Telegram Web Link
የቅዱስ ሲኖዶስ  መግለጫ

ግንቦት ፳/፳፻፲፯ ዓ.ም

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 በተደነገገው መሠረት የርክበ ካህናት መደበኛ ስብሰባውን ከግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም እስከ ግንቦት 19 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ አካሂዷል፡፡
የመንበረ ሐዋርያት ወራሽ የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ ለቤተ ክርስቲያናችን አንድነትና እድገት፣ ለሀገር ሰላምና መረጋጋት፣ ለሐዋርያዊ ተልእኮ መስፋፋትና ለመንፈሳዊ ልዕልና ልዩ ትኩረት በመስጠት አስፈላጊ ውሳኔዎችን አሳልፎአል፡፡
በዚሁ መሠረት፡-
1. ለሰላምና ለአንድነት ቅድሚያ መስጠት፣ምትክ ለሌለው የሰው ልጅ ሕይወት ባለአደራ የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ ስለ ሰላም ያለማቋረጥ መጸለይ፣ ጸሎተ ምሕላ ማወጅ፣ የሰላምና የአንድነት ጥሪ ማስተላለፉ እንደተጠበቀ ሆኖ ለሰላምና ለአንድነት ልዩ ትኩረት ሰጥተው ሁሉን አቀፍ ሥራ የሚሠሩ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን “የሀገራዊ ሰላምና የቤተ ክርስቲያን አንድነት ኮሚቴ” በማድረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ሰይሟል፡፡
ኮሚቴውም ዘላቂ ሰላምንና አንድነትን ለማስፈን፣ የዜጎችን ሕይወት እየነጠቀ ያለው ግጭት እንዲቆም ጥረት እንዲያደርግ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትን ባካተተ መልኩ በየደረጃው የምክክርና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና፣ ውይይቶችንና የጥናት መድረኮችን እንዲያዘጋጅ፤ አፈጻጸሙንም በየሦስት ወሩ ለቋሚ ሲኖዶስ ሪፖርት እንዲያደርግ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
2. ለሰዋስው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የትርጓሜ መጻሕፍትና የሴሚናሪ ደቀ መዛሙርት የሚሰጠው የምስክር ወረቀት ዲግሪ እንዲሆን በተወሰነው መሠረት በመማር ላይ ያሉትና በቀድሞው ሥርዓተ ትምህርት ተምረው በመመረቅ ቤተ ክርስቲያናችንን በማገልገል ላይ የሚገኙት ምሩቃን ተጓዳኝ ትምህርቱን ተምረው ዲግሪያቸውን ማግኘት እንዲችሉ የቀረበው ሥርዓተ ትምህርት ተግባራዊ እንዲደረግ፣በኮሌጁ የተጀመረው ሁለገብ ሕንፃም በተያዘለት የጊዜ ሠሌዳ መሠረት እንዲጠናቀቅ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
3. በገዳማት አስተዳደር መምሪያ አስፈጻሚነት የተደረገው የአንድነት ገዳማት ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ በየዓመቱ እንዲካሄድና የአቋም መግለጫው ላይ የቀረቡት ሐሳቦች በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት በኩል እየታዩ በቅደም ተከተል እንዲፈጸሙ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አስልፏል፡፡
4. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለሀገራችን እድገትና ሥልጣኔ ፈር ቀዳጅ በመሆን ያበረከተችው አስተዋጽኦ በታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ጉልህነት ያለው ሲሆን፣ አሁንም እየተሠራ ባለው የኮሪደር ልማት መርሐ ግብር ላይ ኃላፊነቷን እየተወጣች ትገኛለች፡፡
ይኽን ቋሚ ታሪክ ያልዘነጋው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ክብርት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ የቤተ ክርስቲያንን ይዞታ ለግንባታ በሚያመች ሁኔታ አሰባስቦ በመስጠት ለፈረሱ ቤቶች ካሣ በመክፈል፣ በጽርሐ ምኒልክ ሕንጻ ምትክ በነባሩ ቦታ ላይ B+G+4+ቴራስ በመንግሥት በጀት መልሶ እንዲገነባ በማድረጋቸው ቅዱስ ሲኖዶስ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡

በይዞታዎቻችንም ላይ ደረጃውን የጠበቀ ግንባታ ለማካሄድ የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ ተሰይሞ ገቢ የማሰባሰብ ሥራው በሕጋዊ መንገድ እንዲከናወን ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ ሰጥቷል፡፡
በመሆኑም በፈረሱት ቤቶች ምትክ የተረከብናቸውን ክፍት ቦታዎች በአጭር ጊዜ ማልማት ግዴታ ስለሆነ በዓለም ዙሪያ ያላችሁ ኦርቶዶክሳውያን የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን እንደ አባቶቻችሁ የታሪክ ባለቤቶች ትሆኑ ዘንድ ልማቱን በገንዘብና በእውቀት እንድታግዙ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
5. በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት የተፈጠረውን የአስተዳደር ችግር አስመልክቶ በብፁዓን አባቶች የሚመራው አጣሪ ልዑክ ባቀረበው ሪፖርት መሠረት ውይይት በማድረግና የሥራ ኃላፊዎቹን በማንሣት ቅዱስ ሲኖዶስ አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን አስተላልፏል፡፡
ወደፊትም በየደረጃው ያለውን ችግር ማስተካከል ይቻል ዘንድ ችግሩን እያጠና የሚያቀርብ ኮሚቴ እንዲቋቋም ምልአተ ጉባኤው ወስኗል፡፡

6. ዝክረ ኒቅያ በሚል መሪ ቃል ከመላው ሀገራችን በተወከሉ የምስክር ጉባኤ ቤቶች መምህራን በተካሄደው ጉባኤና የጥናት ውይይት የቀረበው ምክረ ሐሳብ እጅግ የሚጠቅም የሊቃውንት ድምጽ በመሆኑ፣በነገረ ማርያም፣ በነገረ ክርስቶስና በሌሎችም አስተምህሮዎች ዙሪያ የተሰጡት ሐሳቦች የቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜን መሠረት በማድረግ ተብራርቶና ተስተካክሎ፣ የጎደለው ሞልቶ፣ የጠመመው ተቃንቶ በሊቃውንት ጉባኤ በኩል በመጽሐፍ መልክ እንዲታተም፣በሚዲያ ሊተላለፍ የሚገባው አስተምህሮ ደግሞ በሊቃውንት ጉባኤ ብቻ እንዲተላለፍ፣
የሊቃውንት ጉባኤውም በተሟላ የሰው ኃይልና በጀት ተጠናክሮ እንዲደራጅ፣ሀገር አቀፍ ጉባኤው በዓመት ሁለት ጊዜ እንዲደረግና የጉባኤው መዋቅር በየአህጉረ ስብከቱ እንዲጠናከር ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

7. የመናገሻ አምባ ማርያምና የጋራው ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም አንድነት ገዳም ጥንታዊ የሆነ ሰፊ ታሪክ ያለው በመሆኑ ሁለቱ ገዳማት በአንድ አበምኔት በአንድነት ገዳም ሥርዓት በጋራ እንዲመሩ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤

8. በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ገዳማት መነኰሳትን ከመላክ ጀምሮ፣በአስተዳደራዊና ቀኖናዊ አሠራር ክፍተት ምክንያት የተከሰቱ ችግሮችን በማረምና ሊቀ ጳጳሱን በማዛወር ማእከላዊ መዋቅር እንዲጠበቅ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰነ ሲሆን፣ነባሩ መተዳደሪያ ደንብ ተሻሽሎ እንዲቀርብ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የሚመራ ኮሚቴ ሰይሟል፤

9. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሕገ ልቡና፣በሕገ ኦሪትና በሕገ ወንጌል ያገኘቻቸው ዶግማዊ፣ ቀኖናዊና ትውፊታዊ ሀብቶቿ የሕግ ጥበቃና ከለላ አግኝተው ሃይማኖታዊ፣ታሪካዊና ሁለንተናዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ ተከብረውና ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
10.  የ2018 ዓ.ም የመደበኛ እና የካፒታል ዓመታዊ በጀት ብር 5,407,415,607.25/አምስት ቢሊየን አራት መቶ ሰባት ሚሊዮን አራት መቶ ዐሥራ አምስት ሺህ ስድስት መቶ ሰባት ብር ከሃያ አምስት ሣንቲም/እንዲሆንና የበጀት አርዕስቱ ተጠብቆ ሥራ ላይ እንዲውል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

11. በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ በመገንባት ላይ የሚገኘውን ሕንጻ በተመለከተ የተፈጠረው የአሠራር ግድፈት እንዲታረም፣ዩኒቨርስቲው ከባንክ ጋር የገባው የብድር ውል እንዲቋረጥና የተጀመረውን ሕንፃ በራሱ አቅም እንዲገነባ ሆኖ፤ የቤተ ክርስቲያናችንን አንጡራ ሀብት ማለትም ሕንጻዎችን፣መሬቶችንና ሌሎች ቋሚ ንብረቶችን በማስያዝ የሚደረጉ ብድሮች ተፈጻሚ እንዳይሆኑ የሚያደርግ መመሪያ ለሁሉም አህጉረ ስብከት እንዲተላለፍ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
12. የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደር ልማት ድርጅትን አስመልክቶ በቀረበው ሪፖርት መሠረት የሥራ ክፍተቱን በማረም በየደረጃው ያሉ ኃላፊዎች እንደየጥፋታቸው እንዲጠየቁና እንዲታረሙ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
13. የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ምርጫን አስመልክቶ በሥራ ላይ የነበሩት ብፁዓን አባቶች የሥራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁ በመሆኑ ለቀጣይ ሦስት ዓመታት የሚሠሩ ብፁዓን አባቶችን ለመምረጥ ዕጩዎችን የሚያቀርቡ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን በመሰየም ምልዓተ ጉባኤው ተገቢውን ምርጫ አከናውኗል፡፡
በዚሁም መሠረት ፡-
*. ለቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊነት ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ በደቡባዊ ዞን ማይጨው፣ የደቡባዊ ምሥራቅ ትግራይና የራያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን መርጦ ሰይሟል

*. ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪጅነት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣የሸገር ከተማ እና የምስካዬ ኀዙናን መድኃኔዓለም ገዳም የበላይ ኃላፊ ሊቀጳጳስን መርጦ ሰይሟል፡፡
* ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የሀድያና ስልጤ አህጉረ ሰብከትን እንደያዙ  የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
* ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ ሆነው እንዲሠሩ ቅዱስ ሲኖዶስ መርጦ ሰይሟል፡፡
* ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የደቡብና ምዕራብ አፍሪካ ሀገረ ሰብከት ሊቀ ጳጳስ
* ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የሜኖሶታና የኮሎራዶ አህጉረ ሰብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው እንዲሠሩ ቅዱስ ሲኖዶስ መድቧል፡፡

14. ብፁዕ አቡነ ገብርኤል የምዕራብ ሸዋ ሀገረ ሰብከት ጳጳስ፣ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የደቡብ ኦሞና አሪ ዞኖች አህጉረ ሰብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዕ አቡነ በርናባስ የደቡብ ካልፎርኒያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሚዲያ ያስተላለፏቸው ትምህርቶች ስሕተትና ነቀፋ ያለባቸው  መሆናቸውን አምነው ቅዱስ ሲኖዶስንና መላውን ሕዝበ ክርስቲያን ይቅርታ በመጠየቅ ሊቃውንት ጉባኤ ከቅዱሳት መጻሕፍት በማጣቅስ ያቀረበውን አስተምህሮ የተማሩት የሚያምኑትና የሚያስተምሩት መሆኑን በመግለጻቸው ቅዱስ ሲኖዶስ የሦስቱን አባቶች ይቅርታ ተቀብሎ ወደፊት እንዲህ ዐይነት የስሕተት  ትምህርት ውስጥ
እንዳይገኙና ነቀፋ ያለበትን ትምህርታቸውን በማረምና በማስተካከል  ርቱዕ የሆነውን የቤተ ክርስቲያናችንን አስተምህሮ መሠረት በማድረግ በኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  መገናኛ ብዙኀን ሥርጭት ድርጅት በመቅረብ ትምህርት እንዲሰጡ በማለት ምልዓተ ጉባኤው ወስኗል፡፡
15. በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚኖሩ በግልና በቡድን ተደራጅተው ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመክፈት ከሃይማኖት ሥነ ምግባር በወጣ መልኩ የቤተ ክርስቲያናችንን ልዕልና የቅዱስ ሲኖዶስን ክብር የሚጋፋ ፣የአባቶችንና የአገልጋዮችን ተልእኮ የሚያደናቀፍ ያልተገባና መሠረት የሌለው መግለጫ የሚያሰራጩ አካላት እንዲታረሙ ቅዱስ ሲኖዶስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በጥብቅ ያሳስባል፡፡

በመጨረሻም በሀገራችን በአንዳንድ ቦታዎች የሚታየው ግጭትና መፈናቀል ተወግዶ፣የሰው ልጅ የመኖርና የመዘዋወር መብት ተከብሮ፣ ሰብዓዊ ክብሩ ተጠብቆ ሁሉም ዜጋ በእኩልነት፣ በሰላምና በፍቅር ተከባብሮ በጋራ እንዲኖር፤ አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ ቤተ ክርስቲያን የሰላም ጥሪዋን ታስተላልፋለች፡፡

ግጭት፣ ጥላቻና ደም መፋሰስ፣ አካል ከማጉደልና ንብረት ከማጥፋት በቀር የሚያመጡት ክብርና ዘላቂ ሰላም ስለሌለ ልጆቻችን ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ እንድትፈቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ደጋግሞ ጥሪውን በማቅረብ በመላው ዓለም ጦርነት ባለባቸው ሀገራት ሁሉ ሰላምና ዕርቅ እንዲሰፍን በመጸለይ ቅዱስ ሲኖዶስ ግንቦት 20 ቀን 2017 ዓ.ም ዓመታዊ ጉባኤውን በጸሎት አጠናቋል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ

                  አባ ማትያስ ቀዳማዊ
      ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ግንቦት ፳ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ

ምንጭ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
የግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዋድሮስ ዳግማዊ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ግብፅ ሀገር የገባበት በዓል ላይ 8 አዲስ ኤጲስ ቆጶሳትን ሾመዋል።

አዳዲሶቹ ኤጲስ ቆጶሳት በተለያዩ አህጉረ ስብከት እና በታላላቅ ገዳማት ኃላፊነት የተሾሙ ናቸው። ኤጲስ ቆጶሳቱ በቅርቡ ያረፉትን ብፁዓን ጳጳሳትን ሜትሮፖሊታን ጳኩሚስ፣ ኤጲስ ቆጶስ አግቢዮስን እና ኤጲስ ቆጶስ ሚካኤልን ክፍተትና ሌሎች ክፍተቶችን ለመሙላት የተደረገ መሆኑን ቅዱስነታቸው ተናግረዋል። በፓትርያርክ አቡነ ታዋድሮስ አንብሮተ ዕድ የተሾሙ መነኮሳት

1. አባ ገብርኤል አል-ማህራቂ  በኤጲስ ቆጶስ ጳኩሚስ ስም በአል-ቃላሊ ተራራ ኤልቃላሊ የእስክንድርያ የቅዱስ መቃርስ ገዳም ሊቀ ጳጳስ እና አበምኔት
2. አባ አንድራዎስ አል-ሶሪያኒ - ብፁዕ አቡነ ካራስ  ተብለው የማትሮው ሀገረ ስብከት እና የአምስቱ ምዕራባዊ ከተሞች ጳጳስ
3. አባ ቴዎፋን አቫ ሚና - ብፁዕ አቡነ ሚና ተብለው የቦርግ አል አረብ ሀገረ ስብከት ጳጳስ
4. አባ ዳንኤል አል-ጊዮርጊስ - ብፁዕ አቡነ ቦክተር ተብለው የዲርምዋስ እና ዴልጋ ሀገረ ስብከት ጳጳስ
5. አባ ዲስኮረስ አል-አንቱኒ - ብፁዕ አቡነ ዲስኮረስ ተብለው የደቡባዊ ጀርመን እና በክሮፍልባች የቅዱስ አንቶኒ ገዳም አበምኔትና ጳጳስ
6. አባ ኦሎጊዩስ አል-ባራሞሲ - ብፁዕ አቡነ ኦሎጊዩስ ተብለው በአይን ሻምስ፣ ማታሪያ እና ሄልሚት ኤል-ዘይቱን ላሉት አብያተ ክርስቲያናት ጳጳስ
7. አባ ያኮቦስ አንባ ቢሾይ - ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ ተብለው በሃዳቅ አል-ቁባ፣ አል-ዋይሊ፣ አባሲያ እና ማንሺየት አል-ሳድር ላሉት አብያተ ክርስቲያናት  ጳጳስ።
8. አባ ኢግናቲየስ አል-ሶሪያኒ - ብፁዕ አቡነ ኢግናቲየስ ተብለው የቄና ሀገረ ስብከት ጳጳስ እና የሜትሮፖሊታን ሻሮቢም ረዳት ጳጳስ ሆነው ተሹመዋል።

/ፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ሚድያና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ማስተባበሪያ ክፍል።/
@zemarian
የጎፋ መካነ ሕያዋን ሰንበት ት/ቤት ለመቄዶንያ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ አደረገ !

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የጎፋ መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል ሰንበት ት/ቤት በርቀት ከሚያስተምራቸው ተማሪዎች ያሰባሰበውን አንድ ሚሊየን አንድ መቶ ሰባ ሺህ ብር በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ቡራኬ ለመቄዶንያ መሥራች ለክቡር ዶክተር ብኒያም አስረክበዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከሚገኙ አገር በቀል  ተቋማት መካከል  በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሰው መቄዶኒያ  የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል  ከተቋቋመ ስምንት ዓመታትን  ባስቆጠረው በመቄዶኒያ ከ8,000 በላይ በተለያየ  ዕድሜ  ክልል  ውስጥ  የሚገኙ የተለያዩ ተረጂዎች ይገኙበታል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ባስተላለፉት አባታዊ መልእክት “መቄዶንያ ለተቸገሩ ሰዎች የሚረዳ ትልቅ ተቋም ነው፡፡ መንግሥትም የማይችለውን ነው መቄዶንያ የያዘው፤ ለዚህ ተቋም ርዳታ የሚያደርጉ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ትልቅ ዋጋ ያገኛሉ፡፡ ሀብታቸውም ይባረክላቸዋል፡፡ እስከ አሁንም ርዳታ ላደረጉት ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡” ብለዋል፡፡ ቅዱስነታቸው አያይዘውም “በሀገራችን በተለያዩ ምክንያቶች ችግረኞች እየተበራከቱ በመሆኑ፤ የጎፋ መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል ሰንበት ትምህርት ቤት በኩል ለመቄዶንያ የምትችሉትን ርዳታ በመርዳታችሁ በረከት ታገኛላችሁ፤ብዙ ዋጋ ያስገኝላችኋል፤ይሄ በጎ ሥራችሁ ለሁሉም አርአያ በመሆኑ እግዚአብሔር ይባርካችሁ” በማለት አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡  

የሰንበት ትምህርት ቤቱ ሰብሳቢ ቀሲስ ዮናስ ኢሳይያስ እንደገለጹት “የጎፋ መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል ሰንበት ት/ቤት ከ6‚500 ተማሪዎች ይገኛሉ፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤቱ መደበኛ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች አንዱ በርቀት ትምህርት ማስተማር ነው፡፡ በርቀት ትምህርት የሚማሩት በተሠማሩበት የሥራ ዘርፍ ክርስትናቸውን እንዲገልጹ ማድረግ” መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አያይዘውም “በቤተክርስቲያን ተቋማት በርካታ ወጣቶች ይገኛሉ፡፡ ቤተክርስቲያን ከመንፈሳዊ ትምህርቷ በተጓዳኝ በማኅበራዊ ጉዳይ ተሳታፊ እንዲሆኑ መቄዶንያ አረጋውያንን እንዲረዱ እያደረግን ነው፤ በዚህም መሠረት የሰንበት ትቤቱ የርቀት ትምህርት አስተባባሪዎች ተወካዮች ቅዱስነትዎ ጋር መጥተን ለመቄዶንያም የበኩላችንን አስተዋጽኦ እንድናደርግ አባታዊ በረከትዎን ለመቀበል መጥተናል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

“የካቴድራሉ አስተዳዳሪ መልአከ ፀሐይ አባ ኃይለ ኢየሱስ ተመስገን እንዳብራሩት “የሰንበት ትምህርት ቤቱ ወጣቶች በርካታ ሥራዎችን እየሠሩ እንደሚገኙ” ገልጸዋል፡፡ በሰንበት ትምህርት ቤቱ ባዘጋጀው የርቀት ትምህርት በርካታ ተማሪዎች ከተለያዩ ቦታዎች መጥተው ይማራሉ፡፡ ዶክተር ቢኒያም በሀገራችን ላይ በየመንገዱ ወድቀው የሚኖሩ ወገኖቻችንን እያነሡ የጀመሩት ራዕይ ተስፋፍቶ አሁን ፍሬ አፍርቷል፡፡ እኛም በበኩላችን ይህን ለምን አንደግፍም ብለን  ካቴድራሉ፣ሰንበት ት/ቤቱ በማስተባበር የገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል፤ቅዱስነትዎ ለዶክተር ቢኒያም እንዲሰጡልን” ነው የመጣነው ብለዋል፡፡

አረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማንን ከጎዳና በመሰብሰብ “ሰው ለመርዳት ሰው ብቻ መሆን በቂ ነው” የሚል መርህ አንግቦ ከተነሣ ዓመታት ያስቆጠረው መቄዶንያ፤ በእነዚህ ዓመታትም በርካታ አረጋውያንንና የአዕምሮ ሕሙማንን ከጎዳና ሕይወት መታደግ ችሏል፡፡ የተቋሙ መሥራች ክቡር ዶክተር ቢኒያም እንደገለጹት “መቄዶንያ ምንም ገቢ የለውም፡፡ በቀን ከ 2.5 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የሚያወጣ ማዕከከል ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት  በ46 ከተሞች ላይ ከጎዳና ሰዎች ተነሥተው እየተረዱ ይገኛሉ፡፡” ብለዋል፡፡  

“ዛሬ የአንድ ቤተክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት 1.2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ያደረገው ሌሎችም አብያተ ክርስቲያናትና ሰንበት ት/ቤቶች ተመሳሳይ ድጋፍ እንዲያደርጉ የሚያነሣሣ ነው፡፡ ሌሎችም ይህን አርአያ አድርገው ተመሳሳይ ድጋፍ እንዲያደርጉ ነው፡፡ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናትም የረዱን አሉ፤ ሌሎችም  ድጋፍ በማድረግ እንዲሳተፉ ቢያደርጉ፤ ድጋፍ የሚያደስፈልጋቸውን እነዚህ መርዳት ከእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ ስለሚያሰጥ ሁሉም ኅብረተሰብ እንዲሳተፍ ቅዱስነትዎ መመሪያ ለሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ቢያስተልላልፉልን” ብለዋል፡፡

©️ EOTCTV
2025/07/05 17:16:44
Back to Top
HTML Embed Code: