን ክብር እና ልዕልና እንዲያከብር፣ በሃይማኖታችን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን እንዲያቆምና ወደ ውስጡ ማየት እንዲችል ነበር:: ይህ ድርጊት እስከ አሁን ድረስ ግን መንግሥት ለዘመናት ሕጋዊ ተቋም እና የሀገር ባለውለታ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያንን ከመስማት እና ችግሯን ከመቅረፍ ይልቅ የማዋከቡን ሥራ አጠናክሮ ቀጥሎበታል፡፡ በዚህም መንግሥት ችግሮችን ኃላፊነት ተሰምቶት እንዲፈታ ያደርገዋል የሚል እምነት ቢኖረንም አገዛዙ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ልቡ መደንደኑን መመልከታችን በእጅጉ ልባችንን ሰብሮታል፡፡

በተለይም ቤተ ክርስቲያናችን ያወጀችው የ፫ ቀናት ጸሎትና ምህላ በአግባቡ እንኳን ሳይጠናቀቅ ከመንግሥት ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ወቅታዊ የፀጥታ ጉዳይን አስመልክቶ በየካቲት ፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም የተሰጠው የሰልፍ ክልከላ መግለጫ መንግሥት አሁንም ችግሩን ለመፍታት ሳይሆን ቤተክርስቲያኒቱን ለአንዴና ለመጨረሻ ለማውደምና ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማጥፋት የታወጀ አዋጅ መሆኑን በጽኑ እንድናምን አድርጎናል፡፡

በመግለጫውም፡-
፩ኛ. በእምነቱ አባቶች በተመሳሳይ መልኩ ሰልፍ ተጠርቷል በማለት መጥቀሱ የቤተክርስቲያን የመጨረሻው አካል የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ አውግዞ የለያቸውን አካላት የእምነቱ ተከታይ ማድረግ ብቻ ሳይሆን መብት ያላቸው ሕጋዊ አካላትና የቤተ ክርስቲያን አባቶች አድርጎ መጥራቱ አሁንም ላይ ማብራርያ ለመስጠት መሞከሩ የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር የሚነካ እና የሚያጠለሽ እንዲሁም ሕግና ሥርዓትን ከማስከበር ይልቅ ለሕገ ወጦች ጠበቃ ሆኖ የሚከራከረው መንግሥት መሆኑን ጭምር ለመረዳት ችለናል፡፡ በመሆኑም ቤተክርስቲያን በመንግሥት የደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ተሰጠ የተባለው መግለጫ የቤተ ክርስቲያናችንን ሕጋዊ መብት የገፈፈ እና ሕገ ወጥ መግለጫ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያን አትቀበለውም፡፡
፪ኛ. ጉዳዩን የውጪ እና የውስጥ ጠላቶች የፈጠሩት ነው በማለት የተለመደውን ፖለቲካዊ ቅርፅ ለማስያዝ መሞከርም ቤተክርስቲንያንም ሆነ ሕዝብን መናቅ በመሆኑ የምንቀበለው አይሆንም፡፡ ቤተ ክርስቲያን በተለይ ላለፉት ፬ ዓመታት በሀሰተኛ ትርክት ልጆቿ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል መከራን ሲቀበሉ ችግሮችን በሆደ ሰፊነት ችላ ያለፈችው የሀገር መሠረት እንዳይናጋ፣ ቅጥሯ እንዳይደፈር በማሰብና በሀገር አንድነት ላይ ባላት የማይናወጽ ጽኑ አቋም ምክንያት መሆኑን መንገር ለቀባሪው ማርዳት ነው፡፡ ጉዳዩ ግልፅ የሆነ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ሆኖ እያለና መፍትሄውም በመንግሥት እጅ የሚገኝ ብቻ መሆኑ እየታወቀ የፖለቲካ ቅርፅ ለማስያዝ መሞከር ችግሩን ያባብሰው እንደሆን እንጂ አይፈታውም፡፡

በሰሞኑም ቤተ ክርስቲያናችን በመዋቅር የምትመራ እና ልጆቿም ድምጽዋን አውቀው በአግባቡ የሚሰሟት መሆኑ እየታወቀ ሆነ ተብሎ ቃላት አጠቃቀሙ እንኳን ኦርቶዶክሳዊ ያልሆነ የሀሰት እና ጸብ አጫሪ የሆኑ መልእክቶችን በአደባባይ የተለጠፉ መሆናቸውን ሲታይ ምን ያህል ጉዳዩን ላልተገባ ፖለቲካዊ ጥቅም እንደተፈለገ ለመረዳት ችለናል፡፡ ይህ ተለጠፈ የተባለውም ሕገ ወጥ ጽሑፍ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ያልሆነና ፈጽሞም ሊሆን የማይችል መሆኑን ጭምር ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡

፫ኛ. የትኛውም ሰልፍ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ማድረግ አይቻልም በማለት የተደረገው ክልከላን በተመለከተም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ውስጥ መሠረታዊ መብት ሆኖ የተጠቀሰ እና በሕገ መንግሥቱም አንቀፅ ፴ ላይ በግልጽ የተደነገገ በመሆኑ መንግሥት ራሱ የሚመራበትን ሕገ መንግሥት ማክበርና ማስከበር ይኖርበታል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ላይ ከላይ የተጠቀሰው ከፍተኛ መከራና በደል ምክንያት ከብዙ ሺህ ዓመታት በላይ ጸንታ የመጣችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በእኛ በልጆቿ ዘመን ስትፈርስ ዝም ብሎ መመልከት በጭራሽ የሚታሰብ አይሆንም፡፡

ይህን በደላችንን ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ለማሳወቅ እና መንግሥትም ከሚያደርገው ጣልቃ ገብነትና አፈና ወጥቶ ሕግ እንዲያከብር እና እንዲያስከብር የጠራነው የየካቲት ፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ሰላማዊ ሰልፍም መንግሥት ተገቢውን ጥበቃ በማድረግ እንድናከናውን መፍቀድ አሊያም የጠየቅናቸውን ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄዎቻችንን በአግባቡ እና አንድ በአንድ መመለስ አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን ደግመን ደጋግመን ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥም የሚደርስብንን ሞት፣ መከራና ስደት እኛ አባቶች ከመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ጋር ደስ ብሎን የምንቀበለው እንጂ ቤተ ክርስቲያናችን እና ሀገራችን ስትፈርስ ቆመን የምንመለከት፣ ዝም የሚል አንደበትና የሚሸከም ኀሊና የማይኖረን መሆኑን በአጽንዖት እናሳስባለን፡፡
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ - ‌🇴‌🇷‌🇹‌🇭‌🇴‌🇩‌🇴‌🇽 ‌🇹‌🇪‌🇼‌🇦‌🇭‌🇩‌🇴
Photo
መንግስት ከአጉል እልከኝነቱ ወጥቶ ከሕገ ወጦቹ ግለሰቦች ጋር በመተባበር በአደባባይ እየፈጸመ ያለውን የሕግ ጥሰት ዛሬን ጨምሮ በቀጣዮቹ ፪/ሁለት/ ቀናት ውስጥ እንዲያቆም እና ሕግ እና ሥርዓትን እንዲያስከብር፣ በኃይል የወረራቸውን መንበረ ጵጵስና እና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ለቆ ለቤተክርስቲያኒቱ ሕጋዊ መዋቅር እንዲያስረክብ፣ ያለአግባብ ያሠራቸውን ካህናት እና ምእመናን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቅ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ለፈፀመው በደል በአደባባይ ይቅርታ እንዲጠይቅ፤ በካህናት እና ምእመናን ላይ ለደረሰው ሞት እና የአካል ጉዳት ተገቢውን ካሳ እንዲክስ እና የወደሙ ንብረቶቿን እንዲጠግን በጥብቅ እንጠይቃለን ፡፡

መንግሥት በዚሁ አካሄድ ሕግ እየጣሰ እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር እና ልእልና እያዋረደ የሚቀጥል ከሆነ ቤተ ክርስቲያን መንግሥት የጣሰውን ሕግ መሠረት በማድረግ መብቷን ለማስከበር እስከአሁን ድረስ ፍጹም ሰላማዊ የሆነውን እንቅስቃሴዋን አድማሱን በማስፋት በየካቲት ፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ለማድረግ ያቀደችውንና ያሳወቀችውን ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ ያለማንም ከልካይነት በራሷ አደባባይ የምታከናውን መሆኑን እያሳወቅን መንግሥትም ድርሻው ሰልፉ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ብቻ መሆኑን እያሳሰብን ዛሬም ቢሆን መንግሥት ቆም ብሎ በማሰብ ከእኛ ከአባቶች ጋር ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊና መንፈሳዊ የአስተዳደር ሥርዓታችንን ባልጣሰ መልኩ ለመነጋገር እና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ጥረት ካደረገ በውይይት ለመፍታት መንፈሳዊ በራችን ክፍት መሆኑንም እናሳውቃለን፡፡

ከዚህ ውጭ ግን በሁለቱ አባቶች መካከል የተፈጠረ ችግር እየተባለ የሚነገረው ፖለቲካዊ ጨዋታ የመንግሥት እንጂ በሀገሪቱ ሕጋዊ ሰውነት የሌላቸውና ከቤተ ክርስቲያን የተለዩ ግለሰቦች ጋር ማነጻጸር ሕገ መንግሥታዊም ሆነ ሞራላዊ የሕግ መሠረት የለውም፡፡

ስለዚህ ቤተ ክርስቲያናችን የጠራችውን ሰላማዊ እና ሕጋዊ የሆነ የመብት ጥያቄ የማፈን ሂደትን በጥብቅ እንቃወማለን፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን እስከአሁን ባደረጋችሁት ጽናትና ተጋድሎ ሃይማኖታችሁንና ቅድስት ቤተ ክርስቲያንችሁን እንዳላሳፈራችሁ ሁሉ አሁንም ከስሜታዊነት በወጣ ሁኔታ በከፍተኛ ጽናት እና ጥንካሬ የአባቶቻችሁን ድምጽ ብቻ እንድትሰሙ፣ ቤተ ክርስቲያንን በየአጥቢያችሁ ተደራጅታችሁ እንድትጠብቁ፤ ለአባቶቻችሁ መንፈሳዊ ጥሪ ፈጣን ምላሽ እንድትሰጡ፣ እየመጣው ላለ መከራና ስደት ለመንፈሳዊ ተጋድሎ እንድትዘጋጁና በፍፁም መንፈሳዊ ጨዋነት በአንድነት የመጣብንን ፈተና እንድትወጡ አደራ እያልን አባታዊ መልእክታችንን እያስተላለፍን ሰላማዊ ሰልፉን በተመለከተም በአጭር ጊዜ ውስጥ ዝርዝር መግለጫ የምንሰጥ መሆኑን እያሳውቅን በዚህ ጥቃት መስዋእትነት የከፈሉ እና ያረፉ ልጆቻችንን ነፍሳቸውን በአጸደ ገነት በክብር ያሳርፍልን እያልን ጸሎተ ፍትሐትም በየደረጃው የሚከናወን መሆኑን እያሳወቅን በተለያዬ ጊዜ ዛሬን ጨምሮ በወለቴ እና በሰበታ ከተሞች የደረሰውን የአካል ጉዳት እና ሞት እግዚአብሔር ምህረት እና መጽናናቱን ያድልልን፡፡ እግዚአብሔርም ገድላችሁን፣ ጽናታችሁንና ጸሎታችሁን ይቀበል፤ የቅዱሳን አምላክ ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

“እግዚአብሔር ሀገራችንን ይባርክ”
የካቲት ፪ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም.
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
አፀምእ ዘይነብበኒ እግዚአብሔር አምላኪየ

እግዚአብሔር አምላኬ የሚናገረኝን እሰማለሁ

Wanta waaqayyo dubbatu kophaa nan dhaggeeffadha

ነቲ እግዚአብሔር ኣምላኽ ዚብሎ ኽሰምዕ እየ

I will hear what God the LORD will speak
.
.
.
🖤 መዝሙረ ዳዊት መዝሙር ፹፬ ቁጥር ፰ 🖤
የቅዱስ ሲኖዶስን መግለጫ በቤተ ክርስቲያናችን ኦፊሻል የዩቱብ ቻናል ተከታተሉ ። በዚያውም ሰብስክራይብ አድርጉ ። በጣም አሳዛኙ ነገር አሁን ሰሞኑን ነው 373k የገባው እንጂ 260k ነው የነበረው ። ይኸ ምን ማለት መሰላችሁ የራሳችንን ትተን የሌላውን ያውም የማይጠቅመንን ነው የምናሞቀው ። ስለሆነም ሚዲያችንን እናበረታታ ።



https://www.youtube.com/live/5m0qgfjKolU?feature=share
2025/07/06 09:45:47
Back to Top
HTML Embed Code: