Telegram Web Link
🌟🌟🌟በገና አባት የተሸፈነ ቅዱስ አባት🌟🌟🌟

+++ቅዱስ ኒቆላዎስ ገባሬ መንክራት (St.Nicholas the wonder worker)+++

ቅዱስ ኒቆላዎስ (St.Nicholas-Santa Claus) በሮማ መንግስት ዘመን በኤዥያ ውስጥ በምትገኝ ሜራ በምትባል አገር (የአሁኗ ቱርክ) ግሪካዊ ከሆኑ ክርስቲያን ቤተሰቦቹ ተወለደ፡፡ የዚህም ቅዱስ እናቱ ጦና (Tona) አባቱ ኤጲፋንዮስ ይባላሉ፡፡ እኒህም እግዚአብሔርን የሚፈሩና ባለጠጎችም ነበሩ፡፡ ነገር ግን ከሞቱ በኋላ ንብረታቸውን የሚያወርሱት፣ ለልባቸውም ደስታን የሚመግብ ልጅ አልነበራቸውም፡፡ ዕድሜያቸው እየገፋ በመምጣቱም ምክንያት በተስፋ መቁረጥ ተከበው ይኖሩ ነበር፡፡ በልብ መታሰቡ በቃል መነገሩ ከፍ ከፍ ያለ አምላክ በእርጅና ዘመናቸው ልክ ጻድቁ ዘካርያስና ሚስቱ ኤልሳቤጥን እንደጎበኘ እነርሱንም በቸርነቱ ጎበኛው፡፡ ቅዱስ የሆነም ልጅን ሰጣቸው፡፡ ይህም ልጅ ገና ታናሽ ሳለ መንፈሰ እግዚአብሔር የሞላበት ነበር፡፡ ዕድሜውም ለትምህርት በደረሰ ጊዜ ዕውቀትና ጥበብን ይቀስም ዘንድ ወደ መምህራን የተላከ ቢሆንም፣ ከመምህሩ ከተማረው ይልቅ ከመንፈስ ቅዱስ የተረዳው ይበልጥ ነበር፡፡

መሠረታዊ የሆኑትን የቤተ ክርስቲያንን ትምህርቶች በልጅነቱ ተምሮ በማጠናቀቁ በዲቁና መዓርግ ተሾመ፡፡ በኋላም የአጎቱ ልጅ አበምኔት በሆነበት በአንዱ ገዳም አርዑተ ምንኩስናን (የምንኩስናን ቆብ) ጭኖ የቅድስና እና የትሕርምት ሕይወትን ኖሯል፡፡ በአሥራ ዘጠኝ ዓመቱም የቆሞስነትን መዓርግ አግኝቷል፡፡

ለዚህም ቅዱስ አባት እግዚአብሔር ተአምር እና ድንቅን የማድረግ ፤ሕሙማንንም የመፈወስ ታላቅ ጸጋ ሰጥቶታል፡፡

#ለጋስ (የስጦታ) አባት

በሜራ ከተማ የሚኖር ቀድሞ ባለጠጋ የነበረ በኋላ ግን ሃብት ንብረቱን ያጣ አንድ ሰው ነበረ፡፡ በድህነቱ ምክንያት ሊድራቸው ያልቻለ ሦስት ዕድሜያቸው ለጋብቻ የደረሱ ሴቶች ልጆች ነበሩት፡፡ ሰይጣንም እነዚህን ልጆቹን በዝሙት ሥራ ገንዘብ እየሰበሰቡ ሕይወታቸውን እንዲመሩ ያደርጋቸው ዘንድ ክፉ ሐሳብን በሕሊናው አመጣበት፡፡ እግዚአብሔርም በዚህ ሰው ልቡና ውስጥ ሰይጣን የተከለበትን ክፉ ሐሳብ እና ምን ሊያደርግ እንደተነሣሣ ለቅዱስ ኒቆላዎስ ገለጠለት፡፡

ቅዱስ ኒቆላዎስም የእናት የአባቱ ገንዘብ ከሆነው ላይ መቶ ዲናር ወስዶ በስልቻ (sack) ጠቅልሎ ማንም ሳያየው በምሽት ወደዚያ ደሃ ሰው ቤት በመሄድ በመስኮት በኩል ወረወረለት፡፡ ያም ደሃ ከየት እንደመጣ ያላወቀውን 100 ዲናር በቤቱ ባገኘ ጊዜ ተደነቀ አምላኩንም አመሰገነ፡፡ ያሰበውንም ክፉ ሐሳብ ተወ። በገንዘብ እጦት ምክንያትም ከትዳር የዘገየችውን የመጀመሪያ ልጁን ዳረ፡፡ በሌላም ቀን ቅዱስ ኒቆላዎስ ሁለተኛ ልጁን መዳር ይችል ዘንድ፣ አሁንም ተጨማሪ መቶ ዲናር ገንዘብ በጥቅል ስልቻ አድርጎ በመስኮቱ በኩል ወረወረለት፡፡ ይህንንም ገንዘብ ዳግመኛ በቤቱ ያገኘው ደሃ ሰው እንዲህ ያለውን ቸርነት በስውር የሚያደርገው ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ አይቶ ያውቅ ዘንድ ጉጉት አደረበት፡፡ ቤቱንም በንቃት መከታተል ጀመረ፡፡

ቅዱስ ኒቆላዎስም እንደ ለመደው ለሦስተኛ ጊዜ መቶውን ዲናር የያዘውን ስልቻ በመስኮት ሲወረውር ወዲያው ተዘጋጅቶ ይጠብቀው የነበረው ሰው ፈጥኖ በሩጫ ከቤቱ ወጣ። ሊያየው ይመኘው የነበረ ያንንም ቸር ሰው ሊቀ ጳጳሱ ኒቆላዎስ ሆኖ አገኘው፡፡ ከእግሩ ስርም ተደፍቶ ልጆቹን ከድህነት እና ከኃጢአት ሕይወት ስለታደገለት ሊያመሰግነው ቢሞክርም ቅዱስ ኒቆላዎስ ግን ምስጋናውን እምቢ አለ፡፡ ይህን ሐሳብ በልቡ ያኖረ እግዚአብሔርንም ያመሰግን ዘንድ ለመነው፡፡

ከዚህ ታሪክ በተጨማሪም ለሕፃናት እና ለተቸገሩ ሰዎች ያደረገው ልግስና የብዙ ብዙ ነው። ለዚህም ይመስላል በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት መታሰቢያውን በልግስና የሚያከብሩት።

በአጠቃላይ ይህ ቅዱስ አባት በዘመነ ዲዮቅልጥያኖስ ስለ እምነቱ ብዙ ስቃይ እና እስራት ደርሶበታል፡፡ ፋታ በማይሰጥ መከራ እና ግርፋት ውስጥ እያለ የራሱን ሕመም ከማዳመጥ ይልቅ በውጪ ላሉ ለልጆቹ ምዕመናን የሚያበረታታ እና በእምነታቸው እንዲጸኑ የሚያደርግ መልእክትን ይጽፍላቸው ነበር፡፡ ቅዱስ ኒቆላዎስ በ325 ዓ.ም ለአውግዞተ አርዮስ ከተበሰቡት 318ቱ ሊቃውንት መካከል አንዱ የነበረ የዚህች ኦርቶዶክሳዊት እምነት ባለውለታ ነው፡፡ ከአርባ ዓመታት በላይ በሊቀ ጵጵስና መንበር በጎቹን ከነጣቂ ተኩላ እየጠበቀ ቤተ ክርስቲያንን ካገለገለ በኋላ በሰማንያ ዓመቱ አርፏል፡፡

(ቅዱስ ኒቆላዎስ በእኛ (በኢትዮጽያ) የስንክሳር መጽሐፍ ላይ የእረፍቱ መታሰቢያ የሚያዝያ ወር በገባ በአስራ አምስተኛው ቀን እንደሆነ ተመዝግቧል፡፡ ኒቆላዎስም ማለት ‹መዋኤ ሕዝብ - ሕዝብን የሚያሸንፍ› ማለት ነው።)

የልደት በዓል እግዚአብሔር አብ ልጁን ለዓለም የሰጠበት በመሆኑ ‹የሥጦታ በዓል› በመባል ይጠራል፡፡ ይህንንም በማሰብ ለድሆች በመራራት ለተቸገሩት ቸርነት በማድረግ እናከብረው ዘንድ ምሳሌ እንዲሆነን ቅዱስ ኒቆላዎስን እናስባለን፡፡ ምንም ዓለም አፈ ታሪክ አድርጋ ብታወራውም፣ የዚህንም ቅዱስ ማንነት እንዳይታወቅ በፈጠረቻቸው ተረቶች ብታጠለሸውም እኛ ግን የ‹ገና አባት› ብላ ከሰየመቻቸው የፈጠራ ሰው ጀርባ እውነተኛ የሆነውን ይህን ቅዱስ አባት እናስበዋለን፡፡

+++++ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ እኛ ኃጢአተኞቹንም በዚህ ጻድቅ ሰው ጸሎት ይማረን!!!+++

ምንጭ:– -መጽሐፈ ስንክሳር
-Coptic synaxarium

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
+++ "ሰይጣን የሚጠላው መጽሐፍ" +++

ሰይጣን የሰው ልጆችን ጥፋት ከሚያፋጥንበት ዘዴዎቹ መካከል አንዱ መዳን የሚገኝበትን ትምህርት በማጣጣል እና ውሸት ነው በማስባል ነው። ለዚህም ደግሞ ከነመርቅያን፣ ከነሴልሰስ ጀምሮ አሁን እስካለንበት ዘመን ድረስ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተደረጉ ብዙ የሐሰት ክስ ዘመቻዎች ማስረጃ ሆነው መቅረብ ይችላሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉት ቃላት ነፍስን ከክፋት የሚመልሱ እና የሰውን ልብ እስከ ጥልቁ ወርደው የሚመረምሩ፣ የሚወጉ ስለሆኑ ሰይጣን መጽሐፍ ቅዱስን ይጠላል። ነገር ግን ሰይጣን ከመጽሐፍ ቅዱስም በላይ በጣም የሚጠላው ደግሞ ሌላ ነገር አለ። ምን ይመስላችኋል? የገድላት መጻሕፍትን!

መጽሐፍ ቅዱስን እንቀበላለን የሚሉ ወገኖች መጽሐፍ ቅዱስን ከሚያጣጥሉ ኢ-አማንያን በበለጠ መንገድ የገድላትና የተአምራት መጻሕፍትን በፍጹም ጥላቻ እና መራርነት ለማብጠልጠል ሲሞክሩ ስታይ "ሰይጣን ከመጽሐፍ ቅዱስም በላይ ገድላትና ተአምራትን እንደሚጠላ ግልጽ ሆኖ ይታይሃል። የሐዋርያት ሥራን የሚያህል የሐዲስ ኪዳን የመጀመሪያ የገድል መጽሐፍ ይዘው የቅዱሳን ገድል ለምን ይጻፋል? ገድላትና ተአምራት ክርስቶስን የሚሸፍኑ መጋረጃዎች ናቸው ሲሉ ስትሰማ ከያዙት መጽሐፍ ቅዱስ ሳይሆን ከያዛቸው መንፈስ የተነሣ ተቃዋሚዎች እንደ ሆኑ ትረዳለህ።

ለመሆኑ ሰይጣን የገድላት መጻሕፍትን ለምን ይጠላቸዋል?

ገድላት የመጽሐፍ ቅዱሱ ትምህርት በሕይወት መተርጎም የሚችል እንደ ሆነ የሚያስረዱ ዝርዝር ተግባራዊ ማስረጃዎች ስለሆኑ፣ የሚያነቧቸውን ክርስቲያኖች "ለካስ እንዲህም መኖር ይቻላል" ብለው ከሰሚነት ወደ ሠሪነት እንዲሻገሩ የሚያደርጉ ድልድዮች ስለሆኑ ይጠላቸዋል። እንደምታውቁት ሰይጣን እኛን ከእግዚአብሔር የሚያርቅበት አንደኛው ተንኮሉ የቅድስናን ሕይወት በጣም ሩቅ እና ልንወጣው የማንችለው ግዙፍ ተራራ አስመስሎ በልቡናችን ላይ በመሣል ነው። ታዲያ ይህን ጠላት በልባችን ላይ የሳለውን ክፉ ሥዕል ሰባብሮ የሚጥለው እና ያራቀብንን የቅድስና መዓዛ የሚያቀርበው ወድቆ ተነሥቶም ወደ እግዚአብሔር መድረስ እንደሚቻል የሚያሳየው የአንድ ቅዱስ ወይም የአንዲት ቅድስት የገድል መጽሐፍ ነው።

ሰውነት ማለት ምን ማለት ነው? የሰውስ ክብሩ ምን ድረስ ነው? በዚህ ዘመን ያለን የብዙዎቻችን ሕይወት ለዚህ ጥያቄ መልስ ለመሆን የሚበቃ አይደለም። ሁለመናችንን የከበበው ኃጢአት ፍጥረታችንን እና የተሰጠንን ክብር እንዳናይ ከልክሎናል። መጽሐፍ ቅዱስ "እግዚአብሔር ሰውን በመልኩ እንደ ምሳሌው ፈጠረው" ይለናል። "የእግዚአብሔር ምሳሌነት" ምንድር ነው? ከውድቀት በኋላ ደግሞ የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ ተብሎ በሐዲስ ተፈጥሮ "እግዚአብሔርን የመምሰል ምሥጢር"ን አስተማረን። "እግዚአብሔርን የመምሰል ምሥጢር" ምንድር ነው? የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ የሚገኘው ከሐዋርያት ሥራ ጀምሮ ከዚያ በኋላ በተጻፉ የገድላት መጻሕፍት ላይ ነው። በውስጣቸውም አምላክ ምን ያህል የሰውን ባሕርይ እንዳከበረው ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ።

የተሰጠውን ያላወቀ እንደ ተሰጠው መጠን ለመመላለስ (ለመኖር) ይቸገራል። ሰይጣን የተሰጠንን ሰውነት እና ክብሩን ከእኛ በመሰወር ላልተፈጠርንበት እየደከምን የኃጢአት ባሪያ እንድንሆን ያደርገናል። የጥንት ክብራችንን አስረስቶ ለእርሱ እስክንሰግድ ድረስ ያስጎነብሰናል። ከዚህ የግዞት ቀንበር መውጫ ቁልፉ ደግሞ "ሰውነትና ክብሩን" ለማወቅ መነሣት ነው። ታዲያ ስለ ሰውነት ከነሙሉ ክብሩ በቤተ ክርስቲያን ካሉት የገድላት መጻሕፍት በላይ ምን ሊያስተምረን ይችላል?

የገድል መጽሐፍን በሌላ ተለዋጭ ስም እንጥራው ብንል "ክርስቶስን የመምሰል ሕይወት" መጽሐፍ የሚለው አቻ ስያሜ ይሆነዋል። ክርስቶስን የመምሰል ሕይወት ደግሞ ሰይጣንን እንደ እሳት ያቃጥለዋል፣ እንደ ሰይፍ ይቆራርጠዋል። ስለዚህም ሰይጣን ከመጻሕፍት ሁሉ ይልቅ የገድላት መጻሕፍትን አብልጦ ይጠላቸዋል!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
ታኅሣሥ 13/ 2015 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
❤1
ገብርኤል ሆይ፤ ከሰው ወገን ጠዋትና ማታ ከቶ እንደ እኔ ኀዘንና ትካዜ የሚበዛበት የለም፣
ከመላእክትም ወገን እንደ አንተ ያዘኑትን የሚያረጋጋ የለም፣
ገብርኤል ሆይ፤ ስለዚህ እኔም አውቄና አንተን አምኜ ያቀረብኩትን ይህን ጸሎት እንደ ትልቅ ዋጋ ቆጥረህ የሚያረጋጋ ቃልህን አሰማኝ።

መልክአ ገብርኤል

እንኳን ለሊቀ መላእክት ለቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሰን!
+++ "ፍቅርና ፍርሃት"+++

በሰው መካከል ያለ ቀረቤታ ሲጠነክርና ፍቅሩ ያደገ ሲመስል መከባበርና ሐፍረት እየቀነሰ ሊመጣ ይችላል። "አሁንማ መፈራራት አያስፈልግም"፣ "እንደ ስሜትህ መሆን ትችላለህ?" የሚሉ ቃላቶችን በጊዜው ለጠበቀው ወዳጅነታቸው መመሪያ ጥቅስ ሊያደርጉትም ይችላሉ። ነገር ግን ጉዳዩ ለከቱን ያለፈ ቀን ይዞባቸው የሚመጣው የጠብ ጦስ እንዲህ በቀላሉ የሚመለስ አይደለም። ሁል ጊዜ በጸና ፍቅር ውስጥም ቢሆን መኖር ያለበት "ንጹሕ ፍርሃት እና ሐፍረት" አለ። እርሱ ደግሞ መከባበርን ያመጣል።

የእግዚአብሔርን ፍቅር በሚገባ ላልቀመሰ ሰው ከገጸ ምሕረቱ ይልቅ ገጸ መዓቱ ይጎላበታል። ስለዚህ ትእዛዛቱን ለመፈጸም የመጀመሪያ ምክንያት የሚሆነው "በሥጋዬ እንዳይቀስፈኝ፣ በነፍሴ እንዳያጠፋኝ" የሚለው ፍራቻው ነው። እንዲህ ያለውን ፍርሃት መጽሐፈ መነኰሳት "ፍርሃተ አግብርት"/"የባሮች ፍርሐት" ብሎ ይጠራዋል። ይህም እንደ እኛ ባሉ ጀማሪ ክርስቲያኖች ኅሊና ውስጥ የሚሯሯጥ ፍርሃት ነው። ፍቅሩን ለሚያስብ የበረታ ክርስቲያን ግን ባላደርግ እቀጣለሁ ብሎ ሳይሆን፣ ፈጣሪውን ስለሚወድ ብቻ ትእዛዙን ይፈጽማል።(ዮሐ 14)

ይሁን እንጂ ከፍቅር ላይ የደረሱም ቅዱሳን ቢሆኑ እግዚአብሔርን መፍራታቸው የማይቀር ነገር ነው። ለእግዚአብሔር ያላቸው ፍቅር መልሰው እርሱን እንዲዳፈሩት ምክንያት አይሆናቸውም። የቅዱሳኑ ፍርሃት ግን "ምን ያደርገኝ ይሆን" የሚል የባርያ ፍርሃት ሳይሆን፣ "እንዳያዝንብኝ፣ እንዳይከፋብኝ" ከሚለው ልጃዊ ፍቅር የመነጨ ነው።

በተጨማሪም የመለኰቱ ርቀት፣ የባሕርዪው ምልዓት በልብ ታስቦ የማይደረስበት መሆኑን ዐውቀው፣ በልባቸው ጉልበት እየራዱ አይመረመሬነቱን በአንክሮ ማድነቃቸው ነው "እግዚአብሔርን መፍራታቸው"።

ሐዋርያው "ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል" ይለናል።(1ኛ ዮሐ 4፥18) ምን ማለት ነው? ስለ የትኛው ፍርሃት እየተናገረ ይሆን? ቅዱስ ዮሐንስ የሚናገረው አንደኛ "ፍርሐተ አግብርት" ስለተባለው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ እሳት ስለቱን እንዲሁም በሥጋ የሚመጣውን ስቃይ ተሰቅቆ እርሱን ከመካድ ስለሚያደርሰው "ጎጂ ፍርሃት" ነው።

በቀረው ግን ፍጹም ፍቅር ሥጋዊ ፍርሃትን እንጂ፣ እግዚአብሔርን መፍራትን ከውስጣችን አውጥቶ አይጥልም!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
በኃጢአት የጎሰቆለው አዳም የሚታደስበትን ዜና ሊያበስር መልአኩ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፤

ንጹሕ ለሆነው ሙሽራ የተገባች አዳራሽ ትሆነው ዘንድ መመረጧን ሊያበሥራት መልአኩ ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፤

ከኃጢአት ንጹሕ የሆነው መልአክ በደል ወዳልተገኘባት ንጽሕት ድንግል ተላከ፤

የፀሐየ ጽድቅን መምጣት ያበሥር ዘንድ ብርሃናዊው መልአክ ተላከ፤

በአባቱ እቅፍ ያለው አንድያ ልጅ በእናቱም እቅፍ እንደሚሆን ያበሥር ዘንድ መልአኩ ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፤

እንኳን ለበዓለ ብሥራት በሰላም አደረሰን!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
ታኅሣሥ 13/ 2015 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com

ቴሌግራም
https://www.tg-me.com/Dnabel
"በዕብራይስጥ ማሪሃም የተባልሽ የተመረጥሽ ድንግል እመቤቴ ማርያም ሆይ፤ አምላክን በሥጋ የወለድሽ ከትንሽነቴ ጀምሮ ተስፋዬ፣ አለኝታዬ፣ አምባዬ፣ መጠጊያዬ፣ ጉልበቴ፣ የመድኃኒቴ ሽቱ ብልቃጥ፣ የመመኪያየ አክሊል፣ ክብሬ፣ ገናንነቴ፣ የራሴ ከፍ ከፍ ማያ ሆይ፤ በክርስቲያን ሥርዓት ጠብቂኝ። በክርስቲያን ሃይማኖት አጽኝኝ፣ ክርስቲያን አድርጊኝ"

የፍቅሯ ኃይል ያረፈበት የስም አጠራሯ ከአንደበቱ የማይለየው አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ

ፍቅሯ ይደርብን!!!
ሰማይን ያለ ባላ ምድርን ያለ ካስማ ያጸና፣ ብቻውን ታላላቅ ነገሮችን ያደረገ፣ በማኅጸን ደም አርግቶ አጥንት ሰክቶ ጽንስ የሚፈጥር ሠዓሌ ሕፃናት ዛሬ ሥጋ ማርያምን መሰወሪያው አድርጎ ወደ ፈጠራት ምድር በትሕትና ገባ። አዳምን የሚናገር የሠላሳ ዓመት ጎልማሳ አድርጎ የፈጠረው ጌታ ዛሬ አፍ ያልፈታ የአንድ ቀን ልጅ ሆኖ ከእናቱን ወተት እየለመነ እንደ ሕፃናት ሲያለቅስ ታየ። ስፍራ የማይወስኑት አምላክ ወደ ዓለም ሲገባ ስፍራ ስላልተገኘለት በከብቶች ማደሪያ በረት ተወልዶ እንስሳት ትንፋሽ ሲገብሩለት አደረ። ሲያሟሙቁት።

የእግዚአብሔር አብ ቸርነቱ ምን ይደንቅ?! ቀድሞ የፈጠረው አዳም በበደል ቢወድቅበት እርሱን አጥፍቶ በምትኩ አዲስ ሰው መፍጠር እየቻለ፣ ነገር ግን ለወደቀ ባሪያው ምትክ የሌለው አንድያ ልጁን ሞቶ ተሰቅሎ እንዲያድነው ወደ ዓለም ላከ። ስለ ባሪያ ፈንታ ልጅን ቤዛ አድርጎ የሚሰጥ ከአብ በቀር ማን አለ? አብርሃም ልጁን ሳያቅማማ ሊሠዋ የተነሣው ፈጥሮ ላኖረው ከሁሉ ለሚበልጥበት አምላኩ ነበር። አብ ግን ልጁን የሰጠው በኃጢአት ምክንያት ጠላቶቹ ለነበርነው ለእኛ ነው።

ይህ ሁሉ የሆነው ስለ ሰው ቢሆንም ሰው ግን የተደረገለትን ቸርነት አላወቀም። አምላክ የገባውን "የአድንኃለሁ" ቃል ጠብቆ ወደ ምድር ሲወርድ፣ ሰው ግን "የሚመጣውን አምላክ" ረስቶ የሚወለድበት እንኳ ስፍራ አሳጣው። መላእክት መጥተው እስኪያነቁት ሰው በሜዳ በዋሻ አንቀላፋ። በዚያን ጊዜ የተኙት እረኞችስ መላእክት ቀስቅሰዋቸው ተነሡ። እኔ ግን እስከ አሁን ተኝቻለሁ። ኃጢአት እያባከነኝ አንተ ከተወለድህበት ርቄ ከሜዳ ቀርቻለሁ። መልአክህን ልከህ በምሥራች ቃል የምትቀሰቅሰኝ መቼ ነው? ሕይወቴ መወለድህን እንዳልሰማ ሰው ሆኗል። የበደል እንቅልፍ ከብዶባቸው ዓይኖቼ ማዳንህን ማየት ተስኗቸዋል። ቀስቅሰኝና ልደትህን እንደ አዲስ ተወልጄ ላክብር? አንቃኝና እስከ ቤተልሔም ሄጄ ለእኔ ስትል የሆንከውን አይቼ እያመሰገንኹ ልመለስ?!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
ታኅሣሥ 28/ 2015 ዓ.ም.

Church of Nativity
ቤተልሔም
(ፍልስጥኤም)

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
❤1
+++ ያለ እግዚአብሔር "እንደ እግዚአብሔር" +++

በእባብ ሥጋ ተሰውሮ ወደ ሔዋን የመጣው ሰይጣን ሴቲቱን ያታለለበት የሐሰት ቃል "ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው" የሚል ነበር።(ዘፍ 3፥5) ይገርማል! በእግዚአብሔር መልክ የተፈጠረ የሰው ልጅ እንደ እግዚአብሔር (እርሱን መስሎ) የመኖር ፍላጎት እንዳለው ሰይጣን ያውቃል። ይህ ውሳጣዊ ፍላጎቱ ላይ ለመድረስ በሃይማኖትና በበጎ ምግባር ከማደግ ይልቅ ባልተገባ መንገድ ፍለጋውን ያደርግ ዘንድ አዲስ ስብከት አመጣለት። ምን የሚል? "ያለ እግዚአብሔር 'እንደ እግዚአብሔር' ትሆናላችሁ" የሚል። በምን? በቅጠል።

ዛሬም ሰይጣን ያለ እግዚአብሔር "እንደ እግዚአብሔር" ትሆኑባችኋላችሁ ሲል የሚያሳየን እንደ ገንዘብ፣ ዕውቀት፣ ጉልበት ያሉ ብዙ ቅጠሎች አሉ።  ነገር ግን እኛ ክርስቲያኖች እርሱን ወደ መምሰል የምናድግበት ብቸኛው መሰላላችን ረድኤተ እግዚአብሔርና የማይቋረጥ የእኛ ሩጫ ነው። እርሱ ሳይኖር እና  ሳያካፍል እኛ በራሳችን የምንካፈለው ምንም አምላካዊ ምሳሌነት የለም።(2ኛ ጴጥ 1፥4)

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
ናዝሬት ገሊላ
(እስራኤል)

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
+++ እግዚአብሔር ለአንተ ፍትሐዊ ነው? +++

ጋሽ ስብሐት ለአብ ገብረ እግዚአብሔር በአንድ የሬዲዮ ጣቢያ ላይ ቃለ መጠይቅ ሲደረግለት ለጋዜጠኛው "እግዚአብሔር በአንዳንድ ነገሮች ጥሩ አላደረገም" አለው። ጋዜጠኛውም "እንዴት? እስኪ ለምሳሌ?" ቢለል፣ "ለምሳሌ ለእኔ ያደላል" ሲል መለሰለት።

እኛስ እንዲህ የምንልባቸው አጋጣሚዎች የሉም? በእርግጥ "እግዚአብሔር ለእኔ ያደላል" ስንል "ከሌላው ያስበልጠኛል" እያልን አይደለም። በዚህስ "እግዚአብሔር የሰውን ፊት አይቶ አያደላም"።(ገላ 2፥6) ነገር ግን እርሱ እያንዳዳችንን ልክ እንደ አንድና ብቸኛ ልጅ ያህል የሚወድ አምላክ ስለሆነ ከዚህ ተአምራዊ የአባትነት ፍቅሩ የተነሣ ሁላችንም ለእኛ "የሚያደላ" መስሎ ይሰማናል።

ለመሆኑ "አምላክ ለእኔ ያደላል" ስንል ምን ማለታችን ይሆን? እግዚአብሔር ያደላልኛል ስንል እኔ ምንም ሊደረግለት የማይገባ አመጸኛ ሰው ሆኜ ሳለሁ ክፋቴን ሳይሆን ደግነቱን እያሳየ ያኖረኛል ማለታችን ነው። አንዲት እናት መልካም ከሆኑ ልጆቿ መካከል አንድ አስቸጋሪ ልጅ ቢኖራት ይጎዳብኛል ብላ ለእርሱ እንደምትሳሳ፣ ፈጣሪዬ እኔ አመጸኛ ልጁን ከስንፍናዬ የተነሣ እንዳልጠፋበት በስስት ያየኛል ይጠብቀኛል እያልን ነው።

ሶርያዊው ማር ይስሐቅ እግዚአብሔር እኛ ኃጢአተኞቹ ላይ በሚያደረገው ሁሉ ፍትሑ አልታየምና እንዴት "ፍትሐዊ ነው" ብለን ልንናገር እንችላለን ይለናል። እውነት ነው፤ እስኪ አስቡት:- በአመሻሹ ገብተን በሠራናት ጥቂት ሥራ ከጠዋት ጀምረው ከደከሙት ጋር እኩል ዲናር የሚከፍለንን፣ ገንዘቡን ወስደን በማይገባ ኑሮ ስላባከንን ፈንታ ጸጸታችንን ብቻ ተመልክቶ ወደ እኛ ሲሮጥ በመምጣት አንገታችንን አቅፎ የሚስመንን እና መልሶ በገንዘቡ ሁሉ ላይ የሚያሰለጥነንን ጌታ እንዴት "ለእኔስ ፍትሐዊ ነው" ልንለው እንችላለን?

እግዚአብሔር ከሕይወት ይልቅ ሞት፣ ከበረከት ይልቅ እርግማን ለሚገባን ለእኛ በደለኞቹ አንድም የሚገባንን አላደረገብንም። ታዲያ እግዚአብሔር እኛ ላይ ባሳየው ነገር "ፍትሐዊ" ነው ትላላችሁ?

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
ኢየሩሳሌም
(እስራኤል)

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
+++ የማርታ ጸሎት +++

ማርያም: ትእዛዙን ሰሚ
ማርታ: የማይታዘዘውን አምላክ አዛዥ፣ "ንገራት" ባይ። (ሉቃ 10፥40)

እኛስ የእርሱን ትእዛዝ በትሕትና እንሰማለን ወይስ እንደ ማርታ "እንዲህ አድርግ? እንዲህ ተናገር?" ብለን የምንፈልገውን እናዘዋለን?

እስኪ ጸሎታችንን እናስተውል?!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
+++የሕፃናት ጥምቀት+++

አዳምና ሔዋን ሕግ አፍርሰው ከተከለከሉት ዛፍ ፍሬ ከበሉባት ሰዓት ጀምሮ ጸጋ እግዚአብሔርን ተገፈው እርቃናቸውን ቀርተዋል፡፡ በወቅቱም የተሰማቸውን እንግዳ የሐፍረት ስሜት መቆጣጠር ስለተሳናቸው ዕርቃናቸውን የሚሸፍኑበትን ቅጠል በገነት ካሉት ዛፎች ቆርጠው በሰውነታቸው ላይ አገለደሙ፡፡ እግዚአብሔርም ከገነት ባስወጣቸው ጊዜ ያገለደሙት የቅጠል ስፌት የዚህን ዓለም ብርድ እንደማይቋቋምላቸው ስላወቀ ከእንስሳት ለምድ የተዘጋጀ የሚሞቅ የቁርበትን ልብስ አለበሳቸው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም የሰው ልጅ ሁሉ ልብስ ያስፈልገው ጀመር፡፡ የዕድሜ ክልል ገደብ ሳይኖረው አረጋዊውም ፣ዛሬ የተወለደውም ሕፃን በጨርቅ የሚጠቀለል ሆነ፡፡

ማንኛውም ሕፃናት ልጆች ያሉት ጤናማ ወላጅ ልጆቹ የልብስን ጠቀሜታ ስላልተረዱ ‹አድገው እስኪረዱት ድረስ እርቃናቸውን ይቆዩ› በማለት እንደማይተዋቸው የታወቀ ነው፡፡ ምንም ክፉና ደጉን ባይለዩ፣ ራቁት የመሆን የሐፍረት ስሜት ባያሸንፋቸውም ፤ ከጤናቸው አንጻር በብርድ እንዳይታመሙበት ሲል ለልጆቹ በማሰብ ልብስ ያለብሷቸዋል፡፡

የሰው ልጅ ሥጋዊ ወይም ቁሳዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊም ፍጥረት ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ለግዙፍ ሥጋው መጎናጸፊያ ልብስ እንደሚያስፈልገው ፤ ለረቂቅ ነፍሱም ልብስ ያስፈልጋታል፡፡ በልብስ ያልተሸፈነ ሰውነት ለብርድና ለተለያዩ በሽታ አምጪ ሕዋሳት እንደሚጋለጥ ፣እንዲሁ በልብስ ያልተሸፈነች ነፍስም በኃጢአት ከሚመርዟት አጋንንት ማምለጥ አትችልም፡፡ ታዲያ ይህ የነፍሳችን ልብስ ምንድር ነው? እንዴትስ ነው የምትለብሰው?

ድንኳን ሰፊ የነበረው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ነፍሳችን ስለምትለብሰው ረቂቅ በፍታና ስለምትለብስበትም መንገድ ምንነት ለገላትያ ሰዎች በላከው መልእክቱ ‹የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋል› ሲል ይናገራል (ገላ 3፡27)፡፡ ከዚህም የሐዋርያው ትምህርት በመነሣት የነፍስ ልብስ የተባለው ‹ክርስቶስ› ሲሆን ፤ እርሱን የምንለብስበት መንገድ ደግሞ ‹ጥምቀት› መሆኑን እንረዳለን፡፡

በዛሬ ጽሑፋችን ምሥጢራትን በመመገብ የእናትነት ድርሻዋን የምትወጣው ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ለምን በሕፃንነት ዕድሜያችን እንድንጠመቅ እንደምታደርገን በጥቂቱ እንመለከታለን፡፡ ብዙ ጊዜ ይህ ርዕሰ ጉዳይ ሲነሣ በተቃራኒ የትምህርት ጎራ ውስጥ ያሉ ወንድሞቻችን ከሚያቀርቧቸው የተቃውሞ አሳቦች መካከል ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡ አንደኛው ‹ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ› የሚለውን የቅዱስ ጴጥሮስን የስብከት ቃል ይዘው ‹እነዚህ የምታጠምቋቸው ሕጻናት ምን ኃጢአት አለባቸው?› ሲሉ የሚጠይቁት ሲሆን ፣ሁለተኛው ደግሞ ‹ገና ሕጻናት ሲሆኑ ምን አውቀው ነው ያለ ፈቃዳቸው የምታጠምቋቸው?› የሚል ከማወቅ ጋር የተያያዘ ጥያቄ ነው፡፡(ሐዋ 2፡38)

የመጀመሪያው ጥያቄ የጥምቀትን ጥቅሞች ካለመረዳት የመጣ ጥያቄ ይመስላል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ጥምቀት ከሚፈጸምባቸው ምክንያቶች አንዱ ለኃጢአት ስርየት እንደሆነ ቢናገርም ‹ለኃጢአት ሥርየት ብቻ› ግን አይልም፡፡ ከሁሉም በላይ በጥምቀት የምናገኘው ትልቁ ጸጋ ‹ልጅነት›ን ነው፡፡ ስለዚህም ታላቅ ጸጋ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአይሁድ አለቃ ለኒቆዲሞስ ‹ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ… › በማለት በጥምቀት ስለሚገኘው የእግዚአብሔር ልጅነት አስተምሮታል፡፡(ዮሐ 3፡5) ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም እንደሚናገረው ቤተ ክርስቲያን ሕጻናትን የምታጠምቀው ኃጢአት ፣በደል አለባቸው ብላ ሳይሆን ፤ ከለጋነት ዕድሜያቸው ጀምረው ፍቅሩን እያጣጣሙ እንዲያድጉ የሚያስችላቸውን የእግዚአብሔር ልጅ የመሆንን ጸጋ ልትሰጣቸው ነው፡፡

ወደ ሁለተኛው ጥያቄ ስንመጣ በራሱ በጥያቄው መነሻ አሳብ ላይ የምንመለከተው እንደ ገደል የሰፋ ክፍተት አለ፡፡ ይህም ክፍተት ጥያቄውን የሚጠይቁ ሰዎች የተነሡበት ‹ሕፃናት አያውቁም› የሚለው ጭፍን መንደርደሪያ ነው፡፡ እነርሱ ‹ሕጻናት እንደማያውቁ በምን አወቁ? አንድ ሕፃን ስላልተናገረና አሳቡን በቃላት ስላልገለጸ ብቻ አያውቅም ሊባል ይችላል? ፡፡ እንዲህ ካሉ ደግሞ የጌታ እናት እመቤታችን ወደ እርሱ እንደቀረበች አውቆ በስግደት የደስታውን ስሜት ስለገለጸው የስድስት ወር ፅንስ ምን ይላሉ? ሳያውቅ ነው የዘለለው ሊሉን ይሆን? ቢቀበሉ ደግሞ ይህን የመሳሰሉ ድንቅ ማስረጃዎችን ከቅዱሳን አበው ገድላት እናቀርብላቸው ነበር፡፡ ነገር ግን እንኳን የአዋልዱን ይቅርና የአሥራው መጻሕፍቱንም ምስክር ለማመን ስለሚቸገሩ ማስረጃ አናባክንም፡፡

ታዲያ እነዚህን ጥያቄዎች ስንጠይቅ እኛ ደግሞ በተቃራኒው ሕጻናት ያውቃሉ ወደሚል ሌላ ጽንፍ እያመራን አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሕፃናትን የምታጠምቀው ያውቃሉ ወይም አያውቁም ብላ አይደለም፡፡ የቤተሰቦቻቸውን እምነት ምስክር በማድረግ ነው እንጂ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በልጅነታቸው ጥምቀተ ክርስትና የተፈጸመላቸው እንዳሉ የሚያሳዩ ልዩ ልዩ የንባብ ክፍሎች አሉ፡፡ ለአብነትም በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በተመሳሳይ ምዕራፍ ላይ የምናገኛቸውን ሐር ሸጯ ልድያንና የወኅኒ ቤተ ጠባቂውን ማቅረብ እንችላለን፡፡ መጽሐፉ ሁለቱም ሰዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንደተጠመቁ ይናገራል (ሐዋ 16፡15 ፣34)፡፡ ታዲያ ከቤተሰቦቻቸው መካከል ሕፃናት ሊኖሩ አይችሉምን?

ሌላው በበዓለ ሃምሳ ከተሰጠው የቅዱስ ጴጥሮስ ስብከት ውስጥም ስለ ሕፃናት ጥምቀት የሚናገር ግልጽ ማብራሪያ እናገኛለን፡፡ ይኸውም ‹ኃጢአታችሁ ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ… የተስፋው ቃል (ተጠምቆ መንፈስ ቅዱስን መቀበል) ለእናንተና ለልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ነውና› የሚለው ሲሆን በዚህ አረፍተ ነገር ውስጥ ‹ለልጆቻችሁ› የሚለው ቃል ያለ ማብራሪያ ጥምቀት ለሕፃናት እንደሚፈጸም የሚያሳይ ነው፡፡(ሐዋ 2፡38-39) ጌታችንም በወንጌል ‹ሕፃናትን ተዉአቸው ፤ ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሉአቸው› ሲል የተናገረውን ቃል እንዴት እንረዳዋለን? ሕፃናት ወደ እግዚአብሔር እንዴት ይቀርባሉ? ሕፃናት ወደ እግዚአብሔር መቅረብ የሚችሉት በምሥጢራት (Sacraments) ነው፡፡ ታዲያ ከምሥጢረ ጥምቀት የበለጠ ሕፃናት እና አምላክን በአባትና ልጅነት የሚያቀራርብ ምን አለ? ሕጻናት እንዳይጠመቁ ከመከልከል የበለጠስ እነርሱን ከፈጣሪ የማራቅ ሥራ ከየት ሊገኝ ይችላል?፡፡(ማቴ 19፡14)
እነ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮትም ቅዱስ ጳውሎስ ለጥምቀት ምሳሌ አድርጎ ያነሣውን የግዝረት ሥርዓት ለሕፃናት ጥምቀት ማስረጃ አድርገው አስተምረውበታል፡፡ በአብርሃም ዘመን ግዝረት የእግዚአብሔር ሕዝብ ወይም ወገን ለመሆን ምልክት ነበር፡፡ ስለዚህም በአብርሃም ቤት የሚወለዱ ሕፃናት ስምንት ቀን ሲሆናቸው እንዲገረዙ ሕግ ወጥቷል፡፡(ዘፍ 17፡10-14) ሕፃኑም በዚያ የቀናት ዕድሜ ላይ እያለ ይገረዛል እንጂ ቆይ ይደግና ጠይቀነው አይባልም፡፡ ልክ እንደ ግዝረቱ በሐዲስ ኪዳንም ጥምቀት ከእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ጋር በሕዋስነት የምንቆጠርበት ምሥጢር ነው፡፡ ግዝረት በሕፃንነት ይፈጸም እንደነበር፣ ጥምቀትም በሕፃንነት ይፈጸማል፡፡ እንደ ቅዱስ ጎርጎርዮስም አባባል ‹የጣቶቻቸው ጥፍር ሳይጸና› በጨቅላነት ዕድሜያቸው ይጠመቃሉ፡፡ ይኸው ሊቅ ሌላው የጥምቀት ምሳሌ የሆነውን ባሕር መሻገር በማንሣት ፣ ባሕሩን የተሻገሩት ሕፃናትም ጭምር እንደሆኑ ፣ጥምቀተ ክርስትናም ለሕፃናት ይፈጸማል ሲል ይናገራል (1ኛ ቆሮ 10፡1-2)፡፡

ጥምቀተ ክርስትና ሁል ጊዜ ተጠማቂው ተጠይቆ ላይፈጸም ይችላል፡፡ ለምሳሌ የመጀመሪያው ሰው አዳም የተፈጠረው የሠላሳ ዓመት ጎልማሳ ሆኖ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አዳምን ከፈጠረው በኋላ በአፍንጫው የሕይወት እስትንፋስን እፍ ብሎበታል፡፡ ይህም እፍታ ለአዳም የልጅነትን ጸጋ ያገኘበት ጥምቀቱ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህን ታሪክ በያዘው የኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ እግዚአብሔር ለአዳም የልጅነት ጸጋውን ከመስጠቱ በፊት እንደ ጠየቀው አይናገርም፡፡ ታዲያ እንዴት የሠላሳ ዓመቱ ጎልማሳ አዳም ያልተጠየቀውን ጥያቄ የአርባን ቀን ልጅ ጠይቁ ይሉናል? ፡፡ እግዚአብሔር አዳምን አልጠየቀውም ማለት አስገደደው ማለት አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ሕፃናትን በቀጥታ እነርሱን አልጠየቀችም ማለት አስገድዳቸዋለች ማለት አይደለም፡፡ አዳም የኋላ ኋላ በፈቃዱ ፈጣሪውን ክዶ ልጅነቱን እንዳጣ እንዲሁ የእግዚአብሔርን አባትነት ያልፈለጉትም አድገውም ቢሆን የመካድ መብታቸው የተጠበቀ ነው፡፡

ሌላው አንዳንድ ጊዜ ከማመን (ከትምህርት) ጥምቀት ሊቀድም የሚችልባቸውም ሁኔታዎች እንዳሉ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ነው አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያቱን ወደ ዓለም ሲልካቸው ‹ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው› ሲል ያዘዛቸው (ማቴ 28፡19)፡፡ ልብ በሉ በዚህ የጌታችን ትዕዛዝ ውስጥ በቀዳሚነት የተነገረው ‹አስተምሩ› የሚለው ሳይሆን አጥምቁ የሚለው ነው፡፡ ስለዚህ አድገው ወደ ቤተ ክርስቲያን ለሚገቡ ካልሆነ በቀር ለሕፃናት ጥምቀት ሊቀድም ይችላል፡፡ ደቀ መዝሙርነት የሚገኘው ከጥምቀት በኋላ ነው፡፡ ሳይጠመቁ ደቀ መዝሙርነት የለም፡፡

በአጠቃላይ ከላይ ያቀረብናቸው ነጥቦች የሕፃናትን ጥምቀት ተገቢነት የሚያሳዩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶች ሲሆኑ በተቃራኒው ግን የሕፃናትን ጥምቀት የሚከለክል ምንም ዓይነት ትምህርት ወይም ማስረጃ በመጽሐፍ ቅዱስ አናገኝም። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያናችን በዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተግባሯ ብትመሰገን እንጂ የምትነቀፍ አይደለችም።

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
ዛሬ ወደ ዮርዳኖስ እንዴት ወረድን?

እድሜ ዘመኑን በበረሃ የኖረው ቆዳ ለባሽ፣ ጠፍር ታጣቂው መናኝ ቅዱስ ዮሐንስ "ንስሐ ግቡ" እያለ በመስበክ የጌታን መንገድ ያዘጋጅ፣ ጥርጊያውንም ያቀና ነበር። በዮርዳኖስም ወንዝ ሲያጠምቅ በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳ፣ በዮርዳኖስም ዙሪያ ባሉ አገራት የሚኖሩ ሰዎች ወደ እርሱ እየመጡ ኃጢአታቸውን በመናዘዝ ይጠመቁ ነበር። ራሱ አጥማቂው ቅዱስ ዮሐንስ "እኔ ለንስሐ በውኃ አጠምቃለሁ" ሲል እንደ ተናገረ ጥምቀቱ ሰው በደሉንና ክፋቱን አስቦ በመጸጸት የሚጠመቀው "የንስሐ ጥምቀት" ነበር።

ንስሐ ለሚለው ቃል የግሪኩ አቻው ሜታኖያ (metanoia) ሲሆን ትርጉሙም የአስተሳሰብ ለውጥ (change of mind) ማለት ነው። ስለዚህ ወደ መጥምቁ ዮሐንስ ይመጡ የነበሩት ተጠማቂዎች የቀድሞ ክፋታቸውን ትተው፣ በተቀደሰ ቁጭት ሕሊናቸውን ወደ ጽድቅ ለመመለስ እና ራሳቸውን ለመለወጥ የወሰኑ ነበሩ። አመጣጣቸውም በተሰበረ ልብ ነው።

ይሁን እንጂ ልባቸው እንደ ዐለት የጸና ፈሪሳውያን እና ሰዱቃውያን ግን እንደ ሌሎች ሰዎች በጸጸትና በትሕትና ሳይሆን በትዕቢት እንደ ታጀሩ ወደ መጥምቁ ዮሐንስ መጡ። እንደ ቅዱስ ዳዊት የተሰበረ አጥንት (ልብ) ሳይኖራቸው፣ በኃጢአት ያረጀ ፊተኛው ልባቸውን በመጠየፍ "አቤቱ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ" ብለው ሳይለምኑ፣ ታጥበው ብቻ ከበረዶ ይልቅ ነጭ ለመሆን ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ወረዱ።

ቅዱሱም መናኝ ባያቸው ጊዜ አመጣጣቸውን ያውቀዋልና "እናንተ የእፉኝት ልጆች" ሲል ገሰጻቸው። ከእፉኝት ጠባያት ውስጥ አንዱ ተናድፋ ወደ ውኃ (በቅርቧ ወዳለ ባሕር) መሸሿ ነው። ፈሪሳውያኑም እንዳሻቸው ክፋት አድርገው ሲያበቁ፣ የእርሱን የንስሐ ጥምቀት መሸሸጊያ ለማድረግ ወደ ዮርዳኖስ ያለ ምንም ጸጸት ይሮጣሉና እንዲህ አላቸው። እኛስ የዮርዳኖስ ባሕር ተምሳሌት ወደምትሆነው ጥምቀተ ባሕር እንዴት ወረድን? በንስሐ እና በጸጸት፣ የቀደመውን ክፋት ለመተው በቆረጠ የተለወጠ ሕሊና ወይስ እንዲሁ ባልተጸጸተ ፈሪሳዊና ሰዱቃዊ ሕሊና? ዛሬ ወደ ዮርዳኖስ እንዴት ወረድን?

እንኳን ለበዓለ ጥምቀት በሰላም አደረሳችሁ!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
+++ "ሰማያት ተከፈቱ" ማቴ 3፥16 +++

ጌታችን እንደ አይሁድ ሕግ በአደባባይ የሚያስተምርበትና አገልግሎቱን የሚጀምርበት እድሜው ሲደርስ (በ30 ዓመቱ) ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ሊጠመቅ መጣ። የጽድቅ ፀሐዩ ክርስቶስ ለጥቂት ጊዜ እያበራ እና እየነደደ ሕዝቡን ደስ ያሰኝ ወደ ነበረው የአጥቢያው ኮከብ ዮሐንስ ዘንድ ሊጠመቅ በትሕትና መጣ።(ዮሐ 5፥35) ቅዱስ ዮሐንስ ግን እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል እንጂ አንተ ወደ እኔ ለመጠመቅ ትመጣ ዘንድ አይገባም? በጎ ሥጦታዎች ሁሉ ፍጹምም በረከት የብርሃናት አባት ከሆንከው ከአንተ ወደ እኛ ይወርዳሉ እንጂ እንዴት ከምድር ወደ ሰማይ ይወጣሉ? ይህስ አይሆንም ብሎ ይከለክለው ነበር። ጌታም ዮሐንስን "አጥምቀኝ እኮ ነው የምልህ?!" ሲል አልተቆጣውም። ይልቅስ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና "አሁንስ ፍቀድልኝ" ሲል ሊነገር በማይችል ትሕትና ለመነው። ይህን ታላቅ አምላካዊ ተማጽኖ ሰምቶ እንዴት የዮሐንስ ልብ ሊጸና ይችላል?! ያን ጊዜ ሎሌው ዮሐንስ ፈቀደና ጌታውን አጠመቀ።(ማቴ 3፥15)

ጌታችን ኢየሱስም ተጠምቆ ከውኃ ሲወጣ እነሆ ሰማያት ተከፈቱ። ወንጌላዊው "ሰማያት ተከፈቱ" እንጂ "ሰማያት ተከፈቱለት" ብሎ አልጻፈም። ምክንያቱም እርሱ እኛን ለመቤዠት ሰው ቢሆንና በባሕር መካከል ቆሞ ቢታይም በሰማይ ካለው መንበሩ ስላልጎደለ በሰማያትም ለሚኖረው ለእርሱ "ሰማያት ተከፈቱለት" አይባልም። ይልቅስ "ሰማያት ተከፈቱ" የሚለው ቃል ለእኛ በጌታ ጥምቀት ያገኘናቸውን ሰማያዊ በረከቶች የሚያሳይ ነው።

ጌታችን ተጠምቆ ወዲያው ከውኃው እንደ ወጣ ሰማያት ተከፈቱ ማለቱ፣ መድኃኒታችን በሰማይ ወዳለው መንግሥቱ እንድንገባ ተዘግቶ የነበረውን በር በጥምቀቱ እንደ ከፈተልን ለማስረዳት ነው። የማዳን ሥራውን ሲጀምር ተጠምቆ የሰማዩን ደጅ እንደከፈተልን፣ ማዳኑን ሲፈጽም ደግሞ ተሰቅሎ በመሞት የሲዖልን ደጆች ሰባብሮልናል።

ሌላው ከጥምቀቱ በኋላ ሰማያት መከፈታቸው፣ ተዘግቶ የቆየ ቤት በሩ በተከፈተ ጊዜ በውስጥ ያሉ ነገሮች እንዲታዩ በዘመነ ብሉይ ተሰውሮ የነበረው በሰማያት የሚኖረው የእግዚአብሔር የሦስትነቱ ምሥጢር አሁን ግልጥ ሆኖ መታየቱን ያመለክታል። ይኸውም ወልድ እግዚአብሔር በባሕረ ዮርዳኖስ ቆሞ በመታየቱ፣ አብ በደመና "የምወደው ልጄ ይህ ነው" ብሎ በመናገሩ እና መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በርግብ አምሳል በመውረዱ ነው።

ሁላችንም እንደምናውቀው ሰማይ ለሚያምንም ሆነ ለሚጠራጠር ሁሉ የሚታይ ነገር ነው። ይሁን እንጂ ሁሉም የሚያዩት ሰማይ ግን "ሲከፈት" ለመመልከት መጠመቅ ያስፈልጋል። ልክ እንደዚህ ሰማይ በሚያምነውም በማያምነውም እጅ የሚገኝ እና ሁሉም የሚያየው (የሚያነበው) መጽሐፍ "መጽሐፍ ቅዱስ" ነው። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስን ሁሉም ያንብቡት እንጂ የምሥጢር በሩ እንዲከፈትና ውሳጣዊ መልእክቱን ለመረዳት ግን መጠመቅ ያስፈልጋል።

እንኳን ለበዓለ ጥምቀቱ በሰላም አደረሰን!!!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
"ከቤተ ክርስቲያን የሚበልጥ ብርቱ (ጠንካራ) ምንም የለም። ይህችውም ከሰማይ ከፍ ያለች ከምድርም ይልቅ የሰፋች ናት። አታረጅም ነገር ግን ዘወትር ታበራለች።" … " ቤተ ክርስቲያን በዘመናት ሁሉ ትሰፋለች። መታሰቢያዋም የሚጠፋ (የሚሞት) አይደለም።" … "ቤተ ክርስቲያን በስንቶች ውጊያ ተደርጎባት ነበር? አልተሸነፈችም እንጂ። የተዋጓት አላውያን ፣ የጦር መሪዎች ፣ ነገሥታቱስ ምን ያህል ናቸው? ። የተማሩና ኃይልን የተሞሉ ጎበዞች ሐዲሲቷን ቤተ ክርስቲያን በብዙ ጎዳናዎች ተዋግተዋት ነበር። ሊነቅሏት ግን አልቻሉም። ነገር ግን እርሷን የተዋጉ ጥቂቶች ለዝምታና ቶሎም ለመረሳት ተላልፈው ተሰጥተዋል። የወጓት ቤተ ክርስቲያን ግን ከሰማይ በላይ ከፍ ከፍ ብላለች። ቤተ ክርስቲያንን ድል ከማድረግስ ፀሐይን ማጥፋት (ማጨለም) ይቀላል። ሰው ሆይ! ከቤተ ክርስቲያን የሚበልጥ ኃያል ምንም የለም። ከሰው ብትጣላ ወይ ታሸንፋለህ አልያም ትሸነፋለህ። ቤተ ክርቲያንን ግን ብትጣላ፣ ታሸነፍ ዘንድ የሚቻልህ አይደለም። እግዚአብሔር ከሁሉ ይልቅ ኃያል ነውና። እግዚአብሔር መስርቷታል፣ እንግዲህ ማን ሊነቀንቃት ይችላል? "

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
(ከተለያዩ ድርሳኖቹ ላይ ስለ ቤተ ክርስቲያን ከተናገራቸው የተሰበሰበ።)

#ቤተክርስቲያን_መዋዒት
#ቤተክርስቲያን_አሸናፊት

ትርጉም: ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com

ቴሌግራም
https://www.tg-me.com/Dnabel
እንደ እመቤታችን ይህ ዓለም ያልተገባው ማን ነው? የእርሷ ስደት የሚጀምረው ገና በእናቷ ማኅጸን ሳለች ነው። ከተወለደችም በኋላ ሰይጣን ዕረፍት አልሰጣትም። ክፉ መንፈስ ባደረባቸው አይሁድ ምክንያት ብዙ መከራ ተቀብላለች። ከወለደችው የበኩር ልጇ የተነሣ እንደ ሰይፍ የሚወጉ ብዙ የልብ ኃዘኖች ደርሰውባታል። ልጇ የተሰደባቸው ስድቦች በላይዋ ወድቀዋል። በጅራፍ መገረፉ፣ በዘንግ መመታቱ፣ በጦር መወጋቱ የእናትነት አንጀቷን እንደ እሳት አቃጥለዉታል። የማዳን ሥራውን ፈጽሞ ከዐረገ በኋላም የትንሣኤው ጠላት የነበሩት አይሁድ የትንሣኤን እናት ድንግልን አሳድደዋታል። ይህች ዓለም ለአንዲት ደቂቃ እንኳን ለእመቤታችን ተገብታት አታውቅም ነበር።

ስለዚህ ከምድራዊቷ ወደ ሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም ሊያሸጋግራት፣ ከክፉው ወደ መልካሙ ዓለም ሊጠራት ልጇ በታላቅ ልዕልና ወደ እርሷ ወረደ። ጌታ ወደ ማኅጸኗ እቅፍ በገባ ጊዜ "ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች። መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች። የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና" ስትል እንዳመሰገነችው፣ ዳግመኛም እናቲቱ ወደ ልጇ እቅፍ በገባች ጊዜ በዚህ ቃል መልሳ አመስግናዋለች።

እንኳን ለእመቤታችን በዓለ ዕረፍት በሰላም አደረሰን!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
ፎቶ: የእመቤታችን መቃብር በሚገኝበት ጌቴሴማኒ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com

ቴሌግራም
https://www.tg-me.com/Dnabel
2025/07/14 08:56:08
Back to Top
HTML Embed Code: