Telegram Web Link
ከጁቡቲ እስከ ጋላፊ እና ደወሌ ተሽከርካሪዎች ጉዳት ደርሶባቸዉ ለማስነሳት ከ2.5 ሚሊዮን ብር በላይ እንጠየቃለን ሲሉ የፈሳሽ ጭነት ተሽከርካሪ ባለንብረቶች ተናገሩ

የጁቡቲ መንገድ ለተሽከርካሪዎችና አሽከርካሪዎች ምቹ አለመሆኑ የተገለፀ ሲሆን በመንገድ ትራንስፖርት ፣በጁቡቲ ባለስልጣናት ፣በኤምባሲ እና በሌሎችም አካላት አከባቢዉን ምቹ ለማድረግ ይሠራል ቢባልም ከ1991 ጀምሮ ምንም የተስተካከለ ነገር አለመኖሩ ተነግሯል ።

በጁቡቲ ማቆሚያ ተርሚናሎች አከባቢ ለአደጋ ለሚጋለጡ አሽከርካሪዎች የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና መስጫ ተቋማት አለመኖራቸው ሌላኛው ችግር ነዉ ተብሏል ።ከብስራት ሬዲዮ ጋር ቆይታ ያደረጉ የፈሳሽ ጭነት ተሽከርካሪ ባለንብረቶች እንደተናገሩት ከሆነ አንድ መኪና ጁቡቲ ላይ ብልሽት ሲደርስበት ተሳቢዉንና መኪናዉን ለማስነሳት ወደ 1.2ሚሊዮን ብር የሚጠየቅ ሲሆን ከቦታው ቀና ለማድረግ 500ሺህ ብር ፣የማፃፊያ ፣የጀንደር በሪ ፣የጉምሩክ አበል እና የፖምፕ ኪራይ ተደማምሮ ከ2.5 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚጠየቁ ተናግረዋል ።

ይህም መኪናዉ ያለማቋረጥ በወር አራት ጊዜ ቢሰራ በሁለት ዓመት የማይሰራው ብር መሆኑን የገለፁት ባለንብረቶቹ የምንጠየቁ ገንዘብ መኪናዉን ከመጣል አይተናነስም ብለዋል ። ከዛ ባለፈም ተሽከርካሪዉ የሚነሳበት መንገድ የመኪናዉን ደህንነት በጠበቀ መልኩ ሳይሆን ሀይልና ጉልበትን በመጠቀም የተሽከርካሪውን አካላት  በማዉደምና በይበልጥ በማበላሸት መሆኑ ተጠቁሟል ።

አንድ ተሽከርካሪ በጁቡቲ ጋላፊ ኬላ ከመጣ 200 ኪሎ ሜትር ፣በደወሌ ከመጣ 130 ኪሎ ሜትር ሲሆን ጎትተዉ አምጥተው የሚጠይቁት ክፍያ ከ600 እስከ 700ሺህ ብር ነዉ ብለዋል ። እስከ አዲስ አበባ ለማምጣት ሌላ ተጨማሪ ወጪ እንደሚወጣ ተገልጿል ።

በተጨማሪም ከአዳማ እስከ መተሀራ ባለዉ ተሽርካሪ ላይ ጉዳት ደርሶ እዛዉ ሲቆም በአከባቢዉ ያሉ ሚሊሻ ታጣቂዎች በቀን እስከ 20ሺህ ብር የሚጠይቁ በመሆኑ ይህም ከአቅም በላይ ስለሆነብን የሚመለከተዉ የመንግስት አካል አስፈላጊውን ቁጥጥር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል ። ከየትኛውም የመኪና ጥበቃ ክፍያ አከባቢዎች ከመተሀራ እስከ አዳማ ያለዉ ከባድ ክፍያ የሚጠየቅበት መሆኑን ከጣቢያችን ጋር ቆይታ ያደረጉት የፈሳሽ ጭነት ተሽከርካሪ ባለንብረቶች ተናግረዋል ።

በመባ ወርቅነህ
#ዳጉ_ጆርናል
አያቶላህ አሊ ካሜኔይ ኢራን በእስራኤል ላይ 'ድል' እንዳገኘች ተናገሩ

የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ካሜኒ አሜሪካ በኢራን እና በእስራኤል መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት መደረሱን ካወጀች በኋላ የመጀመሪያ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ካሜኔይ ንግግር፣ በኤክስ ላይ በለጠፉት መልዕክት የኢራን ህዝብ በእስራኤል ላይ ላገኘዉ “ድል” እንኳን ደስ አለህ ለማለት እወዳለሁ በአስፈሪው የጽዮናዊ አገዛዝ ላይ ስላገኘነዉ ድል እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉ ጽፈዋል።አያቶላህ ኸሚኒ ሌላ በቴሌግራም አካውንታቸው በፋርሲ ቋንቋ ባስተላለፉት መልዕክት በኢራን ብሄራዊ አንድነት አሞካሽተዉ በወደ 90 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ በአንድ ድምፅ፣ ትከሻ ለትከሻ፣ የታጠቁ ሀይሎችን በመደገፍ በአንድነት ቆሟል ሲሉ ተደምጠዋል።

የአሜሪካን የጦር ሰፈሮች መምታት በጣም ጥሩ ነገር ነው እናም ወደፊት ሊደገም ይችላል ሲሉ ካሜኒ አክለዋል፡፡የኢራን ህዝብ ልዩ ባህሪውን አሳይቷል እናም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ አንድ ድምጽ ከዚህ ህዝብ እንደሚሰማ አሳይቷል ብለዋል፡፡ወደፊት በኢራን ላይ የሚደረግ ማንኛውም ጥቃት ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል።ኢራን ዋና ዋና የአሜሪካን ጦር ሰፈሮችን ማግኘት እና መድረስ መቻሏ ትልቅ ነገር ነው ወደፊትም እንደገና ጥቃት ቢሰነዘርበት ሊደገም ይችላል ሲሉ ተደምጠዋል።የኢራን ጠላቶች እኛን ለማጥቃት እንደ ሚሳኤሎች ወይም የኒውክሌር መርሃ ግብሮች ሰበብ ይጠቀማሉ፣ ነገር ግን  እጅ እንድንሰጥ እየፈለጉ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

ሀገራቸው ከእስራኤል ጋር በነበረችበት ጦርነት በኢራን ውስጥ ወደ ሁለት ሳምንታት የሚጠጋ ሚስጥራዊ ስፍራ ከቆዩ በኋላ የ86 አመቱ የበላይ መሪ የሆኑት አያቶላ አሊ ካሜኒ በእስራኤል እንዳይገደሉ በመፍራት ወደ ጥብቅ ጉድጓድ ውስጥ እንደገቡ ይታመናል። ከመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳልነበራቸው ተመላክቷል፡፡በጦርነቱ ወቅት እስራኤል የኢራንን የአየር ክልል በፍጥነት የተቆጣጠረች ሲሆን ወታደራዊ መሠረተ ልማቷን አጥቅታለች። የአብዮታዊ ጥበቃ እና የሰራዊቱ ከፍተኛ አዛዦች በፍጥነት ተገድለዋል፡፡

በጦር ኃይሉ ላይ የደረሰው የጉዳት መጠን አሁንም ግልጽ ያልሆነ እና አከራካሪ ቢሆንም በሠራዊቱ እና በአብዮታዊ የጥበቃ ማዕከሎች እና ተቋማት ላይ የሚደርሰው ተደጋጋሚ የቦምብ ጥቃት የኢራንን ወታደራዊ ኃይል በከፍተኛ ደረጃ ማሽቆልቆሉን ያሳያል። ወታደራዊ ሃይል ከፍተኛ መጠን ያለው የሀገር ሀብት ፈሰስ ሲደረግበት ቆይቷል።በ1989 ለመጀመሪያ ጊዜ መሪ የሆኑት አያቶላህ ካሜኔይ ኢራንን ከእስራኤል እና ከአሜሪካ ጋር በፈጠረችዉ ዉዝግብ ተጠቃሽ ሰዉ ተደርገዉ ይወሰዳሉ፡፡

በስምኦን ደረጄ
#ዳጉ_ጆርናል
በደን ወረራ የተከሰሱ 12 ግለሰቦች በፅኑ እስራት እና በገንዘብ ተቀጡ

በኮሬ ዞን ከ100 ዓመታት በላይ ተጠብቆ በቆየዉ የተፈጥሮ ደን ላይ ወረራ ያደረጉ 12 ግለሰቦች መቀጣታቸውን የደቡብ ኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሚሽን ህዝብ ግንኙነት እና ገጽታ ግንባታ ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር አሸናፊ ኃይሌ ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።ግለሰቦቹ  በህገ ወጥ መንገድ  የደን ጭፍጨፋ፣ የመሬት ወረራ፣ መሸጥ እና በሌላቸው ሥልጣን መሬትን ለሌሎች ህገ- ወጦች በመምራት የወንጀል ድርጊት ነው ሊቀጡ የቻሉት።

ተከሳሾቹ  የኢፈዲሪ መንግስት ስለ ደን እና አከባቢ ጥበቃ ያወጣውን አዋጅ ቁጥር 1065/2010 አንቀጽ 26(4) እና መሬት ስለመሸጥ እና መለወጥን ለመከልከል የወጣውን የዚሁ አዋጅ ድንጋጌ ተላልፈው ወንጀል የፈጸሙ መሆናቸውን የክስ መዝገባቸው  ያስረዳል።የምርመራ መዝገቡ የደረሰዉ የጎርካ ወረዳ ፍርድ ቤት የተከሳሾችን የእምነት ቃልና የምስክሮችን ቃል በመስማት ጥፋተኛ መሆናቸውን በማረጋገጥ ብይን ሰጥቷል።

በዚህም መሠረት በ1ኛና 2ኛ ተከሳሾች ላይ የ5 ዓመት እስራት እና 20 ሺህ ብር፣ በ3ኛ ተከሳሽ  አራት ዓመት ጽኑ እስራትና 20 ሺህ ብር፣ አራተኛ ተከሳሽ 3 ዓመት ጽኑ እስራት እና 20 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ዉሳኔ ተላልፎባቸዋል።ሌሎች ተከሳሾችን በተመለከተ በእያንዳንዳቸው ላይ 2 ዓመት ከ6 ወር እና 15 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ በማለት ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ማስተላለፉን ኮማንደር አሸናፊ ኃይሌ ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።

በሳምራዊት ስዩም
#ዳጉ_ጆርናል
ሰሜን ኮርያ ቱሪዝምን ለማነቃቃት የባህር ዳርቻዎችን ክፍት አደረገች

የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን በሚስጥራዊቷ የኮሚኒስት አገዛዛቸዉ ቱሪዝምን ያሳድጋል ብለው ያሰቡትን የባህር ዳርቻ ሪዞርት እየከፈቱ መሆናቸዉን የመንግስት ሚዲያዎች ዘግበዋል።በምስራቅ የባህር ዳርቻ የሚገኘው ዎንሳን ካልማ ሊጠናቀቅ ከታቀደበት ከስድስት ዓመታት በኋላ ቆይቶ ጁላይ 1 ላይ ለአገር ውስጥ ቱሪስቶች ክፍት ይሆናል። የውጭ ዜጎችን መቼ እንደሚቀበል ግን ግልጽ አይደለም::

ኪም በቅንጦት ያደጉት ዎንሳን ውስጥ ነው፣ በርካታ የሀገሪቱ ልሂቃን የግል ቪላዎች ያሏቸው ሲሆን በአንድ ወቅት የሚሳኤል መሞከሪያ ቦታ የነበረችዉን ከተማዋን ለመለወጥ እየሞከሩ ይገኛል።የመንግስት መገናኛ ብዙሃን የሆነዉ ኬሲኤንኤ እንደዘገበዉ ሪዞርቱ እስከ 20,000 ጎብኝዎችን ማስተናገድ የሚችል ሲሆን 4 ኪሎ ሜትር የባህር ዳርቻ፣ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ የገበያ ማዕከሎች እና የውሃ ፓርክ አላቸዉ ብሏል፡፡

ለአስርት አመታት በኒውክሌር ጦር መሳሪያ መርሃ ግብሯ ምክንያት ከፍተኛ ማዕቀብ የተጣለባት ሰሜን ኮሪያ ከአለም ድሃ ሀገራት ተርታ ትጠቀሳለች። ከ1948 ዓ.ም ጀምሮ አገሪቱን ሲመራ የነበረውን የኪም ቤተሰብ ነዉ፡፡ አብዛኛው ሀብቷን ወደ ወታደራዊ፣ የኪም  ቤተሰብ ሐውልቶች እና ምልክቶች ላይ በፒዮንግያንግ - ፈሰስ ሲደረግ ቆይቷል። አንዳንድ ታዛቢዎች ይህ ለፒዮንግያንግ ገንዘብ የምታገኝበት ቀላል መንገድ ነው ይላሉ። የውጪ ቱሪስቶች ወደ ውስጥ እንዲገቡ ቢፈቀድም፣ የቱሪስት ቡድኖች በአብዛኛው የሚመጡት ከቻይና እና ሩሲያ ነው፣ ፒዮንግያንግ ከረጅም ጊዜ በፊት ወዳጅነት ከሁለቱ ሀገራት ጋር አላት።

በስምኦን ደረጄ
#ዳጉ_ጆርናል
በሱሉልታ ፍተሻ ጣቢያ አካባቢ በደረሰው የትራፊክ አደጋአራት ሰዎች ህይወት አለፈ

ዛሬ ሰኔ 19 ቀን 2017 ዓ.ም ከረፋዱ 4:50 ገደማ በጉለሌ ክፍለ-ከተማ ወረዳ 7
ሱሉልታ ፍተሻ ጣቢያ ከመድረሱ በፊት ባለዉ ቁልቁለት መንገድ ላይ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የአራት ሰዎች ህይወት ማለፉን የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።

አደጋው የደረሰው ከባድ ጭነት ጭኖ ይጓዝ የነበረ ከባድ ተሽከርካሪ የጫነዉ ጭነት ተሳፋሪ ጭኖ ወደ ሱሉልታ ይጓዝ በነበረዉ ሚኒባስ ተሽከርካሪ ላይ በመወደቁ መሆኑን የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል። በአደጋዉ በሚኒባስ ታክሲ ዉስጥ የነበሩ አራት ተሳፋሪዎች ህይወታቸዉ አልፏል።

የኮሚሽኑ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ህይወታቸዉ ያለፈዉን ሰዎች ከአራት ሰዓታት ጥረት በኋላ  አስከሬናቸውን ከተጫናቸዉ ጭነትና ከተሽከርካሪ ዉስጥ አዉጥተዉ ለፖሊስ አስረክበዋል።

የሟቾችን አስከሬን ለማዉጣት የኮሚሽኑ እና የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ክሬኖች ጥቅም ላይ የዋሉ ሲሆን በሂደቱም የአዲስ አበባ ፖሊስና ሌሎች የጸጥታ አመራርና አባላት ድጋፍ አድርገዋል።

በትግስት ላቀው
#ዳጉ_ጆርናል
Forwarded from ዳጉ ጆርናል-ስፖርት (Beⓒk)
Breaking : አርሰናሎች ኤብሪቼ ኤዜን የዝዉዉር እቅዳቸዉ ዉስጥ እንዳስገቡት ቤን ጄኮብስ ዘግቧል። የ 68 ሚሊዮን ፓዉንድ ዉል ማፍረሻ ያለዉ ሲሆን ቶትንሃምም የተጨዋቹ ፈላጊዎች ናቸዉ።

ስካይ ስፖርት በአንጻሩ አርሰናል እና ኤዜ በግል ጉዳዮች መስማማታቸዉን ዘግቧል። ፓላስም በሶስት ጊዜ ተቆራርጦ የሚከፈል በየአመቱ 20 ሚሊዮን ፓዉንድ እና 8 ሚሊዮን ተጨማሪ ክፍያ ይፈልጋል። ተጨዋቹም ወደ አርሰናል ለመዘዋወር ግፊት እያደረገ ነዉ ብሏል።

አርሰናል የሮድሪጎንም ሁኔታ እየተከታተለ ሲሆን ተጨዋቹ ስለ ዝዉዉር ከማሰቡ በፊት በቅድሚያ ከዣቪ አሎንሶ ጋር ስለሚኖረዉ ቆይታ ማየት ይፈልጋል።

#ዳጉ_ጆርናል_ስፖርት
@Dagujournalsport
በደቡብ ጎንደር ዞን የትራንስፖርት አገልሎት ለሶስት ቀናት በመቋረጡ ማህበረሰቡ ለእንግልት መዳረጉ ተገለፀ

በደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ መካነ ኢየሱስ የትራንስፖርት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ በመቋረጡ ህብረተሰቡ ለከፍተኛ እንግልት እየተጋለጠ መሆኑን የመካነ-ኢየሱስ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ተጠሪ ጽ/ቤት አስታውቋል።በዞኑ የኮሚኒኬሽን መምሪያ ሀላፊ አቶ እሱባለው መስፍን ለብስራት ሬድዮ እንደተናገሩት በአካባቢው የትራንስፓርት አገልግሎቱ ከተቋረጠ ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን ይዟል።

በሁሉም አቅጣጫ ሙሉ በሙሉ የትራንስፖርት ሊቋረጥ የቻለው በፀጥታ ችግር እንደሆነ አቶ እሱባለው ጠቅሰው ይህም አሽከርካሪዎች ለከፍተኛ ድብደባ እንዲሁም ግድያ እና እንግልት መጋለጣቸውን ተናግረዋል።ባለሀብቶች በንብረታቸው ማዘዝና በገንዘባቸው መጠቀም፤ ነጋዴዎች ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ ሸቀጣ ሸቀጥ ማቅረብ አለመቻላቸውም ተጠቅሷል።

በተጨማሪም የትራንስፖርት አገልግሎቱ በመቋረጡ የተነሳ ሰኔ 23/2017 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠውን የ12ኛ ክፍል ፈተና ለማደናቀፍ ተማሪዎች ፈተናው ወደ ሚሰጥበት ማዕከል እንዳይሄዱ አሉታዊ ጫናን ፈጥሯል ተብሏል።አሁን ላይ ችግሩን ለመፍታት የከተማው አስተዳደርና የወረዳው አመራሮች ከባለሀብቶችና አሽከርካሪዎች ጋር ውይይት እያደረጉ እንደሚገኙ ተገልጿል።

ቅድስት ደጀኔ
#ዳጉ_ጆርናል
የእስራኤል የደህንነት ሚኒስተር ለጋዛ የሚሰጠውን እርዳታ በሙሉ እንዲቋረጥ በድጋሚ ጥሪ አቀረቡ

የእስራኤል ብሄራዊ ደህንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤን-ጊቪር "በአሁኑ ጊዜ ወደ ጋዛ እየገባ ያለው የሰብአዊ እርዳታ ፍጹም አሳፋሪ ነው" ብለዋል። “በተደጋጋሚ ባስጠነቀቅኩ ጊዜ እና በሚያሳዝን ሁኔታ ከአንድ ወር ተኩል በፊት እርዳታ እንዳይገባ ድምጽ የሰጠ ብቸኛው ሰው ሆኜ ለሃማስ የህይወት መስመር እንደሚሰጥ እርግጠኛ ነበርኩ” ሲሉ የቀኝ አክራሪውና እና ብዙ ጊዜ አነጋጋሪ አስተያየት በመስጠት የሚታወቁተወ ሚኒስትር በኤክስ ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ተናግረዋል።

ቀጥሎም “በዚያን ጊዜ አንዳንዶች ‘እርዳታው ወደ ሰሜናዊው ሴክተር እና ለ10 ቀናት ብቻ ነው የሚሄደው’ ብለው ያፌዙብኝ ነበር፣ እናም ዛሬ ምን እየተፈጠረ እንደሆነ ግልፅ ነው። ሃማስ የምግብ እና የሸቀጦችን መጠን ይቆጣጠራል፣ ይህም ለህልውናው አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል።

"ዕርዳታውን ማቆም ድል ያፋጥናል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚቀጥለው የካቢኔ ስብሰባ ላይ ወደ ጋዛ በሚገባው ዕርዳታ ዙርያ እንደገና ድምፅ እንዲሰጥ እጠይቃለሁ " ሲሉ የእስራኤል የደህንነት ሚንስቴሩ ኢታማር ቤን ጊቨር ተናግረዋል።

በሚሊዮን ሙሴ
#ዳጉ_ጆርናል
ደሞዝ አልከፈልከኝም በሚል ምክንያት አሰሪውን የገደለው በእስራት ተቀጣ

ተከሳሹ ጌቱ መስፍን ይባላል፤ የወንጀል ድርጊቱን የፈፀመው ነሀሴ 27 ቀን 2014 ዓ/ም ከረፋዱ 4 ሰዓት ከ30 ሲሆን በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ለገሃር ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ኖህ ሪል ስቴት ከሚያሰራው ህንፃ 16ኛ ጅምር ፎቅ ላይ ነው።

ሟች ሀጂብ ያሲን የተባለው ግለሰብ ከኖህ ሪል እስቴት ኮንትራት በመውሰድ ከስሩ በርካታ ሰራተኞችን ቀጥሮ የሚያሰራ ግለሰብ ነው።

ሟች የዘወትር ስራውን ለማሰራት ሰራተኞችን ወደ የስራቸው ያሰማራል። ተከሳሽም ሟች የነበረበት ቦታ ጭር ማለቱን እና ማንም አለመኖሩን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመውሰድ ደሞዜን ከለከልከኝ በሚል ምክንያት በተፈጠረ አለመግባባት ሟች ሀጂብ ያሲንን ስራ እየሰራ ባለበት 16ኛ ፎቅ ላይ በፌሮ ብረት ግንባሩን በመምታት እና አንገቱን በሽቦ ገመድ በማነቅና በማሰር ህይወቱ እንዲያልፍ በማድረግ ሟችን ከህንፃው ተሸክሞ በማውረድ የህንፃው መሰረት ስር የሚገኝ የተጠራቀመ ውሃ ውስጥ አስከሬኑን በመጣል ከአካባቢው ይሰወራል።

የወንጀሉ መፈፀም ሪፖርት የደረሰው ፖሊስ የምርመራ ክፍሉና የክትትልና ኦፕሬሽን ቡድኑ በመዋቀርና በመቀናጀት ወንጀል ፈፃሚውን ለመያዝ በተደረገ ጥረት ተከሳሽ ጌቱ መስፍን ወንጀሉን ከፈፀመ በኋላ ምንም እንዳልተፈፀመ በኔጌሌ ቦረና ከተማ በአንድ ተቋም ውስጥ ተቀጥሮ በመስራት ላይ እንዳለ በቁጥጥር ስር ሊውል መቻሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ገልጿል።

በተከሳሽ ጌቱ መስፍን ላይ የምርመራ መዝገቡን በሰውና በሰነድ ማስረጃ በማጠናከር ለሚመለከተው የፍትህ አካል በመላክ ክስ እንደተመሰረተበት የገለፀው የአዲስ አበባ ፖሊስ ተከሳሽ ጌቱ ጥፋተኛ ሆኖ በማግኘቱ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት በ21 አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ እንደተወሰነበት ገልጿል።

ማንም ሰው ወንጀል ፈፅሞ ከህግ እና ከማህበረሰቡ ማምለጥ እንደማይቻል የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ጠቅሶ ያለመግባባት በሚፈጠርበት ወቅት በመነጋገር መፍታት ይገባል ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል።

#ዳጉ_ጆርናል
2025/06/28 13:48:30
Back to Top
HTML Embed Code: