Telegram Web Link
የእግዚአብሔርን ፈቃድ ልትረዳ የምትችለው ሁልጊዜ አንተ በምትፈልገው መንገድ ብቻ እንዲሠራ ባለመጠበቅ ነው። አንዳንዴ በአንተ እና በአምላክህ ሐሳብ መካከል የሰማይና የምድር ያህል ልዩነት ሊኖር ይችላል። ራሱ ባለቤቱም "ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፥ እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው" ብሎናል።(ኢሳ 55፥9) "ፈቃድህ ይሁን" ብለህ ከጸለይህ በኋላ "የምትፈልገውን ብቻ በመጠባበቅ" ፈጣሪህን የፈቃድህ አገልጋይ አታድርገው። በጸሎትህ አምላክ የሚወደውን ወይም ፈቃዱን ማወቅ ከፈለግህ "አንተ የምትወደውን" እንደ ብቸኛ መልስ አትጠባበቅ።

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
ኅዳር 17/ 2015 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com

ቴሌግራም
https://www.tg-me.com/Dnabel
+++ ጸልየህ ልታደርገው ትችላለህ? +++

ማልዶ ቤተ ክርስቲያን ተሳልሞ ወደ ሥራ የሚሄድ አንድ መንፈሳዊ ሰው በጉዞው ከሌላ መንገደኛ ሰው ጋር ይገናኛል። ጥቂት እንደ ተጨዋወቱ ይህ በመንገድ ያገኘው ሰው ከደረት ኪሱ የሲጋራ ፓኮ በማውጣት አንዱን መዝዞ እንዲወስድ ይጋብዘዋል። ያም መንፈሳዊ ሰው "አይ ይቅርብኝ" ሲል እምቢታውን ገለጸ። ባለ ሲጋራውም "ኃጢአት ነው ብለህ ስላሰብህ ነው እምቢ ያልከኝ? ማጨስ እኮ ከአስጨናቂዋ ሕይወት ፋታ ለመውሰድና ራስን ዘና ለማድረግ ይረዳል። ግድ የለህም አንዱን ሞክር" እያለ ሊያግባባው ጣረ። በመጨረሻም መንፈሳዊው ሰው "ግድ የለም ለእኔ ይቅርብኝ። ባይሆን አንተ ይጠቅመኛል ካልህ በቃ ሲጋራውን ከመለኮስህ በፊት አንድ "አባታችን ሆይ" ጸልይና ጀምር" አለው። በዚህ ጊዜ ያ መንገደኛ ደንግጦ እንዲህ ሲል መለሰ "ጸሎት ጸልዬማ እንዴት እንዲህ አደርጋለሁ?!"

በጸሎት ልትጀምር የማትችላቸው ማናቸውም ነገሮች ለአንተ መልካም አይደሉም። በልብህ ኃጢአት እንድታደርግ የሚገፉፉህ ክፉ ሐሳብ ሲመጣ "ይህን ጸልዬ ማድረግ እችላለሁ?" ብለህ ራስህን ጠይቅ። ከጸሎት ጋር የማይጣጣም ከመሰለህ እርሱ ኃጢአት ነውና ተወው። ጸልዮ የሚዘሙት፣ ጸልዮ የሚሰርቅ፣ ጸልዮ ባልንጀራውን የሚሳደብ፣ ጸልዮ በወንድሙ ላይ ክፉ የሚያደርግ ማን ነው?

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
+++ ልሸፈንላችሁ? +++

ሙሴ ከሲና ተራራ ወርዶ ከሕዝቡ ጋር ሲገናኝ የፊቱን ማንጸባረቅ አይተው "ተሸፈንልን" ያሉት ሕዝቡ ናቸው። እርሱ "ከእግዚአብሔር ጋር ስነጋገር ቆይቼ እኮ አሁን መውረዴ ነው? ምነው የፊቴ ብርሃን አስቸገራችሁ? ልሸፈንላችሁ እንዴ?" አላለም። እንዲያውም ቅዱስ መጽሐፍ "ሙሴም ከተራራው በወረደ ጊዜ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ተነጋገረ የፊቱ ቁርበት እንዳንጸባረቀ አላወቀም ነበር" ነው የሚለው።(ዘጸ 34፥29) ለቅዱሳን እግዚአብሔር በፊታቸው የሚሥለው የክብር ብርሃን እነርሱን ለሚመለከታቸው እንጂ ለራሳቸው አይታወቃቸውም። እውነተኞቹ ቅዱሳን "ተሸፈኑልን" የሚባሉ እንጂ "ልሸፈንላችሁ" የሚሉ አይደሉም።

ጥቂት በጎ ሥራ ሠርተህ ጻድቅነትህን በግድ ለማሳየት አትሞክር። ሌሎች ተሸፈንልን ይበሉህ እንጂ፣ አንተ ራስህ "ልሸፈንላችሁ" እያልህ የዋሐንን አታስጨንቅ።

በአገራችን የሚታወቅ ተረት አለ። አንድ ጊዜ ትንኝ በሬ ቀንድ ላይ ቆመችና "ከብጄህ እንደ ሆነ ንገረኝና ልነሣልህ" አለችው። በሬውም "እንኳን ልትከብጅኝ መኖርሽንም አላወቅሁም" አላት።

"ጻድቃን እንደ ሆኑ በራሳቸው ለሚታመኑና ሌሎቹን ሁሉ በጣም ለሚንቁ ይህን ምሳሌ ነገራቸው" ሉቃስ 18፥9

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com

ቴሌግራም
https://www.tg-me.com/Dnabel
እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንኹት፥ እርስዋንም እሻለሁ፥ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ የዘላለም ማረፊያው በሆነች በእናቱ ፍቅር እኖር ዘንድ፤ እርሷን ደስ አሰኝ ዘንድ ፤ ያማረው የፊቷንም ብርሃን እመለከት ዘንድ፤ በዓለም ካሉት አእላፋት ዝና ይልቅ ልቤ የድንግልን ፍቅር ይመኛል፣ የዓለሙ ዝና ነፍስን ለሚያቆስል ትዕቢት አሳልፎ ስለሚሰጥ ምን ይጠቅመኛል? የድንግል ፍቅር ግን ዕረፍትና ጸጥታ ይሆነኛል፣ ወደ መዳን መንገድም ስቦ ያስገባኛል፤ ልቡናዬ የክብርሽን ገናንነት ይናገር ዘንድ ይወዳል፥ መላሴ ግን በኃጢአት ፍሕም የተበላ ኮልታፋ ሆኖ ተቸግሯል፤ የልሳኔን ልቱትነት አርቀሽ፥ እኔ ደካማ ባሪያሽን በምስጋናሽ ቃል የምትሞይበት የኃይል ቀን መቼ ነው? ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ እንደ ምትናፍቅ እኔም ምስጋናሽን እየተጠማሁ ያቺን ቀን እናፍቃለሁ። መቼ እደርሳለሁ? መቼስ አንቺን አመሰግንሻለሁ?

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com

ቴሌግራም
https://www.tg-me.com/Dnabel
+++ የጽሙና ጊዜ አለህ? +++

የቆርቆሮና የብረት ጩኸት ጋጋታ ባለበት ውብና ለስላሳ የሆነውን የዋሽንት ድምጽ መስማት የሚቻለው ማን ነው? ሁከትና ረብሻ በሚነግስበት፣ የማይቋረጥ ግፊያና አለመረጋጋት ባለበት የሰዎች ግርግር ውስጥ ሆነህ እንዴት የመንፈስ ቅዱስን ድምጽ ልትሰማ ትችላለህ? የእግዚአብሔርን ድምጽ በአውሎ ነፋስ ፋጨት፣ በምድር መናወጥ፣ በሚያስገመግም የእሳት ድምጽ ውስጥ አታገኘውም። እርሱ የሚናገረው ከእነዚህ ሁሉ በኋላ በሚሆነው "ትንሽ የዝምታ" ጊዜ ነው።(1ኛ ነገ 19፥12)

ልክ የመድኃታችንን የልብሱን ጫፍ በስውር ነክታ ከቁስሏ እንደ ተፈወሰችው ሴት፣ አንተም የነፍስህን ቁስል ለማድረቅ በመቅደሱ የሞላውን የጌታን የልብሱን ዘርፍ በምሥጢር የምትዳስስበት የብቻ ጊዜ ያስፈልግሃል?

ከእሾህ ወይን ከኩርንችትም በለስ እንደማትለቅም፣ ራስህን ከዚህ ዓለም ሁከት የምትለይበት ጊዜ ሳይኖርህ እውነተኛ የነፍስ መጽናናትን ልታገኝ አትችልም። ለዚህም ነው ጌታችን በወንጌል "ስትጸልይ ወደ እልፍኝህ ግባ፤ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ" በማለት ያስተማረን። ላዘነችው ነፍስህ መጽናናትን፣ ለልቡናህ ዕረፍትን ትፈልጋለህ? ስለ ኃጢአትህ የምታፈሰው የንስሐን እንባስ ትሻለህ? እንግዲያውስ ከሰው ርቀህ በርረህ ወደ ፈጣሪ የምትሄድበት የጽሙና ጊዜ ይኑርህ።

ጌታን ያጠመቀውና ለብዙዎች በብርሃኑ ደስ የሚያሰኝ "የሚነድ መብራት" የነበረው ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ ሁሉ በፊት ብቻውን ከአምላኩ ጋር በበረሃ ነበር። የሐዲስ ኪዳኑ ባለ ራእይ ቅዱስ ዮሐንስ እነዚያን ሁሉ ሰማያዊ ምሥጢራት የተመለከተው ብቻውን በፍጥሞ ደሴት ሆኖ ነው። ስሙን በአሕዛብ፣ በነገሥታቱና በእስራኤል ልጆች ሁሉ ፊት ይሸከም ዘንድ የተመረጠው ቅዱስ ጳውሎስ፣ ከሁሉ አስቀድሞ ግን የመረጠው አምላኩ መንፈሳዊውን ኃይል ያስታጥቀው ዘንድ የገዛ ድክመቶቹን ተሸክሞ ብቻውን ወደ አረብ በረሃ ገስግሶ ነበር።

ያንተስ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ በመንፈስ የምትጎለምስበት በረሃህ ፣ እንደ ወንጌላዊው ዮሐንስ ጣዕመ መንግስተ ሰማያትን የምትዘከርበት ፍጥሞ ደሴትህ፣ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ በነፍስ ታድሰህ የምትወጣበት አረባዊ ገዳምህ የት ነው? መቼ መቼስ ወደዚያ ትወርዳለህ?

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
+++ ማሰብና ማድረግ እኩል ናቸው? +++

በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ዘመን የኖሩ እጅግ ለእምነታቸው የሚቀኑ ጽኑዕ ክርስቲያኖች ነበሩ። ታዲያ በአንድ ወቅት ኃጢአትን በማሰብ እና በማድረግ መካከል ስላለው ልዩነት አንሥተው ይከራከሩ ጀመር። ብዙዎቹም "ማሰብና ማድረግ ምንም ልዩነት የላቸውም" የሚል የሚል አቋም ነበራቸው። በስተመጨረሻም ይህን ጥያቄ እንዲመልስላቸው ወደ ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይዘው ቀረቡ። ቅዱሱ በምሳሌ ሊያስተምራቸው ስለ ፈለገ አንድ ቀን ሙሉ ምንም ምግብ ሳይቀምሱ ቆይተው ማታ ለእራት እርሱ ዘንድ እንዲመጡ ጠራቸው። በቤቱም ለዓይን ያማረ ለመብላት ደስ የሚያሰኝ ፈታኝ ማዕድ እንዲያዘጋጁ ለአርድእቱ ተናገረ። እነርሱም እንዳላቸው አዘጋጁ።

እንግዶቹም በመጡ ጊዜ በየቦታቸው ተቀመጡ። የተዘጋጀውም መዓድ ከፊት ቀረበ። የምግቡ መዓዛ የምግብ ፍላጎት የሚከፍት ብቻ ሳይሆን የሰዎቹን ረሃብ የሚያባብስም ጭምር ነበር። ከዚያም ቅዱስ ዮሐንስ በቤቱ የሚያገለግለውን ዲያቆን ከመዝሙራት እያወጣ እንዲያነብ አዘዘው። ዲያቆኑም ረዘም ላሉ ሰዓታት ማንበቡን ቀጠለ። እንግዶቹ ግን ከመጎምዠት ብዛት በአፎቻቸው ምራቅ ሞላ። ጸሎቱ አልቆ እስኪመገቡ መቆየት ጣር ሆነባቸው።

አሁን ጸሎቱ ተጠናቋል። ይሁን እንጂ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ግን እንግዶቹን ለመዓዱ እንዲቀመጡ በመጋበዝ ፈንታ "በቃ ወደየቤታችሁ በሰላም ግቡ" ብሎ አሰናበታቸው። ወደ ቤቱ ተጠርተው የመጡት እንግዶችም ደነገጡ። ይህን ያየው ቅዱሱ "ምነው ግራ የገባችሁ ትመስላላችሁ? ምግቡን በደንብ አላያችሁትም? ልትበሉስ እጅግ ተመኝታችሁ አልነበረም?" ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም "አዎን" አሉት። አፈወርቅም "ጥሩ፤ እንግዲያውስ እንደ በላችሁ ይቆጠራላ" ቢላቸው ሁሉም ፈገግ አሉ። በዚህ ጨዋታ መካከል የእነዚያ ክርስቲያኖች ጥያቄ በሚገባ ተመለሰላቸው።

ክፉን ነገር በማሰብና በማድረግ መካከል ያለው ልዩነት ምን እንደ ሆነ በዚህ ታሪክ ውስጥ ግልጽ ሆኖ ይታያል። ክርስትና ሐሳብ እና ሥራን መቀደስ ነው። ነገር ግን የሐሳብ ንጽሕና ባይኖርህ "ማሰብ ከማድረግ ጋር እኩል አይደል!" ብለህ በኅሊናህ የቋጠርከውን ክፋት ለማድረግ ራስህን አታደፋፍር። ያሰብከውን እስካልፈጸምህ ድረስ አሁንም ከኃጢአት ወጥመድ የማምለጥ እድሉ በእጅህ ነው።

"ኃጢአት በደጅ ታደባለች፤ ፈቃድዋም ወደ አንተ ነው፥ አንተ ግን በእርስዋ ንገሥባት" ዘፍ 4፥7

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
አንድ በጣም ትልቅ ቆሻሻ የጫነ ጋሪ የሚገፋ ሰው ወደ ቤትህ መጥቶ "እባክህ በርህን ክፈትልኝና ይህን ቆሻሻ አንተ ቤት ላራግፈው?" ቢልህ፣ "ውይ የሚጥልበት ቢያጣ ነው። ባይቸገር ወደ እኔ አይመጣም ነበር" ብለህ ደጅህን ከፍተህ ታስገባዋለህ? በፍጹም፤ እንደውም "እንዴት ብታስበኝ ነው? ምነው ስታየው ቤት አልመሰለህም? እንዴት ሰው በሚኖርበት ቤት ቆሻሻ ካልደፋሁ ትላለህ? ስትል ለጠብ ትጋበዛለህ። መደፈርህ እያንገበገበህ "እምቢ!" ብለህ ትቆጣለህ። በእርግጥም ያስቆጣል።

ግን ሌላ የሚከፋ ሽታ ያለው ቆሻሻን ጭኖ ለመጣ ባላጋራ እኮ በፈቃድህ የከፈትከው ቤት አለ። የምን ቤት? ልብህ ነዋ፤ ማን ይኖርበታል አልኸኝ? እግዚአብሔር ነዋ። አንተ ለመኖሪያ ቤትህ ጽዳት የምትጠነቀቀውን ያህል የያዕቆብ አምላክ ለሚያርፍበት ኅሊናህ ተጠንቅቀህ ታውቃለህ? ሰይጣን ጭኖ የሚያመጣውን የኃጢአት ቆሻሻ ሁሉ እሺ ብለህ ወደ ልብህ በማስገባት የፈጣሪህን መቅደስ ለምን ታቆሽሻለህ? ንጹሑ እግዚአብሔር የሚያድርበትን ቤት ሊያቆሽሽ በመጣ ሰይጣን ላይ እንዴት አልተቆጣህም? ድፍረቱ ለምን አላብከነከነህም?

እግዚአብሔር አንተ ልትኖርበት ከምትፈልገው ንጹሕ ቤት የበለጠ ጽዱ መቅደስ የማይፈልግ ይመስልሃል?

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com

ቴሌግራም
https://www.tg-me.com/Dnabel
+++ ስለ ታሰሩ ሰዎች +++

አንዳንድ ነገሮች አሉ። እንዴት እንደምንጀምር እንጂ እንዴት እንደምናቆም ጨርሶ የማናውቃቸው። አጀማመሩን ስላወቅን እና ስለቀለለን ብቻ አቋቋሙም የዚያኑ ያህል ቀላል የሚመስለን። እውነታውስ? በነጻ ፈቃዳችን መርጠን እንጀምራለን። ነገር ግን ያ የተሳሳተውን ነገር መምረጥ በመቀጠላችን የመረጥነው እርሱን ያለመምረጥ ነጻነታችንን እስኪነጥቀንና ጌታ እስኪሆንብን እንደርሳለን።

በሱስ የተያዘ ሰው ከዚያ ነጻ ለመሆን ማናቸውንም ነገር ቢያደርግ ደስ ይለዋል። ግን ሱሱ ልማድ ሆኖበት አንቆ ይይዘዋል። በዚህ ከቀጠለ መጨረሻው ሞት እንደ ሆነ ቢያውቀውም፣ ራሱ በፈጠረው ነገር እንዲህ በመሰቃየቱ ምክንያት መልሶ ራሱን ቢጠላውም በእጁ የያዘውን የመጠጥ ብርጭቆ ግን ወርውሮ መስበር አይችልም። መላ ሰውነቱን ስለተቆጣጠረው እርሱ የጨበጠው ጠርሙስ እስረኛ ነው።

ይህን ግን ስለ መጠጥ ብቻ የምንናገር አይደለም። በጥቂቱ ብንጀምራቸውም በኋላ ግን አርቀን መጣል ያልቻልናቸው እና ሱስ ስለሆኑብንን ኃጢአቶች ሁሉ ይመለከታል።

እንዲህ በራሳችን ወህኒ ለታሰርን ምስኪኖች ቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜ በቅዳሴዋ "እግዚአብሔር ከእስራታቸው ይፈታቸው ዘንድ ስለ ታሰሩ ሰዎች እንማልዳለን" ስትል ትማልዳለች። እኛም ከመዝሙረኛ ጋር "አቤቱ ስምህን አመሰግን ዘንድ፥ ነፍሴን ከወህኒ አውጣት" እያልን ልንማጸነው ይገባል።(መዝ 142፥7) እኛ በራሳችን ላይ ያደረግነው የትኛውም ዓይነት እስራት የሲኦልን ደጆች ከሰባበረው የብረቱንም መወርወሪያ ከቆረጠው ከክርስቶስ ኃይል አይበልጥም። ስለዚህ ከፈቀድንለትና አብረነው ሠራተኛ ለመሆን ከወሰንን ዛሬም ከገባንበት ሲኦል ሊያወጣን የታመነ አምላክ ነው።

ሰው በራሱ ፍላጎት ብቻ ወደ ኃጢአት ጉድጓድ መግባት ቢችልም ያለ እግዚአብሔር ረድኤት ግን ከገባበት መውጣት አይችልም። ስለዚህ "እንዴት ከገባኹበት ጉድጓድ በራሴ መውጣት አልቻልኩም?!" እያልህ አትበሳጭ። ይልቅ ረድኤተ እግዚአብሔርን እየለመንህ በምትችለው ሁሉ ታገል።

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
+++ የተሰጠ እንባ +++

የሰው ልጅ ደካማ ነው። በውስጡ የሚፈራረቁበትን ስሜቶች ተሸክሞ ለማቆየት ይቸገራል። በጣም ሲደሰት ወይም በጣም ሲያዝን እነዚህን ስሜቶች የሚያስተነፍስበት ሳቅ ወይም ልቅሶ ይፈልጋል። ይህ ካልሆነ ግን ሰውነት ይጨነቃል። አዲስ የወይን ጠጅ እንደ ገባበት አሮጌ አቁማዳ እቀደድ እቀደድ ይላል። ከባዱን የስሜት ሰደድ እሳት የሚያበርድበት ትኩስ እንባ ከዓይን ካላዘነመ ዕረፍት የሚባል ነገር አያገኝም። ዓይን አላነባ ሲል የውስጥ ሕዋሳት የሕመም እንባ ማንባት ይጀምራሉ።

የሕክምና ሰዎች እንደሚናገሩት ሦስት ዓይነት እንባዎች አሉ። የመጀመሪያው ዓይን ውስጥ ባዕድ (ቆሻሻ) ነገር ሲገባ የምናነባው ቅጽበታዊ እንባ (Reflex tear) ሲሆን፣ ሁለተኛው ዓይናችን እንዳይደርቅና ራሱን ከinfection ለመከላከል ሲል የሚያመነጨው የማይቋረጥ እንባ (Continuous tear) ነው። ይህም እንባ 98% ውኃ ነው። ሦስተኛውና በጣም ጠቃሚው እንባ ደግሞ የውስጥ ስሜት ፈንቅሎ የሚያወጣው እንባ (Emotional tear) ነው። ተጨማሪ ጥናቶች ቢፈልግም የዘርፉ ሊቃውንት እንደሚሉት በተለይ በኃዘን ጊዜ የሚፈስሰው እንባ ከሌሎቹ እንባዎች በተለየ በሰውነት ውስጥ የተለቀቀውን stress hormone ይዞ በማስወጣት ውጥረትን ለመቀነስ ትልቅ ፋይዳ አለው። ከዚህ እንባ ጋር ተያይዘው በሰውነት ውስጥ የሚለቀቁት እንደ oxytocin እና endorphins ያሉት ሆርሞኖች ደግሞ መረጋጋትና ዕረፍትን እንድናገኝ ያግዙናል።

ይህን የእንባ ጸጋ ለእኛ የሰጠ የሰውን ድካም የሚያውቅ እግዚአብሔር ነው። ልቅሶውንም ለውስጥ ውጥረት ማስተንፈሻ ብቻ ሳይሆን፣ የነፍሳችንን ጉድፍ የምናጠራበትና ወደ እርሱ ይዘን የምንቀርበው የተወደደ መባ አደረገልን። የፈጣሪን የምሕረት ልቡን የምናውክበትና ፈጥኖ እንዲታረቀን ደጅ የምንጠናበትን የእንባ ምንጭ እርሱ ባለቤቱ ከዓይናችን ሥር አኖረ።(መኃል 6፥5) ሊቁ ዮሐንስ ዘሰዋስው እንደ ተናገረው ይህንንም እንባ ወደ ሰማይ ለምንወጣበት የብርሃን መሰላል አንደኛው እርከን አድርጎ ሰጠን።

የምትወደውን ሰው አጥተህ የምታነባ አንተ ሰው "እንዲህ ሳዝን ወዴት አለህ?" ብለህ ፈጣሪህን አትክሰስ። እግዚአብሔርን እንባህ ውስጥ ፈልገው ታገኘዋለህ። የውስጥህን ኃዘን ከሚያበርድበትና ስብራትህን ከሚጠግንበት መንገዶቹ አንዱ "በሰጠህ እንባ" ነው።

"በደሌንና ነውሬን የሚያጥብ ዕንባ ስጠኝ። አቤቱ አንተን የሚያገለግል ዕንባን ስጠኝ። አቤቱ ልዩ ዕንባን ስጠኝ"
(ውዳሴ አምላክ)

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
+++ "ስንሞት ያመናል እንዴ?" +++

ሕፃናት መጠየቅ ይወዳሉ። አንዴ መጠየቅ ከጀመሩ በኋላ ደግሞ ከእነርሱ የሚወጣው "ለምን ሆነ?" የሚለው የጥያቄ ዝናብ እንዲህ በቀላሉ ቶሎ የሚያባራ አይደለም። እኛም በእነዚህ ጥያቄዎቻቸው ቶሎ ተሰላችተን ወይም ተበሳጭተን ይሆናል። ይሁን እንጂ ጉዳዩ ግን የሕፃናቱ አዲስ አእምሮ ራሱን የሚያሳድግበትና የነገ ማንነታቸውን የሚቀርጽበት ወሳኝ ሂደት ነው። የነገ ወጣቶችን ማንነት የሚቀርጹት ዛሬ "ለምን?" እያሉ ለሚጠይቁ ሕፃናት የምንመልሳቸው መልሶች ናቸው። ስለዚህ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባናል።

በጠና የታመመ ሕፃን ልጅ ያላት አንዲት እናት ነበረች። ይህች እናት በምትችለው ሁሉ ልጇን አሳክማና ተንከባክባ ለማዳን ብትጥርም፣ ይህ ልፋቷ ግን ሊሳካላት አልቻለም። ልጇን የያዘው በሽታ መድኃኒት ስላልነበረው ወደ ሞት አፋፍ አቅርቦታል። ታዲያ አንድ ቀን ሕፃኑ ልጅ እናቱን እንዲህ ሲል ጠየቃት :- "እናቴ፣ መሞት ምን ይመስላል? ስንሞት ያመናል እንዴ?"

በእናትየው ዓይኖች እንባዎች ሞሉ። ፊቷም በኃዘን ደፈረሰ። የረሳችው ነገር ያለ ይመስል "ቆይ መጣኹ" ብላ ሮጣ ከክፍሉ ወጣች። ብቻዋን ስቅስቅ ብላ አለቀሰች። ልጇ የጠየቃትን ጥያቄ መመለስ እንዳለባት ብታውቅም ለዚህ ለጋ አእምሮ እንዴት አድርጋ መልስ እንደምትሰጥ ግራ ገብቷታል። እንደ ምንም ራሷን አረጋግታና ጥበቡን እንዲሰጣት ወደ ፈጣሪዋ ተማጽና ተመልሳ ወደ ልጇ ክፍል ገባች።

ሕፃኑ መልሱን በጉጉት ይጠብቃል። እናትየውም የውስጧን ኃዘን ለመሰወር ለይምሰል ፈገግ ብላ እንዲህ አለችው "ልጄ፣ ታስታውሳለህ አንድ ጊዜ ጎረቤት ያለ ጓደኛህ ቤት ሄደህ ስትጫወት አምሽተህ ስለደከመህ በዚያው እንቅልፍ ወስዶህ ነበር። ከዚያም በማግስቱ ግን ስትነቃ ራስህ ያገኘኸው በመኖሪያ ቤታችን ውስጥ ስለሆነ 'እንዴት እዚህ መጣኹ?' እያልክ ስትጠይቀኝ ነበር። እኔም አባት ወደዚያ መጥቶ በጥንካራ ክንዶቹ ተሸክሞህ የአንተ ወደ ሆነው ቤትህ እንዳመጣህ ነግሬሃለኹ። አስታወስክ?"

ልጅየው :- "አዎን እናቴ"

እናትየው ቀጠለች :- "የኔ ልጅ፣ ሞትም እንደዚሁ ነው። እኛ መኖሪያችን ባልሆነች በዚህ ዓለም ሆነን እናንቀላፋለን። የሰማይ አባታችን እግዚአብሔር ደግሞ ብርቱ በሆኑ እጆቹ አቅፎ ወደ ሰማይ ይወስደናል። ከዚያም ነግቶ እንደ ገና ስንነቃ ራሳችንን በገዛ አባታችን ቤት ውስጥ እናገኘዋለን" አለችው።

እውነት ነው! ሞት ለክርስቲያኖች ሁሉ የሚኖረው ትርጉም ይህ ነው። ከእግዚአብሔር ተልከን ወደዚህ ዓለም እንደ መጣን ወደ እርሱ መመለሳችን ደግሞ የማይቀር ነው። ሞት ማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ "ድንኳን" ብሎ ከገለጸው ከጊዜያዊው መቆያችን ወደ እውነተኛው መኖሪያ አገራችን መሸጋገር ነው።

በ2ኛው ክፍለ ዘመን የነበረው ግሪካዊው ፈላስፋ አርስጣደስ በጊዜው አዲስ ሃይማኖት ስለሆነበት ስለ ክርስትና እና ይህ የክርስትና እምነት በሞት ላይ ስላለው እሳቤ ለአንድ ወዳጁ በጻፈለት ደብዳቤ ላይ እንዲህ የሚል ንግግር አስፍሮ ነበር። "ከክርስቲያኖቹ ውስጥ አንድ ጻድቅ የሆነ ሰው ከዚህ ዓለም በሞት ቢለይ ምእመናኑ ደስ ይሰኛሉ። ለፈጣሪያቸውም ምስጋናን ያቀርባሉ። ያም ሰው ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላ ቅርብ ሥፍራ የተሸጋገረ ይመስል ሰውነቱን በመዝሙራትና በምስጋና አጅበው ይሸኙታል" ይላል። ክርስትና እንዲህ ነዋ!

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም ክርስቲያኖች በሞት ላይ ሊኖራቸው ስለሚገባ እይታ ሲናገር "ከእኛ መካከል አንድ ሰው በሞተ ጊዜ፣ የማያምነው ሬሳ ሲያይ ክርስቲያኑ ግን ያንቀላፋ ሰውነት ይመለከታል። ያላመነው "የሞተው ሰው ሄደ" ይላል። በርግጥ በዚህ እኛም እንስማማለን። ነገር ግን ወደ የት እንደሚሄድም እናውቃለን። የሚሄደው ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ጴጥሮስ እንዲሁም ሌሎች የቅዱሳን ማኅበር ወደ አሉበት ነው። በኋላም ተስፋ መቁረጥ ባለበት እንባ ሳይሆን፣ በክብርና በማንጸባረቅ እንደሚነሣ እናስባለን!"

+++ "ለባሪያዎችህ ሞት የለባቸውም ፍልሰት እንጂ" +++

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
"ማርያም ሆይ፣ የሐናን ጡት እየጠባሽ ወደ ቤተ መቅደስ በገባሽ ጊዜ ያገኘሽ ያለ እናት ማደግ ያሳዝነኛል፤ ዳግመኛም በደመና የሚጫን የእሳት አበባ የለበሰ ፋኑኤል እንደ አባት ከመላእክት ጋር መናን እየመገበሽ በቅድስና የማደግሽ ምሥጢር ያስደስተኛል"

አባ ጽጌ ድንግል

እንኳን ለእመቤታችን ወደ መቅደስ የመግባት በዓል በሰላም አደረሰን!!!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com

ቴሌግራም
https://www.tg-me.com/Dnabel
+++‹‹አትፍረዱ አይፈረድባችሁምም›› ሉቃ 6፡37+++

ብዙ ጊዜ ምንም ዓይነት የጥፋተኝነት ስሜት ሳይሰማን ከምንሠራቸው ኃጢአቶች መካከል አንዱ ‹‹በሌሎች ላይ መፍረድ›› ነው፡፡ ደግሞ ነገሩን ከባድ የሚያደርገው የምንፈርድባቸው የወንድሞቻችንን ውድቀት በዓይናችን ማየታችን በጆሯችን መስማታችን ነው፡፡ ያዩትን አይተው፣ የሰሙትን ሰምተው ሲጨርሱ ወዲያው አለመፍረድ እንደ ተራራ የረጋ ትልቅ ሰብዕናን ይፈልጋል፡፡ ትሑት የሆነ ሰው የሌሎች ሰዎችን ድክመት ለማየት የሚገለጥ ዓይን የለውም፡፡ ዘወትር ራሱን እየመረመረ ድክመቶቹን በመቁጠር ላይ ይጠመዳል፡፡ ዓይኖቹም እንደ አሸዋ በበዛው በገዛ ኃጢአቱ ላይ ብቻ ናቸው፡፡ ደግሞ ወደ ሌላው ከተመለከቱ ሊያመሰግኑ እና ሊራሩ እንጂ ሊንቁና ሊፈርዱ አይደለም፡፡

በወንድሞች ላይ መፍረድ የእግዚአብሔር የሆነውን የጌትነቱን ንብረት እንደ መስረቅ፣ በክርስቶስም የፍርድ ዙፋን ላይ ራስን እንደማስቀመጥ ይቆጠራል፡፡ ታዲያ ከዚህ በላይ ድፍረት፣ ከዚህ የሚበልጥ ኃጢአትስ ከየት ይገኛል? አበው ‹ሌሎች ላይ መፍረድ› የትዕቢት ታማኝ ልጅ ሲሆን፣ መጋቢና አሳዳጊውም እርሱው (ትዕቢት) እንደ ሆነ ይናገራሉ፡፡ ራስን መውደድ እና በራስ አስተዋይነት ላይ መደገፍ ሌላው ላይ ጨክኖ ከመፍረድ እንደሚያደርስም ያስተምራሉ፡፡ በርግጥ በሌሎች መፍረድ የሚወድ ሰው ‹‹ክፉ ሲደረግ ተመልክቼ ማለፍ አልችልም!›› እያለ ለከሳሽነቱ ምክንያት ይደረድር ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ በሰዎች ላይ የመፍረድ ኃጢአት ምንጩ የሌሎች ደካማ ምግባር ሳይሆን የተመልካቹ (የፈራጁ) የልብ ክፋት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ የልብ ቅንነቱ ቢኖርማ በተሳሳተ ወንድሙ ፊት ቆሞ ወይ የራሱን ድክመት እያሰበ የሚያለቅስ፣ አልያም ደግሞ ለወደቀው ወንድሙ እየራራ የሚመክርና የሚጸልይ ይሆን ነበር፡፡

በሌሎች መፍረድና አቃቂር ማውጣት የለመደ ሰው ዓለሙ ሁሉ በእርሱ ፊት ሞኝ ሆኖ ይታየዋል፡፡ ሰው ሁሉ አስተዋይነት በጠፋበት ሰፊ ጎዳና ሲርመሰመስ፣ እርሱ ግን ከፍ ካለው የብስለት ሰገነት ላይ እንደ ቆመ ስለሚሰማው፣ ቁልቁል እያየ የሚሰጠው እርማትና የትዝብት እይታው አይጣል ነው፡፡ ፈራጅ ‹እኔ ተሳስቼ ይሆን?› የሚል ትሑት ሕሊና የለውም፡፡ ልክ በአገጩ ላይ ያለው ሪዝ (ጽሕም) ከመቆሸሹ የተነሣ በፈጠረው መጥፎ ጠረን በሄደበት ሁሉ አፍንጫው ሲረበሽ (መጥፎ ጠረን ሲሸተው) ‹ዓለሙ ሁሉ ሸቷል› እንዳለው ሰው፣ በራሱ ድክመት ምክንያት በተፈጠረበት የእይታ መንሸዋረር ሁሉን ሲተች በሁሉ ሲፈርድ ይኖራል፡፡ የሥነ ልቡና ሳይንሱም እንደሚናገረው አንዳንድ ጊዜ በራስ ውስጥ ያለ የዕውቀት እና የልምድ ክምችት እያነሰ ሲመጣ፣ በሰው ፊት ዝቅ ብሎ ላለመታየት ሲባል በሁሉን ፈራጅና ነቃፊነት መጋረጃ ራሳችንን ልንከልል እንሞክራለን። ይህም አንዱ የሰብዕና መቃወስ (personality disorder) ምልክት ነው።

ቅዱስ አንስታስዮስ ዘሲና ‹‹ማንም ላይ አለመፍረድ››ን በተመለከተ በአንድ ወቅት በገዳሙ ይኖር ስለ ነበረ ደግ መነኩሴ ታሪክ የተናገረውን አንሥተን ጽሑፋችንን እንቋጭ፡፡ ይህም መነኩሴ እርሱ በሚኖርበት ገዳም እንዳሉት ሌሎች መነኮሳት ከፍ ያለ ትጋት አልነበረውም፡፡ ታዲያ የሚሞትበት ቀን ደርሶ በአልጋው ላይ ሳለ ከሞት ፍርሐት ይልቅ በፊቱ ላይ የሚነበበው ታላቅ ደስታ ነበር፡፡ በሁኔታው የተገረሙት በዙሪያው የተቀመጡ መነኮሳትም ‹‹ወንድማችን ሆይ! ሕይወትህን በስንፍና (ትጋት ሳታበዛ) እንዳሳለፍክ እናውቃለን፡፡ አንተስ ይህን ስታውቅ በዚህ በመጨረሻው ሰዓት ስለ ምን ደስተኛ ሆንክ? ምሥጢሩን ልናውቅ አልተቻለንም›› ሲሉ ጠየቁት፡፡ ያም ደግ መነኩሴ ‹‹አዎን! ክቡራን አባቶቼ! ሕይወቴን ሁሉ በስንፍና እና በእንቅልፍ ነው ያሳለፍኩት፡፡ ነገር ግን አሁን በዚህች ሰዓት መላእክት መነኩሴ ከሆንኩበት ጊዜ ጀምሮ የሠራኋቸው ሥራዎች ሁሉ የተመዘገቡበትን አንድ መጽሐፍ አምጥተውልኛል፡፡ ይህንንም መጽሐፍ ስመለከት በማንም ላይ እንዳልፈረድኩ፣ ማንንም እንዳልጠላኹ፣ በማንም እንዳልተቆጣኹ ተረዳኹ፡፡ ስለዚህም ‹አትፍረዱ አይፈረድባችሁምም› የሚለው የጌታዬ ቃል በእኔ ላይ እንደሚፈጸም ተስፋ አደረኩ፡፡ በዚህም ቅጽበት ይህችን ትንሽ ሕግ ስለፈጸምኩ ሌላው ሁሉ የዕዳ ጽሕፈቶቼ ተቀደዱልኝ›› አላቸው፡፡ ይህንንም ከተናገረ በኋላ ነፍሱ ከሥጋው ተለየች፡፡ መነኮሳቱም በምክሩ ተምረው የእግዚአብሔርን ሥራ እያደነቁ በምሥጋና ቀበሩት፡፡

በእውነትም ‹‹አትፍረዱ አይፈረድባችሁም›› የሚለው የመድኃኒታችን ቃል በዚህ ታሪክ ውስጥ ትክክለኛ ትርጉሙን አግኝቷል፡፡ በወንድሞች ድክመት አለመሳለቅና በውድቀታቸው አለመፍረድ ወደ ዘላለማዊው እሳት ከመጣል ያድናል፡፡

+++እግዚአብሔር በሰው ያልፈረዱ ቅዱሳን ካሉበት ገነት በቸርነቱ ያግባን!+++

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
+++ "አሁንስ ተስፋዬ ማን ነው?" +++

በሕይወትህ ውስጥ በጣም የሚያስፈራህ ነገር ምንድር ነው? ተብለህ ብትጠየቅ ምን ትመልሳለህ? "ሞት" ልትል ትችላህ። በእርግጥ ላልተዘጋጀን ኃጥአን የሞታችን ቀን መጠየቅን ወደሚወድ አምላክ የምንሄድበት ዕለት በመሆኑ እጅግ የሚያስፈራ ቀን ነው። ይሁን እንጂ ለሰው ከተስፋ ቢስነት በላይ የሚያስፈራው ነገር የለም። ሰው ተስፋውን ያጣ ቀን ሁሉ ነገሩን ያጣል። የሚያየው ሁሉ ትርጉም የለሽ ይሆንበታል። እሳቷ ፀሐይ ጥቁር ዐለት ትመስለዋለች፣ ጣፋጩ ይጎመዝዘዋል፣ የቀናው ይጎረብጠዋል። የመኖር ጉጉቱ ሁሉ ይጠፋል። ተስፋ ስትቆርጥ ሞት ወደ አንተ እስኪመጣ ድረስ አትጠብቅም። አንተ ወደ ሞት ትገሰግሳለህ። ታዲያ ለሰው ልጅ "ተስፋ ከመቁረጥ" በላይ ምን የሚያስፈራ ጠላት ሊኖረው ይችላል?

በሰው ሕይወት ውስጥ "ተስፋ" ትልቅ ገፊ ኃይል ነው። ማናቸውንም የዕለት ሥራዎቻችንን የምናከናውነው ባለ ተስፋ ፍጥረት ስለሆንን ነው። ለዚህም ነው መዝሙረኛው "ሥጋዬም ደግሞ በተስፋ ታድራለች" ሲል የሚዘምረው።(መዝ 16፥9) ደስታም ያለው በተስፋ ውስጥ ነው። ሰው በወደቀ ጊዜ አዝኖ የማይቀረው "እነሣለሁ" ብሎ ተስፋ ስለሚያደርግ ነው። በገጠመው ከባድ ኃዘን የማይሰበረው የተስፋን ምርኩዝ ስለሚይዝ ነው። ይህ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ሊደገፈው የሚገባ የማይሰበር የተስፋ ምርኩዝ ማን ነው? ይህ ሊጠፋ የሚጤሰውን የተስፋ ጥዋፍ እንደ አዲስ የሚያበራው፣ ተቀጥቅጦ የደቀቀውንም የተስፋ ሸንበቆ ጠግኖ ወደ ቀድሞ ማንነቱ የሚያድሰው ኃያል እርሱ ማን ነው?

"መድኃኒታችን እግዚአብሔር ተስፋችን ኢየሱስ ክርስቶስ" አይደለምን!!! (1ኛ ጢሞ 1፥1)

ክርስቲያኖች በራሳቸው ማስተዋል ወይም በሀብታቸው አይደገፉም። እንደ እነርሱ ተሰባሪ በሆነ ሰው ላይም ተስፋቸውን አያደርጉም። የክርስቲያን ተስፋው "የተስፋ አምላክ" ክርስቶስ ነው።(ሮሜ 15፥13) ክርስቶስን ለምን ተስፋ እናደርጋለን? "ሁሉ በእርሱ ስለሆነ፤ ከሆነውም አንዳች እንኳን ያለ እርሱ የሆነ" ስለሌለ፣ ኃይልና ችሎታ በእጁ ስለሆነ፣ ያጎበጠንን ሸክም አራግፎ ሊያሳርፈን "እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ።" ብሎ ስለ ጠራን፣ ወደ ጠራን አምላክ ቀና እንላለን።(ዮሐ 1፥3፣ 2ኛ ዜና 20፥6፣ ማቴ 11፥28) እርሱን ተስፋ ብናደርግ እንደ ሰው አይለወጥብንም። እስከ ሽበት እንኳን ተሸክሞን አይሰለቸንም።(ኢሳ 46፥4) ነፍሱን እስኪሰጥ ስለወደደን፣ በብዙ ሕማም በእጁ መዳፍ ላይ ስለቀረጸን ፍቅሩ ቀዝቅዞ ጨርሶ ሊረሳን አይችልም።(ኢሳ 49፥16)

በቸገረህ ጊዜ ብርና ወርቅ የለኝም ብለህ ተስፋ አትቁረጥ። "ሁሉን የሚችል አምላክ ወርቅና የሚብለጨለጭ ብር ይሆንልሃል"።(ኢዮ 22፥25) ስትታመምም "ማን ይረዳኛል?" አትበል። እግዚአብሔር በሕመም አልጋ ሳለህ ይረዳሃል። በበሽታህም ጊዜ አልጋህን እያነጠፈ ይንከባከብሃል።(መዝ 41፥3) እርሱ ካልተውከው አይተውህም፣ ካልሸሸኸው ከአንተ አይርቅም። ተስፋ ቆርጠህ ከሕይወትህ ካላስወጣኸው አንተን መፈለግ አይደክመውም።

ሰይጣን በአንድ ኃጢአት ደጋግሞ በጣለህ ጊዜም ፈጥነህ ተስፋ አትቁረጥ። የፈጣሪህንም መሐሪነት አትጠራጠር። ለጠላትህም እንዲህ በቀላሉ እጅ አትስጥ። ስለዚህ ነገር በገነተ አበው (Paradise of fathers) የተጻፈን ታሪክ እስኪ እናስታውስ። ሰይጣን በተመሳሳይ ኃጢአት ብዙ ጊዜ እያሰነካከለ የሚጥለው አንድ መነኩሴ ነበር። ታዲያ ይህ መነኩሴ ሁል ጊዜ በአንድ ኃጢአት እየደጋገመ መውደቁ ቢያሳዝነውም፣ መልሶ ንስሐ እየገባ ፈጣሪውን "አውጣኝ" ብሎ መማጸን ግን አላቆመም ነበር። ከዕለታት በአንዱ ቀን መነኩሴው ቆሞ መዝሙረ ዳዊት ሲጸልይ ሳለ ድንገት ሰይጣን ወደ እርሱ መጣና:- "ፊቱ ቆመህ በእነዚህ ንጹሕ ባልሆኑ ከንፈሮችህ የእግዚአብሔርን ስም ስትጠራ አታፍርም?" አለው። ያም መነኩሴ "አንተ እኔን ጨክነህ ታሰናክላለህ። እኔ ደግሞ መሐሪውን አምላክ እንዲያዝንልኝ ሳላቋርጥ እለምነዋለሁ። እስኪ ከአንተ ጭካኔ እና ከአምላክ ምሕረት የቱ እንደሚበልጥ እናያለን።" ሲል መለሰለት። ሰይጣንም የመነኩሴውን ተስፋ አለመቁረጥ ባየ ጊዜ ከእርሱ ሸሽቶ ሄደ።

የፈተና ማዕበል በሚበዛባት በዚህች ዓለም ስንኖር፣ ዐውሎና ወጀቡ ከሚያመጣው ጥፋት ለመዳን መልሕቃችንን የምንጥልበት የተስፋ መሬታችን አምላካችን እግዚአብሔር ነው።

"ኢሰማዕነ ወኢርኢነ ወኢነገሩነ አበዊነ ከመ ቦ ባዕድ አምላክ ዘእንበሌከ"

"ከአንተ በቀር ሌላ አምላክ እንዳለ አባቶቻችን አልነገሩንም። እኛም አልሰማንም፤ አላየንምም!"

"አሁንስ ተስፋዬ ማን ነው? እግዚአብሔር አይደለምን? ትዕግሥቴም ከአንተ ዘንድ ነው።"
መዝ 39፥7

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
+++ ሕማም የማያውቀው +++

በአካላዊ ቅርጹ ከእንጉዳይ (የጅብ ጥላ የምንለው) ጋር የሚመሳል፣ በክብደት መጠኑ ደግሞ በአማካይ ከ1.5 ኪሎ ግራም በላይ የማይመዝን፣ ነገር ግን ባለው የሥራ ድርሻ እና በማከማቻ ቋትነቱ ከምንኖርባት ዓለም በብዙ እጥፍ የሚበልጥ እጅግ በጣም ውድ የሆነን ስጦታ እግዚአብሔር በሰው ልጅ ሰውነት ውስጥ አኑሯል፡፡ ስለዚህ ስጦታ ምንነት እና ያለውን እምቅ ኃይል ፈልጎ ለማግኘት ብዙ ምርምሮች እና ብዙ ጥናቶች ተደርገዋል፡፡ የሚያስገርመው ግን አጥኚውም ተጠኚውም አንድ መሆኑ ነው፡፡ ራሱን በራሱ ያጠናል፣ ከጥናቱም ባገኘው አዲስ መረጃ በራሱ ይገረማል፣ ስለ ራሱም ብዙ የጥናት ወረቀቶችን ያሳትማል፡፡ አሁንም ይህን የምታነቡትን አጭር ጽሑፍ እያደረሳችሁ ያለው እርሱ ነው፡፡ ለመሆኑ እርሱ ማነው? የዚህም ጥያቄ ጠያቂና መላሹም እርሱ ነው፡፡ ማን? የሰው ልጅ ናላ (Human Brain)

ለዛሬ ስለዚህ እጅግ አስደናቂ ሕዋስ ምንነት ሰፊ ትንታኔ ማቅረብ ወይም ስለ ሥሪቱ መናገር የጽሑፋችን ዓላማ አይደለም፡፡ ነገር ግን ስለ ሰው ልጅ ናላ ሳይንሱ ከነገረን እውነታዎች ውስጥ አንዱን ብቻ መርጠን ጥቂት ነገር ለማለት ነው፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው አብዛኛው የሰውነታችን ክፍሎች የሕመምን ስሜት ተሸክመው ወደ ናላ የሚወስዱ ጥቃቅን መልእክተኞች (pain receptors) ስላሏቸው፣ አንድ ሰው እጁ አካባቢ በመርፌ ቢወጋ ቶሎ የሕመሙ ስሜት ይሰማዋል፡፡ ይሁን እንጂ ናላን (Brain) ግን ክፍት ሆኖ የማግኘት ዕድሉ ቢኖረንና በዚሁ መርፌ የላይኛውን ክፍል (Cortex) ብንወጋው እንደ ቀድሞው ተመሳሳይ የሆነ የሕማም ስሜት አይኖረንም፡፡ ምክንያቱም ናላችን የራሱን ሕመም የሚሸከሙለት መልእክተኞች (pain receptors) የሉትም። (አሁን እየተናገርን ያለነው በዋናነት ስለ ናላ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ከናላ በላይ ያለው እርሱን የሸፈነው ክርታስ (membrane) pain receptors ስላሉት የሕመም ስሜት ይፈጥራል፡፡)

በዚህም ምክንያት የናላ ቀዶ ሕክምና የሚደረግላቸው አንዳንድ ሕመምተኞች ንቁ ሆነው ሳለ ቀዶ ሕክምናው ሊከናወን ይችላል፡፡ በዚህም ጊዜ የትኛው የናላቸው ክፍል የበለጠ ጉዳት እንደ ደረሰበት በመሳሪያ ታግዘው ጥቆማ በማድረግና በሌላም አስፈላጊ በሆኑ መንገዶች ሐኪሞቻቸውን ሊያግዙ ይችላሉ፡፡ (በቀዶ ጥገናዋ ጊዜ የእጇን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠረው የአዕምሮ ክፍሏ እንዳይጎ ቫዮሊን በመጫወት ሐኪሞቹን ታግዛቸው የነበረችው ዳግማር ተርነር (Dagmar Turner) የተባለች የ53 ዓመቷ ታካሚ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ናት፡፡) ይገርማል የሰው ልጅን የሕመም ስሜቶች ሁሉ የሚቆጣጠረው ሕዋስ ለራሱ ግን ሕመም ተቀባይ የለውም።

ይሁን እንጂ ይህ ውጋት የማያውቀው፣ በሕመም ለሚገኙ የአካል ክፍሎቻችንም የሚድኑበትን እዝ የሚያስተላልፈው ሕዋስ አንዳንድ ጊዜ ግን ለሰውነታችን መታመም ምክንያት ሊሆን ይችላል። ይኸውም ክፉ የኃጢአት ሐሳቦችን በሕሊናችን ባነገስን ጊዜ ናላ የሚያመነጨው ኮርቲሶል (Cortisol) የሚባል ኬሚካል አለ። ኮርቲሶል የውጥረት ኬሚካል (Stress chemical) ሲሆን፣ ንቁ የሆነውን የአዕምሮ ክፍል እንቅስቃሴ የሚቀንስ ነው። በመሆኑም ይህ ኬሚካል በመነጨ ጊዜ አመክንዮአዊነት፣ ችግር ፈቺነት፣ የሌሎችን ስሜት መረዳት፣ ርኅራኄና ይቅር ባይነት በአዕምሮአችን ቦታ አይኖራቸውም።

ክፉ ስላሰብን ናላችን ባመነጨው ኬሚካል (ኮርቲሶል) ምክንያት የሚፈጠረው ውጥረት (stress) ደግሞ መዘዙ ቀላል አይደለም። ሌሎች የአካል ክፍሎቻችንም እንዲታመሙ (psychosomatic disorder ይባላል) ሊያደርግ ይችላል። ታዲያ ወደዚህ ሁሉ የጤና ቀውስ ላለመግባት ሕሊናን ከክፋት መጠበቅ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው። ሰይጣን በሚያመጣብን የክፉ ሐሳብ ሞገድ ላለመናወጽ ራስን በበጎነት አጽንቶ መጠበቅ ግድ ይለናል። አበው የክፉ ሐሳብ አማራጮችን በሕሊናችን የሚያንሸራሽረውን ሰይጣን በዝንብ ይመስሉታል። ዝንብ ወደ ቤታችን የሚገባው በር ወይም መስኮታችንን ክፍት ስናደርግ ነው። ባገኘው ክፍተት የገባውም ዝንብ ማረፊያ ቆሻሻ ነገር በቤትህ ካገኘ ይሰነብታል፣ ይራባል (ይባዛል)። ቤትህ ንጹሕ ከሆነ ግን እንደ ገባ ፈጥኖ ይወጣል። ሰይጣንም እንዲሁ ነው፤ ክፉ ሐሳብን ይዞ ወደ ሕሊናህ ሲበር ይመጣል። ለእርሱ ክፋት የሚስማማ ማንነት ይዘህ ከጠበቅኸው፣ ያድርብሃል። አዕምሮህን መናገሻ ከተማው ያደርገዋል። በንጹሕ ሕሊና በበጎ ሰብዕና ሆነህ ካገኘህ ደግሞ እንዲህ ካለው አዕምሮ ውስጥ ማደር ስለማይቻለው ፈጥኖ ከአንተ ይለያል። የውስጥ ሰላምህም እንደ ወንዝ ይፈስሳል። ነፍስህ እና ሥጋህንም ከሕመም ታድናቸዋለህ።

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
+++ "እግዚአብሔርን የተጠማች ነፍስ" +++

ቅዱስ ባስልዮስ "ሰውነታችን ያለ እስትንፋስ መኖር እንደማይችል፣ ነፍሳችንም ፈጣሪዋን ሳታውቅ ሕያው ሆና ልትኖር አትችልም። የነፍስ ሞቷ እግዚአብሔርን አለማወቋ ነውና" ይለናል፣ እውነት ነው፤ እግዚአብሔር ሕያው ነፍስ ላለው የሰው ልጅ ሁሉ የሰጠው ትልቁ ጸጋ "እርሱን ማወቅ" ነው። ነፍስም ያለዚህ መኖር እንደማትችል ታውቃለችና ዘወትር ይህን ስትጠማ ትኖራለች።

እግዚአብሔርን ማወቅ ማለት ስለ እርሱ የተጻፉ መጻሕፍትንና የተነገሩ ትምህርቶችን ማንበብ፣ መስማት ብቻ አይደለም። እነዚህ ብቻቸውን "ስለ እግዚአብሔር እንድናውቅ" እንጂ "እግዚአብሔርን እንድናውቀው" አያደርጉንም። "ስለ እግዚአብሔር ማወቅ" የመጨረሻው ዓላማችን ወደ ሆነው "እግዚአብሔርን የማወቅ ሕይወት" የምንገሰግስበት መንገድ እንጂ ራሱን ችሎ መዳረሻና ማረፊያ ወደብ አይደለም።

"እግዚአብሔርን ማወቅ" ግን በተግባር የሚገለጥና ከፈጣሪ ጋር የምናደርገው የአንድነት ሕይወት ነው። እኛ በእርሱ፣ እርሱም በእኛ የሚኖርበት ልዩ ምሥጢራዊ ውሕደት ነው። "እግዚአብሔርን ማወቅ" ማለት ስለ እርሱ ሲነገር በጆሮ የሰሙለትን አምላክ ከብቃት ደርሶ ማየትና በፍጹም ልብ መውደድ ነው። ይህ ደግሞ ራሱ ጌታችን በወንጌል እንደተናገረው የዘላለም ሕይወት ነው።(ዮሐ 17፥3)

ይህን ሕይወት ቀምሶ ያጣጣመው ቅዱስ ዳዊት "ሁልጊዜ እግዚአብሔርን በፊቴ አየዋለሁ፤ በቀኜ ነውና አልታወክም። ስለዚህ ልቤን ደስ አለው" እያለ በሐሴት የከንፈሩን መሥዋዕት ለአምላኩ ያቀርባል።(መዝ 16፥8) በሌላ ጊዜ ደግሞ ይኸው መዝሙረኛ አይቶት እንደማያውቅ ነገር "ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ እንደሚናፍቅ፥ አቤቱ፥ እንዲሁ ነፍሴ ወደ አንተ ትናፍቃለች። ነፍሴ ወደ ሕያው አምላክ ተጠማች፤ መቼ እደርሳለሁ? የአምላክንስ ፊት መቼ አያለሁ?" እያለ በናፍቆት ይዘምራል።(መዝ 42፥1-2) ምን ማለቱ ይሆን?

የዋልያ መኖሪያ ከፍ ካለ ኮረብታ ላይ ነው። ታዲያ ይህ የበረሃ ፍየል ውኃን በተጠማ ጊዜ ምንጭ ያለው ከተራራው ግርጌ ስለሚሆን እርሱን ፍለጋ ወደታች ይወርዳል። ወርዶም ምንጩን ካገኘና ከጠጣ በኋላ፣ ወደ መጣበት ኮረብታ ሲመለስ ገና ከተራራው ወገብ ሳይደርስ አካሉ ይደክምና ውኃ ይጠማል። መልሶ ከምንጩ ወርዶ ይጠጣል። ወደ ተራራው ሲመለስ አሁንም ይጠማዋል። እንደ ገና ወደ ምንጩ ይመለሳል።(ስለ ዋልያ ውኃ መጠማት የሚሰጥ ሌላው ሐተታ እንደ ተጠበቀ ሆኖ) ታዲያ ይህን ያየ ክቡር ዳዊት ዋልያ እንዲህ ወደ ውኃ ምንጭ እንደሚናፍቅ፣ ነፍሴም ወደ አንተ ትናፍቃለች። ነፍሴ ወደ ሕያው አምላክ ተጠማች፤ መቼ እደርሳለሁ? የአምላክንስ ፊት መቼ አያለሁ? ብሎ ዘመረ። (መዝ 41(42)፥1-2)

ይህም የቅዱስ ዳዊት ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን ያወቀችና ፍቅሩን የቀመሰች፣ እርሱንም መዘከር የማትጠግብ ነፍስ ሁሉ የዘወትር መዝሙር ነው።

እኛስ ስለ እግዚአብሔር ከማወቅ አልፈን፣ እርሱን በሕይወታችን ተዋውቀን፣ ፍቅሩን ቀምሰን "ተጠማሁ" እያልን በመናፈቅ የምንዘምርበት ቀን መቼ ይሆን?

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
2025/07/14 17:42:36
Back to Top
HTML Embed Code: