Telegram Web Link
+++ "አሁንስ ተስፋዬ ማን ነው?" +++

በሕይወትህ ውስጥ በጣም የሚያስፈራህ ነገር ምንድር ነው? ተብለህ ብትጠየቅ ምን ትመልሳለህ? "ሞት" ልትል ትችላለህ። በእርግጥ ላልተዘጋጀን ኃጥአን የሞታችን ቀን መጠየቅን ወደሚወድ አምላክ የምንሄድበት ዕለት በመሆኑ እጅግ የሚያስፈራ ቀን ነው። ይሁን እንጂ ለሰው ከተስፋ ቢስነት በላይ የሚያስፈራው ነገር የለም። ሰው ተስፋውን ያጣ ቀን ሁሉ ነገሩን ያጣል። የሚያየው ሁሉ ትርጉም የለሽ ይሆንበታል። እሳቷ ፀሐይ ጥቁር ዐለት ትመስለዋለች፣ ጣፋጩ ይጎመዝዘዋል፣ የቀናው ይጎረብጠዋል። የመኖር ጉጉቱ ሁሉ ይጠፋል። ተስፋ ስትቆርጥ ሞት ወደ አንተ እስኪመጣ ድረስ አትጠብቅም። አንተ ወደ ሞት ትገሰግሳለህ። ታዲያ ለሰው ልጅ "ተስፋ ከመቁረጥ" በላይ ምን የሚያስፈራ ጠላት ሊኖረው ይችላል?

በሰው ሕይወት ውስጥ "ተስፋ" ትልቅ ገፊ ኃይል ነው። ማናቸውንም የዕለት ሥራዎቻችንን የምናከናውነው ባለ ተስፋ ፍጥረት ስለሆንን ነው። ለዚህም ነው መዝሙረኛው "ሥጋዬም ደግሞ በተስፋ ታድራለች" ሲል የሚዘምረው።(መዝ 16፥9) ደስታም ያለው በተስፋ ውስጥ ነው። ሰው በወደቀ ጊዜ አዝኖ የማይቀረው "እነሣለሁ" ብሎ ተስፋ ስለሚያደርግ ነው። በገጠመው ከባድ ኃዘን የማይሰበረው የተስፋን ምርኩዝ ስለሚይዝ ነው። ይህ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ሊደገፈው የሚገባ የማይሰበር የተስፋ ምርኩዝ ማን ነው? ይህ ሊጠፋ የሚጤሰውን የተስፋ ጥዋፍ እንደ አዲስ የሚያበራው፣ ተቀጥቅጦ የደቀቀውንም የተስፋ ሸንበቆ ጠግኖ ወደ ቀድሞ ማንነቱ የሚያድሰው ኃያል እርሱ ማን ነው?

"መድኃኒታችን እግዚአብሔር ተስፋችን ኢየሱስ ክርስቶስ" አይደለምን!!! (1ኛ ጢሞ 1፥1)

ክርስቲያኖች በራሳቸው ማስተዋል ወይም በሀብታቸው አይደገፉም። እንደ እነርሱ ተሰባሪ በሆነ ሰው ላይም ተስፋቸውን አያደርጉም። የክርስቲያን ተስፋው "የተስፋ አምላክ" ክርስቶስ ነው።(ሮሜ 15፥13) ክርስቶስን ለምን ተስፋ እናደርጋለን? "ሁሉ በእርሱ ስለሆነ፤ ከሆነውም አንዳች እንኳን ያለ እርሱ የሆነ" ስለሌለ፣ ኃይልና ችሎታ በእጁ ስለሆነ፣ ያጎበጠንን ሸክም አራግፎ ሊያሳርፈን "እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ።" ብሎ ስለ ጠራን፣ ወደ ጠራን አምላክ ቀና እንላለን።(ዮሐ 1፥3፣ 2ኛ ዜና 20፥6፣ ማቴ 11፥28) እርሱን ተስፋ ብናደርግ እንደ ሰው አይለወጥብንም። እስከ ሽበት እንኳን ተሸክሞን አይሰለቸንም።(ኢሳ 46፥4) ነፍሱን እስኪሰጥ ስለወደደን፣ በብዙ ሕማም በእጁ መዳፍ ላይ ስለቀረጸን ፍቅሩ ቀዝቅዞ ጨርሶ ሊረሳን አይችልም።(ኢሳ 49፥16)

በቸገረህ ጊዜ ብርና ወርቅ የለኝም ብለህ ተስፋ አትቁረጥ። "ሁሉን የሚችል አምላክ ወርቅና የሚብለጨለጭ ብር ይሆንልሃል"።(ኢዮ 22፥25) ስትታመምም "ማን ይረዳኛል?" አትበል። እግዚአብሔር በሕመም አልጋ ሳለህ ይረዳሃል። በበሽታህም ጊዜ አልጋህን እያነጠፈ ይንከባከብሃል።(መዝ 41፥3) እርሱ ካልተውከው አይተውህም፣ ካልሸሸኸው ከአንተ አይርቅም። ተስፋ ቆርጠህ ከሕይወትህ ካላስወጣኸው አንተን መፈለግ አይደክመውም።

ሰይጣን በአንድ ኃጢአት ደጋግሞ በጣለህ ጊዜም ፈጥነህ ተስፋ አትቁረጥ። የፈጣሪህንም መሐሪነት አትጠራጠር። ለጠላትህም እንዲህ በቀላሉ እጅ አትስጥ። ስለዚህ ነገር በገነተ አበው (Paradise of fathers) የተጻፈን ታሪክ እስኪ እናስታውስ። ሰይጣን በተመሳሳይ ኃጢአት ብዙ ጊዜ እያሰነካከለ የሚጥለው አንድ መነኩሴ ነበር። ታዲያ ይህ መነኩሴ ሁል ጊዜ በአንድ ኃጢአት እየደጋገመ መውደቁ ቢያሳዝነውም፣ መልሶ ንስሐ እየገባ ፈጣሪውን "አውጣኝ" ብሎ መማጸን ግን አላቆመም ነበር። ከዕለታት በአንዱ ቀን መነኩሴው ቆሞ መዝሙረ ዳዊት ሲጸልይ ሳለ ድንገት ሰይጣን ወደ እርሱ መጣና:- "ፊቱ ቆመህ በእነዚህ ንጹሕ ባልሆኑ ከንፈሮችህ የእግዚአብሔርን ስም ስትጠራ አታፍርም?" አለው። ያም መነኩሴ "አንተ እኔን ጨክነህ ታሰናክላለህ። እኔ ደግሞ መሐሪውን አምላክ እንዲያዝንልኝ ሳላቋርጥ እለምነዋለሁ። እስኪ ከአንተ ጭካኔ እና ከአምላክ ምሕረት የቱ እንደሚበልጥ እናያለን።" ሲል መለሰለት። ሰይጣንም የመነኩሴውን ተስፋ አለመቁረጥ ባየ ጊዜ ከእርሱ ሸሽቶ ሄደ።

የፈተና ማዕበል በሚበዛባት በዚህች ዓለም ስንኖር፣ ዐውሎና ወጀቡ ከሚያመጣው ጥፋት ለመዳን መልሕቃችንን የምንጥልበት የተስፋ መሬታችን አምላካችን እግዚአብሔር ነው።

"ኢሰማዕነ ወኢርኢነ ወኢነገሩነ አበዊነ ከመ ቦ ባዕድ አምላክ ዘእንበሌከ"

"ከአንተ በቀር ሌላ አምላክ እንዳለ አባቶቻችን አልነገሩንም። እኛም አልሰማንም፤ አላየንምም!"

"አሁንስ ተስፋዬ ማን ነው? እግዚአብሔር አይደለምን? ትዕግሥቴም ከአንተ ዘንድ ነው።"
መዝ 39፥7

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
+++ ሦስቱ ስሜቶች +++

አንድ በጨለማ ቤት ውስጥ ለረጅም ሰዓታት የተቀመጠ ሰው የቤቱን መስኮት በከፈተ ጊዜ ከውጪ የሚገባውን ብርሃን ሲመለከት መልሶ ለጥቂት ደቂቃዎች ዓይኑ እንደሚጭበረበር (እንደሚታወር)፣ እንዲሁ ፈጣሪውን ካለማወቅ ጨለማም እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ ብርሃን የሚቀርብ ሁሉ አላዋቂነቱን ይረዳል፡፡ ይህን በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ለመደገፍ የሙሴን ታሪክ ማስረጃ አድርገን እስኪ እናቅርብ፡፡

ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ቤዛ እንዲሆን የመረጠው ሙሴን እግዚአብሔር ለመጀመሪያ ጊዜ ራሱን ሲያስተዋውቀውና ወደ አገልግሎት ሲጠራው የተገለጠለት በቁጥቋጦ ላይ በሚነድ ብሩህ እሳት አምሳል ነበር፡፡(ዘጸ 3፡2) ቀጥሎም ሙሴ ወደ ፈጣሪው ከቀረበ በኋላ ደግሞ ወደ ከነዓን የነጻነት ጉዞ ሲያደርጉ እግዚአብሔር ‹በደመና እና በእሳት ዓምድ› ተገልጦ መንገድ ይመራቸው ነበር፡፡(ዘጸ 13፡21) በስተመጨረሻም በሲና ተራራ ሕግን በሰጠው ጊዜ ራሱን ለሙሴ የገለጠለት ‹በጨለማ ፣በነፋስ ፣በጢስ› ነበር፡፡(ዘጸ 20፡18-21)

እስኪ የተገለጠባቸውን ሦስቱን ምሳሌዎች ቅደም ተከተሉን በደንብ እናስተውል፡፡ መጀመሪያ በብርሃን ፣ሁለተኛ ደመና በቀላቀለ የተከፈለ ብርሃን ፣በስተመጨረሻም በጨለማ ነበር፡፡ ይህም ሰው እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ በር ሲገባ የሚሰሙትን ሦስቱን ውስጣዊ ስሜቶች የሚያሳይ ነው፡፡ በመጀመሪያ በተማረው ጥቂት ትምህርት ብዙ ነገር ያወቀ፣ እግዚአብሔርንም በሰፊው የተረዳውና ሁሉ ነገር ብርሃን መስሎ ይሰማዋል፡፡ ከእኔ በላይ ዕውቀት ለሐሳር ይላል። ሆኖም ግን መንፈሳዊ ትምህርቱን እና ንበባቡን እያጠናከረ ሲመጣ ልክ ብርሃኑ በደመና እንደተከፈለ፣ ስለ እግዚአብሔር የሚያውቀው ዕውቀት ብዙ ተከፍሎ እንዳለበት እየተረዳ ይመጣል፡፡

በስተመጨረሻም የበለጠ ከቤተ ክርስቲያን ትምህርትና ከቅዱሳት መጻሕፍት ጋር እየተቆራኘ ሲመጣ እስከዛሬ የተማረው እና ስለ ፈጣሪው ያወቀው ዕውቀት ሁሉ ወደ ኢምንትነት ይለወጥበታል፡፡ በብዙ ትምህርት ውስጥ ቢያልፍም ምን ያህል አላዋቂ እንደሆነ ይረዳል፡፡

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
ጡቶችዋ የድንግልናን ወተት ማመንጨት በጀመሩ ጊዜ በክንዷ ደግፋ የምታጠባው ሕፃን፣ ፀሐይን እያወጣ ዝናምን እያዘነበ ፍጥረቱን የሚመግብ አምላክ መሆኑን ታውቅ ነበር። በእርሷ ማኅጸን በዝምታ ያደረው ጽንስ፣ በሰማይ ኃይላት "ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ" እየተባለ የመድረኩ መሠረት እስኪናወጽ ድረስ በታላቅ ድምፅ የሚመሰገን መሆኑ አልተሰወራትም።(ኢሳ 6፥4) ስለዚህም ራሷን ወደ ሆዷ ዘንበል በማድረግ የመላእክቱን ቅዳሴ ታደምጥ ነበር።

ድንግል ወደ እርሷ ማኅጸን የገባው "የሚሳነው ነገር የሌለ የልዑል ልጅ" እንደ ሆነ ብታውቅም ሁሉን አልጋ በአልጋ እንዲያደርግላት ግን አልተማጸነችውም። የልጇን ሁሉን ቻይነት ወልደው በሚያሳድጉ ሁሉ ከሚደርሰው የእናትነት ጭንቅ ማምለጫ አላደረገችውም። ከጡቶቿ ወተት ፈልጎ እንደ ሕፃናት ሲያለቅስ "አምላክ አይደል አይርበውም" ብላ ቸል አላለችም። ክፉው ሄሮድስ ሊገድለው በፈለገ ጊዜ "የአሸናፊ የእግዚአብሔር እናቱ" እመቤታችን ድል ነሺነቱ ወዴት አለ? አላለችም። ስለ ሄሮድስ ሠራዊት አስጨናቂነት ጉንጮቿ እስኪቃጠሉ ድረስ አነባች፣ የበኩር ልጇንም አንዴ በጀባዋ አንዴ በጎንዋ እያዘለች የግብጽን ተራሮች እንደ ወፍ ዞረች እንጂ።

በእነዚያ የረሃብ ጊዜያት ድንግል ከሃሊ ልጇ ከሰማይ መና እንዲያዘንምላት ወይም ድንጋዩን ዳቦ እንዲያደርግላት ጠይቃ አልተፈታተነችውም። እስራኤላውያን በበረሃ ጉዟቸው ወቅት የሚከተላቸው (ይዘው የሚጓዙት) ዓለት ነበራቸው። እነርሱም በተጠሙ ጊዜ የሚጠጣ የሚያገኙት ከዚያ ዓለት ከሚፈልቀው ውኃ ነበር። ቅዱስ ጳውሎስም ይህን ታሪክ በማስታወስ በበረሃ ውኃ ያፈልቅላቸው የነበረው ዓለት በምሥጢር የክርስቶስ ምሳሌ መሆኑን ሲናገር "ያም ዓለት ክርስቶስ ነበረ" ይላል።(1ኛ ቆሮ 10፥3) እመቤታችን የማይቋረጥ የሕይወት ውኃ የሚፈልቅበትን ይህን መንፈሳዊ ዓለት ይዛ ስትሰደድ አንድ ቀን ስለ ጥሟ አላማረረችውም። ራሱን በፈቃዱ ባዶ ላደረገው አምላኳ ከሁሉ ይልቅ በሥጋ ባዶ መሆንን በደስታ ለመቀበል የተዘጋጀ ቆራጥ ኅሊና ነበራት። ስለዚህም በልጇ ምክንያት ከደረሰባት መከራ በአንዱ እንኳን አላማረረችም።

+++ ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ +++

ዲያቆን አቤል ካሳሁን

https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
እግዚአብሔር ሁልጊዜ ወደ መከራ እንዳትገባ አያደርግም። አንዳንድ ጊዜ በወጀብ ውስጥ መንገድ ያዘጋጅልሃል። ግፊው በሚበዛበት ዐውሎ ነፋስ እያለፍህ ተፍገምግመህ እንዳትወድቅ ጉልበትህን ያጸናል፤ ኃይልን ያስታጥቅሃል። እንዲህ እያደረገ በመንፈስ ያጎለምስሃል።

እግዚአብሔር ዳንኤልን በአናባስት ጉድጓድ ከመጣል፣ ሠለስቱ ደቂቅን ወደ እቶን እሳት ከመግባት፣ ጳውሎስና ሲላስን ወደ ወኅኒ ከመውረድ ሊያድናቸው ይችል ነበር። ይሁን እንጂ እንዲህ አላደረገም። አምላካችን ፈተና ካለባቸው ቦታዎች ሁሉ ሊያወጣን ቃል አልገባምና። ነገር ግን በመከራ ጊዜያችን ሁሉ ከእኛ እንደማይለይና በእውነት ይዘነውም እንደ ሆነ በድል ነሺነት እናጠናቅቅ ዘንድ እንደሚረዳን ቃሉን ሰጥቶናል።

የጌታ እናት እመቤታችን የተወደደ ልጇን ይዛ በግብጽ በረሃ እንደ ወፍ ከተንከራተተች በኋላ ሕፃኑን የሚፈልገው ክፉ ሄሮድስ ሲሞት ተመልሳ ወደ ገሊላ ገብታለች። እንደ ድንግል ጌታን በመሐል እጅህ ብትታቀፍ እንኳን ግብጽ መውረድ አይቀርልህም። ይሁን እንጂ የመጣብህን መከራ ድል ነሥተህ ወደ ገሊላ መመለስህም እርግጥ ነው።

"ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል"
1ኛ ቆሮ 10፥13

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

https://www.tg-me.com/Dnabel
+++ እግዚአብሔር ለአንተ ፍትሐዊ ነው? +++

ጋሽ ስብሐት ለአብ ገብረ እግዚአብሔር በአንድ የሬዲዮ ጣቢያ ላይ ቃለ መጠይቅ ሲደረግለት ለጋዜጠኛው "እግዚአብሔር በአንዳንድ ነገሮች ጥሩ አላደረገም" አለው። ጋዜጠኛውም "እንዴት? እስኪ ለምሳሌ?" ቢለል፣ "ለምሳሌ ለእኔ ያደላል" ሲል መለሰለት።

እኛስ እንዲህ የምንልባቸው አጋጣሚዎች የሉም? በእርግጥ "እግዚአብሔር ለእኔ ያደላል" ስንል "ከሌላው ያስበልጠኛል" እያልን አይደለም። በዚህስ "እግዚአብሔር የሰውን ፊት አይቶ አያደላም"።(ገላ 2፥6) ነገር ግን እርሱ እያንዳዳችንን ልክ እንደ አንድና ብቸኛ ልጅ ያህል የሚወድ አምላክ ስለሆነ ከዚህ ተአምራዊ የአባትነት ፍቅሩ የተነሣ ሁላችንም ለእኛ "የሚያደላ" መስሎ ይሰማናል።

ለመሆኑ "አምላክ ለእኔ ያደላል" ስንል ምን ማለታችን ይሆን? እግዚአብሔር ያደላልኛል ስንል እኔ ምንም ሊደረግለት የማይገባ አመጸኛ ሰው ሆኜ ሳለሁ ክፋቴን ሳይሆን ደግነቱን እያሳየ ያኖረኛል ማለታችን ነው። አንዲት እናት መልካም ከሆኑ ልጆቿ መካከል አንድ አስቸጋሪ ልጅ ቢኖራት ይጎዳብኛል ብላ ለእርሱ እንደምትሳሳ፣ ፈጣሪዬ እኔ አመጸኛ ልጁን ከስንፍናዬ የተነሣ እንዳልጠፋበት በስስት ያየኛል ይጠብቀኛል እያልን ነው።

ሶርያዊው ማር ይስሐቅ እግዚአብሔር እኛ ኃጢአተኞቹ ላይ በሚያደረገው ሁሉ ፍትሑ አልታየምና እንዴት "ፍትሐዊ ነው" ብለን ልንናገር እንችላለን ይለናል። እውነት ነው፤ እስኪ አስቡት:- በአመሻሹ ገብተን በሠራናት ጥቂት ሥራ ከጠዋት ጀምረው ከደከሙት ጋር እኩል ዲናር የሚከፍለንን፣ ገንዘቡን ወስደን በማይገባ ኑሮ ስላባከንን ፈንታ ጸጸታችንን ብቻ ተመልክቶ ወደ እኛ ሲሮጥ በመምጣት አንገታችንን አቅፎ የሚስመንን እና መልሶ በገንዘቡ ሁሉ ላይ የሚያሰለጥነንን ጌታ እንዴት "ለእኔስ ፍትሐዊ ነው" ልንለው እንችላለን?

እግዚአብሔር ከሕይወት ይልቅ ሞት፣ ከበረከት ይልቅ እርግማን ለሚገባን ለእኛ በደለኞቹ አንድም የሚገባንን አላደረገብንም። ታዲያ እግዚአብሔር እኛ ላይ ባሳየው ነገር "ፍትሐዊ" ነው ትላላችሁ?

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]


ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
+++ የተሰጠ እንባ +++

የሰው ልጅ ደካማ ነው። በውስጡ የሚፈራረቁበትን ስሜቶች ተሸክሞ ለማቆየት ይቸገራል። በጣም ሲደሰት ወይም በጣም ሲያዝን እነዚህን ስሜቶች የሚያስተነፍስበት ሳቅ ወይም ልቅሶ ይፈልጋል። ይህ ካልሆነ ግን ሰውነት ይጨነቃል። አዲስ የወይን ጠጅ እንደ ገባበት አሮጌ አቁማዳ እቀደድ እቀደድ ይላል። ከባዱን የስሜት ሰደድ እሳት የሚያበርድበት ትኩስ እንባ ከዓይን ካላዘነመ ዕረፍት የሚባል ነገር አያገኝም። ዓይን አላነባ ሲል የውስጥ ሕዋሳት የሕመም እንባ ማንባት ይጀምራሉ።

የሕክምና ሰዎች እንደሚናገሩት ሦስት ዓይነት እንባዎች አሉ። የመጀመሪያው ዓይን ውስጥ ባዕድ (ቆሻሻ) ነገር ሲገባ የምናነባው ቅጽበታዊ እንባ (Reflex tear) ሲሆን፣ ሁለተኛው ዓይናችን እንዳይደርቅና ራሱን ከinfection ለመከላከል ሲል የሚያመነጨው የማይቋረጥ እንባ (Continuous tear) ነው። ይህም እንባ 98% ውኃ ነው። ሦስተኛውና በጣም ጠቃሚው እንባ ደግሞ የውስጥ ስሜት ፈንቅሎ የሚያወጣው እንባ (Emotional tear) ነው። ተጨማሪ ጥናቶች ቢፈልግም የዘርፉ ሊቃውንት እንደሚሉት በተለይ በኃዘን ጊዜ የሚፈስሰው እንባ ከሌሎቹ እንባዎች በተለየ በሰውነት ውስጥ የተለቀቀውን stress hormone ይዞ በማስወጣት ውጥረትን ለመቀነስ ትልቅ ፋይዳ አለው። ከዚህ እንባ ጋር ተያይዘው በሰውነት ውስጥ የሚለቀቁት እንደ oxytocin እና endorphins ያሉት ሆርሞኖች ደግሞ መረጋጋትና ዕረፍትን እንድናገኝ ያግዙናል።

ይህን የእንባ ጸጋ ለእኛ የሰጠ የሰውን ድካም የሚያውቅ እግዚአብሔር ነው። ልቅሶውንም ለውስጥ ውጥረት ማስተንፈሻ ብቻ ሳይሆን፣ የነፍሳችንን ጉድፍ የምናጠራበትና ወደ እርሱ ይዘን የምንቀርበው የተወደደ መባ አደረገልን። የፈጣሪን የምሕረት ልቡን የምናውክበትና ፈጥኖ እንዲታረቀን ደጅ የምንጠናበትን የእንባ ምንጭ እርሱ ባለቤቱ ከዓይናችን ሥር አኖረ።(መኃል 6፥5) ሊቁ ዮሐንስ ዘሰዋስው እንደ ተናገረው ይህንንም እንባ ወደ ሰማይ ለምንወጣበት የብርሃን መሰላል አንደኛው እርከን አድርጎ ሰጠን።

የምትወደውን ሰው አጥተህ የምታነባ አንተ ሰው "እንዲህ ሳዝን ወዴት አለህ?" ብለህ ፈጣሪህን አትክሰስ። እግዚአብሔርን እንባህ ውስጥ ፈልገው ታገኘዋለህ። የውስጥህን ኃዘን ከሚያበርድበትና ስብራትህን ከሚጠግንበት መንገዶቹ አንዱ "በሰጠህ እንባ" ነው።

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
እግዚአብሔር ቢፈቅድ በቅርብ ጊዜ እጃችሁ የሚደርስ አዲስ መጽሐፍ!

(በብዙ ምክንያት የዘገየችው አባቶችህን ዕወቅ ፪ መጽሐፍም ተከትላው ትወጣለች)

“ደካማ ባሮቹን ለሚያጸና ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን!”
+++ "ለዚህ መች ጸለይን?" +++

በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ቤተሰባዊ የሆኑ ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲረዳ የተቋቋመ የካህናት (የቀሳውስት) ጉባኤ ነበረ። የቀድሞው የቅብጥ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ሺኖዳም ይህን ስብስብ እንዲቀላቀሉ ለአባ ሚካኤል ባቀረቡላቸው ጥሪ መሠረት የዚህ ጉባኤ አባል ሆኑ። ታዲያ አንድ ቀን አባ ሚካኤልን ጨምሮ የጉባኤው የበላይ ኃላፊ የሆኑት ጳጳስና ሌሎችም ካህናት የተጣሉ ባልና ሚስትን ሊያስታርቁ ተሰበሰቡ። ይሁን እንጂ የባልና የሚስትየው ጠብ እንዲህ በቀላሉ ሊበርድ የሚችል አልነበረምና ጳጳሱም ሆኑ ቀሳውስቱም ሁለቱን ለማስማማት ብዙ ቢጥሩም ግን አልተሳካላቸውም።

በስተመጨረሻም ጳጳሱ ወደ አባ ሚካኤል እየጠቆሙ "አባ ሚካኤል ለምን ዝም ብለው ተቀመጡ? እስኪ እርሶ ይሻላል ብለው የሚያስቡትን ይንገሩን?" አሏቸው። አባ ሚካኤልም "ብፁዕነትዎ፣ እንጸልይበት!" አሉ። ጳጳሱም "ይህን ጉባኤ ከመጀመራችን በፊት እኮ ጸልየናል" ቢሏቸው አባ ሚካኤል "አዎን አባታችን፤ ለዚህ ችግር ግን አልጸለይንም" አሉ። ከዚያ ሁሉም ለጸሎት ተነሡ። በጳጳሱ ፈቃድ በአቡነ ሚካኤል መሪነት ጸሎት አደረጉ። ጸሎቱ እንዳለቀም እነዚያ የተጣሉት ባልና ሚስት ክርክራቸውን ሁሉ ትተው በጉባኤው ፊት በፍቅር ተቃቀፉ። ሰላም አወረዱ። ይህን ጊዜ ከቀሳውስቱ አንዱ "አባታችን ከመጀመሪያ እንዲህ ቢሉን ምን ነበር?! አሳረፉን እኮ" ብለው ጉባኤውን ፈገግ አሰኙት።

እኛስ ያልጸለይንባቸው ስንት ችሮች አሉብን?

ብዙ ቋጠሮ የሚፈታው ግን በብዙዎች የሚረሳው ትልቁ መፍትሔ፣ ጸሎት!!!

(አባ ሚካኤል ኢብራሂም (1899-1975) የግብጽ ቤተ ክርስቲያንን ለበርካታ ዓመታት በትጋት ያገለገሉና እጅግ የሚያስቀና የጸሎት ሕይወት የነበራቸው አባት ናቸው።)


ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
"ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል" ማቴ 28፥7

ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ብዙ እና ጥቂት ሆነው ሳለ በተለያየ ጊዜ ራሱን ገልጦ አሳይቷቸዋል። አሁን ደግሞ አስቀድሞ በሴቶች በኩል "ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል" ብሎ ያስነገረውን ትንቢት ሊፈጽም፣ ዓሣ ለማጥመድ ወደ ገሊላ ባሕር ለወረዱ ለጴጥሮስና ለስድስቱ ወንድሞቹ የተገለጠበትን ሦስተኛ ታሪክ ዮሐንስ ይጽፍልናል።(ዮሐ 21፥1)

ቅዱስ ጴጥሮስ "ሰላም ለእናንተ ይሁን" የሚለውን የትንሣኤውን ጌታ ድምጽ ከሰማ ፣ የተጠራጠረው ቶማስ እጁን በጎኖቹ አግብቶ "ጌታዬ አምላኬ" ብሎ ሲያምን ከተመለከተ በኋላ "ዓሣ ላጠምድ እሄዳለሁ" ብሎ ሲናገር እናገኘዋለን።(ዮሐ 21፥3) ክርስቶስ ተላልፎ በተሰጠበት በሐሙስ ምሽት ከእሳት ዳር ተቀምጦ ያደረገውን ሊረሳውና ራሱን ይቅር ሊል ስላልቻለ፣ ጌታው ቀድሞ የሰጠውን የወንጌል መረብ ተወና የዓሣውን መረብ ጨብጦ ወደ ገሊላ ባሕር ሮጠ።(ማቴ 4፥19) በኃጢአት ምክንያት የተሰማው ኃፍረትና መሸማቀቅ ሐዋርያነቱን ትቶ በድሮ ማንነቱ ውስጥ ራሱን እንዲደብቅ አደረገው። የካደን ማን ለምስክርነት ይፈልገዋል በሚል ዓይነት ስሜት ለወንድሞቹ "ዓሣ ላጠምድ እሄዳለሁ" አላቸው።

ደስ የሚለው ነገር ግን ይህን አስቀድሞ የሚያውቅ ይቅር ባይ አምላኩ ጴጥሮስን "በገሊላ ቀድሞት ነበር"። በበደሉ ተሸማቆ የተወውን ሐዋርያነት ሥልጣን በፍቅሩ መማለጃነት መልሶ ሊሰጠው፣ አይገባኝም ብሎ ያስቀመጠውን የወንጌል መረብ ዳግመኛ ሊያሲዘው በገሊላ ባሕር ዳር ቀደመው። እኛም አንድ ኃጢአት ይኖረናል። መርሳት ያልቻልነው፣ ንስሐ እንኳን ብንገባበት ራሳችንን ይቅር ለማለት የተቸገርንበት፣ "ከዚህ በኋላማ..." እያሰኘ የድሮ መረብ አስይዞ ወደ ገሊላ የሚመልስ አንድ በደል ይኖረናል። ነገር ግን ጌታ ለቅዱስ ጴጥሮስ እንዳደረገው ለእኛም እንዲሁ ያደርጋል። ከባሕሩ ዳር ይጠብቀናል፣ "ትወደኛለህ" ብሎ ይጠይቀናል፣ ከዚያ በማይለወጥ ፍቅሩ ወልውሎ ሰንግሎ አፍረን ወደ ሸሸነው መንፈሳዊነት ይመልሰናል።

+++ ጌታችን በገሊላ ይቀድመናል! +++

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
ግንቦት 6/ 2015 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
+++ትሕትና ምንድር ነው?+++

ትሕትና ምንድር ነው? ብዙ ጊዜ በእኛ ዘንድ የተናቀ ልብስ መልበስ ፣ አንገት መስበር ፣ ዝግ ብሎ ማውራት እና ‹እኔ በደለኛ የማይገባ ሰው ነኝ› እያሉ ደጋግሞ መናገር እንደ ትሑት ያስቆጥር ይሆናል፡፡ ነገር ግን የትሕትና ትርጉም ከዚህም በላይ ነው፡፡ በርግጥ ከላይ የዘረዘርናቸው ነገሮች የአንድ ትሑት ሰው ከፊል መገለጫ ጠባያት ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህን በማድረግ ብቻ ትሑት መሆን ቢቻል ኖሮ ፤ በዓለም ላይ ያለው የትዕቢተኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀንስ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ትሕትናን በተጠቀሱት ውጫዊ ምግባራት ብቻ የምንረዳው ከሆነ ከእውነተኛ ትርጉሙና ማንነቱ እንዳናሳንሰው ስጋት አለኝ፡፡

ትሕትና በእኛ እና በእግዚአብሔር መካከል ያለ እውነተኛ ኑሮ ነው፡፡ አንድ ክርስቲያን ስለ ትሕትና ሲያስብ እነዚህን ሁለት ነገሮች አብሮ በትኩረት ሊያሰላስል ይገባዋል፡፡ እነርሱም አንደኛ ተፈጥሮውን (መሬታዊ ፣ትቢያ መሆኑን) አለመዘንጋት ሲሆን ፣ ሁለተኛው ደግሞ ተቀባይነቱን ለዘወትር ማስታወስ ነው፡፡ ሰው በጫማው እየረገጠ የሚራመደው አፈር እንደሆነ ሲያስብ ደካማነቱን ይረዳል፡፡ ስለዚህም በነገሮች ሁሉ ‹አቤቱ እኛ አፈር እንደ ሆንን አስብ› እያለ ረድዔተ እግዚአብሔርን የሚማጸን ትሑት ይሆናል፡፡ (መዝ 103፡14) ተቀባይነቱንም ሁል ጊዜ የሚያስታውስ ከሆነ ለሌሎች በሚያደርጋቸው በጎ ሥራዎች አይኩራራም፡፡ ብልጫም አይሰማውም፡፡ ምክንያቱም የራሱን ሳይሆን ከአምላኩ ከተሰጠው ላይ ቀንሶ የሚያካፍል ምስኪን ምጽዋተኛ ስለሆነ፡፡ ሐዋርያውስ ቢሆን በቆሮንቶስ መልእክቱ በታላቅ ቃል ‹አንተ እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ? የተቀበልህ ከሆንህ ግን እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለምንድር ነው?› ሲል የሚገስጸው ስለዚሁ አይደለምን? (1ኛቆሮ 4፡7)፡፡

ሶርያዊው አባት ማር ይስሐቅ ስለ ትሕትና ትርጉም አንድ ቁም ነገር ያካፍለናል፡፡ ምን አለ? ‹ውድቀትና ኃጢአቱን እያነሣ ራሱን የሚወቅስና የሚያዋርድ ጥሩ ቢያደርግም ትሑት ተብሎ ግን አይጠራም፡፡ ትሑት ሰው ራሱን ማሳመንና ኅሊናውም ይህን ሐሳብ እንዲይዝ መጫን አይጠበቅበትም፡፡ እንዲሁ ራሱን ምንም አድርጎ ይቆጥራል እንጂ› ሲል አስተማረ፡፡ እንደ ማር ይስሐቅ ትምህርት ከሆነ ትሑት ለመሆን ሲባል ራስን ማስጨነቅ ወደ ትሕትና ጫፍ ለመድረስ ሯጭ(ተጋዳይ) መሆንን የሚያሳይ እንጂ ‹ትሑት› አያሰኝም፡፡ እውነተኞቹ ትሑታን ሌላ የሚጋፋ እና ትግል የሚጠይቅ አንዳች የበላይነት (የእኔነት) ስሜት ሳይሰማቸው እንዲሁ ራሳቸውን የሰው ሁሉ መጨረሻ አድርገው የሚቆጥሩ ናቸው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ባሕታዊም ‹ትሑት ሰው የሚባለው ራሱን የሚሰድብና የሚያዋርድ ሳይሆን ፤ ከሌሎች ሰዎች በሚደርስበት ስድብና ትችት ፊት ፍቅሩ ሳይቀንስበት መቆም የሚችል ሰው ነው› በማለት ያስተማረው ይህን የፍጹማኑን ትሕትና ለማሳየት ነው፡፡

አባ መቃርዮስ እንደተናገረ የትሕትና ተቃራኒ የሆነች ትዕቢት የኃጢአቶች ሁሉ ራስ (እናት) ናት፡፡ ታዲያ ትዕቢት ለኃጢአቶች ሁሉ እናት ከሆነች ትሕትና ለጽድቅ ሥራዎች ሁሉ ራስ ብትሆን ምን የሚያስደንቅ ነገር አለ?!፡፡ ለዚህም ነው እኮ ቅዱሳን አበው ትሕትናን ‹እጸ ሕይወት›/‹የሕይወት ዛፍ› እያሉ የሚጠሯት፡፡ አዳም በገነት አንድ ሺ ዓመት ከኖረ በኋላ ወደማታልፈው መንግሥት (መንግሥተ ሰማያት) ለመግባት የሚታደስባትን እጸ ሕይወት አምላኩ በገነት ዛፎች መካከል ፈጥሮለት ነበር፡፡ እርሱም ትእዛዘ እግዚአብሔርን ጠብቆ ሺ ዘመን ቢቆይ ኖሮ ፤ ላይወድቅ ላይጎሰቁል በእጸ ሕይወት ታድሶ መንግሥተ እግዚአብሔርን ይወርስ ነበር፡፡ ከእጸ ሕይወት በኋላ መውደቅ የለምና፡፡ እንዲሁ ትሕትናም እጸ ሕይወት ነች፡፡ ትሕትናን ገንዘብ ካደረጉ በኋላ ውድቀት እና ከእግዚአብሔር መለየት የለም፡፡

ትሕትና በጎ ሥራዎች ሁሉ የሚጠበቁባት አጥር ቅጥር ነች፡፡ ከእግዚአብሔር የምናገኛቸው ጸጋዎችም ያለ ትሕትና ሊጸኑ ፣ ሊሰነብቱ አይችሉም፡፡ ቅዱሳን በጽኑዕ ተጋድሎ እና በፈጣሪ ቸርነት የገነቡትን የጸጋ ግንብ ሰይጣን እንዳያፈርስባቸው ፈጣሪያቸው የሚከላከልላቸው ትሑታን የሚሆኑበትን ደዌ ወይም አንዳች ነገር በእነርሱ ላይ በማምጣት ነው፡፡ ባለ ብዙ ጸጋ የነበረው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን የእግዚአብሔር አሠራር ሲያስረዳን ‹በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ የሥጋዬ መውጊያ…ተሰጠኝ ይኸውም እንዳልታበይ ነው› በማለት ግልጽ አድርጎ ይናገራል፡፡(2ኛ ቆሮ 12፡7) በሰውነቱ ጥላ እና በልብሱ እራፊ ሙት የሚቀሰቅሰው ፣ሕሙም የሚፈውሰው ሐዋርያ እንደ ስንጥር በሚወጋ ራስ ምታት መያዙ ፤ ተአምር ሲያደርግ በተመለከቱት ሰዎች በስህተት እንዳይመለክና ልብን ሰቅዞ በሚይዝ አጉል ውዳሴ እንዳይጠለፍ አድርጎታል፡፡ በርግጥም የገባሬ ተአምራት የቅዱስ ጳውሎስን ሕመም ያዩ ሰዎች በእርሱ ድካም ውስጥ የሚሠራ የእግዚአብሔርን ኃይል በግልጽ ተረድተዋል፡፡

እግዚአብሔር በጎውን ዋጋ የሚሰጠን መልካም ስላደረግን ይመስላችኋል? አይደለም፡፡ በዚህ ዓለም ላይ መልካም የሚያደርጉ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች ከእግዚአብሔር በጎውን ዋጋ ላይቀበሉ ይችላሉ፡፡ ለምን? ከአምላክ ዘንድ በጎ ዋጋ የሚያሰጠው መልካም ማድረግ ሳይሆን ፤ መልካሙን ነገር በትሕትና ማድረግ በመሆኑ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክም ከተነሡ ውዝግቦች (ክህደቶች) መካከል አንዱ የሆነው የ‹Pelagius controversy› ለዚህ ጉዳይ ተጠቃሽ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም የአየርላንድ መነኩሴ በሆነ ፔላጊዮስ የተጠነሰሰ ሲሆን ፤ አጠቃላይ ምልከታውም ‹ሰው ብቻውን በሚያደርገው በጎ ሥራ ይድናል› የሚል በረድዔተ እግዚአብሔር መደገፍንና ትሕትናን አውልቆ የሚጥል የክህደት ትምህርት ነበር፡፡ በእውነትም የማታልፍ የማትለወጥ የእግዚአብሔርን ርስት ፣ ፈራሽ በስባሽ በሆነው ሰውነቴ ብቻ ሠርቼ ገንዘብ አደርጋለሁ ከማለት በላይ ተሻለ ክህደት ከወዴት ሊመጣ ይችላል?

እስኪ ጽሑፋችንን በቅዱስ መቃርስ ምሳሌ እንዝጋው፡፡ አባ መቃሪ በአንድ ወቅት ስለ ትሕትና ሲያስተምር ‹አንድ ባለጠጋ የነበረ ንጉሥ ያለውን ሀብት በአደራ መልክ ከአንድ ደሃ ዘንድ ቢያኖር ፤ ያ ደሃ በእነዚያ ብሮች እና ወርቆች ሊመካ ይችላልን? እንደ ራሱ ንብረትስ በመቁጠር የባለቤትነት ስሜት ሊሰማው ይገባል?› ሲል ይጠይቃል፡፡ በዚህ ቅዱስ አባት ምሳሌ መሠረት ያ ባለጠጋ ንጉሥ እግዚአብሔር ነው፡፡ አደራ ተቀባዩ ነዳይ ደግሞ እኛ ነን፡፡ አደራውም በእጃችን ያሉ በጎ ነገሮች ሁሉ ናቸው፡፡ ያሉንን መልካም ነገሮች እንደ ራስ ንብረት መቁጠርና በሌላው ላይ መኩራራት አደራ ተቀባይነትን እንደ መርሳት ነው፡፡ ሰው ባልፈጠረው በጎነት እንዴት ይኩራራል?

በትሑታኑ ቅዱሳን ጸሎት ይጠብቀን!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
እስኪ የርእሰ ማዕምራን መሪጌታ ብርሃኑ ውድነህን ውድ መዝሙር ልጋብዛችሁ። እጅግ በሚመስጥ ግጥም እና በሚያራራ ዜማ የተከሸነ ነው። ታዲያ ከዚህ በላይ የጾም ቁርስ ከየት ልታገኙ?

https://youtu.be/ufcU-6jLDxU?si=P881REKjOEGWM5ZP
በውጭው ካሉት ይልቅ በአንተ ውስጥ የሚገኙት ፍትወታት ጠንካራ ጠላቶችህ ናቸው። ልክ ያልተሠራለት ምኞት ከባቢሎን እሳት ይልቅ ያቃጥላል። አልጠግብ ባይነትም ከጥፉት ውኃ ይልቅ ያሰጥማል። ያልተገራ ፍላጎት ማንነትን አስጥሎ የሰይጣን ባሪያ ያደርጋል። ራስን መግዛት የሰው ልጆች ጌጥ ነው። ዮሴፍ ግብጽን ከፈርዖን ሁለተኛ ሆኖ ከገዛበት ታላቅ ሥልጣን ይልቅ፣ በጌታው ሚስት ፊት ያሳየው ራስን መግዛት ይበልጥ ይደነቃል። ጠቢቡ "በመንፈሱ ላይ የሚገዛ ከተማ ከሚወስዱ (ከሚገዙ) ይበልጣል" እንዳለ።(ምሳ 16፥32)

ራስህን ነጻ ማውጣት ትፈልጋለህ? እንግዲያውስ ከውስጥህ ጀምር። ሁል ጊዜ ካልበላሁ የሚለው ሆድህ ስስት አስለምዶ በወንድምህ ላይ ጨካኝ እንዳያደርግህ ለሰውነትህ ጾም አስተምረው። "ነገ እሞታለሁና ልብላ ልጠጣ" የሚለውን የዐሣማ ፍልስፍናህን (Pig philosophy) ተውና አንተ በፈቃድህ እየተራብህ (እየጾምህ) ያለ ፈቃዱ የተራበው ወንድምህን በምጽዋት አጥግበው።

ጌታ ወደ እስራኤል የተመለሰው ሄሮድስ ከሞተ በኋላ ነበር።(ማቴ 2፥20) አንተ ውስጥ ያለውን ሄሮድስ የተባለ ክፉ ምኞት እንዲሞት ካላደረግኸው በቀር የተሰደደው ክርስቶስ ወደ አንተ ሊመለስ አይችልም። ይህ ክርስቶስን ከልብህ የሚያሳድድብህን ሄሮድስ እንዴት ልትገድለው ትችላለህ? እርሱንስ ወግተህ የምትጥልበት የብረት ካስማ ምን ይሆን? ለዚህስ ከጾም እና ከጸሎት የሚበረታ ምንም ዓይነት የጦር ዕቃ አታገኝም። በል እነዚህን ይዘህ ዝመትበት።


ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com

ቴሌግራም
https://www.tg-me.com/Dnabel
ንጹሕ ሆነን የረከሰ ምራቅን አለመጠየፍ እንዴት ይቻለናል? ያለ በደል የሚደረግ ውንጀላ እና ግፍንስ "በቃ" አለማለት እንዴት ይሆናልናል?

ያለ ጥፋት የሚመጣብንን ምን ያህል ጥፊዎች እንታገሳለን? ስንት ጅራፎችንስ እንቀበላለን? ስንት ውርደቶችንስ እንሸከማለን? መድኃኔዓለም ይህን ሁሉ ነገር የተቀበለው ስለ እኛ መዳን ነው።

እኔ ግን ስለ ራሴ መዳን በጀርባህ ላይ ካረፉት ጅራፎች የአንዲቱን ሰንበር ያህል እንኳን መከራ ለመቀበል ትዕግስቱ የለኝም።

"ተሰሃለኒ እግዚኦ ወበከመ ዕበየ ሳህልከ" - "አቤቱ እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ" መዝ 50፥1

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
https://www.tg-me.com/Dnabel
+++ ምክር እና ቡጢ... +++

አንዳንዴ ሰው ተቸግሮ ወደ እኛ መጥቶ ሲያወያየን ከግለሰቡ በላይ የምንሰጠውን ምክር የምንወድ ሰዎች አለን። ያ ሰው ምን ሁኔታ ላይ ነው? ምን ይሰማዋል? ብሎ ለመረዳት ከመጣር ይልቅ ልንነግረው ባሰብነው ምክር ቀድሞ ደስ መሰኘት። አውርቶ እስኪጨርስ ትዕግሥት ማጣት። እንዴት ሰምቼ ላሳርፈው ከማለት ይልቅ ከመቼው ነግሬው ላስደንቀው (ይደነቅብኝ) የሚል ጉጉት። 

መፍትሔ ብለን የምንነግረው ደግሞ ሸክም ያደከመው ሰውነቱን ጨርሶ ያላገናዘበ የሚሆንበት አጋጣሚ በጣም ብዙ ነው።

አንድ በchildhood psychology የተመረቀ አንድ ወጣት ሰው ነው አሉ። ወላጆች በተሰበሰቡበት የመጀመሪያውን ሥልጠና ሲሰጥ ለጥናቱ የመረጠው ርእስ "ዐሥርቱ ትእዛዛት ለወላጆች"/"Ten commandments for parent" በሚል ነበር። ታዲያ እርሱም እንደ ሌሎች የትዳር ወጉ ደርሶት ልክ አንድ ልጅ ወልዶ ማሳደግ እንደ ጀመረ ያ ይሰጠው የነበረውን የሥልጠና ርእስ መቀየር እንዳለበት ተሰማውና "ዐሥር ማሳሰቢያ ለወላጆች" አለው። ቀጥሎ ሁለተኛ ልጅ ወልዶ ሲያሳድግ አሁንም የቀየረው የሥልጠና ርእስ ድጋሚ ማሻሻያ እንደሚያስፈልገው ተረዳ። ስለዚህ በስተመጨረሻ ርእሱን "ዐሥር ጥቆማ ለወላጆች" አለው ይባላል። አንዳንዴ ለሰዎች የምንሰጠው ምክር ምን ያህል ከባድ እንደ ሆነ ሕይወት እስክታስተምረን ድረስ የምንጨክን እንኖራለን።

አንዳንድ ጊዜ ሰው ጨንቆት ወደ አንተ ሲመጣ ግዴታ የሆነ ወርቃማ አባባል እንድትነግረው ወይም በአነቃቂ ቃላት እንድታግለው ላይሆን ይችላል። ያን ሰው በዝምታ መስማት እና የተዘበራረቀው ሐሳቡን ጊዜ ወስዶ ለአንተ በመናገር እንዲያጠራ ማድረግም ትልቅ እርዳታ ነው።

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
በሕይወት ውስጥ መጀመሪያ ከፊት የሚመጡት ሰዎች "ሔዋንህ" ወይም "አዳምሽ" ላይሆኑ ይችላሉ። ልክ አዳም ከተፈጠረ በኋላ መጀመሪያ በእርሱ ፊት እንስሳትን እንዳገኘ እና ለእነርሱም የሚገባቸውን ስም እየሰጠ እንዳሰናበታቸው፣ አንተም አንዳንዴ በኑሮህ ቀድመህ የምታገኛቸው አካላት "ጎረቤት፣ የሥራ ባልደረባ፣ ጓደኛ" እያልክ ስም የምታወጣላቸው ብቻ ይሆናሉ። ለምን? "እንደ አንተ ያሉ (የሚመቹ) ረዳቶች" አይደሉማ። አዳም ለእንስሳት፣ ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ሁሉ ስም ካወጣላቸው በኋላ መጽሐፉ "ለአዳም እንደ እርሱ ያለ ረዳት አልተገኘለትም ነበር" ይላል።(ዘፍ 2፥20)

አዳም እንደ እርሱ ያለ ረዳት ከእንስሳቱ መካከል ፈልጎ በማጣቱ "በቃ የምን መኩራት ነው? ያሉት እነዚህ ስለሆኑ እኔን ባትመስል እንኳ ትንሽ ለእኔ የቀረበችውን ብመርጥ ይሻላል" አላለም። ከሌሎች ይልቅ በአካላዊ ቁመና ለእርሱ የምትቀርበውን ትልቅ ጦጣ (Chimpanzee) መርጦም ወደ ፈጣሪው በመውሰድ "እባክህ ጌታዬ፣ ለአንተ የሚሳንህ የለምና ትንሽ ጸጉሯን ብትቀንስ፣ ጅሯቷን ብታጠፋ እና ፊቷ አካባቢ ማስተካከያ ብታደርግላት እንደ እኔ ያለ ረዳት ትሆናለች" ብሎ ሲማጸን አናገኝም። ይህን ቢያደርግ ኖሮ አሁን የአዳምን ታሪክ የምናነብ ሰዎች ሁሉ በችኮላው እየተገረምን እንስቅበት ነበር። ምክንያቱም እግዚአብሔር ከጥቂት ቀን በኋላ አጥንቷ ከአጥንቱ፣ ሥጋዋ ከሥጋው የተፈጠረ ሔዋን የተባለች እጅግ ውብ ሚስት እንደሰጠው ስለምናውቅ።

ከአንተ ጋር በሃይማኖት፣ በአመለካከትና ይህን በመሳሰሉት ነገሮች ጨርሳ ልትገጥም የማትችል የማትመችህን ረዳት "ለአንተ ምን ይሳንሃል? አስተካክልልኝ" እያልክ ለምን ትታገላለህ። በፍጹም ስለማይሆንሽ ሰው ለምን የmodification ጥያቄ ታቀርቢያለሽ? ጥቂት ጊዜ ከታገስህ እግዚአብሔር ለአንተ የምትመችህን (compatible) ረዳት ያመጣልሃል። አሁን ግን ፊት ለፊት ያገኘሃት ጥሩ የሥራ ባልደረባ ወይም ጓደኛ እንጂ የምትመች ረዳትህ አይደለችም።

በሕይወት ውስጥ ቀድሞ የመጣ ሁሉ ባል ወይም ሚስት አይሆንም። መጽሐፍ ቅዱስም "ቢቻላችሁስ... ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ" ይላል እንጂ "ከሁሉ ጋር ተጋቡ" አላለንም።(ሮሜ 12፥18)

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
2025/07/08 00:25:16
Back to Top
HTML Embed Code: