Telegram Web Link
+++ "ስንሞት ያመናል እንዴ?" +++

ሕፃናት መጠየቅ ይወዳሉ። አንዴ መጠየቅ ከጀመሩ በኋላ ደግሞ ከእነርሱ የሚወጣው "ለምን ሆነ?" የሚለው የጥያቄ ዝናብ እንዲህ በቀላሉ ቶሎ የሚያባራ አይደለም። እኛም በእነዚህ ጥያቄዎቻቸው ቶሎ ተሰላችተን ወይም ተበሳጭተን ይሆናል። ይሁን እንጂ ጉዳዩ ግን የሕፃናቱ አዲስ አእምሮ ራሱን የሚያሳድግበትና የነገ ማንነታቸውን የሚቀርጽበት ወሳኝ ሂደት ነው። የነገ ወጣቶችን ማንነት የሚቀርጹት ዛሬ "ለምን?" እያሉ ለሚጠይቁ ሕፃናት የምንመልሳቸው መልሶች ናቸው። ስለዚህ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባናል።

በጠና የታመመ ሕፃን ልጅ ያላት አንዲት እናት ነበረች። ይህች እናት በምትችለው ሁሉ ልጇን አሳክማና ተንከባክባ ለማዳን ብትጥርም፣ ይህ ልፋቷ ግን ሊሳካላት አልቻለም። ልጇን የያዘው በሽታ መድኃኒት ስላልነበረው ወደ ሞት አፋፍ አቅርቦታል። ታዲያ አንድ ቀን ሕፃኑ ልጅ እናቱን እንዲህ ሲል ጠየቃት :- "እናቴ፣ መሞት ምን ይመስላል? ስንሞት ያመናል እንዴ?"

በእናትየው ዓይኖች እንባዎች ሞሉ። ፊቷም በኃዘን ደፈረሰ። የረሳችው ነገር ያለ ይመስል "ቆይ መጣኹ" ብላ ሮጣ ከክፍሉ ወጣች። ብቻዋን ስቅስቅ ብላ አለቀሰች። ልጇ የጠየቃትን ጥያቄ መመለስ እንዳለባት ብታውቅም ለዚህ ለጋ አእምሮ እንዴት አድርጋ መልስ እንደምትሰጥ ግራ ገብቷታል። እንደ ምንም ራሷን አረጋግታና ጥበቡን እንዲሰጣት ወደ ፈጣሪዋ ተማጽና ተመልሳ ወደ ልጇ ክፍል ገባች።

ሕፃኑ መልሱን በጉጉት ይጠብቃል። እናትየውም የውስጧን ኃዘን ለመሰወር ለይምሰል ፈገግ ብላ እንዲህ አለችው "ልጄ፣ ታስታውሳለህ አንድ ጊዜ ጎረቤት ያለ ጓደኛህ ቤት ሄደህ ስትጫወት አምሽተህ ስለደከመህ በዚያው እንቅልፍ ወስዶህ ነበር። ከዚያም በማግስቱ ግን ስትነቃ ራስህ ያገኘኸው በመኖሪያ ቤታችን ውስጥ ስለሆነ 'እንዴት እዚህ መጣኹ?' እያልክ ስትጠይቀኝ ነበር። እኔም አባት ወደዚያ መጥቶ በጥንካራ ክንዶቹ ተሸክሞህ የአንተ ወደ ሆነው ቤትህ እንዳመጣህ ነግሬሃለኹ። አስታወስክ?"

ልጅየው :- "አዎን እናቴ"

እናትየው ቀጠለች :- "የኔ ልጅ፣ ሞትም እንደዚሁ ነው። እኛ መኖሪያችን ባልሆነች በዚህ ዓለም ሆነን እናንቀላፋለን። የሰማይ አባታችን እግዚአብሔር ደግሞ ብርቱ በሆኑ እጆቹ አቅፎ ወደ ሰማይ ይወስደናል። ከዚያም ነግቶ እንደ ገና ስንነቃ ራሳችንን በገዛ አባታችን ቤት ውስጥ እናገኘዋለን" አለችው።

እውነት ነው! ሞት ለክርስቲያኖች ሁሉ የሚኖረው ትርጉም ይህ ነው። ከእግዚአብሔር ተልከን ወደዚህ ዓለም እንደ መጣን ወደ እርሱ መመለሳችን ደግሞ የማይቀር ነው። ሞት ማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ "ድንኳን" ብሎ ከገለጸው ከጊዜያዊው መቆያችን ወደ እውነተኛው መኖሪያ አገራችን መሸጋገር ነው።

በ2ኛው ክፍለ ዘመን የነበረው ግሪካዊው ፈላስፋ አርስጣደስ በጊዜው አዲስ ሃይማኖት ስለሆነበት ስለ ክርስትና እና ይህ የክርስትና እምነት በሞት ላይ ስላለው እሳቤ ለአንድ ወዳጁ በጻፈለት ደብዳቤ ላይ እንዲህ የሚል ንግግር አስፍሮ ነበር። "ከክርስቲያኖቹ ውስጥ አንድ ጻድቅ የሆነ ሰው ከዚህ ዓለም በሞት ቢለይ ምእመናኑ ደስ ይሰኛሉ። ለፈጣሪያቸውም ምስጋናን ያቀርባሉ። ያም ሰው ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላ ቅርብ ሥፍራ የተሸጋገረ ይመስል ሰውነቱን በመዝሙራትና በምስጋና አጅበው ይሸኙታል" ይላል። ክርስትና እንዲህ ነዋ!

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም ክርስቲያኖች በሞት ላይ ሊኖራቸው ስለሚገባ እይታ ሲናገር "ከእኛ መካከል አንድ ሰው በሞተ ጊዜ፣ የማያምነው ሬሳ ሲያይ ክርስቲያኑ ግን ያንቀላፋ ሰውነት ይመለከታል። ያላመነው "የሞተው ሰው ሄደ" ይላል። በርግጥ በዚህ እኛም እንስማማለን። ነገር ግን ወደ የት እንደሚሄድም እናውቃለን። የሚሄደው ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ጴጥሮስ እንዲሁም ሌሎች የቅዱሳን ማኅበር ወደ አሉበት ነው። በኋላም ተስፋ መቁረጥ ባለበት እንባ ሳይሆን፣ በክብርና በማንጸባረቅ እንደሚነሣ እናስባለን!"

+++ "ለባሪያዎችህ ሞት የለባቸውም ፍልሰት እንጂ" +++

የወንድማችንን የገብረ ኢየሱስን ነፍስ በዕረፍት ቦታ ያኑርልን!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲሱ ዓመት ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር የተሰጠን ሌላ አዲስ ዕድል ነው። አማኑኤል ከእኛ ጋር ለመሆን የእኛን ሥጋ ተዋሕዷል። አምላክነቱ ሳያሳስበው የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አድርጉዋል። በደሃ ቤት አድሯል፣ በበረት ተወልዷል፣ ከብርድ መከለያ ጨርቅን ፈልጓል፣ ፍጥረትን የሚመግብ እርሱ ከእናቱ የድንግልናዋን ወተት ለምኖ አልቅሷል፣ እንደ ሕፃናት በጉልበቱ ድኋል፣ ለእናቱ እየታዘዛት ጥቂት በጥቂት አድጓል። ከአደገም በኋላ ራሱን የሚሰውርበት ጎጆ ሳይኖረው በተራራ ተንከራቷል፣ ተርቧል፣ ከኃጢአተኞች በደረሰበት ተቃውሞ ተሰድቧል፣ ተገፍቷል። ከብቻዋ ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ሆኗል።

ከእኛ ጋር ለመሆን ብቻ ሳይሆን በእኛ ውስጥ ለመኖር ደግሞ በእለተ አርብ በመስቀል ተሰቅሎ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ ተሰጥቶናል። እኛስ ወደ እርሱ ሊያቀርበን ይህን ሁሉ ከሆነልን አምላክ ጋር ለመኖር ምን አደረግን? ለእርሱ ብለን ክፋትን አወገዝን? የተሸከምነውን ኃጢአት በንስሐ አራገፍን? ሥጋ ወደሙን ተቀበልን?

ከእግዲህስ በኃጢአት ያረጀ ማንነታችንን እንተው። አዲሱን ዓመት "ማለዳ ማለዳ አዲስ" ከሆነው ፈጣሪያችን ጋር ለመኖር ለራሳችን ብሩህ ተስፋ እንሰንቅ። እስኪ አምና ወድቀን ከተሰበርንበት የዘር፣ የጥላቻ ጉድጓድ ወጥተን ዘንድሮን ተዋድደን፣ ተፋቅረን በሰላም እንኑር። እስኪ ደግሞ ወደ ሰላማዊ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀርበን ይህችን ዓመት በሰላም ጀምረን እንፈጽማት።

መልካም አዲስ ዓመት!!!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን

https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
ሐመረ ብርሃን የብራና መጻሕፍት አዘጋጆች በአዲሱ ዓመት በዓል እየበላን ቁም ነገር የምንሠራበትን ዕድል አመቻችተውልናል። እንጠቀምበት!

ሥጋውን ለመብል ቆዳውን ለንባብ!
+++ "የእኛ የጥፋት ውኃ የሚጎድለው መቼ ነው?" +++

በኖኅ ዘመን የነበሩት ሰዎች አመጸኞች ሆኑ። የእግዚአብሔርን የምሕረት ጥሪ እምቢ ብለው መንገዳቸውን በፊታቸው አበላሹ። ምድሪቱንም በግፋቸው ሞሏት። ስለዚህም እግዚአብሔር ከትውልዱ ጻድቅ የነበረው ኖኅና ቤተሰቡን አስቀርቶ ሌሎቹን ከምድር ጋር ያጠፋቸው ዘንድ የጥፋት ውኃን አዘነመ። የታላላቅ ቀላያት ምንጮች ሁሉ ተነደሉ። የሰማይ መስኮቶችም ከፈቱ። ምድር በአምላክ የቁጣ ውኃ ተጥለቀለቀች። በመርከቢቱ ከነበሩት በቀር ምድር አንዲት ነፍስ አልቀረላትም።

እግዚአብሔር ከዚህ ሁሉ ቁጣ በኋላ በመርከቡ የነበሩትን ኖኅንና እንስሳት አራዊቱን አሰበ። በምድርም ላይ ነፋስን አሳለፈ። የቀላያቱን ምንጮች የሰማዩንም መስኮቶች ደፈነ። ዝናሙንም ከሰማይ ከለከለ። ሞልቶ የነበረውም ውኃ ቀስ በቀስ እየጎደለ መጣ። በመጽሐፈ ኩፋሌ እንደ ተቀመጠው በውኃ ተጥለቅልቃ የነበረችው ምድር ግልጥ ሆና የታየችው በመጀመሪያው ወር መባቻ ላይ ነበር።(ኩፋ 7፥1)

ባለ ዘመኖቹ እኛ ልክ በኖኅ ጊዜ እንደ ነበሩት የቀድሞ ሰዎች ክፋታችን ተካክሏል። መንገዳችንን በእግዚአብሔር ፊት አበላሽተናል። ምድርን በግፋችን ሞልተናታል። ስለዚህ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ያወረደው የጥፋት ውኃ ለእኛም ይገባን ነበር። እኛ ግን እርሱ እስኪቀጣንም አልጠበቅንም። እርስ በእርሳችን እየተጋደልን ምድራችንን በጥፋት ደም አጥለቀለቅናት። ወንድም ወንድሙን በጥይት ነደለ፣ በስለትም ሰውነቱን ከፈተ። የቁጣው ደም ከሰው እየመነጨ ምድርን ሸፈነ።

ታዲያ በዚህች ጎስቋላ ምድራችን ላይ የፈሰሰውን ደም የሚያደርቅ የይቅርታ ነፋስ መቼ ይነፍሳል? እንደ ውኃ ያጥለቀለቀንስ ደም መቼ ይጎድላል? የምንሰማው መጨካከንስ እያደር እያደር የሚቀለው መቼ ነው? አሁን እኮ የመጀመሪያው ወር (መስከረም) መባቻ ነው። ምድራችን የሸፈናት ጥላቻ እና መገዳደል ተገፍፎላት ዳግመኛ ግልጥ ሆና አናያትም?

የእኔ የአዲሱ ዓመት ስእለቴ ይህ ነው። የእናንተስ?

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ቤተሰብ ይሁኑ

https://www.facebook.com/AbelKassahunMekuria12
https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
የጌታውን እናት የሰላምታ ድምጽ ሰምቶ በማኅጸን በደስታ የዘለለውን (የሰገደውን) ጽንስ፣ በንጉሡ ፊት በክፉት የደነሰችው ልጅ አንገቱን አስቆረጠችው።

ጽንሱ ስለ ሕይወት መምጣት በጠባቡ አዳራሽ በማኅጸን ሲያመሰግን፣ የሄሮድያዳ ልጅ ግን የነቢዩን ሕይወት ስለ ማስጠፋት በሰፊው የንጉሡ አዳራሽ ዘፈነች።

አዲሱ ዓመት የኢትዮጵያ ልጆች በሄሮድያዳ ምክር የማይሄዱበት፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተማሩ ሆነው የሚያድጉበት በጎ ዘመን ያድርግልን!!!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
https://www.tg-me.com/Dnabel
https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
+++ ስለ ታሰሩ ሰዎች +++

አንዳንድ ነገሮች አሉ። እንዴት እንደምንጀምር እንጂ እንዴት እንደምናቆም ጨርሶ የማናውቃቸው። አጀማመሩን ስላወቅን እና ስለቀለለን ብቻ አቋቋሙም የዚያኑ ያህል ቀላል የሚመስለን። እውነታውስ? በነጻ ፈቃዳችን መርጠን እንጀምራለን። ነገር ግን ያ የተሳሳተውን ነገር መምረጥ በመቀጠላችን የመረጥነው እርሱን ያለመምረጥ ነጻነታችንን እስኪነጥቀንና ጌታ እስኪሆንብን እንደርሳለን።

በሱስ የተያዘ ሰው ከዚያ ነጻ ለመሆን ማናቸውንም ነገር ቢያደርግ ደስ ይለዋል። ግን ሱሱ ልማድ ሆኖበት አንቆ ይይዘዋል። በዚህ ከቀጠለ መጨረሻው ሞት እንደ ሆነ ቢያውቀውም፣ ራሱ በፈጠረው ነገር እንዲህ በመሰቃየቱ ምክንያት መልሶ ራሱን ቢጠላውም በእጁ የያዘውን የመጠጥ ብርጭቆ ግን ወርውሮ መስበር አይችልም። መላ ሰውነቱን ስለተቆጣጠረው እርሱ የጨበጠው ጠርሙስ እስረኛ ነው።

ይህን ግን ስለ መጠጥ ብቻ የምንናገር አይደለም። በጥቂቱ ብንጀምራቸውም በኋላ ግን አርቀን መጣል ያልቻልናቸው እና ሱስ ስለሆኑብንን ኃጢአቶች ሁሉ ይመለከታል።

እንዲህ በራሳችን ወህኒ ለታሰርን ምስኪኖች ቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜ በቅዳሴዋ "እግዚአብሔር ከእስራታቸው ይፈታቸው ዘንድ ስለ ታሰሩ ሰዎች እንማልዳለን" ስትል ትማልዳለች። እኛም ከመዝሙረኛ ጋር "አቤቱ ስምህን አመሰግን ዘንድ፥ ነፍሴን ከወህኒ አውጣት" እያልን ልንማጸነው ይገባል።(መዝ 142፥7) እኛ በራሳችን ላይ ያደረግነው የትኛውም ዓይነት እስራት የሲኦልን ደጆች ከሰባበረው የብረቱንም መወርወሪያ ከቆረጠው ከክርስቶስ ኃይል አይበልጥም። ስለዚህ ከፈቀድንለትና አብረነው ሠራተኛ ለመሆን ከወሰንን ዛሬም ከገባንበት ሲኦል ሊያወጣን የታመነ አምላክ ነው።

ሰው በራሱ ፍላጎት ብቻ ወደ ኃጢአት ጉድጓድ መግባት ቢችልም ያለ እግዚአብሔር ረድኤት ግን ከገባበት መውጣት አይችልም። ስለዚህ "እንዴት ከገባኹበት ጉድጓድ በራሴ መውጣት አልቻልኩም?!" እያልህ አትበሳጭ። ይልቅ ረድኤተ እግዚአብሔርን እየለመንህ በምትችለው ሁሉ ታገል።

ዲያቆን አቤል ካሳሁን

https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
ብዙ ሰው "ያሰብኹት ሁሉ ምንም ሊሳካልኝ አልቻለም" እያለ ያጉረመርማል፤ "እግዚአብሔርማ እኔን ሳይተወኝ አልቀረም!" እያለ ፈጣሪውን ያማርራል። "ይሰጠኛል" ሳይሆን "አገኘዋለሁ" ብሎ ይጀምርና ሳይሆን ሲቀር በእጁ የነበረውን የነጠቀው ያህል አምላኩ ላይ ያለቅሳል። ስታቅድ ያላስታወስከውን አምላክ ያቀድከው ሲፈርስ ስሙን እየጠራህ ስለምን ትወቅሰዋለህ? በሕይወትህ መቼ ቦታ ሰጠኸው? እንደ ፈቃዴ ካልሆነ አልህ እንጂ መቼ "እንደ ፈቃድህ ይሁን" ብለህ ጸለይህ? ባላማከርከው ለምን ተከሳሽ ታደርገዋለህ?

ልሥራ ብለህ በተነሣህበትም ቀን እንዲሁ በግዴለሽነት ስሙን ጠርተህ እንደ ሆነም ራስህን መርምር? በትክክል ጸልየህና በመንገድህ ሁሉ ይመራህ ዘንድ ፈቅደህ ከጀመርህ ግን ግድ የለም እረኛህን እመነው። አንተ እንደ ሎጥ ከመረጥኸው እና ለጊዜው የገነት አምሳል ሆኖ ከሚታይህ ነገር ግን እግዚአብሔር ከማይከብርበት ከለምለሙ ሰዶምና ገሞራ ይልቅ፣ አሁን ብዙም ለአይን የማይስበው በኋላ ግን ወተትና ማር የሚያፈሰው ለልጅ ልጆችህም ርስት የሚሆነው እግዚአብሔር የሚሰጥህ ከነአን ይሻልሃል።

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
አዲስ አበባ

ቤተሰብ ይሁኑ

https://www.facebook.com/AbelKassahunMekuria12
https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
+++ ዝምተኛው ፓትርያርክ +++

ከእለታት በአንዱ ቀን በግብጽ መንበረ ፓትርያርክ ሕንፃ እንግዳ መቀበያ ክፍል ውስጥ አረጋዊ ጳጳስ ቆመው ሳሉ አንድ ሰው ወደ ውስጥ ሲገባ ‹‹ብዙ ልጆች ያሉህ፣ ሸክምህ የከበደብህ ልጄ ሆይ ና!›› ሲሉ ጠሩት፡፡ ሰውየውም ግራ እየተጋባ ‹‹ማን? እኔን ነው አባቴ? እኔ እኮ አንድ ልጅ ብቻ ነው ያለኝ›› አላቸው፡፡ ጳጳሱም ‹‹ልጄ ሆይ፣ አልተረዳህም እንጂ ሸክምህ ከባድ ልጆችህም ብዙ ናቸው›› አሉት፡፡ እርሱ ግን ‹‹እመኑኝ አንድ ልጅ ብቻ ነው ያለኝ›› እያለ ተከራከራቸው፡፡ በዚህም ጊዜ አረጋዊው ‹‹ልጄ፣ እንግዲያውስ ነገ ትረዳዋለህ›› ብለው ጥለውት ሄዱ፡፡ ይህ በሆነ በማግስቱ ሰባት ልጆች የነበሩት የዚህ ሰው ወንድም ድንገት በአደጋ ምክንያት ሞተ፡፡ ታዲያ የወንድሙን ሰባት ልጆች የማሳደግ ኃላፊነት በእርሱ ላይ ወደቀ፡፡ ትናንትና አንዲት ሴት ልጅ ብቻ የነበረው ዛሬ ግን የ8 ልጆች አባት ሆነ። ይህም ሰው ነገሩን ቀድመው ወደ ነገሩት እኚህ አባት ሄዶ የሆነውን ሲያብራራላቸው ‹‹ልጄ፣ ሸክምህ የከበደና ብዙ ልጆች ያለህ እንደ ሆንህ ስነግርህ እኮ አላመንከኝም?!›› አሉት፡፡ ለመሆኑ እኚህ አባት ማን ይሆኑ?

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1950ዎቹ መጀመሪያ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን በሙስና የተጥለቀለቀችበትና ትልቅ አስተዳደራዊ ችግር ውስጥ የገባችበት አሳዛኝ ጊዜ ነበር፡፡ በኋላም የሕዝቡ ቁጣ ገንፍሎ ፓትርያርኩን አግቶ እስከ መውሰድና ‹‹ሥልጣኔን በፈቃዴ ለቅቄያለሁ›› የሚል ደብዳቤ ላይ ተገድደው እንዲፈርሙ እስከ ማድረግ ደርሶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ግርግር መሐል የጸጥታ አስከባሪ ፖሊሶች ደርሰው ፓትርያርኩን ከዚህ እገታ በማዳን ወደ መንበራቸው እንዲመለሱ አድርገዋል፡፡ ይህ ከሆነም ከአንድ ዓመት በኋላ የቤተ ክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ባደረገው ጉባዔ ፓትርያርኩ ዮሳብ (ዳግማይ ዮሴፍ) ከኃላፊነታቸው እንዲነሡና በግብጽ ካሉ ገዳማት በአንዱ ገዳም እንዲኖሩ በአንድ ድምጽ ወሰነ፡፡ የግብጽ ቤተ ክርስቲያንም ከሦስት ዓመት በላይ ያለ ፓትርያርክ ቆየች፡፡ ይህም የቅብጥ ቤተ ክርስቲያንን መንፈስ ያወከና በጉልበቷ ያንበረከከ አሳዛኝና የማይረሳ ጥቁር ትውስታ ሆነ፡፡

እንደ ጎልያድ ክንዱን አፈርጥሞ ይገዳደራት የነበረን የሙስና እና የብልሹነትን መንፈስ አንገቱን ቆርጠው የሚጥሉ እንደ ዳዊት ያሉ አባት ለግብጽ ቤተ ክርስቲያን ተገኙላት፡፡ እኚህም የከተማው መናኝ ፓትርያርኩ አቡነ ቄርሎስ ናቸው፡፡ አቡነ ቄርሎስ በሙስና እና በብልሹ አስተዳደር ምክንያት የምታነባ እና በልጆቿ ተወግታ እየደማች ያለች ቤተ ክርስቲያንን ቢረከቡም፣ በአሥራ ሁለት ዓመት (1959-71) ውስጥ ግን ይህ ሁሉ ተቀይሮ የቅብጧ ቤተ ክርስቲያን እንደ አዲስ ያንጸባረቀችበትና ያበራችበት ጊዜ ሆኗል፡፡ ይህ ወቅት የቅዱስ ማርቆስ አጽም ወደ ግብጽ የመጣበት፣ የቅብጥ ቤተ ክርስቲያን ወደ ዓለም መስፋፋት የጀመረችበት ወርቃማ ጊዜ ነው።

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የራሷ ፓትርያርክ እንዲኖራት ይደረግ በነበረው የንጉሡና የእኛ ሊቃውንት እንቅስቃሴም ላይ እርሳቸውም ጉዳዩ የራሳቸው እስኪመስል ድረስ ትልቅ ጥረትና ትግል አድርገዋል፡፡ በዚህም ድርጊታቸው የቅብጧ ቤተ ክርስቲያን ኢትዮጵያን በተመለከተ አቅሌስያዊ አትሕቶን (Ecclesial kenosis) እንድትላበስ አድርገዋታል፡፡

አቡነ ቄርሎስ ለፓትርያርክነት ሲታጩ የታቃወሙ ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ተቃዋሚዎች አንዱ በኋላ የቅዱሱ ቅርብ ወዳጅ የሆነው ናዝሚ ቡትሮስ የተባለው ጠበቃ ነበር፡፡ ይህም ጠበቃ ምንም የዚያን ጊዜውን አባ ሚናስን በአካል ባያውቃቸውም፣ ስለ እርሳቸው ሲወራ በሰማው አሉባልታ ግን የእርሳቸውን ለፓትርያርክነት እጩ መሆን በኃይል ተቃውሞ ጋዜጣ ላይ ጽፎባቸው ነበር፡፡ አባ ሚናስም ‹‹አቡነ ቄርሎስ›› ተብለው ከተሾሙ በኋላ ‹‹እንኳን ደስ አልዎት›› ለማለት ወደ እስክንድርያ መጣ፡፡ ፓትርያርኩም ደስ ብሏቸው ተቀበሉት፡፡ እርሱም ፊታቸው ላይ ያለውን የደስታ ስሜት ሲመለከት ‹‹እርሳቸውን ተቃውሞ ጋዜጣ ላይ የጻፈው ሰው እኔ መሆኔን ባያውቁ ነው›› ብሎ አሰበ፡፡ ቁጭ ብለው ግን ሲጨዋወቱ ‹አንዳንዶች ግን ስለ እኔ ይህንንም ያንንም ሲሉ ነበር…› ብለው እርሱ የጻፈባቸውን ክስ የሚመለከት ነገር ነገሩት፡፡ በዚህ ጊዜ ያ ጠበቃ እያፈረ ‹‹ቅዱስነትዎ፣ እባክዎ ይቅር ይበሉኝ፡፡ እርሶን በሚገባ ባለማወቄ ነው፡፡›› አላቸው፡፡ አቡነ ቄርሎስም ፈገግ እያሉ ‹‹አይዞህ፣ ለዓለሙ ሙት የነበረውን ባሕታዊው አባ ሚናስን እንጂ እኔን አላጠቃህም፡፡ አሁን እኔ ቄርሎስ የሁሉ አባት ነኝ›› አሉት፡፡ ይህም ጠበቃ እውነተኛ ፍቅራቸውንና ይቅር ባይ ልባቸውን አይቶ የልብ ወዳጃቸው ሆኖ ቀረ፡፡

በSt. Vladmir Seminary press የታተመው የ‹‹A Silent Patriarch›› የተሰኘው መጽሐፍ ጸሐፊ ዶ/ር ዳንኤል ፋኑስ እንደሚናገረው የአቡነ ቄርሎስን የግል ሕይወት በተመለከተ የሚታወቁት በጣም ጥቂት ነገሮች ናቸው። የቅርብ አገልጋያቸው የነበረ ሰው እንኳን ስለኖሩት(የግል) ሕይወት ብዙ አያውቅም፡፡ በእርግጥም ዝምታ እንደ ጸጋ የሆነላቸው፣ የጸጥታን ሕይወት የመሩ፣ መላ የአገልግሎት ዘመናቸውን በቅዳሴና በጸሎት ያሳለፉ አባትን የተሰወረ ሕይወት እንዴት በቀላሉ መርምረን ማወቅ እንችላለን? ቅዱስነታቸው በኃዘናቸውም ቢሆን በሰዎች ከመከበብ ይልቅ መሸሸጊያና መጽናኛ ያደርጉት የነበረው ብቸኛው ቦታ ከመሠዊያው ታቦት ስር ሄዶ መውደቅ ነበር፡፡

አቡነ ቄርሎስ የግብጽን ቤተ ክርስቲያን አሥራ ሁለት ዓመት በቅድስና እና በጸሎት መርተው ክፋውን ዘመን ያሻገሩ ጻድቅ አባት ናቸው። ችግሮች ሁሉ የድርሻን ከመወጣት ጋር በጸሎት ይፈታሉ ብለው የሚያምኑ፣ "አባ ይህ ችግር አጋጠመን?" ሲሏቸው "እንጸልይበታለን" የሚለው መልስ ከአፋቸው የማይጠፋ በጸሎት ኃይል የሚተማመኑ ቅዱስ ነበሩ። የግብጽ ቤተ ክርስቲያን አቡነ ቄርሎስ ካረፉ ከ42 ዓመታት በኋላ በ2013 ዓ.እ. ባደረገችው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ቅድስናቸውን በግልጽ ለልጆቿ አሳውቃለች፡፡

ቅዱስነታቸው በሕይወት እያሉም ሆነ ካረፉ በኋላ በእርሳቸው ምልጃና ጸሎት የተፈጸሙ ተአምራትን የያዙ ወደ አሥራ ስምንት የሚሆኑ ተከታታይ ቅጽ ያሏቸው መጻሕፍትም ታትመዋል፡፡ አቡነ ቄርሎስ በግብጽ በጣም የሚወደዱ አባት ናቸው፡፡ በመላዋ ግብጽ ከሚኖሩ የክርስቲያን ቤቶች ውስጥ የእርሳቸው ፎቶዎች ያልተሰቀሉበት ቤት ማግኘት በጨለማ መርፌ የመፈለግ ያህል ከባድ ነው፡፡

እስኪ እኛም ለበረከት እንዲሆነን ከዕረፍታቸው በፊትና በኋላ ከአደረጓቸው ተአምራት ሦስቱን አንሥተን እንሰነባበት።

+++ "ለምን አልደወልሽም?" +++

የሴቶች ገዳም እመምኔት የነበረች አንዲት መነኩሲት አቡነ ቄርሎስን በስልክ ማናገር ስለፈለገች ወደ በቢሯቸው ሄዳ በግል የሚጠቀሙበትን የስልክ ቁጥር እንዲሰጧት ጠየቀች። በጊዜው እርሳቸው በሕመም ላይ ስለ ነበሩ የቢሮው ሠራተኞቹ ሲሻላቸው በአካል ታገኛቸዋለሽ ብለው ከለከሏት። ቅዱስነታቸው ግን በዚያው ቀን ሌሊት ለመነኩሲቷ በሕልሟ ተገልጠው አጽናንተው የስልክ ቁጥራቸውን ነገሯት። እርሷ ግን ነገሩን ችላ ብላ ሳትደውል ቀረች። ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ እመምኔቷ ከአቡነ ቄርሎስ ጋር በአካል ስትገናኝ "የግል ቁጥሬን ሰጥቼሽ አልነበር? ለምን አልደወልሽም?" ሲሉ ጠየቋት። እርሷም በነገሩ ስለተደናገጠች አፏ ተሳሰረ። የምትመልሰውም አጥታ ዝም አለች።

+++ "ቁርሷን በልታለች" +++
ቅዱስነታቸው ቅዳሴ ቀድሰው በሚያቆርቡበት ጊዜ አንዲት እናት ሴት ልጇን እንዲያቆርብላት ዲያቆኑ ሳሊብን ጠየቀችው። እርሱም ሕፃኗን ታቅፎ ወደ አቡነ ቄርሎስ ሲያመጣት "ይህችን ልጅ መልሳት። ቁርሷን የባቄላ ቅቤ በልታ ነው የመጣችው" አሉት። ዲያቆኑም ልጅቷን ወደ እናቷ መልሶ "ቁርሷን በልታለች?" ብሎ ቢጠይቃት፣ "አዎ፤ ትንሽ ዳቦ በባቄላ ቅቤ በልታ ነው የመጣነው" አለችው። ዲያቆኑም በልቶ መቁረብ እንደማይቻል ለእናትየው ካስረዳ በኋላ፣ በአቡነ ቄርሎስ ይህን ማወቅ ግን እየተገረመ ወደ ቅዳሴው ተመለሰ።

(ከዕረፍታቸው በኋላ)

+++ "ማንም አይናደድም" +++

በእስክንድርያ የምትኖር አንዲት ሴት ልጅ የነበረቻት እመቤት፣ ለልጇ ወንድም የሚሆን ልጅ እንዲሰጧት ወደ አቡነ ቄርሎስ ጸለየች፡፡ ጸሎቷን ሰምተው ወንድ ልጅ ከሰጧትም ስሙን ‹ቄርሎስ› ብላ እንደምትጠራው ተሳለች፡፡ ያቺም ሴት ልመናዋ ተሰምቶ ጸነሰች፡፡ ባለቤቷም ‹‹የሚወለደው ወንድ ልጅ ከሆነ ለአባቴ መታሰቢያ እንዲሆን በእርሱ ስም ዛኪ ብዬ መጥራት እፈልጋለሁ›› አላት፡፡ እርሷም ወንድ ከሆነ ስሙን ‹ቄርሎስ› ልትለው ስእለት እንደ ገባች ብትነግረውም ባለቤቷ ግን በሞተው አባቴ ስም ካልተጠራ አይሆንም ብሎ ተቃወማት፡፡ እመቤቲቱም ነገሩን ለእግዚአብሔር እንዲያስተካክለው ተወችው፡፡ የመውለጃዋ ሰዓት በደረሰ ጊዜም መንታ ወንድ ልጆችን ተገላገለች፡፡ ለልጆቿም ስም ስታወጣ አንዱን እንደ ስእለቷ ቄርሎስ አለችው። ለሌላኛውን ደግሞ እንደ ባለቤቷ ፈቃድ ዛኪ ብለው ጠሩት፡፡ አቡነ ቄርሎስም በሆስፒታሉ ውስጥ ሳለች ወደ እርሷ መጥተው ‹‹አንቺ ሴት አሁን ደስ አለሽ? በዚህ መንገድ ከሆነ ማንም አይናደድም›› አሏት፡፡

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
Www.dnabel.com
+++ "የእግዚአብሔር ዝምታ" +++

እግዚአብሔር ፍጥረታትን ከፈጠረባቸው መንገዶች አንዱ ‹በአርምሞ› ወይም ‹በዝምታ› ነው፡፡ ዝምታ የመናገር ተቃራኒ ወይም ያለ መሥራት ውጤት ነው፡፡ ሰው ዝም አለ የሚባለው ባልተናገረ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሥራ መሥራት ባቆመም ጊዜ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሶምሶምን ነፍስ ይፈልጉ የነበሩ የጋዛ ሰዎች ሶምሶም ወደ ጋዛ መምጣቱንና ወደ አንዲት ጋለሞታ ቤት መግባቱን ባወቁ ጊዜ፣ እርሱ ያለበትን ሥፍራ ከበው ማለዳ ላይ እንገድለዋለን በማለት ሌሊቱን ሙሉ አንዳች ክፋት እንዳላደረጉበት ሲናገር ‹ማለዳ እንገድለዋለን ብለው ሌሊቱን ሁሉ በዝምታ ተቀመጡ› ይላል፡፡ በሌላም ሥፍራ ኃጢአተኞች ጽድቅን በመሥራት ኃጢአትን እንደማይቃወሟት ለመናገር ‹እርሱ የቅዱሳኑን እግር ይጠብቃል፡፡ ኃጥአን ግን ዝም ብለው በጨለማ ይቀመጣሉ› ሲል እናነባለን፡፡(መሳ 16፥2 ፣1ኛ ሳሙ 2፥9)

ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ ‹በመኝታችሁ ሳላችሁ በልባችሁ አስቡ፤ ዝም በሉ› ብሎ እንደዘመረው የሰው ልጅ ዝም ባለ ጊዜ በአእምሮው ከማሰብ በቀር ምንም ዓይነት የሚያከናውነው ሥራ የለም፡፡ ምክንያቱም ማሰቡ ብቻ ተግባር ስለማይሆንለት ያሰበውን ለማሳካት የግድ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ ወይም መሥራት አለበት፡፡ የእግዚአብሔር ዝምታ ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ እግዚአብሔር ዝም ባለ ጊዜ በእርሱ ዘንድ የሥራ እፎይታ የለም፡፡

ዝምታ ለእግዚአብሔር ሲሆን ኃይሉን የሚገልጥባት የሥራ ወቅት ትሆናለች፡፡ በእግዚአብሔርም ዝምታ ውስጥ ያለች አሳብ ፍጥረታትን የማስገኘት አምላካዊ ኃይል አላት፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር ‹አሰበ› ተብሎ ሲነገር እንደ ፍጥረታት አሳብ ታስቦ ብቻ የሚቀር ሥራ መሥራት የማይችል ዝርው አድርገን እንዳንረዳ፡፡ የእርሱ አሳብ ኃይል አለው፡፡ በአሰበ እና በፈቀደ ጊዜ ሁሉን ካለመኖር ወደ መኖር የሚያመጣ ሥራን የሚሠራ ልዩ አሳብ ነው፡፡

እግዚአብሔር ዝም ብሎም ሥራ ይሠራል!!!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
+++ ያለ እግዚአብሔር "እንደ እግዚአብሔር" +++

በእባብ ሥጋ ተሰውሮ ወደ ሔዋን የመጣው ሰይጣን ሴቲቱን ያታለለበት የሐሰት ቃል "ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው" የሚል ነበር።(ዘፍ 3፥5) ይገርማል! በእግዚአብሔር መልክ የተፈጠረ የሰው ልጅ እንደ እግዚአብሔር (እርሱን መስሎ) የመኖር ፍላጎት እንዳለው ሰይጣን ያውቃል። ይህ ውሳጣዊ ፍላጎቱ ላይ ለመድረስ በሃይማኖትና በበጎ ምግባር ከማደግ ይልቅ ባልተገባ መንገድ ፍለጋውን ያደርግ ዘንድ አዲስ ስብከት አመጣለት። ምን የሚል? "ያለ እግዚአብሔር 'እንደ እግዚአብሔር' ትሆናላችሁ" የሚል። በምን? በቅጠል።

ዛሬም ሰይጣን ያለ እግዚአብሔር "እንደ እግዚአብሔር" ትሆኑባችኋላችሁ ሲል የሚያሳየን እንደ ገንዘብ፣ ዕውቀት፣ ጉልበት ያሉ ብዙ ቅጠሎች አሉ።  ነገር ግን እኛ ክርስቲያኖች እርሱን ወደ መምሰል የምናድግበት ብቸኛው መሰላላችን ረድኤተ እግዚአብሔርና የማይቋረጥ የእኛ ሩጫ ነው። እርሱ ሳይኖር እና  ሳያካፍል እኛ በራሳችን የምንካፈለው ምንም አምላካዊ ምሳሌነት የለም።(2ኛ ጴጥ 1፥4)

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
የጠሉህን ሳትወድድ፣ መከራ ያከበዱብህን ተቀይመህ፣ ስለ አሳዳጆችህ ሳትጸልይ እንዴት ጣቶችህን አመሳቅለህ የመስቀል ምልክት ትሠራለህ? በጣቶችህ ያለው መስቀል ጠላት የተወደደበት፣ ለሰቃልያን በቃል የማይነገር ትዕግስት የታየበት፣ ተሳዳቢ የተመረቀበት፣ ለሚወጉ ምሕረት የተደረገበት የፍቅር አውድማ ነው። ሰውን ለመወንጀል በቀሰርከው ጣትህ እንዴት መልሰህ የይቅርባነት ምልክት የሆነውን መስቀል ለመሥራት ሌላው ጣትህን አግድም ታስተኛለህ?

እያማተብህ አትጥላ፣ እያማተብህ አትፍረድ፣ እያማተብህ አትቀየም፣ እያማተብህ አትርገም።

"ገብረ ሰላመ በመስቀሉ" - "በመስቀሉ ሰላምን አደረገ"

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
የአገልግሎትዎ ድካም በረከት ይደርብን!
"በዕብራይስጥ ማሪሃም የተባልሽ የተመረጥሽ ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ አሁንም ልጅሽን እለዋለሁ...
ለቤተ መቅደስህ ተክል ያደረግኸኝ አቤቱ ሆይ፤ የውጭ ተክል አታድርገኝ... የመጻሕፍት መጀመሪያ የምትሆን ኦሪት ደመና የምትጋርደኝ፣ ከቅዱስ ወንጌል ፈሳሽ የምጠጣ ከጎንህ ከፈሰሰው ደም የምረካ ልሁን፡፡ በእናትህ በድንግል ጸሎት የሃይማኖት አበባ ላብብ፣ የጽድቅ ፍሬን ላፍራ። ከቅዱሳንህ ሐዋርያትም ከቃላቸው ፍሬ የተነሣ እስከ ዘለዓለሙ ድረስ የተባረከ የወይን ቦታ ልባል። የጽድቅን ፍሬ የሚያስቀረውንም የኃጢአት እሾህ ጠምዝዘው፤ ከደጁም አሜከላውን አረሙንም ሙጃውንም ንቀለው፡፡ አቤቱ ከእኔም አርቀው"

አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ

የውጭው ተክል አርዮስን ለማውገዝ ሃይማኖታቸው የቀና ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱ ሊቃውንት ለተሰበሰቡበት "የብዙኃን ማርያም" በዓል እንኳን በሰላም አደረሰን!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
https://www.tg-me.com/Dnabel
2025/07/08 04:21:14
Back to Top
HTML Embed Code: