Warning: mkdir(): Permission denied in /var/www/bootg/function.php on line 101

Warning: file_put_contents(aCache/detail/y/e/m/e/yemetshaf_qdus_tinat.txt): Failed to open stream: Permission denied in /var/www/bootg/function.php on line 103
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት - Telegram Web
📖መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መግቢያ📖
✞ክፍል ሶስት✞

መጽሐፍ ቅዱስ በቁጥርና በምዕራፍ ማንና ለምን ከፈለው?
መጽሐፍ ቅዱስ በምዕራፍ መከፋፈሉ ከመጻሕፍቶቹ አንዱ ክፍል የያዘውን ሐሳብ በደምብ ለማጥናትና የት እንደሚገኝ ለማስታወስ ጥቅሙ ስለተረዳ የእንግሊዝ ካንተር በሪ ካርዲናል(ሊቀ ጳጳስ) ስቴቨን ላንግተን በ13ኛው ክ.ዘ. የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን በምዕራፍ ከፋፈለው።ሶስት መቶ ዓመታት አለፍ ብሎም በ1551ዓ.ም ሮበርት ስቴፋነስ የተባለ ፈረንሳዊ በምዕራፍ ያሉትን ሙሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በቁጥር ከፋፈላቸው ይህም በምዕራፍ ውስጥ ያሉትን ሐይለ ቃላት ቶሎ ለማግኘት በጣም አጋዥ ሆነ።የእነዚህ ሁለት ሰዎች ስራ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለቤተ ክርስቲያን ትልቅ ውለታ ነው።ውለታቸውም በስነ መለኮት ትምህርት(theology)፣በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ከመጽሐፍ ቅዱስ እያጣቀሱ በሚጻፉ መጻህፍት እንዲሁም በሰባክያን ዘንድ የጀርባ አጥንት በመሆን በቤተ ክርስቲያን አሰራር ላይ የማይረሳና የማይቀየር የሚመሰገንም አሻራ ሆኗል። እግዚአብሔር የድካማቸውን ዋጋ ይስጣቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎች ፈጠራ አለመሆኑና እውነተኛነቱ በምን ይታወቃል? ተብሎ ለቀረበው ጥያቄ፡-
☞በመጻሕፍቱ አንድነት ይታወቃል ይህም በተለያዩ ፀሐፊዎችና በተለያዩ ጊዜያት ውስጥ ቢፃፍም አንድ ሐሳብ አንድ ዓይነት ስሜት አላቸው።በዚህም አንዱ የእግዚአብሔር መንፈስ እንዳፃፋቸው እናውቃለን።
ስለ ነቢያቱ መጻሕፍት "21፤ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።"
(2ኛ የጴጥሮስ መልእክት 1:21፤)
በሐዋርያት ላይ መንፈስ ቅዱስ እንደሚሞላና እንደሚመራቸው እንጂ ከራሳቸው ፈጥረው እንደማይናገሩ

(የዮሐንስ ወንጌል 16)
----------
"13፤ ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል።

14፤ እርሱ ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና።

15፤ ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህ። ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል አልሁ። "

ደግሞም
(የዮሐንስ ወንጌል 15)
----------
"26፤ ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፤

27፤ እናንተም ደግሞ ከመጀመሪያ ከእኔ ጋር ኖራችኋልና ትመሰክራላችሁ።"

ከዚህ እንደምንረዳው ነቢያቱን የመራውና የተናገረው የእግዚአብሔር መንፈስ፤ሐዋርያቱንም የመራና የተናገረው ነው ስለዚህ መጻሕፍቱ የሐሳብ አንድነት አላቸው ከእግዚአብሔር እንጂ ከሰው ፈቃድ እንዳልሆኑ እናውቃለን።

☞በተለይም በመጻሕፍቱ አንድነት ውስጥ የምናየው ስለ ክርስቶስ ያላቸው ምስክርነት ነው ለምሳሌ
ዘፍ፡-የሴቲቱ ዘር
ዘጸ፡-የፋሲካው በግ
ዘሌ፡-የመጨረሻው መስዋዕት
ዘኁ፡-የያዕቆብ ኮከብ
መዝ፡-መልካሙ እረኛ
ኢሳ፡-የሰላም አለቃ የዘላለም አምላክ የድንግል ልጅ
ኤር፡-የጽድቅ አምላክ
ዳን፡-የተቀባው(መሲሕ)
ሐጌ፡-የሁሉም ሕዝቦች ምኞት
ዘካ፡-የጌቶች ጌታ የአማልክት አምላክ
ሚል፡-የኪዳኑ መልእከተኛና የጽድቅ ፀሐይ
ማቴ፡-አማኑኤል የድንግል ልጅ
ማር፡-የእግዚአብሔር ልጅ፣የሰው ልጅ
ሉቃ፡-የመዳን ቀንድ
ዮሐ፡-ቃል፣የሕይወት ውሃ፣ትንሣኤና ሕይወት፣የዓለም ብርሃን፣የእግዚአብሔር በግ፣መልካሙ እረኛ
ሐዋ፡-የሚፈርደው
መልእክታት፡-ፋሲካችን፣የማዕዘን ድንጋይ፣የማይታይ አምላክ ምሳሌ፣አስታራቂ መስዋዕት፣በስጋ የተገለጠ
ራዕ፡-የይሁዳ አንበሳ፣አልፋና ኦሜጋ፣ፊተኛና ኋለኛ፣የሚያበራ የንጋት ኮከብ፣በብረት በትር የሚገዛ፣የአማልክት አምላክ የጌቶችም ጌታ፣የታመነው ምስክር ወዘተ

(የዮሐንስ ወንጌል 5)
----------
"46፤ ሙሴንስ ብታምኑት እኔን ባመናችሁ ነበር፤ እርሱ ስለ እኔ ጽፎአልና።

47፤ መጻሕፍትን ካላመናችሁ ግን ቃሌን እንዴት ታምናላችሁ?"

ስለዚህ በእግዚአብሔር መንፈስ ምሪት ስለተፃፉ የሐሳብ አንድነት ኣላቸው፡፡

(የሉቃስ ወንጌል 24)
----------
"44፤ እርሱም። ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው አላቸው።

45፤ በዚያን ጊዜም መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው፤

46፤ እንዲህም አላቸው። ክርስቶስ መከራ ይቀበላል በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፥

47፤ በስሙም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ ይሰበካል ተብሎ እንዲሁ ተጽፎአል።

48፤ እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ።"
እንዳላቸው በወንጌልና በመልክታቸው ስለ ክርስቶስ ይመሰክራሉ፡፡ አጠር ባለ መልኩ ይህን ይመስላል።

☞የአሁኑ መጽሐፍ ቅዱስ ከድሮው በዘመን ሂደት ተበርዟል?
አልተበረዘም!!
መጽሐፍ ቅዱስ ሶስት ቅጂዎች ማለትም ዕብራይስጥ፣ ግሪክ፣ ሱርስት(ኣራማይክ) ቅጂዎች አሉት እነዚህ ቅጂዎች ቀዳሚ እንደ መሆናቸው በተለይም ግሪኩና ዕብራይስጡ ማመሳከሪያም ናቸው።በሌላ ቋንቋ ሲታተምም በነዚህ ሚዛንነት ነው።ወደ ሌላ ቋንቋ ተርጓሚው እንደ ትውልድ ቋንቋው ተናጋሪ(native speaker) ካልሆነ የትርጉም ክፍተት ሊፈጠር ይችላል።ከቀደምት መጻሕፍት ጋር በማስተያየት ግን በታተመው ላይ ያለው ልዩነት ይታወቃል።ስለዚህ እነዚህ ማመሳከሪያዎች ስላሉ ትርጉም ስራ ላይ የቃላት ለውጥ ቢፈጠር ይታረማል እንጂ ለመበረዝ ክፍተት የለውም።ጌታም እንዳለው ቃሉ ሕያውና የታመነ ነው አይሻርም አይበረዝም
"ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም" ማቴ24፥35
ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁን!!
📖የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መግቢያ📖
✞ክፍል አራት✞
🔐አጭር የጥናት መመሪያ🔐

መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች ቋንቋ እንደ መጻፉ እግዚአብሔር የጸሐፊዎቹን ቋንቋ፣ ባህል፣ የሚኖሩበት አካባቢ መልክዐ ምድራዊ አቀማመጥ፣ስነ ቃል ወዘተ ተጠቅሞ ስላፃፋቸው የመጽሐፉን ክፍል ስናጠና መጀመሪያ ስለፀሐፊው ማንነት ቀጥሎም የስነ ጽሑፉ ቅርፅ ባሕርይ(ዓይነት)፣ የሐገሩ ሰዋስው(አገባብ) ወዘተ መረዳት ያስፈልጋል።ለዛሬ በጥናት ጊዜ የሚጠቅሙን አንኳር ሐሳቦችን እንይ

1ኛ.መመልከት ፦ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ግምታዊ አሰተሳሰብ ሳንሰጥ እንዲሁም ከሌሎች ወይም በስብከት የሰማነውን ትርጉም ቶሎ ሰጥተን አንለፍ ይልቅ ጥቅሶቹ በደምብ ሐሳባቸውን መረዳት "የተባለውን ነገር እውነት ይገልፃሉ?"ብሎ ማንበብ እንጂ ትርጉም ለመስጠት አለመቸኮል።ጸሐፊው በዚህ ክፍል ምን ማለት እንደፈለገ አንብበን በጥሞና መረዳት። በሚከትሉት ጥያቄዎችም በመደገፍ እውነቱን ማስተዋል ይገባል
★ባለታሪኮቹ እነማን ናቸው? ምን ተሰራ ምንስ ተደረገ? የት ቦታ በምንስ ሁኔታ? መቼ? እንዴት? ለምንስ? ውጤቱስ ምን ነበር? ምንስ ተፈጠረ?
የምናጠናውን ክፍል ከአውደንባቡ ለይተን ማውጣት የለብንም!!

★2ኛ.መተርጎም ፦ምን ማለቱ ነው? የሚለውን በመጠየቅ ፍቺ መስጠት። በአሁኑ ጊዜስ ተመሳሳይ የሆነው ፍቺው ምንድነው? መዝገበ ቃላት በመጠቀም ቃላቶቹን ፣ ሐረጎቹን፣ ቅኔያዊ አነጋገሮችንና ዐረፍተ ነገሮችን መተንተን

★3ኛ.ማዛመድ
ለምን ይህንን ሃሳብ ፣ ሐረግ፣ ቃል ተጠቀመ? ለምንስ ይህንን እዚህ መጥቀስ አስፈለገው? ያሉት የተለያዩ ሃሳቦችስ እንዴት ይዛመዳሉ?
ጠቃሚውን ሃሳብ ማግኘት።
ጎልቶ የሚታየውን መንፈሳዊ ሃሳብ ወይም መልዕክት ለይተን ማውጣት።ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ጋረ መስማማቱን ማረጋገጥ።
ዋናውን መልዕክት ቸል ብለን በጥቃቅን ነገሮች ላይ እንዳናተኩር ያልገባንን ለሌላ ጊዜ ጥናት ማስተላለፍ ወይም ሌሎችን በመጠየቅ መረዳት።

★4ኛ.የተለያዩ ሊቃውንት ትንታኔዎችን መመልከት
የአንዱን ሊቅ ሐሳብ ብቻ በመያዝ ትርጉም ሰጥቶ አይታለፍም!! ምክንያቱም በሊቃውንቱ አፈታት ወይም አተናተን ላይ መራቀቅ ሊኖር ይችላል ማለትም የአውደንባቡ ሐሳብ ሌላ ሊሆን ይችላል ነገር ግን በመራቀቅ እንዲህ ብለን ብንገልፀውም ያስኬዳል በሚል ንጽጽር ሐሳቡን ሊያሳዩን ይችላሉ።
★እዚህ ላይ ቅድሚያ ርቀ'ታዊ ሀሳቡ ሳይሆን የሚፈለገው ቀዳሚ አውደ ንባባዊ ትንታኔው ወይም ትርጉሙን ነው መጀመርያ የጸሐፊው(የነቢዩ ወይም የሐዋርያው) ሐሳብ ማግኘትና መረዳት ነው ያለብን። ስለዚህ ምክንያት የተለያዩ ትንታኔዎችን ማየት አለብን።አንዱ ሊቅ ምን ብሎ ተነተነው?ሌላውስ ምን አለ? ማእከላዊ (ሁሉንም ሊቃውንት የሚያቀራርበው) ትንታኔስ የትኛው ነው? በሚሉት ላይ በማተኮር ማጥናት።
እነዚህ ጠቅለልና አጠር ባለ መልኩ በጥናት ሂደት የሚጠቅሙን መመሪያዎች ናቸው።
በቀጣይ ክፍል ኦሪት ዘፍጥረት ትንታኔ እንጀምራለን
✞❀✞❀✞❀✞❀✞❀✞
"19፤ ደግሞ የወንጌልን ምሥጢር በግልጥ እንዳስታውቅ አፌን በመክፈት ቃል ይሰጠኝ ዘንድ ስለ እኔ ለምኑ፤"
(ወደ ኤፌሶን ሰዎች 6:19፤)
✞❀✞❀✞❀✞❀✞❀✞
መዝሙረ ዳዊት 118(119)
"76. ምሕረትህ ለመጽናናቴ ትሁነኝ፥ እንደ ቃልህም ለባሪያህ ይሁነው።
'
'
130. የቃልህ ፍቺ ያበራል፥ ሕፃናትንም አስተዋዮች ያደርጋል።

131. አፌን ከፈትሁ፥ አለከለክሁም፤ ወደ ትእዛዝህ ናፍቄአለሁና።"
✞❀✞❀✞❀✞❀✞❀✞
"5፤ ቆማችሁ ከዘላለም እስከ ዘላለም አምላካችንን እግዚአብሔርን ባርኩ። እንዲህም በሉ። በበረከትና በምስጋና ሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያለው ክቡር ስምህ ይባረክ። "
(መጽሐፈ ነሀምያ 9:5፤)
አሜን!!
📖ኦሪት ዘፍጥረት መግቢያ📖
⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️
ኦሪት ❀ኦራይታ❀ ከሚል የሶርያ(አራማይክ) ቃል የተገኘ ነው።ትርጓሜውም ❀ሕግ❀ ወይም ❀ትምህርት❀ ማለት ነው።የመጠሪያ ምንጩም ከዕብራይስጡ ኣቻ ትርጉም ❀ቶራሕ❀ የሚለው ሲሆን አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት የሚጠሩበት ነው።እነርሱም ዘፍጥረት፣ዘጸአት፣ ዘሌዋውያን ፣ዘኁልቊ፣ዘዳግም ናቸው።በሃገርኛው መጠሪያም ብሔረ ኦሪት ይባላሉ።በግሪክም "Penta-teuch" "አምስቱ መጻሕፍት" የሚል መጠሪያ አላቸው።
መጻሕፍቱም ከ1446-1440 ዓ.ዓ(ቅ.ል.ክ) በሊቀ ነቢያት ሙሴ ተጽፈዋል። ኦሪት ዘፍጥረት የፍጥረት ትምህርት የሚል ሐገርኛ መጠሪያ(ትርጉም) ሲኖረው በዕብራይስጥ "በረሺት" በግሪክ "ጄኔሲስ" ማለትም "ጅማሬ አጀማመር" የሚል አቻ ትርጉም አለው እንግሊዘኛውም የግሪኩን መጠሪያ ይዋሳል።ይህንን ስያሜ የተሰጠውም ከመጽሐፉ ይዘት(ባሕርይ) አንፃር ነው።
እንዴት ብንል
ስለ ሁሉም ፍጥረታት
ስለ ሰው ልጅ
ስለ የእግዚአብሔር በረከት በፍጥረቱ ላይ
ስለ የእግዚአብሔር ትእዛዝ በሰው ልጅ ላይ
ስለ ሰው ልጅ ሐጢአት
ስለ ሰው ልጅ ከእርግማን በታች መሆን(መረገም)
ስለ ሰው ልጅ በምድር ላይ መብዛት
ስለ ሰው ልጅ ክፋትና የተሰጠው ቅጣት(የጥፋት ውሃ)
ስለ ሰው ልጅ እንደገና በምድር ላይ መብዛት
ስለ አይሁድ ቤተሰብ ማለትም ከአብርሃም እስከ ግብጽ መውረድና መብዛት ብሎም ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ግንኙነት
አጀማመር/ጅማሬ ስለሚተርክ ነው።በዚህም በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የጸሐፊው ልዩ ትኩረት እንረዳለን።እርሱም ወደ ሐዲስ ኪዳን የሚመሩን ሐሳቦቹ ናቸው።
በቀጣይ ምዕራፍ አንድ እንጀምራለን አገልግሎቱን ቶሎ ለማድረስ ትጋቱ ይሰጠኝ ዘንድ ጸልዩልኝ አባታችን ሆይ ስትሉ አስቡኝ🙏🙏🙏
✿✞❀✞✿✞✿✞❀✞✿✞❀
"የሰላምም ጌታ ራሱ በሁሉ መንገድ ዘወትር ሰላምን ይስጣችሁ። ጌታ ከሁላችሁ ጋር ይሁን።"
(2ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 3:16፤)
ሠላመ እግዚአብሔር ከሁላችሁም ጋር ይሁን.. 🙏
ከዛሬ ጀምሮ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይቀጥላል...
በነገር ሁሉ አብርሆቱን ይስጠን አሜን!!

NB:-አዳዲስ የተቀላቀላችሁን ደግሞ ወደ ላይ መለስ ብላችሁ አራቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መግቢያ አንብባችሁ ስለመጽሐፍ ቅዱስ ምንነት፣ አመጣጥና እድገት እንዲሁም ስለ ኦሪት ዘፍጥረት መግቢያ በቂ ግንዛቤ ይዛችሁ እንድትጀምሩ አሳስባለሁ
ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 1፥1📖
"በመጀመርያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ"
👉#<በመጀመርያ_እግዚአብሔር>
ቀደም ብለን መግቢያው ላይ እንዳየነው የመጽሐፉ ስያሜ አጀማመር ወይም መጀመርያ የሚል ነው።ይህም የፍጥረታት ጅምርን (አፈጣጠርን) ይገልጥልናል ማለትም ለሁሉም ፍጥረት መጀመርያ አለው፥መጀመርያ ካለው ከዛ በፊት አልነበረም።ለመኖሩ ጅምር በእግዚአብሔር ሐይል መፈጠሩ ብቻ ነው።ለፍጥረት መጀመርያው እግዚአብሔር ነው ማለትም ከእግዚአብሔር መፈጠራቸው ነው።ለእግዚአብሔር ግን መጀመርያ የለውም እርሱ ለፍጥረት መጀመርያ ወይም ጀማሪ(ፈጣሪ) ነው እንጂ።ከመፍጠሩ በፊትም ብቻውን ነበር።ለመኖር ጀማሪውም ራሱ ነው ይህም ስንል ሕያው ሆኖ የነበረ እርሱ ብቻ ነበር ፍጥረታትን ከፈጠረ በኋላ መኖርን ፍጥረታት ሁሉ ተካፈሉ ካለ መኖር ወደ መኖር መጡ።በኩር መጀመርያ ማለት እንደመሆኑ እግዚአብሔር በመኖር በኩር(ቀዳሚ) ነው።የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ሐሳቡን ያጠናክርልናል

📖"...በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት #በኩር ነው፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሯል፤" (ወደ ቆላስይስ ሰዎች 1: 15-16)
ዮሐንስም በወንጌሉ
📖"በመጀመርያ ቃል ነበረ፥ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ቃልም እግዚአብሔር ነበረ" ዮሐ1፥1
ብሎ ስለ ክርስቶስ ፊተኛነት ይነግረናል።ሌሎችም ይህን ሐሳብ በደምብ የሚያብራሩልን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ከዮሐንስ ራእይ እናገኛለን

📖" አለኝም፦ አልፋና ዖሜጋ፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ። ለተጠማ ከሕይወት ውኃ ምንጭ እንዲያው እኔ እሰጣለሁ።"
(የዮሐንስ ራእይ 21: 6)

📖" አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ።"
(የዮሐንስ ራእይ 22: 13)

ፊተኛ(መጀመርያ የነበረ) እና ኋለኛ(ፍጥረታትን ኣሳልፎ የሚኖር መጨረሻ) አልፋ እና ኦሜጋ(በግሪክ መጀመርያ እና መጨረሻ ማለት ነው)

📌ሥላሴ (አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ) አልፋና ኦሜጋ ነው። በአንድነት መጠርያ በግእዝ እግዚአ ብሔር (የዓለም ጌታ) ተብሎ በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የተቀመጠልን ለሥላሴ ነው።ሰማይና ምድር ሳይፈጠሩ ያለመቀዳደም አንዱ አካል አንዱን ሳይቀድም በአንድነት ነበሩ።ፍጥረታትን ሲፈጥሩም በአንዲት ሥልጣን በአንድነት ሥራ(coordination) ነው።የሰው ልጅ የተለያዩ የሰውነት ክፍለ አካላት በአንድነት ኖረው አንድ ማንነት ያቆማሉ (ይወክላሉ፣ይገልጣሉ) በአንድነትም ይሰራሉ።አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስም በአንድነት እግዚአብሔር የሚለውን ማንነት ይገልጣሉ በአንድነትም ይሰራሉ።ሥላሴ በአብ ህሊናነት አስበው በወልድ ቃልነት ይሁን ብለው ተናግረው በመንፈስ ቅዱስ ህያው አድርገው ካለ መኖር ወደመኖር አምጥተው ፍጥረታትን ፈጠሩ።

👉#<ሰማይንና ምድርን ፈጠረ>
ነብዩ ሙሴ ሰማይንና ምድርን ፈጠረ ሲል ሙሉውን ሳይሆን ከፊል ይዘታቸውን ነው፥ይህም ስንል ጅምር ሰማይና ምድር (ያላለቁ) መሆናቸውን ቀጥሎ በጠቀሰው የስነፍጥረት ሒደት እንመለከታን ማለትም የብርሃን መፈጠርና መከፈል፣የውሃ በጠፈርና በምድር መከፈል(ተከፍሎ መቀመጥ)፣የየብስ መገለጥ፣በምድር ስለሚኖሩ እንስሳትና እፅዋት መፈጠር፣የፀሐይ ጨረቃና ከዋክብት መፈጠር ወዘተ የእነዚህ የመፈጠር ሒደት ሰማይንና ምድርን ፈጠረ ካለ በኋላ ስለሚገልጥልን ነው::ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬምም ይህንን ሲያጠናክር በኦሪት ዘፍጥረት ትንታኔ መጽሐፉ እንዲህ ይለናል

➡️"ሰማይንና ምድርን ፈጠረ ሲል ሙሉ ይዘታቸውን ሳይሆን ንጥረ ነገሮቻቸውን(substances) ነው።ሰማይ ሰማይ እንዲሆን የሚያስችለው መሰረት፥ምድርም ምድር እንድትሆን የሚያስችላት ይዘት ሲሆን፤ ቅጽና ቅርፅ የሌላቸው (formless፡void) ሆነው መጀመርያ ላይ የነበራቸው ይዘትን ነው ሚገልጠው።"

ይህ ማለት ቀለል ባለ ምሳሌ ልክ አንድ ቤት መጀመርያ መሰረቱ ተጥሎ "beam" ና "colon" ታስሮ ወደ ቀጣዩ የግምባታ ሂደት ሲዘጋጅ ለማለት ነው።በተቀመጠው ጠርዝ ቅርፅ(design) ብሎኬት ወይም ድንጋይ እየተደረደረ ይገነባል፣በደምብ በሲሚንቶ ይለሰናል፣በርና መስኮት ይገጠምበታል፣ቀለም ይቀባል፣መብራትም ይገባበታል ያኔ ቤት ይሆናል።

⚠️ማሳሰብያ:-በዚህ መጽሐፍ ማስተዋል ያለብን ነገር ሙሴ ዘፍጥረት ሲፅፍ ስለሁሉም ፍጥረታት አፈጣጠር አልጠቀሰም።አጠርና ጠቅለል አድርጎ ስለ ፍጥረታት ፃፈልን እንጂ።
በቀጣይ ከቁጥር 2 ጀምሮ ያለውን እንመለከታለን እግዚአብሔር አምላክ ቃሉን እንድናስተውል አእምሯችንን ይክፈትል

ፍጥረታትን ካለ መኖር ወደ መኖር ያመጣ ያከናወነም ሁሉንም ለፈጠረ ለሥሉስ ቅዱስ እግዚአብሔር ክብር ይሁን አሜን!!
🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏
📖ኦሪት ዘፍጥረት 1፥2-3📖
"ምድርም ባዶ ነበረች፥ አንዳችም አልነበረባትም፤ ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር።
እግዚአብሔርም፦ ብርሃን ይሁን አለ፤ ብርሃንም ሆነ።"


📝👉<< ምድርም ባዶ ነበረች አንዳችም አልነበረባትም >>
ባለፈው ክፍል እንዳየነው ቅፅና ቅርፅ የለሽ የነበረው ምድር መሬታማው አካል ብቻ ነበረ ይህም ስንል ዕፅዋትም ይሁን ሌላ ነገር ሳይኖረው ከውሃማ አካል ጋራ ተቀላቅሎ(ተውጦ) መኖሩን ነው።

📝👉<< ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ >>
የጨለማው አፈጣጠር በመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ዘንድ በሁለት ጎራ ይተነተናል።
🌑1.የመጀመርያዎቹ <<ጨለማ የብርሃን አለመኖር ነው እንጂ ራሱን የቻለ የተፈጠረ ረቂቅ አካል አይደለም ብርሃን ገና ስላልተፈጠረ የውሃውና የምድሪቱ አካላት(ከፍተኛና ዝቅተኛ ቦታዎች) ጥምረት ጥላው በጥልቁ(abyss) ላይ ጨለማን አሰልጥኗል🌊🏔🌊።የጨለማው መኖር የተገለጠው በጥልቁ ላይ መሆኑ አንዱ ማሳያ ነው>> ይላሉ።
📍ቅዱስ ኤፍሬምም በዘፍጥረት ትንታኔው <<የእግዚአብሔር ነፋስ በውሃው ላይ ሰፍፎ ነበር ካለን የግድ ከባድ ደመናት ይፈጠራሉ ደመናቱም ጥልቁን በጥላቸው ያጨልሙታል..በዘጸ10፥22 እንደተገለፀም ግብጽን ሶስት ቀንና ሌሊት ያጨለማት ብርሃንን እንዳታገኝ በመከልከል ነው>> በማለት ሐሳቡን ይደግፋል።

🌌2.ሁለተኞቹ ደግሞ <<ጨለማ ረቂቅ አካል ሆኖ ብርሃንን ቀድሞ የተፈጠረ ነው።የጨለማ መኖር የሚታወቀው በብርሃን አማካኝነት ማለትም በብርሃን አለመኖር መሆኑ አንድ ላይ መገለጥ ስለማይችሉና ብርሃን ከጨለማ በላይ ሐይል ስላለው ነው። ቢሆንም ብርሃንን ተፅእኖ ፈጣሪ አካል ጨለማን ግን እንደ ውጤት የምንረዳው አይደለም።የብርሃን አካል መኖር በተፅእኖው(በሚበራው በብርሃኑ) እንደምናየው ሁሉ ጨለማም በራሱ አካል መሆኑ በተፅእኖው እናየዋለን።>> ይላሉ ።የአክሲማሮስ መጽሐፍ ደራሲም ይሄንን ይደግፋል።

💡የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅም <<ጨለማ አካል ቢሆንም ባይሆንም ፍጥረት ነው… ጨለማ እንዲፈጠር የግድ አካል መኖር ካለበትም ያው ከተፈጠረ አካል የሚገኝ ፍጥረት ነው ማለት ነው ጨለማው።ራሱን ችሎ የተፈጠረ አካል ከሆነም ጨለማው ያው ፍጥረት ነው።>> በሚል ይደመድማል

📝👉<<የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር >>
እዚህ መንፈስ ተብሎ የሰፈረው ቃል በአይሁድ ሊቃውንት ነፋስ ወይም ኃይለኛ ነፋስ(wind,mighty wind) የሚለውን ለመወከል ነው ሲሉ ቃል በቃል ሲወሰድ ደግሞ "የእግዚአብሔር(ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ) ነፋስ" የሚል በኢሳ 40፥7 "፤ የእግዚአብሔር እስትንፋስ ይነፍስበታልና ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል፤" ተብሎ ከተቀመጠው አገላለጽ ጋር አንድ ያደርጉታል።
📍ቅዱስ ኤፍሬምም "ይሄኛው አገላለጽ በ1ኛ ሳሙ16፥14 <ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያሰቃየው ነበር> ተብሎ እንደተጠቀሰ ዓይነት ነው ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ ነፋስ ወይም የእግዚአብሔር ነፋስ።ኤሎሂም ብሎ ሶስቱን አካላት(ሥላሴ በክርስትናው) ከጠራ በኋላ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን ለይቶ የሚጠራበት አሳማኝ ምክንያት አናገኝም።ሥላሴ በአንድነት እየፈጠሩ እንዳለ ነግሮን መንፈስ ቅዱስን ለይቶ የሚጠራበት ምክንያት ምንድነው? ፈጣሪነቱን ለማሳየት ነው የሚል ካለ "ሰፍፎ ነበር" የሚለውን የነፋስ በውሃ ላይ የመስፈፍ ባሕርይን ገለጠ እንጂ በውሃው ላይ ምን አደረገ ምንስ ፈጠረ? ከውሃውስ ምን ወጣ? ምንም የተፈጠረ ወይም የወጣ ነገር የለም።በአምስተኛው ቀን "እግዚአብሔር ውሃ ሕያው ነፍስ ያላቸውን ተንቀሳቃሾች ታስገኝ" ብሎ አሶችንና ወፎችን ሲፈጥር ውሃው ላይ ለምን ሰፍፎ ነበር ብሎ አልገለጸም ለመፍጠር ብንል እዚህ የተመቸ ነበርና።ነገር ግን መንፈስ ብሎ ነፋስን እንጂ መንፈስ ቅዱስን ለመግለጥ እንዳልሆነ ይህ ያሳየናል።ከአራቱ ባሕርያት(ንጥረ ነገሮች) ነፋስን ለመግለፅ ነው።" በማለት ሐሳቡን ያጠነክረዋል። ኢትዮጵያውያን ሊቃውንትም በዚህ ትንታኔ መሰረት ዓውደ ንባቡን ተርጉመውታል(ከስር ያለውን ፎቶ ይመልከቱ)👇📸

📝👉<<እግዚአብሔርም ብርሃን ይሁን አለ ብርሃንም ሆነ>>
ከአራቱ የሥነ ፍጥረት ንጥረ ነገሮች ወይም ባሕርያት(four elements) የመጨረሻው ፍጥረት ብርሃን ነው። አራቱ ባሕርያት 1.ምድር(መሬት፥ደረቅ አካል)፣2.ነፋስ(አየር)፣3.ውሃ(ፈሳሽ አካል)፣4.ብርሃን(እሳት፥ብሩህና ሞቃት አካል) ናቸው።እነዚህ ባሕርያት(ንጥረ ነገሮች) ለፍጥረት ሁሉ እንደየ ወገኑ መስሪያው መሠረቱ ናቸው።ከቁጥር 1 እስከ 3 የተጠቀሱት ፍጥረታት ካለ መኖር ወደ መኖር(እም ኀበ አልቦ ኀበ ቦ) የመጡ ናቸው።ከዚህ ቀጥለው የምናገኛቸው ፍጥረታት ደግሞ ከነዚህ ባሕርያት የሚፈጠሩ(ግብር እም ግብር) ናቸው።
🌪🌪🌪🌪🌪🌪🌪🌪🌪🌪🌪🌪🌪🌪
"፤ ሰማያትን የፈጠረ እግዚአብሔር፥ እርሱም ምድርን የሠራና ያደረገ ያጸናትም፥ መኖሪያም ልትሆን እንጂ ለከንቱ እንድትሆን ያልፈጠራት አምላክ፥ እንዲህ ይላል፦ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ከእኔም በቀር ሌላ የለም።"
(ትንቢተ ኢሳይያስ 45: 18)
🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏
ሁሉን በኃይሉ ካለመኖር ወደመኖር ያመጣ የፈጠረም ሥሉስ ቅዱስ እግዚአብሔር ይባረክ!!አሜን
"እግዚአብሔርም ብርሃኑ መልካም እንደ ሆነ አየ፥ እግዚአብሔርም ብርሃንንና ጨለማን ለየ። እግዚአብሔርም ብርሃኑን ቀን ብሎ ጠራው፥ ጨለማውንም ሌሊት አለው። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አንድ ቀን።" (ኦሪት ዘፍጥረት 1፥4-5)

📍<<እግዚአብሔርም ብርሃኑ መልካም እንደ ሆነ አየ>>
የተፈጠረው ብርሀን በጨለማው ተውጠው የነበሩትን ፍጥረታት ሲገልጥ፣ለወደፊትም ከሚፈጠሩት ፍጥረታት ጋር ያለውን ቁርኝት ማለትም ከዕፅዋት፣ከእንስሳትና ከሰው ልጆች፣ከአየርም ያለውን ቀጥተኛ ግንኙነትና #ጠቃሚነቱን እንዳሰበው መልካም ነው።

📌<<እግዚአብሔርም ብርሃንንና ጨለማን ለየ፥ እግዚአብሔርም ብርሃኑን ቀን ብሎ ጠራው፥ ጨለማውንም ሌሊት አለው።>>

👉ጨለማን እንደ አንድ ፍጥረት(አካል) የሚቆጥሩቱ ይህንን አውደ ንባብ "የሁለቱ አካላት(ብርሃንና ጨለማ) ስራቸውንና ስልጣናቸውን መለያየቱ ያሳያል ብርሃናዊ አካል ሲሰለጥን ቀን ይሆናል ጨለማው አካል ሲሰለጥን ሌሊት ይሆናል" ሲሉ።
👉ጨለማን የብርሃን አለመኖር ነው ከሚሉቱ አንዱ ቅዱስ ኤፍሬም ደግሞ "ብርሃንና ጨለማ ተደባልቀው ስለነበረ ሳይሆን ብርሃን ይሁን ባለ ቅፅበት ብርሃን ተፈጠረ ነገር ግን ሁሉንም ቦታ አልሸፈነም(ጨለማን ሙሉ በሙሉ አላስወገደም) ብርሃኑ ባልተዳረሰበትና ባልነካበት ቦታ አሁንም ጨለማ አለ።ስለዚህ ለየ የሚለው ብርሃኑ ዑደት እንዲያደርግ ማዘዙን ነው ይህም አንዱ ቦታ ሲያበራ ሌላኛው ይጨልማል፥የጨለመውጋ ሲያበራ በርቶ የነበረው ይጨልማል።በእንዲህ ዓይነት ዑደት ብርሃንና ጨለማ እንዲኖሩ ማዘዙን ማለትም የስራና የቦታ ተፅዕኖ ልዩነታቸውን ቀንና ሌሊት ነው የሚያሳየን " ይላል።

#ለየ ስራቸውን እንዲጀምሩ አደረገ

📍<<ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አንድ ቀን>>

💡የአዘጋጁ እይታ
በመጀመርያ ብርሃን ከመፈጠሩ በፊት ሰልጥኖ የነበረው ጨለማ(ሌሊት,ማታ) ነው።ብርሃን ይሁን ካለ በኋላም ብርሃን(ቀን,ጥዋት) ነው የሆነው።ስለዚህ አንድ ቀን ይሆናል።የተጠቀሰው ምንባብም ጠቅለል አድርጎ የሚገልፀው ይህንኑ ነው።
ነገር ግን ብርሃን ከተፈጠረ በኋላ ዑደቱ በጨለማ እንዲጀምር አድርጎት ይሆናል የምንል ካለን አንድ ቀን (የጨለማንና ብርሃንን አንድ ዙር ወይም ዑደት) ዘለን እየጀመርን ስለሆነ ሁለተኛ ቀን ነው የሚሆንብን ስለዚህ አያስኬድም!!።

ጨለማው ለስንት ጊዜ እንደሰለጠነ አይታወቅም ቆይታው ቅፅበት ይሁን ረጂም ዘመናት አልተገለፀም።ብርሃን ሲፈጠርም እንደዛው የጊዜ መለኪያም የለም(አልነበረም)።ይልቁን ጊዜ ማለት(መለኪያ) የብርሃንና ጨለማ መፈራረቅ ነው።ስለዚህ ብርሃንና ጨለማ ከተለያዩ ጊዜ ተፈጠረ ማለት ነው።ልብ ማለት ያለብን ነገር ግን የብርሃንና የጨለማን እርዝማኔ እኛ እንደምናስበው የ12 ሰዓታት ቆይታ አይደለም እኛ የምናሰላው አቆጣጠር በስርዓተ ፀሐይ(solar system) ነው ፀሐይ ደግሞ ገና አልተፈጠረችም።ይህ አቆጣጠር ለእግዚአብሔር የስራ ጊዜ ቆጥሮበት(ተጠቅሞበት) ኋላ ያቆመዋልና ጊዜው በኛ አቆጣጠር አይደለም።የብርሃኑና የጨለማው መፈራረቅ ብቻ እንጂ የቆዩበት ሰዓታት አያመላክትም ስለዚህ ዘመናትም ሊሆን ይችላል። የጨለማው ጊዜ አልፎ ብርሃን ሆነ አንድ ቀን።

(መዝሙረ ዳዊት135 (136 )
------------
1፤ እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ቸር ነውና፥ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና።
2፤ የአማልክትን አምላክ አመስግኑ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና።
3፤ የጌቶችን ጌታ አመስግኑ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤
4፤ እርሱ ብቻውን ታላቅ ተኣምራትን ያደረገ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤
5፤ ሰማያትን በብልሃት የሠራ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤
6፤ ምድርን በውኃ ላይ ያጸና፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤
7፤ ብቻውን ታላላቅ ብርሃናትን የሠራ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤
👼👼👼👼👼👼👼👼👼👼👼👼👼👼
ኦሪት ዘፍጥረት 1፥6-15
6." እግዚአብሔርም፦ በውኆች መካከል ጠፈር ይሁን፥ በውኃና በውኃ መካከልም ይክፈል አለ።"
ምድርን ውጦና ሞልቶ የነበረው ውሃ በመሃሉ ጠፈር(space) ይሁን ውሃውም ይከፈል ብሎ በቃሉ አዘዘ።
@yemetshaf_qdus_tinat

7." እግዚአብሔርም ጠፈርን አደረገ፥ ከጠፈር በታችና ከጠፈር በላይ ያሉትንም ውኆች ለየ፤ እንዲሁም ሆነ።"
እግዚአብሔር በውሃው መሃል ክፍተትን አደረገ ውሃው ከጠፈር በላይና በታች ሆነ ለሁለት ተከፈለ።ይህ ባዶ ይዞታ(space) ከምድር ወደ ላይ ከፍታ ኣስከ ውሃው ድረስ ተዘርግቷል።በቃሉ እንዳዘዘውም ሆነ።
@yemetshaf_qdus_tinat

8." እግዚአብሔር ጠፈርን ሰማይ ብሎ ጠራው። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ሁለተኛ ቀን።"
እግዚአብሔር ይህ ከምድር ወደላይ እስከ ውሃው ድረስ የዘረጋው ውሃውን ለሁለት የሚለይ ጠፈር (ክፍተት) "ሰማይ" ብሎ ጠራው። ጨለማ ሆነ ብርሃንም ሆነ በዚህ በሁለተኛው ቀን ይህ ሆነ።ከሰማይ በታች ያለው ውሃ ያው የምናየውና የምናውቀው ውሃ ነው ከሰማይ በላይ ያለው ውሃ ደግሞ ዳዊት በመዝሙሩ
<ሰማየ ሰማያት እና ከሰማያት በላይ ያላችሁ ውሆች እግዚአብሔርን አመስግኑት>መዝ 147(48)፥4 በማለት ይገልፀዋል።
@yemetshaf_qdus_tinat

9." እግዚአብሔርም፦ ከሰማይ በታች ያለው ውኃ በአንድ ስፍራ ይሰብሰብ፥ የብሱም ይገለጥ አለ፤ እንዲሁም ሆነ።"
ምድርን ሞልቶ ያለው ውሃ በአንድ ስፍራ ይሰብሰብ ደረቁን የምድር አካልም ይገለጥ(ይታይ) ብሎ አዘዘ እንደቃሉም ተከናወነ።ደረቅና ውሃማ አካላት ተለያዩ።
@yemetshaf_qdus_tinat

10." እግዚአብሔርም የብሱን ምድር ብሎ ጠራው የውኃ መከማቻውንም ባሕር አለው፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።"
ከውሃው ውጭ ያለው ደረቁን አካል አፈሩ ድንጋዩ ወዘተ አንድ ላይ #ምድር ብሎ ጠራው።ውሃው አንድ ላይ የተሰባሰበበት የውሃው ክምችት ደግሞ #ባሕር ብሎ ሰየመው በቃሉ እንዳዘዘውም ሆነ።
@yemetshaf_qdus_tinat

11." እግዚአብሔርም፦ ምድር ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን በምድርም ላይ እንደ ወገኑ ዘሩ ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን ታብቅል አለ፤ እንዲሁም ሆነ"
ምድር(ደረቅ አካል) ሁሉም የዕፅዋትና አዝርእት ዓይነቶች ከትንሹ ተክል እስከ ዛፍ ታብቅል ታውጣ ብሎ እግዚአብሔር እንዳዘዘ ተከናወነ ተፈጠረ።
🌿🌲🌴🌵

12." ምድርም ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን እንደ ወገኑ ዘሩም ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን እንደ ወገኑ አበቀለች። እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።"
እግዚአብሔር እንዳዘዛትም ምድር እፀዋትና አዝርእትን እንደየወገኑ አበቀለች ይህም ፍጥረት መልካም እንደ ሆነ አየ።
🌳🍋🍍🍀🍒🌽🌾🥕

13." ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ሦስተኛ ቀን።"
በጨለማውና በብርሃኑ ሶስተኛ(ሰሉስ፡ማክሰኞ) ዑደት (ቀን) ይህ ሁሉ ተከናወነ
@yemetshaf_qdus_tinat

14." እግዚአብሔርም አለ፦ ቀንና ሌሊትን ይለዩ ዘንድ ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ይሁኑ ለምልክቶች ለዘመኖች ለዕለታት ለዓመታትም ይሁኑ፤"
የሥርዓተ ፀሐይን ጨረቃና ከዋክብትን በሰማይ ጠፈር መፈጠርን ያሳይል።

👉<ለምልክቶች> የእግዚአብሔርን መኖር ቸርነትና ርህራሄ ማሳያ፣አቅጣጫ ለማመልከት ወዘተ

👉<ለዘመኖች (seasons)>ወቅቶችን ማለትም ዘመነ መፀው ዘመነ ክረምት ዘመነ ሐጋይና ዘመነ በልግ(ጸደይ) በብርሃኑና ሙቀቱ መጠን የሚያሳድረው ተፅዕኖ አዝማናት ይለያሉ።

👉<ለዕለታት>የፀሐይ መግባትና መውጣት ፥የጨረቃም ከአስራ አምስት ቀን በኋላ ያለው መታየት

👉<ለዓመታት>ከላይ የተጠቀሱት ዑደት(ዙር)፥የጨረቃ ግርዶሽ ወዘተ ለማሳየት ይሁኑ።
@yemetshaf_qdus_tinat

15." በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር ብርሃናት ይሁኑ፤ እንዲሁም ሆነ።"
የነዚህ ብርሃናት መፈጠር ጥቅምና ተፅዕኖ በምድር በተፈጠሩትና በሚፈጠሩት ላይ ነው።(ዕፅዋት፣አእዋፋት፣እንስሳት፣የሰው ልጅ ወዘተ) የፀሐይ ስርዓት ያስፈልጋቸዋልና።እንዳሰበውም በሰማይ ጠፈር ፀሐይ ጨረቃና ከዋክብት ሆኑ (ተፈጠሩ)።
☀️ 🌚 💫 🌞 🌘
ዋናው ልብ ማለት ያለብን ነገር ሌላ ሁለተኛ ብርሃን ሳይሆን የተፈጠረው የብርሃን መሽከርከርያና ማድረሻ አካላት ናቸው የተፈጠሩት።

🌹🌼🌻🌷🌺🌸💐🏵🍁🍂
(መዝሙረ ዳዊት 148 )
------------
3፤ ፀሐይና ጨረቃ፥ አመስግኑት፤ ከዋክብትና ብርሃን ሁሉ፥ አመስግኑት።
4፤ ሰማየ ሰማያት፥ አመስግኑት፤ የሰማያት በላይም ውኃ።
5፤ እርሱ ብሎአልና፥ ሆኑም፤ እርሱም አዝዞአልና፥ ተፈጠሩም፤ የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑት።
🌍🌏🌎🌏🌍🌏🌎🌏🌏🌎🌍
ኦሪት ዘፍጥረት 1፥16-25

16." እግዚአብሔርም ሁለት ታላላቆች ብርሃናትን አደረገ ትልቁ ብርሃን በቀን እንዲሠለጥን፥ ትንሹም ብርሃን በሌሊት እንዲሰለጥን ከዋክብትንም ደግሞ አደረገ።"

👉#ሁለት_ታላላቅ_ብርሃናት እነዚህ ፀሐይና ጨረቃ ናቸው ከከዋክብት ብርሃን አንፃር የሁለቱ ይበልጣልና ታላላቅ ብሎ ጠራቸው።

🌞#ትልቁ_ብርሃን_በቀን_እንዲሰለጥን አሁን ደግሞ ከተጠቀሱት ሁለት ታላላቅ የብርሃን አካላት የሚበልጠውን የብርሃን መሽከርከርያ ማዳረሻ(ፀሐይ) በቀን እንዲሰለጥ(በቀን እንዲያገለግል) አደረገው።

🌜#ትንሹም_ብርሃን_በሌሊት_እንዲሰለጥን ሁለተኛውና ከፀሐይ አንፃር ያነሰው የብርሃን አካል ወይም መሽከርከርያ(ጨረቃ) በሌሊት እንዲያገለግል ከከዋክብት ጋር አደረገው።
@yemetshaf_qdus_tinat
17. እግዚአብሔርም በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር አኖራቸው፤
18. በቀንም በሌሊትም እንዲሠለጥኑ፥ ብርሃንንና ጨለማንም እንዲለዩ፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።

👉እነዚህ በሰማይ ጠፈር ይሁኑ ተብለው የተፈጠሩት የብርሃን አካላት ብርሃንና ጨለማን እየለዩ በምድር ላይ እንዲያበሩ ነው።በዛውም በምድር የተፈጠሩትና የሚፈጠሩት በነዚህ የብርሃን አካላት ተፅዕኖ ውስጥ የሚኖሩ ይሆናሉ።
🌑🌔🌑🌔🌑🌔🌑🌔
19." ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አራተኛ ቀን።"
ይህ ሁሉ በአራተኛው የጨለማና የብርሃን ዙር ሆነ

20." እግዚአብሔርም አለ፦ ውኃ ሕያው ነፍስ ያላቸውን ተንቀሳቃሾች ታስገኝ፥ ወፎችም ከምድር በላይ ከሰማይ ጠፈር በታች ይብረሩ።"

👉እግዚአብሔር በውሃ ውስጥ የሚኖሩ ሕይወት ያላቸው ተንቀሳቃሾችና ወፎች ይፈጠሩ ይብረሩም አለ።
@yemetshaf_qdus_tinat
21." እግዚአብሔርም ታላላቆች አንበሪዎችን፥ ውኃይቱ እንደ ወገኑ ያስገኘቻቸውንም ተንቀሳቃሾቹን ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ፥ እንደ ወገኑ የሚበሩትንም ወፎች ሁሉ ፈጠረ፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።"

👉እንዳለውም በቃሉ ትእዛዝ ሕይወት ያላቸው ተንቀሳቃሾች ከአንበሪዎች (አሶችና ሌሎች ግዙፋን የውሃ ውስጥ አውሬዎች) ጀምሮ እስከ ትናንሽ ተንቀሳቃሾችና ወፎች ተፈጠሩ እነዚህም ፍጥረታት መልካም እንደሆኑ አየ
🐳🐋🐊🦀🐢🦐🦑🦞🐡🦅🦉
22." እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ባረካቸው፦ ብዙ፥ ተባዙም፥ የባሕርንም ውኃ ሙሉአት፤ ወፎችም በምድር ላይ ይብዙ።"
@yemetshaf_qdus_tinat
👉በባህር ውስጥ የሚኖሩትን ውሃውን እንዲሞሉ በምድር ላይ የሚኖሩ አእዋፋት ደግሞ እንዲበዙ እግዚአብሔር መረቃቸው ባረካቸው።
🐧🐥🐟🐠🦎
23." ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አምስተኛ ቀን።"
በአምስተኛው የብርሃንና የጨለማ ዙር (ዑደት) ይህ ሁሉ ሆነ።
🌚🌞🌚🌞🌚🌞🌚🌞🌚🌞
24." እግዚአብሔርም አለ፦ ምድር ሕያዋን ፍጥረታትን እንደ ወገኑ፥ እንስሳትንና ተንቀሳቃሾችን የምድር አራዊትንም እንደ ወገኑ፥ ታውጣ፤ እንዲሁም ሆነ።"
@yemetshaf_qdus_tinat
👉ምድር ሕይወት ያላቸው እንስሳትና ተንቀሳቃሾች(ለሰው ቅርብ የሚሆኑ ለማዳዎች) አራዊትም እንድታወጣ እግዚአብሔር በቃሉ አዘዘ እንደቃሉም ተፈጠሩ።
🐯🐺🐮🐷🦊🐶🦍🐪🦘
25." እግዚአብሔር የምድር አራዊትን እንደ ወገኑ አደረገ፥ እንስሳውንም እንደ ወገኑ፥ የመሬት ተንቀሳቃሾችንም እንደ ወገኑ አደረገ፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።"
🐒🐴🐔🐇🐿🦔🐈🐏🐄🦌
ምድር ታውጣ ብሎ ያዘዛትን ፍጥረታት እንደየወገናቸው ፈጠረ መፈጠራቸውም መልካም እንደሆነ አየ።
🌏🌍🌎🌏🌍🌎🌍🌏🌎🌏
(መዝሙረ ዳዊት 104 )
------------
24፤ አቤቱ፥ ሥራህ እጅግ ብዙ ነው፤ ሁሉን በጥበብ አደረግህ፥ ምድርም ከፍጥረትህ ተሞላች።

25፤ ይህች ባሕር ታላቅና ሰፊ ናት፤ በዚያ ስፍራ ቍጥር የሌለው ተንቀሳቃሽ፥ ታላላቆችና ታናናሾች እንስሶች አሉ።
'
'
31፤ የእግዚአብሔር ክብር ለዘላለም ይሁን፤ እግዚአብሔር በሥራው ደስ ይለዋል።
🐆🦒🐃🐑🦃🕊🐉🦢🦚
📖ኦሪት ዘፍጥረት 1: 26-31📖
26." እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ።"
#በመልካችን_እንደ_ምሳሌአችን:- ይህ ቃል በቀዳሚነት የእግዚአብሔር አካላት ሥላሴን ያሳየናል።ይህ አንቀጽ እየተናገረ ያለው "እግዚአብሄርም አለ" ብሎ፥ አንድ መሆኑን ካሳየ በኋላ "በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር" ብሎ ደግሞ ከአንድ በላይ የውሳኔ ምክረ ሐሳብን ነው።
@yemetshaf_qdus_tinat
ከማን ጋር እየተማከረ ነው ከመላእክት ጋር ነው? አይደለም ከመላእክት ጋር እየተማከረ ቢሆን ኖሮ "ልፍጠር" እንጂ "እንፍጠር" አይላቸውም ነበር ምክንያቱም መፍጠር የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው እንጂ መላእክት ፍጡራን ሳሉ ሊፈጥሩ አይችሉምና።
በትንቢተ ኢሳይያስ ላይ እንደተናገረም ሲፈጥር ያማከረው የለም
<< ፤ ውኆችን በእፍኙ የሰፈረ፥ ሰማይንም በስንዝር የለካ፥ የምድርንም አፈር በመስፈሪያ ሰብስቦ የያዘ፥ ተራሮችን በሚዛን ኮረብቶችንም በሚዛኖች የመዘነ ማን ነው?የእግዚአብሔርን መንፈስ ያዘዘ፥ ወይስ አማካሪ ሆኖ ያስተማረው ማን ነው?ወይስ ከማን ጋር ተመካከረ? ወይስ ማን መከረው?>>ኢሳ 40፥12-14
ስለዚህ ከሌላ አካል ጋር ሳይሆን እግዚአብሔር በራሱ ከራሱ ጋር ማለትም በአንድነቱ አብ ወልድና መንፈስቅዱስ ማሰቡንና መወሰኑን ነው የሚያሳየን
ማለትም አንዳንዴ ለሌላ ሰው ሳይሆን ለራሳችን "እስቲ ዛሬ እንዲህ ልስራ ይሄን ላድርግ" ብለን በህሊናችን ከራሳችን ጋር እንድምንማከረው ዓይነት ነው።
@yemetshaf_qdus_tinat
ሰው እግዚአብሔርን የሚመስለው በምኑ ነው? በስጋው እንዳንል የቆዳው ቀለም ነጭ ነው ጥቁር? የፊቱን ቅርጽስ የኔግሮይድ ነው ካውካሶይድ ወይስ ሞንጎላይድ? በዚህ ሊሆን አይችልም ምክንያቱም በዚህ ከተረዳነው የእግዚአብሔር መልክ ኣለው የምንለው አንዱ ጎሳ ብቻ ቢሆን ነው፥ ሌላውስ የሰው ልጅ በማን መልክ ተፈጠረ ልንል ነው?....በአጭሩ ስጋ ከምድር የተገኘ እንደመሆኑ የእግዚአብሔር መልክ ሊሆን አይችልም።እንስሳት የተፈጠሩት ከምድር(አፈር) ነው የሰው ልጅ ስጋም ከምድር(አፈር) ነው።ይህ በመሆኑም ከእንስሳት ፀባይ ጋር አንድ የሚያደርገው ነገር አለው ፤ይበላል ይጠጣል ይደክማል ይተኛል ወዘተ ይህ እንስሳዊ ባሕሪው ነው። ይህ ባሕርይ ደግሞ በእግዚአብሔር ዘንድ ስለሌለ የእግዚአብሔር መልክ(ማሳያ) ወይም ከእግዚአብሔር የተጋራው ሊሆን አይችልም።
@yemetshaf_qdus_tinat
👨👼👦🏼👼🏽👦🏿👼🏿
ታድያ ከእግዚአብሔር የተጋራው ነገር ምንድነው ካልን የነፍስ ባሕርይን ነው ረቂቅ የሆኑ መገለጫዎች(የእግዚአብሔር መልክ)።ከአብ ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ ማንነት ሁኔታ ወይም መሆን(ኩነት) ልብን ቃልን እስትንፋስን በእግዚአብሔር ባሕርይ ምሳሌ ተካፍሏል።ሰው ማለት የስጋና የነፍስ ውህድ ነው።ነፍሱ በሶስት የኩነት(መሆንን) ባሕርያት ማለትም የማንነት መገለጫዎች እግዚአብሔርን ትመስላለች ማለትም በአንዱ እግዚአብሔር ውስጥ ያሉ ሶስት አካላት መገለጫ ምሳሌ(አምሳል)
1.ለባዊነት #ልብ ማድረግን ማለትም ማስተዋልን(መመራመርን) ማወቅን መረዳትን
2.ነባቢነት መናገርን #ቃል ማውጣትን
3.ሕያውነት የማይጠፋ(የማይሞት) ለዘለአለም ኗሪነትን ሕያው #እስትንፋስን
ሲሆኑ ቸርነት፣ፍቅር፣ርህራሄ፣ምልክና(ገዢነት) ጽድቅ(እውነተኛነት)፣ፍትሐዊነት ወዘተ በተጨማሪም ውስጣዊ(ረቂቅ) የሆኑ አካላት ዓይነ-ልቦና እግረ-ልቦና እዝነ-ልቦና ወዘተ ያጠቃልላል።የሰው ልጅ በነዚህ ባሕርያት ምሳሌ የእግዚአብሔር መልክ አለው።
የእግዚአብሔር አምሳያ እንደመሆኑም በፍጥረታት ሁሉ ላይ ስልጣን ተሰጠው በውሃ ውስጥ በምድር ላይ እንዲሁም በአየር ላይ በሚሽከረከሩትም ፍጥረታት ሁሉ ገዢ እንዲሆን።
👑👑👑👑
27." እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።"
#ወንድና_ሴት_አድርጎ_ፈጠራቸው :- ጠቅለል አድርጎ የአዳምና የሔዋን በእግዚአብሔር መልክ መፈጠርን ነው የሚጠቅሰው።እንዴት እንደተፈጠሩ ግን በኋላ በሁለተኛው ምዕራፍ ያብራራዋል።
👱‍♂️ @yemetshaf_qdus_tinat 👱‍♀️
28-29. "እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው።
እግዚአብሔርም አለ፦ እነሆ መብል ይሆናችሁ ዘንድ በምድር ፊት ሁሉ ላይ ዘሩ በእርሱ ያለውን ሐመልማል ሁሉ፥ የዛፍን ፍሬ የሚያፈራውንና ዘር ያለውንም ዛፍ ሁሉ ሰጠኋችሁ"
ፈጥሮም እንዲበዙ ምድርን እንዲሞሏት በእግዚአብሔር መልክ ምሳሌ እንደ መፈጠራቸውንም በምድር ባሉት ፍጥረታት ላይ ገዢዎች እንዲሆኑ አትክልትም ለምግባቸው እንዲሆናቸው አዳምንና ሔዋንን መረቃቸው(ባረካቸው)።
🍍🍐🍒🌽🥕🥝🍎🍈🍋🌶
30." ለምድርም አራዊት ሁሉ፥ ለሰማይም ወፎች ሁሉ፥ ሕያው ነፍስ ላላቸው ለምድር ተንቀሳቃሾችም ሁሉ የሚበቅለው ሐመልማል ሁሉ መብል ይሁንላቸው፤ እንዲሁም ሆነ።"
ከሰው ውጪ ያሉትም እንስሳት የሚበቅለው ተክል ለምግብ ይሁናቸው።
@yemetshaf_qdus_tinat
31." እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ስድስተኛ ቀን።"
እግዚአብሔር በስድስተኛው የብርሃንና የጨለማ ዑደት(ዙር) የፈጠረው #እጅግ_መልካም_ሆነ ።የዚህ ቀን ፍጥረት እጅግ መልካም መሆኑ በእግዚአብሔር መልክ መፈጠሩ ነው።
🕎📖🕎📖🕎📖🕎📖🕎📖🕎
(መዝሙረ ዳዊት 8 )
4፤ ታስበው ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ትጐበኘውም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድር ነው?
5፤ ከመላእክት እጅግ ጥቂት አሳነስኸው፤ በክብርና በምስጋና ዘውድ ከለልኸው።
6፤ በእጆችህም ሥራ ሁሉ ላይ ሾምኸው፤ ሁሉን ከእግሮቹ በታች አስገዛህለት፥
7፤ በጎችንም ላሞችንም ሁሉ ደግሞም የምድረ በዳውን እንስሶች፥
8፤ የሰማይንም ወፎች የባሕርንም ዓሦች፥ በባሕር መንገድ የሚሄደውንም ሁሉ።
9፤ አቤቱ ጌታችን፥ ስምህ በምድር ሁሉ እጅግ ተመሰገነ::
🕎📖🕎📖🕎📖🕎📖🕎📖🕎
📖ኦሪት ዘፍጥረት 2፥1-3📖
1.“ሰማይና ምድር ሠራዊታቸውም ሁሉ ተፈጸሙ።”
#ሠራዊቶቻቸውም : - በውስጣቸው ያሉት ፍጥረታትንም ሁሉ ፈጥሮ ጨረሰ።
🌍 @yemetshaf_qdus_tinat 🌌
2.“እግዚአብሔርም የሠራውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ፈጸመ፤ በሰባተኛውም ቀን ከሠራው ሥራ ሁሉ ዐረፈ።”
#ሰባተኛው_ቀን : - ብርሃንና ጨለማ የተለያዩበት ከስነ ፍጥረት የመጀመርያው ቀን(እሁድ) አንስተን አዳም እስከ ተፈጠረበት(አርብ) ያለውን የብርሃንና የጨለማ ዑደት(ዙር፣መፈራረቅ) ብንቆጥር 6ቀን ይሆናል ስለዚህ ሰባተኛዋ ቀን ቀዳሚት ሰንበት (የመጀመርያዋ ሰንበት) በአይሁድ "sabbath" የምትባለዋ ናት።የመጀመርያዋ ሰንበት ወይም ቀዳሚት ሰንበት (በተለምዷዊ አጠራር ቅዳሜ) የመባልዋ ምክንያት #እሁድም ሁለተኛዋ ሰንበት(የክርስቲያን ሰንበት፣ሰንበት ዓባይ፣የጌታ ቀን) ተብላ ስለምትጠራ ነው።ስለዚህ እግዚአብሔር ከመፍጠር ያረፈው በሰባተኛይቱ ቀን ቀዳሚት ሰንበት ላይ ነው።
@yemetshaf_qdus_tinat

#ዐረፈ : -በስድስቱ ቀናት ከፈጠራቸው ፍጥረታት ተጨማሪ መፍጠርን #አቆመ #ተወ ማለት ነው እንጂ ፈጣሪ ውጣ ውረድ ድካም የለበትም!!።ይህ ቃል እግዚአብሔር ከፍጥረቱ ጋር ያለው ግንኙነት መገለጫም ነው። እንዴት? በሰባተኛይቱ ቀን ከስራው ሁሉ ዐረፈ ካለ በኋላ ማታም ሆነ ጠዋትም ሆነ አይልም አንድ የዕረፍት ቀን ላይ ነው።ፍጥረቱ የሆነው የሰው ልጅ ደግሞ ወደእርሱ እንዲመጣ(እርሱን እንዲያውቅ) በቃሉም እየኖረ እንዲያመልከው ከፈጣሪው ጋር ህብረት እንዲያደርግ ይፈልጋል።
📜 @yemetshaf_qdus_tinat 📜
እስራኤል ከግብፅ ሲወጡ ለአብርሃም ወደ ማለለት ምድር ይገቡና እርሱን እያመለኩ በመንፈሳዊ ሐሳብ ከእግዚአብሔር ጋር ህብረት እንዲኖራቸው ነበረ ዓላማው ይህም ለዘለአለማዊው ከእግዚአብሔር ጋር የመኖርን ምሳሌ ነው።በእምነት ቃሉን ሰምተው እየታዘዙት መኖር በመንፈስ ዕረፍቱን መውረስ መካፈል ነው።ነገር ግን ከግብፅ የወጡት ቃሉን ሰምተው አላመኑም ባለመታዘዝ አሳዘኑት ፈጣሪም ከኔ ጋር አንድነት ዕድል ፈንታ የላቸውም አለ።
@yemetshaf_qdus_tinat
⚠️“ነገሬንም ስላልሰሙ፥ በእውነት ለአባቶቻቸው የማልሁላቸውን ምድር አያዩም፤ ከእነርሱም የናቀኝ ሰው ሁሉ አያያትም፤”— ዘኍልቁ 14፥23

⚠️መዝ94(95)፥10-11 “ያችን ትውልድ አርባ ዓመት ተቈጥቻት ነበር፦ ሁልጊዜ ልባቸው ይስታል፥ እነርሱም መንገዴን አላወቁም አልሁ።ወደ #ዕረፍቴም እንዳይገቡ በቁጣዬ ማልሁ።”

💠ቅዱስ ጳውሎስም ይህን ዕረፍት በዕብራውያን መልእክቱ ሲያብራራው እንዲህ ይላል
👉“ለእነዚያ ደግሞ እንደ ተነገረ ለእኛ የምስራች ተሰብኮልናልና፤ ዳሩ ግን የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር #በእምነት_ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም።ሥራው ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ምንም እንኳ ቢፈጸም፦ እንዲህ፦ ወደ #ዕረፍቴ አይገቡም ብዬ በቁጣዬ ማልሁ እንዳለ፥ እኛስ ያመንን ወደ ዕረፍቱ እንገባለን።ስለ #ሰባተኛው_ቀን በአንድ ስፍራ፦ እግዚአብሔርም በሰባተኛው ቀን ከሥራው ሁሉ ዐረፈ ብሎአልና፤በዚህ ስፍራም ደግሞ፦ ወደ #ዕረፍቴ አይገቡም።እንግዲህ አንዳንዶች በዚያ እንዲገቡ ስለ ቀሩ፥ ቀድሞም የምስራች የተሰበከላቸው ባለመታዘዝ ጠንቅ ስላልገቡ፦ #ዛሬ_ድምፁን ብትሰሙት ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ በፊት እንደ ተባለ፥ ይህን ከሚያህል ዘመን በኋላ #በዳዊት ሲናገር፦ ዛሬ ብሎ #አንድ_ቀን እንደ ገና ይቀጥራል(ይወስናል)።” ዕብ4፥1-7
🛐 @yemetshaf_qdus_tinat 🛐

3.“እግዚአብሔርም ሰባተኛውን ቀን ባረከው ቀደሰውም እግዚአብሔር ሊያደርገው ከፈጠረው ሥራ ሁሉ በእርሱ ዐርፎአልና።”
#ባረከው_ቀደሰውም : - መልካም ነገር እንዲያስገኝ መልካም እንዲሆን መረቀው ለራሱም ለየው።
#በረከቱም እስራኤላውያን በነቢዩ ሙሴ መሪነት ከባርነት ወጥተው አምላካቸውን አውቀው ህግም በተሰጣቸው ጊዜ ከባርነት ወጥተው ብቻ ሳይሆን ከስጋ ስራም በእግዚአብሔር ስራና ዕረፍት ምሳሌ 6 ቀን ሰርተው በሰባተኛይቱ ቀን እንዲያርፉ ሲታዘዙ፤ከሰማይ ይዘንብላቸው የነበረው መና ለነገው ማሳደር አልተፈቀደላቸውም ለቀኑ በቅቷቸው ካደረ መናው ይበላሻል ለየቀኑም አዲስ የዘነበ ይበሉ ነበር በስድስተኛይቱ ቀን ግን ከዘነበው መና የሁለት ቀን ይሰበስቡና በሰባተኛይቱ ቀን መናም አይዘንብም ያደረውም አይበላሽም አርፈው ይመገቡት ነበር (ዘጸ16)።
📖🕎📖🕎📖🕎📖🕎📖🕎📖🕎
ዕብራውያን 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁹ እንግዲያስ የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ቀርቶላቸዋል።
¹⁰ ወደ ዕረፍቱ የገባ፥ እግዚአብሔር ከሥራው እንዳረፈ፥ እርሱ ደግሞ ከሥራው አርፎአልና።
¹¹ እንግዲህ እንደዚያ እንደ አለመታዘዝ ምሳሌ ማንም እንዳይወድቅ ወደዚያ ዕረፍት ለመግባት እንትጋ።
📖🕎📖🕎📖🕎📖🕎📖🕎📖🕎
📖ኦሪት ዘፍጥረት 2፥4-7📖
ከዚህ በኋላ ያለው የጸሐፊው(ነቢዩ ሙሴ) ሙሉ ትኩረት ወደ ሰው ልጅ ያደርጋል ይተነትናል
4.“እግዚአብሔር አምላክ ሰማይንና ምድርን ባደረገ ቀን፥ በተፈጠሩ ጊዜ የሰማይና የምድር ልደት(ትውልድ) ይህ ነው።”

#የሰማይና_የምድር_ልደት : - እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ባከናወነ በፈጠረ ጊዜ ካለ በኋላ ተመልሶ የሰማይና የምድር ልደት ይህ ነው የሚለው ስለሌላ እንጂ በቁሙ ስለ ሰማይና ምድር ልደት እንዳልሆነ እናስተውል!! ምክንያቱም ስለሰማይ ልደት በምዕራፍ አንድ ከጠቀሰው ጋር የሚመሳሰል ምንም አይተነትንም ስለምድርም ልደት ቢሆን ምንም አይገልፅም። በሰማይና(ፀሐይ፡ጨረቃ፡ከዋክብት ወዘተ) በምድር(እንስሳት፡ዕፅዋት፡ ወዘተ) ተፈጠሩ ያለውን ፍጥረታት ትውልድ በመጀመርያው ምዕራፍ ስለገለጠው አሁን መድገምም አያስፈልገውም። የሰማይና የምድር ልደት ይህ ነው የሚለን ስለማን ነው ካልን ግን ስለ ሰው ነው።

ከፍጥረታት ከሰማይም ከምድርም ባሕርይ የሚካፈል ከሰው ልጅ በቀር ማንንም አናገኝም።የሰው ልጅ በእግዚአብሔር መልክ መፈጠሩ(ነፍሱ) ሰማያዊ፤ ከምድር በሆነው ግዙፍ አካሉ(ስጋው) ደግሞ ምድራዊ ነው።ስለዚህ ከሰማይና ከምድር የሆነ ባሕርይ ስላለው ብቸኛው ፍጡር ሊያብራራ ርእሱ የሰማይና የምድር ልደት ይህ ነው አለ።ምክንያቱም በምዕራፍ1፥27 ሰው በእግዚአብሔር መልክ መፈጠሩና ወንድና ሴት አድርጎ እንደፈጠራቸው እንጂ እንዴት እንደነበረ አፈጣጠራቸው አልገለፀም ነበር።አሁን ግን ገና ከጅምሩ ይህን ሊተነትን ነው።

5.“የሜዳ ቁጥቋጦ ሁሉ በምድር ላይ ገና አልነበረም፤ የሜዳውም ቡቃያ ሁሉ ገና አልበቀለም ነበር፣ እግዚአብሔር አምላክ ምድር ላይ አላዘነበም ነበርና፥ ምድርንም የሚሠራባት ሰው አልነበረም፤”

ቅዱስ ኤፍሬም ይህንን ሲያብራራው
“በምድር የሚፈጠረው ሁሉ ከውሃና ከአፈር ጥምረት ነው ሙሴም ሊያሳይ የፈለገው ይህንን ነው የሜዳ ቁጥቋጦና ቡቃያ አልበቀሉም ምክንያቱም እግዚአብሔር ገና ስላላዘነበ። ”ይላል።
ለሰው ልጅ ምግብ ይሆኑ ዘንድ አትክልት ሳይፈጠሩ ምድርን ያርሳትና ያለማት ዘንድ ሰውም ገና አልተፈጠረም ነበር።

6.“ነገር ግን ጉም ከምድር ትወጣ ነበር፥ የምድርንም ፊት ሁሉ ታጠጣ ነበር።”

🌫ጉም ከምድር ወጥታ የብሱን ሁሉ አጠጣችው አረሰረሰችው ስለዚህ አትክልቱ በዋናነት ደግሞ የሰው ልጅ ይፈጠሩባት ዘንድ ዝግጁ ሆነች።አትክልቱ እንዴት እንደተፈጠሩ በምዕራፍ1 ስለገለጠው እዚህ ላይ አይደግመውም ዋና ትኩረቱ የሰው ልጅ አፈጣጠር ላይ ነውና።

7.“እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ።”

#ከምድር_አፈር_አበጀው : - አፈር ሲል ደረቅ አፈር ላለመሆኑ ጉም ምድሪቱን እንዳረጠበቻት ነግሮናል ስለዚህ የሰው ልጅ ግዙፉ አካል(ስጋ) ከጭቃ እንደተሰራ እንረዳለን።
“እኛ #ጭቃ ነን አንተም ሠሪያችን ነህ፥ እኛም ሁላችን የእጅህ ሥራ ነን።”— ኢሳይያስ 64፥8
“እነሆ፥ በእግዚአብሔር ፊት እኔ እንደ አንተ ነኝ እኔ ደግሞ #ከጭቃ የተፈጠርሁ ነኝ።”— ኢዮብ 33፥6
በምዕራፍ1 እንዳየነው ሰው በዚህ ተፈጥሮው ባሉት ስጋዊ(ምድራዊ) ባሕርያት እንስሳትን ይመስላል።

#ሰውም_ሕያው_ነፍስ_ያለው_ሆነ :- ሕያዋን ፣ሕያው ነፍስ ያላቸው ብሎ በምዕራፍ 1 ለእንስሳት ከተጠቀመበት አገላለፅ ፍፁም የተለየ ነው። ምክንያቱም የእንስሳቱ ተፈጥሮ “ታስገኝ፥ታውጣ” ብሎ ምድርን በቃሉ በማዘዝ ብቻ ነው የተፈጠሩት በዚህም ሕይወታቸው ከምድር ነው ደማዊ ነፍስ ነው ያላቸው ማለትም ነፍሳቸው ደማቸው ነው። ደማቸው ከፈሰሰ ወይም በሌላ ምክንያት ከሞቱ ደግሞ በቃ ሞቱ ነው።ሰው ግን ከእግዚአብሔር ባሕርይ የተከፈለች የእግዚአብሔር መልክ ሰማያዊነት ተሰጠችው። ይህችም #ነፍስ ነች።እንደ እንስሳቱ አካሉ ከምድር በተሰራ ጊዜ ሕያው አልሆነም ሰማያዊ ማንነት የእግዚአብሔር መልክ ባሕርይ በተካፈለ ጊዜ እንጂ።እግዚአብሔር ዘለአለማዊና ሕያው እንደሆነ የሰው ልጅም እንደ እንስሳት ሞቶ የማይቀር ሕያው ነው ነፍሱ አትሞትም ስጋውም ሕይወት የሚኖራት ከነፍሱ የተነሳ ነው።
📖🕎📖🕎📖🕎📖🕎📖🕎📖🕎
“ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፥ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች።”— መዝሙር 139፥14
📖🕎📖🕎📖🕎📖🕎📖🕎📖🕎
📖ኦሪት ዘፍጥረት 2፥8-10📖
8.“እግዚአብሔር አምላክም በምሥራቅ በዔድን ገነትን ተከለ የፈጠረውንም ሰው ከዚያው አኖረው።”

#በምሥራቅ :- ፀሐፊው (ነቢዩ ሙሴ) ካለበት አቅጣጫ ማለትም ከሲናይ ወደ ምስራቅ

#በኤደን :- ኤደን የኤፍራጥስና ጢግሪስ ተፋሰስ ሃገራት ሶርያና ኢራቅ እስከ የፋርስ ባሕረ ሰላጤ የሚያጠቃልል ቦታ ነው (ሜሶፖታሚያ)።

#ገነትን ተከለ : - በኤደን የተለየ የአትክልት ስፍራን(garden) ኣደረገ።

9.“እግዚአብሔር አምላክም ለማየት ደስ የሚያሰኘውን፥ ለመብላትም መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ ከምድር አበቀለ፤ በገነትም መካከል የሕይወትን ዛፍ፥ መልካምንና ክፉን የሚያስታውቀውንም ዛፍ አበቀለ።”

በምድር ሁሉና በዚያች የተለየች የኣትክልት ስፍራ(ገነት) በአንድነት የተደረገን የእጽዋት ተፈጥሮን ያሳየናል።ምክንያቱም እጽዋት የተፈጠሩት በሶስተኛው ቀን እንደ መሆኑ፥ "አበቀለ" ማለቱም በዚያን ቀን(በሶስተኛው) እንደሆነ ልብ በል።

#የሕይወት _ዛፍ :- የተባለችው አዳም እርሷን ከበላ ሕያው የሚሆንባት ዛፍ ናት።ሕያው የሚሆነውም ስጋና ነፍስ እንዳይለያዩ ስለምታደርግ ነው ምክንያቱም ስጋና ነፍስ የሚለያዩት ስጋ በጉዳት አልያም በዕድሜ ብዛት ለመቆም ብቁ ባልሆነ ጊዜ ስለሆነ ይህች ዛፍ ደግሞ ስጋን አድሳ ሕያው ታደርገዋለች ነፍስን ግን አይደለም ነፍስ ከእግዚአብሔር ባሕርይ እንደመከፈሏ በራሷ ሕያው ናትና።

#መልካምንና_ክፉን_የሚያስታውቀውንም_ዛፍ :- ይህ ዛፍ በውስጡ የዕውቀት ሐይል ኖሮት አይደለም።ነገር ግን ባይነካው ፍጥረታት ሁሉ መልካም እንደሆኑ የተፈጥሮን መልካምነት ብቻ ያውቃል ቢበላው ደግሞ መቀጣትን መጎስቆልን ይቀምሳል ስለዚህ ዛፉ የሚያስታውቀው ኑሮን ነው ከመታዘዝ በፊትና በኋላ ያሉ መልካምና ክፉ ኑሮዎች በዛፉ ላይ በሚፈፀሙ ድርጊቶች ይወሰናል።ለምርጫ የተዘጋጀ ዛፍ ነው።

10.“ወንዝም ገነትን ያጠጣ ዘንድ ከዔድን ይወጣ ነበር፤ ከዚያም ለአራት ክፍል ይከፈል ነበር።”

ወንዙ ከኤደን ፈልቆ ገነትን ኣጠጥቶ ሲወጣ ወደ አራት ወንዞች ይከፈላል

ልብ በል:- ወንዞቹ ለአራት ተከፍለው የሚኖራቸውን ፍሰት በመፅሓፉ የተፃፈውና ኣሁን ያለው ጂኦግራፊያዊ የግዛቶቹ ኣቀማመጥ የተለያየ ነው በምዕራፍ 1፥9 ላይ
“⁹ እግዚአብሔርም፦ ከሰማይ በታች ያለው ውኃ #በአንድ ስፍራ ይሰብሰብ፥ የብሱም ይገለጥ አለ፤ እንዲሁም ሆነ።¹⁰ እግዚአብሔርም የብሱን #ምድር ብሎ ጠራው የውኃ መከማቻውንም #ባሕር አለው፤”
ብሏል ስለዚህ የብሱ እንዳሁኑ ክፍለዓለማት ተብሎ በባሕር ያልተከፋፈለ አንድ የብስ ነበረ ባሕሩም በአንድ የተሰበሰበ ውሃ ነበር ማለት ነው።እንዲህ ከነበረ የምድሪቱ ገፅታ እንዴት ሊቀየር ቻለ ካልን በኖህ ዘመን የነበረው የጥፋት ውሃ የብሱ መጀመርያ ላይ አንድ ከነበረበት ገፅታ እየተሰነጣጠቀና እየተንሸራተተ በመሃሉም ባህር እየፈጠረ አሁን ላይ ያለውን በኣህጉር የተከፋፈለ መልክአ ምድር እንዲይዝ ኣድርጎታል።
📌ለማስታወስ ያክል
#መልካምንና_ክፉን_የሚያስታውቀውንም_ዛፍ :- ይህ ዛፍ በውስጡ የዕውቀት ሐይል ኖሮት አይደለም።ነገር ግን ባይነካው ፍጥረታት ሁሉ መልካም እንደሆኑ የተፈጥሮን መልካምነት ብቻ ያውቃል ቢበላው ደግሞ መቀጣትን መጎስቆልን ይቀምሳል ስለዚህ ዛፉ የሚያስታውቀው ኑሮን ነው ከመታዘዝ በፊትና በኋላ ያሉ መልካምና ክፉ ኑሮዎች በዛፉ ላይ በሚፈፀሙ ድርጊቶች ይወሰናል።ለምርጫ የተዘጋጀ ዛፍ ነው።

10.“ወንዝም ገነትን ያጠጣ ዘንድ ከዔድን ይወጣ ነበር፤ ከዚያም ለአራት ክፍል ይከፈል ነበር።”

ወንዙ ከኤደን ፈልቆ ገነትን ኣጠጥቶ ሲወጣ ወደ አራት ወንዞች ይከፈላል

ልብ በል:- ወንዞቹ ለአራት ተከፍለው የሚኖራቸውን ፍሰት በመፅሓፉ የተፃፈውና ኣሁን ያለው ጂኦግራፊያዊ የግዛቶቹ ኣቀማመጥ የተለያየ ነው በምዕራፍ 1፥9 ላይ
“⁹ እግዚአብሔርም፦ ከሰማይ በታች ያለው ውኃ #በአንድ ስፍራ ይሰብሰብ፥ የብሱም ይገለጥ አለ፤ እንዲሁም ሆነ።¹⁰ እግዚአብሔርም የብሱን #ምድር ብሎ ጠራው የውኃ መከማቻውንም #ባሕር አለው፤”
ብሏል ስለዚህ የብሱ እንዳሁኑ ክፍለዓለማት ተብሎ በባሕር ያልተከፋፈለ አንድ የብስ ነበረ ባሕሩም በአንድ የተሰበሰበ ውሃ ነበር ማለት ነው።እንዲህ ከነበረ የምድሪቱ ገፅታ እንዴት ሊቀየር ቻለ ካልን በኖህ ዘመን የነበረው የጥፋት ውሃ የብሱ መጀመርያ ላይ አንድ ከነበረበት ገፅታ እየተሰነጣጠቀና እየተንሸራተተ በመሃሉም ባህር እየፈጠረ አሁን ላይ ያለውን በኣህጉር የተከፋፈለ መልክአ ምድር እንዲይዝ ኣድርጎታል።
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
ምድር አንድ ወጥ የብስ መኖሯንና በተለያዩ ጊዜያትና ምክንያት እንደተሰነጣጠቀች የስነ ምድር ሳይንስ ያምናል።የምድሪቱ ገፅታ አንድ መኖሩ የሚያሳየን ደግሞ #አህጉራቱ እርስ በርሳቸው የሚገጥሙ መሆናቸውን ነው።ከላይ ያለው ሳይንሳዊ ምስል የመጽሀፉ ምንባብ በቀላሉ እንዲገባን ያግዛል!!
📜ኦሪት ዘፍጥረት 2፥11-15📜
_____
#ማስታወሻ ፦ የተለያዩ ትናንሽ ምንጮች በተለያየና ዝቅተኛ ወደሆነ ቦታ በመፍሰስ እየተቀላቀሉ #መጋቢ_ወንዝን ይፈጥራሉ፤እነዚህ የተፈጠሩት መጋቢ ወንዞችም እየተቀላቀሉ አንድ ትልቅ ወንዝ ይፈጥራሉ።ትላልቅ የተባሉት ወንዞችም ወደሌላ ቦታ እንደፈሰሱ ከነርሱ ለሚበልጥ ወንዝ መጋቢ ሊሆኑ ይችላሉ።ይህ በዘመናችን ያለ የወንዝ አፈጣጠር ሂደት ነው። የመጀመርያው ግን የተለየ ነበረ ከኤደን የሚፈልቀው ትልቁ ወንዝ ወደ አትክልቱ ስፍራ(ገነት) ገብቶ እንዳጠጣ ሌላ አራት ወንዞችን ፈጥሮ ይወጣል።እዚህጋ መጋቢው ትልቁ ወንዝ ነው።
🌊🌊🌊🌊🌊🌊🌊🌊
11.“የአንደኛው ወንዝ ስም ፊሶን ነው እርሱም ወርቅ የሚገኝበትን የኤውላጥ ምድርን ይከብባል የዚያም ምድር ወርቅ ጥሩ ነው፤”

#ኤውላጥ(ሐዊላ) ፦ በኩሽ ልጅ (ዘፍ10፥7) የተሰየመ በሲና አከባቢ ያለ አገር(ዓረቢያ) ነው።ከገነት የወጣው የወንዙ አንደኛው ክፍል(ፊሶን) በዚህ አካባቢ ይፈስ የነበረ።
------------------------------------
13.“የሁለተኛውም ወንዝ ስም ግዮን ነው፤ እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል።”
 
#ኢትዮጵያ ፦ ይህ በዕብራይስጡ የኩሽ ምድር ብሎ ነቢዩ ሙሴ የፃፈውን  ”ኢትዮጵያ” ተብሎ በግሪክኛ ሰባ ሊቃናት(septuagint) የተተረጎመ ነው።ፀሓፊው (ነቢይ ሙሴ) ቦታውን በቀጥታ ሲገልጥ፥የሰባ ሊቃናት ትርጉም ግን የፊትን ቀለም ስለሚገልፅ አሻሚ እሳቤ እንዲፈጠር አድርጓል።ምክንያቱም በግሪክኛ «ኢትዮጵያ» #ጥቁር ማለት ስለሆነ። ብዙ ሊቃውንት ደግሞ ወንዙ ከቪክቶሪያ ሃይቅ የሚነሳውና ዓባይን ጨምሮ ብዙ የብዙ ሃገራት ወንዞች እየመገቡት ወደ ግብፅ የሚፈሰው «የናይል-ወንዝ» ነው ብለው ተርጉመውታል።ነገር ግን ናይል ከጥፋት ውሃ በኋላ ባለው የመልክአ ምድር አቀማመጥ የተፈጠረ ወንዝ ስለሆነ ትርጓሜው አያስኬድም አመጣጡ ከኤደን እንደመሆኑ።ዞሮ ዞሮ ግዮን ወደ የአሁኑ አፍሪካ ይፈስ የነበረ ወንዝ ነው።
--------------------------
14.“የሦስተኛውም ወንዝ ስም ጤግሮስ ነው እርሱም በአሦር ምሥራቅ የሚሄድ ነው።”

#አሦር ፦ በሴም ልጅ ዘፍ10፥11 የተሰየመና ነነዌ መናገሻውን ያደረገ የአሁኖቹ ኢራቅ፣ቱርክ፣ኢራን ወዘተ የሚያጠቃልል ግዛት ነው።ጤግሮስ(tigris,hiddekel) በዚህ ግዛት በስተምስራቅ የሚፈስ ወንዝ ነው።
---------------------------
15.አራተኛውም ወንዝ ኤፍራጥስ ነው።”
ኤፍራጥስ ከአሶር በስተምዕራብ የሚፈስ ወንዝ ነው።እግዚአብሔር ለአብርሃም የሚሰጠው ርስት ድንበሩ እስከዚህ ወንዝ እንደሆነ ተጠቅሷል።👇👇

“በዚያ ቀን እግዚአብሔር ለአብራም እንዲህ ብሎ ቃል ኪዳን አደረገ፦ ከግብፅ ወንዝ ጀምሮ እስከ ትልቁ ወንዝ እስከ #ኤፍራጥስ_ወንዝ ድረስ ይህችን ምድር ለዘርህ ሰጥቼአለሁ፤”— ዘፍጥረት 15፥18
📜ዘፍጥረት 2፥15-18📜
------------------------------
15.“እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ወስዶ ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በዔድን ገነት አኖረው።”

#ያበጃት_ይጠብቃትም_ዘንድ ፦ ስለዚህ ክፍለ ምንባብ ሰቨርያን እንዲህ ይላል «ይሰራና ይጠብቃትም ዘንድ የሚለው ሌባ ሳይኖር አላፊ መንገደኛም ሳይኖር ወይም ሆን ብሎ ክፉ የሚያደርግ ሰውም ሳይኖር ከማን ነው የሚጠብቃት? ከራሱ ነው የሚጠብቃት።ትእዛዙን ካልተላለፈ ገነትን አያጣትም፥ትእዛዙን መጠበቅ ለሰውልጅ ስራ ነው በዚህ ስራም ራሱን ይጠብቃል የተሰጠችውን ገነትንም ይጠብቃል»
ሰውን በመልኩ እንደ ምሳሌው ከፈጠረው በኋላ በኤደን ወደ አዘጋጀለት ልዩ የአትክልት ስፍራ አስገባው።
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
16.“እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤
17.ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና።”

የታዛዥነቱ መለኪያ ቀዳሚው ትእዛዝ ይህ ነው ዛፉ መርዛማ ሆኖ ወይም የሆነ ልዩ የዕውቀት ሃይል ኖሮት ሳይሆን ቁጥር 9 እንደተብራራው መልካምና ክፉ የተባሉት የመኖር ሁኔታዎች የሰው ልጅ ለተሰጠው ትእዛዝ ባለው ግብረ መልስ የሚወሰን ነው።ምክንያቱም መልካም ብቻ ነው የሚያውቀው ዛፏን አትንካት ተብሏል ካልነካትም በዚህ መልካምነት ብቻ ይኖራል፥ትእዛዙን ከተላለፈና ዛፏን ቢበላ ግን ክፉን ያውቃል ማለትም በሞት(ከእግዚአብሔር መለየት፥የስጋና የነፍስ መለያየት) መቀጣት መጎስቆልን ያውቃል።ክፉና መልካም የሚያስታውቅ መባሉ ስለዚህ ነው።
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
18.“እግዚአብሔር አምላክም አለ፦ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት።”

#የሚመቸውን_ረዳት ፦ ረዳት ባርያ ወይም ተገዢ ሳይሆን በባህርይ በሙላት እርሱን የምታክል ሆና ለዓይኑ ደስ የምታሰኝ ከእርሱ ጋር በደስታ የምትነጋገር በሁሉም ከእርሱ ጋር የምትስማማ ለሁኔታውና ለፍላጎቱ በሙሉ መልስ የምትሰጥ...

#እንፍጠርለት ፦ በምዕራፍ 1፥26 እንዳለው ትንታኔ በተመሳሳይ እዚህ ምንባብም እንጠቀመዋለን። እግዚአብሔር ሌሎች ፍጡራንን እያማከረ ሳይሆን፥ የመፍጠር ውሳኔ ምክረ-ሐሳብ ከራሱ ጋር ብቻ እንጂ ሌሎችን አላማከረምና በራሱ ከራሱጋር ማሰቡንና መወሰኑን የሚያሳይ ነው፥ ልክ እኛ እስኪ ዛሬ ይሄን ላድርግ ይሄን ልስራ ብለን በህሊናችን ከራሳችን ጋር እንደምንመክረው ነው።
2024/05/03 04:23:51
Back to Top
HTML Embed Code: