Telegram Web Link
እኔንም ያውቀኛል ማለት ነው🤔
...

ሁለት ጓደኛሞች ነበሩ፤ ገጽታቸው የሚለያዩ ጓደኞች፤ አንደኛው በመንፈሳዊ ሕይወቱ የበረታ የጠነከረ ፤ ዘወትር ቃለ እግዚአብሔርን የሚሰማ ቅዱሳት መጻሕፍትንም የሚያነብ ነበር፥ ጓደኛው ግን ኃጢአት ጀርባውን ያጎበጠችው ፤ ለእግዚአብሔር ጊዜ መስጠትን መለማመድ ያቃተው ሰው ነበር፤

በአንድ ወቅት በአቅራቢያቸው ባለች ቤተ ክርስቲያን አንድ ትልቅ ጉባኤ ተዘጋጀ፤ በጉባኤውም ትልቅ መምህር እንዲያስተምሩ ተጋብዘው ነበር፤ በመንፈሳዊ ሕይወቱ የበረታው ልጅ ይህን ሲመለከት ጓደኛውን እንደምንም ወትውቶና ይህ መምህር ይመጣል ተብሏል፤ ና እንሂድ እስኪ ጉባኤ እንሳተፍ ብሎ አሳምኖ ይዞት ይሄዳል፤

ጉባኤውን ይመራ የነበረው መርሐግብር መሪ ግን ለጉባኤው መክፈቻ መዝሙር ካዘመረ በኋላ፤ "ለዛሬ የጋበዝናቸው መምህር ሊገኙልን አልቻሉም፤" ብሎ ተነገረ፤ "ያው ግን በእግዚአብሔር ቤት በጉባኤ የተሰባሰብነው የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ስለሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ ክፍል አውጥቼ ላንብብላችሁና ጉባኤያችንን እንፈጽማለን" አለ፤

በዚህ ጊዜ ሁሉም የሚነበበውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ለማዳመጥ ተዘጋጀ፤ መርሐግብር መሪውም ከማቴዎስ ወንጌል ይህን ክፍል አነበበ፤
"...
የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ የዳዊት ልጅ የአብርሃም ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ትውልድ መጽሐፍ።
² አብርሃም ይስሐቅን ወለደ፤ ይስሐቅም ያዕቆብን ወለደ፤ ያዕቆብም ይሁዳንና ወንድሞቹን ወለደ፤
³ ይሁዳም ከትዕማር ፋሬስንና ዛራን ወለደ፤ ፋሬስም ኤስሮምን ወለደ፤
⁴ ኤስሮምም አራምን ወለደ፤ አራምም አሚናዳብን ወለደ፤ አሚናዳብም ነአሶንን ወለደ፤ ነአሶንም ሰልሞንን ወለደ፤


¹⁵ ኤልዩድም አልዓዛርን ወለደ፤ አልዓዛርም ማታንን ወለደ፤ ማታንም ያዕቆብን ወለደ፤
¹⁶ ያዕቆብም ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን የወለደች የማርያምን እጮኛ ዮሴፍን ወለደ።
... "


ይህን ካነበበ በኋላ ስለ ቃሉ የአምላካችን ስም የተመሰገነ ይሁን ብሎ በጸሎት አሳርገ፤

ይህ በሕይወቱ ብርቱ የሆነው ልጅ በመርሐ ግብር መሪው ደስተኛ አልሆነም፤ ይመጣሉ ብሎ ያሰባቸው መምህር መቅረት ሳያንስ ስንትና ስንት የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ተግሳጽ ትምህርት እያለ እንዴት ይህን መርጦ ያነባል ብሎ ተናዷል፤ ሁሉንም አስቦ... ና እንማር ብሎ ጎትጉቶ ለምኖ ያመጣውን ጓደኛውን ፊት ማየት ከበደው፤ ጓደኛው ግን አንገቱን ደፍቶ ስቅስቅ ብሎ እያለቀሰ ነበር፤ ለምን ታለቅሳለህ ሲለው መልሱ ይህ ነበር፤

"... እነዚህ ሁሉ ሰዎች በእግዚአብሔር የታወቁና የታሰቡ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ያሉ ናቸው፤ በዚህ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሱት፤ እነዚህን ሁሉ እግዚአብሔር የሚያስታውስና የሚያውቅ ከሆነማ እኔንም ይስባል ያውቀኝማል ማለት ነው..."

የጓደኛው መልስ ከሁሉም ነገር በላይ አስደነቀው፤ ብርቱ ነኝ ብሎ የሚያስብ የራሱን ሕይወት እንዲመለከትም አደረገው፤

ወንድም እህቶቼ እመኑኝ እግዚአብሔር እያንዳንዳችንን ያውቀናል ፤ ያስበንማል፤ ዝም ያለ ቢመስለን እንኳ ለጊዜው ነው የምንከብርበት ጊዜ እስኪደርስ ድረስ ነው፤ በስኬት ላይ ስኬት ቢሰጠንም ሁሌም አብሮን እንዳለ ሲነግረን ነው፤

ጌታም ይላል...

ማቴዎስ 10
...
²⁹ ሁለት ድንቢጦች በአምስት ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ያለ አባታችሁ ፈቃድ በምድር ላይ አትወድቅም።
³⁰ የእናንተስ የራሳችሁ ጠጉር ሁሉ እንኳ ተቈጥሮአል።
³¹ እንግዲህ አትፍሩ ከብዙ ድንቢጦች እናንተ ትበልጣላችሁ።



ሐምሌ ፪ - ፳፻፲፯ ዓ.ም
መነሻ ሐሳብ - በአንድ ወቅት ከተሰጠ ስብከት

             
#ለመቀላቀል

@ortodoxtewahedo

#ለሃሳብ አስተያየት

@ortodoxtewahedoo

#ወስብሐት_ለእግዚአብሔር
37👏6🥰3
ብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አባቶቻችን ሐዋርያትን ሰማዕትነት በተቀበሉበት ቀናት በዓላት ሰይማ ታከብራቸዋለች፡፡ እንዲሁም በስማቸው የተሰየመውን ጾም በመጾም አሠረ ፍኖታቸውን ይከተሉ ዘንድ ምእመናንን ታሳስባለች፡፡ በሐምሌ ፭ ቀን ደግሞ የደጋጎቹን ሐዋርያት የቅዱስ ጴጥሮስና የቅዱስ ጳውሎስን በዓል ታደርጋለች፡፡ የእነዚህ ቅዱሳን አባቶቻችን በዓል መደረጉ በአንድ ቀን ሰማዕትነት በመቀበላቸው ነው፡፡

ሁለቱ ቅዱሳን ሐዋርያት አመራረጣቸው በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ የጥሪው መንገድ ግን ይለያይ ነበር፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ለሐዋርያነት የተመረጠው ጌታችን በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲመላለስ ከወንድሙ እንድርያስ ጋር ሆኖ ዓሣ ለማጥመድ መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ፤ ወደ እነርሱም ቀርቦ “በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ” አላቸው፡፡ ወዲያውም መረባቸውን ትተው ተከተሉት፡፡ (ማቴ.፬፥፲፰‐፳)

በአንጻሩ የቅዱስ ጳውሎስ አመራረጥ ደግሞ በተአምር ነው፤ ይኸውም እንዲህ ነው፡፡ በቀደመ ስሙ ሳውል ተብሎ የሚታወቀው ይህ ሐዋርያ የቤተ ክርስቲያን አሳዳጅ ነበር፡፡ ቀዳሜ ሰማዕት እስጢፋኖስ በአይሁድ እጅ ሲወገር የተስማማ የገዳዮቹንም ልብስ ጠባቂ ነበር፡፡ (የሐዋ. ፯፥፶፰-፷)

ቅዱስ መጽሐፍ “ሳውል ግን ቤተ ክርስቲያንን ያፈርስ ነበር ወደ ሁሉም ቤት እየገባ ወንዶችንም ሴቶችንም እየጐተተ ወደ ወህኒ አሳልፎ ይሰጥ ነበር፡፡ . . . ሳውል ግን የጌታን ደቀ መዛሙርት እንዲገድላቸው እየዛተ . . .” እንዲል፡፡ (የሐዋ.፰፥፫፤፱፥፩) በክርስቶስ አምነው የተጠመቁ ክርስቲያኖችን ለማሳደድ ከሊቁ ካህናቱ ዘንድ የፈቃድ ደብዳቤ ጠየቀ፡፡ ይህን ዓላማውን ለማስፈጸም ወደ ደማስቆ ሲጓዝ በርሱ ዙሪያ ከሰማይ መብረቅ ወረደ፤ ዐይኖቹም ታወሩ፤ ወደ ምድርም ወደቀ፡፡

በዚያም ሳለ “ሳውል ሳውል፥ ስለምን ታሳድደኛለህ” የሚለውን ድምፅ ሰማ፡፡ ያነጋገረው ሳውል የሚያሳድደው ጌታ ነበር፡፡ “አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ፤ የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብኻል” አለው፡፡ ከዚያም በመፍራትና በመንቀጥቀጥ ተነሥቶ ወደ ከተማው ገባ፡፡ ሦስት ቀንም ሳይበላ ሳይጠጣ ተቀመጠ፡፡ ሐናንያ የተባለው ከደቀ መዛሙርት ወገን የሆነ ወደ እርሱ ዘንድ ቀርቦ ጸለየለት፤ ዐይኖቹም ተፈወሱ፤ ተነሥቶም ተጠመቀ፡፡ (የሐዋ.፱፥፩‐፲፰)

ቅዱስ ጳውሎስ በወቅቱ ስለሆነው ነገር ለቆሮንቶስ ምእመናን ሲተረክላቸው “ ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ፡፡ እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ ነኝና፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስላሳደድሁ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ” እንዲል፡፡ (፩ኛቆሮ.፰፥፱)

የቤተ ሰብ ሕይወታቸው
ቅዱስ ጴጥሮስ የተወለደው በቤተ ሳይዳ ነው፡፡ ቤተ ሰቦቹ ደግሞ በቅፍርናሆም ይኖሩ ነበር፡፡ የኦሪት መጻሕፍትን ያልተማረ ከዝቅተኛው የማኅበረሰብ ክፍል የተገኘ ሰው ነበር፡፡ (የሐዋ. ፬፥፲፫) ጳውሎስ ደግሞ በኪልቅያ በምትገኘው በጠርሴስ ተወለደ፡፡ ከአይሁድ ወገን ከብንያም ወገን ነበር፡፡ (ፊል.፫፥፭) በጠርሴስም ሳለ በገማልያል እግር ሥር የኦሪት ትምህርቱን ተማረ፤ በትምህርቱም የተመሰከረለት ነበር፤ (የሐዋ.፳፪፥፫፤፳፮፥፳፬) ይህ የሚያሳየው የእግዚአብሔር መንግሥት ለተማሩትም ላልተማሩትም፣ ለባለጸጎችም ለድሆችም የተዘጋጀ መሆኑን ነው፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ ባለ ትዳር ነበር፡፡ አማቱም ታማ በነበር ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤቷ ገብቶ እንደፈወሳት በወንጌል ተጽፏል፡፡ (ማቴ.፰፥፲፬‐፲፭) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ድንግል ነበር፡፡ “ሰው ሁሉ እንደ እኔ ሊሆን እወዳለሁና ነገር ግን፥ እያንዳንዱ ከእግዚአብሔር ለራሱ የጸጋ ስጦታ አለው፥ አንዱ እንደዚህ ሁለተኛውም እንደዚያ፡፡ ላላገቡና ለመበለቶች ግን እላለሁ፡- እንደ እኔ ቢኖሩ ለእነርሱ መልካም ነው፤ ነገር ግን፥ በምኞት ከመቃጠል መጋባት ይሻላልና፥ ራሳቸውን መግዛት ባይችሉ ያግቡ” በማለት ለቆሮንቶስ ምእመናን ጽፏል፡፡ (፩ኛቆሮ. ፯፥፯‐፱) ቤተ ክርስቲያን እንደ ጴጥሮስ ያገቡ እንደ ጳውሎስ ያሉ ደናግላንን ይዛ የምትገኘው ጌታችን ሁሉንም ወደ እርሱ ስለጠራ ነው፡፡

የስማቸው መለወጥ
ቅዱስ ጴጥሮስ የዮና ልጅ ስምዖን ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡ (ዮሐ.፳፩፥፲፭) ነገር ግን ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን “እናንተስ ማን ትሉታላችሁ” ብሎ ሲጠይቃቸው ሐዋርያው ተነሣና፡- “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብሎ መለሰለት፡፡ ያን ጊዜም ጌታችን “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ፡፡ እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም አለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሏትም” በማለት ጴጥሮስ ብሎ ሰየመው፡፡ (ማቴ.፲፮፥፲፯—፲፰)

ጳውሎስን ደግሞ ጌታችን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጠራው በመጀመሪያ ስሙ ሳውል ብሎ ጠራው፤ በምስክርነቱ ጊዜ ደግሞ “ጳውሎስ ሆይ፥ በኢየሩሳሌም ስለ እኔ እንደ መሰከርህ እንዲሁ በሮሜም ትመሰክርልኝ ዘንድ ይገባሃልና፥ አይዞህ አለው፡፡” (የሐዋ.፳፫፥፲፩)

አገልግሎታቸው
የቅዱስ ጴጥሮስ አገልግሎቱ በአብዛኛው ሕግ ለተጻፈላቸው፣ ነቢያት ለተላኩላቸው፣ መሥዋዕት ለሚያቀርቡ፣ ግርዛት ለተሰጣቸው ለአይሁድ ነበር፡፡ በአንጻሩ ደግሞ የቅዱስ ጳውሎስ አገልግሎት የነበረው በአሕዛብ መካከል ነበር፡፡ ይህንንም ሲመሰክር “ለተገረዙት ሐዋርያ እንዲሆን ለጴጥሮስ የሠራለት፥ ለእኔ ደግሞ ለአሕዛብ ሐዋርያ እንድሆን ሠርቷልና፡፡” ብሏል፡፡ (ገላ.፪፥፯‐፰) እንዲያውም በአንድ ወቅት ጳውሎስና በርናባስን አይሁድ ትምህርታቸውን በተቃወሟቸው ጊዜ “እነሆ ወደ አሕዛብ ዘወር እንላለን እንዲሁ ጌታ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ለማዳን ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ ብሎ አዞናልና” ብለው ነበር፡፡ (የሐዋ. ፲፫፥፵፮—፵፯)

በበዓለ ኀምሳ ቅዱሳን አባቶቻችን ሐዋርያት የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ከተቀበሉ በኋላ ጴጥሮስና ዮሐንስ በትምህርታቸው በኢየሩሳሌም ለነበሩ ነፍሳት ደረሱ፡፡ በአንድ ቀን ብቻ ሦስት ሺህ ነፍሳት ወደ ቤተ ክርስቲያን ተጨመሩ፡፡ (የሐዋ.፪) ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ “ከሁላችሁ ይልቅ በልሳኖች እናገራለሁና እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ” በማለት ስለተሰጠው የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ መስክሯል፡፡ (፩ኛቆሮ. ፲፬፥፲፰) ሁለቱም ሐዋርያት በምእመናን ላይ እጃቸውን በመጫን ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ያሳድሩ ነበር፡፡ (የሐዋ.፰፥፲፬፤፲፱፥፭‐፮)

በአገልግሎታቸው ድንቅ ተአምራትን ፈጽመዋል፡፡ ለምሳሌ ስለ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፡፡ “እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ የሚያስገርም ተአምራት ያደርግ ነበር፤ ስለዚህም ከአካሉ ጨርቅ ወይም ልብስ ወደ ድውዮች ይወስዱ ነበር፥ ደዌያቸውም ይለቃቸው ነበር ክፉዎች መናፍስትም ይወጡ ነበር፡፡” (የሐዋ.፲፱፥፲፩—፲፪) በኢዮጴም ጣቢታ የምትባል አገልጋይን ከሞተች፤ አጥበውም በሰገነት ከአኖሯት በኋላ ቅዱስ ጴጥሮስ ካለበት ተጠርቶ ከጸለየ በኋላ ጣቢታ ሆይ ተነሽ ሲላት ዐይኖቿን እንደከፈተች ተጽፏል፡፡ (የሐዋ.፱፥፴፮—፵፪) በተመሳሳይ ቅዱስ ጳውሎስ አውጤኪስ የሚባል ከሦስተኛ ደርብ ወደ ታች ወድቆ የሞተን ጎልማሳ እንዲነሣ አድርጓል፡፡ (የሐዋ.፳፥፯—፲፪)

             
#ለመቀላቀል

@ortodoxtewahedo

#ለሃሳብ አስተያየት

@ortodoxtewahedoo

#ወስብሐት_ለእግዚአብሔር
5
...ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ሲሆን ከሰማይ ታላቅ ነጎድጓድ ድምጽ ተሰማ ጌታችን መላአክትን አስከትሎ ወደ አባታችን ወረደ፤ ከሰማይ ወደ ምድር ህብሩ አምሳያው ልዩ ልዩ የሆነ እንደ ጸሐይና እንደ ጨረቃ የሚያበራ እንደ ወንጪፍ ድንጋይ ይወረወር ነበር ከዚያ የነበሩ ሁሉ ፈሩ ወደ ኃላም ሸሹ ምድር ራደች ተራሮች ኮረብቶች ተናወጡ ብርቱ ጩህት ንውጽውጽታም ሆነ።

« ወዳጄ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሰላም ላንተ ይሁን እነሆ የማይታበል ቃል ኪዳን እገባልኃለው ስምህን የጠራ መታሰቢያህን ያደረገውን፤ እጣን ቋጥሮ ግብር ሰፍሮ መባ ይዞ ቤትህ የመጣውን እምርልኃለው አንተ ከገባህበት ገነት መንግስተ ሰማያት አገባዋለሁ አለው ። »

#የአባታችን_በረከታቸው_ረድኤታቸው_አማላጅነታቸው_አይለየን_አሜን

             
#ለመቀላቀል

@ortodoxtewahedo

#ለሃሳብ አስተያየት

@ortodoxtewahedoo

#ወስብሐት_ለእግዚአብሔር
42🙏4
ሀምሌ ➎ ጴጥሮስ ወ ጳውሎስ እንኳን አደረሳችሁ

ሐምሌ ➎ ብርሃናተዓለም ቅዱስ ጴጥሮስ ወ ቅዱስ ጳውሎስ የእረፍታቸው መታሰቢያ እለት ነው።

ቅዱስ ጳውሎስ ወንጌል በማሰፋፋቱ ምክንያት ታስሮ ከዚያም አንገቱን በስለት ተሰይፎ ሰማዕትነትን ተቀብሏል

ቅዱስ ጴጥሮስ‹‹እንደ ክብር ንጉሥ እንደ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ አቁማችሁ ሳይኾን፣ ዘቅዝቃችሁ ስቀሉኝ›ብሎ በመስቀል ተዘቅዝቆ በመሰቀል በሮም አደባባይ ሰማዕትነትን ተቀብሏል።

በረከታቸው ይደርብን አሜን 🙏

             
#ለመቀላቀል

@ortodoxtewahedo

#ለሃሳብ አስተያየት

@ortodoxtewahedoo

#ወስብሐት_ለእግዚአብሔር
15🙏2
2025/07/12 21:32:33
Back to Top
HTML Embed Code: