Telegram Web Link
#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል አስራ ሰባት)
(ሜሪ ፈለቀ)

የምጣደፈው ጎንጥን ሽሽት ይሆን ኪዳንጋ ለመድረስ ተቻኩዬ ወይም በሁለቱም ምክንያት የታክሲው ሹፌር ትዕግስቱን እስኪያንጠፈጥፍ ድረስ አቻኩለው ጀመር። <ምን ያህል ቀረን?> ፤ <ትንሽ ፈጠን ማለት አትችልም?> ፤ < ሌላ ያልተዘጋጋ አማራጭ መንገድ አይኖርም?> ፤ < አሁንም ብዙ ይቀረናል?> አንድ አይነት ጥያቄ በየሁለት ደቂቃው እየደጋገምኩ ፤ ግማሽ ጎኔ ወደፊት ግማሽ ጎኔ ወደኋላ በሆነ አቀማመጥ ፤ በአንድ ዓይኔ ወደኪዳን (ወደፊት) በአንድ ዓይኔ ወደጎንጥ (ወደኋላ) ሳማትር

«ሴትዮ ካልሆነ ውረጂ እና ሌላ ታክሲ ተሳፈሪ! አይታይሽም እንዴ በማይነዳበት እየነዳሁልሽ? ሆ! ዛሬ ምኗን ነው የጣለብኝ ባካችሁ?» አለ ያለመታከት ሲመልስልኝ ቆይቶ ከትዕግስቱ በላይ ስሆንበት

«ይቅርታ በጣም ስለቸኮልኩ ነው። ይቅርታ በቃ እንደሚመችህ አድርገህ ንዳ!!» አልኩኝ። ታክሲው ውስጥ በቦርሳ የያዝኩትን የቱታ ሱሪ ከቀሚሴ ስር ለብሼ ሳበቃ ቀሚሴን አውልቄ ወደቦርሳው ከተትኩ።

እያደረግኩት ያለሁት ድፍረት ይሁን ድድብና መመዘን የምችልበት መረጋጋት ላይ አልነበርኩም። ምናልባት አለማወቅ ደፋር ያደርግ ይሆናል ወይም ደደብ!! ጎንጥ ሰዎቹን ስለሚያውቃቸው ይሆናል የሚጠነቀቀው እና የሚፈራልኝ። የማላውቀውን ሰው ወይም ልገምት የማልችለውን የሚገጥመኝን ነገር በምነኛው መጠን ልፈራ እችላለሁ? እስከገባኝ ድረስ ቢያንስ አለማወቄ ጎንጥን እስከአለመከተል ድረስ ደፋር ወይም አላዋቂ አድርጎኛል።

የተባለው ቦታ ስደርስ ለቀጠሯችን 20 ደቂቃ ይቀረኛል። ከታክሲው ከወረድኩ በኋላ እንደማንኛውም በአካባቢው እንዳለ ተንቀሳቃሽ ግለሰብ የአዘቦት ክንውን እየከወንኩ ለመምሰል ጣርኩ እንጂ እንደሌባ ዓይኖቼም አካሌም እየተቅበጠበጠ ነበር። እስከዚህ ደቂቃ ያልተሰማኝ ፍርሃት አጥንቴ ድረስ ዘልቆ ይገለባበጥ ጀመር። መቆምም መራመድም መቀመጥም ሰው ይቸግረዋል? ወደላይ ትንሽ ራመድ እልና ደግሞ በተቃራኒው አቅጣጫ እመለሳለሁ። በመሃል እንደማቅለሽለሽም ያደርገኝና መሃል የእግረኛ መንገድ ላይ ቁጢጥ እላለሁ። ከመንበጭበጬ ብዛት ሽንቴን እላዬ ላይ የምለቀው መሰለኝ። ሰዓቴን በ60 ሰከንድ ውስጥ 120 ጊዜ አያለሁ። ደቂቃው ሰዓቴ መስራቱን ያቆመ ይመስል ፈቅ አይልም። ለአፍታ የጎንጥ እጅ ናፈቀኝ። ወላ ተከትሎ ደርሶብኝ በሆነና የፈራሁ ሲመስለው ሁሌም እንደሚያደርገው በዛ ሰፊ መዳፉ እጄን አፈፍ አድርጎ እጁ ውስጥ ቢደብቀው። «……. እኔ የት ሄጄ? …… ማን አባቱንስ እና ነው? » ቢለኝ። ሜላት ምንድነው ያደረግሽው?

የምጠብቀው እንዲህ ነበር። የሆነ ቀን እንዳየሁት የሆነ ፊልም። ጥቁር መኪና መጥቶ አጠገቤ ገጭ ብሎ ይቆምና ! በሩ ብርግድግድ ብሎ በተጠና ስልት ሲከፋፈት ፊታቸው የማይታዩ መሳሪያ የታጠቁ ግባብዳ ሰዎች ከመኪናው ዱብ ዱብ ብለው ያስቀመጡትን የሆነ ሻንጣ ብድግ እንደማድረግ ብድግ አድርገውኝ እየጮህኩ እግሬ አየር ላይ ተንጠልጥሎ ስፈራገጥ ምንም ሳይመስላቸው ወደመኪናው ይወረውሩኝና ልክ እንደቅድሙ በተጠና መንገድ በሩን ድው ድው አድርገው ዘጋግተው ይዘውኝ ይሄዳሉ።

የሆነው እንዲህ ነው። እግሬን ብርክ ይዞት ጉልበቴን ደገፍ ብዬ ባጎነበስኩበት አንዲት ቆንጅዬ ጅንስ ሱሪ በቲሸርት ለብሳ አጭር ጥቁር ጃኬት የደረበች ወጣት ሴት ከጀርባዬ ጠራችኝ። «ሜላት!» ለሰላምታ እጇን ዘረጋችልኝ። እነሱማ ሰላም ሊሉኝ አይችሉም ብዬ እያሰብኩ እጄን ዘረጋሁ!!

«ዝግጁ ነሽ?» ስትለኝ ማሰቢያዬ ተዛባ! ለምኑ ነው የምዘጋጀው? ለመታገት ዝግጅት? <አዎ! እጄን ለካቴና በቅባት አሸት አሸት አድርጌ አዘጋጅቸዋለሁ። ድንገት እጃችሁ ካረፈብኝ ዱላ መቻያ ደንደን እንዲል ቆዳዬን ወጠርጠር አድርጌ አለማምጄላችኋለሁ….. > እንድላት ነው ተዘጋጀሽ የምትለኝ? እሷ ቀጠል አድርጋ ከፊቴ ወደቆመ ዘናጭ ነጭ መኪና እየጠቆመችኝ ፈገግታዋ የሆነ የተንኮል ዓይነት እየሆነ « …. ግርግር አንፈልግም አይደል?» ብላ አጭሩን ጃኬቷን ከፈት አድርጋ ሽጉጧን አሳየችኝ። ለስሙማ እኔምኮ ሽጉጤን ጎኔ ላይ ሽጬዋለሁ። ምን ላደርግበት እንደሆነ ያሰብኩት ባይኖርም ለዝህች በቆንጆ ፊቷ ለሸወደችኝ ልጅ ግን ሽጉጥ ሳይሆን የመዘዝኩት እጄን ነው ለሰላምታ የዘረጋሁት።

ወዳሳየችኝ መኪና ሄድኩ። እያገተችኝ ሳይሆን የሆነ በክብር እንግድነት የተጠራሁበት ቦታ ልታደርሰኝ ነው የሚመስለው። የኋላውን በር ከፍታ ያንን ተንኮለኛ ፈገግታዋን እያሳየችኝ እንድገባ ጋበዘችኝ። በአጠገባችን የሚያልፉ ሰዎችን <ኸረ በትኩረት ለአፍታ እዩኝ እየወሰዱኝ ነው!> ብል ደስ ባለኝ። ማንም ለአፍታ እንኳን ገልመጥ አድርጎ ያየኝ የለም። በየእለት ተእለት ውሏችን ልብ ያላልናቸው ስንቶች ይሆኑ ከአይናችን ስር ብዙ የሆኑት?

መኪና ውስጥ ከኋላ ታግቼ ባይሆን « ምን ሆኖ ነው እንዲህ የቆነጀው?» የምለው የሚመስለኝ ፈርጣማ ወንድ ተቀምጧል። እንደገባሁ ቀለበኝ ማለት ይቀላል። ፓንቴ ስር መግባት እስኪቀረው እንያንቀረቀበ ሲፈትሸኝ ልጅቷ ከፊት ወንበር ሆና ሽጉጧን አስተካክላ ትጠብቀቃለች። የምራቸውን ነው? እዝህች የክብሪት ቀፎ የምታክል መኪናቸው ውስጥ ከነሹፌሩ ለሶስት ከበውኝ ታጠቃናለች ብለው ነው ሽጉጡ? ሽጉጤን ከፊት ለተቀመጠችው ሴት እንደመወርወር አድርጎ አቀብሏት በምትኩ የሆነ ጨርቅ ስትወረውርለት ነገረ እቅዴ ሁሉ ጎንጥ እንዳለው የጅል መሆኑ ገባኝ። የሰውየው መዋከብ ቶሎ የመጨረስ ውድድር ያለበት ነው የሚመስለው። በጨርቁ ዓይኔን ሲሸፍነው መኪናው መንቀሳቀስ ጀመረ። በዚያው ፍጥነት እጄ ላይ ካቴና አሰረ።

ለምን ያህል ደቂቃ እንደተጓዝን አላውቅም!! ወይ ከላይ ወይ ከታች እንዳያመልጠኝ ከሰውነቴ ጋር ግብ ግብ ላይ ነበርኩ። የእነርሱ ዝምታ ደግሞ ጭራሽ ያለሁት መኪና ውስጥ ሳይሆን ከሞት በኋላ የሰይጣን ፍርድ ዙፋን ስር ቀርቤ አስፈሪ ፍርድ ለምሳሌ እንደ < ለእሷ እሳቱ አስር እጥፍ ይጨመር!! ይሄማ ለሷ ሻወር መውሰጃዋ ነው!! ይንተክተክላት ውሃው እንጂ! > የሚል ፍርድ እየተጠባበቅኩ መሰለኝ። ከመኪናው ወርደን የበረበረኝ ሰውዬ ይመስለኛል ብብቴ ስር ገብቶ ጨምቆ ይዞኝ እየነዳኝ በእግር የሆነ ያህል እንደተጓዝን አይኔን የሸፈነኝ ጨርቅ ሲነሳ የተንጣለለ በውብ እቃዎች የተሞላ ሳሎን ራሴን አገኘሁት። ያሰረልኝ ሰውዬ ከእጄ ላይ ካቴናውን አወለቀው።

እንግድነት የሄድኩ ይመስል እንድቀመጥ ታዘዝኩ። ያ ሰውዬ በቪዲዮ ያወራሁት ሰውዬ እና አንዲት መሬቱን የነካ ጌጠኛ ቀይ ቀሚስ የለበሰች ሴት ተቀምጠዋል። ከእነርሱ በተጨማሪ ይዞኝ የገባው ሰውዬ እና ትንሽ ቁመቱ አጠር ያለ መሳሪያ የታጠቀ ሰውዬ ብቻ ናቸው ክፍሉ ውስጥ ያሉት። ሴትየዋ የጠቆመችኝ ከፊታቸው ያለ ሶፋ ላይ ለመቀመጥ ቂጤን ሳሾል
«ከመጨዋወታችን በፊት እንዳው ለመተማመኑ ….. » ብላ አጠገቤ ደርሳ የለበስኩትን ሹራብ ግልብ ስታደርገው ግራ ገባኝ እና መነጨቅኳት። የቆሙትን ጠባቂዎች (መሰሉኝ) ፊታቸውን እንዲያዞሩ ምልክት ስትሰጣቸው ሶፋው ላይ ያለው ሰውዬ እራቁቴን የማየት መብት እንዳለው ሁሉ ዝም አለችው። ከንግግሯ ምናልባት የምናወራውን የምቀዳበት ነገር ሰውነቴ ላይ ደብቄ እንደሆነ እያጣራች መሆኑ ገባኝ። በፓንት እና በጡት ማስያዣ ስቀር አይኑን ከሰውነቴ ላይ ለመንቀል ምንም ሀሳብ የሌለውን ሰውዬ እያየሁ መዋረድ አንገበገበኝ። ሴትየዋ ጡቴ ስር ገብታ ስታንቀረቅበኝ ጡቶቼን የምትመዝናቸው እንጂ የሆነ መቅጃ ያለችውን ነገር እየፈለገች አይመስልም። ጥርሴን ነክሼ ዋጥኩት። ሆነ ብላ የምታደርግ ነው የሚመስለው። ጣቷ የእንትኔን ጫፍ እስኪነካው ድረስ እጇን ፓንቴ ውስጥ ስትሰድ እስኪያማት ድረስ የእጇን አልቦ ማሰሪያ ጨመደድኩት።

«ok ok » ብላ እጇን አወጣች። የያዝኳትን ስለቀው ቦታው ደም መስሏል። ፊቷ ላይ ያስታውቃል። ከመፈተሿ በላይ እኔን ማዋረዷ ተመችቷታል። እንድለብሰው ልብሴን ከመሬት አንስታ ወረወረችልኝ። ከሰውየው ጋር ተያይተው ያልገባኝን መልዕክት ተለዋወጡ። ይዤው የነበረውን ቦርሳ አንስታ አመሳቅላ በረበረችው።

«አላመንከኝም እንጄ ነግሬህ ነበር,» አለችው። ሰውየው ባለችው ነገር ሙሉ በሙሉ ያመነ አይመስልም።

«እሺ ሜላት!! የታሉ ቪዲዮዎቼ?» አለ

«ወንድሜን በአይኔ ሳላየው ምንም ነገር አልነግርህም!!» አልኩት ለመኮሳተር እና ያልፈራ ለመምሰል እየሞከርኩ።

«ሜላት ይሄ ኔትፍሊክስ ላይ ተጥደሽ ስታዪ የምትውዪው የሆሊውድ ፊልም አይደለም። አጉል ጀግና ጀግና አትጫወቺ!! የትም አትደርሺም!!» አለ ልጥጥ ብሎ እንደተቀመጠ። አልመለስኩለትም።

«እየሰማሽኝ አይደለም? ዛሬ የምጫወትበትን ጠጠር የምመርጠው እኔ ነኝ። ያልኩሽን ነው የምታደርጊው።» ብሎ አምባረቀ።

«ወንድሜን ካላየሁ ምንም የማደርገው ነገር የለም አልኩ እኮ!!» ብዬ ለመጮህ ሞከርኩ።
ለቆመው አጭሩ ጠባቂ ምልክት ነገር ሰጠው። የታመቀ ትንፋሼን በረዥሙ ለቀቅኩት። ኪዳን ሲገባ ምንም የተጎዳ ነገር ያለው አይመስልም። ሲያየኝ ፊቱ ላይ ከቃላት በላይ የሆነ ስቃይ አየሁበት።

«I am so sorry» አለኝ ገና ስንተያየኝ። አልከለከሉኝም! ሄጄ አቀፍኩት። አጥብቆ አቀፈኝ። «ይቅርታ ሜል!»

«መልሰው!!» ብሎ ጮኸ ሰውየው። አብሬው እንድቆይ ብለምንም ሊሰማኝ እንኳን ግድ አላለውም። ምንድነበር ያሰብኩት? 'ናፍቆትሽ እስኪወጣልሽ እንጠብቅሻለን ከወንድምሽ ጋር ትንሽ ተወያዩ' እንዲሉኝ ነበር? የምርም እንዴት ያለ የቂል እቅድ ነው ያወጣሁት? ኪዳን ተመልሶ ሲሄድ የተሸነፍኩ መስዬ ላለመታየት ሞከርኩ። ሰውየው ወደእኔ አፈጠጠ።

«ሁሉንም ኮፒ እንዳመጣልህ አይደል ፍላጎትህ? በሰጠኸኝ አጭር ጊዜ ላመጣልህ አልችልም!! ተጨማሪ 24 ሰዓት ስጠኝ እና የምትፈልገውን በሙሉ እሰጥሃለሁ።» ስለው ያሳቃቸው ጉዳይ አልገባኝም ሁለቱም ከጣሪያ በላይ ሳቁ።

«ብዬህ ነበርኮ! በል ብሬን ወዲህ በል!» አለችው ሰትየዋ እጇን እየዘረጋች።

«እያወቅሽኝ ካላረጋገጥኩ መች አምናለሁ?» መለሰላት። እየሆነ ያለው ሙሉው ባይገባኝም እያላገጡብኝ እንደሆነ ገብቶኛል። ከኪሱ የሆኑ ብሮች ኖት አውጥቶ አቀበላት።

«ባንቺ ቤት አቃቂለሽኝ ሞተሻል!! ካንቺ ውጪ ማንም መረጃዎችሽን የት እንደምታስቀምጪ እንደማያውቅ ገምቻለሁ። እመቤትን ነበር የጠረጠርኩት እንደገባኝ እሷም የረዳችሽ ነገር የለም። አንቺም የት እንዳስቀመጥሽ እንዳታስታውሺ ትውስታሽ ላይመለስ ከድቶሻል። ንገሪኝ እስኪ ምን ልሁን ብዬ 24 ሰዓት ልጠብቅሽ?» ሲለኝ የበለጠ ጅልነት ተሰማኝ።

ባለፈው ከደበደቡኝ ጎረምሶች የተሻለ እነዚህ ሰዎች መረጃ ከፈለጉ በቀላሉ ማግኘት አይችሉም ብዬ እንዴት አሰብኩ? ምኗ ቂል ነበርኩ? አሁን ይገድሉኛል? እሺ ኪዳንንስ? ምንድነው ያደረግኩት?

በሩ ተከፍቶ የቅድሟ ሴት በሩ ላይ ላለው ጠባቂ የሆነ ነገር አንሾካሽኳ ወጣች። ጠባቂውም የሆነ ነገር ለሰውየው አንሾካሾከ። ሰውየው በጣም የተገረመ መሰለ።

«ያንቺው ጉድ ነው!» አላት ወደሴትየዋ እያየ። ሴትየዋ ግራ የተጋባች መሰለች። በጣም በመገረም ወደበሩ እያየች።
«ምን ልሁን ነው የሚለው አስገቡት እስኪ!»

ዓይኔ የሳተው ነገር ቢኖር ነው። ጆሮዬም እንደዛው? <የሷው ጉድ> ነው ያለው ወይስ <የአንቺው ጉድ> ነው ያለው? የእኔው ጉድ ጎንጥማ የሷው ጉድ ሊሆን አይችልም። ወይም ሌላ ጎንጥ ይሆናል እንጂ የእኔው ጎንጥማ አይሆንም!! በሩን አልፎ ሲገባ ቤቱ ነው የሚመስለው!! ልክ የእናት አባቱ ቤት እራት ሊበላ እንደመጣ ነገር ዘና ብሎ ከሶፋው ተሻግሮ ያለ ወንበር ሳብ አድርጎ ተቀመጠ።

እስከአሁን የነበረው ምኑም ያየኋቸውን ፊልሞች አይመስልም ነበር። ይሄ ግን ፊልም እንጂ እውን አይመስልም።

«ምን ትሰራለህ?» ብላ ሴትየዋ ጮኸች።

«ስራዬን ነዋ!!» አለ እንደማላገጥ ብሎ

ሆድቃዎቼ ቦታ የተቀያየሩ ነገር መሰለኝ። ሆዴ ውስጥ ተለዋወሰብኝ።

........... .... አልጨረስንም ...........
ውብ ምሽት ውብኛ አምሹልኝማ!!❤️❤️❤️
#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል አስራ ስምንት)
(ሜሪ ፈለቀ)

መቼም ሰው <ልቤ ዝቅ አለብኝ> የሚለው አሁን እኔ እንደሚሰማኝ ልቤ አቃፊዋን ለቃ የወጣች የሚመስል ስሜት ሲሰማ ነው የሚሆነው። የኔዋማ ዝቅ ከማለትዋም እነ ሳንባ ጉበትን <ዞር በሉ በናታችሁ> ብላ ገፋ ገፋ አድርጋ አንጀቴ ላይ ዛል ብላ ጋደም ያለች ይመስለኛል። አጅሬው እኔን ድዳና ሽባ አድርጎ በድንጋጤ አደንዝዞኝ እሱ እቴ በሙሉ አይኑ እንኳን አላየኝምኮ!!

ለመሆኑ ስሙስ የምር ጎንጥ ነው? የሚያወራው የሀገርኛ ለዛውስ ዘበኛ ለመምሰል ያስመሰለው ይሆን? ቅድም እንዴት ነበር ያወራው? ንፋስ ሲሆን ትከሻው ላይ ጣል የሚያደርጋት ፎጣውስ የትወናው አካል ትሆን? ዘበኛም ሆኖ አንዳንዴ ስንወጣ የሚለብሰውን ዓይነት ጅንስ በሸሚዝ ስለለበሰ የአለባበሱን ትወና መለየት ይቸግራል።

«ስራህንማ በአግባቡ ተወጣህ!» አለችው ሴትየዋ። ሙገሳ አይደለም! የሆነ ለበጣ ያለበት ነገር ነው! ቀጥላ የሆነ በእኔ ፊት ወይም በሰውየው ፊት መናገር ያልፈለገችውን ነገር ለብቻቸው እንዲያወሩ መሰለኝ። « ….. እኔ እና አንተ ብዙ የምናወራርደው ነገር አለ።» ብላ እጁን መንጨቅ አድርጋ ይዛው ልትሄድ ስትሞክር ከተቀመጠበት ሳይነሳ እጁን መነጨቃት። አስከትሎ ከእግሯ እስከ አናቷ በግልምጫ ካበጠራት በኋላ ራሱ ከተቀመጠበት ተነስቶ ቀድማው ከሳሎኑ እንድትወጣ ምልክት አሳያት። (እንደለመደው ነዳት ብል ይቀላል) በተጫማችው ሂል ጫማ እንደዝግዛግ ያለ አረማመድ እየረገጠች ሳሎኑን ለቃ ስትወጣ ተከትሏት እየተቆለለ ወጣ!! ከትውውቅ አልፈው መደነቋቋል ላይ የደረሱ ወዳጃማሞች መሆናቸውን ለማወቅ ምንም ሂሳብ አያስፈልግም!!

< ሄሎ!! እዚህ ነኝ! ሜላት! አስታወስከኝ? ከአንድ ቀን በፊት እመኚኝ ብለህ እንደወፍጮ ቤት እህል አየር ላይ ያንቀረቀብከኝ? አልታይህም?> ይላል ውስጤኮ አፌን ቃል ማን ያበድረው? ከሳሎኑ ከወጡ በኋላ የሚያወሩት ባይሰማኝም ጭቅጭቅ ላይ መሆናቸው ከድምፃቸው ያስታውቃል። ጎንጥ እንዲህ ይጮሃል እንዴ ሲያወራ? እኔ ንግግሩን ሳልሰማ ድምፁ እንዲህ ያስደነገጠኝ እሷ እዛች ሚጢጥዬ ፊቷ ላይ ሲጮህባት ወትሮም ያነሰች ፊቷ አለመትነኗ!!

የሁለቱ ሁኔታ ግራ የገባው ከመሰለው ሰውዬ ጋር ተፋጠን ሁለታችንም ከማይሰማው የሁለቱ ጭቅጭቅ ቃላት ለመልቀም ጆሯችንን አሹለን እንቃርማለን!! ፀጥ ያሉ መሰለ ወይም ድምፃቸው ለኛ መሰማቱን አቆመ።

«ለመሆኑ እኔ ማን እንደሆንኩ ታውቂያለሽ?» አለኝ ሰውየው በተፈጠረው ክፍተት። የሆነ ተራ ጥያቄ የጠየቀኝ አስመስዬ አፍንጫዬን ነፍቼ ለማለፍ ሞከርኩ።

«ጊዜ ግን ሲገርም!! በተሰቀለው!! ምንም ምንም አታስታውሺም?» ብሎ ሊገለፍጥ ዳዳው « መቼም ግፍሽ ነው!! በቁጥር እኮ አይደለም አንቺ የህዝብ ግፍ ነው ያለብሽ!! ሃሃሃሃ ሰውኮ የዘራውን ነው የሚያጭደው ሃሃሃ ስንቱን እንዳልከዳሽ የራስሽ ጭንቅላት ይክዳሽ? እረስታለች ሲሉኝ ማመን ያቃተኝ ቀጥ ብለሽ ስትመጪ ነው። ምንም የምታውቂው እና የምታስታውሺው ሳይኖር …… » ብሎ ሲጨርስ

«እኔ እንዳልረሳው አይጠፋህምሳ መቼም!» እያለ ገባ ጎንጥ!! ሴትየዋ ትንሽ ቀይ ፊቷ ሚጥሚጣ የተነፋበት ሰሃን መስሎ ተበሳጭታ ተከትላው ገባች።

«እሷ ትሄዳለች። ወንድምየው እኛጋ ይቆያል።» አለች በኮሳሳ ድምፅ ትዕዛዝም ሀሳብ ማቅረብም በመሰለ አነጋገር - ለሰውየው። ሰውየው ከተቀመጠበት ተነስቶ ሲደነፋ እና ሲጯጯሁ «ኪዳንን ትቼ አልሄድም!» ያልኩትን የሰማኝ የለም!! ጎንጥ አጠገቤ ደርሶ ቁጢጥ እንደማለት አለ እና

«እባክሽ እንዳታስቸግሪኝ (ይሄኛው ልመና ነገር ነበር) የምልሽን አድርጊ! ካለበለዚያ ያንቺንም የእኔንም የኪዳንንም ህይወት ነው እሳት ምትሰጅበት (ትዕዛዝ ነገር ሆነ) ለዛሬ! ለዝህች ደቂቃ ልታምኝኝ ይቻልሻል? (ልምምጥ ነገር ሆነ)» አልመለስኩለትም!! ሰውየውና ሴትየዋ በጥፍራቸው ቆመው ይጨቃጨቃሉ።

«ታምኚኛለሽ?» ሲል ግን በፍጥነት
«አላምንህም!!» አልኩት። ይህችን ለመተንፈስ ሰዓት እየጠበቅሁ ይመስል ተቅለብልቤ

«ሜላት እኔና አንቺ የምንነታረክበት ጊዜ የለንም! ስትፈልጊ አትመኚኝ ያልኩሽን ካልሰማሽ ሙት ነሽ!! (ይሄ ድብን ያለ ቁጣ ነው!!) እኔ እና አንቺ አሁን ወጥተን እንሄዳለን!! አንቺን እንጂ ኪዳንን አይፈልጉትም!! በምትወጅው ኪዳን ይሁንብሽ ለአንዴ እመኝኝማ! (እዚህጋ እኔን ማስረዳት የደከመው መሰለ) ኪዳን ምንም አይሆንም!! (ድምፁን ቀነስ አድርጎ) ኪስሽው ውስጥ አሁን እንዳታስታውቂ ! ኪዳን መልዕክት አኑሮልሻል!! ከዚህ ከወጣን በኋላ ታይዋለሽ!! አሁን እንሂድ? (ይሄ እባክሽ እንቢ እንዳትዪኝ የሚል ማባበል ነው።)።» ምላሴን ምን ያዘብኝ? እሺም እንቢም ማለት ጠፋኝ!! ሰዎቹ ጭቅጭቃቸውን ማቆማቸውን ያወቅኩት

« I knew it!! ወደሃት ነዋ!» ብላ እግሬ ስር ቁጢጥ ያለውን ጎንጥ በትንግርት እያየችው የሆነ ግኝት የተገለጠላት ዓይነት አስመስላ ስትጮህ ነው። ጎንጥ አቀማመጡን ገና አሁን ያስተዋለው ይመስል ተመንጭቆ ተነስቶ ክምር ተራራ አክሎ ተገተረ። ሴትየዋ አላቆመችም። እንደንቀትም፣ እንደ መገረምም ፣ እንደመናደድም …… እንደብዙ ነገር በሆነ ድምፅ እና እይታ « ጎንጥ ለዝህች? (በአይኗ አቅልላ የጤፍ ፍሬ አሳከለችኝ) ማን ያምናል? በምን አገኘችህ በናትህ?»

«አፍሽ ሲያልፍኮ አይታወቅሽም!! እረፊ ብያለሁ!» ብሎ ተቆጣ።

ቆይ እዚህጋ የትኛውን ሀሳብ አስቀድሜ የትኛውን አስከትዬ የቱን ምኑጋ ሰካክቼ ልከኛውን ምስል ላግኝ? ሰው ሀሳብ ይበዛበታል አይሉም በአንዴ ራሱን ጎንጥን የሚያካክል መአት ሀሳብ ወርውረውብኝ እዛ እንደተቀመጥኩ የሚዘነጉት? ኸረ ቆይ ጎንጥ ወዶኝ ነው የሚለውን ላስቀድም? ኸረ አይደለም! <ይህችን?> ብላ ምላሷ ላይ ያሟሸሸችኝ እኔ አስቀያሚ ነኝ እንዴ? አይደለም ኸረ ቆይ ጎንጥ ሴትየዋን ምን ቢላት ነው እኔን ይዞ እንዲሄድ የተስማማች? ኸረ ሌላው ደሞ እሱስ <ወድጃት አይደለም> ከማለት ይልቅ የሚደነፋው ወዶኝ ነበር ማለት ነው? አይ እነዚህ ሁሉ ይቅሩ እንዴት አምኜው ነው ኪዳንን ትቼው የምሄደው? ግን ምርጫስ አለኝ? ኸረ ኪዳን በምን ቅፅበት ነው መልዕክት ያስቀመጠልኝ? ምን ይሆን የሚለውስ? ደሞ ሌላ አለ እንጂ ቆይ ጎንጥ እኔን ቢወደኝ እሷ ምን እንዲህ ይንጣታል?

በአይኑ ከተቀመጥኩበት እንድነሳ ምልክት ሰጠኝ። በአይኑ አስነሳኝ። እጁን ሰጠኝ ወይም እጄን ተቀበለኝ እኔእንጃ ብቻ እጄን ያዘው እና ወደበሩ መራመድ ጀመረ። ጠባቂዎቹ ትዕዛዝ የሚጠብቁ ይመስላል ከበሩ አልተንቀሳቀሱም!! ሰውየው በአገጩ የሆነ ምልክት ሰጣቸው!! ከበሩ ገለል አሉ!! ሴትየዋ መናጥዋ በረታባት!!

«እመነኝ ጎኔ ይህችን አታልፋትም!! አስከፍልሃለሁ!! እመነኝ ትከፍላታለህ!!» አለች እየጮኸች። <ጎኔ> ብላ ነው ያቆላጰሰችው? ዛሬማ የሆነኛው ፊልም ተዋናይት ሆኛለሁ እንጂ እየሆነ ያለው እውን በእኔ ህይወት እየሆነ ያለ አይደለም!! እንዲህ አፍና ጭራው ያልተለየ እውነተኛ ህይወት ሊኖር አይችልም።
በሩን አልፈን እንደወጣን የቅድሟ ሴት ተቀበለችን። ስመጣ ያሰሩልኝን ጨርቅ ይዛ ስትቀርበኝ የያዘኝን እጁን ለቅቄ በጥያቄ አየሁት!! የታከትኩት መሰለ እና በቁጣ ጮኸ « እየገባሽ አይደለም አንቺን መምረጤ? ከዚህ በላይ ምን ባደርግ ነው የምታምኝኝ በይ? ያለፈውን ካላወቅኩ ነው? አንድም ሳይቀር አወጋሻለሁ! እዝህችው ቆመን 19 መቶ ብዬ እንዳወጋሽ አይደለማ ሀሳብሽ?» ቅድም ሴትየዋ ላይ እንደጮኸው ነው የጮኸው!! ጨርቁን እንድትሰጠው ለልጅቷ እጁን ሲዘረጋ ልጅቷ እንደማቅማማት አለች። ጮክ ብሎ ሲያፈጥባት የመወርወር ያህል እጁ ላይ ጣለችው። ከሁኔታዋ ከዚህ በፊት የሚተዋወቁ የምትፈራው ሰው መሆኑ ያስታውቃል። ምናልባት አለቃዋ ነበር? ዛሬማ የሆነ ፊልም ገፀ ባህሪ ሆኛለሁ።

ከሴትየዋ እጅ ተቀብሎ እሱ እያሰረልኝ እንደዛ እንዳልጮኸ ልስልስ ብሎ ነገር «መግቢያ መውጫቸውን እያየሽ እንድትሄጂ በጀ አይሉሽም!! ለዛሬ የምልሽን እሽ በይ በሞቴ?» አለ። ማደንዠዣ እንደወጉት በሽተኛ ፍዝዝ ድንግዝ አልኩ። ጨርቁን ካሰረልኝ በኋላ እጄን አጥብቆ ይዞ መራመድ ጀመረ። የምረግጠው ምን እንደሆነ ሳላውቅ እግሬን እያነሳሁ ተከተልኩት። መኪና ውስጥ ገባን!! ባላይም መኪናው ውስጥ ከእኔና ከእርሱ በተጨማሪ ያቺ እንደጥላ የምታጅበኝ ሴት እና ሹፌር እንዳሉ አውቂያለሁ። እኔእና እሱ መጓዝ ጀምረን የያዘኝ እጁ መያዝ ብቻ ሳይሆን መዳበስ ነገር ያደርገኛል። ልቤ የምን አጃቢ ናት አብራ የምትቀልጠው? ትንፋሹ እንዳልተረጋጋ ያስታውቅበታል። አካሉም ይቅበጠበጣል። ከእርሱ ሁኔታ በመነሳት አሁንም እርግጠኛ የሆነ ማምለጥ አለማምለጤን ጠረጠርኩ። ቆይ እራሱ የሆነ ቦታ አግቶ ይዞኝ እየሄደ ቢሆንስ? እሱንስ እንዴት አመንኩት?

«ሴትየዋ ማናት? ምንህ ናት?» አልኩት ከዛ ሁሉ አናቴን ከወጠረው ጥያቄ ይሄን ለምን እንዳስቀደምኩ አላውቅም!! በረዥሙ ተንፍሶ

«የልጄ እናት ናት!! ምሽቴ ነበረች» አላለኝም? ከዚህ በላይ ከእውነታ የራቀ ቀን አለ እሺ?
«እ?» የምትለዋ ፊደል ከየትኛው ቃል አምልጣ በአፌ እንደሾለከች አላውቅም!! ብቻ ለምሳሌ <እንደ> ከሚለው ቃል ቢሆን ተጣልተው የፈረጠጠችው …… <ን> ን እና <ደ>ን ትርጉም አልባ አድርጋ ጥላቸው ብቻዋን ስትፈረጥጥ …… ተንደርድራ አምልጣ መሆኑ የሚያስታውቀው አፌ ፊደሏን ሊያስወጣ እንደተበረገደ አልተከደነም!!

«ባሏ ነው!!» አለ አክሎ። ሰውየውን መሆኑ ገባኝ ግን ጭንቅላቴ ውስጥ ሀሳቦቹ ተጠላለፉ ነገር። የሰውየው የአሁን ሚስት የጎንጥ የድሮ ሚስት የልጁ እናት! ከዛ ግን ዛሬም ውሉን ያልጨበጥኩትን ስራ (እገታ እና ስለላ ማለት ይቀላል) አብረው የሚሰሩ? ነው ወይስ ያልገባኝ ነገር አለ? ይሄ ቢገባኝም እንኳን በ2 ወር ከአስር ቀኔ እንደምንም ያጠራቀምኩትን አዲስ ትውስታ ሁላ ነው የሚያጠፋብኝ።


መኪናው ቆመ። ከአይኔ ላይ ጨርቁ ሲነሳ መኪናዋ የቆመችው ከከተማ የራቀ ጭር ያለ ቦታ መሆኑን አስተዋልኩ። በቅርብ ርቀት የእኔ መኪና ቆማለች። እዚህ ደቂቃ ላይ ማመንም መጠራጠርም አይደለም የተሰማኝ። ምንም ነው!! ጎንጥ ግን የሆነ ነገር እንዳላማረው ያስታውቃል። ዙሪያ ገባውን ከቃኘ በኋላ እስከአሁንም ያልለቀቀውን እጄን አፈፍ አድርጎ ወደመኪናችን እየሄድን።

«ከአይናችን ተሰወሩ ማለት የሉም ማለት አደለም!! አሁን አንቺን ማጥፋት ቀላሉ መፍትሄያቸው ስለሆነ ማስታወስ ችለሽ ከምትፈጃቸው በፊት የአቅማቸውን ይሞክራሉ።» እያለኝ እኔን ባልያዘው እጁ ወገቡ ላይ ያለ ሽጉጡን ጨብጦ ወደኋላ እና ወደጎን እየተገለማመጠ መሬቱን በረጃጅም እርምጃው ይመትረው ጀመር። ያደረሰችን መኪና ከኛ በተቃራኒ አቅጣጫ ሄደች። ከአይናችን ስትሰወር መኪናችንጋ ደርሰናል። ስንቀርብ የመኪናችን ጎማ መተኛቱን አይቶ ጎንጥ ጎማውን በእግሩ ሲነርተው አየሁ።

ከየት መጣ ሳይባል አንድ ፒካፕ መኪና እየበረረ ፒስታውን መንገድ አቧራ እያጨሰ መጣ። እየሆነ ያለው ነገር ከመፈጣጠኑ የተነሳ ውዥብርብር አለብኝ። በቅፅበት የተኩስ ድምፅ ተሰማ!! ማናቸው ቀድመው እንደተኮሱ እንኳን አላውቅም ምክንያቱም ጎንጥም እየተኮሰ ነው። በየትኛው ቅፅበት ሽጉጡን እንዳወጣ እንኳን አላየሁም!! የትኛው ቅፅበት ላይ እጄን እንደለቀቀኝም አላውቅም! ማየት እስኪያቅተን የበዛ አቧራ እያቦነነ እና እየተኮሰ አልፎን የሄደው መኪና በሄደበት ፍጥነት አዙሮ ተመልሶ ወደእኛ ሲመጣ በአንድ እጁ የመኪናውን በር ከፍቶ

«ግቢ!! ገብተሽ ወደታች ዝቅ በይ!!!! ከወለሉ ተኝ!» ብሎ ጮኸ! ምንድነው እግሬን ከመሬቱ የሰፋው? እኔ የድርጊቱ አካል ያልሆንኩ ይመስል ዓይኔ አንዴ ጎንጥን አንዴ በፍጥነት እየመጣ ያለውን መኪና ያያል። በሩን ከፍቶበት በነበረው እጁ ከጎኑ ወደጀርባው ገፈተረኝ። አፈሰኝ ማለት ይገልፀዋል። እኔንም ራሱን መከላከል የማይችልበት አጣብቂኝ ውስጥ እንደከተትኩት ገብቶኛል ግን በምን በኩል ሰውነቴን ልዘዘው? ዓይኔ ስር ፊልም እየተሰራ ያለ ዓይነት ስሜት ነው ያለው። እኔን ወደጀርባው በደበቀኝ ቅፅበት ለጊዜው ምኑጋ እንደሆነ ያልለየሁት ቦታ እሱ ተመታ። እኔ የተመታሁ ዓይነት መሰለኝ። ጭንቅላቴ ለቅፅበት ያን ቦታ ትቶ ሄደ። ቅፅበት ናት ግን ድንዝዝዝ ያለ..... ብዥዥዥ ያለ ቅፅበት .... ጎንጥ የተመታበትን ቦታ በአንድ እጁ ይዞ

«ወዳጄ ይደርሳል። ከእርሱ ጋር ሂጂ!! እቤት እንዳትሄጅ!! » ይለኛል ጮክ ብሎ!!

«ትቼህማ አልሄድም!!» ዓይኔ ከፒካፑ መኪና ጀርባ እየመጣ ያለ መኪና በአቧራው ውስጥ ቢያይም ጭንቅላቴ ግን እዛው ገትሮኝ ሄዷል። አንድ ጥይት በጎኔ አልፎ መኪናውን ደነቆለው:: ሰውነቴ አይታዘዝም!! ደንዝዟል::

"ዝቅ በይ!" እያለ ይጮሃል ጎንጥ በከፊል ዘወር ሲል ከጎኑ የሚፈስ ደሙን እያየሁ ሀሳቤ ሄደ .... እዛ ቀን ላይ!!

ጥይቱ የተከፈተ የመኪናዬን መስኮት አልፎ ጡቴ ስር ሲመታኝ!! የመጀመሪያውን ህመም በቅጡ አስተናግጄ ሳልጨርስ ሁለተኛው ተመሳሳይ ቦታ ሲያገኘኝ። - የተመታሁ ቀን!! አንድ በአንድ ቁልጭ ብሎ ስዕሉ ጭንቅላቴ ውስጥ መጣ!! የማደርገው እና የማስበው በአንድ እኩል ቅፅበት ነበር። እጄን ማዘዜን አላስታውስም ብቻ ከጎንጥ እጅ ላይ ሽጉጡን እንደቀማው አውቃለሁ። ክፍቱን በተተወው የመኪና በር ግማሽ ሰውነቴን ከልዬ ሳደርገው የኖርኩት ልምዴ መሆኑን እርግጠኛ የሆንኩበትን ድርጊት እከውናለሁ። ከኋላ የመጣው መኪና በእኛና በፒካፑ መሃል ገብቶ ቆመ።

« ሂጅ እኮ አልኩ!!» ብሎ አምባረቀብኝ። በእጁ ጎኑን ደግፎ መሬቱ ላይ ተቀምጦ የመኪናውን ጎማ እንደተደገፈ።

«ደፋር እየሸሸ አይሞትም! እየተዋጋ እንጂ!» ስለው በህመሙ መሃል በስቃይ የታጀበ ፈገግታ አሳየኝ። ትውስታዬ ሳይከዳኝ በፊት አዘውትሬ የምለው አባባል ስለነበር ገባው። ጭንቀቱ የቀለለው መሰለ እና ህመሙን ማድመጥ ጀመረ። ፒካፕዋ መኪና ከአይኔ ራቀች። ወዳጄ ነው ያለው ሰውም ከመኪናው ወርዶ ወደኛ መጣ!! ሁለት ቦታ ነው የተመታው። አንዱ ከትከሻው ዝቅ ብሎ ሌላኛው ጎኑ ላይ የጎድን አጥንቶቹ መሃል ……. የለበስኩትን ሹራብ አውልቄ የሚንዥቀዥቅ ደሙን ለማቆም ከአንዱ ቁስል ወደ አንዱ እላለሁ።

« ሁሉንም?» ይለኛል አይኑን ላለመክደን እየታገለ።
« ምኑን ነው ሁሉንም?»
«ያስታወሽው?»
«መሰለኝ!!» አልኩት። ሁሉንም ላስታውስ የጎደለ ይኑረው በምን አውቃለሁ?

.............. አልጨረስንም!! ...................

ውብ አዳር ውብኛ እደሩልኝ!!!! ❤️❤️❤️❤️
ማንም ሰው <ሞት ምን ምን ይል እንደሆነ ልቅመስ > ብሎ ራሱን አያጠፋም!! ማንም <እስቲ በዚህ ዓመት ልደበር እና ከሰው ተገልሎ እንቅልፍ አልባ ለሊት ማሳለፍ ምን እንደሚመስል ጉዱን ልየው > ብሎ ዲፕረስድ አይሆንም!!!

አንድ ወዳጅ ከዚህ መንደር «ሜ ምን ሆነሽ ነው የጠፋሽው? በደህናሽ ነው?» ሲለኝ «ትንሽ ድብርት ውስጥ ገብቼ ነበር።» አልኩት!! ከዛ ያለኝ ነገር ተደበርኩ የምንል ሰዎችም ልንረዳቸው የምንፈልግ ወዳጆቻቸውስ የእውነት የነገሩን ጥልቀት እናውቀው ይሆን? የሚለውን እንዳስብ አደረገኝ!!
«የሀገር ቤቱ ነው ወይስ የዚህ ሀገሩ ክፉው?» ነበር ያለኝ!!

<የሀገር ቤቱ> ያለበት ምክንያት ወዲያው ገባኝ። ባለፉት ዓመታት በሃገሬ በአብዛኛው ወጣት በብዙ መታከት ፣ በብዙ ተስፋ መቁረጥ ፣ በብዙ ነጋ ጠባ ለውጥ የሌለው ልፋት ውስጥ ተነክሯል። ጦርነቱ ፣ ኢኮኖሚው ፣ ፖለቲካው ፣ ሶሻል ሲስተሙ ፣ ስራ ማጣቱ ፣ ቢሰሩም ጠብ አለማለቱ …… ሁሉም ተዳብሎ ትከሻ ላይ እንደተሸከሙት ኩንታል እንደሚያጎብጥ ግልፅ ነው። አንድ ነገር አስምሩልኝኝማ!! የማንንም ፈተና እያቀለልኩ አይደለም። ደግማቹ አስምሩልኝማ!! ሁላችንም የምናልፍበት ውጣውረድ እና አበሳ ለራሳችን በወቅቱ ዙሪያችንን እስከመጥላት ሊያደርስ የሚችል እንደሆነም በደንብ እረዳለሁ።

ነገር ግን ከአለቃህ ጋር ተጋጭተህ የሚደብርህ መደበር ወይም ነገ መልሰሽ እንደምትታረቂው ከምታውቂው ፍቅረኛሽ ጋር ተኳርፈሽ የሚደብርሽ መደበር ዲፕረሽን አይደለም!! እንደእነዚህ ያሉ ጥቃቅን ነገሮች ተደማምረው ወደ ዲፕረሽን ይመራሉ!! ሀቅ ነው!! እንደገባኝ ከሆነ ለአፍታ ግራ የገባውም የእውነት ዲፕረስድ ሆኖ የዝቅታ ወለል ላይ የሚንፈራገጠውም <ተደብርያለሁ> ስለሚል አብዛኛው ሰው የነገሩን ክብደት አልተገነዘበም!! ሁሉም የየራሱ ውጣ ውረድ አለበት እና ሌላውን ከመስማት ይልቅ የራሱን ወልጋዳ ማቅናት ላይ ይጠመዳል። በዚህ መሃል የእውነት እርዳታ የሚያስፈልገውም ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ ነገር ሆኖ ሳንደርስለት ለቀብሩ ከንፈር ለመምጠጥ እንደርሳለን። በትንሽ በትልቁ (መቀፈል ሁላ ስትፈልጉ) የእውነት ያልሆነ ራሴን አጠፋለሁ የምትሉ ሰዎች እረፉ!! ማስፈራርያ አይደለም!! በእናንተ ያልተገባ ባህሪ ምክንያት የእውነት ሀሳቡ የሚፈታተናቸውንም ችላ ብለናቸው ሞታቸውን እየሰማን ነው።

ስለዲፕረሽን የማውቀውን ልንገራችሁ!!

ድባቴ ወይም ዲፕረሽን ቀልድ አይደለም!!!! ምክንያቱ ብዙ ጊዜ ላይታይ ሁሉ ይችላል!! የአንድ ወይ የብዙ ነገሮች ፣ ያለፈ ወይም አሁንም እየሆነ ያለ የህይወታችን ክስተት ፣ በተለያዩ ነገሮች የሚከሰት ሜንታል ክራይሲስ ሰበብ …….. በብዙ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል። ራሱ ሰውየውም ለምን እዛ እንደተገኘ ማብራሪያ ላይሰጥ ይችላል። ምክንያቱ ስላልገባህ ወይም ሰውየው ካንተ መመዘኛ አንፃር ምንም ያልጎደለው ስለመሰለህ አታቅልልበት!!

ዲፕረሽን በአንድ ጊዜ ፍርሃትም ደግሞም ድካም/መዛልም ነው (እጅ መስጠት) ። መፈለግም አለመፈለግም!! መውደቅን ትፈራለህ ግን ላለመውደቅ ምንም ሙከራ ለማድረግ ከልክ በላይ ዝለሃል። አቅሙ የለህም!!
ጎደኞች እንዲኖሩህ ትፈልጋለህ ግን ወጥቶ ሰው ማግኘት ወይም ምንም ዓይነት ከሰዎች ጋር የሚያገናኝህን ገመድ ትፈራዋለህ!! ለብቻህ መሆን ትፈልጋለህ ግን ደግሞ ብቸኝነትን ትፈራለህ። እንቅልፍ እንዲወስድህ ትፈልጋለህ ፤ ቀናትን አልጋህ ውስጥ ትገላበጣለህ ግን እንቅልፍህ ተጣልቶሃል። ለምትወዳቸው እና ለሚወዱህ ስትል መበርታት አጥብቀህ ትፈልጋለህ ግን ከሰውነትህ ውስጥ አንዳች አቅም አያግዝህም!! እንደውም ለእነሱ ሀዘን ወይ ሀሳብ ማቀበልህ ተስፋ መቁረጥህ ላይ ይደረብልሃል። ነፍስህ አጥብቃ የምትነዘንዝህ በራስህ ላይ ተስፋ እንድትቆርጥ ነው።

ማንም ፈልጎት ወይም መርጦት አይደበርም!!! ይሄን መንገድ እያለፈ የመሰለህን ወዳጅህን «ተነስ! ንቃ! ተገልበጥ! የማይቻል የለም!! ከዚህ የበለጠ ስንት መከራ አልፈሃል?....... » ምናምን ብለህ የሰማኸውን ያልበሰለ ሞቲቬሽናል ስፒች ስለቀደድክለት አይበረታልህም!! እሱም ከራሱ ጋር ትግሉ « ያን ሁሉ መንገድ አልፌ እንዴት ዛሬን ተሸነፍኩ?» ነው።

<ትናንት ሲስቅ ሲጫወት አልነበር?> አትበለው። እሱም ተሽሎኛል ደህና ሆኛለሁ ብሎ ነበር ሲስቅ የዋለው። ከየት መጣ ያላለው ስሜት ዛሬ ላይ እንደጎርፍ ይዞት ሄዶ ጨለማ ውስጥ ራሱን አገኘው እንጂ!!

ለቀናት መልእክትህን አይከፍትልህም!!! ወይም ሚስድኮልህን አይመልስም!! ! ካንተ ጋር አታያይዘው! እልህ መጋባቱን ትተህ ደውል!! አሁንም ደውል! ለአስረኛ ጊዜ ደውል!! አላነሳልህም እንጂ ባንተ ተደጋጋሚ ሚስድኮል ውስጥ በድቅድቅ ቀኑ ላይ ….. ለሆነ ሰው ዋጋ አለኝ፣ መጥፋቴ ግድ የሚለው ሰው አለ ፣ ብጎድልበት የማጎድለው ሰው አለ ፣ የሚወደኝ ሰው አለ ……. የሚል መልዕክትህ ከሚታገለው እጅ መስጠት ጋር እንዲፋለም አቅም ይሆነዋል። ባይመልስልህም መልዕክት ላክለት። የእሱ መኖር ላንተ ምን ማለት እንደሆነ ፃፍለት !! <ለእኔ ስትል ጎብዝልኝ> በለው።

ካለበት ስሜት ለመውጣት እየሞከረ አይደለም ብለህ ልታስብ ትችላለህ!! <እዚህ ተኝተህ እየዋልክ እንዴት አይደብርህም ድሮ? እየተብሰለሰልክ ስለሆነ ነው የሚብስብህ > ምናምን አትበለው። አልገባህምኮ ድባቴ ውስጥ ላለ ሰው ከአልጋው ወርዶ መብራት ማብራትን ዓይነት ቀላል ክንውን እንኳን የማይገፋ ዳገት እንደሚሆንበት። ከራስህ ጋር እያወዳደርክ አትፍረድበት። እየታገለኮ ነው አቅቶት እንጂ!!

ሲኦል የሆነ የህይወቱን ቀን እያለፈ ስለሆነ የተቀየረ ፣ የገፋህ ፣ ያልፈለገህ ሊመስልህ ይችላል። እመነኝ ከመቼውም በላይ የምታስፈልገው ጊዜ ያ ነው። ባታወራውም አጠገቡ ሁንለት!! በዛች ሰዓት <መኖር በቃኝ !> እያለች የምትፈታተነውን ነፍሱን አጠገቡ ስለተጋደምክ ብቻ ልታስመልጠው ትችላለህ!! ማውራት ከፈለገ ያለምንም ፍርድ ጆሮህን ስጠው!! ብቻዬን መሆን ነው የምፈልገው ቢልህም <እኔ ግን ታስፈልገኛለህ!! አለሁልህ > በለው!! በሚያምንበት እምነት ወደአምላኩ እንዲለምን ምክንያት አቀብለው!! አብረኸውም ፀልይ!! ህክምና የሚያገኝበትን መንገድ ማስተካከል ከቻልክ እባክህ እርዳው!!!

አንተ ያልገባህ ነገር ሁሉ ተራ ፣ ትንሽ ፣ ቀላል ..... ነው ማለት አይደለም!! simply አንተ አልገባህም ማለት ብቻ ነው!! በማይቀለድ ነገር አንቀልድ!! ትኩረት የሚሻን ደግሞ ችላ አንበል!!!

(ትናንት ለራሱ ፕሮፋይሉን አጥቁሮ እንደሚሞት ተናግሮ ራሱን ያጠፋውን ልጅ ሳየው ተሰምቶኝ የፃፍኩት ነው።)

በተረፈ ደግሞ ውብ ሰንበት ዋሉልኝ ❤️❤️❤️
ቤተሰብ❤️❤️❤️ የዛሬውን ክፍል 19 ነገ ጠዋት ነው የምለጥፍላችሁ❤️❤️❤️ 🙏🏽🙏🏽🙏🏽🙏🏽

አትጠብቁኝ ተኙ ለማለት ነው!!! ... ፊልም ቢሆን ሲዝን አንድ እንዳለቀ ቁጠሩትና አንድ ቀን አርፈን እንቀጥላለን 🤣🤣🤣🤣

ይሄ በእንዲህ እንዳለ ግን ባትነጫነጩ ደስታዬ ወደር የለውም!! 🤪🤪

ውብ ምሽት አምሹልኝ❤️❤️❤️❤️
#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል አስራ ዘጠኝ)
(ሜሪ ፈለቀ)

እንዲህ ነው የሚመስለኝ :- የራሴን ህይወት ራሴው ኖሬው እና ሌላ ሰው ሆኜ ደግሞ ከውጪ ሳየው!! ራሴን ሌላ ሰው ሆኜ ባየው ምን አይነት ሰው ነኝ ብሎ አስቦ የሚያውቅ ሰው ይኖራል? እድሉ ተሰጥቶትስ ራሱን ከውጪ ቢያየው ስንት ሰው ራሱን ይወደዋል? ወይስ ይፀየፈዋል?

እንግዲህ መታደል ይሁን መረገም እኔ የደረሰኝ ይህ እጣ ነው!! እንደ ሌላ ሰው ከውጪ ያየኋትን የድሮዋን ሜላት ድጋሚ መኖር ወይም ሌላ ሜላትን መፍጠር ደግሞ ከፊቴ ያሉ ምርጫዎች ናቸው። ሁለቱም አስፈሪ ምርጫ ነው!!!

በደም በተለወሰ ልብሴ ደሙ እጅና ፊቴ ላይ ደርቆ የሆስፒታሉ መጠበቂያ ቦታ ለሰዓታት ከአንዱ ቦታ ወደሌላው እንደፌንጣ እየዘለልኩ ነው ይሄን የማስበው። ስንት ሰዓት እንደጠበቅን ከማላውቀው ጊዜ በኋላ ከዛ ውጥንቅጥ ቦታ ይዞን የመጣው የጎንጥ ወዳጅ ወንበሩ ላይ ከነበረው ሰውነት በግማሽ ያነሰ መስሎ ተኮራምቶ እንደተቀመጠ

«መታጠቢያ እኮ አለ ቢያንስ ደሙን ከሰውነትሽ ታጠቢ!! ወይ መቀየሪያ ልብስ ላምጣልሽ?» ያለኝ እሱም እንደእኔ ሰውነቱ በደም መቅለሙን ሳያውቀው ይሆን እንጃ!! <አንተምኮ ደም ብቻ ነህ!> ማለት እፈልጋለሁ ግን አፌ ተለጉሟል። አውልቄ የጎንጥን ደም ለማስቆም ቁስሉ ላይ ይዤው የነበረውን ሹራቤን ይዞት ነው የተቀመጠው። - የኪዳን መልዕክት!! ዘልዬ ተነስቼ ሹራቡን ስወስድበት ብርግግ ብሎ አፈጠጠብኝ!!

«ሜል ይቅርታ እሺ!! ብዙ የምፅፍበት ጊዜ እና ሁኔታ ላይ አይደለሁም!! ማስታወስ እንደማትችዪ ሲያወሩ ሰምቻለሁ። ነገሮችን ስገጣጥማቸው ገባኝ!! እመቤትን እመኛት!! ያለችሽ ብቸኛ ጓደኛ እሷ ብቻ ናት!! ሌላው እኔ ማን እንደሆነች ብዙ ያልገባኝ አምነሽ ቪዲዮዎቹን ኮፒ ያስቀመጥሽባት ሴት አሁን ከእነርሱ ጋር ናት!! በቢዲዮዎቹ እየተደራደረች ነው!! እንዳታምኛት!! ታውቂ የለ እወድሽ የለ?»

«ይህቺ ከንቱ!» አልኩኝ ሳላስበው!! ወትሮም ጓደኛዬ አይደለችም!! ጥቅም ነው ያገናኘን!! እኔ ለጥቅሟ የምደምርላት ነገር እንደሌለ ባወቀች ቅፅበት ልትቀብራቸው ጉድጓድ ስትምስ የኖረችባቸው ሰዎች ጋር ሌላ የጥቅም ወጥመድ የዘረጋችበት ፍጥነት ……. ድሮም ትርፍ ካገኘችበት የገዛ ባሏን ከመሸጥ የማትመለስ ነጋዴ መሆኗን አውቃለሁ። የከንቲባው ሚስት ናት!! ባሏ ከንቲባ ከመሆኑ በፊት ከደሳለኝ (ኪዳንን ያገተው ሰውዬ) ጋር ወዳጃሞች ነበሩ!! ለአንድ ቦታ ለመመረጥ ፉክክር እስከጀመሩባት ጊዜ አንዳቸው ከሌላቸው ቤት የማይጠፉ፣ ልጆቻቸው እንደእህትና ወንድም የተቋለፉ ፣ ሚስቶቻቸው ከፀጉር ቤት እስከ ትልልቅ የህዝብ መድረክ ተቆላልፈው የሚተያዩ ዓይነት ነበሩ። ከንቲባው ሞተሩ ሚስቱ ናት እንደፈለገች በቀን ሙዷ የምታሾረው እንጂ የዋህ ቢጤ ነው። ደሳለኝ በገዛ ፍቃዱ ከውድድሩ ራሱን እንዲያገል ያን መረጃ ከእኔ ጋር በልዋጭ ጥቅም ተደራድራ ነው!! ተማምነን አይደለም የጠላቴ ጠላት በሚለው ተወዳጅተን እንጂ!! እከኪልኝ ልከክልሽ ተባብለን ነገር ……. እኔ አደጋ ላይ ብወድቅ እሷጋ ያለው ቅጂ ማስያዣ እንዲሆን ፤ እሷ አደጋ ላይ ብትወድቅ እኔ ጋር ያለው ቅጂ መገበያያ እንዲሆን ነበር ውላችን!! ድንገት በአንድ ቀን ጀንበር ያለድካም የተገነባ መተማመንም አልነበረም!! ከአንዲት 10 ሺህ ህዝብ ከሚኖርባት መንደር ወጥቼ ስልጣኑና አቅሙ አለን ከሚሉት ወንበዴዎች ጋር ለመግባት ለመውጣትስ የተጓዝኩት ጉዞ ቢሆን በቀላል ድካምና ላብ የተገነባ መች ነበር?

«የአቶ ጎንጥ ቤተሰቦች?»

ዘልዬ ተነሳሁ!! ዶክተሩ ከማውራቱ በፊት ነገረ አካላቴን በሀዘኔታ እያየ ነው ቀዶ ጥገናውን በስኬት መጨረሱን የነገረን።

«እስኪነቃ ድረስ እቤት ሄደሽ ተጣጥበሽ ልብስሽን ቀይረሽ መምጣት ትችያለሽ!!» አለኝ የጎንጥ ወዳጅ!! አልሄድኩም!! ተናኜጋ ደውዬ የምቀይረው ልብስ እንድታመጣልኝ አደረግኩ። ስልኩን ስዘጋ ተናኜ መርሳቴን አስታክካ የተቀበለችውን ደሞዝ ድጋሚ እንደተቀበለችኝ አስታውሼ ፈገግ አልኩ። የጎንጥን መመታት ስነግራት ያዙኝ ልቀቁኝ ማለቷስ? የአባቷን ለቅሶ የተረዳች አስመስላ አረፈችው። ልብሴን ቀያይሬ እንድትረጋጋ ላሳያት የተኛበት ክፍል ይዣት ብገባ ተኝቶ ስታየው ያን ለቅሶዋን አመጣችው። የልብሷን አንገትጌ በእጇ ጨምድዳ ይዛ ወደአፏ አስገብታ ንክስ አድርጋ…… <ህእእ > እያለች ሳጎን ወደ ውስጥ እየሳበች ተነፋረቀች።

«ምን ልሁን ነው ምትይ?» ሲል ነው መንቃቱን ያየነው። ይሄኔ ግራ የገባው ስሜት ተሰማኝ። የሆነኛው ልቤ (የሁለት ወሯ ሜላት ልብ ይመስለኛል) ስለነቃልኝ መፈንጠዝ ፣ አጠገቡ ሄጄ መነካካት ያምረዋል። የሆነኛው ልቤ (የድሮዋ ሜላት ልብ ይመስለኛል) ቆጠብ ማለት ፣ ኮስተር ማለት ያምረዋል። አጠገቡ ደረስኩ ግን እጁን ሊይዘው የተዘረጋ እጄ መንገድ እንደሳተ ነገር የአልጋውን ጫፍ ጨበጠ። ቅድም ሁለት ምርጫ አለኝ አላልኳችሁም? ወይ አሮጌዋን መሆን ወይ አዲስ መሆን? ሁለቱንም መሆን እንደማልችል እዚህ ጋር ገባኝ!! ቢያንስ በጎንጥ ጉዳይ!! ልቤ እና ሰውነቴ እንዳልተስማሙ ገብቶታል መሰለኝ ተናኜም ወዳጁም እግራቸው እንደወጣ ጠብቆ

«ተቀይመሽኝ ነው እንዴ?» ሲለኝ እስካሁን ስለማንነቱ፣ ስለዋሸኝ ዘበኝነቱ …… ተያያዥ ነገር ጭራሽ አለማሰቤ ገረመኝ። እዛ መኪናው ጋር ራሱን ከፊቴ አድርጎ የእኔን ሞት የተጋፈጠልኝ ሰዓት መቀየሜን ተውኩት? እዛጋ የበደለኝን አጣፋሁት?

«ቅያሜ አይደለም ያለኝ ጥያቄ ነው» አልኩት። ፈገግ ብሎ <ጠይቂኝ> እንደማለት በእጁ ወዲህ በይው ዓይነት ምልክት ሰራ። ወንበሩን ስቤ ከፊቱ እየተቀመጥኩ። <እዝህችው ቆመን 19 መቶ ብዬ እንዳወጋሽ አይደለማ ሀሳብሽ?> ብሎ የጮኸብኝ ትዝ ብሎኝ

«ገና ከመንቃትህ 19 መቶ ዓመተምህረት ብለህ ልታወጋኝ አይደለምኣ ሀሳብህ? (ፈገግ አለ) አንተ ጥለኸኝ የመጥፋት ሀሳቡ ከሌለህ በቀር እኔ የትም አልሄድም ያንተ እና የእኔ ጉዳይ ይደርሳል። ኪዳንን ጭረት ሳይነካው ዛሬውኑ ከዛ ቤት እንዲወጣልኝ ማድረግ አለብኝ።» አልኩት።

******

ልጅነቴ አጎቴ እንዳለው በጀግንነት እና ጀብድ ብቻ የተሞላ አልነበረም። ያ እነሱን ሆነው ሲያዩት የገባቻቸው ሜላት ናት። አባቴ የሞተበት ቦታ እየሄድኩ ሬሳው የነበረበት ቦታ ተቀምጬ በለቅሶ የምደነዝዝባቸውን የትዬለሌ ሰዓታት እሱ አያውቅም!! እናቴን የደፈራት ሰውዬ ፊት ለዓመታት በህልሜ እኔኑ ሲደፍረኝ እያየሁ በላብ ተጠምቄ ስንቀጠቀጥ የነጉትን ቁጥር አልባ ለሊቶች እሱ አያውቅም። ከሞቱ በፊት የነበረው የአባቴ ፊት ጠፍቶብኝ አባቴን ሳስብ የማስታውሰው የዛን ቀን ያየሁትን ፊቱን እየሆነብኝ ተሰቃይቼ ፎቶውን አቅፌ ማደሬን አያውቅም!! እናቴ ተመልሳ ትመጣ ይሆናል ብዬ ስንት ቀን እንደጠበቅኩ አያውቅም። አባቴን የገደሉብኝን ሰዎች ኮቲያቸውን ልኬት ሳይቀር በጭንቅላቴ ውስጥ ስዬ እንዳስቀመጥኩ አያውቅም!! ብዙ አያውቅም !! ብዙውን አልተናገርኩም!!

የማይቆጠር ጊዜ ቀዬውን ጥዬ ልሄድ አስቤ አውቃለሁ። አንድ ቀን ኪዳን ከትምህርት ቤት ሲመጣ እኔ እቤት አልነበርኩም!! እያለቀሰ ስሜን እየተጣራ ሲፈልገኝ አገኘሁት
«ምን ያስለቅስሃል? ማን መታህ?» ነበር እንዳየሁት ያልኩት
«እ እ…. አንቺም እንደእማዬ ትተሽኝ አትሂጂ !! እንደአባዬ አትሙቺብኝ!» ብሎ ሲንሰቀሰቅ መቼም እንደማልተወው ለራሴ ቃል ገባሁ። በጊዜው እኔ ራሱ የሚያባብለኝ የሚያስፈልገኝ እንጭጭ ብሆንም ከእድሜዬ በላይ ሀላፊነትን ለራሴ ሰጠሁት። ከዛ በኋላ ነው ትምህርት ቤት ራሴ አድርሼ እመልሰው የጀመርኩት። ሁሌ ለሊት ተኝቶ ሲነቃ መጀመሪያ የሚያረጋግጠው የእኔን አልጋዬ ላይ መኖር ነው። ድንገት ቀድሜው ተነስቼ ካጣኝ በማጣት ሰቀቀን ሲፈልገኝ አገኘዋለሁ። የትም ጥየው እንደማልሄድ እንዲያምነኝ ብዙ ለሊት አቅፌው ካደርኩ በኋላ ነው ያመነኝ። የአባቴን ገዳዮች ከጠላኋቸው በላይ ጠላኋቸው።

በሽምግልና የታረቁ ጊዜ የተሰማኝ አጎቴ እንዳለው ቁጣ ብቻ አይደለም። መከዳት ነው የተሰማኝ!! የራሴን ወገኖችም ነው የተቀየምኩት። የእኔ እና የኪዳን ህመም ያላመማቸው ፣ እኔን አግልለው እነሱ የደስታ ጠቦት ጥለው የተቃቀፉ ……

አልገባቸውም!! አድጋ የአባቷን ደም ትበቀላለች ብለው ያጀገኑት ልቤ ውስጥ የበቀል ጥንስሴን እርሾ አድርገውበት ልቤ ልትፈነዳ እንደደረሰች። አልገባቸውም እሷማ ይሄን መንደር ታስከብራለች እያሉ ባሽሞነሙኑኝ ቃላት በጭንቅላቴ ውስጥ ያሉ ሌሎች የሰው ልጅ የመኖር መሰረታዊ ፍላጎቶቼን ሁሉ አንድ በአንድ በበቀል እንደተካሁ። አይዞሽ፣ በርቺ ብለው እጄን ይዘው ከድልድዩ ካደረሱኝ በኋላ እነርሱ ከጠላቶቼ ጋር ተመሳጥረው ቺርስ የተባባሉብኝ ዓይነት ስሜት ነው የተሰማኝ።

የአባቴ ገዳዮች ላደረጉት ነገር ሊቀጡ ሲገባቸው ግፋቸው ጭራሽ ክብር ሆኗቸው ስልጣን ሲሾማቸው የእኔው ወገን ሲያጨበጭብላቸው ብቸኝነት አጥንቴን ሰረሰረኝ። ብቻዬን የቀረሁ። ያውም ከነበቀል ጥማቴ!!

ባገኘሁት ሰው ላይ ሁሉ ከመደንፋት እና ከመደባደብ ውጪ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ስላላወቅኩ የማደርገው ጠፍቶኝ ሳለ ነበር አንድ ቀን ለክረምት ለክረምት አዲስ አበባ የሚሄደው ካራቴ አሰልጣኛችን በጉራ ሰውመሆንና የእሱ ቤተሰቦች አዲስ አበባ የሚጠያየቁ ወዳጃሞች መሆናቸውን ሲያወራ የሰማሁት ……. የዛን ቀን እንቅልፍ አልወሰደኝም!!! ከብዙ ጊዜ በኋላ የበቀል እቅዴን የማሳከበት መንገድ ጭላንጭል የታየኝ ስለመሰለኝ ሳቅኩኝ።

አዲስ አበባ መሄድ የሚለውን ሳስብ ደግሞ ከዚህ መንደር መራቅን አብዝቼ ሻትኩ። አዲስ ህይወት መጀመር የሚል ሀሳብ ልቤን በሀሴት ሞላው። አዲስ ያልኩት ህይወት መሰረቱ በቀል መሆኑ ካለፈው ህይወት ጋር እያመላለሰ እንደሚያላትመኝ የምረዳበት የአዕምሮ ብስለት አልነበረኝም!! ጭራሽም ከበቀል እና ከጥላቻ የተረፈ አዕምሮም አልነበረኝም!! የሚጠረጥርበት ምንም ፍንጭ ያልነበረው አሰልጣኝ አዲስአበባ ለክረምት መሄድ ማሰቤን እና ከተማውን እንዲያስለምደኝ ስጠይቀው ደስ ብሎት ነው የተስማማልኝ። ሰዎችን መጠቀሚያ ማድረግ የጀመርኩበት የመጀመሪያ ቀን መሆኑ ነው። ደሜ ውስጥ ከሚንቀለቀል በቀል ውጪ የሚሰማኝ የህሊና ደውል ስላልነበረ ያደረግኩት ብልጠት እንጂ ክፉት አልነበረም!! እንድደውልለት ስልክ ፅፎ ሰጠኝ።

«ኪዳንዬ ለሆነ ጉዳይ አዲስአበባ ደርሼ እመጣለሁ። ከዛ ግን መጥቼ እወስድህና አብረን እንኖራለን» አልኩት በራችን ላይ ቆሜ እሱ ከትምህርት ቤት መጥቶ እግሩን እየታጠበ ነበር። ያሰብኩት የነበረው ብቻዬን ሄጄ ከሸክም ጀምሮ ምንም ብሰራ ፣ ከዛ የተወሰነ ፍራንክ አጠራቅምና ኪዳንን አዲስ አበባ አምጥቼ አስተምረዋለሁ። ነው። የያዘውን ጆክ በቁሙ ለቀቀው እና እኔጋ መጥቶ እግሬ ላይ ተጠመጠመ። 15 ዓመቱ ነበር። ሁለቱንም እግሬን እንዳልፈናፈን አንድ ላይ ጨምቆ ይዞ

«የትም ትቼህ አልሄድም! ብለሽኝ አልነበር? ለምንድነው ይዘሽኝ የማትሄጂው? በዛው ልትቀሪ ነውኣ? አብሬሽ እሄዳለሁ!!» አለኝ እየጎረመሰ ባለ ድምፁ። አያለቅስም ግን ድምፁ ውስጥ ከለቅሶ የከበደ ሀዘን አለው።

«ኪዳንዬ አሁን ወስጄህ ምን አደርግሃለሁ? የምናድርበት ባይደላን ምን በወጣህ ውጪ ታድራለህ? የምንበላው ባይመቻች በምን እዳህ ትራባለህ? አንተ ገና ልጅ ነህ!! እኔ ይሰናከልብኛል የምለው የለኝም። አንተ ከትምህርትህ ለምን ትሰናከልብኛለህ?»

«ይኸው ትተሽኝ ሄደሽ ላትመለሽ ነው እንዲህ የምትዪኝ» አለ እግሬን ሳይለቅ

«እሺ በቃ ትቼህ አልሄድም!! አብረን እንሄዳለን!» ስል ራሴን ሰማሁት!! እዛው ላይ እንዴትም ብዬ ገንዘብ ማግኘት አለብኝ የሚለውንም አሰብኩ።

አስቤው አቅጄው ተለማምጄው ያደረግኩት ነገር አይደለም። 19 ዓመት እስኪሆነኝ ድረስ መግደልን እንጂ መስረቅን ለዓፍታም አስቤው አላውቅም!! ለመግደል ለራሴ በቂ ምክንያት ስለሰጠሁት ከመግደል ይልቅ መስረቅ ፀያፍ መሆኑን ነው ህሊናዬ የመዘገበው። በዛው ሳምንት ከአጎቴ ጋር እህል ልንሸጥ ትልቁ ገበያ አጅቤው ሄድኩ። አጎቴ እህሉን እያስረከበ አይኔ ተሻግሮ ከብት የሚገበያዩት ጋር ቀላወጠ። ነጋዴው ምን ያህል ከብት ቢሸጥ ነው እጁን ሞልቶ የተረፈ ገንዘብ የያዘው ብዬ እያሰብኩ ጭንቅላቴ ወዲያው ይሄ ሁሉ ብር ቢኖረኝ ኪዳንን ይዤ አዲስ አበባ የምኖረው ህይወት ታየኝ። ሰውየውን አየሁት አየኝ። ራሴን ገሰፅኩ!!

መረኑ ሀሳቤ <ያውም ጠላትሽ ነው> አለኝ። ለምሰራው ከእነርሱ ለባሰ ክፋት እና በቀሌ የምሰጠው ምክንያት ያ ነው። ድክመቴ!! እናት እና አባት ያሳጡኝ ሰዎች ናቸው!! ከሰውየው አይን ተሰውሬ ገበያውን ለቆ ሲወጣ ተከተልኩት። መውጫው ላይ ከሌሎች ሁለት ሰዎች ጋር ገጥመው ወደቀያቸው የሚወስዳቸውን መንገድ ተያያዙት። አድብቼ ተከተልኳቸው። አስር ወንድ ገጥሜ የማልፈራዋ ሴት እግሬ ተልፈሰፈሰብኝ!! እጄ አላበው!! በጥሻው አልፌ ከፊታቸው ብቅ አልኩ

«ልጎዳችሁ አልፈልግም!! እንደዛ እንዳደርግ አታስገድዱኝ!! ብር ነው የምፈልገው ብራችሁን ብቻ አውጥታችሁ እዚጋ አስቀምጡና ሂዱ!» አልኳቸው። እኔ መሆኔን ሲያውቁ ገና ብርክ ያዛቸው ….. ሽጉጥ መያዜን ሲያዩ በያዙት ሽመል ተስፋ ቆረጡ። አንደኛው ግን ወንድነቱ አነቀው። ሁለቱ ብራቸውን አስቀምጠውት መንገድ ሲጀምሩ እሱ ካልገጠምኩሽ አለ። አልምታህ ብዬ ለመንኩት።

«ግደይኝ» አለ። ቶሎ ካልሄድኩ መንገደኛ መጥቶ ሌላ አምባጓሮ ሊፈጠር እና ፖሊስ ሊመጣ ሆነ። በቆመበት ጉልበቱን ወደጎን ስረግጠው ህመሙ የእኔ ጉልበት እስኪመስለኝ ታወቀኝ። ብሩን አንስቼ ጢሻው ገባሁ። ለዘመናት ያላነባሁትን እንባ እያነባሁ ወደቤት ሮጥኩ። ሰውነትንም ከእንባዬጋ አብሬ አጥቤ ከሰውነቴ አስወጣሁት።

......... አልጨረስንም .........

ውብ ቀን ውብኛ ዋሉልኝማ ❤️❤️❤️

(እባካችሁ አንዳንዶች በኮመንት ያልሆነ ነገር አትበሉ። (ስድብ ማለቴ ነው) ስቀርና ስመጣ የማሳውቃችሁ አክብሬያችሁ እንጂ ስለቀረሁ ወይ ስላረፈድኩ የምቀጣው ደሞዝ ኖሮኝ አይደለም!! ትህትናዬን እንደመተናነስ አትቁጠሩብኝ!! ደስ አይልም!! )
ክፍል 20 አይደለም!!! ዛሬ የእኔ ቀን ነው!! ዛሬ ልደቴ ነው!! ለሊት ዘጠኝ ሰዓት አላርሜ ሲጮህ የነቃሁት ክፍል 20 ልፅፍ ነበርኮ !! ድንገት ስልኬን ስከፍት ልጄ የላከችልኝን የመልካም ልደት መግለጫ ፅሁፍ አገኘሁ!! ተነፋርቄ ሳላበቃ ጓደኞቼ የላኩልኝን ስብስብ ቪዲዮ አገኘሁ። (ወደኋላ ፌቡ ላይ ሁሉንም አጋራለሁ!!) ለካ ባላውቀውም መስማት የምፈልገው ነገር ነበር። ከፍቶኝ ከማለቅስ ደስ ሲለኝ የማለቅሰው ይበዛል!! ይኸው በዚህ ለሊት ደጋግሜ እየሰማሁ እየተነፋረቅሁ ነው። እና ምን ልላችሁ ነው! ዛሬ የእኔ ቀን የምንም ጎንጥ የምንም ሜላት የሉም!! ዛሬ የሜሪ ቀን ነው!! ዛሬ ሜሪ ናት!! 38 ዓመቴ ነው!! ቴሌግራም ላይ በፅሁፉ መሃል ስለራሴ እየፃፍኩ እንዳልቆራርጠው (ምክንያቱም ነፍፍፍ ጊዜ ነው የምፅፈው) ፌስቡክ ላይ ስመላለስ እውላለሁ። አብራችሁኝ ማክበር ካሻችሁ የፉስቡክ ገፄን ከዚህ ታች አኖርላችኋለሁ።
#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል ሀያ)
(ሜሪ ፈለቀ)

እነዛ ጫማ ያልለበሱ እግሮቻቸው ፣ የከብት ሽታ የሚሸት አዳፋ ልብሳቸው ፣ ያለፉበት መከራ የተፃፈበት የግንባራቸው መስመር ፣ ዘመናቸው ድሎት እንዳልጎበኘው የሚያሳብቁት ሻካራ እጆቻቸው ፣ ብራቸውን ስወስድባቸው እንድራራላቸው የሚለማመጡ ከርታታ ዓይኖቻቸው …….. ከአጠገባቸው ርቄ እንኳን አልራቀኝም!! የስንት ቀን የልጆቻቸው ምሳና እራት ይሆን? ምናልባት የሚያፈስ ቤታቸውን ሊያድሱ ይሆናል! ምናልባት የሚከፍሉት እዳ ይኖርባቸዋል! …… ብዙ ርቄያቸው ከሄድኩ በኋላ በጉልበቴ መሬቱ ላይ ዘጭ አልኩ!! አባቴ <ጀግና አያለቅስም!> ብሎ ቢያሳድገኝም ዛሬ መጀገን አቃተኝ! ለአፍታ ተመልሼ ሄጄ ብሩን ሰጥቻቸው የመምጣት ሀሳብ ሁላ ሽው ብሎብኝ ነበር። ይሄ ምስላቸው ለዓመታት ስቃዬ ነበር። ከበደሉኝ ሰዎች እኩል የበደልኳቸው ሰዎች ፊት እንቅልፍ የማያስተኛ ቅዠቴ ነበር። ለደቂቃዎች እዛው በጉልበቴ ከተንበረከኩበት የመጨረሻዋን አውቶቡስ ተሳፍረን አሁኑኑ ካልወጣን ፖሊሶቹ እኛ ቤት ለመድረስ ምንም የምርመራ ሂደት እንደማይፈጅባቸው ሳስታውስ ተነሳሁ::

እንባዬን ጠራርጌ ሮጥኩ!! ያገኘሁትን የእኔን እና የኪዳንን ልብስ በፔስታል ጨመርኩ። ያለችንን አንድ ለእናቱ ጫማ ተጫምተን ወደመነሃሪያ እጁን ይዤ መሮጥ ጀመርኩ። መነሃርያው አካባቢ ስንደርስ ከኋላዬ ሁለት በእድሜ ጠና ያሉ የኛ አካባቢ የማይመስሉ ሰዎች ሲያወሩ ወሬያቸው ጆሮዬን ጠለፈው።

«የወዲያ ቀዬ ሰዎችን ዛሬ ሽፍታ ዘረፋቸው የሚሉትን ወሬ ሰማህ?»

«ኸረ አልሰማሁም!! ወደየት ግድም?»

«ከገበያው ጫፍ ትንሽ ቢርቁ ነው አሉ!! አንደኛው ይሄ በሬ ሻጩ አያልነህን አታውቀውም?»

«አያልነህ? አያልነህ?»

«ይሄ ሲያወራ ምራቁን እንትፍ የሚለው? ይህ እንኳን ወንድ ወልዳለሁ ብሎ ሲተኛ ስድስት ሴት ያሳደገው? በመጨረሻ ሚስቱ ወንድ ልጅ ሰጥታው እንዴየውም ደግሶ ያበላ ጊዜ አቅልህን እስክትስት ጠጥተሃልይ!!»

«እንዴ? እንዴ? አያልነህ በሬ ሻጩ?»
«ኤድያ እንዴት ያለው እንከፍ ነው? ምን እያልኩት ምን ይላል?»

ፍጥነቴን አቀዝቅዤ ወሬያቸውን ከሰማሁ በኋላ ድጋሚ መፍጠን ጀመርኩ። <አያልነህ> የሚለው ስም ጭንቅላቴ ውስጥ ልክ እንደዛ የአባቴን ሬሳ ተራምዶት እንዳለፈው ሰውዬ ኮቴ ታተመ።

«ሜል? ምን ሆነሽ ነው የምታለቅሽው?» ብሎ ኪዳን ዓይን ዓይኔን እያየ ሲቁለጨለጭ ነው እንባዬ እየወረደ መሆኑን ያወቅኩት።

«ምንም አልሆንኩም!!»
«ምንም ሳትሆኚ ታዲያ እንባሽ ይፈሳል? እኔ ይዘሽኝ ካልሄድሽ ብዬ ስላስጨነቅኩሽ ነው?»

«ይሄ ደግሞ! ለምን አርፈህ አትሄድም? እኔ አስጨንቀኸኛል አልኩህ?» እየተነጫነጭኩ እንባዬን ጠርጌ ትኬታችንን ቆርጠን አውቶብስ ውስጥ ገባን!! ከከተማዋ እየወጣሁ በአውቶብሱ መስኮት ወደኋላዬ የሚያልፈውን ተወልጄ ያደግኩበት መንደር ሸኘሁት። ድብልቅልቁ የወጣ ስሜት ተሰማኝ። ትቼው ስሄድ ሀዘን ካጠላበት ጊዜያቶች ይልቅ የታሰበኝ

የአባቴ ትከሻ ላይ እሽኮኮ ተደርጌ ከጫካው እስከ ጠላ ቤት ግርግሩ ስዞር ጠላ ቤት እግሩ ላይ አስቀምጦኝ በሰዓቱ የማይገቡኝን ወሬዎች እየቀደደ ጠላውን ሲጠጣ እናቴ ከሩቅ እየተራገመች መጥታ «ልጅቱን ጭራሽ አምቡላችሁ መሃል ይዘሃት ትመጣ?» ብላ ከእግሩ አንስታኝ የምትሄደው

አባቴ ገበያ መሃል ጠብመንጃውን እንዳነገተ ሲያልፍ አላፊ አግዳሚ ከአንገቱ ጎንበስ ብሎ ከልብ በሆነ አክብሮት ሰላምታ ሲያቀርብለት ትከሻው ላይ ሆኜ የተቆነንኩት

ከወዳጆቹጋ ሰብሰብ ብሎ ዳማ ከሚጫወትበት አብሬያቸው ሳነግስ እማዬ ትመጣና <ልጄን በቃ ወንዲላ አድርገህ ባልም ልታሳጣብኝ ነው!> ብላ ገና በ10 እና በ11 ዓመቴ ሀሳብ የሚገባት የነበረው

አንድ ቀን አባቴ ሽጉጡን አስይዞኝ ስታይ ለቅሶ እንደተረዳች ጭንቅላቷን ይዛ እሪሪሪሪሪሪ ብላ ጮሃ ጎረቤት አሰብስባ «ይሄን ሰው አንድ በሉኝ» እያለች ወገቧን ይዛ የተንጎራደደችው

እናቴ ከምትሸጠው ፍራፍሬ ላይ ከገበያ ስትመለስ ለምድረማቲ ትሰጥና እኛ ቤት ደጅ ላይ የተሰጠንን እየበላን የምንዘለው

ከትምህርት ቤት ስንመለስ ከቤተሰብ ተደብቀን ወንዝ ወርደን እየተንቦጫረቅን ባልተገረዘው ልጅ ወ*ላ ንፍር ብለን የምንስቀው

ክረምት ላይ እማዬ ቡና እያፈላች የተቀቀለ በቆሎ እየጋጥን እጣኑን ስትሞጅረው <አስካል ጥይት ያልገደለኝን ጀግና በጭስ ልትገይኝ ነው ሀሳብሽ?> ሲላት ከተናገረው ውጪ እሷ ምን እንደገባት ሳይገባን እንደመሽኮርመም እያደረጋት <እንደው ወሬ ስታሳምር ቅም!> እያለች ጭሱን በተን በተን ስታደርግለት የነገሩ ውል ምን እንደሆነ ባይገባንም እኔና ኪዳንም አብረናቸው የምንሽኮረመመው

<አስካል ነይ እስኪ ጀርባዬን ዳበስ ዳበስ አድርጊኝ በሞቴ!!> ሁሌም መምጣቷ ላይቀር ጓዳ ሆና <እስኪ ስራ አታስፈታኝ አንተ ሰውዬ> ስትል <ተይዋ ነይማ አምሳሌ!> ይለኛል እንደመጥቀስ እያደረገኝ። እጇን እያደራረቀች እያጉረመረመች መጥታ ትከሻውን ጀርባውን የምታሸው

እንዲህ እንዲህ ዓይነቱን ቀን ነው ያስታወስኩት! አስታውሼም በአውቶብሱ መስኮት የሸኘሁት!! አባቴ የሞተ ቀን ይሄ ሁሉ አብሮ ከአባቴ ጋር የተቀበረ ሳይሆን ልቤ ያን ንፁህ የልጅነት ጊዜም ልብም ዳግም ላላገኘው ልክ የዛን እለት የተሰናበትኩት ያህል አንሰፈሰፈው ……. ሁሉም ነገር ልክ የዛን ቀን የተሰናበትኩት ያህል….. የሚገጥመው አቀበት ታውቆት ነበር መሰለኝ! የአብቶብሱ መቀመጫ ላይ አጠገቤ የተቀመጠውን ኪዳን ጭምቅ አድርጌ አቅፌ
«አንተ አብረኸኝ ስላለህ ደስ ነው ያለኝ!! የማለቅሰው አጎቴ ስለሚናፍቀኝ ነው!! ሰፈሩ ስለሚናፍቀኝ ነው!! ባንተ አይደለም እሺ!!» እያልኩት ተደጋግፈን እንቅልፍ ወሰደን!!

አዲስ አበባ

አዲስ አበባ <እንኳን ደህና መጣችሁ!> ብላ አልተቀበለችንም!! አውቶብስ ተራ እንደወረድኩ ነው ይሄ ከእኔ ዓለም በምንም የማይገጣጠም ውቅያኖስ እንደሆነ የገባኝ!! አዲስ አበቤዎች ሲያወሩ እንኳን የሚደማመጡ አይመስሉም። ሁሉም ያወራል፣ ሁሉም ይራወጣል፣ የተረጋጋ የለም! የት ሊሄዱ እንደሚቸኩሉ እንጃ ቸኩለው እያወሩ ቸኩለው እየተገጫጩ ይተላለፋሉ። ከራሱ መንገድ ውጪ ማንም በአካባቢው ያለውን አያስተውልም። በጩኸቱ ጆሮዬ ዛለ። ኪዳንን በአንድ እጄ ጥፍንግ አድርጌ ይዤ በሌላ እጄ ልብሳችን ያለበትን ፔስታል ይዤ <አልጋ> የሚሉ ልጆችን ተከትዬ የዛን ቀን የትኋን እራት ሆነን አደርን!! አዲስአበባ ቀማኛው ብዙ ነው ሲሉ ስለሰማሁ ምግብ ልንበላ በገባንበት ሁሉ የማየውን በጥንቃቄ እከታተላለሁ። በሀገሬ ባለፍኩ ባገደምኩበት ሰው የሚጎነበስልኝ ፣ ሁሉ የሚያውቀኝ ነበርኩ:: ….. እዚህ ባዳነት ተሰማኝ። እዚህ ማንም ነኝ!! ከኪዳን ውጪ የሚያነጋግረኝ እንኳን የሌለ ማንም ነኝ!!

በበነጋታው ስልክ መደወያ ቦታ ፈልጌ አሰልጣኙጋ ስልክ ደወልኩ እና ያለንበት መጣ!!! የምንከራየው ቤት እስካገኝ እቤቱ ይወስደኛል መቼም የእግዜር እንግዳ ዝም አይባልም ብዬ ስጠብቅ እሱ እቴ!! የዛኑ ቀን በእጁ በያዛት ስልክ ለደላሎች ደውሎ ቤት እንዲፈልጉ ነግሮልኝ የማላውቅበት ምድረ ገበያ ህዝብ የሚተራመስበት ሰፈር አልጋ አስይዞን ሄደ። አሁን ብቻዬን እንደሆንኩ አወቅኩ!! አባት እና እናቴ የሉም! አጎቴ የለም! አሁን ለኪዳን እነሱን መሆን ያለብኝ እኔ ነኝ ለካ!!

አንዲት ትንሽዬ የጭቃ ቤት በአስጠኚው በኩል አጊንተን ተከራየን!! የምንተኛበት እና የምናበስልበት ዕቃ ገዛን!! ኑሮ ተጀመረ!! መጀመሪያ አካባቢ መኪና ማጠብ ስራ አገኘሁ። አምስት መኪና በነፃ ካጠብኩ በኋላ ነው የቀጠሩኝ። ሰፈሩን መውጫ መግቢያ ተሽሎክልኬ አወቅኩት። የሆነ ቀን ጠዋት ከኪዳን ጋር ዳቦ በሻያችንን በልተን ከቤት ልወጣ ስል

«ሜል?»
«ወዬ»
«እንዳትቆጭኝ! አልቆጣህም አባባ ይሙት በይ!» አለኝ ከዓመታት በኋላም የሞተውን አባቴን እየገደልን ነው የምንምለው።
«አባባ ይሙት አልቆጣህም ምንድነው?»
«እኔምኮ ትልቅ ልጅ ሆኛለሁ!! ስራ ፈልጌ የማልሰራው ለምንድነው?» አለኝ እንዳልቆጣው እየተሳቀቀ

«አባባ ይሙት እቆጣሃለሁ!! ሁለተኛ እንዲህ እንዳትለኝ!! አንተ አርፈህ ተቀመጥ ከወር በኋላ ትምህርት ሲጀመር ትምህርትህን ወጥረህ ትማራለህ!! ስራህ ትምህርትህ ነው!! ተግባባን?» ብዬ እንደፈራውም ጮህኩበት

«አዎ» ሲለኝ ስቅቅ ብሎ አሳዘነኝ እና አቀፍኩት።

«ላንተ ብዬኮ ነው!! ታውቅ የለ እንደምወድህ? አንተ ተምረህ ስራ ስትይዝ ያኔ አንተ ትሰራለህ እኔ እቤት እቀመጣለሁ!! አሁን ግን እኔ ታላቅህ አይደለሁ? እኔ እሰራለሁ አንተ ትማራለህ!!» ስለው ጭንቅላቱን ነቀነቀ። እናት መሆን ፣ ልጅ ማሳደግ : እናት መቼ እንደምትቆጣ: መች እንደምታባብል : መች እንደምትቀጣ ... ምኑም በቅጡ ሳይገባኝ ለካ እናትም የመሆን ሀላፊነትን ወስጃለሁ።

የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት አንዱ በጉልቤነቱ የሚፈሩት ጥጋበኛ ሴት ሆኜ ከወንዶቹጋ መኪና ማጠቤን ሊያፌዝበት ሞከረ። ያልፈጠረብኝን አይ አለመተዋወቅ ብዬ ታገስኩት። በሌላኛው ቀን መጥቶ ግን ከኋላ ቂጤን ሲመታኝ መታገስ የምችልበት ልብ አጣሁ እና አፍንጫውን አልኩት። በቦታው የነበረው ሁሉ ደንግጦ ብድግ አለ። ልጁ ያልጠበቀው ቡጢ ስለጠጣ መጀመሪያ ተደናግጦ የደማ አፍንጫውን መጠራረግ ጀመረ። ቀጥሎ ግን ያዙኝ ልቀቁኝ ብሎ ሊገለግሉት የያዙትን ሁሉ እየተወራጨ ደነፋ!! እኔ በናታችሁ ልቀቁት ስል ፣ እሱ ከወድያ ልቀቁኝ ሲል …. አንድ በአንድ ሰው እየተሰበሰበ የፈሪ ድብድብ ሆነ። ድንገት ለቀቁት እና እኔና እሱ ተያይዝን። ለካስ ሲገላግሉ የነበሩት ልጆች የሸሹት ፖሊሶች መምጣታቸውን አይተው ነው። ፖሊሶቹ ማናችንንም ምንም የጠየቁትም ያጣሩትም የለም! አፋፍሰው ብቻ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱን።

<እባካችሁ ትንሽ ወንድሜ ብቻውን ነው> ብል ማን ይስማኝ? ጀርባዬ ላይ ካሳረፈው ጥቁር ዱላ ህመም በላይ የተሰማኝ የኪዳን ብቻውን በፍርሃት መራድ ነው። ትቼው የጠፋሁ ይመስለዋል? ሊፈልገኝ ወጥቶ መንገድ ይጠፋበት እና የማያውቀው መንደር መንገድ ላይ ሲያለቅስ ታየኝ። ብዙ ክፉ ነገር ታየኝ። ተንዘፈዘፍኩ። ደቂቃ ባለፈ ቁጥር ፍርሃት ከአንጀቴ ይተራመሳል። ሰዓቱ አይሄድም!! ማልቀስ እፈልጋለሁ ግን እንባ አይወጣኝም።

<ጥጋባቸው በርዶላቸዋል> ብለው በሚቀጥለው ቀን ጠዋት ሲለቁን እግሬ መሮጥ አቅቶት ተንቀጠቀጠ። የቤቱን በር አልፌ ስገባ ኪዳን ባይኖር የት ብዬ ነው የምፈልገው? ራሴን ረገምኩ! ደህና ተደላድሎ ከሚኖርበት ቤት ይዤው የወጣውበትን ቀን ረገምኩ። ሰውነቴ እየተንቀጠቀጠ በሩን ከፍቼ ስገባ ኪዳን ኩርምት ብሎ ፍራሹ ላይ ተቀምጧል። ሲያየኝ ዘሎ እላዬ ላይ ተሰቅሎ እንደህፃን ድምፅ አውጥቶ ማልቀስ ጀመረ። የሱ መርበትበት ይብስ አርበተበተኝ እና አብሬው እዬዬ ማለት ጀመርኩ። እህል ሳይበላ ከአሁን አሁን መጣች ብሎ ኩርምት ብሎ በር በሩን ሲያይ ነው ያደረው።

ፈሪ ሆንኩ! ለኪዳን ስል ፈሪ ሆንኩ!! ለእሱ ስል ብቻዬን ብሆን የማልውጠውን ብዙ መናቅ ዋጥኩ። ለእሱ ስል የማላልፈውን ውርደት አለፍኩ። አንገቴን ደፋሁለት!!! ከብዙ ስራ ቅየራ በኋላ …… ኪዳንም ትምህርቱን ብዙ ቀን ከተማረ በኋላ ….. ብዙ ጥጋበኛ አንገቴን ደፍቼ ካሳለፍኩ በኋላ …..….. በራሴው ሰውንም ከተማውንም መልመድ ከጀመርኩ በኋላ……. የከተማ ሚኒባስ ወያላ ሆኜ እቁብ መጣል ከጀመርኩ በኋላ …… አንድ ቀን ተሰብስበን ተራ የምንጠብቅበት ቦታ ኪዳን መጥቶ ሲፈልገኝ በእድሜ በጣም ከሚበልጠው ልጅ ጋር ነገር ተፈላለጉና ኪዳንን በቁመቱ አንስቶ በጠረባ ጣለው። ደርሼ ልጁን ሳንጠለጥለው ከሚፈላው ደሜ ውጪ የሚሰማኝ ነገር አልነበረም። ምን እንዳደረግኩ አላውቅም!

«ሜል!» ብሎ ኪዳን ሲለምነኝ ነው ጆሮዬ ድምፅ መስማት የቻለው። ፖሊስ ከመቼ መጥቶ ብዬ ስሳቀቅ ግርግሩ ሰክኖ የሆነ ሰውዬ ተጠጋኝ እና

«ስራ ልስጥሽ! እዚህ ከተሳፋሪ ፍራንክ እየለቃቀምሽ ፀሃይ እና ዝናብ እየተፈራረቀብሽ ከምታገኝው እልፍ እጥፍ ደመወዝ የሚከፈልሽ ስራ ላስቀጥርሽ! » አለኝ

«እንዴ ምንድነው ስራው ?» አልኩት

«ደውዪልኝ» ብሎ ስልኩ ያለበት ቢዝነስ ካርድ ሰጥቶኝ ሄደ። ተሰብስቦ የነበረውን ወሬኛ አላስተዋልኩትም ነበር።

«ኸረ በለው! በአንድ ቦክስኮ ስሙን ሁሉ ነው ያስረሳሽው!! መሬት ሲደርስ ኦልሬዲ ቤተሰቡን ዘንግቷል!!» እያሉ ትከሻዬን አቅፈው ማውራት ጀመሩ። ሊያዋራኝ ይኮራ የነበረ ሁላ ጓደኛዬ ሊሆን ሰበብ ይፈልግ ጀመር።

...... አልጨረስንም!!! ....
(ስለመልካም የልደት ቀን ምኞታችሁ ሁሉ አምላክ አብዝቶ ይባርክልኝ!! ውብ ቀን ውብኛ ዋሉልኝ!! ❤️❤️❤️❤️)
ቤተሰብ አፉ በሉኝ!! ለሊት early flight ስለነበረብኝ 11 ሰዓት የወጣሁ ስጦዝ ውዬ አሁን ገና ነው መቀመጫዬ ቤቱ ገብቶ መቀመጫ ያገኘው!! (የቡዴና ጉዳይ ነው!) ለሊት ነቅቼ እፅፋለሁ እንጂ አንድ መስመር እንኳን መጨረስ አልችልም!! ትወዱኝ የለ? ፌንት በልቼ (ማነው ግን ፌንት ይበላል ያለን? ምን ምን ይላል?) እናላችሁ ፌንት በልቼ ሜላት ስሙን እንዳዘነጋችው ሰውዬ የታሪኩን ሂደት ከምረሳባችሁ እረፍት አድርጌ በአዲስ መንፈስ ብፅፍ ይበጀናል።

ውብ አዳር!!❤️❤️
#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል ሀያ አንድ)
(ሜሪ ፈለቀ)

« የበፊቷን ሴት መሆን አልፈልግም!!!» አልኩት ኪዳንን እንዴት እንደምናስወጣው የሚያቀርበው አማራጭ ሁሉ የሆነን ሰው ህይወት አደጋ ላይ የሚጥል ሲሆንብኝ

«ይሆንልሻል ?» አለ ማደንዘዣው እየለቀቀው የቁስሉ ህመም እየተሰማው ሲያወራም ጭምር እየተሰቃየ ።
«ውስጥ ያለህ ሰው ካሜራ መግጠም የሚያስችል ቅርበት አለው?»
«ይመስለኛል!! ምን አስበሽ ነው? ስልኬን ከኪሴ ውስጥ ወዲህ በይውማ እርግጡን ልንገርሽ! በቅድሚያ ግን ያሰብሽውን ልስማው?»

አመነታሁ! ከራሴ ውጪ ማንንም ሰው አምኜ የማውቅ ሰው አልነበርኩም! አለማመን በደሜ ውስጥ ያለ ነገር ነው። በሁለት ወር ከምናምን ጊዜ ሙልጭ ብሎ ሊጠራ አይችልም። የብዙ ዓመት ልምዴ ሁሌም ጀርባ እና ፊቴን ራሴው ስጠብቅ ፣ በመንገዴ የተደገፍኳቸው ሲንሸራተቱብኝ ፣ ከጎኔ ናቸው ያልኳቸው ጎኔን ሲወጉኝ ….. ነው። አውቃለሁ እኮ ደረቱን ለጥይት ሰጥቶልኛል። በማንም ሰው ሚዛን ከዚህ በላይ ከእኔ ጎን መሆኑን ሊያሳይለት የሚችል ምንም ማረጋገጫ አይኖርም። በቃ ግን የዛች ሜላት ልብ አመነታ። ለአፍታ ዝም ስል ገብቶታል።

«አሁንም እምነትሽን አላገኘሁም ማለት ነው?? እንዲያው ምን ባደርግልሽ ነው የምታምኝኝ ዓለሜ?» የጎንጥ ድምፅ አይመስልም። ሳላምነው እንኳን የሚቆጣኝ ድምፅ ሳይሆን ምንም ማድረግ የማይችል በጣም የተከፋ ድምፅ ነው። ለሁለተኛ ጊዜ <ዓለሜ> ብሎ እንደጠራኝ ያላስተዋልኩ መስዬ አለፍኩ።

«እሺ ይሁን!! ዝርዝሩን አትንገሪኝ!! እንዲሆን የምትፈልጊውን ብቻ ንገሪኝ!!» አለ በዛው በከፋው ድምፁ

«ውስጥ ያለህን ሰው ምን ያህል ታምነዋለህ?»
«በመድሃንያለም!! አንች የምታውቂያቸውን ሰዎች አላውቅም!! እኔ የማውቃቸው ግን እስከህይወት የሚታመኑኝ ሰዎች አሉኝ!!»

ለእኔ የማመን ትርጉም እርሱ ካለው ይለያል። አመኔታ ከሚታመነው ሰው ይልቅ የሚያምነው ሰው ላይ ይመስለኛል ጫናው። ማንንም ሰው <እገሌ በፍፁም አይከዳኝም! በፍፁም ፊቱን አያዞርብኝም!> ብሎ መቶ ፐርሰንት ሰውየው ላይ መዘርፈጥ የዋህነትም ጅልነትም ነው። ምክንያቱም ማንም ሰው በማይደራደረው ነገር ከመጡበት አሳልፎ ይሰጥሃል። እኔ እገሌን አምነዋለሁ ስል ፍፁም አይከዳኝም ማለቴ ሳይሆን ቢከዳኝ ወይ ፊቱን ቢያዞርብኝ እንኳን ያለበቂ ምክንያት አልከዳኝም ብሎ ምክንያቱን ለማወቅ ክፍት እስከመሆን የሚደርስ ልብ አለኝ ማለት ነው። ከበቀል በፊት <ለምን?> ብዬ መጠየቅ የምችልበት ልብ ካለኝ ያን ሰው አምኜዋለሁ ማለት ነው።

ሰዎች በፍቅር ለወደቁለት ሰው <አምንሃለሁ> ወይም <አምንሻለሁ> ብለው ልባቸውን ሲሰጡ ያን የወደዱትን ሰው <በፍፁም ልቤን እንደማትሰብረው አውቃለሁ!> እያሉት ነው እንዴ? እኔ አይመስለኝም። <ብትሰብረው እንኳን ልሰጥህ ዝግጁ ነኝ! ብትሰብረው እንኳን ህመሙን እስከመቀበል ድረስ ነው ፍቅሬ!> እያሉት እንጂ!


«አትፍረድብኝ! የመጣሁበት መንገድ ከሚታመኑት ይልቅ የማይታመኑት የበዙበት ነው! በዛ ላይ አንዲት ስህተት ብሰራ አደጋ ላይ ያለው ኪዳን ነው! በሱ ጉዳይ ማንም ላይ ባልታመን ተረዳኝ!! ደግሞም እኮ ጎንጥ ለልጅህ …… » ብዬ ነገሩን መጨረስ ይቅር ያላልኩት ያስመስልብኛል ብዬ ተውኩት

«ላውጋሽ ሁሉንም ከስር መሰረቱ አልኩሽ እኮ ዓለሜ? ስሚኝና ቅያሜሽን ያዥው ካሻሽ!»
«ቅያሜ አይደለምኮ! ግን እረስቼዋለሁ ብልህ ውሸቴን ነው!»

እውነታው ይቅርታ ማድረግ እና መርሳት ይለያያል። ይቅር ብዬዋለሁ ማለት ከዛ በኋላ ያደረገኝን ነገር ሳስታውስ ቁጣ ወይም በቀል ወይም ጥላቻ ሳይሰማኝ አልፈዋለሁ ማለት ነው እንጂ ድርጊቱን ረስቼዋለሁ ማለት አይደለም!! ይቅር ብያለሁ ማለት የበደለኝን ሰው ሳየው ለቡጢ የሚዘረጋው እጄ ለማቀፍ መዘርጋት ይችላል ማለት እንጂ ያ ሰው በዛው ወጥመድ እንደማይጥለኝ አምኜ (መጃጃል ብለው ይቀለኛል) መጠንቀቅ እተዋለሁ ማለት አይደለም!! በኔ ልምድና ፍቺ ይቅርታ ይህ ይመስለኛል። ሀይማኖተኛም ባልሆን ከሰማኋቸው ጥቂት የመፅሃፍ ቅዱስ ስብከቶች በመነሳት እራሱ እግዚአብሄርም ይቅር ብዬሃለሁ ሲል በጥፋትህ አልቀጣህም ምህረት አጊንተህበታል ማለቱ እንጂ ስራህን ረስቸዋለሁ ማለቱ አይመስለኝም። ቢሆን ኖሮ እስራኤሎችን አንድ ሺህ አንድ ጊዜ ይቅር ካላቸው በኋላ አንድ ሺህ ሁለተኛ ጊዜ ባዕድ ሲያመልኩ ከግብፅ ካወጣቸው ጀምሮ የበደሉትን ባልዘረዘረላቸው ነበር።
ጎንጥ እኔጋ መስራት ከጀመረ ከተወሰነ ወር በኋላ ልጁ ታማበት ነበር። ለሳምንት አስፈቅዶኝ ጠፍቶ ተመልሶ ሲመጣ ልቡ ተሰብሮ ልጁ ኩላሊቷ መቀየር እንዳለበት እና የሱ ኩላሊት ማች እንዳላደረገ ሲነግረኝ ምክንያቴ ለሷ ማዘን ይሆን ለሱ ወይም በደም የጨቀየ ህይወቴን በደል መቀነስ ለማላውቃት ህፃን ኩላሊቴን ልሰጥለት ፈቃደኛ ነበርኩ። ሄጄ ምርመራውን አድርጌላት ነበር።

የዛን ቀን ለእመቤት ይገርማታል ብዬ ለጎንጥ ልጅ ላደርግ ያሰብኩትን ስነግራት እሷ ግን በሚያሳዝን አይን እያየችኝ
«ሜልዬ? የመረጥሽውን ህይወት ድጋሚ የማስተካከል እድል ቢኖርሽ ምርጫሽ ይለይ ነበር?» አለችኝ

«አላውቅም! አስቤው አላውቅም! ምናልባት እንደማንኛውም ሰው ዓይነት ህይወት ኖሮኝ ቢሆን ምን እንደምመርጥ አላውቅም!! ግን ማንኛዋም ህፃን እኔ ያለፍኩበትን መንገድ አላለፈችም!! ማንኛዋም ህፃን እኔ ያየሁትን አላየችም!!»

«እኔ ግን ሲመስለኝ እንደማንኛዋም ሴት ሚስት መሆን እናት መሆን ….. ስስ መሆን …. ማፍቀር …. ባፈቀሩት ሰው ልብ መሰበር ….. ማለቃቀስ ….. እነዚህን ሁሉ የማድረግ ፍላጎት ልትሰሚው ስለማትፈልጊ እንጂ የሆነ ልብሽ ጥግ ተደብቆ ያለ ይመስለኛል።» አለችኝ። ጋዜጠኛ አይደለች? ወሬ ማዳመቅ ትችልበታለች።

«ሌላውስ ይሁን ልብ ተሰብሮ ማልቀስ መፈለግ የጤና ነው?» አልኳት ወሬው ሲኮሳተር ራሴን እፈልግ ይሆን አልፈልግ መጠየቅ ሽሽት። አፍቅሬ አላውቅም ወይም ፍቅር ይሉት ነገር በእኔ የህይወት ጉዞ ገደቡን ያለፈ ቅብጠት ነው። ከቅፅበት ስጋዊ መንደድ አልፎ አቅሉን ስቶ በፍቅሬ የነሆለለ ወንድም አላስታውስም!! ጭራሹኑ ከልብሴ ስር የሴት ገላ መኖሩ ትዝ የሚለው ወንድ ልብሴን አውልቄ ያየኝ ብቻ ይመስለኛል።

«እሱ ራሱ ጣዕም እንዳለው ብታውቂ? አፍቅረሽ ጧ ብለሽ! ከሌላ ሴት ጋር አየሁት ብለሽ ግንባርሽ ላይ ሻሽ ሸብ አድርገሽ ትኩስ ነገር የሞላው ኩባያ ይዘሽ ለጓደኛሽ ማውራት ……. »

«በይ እናቴ ያንቺ የጤና ፍቅር አይደለም! ታየኝኮ ማግ ይዤ ለወንድ ስንሰቀሰቅ!» ብያት ስቄ ከደንኩት።

የጎንጥን ልጅ ሆስፒታል ሄጄ ሳያት ተስፋ ባዘሉ የልጅነት ዓይኖቿ ውስጥ የራሴን ልጅነት አየሁት። ኩላሊቴ ሊያድናት እንደሚችል ሲነገረኝ የነበረኝን የደስታ ስሜት የዛሬን ያህል አስታውሰዋለሁ። ከዛን ቀን በፊት ሆስፒታል የመተኛት ከፍተኛ ፍርሃት ነበረብኝ። በተለይ ማደንዘዣ የሚያስወስድ ነገር ከሆነ። ራሴን ባላወቅኩበት ቅፅበት የሆነ ሰው የሆነ ነገር ያደርገኛል ብዬ እፈራለሁ። በጥይት ተመትቼ ሀኪም አምኜ ሆስፒታል የማልተኛ ሴት በገዛ ፈቃዴ ቅደዱና ኩላሊቴን አውጡ ብዬ የሆስፒታል አልጋ ላይ ልተኛ ዝግጁ ነበርኩ። ማንም ምንም ቢያደርገኝ ይሁን ከዛች ህፃን አይበልጥም ራሴን አስቱኝ ብዬ ፍርሃቴን ልውጥ ዝግጁ ነበርኩ። መኪናዋን ጊቢ እስካስገባ እንኳን አቅበጥብጦኝ

«እንኳን ደስ አለህ!!» ስለው ፊቱን ወደሌላ ቦታ አዙሮ እየተገማሸረ
«በአምላክዎት! ግን ሀሳቤን አንስቻለሁ!! ከዚህ ወድያ የእርሶ እርዳታ አያሻኝም!» አለ ሁኔታው ንቀት ወይ ፅያፌ በሚመስል ሁኔታ እየጎፈላ !! የተሰማኝ ስሜት ልሰጠው የነበረውን ኩላሊት አልፈልግም የተባልኩ ሳይሆን ሊሰጠኝ የነበረ ኩላሊት ተከልክዬ ሞቴ የፈጠነ አይነት ነገር ነበር። ምክንያቱን ደጋግሜ ብጠይቀውም መልሱ

«ራሴን እንዳብራራ አያስገድዱኝ!! ሌላ ሰው ተገኝቷል!» ብቻ ነው። የሆነ የማላውቀው ተስፋ ልበለው ደስታ አላውቅም የተነነ! የሆነ ነገሬን የቀማኝ መሰለኝ። ያበሳጨኝ ደግሞ ንግግሩ ትህትና እንኳን ያልነበረው መሆኑ ነው። የሆነ በድክመቴ ያገኘኝ ነገር መሰለኝ።

«ድሮምኮ የሰው ልጅ ያለቦታው ክብር ሲሰጡት ሽቅብ ካልሸናሁ ይላል።» አልኩት ብስጭት እያልኩ

«እትዬ ይልቅ እላፊ አንነጋገር!! ስራዬን መልቀቅ ስለምሻ ሌላ ዘበኛ ቢፈልጉ ጥሩ ነው!» ሲለኝ የተናደድኩበት ምክንያት የቱ እንደሆነ ሳይገባኝ ጨስኩ!

«ለአንድ አመት ነው ልትሰራ የፈረምከው!! ኮንትራትህን ሳትጨርስ ወዴትም አትሄድም! ሞክረኝና ታያታለህ!» ብዬው ገባው።

በነጋታው ለራሴ ራሱ በማይገባኝ ምክንያት ልጁ ደህና መሆኗን ማወቅ ፈለግኩ። አላውቅም ብቻ እጇን ይዤ <አይዞሽ> ማለት አማረኝ። ምናልባት እሙ እንዳለችው የከደንኩት እናት የመሆን ስሜት ይኖር ይሆናል። እልሄን ውጬ ልጁን ላያት እንደምፈልግ ስነግረው።

«ይቅርታ ያድርጉልኝ እትዬ ለጊዜው ከቤተሰብ ውጪ ማንም እንዲያያት አልፈቅድም!! በሌላ አይዩብኝ ልነግሮት በማልችለው ምክንያት ነው!! " አለኝ። የፈረደባት እመቤት ጋር ሄጄ

«ይሄ የማይረባ! ሌላ ሰው ስለተገኘ አያስፈልግም አይለኝም? ቱ! » እያልኩ ስደነፋ እንባዋ እስኪፈስ እየሳቀች

«እንዲህ ያበሳጨሽ ለምን ኩላሊቴ አልወጣም ነው ወይስ ለምን እሱ እንደሌሎች በዙሪያሽ ያሉ ሰዎች እቴጌ እመቤቴ አላለኝም አልተሽቆጠቆጠልኝም ነው? ይሄ ሰውዬማ ከገባ ጀምሮ ነርቭሽን ነክቶታል።»

«ባክሽን አንቺ ደግሞ! ጭራሽ ስራዬን እለቃለሁ ይበለኝ?» እኔ እበሳጫለሁ እሷ ትስቃለች። «ምኑ ነው አሁን ይሄ የሚያስቀው?»

«ለማንም ሰውኮ እንዲህ ቦታ ሰጥተሽ አታውቂም! ያውም ለዘበኛሽ? ጥጋቡ ነው የሚያንተከትክሽ ወይስ ሌላ ነገር አለ?» አለችኝ መሳቋን ሳታቆም። ከዛን ቀን በኋላ ስለጎንጥ ስናወራ < ጎንጤ ጥጋቡ> ነበር የምትለው።

ከቀናት በኋላ እሙ እንዳለችው የመንተክተኬ ምክንያቱ አልገባ ሲለኝ። ስራውን መልቀቅ እንደሚችል ሌላ ዘበኛ እንዳገኘው ስነግረው ደግሞ

«ሀሳቤን አንስቻለሁ! ኮንትራቴን ሳልጨርስ ወየትም ፍንክች አልልም» ብሎ አናቴን በብስጭት አዞሮው።

«እኔ ነኝና ሜላት! ሰውዬ ስትፈልግ እወጣለሁ ስትፈልግ እገባለሁ እያልክ እንደፈለግክ ሀሳብህን የምታነሳ የምትጥልበት የሰፈርህ ጠጅ ቤት አይደለም ይሄ! የቀጠርኩህ እኔ ነኝ! ስፈልግ ደግሞ በቃኝ ብዬ የማባርርህም እኔ ነኝ! ከነገ ጀምሮ ላይህ አልፈልግም!»

«ተናገርኩኮ ፍርማዬን ሳልጨርስ አልሄድም!» ብሎ እያወራሁት ትቶኝ ሌላ ስራ መስራቱን ቀጠለ።

አሁን ሲመስለኝ ያልጨረሰው ስራ ስለነበረ ነው የቆየው። ከዛ ቀን በኋላ የሰላም ቃላት ተለዋውጠን አናውቅም ነበር። አሁን ልለው የነበረው። <ለልጅህ ስልኮ እዛ አልጋ ላይ ተኝቼ ልደነዝዝ ዝግጁ ነበርኩ። ያ እንኳን ለጠላቶቼ ከመስራት አላገደህም!> ልለው ነበር። ይቅር አልኩት እንጂ አልረሳሁትም።

***********************************


ያቀበልኩትን ስልኩን ባልተመታበት ጎን እጁ እየነካካ ያልኩትን እንዳልሰማ ዝም ብሎ አልፎ!!
«ማንም ሰው እንዳልተከተለሽ እርግጠኛ ሆነሽ እዚህ ቦታ ሂጂ! የምትፈልጊውን ንገሪው።» ብሎ የምንገናኝበትን አድራሻ ሰውየው የሚለብሰው ልብስ እና ኮፍያ ቀለም። የምንግባባበት ኮድ ፣ የምንገናኝበትን ሰዓት እና የሰውየውን ፎቶ በጭንቅላቴ መያዝ እስክችል አስደጋገመኝ።

«እሺ ግን አንተ እርግጠኛ ነህ ምንም አትሆንም?»

«አታስቢ! ለጊዜው እኔን ለማጥቃት ሆስፒታል ድረስ የሚያስመጣ ምክንያት ያለው ጠላት የለኝም!» አለ እንድሄድ መውጫውን እየጠቆመኝ። ተነሳሁ ግን እግሬ አልተራመደም! ቆሜ ግራ በገባው ስሜት ዘቅዝቄ እያየሁት ቆየሁ። እጄን በሚይዘኝ አያያዙ ያዘኝ እና

« ድንገት ካንቺ አቅም በላይ የሆነ ነገር ቢፈጠር ቢያንስ ምንም ምርጫ ከጠፋሽ የምትደውይለት የመጀመሪያ ሰው እንደሆንኩ ቃል ጊቢልኝ!» አለኝ

«ብደውልልህስ? ቀና ማለት እንኳን የማትችል ሰው ምን እንድታደርግ ነው?»
«ብቻ ደውይልኝ! ምልክት ስጭኝ! ያን እንደምታደርጊ ቃልሽን ስጭኝ!!» እያለኝ ስልኩን ወደ ስልኬ ደወለ። «ስልክሽ ፊት ለፊት የኔ ቁጥር ይኑር!»

«እሺ በራሴ የማልወጣው ነገር ከገጠመኝ እደውላለሁ።» አልኩት እጄን አልለቀቀኝም። ላስለቅቀውም አልቸኮልኩም። በእጁ የአውራ ጣት እንደመደባበስ ካደረገው በኋላ አንስቶ ወደ ከንፈሩ አስጠጋው። የእጄን አይበሉባ ሳይሆን ገልብጦ መዳፌን የውስጥ እጄን መሃሉን በከንፈሩ በስሱ ሳመው። ሳመው ወይ ዳሰሰው ወይ ተጫነው። የሆነ ነገር …….. የእጅ ውስጥ ተስሞ ሰው እንዲህ እንደመስከርም እንደመጦዝም ያለ ስሜት ይሰማዋል?

«…. ተደናበርኩልሽ ጥይት እንደሳተው!» ያለው ዘፋኙ እንዲህ ተሰምቶት ነው የሚሆነው።

.............. አልጨረስንም ..............
ውብ ቀን ውብና አዋዋል ዋሉልኝማ❤️❤️❤️❤️
#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል ሀያ ሁለት)
(ሜሪ ፈለቀ)

የሳመውን እጄን ተቀብዬው ከሆስፒታሉ ወጥቼኮ ታክሲ ተሳፍሬ ወደቃሊቲ መንገድ ከጀመርኩ ቆይቻለሁ። እጄን ተቀብዬው አልኩኝ እንጂ እየተሰማኝ ያለው ወይ ከንፈሩ እጄ ላይ የቀረ ወይ ደግሞ እጄ እዛው እሱጋ ከንፈሩ ላይ የቀረ አይነት ስሜት ነው። የሳመኝን እጄን የሳመኝን ቦታ አንዳች የእግዜር ተአምር የፈለቀበት ነገር ይመስል እየደጋገምኩ አየዋለሁ። ደግሞ እየደጋገምኩ እሱ እንደሳመው እስመዋለሁ። ቀስ ብሎ ልስልስ ያለ …… እርጥበት ያለው ግን የሚሞቅ …….. ከዛ ደግሞ ከእግሬ ጥፍር ድረስ እስከ አናቴ እንደኤሌክትሪክ ሞገድ ጥዝዝዝ ብሎ በደምስሬ ውስጥ ይሆን የተጓዘው ፣ ከጅማቶቼ ጎን ለጎን ባገኘው ክፍት ቦታ ይሆን እየተሽሎከለከ የተጓዘው ባልገባኝ አካሄድ የናጠኝ …… የሆነ መለኮታዊ የሆነ መሳም ነገር …..

ስሳም የመጀመሪያዬ ሆኖ አይደለም። በትግል ፣ ኑሮን ለማሸነፍ በመጋጋጥ ፣ ኪዳንን ትልቅ ቦታ እንዲደርስ በመታተር ፣ በበቀል ፣ ሴራ በመጎንጎን ፣ ገንዘብ እና ጉልበትን በማካበት …… እና ሌሎች ብዙ ለሌላው ሰው ስሜት የማይሰጡ ነገሮችን በማድረግ ውስጥ ከወንድ ጋር የሚደራረጉ አልባሌ ነገሮችን ከማድረግ አልታቀብኩም። እንደእውነቱ ከሆነ ብዙ አድርጌያለሁ። አብሮ በመግባት እና በመውጣት እንደፍቅረኛ ወግ ያሳለፍኩት ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ከዳዊት ጋር ነበር። ዳዊት በከተማችን ውስጥ አለ የሚባል ባለሃብት ልጅ ነው። አባቱ በገንዘቡ ባለስልጣናትን የሚሾፍር ተፅዕኖ ፈጣሪ ነው። የእድሜ ልክ እስራት ፍርዴን በ6 ዓመት ያቀለለልኝ እሱ ነው። ውለታ ውሎልኝ አይደለም! በልዋጩ ሶስት ነገር ሰጥቼዋለሁ። አንድ የነበረኝን 48% የሚሸፍን የአንድ ባንክ አክስዮን (እሱ 20% ስለነበረው የእኔን ሲጨምር በባንኩ ላይ ፈላጭ ቆራጭ ያደርገዋል።) ሁለት የራቁት ዳንስ ቤቱን ግማሽ ልሸጥለት (ዳዊት የገባው በዛ ነው) ሶስተኛው እና ዋነኛው (ሌሎቹ ተጨማሪ ናቸው) የአንድ እሱ የሚፈልገው ከፍተኛ ባለስልጣን ሚስጥር (ለምን እንደፈለገው አልገባኝም ምክንያቱም እስካሁን አልተጠቀመበትም። ወይም እያስፈራራበት እየተጠቀመበት ይሆናል አላውቅም! ሰውየው ግን እስካሁን ስልጣኑ ላይ ነው።)

አንዲት ከትንሽ መንደር መጥታ ኑሮን ለመግፋት ትፍጨረጨር የነበረች ሴት የባለስልጣናት ሚስጥር እጇ ላይ እንዴት ወደቀ? ይሄ ሁሉ ሀብትስ እንዴት ተቆለለ? የሚሆን አይመስልም አይደል? ሆኗል!!

እዚህ ሀገር አንድ የገባኝን ነገር ልንገራችሁ! በተለይ እላይኛው የኑሮ መደብ እና ስልጣን ላይ የተፈናጠጡት ሰዎቻችን ዘንድ ….. በገንዘብ አቅም የማይሆን ምንም ነገር የለም። የሚለያየው የገንዘቡ መጠን ብቻ ነው። በመቶ ሺህዎች <ሀቀኝነቴን ፣ እምነቴን ፣ ህሊናዬን > ሲል የነበረ ለሚሊየኖች እጅ ይሰጣል። ለሚሊየኖች <ቤተሰቤን ፣ አምላኬን ፣ ቃሌን ፣ ህዝቤን > ያለው ደግሞ ለቢሊየን ወድቆ ይሰግዳል። ገንዘቡን የምታቀርብለት ሰው ወይም ድርጅት የሌለውን ያህል ወይም በቀላሉ ሊያገኝ የማይችለውን ያህል ገንዘብ መጠን አቅርብለት! የምትፈልገውን ይሸጥልሃል። ለምን ሚስቱ አትሆንም!!! በስህተት አምልጦ የሾለከ <በገንዘብ የማልሸጠው ህሊና አለኝ> ያለ ጎርባጭ ከተገኘ …… በነዛኛዎቹ ይሰለቀጣል። <ህዝብን በተገቢ ሁኔታ ባለማገልገል፣ የህዝብን ጥቅም ባለማስቀደም > ምናምን ምናምን የሚባሉ ፖለቲካዊ ሀቅ የሚመስሉ ውስልትናዎች ተለጥፈውበት እንደ እድሉ አርፎ የማይቀመጥ ቅብጥብጥ ከሆነ ወደ እስር ቤት ……. ለቤተሰቤ አንገቴን ልድፋ ያለ የቤተሰብ ሰው ከሆነ ደግሞ ወደቤት ይላካል።

እንግዲህ ከዳዊት ጋር አብረን መስራት የጀመርነው ከእስር ቤት ከወጣሁ በኋላ መሆኑ ነው። ወድጄው አይደለም! ማለቴ እንደፍቅረኛ! እንደስራ ባልደረባ ጭንቅላቱ ለቢዝነስ የተፈጠረ፣ ለተንኮል እና ሴራ እኔን የተስተካከለ ፈጥኖ አሳቢ ፣ አባቱ ስለሚንቀው ለአባቱ የሆነ ጀብድ ሰርቶ ራሱን ማስመስከር አብዝቶ የሚሻ ሰው ነው። ከምለብሳቸው የወሮበላ ልብሶች ውስጥ ያለ የሴት ገላዬን ራቁቱን ሳያየው የተመኘ ብቸኛ ወንድ ይመስለኛል። ባለገንዘብ ፣ ባለጉልበት ፣ ባለሀይል ከሆንኩ በኋላ ለአመታት በዙሪያዬ ያለ ሰው ሁሉ እንደአለቃ የሚፈራኝ ፣ እንደሰው የሚያከብረኝ ፣ በዛ ካለ ትንሽ የሚቀርቡኝ እንደወዳጅ የሚያዩኝ ሴት ነበርኩ እንጂ ማንም በሴትነቴ የተመኘኝ አላስታውስም። ሴት መሆኔ ትዝ የሚላቸውም አይመስለኝም። እሱ ግን እንደስራ ባልደረባው ሳይሆን እንደሴት አየኝ!! የሚጋረፍ ፊቴ ሳያግደው ለወራት አበባ አመላለሰልኝ (እያየ ፊቱ ላይ አበባውን በጫጭቄ እበትነዋለሁ) ። <ደነዝ ነህ ወይ አትሰማም? አንተ ምኔም መሆን አትችልም!> እያልኩት በየቀኑ ቆንጆ መሆኔን ነገረኝ። በግልፅ <አይደለም ፍቅረኛዬ ልትሆን ለአንድ ቀን ተሳስቼ አብሬህ ብተኛ የምፀፀትብህ አይነት ሰው ነህ!> እያልኩት እንኳን በየቀኑ ሳይደክመው እንደሚወደኝ እየነገረኝ ዓመት ተቆጠረ። አንድ ቀን ከአባቱ ጋር ተጣልቶ ቢሮ ተቀምጦ እንደ ትንሽዬ ሴት ልጅ ሲንሰቀሰቅ ደረስኩ። ምን እንደሆነ ስጠይቀው እንባውን ከንፍጡ እየደባለቀ ማልቀሱን ሳያቆም በአባቱ ፊት ሁል ጊዜ ትንሽ መሆኑን ነገረኝ። አሳዘነኝኮ ግን ከማልወደው ነገሩ አንዱ ይሄ ልፍስፍስ ሴታ ሴት ነገሩ ነው። የዛን ቀን ግን

«ዛሬ እራት ልጋብዝህ?» አልኩት። እንባው ጥሎት ጠፋ! ከዛ በኋላ እንደፍቅረኞች የሚፈፃፀመውን ነገር ሁሉ እንፈፃፅማለን። አልጋ ላይ ሲያዩት ስልባቦት እንደሚመስለው ገላው አይደለም ወይም እንደሴታሴት አኳኋኑ። ስለዚህ ሴታዊ ፍላጎቴን ለማግኘት የማላውቀው ሰው ጋር ከምሄድ ጥሩ ቅብብሎሽ ነበር። አንዳንዴ ምንችክ ሲልብኝ እዘጋዋለሁ። ደግሞ መልሰን እንጀምራለን። ስለእውነቱ ግንኙነታችን ምን እንደሆነ ወይም ወዴት እንደሚሄድ እንኳን ውልም ስምም የለውም ነበር። እንኳን እጄን ስሞኝ የስሜቴ የመጨረሻ ጡዘት ጠርዝ ላይ እንኳን እንዲህ ዛሬ ጎንጥ እጄን ሲስመኝ እንደተሰማኝ አይነት ስሜት ተሰምቶኝ አያውቅም!! ኸረ እንኳን ሊሰማኝ መኖሩንም አላውቅም!! ፊልም ላይ እንኳን ትኩረታቸው ከንፈር እንጂ እጅ እና ከንፈር ሲገናኝ እንዲህ አስማታዊ ስሜት እንዳለው መች ይነግሩናል?
ቃሊቲ በሩ ላይ እንደደረስኩ ዘበኛው ሲያየኝ እንደተለመደው በወዳጅነት «ቁርጠትዬ እስቲ ዛሬ ደህና ጊቢልኝ ታውቂ የለ ሚስትየው ስታላምጠኝ ነው የምትከርመው?» አለኝ።

«ይገባልሃል! ሂድ ባርችን ጥራልኝ!! እዚህ ስትቅለሰለስ እኮ እኔን አማክረህ አራት የወለድክ ነው የምትመስለው!»

«እሱማ ይጠራልሻል!! ግን ሰሞኑን ምርጫ ደርሷል ብለው የሌለ ህግ እያጠበቁ ነው!!»

«በቃ እሱ ታሳቢ ተደርጎ ይገባልሃል! መርዶ ሊነገራት ነው …. ወንድሟ ራሱን አጥፍቶ ነው …. መዓተኛ አይደለህ? አንዱን ቀባጥርና ጥራልኝ» ብዬ ከኪሴ ብር አውጥቼ አቀበልኩት። እሱ ወደ ውስጥ ሲገባ እየሆነ ያለውን ባላየ ዝም ብሎ የተቀመጠውን ሌላ ጠባቂ ብር በያዘ እጄ ጨበጥኩት። እየወተወተ አመሰገነኝ!!

«ያልጠየቅሽኝን እያካካስሽ ነው በየቀኑ?» አለች እሙ ገና ከመድረሷ «ጎንጤ ጥጋቡስ ዛሬ የለም?»

« ሁሉንም ነገር ላስረዳሽ ጊዜ አይበቃኝም!! እርዳታሽን ፈልጌ ነው የመጣሁት!! ከዛ ደግሞ በአጭሩ ትናንት ላይሽ የመጣሁ ጊዜ የማውቀው ታሪክ አልነበረም። የተመታሁ ጊዜ ሚሞሪዬን እንዳለ አጥቼ ነበር።»

«እና አሁን?» ብላ ግራ ገብቷት ከላይ እስከታች አስተዋለችኝ።
«ከትናንት እስከአሁን በ24 ሰዓታት ያልተፈጠረ ነገር የለም ብልሽ ይቀላል። አንድ ቀን ሳይሆን አንድ ዓመት የሆነ ነው የሚመስለው። ኪዳንን ላስለቅቅ በነበረ ሂደት የተኩስ ልውውጥ ነበር። በዛ መሃል ሲመስለኝ የሽጉጥ ተውሱ ትውስታዬን የወሰደብኝ ተኩስ አደጋን አስታወሰ እና ትውስታዬን ቀሰቀሰው። አላውቅም የተከሰተውን ብቻ አስታወስኩ ሁሉንም!!»

«wait a minute …. It’s too much information eko (ጭንቅላቷን የሆነ ከደነዘዘበት እንደማባነን፣ እንደማንቃት ያለ እየወዘወዘች) እሺ የትውስታ መሄድ መምጣቱ ይቆየኝ! ኪዳን safe ሆነ? ሆ! አይገርምሽም? I felt it ደግሞ እኮ……. Something was off » አለች አሁንም ዓይኗ እላዬ ላይ መርመስመሱን ሳታቆም!

«አልሆነም!! አሁንም እነሱጋ ነው ለዛ ነው እርዳታሽን የምፈልገው!!»
«ምንም እየገባኝ አይደለም! ተኩስ ነበር አላልሽኝም? አንቺ ታዲያ እንዴት እዚህ ተገኘሽ?»
«እሙዬ እመኚኝ ስናወራ ውለን ብናድር አይገባሽም!! ጎንጥ ከነርሱ አንዱ ነው። እኔ በሱ ምክንያት ነው እዚህ ያለሁት! እሱ ደግሞ ሆስፒታል ነው ተመትቶ!! (ይበልጥ ሲዞርባት አየሁ) ሌላ ቀን እነግርሻለሁ እሱን!!»

«ጎንጤ ጥጋቡ የእነሱ? እኮ ዘበኛሽ ሰላይ? እመኚኝ አመትም ብትነግሪኝ ይሄ ነገር አይገባኝም!!»
«እኔም ብዙ አልገባኝም ኪዳኔን ቅድሚያ ልስጥ ብዬ እንጂ!!»
«እሺ ምንድነው እንዳደርግልሽ የምትፈልጊው?»
«እናንተ ቴሌቭዥን ጣቢያ አሁን በምርጫው ዙሪያ እየሰራ ያለ ጋዜጠኛ እንዲተባበረኝ እንድታደርጊልኝ እፈልጋለሁ። እና ደግሞ ዛሬ የሁለት ሰዓቱን ዜና የሚያነበውን ሰው!»

«እሺ አገኘሁልሽ! ምን አስበሽ ነው?» አለች ጭራሽ ግራ ተጋብታ!!
«የምርጫው ዜና ሲተላለፍ አቶ ደሳለኝም አንዱ እጩ ተወዳዳሪ እንደመሆናቸው አንዱ ጋዜጠኛችሁ እቤታቸው ተገኝተው ላይቭ አጭር ቃለመጠይቅ ያደርጉላቸዋል። የምታደርጉትን አድርጉ ስትፈልጉ ሙሉውን ቃለመጠይቅ ከዜና በኋላ ያቅርቡት። እኔ የምፈልገው ከእኔጋ በተቀናጀ ሰዓት ላይቭ መግባታቸውን ነው።»

«እየገባኝ አይደለም!! የማስበውን እያሰብሽ ከሆነ በጣም ሪስክ አለው!»
«አውቃለሁ ግን ከዚህ የተሻለ ደም ሳይፈስ፣ ህይወት ሳይጠፋ ኪዳንን ላገኝ የምችልበት ምንም አማራጭ አልታየኝም!! ብቻ አንቺ ይሄን ማድረግ ትችዪ እንደው ንገሪኝ?»

«ወይ ጉድ! እስኪ ስልክሽን ስጪኝ ልደዋውል!!»

«እሺ በስልኬ ግን ምንም አይነት መረጃ እንዳትቀያየሪ! ከእኔ ጋር እንዲገናኑ ብቻ በሆነ መላ ንገሪያቸው። ምናልባት አላውቅም!! ስልኬን ሲሰጡኝ ውስጡ የነበረ ብዙ ነገር አፅድተው ነው የሰጡኝ። ሁሉንም ሶሻል ሚዲያዎቼን አዘግተውታል። መቼም የማላስታውስ ነበር የመሰላቸው መሰለኝ ወይም ከማስታወሴ በፊት እንደሚደፉኝ እርግጠኞች ነበሩ።»

«እንደዛ ከሆነ መደወሉ በራሱ ሪስክ አለው!! (ዘወር ብላ ወደ ጠባቂው) ሼባው? ዛሬ ለሚስትህ ዓመትበዓል ማስመሰል አላማረህም? ስልክህን ለ5 ደቂቃ ልደውልበት ?» አለችው። የጠባቂውን ስልክ ተቀብላ ሁለት ቦታ ስልክ ደዋወለች። ስልኮቹንም ለእኔ እንድመዘግብ ነገረችኝ። እኔ በምፈልገው መንገድ አዘጋጀችልኝ። መልሳ ለጠባቂው ከሰጠኋት ብር ጋር ስልኩን እየሰጠችው

«ሳመኝኮ!» የሚለው ቃል አፌን አምልጦ ሲወጣ እኔው ራሴ ስሰማው እና እሷ ጆሮ ጠልቆ ሽው ብላ ዞራ ስታፈጥብኝ አንድ ቅፅበት ነው።

«ጎንጥ! ከንፈሬን አይደለም ደግሞ እጄን ነው! እዚህጋ! » ብያት የሳመኝን እጄን እንደሌላ ሰው ባዕድ እጅ ሳየው አይታ

«እርፍ መጃጃል!! እጅሽን ስሞሽ ድንግልናዋን ዛሬ እንደሰጠች ልጃገረድ እንዲህ የተሽኮረመምሽ ሌላ ነገር ቢያደርግሽ ክንፍ አውጥተሽ ልትበሪ ነው?» ብላ መሳሜን ስላቀለለችብኝ ተናደድኩ። እንዲህ ያለ መሳም ተስማ ባታውቅ ነው ያልገባት። ወዲያው ቀጥላ «እንዴ ደግሞ ቆይ አሁን ከደቂቃዎች በፊት የእነርሱ ወገን ነው አላልሽኝም? አንቺ ሴት ዛሬ ግራ ያልተጋባ ምንም ወሬ ያለሽ አልመሰለኝም!»


«እንዳልሽው ነው ሁሉም ነገር ግራ የተጋባ ነው!! እጄን የሳመኝ ግን ግራ አያጋባም ሃሃሃሃሃሃ ኩልልል ብሎ ጥርት ያለ ነው።» ብያት ዝርዝሩን ከሰሞኑ መጥቼ ልነግራት ተስማምተን ተለያየን።

ተመልሼ ወደከተማ እየሄድኩ ተናኜጋ ደውዬ የተወሰነ ጥሬ ብር እና ለእንዲህ አይነት ጊዜ ለመጠቀም ገዝቼ አስቀምጫቸው ከነበሩ ሲሞች አንዱን እንድታመጣ ቦታውን ነገርኳት። በመንገዴ አዲስ የስልክ ቀፎ ገዛሁ። ዳዊትጋ ስልክ ደውዬ መኪናዬ ስለተበላሸች አሁኑኑ የእርሱን እንዲያውሰኝ ስጠይቀው በዛ ጭንቅንቅ መንገድ ነድቶ ሳይሆን በአየር ላይ በሮ በሚመስል ፍጥነት ያልኩት ቦታ ደረሰ። መኪናዋን ልነዳ ከተቀመጥኩ በኋላ ምንም እንኳን ሁሉም ትውስታዬ ቢመለስ ለሰከንዶች መንዳት መቻሌን እርግጠኛ አልሆንኩም ነበር። ወይም ፍርሃት ተሰምቶኝ ነበር።

ሁሉንም ነገር ባቀድኩት መሰረት ማስተካከሌን ለመቶኛ ጊዜ ካረጋገጥኩ በኋላ መፀለይ አሰብኩ። ሰዓቱ ገና ስለነበር የቀረበኝ ቤተክርስቲያን ገባሁ እና በሩ አካባቢ ቆምኩ። ከዛ ግራ ተጋባሁ!!! ላለፈው በደሌ ሁሉ አንድም ቀን መጥቼ ንሰሃ አልገባሁም!! በደም የተነከረ እጄን ወደ እርሱ መዘርጋት ድፍረትም ሆነብኝ!! ከዛ ደግሞ ያለፈውን ሁ,ለት ወር ከምናምንኮ ፀልዬ ነበር!! ሰምቶኝ ይሆን ወይስ አያውቀኝ ይሆን? ወይስ ባኮረፈ ፊቱ ነው ሲያየኝ የነበረው? ደግሞ መልሼ ከሰማኝ ይስማኝ ብዬ መፀለይ ጀመርኩ።

«አምላክ ሆይ ታውቀኛለህ ብዬ አስባለሁ። ካላወቅከኝ ሜላት ነኝ። ያለፈውን ሀጥያቴን ሁሉ ብናዘዝ መሽቶ ይነጋል። ከዛ በፊት ግን ያንተን እርዳታ እሻለሁ ተለመነኝ!! አሁንም የምሰራው ባንተ ዘንድ ልክ ይሆን ስህተት አላውቅም! ግን የተሻለ የመጨረሻ አማራጭ የምለውን ነው የመረጥኩት። እኔም ራሴ የድሮዋን ሜላት መሆን አልፈልግም! አንተም እንደማትወዳት ነው የማስበው!! ያለፈውን ሁሉ ማረኝ እና ለእኔ ስትል ሳይሆን ለወንድሜ ስትል፣ ለዛች ደጅህ ለማትጠፋ ምስኪን እናቴ ስትል ….. ወንድሜን ይዤው እንድመለስ እርዳኝ!! እባክህ እ? ከፈለግክ አትማረኝ! ከፈለግክም ቅጣኝ ግን በወንድሜ አትቅጣኝ!! እ? » የሆነ ከሰማይ <እሺ> የሚል ድምፅ እሰማ ይመስል አንጋጥጬ ቆየሁ!!

መኪናዬ ውስጥ ገብቼ ኪዳን ወዳለበት ቦታ መንዳት ጀመርኩ። ትናንት ከነበረበት ቤት ቀይረውታል። ከምሽቱ 3 ሰዓት የሚፈልገውን ይዤለት እንደምመጣ ስለነገርኩት እኔን ለመጠበቅ በጊዜ ከሚስትየው ጋር ወደዛው መሄዳቸውን አረጋግጫለሁ። የእሱ እቅድ ያው እንደተለመደው የራሱን ሰዎች እና መኪና ልኮ ይዘውኝ ልሄዱ ነው። እኔ ቀድሜ እዛው እንደምደርስ የሚጠረጥርበት ምንም ፍንጭ የለውም። በገዛሁት ስልክ እቤቱ ውስጥ የተጠመዱትን ካሜራዎች መቆጣጠር እችላለሁ። ሳሎኑን በሁለት አንግል፣ ኮሪደሩን እና ኪዳን ያለበትን ክፍል። ኪዳን አልጋው ላይ ኩርምት ብሎ ከመጋደሙ ውጪ ምኑም ታግቶ ያለ አይመስልም። ደጁ ላይ ጠብደል ጠባቂ ቆሟል። ለአፍታ ጎንጥን አሰብኩ> አሁን በዚህ ውጥንቅጥ ውስጥ ሆኜ የእሱን አሳሳም ማሰብ ነበረብኝ? አስቤስ እጄን መሳም ነበረብኝ?
አቅራቢያው ስደርስ የጋዜጠኛው ቡድን እኩል ደረሰ። ስልኬ ላይ የማየውን እቤት ያሉት ካሜራዎች እይታ አቀበልኳቸው። እነርሱ በኮምፒውተር ፣ በተለያዩ ገመዶች ፣ ማይክራፎኖች እና ሌሎች ነገሮች በሞላው የመኪናቸው ጀርባ የሚሰካካውን ሰካክተው ዝግጁ መሆናቸውን ሲነግሩኝ መኪናችንን የአጥር በሩጋ አስጠግተን አቁመን እኔ እና አንድ ማይክራፎን የያዘ ጋዜጠኛ እና ሌሎች ሁለት ካሜራ እና ካሜራ ረዳት ወርደን ስንጠጋ ጠባቂው የያዘውን መሳሪያ ወደፊት አስቀድሞ ወደእኛ ቀረበ።

«ጋዜጠኞች ነን!! ላይቭ ነው! አቶ ደሳለኝ ስለምርጫው ትንሽ እንዲሉልን ነው!» አለው አብሮኝ ያለው ጋዜጠኛ። ጠባቂው ምኑም አልተመቸውም። ለሌላኛው ጠባቂ መልዕክቱን ለአቶ ደሳለኝ እንዲያስተላልፍ ጮክ ብሎ ተናግሮ እኛን እንድንጠብቅ አዘዘን። ሌላኛው ጠባቂ ከደቂቃዎች በኋላ አቶ ደሳለኝን አስከትሎ ብቅ አለ።

«እኔ ከምንም ዓይነት ጋዜጠኛ ጋር ቀጠሮ አልያዝኩም!! ምን አይነት ጣጣ ነው! ሰው ማረፍ አይችልም? ደግሞ ይሄን ቤት ማን አሳያችሁ?» እያለ እየተነጫነጨ ቀና ሲል ከእኔ ጋር ተያየን። ሊቀየር ሲዳዳው አብሮኝ ያለው ጋዜጠኛ ለካሜራ ማኑ እንዲጀምር ምልክት ሰጠው። ቀጥሎም የቴሌቭዥን ጣቢያውን ፈቃድ እያቀበለው

« አቶ ደሳለኝ ላይቭ የኢትዮጵያ ህዝብ እየተከታተሎት ነው። በዚህ ምርጫ ለየት ባለ የምርጫ ቅስቀሳዎ የህዝብን ቀልብ የሳቡ ይመስላል። ወደ ውስጥ ገብተን አንድ ሁለት ነገር ቢሉን? » አለው። ግራ ተጋባ እና እየተወነባበደ ሳቅ አይሉት ስላቅ ያልለየለት ፈገግታ ፈገግ እያለ ወደውስጥ ጋበዘን። ይሄኔ ፅፌ አዘጋጅቼው የነበረውን መልዕክት ኪዳን ያለበትን ክፍል ጨምሮ ካሜራ የተገጠመባቸውን ክፍሎች ምስል ከሚያሳየው ምስልጋ ላኩለት። ስልኩ መልዕክት መቀበሉን ቢሰማም አላየውም።

«አቶ ደሳለኝ መልዕክቱ የሚያስፈልጎ መልዕክት ይመስለኛል።» አልኩት ጠጋ ብዬው። በጥፍሮቹ ቢቦጫጭረኝ ደስ እንደሚለው እያስታወቀበት የግዱን ፈገግ ብሎ ወደሳሎን እየመራን መልዕክቱን አነበበው።

« ቴሌቭዥንህን ክፈተው ካላመንከኝ ላይቭ ነህ!! ኪዳን ያለበት ክፍል ጨምሮ ኮሪደርህ እና ሳሎንህ በድብቅ ካሜራ እይታ ውስጥ ነው። የምስሉ መዳረሻ መቼም ይገባሃል የኢትዮጵያ ህዝብ አይን ነው። አርፈህ በቀጣፊ ምላስህ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያለህን ፍቅር እና ብትመረጥ የማታደርገውን የውሸት ቃልህን ላይቭ ዘብዝበህ የምርጫ ቅስቀሳህን ብታደርግ ይሻልሃል ወይስ ዜናውን ከምርጫ ቅስቀሳ ወደአፈና ወንጀል ብንቀይረው? ምርጫው ያንተ ነው!! ከጋዜጠኞቹ ጋር እያወራህ ወንድሜን ሳሎን አስመጣልኝ። ምንም ግርግር ሳንፈጥር ከጋዜጠኞቹ ቀደም ብዬ ውልቅ ብዬ እወጣልሃለሁ!! አይ ካልክ ግን እዚሁ ላይቭ ወንድሜን እንዳገትከው ከነምስሉ ለጋዜጠኛው ሹክ እለዋለሁ። እዛው ላይቭ ጮማ ዜና አይመስልህም? በዛ ላይ ያን የቪዲዮ ቅጂ እመርቅላቸዋለሁ።!!» እያነበበ ጋዜጠኛው ደጋግሞ ስሙን ይጠራዋል። አልሰማውም!! እንደመባነን ብሎ

«እ እ!! የሆነ ትንሽ አስቸኳይ መልዕክት ደርሶኝኮ እ!!» ተንተባተበ።
«አዝናለሁ መጥፎ ዜና ነው?» አለው ጋዜጠኛው።
«አይ እንደው ትንሽ ነገር ነው። እኔ የምልህ እና አሁን ይሄም ላይቭ እየተላለፈ ነው?» ብሎ የቴሌቭዥኑን ሪሞት አንስቶ እየከፈተ የሆነች ተንኮል ያለበት አስተያየት ወደእኔ አየ። ልቤ በመጠኑም ቢሆን መደለቅ ጀመረ። ደቂቃ እንኳን ዝንፍ ያለ ክፍተት ከተፈጠረ ሰውየው እዛ ያለነውን በሙሉ ጭጭ አድርጎ የቀደመ እቅዱን ለማሳካት የጋዜጠኞቹ ብዛትም ማንነትም የሚያሳስበው ሰው አይደለም። ጋዜጠኛው ነውም አይደለምም ሳይለው (ምክንያቱም እስከዛ ደቂቃ ድረስ ላይቭ አልነበረም) ቀጠለ። በቴሌቭዥኑ ዜና የምታቀርበዋ ሴት ስለአቶ ደሳለኝ አውርታ ስታበቃ ባልደረባዋን ጋበዘችው። ጋዜጠኛው ጥያቄውን ቀጠለ። መልሱም መላ ቅጡ የጠፋበት ወሬ ከመሆኑ በተጨማሪ በተቀመጠበት ላብ ያጠምቀው ጀመር። እየተንተባተበ ጥቂት እንዳወራ ሚስትየው ብቅ እንዳለች እየሆነ ባለው ነገር ግራ ተጋብታ ፍሬን ያዘች። በሚቀባጥረው ወሬ መሃል ወደሚስቱ ዞሮ «እስቲ ኪዳንን የሚጠጣ ውሃ እንዲያመጣ አድርጊልኝ! ቡናም ሻይም ሳልላችሁ በሞቴ ለእናንተስ ምን ይምጣላችሁ?» አለው ጋዜጠኛውን! ጋዜጠኛው ቀጥታ በዜና መሃል እየተላለፈ ያለ ፕሮግራም ላይ መዘለባበዱ እያናደደው ግን በጨዋ ደንብ ቀጠለ።

«በእውነቱ አቶ ደሳለኝ በዚህ አጋጣሚ ሳይዘጋጁ የመጣንቦት ቢሆንም እንግዳ ተቀባይነትዎ እና ልግስናዎ አልተለየንም። ከልብ እናመሰግናለን!! ባልደረባዬ የቀሩትን ዜናዎች ለማቅረብ እየተጠባበቀች ስለሆነ ለህዝቤ ማለት አለብኝ የሚሉት መልዕክት ካለ እድሉን ልስጦት!! »

ጋዜጠኛውን በቅጡ የሰማው አይመስልም። ሚስቱ እንደጅብራ መገተሯ አሳስቦት በግንባሩ መልዕክት ሊያስተላልፍላት እየሞከረ ነው። እያመነታች ከሳሎኑ ስትወጣ ልቤ መደለቋን ቀጠለች። እሱም ለዚህ የፈረደበት የኢትዮጵያ ህዝብ ላቡንና ወሬውን በቲቪ ማስተላለፉን ቀጠለ። ኪዳን የመጠጥ ውሃ የሞላው ብርጭቆ ይዙ ወደሳሎን ብቅ ሲል ልቤ ወደቦታዋ ተመለሰች። እዚህ ድረስ ያለውን በድል ተወጥቼዋለሁ!!


.......... አልጨረስንም!! .........

(ዛሬ አጠረ የሚል ሰው እጋጨዋለሁ!!! 😂😂ይልቅ እያነበባችሁ ላሽ የምትሉ ልጆች እስኪ ቢያንስ ሪአክት አድርጉ። ጌታን አይቆጥርም!! ካያችሁት ውስጥ ምን ያህላችሁ እንዳነበባችሁት እንዳውቅ ነው!! ኮመንት ላይ ፊልም መሆን ነው ያለበት የምትሉኝ ልጆች ደግሞ እስኪ ገፀባህርያቱን እገሌ ቢሰራው የምትሉትን ፃፉ!! )

ውብ ቀን ውብኛ አዋዋል ዋሉልኝማ!❤️❤️❤️❤️
#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል ሀያ ሶስት)
(ሜሪ ፈለቀ)


ኪዳን የመጠጥ ውሃ የሞላው ብርጭቆ ይዞ ወደሳሎን ብቅ ሲል ልቤ ወደቦታዋ ተመለሰች። እዚህ ድረስ ያለውን በድል ተወጥቼዋለሁ!! ብርጭቆውን ተቀብዬው ለደሳለኝ ከወገቤ ጎንበስ ብዬ በሁለት እጄ ሳቀብለው ጭራሽ የሚያወራው ተወነባበደበት። ጋዜጠኛው በሚሆነው ትርምስ ትዕግስቱ ነው ያለቀው። ኪዳን እየሆነ ያለው ነገር ግር ብሎት አይኑን ከወድያ ወዲህ ያንቀዋልላል። ወደጆሮው ጠጋ ብዬ «አምላክን በልመና አታድክም!! » አልኩት እና ጠቀስኩት። ፈገግ ብሎ ደረቱን እንደመንፋት አድርጎ ጎምለል እያየ ዙሪያውን መቃኘት ጀመረ። አተኩሮ ላየው የሆነ ቁራጭ የፊልም ትወና እየከወነ ነው የሚመስለው። ሁሌም እንዲህ ነው! ከልጅነታችን ጀምሮ ከልጆች ጋር ተደባድቤ እኔ ከሆንኩ ያሸነፍኩት የፀቡ መሃል ሜዳ ይገባና ደረቱን ነፍቶ ይንቀባረራል። «ማን መሰለችህ? የእኔ እህት እኮ ናት!!» ይላል እየተጀነነ።

• * * * * * * * * * * * * *

ድሮ ልጅ እያለን አባቴ እናቴ ላይ ሙድ የሚይዝበት መላው ነበር አሁን እኔ እና ኪዳን የምንግባባበት ኮድ። እናቴ ብር እጇ ላይ ቢኖርም ባይኖርም አለኝ አትለውም!! ብር ጨርሰሻል ወይ ብሎ ቀጥታ ከጠየቃት መልሷ ሁሌም አዎን ነው። በአቋራጭ ነው የሚያጣራው

«አስካል እንደው ከአባወራዎቹ ልደብለቅበት እስኪ መቀነትሽን ፈትሽልኝ!» ይላታል

«አይ እንግዲህ እንኳን ላንተ አምቡላህን መጋቻ ለልጆቼም የሚቀምሱትን ማሰናዳበት አልሞላልኝ» ትለዋለች

«ውይ በሞትኩት እናቴን! አያ ተካን አበድረኝ ልበለው ይሆን? እንደው ቸሩ መድሃንያለም ለልጆቼ የምሰጠው አታሳጣኝ» ይላል ወደላይ እንደማንጋጠጥ ብሎ በአንድ አይኑ እሷን አጮልቆ እያየ እና እያስተዛዘነ (ልበደራቸው የሚላቸው ሰዎች ስም ይቀያየራል)

«አይ እንግዲህ አምላክን በልመና ማድከም ደግም አይደል!! የምንችለውን እናደራርግና በተረፈው ማመስገን ነው። ያመሰገንነው አምላክ የጎደለውን ይሞላል!» ትለዋለች ልትወጣ ነጠላዋን እላይዋ ላይ እያደረገች። አለኝም እንዳትለው ለእሱ መጠጫ መስጠት አትፈልግም። የለኝም እንዳትለው ባሏ የሰው ፊት ሊያይባት ሲሆን በዘዴ አድበስብሳ! አባቴ እሷ ዞር ስትል ጠብቆ እየሳቀ

«እም! መች አጣኋት እናታችሁን? አላት ማለት ነው! አሁን ዘንቢል ሙሉ ሸምታ ትመጣ የለ? ምንአለ በሉኝ!» ይላል። እንዳለውም ከገበያ መዓት ነገር ሸማምታ ስትመጣ አባቴ ያላትን አንነግራትም ተያይዘን እንስቃለን!!

የእውነትም እጇ ላይ ብር ከሌላት መልሷ ይለያል። የአባዬ ጥያቄ ስሞቹንና አጠያየቁን ቀይሮ ያው ነው። የመጨረሻው <ለልጆቼ የምሰጠው አታሳጣኝ> የሚልበት ጋር ሲደርስ

«እንግዲህ አንድዬ ያውቃል!! እርሱ የከፈተውን ጉሮሮ ሳይዘጋው አያድር!!» ካለች አባቴ አሁንም እሷ ዞር ስትል ጠብቆ

«አሁን የእውነቷን ነው የላትም ማለት ነው!!» ብሎ ከኛ ፊቱን አዙሮ ብር ይቆጥር እና « ገበያ ውረጅበት ብሎሻል! ብላችሁ ስጧት» ብሎ ለአንዳችን ያቀብለናል። ለምን እራሱ እንደማይሰጣት አሁንም ድረስ አይገባኝም!! ምናልባት ለእኛ ማስተማር የፈለገው ነገር ይኖር ይሆን ነበር። ሁሌም መልሷ እንዲሁ ነው። ሁሌም የእርሱ አጠያየቅ ተመሳሳይ ይዘት ያለው ነው። ገና እሱ ሲጠይቃት በተለይ እኔ ሳቄ ይመጣል። ለእማዬ <እየፈተነሽ ነው!> አልላትም!! ለትንሿ ልቤ የእነርሱ የፍቅር ቋንቋቸው መሆኑ ገብቷት ነው መሰለኝ በተለይ የሌላት ጊዜ እሱ ሲያዝንላት ልቤ በሙቀት ቅልጥ ትላለች።

ከኪዳን ጋር ልጆች ሆነን እናታችንን የምናስታውስበት አንዱ ጨዋታችን ነበር። አድገን የህይወት ውጥንቅጥ ውስጥ የተነከርን ጊዜ ደግሞ ምልክት መሰጣጫችን ሆነ። ያለንበት ሁኔታ ተስፋ ያለው፣ መውጫ ያለው ፣ ደህንነታችን ጥሩ ሁኔታ ላይ ከሆነ። «አምላክን በልመና አታድክሚ….. » የምትለዋ! ለምሳሌ ባለፈው ኪዳን እንዳለኝ « ደህና ነኝ አታስቢ! አልጎዱኝም!! ተረጋግተሽ መላውን ፈልጊ!» እንደማለት ነው!! ወይም ደግሞ « አንድዬ ያውቃል» ብዬ መልዕክት ካደረስኩት «እንዳትደውልልኝ፣ በምንም መንገድ ልታገኘን አትሞክር! ያለሁበት ሁኔታ ሲሪየስ ነው!!» እንደማለት ነው። እንደገባንበት ማጥ መልእክቱ ይለያያል። እኔ እና እሱ እንግባባበታለን!! በደፈናው ያለንበትን ሁኔታ አስከፊነት የምንለዋወጥበት ነው።


• * * * * * * * * *

ጋዜጠኛው ከዚህ በኋላ ላይቭ እንዳለ ሊቆይ የሚችለው ከ2 ደቂቃ አይበልጥም!! እንደየትም ብሎ ቢያራዝምልኝ ሊጨምርልኝ የሚችለው 1 ደቂቃ ነው። በዛ 2 ደቂቃ ደግሞ መኪናችን ጋር መድረስ አለብን። ለጋዜጠኛው ተጨማሪ ደቂቃ ማስረዘም ከቻለ ምልክት ሰጠሁት። ትከሻውን ሰበቀ። እሞክራለሁ እንደማለት ነገር።

«አንቺ እስከበሩ ትሸኝናለሽ እኮ!!» አልኳት ሚስትየውን። ባሏ አፉ እዛ ይለፍልፍ እንጂ አይኑም ቀልቡም እኛጋ ነው። ባይገባትም እየመራችን ወጣች። በፍጥነት ወደአጥሩ በር እየተጓዝኩ

«ልትከተሉኝ ብታስቡ! መንገዴ ላይ የሆነ ነገር ልትፈጥሩ ብትሞክሩ ውርድ ከራሴ!! ወጥተሽ ጋዜጠኞቹ መኪና ውስጥ ገብተሽ ማረጋገጥ ትችያለሽ!! አሁን ላይቭ እየተላለፈ ያለው የባልሽ ቃለመጠይቅ ብቻ ነው። አንዲት ዝንፍ ያለች ነገር አደርጋለሁ ብላችሁ ብትሞክሩ እዛ መኪና ውስጥ ያሉት ባለሞያዎች አንድ በተን ብቻ ነው መጫን የሚጠበቅባቸው። ቤትሽ እያንዳንዱ ክፍል ካሜራ አስቀምጫለሁ!! እየሆነ ያለው ነገር አሁን እኔና አንቺ የምናወራውም ምስል ሳይቀር ሪከርድድ ነው። መኪናዬ በስህተት ጎማዋ ቢቀንስ አልኩሽ ሁሉንም ምስል ገጣጥሞ ዜና ማዋቀር አይከብድምኣ? ቻው! መልካም እድል በይልኝ ባልሽን!! እም ጷ» በእጄ የመሳም ምልክት አሳይቻት ራሷ ለዘበኞቹ እንዲያሳልፉኝ ምልክት ሰጠቻቸው እና እኛ ስንወጣ

«ቱ » ብላ በንዴት እና በጥላቻ ምራቋን ስትተፋ እሰማታለሁ። እኔና ኪዳን በሩጫ መኪናችን ውስጥ ስንገባ ጋዜጠኛው የላይቭ ስርጭቱን ጨርሷል። ከአካባቢው እስክርቅ ድረስ በማይነዳ ፍጥነት እየነዳሁ ምንም ቃል ሳልተነፍስ ሸመጠጥኩት። ብዙ እርቀን እንኳን እንዳልተረጋጋሁ ያወቅኩት ኪዳን

«ሜል በፍፁም እዚህ ድረስ ሊከተሉሽ አይችሉምኮ!» ሲለኝ ነው።

«አይችሉም ብሎ ተዘናግቶ ወጥመዳቸው ውስጥ ከመውደቅ ሊሞክሩ ይችላሉ ብሎ መጠንቀቅ ነው የሚያዋጣው!! አታውቃቸውም እስከምን ጥግ መሄድ የሚያስችል ጭካኔ እንዳላቸው።» እጁን ሰዶ ትከሻዬን ዳሰስ ዳሰስ ሲያደርገኝ ዞሬ አየሁት። የናፍቆቴ መጠን እየሆኑ በነበሩት ክስተቶች ተከድኖ እንጂ ገደቡን የጣሰ እንደነበር የገባኝ ዓይኖቹን ሳያቸው ነው። መኪናዬን ጥጉን አስያዝኩት እና አቀፍኩት!!

«ለምን መጣህ? በዝህች ዓለም ያለኝ ብቸኛ ነገሬ አንተ መሆንህን አታውቅም? የሆነ ነገር ሆነህብኝስ ቢሆን? ሰው እንደማልሆን አታውቅም?» ቁጣም ፍቅርም እንባም ሳግም ያንቀረቅቡኝ ጀመር። ያውቀዋል ስስቴን!! ሁሌም እየተቆጣሁት ወይ እየጮህኩበት ሳለቅስ አይመልስልኝም። ስረጋጋ ነው ምክንያቱን የሚነግረኝ!!

«ይቅርታ ሜል! ይቅርታ እሺ!» አለኝ ከእኔ በላይ አጥብቆ አቅፎኝ እያባበለኝ!! መረጋጋቴን ሲያይ!!
«ብዙ ጠበቅኩሽኮ ሜል! አንድም ሶሻል ሚዲያ አካውንትሽ አክቲቭ አይደለም!! ካንቺ ሳልሰማ ብዙ የቆየሁበት ቀን 12 ቀን ነው መጀመሪያ የታሰርሽ ጊዜ!! ቢያንስ እንዳላስብ በሰው ትልኪብኝ ነበርኮ!! ቢቸግረኝ መልዕክት ላኩልሽኮ (ትዝ አለኝ! ቁጥሩ ከማይታይ ላኪ ላመስግን ወይስ ልፀልይ? የሚል መልዕክት ስልኬ ነበረው! ስላልገባኝ እንጂ!! ምንም ቢፈጠር የምደውልለት እኔ ነኝ እንጂ እሱ እንዳይደውል ህግ አለን!! ስልኩን በቃሌ ነው የማውቀው እንጂ ሴቭ አላደርገውም!!)

…… በእኔ አስችሎሽ በጤናሽ ሁለት ወር እንደማትቆዪ አውቃለሁ። እኔስ አንቺን ባጣ ሰው እንደማልሆን አታውቂም? ከዛ በላይ መጠበቅ አልችልም ነበር ትኬቴን ቆርጬ መጣሁ!! የያዝኩትን ሻንጣ የያዝኩት ሆቴል ክፍል ወርውሬ ልብሴን እንኳን ሳልቀይር ማንን መጠየቅ እንደነበረብኝ እርግጠኛ ስላልነበርኩ እቤት መሄዱ አደገኛ ሊሆን ስለሚችል ብዬ ክለቡጋ ሄድኩ!! መምጣቴንም እዛ መሆኔንም ማን እንደነገራቸው አላውቅም!! ከዛ ወጥቼ ታክሲ ልይዝ ስጠብቅ መጥተው በመኪናቸው ከበቡኝ!!»

«ቆይ ቆይ ቆይ (ከእቅፉ ወጣሁ!) ክለብ ማንን አገኘህ? ማንን አናገርክ? ስንት ሰዓት ነው የሄድከውስ?»

«አመሻሽ ነገር 11 ወይ 12 ሰዓት ገደማ!! ብዙ ሰው ነበርኮ እኔእንጃ!» አለኝ ግራ እየገባው።

«ከበር ጀምሮ ያናገርከውን ሰው አንድ በአንድ ንገረኝ!! ለማስታወስ ሞክር!» እያልኩት መኪናውን አስነስቼ መንዳት ጀመርኩ።

«ጋርዶቹን? መግባት አይቻልም ሰዓት ገና ነው ብለው እንቢ አሉኝ መጀመሪያ እ ….. ከዛ አንቺን ፈልጌ እንደሆነ ከካናዳ የተላከ ዕቃ ላደርስ እንደሆነ ነገርኳቸው እና ከውስጥ የሆነ ሰው ጠርተው አገናኙኝ። ከዛ ለእነርሱ የነገርኳቸውን ስነግረው ሄደሽ እንደማታውቂ …. አንድ ቀን ብቅ ብለሽ እንደነበር ነገረኝ። የግድ ማድረስ ያለብኝ እቃ አለ ስለው እሱም ገብቶ ዳዊት የሚባል ሰው ጠራልኝ። ፍቅረኛሽ መሆኑን ነገረኝ (እዚህጋ የአይመስለኝም ሽርደዳ ያለበት ፈገግታ ፈገግ ብሎ በቁም ነገር የሚያወራውን እየተከታተልኩ እንደሆነ ሲያውቅ ወደ ቁምነገሩ ተመለሰ።) እሱ ወደ ውስጥ እንድገባ ጋበዘኝ እና ከዛ በቃ ያልታወቀ ሰው በሽጉጥ መትቶሽ እንደነበር ከዛም ድጋሚ ከሰዎች ጋር ተጣልተሽ እስከሆስፒታል የሚያደርስ ጉዳት ደርሶብሽ እንደነበር እና እቤት እንደማገኝሽ ነገረኝ።»

« ከኤርፖርት ሆቴልህ? ከሆቴልህ ክለብ? በመሃል የሄድክበት ቦታ አለ? አስታውስ? ያናገርከው ሰው? ሁለቴ የገጠመህ ሰው?»

«ሜል? እኔን ታውቂኝ የለ? ጀርባዬን እያየሁ የምሄድ ሰውኮ አይደለሁም!! ግን ማንንም አላገኘሁም!! ከዛ ውጪ የትም አልሄድኩም! ያናገረኝም ያናገርኩትም ሰው የለም ከሪሴፕሽኖቹ ውጪ!!» አለኝ ተጨንቆ

«ክለብ ውስጥ ሌላ ማን ነበር?»
«የሚሰሩ ሰዎች ነበሩ!! ቤቱን እያስተካከሉ ምናምን የነበሩ እኔ እንጃ በደንብ አላስተዋልኩም ግን ሴቶችም ነበሩ!!»

«ስምህን የነገርከው ወይም የእኔ ወንድም መሆንህን የነገርከው ሰው አለ?»
«ለዳዊት! ስሜን ነግሬዋለሁ ግን ያንቺ ወንድም መሆኔን አልነገርኩትም!! ዳዊት እባላለሁ ሲለኝ ኪዳን! ብዬዋለሁ!!»

«ምን ያህል ይሆናል ውስጥ የቆየኸው?»
«እኔ እንጃ አንድ ሰዓት!! የሚጠጣ ጋብዞኝ አንድ አንድ ብርጭቆ ይዘን ነው የሆነውን የነገረኝ!! ይኸው ጀመረሽ ነገር ስትቀምሪ መሃል ቤት እኔን የምታጦዥኝ ነገርሽ!»

«ጥርጣሬ እንጂ ያረጋገጥኩት ነገር ስለሌለ ልነግርህ አልችልምኮ ኪዳንዬ! መጠጡን የጋበዘህ እሱ ነው? አልጠጣም ብለኸው ነበር? እንድትጠጣ ወተዋተህ?»

«አይ እውነትም ፍቅረኛሽ ነበር በሚገባ ነው የምታውቂው!! አዎ አልጠጣም እቸኩላለሁ ስለው። <እዚህ ድረስ መጥተህ ሳላስተናግድህ መሄድህን ሜሉ ብትሰማ ትቀየመኛለች፤ አንድ ብርጭቆ ይዘን የሆነውን ላውራህ አለኝ!!»

«ይሄ የውሻ ልጅ!! እውነት ባይሆን ነው የሚሻለው እንጂ አልለቀውም! (ይሄ ጤነኛ ንዴት ይሆን አልገባኝም! ጭንቅላቴ ከውስጥ የተወጠረ አይነት ስሜት ነው የሚሰማኝ የሆነ ሊፈነዳ የቀረበ ነገር። ደረቴ ላይ እልህ እና ቁጣ ከትንፋሼ ጋር እኔ ልውጣ እኔ ልቅደም ግብ ግብ የገጠሙ አይነት ስሜት) ይሄ ሙት እሱም ሰው ሆኖ መሆኑ ነው?» ኪዳን እየሆነ ያለው ግራ ገብቶት

«ሜል? እሱ ደውሎላቸው ነው የመጡት ብለሽ ነው የምታስቢው? ከአጠገቤኮ ለአፍታም ዞር አላለም ነበር። ኸረ በፍፁም እንዲህ የሚያደርግ ሰው አይመስልም! ግማሹን ሰዓትኮ እንዴት እንደሚወድሽ ነው ሲነግረኝ የነበረው። ደግሞ ፍቅሩ አይኑ ላይ ያስታውቃል። ምንም ከማድረግሽ በፊት አጣሪ እህትዬ በእኔ ሞት? እ?»

«ሌባ አይኑ እና ቅቤ ምላሱ አይሸውድህ!! በእርግብ ላባ ያጌጠ እባብ ነው!! ታውቀኛለህ ደግሞ ባልተረጋገጠ ነገር ምንም አላደርግም!!» እያልኩት ስልኬን አውጥቼ ደወልኩ!!

«ሻለቃ! ሜላት ነኝ!!»
«ሜላት ሜላት?»
«አውቀኸኛል ባክህ! እንዴት አስታውሳ ደወለች ብለህ ከሆነ ግራ የተጋባኸው አዎ አስታውሼ ነው!! አደጋ የደረሰብኝ ቀን ለኤግዝቢትነት በሚል የወሰዳችሁትን ስልኬን መረጃውን ከውስጡ አፅድታችሁ እንደመለሳችሁልኝም ጭምር ነው ያስታወስኩት! ለሶስተኛ ወገን አሳልፋችሁ ሰጥታችሁ ማለቴ ሸጣችሁ የግሌን መረጃ እንደነገዳችሁበትም ጭምር!! ልቀጥል?»

«ምን እንደምታወሪ ታውቂዋለሽ? ወይስ ጥይቱ ሚሞሪሽን ብቻ ሳይሆን ማሰቢያሽንም ነው የወሰደው?»

«ምን እንደማወራ አሳምረህ ታውቃለህ!! ፌስቡኬ የእኔ መሆኑን ሰይጣን እንኳን አይደርስበትም። ድንገት እኔ በተመታሁ በነጋታው 10 ዓመት ሙሉ ማን መሆኔ ሳይታወቅ የተጠቀምኩበት አካውንት በአስማት ታወቀና ዘጉት ነው የምትለኝ ያለኸው? ኦው ለምን ስልኬን እንደሚፈልጉት አልነገሩህም ማለት ነው?» ዝም አለ ለአፍታ

«የውልህ! በጣም በተቻለኝ አቅም ጥሩ ሴት ልሆን እየሞከርኩ ያለሁበት ሰዓት ላይ በመሆኑ ፈጣሪህን አመስግን!! ከናንተ ጋር አውጫጭኝ የምጫወትበት ጊዜ የለኝም!! አንድ መረጃ ብቻ ነው የምፈልገው!! የመታኝን ሰው ማወቅ ነው የምፈልገው!! መሃል ከተማ ነው! አመለጠ ምናምን በሚል ተረት ተረት እኔን አትሸውደኝም!! ግማሽ መንገድ ላግዝህ? ጥቁር ጃጓር መኪና የጎማው ቸርኬ ወርቅማ ፣ ከኋላው መስታወት በቀኝ በኩል ጠርዝ ላይ ትንሽዬ ቀይ ስቲከር ያለበት፣ ታርጋ ቁጥሩ የመጨረሻ ሁለት ቁጥር 52 ነው!! እኔ ሁለት ጥይት መትቶኝ ይሄን ሁሉ መረጃ ስቶር ማድረግ ከቻልኩ ምርመራውን የያዘው ወይም ይዞ የለቀቀው ባልደረባህ በአንድ ሰዓት ውስጥ ሙሉ መረጃውን ጠረጴዛህ ላይ ማኖር አይቸግረውም!! ሌላው ደግሞ ሴት ናት!! ወንድ ለመምሰል የሞከረች ሴት ናት!! መኪናው በማን ስም እንደተመዘገበ እና ሴትየዋ ማን እንደሆነች ብቻ ነው ማወቅ የምፈልገው። ከአንድ ሰዓት በኋላ እደውልልሃለሁ! ከዛ ቀድመህ አሁንም ቢሆን የምትነግረኝ ነገር ካለህ ግን ዝግጁ ነኝ!!» ዝም አለኝ። ስልኩን ዘጋሁት!! እና ወደኪዳን ዞሬ

«ያረፍክበት ሆቴል ደውል እና ሻንጣህን መውሰድ እንደምትችል አረጋግጥ!! የምታርፍበት ሌላ ቦታ እንፈልጋለን። ለጊዜው እኔም ወደቤት መሄድ ያለብኝ አይመስለኝም!!»


«በእንዲህ ዓይነት ሰዓትኮ ሌላ የማላውቃት ሴት ነው የምትሆኝብኝ!! ውስጥሽ ሁለት ሴት ያለች ነው የሚመስለኝ! የእኔ ሜል እና የሌላ ሰው ሜላት! የእኔዋ እናት፣ እህት፣ ስስ ፣ የምታለቅስ ፣ የምታቅፍ ፣ የምታባብል ፣ ቀድማኝ የምትሞትልኝ …….. ያችኛዋ አያድርስ ነው!! » አለ ኪዳን በመገረም ሲያየኝ ቆይቶ!!
2025/07/05 06:16:13
Back to Top
HTML Embed Code: