Telegram Web Link
#ቅድስት
#የዐቢይ_ጾም_ሁለተኛ_ሳምንት

የቅድስና ባለቤት የሆነው እርሱ እግዚአብሔር አምላክ ነው። እቀደስ አይል ቅዱስ፣ እባረክ አይል ቡሩክ ነው። በእርሱ የባሕርይ ቅድስና እኛን በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮ ቡሩክ ሆኖ ባረከን፣ ቅዱስ ሆኖ ቀደሰን፣ሕያው ሆኖ ሕያዋን አደረገን። የጸጋ ቅድስናንም ከእርሱ አገኘን። ቅድስናው የተለየ፣ የከበረ፣ የሚመሰገን፣ የሚሰጥ/የሚያድል፣ የሚያነጻ፣ የሚባርክ እናም የሚያስተሰርይ ስለሆነ እንከን፣ ጉድለት የሌለበት ምሉዕ ነው። ለባለሟሎቹ ቢሰጠው የማይጎድል፣ ተከፍሎ የሌለበት ቅድስና ሆኖ እኛም የቅድስና በጸጋ ተካፋይ ሆነናል።

የተሰጠንን ቅድስና ገንዘብ እንድናደርግ እና እንድንጠቀምበት ደግሞ በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ በምጽዋትና በሌሎች በጎ ምግባራት መትጋት ይገባናል። ‹‹እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ›› እንዲል፡፡ (ዘፍ.፪፥፫፣ ዘሌ.፲፱፥፪) የት መሄድ እንዳለብንም በግልጽ ልበ አምላክ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ‹‹ወደ ቅዱስ መቅደስህ እሰግዳለሁ፤ ስለ ትምህርትህና ስለ እውነትህ ስምህን አመሰግናለሁ፤ በሁሉ ላይ ቅዱስ ስምህን ከፍ ከፍ አድርገሃልና›› ይላል። (መዝ.፻፴፯÷፪) የተቀደሰን መሥዋዕት በተቀደሰ ቦታ እንፈጽማለን። መቼ ቢሉ፣ በሰንበት፣ በበዓላት በማኅበረ ዐቢይ/ክርስቲያኖች በሚሰበሰቡበት፣ ስመ እግዚአብሔር በሚጠራበት፣ ታቦት  ባለበት፣ እግረ እግዚአብሔር በቆመበት ቅዱስ ስሙን ከፍ ከፍ በማድረግ ቅድስናን ገንዘብ እናደርጋለን።

ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ለዐቢይ ጾም ሁለተኛው እሑድ በአዘጋጀው ምስጋና አማካኝነት ዕለቱ ‹‹ቅድስት›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ትርጉሙም ‹‹የተለየች፣ የተመረጠች፣ የከበረች›› ማለት ነው።  (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ገጽ ፯፻፹፬) ቅድስት የሚለው ቃል ዕለቱ ‹‹ቅድስት›› ተብሎ የተሰየመበት ምክንያት ስለ ዕለተ ሰንበት እንዲሁም ስለ እግዚአብሔር አምላክ ፍጹም ቅድስና የሚያወሳ በመሆኑ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክም ፍጥረታቱ የእርሱን ስም በማመስገን ይኖሩ ዘንድ ለቅድስና ሕይወት ፈጥሯቸዋልና በሰንበት እሑድ ክርስቲያኖች የቅድስና ተግባራትን ከሌላው ቀን አብዝተው ይፈጽማሉ፡፡ ዕለት ከተግባር፣ ስም ከክብር የተባበረባት ክብርት ሰንበት ቅድስት ስለሆነች ቅዱስ ያሬድ “ቅድስት” ብሎ ጠራት። ይኸውም የምትቀድስ፣ ከብራ የምታከብረን፣ አክብረናት የምንከብርባት በመሆኗ ነው።

ለዚህም ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓ “ግነዩ ለእግዚአብሔር ወጸውዑ ስሞ ወንግርዎሙ ለአሕዛብ ምግባሮ፤ ሀቡ ስብሐተ ለስሙ፤ አክብሩ ሰንበተ ተገበሩ ጽድቀ፤ ዝግቡ ለክሙ መዝገበ ዘበሰማያት ኀበ ፃፄ ኢያማስኖ ወኢይረክቦ ሰራቂ፤ ድልዋኒክሙ ንበሩ ዘበላዕሉ ጸልዩ ኀበ ሀሎ ክርስቶስ” ትርጉም፦ “ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ስሙንም ጥሩ፤ ሥራውንም ለአሕዛብ ንገሯቸው፤ ለስሙም ምስጋናን አቅርቡ ሰንበትን አክብሩ፤ እውነትንም አድርጉ፤ ብል የማያበላሸው ሌባም የማያገኘው በሰማያት ያለ መዝገብን ለእናንተ ሰብስቡ፤ ተዘጋጅታችሁም ተቀመጡ፤ ክርስቶስ ወዳለበት ወደ ላይ አስቡ፡፡“  ስለዚህ ሰው ሰንበትን አክብሮ ጾሞ ጸልዮ፣ ቅድስናን ጠብቆ መኖር እንዲችል እግዚአብሔር የፍቅሩ መገለጫ የሆኑ ትእዛዛቱ ይነግሩናል።

#ቅዱስ_ያሬድም_ወቅቱን#ቅድስት” ብሎ ሲሰይም፦

፩.
#የአርባ_ቀን_ጾም_መጀመሪያ_በመሆኑ፦ ዕለቱ ከዐቢይ ጾም ቀናት ውስጥ አርባው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ጾም መጀመሪያ ስለሆነች፣

፪.
#ቅድስት_ሰንበት_ላይ_በመዋሉ፣ እንግዲህ “የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ” ተብሏል፡፡ (ዘፀ.፳፥፰) የሰንበትን ቀን አስቀድሞ የቀደሰ የባረከ ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔርም ሰባተኛውን ቀን ባረከው፤ ቀደሰውም፤ እግዚአብሔር ሊያደርገው ከፈጠረው ሥራ ሁሉ በእርሱ ዐርፎአልና፡፡” (ዘፍ.፪፥፫)

“ከምእመናን ወገን አንድስ እንኳን በእሑድ ቀን ለገንዘብ መትጋት፣ ገንዘቤን አምጣ ብሎ መጣላት እና ዋስ መያዝ አይገባውም። ሁሉም ምእመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን በንጽሕና በትሕትና ሆነው። ዳኛ ግብሬን፣ አበዳሪ ብድሬን፣ ኤጲስ ቆጶስ ዐሥራት በኵራት፣ ነጋ ድራስ ቀረጥ አምጡ ይሉናል ብለው ሳይፈሩ ይምጡ።

፫.
#ወቅቱ_ወርኃ_ጾም_በመሆኑ፦ ምእመናን ይህንን ወቅት በጾም፣ በጸሎት፣ በእንባ፣ በስግደት፣ በአርምሞ፣ በመልካም ሥራ ቅድስናን የምናገኝበት፣ ጊዜው ሰው ወደ እግዚአብሔር አብዝቶ የሚተጋበት ወቅት በመሆኑ፣ ለእግዚአብሔር የሚገባ ነገር ለማድረግ የነገር ሁሉ መጀመሪያ፣ ለመልካም ነገር መነሻው በቅድስና በንጹሕ ልቡና መቅረብ ስለሆነ ቅድስት ብሏታል።  “እስመ ጾም እማ ለጸሎት ወእኅታ ለአርምሞ ወነቅዓ ለአንብዕ መቅድመ ኩሉ ግብር ሠናይት፤ ጾም ማለት የጸሎት እናት፣ የትሕትና እኅት፣ የእንባ ምንጭ፣የመልካም ሥራ ሁሉ መጀመሪያ ናት” እንዳለው ቅዱስ ያሬድ። ”ጾምን ቀድሱ፤ ጉባኤውንም ዐውጁ” የተባልን የተሰጠንን የጸጋ ቅድስና በእጃችን ላይ መኖሩን አመላካች ቃል ነው። (ኢዩ.፩፥፲፬)

፬.
#የወንጌል_ትእዛዝ_በመሆኑ፡ ዕለቱን ተጠቅሞ ዓለምን አስተምሮበታል። “ዛቲ ዕለት እንተ ገብረ እግዚአብሔር ንትፈሣሕ ወንትሐሠይ ባቲ”  ትርጉም፡- “ይህች ዕለት እግዚአብሔር የሠራት ቀን  ናት፤ ሐሤትን እናድርግ፥ በእርስዋም ደስ ይበለን።” (መዝ.፻፲፯፥፳፬) ቅዱስ ዮሐንስም በራእዩ ሰንበት የጌታ ቀን ስለመሆኗ እንዲህ ይላል፤ “በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ፡፡” (ራእ. ፩፥፲)

ሊቃውንቱ በፍትሐ ነገሥት “ተጋብኡ ኵሎ ዕለት ኀበ ቤተ ክርስቲያን ወፈድፋደሰ በዕለተ ሰንበት ወበበዓላት ወበዕለተ ትንሣኤ ዘውእቱ ዕለተ እሑድ” ትርጉም፦ “ሁልጊዜ በቤተ ክርስቲያን ተሰብሰቡ፤ ይልቁንም በዕለተ እሑድ፣ በዕለተ ቀዳሚት፣ በጌታ በዓላት ወደ ቤተ ክርስቲያን ተሰብሰቡ” በማለት አዘውናል፡፡ (ፍትሐ ነገሥት፣ ገጽ ፪፶፬)

በትጋት ጾመን፣ ጸልየን ርስቱን እንድንወርስ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃ፤ የቅዱሳን በረከት ይጠብቀን።

የዕለቱ መዝሙር (ከጾመ ድጓ)፦ ግነዩ ለእግዚአብሔር

#ምንባባት
➛ ፩ኛ ተሰ.፬÷፩-፲፫
➛ ፩ኛ ጴጥ.፩÷፲፫-ፍጻ.
➛ ሐዋ. ፲÷፲፯-፴

#ምስባክ
“እግዚአብሔርሰ ሰማያተ ገብረ::
አሚን ወሠናይት ቅድሜሁ፣
ቅድሳት ወዕበየ ስብሐት ውስተ መቅደሱ፤

(እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ፈጠረ፡፡ እምነትና በጎነት በፊቱ፣ ቅድስናና የክብር ገናናነት በመቅደሱ ውስጥ ናቸው፡፡”
(መዝ.፺፭÷፭)

#ወንጌል
(ማቴ.፮÷፲፮-፳፭)

#ቅዳሴ
ዘኤጲፋንዮስ 

(ማኅበረ ቅዱሳን)

ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE

    
https://www.tg-me.com/sratebetkrstyane
ካህኑ ለምን በእጁ ያሳልሙናል ?

የካህኑን እጅ መሳለም አንዳንድ ሰዎች ካህኑ ለምን በእጁ ያሳልመናል ይላሉ። ነገር ግን ሚስጢሩ ይህ ነው
የካህኑ እጅ እኮ እሳታዊያን የሆኑ መላእክት መንካት
የማይቻላቸውን ቅዱስ ሥጋውን ክብር ደሙን የዳሰሱበት
ነው።
በቅዳሴ ላይ ቅዱስ ሥጋውን መንካት የሚችለው ዋናው ካህን ብቻ ነው ፤ ሁለተኛው ካህን እንኳን መንካት አይችልም።
ቅዱስ ሥጋውን ክብር ደሙን የዳሰሰበት ስለሆነም ካህኑ በእጁ ያሳልመናል እኛም የተቀደሰውን የጌታ ስጋና ደም
የዳሰሱበት እጅ እየተሳለምን አሜን አሜን አሜን እንላለን።

ድንቅ መለኮታዊ ሚስጥር ማለት
እንዲህ ነው

አንሥኡ እደዊክሙ ቀሳዉስ
ዲያቆኑ ይህን በሚልበት ጊዜ ንፍቀ ካህኑ ማሕፈዱን
ከጻሕሉ ላይ ያነሳል ፤ ይህም የጌታ መላአክ የመቃብሩን
ድንጋይ የማከባለሉ ምሳሌ ነው።ከዚህ በኋላ ጌታችን
በምሴተ ሐሙስ ሕብስቱን እንደያዘው ዋናዉ ካህንም
ሕብስቱን ከፍ አድርጎ ይይዘዋል ፤ ይህም የጌታ ትንሳኤ ምሳሌ ነው።

እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ
በእግዚኦታ ላይ ካህኑ ሕብስቱን ይበልጥ ከፍ አድርጎ
ይይዘዋል ይህም የዕርገቱ ምሳሌ ነው።ከካህኑ ጋር ሆነን
41 ግዜ እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ እንላለን ፤ ይህም አርባው እግዚኦታ አይሁድ ጌታችንን 40 ግዜ እንገርፋለን ብለው እያዛቡ ብዙ ጊዜ የመግረፋቸው ምሳሌ ሲሆን በመጨረሻ ካህኑ ብቻውን የሚላት እግዚኦታ ደግሞ የአዳምና የሔዋን የንስሃ ምሳሌ ነው። 12 ግዜ እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ ስንል ደግሞ ስለስምህ ብለህ ይቅር በለን ነው። አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የሚለውን እያንዳንዱን ፊደል ስንቆጥር 12 ይሆናል!!! እንዲሁም 12 ጊዜ በእንተ እግዚትነ ማርያም መሐረነ ክርስቶስ ስንልም ደግሞ ስለእናትህ ብለህ ማረን ማለታችን ሲሆን ቅድስት ድንግል ማርያም የሚለውን እያንዳንዱን ፊደል ስንቆጥር 12 ይሆናልና

ወንጌል
የመጀመሪያዉ መልዕክት ሲነበብ ዲያቆኑ ፊቱን ወደ ምዕራብ አዙሮ ያነባል፡ ሁለተኛው ዲያቆን ፊቱን ወደ ሴሜን አዙሮ ያነባል ፡ ንፍቀ ካህኑ ወደ ደቡብ ዙሮ ያነባል የሐዋርያት ሥራ ሲያነብ ዋናው ካህን ደግሞ ወደ ምስራቅ ዙሮ ወንጌል ያነባል ፤ ይህም ግሩም የሆነ ምሳሌ አለው አንድም ወንጌል በአራቱም አቅጣጫ መስበኩን ለመግለጽ ነው አንድም ገነትን የሚጠጡ 4 ወንዞች አሉ ኤፍራጠስ ጤግሮስ ጊዮን (አባይ) እና ፊሶን ናቸው። ገነትን አጠጥተው ለምለም እንደሚያደርጓት ጌታችንም የተጠማ ቢኖር የህይወት ውሃ በነፃ ይጠጣና ይርካ እንዳለው ወንጌልም እንዲሁ ያለመልማል ሲሉ ነው።

ቤተክርስቲያን ከጣራዋ እስከ መሬቷ ሁሉም ስርዓቷ
ያስተምራል ፤ ባህረ ጥበብ ቤተክርስቲያን እየተናገረች
ታስተምራለች ሳትናገርም ዝም ብላ ታስተምራለች!!!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለ ወላዲቱ ድንግል
ወለ መስቀሉ ክብር ይቆየን
https://www.tg-me.com/sratebetkrstyane
✝️ስርዓተ ቤተክርስቲያን መመሪያ ✝️ pinned «ካህኑ ለምን በእጁ ያሳልሙናል ? የካህኑን እጅ መሳለም አንዳንድ ሰዎች ካህኑ ለምን በእጁ ያሳልመናል ይላሉ። ነገር ግን ሚስጢሩ ይህ ነው የካህኑ እጅ እኮ እሳታዊያን የሆኑ መላእክት መንካት የማይቻላቸውን ቅዱስ ሥጋውን ክብር ደሙን የዳሰሱበት ነው። በቅዳሴ ላይ ቅዱስ ሥጋውን መንካት የሚችለው ዋናው ካህን ብቻ ነው ፤ ሁለተኛው ካህን እንኳን…»
መጋቢት ፲
በዓለ ቅዱስ መስቀል

መጋቢት አስር በዚህች እለት የክብር ባለቤት ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል የተገለጠበትና የተገኘበት ነው። የዚህም የከበረ ዕፀ መስቀል መገለጡና መገኘቱ ሁለት ጊዜ ሆኗል።

መጀመሪያ የፃድቁ ንጉስ የቆስጠንጢኖስ እናት በሆነች በንግስት እሌኒ እጅ ነው።
እርሷ ለእግዚአብሄር ተስላ ነበርና ልጇ ቆስጠንጢኖስ ወደ ክርስቲያን ሀይማኖት ቢገባ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዳ መስቀሉን እስከ አገኘችው ድረስ ልትፈልግው በኢየሩሳሌም ያሉ ቅዱሳት መካናትንና አብያተ ክርስቲያናትን ልታንፃቸው ነው።

ከዚህ በኋላ ልጇ አምኖ የክርስትና ጥምቀትን በተጠመቀ ጊዜ እሌኒ ቅድስት ወደ ኢየሩሳሌም ሄደች ከእርሷ ጋርም ብዙ ሰራዊት ነበር ደርሳም ስለ ከበረ መስቀል መረመረች የሚያስረዳት አላገኘችም የአይሁድ ወገን የሆነ አንድ ሽማግሌ ሰው አስራ በርሀብና በጥማት አስጨነቀችው።
በተጨነቀም ጊዜ ለንግስት እሌኒ "የጉልጎታን ኮረብታ አስጠርጊ" ብሎ ነገራት እርሷም ይጠርጉ ዘንድ አይሁድን አዘዘቻቸው።

ቤቱን የሚጠርግ ሰው ሁሉ ጥራጊውን በውስጡ የከበረ መስቀል በአለበት በጌታችን መቃብር ላይ እንዲጥል አይሁድ አስቀድመው አዝዘው ነበርና ንግስት እሌኒ እስከደረሰችበት ጊዜ ከሁለት መቶ አመት በላይ ጥራጊያቸውን ሲጥሉበት ኖሩ ኮረብታም ሆነ። አይሁድም በጠረጉ ጊዜ ሶስት መስቀሎች ተገለጡ የክብር ባለቤት ክርስቶስ የተሰቀለበት የትኛው እንደሆነ አላወቁም።
የሞተ ሰውም አግኝተው አመጡ። አንዱንም መስቀል አምጥተው በሞተው ሰው ላይ አኖሩት አልተነሳም ደግሞ ሌላውን መስቀል አምጥተው በሙቱ ላይ አኖሩ አሁንም አልተነሳም ከዚህም በኋላ ሶስተኛውን መስቀል አምጥተው በሙቱ ላይ አደረጉት ያንጊዜ የሞተው ሰው ተነሳ እሌኒም የክርስቶስ መስቀል እንደሆነ አውቃ ሰገደችለት የክርስቲያንም ወገኖች ሁሉ ሰገዱለት።

ለልጇ የላከችው ይህ መስቀል ነው የሚል በሌላ መፅሀፍ ይገኛል የቀረው ግን ግንዱ በውስጡ ተተክሎበት የነበረው ከእርሱም እኩሌታውን ከቅንዋቱ ጋራ ወደ ልጅዋ የላከችው ነው።

ከዚህም በኋላ ስርዓታቸውና የህንፃቸው ነገር በመስከረም ወር በአስራ ሰባት ተፅፎ የሚገኝ አብያተ ክርስቲያናትንና የከበሩ ቦታዎችን አነፀች።

ሁለተኛው በሮሙ ንጉስ በህርቃል ዘመን የሆነው ሲሆን የፋርስ ሰዎች በግብፅ አገር ሳሉ ወደ አገራቸው ሊመለሱ ወደዱ። ከሹማምንቶቻቸው አንዱ የጦር መኰንን ተነጥሎ ወደ ኢየሩሳሌም አልፎ ደረሰ ወደ ከበረ መስቀል ቤተ ክርስቲያንም ገባ። መስቀሉም በላዩ በተተከለበት ግንድ ፊት ታላቅ ብርሀን ሲበራ አይቶ ሊያነሳው እጁን ዘረጋ። እሳትም ወጥታ እጁን አቃጠለችው።

ከክርስቲያን በቀር ማንም ሊነካው እንደማይችል የመስቀልን የክብሩን ነገር ሰዎች ነገሩት። ሁለት ዲያቆናትንም ይዞ የከበረ መስቀልን እንዲሸከሙ አዘዛቸው ከኢየሩሳሌምም ብዙ ሰዎችን ማርኮ ወደ አገሩ ተመለሰ።

የፋርስ ሰዎች ኢየሩሳሌምን እንዳጠፏት ብዙዎች ሰዎችንም እንደማረኩና የከበረ የክርስቶስንም መስቀሉን እንደወሰዱ የሮም ንጉስ ህርቃል በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ። ስለርሱም እንዲፆሙ ምእመናንን አዝዞ ወደፋርስ ዘምቶ ወጋቸው ብዙዎችንም ገደላቸው የከበረ እፀ መስቀልንም እየፈለገ በሀገራቸው ሁሉ ዞረ ግን አላገኘውም።

ያ ዲያቆናቱና መስቀሉን የወሰደ መኰንን ከቦታዎች በቤቱ አንፃር ባለ በአንድ ቦታ ላይ ወስዷቸው ጥልቅ ጉድጓድ እንዲቆፍሩ አዝዞ በዚያ የከበረ መስቀልን አስቀበረ እነዚያንም ዲያቆናት ገደላቸው።

ነገር ግን ያ መኰንን የማረካት የካህናት ወገን የሆነች በእርሱ ቤት የምትኖር አንዲት ብላቴና ነበረች። እርሷም የከበረ መስቀልን ሲያስቀብርና ሁለቱን ዲያቆናት ሲገድላቸው በቤቱ ውስጥ ሁና በመስኮት ትመለከት ነበር ወደ ንጉስ ህርቃልም ሂዳ መኰንኑ ያደረገውን ሁሉ ነገረችው።
ይህም ንጉስ ሰምቶ እጅግ ደስ አለው ያቺ ብላቴናም መራችው ከእርሱም ጋራ ብዙ ሰራዊት ሆኖ ኤጲስቆጶሳትና ካህናትም ነበሩ ።ወደ ቦታውም እስከምታደርሳቸው ያቺን ልጅ ተከተሏት ቆፍረውም የከበረ እፀ መስቀልን አገኙት ከአዘቅቱም አወጡት ንጉሱና ሰራዊቱም ሰገዱለት።

በልብሰ መንግስቱም አጎናፀፈው ታላቅ ክብርንም አከበረው ከሰራዊቱም ጋር እጅግ ደስ አለው። የዚህም መስቀል ሁለተኛ የተገለጠበትና የተገኘበት በዚች ቀን በመጋቢት አስር ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ንጉሱ የከበረ እፀ መስቀልን ተሸክሞ ወደ ቁስጥንጥንያ ከተማ ወሰደው፡፡

የመድኃኒታችን የመስቀሉ በረከት ከሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን።
https://www.tg-me.com/sratebetkrstyane
+ አባቶቻችን እንዲህ አሉ +

"መጥፎ ቀን እና ጥሩ ቀን የሚባል ነገር የለም:: ያለው ጸሎት አድርገህ የወጣህበት ቀን እና ጸሎት ሳታደርግ የወጣህበት ቀን ነው:: ያልጸልክባቸው ቀናት በክፉ ምኞትና የሥጋ ፍላጎት የተሞሉ ስለሆኑ ክፉ ቀናት ናቸው"
ቅዱስ ቄርሎስ ሳድሳዊ

"የምንቆጥረው ሬሳዎችን አይደለም:: ሰማዕታትን ነው:: ሙታንን ሳይሆን ሙሽሮችን ነው:: ሰማዕታት ሆይ ስለ እኛ ማልዱ" ከአኃው አንዱ

"ሰዎችን የሚሳደብን ሰው አንደበት መዝጋት አትችልም ከእርሱ ጋር አለመነጋገር ግን ትችላለህ"
ቅዱስ ማር ይስሐቅ

"እኔ ካህን ነኝ መግደል አልችልም:: በግድ ዝመት ካላችሁኝ ደግሞ ከጦር ሜዳ ውሰዱኝ:: የቆሰሉትን እረዳለሁ:: ለሞቱት ጸሎት አደርጋለሁ:: የወደቁትን አነሣለሁ:: መሞትን አልፈራም:: መግደልን ግን እፈራለሁ"
በዘመነ ሰማዕታት የነበረ ሕጽው ካህን

"ሰዎች አንድ ሰው ተነሥቶ ሌላውን ሲገድል ወንጀለኛ ነህ ይሉታል። አንድ ላይ ተሰባስበው ብዙ ሰዎችን ሲገድሉ ግን ውጊያ ይሉትና መግደላቸውን ጀግንነት ይሉታል" ቅዱስ ቆጵሮሳዊ

"ገድዬ እጸድቃለሁ ብሎ ክርስቲያኖችን የሚገድል ሰው የተሳሳተ ቢሆንም ያደረገው ያጸድቀኛል ብሎ ያመነበትን ነው:: እኛ የምናምንበት መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ "ጠላቶቻችሁን ውደዱ ለሚያሳድዱአችሁ ጸልዩ" ይላል:: ነፍሰ ገዳይ ለሚያምንበት ነገር ከታዘዘ እኛም ለምናምንበት ይቅር ባይነት መታዘዝ አለብን” አቡነ አትናቴዎስ እስክንድር

"የክርስቲያኖች መሣሪያ በእጃቸው ሰይፍን መታጠቅ ሳይሆን እጃቸውን ወደላይ ለጸሎት መዘርጋት ነው"
ቅዱስ አትናቴዎስ ዘእስክንድርያ

"እግዚአብሔር ለአብርሃም "ከሀገርህ ውጣ ከወገኖችህ"ተለይ ብሎት ነበር። በዚህ ጥሪ እግዚአብሔር ሁላችንንም የተወለድንበት ዘር እንድንተው ይጠራናል።
ሰማዕቱ ዮስጦስ (100 AD-165 AD)

"ክርስቶስ ጴጥሮስን "ሰይፍህን ወደ ሰገባው አስገባ" ሲለው ትጥቅ ያስፈታው ጴጥሮስን ብቻ ሳይሆን እንደ ጴጥሮስ በእርሱ የሚያምኑትን ሁሉ ነበር"
ሊቁ ጠርጡለስ (160 AD - 220 AD)

"የእኛ መሣሪያ ወደ ላይ የምንረጨው ዕንባ ነው:: ፈርዖንን ከነፈረሶቹ ያሰጠመው የኤርትራ ባሕር ሳይሆን የራሔል የጸሎት ዕንባ ነው" ከአኃው አንዱ

"አምላኬ ሆይ ልቤ እንደ ጠባብ ቤት ነው:: አንተን ለማስገባት የማይችል በጣም ትንሽ ነው:: አንተ ሰፊ እንድታደርገው እለምንሃለሁ:: በልቤ ቤት ውስጥ ስታያቸው ደስ የማያሰኙህ ነገሮች እንዳሉ አውቃለሁና አልደብቃቸውም:: ከአንተ በቀር የውስጤን ቆሻሻ ሊያስወግድ የሚችል ማንም እንደሌለ አውቃለሁ"
ቅዱስ አውግስጢኖስ


"...........እነሆ፥ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ የመዳን ቀን አሁን ነው"
--2ኛ ቆሮ 6፥2
https://www.tg-me.com/sratebetkrstyane
#ምኩራብ
(የዐቢይ ጾም ሦስተኛ ሳምንት)

ምኩራብ ማለት ለአምልኮትና ለትምህርት ለህብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጥ የአይሁድ ቤተ ጸሎት ነው። ጌታ በመዋዕለ ስብከቱ በእስራኤል ሀገር ብዙ ምኩራቦች ስለነበሩ እየገባ ወንጌልን አስተምሮባቸዋል። በዚህም “ቦአ ኢየሱስ ምኩራበ አይሁድ ወመሀረ ቃለ ሃይማኖት” እንዲል ቅዱስ ያሬድ ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኩራብ ገብቶ የሃይማኖት ቃልን አስተማረ። ከሚለው የቅዱስ ያሬድ ዜማ ሥያሜውን አግኝቷል።

በምኩራብ ጸሎትና ትምህርት ይፈጸምበታል። መሥዋዕት ግን አይከናወንም። መሥዋዕት ግን በታላቁ ቤተ መቅደስ በኢየሩሳሌም ብቻ ይፈጸም ነበር። በዚህ ሳምንት የሚነገረው ታሪክ ጌታ ቤተ መቅደሱን የገበያ ማዕከል አድርገው ሸቀጥ ዘርግተው በጉን ላሙን ርግቡን እየሸጡ አገኛቸው። በዚህ ተቆጥቶ በጉን ላሙን ርግቡን ከምኩራብ አስወጥቶ ሸቀጣቸውንና መደርደሪያቸውን እንዲሁም ወርቅና ብራቸውን በነፋስ በተነባቸው ይላል።

በዚህ ሁኔታ ከቤተ መቅደስ አስወጥቶ "ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች እናንተ ግን የሽፍቶችና የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችኋት" በማለት ወቅሷቸዋል። “አሰስሉ ወአውፅኡ ዘንተ እምዝየ ወኢትረስዩ ቤተ አቡየ ቤተ ምሥያጥ” እንዲል ዮሐ. 2፥16፤ ማቴ. 21፥13። ይህን ተአምር በማሳየት ቤተ ጸሎት የተቀደሰ ከገበያ የተለየ መሆኑን አስተምሮበታል።

በሰንበተ ምኩራብ ጌታ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ ለዋጮችን ማስወጣቱ ወርቅና ብሩን በነፋስ መበተኑ ላሞችን በጎችን በጅራፍ መግረፉ ቤተ መቅደሱን ማንጻቱ ወዘተ ይነገራል።

(የዚህም በዓል ታሪክ ዝርዝር ሁኔታው ማቴዎስ 21፥12-13 ላይ ተጠቅሷል፡፡)

#የቅዳሴ_ምንባባት

ቆላስ. 2፥16-23
«እንግዲህ በመብል ወይ በመጠጥ ወይም ስለ በዓል ወይም ስለ ወር መባቻ ወይም ስለሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ እነዚህ ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና፣ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው፡፡ .......፡፡»

ያዕ. 2፥14-26
«ወንድሞቼ ሆይ፣ እምነት አለኝ የሚል፣ ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን ......፡፡»

ሐዋ. 1ዐ፥1-9
«በቂሣርያም ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራ የመቶ አለቃ የሆነው ቆርኔሌዎስ የሚሉት አንድ ሰው ነበር፡፡ እርሱም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ ለሕዝብም እጅግ ምጽዋት የሚያደርግ ወደ እግዚአብሔርም ሁልጊዜ የሚጸልይ ነበረ፡፡ ....፡፡"

#ምስባክ- መዝ 68፥9
እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ
ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዕሌየ
ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ፡፡

(የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና
የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና
ነፍሴን በጾም አስመረርኋት፡፡)

#ወንጌል፡- ዮሐ 2፥12-25
«ከዚህ በኋላ ከእናቱና ከወንድሞቹ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፣ በዚያም ጥቂት ቀን ኖሩ፡፡ የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ፡፡ ወደ መቅደስም በሬዎችንና በጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፤ የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፣ .....፡፡»

(ከመድብለ ታሪክ እና ግጻዌ የተወሰደ)

ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE

    
https://www.tg-me.com/sratebetkrstyane
#መጻጉዕ (የዐቢይ ጾም አራተኛ ሣምንት)

በዐቢይ ጾም ውስጥ ካሉት ሳምንታት መካከል አራተኛው እሑድ መጻጉዕ ይባላል፡፡ መጻጉዕ የተባለበት ምክንያት በዚሁ ሰንበት ከዋዜማው ጀምሮ የሚዘመረው ጾመ ድጓ ድውያንን መፈወሱን ዕውራንን ማብራቱን የሚያነሣ በመሆኑ ነው፡፡ «38 ዓመት የታመመውን መጻጉዕን ኢየሱስ አዳነው» እንዲሁም ልጁ የታመመበት የመቶ አለቃው "ጌታዬ በቃልህ እዘዝ ልጄ ይድናል፡፡ በቤቴ ጣርያ ሥር አንተ ልትገባ አይገባህም" አለው። "ጌታ በሚያልፍበት መንገድ አንድ ዕውር ፈውሰኝ" ብሎ ጮኸ የሚመሩት ሰዎች ዝም በል አሉት፡፡ ዕውሩ ግን እምቢ ብሎ "የዳዊት ልጅ ጌታ ይቅር በለኝ ዕርዳኝ" እያለ ጩኸቱን ቀጠለ፡፡ "በሰንበት ኢየሱስ መጻጉዕን ተነሥ አልጋህን ተሸከም ባለው ጊዜ ቀኑ ሰንበት ነበረ፡፡ መጻጉዕም አልጋውን ተሸክሞ ወደ ቤቱ ገባ የእግዚአብሔር ልጅ በሰንበት ፈውሷልና "በሰንበት ድውያንን ፈወሰ የዕውራንንም ዓይኖች አበራ" እያለ 38 ዓመት በአልጋ ቁራኛ በደዌ ዳኛ ተይዞ ሲማቅቅ የኖረውን መጻጉዕንና ሌሎቹን በልዩ ልዩ ደዌ የተያዙትን ሕሙማን መፈወሱን በጠቅላላው ለምፅ ማንጻቱን፣ ዕውር ማብራቱን፣ አንካሶችን ማርታቱን፣ ልምሾዎችን ማዳኑን፣ አጋንንትን ማውጣቱን፣ ወዘተ እየጠቃቀሰና እያነሣሣ ስለሚዘምር ዕለቱና ሳምንቱ መጻጉዕ ተብሏል፡፡

ስለዚህም ይህ ሰንበት የሕሙማን ፈውስ መታሰቢያ ዕለት ነው ማለት ይቻላል፡፡ በነዚህ ሁሉ ታሪኮች የመጻጉዕንና የሌሎቹን ሕሙማን ሁሉ ደኅንነት ታሪክ እንረዳለን፡፡ የሰንበቱም ስያሜ ልብ ወለድ አጠራር ሳይሆን የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢርና የጾመ ድጓውን ይትበሀል ተከትሎ የተሰየመ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡

#የዕለቱ_ምንባቦች
1ኛ. የቅ.ጳውሎስ መልእክት ወደ ገላ. 5÷1-26
2ኛ. የቅ. ያዕቆብ መልእክት 5÷14-20
3ኛ. የሐዋርያት ሥራ 3÷1-12

#የዕለቱ_ምስባክ
መዝ 4ዐ(41)÷3
እግዚአብሔር ይረድኦ ውስተ ዐራተ ሕማሙ
ወይመይጥ ሎቱ ኵሎ ምስካቤሁ እምደዌሁ
አንሰ እቤ እግዚኦ ተሣሃለኒ።

(እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ላይ ሳለ ይረዳዋል፡፡ መኝታውን ሁሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል እኔስ አቤቱ ማረኝ፡፡) መዝ 4ዐ÷3  የሚለው ይሆናል፡፡

#የዕለቱ_የወንጌል
በዮሐንስ ወንጌል 5፥1-25 ድረስ ያለው ነው፡፡

ያንን ተስፋ ያልነበረውን በሽተኛ ከደዌ ሥጋው ፈውሶ ሕይወትን የሰጠው አምላክ፣ እኛንም በውስጥ በአፍአ ካለብን ደዌ ሥጋና ደዌ ነፍስ እንዲፈውሰን፤ ቁስለ ኃጢአታችንን እንዲያደርቅልን፣ በሕይወትና በጤና እንዲጠብቀን የእርሱ የጌታች ቅዱስ ፈቃድ ይሁንልን፡፡

ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE

    
https://www.tg-me.com/sratebetkrstyane
#የግዝት_በዓላት (#የማይሰገድባቸው_ጊዜያት)

የሚሰገድባቸው ጊዜያት እንዳሉት ሁሉ የማይሰገድባቸው ጊዜያትም አሉ። የግዝት በዓላት 5 ሲሆኑ
#የወልድ_በዓል#የእመቤታችን_በዓል#የቅዱስ_ሚካኤል በዓል፣ #ቀዳሚት_ሰንበትና_እሑድ_ሰንበት ናቸው። ከነዚህ በተጨማሪ #ከቁርባን በኋላና የበዓለ #ሐምሳ ወራትም የማይሰገድባቸው ጊዜያት ናቸው። እነዚህ ስግደት የተገዘተባቸው ጊዜያት የሚከተሉት ናቸው።
1ኛ
#በዕለተ_እሑድ

ከአልቦ ነገር ወይም ከምንም (ex- nihilo - from nothingness) ሁሉ ክርስቶስ ዳግም ሲመጣ ጠፍቶ ወደ ምንምነት ሲቀየር ከማይጠፉ ከአምስቱ ፍጥረታት አንዷ ሰንበት ናት። ጌታ የተነሣባት ፣ ዳግምም የሚመጣባት ዕለት ናት። በዚህና በሌሎች ምክንያቶችም ሰንበተ ክርስቲያን እሑድ በዓል ነች። ስለዚህ በዕለተ እሑድ መስገድ የተከለከለ ነው።
2ኛ
#በዕለተ_ቅዳሜ

ሌላው ከዕለታት መካከል ቅዳሜ የግዝት በዓል ተብሎ የተመረጠበት ምክንያት የሁሉ ባለቤት የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዓለማትን ሁሉ በስድስት ቀናት ውስጥ ፈጥሮ ከፈጸመ በኋላ በሰባተኛው ቀን አረፈ። ይህችንም ቀን ቀደሳት ለሰው ልጆችም በዓል አድርጎ ሰጠን። “በሰንበትም እንደ ትእዛዙ ዐረፉ።” ሉቃ 23፥56
3ኛ
#በጌታችን_በዓላት

ፍትሐ ነገሥቱ “በእሑድና በተከበሩት በዓላት ቀን ስግደት አይገባም፤ እነዚህ የደስታ ቀኖች ናቸውና” (ፍት.መን. አን. 19 ቁ. 715) ካለ በኋላ “የተከበሩት በዓላት” ያላቸው የትኞቹን እንደሆነ ሲዘረዝር ትስብእት/ጽንሰት ፣ ልደት ፣ ጥምቀት ፣ ሆሣዕና ፣ ትንሣኤ ፣ ዕርገት ፣ በዓለ ሃምሳ ፣ ደብረ ታቦር በማለት ከጌታ ዘጠኝ ዐበይት በዓላት 8ቱን ይገልፃል። ሳይገለፅ የቀረው ስቅለት ነው፤ ያልተገለፀበትም ምክንያት በስቅለት ስግደት ስለማይከለከል ነው። ስለዚህ ከስቅለት በቀር በጌታ ዐበይት በዓላት (በተቀሩት በ8ቱ) ስግደት የተከለከለ ነው።
4ኛ.
#በእመቤታችን_በዓላት

በፍት. መን. አን. 14 ቁ. 536-537 ድረስ በጌታ በዓላት መስገድ እንደተከለከለው ሁሉ በእመቤታችን በዓላትም መከልከሉን ይጠቁመናል። የወልድ በዓልን እንደምናከብረው የእመቤታችንንም በዓል በ21 አስበን አንሰግድም። ስለዚህ ወር በገባ በ21 ሁሌም የግዝት በዓል ነው፤ አይሰገድበትም።

5ኛ.
#በቅዱስ_ሚካኤል_በዓል

የቅዱስ ሚካኤል በዓል ከሌሎች የመላእክት በዓላት ተለይቶ መከበሩ ለምንድነው ቢሉ

“የቅዱስ ሚካኤል በዓል መላእክትን ወክሎ ወርኃዊ ሆኖ እንዲከበር ታዟል” (በዓላት ፣ ዲ.ን. ብርሃኑ አድማስ ፣ ገጽ 124)። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን በ12 እንዳይሰገድና እንደ ታላላቅ በዓላት በደስታ እንዲከበር ሥርዐትን ሠርታለች።
6ኛ.
#ሥጋና_ደሙን_ከተቀበሉ_በኋላ

የሥርዐት ምንጫችን የሆነው ፍትሐ ነገሥት አሁንም በዚህ ዙሪያ እንዲህ ብሏል፦ “መስገድን የሚተዉባቸው የታወቁ በዓላት እነዚህ ናቸው… ሥጋውንና ደሙን ከተቀበሉ በኋላ” ይላል። ፍት. መን. አን. 14 ቁ. 536- 537። ሥጋውንና ደሙን ከተቀበልን በኋላ ከሚሰገድለት እንጂ ከማይሰግደው ጋር አንድ መሆናችንን ለማጠየቅና ለቅዱስ ሥጋውና ለክቡር ደሙ ክብር ስንል ዝቅ ብለን አንሰግድም።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
#ሼር በማድረግ ለጓደኞቻችሁ አካፍሉ።
https://www.tg-me.com/sratebetkrstyane
ደብረ ዘይት
የዐብይ ጾም አምስተኛ እሑድ(ሳምንት)
(የዐብይ ጾም እኩሌታ)
ደብረ ዘይት ማለት የወይራ ዛፍ ያለበት ተራራ ማለት ነው፡፡ቦታው ከኢየሩሳሌም በስተምስራቅ የሚገኝ የወይራ ዛፍ የበዛበት ተራራ ሲሆን ስሙም ከወይራ ዛፉ:- ደብረ ዘይት (የወይራ ዛፍ ተራራ) በመሰኘት ተገኝቷል። በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ደብረ ዘይት በዓልሆኖ የሚከበርበት ምክንያት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረዘይት ተራራ ላይ ሳለ ለቅዱሳን ደቀመዛሙርቱ ስለ ዓለም ፍጻሜ እና ስለ ዳግም ምጽአቱ ስላስተማራቸዉ በጌታችን ትምህርት መሠረት ነገረ ምጽአቱን እንድናስታውስ ወይም እያሰብን እንድንዘጋጅ ለማድረግ ነው።

ስለ ዓለም መጨረሻና ስለ ዳግም ምጽአቱ ምልክቶች ምን እንደሆኑ ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌል ላይ በሦስት መሠረታዊ ክፍሎች ከፍሎ ጽፎልናል፡፡

፩. ሃይማኖታዊ ምልክቶች

"እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ" /ማቴ 24፥5/፡፡

፪. ፖለቲካዊ ምልክቶች

“ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ” /ማቴ 24፥6/ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና” /ማቴ 24፥7/

፫. ተፈጥሯዊ ምልክቶች

“ራብም ቸነፈርም የምድር መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል” /ማቴ.24፥7/

ከላይ ያየናቸውን ምልክቶች በዓለማችን ላይ ዕለት ተዕለት የምናየው የምንሰማው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ጌታችን ለደቀመዛሙርቱ የነገራቸውን ምልክቶች የቤተ ክርስቲያናችን አራት አይና ሊቃውንት የወንጌሉን ገጸ ንባብ እንዲህ ብለው ያመሰጥሩታል፡፡

“እነዚህ ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያዎች ናቸው” /ማቴ.24፥8/

ምጥ ሲመጣ አስቀድሞ የምጡ መጀመሪያ ሕመም (ጣር) እንዳለ ሁሉ የዓለምም ፍጻሜ በጣር ነው የሚጀምረው። ይህንንም ጌታችን በግልጽ አስረድቶናል፦ ጦርና የጦር ወሬ መሰማት፣ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ መነሳት፣ ርሃብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ መታየት ለዓለም ፍጻሜ የምጥ ጣር መጀመሪያዎች ናቸዉ። እነዚህ ነገሮች በሁሉም ቦታ በአንድ ጊዜ ላይከሰቱ ይችላሉ፤ ነገር ግን በልዩ ልዩ ቦታዎች ለብዙ ዘመናት ታይተዋል፤ እየታዩም ናቸው።

“ስለ ስሜ በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” /ማቴ.24፥9/

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ "ስለ ስሜ ክርስቲያኖች በመሆናችሁ በዓለም ዘንድ ትጠላላችሁ" ብሎናል። ዓለም ክፉ ስለሚሠራ የጥሩ ነገር ተቃራኒ ሆኖ ለብዙ ዘመናት ቆይቷል። ጌታችን “ብርሃንም ወደ ዓለም ስለመጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለወደዱ ፍርዱ ይህ ነው። ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፣ሥራዉም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል” /ዮሐ. 3፥19-21/ እንዳለን በክፉ ሥራ ውስጥ ያለው ይህ ዓለም በጎ ሥራ የሚሠሩትን የክርስቶስን ተከታዮች ይጠላል። ጨለማ ብርሃንን ብርሃንም ጨለማን እንደሚጠላ፤ ይህ ዓለም እኛን እንዲጠላን፣ እኛ ክርስቲያኖች ደግሞ ይህንን ዓለም ልንጠላው ይገባል።
አሁን ባለንበት ዘመን ክርስትና እየተጠላ፣ እየተናቀ ነው ያለው። “ባደጉት” ዓለማት ባዶ አብያተ መቅደሶች ቀርተው እነሆ እንመለከታቸዋለን፤ ትውልዱ በዓለም ስሜትና በሥጋ ፈቃድ ብቻ እየሔደ ነው። ክርስቲያን ነን በሚሉትም አውሮፓውያን ዘንድ የአንገት በላይ የማስመሰል ክርስትና እንጂ እንደ ቅዱስ ቃሉ የሚጓዝ አማኝ ማግኘት አይቻልም። እውነተኞች አይወደዱም፤ ይገፋሉ፤ ይናቃሉ። ሁኔታው የዘመኑ ፍጻሜ እጅግ እየቀረበ መምጣቱን በእርግጥ ያስረዳል።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዚህም በላይ “ስለ ስሜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል፤ ይገድሏችሁማል” ብሏል። ክርስቲያን በመሆናቸው ብቻ ማንንም ሳይበድሉ ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ በልዩ ልዩ ሀገራት ክርስቲያኖች ሰማዕትነትን እስከ አሁን ድረስ እየተቀበሉ ነው፡፡ቅዱስ ጳዉሎስ  “ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፤ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን” /ሮሜ 8፥36/ እንዳለው። ይህ በቅዱሱ በክርስቶስ ስም መጠላትና መከራ መቀበል ከዓለም የሚጠበቅ የፍጻሜዉ ዘመን ምልክት መሆኑን አውቀን መዘጋጀትና ከሐዋርያው ጋር “በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን” /ሮሜ 8፥37/ እያልን በእምነታችን ጸንተን መጋደል ይገባናል።

የክርስቲያኖች ቁጥር እያነሰ መምጣት፣ የአብያተ ክርስቲያናት መዘጋት፣ ሰው ሰው የሚያሰኘውን ክብርና ሞገስ ትቶ በግብሩ እንስሳትን ሲመስል የቅድስና ሕይወት ሲጠላና ሲናቅ፤ በአንጻሩ ደግሞ የሰው ልጅ ለረከሰው ለዚህ ዓለም ምኞትና ፈቃድ ሲገዛ ስናይ የዚህ ዓለም ፍጻሜ ጊዜው እየደረሰ መሆኑን አውቀን፤ ኖኅ በብዙ ኃጢአተኞች መካከል ቢኖርም ራሱን በቅድስና ጠብቆ እንደኖረ /ዘፍ.6-8/፤ ሎጥም እንዲሁ በብዙ ኃጢአተኞች መካከል ሲኖር በነርሱ ኃጢአት እንዳልተባበረ /ዘፍ. 19/ ከዚህ ዓለም ክፉ ሥራ ተለይተን ራሳችንን በቅድስና በመጠበቅ እንጋደል። ዓለሙ ስለ እምነታችን ቢጠላንም እኛም ስለ ክፉ ሥራው ንቀነው መኖር የግድ መሆኑን እንወቅ እንጂ ስለ እምነት፣ ስለ ቅድስናም ከዓለም በጎ ነገር አንጠብቅ። በተለያዩ ሁኔታዎች የሚደርሱብንን ፈተናዎች ሁሉ በትዕግስት እንቀበላቸው እንጂ በማማረር አንዘን፤ ምክንያቱም ስለ ስሜ በዓለም ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ ተብለናልና።

“የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ አንባቢው ያስተውል!” ማቴ.24፥15/

ዓለም ራሱን በማርከስ ብቻ ሳይወሰን በፍጻሜ ዘመን በተቀደሰው ስፍራ እንኳን ሳይቀር የጥፋትን ርኩሰት ያቆማል። የተቀደሰው ስፍራ የተባለው በተቀደሰ ሃይማኖት የሚኖሩትን ሀገራት፣ ሕዝቦች የሚመለከት ነው። እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉትን ሀገራት ዲያብሎስ በመልእክተኞቹ ላይ አድሮ በብዙ ርኩሰት ተፈታትኗቸዋል፤ እየተፈታተናቸውም ነው። የየሀገራቱን እምነትና ታሪክ ለማጥፋት ጥሯል፤ ብዙውንም የቅድስና ሥርዓት በርዟል፤ የቻለውንም ከነጭራሹ አጥፍቶታል። አሁን እንኳ አምልኮተ እግዚአብሔር በሚፈጸምባቸዉ ቅዱሳት መካናትና ገዳማት ሳይቀር በልዩ ልዩ ምክንያት የጥፋት ርኩሰት አዉጇል። ይህም የፍጻሜ ዘመኑ አንዱ ምልክት ስለሆነ አንባቢዉ ያስተዉል እንደተባለ የዘመኑን መፍጠን የጊዜውን መድረስ በመረዳት መዘጋጀት ይገባናል።

“ብዙ ሐሰተኛዎች ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ” /ማቴ.24፥11/፡፡

ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት በየዘመኑ ተነስተው እውነተኛይቱን
ቤተ ክርስቲያን ታግለዋታል፤ ሊያጠፏት ባይችሉም እንኳን ብዙ ልጆቿን ነጥቀው ወስደውባታል። የነዚህን ሐሰተኞች ሠራተኞች አመጣጥ ከባድ የሚያደርገው በተአምራትና በድንቅ ምልክቶች መምጣታቸው ነው። ጌታችን እንደተናገረ “ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳን እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ” /ማቴ.24፥24/ ስለዚህ በምትሐታዊ ምልክቶቻቸው የብዙ የዋሐንን ልብ በማታለል ከተቀደሰ እምነታቸው እያስኮበለሉ አጥፍተዋቸዋል፤ በማጥፋትም ላይ ይገኛሉ። ስለዚህም ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ  “ወዳጆች ሆይ መንፈስን ሁሉ አትመኑ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነዉ እንደሆነ መርምሩ”/1ዮሐ 4፥1-3/ አለን።
ቅዱስ ጳዉሎስም “የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸዉን እየለወጡ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞ ሠራተኞች ናቸው። ይህም ድንቅ አይደለም ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለዉጣልና” ብሏል /2ቆሮ.11፥13-15/። ሐዋርያት ሁሉ በየመልእክቶቻቸው ከሐሰተኞች አስተማሪዎች እንድንጠበቅ ደጋግመው አሳስበዋል። ብዙ ሰው ግን በየዋሕነት ስለሚጓዝ የነዚህ ተኩላዎች ሰለባ ሆኗል።
ጊዜው ክፉ ነውና የሐሰተኞች ነቢያት መረብ ጠልፎ ወደ ሐሰተኞች ክርስቶሶች እንዳይወስደን በጥንቃቄ መጓዝ ይጠበቅብናል። ሐዋርያዉ ቅዱስ ይሁዳም በመልእክቱ ቁ3  “ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኳችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ” ሲል እንደመከረን በተቀደሰ እምነታችን እስከመጨረሻ ጸንተን እንጋደል።

በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ ጥቅሶች
-፩ኛ ተሰ ፬፥፲፫ እስከ ፍጻሜ
-፪ኛ ጴጥ ፫፥፯-፲፭
-የሐዋ ሥራ ፳፬፥፩-፳፪

ምስባኩም፦ መዝ ፵፱፥፫
"እግዚአብሔርሰ ገሀደ ይመጽዕ ወአምላክነሂ ኢያረምም
እሳት ይነድድ ቅድሜሁ"
"እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይመጣል አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም እሳት በፊቱ ይቃጠላል"

ወንጌሉም፦ ማቴ ፳፬፥፩-፴፮
https://www.tg-me.com/sratebetkrstyane
🔔 ከመምህራን የማንን ትምህርት ማግኘት ይፈልጋሉ?👇

┏━━━━━━━━━━━━━━┓
🔔 መምህር ምሕረተአብ አሰፋ
┗━━━━━━━━━━━━━━┛
┏━━━━━━━━━━━━━━┓
🔔 መምህር ዘበነ ለማ
┗━━━━━━━━━━━━━━┛
┏━━━━━━━━━━━━━━┓
🔔 መምህር ሄኖክ ኃይሌ
┗━━━━━━━━━━━━━━┛
┏━━━━━━━━━━━━━━┓
🔔 መምህር ዮርዳኖስ አበበ
┗━━━━━━━━━━━━━━┛
┏━━━━━━━━━━━━━━┓
🔔 አባ ገብረ ኪዳን
┗━━━━━━━━━━━━━━┛
┏━━━━━━━━━━━━━━┓
🔔 መምህር ያረጋል አበጋዝ
┗━━━━━━━━━━━━━━┛
┏━━━━━━━━━━━━━━┓
🔔መጋቢ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ
┗━━━━━━━━━━━━━━┛
┏━━━━━━━━━━━━━━┓
🔔 መምህር እዮብ ይመኑ
┗━━━━━━━━━━━━━━┛
┏━━━━━━━━━━━━━━┓
🔔መምህር ገብረ እግዚአብሔር
┗━━━━━━━━━━━━━━┛
┏━━━━━━━━━━━━━━┓
🔔መምህር አባ ገብረ ኪዳን
┗━━━━━━━━━━━━━━┛

🔗የሁሉንም መምህራን ትምህርት ለማግኘት🔔
🫧🫧🫧🫧🫧🫧🫧🫧🫧🫧🫧🫧🫧🫧
#ገብር_ኄር
(
#የዐቢይ_ጾም_ስድስተኛ_ሳምንት)

የዐቢይ ጾም ስድስተኛው እሑድ ወይም ሳምንት ገብር ኄር ይባላል፡፡ በዚህ ሳምንት የሚዘመረው ዝማሬ፣ የሚሰበከው ስብከት፣ የሚሰጠው ትምህርት ገብርኄርን የሚያወሳ ነው። ማለትም ስለ ታማኝ አገልጋይ ነው፡፡

የማቴ.25፥14-25 የሚነግረን ይህን ነው፦ “አንድ ባዕለ ጸጋ ሰው ባሪያዎችን ጠርቶ ለአንዱ አምስት መክሊት ሰጠው፣ ሁለት መክሊት የሰጠውም አለ፣ አንድ መክሊትም የሰጠው አለ፡፡ ከዚህ በኋላ ወደሩቅ አገር ሄደ፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለውም ወጥቶ ወርዶ ሌላ አምስት አትርፎ አስር አደረገ፡፡ ሁለት የተቀበለውም አትርፎ አራት አደረገ፡፡ አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ መሬቱን ቆፍሮ በሻሽ ጠቅልሎ የጌታውን መክሊት ቀበራት፡፡

ከብዙ ጊዜ በኋላ ጌታቸው መጥቶ ተቆጣጠራቸው፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለው ቀርቦ ጌታዬ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር እነሆ አምስት አተረፍኩ አለው፡፡ “ገብርኄር ወምዕመን ዘበሁድ ምዕምነ ኮንከ ዲበ ብዙህ እሰይመከ ባዕ ውስተ ፍስሐሁ ለእግዚእከ” “አንተ ታማኝ ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ” አለው፡፡ ሁለት የተቀበለውም ቀርቦ ጌታዬ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር እነሆ ወጥቼ ወርጄ ሌላ ሁለት አትርፌ አራት አድርጌአለሁ፡፡ “አንተ ታማኝ በጎ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ” አለው፡፡ አንድ መክሊት የተቀበለው ግን ቀርቦ “ጌታዬ አንተ ክፉና ጨካኝ ካልዘራህበት የምታጭድ ካልበተንህበት የምትሰበስብ እንደሆንክ ስለአወቅሁ መሬቱን ቆፍሬ ቀበርኋት እነኋት መክሊትህ” አለው፡፡ “አንተ ሰነፍ ባሪያ መክሊቴን በጊዜ ልትሰጠኝ በተገባህ ነበር እኔም ወጥቶ ወርዶ ለሚያተርፍ በሰጠሁት ነበር”፡፡ ኑ የዚህን ሀኬተኛ መክሊት ውሰዱና አስር መክሊት ላለው ስጡት፡፡ ላለው ይሰጡታል ይጨመርለታል ለሌለው ግን ያለውን ይቀሙታል፡፡ ኑ ይህን ሰነፍና ሃኬተኛ ባሪያ እጅ እግሩን አሥራችሁ ጽኑዕ ጨለማ ወደአለበት ውሰዱት ጩኸትና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ጨምሩት” አለ ማቴ. 25፥14-25፡፡

ባለ ጸጋ የተባለው ጌታ ነው፡፡ መክሊት የተባለው ልዩ ልዩ የአገልግሎት ጸጋ ነው፡፡ ያተረፉት በሚገባ በታማኝነት ያገለገሉ ቅዱሳን ሰዎች ናቸው መክሊቱን የቀበረው ደግሞ በታማኝነት በተሰጠው ጸጋ ማገልገል ሲገባው ያላገለገለ ነው፡፡ ጌታቸው ሊቆጣጠራቸው መጣ ማለት በዕለተ ምጽአት ለሁሉም በአገለገለው አገልግሎት ዋጋ ለመስጠት እንደሚመጣ ያሳየናል፡፡ ያገለገሉትን ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አላቸው ማለት ታማኝ አገልጋዮች መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉና፡፡ ሰነፎች ደግሞ ጥርስ ማፋጨት ስቃይ ጽኑዕ ጨለማ ባለበት ሲዖል መግባታቸውን የሚያሳይ ነው፡፡

#የዕለተ_ሰንበት_መዝሙር_ከጾመ_ድጓ
መኑ ውእቱ ገብር ኄር ወምእመን ዘይረክቦ እግዚኡ በምግባረ ሠናይ ወይሠይሞ ዲበ ኲሉ ንዋዩ ካዕበ ይቤሎ እግዚአብሔር ገብር ኄር ወምእመን ዘበውኁድ ምእመነ ኮንከ ዲበ ብዙኅ እሠይመከ ባእ ውስተ ፍሥሐሁ ለእግዚእከ፡፡

ትርጉም፦ ጌታው በመልካም ሥራ የሚያገኘው በሐብቱ ኹሉ ላይ የሚሾመው፤ የታመነ በጎ አገልጋይ ማን ነው? ዳግመኛም እግዚአብሔር አንተ የታመንክ በጎ አገልጋይ በጥቂቱ የታመንህ ስለኾንህ በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ ይለዋል፡፡

#መልዕክታት
2ኛ ጢሞ.2÷1-15
"ልጄ ሆይ÷ አንተም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ በርታ፡፡ በብዙ ምስክሮች ፊት ከእኔ የሰማኸውን ትምህርት ለሌሎች ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች እርሱን አስተምራቸው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደሚያገለግል በጎ አርበኛ ሆነህ መከራ ተቀበል፡፡" (ተጨማሪ ያንብቡ)

1ኛ ጴጥ.5÷1-11
"እንግዲህ እኔ ከእነርሱ ጋር ሽማግሌ÷ የክርስቶስም መከራ ምስክር÷ ደግሞም ሊገለጥ ካለው ክብር ተካፋይ የሆንሁ በመካከላቸው ያሉትን ሽማግለዎችን እማልዳቸዋለሁ፡፡ በእናንተ ዘንድ ያሉትን የእግዚአብሔርን መንጋዎች ጠብቁ፤ ስትጠብቁአቸውም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ አይሁን፤ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘትም አይሁን፡፡" (ተጨማሪ ያንብቡ)

#ግብረ_ሐዋርያት
የሐዋ.1÷6-8
"እነርሱም ተሰብስበው ሳሉ÷ "ጌታ ሆይ÷ በዚህ ወራት ለእስራኤል ልጆች መንግሥትን ትመልሳለህን?” ብለው ጠየቁት፡፡ እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው÷ “አብ በገዛ ሥልጣኑ የወሰነውን ቀኑንና ዘመኑን ልታውቁ አልተፈቀደላችሁም፡፡ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኅይልን ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ሁሉ፣ በሰማሪያና እስከ ምድር ዳርቻ ድረስም ምስክሮቸ ትሆኑኛላችሁ።"

#ምስባክ
መዝ. 39÷8
"ከመ እንግር ፈቃደከ መከርኩ አምላኪየ፡፡ ወሕግከኒ በማዕከለ ከርሥየ፡፡ ዜኖኩ ጽድቀከ በማኅበር ዐቢይ፡፡"

ትርጉም፦ አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ለማድረግ መከርሁ፥ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው። በታላቅ ጉባኤ ጽድቅህን አወራሁ

#ወንጌል
ማቴ. 25÷14-30
“መንገድ እንደሚሄድ÷ አገልጋዮቹንም ጠርቶ ሊያተርፉበት ገንዘቡን እንደ ሰጣቸው ሰው እንዲሁ ይሆናልና፤ ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው ለአንዱ አምስት÷ ለአንዱ ሁለት÷ ለአንዱም አንድ ሰጠና ወዲያውኑ ሄደ፡፡” (ተጨማሪ ያንብቡ)

#የዕለቱ_ቅዳሴ ➛ ቅዳሴ ባስልዮስ
https://www.tg-me.com/sratebetkrstyane

       ❍ㅤ         ⎙          ⌲         ♡
  ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ      ˢᵃᵛᵉ      ˢʰᵃʳᵉ      ˡᶦᵏᵉ   
ሆሣዕና
የዐብይ ጾም ስምንተኛ እሑድ(ሳምንት)

ሆሣዕና ከጌታችን አምላካችን ከዘጠኙ ዓበይት በዓላት አንዱ ነው፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከኢየሩሳሌም ወደ  ቤተ መቅደስ ለመግባት በፈለገ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ፊታችው ባለው ሀገር "ሂዱና አህያ ከውርጭላዋ ጋራ ታስራ ታገኛላችው ፈታችው እምጡልኝ። 'ምን ታደርጋላችሁ?'  የሚላችሁ  ሰው  ካለ  'ጌታቸው  ይፈልጋቸዋል'  በሉ"  ብሎ  ላካቸው  ከዚህ  በኋላ  ደቀ  መዛሙርቱ እንዳዘዛቸው  ሄደው  ፈተው  አመጡለት  በዚያም  የተሰበሰቡት  ሁሉ  በአህዮች  ላይ  ልብሳቸውን  ጎዘጎዙለት  ጌታችንም በሁለቱ  አህዮች  ላይ  ተቀመጠ  ከሌሎቹ  እንስሳት  አህዮችን  መርጦ  በአህዮች  ተቀምጧል፡ አህዮች  በመጽሐፍ  ቅዱስ ብዙ ታሪክ አላቸውና።

የበልአም አህያ የመልአኩን ክብር ለመግለጥ አፍ አውጥታ ተናግራለች። (ዘሁል 22+28)
ጌታችን በተወለደ ጊዜ አህዮች ከከብቶች ጋር በበረት እስትፋሳቸውን ገብረዋል። (ቅዳሴ ማርያም)
የሆሣዕና እህዮች ከሁሉ ተመርጠው አምላካችን ተቀምጦባቸዋል: 'ለምን የተዋረዱት አህዮችን መረጠ?' ቢባል:-
፩. ደመናን አዝዞ : ነፋስን ጠቅሶ : በእሳት  መንኮራኩር ላይ የሚረማመድ አምላክ ሲሆን ነገር  ግን የመጣው ትሕትናን  ለማስተማር : የትሕትና  ጌታ  መሆኑን  ለመግለጽ ነውና በአህያ ተቀመጠ።
፪.  ትንቢቱን  ለመፈጸም  <<አንቺ  የጽዮን  ልጅ  ሆይ  እጅግ  ደስ  ይበልሽ  አንቺ  የኢየሩሳሌም  ልጅ  ሆይ  እልል  በዪ  እነሆ  ንጉሥሽ  ጻድቅና አዳኝ  ነው  ትሁትም  ሁኖ  በአህያም  በውርንጭላቱ  ላይ  ተቀምጦ  ወደ  አንቺ  ይመጣል  ሰረገላውንም  ከኤፍሬም ፈረሱንም ከኢየሩሳሌም ያጠፋል>> ብሎ ዘካርያስ ትንቢት ተናግሮ ነበርና ለመፈጸም ነው። ዘካ ፱÷፩
፫.  ምሳሌውን  ለመግለጽ
ምሳሌ-  ቀድሞ  ነቢያት  ዘመነ  ጸብእ  ከሆነ  በፈረስ  ተቀምጠው  ዘገር  ነጥቀው  ይታያሉ  ዘመነ  ሰላም  ከሆነ  በአህያ ተቀምጠው መነሳንስ ይዘው ይታዩ ነበርና ጌታችንም ዘመነ ሰላም ነው ሲል በአህያ ተቀምጦ መጥቷል።
፬.  ምሥጢሩን  ለመግለጽ
ምሥጢር-  በአህያ  የተቀመጠ  ሸሽቶ  አያመልጥም  አሳዶም  አይዝም  እሱም  ካልፈለጋችሁኝ  አልገኝም  ከፈለጋችሁኝ አልታጣም ሲል በአህያ ተቀምጦ መጥቷል።
ህድግት የእስራኤል ምሳሌ ህድግት ቀንበር መሸከም የለመደች ናት= እስራኤልም ህግ መጠበቅ ለምደዋልና
እዋል  የአህዛብ  ምሳሌ
እዋል  ቀንበር መሸከም አልለመደችም=አህዛብም ህግ መጠበቅ አልለመዱምና  (አንድም)  ህድግት  የኦሪት  ምሳሌ ህድግት ቀንበር መሸከም እንደለመደች=ኦሪትም የተለመደች ህግናትና
እዋል  የወንጌል ምሳሌ
እዋል  ቀንበር መሸከም አልለመደችም=ወንጌልም ያልተለመደች አዲስ ህግ ናትና
በሁለቱም ላይ መቀመጡ ኦሪትንም ወንጌልንም የሰራሁ እኔ ነኝ ሲል ነው፡፡ ከኢየሩሳሌም እስከ ቤተ መቅደስ ፲፮ ምእራፍ ነው ፲፬ቱን ምእራፍ በእግሩ ሂዶ ሁለቱን ምእራፍ በአህያይቱ ሂዷል በውርጭላይቱ ሁኖ ፫ ጊዜ ቤተ መቅደሱን ዙሯል ፲፬  ምእራፍ የአስርቱ  ትእዛዛትና  የአራቱ ኪዳናት ምሳሌ፤ አስሩ  ምእራፍ የአስርቱ ትአዛዛት፣ አራቱ  ምእራፍ የአራቱ ኪዳናት ምሳሌ ነው፣ አራቱ  ኪዳናት የሚባሉት እነዚህ ናቸው፦ ኪዳነ  ኖህ  :  ክህነተ  መልከ  ጼዴቅ  :ግዝረተ  አብርሀም  እና ጥምቀተ ዮንሐስ ናቸው፡፡
በአህያይቱ  ላይ ልብሳቸውን አንጥፈውለታል::
ልብስ  በአካል ያለውን ነውር ይሸፍናል አንተም ከባቴ አበሳ ነህ  ሲሉ።
በአህያዋ  ላይ  ኳርቻ  ሳያደርጉ  ልብስ  አንጥፈውለታል :-
ኳርቻ  ይቆረቁራል  ልብስ  አይቆረቁርም  የማትቆረቁር  ህግ ሰራህልን  ሲሉ  ነው። 
ስለምን ልብሳቸውን አነጠፉለት ቢባል ? በእዩ  ልማድ ነው ፡
እዩ  የተባለው  ሰው  በእስራኤል  ላይ  ሲነግሥ  እስራኤል  ልብሳቸውን  አንጥፈውለት  ነበረና  በዚያ  ልማድ አንጥፈውለታል እኩሌቶቱ ደግሞ ዘንባባ አንጥፈውለታል ። 🌴
በዕለተ  ሆሳዕና  እስራኤላውያን  ለምን  የዘንባባ  ዝንጣፊ፤  የቴምር  ዛፍ  ዝንጣፊ  እና  የወይራ  ዛፍ  ዝንጣፊ  ይዘው  ዘመሩ?  (ማቴ. ፳፩÷፩-፲፯፣  ማር. ፲፩÷፩-፲፣  ሉቃ.  ፲፱÷፳፱-፴፰፣  ዮሐ. ፲፪÷፲፪-፲፭)
የዘንባባ ዝንጣፊ
ዘንባባ የድል ምልክት የደስታ መግለጫ የምስጋና መስጫ ነው፡፡
✔️ይስሃቅ  በተወለደ  ጊዜ  አብርሃም ደስ ብሎት ዘንባባ ይዞ እግዚአብሄርን አመስግኖበታል።
✔️ይስሐቅም ያእቆብን በወለደ ጊዜ    አምላኩን በዘንባባ አመስግኗል።
✔️እስራኤል  ከግብጽ  በወጡ  ጊዜ  በዘንባባ  ንሴብሆ  እያሉ  እህተ  ሙሴ  ማርያም  ከበሮ  እየመታች  አምላካቸውን አመስግነዋል፡፡
✔️ዮዲት  እስራኤልን  እየገደለ  ያስቸገረው  ሆለፎርኒስን  አንገቱን  ቆርጣ  በገደለችው  ጊዜ  እስራኤል  ዮዲት  መዋኢት  ዮዲት ኀያሊት  ብለው በዘንባባ አመስግነዋታልና።
ዘንባባ ደርቆ እንደገና ህይወት ይዘራል የደረቀ ሕይወታችንን የምታለመልም አምላክ ነህ ሲሉ ነው።
ዘንባባ የሰላም ምልክት ነው የሰላም አምልክ ነህ ሲሉ ነው።
ዘንባባ እሾሃማ ነው አንተ ህያው አሸናፊ አምላክ ነህ ሲሉ ነው።
ዘንባባ እሳት አይበላውም ለብልቦ ይተወዋል እንጅ ጌታም አንተ ባህርይህ የማይመረመር ነው ሲሉ ነው።
ዘንባባ  የነፃነት  ምልክት  ነው  ከባርነት  ነፃ  የምታወጣን  አንተነህ  ሲሉ  ነው  አኛም  ይህን  በማሰብ  ዘንባባ  ይዘን ሆሳእና  በአርያም  እያልን እለቱን  እናስባለን፡፡
የቴምር ዛፍ ዝንጣፊ
የቴምር ዛፍ ፍሬ ጣፋጭ ነው፦ በሃጥያት የመረረውን ህይወታችንን የምታጣፍጥልን አምላክ ነህ ሲሉ ነው።
የቴምር  ፍሬ  የሚገኘው  ከዛፉ  ከፍታ  ላይ  ነው:-  አንተ  አምላካችን  ልዑለ  ባህሪ  ነህ  ከፍ  ከፍ  ያልክ  አምላክ  ነህ  ሲሉ ነው።
የቴምር ዛፍ ፍሬ በውስጡ ያለው ፍሬ አንድ ነው አንድ አካል አንድ ባህሪ ነህ ሲሉ ነው።
የቴምር ፍሬ በእሾህ የተከበበ ነው ይህም የአንት ባህሪ የማይመረመር በእሳት የተከበበ ነው ሲሉ ነው።
የወይራ ዛፍ ዝንጣፊ
የወይራ ቅጠል የሰላም ማብሰሪያ ነው ሰላማችንን የምታበስርልን የምታስገኝልን አንተ ነህ ሲሉ ነው፡፡
የወይራ ቅጠል ከእንጨት ሁሉ ጽኑ ነው አንተም ጽኑ ሃያል አምላክ ነህ ሲሉ ነው።
ወይራ ለመብራት ያገለግላል ፍሬው ዘይት ያወጣል ከወይራ የሚገኝ ዘይት ጨለማን አሸንፎ ብርሃን እንደሚሰጥ ሁሉ አንተም ጨለማ ህይወታችንን የምታስወግድልን አምላክ ነህ ሲሉ ነው።
በኦሪት ግዜ የወይራ ዘይት ለመስዋአትነት ይቀርብ ነበር አንተም እንደ ዘይቱ ለመተላለፋችን መስዋዕት ሆነህ የምትቀርብ አምላክ ነህ ሲሉ ነው። በመስቀል ላይ መስዋዕት ሆኗልና።
ከፊት ከኋላ ያሉት "ሆሣዕና በዓርያም ለዳዊት ልጅ መድኀኒት መባል ይገባዋል" እያሉ አመስግነውታል የምስጋና ጌታም በአህዮች ተቀምጦ ወደ መቅደስ ገብቷል።

በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ ጥቅሶች
-ዕብ ፱፥፲፩ እስከ ፍጻሜ
-፩ጴጥ ፬፥፩-፲፪
-ሐዋ ፳፰፥፲፩ እስከ ፍጻሜ

ምስባኩም፦ መዝ፰፥፪
"እመ አፈ ደቂቅ ወሕጻናት አስተዳሎከ ስብሐተ በእንተ ጸላኢ ከመትንሥቶ ለጸላዒ ወለገፋዒ"
"ከሕጻናት አንደበት ምስጋናን አዘጋጀህልኝ፡፡ ስለ ጠላትና ቂመኛን ለማጥፋት"

ወንጌሉም፦ ዮሐ፭፥፲፩-፲፫
ቅዳሴ ፦ ዘጎርጎርዮስ (ነአኵቶ)[በዕዝል ዜማ]

https://www.tg-me.com/sratebetkrstyane
የሰሙነ ሕማማት ሰኞ፡-

መርገመ በለስ የተፈጸመበት ዕለት ነው፡

ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሆሣዕና ዕለት ቢታንያ አድሮ በማግሥቱም ከቢታኒያ ሲመጡ ተራበ፡፡ (ማር.11፤11-12) ቅጠል ያላት በለስ ከሩቅ አይቶ ወደ በለሲቱ ቀረበ፤ ነገር ግን ከቅጠል በቀር አንዳች ፍሬ አላገኘባትም፡፡ ከአሁን ጀምሮ ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ ብሎ ረገማት። በለስ የተባለች ቤተ እስራኤል ናት፤ ፍሬ የተባለች ሃይማኖትና ምግባር ናት፤ ከእስራኤል ፍቅርን፤ ሃይማኖትን፤ ምግባርን ፈለገ አላገኘም፤ እስራኤል (ሕዝበ እግዚአብሔር) መባልን እንጂ፤ ደግ ሰው አይገኝብሽ ብሎ ረገማት፤ በመርገሙ ምክንያት እርሱ ከለያቸው በስተቀር ደግ ሰው ጠፋባት

በለስ ኦሪት ናት፤ ኦሪትን በዚህ ዓለም ሰፍና ቢያገኛት ኦሪትና ነቢያትን ልሽር አልመጣሁም ልፈጽም እንጂ በማለት ፈጸማት፤ ሕገ ኦሪትን ከመፈጸም በቀር በእርሷ ድኅነት አላደረገባትምና፤ ፍሬ በአንቺ አይሁን አላት፤ ደኅነት በአንቺ አይደረግብሽ ብሏታልና እንደመድረቅ ፈጥና አለፈች፡፡

በለስ ኃጢአት ናት፤ የበለስ ቅጠል ሰፊ እንደሆነች ሁሉ ኃጢአት በዚህ ዓለም ሰፍታ ሰፍና አገኛት፡፡ በለስ ሲበሉት ይጣፍጣል፤ ቆይቶ ግን ይመራል፤ ኃጢአትም ሲሰሩት ደስ ደስ ያሰኛል፤ ኋላ ግን ያሳዝናል፤ ወደ እርሷም ሄዶ ማለትም ከኃጥአን ጋር ዋለ፤ ኃጥእ ከመባል በቀር በአንደበቱ ሐሰት፤ በሰውነቱ ክፋት እንዳልተገኘበት ለማመልከት ፍሬ አላገኘባትም አለ፤ በአንቺ ፍሬ አይገኝ የሚለውም፤ በኃጢአት ፍዳ ተይዞ የሚቀር አይኑር ለማለት ነው፤ ስትረገም ፈጥና መድረቋም፣ በአዳም ምክንያት ያገኘችን ዕዳ በደል በእርሱ ካሣነት እንደጠፋችልን ለመግለጽ ነው፡፡

አንጽሆተ ቤተ መቅደስ የተፈጸመበት ዕለት ነው፦

ጌታችን በለስን ከረገማት በኋላ ወደ ቤተ መቅደስ ሄደ፤ ቤተ መቅደስ፣ ቤተ ጸሎት፣ ቤተ መሥዋዕት መሆኑ ቀርቶ ቤተ ምስያጥ (የንግድ ቤት) ሆኖ ቢያገኘው ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች፤ እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት ብሎ የሚሸጡበትን ሁሉ ገለበጠባቸው፤ ገርፎም አስወጣቸው፤ ይህም የሚያሳየው ማደሪያው ቤቱ የነበርን የአዳም ልጆች ኃጢአት ሰፍኖብን ስንኖር ቢያገኘን ኃጢአታችንን ሁሉ እንዳራቀልን የሚገልጽ ነው

በዚህ በሰሙነ ሕማማት ካህናትና ምእመናን በቤተክርስቲያን ተገኝተው ወዛቸው ጠብ እስኪል ድረስ በነግህ፤ በሠለስተ፣ በስድስቱ ሰዓት፤ በተሰዓቱ ሰዓትና በሠርክ መላልሰው ሲሰግዱና ሲጸልዩ ይሰነብታሉ፤ በተለይም ካህናት በማንኛውም አገልግሎት ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ፤ ምክንያቱም የደረሰብን መከራ ኀዘኑን እና 5ሺ ከ5መቶ ዘመን የሰው ልጅ በጨለማ ይኖር እንደነበረ ለማዘከር ነው

#ሼር
https://www.tg-me.com/sratebetkrstyane
​​​​ሥርዓተ ጸሎት ሰሙነ ሕማማት ከሰኞ እስከ ዕሮብ  ካህናት እያዜሙ እየሰገዱ እኛም እየተቀበልን እያዜምን የምንሰግድበትን   ሥርዓት ለማውቅ እና ለመፈፀም ከስር ያንብቡ

❖ የጸሎተ ሐሙስና የዕለተ ዓርብ ሥርዓተ ጸሎት

👉 ከሰኞ ጀምሮ እስከ ዓርብ ድረስ ባሉት ቀናት ውስጥ  በመጀመሪያ ዲያቆኑ ቤተ ክርስቲያኑን ሦስት ጊዜ ዞሮ ደወል ካሰማ በኋላ መቶ አምሳው ዳዊት ይታደልና ይደገማል፡፡ የሰባት ቀናት ውዳሴ ማርያምና አንቀጸ ብርሃን  እስከ ይዌድስዋ  ድረስ ታድሎ ይደገማል፡፡ ከዚያም “እንበለ ደዌ ወሕማም እንበለ ጻማ ወድካም ዓመ ከመ ዮም ያብጽሐኒ ያብጽሕክሙ አግዚአብሔር በፍሥሓ ወበሰላም” ተብሎ አቡነ ይደገምና  በዐራቱም ወንጌላት መሠረት ለእያንዳቸው በእየዕለቱና  ሰዓቱ የተመደበውን አቡነ ካህናቱ በቀኝና በግራ እየተፈራረቁ  ይመራሉ፡፡ ካህናቱና ሕዝቡም ይቀበላሉ፡፡ በመቀጠል፡- (ትእዛዝ፡ ሕዝቡ በጸሎት በተሰበሰቡ ጊዜ ጠዋት ወይም በ3፣ በ6፣በ9፣ በ11ሰዓተ መዓልት መጀመሪያ ሕዝቡ እየሰገዱና እየተከተሉ እንዲህ ይበሉ፡፡ )

✥ "ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ ለዓለመ ዓለም ፡፡"

✥ "አማኑኤል አምላኪየ ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ ለዓለመ ዓለም፡፡"

✥ " ኦ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ ለዓለመ ዓለም፡፡ "
✥ " ኃይልየ ወጸወንየ ውእቱ እግዚእየ፤ እስመ ኮንከኒ ረዳእየ እብል በአኰቴት ፡፡"

ትእዛዝ፡ በዚህ ጊዜ ካህኑ እየተከተሉ አቡነዘበሰማያት ይድገሙ ።
ይህን የላይኛውን ጸሎት እያመላለሱ ከአቡነ ዘበሰማያት ጋር 12 ጊዜ ይበሉ

❖ " ለአምላክ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም፡፡

❖ "ለሥሉስ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም"፡፡

❖ "ለማሕየዊ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም"፡፡

❖ "ለዕበዩ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም"፡፡

❖"ለእዘዙ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም"፡፡

❖ "ለመንግሥቱ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም"፡፡

❖ "ስለልጣኑ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም"፡፡

❖ "ለኢየሱስ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም"፡፡

"ለክርስቶስ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም"፡፡

❖ "ለሕማሙ  ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም"፡፡

❖ "ለመስቀሉ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም፡፡ "

ትእዛዝ፡- ይህ ሦስት ጊዜ እየተመላለሰ ይባላል፡፡በመጨረሻም የሚከተለውን ሦስት ጊዜ እያመላለሱ ይበሉ፡፡

❖ "ለከ ይደሉ ኃይል፣ ወለከ ይደሉ ስብሐት ወለከ ይደሉ አኰቴት ኦ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለመ ዓለም"

ትእዛዝ፡- ካህኑ ‹ጸልዩ በእንተ ጽንዓ ዛቲ . . .› ብሎ በሚያነብ ጊዜ በየምዕራፉ "እግዚኦ ተሳሃለነ" እየተባለ ይሰገዳል፡፡

ትእዛዝ፡- ከዚህ ሁሉ በኋላ ሕዝቡ የሚከተሉትን ጸሎት በግራና በቀኝ ይበሉ፤

"ክርስቶስ አምላክነ፤ ዘመጽአ ወሐመ በእንቲአነ በሕማማቲሁ ቤዝወነ፤  ንሰብሖ ወናልዕል ስሞ ኅቡረ፤ እስመ ውእቱ ገብረ መድኃኒተ በዕበየ ሣህሉ" (በዐርብ) ዘሐመ ወሞተ በእንቲአነ ይባላል፡፡

ትእዛዝ፡- ቀጥሎም ሕዝቡ በሁለት ክፍል ሆነው የሚከተለውን ጸሎት ሁለት ጊዜ በመከታተል አንድጊዜ በማስተዛዘል ይበሉት፡፡

ኪርያላይሶን፤ኪርያላይሶን፤
#ኪርያላይሶን፤ኪርያላይሶን፤ኪርያላይሶን፤ ኪርያላይሶን፤ኪርያላይሶን፤

#አብኖዲ  ኪርያላይሶን፤
ኪርያላይሶን፤ኪርያላይሶን

#ናይን፣ኪርያላይሶን፤
ኪርያላይሶን፤ኪርያላይሶን ፤

#ታዖስ ናይን፣ ኪርያላይሶን፤
ኪርያላይሶን፤ኪርያላይሶን፤

#ማስያስ ናይን፣ ኪርያላይሶን፤
ኪርያላይሶን፤ኪርያላይሶን፤

#ኢየሱስ ናይን፣ ኪርያላይሶን፤
ኪርያላይሶን፤ኪርያላይሶን፤

#ክርስቶስ ናይን፣ ኪርያላይሶን፤
ኪርያላይሶን፤ኪርያላይሶን፤

#አማኑኤል ናይን፣ ኪርያላይሶን፤
ኪርያላይሶን፤ኪርያላይሶን፤

#ትስቡጣ ናይን፣ ኪርያላይሶን፤
ኪርያላይሶን፤ኪርያላይሶን

ትእዛዝ፡- ከዚህ በኋላ ኪርያላይሶን አርባ አንድ ጊዜ ይባላል፡፡

ይኸውም  በአንድ ወገን 20 ጊዜ በሌላው ወገን 21 ጊዜ በጠቅላላው 41 ጊዜ ኪርያላይሶን  ኪርያላይሶን  ኪርያላይሶን  እየተባለ ይሰገዳል፡፡

በመጨረሻ ጊዜ፡-

✥ ስብሐት ለእግዚአብሔር ኪያነ ዘፈጠረ ከመ ናምልኮ (እናመልከው ዘንድ ለፈጠረን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይገባል)፡፡

✥ ስብሐት ለማርያም እመ አምላክ እግእዝትነ ወመድኃኒትነ (እመቤታችንና መድኃኒታችን ለሆነች ለአምላክ እናት ለማርያም ምስጋና ይገባል)፡፡

✥ ስብሐት ለመስቀለ ክርስቶስ ዕፀ መድኃኒት ኃይልነ ወፀወንነ(ኃይላችን መጠጊያችን ለሆነ ድኅነት ለተገኘበት ለክርስቶስ ምስጋና ይገባል)፤፤ ጸሎተ ሃይማኖትን ሐመ  እስከ ሚለው ድረስ መድገም ነው፡፡  /ከሰኞ እስከ ረቡዕ ይባላል/

#ሼር
https://www.tg-me.com/sratebetkrstyane
🔴 #ማክሰኞ_የትምህርት_እና_የጥያቄ_ቀን

ይህ ቀን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰኞ በተናገረው ባደረገው ላይ አይሁድ ጥያቄ ያቀረቡበት እርሱም መልስ በመስጠት ያስተማረበት ዕለት ነው በዚህም ምክንያት የጥያቄ እና የትምህርት ቀን በመባል ይታወቃል፡፡

ሰኞ ቀን ጌታችን በረገማትን በለስ  መድረቅ ሐዋርያት ሲደነቁ እምነት ያለው ሰው ሁሉን ማድረግ እንደሚችል ያስረዳበት ዕለት ነው፡፡
‹‹ ማለዳም ሲያልፉ በለሲቱን ከሥርዋ ደርቃ አዩአት ጴጥሮስም ትዝ ብሎት መምህር ሆይ፥ እነሆ፥ የረገምሃት በለስ ደርቃለች አለው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ በእግዚአብሔር እመኑ እውነት እላችኋለሁ፥ ማንም ያለው ነገር እንዲደረግለት ቢያምን በልቡ ሳይጠራጠር፥ ይህን ተራራ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ቢል ይሆንለታል። ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ይሆንላችሁማል ለጸሎትም በቆማችሁ ጊዜ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁ ደግሞ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁ፥ በማንም ላይ አንዳች ቢኖርባችሁ ይቅር በሉት። እናንተ ግን ይቅር ባትሉ በሰማያት ያለው አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም። ››ማር 11፥20-26 እያለ ያስተማረበት ዕለት ስለሆነ የትምህርት ቀን ይባላል

ሌላው ይህ ዕለት ጌታችን  ሰኞ ዕለት  ካደረጋቸው ነገሮች ተነስተው አይሁድ ጥያቄ ያቀረቡበት ዕለት ነው
‹‹ ወደ መቅደስም ገብቶ ሲያስተምር የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሎች ወደ እርሱ ቀረቡና በምን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ? አሉት። ኢየሱስም መልሶ፦ እኔ ደግሞ አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፤ እናንተም ያችን ብትነግሩኝ እኔ ደግሞ እነዚህን በምን ሥልጣን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ፤ የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች? ከሰማይ ወይስ ከሰው? አላቸው። . . . ›› /ማቴ 21 ፥23- 27/
ይህ ጥያቄ ጌታችን ሲያደርጋቸው የነበሩ ተአምራትና ድንቅ ድንቅ ሥራዎች የካህናት አለቆችን ስላስቀኗቸው ጌታችንን ከሮማ መንግሥት ባለ ሥልጣናት ጋር ለማጋጨት የቀረቡት ጥያቄ ነበር ጌታችን በቤተ መቅደስ የነበረውን ገብያ ስለበተነው የነጋዴዎቹን  መደባቸውን ስለገለበጠ ነጋዴን ማባረርና መደብን ማስለቀቅ መንግሥታዊ ሥራ ነውና በማን ሥልጣን አደረከው ብለው ጠየቁት ጌታችን ‹‹በራሴ ሥልጣን›› ቢላቸው ጸረ መንግሥት አቋም አለው በማለት ከሮማ መንግሥት ዘንድ ለማሳጣት ነበር ዕቅዳቸው
ጌታችን ግን የፈሪሳውያንን ጠማማ አሳብ ስለሚያውቅ ‹‹የዮሐንስ ጥምቀት ከየት ነው? ከሰማይ ነው ወይስ ከምድር?›› ሲል ጠይቋቸዋል፡፡ ጌታችን ፈሪሳውያን ላቀረቡለት ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ አልሰጠም ምክንያቱም ጥያቄው ለከሳሾቹ ዓላማ መሳካት አመቺ ሁኔታን ስለሚፈጥር ጥያቄውን በጥያቄ መልሶላቸዋል፡፡ እነርሱም ‹‹ከሰማይ ነው›› ቢሉት ‹‹ለምን አላመናችሁበትም?›› እንዳይላቸው፤ ‹‹ከሰው ነው›› ቢሉት ደግሞ ሕዝቡ ዮሐንስን እንደ አባት ይፈሩት፣ እንደ መምህር ያከብሩት ነበርና ሕዝቡ እንዳይጣሏቸው ስለፈሩ ‹‹ከወዴት እንደ ሆነ አናውቅም›› ብለው መለሱለት፡፡ እርሱም ‹‹እኔም በማን ሥልጣን እነዚህን እንደማደርግ አልነግራችሁም›› አላቸው ከዚህ ታሪክ የተነሳ ይሄ ቀን የጥያቄ ቀን ይባላል፡፡
https://www.tg-me.com/sratebetkrstyane
ከትንሳኤ በኋላ ያሉ ዕለታት
        ማክሰኞ
ቶማስ ይባላል
እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ሲፈጥረው የሚያንቀላፋና የሚነቃ አድርጎ ፈጥሮታል፡፡
ማንቀላፋቱ የሞት ፤ መንቃቱ ደግሞ የትንሣኤ ምሳሌ መሆኑን ስናስብ ሁሌም ይደንቃል፡፡ አባቶቻችን የትንሣኤውን ምሥጢር በአበው እና በስነፍጥረትም ይመስሉታል፤ አቤል ከሞተ በኋላ በደሙ መናገሩ እና የሔኖክ ሳይሞት በእግዚአብሔር መሰወሩ የትንሣኤ ምሣሌ ናቸው፡፡ በተፈጥሮ ፀሐይ መውጣቷ የመወለዱ ፤ መጥለቋ የሞቱ እና ዳግመኛ መውጣቷ የትንሣኤው ምሣሌ ነው፡፡
አምላካችን ክብር ይግባውና በእርሱ ያመንን ሁላችን እንደምንነሳ የእርሱ ከሙታን መካከል በሥልጣኑ መነሳት ለሁላችን መነሳት በኩር መሆንና ማረጋገጫም እንደሆነ በቃሉም በተግባሩም ያስተማረን የትንሣኤ ጌታ ነው፡፡
በቃሉ "በመቃብር ያሉት ሁሉ ድምጹን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል ፤ መልካም
ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ፤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ " (ዮሐ፭፡፳፱) እንዲሁም በተግባር የአራት ቀን ሬሳ አልዓዛርን አስነስቷል፡፡(ዮሐ፲፩፡፵፫)
የትንሣኤው ምሥጢር ሁላችን አምላክ የሆንበት ፤ በሁሉ ላይ ሥልጣን ያገኘንበት ፤ነጻ ወጥተን ነጻ አውጪ የሆንበት ፤ ከማይጠፋ ዘር እንደተወለድን ያረጋገጥንበት ፤ ሞትን የተዘባበትንበት ፤ ጨለማን የረታንበት ከዓለም እና ከዲያብሎስ እስራት ነጻ የወጣንበት ልዩ ክብር ኃይል እና ጸጋን ያገኘንበት ምሥጢር ነው፡፡

ይህቺ ዕለትም ይህንኑ ምሥጢር ነው የምትገልጥልን ሐዋርያው #ቶማስ ተብሎ ለምን ተሰየመ የሚለውን ከማየታችን በፊት ማነው የሚለውን ማየት ነገርን ከስሩ እንድንረዳው ይረዳናልና እውነት ሐዋርያው ቶማስ ማነው?
       ሐዋርያው ቶማስ
ሐዋርያው ቶማስ የስሙ ትርጓሜ ፀሐይ ማለት ሲሆን የቀድሞ ስሙ ዲዲሞስ ይባላል ትርጉሙም ጨለማ ማለት ነው፡፡ ቁጥሩ ከ፲፪ ሐዋርያት ነው፡፡ (ማቴ፲፡፫)
(መዝገበ ታሪክ ክፍል ሁለት ገጽ፹፱) ፤ ሐዋርያ ማለት ደጅ አዝማች ፤ ቀላጤ ፤ ምጥው ፤ ፍንው ፤ ሂያጅ ማለት ነው፡፡(ወንጌል ቅዱስ ገጽ፻፶፱)
ሐዋርያው ቶማስ አልዓዛር በሞተ ጊዜ ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም አቅራቢያ ወደነበረው መቃብሩ ለመሄድ በተነሳ ጊዜ አይሁድ ሊገሉት ስለሚፈልጉ ሌሎቹ ሐዋርያት ክርስቶስ እንዳይሄድ ቢፈልጉም ቶማሰ ሌሎቹን ሐዋርያት በድፍረት እኛም ከእርሱ ጋር እንሞት ዘንድ አብረን እንሂድ ያለ የእምነት ሐዋርያ ነው፡፡ (ዮሐ፲፩፲፮)
ሐዋርያው ቶማስ ጌታችንን በእውነት እስከ ሞት ድረስ ያመነው ከሙታን ተለይቶ ከተነሳ በኋላ በ8ኛው ቀን እሁድ ሲሆን ሐዋርያት የነገሩትን ካላየው አላምንም ብሎ የተወጋ ጎኑን ከዳሰሰ በኋላ ነው፡፡ የእምነት ምስክርነቱም ጌታዬ አምላኬም ብሎ የገለጠው፡፡(ዮሐ፳፡፳፬)
ሐዋርያው ቶማስ መንፈስ ቅዱስን ከሐዋርያት ጋር ከተቀበለ በኋላ በ፵፮ ዓ.ም ገደማ በፋርስና በሕንድ እንዳስተማረ የተለያዩ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ይገልጣሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናንዙ ፤ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ፤ ቅዱስ አምብሮስ ተጠቃሾች ናቸው፡፡በመጨረሻም ብዙ ተአምራት እና ድንቅን አድርጓል፡፡ የሐዋርያው ቶማስ ተአምር እና አገልግሎት ብዙ ተአምራትን ቢያደርግም ለአሁኑ አንዱን ብቻ እናያለን፡፡ የኸውም የሉክዮስ አገልጋይ ሆኖ በሕንጻ ማነጽ እና በሐውልት መስራት ተቀጥሮ በሚሰራበት ወቅት የሉክዮስን ሚስት ከእነ ልጆቿ እና አገልጋዮቿ አሳምኖ ያጠመቀ ሐዋርያ ነው፡፡
ሐዋርያው ቶማስ ለሕንጻ እና ለሐውልት ማሰሪያ ከሉክዮስ የተቀበለውን ገንዘብና ወርቅ ሁሉ ለነዳያን በመመጽወቱ ንጉሡ እጅና እግሩን አሥሮ ቆዳውን አስገፍፎ ስልቻ አሰፍቶ በአሸዋ ሞልቶ አሸክሞት ገበያ ለገበያ ሲያዞረው የሉክዮስ ሚስቱ አርሶንዋ ተመልክታ በድንጋጤ ሞታለች፡፡ ንጉሡም ለሚስቴ መሞት ምክንያት አንተ ነህ ካዳንካት እኔም በአምላክህ አምናለው ሲለው ጌታችን ቁስሉን እንደ ውኃ አቀዝቅዞለት ካለችበት ሄዶ ስልቻውን ቢያስነካት ተነስታለች በዚህም ሉክያኖስ አምኖ ተጠምቋል፡፡
ሐዋርያው ቶማስ በራሱ ቆዳ በተሰራ ስልቻ እየተዘዋወረ ሙት አስነስቷል ፤ ድውያንን ፈውሷል አሕዛብን አሳምኖ አጥምቋል ፤ በቀንጦፍያ አንድ ሽማግሌ ሰባት ልጆቹን ገድለውበት ሰባቱንም ከሞት አስነስቷል ፤ በኢናስም በቃሉ ትምህርት እና በእጁ ተአምራቱ ብዙዎችን አሳምኖ አጥምቋል፡፡
    የሐዋርያው ቶማስ ሰማእትነት
በሕንድ የነበሩት የብራሕማን እምነት ተከታዮች የቶማስ ትምህርት የእነርሱን እምነት የሚጻረር እና የሚያጠፋ መሆኑን ተገንዝበው ተነሱበትና በብዙ ስቃይ አሠቃይተው በ፸፪ዓ.ም በሰማዕትነት አርፏል፡፡ በሶርያ ትውፊት መሠረት የሐዋርያው የቶማስ አጽም በአንድ የሶርያ ነጋዴ ተወስዶ በኤዴሳ በክብር አርፏል፡፡ (የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ በምድር ላይ አንደኛ መጽሐፍ ገጽ ፺፪)
  ሐዋርያው ቶማስ ለምን ሰምቶ አላመነም?
እንደ ወንጌል ትርጓሜ ሐዋርያው ቶማስ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዝግ ቤት ገብቶ ሰላም ለእናንተ ይሁን ባለ ጊዜ አልነበረም ፤ በነገሩት ጊዜም አላመነም ያለማመኑ ምክንያት ሰዱቃዊ ስለነበር እና ሐዋርያቱ አይተው እርሱ ሰማው ብሎ ከሚያስተምር ማየት ወዶ ነው፡፡
    
     "ጌታዬ አምላኬም" (ዮሐ፳:፳፰)
https://www.tg-me.com/sratebetkrstyane
   
​​እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

#መዝ. 86፥1
“መሠረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳን፡- መሠረቶቿ የተቀደሱ ተራሮችናቸው”

ዮም ፍሥሐ ኮነ በእንተ ልደታ ለማርያም በእመቤታችን ልደት ምክንያትዛሬ ደስ ሆነ፡፡

በግንቦት 1 ቀን 5ሺ ከ5መቶ የመከራው ዘመን ሊያልቅ 15 ዓመታት ሲቀሩት/ ሊባኖስ በሚባል ተራራ ከፀሐይ  የምታበራ ሴት ልጅ ተወለደች፡፡

ይህቺውም ፍጥረት ሁሉ ደቂቀ አዳም ሁላቸው ተስፋ ሲያደርጓትና ሲጠባበቋት የነበረች የድኅነታቸው ምልክት እመቤታችን ናት፡፡

ሶሪያዊው ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬምም 
“አክሊለ ምክሕነ ወቀዳሚተ መድኀኒትነ፡፡ወመሠረተ ንጽሕነ ኮነ በማርያም ድንግል:- የመመኪያችን ዘውድ የደኅንነታችን  መጀመሪያ የንጽሕናችንም መሠረት በድንግል ማርያም ሆነልን” በማለት መናገሩ ስለዚህ ነው፡፡

አክሊል ምክሐነ አላት ይህም አክሊል የወዲህኛው፣ ምክሕ የወዲያኛው ነው። ከነገሥታት መካከል እንደ ዳዊት የከበረ የለም።

ምንም እንኳን ቅዱስ ዳዊት የከበረ ቢሆን የመመኪያችንን ዘውድ ማምጣት አልተቻለውም፡፡

ወቀዳሚተ መድኀኒትነ አላት፡- ቀዳሚተ የወዲህኛው መድኀኒት የወዲያኛው ነው፡፡ከመሳፍንት ወገን የሚሆን ኢያሱ ምንም የስሙ ትርጓሜ መድኃኒት ቢሆን የደኅንነታ መሆን አልተቻለውም፡፡

ወመሠረተ ንጽሕነ አላት:- መሠረት የወዲህኛው፤ ንጽሕ የወዲያኛው ከነቢያተ እግዚአብሔር ወገን የሚሆን ኤልያስ በድንግልና በንጽሕና መኖሩ የሚታወቅ ነው፡፡ 

ነገር ግን ምንም ንጹሕ ድንግል ቢባል የንጽሕናችንመሠረት መሆን አልተቻለው።

የመመኪያችን ዘውድ፣ የደኅንነታችን መጀመሪያ፤ የንጽሕናችን መሠረት ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፤” በማለት ተናግሯል።

በእርሷ ምክንያትነት መድኀኒዓለም  የሚፈጽምልንን ካሳነቢያትና የቀደሙ አበው ሁሉ 
የእርሷን መወለድ በናፍቆት ሲጠባበቁ ነበር።

ከነቢያት አንዱ የሆነ  ኢሳይያስም
“የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርዘርን ባያስቀርልን 
ኖሮ እንደ ሰዶም በሆንነ  እንደ ጎሞራም በመሰልነ ነበር፡፡” በማለት መናገሩ በእርሷ መገኘት  ከጥፋት መዳናችንን ሲገልጽ ነው፡፡ 
#ኢሳ 1፥9
የቦንጋ ፈ/ሕ/አቡነ ተክለሃይማኖት የበገና ት/ቤት ትምህርት ክፍል ።
https://www.tg-me.com/sratebetkrstyane
🤑💵 🇫 🇴 🇷 🇪 🇽 𝗧𝗿𝗮𝗱𝗶𝗻𝗴 መማር የምትፈልጉ አንድ የሚገርም የ Forex  ቻናል ያውቃሉ

💶  𝗖𝗶𝘁𝘆 𝗙𝗼𝗿𝗲𝘅 𝗘𝘁𝗵𝗶𝗼𝗽𝗶𝗮 💶

@CityForexEthiopia ይባላል ።
ተመዝገባችሁ መማር የምትፈልጉ አናግሯቸው እስከ 𝟰𝟬% Discount የሚደርስ ቅናሽ አድርገዋል !

    ☎️   +251977338586       🇪🇹
    ☎️   +251977338586       🇪🇹

ይህን ይጫኑ የ Telegram ቻናላቸውን ለማግኝት  👇👇

https://www.tg-me.com/+haUXQMQqaqFjNDc8
https://www.tg-me.com/+haUXQMQqaqFjNDc8
https://www.tg-me.com/+haUXQMQqaqFjNDc8


👆👆👆👆👆👆👆👆👆👆👆👆👆

🎯 𝗔𝗱𝗱 𝗬𝗼𝘂𝗿 𝗖𝗵𝗮𝗻𝗻𝗲𝗹
2024/05/09 16:55:18
Back to Top
HTML Embed Code: