Telegram Web Link
"ኒቆዲሞስ የዐብይ ፆም ሰባተኛ ሰንበት"

ኒቆዲሞስ ማን ነዉ?

ኒቆዲሞስ ቃሉ የግሪክ ሲሆን ድል ማድረግን ወይም አሸናፊነትን ያመለክታል፡: ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ፥ ከአይሁድ አለቆችና መምህራና አንዱ ነው። በወንጌለ ዮሐንስ ምዕራፍ ሦስት ከፈሪሳውያን ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የተባለ አንድ ሰው እንደነበረና እርሱም በሌሊት ወደ ጌታችን መጥቶ እንደተማረ ተጠቅሷል። (ዮሐ ፩-፪)

በአይሁድ አለቆች ፊትም ”ሕጋችን አስቀድሞ ሳይሰማ የሠራውንም ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን?” በማለት ስለ መድኃኔዓለም ክርስቶስ የተናገረ እሱ ነው። እነርሱ ግን በክርስቶስ እግዚአብሔርነት ያመኑበት ኦሪትን የማያዉቁ ስሑታን እንደሆኑ ያስቡ ስለ ነበር ”አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ከገሊላ ነቢይ እንደማይነሳ መርምርና እይ“ አሉት እንጂ አልተቀበሉትም። ዮሐ ፯፥፵፰-፶፪። ኒቆዲሞስ የአርማትያስ ሰው ከሚሆን ከዮሴፍ ጋር በመሆን የጌታችንን ቅዱስ ሥጋ በንጹሕ በፍታ ገንዞ በአዲስ መቃብር ቀብሯል። ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ”ቀድሞ በሌሊት ወደ ጌታችን ኢየሱስ ሄዶ የነበረዉ ኒቆዲሞስም መጣ፤ ቀብተውም የሚቀበርበትን መቶ ወቄት የከርቤና የሬት ቅልቅል ሽቶ አመጣ።” እንዳለ። ዮሐ ፲፱፥፴፱። በዚህም ኒቆዲሞስ ከምክረ አይሁድ ያልተቀላቀለ መሆኑ ይታወቃል።

የሌሊት ተማሪው ኒቆዲሞስ የሌሊቱን ጊዜ ለትምህርት ለምን መረጠ
             የሌሊት ተማሪው ኒቆዲሞስ ዮሃ ፫፤፪
   ከፈሪሳዊያን ወገን የሆነ የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው በሌሊት ወደ ጌታ እየሄደ ይማር ነበር ኒቆዲሞስ ከቀኑ ክፍለ ጊዜ ይልቅ የሌሊቱን ጊዜ ለትምህርት ለምን መረጠ ?  ፩. ኒቆዲሞስ መምህር ስለነበር ስማር ሰዎች ቢያዩኝ ውዳሴ ከንቱ መምህር መባል ይቀርብኛል ብሎ ነው እኛስ ዛሬ የዘላለም ህይወት የሚሰጠንን ቅዱስ ቃል ብትህትና መማር ሲገባን ለምድራዊ ክብር ብለን በቀን ጊዜያችን መማር ያልቻልን ስንቶቻችን ነን ስለዚህ ቀን ጊዜአችንን በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል

 ‹ ማንም ሊሰራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለችና › ዮሃ ፱፤፬

 ፪.ኒቆዲሞስ የአይሁድ መምህር ስለነበር እንዳያዩት ፈርቶ ሌሊት እየመጣ ይማር ነበር እኛስ ዛሬ ልባችን የተረዳውን እውነት በግልጥ እንዳንፈጽም በፍራቻ በይሉኝታ የምንሰውር ስንቶቻችን ነን

 ‹ፍጹምፍቅር ፍርሃት የለውም ፍርሃት ቅጣት አለውና› ፩ዮሃ ፬፤፲፰ ፍርሃትን አስወግደን ለእውነት ልንቆም ይገባል

     ፫ ኒቆዲሞስ ከቀን ልብ ይልቅ የሌሊት ልብ የተካተተ ስለሆነ በሙሉ ልቡ በማስተዋል ለመማር ስለፈለገ ከቀኑ ክፍለ ጊዜ ይልቅ የማታውን መረጠ ዛሬስ ስንቶቻችን ነን ቅዱስ ቃሉን በማስተዋል ከልብ ሆነን የምንማር የሰማነው ቅዱስ ቃል በህይወታችን ፍሬ እንዲያፈራ ቅዱስ ቃሉን ከልብ ሆነን በማስተዋል ልንሰማ ይገባናል ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ልብ መልካም መሬት ተብⶀል

‹ በመልካም መሬት የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ነው› ማቴ ፲፫፡፳፫

    አንዳንዶቻችን ጸሎት እያደረግን እንኳን አንደበታችን የእግዚአብሄርን ቃል ይነዳል ልባችን ሌላ ቦታ ይንጎዳጎዳል በማህበር ጸሎትም አብረን እየጸልይን በመሃል ሳይን አውት አርገን ልክ ሲፈጸም አለቀ እንዴ ብለን ሳይን ኢን የምናደርግ አንጠፋም

            ፬ ሌሊት ጨለማ ነው ብርሃን የለም ይህም የኃጢአት ምሳሌ ነው ኒቆዲሞስ በሌሊት መምጣቱ በኃጢአት እንዳለ ንስሃ እንደሚፈግ ያስረዳናል ዛሬስ ስንቶቻችን ነን ቅዱስ ቃሉን ስንሰማ በተአምኖ ኃጢአት በንስሃ ውስጥ ሆነን የምንሰማ ያለንስሃ የምንሰማው ቃል በህይወታችን ፍሬ የማፍራት እድሉ ጠባብ ነው ምክንያቱም በንስሃ ከልባችን ያልጸዱት ክፉ ምኞቶች እንደ እሾህ ሆነው ያንቁታልና

‹ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ እሾህም ወጣና አነቀው› ማቴ፲፫፤፰ ተብሎ የተጻፈው ለዚህ ነው

            ፭ ሌሊት የቆየው ኪዳን ወይም የብሉይ ኪዳን ምሳሌ ነው ኒቆዲሞስም እኔ ምሁረ ኦሪት እንጂ ምሁረ ወንጌል አይደለሁም ወንጌልን ካንተ እማር ዘንድ ያስፈልገኛል ሲል በሌሊት ይመጣ ነበር ብሉያት ከሓዲሳት ጋር ተዋህደው ሲተረጎሙ ሰሙና ወርቁ ተጣምሮ የሕይወት ትምህርት ያስገኛል አንዳንዶች ዛሬ ብሉያት ጭራሽ አያስፈልጉም ሲሉ ይደመጣሉ ነገር ግን እንደ ኒቆዲሞስ ሁለቱን ኪዳናት አዋህዶ መጓዝ ትክክለኛው መንገድ ነው ለዚህም ነው ጌታ ሲያስተምር‹እውነት እላችኋለው ሰማይና ምድረስኪያልፍ ድረስ ከህግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ አታልፍም› ማቴ፭፤፲፰ በማለት አበክሮ የተናገረው ኒቆዲሞስ ምንም እንኳንየቀኑ ክፍለ ጊዜ ባይመቸውም በሌሊቱ ሰአት ለመማር ችⶀል እኛም ከሱ ተምረን ከልብ ካለቀሱ እንባ አይጠፋምና ምንም ስራ ቢበዛብን ለቅዱስ ቃሉጊዜ አይጠፋምና ህይወት ለሚገኝበት ትምህርት ጊዜ ልንሰት ይገባል።

 መዝሙር

    ሖረ ኅቤሁ ዘስሙ ኒቆዲሞስ ወይቤሉ ለኢየሱስ ረቢ ሊቅንሕነ ነአምነ ብከ . . . . . . . .

የቅዳሴ ምንባባት
 ሮሜ 7:1-14   "ወንድሞች ሆይ፥ ሕግን ለሚያውቁ እናገራለሁና ሰው ባለበት ዘመን ሁሉ ሕግ እንዲገዛው አታውቁምን? ያገባች ሴት ባልዋ በሕይወት ሲኖር ከእርሱ ጋር በሕግ ታስራለችና፤ ባልዋ ቢሞት ግን ስለ ባል ከሆነው ሕግ ተፈትታለች። ስለዚህ ባልዋ በሕይወት ሳለ ለሌላ ወንድ ብትሆን አመንዝራ ትባላለች፤ ባልዋ ቢሞት ግን ከሕጉ አርነት ወጥታለችና ለሌላ ወንድ ብትሆን አመንዝራ አይደለችም። እንዲሁ፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ እናንተ ደግሞ በክርስቶስ ሥጋ ለሕግ ተገድላችኋል፤ ለእግዚአብሔር ፍሬ እንድናፈራ፥ እናንተ ለሌላው፥ ከሙታን ለተነሣው፥ ለእርሱ ትሆኑ ዘንድ።በሥጋ ሳለን በሕግ የሚሆን የኃጢአት መሻት ለሞት ፍሬ ሊያፈራ በብልቶቻችን ይሠራ ነበርና፤አሁን ግን ለእርሱ ለታሰርንበት ስለ ሞትን፥ ከሕግ ተፈትተናል፥ ስለዚህም በአዲሱ በመንፈስ ኑሮ እንገዛለን እንጂ በአሮጌው በፊደል ኑሮ አይደለም። እንግዲህ ምን እንላለን? ሕግ ኃጢአት ነውን? አይደለም፤ ነገር ግን በሕግ ባይሆን ኃጢአትን ባላወቅሁም ነበር፤ ሕጉ። አትመኝ ባላለ ምኞትን ባላወቅሁም ነበርና።ኃጢአት ግን ምክንያት አግኝቶ ምኞትን ሁሉ በትእዛዝ ሠራብኝ፤ ኃጢአት ያለ ሕግ ምውት ነውና።እኔም ዱሮ ያለ ሕግ ሕያው ነበርሁ፤ ትእዛዝ በመጣች ጊዜ ግን ኃጢአት ሕያው ሆነ እኔም ሞትሁ፤ ለሕይወትም የተሰጠችውን ትእዛዝ እርስዋን ለሞት ሆና አገኘኋት፤ ኃጢአት ምክንያት አግኝቶ በትእዛዝ አታሎኛልና በእርስዋም ገድሎኛል። ስለዚህ ሕጉ ቅዱስ ነው ትእዛዚቱም ቅድስትና ጻድቅት በጎም ናት። እንግዲህ በጎ የሆነው ነገር ለእኔ ሞት ሆነብኝን? አይደለም፥ ነገር ግን ኃጢአት ሆነ፤ ኃጢአትም በትእዛዝ ምክንያት ያለ ልክ ኃጢአተኛ ይሆን ዘንድ፥ ኃጢአትም እንዲሆን ይገለጥ ዘንድ በጎ በሆነው ነገር ለእኔ ሞትን ይሠራ ነበር። ሕግ መንፈሳዊ እንደ ሆነ እናውቃለንና፤ እኔ ግን ከኃጢአት በታች ልሆን የተሸጥሁ የሥጋ ነኝ።"

1ኛዩሐ 4:18 -ፍፃሜ  "-ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል እንጂ በፍቅር ፍርሃት የለም፥ ፍርሃት ቅጣት አለውና፤ የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም። እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን። ማንም። እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል? እግዚአብሔርንም የሚወድ ወንድሙን ደግሞ እንዲወድ ይህች ትእዛዝ ከእርሱ አለችን። "

 ሐዋ 5:34-ፍፃሜ 3 "ነገር ግን በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የከበረ የሕግ መምህር ገማልያል የሚሉት አንድ ፈሪሳዊ በሸንጎ ተነሥቶ ሐ
ዋርያትን ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጉአቸው አዘዘ፥ እንዲህም አላቸው። የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ ስለ እነዚህ ሰዎች ምን እንደምታደርጉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ከዚህ ወራት አስቀድሞ ቴዎዳስ። እኔ ታላቅ ነኝ ብሎ ተነሥቶ ነበርና፥ አራት መቶ የሚያህሉ ሰዎችም ከእርሱ ጋር ተባበሩ፤ እርሱም ጠፋ የሰሙትም ሁሉ ተበተኑ እንደ ምናምንም ሆኑ። ከዚህ በኋላ ሰዎች በተጻፉበት ዘመን የገሊላው ይሁዳ ተነሣ ብዙ ሰዎችንም አሸፍቶ አስከተለ፤ እርሱም ጠፋ የሰሙትም ሁሉ ተበታተኑ። አሁንም እላችኋለሁ። ከእነዚህ ሰዎች ተለዩ ተዉአቸውም፤ ይህ አሳብ ወይም ይህ ሥራ ከሰው እንደ ሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም፥ በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ።ሰሙትም፥ ሐዋርያትንም ወደ እነርሱ ጠርተው ገረፉአቸው፥ በኢየሱስም ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ፈቱአቸው።እነርሱም ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለ ተቈጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ፤ ዕለት ዕለትም በመቅደስና በቤታቸው ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ማስተማርንና መስበክን አይተዉም ነበር። "

 ምስባክ 
ሐወጽከኒ ለሊተ ወፈተንኮ ለልብየ

           በሌሊት ጎበኘህኝ ልቦናየንም ፈተንከው

አመከርከኒ ወኢተረክበ ዓመፃ በላዕሌየ

          ፈተንከኝ በላየ ምነም በደል አልተገኘም

 ከመ ኢይንብብ አፋየ ግብረ ዕጓለ አመሕያው

           የሰው ልጅ ስራን አፌ እንዳይናገር
 
ወንጌል
ዘዩሐ 3 : 1- 12 '' ከፈሪሳውያንም ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ #ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ። መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን አለው። ኢየሱስም መልሶ። እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው። ኒቆዲሞስም። ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን? አለው። ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል። እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው። ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አታድንቅ። ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፥ ድምፁንም ትሰማለህ፥ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው። #ኒቆዲሞስ መልሶ። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? አለው። #ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው። አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን? እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን፥ ምስክራችንንም አትቀበሉትም። ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ?" 

ቅዳሴ
ቅዳሴ ዘእግዝትነ
**
ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን።

 ምንጭ
Ø  ፍሬ ተዋህዶ
Ø  ማህበረ ቅዱሳን አውሮፓ ማዕከል ድር
Ø  ቃለ ሕይወት (አጭር ግጻዌ)
“ሀገራዊ የጸሎት ጥሪ እንጂ ጾም አልተባለም”
ሊቀ ትጉኃን ታጋይ ታደለ የኢትዮጵያ የሃይማኖተ ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሓፊ
መጋቢት 28/2012 ዓ/ም

የኮሮና ቫይረስ በሀገራችን መከሰቱን ተከትሎ የሃይማኖት ተቋማት የበላይ ጠባቂ አአባቶች በአንድ ላይ ሆነው ብሔራዊ የጸሎት አዋጅ ትናንተ በ27/07/2012 ዓ.ም ማወጃቸው የሚታወስ ነው ፡፡ ይሁን እንጂ የታወጀው የጸሎት አዋጅ ሆኖ እያለ በተለያዩ የማኀበራዊ ድረ ገጾች ለምዕመናን የተሳሳተን መረጃ የሰጡ መሆናቸውን ያነሱት ጠቅላይ ጸሓፊው ሊቀ ትጉኃን ታጋይ ተደለ የሃይማኖት ተቋማት የበላይ ጠባቂ አባቶች ያወጁት ለሁሉም ሃይማኖቶች ለአንድ ወር የሚቆይ ብሔራዊ የጸሎትና የንሥሓ አዋጅ እንጅ የጾም አይደለም ብለዋል፡፡

በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ጾም መሠረት ከትንሣኤ እስከ በዓለ ሃምሳ የጾም ሥርዓት እንደሌለ የሚታወቅ ሲሆን የሃይማኖት ተቋማቱ ጉባኤ በማንኛምው ቤተ እምነት ሕግና ሥርዓት ጣልቃ የማይገባ መሆኑን ብቻ ሳይሆን ፈጽሞ እንደማይችል ጨምረው ገልጠዋል ፡፡

አያይዘውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሆነ የሌሎች አብያተ እምነት የጋራ ጸሎትና በኮሮና ወረርሽኝ እና መሰል ጉዳዮች የትምህርትና የጸሎት መርሐ ግብር በአራት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ከዛሬ ማለትም ከ28/07/2012 ዓ/ም ከምሽቱ 3፡00-4፡00 ለተመልካች እንደሚደርስ ገልጠው ሁሉም እንዲከታተል ጠቁመዋል ፡፡

በመጨረሻም ጠቅላይ ጸሓፊው ሊቀ ትጉኃን ታጋይ ታደለ በዘመናችን የተከሰተው ክፉ ወረርሽኝ በሽታ እንዲወገድ ሁላችንም በበረታ ክንድ ልንጸል ይገባልም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመርሐ ግብር ተራ በአራቱ ጣቢያዎች
ሰኞ፡ በ ETV ከምሽቱ 3፡00-4፡00
ማክሰኞ፡በ FANA ከምሽቱ 3፡00-4፡00
ረቡዕ፡ በ ADDIS TV ከምሽቱ 3፡00-4፡00
ሐሙስ፡ በ WALTA ከምሽቱ 3፡00-4፡00
አርብ ፡ በ ETV ከምሽቱ 3፡00-4፡00
ቅዳሜ፡ በ FANA ከምሽቱ 3፡00-4፡00
እሑድ፡ በ ADDIS TV ከምሽቱ 3፡00-4፡00
©EOTC TV
#GovtofEthiopiaCOVID19

ኮሮና ቫይረስን [ኮቪድ-19] በሚመለከት በጣም ብዙ ሀሰተኛ መረጃዎች አሉ፤ እውነታዎቹ የሚከተሉት ናቸው፦

🔢 በሁሉም የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ሊያዙ ይችላሉ፤ በእድሜ የገፉ ሰዎች እና አስቀድሞ እንደአስም፥ ስዃር እና የልብ በሽታ አይነት በሽታዎች ያሉባቸው ሰዎች በዚህ ቫይረስ በጠና የመታመም አደጋ ሊያጋጥማቸው ይችላሉ።

❄️ ቀዝቃዛ አየር እና በረዶ ኮሮና ቫይረስን መግደል አይችልም።

☀️ ኮሮና ቫይረስ የአየር ንብረታቸው ሞቃትና እርጥበት አዘል በሆኑ አካባቢዎች ሊተላለፍ ይችላል።

🦟 ኮሮና ቫይረስ በትንኞች ንክሻ አይተላለፍም።

🐶 እንደ ውሻ እና ድመት ያሉ የቤት እንስሳዎች ኮሮናን እንደሚያስተላልፉ አልተረጋገጠም።

🛀 በሙቅ ውሀ መታጠብ ቫይረሱን አይከላከለውም።

💨የእጅ ማድረቂያዎች ኮሮና ቫይረስን መግደል አይችሉም።

🟣 ቫይረሱን ለመከላከል የጰሀይ ጨረርን መጠቀም የለብንም፤ የቆዳ መቆጣትን ሊያስከትል ይችላል።

🌡️ የሙቀት መለኪያዎች ሰዎች ትኩሳት ካላቸው ሊለዩልን ይችላሉ እንጂ ሰዎች ኮሮና ቫይረስ እንዳለባቸው አይለዩም።

💦 ክሎሪን ወይም አልኮል ልብሶት ላይ መርጨት አስቀድሞ ወደ ሰውነትዎ የገባን ቫይረስ አይገድልም።

💉 እንደ ኒሞኮካል እና ሄሞፊለስ ኢንፍሉዌንዛ ያሉ ፀረ ኒሞኒያ ክትባቶች ከኮሮና ቫይረስ መከላከያ ሊሆኑ አይችሉም።

👃 በተደጋጋሚ አፍንጫን በጨው ውሀ መታጠብ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ እንዳይያዙ እንደሚያደርግ የተረጋገጠ መረጃ የለም።

🧄 ምንም እንዃን ነጭ ሽንኩርትን መመገብ ጤናማ ቢሆንም ነጭ ሽንኩርት የተመገቡ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ እንዳልተያዙ አልተረጋገጠም።

💊 አንቲባዮቲክስ ቫይረስን አያጠፉም፤ አንቲባዮቲክስ የሚሰራው ለባክቴሪያ ነው።

🧪 እስካሁን ድረስ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከልም ሆነ ለማከም ይረዳል የተባለ መድሀኒት የለም።

እነዚህን መረጃዎች የአለም የጤና ድርጅት ድህረ ገፅ ላይ ይዩዋቸው: https://www.who.int/emergencies/diseases/novel-coronavirus-2019/advice-for-public/myth-busters

https://api.whatsapp.com/send?phone=251962228565&text=hi&source=&data=

@tikvahethiopiaBot @tikvahethiopia
"+" ሆሳዕና የዐብይ ጾም ስምንተኛ ሳምንት "+"
"እንኳን አደረሳችሁ።"

ሆሣዕና ከስምንቱ የዐቢይ ጾም እሑዶች አንዱና የመጨረሻው ሳምንት ተብሎ የሚጠራው ከትንሣኤ ቀድሞ የሚገኝ የሕማማት መገቢያ ዋዜማ ነው።
ሆሣዕና አስቀድሞ ካለው ረቡዕ ጀምሮ የሚታሰብ ታላቅ የቤተክርስቲያን የበዓል ቀን እንደሆነ ይታወቃል። ይህን ስም በዚሁ ሰንበትና በዋዜማዎቹ ዕለታት የሚዘመረው ጾመ ድጓ ‘ሆሣዕና በአርያም’’ ‘ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት’’ ‘ዕለተ ሆሣዕናሁ አርዓየ… ‘ ወዘተ. በማለት ሆሣዕና የሚለውን ቃል ቅዱስ ያሬድና
ሌሎችም አባቶች በየቦታው እየጠቀሱና እየተዘመረለት በአህያ ውርንጭላ ላይ
ተቀምጦ ኢየሩሳሌም የገባበትን ሁኔታ እየተረከ ስለሚዘምር ይህ ሰንበት በጌትነትና በክብር በውዳሴና ቅዳሴ ሆሣዕና በአርአያም እየተባለ
በሽማግሌዎችና በሕፃናት አንደበት በድንጋዮችም ልሳን ሳይቀር እየተመሰገነ ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በከብር ሲገባ ለሰጣቸው ለተቀደሰ ሰላሙና ፍቅሩ መታሰቢያ ሆኖ የተሰጠ ነው።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ሌላ ቀን እንደ ተራ ሰው ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም ይገባ ነበር፡፡ በዚህ ቀን ግን የአይሁድ ንጉሥ ሆኖ በክብር ገባ፡፡ ከቢታንያ ተነሥቶ ደብረ ዘይት ሲደርስ ከሐዋርያቱ ሁለቱን በቤተፋጌ ሰው ተቀምጦባት የማያውቅ
ውርንጭላ እንዲያመጡለት ላካቸው፡፡ “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሒዱ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከእርሷ ጋር ታገኛላችሁ፤
ፈትታችሁም አምጡልኝ፡፡ ማንም አንዳች ቢላችሁ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ" አላቸው፡፡ ማቴ.21፡1-17
ወደ ቤተፋጌም ሄደው አህያዪቱን አገኙአት፡፡ ሲፈቱአትም ሳለ ባለቤቶቹ መጡባቸውና አስቆሟቸው፡፡ እነርሱም ኢየሱስ እንደፈለጋት ነገሩአቸው፡፡ ባለቤቶቹ ይህንን ሲያውቁ ተውአቸው፡፡ ሐዋርያትም የአህያዪቱን ውርንጭላ ፈትተው ወደ ኢየሱስ ወሰዱ፡፡ አጠገቡም ሲደርሱ ልብሳቸውን በአህያዪቱ ውርንጭላ ላይ አንጥፈው ኢየሱስን አስቀመጡት፡፡
ለምን ዘንባባ ያዙ ቢባል፤ ዘንባባ እሾሃም ነው ፤አንተም የኃይል የድል ምልክት አለህ ሲሉ፤በሌላም በኩል ዘንባባ እሳት ለብልቦ ይተወዋል እንጂ አይበላውም አንተም ባህርይህ አይመረመርም ሲሉ፤አንድም ዘንባባ ረጅም /ልዑል/ ነው አንተም ባሕርይህ ልዑል ነው ሲሉ ዘንባባ ይዘው ተቀብለውታል፡፡
ለምን የተምር ዛፍ ዝንጣፊ ነው ቢሉ፤ ተምር ፍሬው አንድ ነው አንተም ባህርይህ አንድ ነው ሲሉ፡፡አንድም፤ተምር ልዑል/ረጅም/ ነው አነተም ልዑለ ባህርይ ነህ ሲሉ፡፡ አንድም፤የተምር ፍሬው በእሾህ የተከበበ ነው በቀላሉ መለቀም አይቻልም ፤የአንተም ምስጢር አነተ ካልገለጠከው አይመረመርም ሲሉ ነው፡፡ የወይራ ዛፍ ዝንጣፊ ነው ቢሉ፤ ወይራ ጽኑዕ/ ጠንካራ/ ነው አንተም ጽኑዓ ባህርይ ነህ ሲሉ፤አንድም ወይራ ለመስዋዕት ይሆናል፤ አንተም መስዋዕት
ትሆናለህ ሲሉ፤አንድም ወይራ ዘይቱ ለመብራት ይሆናል አንተም የዓለም ብርሃን ነህ ሲሉ ይህንን ይዘው አያመሰገኑ ተቀበሉት፡፡
ልብሳቸውንም ማንጠፋቸው፤ እንኳን አንተ የተቀመጥክባት አህያ እንኳን መሬት መርገጥ አይገባትም ሲሉ ልብሳቸውን አነጠፉለት፡፡ እነዚያ ያላመኑ አይሁድ ለተቀመጠባት አህያ ይህንን ያህል ክብር ከሰጡ፤ በድንግልና ጸንሳ ለወለደችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምን ያህል ክብር ልናድረግለት ይገባን ይሆን?፡፡
“የጽዮን ልጅ ሆይ አትፍሪ እነሆ ንጉሥሽ በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ይመጣል” ዘካ.9፡9 የሚለው የዘካርያስ ትንቢት ተፈጸመ፡፡ ሕዝቡም ኢየሱስ በመምጣት ላይ እንዳለ ሲያውቅ ሊቀበለው ወጣ፡፡ አንዳንዶች ያልፍበት በነበረ
መንገድ ልብሳቸውን እንዳንዶቹ ደግሞ የዘንባበ ዝንጣፊ ያነጥፉ ነበር፡፡ ከፊትና በኋላ ያሉት ደግሞ “ሆሳዕና በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ” እያሉ በታላቅ ድምፅ ይጮሁ ነበር፡፡ ኢየሱስ በሕዝቡ እልልታና ደስታ ታጅቦ ሲገባ ተጠንቅቀው ይታዘቡትና ይመለከቱት የነበሩ ፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርቱን ዝም እንዲያሰኛቸው ተናገሩት፡፡ እርሱም ሕዝቡ ዝም ቢል ድንጋዮች
እንደሚጮኹ አስታወቃቸው፡፡ ኢየሱስ ኢየሩሳሌምን ሲያያት አለቀሰላት፡፡ “አንቺ
ኢየሩሳሌም ለሰላምሽ የሚያስፈልገውን ነገር ምነው አውቀሽ ቢሆን ኖሮ አሁን ግን ይህ ነገር ከዓይንሽ ተሰውሮብሻል ጠላቶችሽ በዙሪያሽ እንደ
አጥር ከብበው በዚህም በዚያም አንቺን የሚያስጨንቁበት ጊዜ ይመጣል… ምክንያቱም እግዚአብሔር ሊያድንሽና ሊጐበኝሽ የመጣበትን
ጊዜ ባለማወቅሽ ነው” እያለ ረገማት፡፡
መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም የገባው ሰለ ደኅንተቷ ሊያሳስባት ፈልጐ ነው፡፡ በማያወላዳ መንገድ ንጉሷና መድኃኒቷ እንደሆነ
ገለጸላት፡፡ ወደ ራሷ ተመልሳ ጸጋዋን እንድትቀበል የልቧን ድንዳኔ ትታ እርሱን እንድትሰማ አስጠነጠቃት፡፡ ግን አልተጠነቀቀችም፡፡ ለጊዜው በክብር ተቀበለችው፡፡ ከጥቂት ቀን በኋላ ግን ተወችው፤ በመስቀል ላይ ሰቀለችው፡፡ የደኅንነቷን ቀን ማወቅ ተሳናት፡፡ በዚህም ደግሞ ከብዙ ዓመታት በኋላ መዓት ወረደባት፡፡
ይህ የሚያሳዝን የኢየሩሳሌም ሥራ የእኛም ሥራ ነው፡፡ ኢየሱስን መድኃኒታችንን መቀበል አንፈልግም ወይም ተቀብለን በኃጢአታችን ከእኛ እንዲርቅ እናደርገዋለን፡፡ በቅዱስ ቁርባን ወደ እኛ ሲመጣ በደስታ እንቀበለዋለን፡፡ ትንሽ
ቆየት ብለን ደግሞ እናዋርደዋለን፡፡ ከእርሱ ጋር እንጣላለን፡፡ ከኃጢአት ጋር ጓደኝነት እንይዛለን፡፡ በኃጢአት ስንወድቅ እርሱን እንደገና እንሰቅለዋለን፡፡ ኢየሱስ እኛን “አቤት በዚህ ቀን ለደኅንነትህ የሚደረገውን ብታውቅ ኖሮ …፣ ይህ
ሁሉ ከዓይንህ ተሰውሮብሃል ማወቅን አልፈለግህም፡፡ ይህን እወቅ ግን አንድ
ቀን …” እያለ አዝኖ ይፈርድብናል፡፡ ይህንን በማሰብ ሲመጣና ሲናገረን እምቢ አንበለው አናባርረው፡፡ በኋላ እርሱ ቂም ይዞ እምቢ እንዳይለና እንዳያባርረን ደኅንነታችንን ራሳችን አናጥፋት፡፡
የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)
ወእንዘ ሰሙን በዓለ ፋሲካ ቀርቡ አርዳኢሁ ለአምላከ ጽድቅ ኀበ ደብረ ዘይት ሙራደ ዓቀብ ሀገረ እግዚአብሔር ወተቀበልዎ ሕዝብ ብዙኃን አዕሩግ ወሕፃናት ነሢኦሙ አዕፁቀ በቀልት እንዘ ይብሉ ሆሣዕና በአርያም ተፅዒኖ ዲበ ዕዋል ቦአ
ሀገረ ኢየሩሳሌም በትፍሥሕት ወበሐሴት ይሁቦሙ ኃይለ ወሥልጣነ፡፡…..
ትርጉም: “በፋሲካ በዓል ሰሞን የእውነት አምላክ ደቀ መዛሙርት ወደ ደብረ ዘይት ቀረቡ፤ በሀገረ እግዚአብሔር (ኢየሩሳሌም) አቀበቱ ላይ ብዙ አረጋውያንና ሕፃናት የዘንባባ ቅጠል ይዘው ሆሣዕና በአርያም እያሉ ተቀበሉት፣ በአህያ
ውርንጫ ላይ ተጭኖ በፍጹም ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ። ለእነዚህ ኃይልና
ሥልጣንን ይሰጣቸዋል።

መልዕክታት
ዕብ.8÷1-ፍጻ. ከተናገርነውም ዋናው ነገር ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፡፡ እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፤ እርስዋም በሰው ሳይሆን በእግዚአብሔር
የተተከለች ናት፡፡ (ተጨማሪ ያንብቡ)
1ኛ ጴጥ.1÷13 ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና ነቅታችሁ ኑሩ፤ ኢየሱስ ክርስቶስም ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ፡፡
(ተጨማሪ ያንብቡ)

ግብረ ሐዋርያት
የሐዋ.8÷26-ፍጻ. የእግዚአብሔር መልአክም ፊልጶስን ተናገረው፤ እንዲህም አለው÷ “በቀትር ጊዜ ተነሣና በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ
በሚያወርደው በምድረ በዳው መንገድ ሂድ፡፡” ተነሥቶም ሄደ፡፡” እሆም÷
(ተጨማሪ ያንብቡ)

ምስባክ
መዝ.80÷3 "ንፍሑ ቀርነ በዕለት ሠርቅ፡፡ በእምርት ዕለት በዓልነ፡፡ እስመ ሥርዓቱ ለእስራኤል ውእቱ"
ትር
ጉም፦ በመባቻ ቀን በታወቀችው በዓላችን ቀን መለከትን ንፉ፤ ለእስራኤል ሥርዐቱ ነውና÷ የያዕቆብም አምላክ ፍርድ ነውና፡፡
ወይም
መዝ.80÷2 "እምአፈ ደቂቅ ወሕፃናት አስተዳሎከ ስብሓተ፡፡ በእንተ ጸላዒ፡፡ ከመ ትንሥቶ ለጸላዒ ወለገፋዒ፡፡"

ትርጉም፦ ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ፡፡ ስለ ጠላት÷
ጠላትንና ግፈኛን ታጠፋው ዘንድ፡፡

ወንጌል
ዮሐ.12÷1-11 ፋሲካ ከሚውልበት ከስድስተኛው ቀን አስቀድሞ ጌታችን ኢየሱስ ከሙታን ያስነሣው አልዓዛር ወደ ነበረበት ወደ ቢታንያ መጣ፡፡(ተጨማሪ ያንብቡ)

ቅዳሴ
ቅዳሴ ዘጎርጎርዮስ፡፡

ምንጭ
· ማሕበረ ቅዱሳን ደረገጽ
· መናገሻ ጽጌ ሰ/ት/ቤት ገጽ
· ቃለ ሕይወት(አጭር ግጻዊ)
“+" ሰሙነ ሕማማት ”+"

“ነሥአ ደዌነ መጾረ ሕማመነ በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፣ ሕማማችንን ተሸከመ፣ ስለመተላለፋችን ቆሰለ፣ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን” (ኢሳ. 53÷4-6) በማለት ነቢዩ ኢሳይያስ የተነበየው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ከፍዳና ከዘለዓለማዊ ሞት ለማዳንና ከዲያብሎስም ቁራኝነት ነፃ ለመውጣት
ሲል 13ቱን ሕማማተ መስቀልና ሌሎቹንም ጸዋትወ መከራዎች የተቀበለበት ሳምንት “ሰሙነ ሕማማት” በመባል ይታወቃል፡፡ ትርጓሜውም የመከራ ሳምንት ማለት ነው፡፡ ከፋሲካ በፊት በጸሎትና በጾም፣ በብዙ ስግደት የክርስቶስ አዳኝነትና ቤዛነት የሚታሰብበት ይህ ሳምንት በልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት በተለያዩ ስሞች የሚጠራ ሲሆን እንደኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አጠራር ግን “ሕማማት” በሚል ስያሜ ይጠራል፡፡ እስከ 4ኛው ምእተ ዓመት ድረስ ጌታችን ከጾመው 40 ጾም ጋር ሳይሆን ለብቻው ይታሰብ እንደነበረ ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ መረዳት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእሱ ላይ የደረሱትን ጸሞትወ መከራዎች ሁሉ በትዕግሥት ተቀብሎና በመስቀል
ላይ ተሰቅሎ የሞተው 40ውን ጾም ከፈጸመ በኋላ ወዲያውኑ ሳይሆን ከሦስት ዓመታት በላይ ከአስተማረና ቤተ ክርስቲያንን ካደራጀ በኋላ
ስለሆነ ነው፡፡
በ4ኛው ምእት ዓመት ግን በምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ክርስቶስ ከጾመው 40 ጾም ቀጥሎ ከትንሣኤ በፊት ባለው ሳምንት “ሰሙነ ሕማማት” እንዲታሰብ ተደርጓል፡፡ በዚህም ምክንያት የጾሙ ጊዜ ከ6 ወደ 7 ሳምንታት ከፍ ብሎአል፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ግን ከ40 ጾም በፊት ባለው መጀመሪያ ሳምንት ጾመ
ሕርቃል ተጨምሮ እንዲጾምና ከ40ው ጾም በኋላም “ሰሙነ ሕማማት” በጾም፣ በጸሎትና በስግደት እንዲታሰብ በመደረጉ የጾሙ ጊዜ 55 ቀናት ወይም 8 ሳምንታት ስለሆነ የነዚህ ድምር ውጤት ጾሙን ዐቢይ ጾም ሊያሰኘው ችሏል፡፡ ዐቢይ ጾም ማለትም ታላቁ ጾም ማለት ነው፡፡ የዚህ
የሰሙነ ሕማማት መታሰቢያ ጾም መጨረሻው የዓቢይ ጾምም መጨረሻ ስለሆነ ጾሙ በአክፍሎት ይደመደምና ከእሁድ መንፈቀ ሌሊት ጀምሮ
በዓለ ትንሣኤው ይከበራል፡፡ የምዕራብ ቤተክርስቲያን ደግሞ በኒቆዲሞስ የሰሙነ ሕማማትን መታሰቢያ ታደርግና በሆሳዕና ዕለት
የትንሣኤን በዓል ታከብራለች፡፡
በሰሙነ ሕማማት መጀመሪያ በሆሣዕና ዕለት የሚፈጸሙት አስደሳች ሥርዓቶች በኋላ በ6ኛው ምእት ዓመት እንደተጀመሩ ከቤተክርስቲያን
ታሪክ መረዳት ይቻላል፡፡
ለምሳሌ ያህል የዘንባባ ዝንጣፊ ባርኮ ለምእመናን ማደል፣ የዘንባባውን ዝንጣፊ በእጅ ይዞ መዘመርና በቤተክርስቲያን ዙሪያ ዑደት ማድረግ፣
በቤተክርስቲያኑ በሮችና ማዕዘኖች የዳዊት መዝሙራትን እየዘመሩ ወንጌልን ማንበብ፣ ሌሎችንም በዓሉን የሚመለከቱ ሥርዓተ
ቤተክርስቲያን መፈጸም የተጀመረው በዚሁ በ6ኛው ምእት ዓመት ሲሆን ይህም አስደሳች ሥርዓት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እስከዛሬ ድረስ እየተፈጸመ ይገኛል፤ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡ ዘንባባ የክብርና የድል ምልክት ከመሆኑም በላይ ድርጊቱና አፈጻጸሙ ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በድል አድራጊነት ወደ ኢየሩሳሌም በገባበት ጊዜ የተደረገለትን የክብር አቀባበል የሚያመለክት ነው፡፡
በጸሎተ ሐሙስ ዕለትም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታና መምህር ሲሆን በትኅትና ራሱን ዝቅ አድርጎ የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበ መሆኑን
ለማስታወስና ምሳሌውን ለመከተል ሲባል በፓትርያርክ፤ በሊቃነ ጳጳሳትና በሊቃነ ካህናት የካህናትንና የምእመናንን እግር የማጠብ
ሥርዓትም በዚሁ በ6ኛው ምእት ዓመት ተጀምሮአል፡፡
በሰሙነ ሕማማት የተፈጸሙ ታላላቅ ድርጊቶች:-
እሁድ የሆሣዕና ዕለት፡ – ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በድል አድራጊነት ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ ሕፃናትና ሽማግሌዎች፣
በጠቅላላ ሕዝቡ ሁሉ ልብሳቸውን እያነጠፉና ቅጠል እየጎዘገዙ፣ በእጃቸውም የድል አድራጊነት ምልክት የሆነውን የዘንባባ ዝንጣፊ እያያዙ በዝማሬና በታላቅ ክብር ተቀብለውታል፡፡

ሰኞ፡-በቤተ መቅደሱ ውስጥና በዙሪያው ይሸጡና ይገዙ የነበሩትን ከቤተ መቅደስ ያስወጣቸው፤ የገንዘብ ለመዋጮች ገበታዎችንና የርግብ
ሽያጮችን ወንበሮች ገልብጦ ሁሉንም ከቤተ መቅደሱ በጅራፍ ያባረራቸው፣ ፍሬ አልባ የሆንችውን በለስ የረገማት በዚሁ ዕለታተ ሰኑይ
ነው፡፡ በበለስም አንፃር ኃጢአትን እንደረገመ ሊቃውንት ያትታሉ፡፡

ማክሰኞ፡-ሰኞ የረገማት በለስ ማክሰኞ ደርቃ ተገኝታለች፡፡ የበለሲቱ መረገምና መድረቅ ቀድሞ በአዳም በኩል የመጣውና ከትውልድ ወደ
ትውልድ ሲተላለፍ የኖረው ኃጢአትና መርገም በክርስቶስ ሞት መወገዱን ያመለክታል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚሁ በማክሰኞ ቀን ስለግብር አከፋፈል፣ ስለትንሣኤ ሙታንና የዳዊት ልጅ የሚባል ማን እንደሆነ በመግለጥ መጻሕፍትን እየጠቀሰ ከፈሪሳውያን ጋር ይከራከር የነበረው በዚሁ ማክሰኞ በሚባለው ዕለተ ሠሉስ ነው፡፡ እንዲያውም ጸሐፍትና ፈሪሳውያንን በታላቅ ተግሣጽ ገሥጾአቸዋል (ማቴ. 23÷1-39)፣ በለምፃሙ፣ በስምዖን ቤት ማርያም እንተ እፍረት
ሽቶ የቀባችው፤ የአስቆርቱ ይሁዳ ጌታውን ለማስያዝ ከአይሁድ ጋር በድብቅ የተነጋገረው በዚሁ በዕለተ ማክሰኞ ነው፡፡

ረቡዕ፡-አይሁድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያዝና እንዲገደል ለማድረግ ውሳኔ የወሰኑበት እና ምክር የፈጸሙበት ቀን ነው፡፡ እንዴት እንደሚይዙት ማን እንደሚያስይዛቸውና መቼ እንደሚይዙት በዚሁ ዕለት ወስነዋል፡፡ ለክፉ ሥራቸው ተባባሪ ያደረጉትም ከአሥራ ሁለቱ ደቀ
መዛሙርት መካከል የጥፋት ልጅ የሆነውን የአስቆርቱ ይሁዳን ነበር ስለዚህ ዕለተ ረቡዕ ምክር የተፈጸመበትና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
ተይዞ እንዲገደል ውሳኔ የተላለፈበት ቀን በመሆኑና ውሳኔውም ተግባራዊ ሆኖ ጌታችን የተሰቀለውና የሞተው በዕለተ ዓርብ በመሆኑ
የክርስቶስን መከራና የሰውን ልጅ ድኅነት ለማስታወስ ሲባል ከትንሣኤው በኋላ በአሉት 50 ቀናት ካልሆነ በቀር በየሳምንቱ ረቡዕና
ዓርብ ጾመ ድኅነት በሚል ስያሜ እንዲጾም ተደርጎአል፡፡

ሐሙስ፡-በዚህ ዕለት ጧት የፋሲካን በዓልና ዝግጅት እንዲያዘጋጁ ደቀ
መዛሙርቱን ወደ ከተማ የላከ ሲሆን ሐሙስ ማታ ለመጨረሻ ጊዜ የፋሲካን በዓል ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አክብሮአል፡፡ በዚሁ ዕለት የኦሪቱን
ሥርዓት ለውጦ አዲስ ሥርዓተ ቁርባን ሠርቶአል (ማቴ. 26÷26-27)፡፡ በጌቴ ሴማኒ እየጸለየ ጸሎት ከችግርና ከፈተና እንደሚያድንም ለማስረዳት “ወደፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ” በማለት ለደቀ መዛሙርቱ መመሪያና ትምህርት ሰጠ (ማቴ. 26÷40)፡፡ ይሁዳም የአይሁድን ጭፍሮች እየመራ ወደ ጌታውና መምህሩ በመቅረብ “ሰላም ለአንተ
ይሁን ብሎ ጫማውን በመሳም ለጭፍሮቹ አሳልፎ የሰጠው በዚሁ በዕለተ ሐሙስ ማታ ነው፡፡ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ” እኔ ጌታና
መምህር ስሆን እግራችሁን ከአጠብኩ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል፤ እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ
እናንተ ደግሞ እንዲሁ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁ” (ዮሐ. 13÷13-15) በማለት ትኅትናን በተግባር እየተረጎመና በድርጊት እያሳየ
ለቀደ መዛሙርቱ ያስተማረው በዚሁ ዕለት ነው፡፡ ይህ ቀን ጌታችን በመከራው ጊዜ በተዋሐደው ሥጋ ተገብቶ ወደ ባሕርይ አባቱ የጸለየበትና ስለጸሎትም ያስተማረበት በመሆኑ ዕለቱ ጸሎተ ሐሙስ በመባል ይታወቃል፡፡

ዐርብ፡-ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአይሁድ ተላልፎ ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ሌሊቱን በሙሉ ከአንዱ ገዥ ወደ ሌ
ላው ገዥ፤ ከአንዱም ሊቀ
ካህናት ወደ ሌላው ሊቀ ካህናት እያመላለሱት በሐሰት ሲከሱትና ሲያስመሰክሩበት፤ ሲኮንኑትና ሲወነጅሉት አድረው ዐርብ ጧት ወደ ገዥው ወደ ጲላጦስ ዘንድ ቀርቦ ሞት የማይገባው አምላክ በግርግር፣ በተድእኖና በጩኸት ብዛት በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እንዲሞት የተወሰነበት በመሆኑ በዚሁ በዕለተ ዓርብ በቀትር ጊዜ ስድሰት ሰዓት
ሲሆን በግራና በቀኝ ሁለት ወንጀለኞች፣ ምንም ወንጀልና በደል የሌለበት ንጹሐ ባሕርይ ክርስቶስ ያላንዳች ጥፋት እንደወንጀለኛ ተቆጥሮ በወንበዴዎች መካከል በመስቀል ላይ ተሰቅሏል፡፡ ከ6 -9 ሰዓትም በመስቀል ላይ ሆኖ ብዙ ተአምራትን ሲፈጽምና ለሰው ሁሉ ትምህርት ሰጭ የሆኑ ቃላትን ሲናገር ከቆየ በኋላ በ9 ሰዓት ተጠማሁ ሲላቸው ያቀረቡለትን መራራ ሐሞትና ከርቤ ከቀመሰ በኋላ ተፈጸመ የሚለውን የመጨረሻ ቃል ተናግሮ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው ለይቶ በራሱ ፈቃድ የመጣበትን የማዳን ሥራ ፈጽሞአል፡፡
ክርስቶስ በሰሙነ ሕማማቱና በዕለተ ስቅለቱ የተቀበላቸው ፀዋትወመከራዎች እጅግ በጣም ብዙዎች እንደሆኑ ከቅዱሳት መጻሕፍት
መረዳት የሚቻል ሲሆን በተለይ በግብረ ሕማማቱና ድርሳነ ማሕየዊ በተሰኙ መጻሕፍት በዝርዝር ተገልጠው ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ
13ቱ ሕማማተ መስቀል የተሰኙት ጥቂቆቹ ናቸው እነሱም ተአስሮ ድኅሪት፤ ተስሕቦ በሐብል፤ ወዲቅ ውስተ ምድር፤ ተከይዶ በእግረ አይሁድ፤ ተገፍዖ ማዕከለ ዓምድ፤ ተጸፍኦ መልታሕት፤ ተቀስፎ ዘባን፤
ተኮርዖተ ርእስ፤ አክሊለ ሶክ፤ ፀዊረ መስቀል፤ ተቀንዎ በቅንዋት፤ ተሰቅሎ በዕፅና ሰሪበ ሐሞት ናቸው፡፡
መድኃኒታችን በዕፀ መስቀል ላይ እያለ ዐርብ ከ6 እስከ 9 ሰዓት ባለው ጊዜ 7 ተአምራት ተደርገዋል፡፡
1.ፀሐይ ጨልሞአል፤
2.ጨረቃ ደም ሆኖአል፤
3.ከዋክት ረግፈዋል፤
4.አለቶች (ድንጋዮች) ተፈረካክሰዋል፤
5.መቃብራት ተከፍተዋል፤
6.ሙታን ተነሥተዋል፤
7.የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ማንም ሳይነካው ራሱ ተቀዷል፡፡
ቅዳሜ፡-ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአካለ ሥጋ በመቃብር
ውስጥ ነበር፤ መቃብሩም በዘብ ይጠበቅ ነበር፡፡ ክርስቶስ በአካለ ሥጋ
ከዐርብ 11 ሰዓት እስከ እሁድ መንፈቀ ሌሊት ድረስ በመቃብር ውስጥ የነበረ ሲሆን በአካለ ነፍስ ደግሞ ወደ ሲዖል ወርዶ ከአዳም ጀምሮ
በሲዖል ውስጥ ለነበሩ ነፍሳት ነፃነትን ሰብኮላቸዋል፡፡ ከሲዖል ወጥተው ወደ ገነት እንዲገቡ አድርጓቸዋል፡፡ በአጠቃላይ እስከ ክርስቶስ ሞት ድረስ በፍርድ ግዞት ውስጥ ያሉትን ሁሉ በመከራውና በሞቱ ድል አጎናጽፎአቸዋል፡፡ በኃጢአት ባርነት ውስጥ የነበሩት ሁሉ ሙሉ ነፃነትን አግኝተው የእግዚአብሔርን መንግስት የመውረስ ዕድልን አግኝተዋል፡፡

(በሊቀ ብርሃናት ኢሳይያስ ወንድምአገኘሁ)
ምንጭ:- መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ገፅ
"+" የሰሙነ ሕማማት ሃይማኖታዊና ቱፊታዊ ክንዋኔዎች "+"

በዐቢይ ጾም ከሰርክ ሆሳዕና ጀምሮ እስከ ትንሳኤ ሌሊት ያሉት ዕለታት የሚገኙበት ሳምንታት ሰሙነ ሕማማት ይባላል፡፡ ዕለታቱም የዓመተ ፍዳ፣
የዓመተ ኩነኔ መታሰቢያ ናቸው፡፡ በእነዚህ ዕለታት ውስጥ የተለያዩ ትውፊታዊ እና ሃይማኖታዊ ክንዋኔዎች አሉ፡፡ ከነዚህ ክንዋኖዎች ውስጥ
አለመሳሳም፣ አክፍሎት፣ ቄጤማ ማሰር፣ ጥብጠባ፣ ጉልባን እና ሕፅበተ እግር ይገኙበታል፡፡ ስለእነዚህ ክንዋኔዎች በቅድስት ቤተ ክስቲያን
ስላለው ትውፊታዊ አፈፃፀም መዛግብት አገላብጠን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡

አለመሳሳም፡- በሰሙነ ሕማማት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች መስቀል እንደማይሳለሙት ሁሉ መጨባበጥ፣ መሳሳምን የትክሻ ሰላምታ መለዋወጥን አይፈጽሙም፡፡ ሰላምታ የማንለዋወጥበት ምክንያት አይሁድ ጌታን ለመስቀል ሰኞ እና ማግሰኞ መከሩ
አልሰመረላቸውም፡፡ ምክረቸው የተፈጸመው ረቡዕ ነው፡፡ ስለዚህ አይሁድ እያንሾካሾኩ እንሰቀለው ፤እንግለው ብለው ይማከሩ ነበር፡፡ በዘመነ ፍዳ
ወቅት ሠላምና ፍቅር አለመኖሩን የሚገልፅልን በመሆኑ ያንን ለማስታወስ ስላምታ አንለዋወጥም፡፡ መስቀልም አንሳለምም፡፡ ሳምንቱ
የክፋት ምክር የተመከረበት እንጂ የፍቅርና የደስታ ሳምንት የታየበት ባለመሆኑ ይህንን በማሰብ ሰላምታ አንለዋወጥም፡፡ አይሁዳ ጌታን
በጠላቶቹ ለማስያዝ እኔ የምስመው እርሱ ነው ያዙት ብሎ በሰላምታው ምልክት ሰጣቸው ይህ ሰላምታ አምሐ ቅድሳት አይደለም ተንኮል
የተሞለበት እንጂ፡፡ የዲያቢሎስም ሰላምታ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሔዋንን ስላም ለኪ ብሎ ነው ያታለላት የይሁዳም ሰላምታ ሰይጣናዊ ነው፡፡
ስለዚህ ይህንን ወቅትና ሁኔታ ለማሰብ በሰሙነ ሕማማት ሰለምታ ልውውጥ የለም፡፡ ዛሬ እየተስተዋለ ያለው ይኽው ሰላምታ ያለመለዋወጥ ሁኔታ ስርወ መሰረቱ ይህ ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ እዚህ ትውልድ ላይ ደርሷል፡፡ ይቀጥላልም፡፡

ሕፅበተ እግር፡- ጌታ በፍጹም ትህትና የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበበት፣ ከሐዋርያት ጋር ግብር የገባበትና የክርስትና ህይወት ማሕተም የሆነውን ምስጢረ ቁርባን ያከናወነበት ዕለት ነው ጸሎተ ሐሙስ ሕፅበተ እግር ጌታችን በዚህ እለተ እናንተ ለወንድማችሁ እንዲሁ አድርጎ ለማለት የደቀ መዛሙርቱን አግር በማጠቡ ምክንያት
የተሰጠ ምሳሌ ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው እኔ ለእናንተ እንዳደረኩ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና እውነት እውነት እላችኋለሁ
ባሪያ ከጌታው አይበልጥም መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም ይህን ብታውቁ ብታደርጉትም ብጹዓን ናችሁ፡፡ ዮሐ 13፡16-17 በማለት ትህትናውን አሳይቷል ጌታ በዚህ እለተ የደቀ መዛሙርቱን እግር ሲያጥብ እኔ መምህራችሁ ስሆን እግራችሁን ካጠብኳችሁ አርአዬን ሰጥቻችኋለሁ እናንተም የወንድማችሁን እግር ታጥቡ ዘንድ ይገባል፡፡ ነገር ግን
ከእናንተ አንዱ ለሞት አሳልፎ ይሰጠኛል አለ ደቀ መዛሙርቱም ማንይሆን አሉ፡፡ ጌታም ህብስት ቆርሼ፣ ከወጡ አጥቅሼ የምሰጠው
እርሱ ነው አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ደንግጠዋል ይሁዳን ማመልከቱ ነበር ለጊዜው አልገባቸውም፡፡ ጌታችን መዳኃኒታችን የሐዋርያቶቹን እግር በማጠብ ትሕትናን ካስተማረቸው በኋላ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን የሰጣቸው የኦሪትን መስዋዕት የሻረው እና መስዋዕተ ሐዲስን
የሠራው በዚሁ እለት ነው፡፡

አክፍሎት፡- በሰሙነ ሕማማት እለተ ዓርብ ከስግደት በኋላ ምእመናን በየቤታቸው ጥቂት ነገር ለቁመተ ሥጋ ቀምሰው እስከ እሁድ /የትንሳኤ
በዓል/ ይሰነብታሉ፡፡ ይህ አክፍሎት ይባላል፡፡ ከዓርብ እስከ ቅዳሜ ሌሊት ለእሁድ አጥቢያ ማክፈል የብዙዎች ነው፡፡ አንዳንዶች ግን
ከሐሙስ ጀምረው ያከፍላሉ፡፡ ይህም እመቤታችን ያዕቆብ እና ዩሐንስ የጌታን ትንሳኤ ሳናይ እህል ውኃ አንቀምስም ብለው እስከ ትንሳኤ
መቆየታቸውን ተከትሎ የመጣ ትውፊት ነው፡፡ ይህንን ትውፊት አስመልክቶ ሄሬ ኔዋስ አውሳብዩስ የተባሉ ጸሀፍተ ሐዋርያት በስሙነ
ህማማት ከደረቅ ዳቦ እና ከትንሽ ውሃ በቀር እንደ ማይመገቡ እና ከሐሙስ ጀምረው እንደሚያከፍሉ ጽፈዋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ሐዋሪያት ሌሎቹንም እንዲያከፍሉ እንዳሳሰቡና ከሐሙስ ጀምሮ ያልተቻለው ቢያንስ ከዓርብ ጀምሮ እንዲያከፍል ማዘዛቸውን ጽፈዋል፡፡
የእኛ ቤተ ክርስቲያን ትምህርትም ይኽው ነው፡፡ ቅዳሜ ይበላል ማለት ግን ቅዳሴው ሌሊት ስለሆነ በልቶ እንደ ማስቀደስ እና በልቶ እንደመቁረብ ይቆጠራል፡፡ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን
ተከታዮችም ይህንኑ ትውፊት ሲከውኑ አያሌ ዘመናት ተቆጥሯል፡፡ጉልባን እና ቄጠማ፡- ጉልባን ከባቄላ ክክ፣ ከስንዴ ወይንም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጀና የጸሎት ሐመስ እለት የሚበላ ንፍሮ ነው፡፡ የጉልባን ትውፊት እስራኤላውያን ከግብጽ ተሰደው በሚነጡበት ጊዜ በችኮላ ስለነበር አቡክተው ጋግረው መብላት
ያለመቻላቸውን ሁኔታ ያመለክታል፡፡ ያን ጊዜ ያልቦካው ሊጥ እያጋገሩ ቂጣ መብላት ንፎሮም ቀቅለው ስንቅ መያዝ ተግባራቸው ነበር፡፡ ይህን
ለማሰብ በሰሙነ ሕማማት ቂጣና ጉልባን በማዘጋጀት በዓል ይታሰባል፡፡
በጸሎተ ሐሙስ ይህንን መሰረት በማድረግ የሚዘጋጀው ጉልባን እንዲሁም ቂጣ ጨው በዛ ተደርጎ ይጨመርበታል፡፡ ጨው ውሃ የሚያስጠማ በመሆኑ የጌታን መጠማት ያስታውሳል፡፡ ይህ ትውፊታዊ ስርዓት በእስራኤላውያን የመጣ ሲሆን በኢትዮጵያ አብዛኛዎቹን የትውፊት ክንዋኔዎች የብሉይ ኪዳን መነሻ ስላላቸው ስርዓቱ ዛሬም
ይከበራል፡፡

ጥብጠባ፡- በሰሙነ ሕማማት እለተ ዓርብ ስቅለቱ መታሰቢያ ነው፡፡ ምእመናኑ በሰሙነ ሕማማት የሰሩትን ይናዘዛሉ፡፡ ካህናቱን በወይራ ቅጠል ትከሻቸውን እየጠበጠቡ ቀን ከሰገዱት ስግደት በተጨማሪ ሌላ ስግደት ያዟቸዋል፡፡ ጥብጠባው የተግሳፅ ምሳሌ ነው፡፡ ጥብጠባው የሚደረግለት ሰው በህማማቱ ወቅት የፈጸማ በደል ወይም ኃጢአት ካለ ይህንኑ በመናገር የስግደቱ ቁጥር ከፍ እያለ እንዲል ያደርጋል፡፡ ይህ በስቅለተ ቀን የሚፈጸም ስነ ስርዓት ሲሆን ጥብጣቤ ማለት ቸብ
ማድረግ ማለት ነው፡፡ ህዝብ ክርስቲያኑ በእለተ ስቅለት ሲሰግድ ሲጸልይ ሲያነብ ከዋለ በኃላ ሰርሆተ ህዝብ (የህዝብ መሰነባበቻ) ከመሆኑ በፊት በወይራ ቅጠል እያንዳንዱን ምዕመን ጀርባ ቸብ ቸብ መደረጉ የጌታን ግርፋት ያስተውሳል፡፡ ማቴ 26፡26 ማቴ 19፡1-3
ቄጠማ(ቀጤማ)፡- በቀዳም ስዑር ቀሳውቱን ዲያቆናቱ ቃጭል /ቃለ አዋዲ/ እየመቱ ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሳኤሁ አግሃደ የሚለውን ያሬዳዊ ዜማ በመዘመር ጌታ በመስቀሉ ሰላምን እንደሰጠ እና ትንሳኤውንም እንደገለጠልን በማብሰር ቄጤማውን ለምእመናን ይሰጣሉ፡፡ ምእመኑም ለቤተ ክርስቲን አገልግሎት የሚውል ገጸ በረከት ያቀርባሉ ቀጤማውንም በራሳቸው ያስራሉ፡፡ ይህም አይሁድ ጌታችንን እያሰቃዩ ሊሰቅሉት ባሉ ጊዜ የእሾህ አክሊል ጭንቅላቱ ላይ ያሰሩበትን ድርጊት የሚያስተውስ ነው፡፡ በዚህ እለት ልብስ ተክህኖ የለበሱ ካህናትና ዲቆናትን ቄጠማ ተሸክመው ቃጭል ሲቃጭሉ መታየታቸው እለተ ትንሳኤውን ለሚናፍቅ ምእመን ትልቅ ብስራት ነው፡፡ ቄጠማው የምሥራች ምልክት ተደርጐ የተወሰደው በኖህ ዘመን ከተፈጸመው ታሪክ ጋር በማቆራኘት ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን
በጻድቁ ኖኅ ዘመን የነበሩ ሕዝቦች ከሕገ እግዚአብሔር ውጪ ሆነው እጅግ የሚያሳዝን ኃጢአት በሠሩ ጊዜ በንፍር ውኃ ተጥለቅልቀዋል፡፡
በወቅቱ ጻድቁ ኖኅ ወደ መርከብ ይዞአቸው ከገባው እንስሳት መካከል የውኃውን መጉደል ለመረዳት ርግብን በመርከብ መስኮት አሾልኮ
ይለቃታል፤ እርሷም ቄጠማ በአፍዋ ይዛ
ትመልሳለች፡፡ ዘፍ.9-1-29፡፡ ኖኅም በዚህ ቄጠማ የውኃውን መድረቅ ተረድቶ ተደስቷል፡፡ «ቄጠማ»፣ ለጥፋት ውኃ መድረቅ የምሥራች መንገሪያ እንደሆነ አሁንም በክርስቶስ ሞት ሞተ ነፍስ ከሰው ልጆች ተወገደ ስትል ቤተ ክርስቲያን ለልጆቿ ቄጠማ ታድላለች፡፡ ምእመናንም የምሥራች ተምሳሌት የሆነውን ቄጠማ በግንባራቸው ያስሩታል፡፡ የክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሚያቃጥለው ዋዕየ ሲኦል /የሲኦል ቃጠሎ/ ወደ ልምላሜ ገነት ጥንተ ማኅደራቸው መመለሳቸውን በዚህ አኳሃን እየገለጡ በዓለ ትንሣኤን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያከብራሉ፡፡
ለአስተያየት፣ ጥቆማ እንዲሁም በቻናሉ ላይ የሚለቀቁ ሃይማኖታዊ ጽሁፎች ዙርያ ከ ቻናሉ ቤተሰቦች ጋር በጋራ ለመወያየት እና ሃሳብ ለመስጠት ከታች ያለውን ግሩፕ ይቀላቀላሉ
👇👇👇👇
@rituaHM
"+" ጸሎተ ሐሙስ "+"

ጸሎተ ሐሙስ በብሉይ ኪዳን

ጸሎተ ሐሙስ በብሉይ ኪዳን ለፋሲካ ዝግጅት ተደርጎበታል (ማቴ.፳፮፥፯-፲፫)፡፡ ‹ፋሲካ› ማለት ማለፍ ማለት ነው፡፡ ይኸውም እስራኤላውያን
በግብጽ ምድር ሳሉ መልአኩን ልኮ እያንዳንዱ እስራኤላዊ የበግ ጠቦት እንዲያርድና ደሙን በበሩ ወይም በመቃኑ እንዲቀባ ለሙሴ ነገረው፡፡
ሙሴም የታዘዘውን ለሕዝቡ ነገረ፤ ዅሉም እንደ ታዘዙት ፈጸሙ፡፡ በኋላ ከእግዚአብሔር ዘንድ መቅሠፍት ታዞ መልአኩ የደም ምልክት
የሌለበትን የግብጻውያንን ቤት በሞተ በኵር ሲመታ፤ የበጉ ደም ምልክት ያለበትን የእስራኤላውያንን ቤት ምልክቱን እያየ አልፏል፡፡ ፋሲካ መባሉም ይህን ምሥጢር ለማስታወስ ነው (ዘፀ. ፲፪፥፩-፳)፡፡
በዚህ መነሻነት በየዓመቱ እስራኤላውያን በመጀመሪያው ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን በግ እያረዱ የፋሲካን በዓል ያከብራሉ፡፡ አገራችን
ኢትዮጵያም አስቀድማ ብሉይ ኪዳንን የተቀበለች አገር እንደ መኾኗ ይህን ሥርዓት ትፈጽም ነበር፡፡ በሐዲስ ኪዳንም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ‹ፋሲካ› ተብሎ የተጠራበት ምክንያት ጌታችን በዚህ በፋሲካ በዓል ራሱን የተወደደ ምሥዋዕት አድርጎ ደሙን ስላፈሰሰልን
ነው፡፡ በደሙ መፍሰስም ሞተ በኵር የተባለ ሞተ ነፍስ ርቆልናል፡፡ ስለዚህም ክርስቶስን ‹ፋሲካችን› እንለዋን (፩ኛ ቆሮ. ፭፥፯፤ ፩ኛ ጴጥ. ፩፥፲፰-፲፱)፡፡

የጸሎተ ሐሙስ ስያሜዎች

ጸሎተ ሐሙስ በቤተ ክርስቲያን በርካታ ስያሜዎች አሉት፡፡ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን የተዋሐደ አምላክ መኾኑን ለመግለጥና ለአርአያነት ጠላቶቹ መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ
ያደረበት ቀን ነውና ‹ጸሎተ ሐሙስ› ይባላል (ማቴ. ፳፮፥፴፮-፶፮)፡፡
ጌታችን በዚህ ዕለት የደቀ መዛሙርቱን እግር በፍጹም ትሕትና ዝቅ ብሎ አጥቧል፡፡ ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለምን ዅሉ ኃጢአት ለማጠብ
የመጣ የንጽሕና፣ የቅድስና አምላክ መኾኑን ያጠይቃል፡፡ ስለዚህም ዕለቱ ‹ሕጽበተ ሐሙስ› ይባላል፡፡ ይህን ለማስታወስ ዛሬም ሊቃነ
ጳጳሳትና ቀሳውስት ‹‹በመካከላችን ተገኝተህ የእኛንና የሕዝብህን ኃጢአት እጠብ፤ እኛም የአንተን አርአያነት ተከትለን የልጆቻችንን እግር
እናጥባለን፤›› ሲሉ በቤተ ክርስቲያን የተገኙ ምእመናንን እግር በወይንና በወይራ ቅጠል ያጥባሉ፡፡
ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንዱ ምሥጢረ ቍርባን በዚህ ቀን ተመሥርቷልና ዕለቱ ‹የምሥጢር ቀን› ይባላል፡፡ ይኸውም ጌታችን
ኅብስቱንና ጽዋውን አንሥቶ ‹‹ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቈረሰው ሥጋዬ ነው፡፡ እንካችሁ፤ ብሉ፡፡ ይህ ስለ እናንተ ነገ
በመስቀል ላይ የሚፈስ ደሜ ነው፤ ከእርሱም ጠጡ፤›› በማለት እርሱ ከእኛ፤ እኛም ከእርሱ ጋር አንድ የምንኾንበትን ምሥጢር ከጠላት ዲያብሎስ ሰውሮ፣ ለደቀ መዛሙርቱ የገለጠበት ቀን በመኾኑ የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡ በዚህ ዕለት ክርስቲያን የኾነ ዅሉ በንስሐ ታጥቦ ቅዱስ
ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለመቀበል ይዘጋጃል፡፡
መድኃኒታችን ክርስቶስ መሥዋዕተ ኦሪት ማለትም በእንስሳት ደም የሚቀርበው መሥዋዕት ማብቃቱን ገልጦ፣ ለድኅነተ ዓለም ራሱን
የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበበት ዕለት በመኾኑ ይህ ዕለት ‹የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ› ይባላል (ሉቃ. ፳፪፥፳)፡፡ ‹ኪዳን› ማለት በሁለት
ወገን መካከል የሚደረግ ውል፣ ስምምነት፣ መሐላ ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ጌታችን ለአዳምና ለልጆቹ ዅሉ ዘለዓለማዊውን ቃል ኪዳን
በራሱ ደም የፈጸመበት ዕለት ስለ ኾነ ሐሙስ ‹የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ› ተባለ፡፡
ይህ ዕለት ለኃጢአትና ለዲያብሎስ ባሪያ ኾኖ መኖር ማብቃቱ የተገለጠበት፤ የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት
ቀን ስለ ኾነ ‹የነጻነት ሐሙስ› ይባላል፡፡ ጌታችን ስለ ሰው ልጅ ነጻነት ሲናገር ‹‹ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፡፡ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፤›› በማለት ከባርነት የወጣንበትን፤ ልጆች የተባልንበትን ቀን የምናስብበት በመኾኑ
ሊቃውንቱ ‹የነጻነት ሐሙስ› አሉት (ዮሐ. ፲፭፥፲፭)፡፡ እያንዳንዱ ክርስቲያንም ከኃጢአት ባርነት ርቆ፣ ከእግዚአብሔር ጋር የሚወዳጀውን መልካም ሥራ በመሥራት ሕይወቱን መምራት ይኖርባታል፡፡ ባሮች
ሳይኾን ወዳጆች ተብለን በክርስቶስ ተጠርተናልና፡፡
በዚህ ዕለት እንደ ማክሰኞ ዅሉ ጌታችን በዮሐንስ ወንጌል ፲፬፥፲፮ የሚገኘውን ሰፊ ትምህርት ለደቀ መዛሙርቱ አስተምሯል፡፡
የትምህርቱም ዋና ዋና ክፍሎችም ምሥጢረ ሥላሴን፣ ምሥጢረ ሥጋዌንና ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን ያካትታሉ፡፡ ጌታችን እነዚህን
ትምህርቶች በስፋትና በጥልቀት መማር እንደሚገባ ሲያስረዳ፣ ለደቀ መዛርቱ ምሥጢሩን በተአምራት ሊገልጥላቸው ሲቻለው በሰፊ
ማብራርያ እንዲረዱት አድርጓል፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ያልገባቸውንም እየጠየቁ ተረድተዋል፡፡ ምእመናንም በቤተ ክርስቲያን ተገኝተን መማርና ያልገባንን ጠይቀን መረዳት እንደሚገባን ከዚህ እንማራለን፡፡ መድኃኒታችን ክርስቶስ ራሱን ለአይሁድ አሳልፎ የሰጠውም በዚሁ ዕለት ከምሽቱ በሦስት ሰዓት ነው (ማቴ. ፳፮፥፵፯-፶፰)፡፡

በጸሎተ ሐሙስ በቤተ ክርስቲያን የሚፈጸም ሥርዓት

በዚህ ዕለት ስግደቱ፣ ጸሎቱ፣ ምንባባቱ እንደ ተለመደው ይከናወናሉ፡፡ መንበሩ (ታቦቱ) ጥቁር ልብስ ይለብሳል፡፡ ጸሎተ ዕጣን ይጸለያል፤ ቤተ ክርስቲያኑም በማዕጠንት ይታጠናል፡፡ ሕጽበተ እግር ይደረጋል፡፡ ቅዳሴ ይቀደሳል፡፡ በየቤቱ ደግሞ ጉልባን ይዘጋጃል፡፡

ሕጽበተ እግር

ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት ዲያቆኑ ሁለት ኵስኵስቶችን ውኃ ሞልቶ ያቀርባል፤ አንዱ ለእግር፣ አንዱ ለእጅ መታጠቢያ፡፡ ‹ጸሎተ አኰቴት› በመባል የሚታወቀው የጸሎት ዓይነት ይጸለያል፡፡ ወንጌል ተነቦ ውኃው በካህኑ (በሊቀ ጳጳሱ) ይባረክና የሕጽበተ እግር ሥርዓት ይከናወናል፡፡ ይኸውም
ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ያሳየውን የተግባር ትምህርት ለማሳየት ነው (ዮሐ. ፲፫፥፲፬)፡፡ ከውኃው በተጨማሪ የወይራና
የወይን ቅጠልንም ለሥርዓተ ሕጽበቱ ማስፈጸሚያነት እንጠቀምባቸዋለን፡፡ ምሥጢሩም የሚከተለው ነው፤ ወይራ ጸኑዕ ነው፡፡ ወይራ ክርስቶስም ጽኑዕ መከራ መቀበሉን ከማስረዳቱ
በተጨማሪ እኛም (እግራችንን የሚያጥቡን አባቶች እና የምንታጠበው ምእመናን) መከራ ለመቀበል ዝግጁ ነን ለማለት ሥርዓተ ሕጽበቱን
በወይራ እንፈጽማለን፡፡ የወይኑ ቅጠልም መድኃኒታችን ክርስቶስ በወይን የተመሰለ ደሙን አፍስሶ ለምእመናን የሕይወት መጠጥ አድርጎ
መስጠቱን ለማዘከር በወይን ሥርዓተ ሕጽበትን እናከናውናለን (ማቴ. ፳፮፥፳፮)፡፡ በቀኝና በግራ የቆሙ ሊቃውንትም ‹‹ሐዋርያቲሁ ከበበ እግረ
አርዳኢሁ ሐጸበ›› እያሉ ይዘምራሉ፡፡ ይህ ሥርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ ሥርዓተ ቅዳሴው ተከናውኖ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ምእመናን ይቀበላሉ፡፡

ቅዳሴ
የጸሎተ ሐሙስ ቅዳሴ የሚከናወነው በተመጠነ ድምፅ ሲኾን፣ እንደ ደወል (ቃጭል) የምንጠቀመውም ጸናጽልን ነው፡፡ ልኡካኑ የድምፅ
ማጉያ ሳይጠቀሙ በለኆሣሥ (በቀስታ) ይቀድሳሉ፡፡ ምክንያቱም ይሁዳ በምሥጢር ጌታችንን ማስያዙን ለመጠቆም ሲኾን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የዘመነ ብሉይ ጸሎት ዋጋው ምድራዊ እንደ ነበር ለማስታወስ ነው፡፡
በመቀጠል ክብር ይእቲ፣ ዕጣነ ሞገር፣ ዝማሬ የተባሉ የድጓ ክፍሎች ተዘምረው አገልግሎቱ ይጠናቀቃል፡፡ ሕዝቡም ያለ ኑዛዜና ቡራኬ
ይሰናበታሉ፡፡

ጉልባን

ጉልባን ከባቄላ ክክ፣ ከስንዴ ወይንም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጅና የጸሎተ ሐሙስ ዕለት የሚበላ ንፍሮ ነው፡፡ በጸሎተ
ሐሙስ በቤት ውስጥ ከሚፈጸሙ ተግባራት አንዱ ጉልባን ማዘጋጀት ነው፡፡
ጉልባን እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ሲወጡ በችኮላ መጓዛቸውን የምናስታውስበት ከእስራኤላውያን የመጣ ትውፊታዊ ሥርዓት ነው፡፡ በአገራችን ኢትዮጵያ አብዛኞቹ የትውፊት ክንዋኔዎች የብሉይ ኪዳን መነሻ ስላላቸው ይህ ሥርዓት ዛሬም በኢትዮጵያውያን ምእመናን ዘንድ ይከበራል፡፡
ጉልባን እስራኤላውያን ከባርነት በወጡ ጊዜ አቡክተው፣ ጋግረው መብላት አለመቻላቸውን ያስታውሰናል፡፡ በወቅቱ ያልቦካውን ሊጥ እየጋገሩ ቂጣ መመገብ፤ ንፍሮ ቀቅለው ስንቅ መያዝ የመንገድ ተግባራቸው ነበርና፡፡ ይህን ታሪክ ለማሰብም በሰሙነ ሕማማት በተለይም በጸሎተ ሐሙስ ቂጣና ጉልባን ይዘጋጃል፡፡ በጸሎተ ሐሙስ
የሚዘጋጀው ጉልባንና ቂጣ ጨው በዛ ተደርጎ ይጨመርበታል፡፡ ይኸውም ጨው ውኃ እንደሚያስጠማ ዅሉ፣ ጌታችንም በመከራው ወቅት ውኃ መጠማቱን ለማስታወስ ነው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
ምንጭ፡-
ስምዐ ተዋሕዶ (ልዩ ዕትም ዘሰሙነ ሕማማት)፣ ከሚያዝያ ፩ -፲፭ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም፣ ገጽ ፮-፯፣ ፲፫ እና ፳፤ ማኅበረ ቅዱሳን፣ አዲስ አበባ፡፡
"አባት ሆይ! ቢቻልስ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ"

[ይህ ጽሑፍ የተወሰደው ዓርብ ሌሊት ስድስት ሰዓት ከሚነበበው ከግብረ ሕማማት መጽሐፍ ነው፡፡ የተጻፈውም በጊዜው ለነበሩ መርቅያናውያንና ማኒያውያን ለተባሉ መናፍቃን ምላሽ ሲሆን በእኛ ዘመን ደግሞ በግልጥ
ለሙስሊም፣ ለይሖዋ ምስክሮችና አውቀውም ይሁን ሳያውቁ (ሎቱ ስብሐትና) ክርስቶስን ዝቅ ዝቅ ለሚያደርጉ ለሌሎች መናፍቃን መልስ የሚሆን ድርሳን (Homily) ነው፡፡]
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አስቀድሞ “ይህን ረቂቅ ምክርና ጥልቅ ምሥጢር የማያስተውሉ ጌታ እንዲህ በማለቱ ፈርቶ ነው ይሉታል፡፡ ነገር ግን ወዳጆቼ ሆይ! እኛ ደግመን እንነግራችኋለንና አእምሯቸው ስለ ጠፋባቸው ስለ እነርሱ ዘለፋ ዛሬ
በፊታችሁ እንደ ትልልቆች ያይደሉ አእምሮ እንደሌላቸው ሕፃናት ናቸው ብለን
እንተረጕምላችኋለን” በማለት ይጀምራል፡፡ ቀጥሎም እርሱ ይጠይቅና ጌታ የመለሰለትን መልስ ይነግረናል፡፡
ብጹዕ አባታችን እንዲህ በማለት ጥያቄውን ይቀጥላል፡- “አቤቱ ጌታ ሆይ! ስለ
እኛ መከራ ትቀበል ዘንድ ለምን መጣህ? ለምንስ ለመስቀል ደረስክ? ለምን ወደህ በፈቃድህ ፈራህ? ለምን አባት ሆይ የሚቻል ከሆነ ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ አልክ? የተገዢን ባሕርይ ገንዘብ ታደርግ ዘንድ ያስገደደህ ሳይኖር አንተ በፈቃድህ የተዋሐድክ አይደለምን? አባት ሆይ የሚቻል ከሆነ ይህ የሞት ጽዋ ከእኔ ይለፍ ብለህ ለምን ትማልዳለህ? ይህንንም ጽዋ ትጠጣው ዘንድ አልተጋህምን? አንተ ራስህ የምጠመቀው ጥምቀት አለኝ፤ እፈጽመውም ዘንድ እተጋለሁ፤ እስከምጠጣውም ድረስ እታወካለሁ ያልክ አይደለምን? ትጠጣው ዘንድ የተሰጠህን ዛሬ ስለምን አልተጋህም? ለምንስ እምቢ አልክ? አባት ሆይ የሚቻል ከሆነ ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ ለምን አልክ? ስለ እኛ ትሞት ዘንድ እንዳለህ
አላወቅህምን? አንተ የሰው ልጅ ክርስቶስን አብዝተው መከራ ያጸኑበታል፤ ይሰቅሉታል፤ ይገድሉታል፤ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል ያልክ አይደለምን? ደቀ መዝሙርህ ጴጥሮስን ይህ በአንተ ላይ እንዲህ ይሆን ዘንድ አይገባም ባለህ
ጊዜ፡- ከኋላዬ ወግድ አንተ ባለጋራ እንቅፋት ሁነህብኛልና የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ብለህ የገሰጽከው አይደለምን? እርሱን ጴጥሮስን የከለከልከውን እንግዲህ ለምን አባት ሆይ የሚቻል ከሆነ ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ
አልክ? የሚታየውንና የማይታየውን የፈጠርክ አንተ አይደለህምን? ድውያንን በእጅህ ዳስሰህ እንዳዳንህ በሞት ሥጋው የፈረሰውን አልዓዛርን በቃልህ አጽንተህ እንዳስነሣህ፤ የደም ምንጭም የሚፈሣትን በልብስህ ዘርፍ እንዳደረቅክ፤ በአምስት እንጀራ አምስት ሺህ ሰውን እንዳጠገብክ፤ ባሕሩን ነፋሱን ገስጸህ ጸጥ እንደ አደረግህ፤ ሞትንም ደምስሰህ እንደ አጠፋኸው
እናውቃለን፡፡ ዛሬ ሞትን እንደምትፈራ ሁነህ አባት ሆይ የሚቻል ከሆነ ይቺ የሞት ጸዋ ከእኔ ትለፍ ለምን ትላለህ? ሞትን የምትፈራ ከሆነ ትንሣኤም ሕይወትም እኔ ነኝ ለምን አልክ? ሕይወትም ትንሣኤም ሞትን አይፈራም፡፡ እንግዲህ የሚቻል
ከሆነ ይቺ የሞት ጽዋ ከእኔ ትለፍ ለምን አልክ?
ገና ሳትፈጥረው አስቀድመህ ሁሉን የምታውቅ ሆይ! አላወቅህምን? ይህ የሞት ጽዋ ከአንተ ማለፉ ይቻል እንደሆነ አይቻልም እንደ ሆነ አስቀድመህ አታውቅምን? ከወልድ በቀር አብን የሚያውቀው የለም እንዴት አልክ? ይህም
ጽዋ ማለፉንና አለማለፉን አታውቅምን? አንተስ ጳውሎስ ከእርሱ የተሠወረ ፍጥረት የለም፤ ሁሉም በፊቱ ፈጽሞ የተገለጠ ነው እንዴት አልክ? …አሁንም እኔ አላውቅም የሚቻል ከሆነ እንግዲህ ጽዋ ከእኔ ይለፈ እንዴት አልክ? በዚህ ቃል
ውስጥ ገና ያልተገለጸ ሥውር ምሥጢር ቢኖርበትም ይህ ነገር አቤቱ ላንተ አይገባህም፡፡ አንተ የአምላክ ልጅ አምላክ ነህ፤ የእግዚአብሔር አብ ቃል ነህ፤ ጥበብና ኃይል ነህ፤ ጸዳልና ብርሃን ነህ፤ የእውነት ፀሐይ ነህ፤ በኃጢአት ለሞትን
ለእኛ የትንሣኤያችንና የሕይወታችን ምንጭ ነህ፡፡”
ብጹዕ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህ “አባት ሆይ የሚቻል ከሆነ ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ” የሚለው ቃል “እንደማይታይና እንደማይመረመር እንደ መለኰትና እንደ ትስብእት ተዋሕዶ ይመስላል፤ ስለዚህም ይህች ምሥጢር ለብዙዎች ጭንቅና
ጠባብ መንገድ ሆነች” በማለት “ኢየሱስ ፈርቶ ይህን ቃል ተናግሮታል” የሚሉትን መናፍቃን ይገስጻል፡፡ ከዚያም ጌታ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ ለማስረዳት እርሱ በጌታ ተገብቶ (ለንግግር ያመች ዘንድ) ይመልስልናል፡፡ እንዲህም ይላል፡- “ጥበብ ለራስዋ ቤትን ሠራች ተብሎ እንደተጻፈ ራሴ የተዋሐድኩትን ሥጋ እንደፈጠርኩ፤ በሞት የደከመ ሥጋዬን ሕያው አድርጌ ማሥነሣት እንደምችል፡- አይሁድ እናንተ ግብዞች ሰነፎች ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት በሦስተኛው ቀን አነሣዋለሁ ብያቸው ነበርና፤ አባት ሆይ የሚቻል ከሆነ ይህ ጽዋ ሞት ከእኔ ይለፍ ያልኩት ሞትን በመፍራትና በመደንገጥ እዳልሆነ ለራስህ እወቅ፤ ተጠንቀቅ፤ ይህ ሥውር የሆነ የምሥጢር ቃል ነው እንጂ፡፡ ይህንንም ልመና እኔ በጥበብ ተናገርኩ፡፡ ይህች ቃል ሰይጣንን ጠብቃ የምታጠምድ ወጥመድ ናት፤ በእነዚህም ቃሎች ሰይጣን አጠምደው ዘንድ አለኝና፡፡
ተአምራትን እንዳደረግሁ፣ በሽተኞችን በእጄ ዳስሼ እንዳዳንኩ፣ አጋንንትም በቃሌ እንዳባረርኩ፣ የሸተተ በድን እንዳስነሣሁ፣ ባሕሩን ነፋሱን እንደገሠፅኩ፣ እነርሱም በመፍራትና በመንቀጥቀጥ እንደታዘዙልኝ ሰይጣን አይቶኝ ነበር፡፡ ያደረግሁትን ይህን ተአምራት አይቶ እኔ የአምላክ ልጅ እንደሆንኩ አውቆ እኔም ብሰቀል እርሱ እንደሚጠፋ ወደ ሲዖልም ብወርድ የብረቱን መቆለፍያ ቀጥቅጬ እንደማጠፋ የብረቱን የናሐሱን መዝጊያ ሰብሬ ሁሉን ወደ ሰማይ እንደማሳርግ ልብ ብሎ አስተውሎ ፈርቶ እንዳሸሽ፣ እንዳይጠፋ፣ በመስቀል የሚደረገው
ምሥጢረ ድኅነት እንዳይቀር እንዳይቋረጥ ምን ላድርግ? አልኩ፡፡ ስለዚህ ራሴን ብልህ እንዳጠመደው ወጥመድ አድርጌ ፈርቶ ከሞት እንደሚደነግጥም አባት ሆይ የሚቻል ከሆነ ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ አልኩ፡፡ በእነዚህም የትሕትና ቃሎቼ ዕሩቅ ብእሲ (ሰው ብቻ) እመስለዋለሁ፤ ምሥጢረ ድኅነት የሚፈጸምበት መስቀል በምድር መካከል ይተከል ዘንድ ይቸኩላል፤ በእኔ ላይ የሚጠበብብኝ እየመሰለው እኔ ግን ለሰው ሁሉ ድኅነት ከእርሱ የሚደረግብኝ ሁሉ እታገሥ ዘንድ
አለኝ፡፡እርሱ የመጀመርያውን ሰው አዳምን ያጠፋው ዘንድ እጅግ ተተንኩሎ ተጠብቦበት ነበር፡፡ በተንኰል አነጋገር አዳምን እንደ ተጠበበበት እንግዲህ እኔ ሁሉን ለማዳን በይበልጥ ለምን አልጠበብበት? እንደዚሁ እኔም እርሱ ባመጣው ተንኰል ላጠምደው ትሕትናን በተመሉ ቃሎች ተጠበብኩበት፡፡ በመለኰታዊ
አነጋገርም ለሰይጣን አልተገለጽኩለትም፤ አባት ሆይ የሚቻል ከሆነ ይህ ጽዋ ሞት ከእኔ ይለፍ አልኩ እንጂ፡፡
ዓሣ አጥማጅ መቃጥኑን በመብል ሸፍኖ ወደ ባሕር ውስጥ በሚጥለው ጊዜ ሲስበው ለዓሣው እንደሚያስጐመጀው አንድ ጊዜም ሊጐርሰው ጕረሮውን እንደሚከፍት እንዲሁም እኔ መለኰቴን መብል አድርጌ ጣልኩለት፡፡ ለዘላለሙ
በማትመረመር ተዋሕዶ በሥጋዬ ውስጥ ያለ የመለኰት መቃጥንን ጣልኩለት፡፡
በሚያጠምድበት ላይ የተደረገው የሚጐረስ ትል (ወላፍ) ካልተንቀሳቀሰ ዓሣው መንጠቆውን ለመጕረስ አይጐመጅም፡፡ ስለዚህ ሥጋዬን እንደሚጐረስ (ወላፍ) ትል አድርጌ አሳየሁት፡፡ እኔ ሰው ያይደለሁ ትል ነኝ አልኩ፡፡ ይህን ሰምቶ በዚህ
በሥጋዬ ውስጥ ያለችን መቃጥን ሩጦ ሂዶ ይጐርስ ዘንድ፡፡ እኔም በመቃጥኔ እስበዋለሁ፤ በኢዮብ መጽሐፍ ከይሲን በወጥመድ ትስበዋለህ ተብሎ የተጻፈውን ይፈጸም ዘንድ፡፡ እኔም ፈርቶ እንደሚሸሽ ሰው ሆኜ ነፍሴ እስከ ሞት
ደርሳ አዘነች፤ ተከዘች፤ አባት ሆይ የሚቻል ከሆነ ይህ ጽዋ ሞት ከእኔ ይለፍ አልኩ፡፡ ይህም
ሰይጣን እነዚህን የትሕትና ቃሎች ሰምቶ በአሳቡ ይህ እንደማንም ሰው ነው፤ እውጠዋለሁ (እቆራኘዋለሁ) አለ፡፡ አባቶች ነብያትን እነ አብርሃምን፣ ይሥሐቅን፣ ያዕቆብን እንደዋጥኳቸው (እንደተቆራኘኋቸው) ይህንንም እውጠዋለሁ
(እቆራኘዋለሁ) እንደሚፈራ ሰው አየዋለሁና አለ፡፡ እነሆ እንግዲህ እንደ ዕሩቅ ብእሲ መስየው ዋጠኝ (እቆራኘዋለሁ አለ)፤ ቃጣ፤ ግን በሆዱ አምላክ ሆኜ አገኘኝ፡፡ እርሱም እየተገዛ በሥጋ የተሸለመ (ሥጋን የተዋሐደ) መለኰቴን ዋጠ (ሊቆራኝ ቃጣ)፤ ግን የማይጠፋ የመለኰት ፍም ሆኖ አገኘው፤ ነገር ግን ውስጡን አቃጠለው፤ እንደ ተጻፈ ለዓለም እሳት አምጥቻለሁና፡፡
አባት ሆይ ይቺ ጽዋ ሞት ከእኔ ትለፍ ብዬ የተናገርኩት የተሳለ የመለኰትን ሰይፍ
እንደማላሳየው ሆኜ የበግ ጠቦት ያየ ጅብ (ዲያብሎስ) እንዳይሸሽ እንደ በግ ጠቦት ሆንኩለት፡፡ እንደ በግ ጠቦትም ይውጠኛል፤ ሦስት አፍ በሆነ ሰይፍ ከውስጡ ታረደ፤ ተቆረጠ፤ ሰላምን ልሰጥ አልመጣሁምና ሰይፍን እንጂ ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ አባት ሆይ የሚቻል ከሆነ ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ ያልኩት አነጋገሬ በጠቦት በተመሰለው ሥጋዬ ሁሉን የሚጠብቅ መለኰቴን ሸሸግሁት፤ በምናገረው ጊዜ ጅብ (ዲያብሎስ) እንዳይሸሽ ጠባቂውን መለኰቴን እገልጸው ዘንድ አልወደድኩም፤ ጠባቂ እንደሌለው በግና ረዳት እንደሌለው ሰው ሆንኩ ተብሎ እንደተጻፈ ጠባቂ እንደሌለው በግ ሆንኩ፡፡ እንደ ጠቦት ይውጠኛል፤
ከእረኛውም የተነሣ በውስጡ በመስቀል ፍላጻዎች ይነደፋል፡፡ የሰናፍጭ ቅንጣት ያላምጣል፤ በውስጡም የምታጠርሰውና የምትመረው መለኰታዊ ግብር ሆና አገኛት፡፡ እንደ ዕሩቅ ብእሲ ያላምጠኛል፤ በውስጡም ጥርሶቹን የምትሰብር የጸናሁ ዓለት ሆኜ ያገኘኛል፤ ከዛሬ ጀምሮ ሰውን እንዳያላምጥ ያውቅ ዘንድ፤ አምላክ ጥርሶቹን በአፉ ውስጥ ይሰብራልና ያለውም ጽሑፍ ደረሰ ተፈጸመ፡፡…
በዋጠኝ ጊዜ ወድያውኑ ታውቆኛልና፡፡ ስለ እኔ ባየ ጊዜ ፀሐይ ፈጽሞ ጠፋ፤ ቀኑ ሌሊት ሆነ፡፡ ያን ጊዜም መረረው፤ በበታቹ ሲዖል በተገናኘችው ጊዜ መረረች (ደነገጠች) የሚል ጽሑፍ አለና፡፡…
ደግሞ ይህን ቃል ለሚሰሙ ሁሉ እንደ ደካማ እንደ ሆንኩ ይመስላቸዋል፤ የእግዚአብሔር ድካም ከሰው እንዲበረታ አላወቁምና፡፡ እኔ ጽዋውን በጠጣሁ ጊዜ እርሱ ሰይጣን ሰክሮ እንዲጠወልግ ወገኖች ነቅተው አስተዋዮች እንዲሆን አላስተዋሉም፡፡ የትሕትና ቃሎቼን በሚሰማ ጊዜ ደስ ይሏል፤ በሚውጠኝ ጊዜ ግን አፉ ሲሰነጠቅ፣ መቃብሮች ሲከፈቱ፣ ሙታኖች ሲነሡ ያያል፡፡ ያን ጊዜ በሰማይ ተድላ ደስታ ይሆናል፤ ያን ጊዜ ሰይጣን ያዝናል፤ ስለ እነዚህ የትሕትና ቃሎቼ
በእነርሱ በመጠመዱ ያጸጸታል፤ በአጠመዳት ወጥመድም እንደተጠመደ ያውቃል፡፡ ጕድጓድ ቆፈረ፤ በቆፈረውም ጕድጓድ ይወድቃል፡፡ ደክሞ የሠራው ክፉ ሥራው በራሱ ይመለሳል፤ የሠራትም ዐመፅ በራሱ ላይ ትወርዳለች ተብሎ
እንደተጻፈ፡፡
ለእኔ ያስተከለው መስቀል የሰርግ ቤት እንደ ሆነች፤ ለእርሱ መሰቀያ መጥፊያ እንደሆነው ለእኔ ደስ መሰኛ ለእርሱ መሞቻ እንደሆነው አላወቀም…
አባት ሆይ ሰምተኸኛልና አመሰግነሃለሁ፤ ሁል ጊዜም በየጊዜው እንደምትሰማኝ አውቃለሁ እያልኩ ስናገር ልምሾ የሆነ ሰይጣን በሰማኝ ጊዜ አወቀ፡፡
አሁንም የሞት ጽዋ ታልፍ ዘንድ ጸልያለሁና ይህች ጽዋ ታልፍ ዘንድ ስለ ሞት የተደረገ ጸሎት እንዳይመስልህ፤ ከዚያም ወደ መስቀል መውጣትን ቸል ያልኩእንዳይመስልህ፤ ሞትም እንድትመጣልኝ ስጸልይ አባቴ የእኔ ፈቃድ ያይደለ
የአንተ ፈቃድ ይሁን አልኩ፡፡ ነፍሴን ከሥጋዬ ለይቼ ላኖራት ደግሞም አዋሕጄ ላስነሣት ሥልጣን እያለኝ በሞት ሥልጣን ወደ መያዝ ደረስኩ፡፡ መለኮቴን በነገር ሽፋን ሰውሬ የእኔ ፈቃድ ያይደለ ያንተ ያባቴ ፈቃድ ይሁን ብዬ እንደ ሰው
ተናገርኩ፡፡ ዕውረ ልቡና ሰይጣን ግን የእኔ ፈቃድና የአባቴ ፈቃድ አንድ እንደሆነ አያውቅም፤ የአባቴ የሆነ ሁሉ የእኔ ነው ብዬ እንደተናገርኩ አያውቅም፡፡ ዳግመኛም እኔና አብ አንድ ነን እንዳልኩ፤ እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ
እንዳለ ታውቁ ዘንድ አልኩ ያልኩትን፤ አብ በማንም በማን አይፈርድም ፍርዱን ሁሉ ለልጁ ሰጠው እንጂ ብዬ እንደተናገርኩ፤ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ ይገባል ወልድን የማያከብረው ሁሉ የላከው አብን አያከብረውም እንዳልኩ፤ አባቴ ሁሉን ሰጠኝ እንዳልኩ ረስቶታል፡፡ እኔ ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኬ መጣሁ፤ ሙሴ በምድረበዳ የነሐሱን እባብ እንደ ሰቀለው የሰው ልጅ ክርስቶስ እንዲሁ ይሰቀል ዘንድ አለው ያመነበት ሁሉ እንዳይጠፋ ለዘላለም ሕያው ሆኖ ይኖራል እንጂ እንዳልኩ፤ …የስንዴ ቅንጣት ይሰቀላል፤ በሚውጣትም
ጊዜ ትንታ ሆና ያገኛታል ያልኩትን ቃል ረስቶታል፤ እርሱም በዚች ኃይል ታንቆ ይጠፋል ተሳልቄበታለሁና፡፡
”ብጹዕ የሆነው አባታችን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “ነገር እንዳናበዛባችሁ ዝንጋዔ ልብንም እንዳናመጣባችሁ እናጠቃልለው” ይልና፡- “ጌታችን በአጋንንቶቹና በሰይጣን ዲያብሎስ ላይ ተሣለቀባቸው፤ ይህም “በችሎታዬ እሠራለሁ፤
በጥበቤም የአሕዛብን ግንብ አፍርሼ ፍጥረቱን ሁሉ እንደ ጫጩቶች እጨብጠዋለሁ፤ እንደ ወደቀ እንቁላልም አንሥቼ እወስደዋለሁ፤ ተከራክሮ የሚነጥቀኝ የለም” በማለት በትዕቢት ቃሉን ከፍ አድርጎ በመናገር የሚታበይ ሰነፍ ሰይጣንን እንቡዝ ልብ ያደርጓል፡፡ ሰይጣንም ከአጋንንቶቹ ጋራ መሣለቅያ ይሆን ዘንድ አለው፤ እንደዚሁ የሚመኩ ሁሉ አአምሮ እንደሌላቸው ሕፃናት ይሆናሉና፡፡ ስለዚህም የሚሠሩትን አያውቁም ነበር፤ አውቀውስ ቢሆን የክብር ባለቤት ክርስቶስን ባልሰቀሉትም ነበር፡፡…
ስለዚህ አስቀድመን እንደነገርናችሁ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፈራ አይምሰላችሁ፤ ይቺ ጽዋ ሞት ከእርሱ ታልፍ ዘንድ ስለ ጽዋ ሞት አልጸለየም” በማለት ከማር የጣፈጠውን ትምህርቱ ይጨርሳል፡፡
ከአባቱ ጋር ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ለክርስቶስ ምስጋና እናቀርባለን ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን፡፡
"+"የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት"+"

በጲላጦስ ዘመን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ በገባለት ቃል ኪዳን መሠረት፤ ትንቢቱም ይፈጸም ዘንድ መከራን ተቀበለ፤ ጲላጦስ በ፫ ሰዓት ይሰቅል ዘንድ ሲፈርድበትም፤ ‹‹መስቀሉንም ተሸክሞ በዕብራይስጥ ጎልጎታ ወደ ተባለው ቀራንዮ ወደሚባል ቦታ ወጣ›› (ዮሐ.፲፱፥፲፯) የራስ ቅል ስፍራ ቀራንዮ-ጎልጎታ አዳም ዐጽም የተቀበረበት ቦታ ነበር፡፡ በዚያም የአዳም መቃብር የሆነች ዋሻ አለች፤ የመስቀሉንም እንጨት በዚያ በምድር መካከል አይሁዶች ተከሉት፡፡
የአዳም አጽም ቀድሞ ከአዳም ትውልዶች ሲተላለፍ ከኖኅ ደርሷል፤ ኖኅም ወደ መርከብ እንደታቦት አስገብቶት በኋላ መልከጼዴቅ ቀብሮታል፡፡ ጌታችንም ከአዳም የራስ ቅል በላይ ሊያድነው መስቀል ተሸከሞ ተንገላታ፤ አይሁዶችም የቀራንዮን ዳገት እየገረፉ ከወደ ጫፍ አደረሱት፤ሁለቱንም እንጨት አመሳቅለው ዐይኖቹ እያዩ እጆቹንና እግሮቹን ቸነከሩት፤ በዕለተ ዐርብ ቀትር ፮ ሰዓት ላይም ተሰቀለ፡፡
ጌታችን የተሰቀለበት ሰዓት ፀሐይ በሰማይ መካከል በሆነ ጊዜ የጥላ መታየት በሚጠፋበት፤ ወደ ሰው ተረከዝም በሚገባበት ነበር፡፤ ከ፮ ሰዓት ጀምሮ እስከ ፱ ምድር ጨለመች፤ ፀሐይ፤ ጨረቃ፤ ከዋክብት ብርሃናቸውን ከለከሉ፤ ምክንያቱም የፈጣሪያቸውን ዕርቃኑን ይሸፍኑ ዘንድ ነበር፤ ‹‹ቀትርም በሆነ ጊዜ ፀሐይ ጨለመ፤ምድርም ሁሉ እስከ ፱ ሰዓት ድረስ ጨለማ ሆነ›› ማር.፲፭፥፴፫፡፡
በ፱ ሰዓት በቀኝ የተሰቀለው ወንበዴ ስለ ጌታችን በሰማይ ፫ት በምድር ፬ት ተአምራትን ሲያደርጉ አይቶ በእውነት አምላክ እንደሆነ አመነ፤ ‹‹አቤቱ በመንግሥት በመጣህ ጊዜ አስበኝ›› ባለ ጊዜ በግራ የተሰቀለው ዳክርስ ግን ‹‹እስቲ አምላክ ከሆነ እራሱን ያድን›› ብሎ ተዘባበተ፡፡ ፍያታዊ ዘየማን ግን ‹‹እኛስ በበደላችን ነው የተሰቀልን፤ እርሱ ግን ምንም ሳይበድል ነው፤ እንዴት በአምላክ ላይ ክፉ ነገርን ትናገራለህ›› ብሎ ገሰጸው ፤ፍያታዊ ዘየማንም ጌታችን በጌትነት መንበረ ጸባዖት(መንግሥት) ሆኖ ታየው፤እርሱንም አይቶ ‹‹ተዘከረኒ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ›› ቢለው ጌታችን ‹‹ዮም ትሄሉ ምስሌየ ውስተ ገነት›› ብሎ ደመ ማኅተሙን ሰጥቶታል፤ በኋላ ገነት ሲገባም መልአኩ አንተ ማነህ፤ አዳም ነህ፤ አብርሃም ወይንስ ይስሐቅ? እያለ ጠይቆታል፡፡
መልአኩ ሳያውቅ የጠየቀ ሆኖ አይደለም፤እንኳን በመጨረሻ የጸደቀ ፍያታዊ ቀርቶ በዘመናቸው የኖሩ ጻድቃንን ያውቃል፤ አዳምን ፤አብርሃምን፤ ይስሐቅን ሳያውቅ ቀርቶም አይደለም፡፡ ነገር ግን ሊቃውንት ሲተረጉሙት ‹‹አዳም ነህ›› ማለቱ የአዳምን ያህል ሥራ አለህን? አብርሃም ነህ ሲለው ደግሞ የአብርሃምን ያህል ሥራ አለህን? ለማለት ነው፡፡ ‹‹በጌታችን ኢየሱስ መስቀል አጠገብም እናቱ፤ የእናቱም እኅት፤ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም፤መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር›› (ዮሐ.፲፱፥፳፭) ‹‹እነርሱም ማርያም መግደላዊት፤ የታናሹ ያዕቆብ እና የዮሳ እናት ማርያም፤ የዘብዴዎስም የልጆቹ እናት ሰሎሜም ነበሩ›› (ማር.፲፭፥፵)፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ከተናገራቸው የአደራ ቃላት አንዱ እመቤታችን ለቅዱስ ዮሐንስ መሰጠቷ ነው፤ ለወዳጁ ዮሐንስ ከስጦታ ሁሉ ስጦታ የሆነች እናቱን እናት ትሁንህ ብሎ ሰጠው፤‹‹እነኋት እናትህ፤ እነሆ ልጅሽ›› (ዮሐ.፲፱፥፳፮)፡፡ በኋላ ወደ ቤቱ ወስዷት ፲፭ ዓመት ኖራለች፤ በዚህም የዮሐንስ ቤት በአቢዳራ ቤት ተመስላለች፤እመቤታችንም የሚያጽናናትን ወዳጁ ዮሐንስን ሰጥቷታል፡፡
የእመቤታችን ለዮሐንስ መሰጠት ቀድሞ በሙሴ አንጻር ጽላቷ ለሕዝቡ ሁሉ እንደተሰጠች፤በዮሐንስ አንጻርም እመቤታችን ለሁላችን ለምእመናን ተሰጥታናለች፡፡
፱ ሰዓት በሆነ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ፤አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ›› ብሎ በታላቅ ቃል ተናገረ፤ (ማር.፲፭፥፴፬)፡፡ በዚያም ቆመው የነበሩት ‹‹ አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ፤ ›› የሚለውን ድምጽ የሰሙ ኤልያስን ይጣራል እያሉ አሙት፤ ክህደትንም ተናገሩ፤ ያንጊዜ አንዱ ወታደር ሮጦ ሆምጣጤ የመላበት ዕቃ ተቀምጦ ነበርና በሰፍነግ መልቶ በሂሶጽም አድርጎ በአፉ ውስጥ ጨመረለት፡፡
በመስቀል ላይ ሳለ ጌታችን ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ሁሉ ተፈጸመ አለ፤ (ማር. ፲፭፥፴፯)፤ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በፈቃዱ ለየ፡፡
አይሁድም እኒህ ሰዎች እንደተሰቀሉ አይደሩ፤ ምክንያቱም ቀጣዩ ቀን ሰንበት ነውና ጭናቸውን ሰብረው ያወርዷቸው ዘንድ ጲላጦስን ጠየቁት፤ እርሱም ፈቀደላቸው፡፡ የሁለቱ ወንበዴዎች፤ ፈያታይ ዘየማንንና ፈያታይ ዘጸጋምን አብረው አወረዷቸው፤ ከጌታችን ዘንድ ቢቀርቡ ፈጽሞ ሞቶ አገኙት፤ በዚህም ጭኑን ሳይሰብሩት ቀሩ፡፡ ሌላው ግን የተመሰለው ምሳሌ ፍጻሜ ሲያገኝ ነው፤ የፋሲካውን በግ ‹‹አጥንቱን ከእርሱ አትስበሩ›› የተባለው አሁን ተፈጸመ፤ (በዘፀ.፲፪፥፲)፡፡ ከጭፍሮቹም አንዱ ቀኝ ጎኑን በጦር ወጋው እንዲል ከወታደሮቹ አንዱ የሆነው ለንጊኖስ የጌታችንን ጎን ቢወጋው ትኩስ ደምና ቀዝቃዛ ውኃ ፈሷል፡፡ ለንጊኖስ ጥንተ ታሪኩ አንድ ዐይኑ የጠፋ ሲሆን ጌታችን በተሰቀለበት ጊዜ ወደ ጫካ ሸሽቶ ርቆ ነበር፤ ምክንያቱም ከዚህ ሰው ሞት አልተባበርም በማለት ነው፡፡ አመሻሹ ላይ የአይሁድ አለቆች ሲመለሱ ከመንገድ አገኘቱ፤ ስለምን ከመሢሑ ሞት አልተባበርክም አሉት? እርሱም ምንም ስላላገኘሁበት አላቸው፡፡ ከዚያም በኋላ እንደሕጋቸው እንደሚቀጡት ቢነግሩት እየሮጠ ሔዶ የጌታችንን ጎን ሲወጋው ደሙ በዐይኑ ላይ ፈሰሰ፤ ያን ጊዜ ዐይኑ በራለት፤ ከጌታችን ጎን የፈሰሰው ደም እንደ ለ ቅርጽ ሆኖ በሁለት ወገን ደምና ውኃ ሆነ፡፡ ከጌታችንም የፈሰሰውን ትኩስ ደም መላእክት በጽዋ ቀድተው በዓለም ላይ ረጩት፤ ይህ መሠረት ሆኖ ዛሬ ቤተ ክርስቲያን የሚታነጸው የጌታችን ደም የነጠበበት ነው፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹አሁንም በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ›› ያለው (ሐዋ.፳፥፳፰)፡፡ ከጌታ ጎን የፈሰሰው ውኃ ደግሞ ምእመናን የልጅነት ጥምቀትን ስንጠመቅ ውኃውን ካህኑ ሲባርከው ማየ ገቦ ይሆናል፡፡
ቅዳሜ ከቀድሞው በተለየ መልኩ የጌታችንን መከራ በማሰብ በጾም ታስባ ስለምትውል የተሻረችው ቅዳሜ ትባላለች፤ ይህ ቅዳሜ ጌታችን ሥጋው በመቃብር የዋለበት በመሆኑ እኛም እንደ ሐዋርያት የትንሣኤውን ብርሃን ሳናይ እህል አንቀምስም በማለት በጾም ስለምናሳልፈው ነው፡፡
ቄጠማውንም ምእመናን እስከ ትንሣኤው ሌሊት በራሳቸው ላይ ያሰሩታል፤ የቄጠማው አመጣጥና ምሥጢርም ከአባታችን ከኖኅ ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፤ ምድር በጥፋት ውኃ በጠፋችበት ወቅት የኖኅ ታማኝ መልእክተኛ ርግብ የውኃውን መጉደል ያበሠረችው ቄጠማ ይዛ በመግባት ነው፡፡ ዛሬም ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች ኃጢአት ጠፋ፤
በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነፃነት ተሰበከና ታወጀ በማለት ካህናቱ ቄጠማ ይዘው ምእመናንን ያበስሩበታል፡፡
በዚህች ቅድስት ቅዳሜ፤ ቅዱስ የሆነ እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን አከናውኖ ከፈጠረ በኋላ፤ በዚህች ዕለት ከሥራው ሁሉ ያረፈባት ዕለት ናት፡፡ ጌታችን የተቀበረበትም ስፍራ ለተሰቀለበት ቦታ አቅራቢያ ነበር፤ ዮሴፍ ከኒቆዲሞስ ጋር ሆኖ ጌታችንን እንደፍጡር
በሐዘንና በልቅሶ ሲገንዙት የጌታችን ዐይኖች ተገለጡ ‹‹እንደፍጡር ትገንዙኛላችሁን? በሉ እንዲህ እያላችሁ ገንዙኝ፤ ቅዱስ እግዚአብሔር፤
ቅዱስ ኃያል፤ ቅዱስ ሕያው›› አላቸው፡፡
"+" ቀዳም ሥዑር (የተሻረች ቅዳሜ) "+"

ቀዳም ስዑር ለምለም ቅዳሜ፣ ቅዱስ ቅዳሜ
ትባላለች፡፡ ቀዳም ሥዑር መባሉ ከወትሮው
ዕለታት በተለየ ይህችኛዋ ዕለት በጾም ስለምትታሰብ የተሻረች ቅዳሜ እንላታለን፡፡
ለምለም ቅዳሜ መባሏም ካህናቱ የምሥራች
አብሳሪ የሆነውን ቄጤማ ይዘው ወደ
ምእመናን ቤት ስለሚሔዱ ለምለም ቅዳሜ
ትባላለች፡፡ ቅዱስ ቅዳሜ መባሉም ቅዱስ
እግዚአብሔር አምላካችን በጥንተ ተፈጥሮ
ሃያ ሁለቱን ስነ ፍጥረታት የሚታዩትንና
የማይታዩትን፣ በእግር የሚሄዱትን እና በክንፍ
የሚበሩትን፣ በባሕር የሚዋኙትንና
በመጨረሻም ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ
የፈጠረው በዕለተ ዐርብ ሲሆን ቅዳሜ ዕለት
ደግሞ ከሥራው ያረፈበት ዕለት ናት፡፡ በዘመነ
ሐዲስም የማዳን ሥራውን አከናውኖ በከርሰ
መቃብር አድሮ በአካለ ነፍስም ሲዖልን
በርብሮ ተግዘው የነበሩትን ነፍሳት ያወጣበት
ዕለት በመሆኑ ቅዱስ /ልዩ/ ቅዳሜ ተብላ
ተሰይማለች፡፡
ዕለቱ ዝርዘር አድርገን ስንመለከተውም ይህች
የመጀመሪያው ቅዳሜ ለእግዚአብሔር
የዕረፍት ዕለት ናት፤ እግዚአብሔር ሥነ
ፍጥረትን ፈጥሮ ስላረፈባት ሰንበት ዐባይ
(ታላቋ ሰንበት) ትባላለች (ዘፍ. 1፡3) ይህችን
ታላቋን ሰንበትም እንዲያከብሯት ሕዝበ
እግዚአብሔር የተባሉ እስራኤላውያን ታዘው
ነበር፡፡
ዕለተ ቀዳሚት (ሰንበት ዐባይ) በዘመነ
ሐዲስም የተለየ የድኅነት ሥራ
ተከናውኖባታል፡፡ ጥንት ሥነ ፍጥረትን
በመፍጠር ዕረፍት እንደተደረገባት ሁሉ
በሐዲስ ኪዳንም አዳምን ለማዳን ሕማምና
ሞት የተቀበለው ቸሩ አምላክ በሐዲስ
መቃብር አርፎባታል (ማቴ. 27፡61)፡፡
በዚህች ዕለት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ በከርሰ መቃብር ዐርፎ የዋለባት
ዕለት በመሆኗ በምሥጢር ከሰንበት ዐባይ ጋር
ትገናኛለች፡፡ ቀዳም ስዑር (የተሻረች ቅዳሜ)
የተሰኘችውም በዓመት አንድ ቀን
ስለምትጾም ነው፡፡ እናቱ ቅድስት ድንግል
ማርያም፣ ወዳጆቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታ
ተላልፎ ከተሰጠበት ዕለት አንስተው ብርሃነ
ትንሣኤውን እስከሚያዩ ድረስ እህል ውኃ
በአፋቸው አልዞረም፡፡ ይመኩበትና ተስፋ
ያደርጉት የነበረ መምህራቸው በመቃብር
ስላረፈ ዕለቷን ነገረ ሞቱን በማሰብና
ትንሣኤውን በመናፈቅ በጾም አክብረዋታል፡፡
ከቅዱሳን ሐዋርያት ሲወርድ ሲወራረድ
በመጣው ትውፊት መሠረት ቅዱሳን
ሐዋርያት በሐዘን፣ በጾምና በጸሎት ዕለቷን
እንዳከበሯት ክርስቲኖችም የተቻላቸው
ከዓርብ ጀምረው በማክፈል፣ አሊያም ዓርብ
ማታ በልተው ቅዳሜን በመጾም የጌታን
ትንሣኤን ያከብራሉ፡፡
ቅዳሜ ጧት ምእመናኑና ካህናቱ ወደ ቤተ
ክርስቲን ይሰበሰባሉ፡፡ የጧቱ ጸሎት ሲፈጸም
”ገብረ ሰላመ በመስቀሉ” በመስቀሉ ሰላምን
መሠረተ፣ ሰላምን ፈጠረ፤ የምሥራች እየተባለ
በቤተ ክርስቲያን ለተሰበሰበው ሁሉ ቄጠማ
ይሰጣል፡፡ የምሥራች ምልክት ነው፡፡
ምእመናኑም እየሰነጠቁ በራሳቸው
ያስሩታል፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን ላልመጡት
ምእመናንም ካህናት በየሰበካቸው ልብሰ
ተክህኖ ለብሰው መስቀልና ቃጭል ይዘው
ቄጠማውን የምሥራች እያሉ ያድላሉ፡፡
የዚህ የቄጠማው ታሪክ መነሻው የኖኅ ዘመን
ታሪክ ነው፡፡ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን
በጻድቁ ኖኅ ዘመን የነበሩ ሰዎች በማየ አይህ
ከጠፉ በኋላ የውኃውን መጉደል
እንድትመለከት የተላከች ርግብ የምሥራች
ምልክት የሆነ ለምለም ቄጠማ በአፏ ይዛ
ተመልሳለች፡፡ በዚህም የውኃው መጉደል፣
የቅጣቱ ዘመን ማለፍ ተረጋግጧል (ዘፍ. 9፡
1-29)፡፡
ቄጠማ ለጥፋት ውኃ መድረቅ የምሥራች
መንገሪያ እንደሆነው ሁሉ አሁንም በክርስቶስ
ሞት መተ ነፍስ ከሰው ልጆች ተወገደ ስትል
ቤተ ክርስቲያን ለልጆቿ ቄጠማ ታድላለች፡፡
ምእመናንም የምሥራች ተምሳሌት የሆነውን
ቄጠማ በግንባራቸው ያስሩታል፣ በጣታቸው
ቀለበት ያደርጉታል፡፡
የክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ ከጨለማ
ወደሚደነቅ ብርሃን፣ ከሚያቃጥለው ዋዕየ
ሲዖል (የሲዖል ቃጠሎ) ወደ ልምላሜ ገነት፣
ጥንተ ማኅደራቸው መመለሳቸውን በዚህ
አኳኋን እየገለጡ በዓለ ትንሣኤን በቅድስት
ቤተ ክርስቲያን ያከብራሉ፡፡
ወንድሞቼና እህቶቼ እነሆ ስለ ቀዳም ስዑር
(የተሻረች ቅዳሜ) በማስመልከት ከስምዐ
ተዋሕዶ የስምዐ ጽድቅ ልዩ እትም ዘሰሙነ
ሕማማት፣ ማኅበረ ቅዱሳን፣ ሚያዝያ 2004፣
አዲስ አበባ ያገኘሁትን ስብከት
እንደሚከተለው ላካፍላችሁ፡፡
ቅዳሜ ቀዳም ሥዑር ይባላል፡፡ በዚች ዕለች
ከድሮው በተለየ መልኩ የጌታችንን መከራ
በማሰብ በጾም ታስባ ስለምትውል የተሻረችው
ቅዳሜ ትባላለች፡፡
የማትጾመዋ ቅዳሜ ስለምትጾም ስዑር /
የተሻረች/ ተብላለች በዓል መሻርን
አይመለከትም በቀዳም ሥዑር ሌሊት ሥርዓቱ
የሚጀመረው በመኀልየ ሰሎሞን ምንባብ
ነው፡፡ ማኀሌቱም እዝሉ እየተቃኘ
እየተመጠነ፣ እየተዘመመ እየተመረገደ
እየተጸፋ ያድራል፡፡ ጥዋት አቡን መዋሥዕት
ውዳሴ ማርያም ዜማ ተደርሶ ወለመልአከ
ሕይወትሰ ሰቀልዎ በሚለው ሰላም
ይጠናቀቃል፡፡በዚህ ዕለት ልብሰ ተክህኖ የለበሱ
ካህናትና ዲያቆናት ቄጤማ ተሸክመው ቃጭል
ሲያቃጨሉ መታየታቸው ዕለተ ትንሣኤውን
ለሚናፍቅ ምእመን ትልቅ ብስራት ነው፡፡
ለምለም ቅዳሜ፡- ካህናቱ ለምእመናን
ለምለም ቀጤማ የሚያድሉበት ዕለት ስለሆነ
በዚህ ተሰይሟል፡፡ ቀጤማውንም ምእመናን
እስከ ትንሣኤ ሌሊት በራሳቸው ላይ
ያስሩታል፡፡
በቀዳም ስዑር ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ
ቃጭል /ቃለዓዋዲ/ እየመቱ ገብረ ሰላመ
በመስቀሉ ትንሣኤሁ አግሃደ የሚለውን
ያሬዳዊ ዜማ በመዘመር፤ ጌታ በመስቀሉ
ሰላምን እንደሰጠን እና ትንሣኤውንም
እንደገለጠልን በማብሰር፤ ቄጤማውን
ለምእመናን ይሰጣሉ፡፡
ምእመናኑም በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት
የሚውል ገጸ በረከት ያቀርባሉ፡፡
ቄጤማውንም በራሳቸው ያስራሉ፡፡ ይህም
አይሁድ ጌታችንን እያሰቃዩ ሊሰቅሉት ባሉ ጊዜ
የእሾህ አክሊል ጭንቅላቱ ላይ ያሠሩበትን
ድርጊት የሚያስታውስ ነው፡፡
የቀጤማው አመጣጥና ምስጢርም
ከአባታችን ከኖኅ ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡
ምድር በማየ አይኅ /በጥፋት ውኃ/ በጠፋችበት
ወቅት የኖኅ ታማኝ መልእክተኛ ርግብ
የውኃውን መጉደል ያበሰረችው ቀጤማ ይዛ
በመግባት ነው፡፡
ዛሬም ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች የኃጢአት
ውኃ ጐደለ፣ የኃጢአት ውኃ ጠፋ በክርስቶስ
ሞትና ትንሣኤ ነጻነት ተሰበከ ታወጀ በማለት
ካህናት ቄጠማ ይዘው ምእመናንን
ያበሥሩበታል፡፡
ቅዱስ ቅዳሜ ይባላል፡፡ ቅዱስ ቅዳሜ መባሉ
ቅዱስ የሆነ እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ
ፍጥረታትን አከናውኖ ከፈጠረ በኋላ በዚህ ቀን
ከሥራው ሁሉ ያረፈበት ነው፡፡ በዘመነ ሐዲስ
ደግሞ የማዳን ሥራውን ሁሉ ፈጽሞ በሥጋው
በመቃብር ሲያርፍ፣ በነፍሱ ሲዖልን በርብሮ
ባዶዋን አስቀርቷታል፡፡ በዚያ ለነበሩት
ነፍሳትም የዘለዓለም ዕረፍትን ያወረሰበት
ዕለት ስለሆነ ከሌሎቹ ዕለታት የተለየ ዕለት
ለማለት ቅዱስ ቅዳሜ ተብሏል፡፡
ምእመናን ሆይ፣ በአጠቃላይ ሥርዓተ
ሕማሙን፤ ሰሙነ ሕማማት ብለው የተለየ
ሥርዓት አውጥተው አባቶቻችን ተግተው
ያቆዩልንን ሥርዓተ መላእክት ልንጠብቀውም
ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ የዕለታቱን ክብርና
ስያሜ ከማወቅና ከመረዳት ጋር በዕለታቱ
የታዘዙትን ሃየማኖታዊ ግዴታዎችን መወጣት
ከሁላችንም ይጠበቃል፡፡
ያብጽሐነ ያብጽሕክሙ እግዚአብሔር በሰላም
ከበዓሉ ረድኤት በረከት ያሳትፈን፣ አሜን፡፡
➬ † እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላምና በፍቅር አደረሳችሁ በመላው አለም ለምትገኙ ኢትዮጵያውያን የእምነቱ ተከታዮች በሙሉ †
† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †
† # ብርሃነ_ትንሣኤ †
➬†#የዓለማት_ሁሉ_ፈጣሪ_የዘለዓለም_አምላክ_ወልድ_ዋሕድ_ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በዚህች ዕለት መግነዝ ፍቱልኝ : መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በባሕርይ ኃይሉና ሥልጣኑ ተነስቷልና እንኳን ደስ አለን::
††† ከዚህ በኋላ ለ50 ቀናት እንዲህ እያልን ሰላምታ እንለዋወጣለን:-
††† ክርስቶስ ተንስአ እሙታን!
¤በዐቢይ ኃይል ወስልጣን!
††† አሠሮ ለሰይጣን!
¤አግዐዞ ለአዳም!
††† ሰላም!
¤እምይእዜሰ!
††† ኮነ!
¤ፍሥሐ ወሰላም!
በእርግጥም አምላካችን በሞቱ ሞትን ገድሎ : በትንሣኤው ሕይወትን አድሎናልና ደስታ ይገባናል:: መድኃኔ ዓለም በኅቱም ድንግልና እንደ ተወለደ በኅቱም መቃብር ተነስቷል:: ለደቀ መዛሙርቱም "ሰላም ለእናንተ ይሁን" ሲል
በዝግ ደጅ ገብቷል::
በዕለተ ትንሣኤው የመጀመሪያውን ደስታ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም
ተካፍላለች:: የእርሷን ያህል በሃዘን የተጐዳ የለምና:: ቀጥለው ቅዱሳት አንስት
እነ ማርያም መግደላዊት ትንሣኤውን አይተዋል:: ሰብከዋልም::
††† በዚሕች ቀን ማዘን አይገባም:: በትንሣኤው የደነገጡና የታወኩ የአጋንንትና የአይሁድ ወገኖች ብቻ ናቸውና::
††† አምላካችን ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤው በረከት አይለየን:: በዓሉንም የሰላም : የፍቅርና የበረከት ያድርግልን::
††† የጌታችን በጐ ምሕረቱ በሁላችን ትደርብን::
††† "ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነስቷል እንጂ በዚህ
የለም:: 'የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ሊሰጥና ሊሰቀል: በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ግድ ነው' እያለ ገና በገሊላ ሳለ ለእናንተ እንደተናገረ አስቡ::" †††
(ሉቃ. ፳፬፥፭-፰)
††† "አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነስቷል:: ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኗልና:: ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና::" †††
(፩ቆሮ. ፲፭፥፳)
††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
"+"ነገረ ሃይማኖት"+"

የነገረ ሃይማኖት ትምህርት አጠር ተደርጎ የቀረበ፡-
ክፍል ፩
........ ....... ...... ...... ...... ...... ...... ..........
ሃይማኖት እምነትና መታመን
................ .. ... ... ..... . . ........ ... ..........

"+"ሃይማኖት"+"

ሃይማኖት ማለት ምን ማለት ነው?

+ ሃይማኖት ማለት "ሃይመነ" ከሚለው የግእዝ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጓሜውም "ማመን መታመን" ማለት ነው፡፡

ሃይማኖት ምንድነው?

+ ሃይማኖት እግዚአብሔር ራሱን ለሰው ልጅ የገለጠው መገለጥ ነው። እግዚአብሔር ባህሪው ረቂቅ አኗኗሩ ምጡቅ ስለሆነ የሰውም ሆነ የመላዕክት አእምሮ ተመራምሮ ሊደርስበትና ባሕሪው እንዲህ ያለነው አኗኗሩ እንዲህ ያለነው ይህን ይመስላል ሊለው የማይችለው ነው።እርሱ በጊዜና በቦታ የማይወሰን ዘላለማዊና ምሉዕ ሲሆን ፍጥረቱ ግን በጊዜና በቦታ የተወሰነ ስለሆነ ውስኑ የማይወሰነውን ሊየውቀውና በምርምር ሊደርስበት አይችልም።
.
ሆኖም ግን ምንምእንኲዋ እግዚአብሔር በባርሪውና በአኗኗሩ በራሱ ብቻ የሚታወቅ ረቂቅ አምላክ ቢሆንም እኛ ፈጽመን የማናውቀው እና ስለ እርሱ ምንም ፍንጭ የሌለን ሆነን እንድንቀር አልተወንም። ከቸርነቱ የተነሳ አቅማችን ሊረዳው በሚችለው መጠን ማንነቱን፣ህላዌውን ፣ባህሪውን፣ መግቦቱን፣ ፈታሒነቱን፣ ፈቃዱን... እናውቅ ዘንድ በተለያየ መጠን ገልጦልናል። ሃይማኖት የሚባለው ይህ እግዚአብሔር በራሱ ፈቃድ እናውቀው ዘንድ ስለራሱ የገለጠው መገለጥ ነው።ስለሆነም ሃይማኖት እግዚአብሔር ራሱን ለእኛ ያሳየበት መንገድ፣የሰው ልጅ ሊቀበለው በሚችለው መጠን ስለራሱ ማንነት ለእኛ የገለጠው እውነታ ነው።
.
እግዚአብሔር አንድ ስለሆነ፣ባህሪውም የማይለወጥ ስለሆነ ሃይማኖት አንድና የማይለወጥ ነው። ስለዚህም ሊኖር የሚችለው ብቸኛ ሃይማኖት አንድ ብቻ!ነው። ብዙ ሃይማኖቶች አሉ ማለት ግን ወይ እግዚአብሔር በተለያየ ጊዜ የተለያየ ነገር ይናገራል ማለትን፣ አለዚያም ደግሞ ባህሪው ይለዋወጣል የሚለውን ያስከትላል፤ ሆኖም እነዚህ አነጋገሮች ለእግዚአብሔር ሊነገሩ ቀርቶ ፍጹም ጸያፎች ናቸው። እርሱ በተለያየ ጊዜ እርስ በእርሱ የሚቃረን የተለያየ ነገ አይናገርምና። መለወጥ የፍጡር ባህሪ እንጂ የፈጣሪ አይደለምና። ስለዚህ ሃይማኖት እንድ ብቻ ነው።መጽሐፍ ቅዱስም"አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት" የሚለው ለዚህ ነው። ኤፌ ፬፥፭
... ይቀጥላል
…/…/…/…/…/…/…/…/…/……//…/…/………

በየእለቱ አጥንትን የሚያለመልሙ መንፈሳዊ ጽሁፎችን ለማግኘት ይቀላቀሉን፡-
👉 @rituaH @rituaH
👉 @rituaH @rituaH
👉@rituaH @rituaH
"+" ነገረ ሃይማኖት "+"

የነገረ ሃይማኖት ትምህርት አጠር ተደርጎ የቀረበ፡-
ክፍል ፪

"+" እምነት "+"
……………………///………………………
እምነት እግዚአብሔር የገለጠውን እውነት (ሃይማኖት) አዎ እውነት ነው ትክክል ነው ብሎ "አሜን" ብሎ መቀበል ነው። ይህ ሲባልግን በሰዎች መቀበልና አለመቀበል የተወሰነ አይደለም።ምንጊዜም እውነት ነውና "ባናምነውም እርሱ እንደታመነ ይኖራል፤ራሱን ሊክድ አይችልምና" እንዳለ 1ኛ ጢሞ 3፤3
ነገር ግን ይህን እግዚአብሔር ስለ ባህሪው፣ ስለመግቦቱ በአጠቃላይ እኛ ልናውቀው የምንችለውን ያህል በአባታዊ ቸርነቱ የገለጠው እውነት (ሃይማኖት) እውነት ነው ብለን ስንቀበለው እምነት ይሆናል። ይህ ማመንም ከእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ የሚያስገኝ ይሆናል። ለምሳሌ እግዚአብሔር ከአብርሃም ዘር በመወለድ በዕፅ የተረገመውን አለሙን በእፀ መስቀል ላይ በመሰቀል ይባርከው ዘንድ ፈቃዱ ነበር። ይኽ የማይለወጥና የማይናወጽ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። እግዚአብሔር ይህን እውነት ለአብርሃም ሲገልጥለት በ99አመቱ ልጅ እንደሚወልድና በእርሱ ዘርም አህዛብ ሁሉ እንደሚባረኩ ሲነግረው 'ሸምግያለሁ ይህ እንዴት ይሆናል?' ብሎ ሳይጠራጠር ስላመነ "አብርሃም አመነ እምነቱም ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት" ተባለ። ዘፍ 15፥3-6
በጸሎትና ነገረ ሃይማኖት በሚናገሩ አንቀጾች መሃልም ሆነ መጨረሻ ላይ "አሜን" የሚለው ቃል የጸሎትና የእምነት መግለጫ ማሳረጊያ ሆኖ የሚነገረው ለዚህ ነው። ጸሎት ሲሆን የተጸለየው ጸሎት ይሁንልን ይደረግልን ለማለት የተነገረው ወይም የተነበበው ነገረ ሃይማኖት ሲሆን ደግሞ አዎ እኔም ይህንኑ አምናለሁ የማምነው ይኸው ነው ለማለት ነው። ለምሳሌ ቅ.ጳውሎስ " ክርስቶስ በስጋ መጣ እሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘልአለም የተባረከ አምላክ ነው"፦የሚለውን አዎ እውነት ነው የእኔም እምነት እንደዚሁ ነው ለማለት ነው።

"+" መታመን "+"
………………///……………………………
መታመን ሲባል እግዚአብሔር የሰጠው ቃልና እውነት ተስፋ ለእኔም ይሆንልኛል ይደረግልኛል እርሱ ያድነኛል ይመግበኛል ብሎ ሙሉ ተስፋንና ተአምኖን እሱላይ ማድረግ ነው። ቃሉ ከእምነት ጋር ተቀራራቢነት ያለው ቢሆንም በተለይም በራሳችን ላይ የሚደርሱ ነገሮችን ለመቀልና ለማሸነፍ በእግዚአብሔር ረዳትነትና እዳኝነት ላይ ያለንን የእምነት መጠን የሚገልጽ ነው። ለምሳሌም ሰለስቱ ደቂቅ በፊታቸው አስፈሪ የሆነ እሳት እየተንቀለቀለ እያዩ " የምናመልከው አምላካችን ከሚነደው እቶን እሳት ያድነናል፤ ባያድነን እንኲዋ አንተ ላቆምከው ለወርቅ ምስል አንሰግድም" ብለው ወደ እሳቱ እስከ መግባት ደርሰው በእርሱ ቷምነዋል። ት.ዳን 3፥16-18
ባያድነን እንኲዋ ማለታቸው አዳኝነቱን ወይም የሚያድን መሆኑን የመጠራጠር ስይሆን አንደኛ የእግዚአብሔር ፈቃድ እነርሱ በሰማዕትነት ሞተው እንዲያከብሩት ይሁን ወይም ሌላ ስላላወቁ፣ ሁለተኛ ደግሞ በሃጥያታቸው ምክያት ሳያድናቸው ቢቀር ያላዳናቸው እሱ ማዳን የማይችል ሳይሆን በእነርሱ ለማዳኑ የበቁ አለመሆን ምክንያት ስለሚሆን ነው። ነገር ግን አረማዊው ንጉሥ ንቡ ከደነጾር ይህንን ሁሉ ቢነግሩት የማይገባው ስለሆነ " ባያድነን እንኲዋ " የሚለውን ጨመሩለት ከእሳቱ ባያድናቸው አምላካቸውን እግዚአብሔርን ማዳን የማይችል አድርጎ እንዳይረዳ ለጥንቃቄ የተናገሩት ነገር ነው። ስለዚህ መታመን ሁለንተናችንን በእግዚአብሔር አዳኝነትና አባትነት ጥላ ስር ማሳረፍ ነው።
……………………////……………………
ሁል ጊዜም ክርስቶስን በማመን በጸናች በቅዱሳን አባቶቻችን ሃይማኖት ጠብቆ ያቆየን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር።
ይቀጥላል...
-----------------------------------
በየእለቱ አጥንትን የሚያለመልሙ መንፈሳዊ ጽሁፎችለማግኘት ይቀላቀሉን፡-
👉 @rituaH @rituaH
👉 @rituaH @rituaH
👉 @rituaH @rituaH
2024/06/15 15:26:50
Back to Top
HTML Embed Code: