Telegram Web Link
ኢራን የተኩስ አቁም ስምምነቱን በመጣሷ ከባድ ምላሽ ይጠብቃታል ስትል እስራኤል ዛተች

የእስራኤል መከላከያ ሚንስትር ኢዝራኤል ካትስ ባወጡት የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት "ኢራን የተኩስ አቁምን በመጣሷ በቴህራን እምብርት ላይ ባሉ የአገዛዙ ኢላማዎች ላይ ከፍተኛ ጥቃት በመሰንዘር በሀይል ምላሽ እንዲሰጥ" ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጥቃት የሚያቆመዉ እስራኤል ተመሳሳይ እርምጃ ከወሰደብ ብቻ እንደሆነ ቀደም ብሎ ተናግሯል።የእስራኤል ጦር ከኢራን የተወነጨፉ ሚሳኤሎችን ለይቻለሁ ሲል በዛሬዉ እለት አስታዉቋል፡፡የአየር መከላከያ ዘዴዎች ስጋቱን ለመጥለፍ እየሰሩ ሲሆን ሰዎች ወደ መጠለያ ገብተው እንዲቆዩ እየነገራቸው ይገኛል፡፡

የእስራኤል መከላከያ ሃይል (አይዲኤፍ) ዋና አዛዥ ወታደራዊው ኃይላችን ለኢራን ድርጊት "ከባድ ጥሰት" በማለት "የኃይል ምላሽ ይሰጣል" ብለዋል፡፡ኢያል ዛሚር እንደተናገሩት "በኢራን መንግስት የተካሄደውን የተኩስ አቁም ከፍተኛ ጥሰት ተከትሎ በኃይል ምላሽ እንሰጣለን" ሲሉ በኤክስ ገጻቸዉ ላይ ባወጡት መግለጫ ገልጸዋል፡፡

የኢራን መንግስት ሚዲያ ከተኩስ አቁም በኋላ በእስራኤል ላይ ሚሳኤል ተኮሰች የሚለውን ውንጀላ አስተባብሏል።የኢራን ታጣቂ ሃይሎች ለጠላት ጭካኔ አሳፋሪ እና አርአያነት ያለው ምላሽ መስጠቷን የገለጸችዉ ኢራን ትላንት ምሽት በኳታር በሚገኘው የአሜሪካ ጦር ሰፈር ላይ በደረሰው ጥቃት እና ጎህ ሲቀድ እስራኤል በሚሳኤል መመታቷን አስታዉቃለች፡፡የኢራን ከፍተኛ ብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ቴህራን በግዛቷ ላይ ለደረሰው ጥቃት ተመጣጣኝ እና በጊዜ ምላሽ ሰጥታለች ያለ ሲሆን "ጠላትን በግዳጅ እንዲጸጸት እና ሽንፈትን እንዲቀበል አድርጓል" ብሏል።

በስምኦን ደረጄ
#ዳጉ_ጆርናል
ከፍቼ አዲስአበባ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች በነዳጅ እጦት ምክንያት ስራ ለማቆም ተገደናል ሲሉ ቅሬታቸውን አቀረቡ

ከፍቼ አዲስ አበባ የህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች በነዳጅ እጦት ምክንያት አገልግሎት ሊያቆሙ በመገደዳቸው ተገልጋዮች ለእንግልት መዳረጋቸውን ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።

በዚህም የትራንስፖርት ተጠቃሚው ማህበረሰብ ለእንግልት መዳረጉን ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል። አሽከርካሪዎች በበኩላቸው ትላንት  ነዳጅ ለመቅዳት ቢሞክሩም  ማደያ ላይ አልቋል የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸው በዚህም መንቀሳቀስ አለመቻላቸውን ገልጸዋል። የተወሰኑ አሽከርካሪዎች   ከህገወጥ የነዳጅ ቸርቻሪዎች ላይ አንድ ሊትር ናፍጣ በሁለት መቶ ብር ገዝተው ወደ ስራ መሰማራታቸው ብስራት ሰምቷል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ንግድ ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ደረጀ ሰማ እንደገለጹት የነዳጅ እጥረቱ በዋነኛነት በሀምሌ ወር ይጨምራል በሚል ስጋት አንዳንድ ማደያዎች ከህግ  ውጪ ነዳጅን ለተሽከርካሪዎች በጄሪካን በመሸጥ እንዲሁም ትስስር ላላቸው ነጋዴዎች በመሸጥ የነዳጅ እጥረቱ እንዲከሰት አድርገዋል ። ለዚህም በዋነኛነት፣ አንዳንድ የአስተዳደር ፣ የፀጥታ አካላት የንግዱ ማህበረሰብ እና የትላልቅ ማሽነሪ ተሽከርካሪ ባለቤቶች ከማደያዎች ጋር ያላቸው የጥቅም ትስስር ለነዳጅ እጥረቱ በር መክፈቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም  በዞኑ ካሉት አስራ አንድ ማደያዎች መካከል በገብረ ጉራቻ፣ ሙከጡሪ ፣ጫንጮ  አሌልቱ መናሃሪያዎች ላይ ቅጣት መጣሉን  በመጥቀስ በተለይ የሙከጡሪ ማደያ ተደጋጋሚ የህግ ጥሰት በመፈፀሙ አስተማሪ ቅጣት እንደሚጠብቀው ነግረውናል።

በነዳጅ እጥረት ምክንያት በትራንስፖርት ዋጋ ላይ ጭማሪ ያደረጉ ህገወጥ  አሽከርካሪዎች ላይ አስተማሪ ቅጣት በመስጠት ከማደያ ጣቢያ ያለውን ነዳጅ በተገቢው በማካፈል የትንራንስፖርቱን ፍሰት ማስተካከል መቻሉን ብስራት ሬዲዮ ሰምቷል።በሀገወጥ የነዳጅ ግብይት የተሰማሩ ስድስት ነጋዴዎችም ያጠራቀሙት  ነዳጅ ውርስ ሆኖ ለተጠቃሚዎች እንደሚከፋፈል ተነግሯል።

በኤደን ሽመልስ
#ዳጉ_ጆርናል
አዳማ ከተማ ከፕሪሚየር ሊጉ ወረደ

በ36ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር አዳማ ከተማ በሀዋሳ ከተማ ተሸንፎ ከፕሪሚየር ሊጉ ወርዷል፡፡

ዛሬ 9፡00 ላይ የተደረገው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በሀዋሳ ከተማ 2 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

የሀዋሳ ከተማን ግቦች አቤኔዘር ዮሐንስ እና በረከት ሳሙኤል ሲያስቆጥሩ፥ አዳማ ከተማን ከሽንፈት ያልታደገችውን ግብ ቢኒያም አይተን ከመረብ አሳርፏል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ በ39 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው አዳማ ከተማ፥ ስሑል ሽረ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን ተከትሎ ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዱ ተረጋግጧል፡፡

በሊጉ የመሰንበት እድሉን በራሱ ለመወሰን አንድ ነጥብ ብቻ የሚፈልገው ፋሲል ከነማ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ሲዳማ ቡናን ይገጥማል፡፡

#ዳጉ_ጆርናል
የቱሉቦሎ - ኬላ አስፋልት መንገድ ፕሮጀክት ተጠናቀቀ

የኦሮሚያ እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎችን የሚያገናኘው የቱሉቦሎ - ኬላ አስፋልት መንገድ ፕሮጀክት ግንባታው ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን ተከትሎ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።

የመንገድ ፕሮጀክቱ 80 ኪሎሜትር የሸፈነ ሲኾን፥ በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ ነው የተገነባው። የመንገድ ግንባታውን የቻይናው ዓለም-አቀፍ የሥራ ተቋራጭ ሁናን ሁንዳ ሮድ ኤንድ ብሪጅ ኮርፖሬሽን አከናውኖታል።

ሀገር በቀሉ የተባበሩት የምህንድስና አማካሪዎች የግንባታውን ጥራት በመቆጣጠር እና በማማከር በኩል ተሳትፏል። ለፕሮጀክቱ የዋለው 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ወጪ ሙሉ በሙሉ በፌደራል መንግስት ተሸፍኗል።

በመንገድ ፕሮጀክቱ ሦስት ድልድዮችን ጨምሮ አነስተኛ፣ ከፍተኛ ፍሳሽ ማስተላለፊያዎች፣ ቱቦዎች እና ከልቨርቶች ግንባታም ተካትቷል። መንገዱ በገጠር የመንገድ ትከሻን ጨምሮ 10 ሜትር፣ በወረዳ 20 ሜትር እንዲሁም በቀበሌ 15 ሜትር የጎን ስፋት አለው።

የመንገዱ መጠናቀቅ የአዲስ አበባ-ቡታጅራ -ሆሳዕና እና የአዲስ አበባ - ወልቂጤ - ጅማ መስመር  ያሉትን አውራ መንገዶች ያገናኛል፡፡ ይህም ከዚህ ቀደም ይደረግ የነበረውን ዙሪያ ጥምጥም ጉዞ በማስቀረት የጉዞ ጊዜን ያሳጥራል።

የተቀላጠፈ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዲኖር በማስቻል፣ የማኅበራዊ ተቋማት ተደራሽነትን በማስፋት እንዲሁም የገበያ ትስስሩን በማጠናከር የመንገዱ መገንባት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረክታል።

የቱሉቦሎ፣ ሀርቡጩሉሌ፣ ኮምበል፣ አጨበር፣ ቀሽት እና ኬላን ጨምሮ ሌሎች በርካታ አካባቢዎችን በቅርበት ያገናኛል።

#ዳጉ_ጆርናል
አርኤስኤፍ ከግብፅ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማስተካከል የውይይት ጥሪ አቀረበ

የሱዳን ፓራሚሊተሪ ፈጣን ድጋፍ ሰጭ ሃይል መሪ መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ ከግብፅ ጋር ያሉ አለመግባባቶችን በውይይት መፍታት እንደሚፈልጉ ገልፀዋል። ዳጋሎ በሰፊው በዳርፉር ክልል ለወታደሮቹ ባደረገው ንግግር ከጎረቤት የግብፅ ሃይል ጋር ያለውን ውጥረት አስመልክቶ ተናግረዋል።  ቀደም ሲል ግብፅን ለሱዳን ጦር ኃይሎች ወታደራዊ ዕርዳታ ታቀርባለች በሚል የሰላ ትችት ሰንዝረዉ እንደነበርም ይታወቃል።

"ግብፅንና ሌሎች ጎረቤቶቻችንን እናከብራለን እናም ማንኛውም ችግር በውይይት እና በውይይት ሊፈታ ይችላል" ሲሉ ሄሜቲ በንግግራቸዉ የተደመጡ ሲሆን አርኤስኤፍ በአቅራቢያ ካሉ አገሮች ጋር ያለውን ግንኙነት ለማበላሸት በመሞከር ስማቸው ያልተጠቀሱ “ወንጀለኞችን” ከሰዋል።በሱዳን፣ በሊቢያ እና በግብፅ መካከል የሚገኘውን የኦዋይናት የድንበር ትሪያንግልን በቅርቡ የያዘው አርኤስኤፍ ቀጣናውን ከሽብርተኝነት፣ በኮንትሮባንድ እና በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ለመከላከል እንሰራለንም ሲሉ ዳጋሎ ተናግረዋል።

አክለውም "ፈጣን ድጋፍ ሰጭ ሃይሎች ከጎረቤት ሀገር ጋር ምንም ችግር የለባቸውም" ብለዋል።የአርኤስኤፍ እና የሱዳን ጦር ኃይላቸውን ለማዋሃድ ባወጡት እቅድ ምክንያት የገዢነት አጋርነታቸው ከፈራረሰ በኋላ ከሁለት አመት በላይ ሲዋጉ ቆይተዋል። ግጭቱም ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ ፈጥሮ ሚሊዮኖችን አፈናቅሏል።ዳጋሎ በንግግራቸው በዳርፉር የእርዳታ አቅርቦትን ለማመቻቸት ቃል የገቡ ሲሆን ከሚያዝያ 15 ቀን 2023 ጀምሮ ለወታደሮቻቸው ዕዳ መልሰው እንደሚከፍሉም ተናግረዋል።

በሠራዊቱ ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት በማደስ እና የተቀሩትን ሃይሎች እንደሚያሸንፉ ቃል የገቡት ጀነራሉ ከጦር ኃይሉ ጋር ለተባበሩ ሌሎች የታጠቁ አንጃ መሪዎችም የእርቅ ጥሩ አቅርበዋል። የሱዳን ነፃ አውጪ ንቅናቄ እና የፍትህ እና የእኩልነት ንቅናቄ መሪዎችን በመጥቀስ "ከሚኒ (አርኮ ሚናዊ) እና ከጅብሪል (ኢብራሂም) ጋር ምንም ችግር የለንም ዛሬ ወደ እኛ ቢመጡ እንኳን ደህና መጣችሁ ብለን እንቀበላቸው አለን ሲሉም ተደምጠዋል።

በሚሊዮን ሙሴ
#ዳጉ_ጆርናል
በመቱ ከተማ ወድቆ ያገኙትን ከ173 ሺህ ብር በላይ ለፖሊስ ያስረከቡ ጓደኛማቾች ምስጋና ተቸራቸው

በኢሊባቡር ዞን መቱ ከተማ ነዋሪ የሆኑ ሁለት ጎረቤታም ሴቶች ወደ ገበያ ሲያመሩ መሬት ላይ የወደቀ ጥቁር ፌስታል አይተው ገንዘብ መሆኑን ሲገነዘቡ ለፖሊስ ማስረከባቸውን የመቱ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ገልጿል ።

የመቱ ከተማ ፖሊስ ዋና መምርያ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ኃላፊ ረዳት ኢንስፔክተር አሸብር ጌታሁን ለብስራት ሬዲዮ እንደተናገሩት ወይዘሮ የሺህ ሀረግ ይርጉ እና ወይዘሮ አገርቱ ዴቢሳ የተባሉ የመቱ ከተማ አባ አሳያ ቀበሌ ማርያም ሰፈር ነዋሪ ናቸው።

ሰኔ 16 ቀን 2017 ዓ.ም የሰኞ ገበያ ዕቃ ለመግዛት በመውበት ይህ አጋጣሚ ተከስቷል። ጎረቤታሞቹ የግል ጥቅም እና ፍላጎት ሳያሸንፋቸው በቀጥታ በጥቁር ፌስታል የተጠቀለለውን 173 ሺህ ብር ከሀምሳ ሳንቲም ለመቱ ከተማ ፖሊስ አስረክበዋል።

ሁለቱ ሴቶች በታማኝነት ብሩን እንዳስረከቡ የብሩ ባለቤት አቶ ሰሚር ሙሰማ የተባሉና በመቱ ከተማ አባ አሳያ ቀበሌ ማርያም ሰፈር ነዋሪ የዳቦ መጋገርያ ቤት ባለቤት ከሰዓታት ቆይታ በኋላ በመምጣት ሁለቱ ሴቶች መሬት ላይ ወድቆ ያገኙት ብር የራሰቸው መሆኑን ያመለክታሉ።

ፖሊስም ሁለቱ ሴቶች ያገኙት ብር የአቶ ሰሚር ስለመሆኑ ባደረገው ማጣራት ዱቄት ገዝተው ለመመልስ ወደ ሱቅ መደብር መጓዛቸውን ከዚያም ከቤት ይዘውት የወጡትን ብር ሲያፈላልጉ መገኘቱን በመስማታቸው ወዲያው ወደ ፖሊስ ፅ/ቤት መቅረባቸውን ባቀረቡት ማስረጃ ማረጋገጡን  ገልፀዋል።

ብሩ ምንም ሳይጎድል እንዲያገኙ ላደረጉላቸው ሁለት ሴቶች ትልቅ ምስጋና አቅርበው ለዚህ ታማኝነት ተግባር ወሮታ ከፋይነኝ ሲሉ መግለጻቸውን ረዳት ኢንስፔክተር አሽብር ጌታሁን ለብስራት ሬዲዮ ገልፀዋል።

በኤደን ሽመልስ
#ዳጉ_ጆርናል
የድሬዳዋ ምድር ባቡር ግቢን የቱሪስት መዳረሻ ስፍራ ለማድረግ እየተሰራ ነዉ ተባለ 

የድሬዳዋ የምድር ባቡር ተርሚናል እድሳት ከኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን በተመደበለት በጀት ጥገና ተደርጎለት ከሁለት ወራት በፊት መጠናቀቁን የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት አስታዉቋል ።

ቅርሱ እድሳት የተከናወነለት ታሪካዊ ይዘቱን ሳይለቅ ሲሆን ሙሉ ለሙሉ ዉድመት ደርሶባቸዉ ለነበሩ መስኮቶችም ተመሳሳይ ቁሳቁሶችን በመጠቀም ወደነበረበት የመመለስ ስራ መከናወኑም ተገልጿል ።

በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት የቅርስ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ አብረሃም ያረጋል ለብስራት ሬዲዮ እንደተናገሩት የድሬዳዋ ምድር ባቡር ምድረ ግቢን የቱሪስት መዳረሻ ስፍራ ለማድረግ በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን በተመደበ በጀት በአማካሪ ድርጅት የሰነድ ዝግጅት ለማካሄድ በጨረታ ላይ የሚገኝ ሲሆን ሂደቱ በቅርቡ ተጠናቆ የሰነድ ዝግጅት ይከናወናል ።

በምድር ባቡር ግቢ ውስጥ የሚገኝ የባቡር ፉርጎን ጥቅም ላይ በማዋል የከተማዋን ባህል የሚገልፁ እና ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ እንደ ፈጣን ምግብ ያሉ አገልግሎቶችን ለማቅረብ ፕሮጀክት በመቅረፅ ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር የዲዛይን ስራ እንደሚከናወን ተገልጿል ። ይህም የኮሪደር ልማቱን ባማከለ መልኩ የሚከናወን መሆኑን የገለፁት አስተባባሪዉ ይህንን የባቡር ፉርጎ በመጠቀም የሚሰጠዉን አገልግሎት በድሬዳዋ ከተማ ለገሀር አደባባይ አከባቢ ለመገንባት መታቀዱን አክለዋል ።

በመባ ወርቅነህ
#ዳጉ_ጆርናል
እስራኤል በጋዛ በፈፀመችው ጥቃት ቢያንስ 43 ፍልስጤማውያንን ተገደሉ

በጋዛ በተስፋፋው ረሃብ ውስጥ ቢያንስ 43 አጥብቀው የምግብ እርዳታ የሚሹ ፍልስጤማውያን በማእከላዊ የጋዋ ግዛት አካባቢ በተፈጸመ ጥቃት ተገድለዋል ሲል የአልጀዚራ የእውነታ ማረጋገጫ ክፍል ሳናድ ዘግቧል።

እንደ ዘገባው ከሆነ ተጎጂዎቹ የተገደሉት ከዋዲ ጋዛ በስተደቡብ በሚገኘው የሳላህ አል-ዲን ጎዳና ላይ ምግብ በመጠባበቅ ላይ በነበሩበት ወቅት ነው።

በሳናድ የተገኘ የምስል ቅጅ የተጎጂዎች አስከሬን በጋዛ ናስር ሜዲካል ኮምፕሌክስ እና በአል-አውዳ ሆስፒታል ተከማችቶ ያሳያል። በእስራኤል እና በአሜሪካ የሚደገፈው የጋዛ የሰብዓዊ ፋውንዴሽን እ.ኤ.አ ግንቦት 27 ቀን እርዳታ ማከፋፈሉን ከጀመረ ወዲህ እስራኤል የእርዳታ ማዕከላት አቅራቢያ ፍልስጤማውያን ላይ ባደረሰችው ጥቃት ከ400 በላይ ሰዎችን ሲገደሉ 1,000 የሚያህሉ ቆስለዋልም ተብሏል።

በሚሊዮን ሙሴ
#ዳጉ_ጆርናል
በኢትዮጵያ ህገወጥ የእንስሳት ዝውውርን ማስቆም አልተቻለም ተባለ

ኢትዮጵያ የዱር እንስሳትና የእፅዋት ሀብት ያላት ሀገር ብትሆንም ይህ ሀብቷ ግን በበርካታ ችግሮች ውስጥ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል።በባለስልጣኑ የዱር እንስሳት ህገወጥ ዝውውር ቁጥጥር ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ዳንኤል ጳውሎስ ለብስራት ሬድዮ እንደተናገሩት የዱር እንስሳትና የእፅዋት ሀብትን ለመጠበቅ በመጠለያና ፓርኮች አካባቢ የቁጥጥር ስራን የሚሰሩ ሰራተኞች ጥቃት እንዳይፈፀም የሚያስችል ስራን ያከናውናሉ።

ነገር ግን በእነዚህ ስፍራዎች ከህገወጥ ሰፈራ አንስቶ ህገወጥ የአደን ተግባራት ጭምር ይስተዋላሉ። እነዚህ ሁሉ በተፈጥሮ ሀብቱ ላይ ከተደቀኑ ችግሮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው ያሉት አቶ ዳንኤል የዱር እንስሳት ከነ ህይወታቸው ጭምር እየተያዙ በህገወጥ መልኩ ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ እንደዚሁም ከሀገር አልፈው ወደ ውጪ የሚዘዋወሩበት ሁኔታ መኖሩን ገልፀዋል።እንስሳቱ ለምግብነት፣ለጌጣጌጥ መስሪያነትና ለሌሎች አላማዎች በሚል በህገወጥ መልኩ እንደሚዘዋወሩ  አቶ ዳንኤል ጨምረው ለጣቢያችን ተናግረዋል።

የዱር እንስሳትን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ተገቢውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማግኘት የቁጥጥር ስራዎች መጠናከር እንደሚገባቸው ተገልጿል።ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በህገ ወጥ የዱር እንስሳት ውጤቶቻቸው ዝውውር እና ቁጥጥር ዙሪያ ለሚመለከታቸው አካላት ስልጠና መስጠቱን አስታውቋል።ለአምስት ቀናት በቆየው ስልጠና የዱር እንስሳት ውጤቶቻቸው ዝውውርን ለመከላከል የሚያስችሉ ሰነዶች የቀረቡ ሲሆን ሰልጣኞች ከህገወጦች የሚያዙ የዱር እንስሳት ውጤቶችን መለየት የሚያስችል የተግባር ላይ ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል።

በተጨማሪም በቦሌ አለም አቀፍ ኤርፖርት ላይ የሚገኙትን የአነፍናፊ ውሾች የፍተሻ ተግባር የሚያከናውኑበትን ሁኔታ መጎብኘት ችለዋል።

ቅድስት ደጀኔ
#ዳጉ_ጆርናል
በአሜሪካ የጦር ሰፈር ላይ የተፈጸመዉ ጥቃት ከኳታር ጋር ምንም ግንኙነት የለውም ስትል ኢራን ተናገረች

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሰኞ በአሜሪካ በሚመራው አል ኡዴይድ ወታደራዊ ጦር ሰፈር ላይ የተፈጸመው ጥቃት ከኳታር ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ተናግረዋል ።መሰረቱ በኳታር ነው፣ ያሉት ባካይ ግን የኢራን ድርጊት "ራስን የመከላከል ተግባር" ነው ብሏል።"ኢራን የኳታርን ግዛት እና ሌሎች ጎረቤት ሀገራትን በተመለከተ ለመልካም ጉርብትና ፖሊሲዋ ሙሉ በሙሉ ቁርጠኛ ነች" ሲሉ ባካይ በኤክስ ላይ አጋርተዋል።

የአሜሪካ እና እስራኤላውያን የወንጀል ጥቃቶች በኢራን ላይ የተሳሳቱ ፖሊሲዎች በእኛ እና በቀጠናው ወንድማማች አገሮች መካከል መለያየት እንዳይፈጥሩ ወስነናል ያሉት የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኳታር በአካባቢው ያለውን መባባስ ለመከላከል ስላደረገችዉ ምስጋናቸውን ገልጿል።የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማጂድ ታክት-ራቫንቺ  እና የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሐመድ ቢን አብዱላዚዝ አል-ኩላይፊን ለአገራቸው ስላደረገችዉ "ገንቢ ሚና" አመስግነዋል::

ታክት ራቫንቺ ኢራን "በመልካም ጉርብትና እና ከፍተኛ ጥቅም ላይ የተመሰረተ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለመቀጠል እና ለማጠናከር ቆርጣለች" ሲሉ ተናግረዋል።ኢራን በኳታር አል ኡዴይድ በሚገኘው የአሜሪካ ጦር ሰፈር ላይ በኒውክሌር ተቋሞቿ ላይ ላደረሰችው ጥቃት አጸፋ የተኩስ ሚሳኤሎችን መተኮሷ ይታወሳል። በምላሹ ኳታር ድርጊቱን አጥብቆ በማውገዝ የኢራን አምባሳደርን አስጠርታለች፡፡

በስምኦን ደረጄ
#ዳጉ_ጆርናል
ትራምፕ የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር አልጠፋም በሚል ሾልኮ የወጣውን የደህንነት መረጃ ውድቅ አደረጉ

ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ በኢራን ላይ ባደረሰችው ጥቃት ዙሪያ ሾልኮ ስለወጣው መረጃ ምላሽ ሰጥተዋል። የግል ንብረታቸው በሆነው ትሩዝ ሶሻል ላይ ባጋሩት መረጃ፣ ትራምፕ የአሜሪካን ሚዲያ እና ዘገባዎቻቸውን ነቅፈዋል። የሐሰት ዜና ሲ ኤን ኤን እና ከወደቀው ኒውዮርክ ታይምስ ጋር ተጣምረው አጋርተዋል ብለዋል። በኢራን ውስጥ ያሉ እጅግ በጣም አስፈላጊ ወታደራዊ መሳሪያዎች ታሪካዊ በሆነው ጥቃት ሙሉ በሙሉ ተደምስሷል ሲሉ ተደምጠዋል።

የትራምፕ አስተዳደር አሜሪካ በኢራን ላይ ያደረሰችው ጥቃት የኒውክሌር ፕሮግራሟን አላወደመውም የሚለውን ዘገባ ውድቅ ማድረጉን ቀጥሏል።

በስምኦን ደረጄ
#ዳጉ_ጆርናል
2025/06/29 19:08:37
Back to Top
HTML Embed Code: