Telegram Web Link
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ባሏት ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች ላይ አጋር አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

ግንቦት ፴/፳፻፲፯ ዓ.ም

የቅድስተ ቤተ ክርስቲያን በርካታ አገልግሎት በሁለም ዘርፎች እንዲሰፋ፣እንዲጎለብት እና እንዲያድግ አቅም እና ገንዘብ ያላቸው ምእመናን  መሳተፍ እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡ 

የተለያዩ ገዳማት እና አብያተ ክርስቲያናት ለሚያስፍልጋቸው ድጋፍ እገዛ በማድረግ እና በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ማስፋፋት ረገድ በግልም ሆነ በኮሚቴ አቅም እና ገንዘብ ካላቸው ባለሀብት ጋር አብረው እየሠሩ መሆናቸውን በግል የሥራ ዘርፍ የተሰማሩት ወ/ሮ ሜሮን ታደለ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በግለሰብ ደረጃ ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመለሱ በማድረግ፣በክረምት ወቅት ለሕጻናት፣ለአዳጊዎች  እና ለወላጆች የተለያዩ መንፈሳዊ ሥልጠናዎችን በመስጠት እንዲሁም ከተቋማት ጋር በመተባበር  በሴቶች እና በሕጻናት ላይ ሥራችዎን እየሠሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

ወ/ሮ ሜሮን አክለውም ከባለሀብቶች በተጨማሪ ሌሎች ምእመናን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ያላቸውን ጊዜ እና ገንዘብ እንዲያበረክቱ ከማድረግ በፊት ራሳቸውን እንዲሰጡ ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

አሁን ያለው የተለያዩ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዲሰፋ  የምእመናንን ጎዶሏቸውን ማገዝ እንዲሁም መሳተፍ የሚችሉበትን ዕድል እና ሁኔታ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ወ/ሮ ሜሮን አያይዘው አንስተዋል፡፡

ትንሽ በመስጠት ብዙ ለማትረፍ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ባሏት ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች ላይ ባለሀብቶች በመሳተፍ ኀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባቸው መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ለወጣቶች የሱስ ማገገሚያ ተቋም ለማቋቋም የሚያስችል ጥናታዊ የምክክር ጉባኤ አካሄደ

ግንቦት ፴/፳፻፲፯ ዓ.ም

"ማኅበራዊ ቀውስን በማከም ትውልድን እንታደግ"  በሚል መሪ ቃል ግንቦት 30 ቀን 2017 ዓ.ም በተካሄደው ጉባኤ በማኅበረ ቅዱሳን ሙያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት  ከባለድርሻዎች ጋር ሰፊ ጥናታዊ ሰነድን መነሻ ያደረገ ምክክር ተደርጓል።

በአሁኑ ወቅትም በአገራችን ኢትዮጵያ 46 ከመቶ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ለሱስ (በአልኮል፣ ጫት ወይም የሲጋራ) ተጠቂ ሁነዋል ተብሏል። በተመሳሳይ የንጥረ ነገርም ይሁን የባሕሪ ሱስ የተጋላጮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ስለመሆኑ ተነግሯል።

በዳሰሳ ጥናቱ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች በንጥረ ነገር ሱስ ከመጠቃታቸው ባሻገር ሲሶ የሚሆኑት የኢንተርኔት ሱስ ተጠቂ ናቸው ተብሏል። ይህም ብቻ ያይደለ በጥናቱ  የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎቹም ማኅበራዊ የመገናኛ አውታር መጠቀም የማይችሉበት አጋጣሚ ከተፈጠረ ጭንቀት እንደሚፈጥርባቸው አምነዋል ተብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በጥናቱ 52 ከመቶ ገደማ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በተለያዩ የሱስ አምጭ ንጥረ ነገሮች አማካኝነት የሱስ ተጠቂ ሁነው መገኘታቸው የተገለጸ ሲሆን  ከቤተክርስቲያናችን ምእመናን ውስጥ 50 ከመቶ ገደማ የሚሆኑትም ለተለያዩ ሱሶች ተገዢ መሆናቸው ተጠቅሷል።

በማያያዝም ምእመናን በሱስ ምክንያት የቤተክርስቲያንን ሥርዓት ለመፈጸም እንደሚቸገሩ ነው የተነሳ ሲሆን ቁጥር ልክ የሱሰኛ ወገኖቻችን ቁጥር መጨመሩ ለአገራችን እና ለቤተክርስቲያናችን እጅግ አሳሳቢ ነው ተብሏል።
የንጥረ ነገርም ይሁን የባሕሪ ሱስ ተጠቂ የሆኑ ግለሰቦች የአካልና የአእምሮ ጤናቸው ከመታወኩ ባለፈ ሱሰኝነት በማኅበራዊ ሕይወት ፤ በሰላም እና ደህንነት ብሎም በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳርፈው ጠባሳም ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ተመላክቷል።

ታዲያ ለቤተክርስቲያናችን ብሎም በአገር ደረጃ አሳሳቢ ለሆነው ሱሰኝነት በጊዜ መፍትሔ ማስቀመጡ አግባብነት ያለው ተግባር መሆኑ ነው በምክክር መርሐ ግብሩ የተነገረው።

ማኅበረ ቅዱሳንም በሙያ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት በኩል ለችግሩ መፍትሔ ብሎ ያስቀመጠው ቤተክርስቲያናችን ባሏት ገዳማትና አድባራት "የሱስ ማገገሚያ ማእከል" ማቋቋምን ሲሆን ለምክረ ሐሳቡ ተግባራዊነት ደግሞ ለእያንዳንዱ ሱስ የሚያስፈልገው የማገገሚያ ዓይነትና ተቋም የሚለያይ በመሆኑ ለሁሉም የሱስ ዓይነቶች ማገገሚያ ተቋም በአንድ ላይ እንዲሁም በተናጠል ማቋቋም በርከት ያለ ገንዘብ፣ ጊዜ፣ የሰው ኃይል ማሰናዳት ያስፈልጋል ተብሏል።


በቀጣይ ጊዜም ይህን ሥራ ወደ ተግባራዊ መፍትሔ ለመቀየር የሚቻልበት ዝርዝር መፍትሔዎችን ወደ ተግባር የሚቀየር ግብረ  ኃይል በማቋቋም ጉባኤው ፍጻሜውን አግኝቷል ተብሏል።
በ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ለሚፈተኑ ተማሪዎች የሥነ ልቦና ዝግጅት ሥልጠና መሰጠቱን ጅማ ማእከል አስታወቀ።

ሰኔ ፩/፳፻፲፯ ዓ.ም

በጅማ ከተማ ከሚገኙ ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች ለመጡ ከ150 በላይ ለሚሆኑ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ማኀበረ ቅዱሳን ጅማ ማእከል እና የጅማ ሀገረ ስብከት ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት  በጋራ በመሆን በ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ለሚፈተኑ ተማሪዎች ግንቦት 30 ቀን 2017 ዓ.ም የሥነ ልቡና ዝግጅት ሥልጠና እና የማኅበር ጸሎት መርሐ ግብር በሀገረ ስብከት አዳራሽ አካሂደዋል።

በመርሐ ግብሩ ለብሔራዊ ፈተና ዝግጅት የማኅበር ጸሎት ተደርጓል።

ሥልጠናው የ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በትምህርት ሚኒስቴር የሚሰጠውን የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ተማሪዎች በቀሪ ጊዜያቸው በስነልቦና ዝግጁ እንዲሆኑ ያለመ ነው ተብሏል።

በተጨማርም በ25/09/2017 ዓ.ም ተመሳሳይ ወይም ይሄዉ ሥልጠና በተስፋ ተዋህዶ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሚማሩ  ከ50 በላይ ለሚሆኑ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በትምህርት ቤቱ ላይብረሪ አዳራሽ ተሰጥቷል።

በዕለቱ የሥልጠና ሂደቱ እንዲሳካ የት/ቤቱ ርዕሰ መምህር መ/ር አማረ እና መምህራን ላደረጉት ትብብር ምሥጋናችን የላቀ ነው።

በመጨረሻም ተማሪዎቹ ከሥልጠናው በቂ ግንዛቤ እንዳገኙና ታስቦ ይህ ሥልጠና መዘጋጀቱ አበረታች እንደሆነ አሰተያየታቸውን ሰጥተዋል።
"ያለንበት ወቅት ከምንም በላይ የእውነተኛ እረኝነት ሐዋርያዊ ሕይወት የሚያሻበት፤ ቤተ ክርስቲያንንም እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት የመምራት ጥበብ በእጅጉ የሚያስፈልግበት ጊዜ ነው። “ ብፁዕ አቡነ ሄኖክ

ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የደቡብ አፍሪካና ምዕራብ አፍሪካ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጾመ ሐዋርያትን አስመልክቶ መልእክት አስተላልፈዋል፤ የብፁዕነታቸው መልእክት ከዚህ እንደሚከተለው ይቀርባል።

"ወሰበኩ ከመ ይጹሙ ጾመ ቅድመ እግዚአብሔር፤ በእግዚአብሔር ፊት ጾም ዐወጁ።" ኤር ፴፮፥፱

በቸርነቱ ብዛት ኃጢአታችንን ይቅር ያለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለ፳፻፲፯ ዓ.ም ጾመ ሐዋርያት በሰላምና በጤና አደረሰን አደረሳችሁ።

ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን በተቀበሉ ማግስት ወደ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸው ከመሰማራታቸው አስቀድሞ በጾምና በጸሎት ተወስነው መቆየታቸውን ቅድስት ቤተ ክርስቱያን ታስተምረናለች።

በዚህ በጾመ ሐዋርያት ወቅት የእውነተኛ ሐዋርያዊነት እና አገልጋይነት መሠረቱ ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ በማስገዛት ክርስቶሳዊ በሆነ አካሄድ አገልግሎትን ለመጀመር መታመን መሆኑን የምንረዳበት ነው።

ተወዳጆች ሆይ !

ያለንበት ወቅት ከምንም በላይ የእውነተኛ እረኝነት ሐዋርያዊ ሕይወት የሚያሻበት፤ ቤተ ክርስቲያንንም እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት የመምራት ጥበብ በእጅጉ የሚያስፈልግበት ጊዜ ነው። (ሐዋ ፳፥፳፰)

የሐዋርያት ሕይወት ስለ ክርስትናቸው የተቀበሉትን መከራ ብቻ ሳይሆን ከመንፈሳዊ አገልግሎት የሚገኝ ደስታን ለማግኘት መጓዝ የሚገባንን መንገድ የሚያስተምር ነው፤ ለዚህ ነው በመንፈሳዊ አገልግሎታችን ደስተኞች ሆነን የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን ለማገልገል መነሻችን ሊሆን የሚገባው እውነተኛ ክርስቲያንነት እና የክርስትናን ሕግጋት በሕይወት መኖር መሆኑን አበው የሚያስተምሩት።

በምንጾምበት ጊዜም ከጾሙ የምናገኘው በረከት የእግዚአብሔርን በጎ ምላሽ መሆኑን በማመን በልዩ ልዩ መንገዶች ቤተ ክርስቲያናችን ላይ የተጋረጡ የሚመስሉን ችግሮች ከእግዚአብሔር ሁሉን አዋቂነት እና ሁሉን ቻይነት የማይሰወሩ አንዳቸውም መከራን እንድንቀበል ከማድረግ በቀር ቤተ ክርስቲያንን አሸንፈው ሊወጡ የማይቻላቸው ነገሮች መሆናቸውን መረዳት ይገባል።

በመጨረሻም :- በዚህ የጾም ወቅት በእግዚአብሔር ፊት በምናቀርበው ጸሎትና ልመና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንን በማሰብ በምንሰማራበት ሁሉ አገልግሎታችን ያማረና ለእግዚአብሔር የተመቸ መሆን እንዲችል አብዝተን ልንማጸን ይገባል።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ
+ አባ ሄኖክ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንየደቡብና ምዕራብ አፍሪካ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
ሰኔ ፩ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም
2025/07/13 15:13:27
Back to Top
HTML Embed Code: