Telegram Web Link
+++ትሕትና ምንድር ነው?+++

ትሕትና ምንድር ነው? ብዙ ጊዜ በእኛ ዘንድ የተናቀ ልብስ መልበስ ፣ አንገት መስበር ፣ ዝግ ብሎ ማውራት እና ‹እኔ በደለኛ የማይገባ ሰው ነኝ› እያሉ ደጋግሞ መናገር እንደ ትሑት ያስቆጥር ይሆናል፡፡ ነገር ግን የትሕትና ትርጉም ከዚህም በላይ ነው፡፡ በርግጥ ከላይ የዘረዘርናቸው ነገሮች የአንድ ትሑት ሰው ከፊል መገለጫ ጠባያት ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህን በማድረግ ብቻ ትሑት መሆን ቢቻል ኖሮ ፤ በዓለም ላይ ያለው የትዕቢተኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀንስ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ትሕትናን በተጠቀሱት ውጫዊ ምግባራት ብቻ የምንረዳው ከሆነ ከእውነተኛ ትርጉሙና ማንነቱ እንዳናሳንሰው ስጋት አለኝ፡፡

ትሕትና በእኛ እና በእግዚአብሔር መካከል ያለ እውነተኛ ኑሮ ነው፡፡ አንድ ክርስቲያን ስለ ትሕትና ሲያስብ እነዚህን ሁለት ነገሮች አብሮ በትኩረት ሊያሰላስል ይገባዋል፡፡ እነርሱም አንደኛ ተፈጥሮውን (መሬታዊ ፣ትቢያ መሆኑን) አለመዘንጋት ሲሆን ፣ ሁለተኛው ደግሞ ተቀባይነቱን ለዘወትር ማስታወስ ነው፡፡ ሰው በጫማው እየረገጠ የሚራመደው አፈር እንደሆነ ሲያስብ ደካማነቱን ይረዳል፡፡ ስለዚህም በነገሮች ሁሉ ‹አቤቱ እኛ አፈር እንደ ሆንን አስብ› እያለ ረድዔተ እግዚአብሔርን የሚማጸን ትሑት ይሆናል፡፡ (መዝ 103፡14) ተቀባይነቱንም ሁል ጊዜ የሚያስታውስ ከሆነ ለሌሎች በሚያደርጋቸው በጎ ሥራዎች አይኩራራም፡፡ ብልጫም አይሰማውም፡፡ ምክንያቱም የራሱን ሳይሆን ከአምላኩ ከተሰጠው ላይ ቀንሶ የሚያካፍል ምስኪን ምጽዋተኛ ስለሆነ፡፡ ሐዋርያውስ ቢሆን በቆሮንቶስ መልእክቱ በታላቅ ቃል ‹አንተ እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ? የተቀበልህ ከሆንህ ግን እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለምንድር ነው?› ሲል የሚገስጸው ስለዚሁ አይደለምን? (1ኛቆሮ 4፡7)፡፡

ሶርያዊው አባት ማር ይስሐቅ ስለ ትሕትና ትርጉም አንድ ቁም ነገር ያካፍለናል፡፡ ምን አለ? ‹ውድቀትና ኃጢአቱን እያነሣ ራሱን የሚወቅስና የሚያዋርድ ጥሩ ቢያደርግም ትሑት ተብሎ ግን አይጠራም፡፡ ትሑት ሰው ራሱን ማሳመንና ኅሊናውም ይህን ሐሳብ እንዲይዝ መጫን አይጠበቅበትም፡፡ እንዲሁ ራሱን ምንም አድርጎ ይቆጥራል እንጂ› ሲል አስተማረ፡፡ እንደ ማር ይስሐቅ ትምህርት ከሆነ ትሑት ለመሆን ሲባል ራስን ማስጨነቅ ወደ ትሕትና ጫፍ ለመድረስ ሯጭ(ተጋዳይ) መሆንን የሚያሳይ እንጂ ‹ትሑት› አያሰኝም፡፡ እውነተኞቹ ትሑታን ሌላ የሚጋፋ እና ትግል የሚጠይቅ አንዳች የበላይነት (የእኔነት) ስሜት ሳይሰማቸው እንዲሁ ራሳቸውን የሰው ሁሉ መጨረሻ አድርገው የሚቆጥሩ ናቸው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ባሕታዊም ‹ትሑት ሰው የሚባለው ራሱን የሚሰድብና የሚያዋርድ ሳይሆን ፤ ከሌሎች ሰዎች በሚደርስበት ስድብና ትችት ፊት ፍቅሩ ሳይቀንስበት መቆም የሚችል ሰው ነው› በማለት ያስተማረው ይህን የፍጹማኑን ትሕትና ለማሳየት ነው፡፡

አባ መቃርዮስ እንደተናገረ የትሕትና ተቃራኒ የሆነች ትዕቢት የኃጢአቶች ሁሉ ራስ (እናት) ናት፡፡ ታዲያ ትዕቢት ለኃጢአቶች ሁሉ እናት ከሆነች ትሕትና ለጽድቅ ሥራዎች ሁሉ ራስ ብትሆን ምን የሚያስደንቅ ነገር አለ?!፡፡ ለዚህም ነው እኮ ቅዱሳን አበው ትሕትናን ‹እጸ ሕይወት›/‹የሕይወት ዛፍ› እያሉ የሚጠሯት፡፡ አዳም በገነት አንድ ሺ ዓመት ከኖረ በኋላ ወደማታልፈው መንግሥት (መንግሥተ ሰማያት) ለመግባት የሚታደስባትን እጸ ሕይወት አምላኩ በገነት ዛፎች መካከል ፈጥሮለት ነበር፡፡ እርሱም ትእዛዘ እግዚአብሔርን ጠብቆ ሺ ዘመን ቢቆይ ኖሮ ፤ ላይወድቅ ላይጎሰቁል በእጸ ሕይወት ታድሶ መንግሥተ እግዚአብሔርን ይወርስ ነበር፡፡ ከእጸ ሕይወት በኋላ መውደቅ የለምና፡፡ እንዲሁ ትሕትናም እጸ ሕይወት ነች፡፡ ትሕትናን ገንዘብ ካደረጉ በኋላ ውድቀት እና ከእግዚአብሔር መለየት የለም፡፡

ትሕትና በጎ ሥራዎች ሁሉ የሚጠበቁባት አጥር ቅጥር ነች፡፡ ከእግዚአብሔር የምናገኛቸው ጸጋዎችም ያለ ትሕትና ሊጸኑ ፣ ሊሰነብቱ አይችሉም፡፡ ቅዱሳን በጽኑዕ ተጋድሎ እና በፈጣሪ ቸርነት የገነቡትን የጸጋ ግንብ ሰይጣን እንዳያፈርስባቸው ፈጣሪያቸው የሚከላከልላቸው ትሑታን የሚሆኑበትን ደዌ ወይም አንዳች ነገር በእነርሱ ላይ በማምጣት ነው፡፡ ባለ ብዙ ጸጋ የነበረው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን የእግዚአብሔር አሠራር ሲያስረዳን ‹በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ የሥጋዬ መውጊያ…ተሰጠኝ ይኸውም እንዳልታበይ ነው› በማለት ግልጽ አድርጎ ይናገራል፡፡(2ኛ ቆሮ 12፡7) በሰውነቱ ጥላ እና በልብሱ እራፊ ሙት የሚቀሰቅሰው ፣ሕሙም የሚፈውሰው ሐዋርያ እንደ ስንጥር በሚወጋ ራስ ምታት መያዙ ፤ ተአምር ሲያደርግ በተመለከቱት ሰዎች በስህተት እንዳይመለክና ልብን ሰቅዞ በሚይዝ አጉል ውዳሴ እንዳይጠለፍ አድርጎታል፡፡ በርግጥም የገባሬ ተአምራት የቅዱስ ጳውሎስን ሕመም ያዩ ሰዎች በእርሱ ድካም ውስጥ የሚሠራ የእግዚአብሔርን ኃይል በግልጽ ተረድተዋል፡፡

እግዚአብሔር በጎውን ዋጋ የሚሰጠን መልካም ስላደረግን ይመስላችኋል? አይደለም፡፡ በዚህ ዓለም ላይ መልካም የሚያደርጉ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች ከእግዚአብሔር በጎውን ዋጋ ላይቀበሉ ይችላሉ፡፡ ለምን? ከአምላክ ዘንድ በጎ ዋጋ የሚያሰጠው መልካም ማድረግ ሳይሆን ፤ መልካሙን ነገር በትሕትና ማድረግ በመሆኑ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክም ከተነሡ ውዝግቦች (ክህደቶች) መካከል አንዱ የሆነው የ‹Pelagius controversy› ለዚህ ጉዳይ ተጠቃሽ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም የአየርላንድ መነኩሴ በሆነ ፔላጊዮስ የተጠነሰሰ ሲሆን ፤ አጠቃላይ ምልከታውም ‹ሰው ብቻውን በሚያደርገው በጎ ሥራ ይድናል› የሚል በረድዔተ እግዚአብሔር መደገፍንና ትሕትናን አውልቆ የሚጥል የክህደት ትምህርት ነበር፡፡ በእውነትም የማታልፍ የማትለወጥ የእግዚአብሔርን ርስት ፣ ፈራሽ በስባሽ በሆነው ሰውነቴ ብቻ ሠርቼ ገንዘብ አደርጋለሁ ከማለት በላይ ተሻለ ክህደት ከወዴት ሊመጣ ይችላል?

እስኪ ጽሑፋችንን በቅዱስ መቃርስ ምሳሌ እንዝጋው፡፡ አባ መቃሪ በአንድ ወቅት ስለ ትሕትና ሲያስተምር ‹አንድ ባለጠጋ የነበረ ንጉሥ ያለውን ሀብት በአደራ መልክ ከአንድ ደሃ ዘንድ ቢያኖር ፤ ያ ደሃ በእነዚያ ብሮች እና ወርቆች ሊመካ ይችላልን? እንደ ራሱ ንብረትስ በመቁጠር የባለቤትነት ስሜት ሊሰማው ይገባል?› ሲል ይጠይቃል፡፡ በዚህ ቅዱስ አባት ምሳሌ መሠረት ያ ባለጠጋ ንጉሥ እግዚአብሔር ነው፡፡ አደራ ተቀባዩ ነዳይ ደግሞ እኛ ነን፡፡ አደራውም በእጃችን ያሉ በጎ ነገሮች ሁሉ ናቸው፡፡ ያሉንን መልካም ነገሮች እንደ ራስ ንብረት መቁጠርና በሌላው ላይ መኩራራት አደራ ተቀባይነትን እንደ መርሳት ነው፡፡ ሰው ባልፈጠረው በጎነት እንዴት ይኩራራል?

በትሑታኑ ቅዱሳን ጸሎት ይጠብቀን!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
"ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ነው እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት፤... አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል"

1ኛ ቆሮ 15፥ 14-20

መልካም በዓል!
+++ ‹ወዴት ነው የምናየው?› +++

ለጌታ ቅዱስ ሥጋ ይሆን ዘንድ ያዘጋጀችውን ሽቱ በመያዝ የጨለማውን ግርማ ሳትፈራ መግደላዊት ማርያም በሌሊት ገስግሳ ወደ መቃብሩ መጥታለች፡፡ አይሁድ ያቆሟቸው ወታደሮች ጥቂት ርኅራኄ ካደረጉላት እንደ ልማዱ የጌታዋን ሥጋ ሽቱ ለመቀባት ትፈልጋለች፡፡ ነገር ግን በቦታው ደርሳ የተመለከተችው ነገር በድንጋጤ ሐሞቷን አፈሰሰው፡፡ ጎመድ የታጠቁ ብርቱዎቹ የመቃብሩ ጠባቂዎች የሉም። አይሁድ በሰንበት በመቃብሩ ያተሙትም ማኅተም ከነመዝጊያ ድንጋዩ ወዲያ ተንከባሏል፡፡ በስፍራው አንዳች መልእክት ያለው ዝምታ ነግሧል፡፡ ይህን ጊዜ መግደላዊት ማርያም ኃዘን ባደቀቀው አቅሟ እየወደቀች እየተነሣች ሐዋርያቱ ወደ ተሰበሰቡበት ቤት ሄደች፡፡ ለስምዖን ጴጥሮስ እና ለዮሐንስም ‹ጌታን ከመቃብር ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አናውቅም› ስትል እንባ እየተናነቃት ነገረቻቸው፡፡

ይህን የሰሙ ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም ወደ ጌታ መቃብር መንገድ ጀመሩ፡፡ አብረውም ሮጡ፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ዮሐንስ በወጣትነት ጉልበት ከፊት ከፊት እየፈጠነ ቀድሞ ከመቃብሩ ደረሰ፡፡ አረጋዊው ቅዱስ ጴጥሮስ ግን ቢሮጥም እንኳን እንደ ዮሐንስ ሊሆን አልቻለም፡፡ በእርግጥ ለክርስቶስ ከነበረው ፍቅር የተነሣ በእርጅና ጉልበቱ ቢሮጥም የሐሙስ ምሽቱ ክፉ ትውስታ (ዶሮ ሳይጮህ መካዱ) ግን ከዕድሜው ጋር ተደምሮ ጥቂት ሳያዘገየው አልቀረም፡፡ ወደ መቃብሩም ቀድሞ የደረሰው ሐዋርያው ዮሐንስ ከመጓጓት ብዛት ራሱን ዝቅ ቢያደርግ የመግነዙን ጨርቅ ተመለከተ፡፡ ወደ ውስጥ እንዳይገባ ግን ‹አክብር ገጸ አረጋዊ› - ‹ሽማግሌውን አክብር› የምትለው ደገኛይቱ ሕግ ከለከለችው፡፡ ዘግይቶ የመጣው ቅዱስ ጴጥሮስ ወደ መቃብሩ ቀድሞ በመግባት በመልክ በመልክ የተቀመጡትን የተልባ እግር ልብሱንና ፣ የራስ ጨርቁን አየ፡፡  ነገር ግን በመጽሐፍ የተጻፈውን የክርስቶስን ትንሣኤ አላመነም ነበርና ማየቱ ከኃዘን በቀር የጨመረለት ነገር የለም፡፡ ለካስ ማወቅ ብቻ ሳይሆን አለማወቅም ትካዜን ይጨምራል?! (ቅዱስ ዮሐንስ ግን በሚያስደንቅ ሁኔታ አይቶ አምኗል። ዮሐ 20፥8)

ሐዋርያቱ ‹አይሁድ የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋ ለማንገላታትና ለማዋረድ ከዚህ አውጥተው ሌላ መቃብር ውስጥ አድርገዉት ይሆናል› የሚል ግምት ቢኖራቸውም፣ ነገር ግን እነርሱን ‹የት አደረጋችሁት?› ብሎ የመጠየቅ ድፍረቱ ስላልነበራቸው አንገታቸውን እንደ ሰበሩ በዝምታ ወደ መጡበት ቤት ተመለሱ፡፡ ማርያም መግደላዊት ግን ከመቃብሩ ውጭ ቆማ የፍቅር እንባን ታፈስ ነበር፡፡

በኋላም ወደ መቃብሩ ውስጥ ዝቅ ብላ ብትመለከት ሁለት ነጫጭ የለበሱ መላእክትን የክርስቶስ ሥጋ ተኝቶ በነበረበት ራስጌና ግርጌ ተቀምጠው አየች፡፡ ቅዱስ ማቴዎስና ቅዱስ ማርቆስ ግን በወንጌላቸው ያናገራትን መልአክ ብቻ በመቁጠር መግደላዊት ማርያም አንድ መልአክ እንደታያት ይጽፋሉ፡፡ ይህችም ሴት ከደረሰባት የኃዘን ጽናት የተነሣ እንዳትሰበር የሚያረጋጉ መላእክት ተላኩላት፡፡ እነዚህም መላእክት ቀድሞ በጥል ዘመን (በኦሪት) እንደ ነበረው የምትገለባበጥ ሰይፍ ይዘው በዓይነ መአት (በቁጣ ዓይን) እያዩ ሳይሆን፣ የደስታ ምልክት የሆነውን ነጭ ልብስ ተጎናጽፈው ደስ በተሰኘ ብሩህ ገጽ ተገለጡላት፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ከነፋስ የረቀቁ፣ ሥጋዊ ጉልበት የሌላቸውን መላእክት በመቃብሩ ውስጥ ‹ተቀመጡ› ሲል ይነግረናል፡፡ ይህም አንደኛ መቆም መቀመጥ በሚስማማው ሰው አምሳል መገለጣቸውን የሚያሳይ ሲሆን፤ ሁለተኛ ደግሞ መቀመጥ ዕረፍትን፣ መረጋጋትን እንደሚያሳይ የመቃብር አስፈሪነት ፣የሞትም ጣር እንደ ጠፋ ሲያመለክቱ በመቃብር ውስጥ ተቀምጠው ታዩአት፡፡

ከሁለቱ አንዱም መልአክ ‹አንቺ ሴት ለምን ታለቅሻለሽ?› ሲል ጠየቃት፡፡ ላዘነነ እና ለተጨነቀ ሰው በቀዳሚነት ሸክሙን የሚያቀሉለት በነጻነት ችግሩን እንዲናገር እድል በመስጠት ነውና መልአኩም አላዋቂ መስሎ ጥያቄውን አቀረበላት፡፡ እርሷም ‹ጌታን ከመቃብር ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አናውቅም› ስትል መለሰችለት፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ማርያም መግደላዊት በእነዚያ መላእክት ፊት ላይ የተመለከተችው ነገር እጅግ ትኩረት የሚስብ ነበር፡፡ ልክ ሕፃን ልጅ ገበያ ቆይታ የመጣች እናቱን ሲመለከት በጉጉት እንደሚንሰፈሰፈውና በደስታ የሚሆነውን እንደሚያጣ ፣ መላእክቱም እንደ እናት እንደ አባት የሚመግባቸውን ፣ ዘወትር ‹ሊያዩ የሚመኙትን› የፈጣሪያቸው የኢየሱስ ክርስቶስን ገጽ ባዩ ጊዜ እንደ እነዚያ ሕፃናት ሆኑ፡፡ ገጻቸውን ከእርሷ መለስ አደረጉባት፡፡ ይህን ጊዜ በአንድ አቅጣጫ የተተከለውን የእነርሱን ዓይን ተከትላ ወደ ኋላዋ ብትመለከት ‹ኢየሱስን ቆሞ አየችው›፡፡ ምንም ለጊዜው ባታውቀውም በስሟ ሲጠራት ግን ወዲያውኑ ለይታዋለች፡፡ ከዚህ ሁሉ በፊት ግን መጀመሪያ ክርስቶስን ያየችው የመላእክቱን የእይታ አቅጣጫ ተከትላ ነበር፡፡

እኛስ የእግዚአብሔር ቃል ባለ አደራ የሆንን የወንጌል መልእክተኞች ወዴት ነው የምናየው? ከፊታችን አስቀምጠን ለምናጽናናቸው ምእመናን የዓይናችን አቅጣጭ ወዴት እንዲመለከቱ ይመራቸዋል? አሁን ሕዝብ ሁሉ ጭልጥ ብሎ ወደ ፖለቲካው በመግባት ለሃይማኖቱ ግድ የለሽ ሆኗል፡፡ የእኛን የዓይን አቅጣጫ ተከትለው ይሆን?

በዘመናችን ሰውን ማክበር ፣እግዚአብሔርን መፍራት ብርቅ ሆኗል፡፡ ፍቅር ቀዝቅዞ ጥላቻ ነግሧል፡፡ ግድ የላችሁም ዓይናችን የፍቅር አምላክ የሆነው ክርስቶስን ሳይስት አልቀረም? ምክንያቱም የእኛን የእይታ አቅጣጫ ተከትለው የተመለከቱት ምዕመናን ከጥላቻ እና ይህን ከመሳሰሉት ክፋቶች በቀር ምንም አላተረፉምና? እስኪ አንዳፍታ ቆም ብለን ራሳችንን እንመርምረው? ግን ወዴት ነው የምናየው?

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
👍1
የጠሉህን ሳትወድድ፣ መከራ ያከበዱብህን ተቀይመህ፣ ስለ አሳዳጆችህ ሳትጸልይ እንዴት ጣቶችህን አመሳቅለህ የመስቀል ምልክት ትሠራለህ? በጣቶችህ ያለው መስቀል ጠላት የተወደደበት፣ ለሰቃልያን በቃል የማይነገር ትዕግስት የታየበት፣ ተሳዳቢ የተመረቀበት፣ ለሚወጉ ምሕረት የተደረገበት የፍቅር አውድማ ነው። ሰውን ለመወንጀል በቀሰርከው ጣትህ እንዴት መልሰህ የይቅርባነት ምልክት የሆነውን መስቀል ለመሥራት ሌላው ጣትህን አግድም ታስተኛለህ?

እያማተብህ አትጥላ፣ እያማተብህ አትፍረድ፣ እያማተብህ አትቀየም፣ እያማተብህ አትርገም።

"ገብረ ሰላመ በመስቀሉ" - "በመስቀሉ ሰላምን አደረገ"

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
+++የእስክንድር እንቁላሎች+++

ሕፃኑ እስክንድር እክል ካለበት ሰውነት ጋር የተወለደ ሲሆን፣ መለስተኛ የሆነ የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ችግርም አለበት፡፡ እስክንድር ምንም ዕድሜው አሥራ ሁለት ዓመት ይሁን እንጂ በጊዜው ገና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ነበር፡፡ ካለበት የጤና እክልም የተነሣ መማር ይቸግረው ነበር፡፡ ታስተምረው የነበረች ሴት መምህርቱም በልዩ እንክብካቤ ያለና በእነርሱ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ አብሮ መጓዝ እንደማይችል ተረድታዋለች፡፡ ጥሩ አስተማሪና እውነተኛ ክርስቲያንም ስለነበረች ተማሪዋ እስክንድርን በትኩረት ትከታተለው ነበር፡፡ የፀደይ ወቅት በመድረሱ እንዲሁም የፋሲካም በዓል ከፊታቸው እየመጣ ስለሆነ ከእስክንድር ጋር የሚማሩት ሕፃናት ተማሪዎች በተደሱበት በአንዱ ቀን እንዲህ ሆነ፡፡

መምህርቷ ተማሪዎቿ ሁሉ ትላልቅ የፕላስቲክ እንቁላል በመስጠት ‹ይህን የፕላስቲክ እንቁላል ወደ ቤታችሁ እንድትወስዱትና ነገ መልሳችሁ እንድታመጡት እፈልጋለሁ፡፡ ነገር ግን ስታመጡ በውስጡ አዲስ ሕይወትን ሊያሳይ የሚችል ነገር ማስቀመጣችሁን እንዳትረሱ› ብላ ነገረቻቸው፡፡

በቀጣዩ ቀን ጠዋት ላይ ሕጻናት ተማሪዎቹ የተሰጣቸውን የፕላስቲክ እንቁላል ይዘው ወደ ትምህርት ቤት መጡ፡፡ እየተሳሳቁ እና እየተጫወቱ በክፍላቸው ውስጥ መምህርታቸው ወዳዘጋጀችው ትልቅ ቅርጫት እንቁላሎቻቸውን ወረወሩ፡፡ ከዚያም እንቁላሎቹ ተከፍተው የሚታዩበት ጊዜ ሲደርስ አስተማሪያቸው አንድ በአንድ ከቅርጫቱ ማውጣት ጀመረች፡፡

የመጀመሪያውን እንቁላል ስትከፍተው በውስጡ አበባ አገኘች፡፡ ለሕፃናቱም ‹በትክክል! በርግጥም አበባ የአዲስ ሕይወት ምልክት ነው› ስትል ግርምቷን ገለጸች፡፡ የዚህ እንቁላል ባለቤት የሆነችውም ተማሪ እጇን በማውጣት የእርሷ መሆኑን ስትገልጽ ‹ጥሩ አድርገሻል!› ብላ አመሰገነቻት፡፡ በቀጣይ ያነሣችው እንቁላልም በውስጡ ቢራቢሮ ነበረው፡፡ መምህርቷም እንቁላሉን ወደ ላይ ከፍ በማድረግ ‹አባ ጨጓሬ መሳዩ (ካተርፒለር) ነገር በመቀየር ወደ ውብ ቢራቢሮነች እንደሚሸጋገር እናውቃለን፡፡ በእውነትም ይህም አዲስ ሕይወት ነው፡፡› አለች፡፡

ቀጥላም ሦስተኛውን እንቁላል ከፈተችው፡፡ በውስጡ ግን ምንም የሌለው ባዶ ነበር፡፡ በእርግጠኝነት የእስክንድር እንቁላል መሆኑን አሰበች፡፡ በጊዜው የተናገረችውን ነገር በደንብ ስላልተረዳ ይህን ያደረገ መሰላት፡፡ ልትረብሸውም ስላልፈለገች እንቁላሉን ቀስ ብላ በማስቀመጥ ሌላኛውን ከቅርጫት ሳበች፡፡ ነገር ግን በሁኔታው የተደነቀው እስክንድር በድንገት ‹መምህርት፣ ስላመጣሁት እንቁላል ምንም አትይም እንዴ?› ሲል ጠየቃት፡፡ መምህርቷም ፊቷ ላይ የመረበሽ ምልክት እየታየባት ‹ግን እኮ እስክንድር፣ እንቁላልህ ባዶ ነው› አለችው፡፡ እርሱም ዓይን ዓይኗን እየተመለከታት ለስለስ ባለ ድምጽ ‹አዎ መምህርት! የክርስቶስ መቃብርም እኮ እንዲሁ ባዶ ነበር› አላት፡፡

አስተማሪዋ የቀሩትን እንቁላሎች ለተማሪዎቹ አሳይታ ስትጨርስ ወደ እስክንድር በመሄድ ‹ለመሆኑ መቃብሩ ለምን ባዶ እንደሆነ ታውቃለህ?› አለችው፡፡ እርሱም ‹አዎ፣ ክርስቶስ ተገድሎ በዚያ ውስጥ ተቀብሮ ነበር፡፡ ነገር ግን እርሱ ከሞት ተነሣ፡፡ ታዲያ ይህ ነገር አዲስ ሕይወትን አያሳይምን?› ብሎ መለሰላት፡፡ ያቺም መምህርት በነገሩ ልቧ ተነክቶ ፊቷን ሸፍና አነባች፡፡

ይህም ነገር ከሆነ ከሦስት ወራት በኋላ ተማሪው እስክንድር አረፈ፡፡ የቀብር ሥርዓቱንም ለመከታተል የተሰበሰቡት ሰዎች አንድ እንግዳ ነገር በመቀበሪያው ሳጥኑ ውስጥ ተመለከቱ፡፡ ይኸውም የተከማቹ ሃያ እንቁላሎች ነበሩ፡፡ በክርስቶስ ትንሣኤ ምክንያት ባዶ እንደ ነበረው መቃብር ሃያዎቹ እንቁላሎችም ባዶ ነበሩ፡፡

Source : ‹The Eggs of Alexander› - Orthodox Parables and Stories /ከመለስተኛ ማሻሻያ ጋር

ትርጉም ፡ ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
1
ሰይጣን አንድን ኃጢአት ሊያሠራን ሲፈልግ ቀድሞ ስለ እግዚአብሔር መሐሪነት በሰፊው ይሰብከናል። ያን ኃጢአት ከፈጸምን በኋላ ደግሞ ስለ እውነተኛ ፈራጅነቱና ምንም ቢሆን ከቁጣው የማናመልጥ መሆኑን ከቀድሞው ይልቅ እየጮኸ ይነግረናል። በመጀመሪያው ስብከቱ ኃጢአትን እንዳንቃወም ሰነፎች ያደርገናል። በሁለተኛው ስብከቱ ደግሞ ንስሐ እንዳንገባ ተስፋ ያስቆርጠናል።

ይህ የተገለባበጠ ስብከት "የሰይጣን" ነው። ሰው በኃጢአት ከመውደቁ በፊት ሊያስብ የሚገባው የእግዚአብሔርን ፈታሒነት (ፈራጅነት) ሲሆን በኃጢአት ከወደቀ በኋላ ግን ማሰብ ያለበት የእግዚአብሔርን መሐሪነት ነው።

ፈታሒነቱ ኃጢአትን እንዳንሠራ ይጠብቀናል፤
መሐሪነቱ ንስሐ እንድንገባ ያቀርበናል፤

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
ልክ በእጅ ይዘውት እንደሚጠፋ ፋኖስ የሚወዱትን ሰው በክንድ እንደታቀፉ ሕይወቱ ስታልፍ እንደ ማየት፣ እስከዚያች ቅጽበት ድረስ በሕይወት እሳት ይሞቅ የነበረን የቅርብ ሰው ወዲያው በሞት ሲቀዘቅዝ አጠገቡ ሆኖ እንደ መመልከት እጅግ የሚያሳዝን ነገር የለም። ከንፈሮቹ ሲዘጉ፣ ድምጹ በዝምታ ሲዋጥ፣ በተለይም ደግሞ በምትቀዘቅዝ መሬት ጉያ ውስጥ ለማኖር "አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ" በሚለው ቃል ሲሸኙት የሚሰማን የውስጥ ሁከት በምን ይገልጹታል?!

ነገር ግን ክርስቲያን የእግዚአብሔር ልጅ መጥቶ ሞትን ድል ከነሣው በኋላ "ሞት እንቅልፍ እንደ ሆነ" ያምናል። ስለዚህም የሚወድደው ሰው ሲሞትበትና የመጨረሻዋን ስንብት ሲያደርግ፣ በፍጹም ፍቅርና መሳሳት የከደናቸው እነዚያ ዓይኖች ዳግመኛ ለማየት እንደሚገለጡ እርግጠኛ ነው። አሁን "ወንድሜ" ለሚለው ጩኸቱ የማይመልሰውና የተዘጋው ልሳኑ፣ አንድ ቀን ግን የሸኘው እርሱን ለመቀበል "እንኳን ደኅና መጣህ" ለማለት እንደሚፈታ በማመን ነው።

በኦሪት ከነበሩት አንዳንዶች የሚወዱትን ሰው ሞት በምስጋና ከተቀበሉ፣ በሐዲስ ኪዳን የምንኖር እኛማ እንዴት አብልጠን ልንበረታ ይገባን ይሆን?! ምክንያቱም አሁን ሞት ስሙ እንጂ ሥልጣኑ የለም። ሞት "እንቅልፍና መንገድ፣ ሽግግርና እረፍት፣ ሰላምና የጸጥታ ወደብ" ብቻ ሆኗል። የተኛን ሰው ስናይ መልሶ እንደሚነቃ ስለምናውቅ ውስጣችን በኃዘን አይረበሽም። ተስፋም አንቆርጥም። ከእኛ ወገን ስላንቀላፉትም አንዳንዶች ይህን እናስብ። ሞት ለክርስቲያኖች በሥጋ የሚያንቀላፉት ረጅም እንቅልፍ ነው።

"ነፍሴ ሆይ፥ ወደ ዕረፍትሽ ተመለሺ፥ እግዚአብሔር መልካም አድርጎልሻልና"
መዝ 116፥7

+++ "ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን" +++

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
የእግዚአብሔር ሰው ሰሎሞን ለአምላኩ ሕንፃ መቅደስን ሊያንጽ በተነሣ ጊዜ ፤ "በጥበብና በማስተዋል በብልሃትም የተሞላ" የናሱን ሠራተኛ ኪራምን ከጢሮስ አስመጥቶ ነበር። ከዚህም ጥበበኛ ጋር ሆኖ እጅግ አስደናቂ የሆነውን መቅደስ በታላቅ ጥንቃቄ አንጿል። በእውነት ይህን ሰሎሞን ያሳነጸውን ውብ መቅደስ ማየት ምንኛ ያጓጓ ይሆን? በእርግጥም መቅደሱንና የመሥዋዕቱን ሥርዓት የተመለከተች ንግሥተ አዜብ ማክዳ "ነፍስ አልቀረላትም" ነበር (1ኛ ነገ 10:5)።

ሆኖም ግን እግዚአብሔር በነቢዩ ኢሳይያስ አድሮ "ሰማይ ዙፋኔ ነው ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ ለእኔ ምን ዓይነት ቤት ትሠራላችሁ?" ብሎ መጠየቁ አልቀረም (ኢሳ 66:48)። ለጊዜው በረድኤት የሚያድርበትን መቅደስ ንጉሥ ሰሎሞን ውብ አድርጎ ቢያንጽለትም ፤ በኋላ ግን የሰውን ልጆች ለመቤዠት በአካል የሚያድርበትን ሕያው መቅደስ ማንም ማዘጋጀት አልቻለም ነበር። ስለዚህም "ልዑል የሰው እጅ በሠራችው አይኖርም" ተብሎ ተጻፈ (ሐዋ 7:50)። በመሆኑም መቅደሱን ላነጹ ለሰሎሞን እና ለኪራም ጥበብን የሰጠው ጥበበኛ "ለራሱን ቤት ሊሠራ ፣ሰባት ምሰሶዎችንም ሊያቆም" ፈቃዱ ሆነ። የመቅደሱንም መሠረት እንቁ አደረገ። ቤቱንም እጅግ በከበሩ ድንጊያዎች አነጸ።

ይህች በአምላክ እጅ የታነጸች ፣እግዚአብሔር በረድኤት ሳይሆን በአካል የሚያድርባት ሕያው መቅደሱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት። የተመሠረተችባቸውም አዕናቁ (እንቁዎች) ቅዱሳን ቤተሰቦቿ ናቸው። የታነጸችበትም የከበሩ ድንጊያዎች ንጽሕና ፣ቅድስና ናቸው።

"ይህች ዓለም አይቶ የማያውቃት በተስፋ ትጠበቅ የነበረችው ድንቅ አማናዊት መቅደስ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህች ምድር ላይ የታየችው በዛሬው ቀን ነበር"

ኪራም ያነጸው የሰሎሞንን መቅደስ መጎብኘት "ነፍስ የማያስቀር" ፣ልብን በሐሴት የሚሞላ ከሆነ ፤ በእግዚአብሔር እጅ የታነጸች ፣የአምላክ ጥበብ የፈሰሰባት እውነተኛ መቅደሱን የእመቤታችንን መወለድ የማየትና የመስማት የደስታ ጥጉ ምን ያህል ይሆን?

እንኳን ደስታን ወደ ዓለም ይዞ ለመጣ ተናፋቂው ለድንግል ማርያም ልደት አደረሳችሁ!!!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
ለማዳ እና አጫዋች ወፍ ለመግዛት ወደ ሱቅ የሄደ ሰው አንዲት የምትናገር ወፍ ለመግዛት ዋጋ ቢጠይቅ በጣም አስወደዱበት። "እንዴት ይህችን የምታህል ትንሽ ወፍ በዚህ ብር ትሸጣለች?" ብሎ ተገረመ። ከዚያ ወደ ቤቱ ተመልሶ ያቺ ሚጢጢ ወፍ ይህን ያህል ካወጣች ይሄንማ ብሸጠው ሀብታም ያደርገኛል" ሲል በጥራጥሬ ያፋፋውን ዶሮ ታቅፎ ወደዚያ ሱቅ በፍጥነት ሄደ። ከዚያም ለባለ ሱቁ እያሳየ "ይሄን ዶሮ ውሰደው ልሽጥልህ?" አለው። ባለሰቁም "ዋጋው ስንት ነው" አለው። ባለ ዶሮውም ፈርጠም ብሎ የበቀቀኗን ሁለት እጥፍ ብር ጠራበት። ይህን ጊዜ ባለሱቁ በጣም እየተበሳጨ "ጤነኛ አይደለህም እንዴ? እንዴት እንዲህ ትላለህ? በቀቀኗ እኮ በመጠን ብታንስም ስለምትናገር ነው የተወደደችው። አንተ ምን ልትል ነው?" ቢለው ባለ ዶሮው "አዎ ልክ ነው ያንተ ትናገራለች። የእኔ ግን ፈላስፋ ነች ታስባለች" አለው።

ማሰብ ወይስ መናገር? የቱ የተሻለ ዋጋ አለው?

ሰው ላይ ከተጣሉ ተፈጥሮአዊ ኃላፊነቶች ውስጥ አንዱ ማሰብ ነው። በአካል ትንሽ እና ደካማ የሆነውን ሰው ከግዙፋኑ እንስሳት በላይ የሚያሰለጥነውና ገዢያቸውም የሚያደርገው ይህ የለባዊነት (ምክንያተኝነት) ጸጋው ነው። ይሁን እንጂ ብዙ ሰው ይህን ውድ ጸጋ የሚጠበቅበትን ያህል ሲጠቀምበት አናይም። አንድ ጸሐፊ በቀልድ መልክ "ከምናገኛቸው ሰዎች ጥቂቶቹ የሚያስቡ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ስለማሰብ የሚያስቡ፣ የቀሩት ብዙዎች ደግሞ ከማሰብ ይልቅ ሞታቸውን የሚመርጡ ናቸው" ይላል። በእርግጥም "እኔ እንደማስበው" ብሎ ንግግሩን መጀመር የሚችለው ልዩው ፍጡር ሰው በንግግሩ ውስጥ የሚታየው ትልቁ ክፍተት ግን "አለማሰቡ" ነው።

ሐሳብ ትልቅ ኃይል አለው። በጎነትም ሆነ ክፋት የሚጀምረው ከማሰብ ነው። በሐሳብ ካልበደልህ በሥራ በደለኛ ልትሆን አትችልም። የሲዖልን በር አይተኸዋል? የገነትስ ደጅ የት እንደ ሆነ ጠይቀህ ታውቃለህ? መልሱን እኔ ልንገርህ፤ ሁለቱም ደጆች ያሉት ልብህ ላይ ነው። አስበህ በተናገርከው ቃል፣ ተናግረህ በፈጸምከው ተግባር ወይ የገነትን ወይም የሲዖልን በር ትከፍታለህ።

ሰው የተሰጠውን ትልቅ የማሰብ ጸጋ አለመጠቀሙ ብቻ ሳይሆን መጠቀም ሲጀምር ደግሞ የሚያስባቸው ክፉ ነገሮች የበለጠ ያሳዝናሉ። እንደውም አንዳንዶች "ጥሩ ካላሰብህ ብዙ አታስብ" የሚሉት ለዚህ ይመስላል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን "ብዙ አታስብ" ከሚለው ምክር የሚበልጥ ሌላ መፍትሔ አለው። ይኸውም ልብን ለእግዚአብሔር መስጠት።(ምሳ 23፥26) ልባችን የመልካሙ አምላክ ማደሪያ ከሆነ ከእርሱ የሚወጣው ሐሳብ ሁሉ መልካም እና የተቀደሰ ይሆናል። ያን ጊዜ ጠቢቡ እንደ ተናገረው አፋችን የሕይወት ምንጭ ከንፈሮቻችንም ደስ የሚያሰኝ ነገር ሁሉ የሚፈልቅባቸው ይሆናሉ።

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
1
"ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል" ማቴ 28፥7

ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ብዙ እና ጥቂት ሆነው ሳለ በተለያየ ጊዜ ራሱን ገልጦ አሳይቷቸዋል። አሁን ደግሞ አስቀድሞ በሴቶች በኩል "ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል" ብሎ ያስነገረውን ትንቢት ሊፈጽም፣ ዓሣ ለማጥመድ ወደ ገሊላ ባሕር ለወረዱ ለጴጥሮስና ለስድስቱ ወንድሞቹ የተገለጠበትን ሦስተኛ ታሪክ ዮሐንስ ይጽፍልናል።(ዮሐ 21፥1)

ቅዱስ ጴጥሮስ "ሰላም ለእናንተ ይሁን" የሚለውን የትንሣኤውን ጌታ ድምጽ ከሰማ ፣ የተጠራጠረው ቶማስ እጁን በጎኖቹ አግብቶ "ጌታዬ አምላኬ" ብሎ ሲያምን ከተመለከተ በኋላ "ዓሣ ላጠምድ እሄዳለሁ" ብሎ ሲናገር እናገኘዋለን።(ዮሐ 21፥3) ክርስቶስ ተላልፎ በተሰጠበት በሐሙስ ምሽት ከእሳት ዳር ተቀምጦ ያደረገውን ሊረሳውና ራሱን ይቅር ሊል ስላልቻለ፣ ጌታው ቀድሞ የሰጠውን የወንጌል መረብ ተወና የዓሣውን መረብ ጨብጦ ወደ ገሊላ ባሕር ሮጠ።(ማቴ 4፥19) በኃጢአት ምክንያት የተሰማው ኃፍረትና መሸማቀቅ ሐዋርያነቱን ትቶ በድሮ ማንነቱ ውስጥ ራሱን እንዲደብቅ አደረገው። የካደን ማን ለምስክርነት ይፈልገዋል በሚል ዓይነት ስሜት ለወንድሞቹ "ዓሣ ላጠምድ እሄዳለሁ" አላቸው።

ደስ የሚለው ነገር ግን ይህን አስቀድሞ የሚያውቅ ይቅር ባይ አምላኩ ጴጥሮስን "በገሊላ ቀድሞት ነበር"። በበደሉ ተሸማቆ የተወውን ሐዋርያነት ሥልጣን በፍቅሩ መማለጃነት መልሶ ሊሰጠው፣ አይገባኝም ብሎ ያስቀመጠውን የወንጌል መረብ ዳግመኛ ሊያሲዘው በገሊላ ባሕር ዳር ቀደመው። እኛም አንድ ኃጢአት ይኖረናል። መርሳት ያልቻልነው፣ ንስሐ እንኳን ብንገባበት ራሳችንን ይቅር ለማለት የተቸገርንበት፣ "ከዚህ በኋላማ..." እያሰኘ የድሮ መረብ አስይዞ ወደ ገሊላ የሚመልስ አንድ በደል ይኖረናል። ነገር ግን ጌታ ለቅዱስ ጴጥሮስ እንዳደረገው ለእኛም እንዲሁ ያደርጋል። ከባሕሩ ዳር ይጠብቀናል፣ "ትወደኛለህ" ብሎ ይጠይቀናል፣ ከዚያ በማይለወጥ ፍቅሩ ወልውሎ ሰንግሎ አፍረን ወደ ሸሸነው መንፈሳዊነት ይመልሰናል።

+++ ጌታችን በገሊላ ይቀድመናል! +++

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
ግንቦት 6/ 2015 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
2025/07/13 12:03:38
Back to Top
HTML Embed Code: